Telegram Web Link
ሁለቱን ባሎቼን ላስማማ እያሸማገልኩ ነው
(ክፍል ስድስት)

ሳፈቅር ገገማ ነኝ!! ግግም ያልኩ ሰገጥ!! የተመታሁት እኔ ...... ቢላ አንገቴ ላይ የተደረገው እኔው ...... እሱ ለሰራው ጥፋት ማስተባበያ የምሰጠውም እኔው ....... ሁለቱንም ጊዜ እኔ ስቆጣ ነው ሌላ ሰው የሆነው ስለዚህ እኔ እሱ ሲቆጣ ባልፈው ያኛው እሱ አይመጣም ብዬ አሰብኩ!(ሰገጥ ነኝ አላልኳችሁም?)

እንዴት እንደማስተካክለው .... እንዴት ሁለቱን ማንነቱን እንደማስማማ እንጂ የማስበው ከሱ መለየት በፍፁም ለምርጫ የሚቀርብ አይደለም። ከሚሆነው ሁሉ እሱን የማፈቅርበት ጥግ ያልፋል። እናም ሁለቱን ባሎቼን በአንድ ሱፍ አገባኋቸው!! አባቴ እግሩን ስሜ እንኳን ስወጣ በሙሉ ዓይኑ አላየኝም። እሱኛው ቅፅበት ባሌ ካላሰኝ ጥፊ በላይ ያም ነበር።

በሆነ ጊዜ አንዴ የሚመጣውን ያኛውን እሱን በየቀኑ እንደሚሰበር ነገር ለሚጠነቀቅልኝ እሱ ስል ልችለው ወሰንኩ!! ምን እንደሚያስከፍለኝ የማውቅበት የእድሜም የብስለት ደረጃም ላይ አልነበርኩም። የማውቀው ያለእድሜዬ ያነበብኳቸው የፍቅር መፅሃፍት ውስጥ እና ያየኋቸው ፊልም ላይ ያለውን አድቬንቸር የሆነ ፍቅር ነው። ያ ደግሞ እንኳን ጥፊ ሞት ይጨለጥበታል።

ማሚ "የመጀመሪያ ልጅ እናት ቤት ነው የሚወለደው" ብላ አላፈናፍን ስትለን እሱ ደስ ሳይለው ሄድኩ። ወለድኩ!! ፀግዬን ወለድኩ!! ልክ ተገላግዬ ክፍሉ ውስጥ ሲገባ አልጋዬ አጠገብ በጉልበቱ ተነበርክኮ የሆነው መሆን ....... አምጥተው ህፃኗን ሲያስታቅፉት የተሰፈሰፈው መንሰፍሰፍ በጥይት መቶኝ ቢሆን ሁላ እረሳለት ነበር። (ሰግጣለሁ አልኳችሁኮ)

ልጄን አቅፎ በሚያምር ድምፁ እየዘመረ ሲያስተኛት እያየሁት ለሁለቱ ስል ምንም መሰናክል እንደማልፍ ወሰንኩ። ማሚ ህፃን ማጠብ ለእኔ ሳይሆን ለሱ ነበር ያስተማረችው። ለሊት ተነስታ ስታለቅስ ልናስተኛት አሳራችንን ስናይ የምታሰቃየን ልጅ ልክ እሱ አቅፏት መዘመር ሲጀምር ትተኛለች። እና በዚህ ፍቅር ቂም መያዝ ይቻለኝ ነበር?

የእናቴ ቤት ድሎት ኮሰኮሰኝ ምክንያቱም እሱ ስራ መግባት ስለነበረበት ተመልሶ ሄደኣ። በየቀኑ ስልክ እየደወለልኝ ለሰዓትት እናወራለን። አባቴ አሁንም ከ'ደህና አደርሽ?' እና 'ህፃኗ እንዴት አደረች?' ያለፈ አያወራኝም። ጭራሽ ሆድ ባሰኝ እሪሪሪሪ ብዬ በ45 ቀኔ ወደ ባሌ እቅፍ ተመለስኩ። (መሰስ ብዬ ቦክስ ሪንግ ውስጥ መግባቴ የታወቀኝ ሰንብቶ ነው።)

የሚናደድበት ምክንያትና ሰዓት እስኪዋቀጥብኝ የሚናደድባቸው ነገሮች እየበዙ መጡ። ሲናደድ ምን እንዳደረገ የሚያውቀው ካደረገ በኋላ ነው። ጭራሽ አያውቀውም። ካደረገው በኋላ ለቀናት በሙሉ ዓይኑ አያየኝም። የተለመደ ይቅርታ.... የተለመደ ማሪኝ.... የተለመደ ለቅሶ.... ለሰርጋችን ያልመጡት ቤተሰቦቹ መውለዴን ሲሰሙ ደወሉ። እናቱ ልክ የሆነ አንዳንዴ መክሰስ መብላት ይዘላል አይነት ነገር ቀለል አድርገው

"አንዳንዴ ሲናደድ አብሾ አለችበት ቦግ ይላል !! አይዞሽ ታገሺው ..... እንጂ ልቡ ወርቅ ነው!!" ብለውኝ አረፉት።

"ለምን ነርሲንግ አትማሪም?" አለኝ የሆነ ቀን አለ አይደል? 'ገና አስራሁለተኛ ክፍል ተምረሽ ዩንቨርስቲ መግባት ከልጅ ጋር ይከብድሻል' የሚል አንድምታ የያዘ። ማሚ ናት ለኳሿ እሷን አልሰማ ስላልኩ ነው በሱ በኩል የመጣችው!!

"አባ 12 እማራለሁ አሪፍ ውጤት አመጣለሁ። ህግ እማራለሁ። ምንም የሚቀየር እቅድ የለም።"

"እሺ ካልሽ ከጎንሽ ነኝ አለሁልሽ" አለኝ። ማሚም ንቅንቅ እንደማልል ስታውቅ ይጠቅማታል ያለችውን ሀሳብ ሰነዘረች። እሷጋ ከነልጄ ሄጄ እንድማር እና ስጨርስ ወደባሌ እንድመለስ ወይም ልጄን እሷጋ ትቼ ከባሌጋ ሆኜ እንድማር። ሁለቱንም እንቢ አልኩ። ልጄን እያሳደግኩ ከባሌጋ ሆኜ እማራለሁ። ያለችኝን ነገርኩት። በሆነ መልኩ እናቴ እኔን እየነጠቀችው እንደሆነ ተሰማው ተጠማመዱ።

ማሚ በደወለች ቁጥር ቤታችን በአንድ እግሩ ይቆማል። ሁሌ እምላለሁ "እሱ ሲናገር አልመልስለትም ዝም እላለሁ" ብዬ ሁሌ ያን ማድረግ ያቅተኝና የተዋበች ቡጢ ስቀምስ ፀጥ እላለሁ። እየተደጋገመ ሲሄድ የሚቀጥለው ህይወቴ ቀላል እንዳልሆነ ገባኝ። ይሄ ሁሉ ሆኖ ለእሱ ያለኝ ፍቅር ንቅንቅ አለማለቱ ይገርመኛል። ሁሌም እሱን ብቻ ጥፋተኛ ማድረግ አይሆንልኝም። እንዲህ አድርጌ ቢሆን እንዲያ አድርጌ ቢሆን እላለሁ ግን አይሆንምኮ ሲቆጣ እንደማዕበል ከየት መጣ ሳልለው ነው ዱብ የሚልብኝ። በተጣላን ቁጥር ወይም ሊያስቆጣው ይችላል ብዬ የማስበው ነገር ሲፈጠር ስለት ያላቸውን ነገሮች ሰብስቤ እቆልፋለሁ። ....

የሆነ ቀን እሱ እየተቆጣ ሲያወራ ፀጊ አልቅሳ አላባራ አለች። "ዝም አስብያት" ብሎ ጮኸ። ምንም ባደርጋት ጭራሽ ዝም አልል አለች። ይሄኔ ልብ አይሞትምኮ የሱ ብስጭት ቅውስ አድርጎኝ እኔ ብሼ ተገኘሁ።

"ለጸብ ሰበብ ነው እንዴ የምትፈልገው? ምን ልሁን ነው የምትለው? ጭራሽ ልጅህ አለቀሰች ብለህ ፀብ ታጋግላለህ?" ብዬ ፊጥ ፊጥ ማለት።

ፀጊን ከእጄ ተቀብሎ ሊያባብላት ሲሞክር እኔን ማን ያቁመኝ ብሶቴ ሁሉ ተሰብስቦ መጣብኝ። እያለቀስኩ እደነፋ ጀመር። ፀጊም እሪታዋን አላቆም አለች።

ሰይጣኑ ቆንጆ ተቀባብሎ ሰፈረበታ!! ልጅቷን እንደሆነ ነገር አልጋው ላይ ጥሏት። ብቻ በጠረባ ከታች ወደላይ ሲያነሳኝ አየር ላይ ትንሽ ተንሳፍፌ .... ጣራውጋ ያለችውን እስከዛሬ እርቃኝ ያልደረስኩባትን የሸረሪት ድር እግረመንገዴን አፅድቼ ተመልሼ ፈረጥኩ። የዛን ቀን በዛው ወጥቶ አምሽቶ ገባ። ቁጭ ብዬ አሰብኩ። የትኛው ህመም እንደሚብስ ልጄን ለእናቴ ሰጥቼ ቡጢዬን ለምሳ እየሸከፍኩ ትምህርቴን ከእርሱ ጋር ሆኜ መቀጠል። "አልፈልጋችሁም እሱ ይበልጥብኛል" ያልኳቸው ቤተሰቦቼጋ "እንደወደዳችሁ አድርጉኝ" ብዬ ሽንፈቴን መዋጥ(ይሄ እሱን ማጣት አለው) ወይም ልጄንም ይዤ ቡጢዬንም ችዬ ትምህርቴን መቀጠል። የመጨረሻው የማይታሰብ እንደሆነ የገባኝ ልጄን አልጋው ላይ ወርውሮ እንደጨርቅ ሲያነጥፈኝ ነው። እሱን ማጣትም አልችልም!! ከዛ በሚያነክስ ልብ ትምህርቴን ተምሬ ውጤት ማምጣት እንደማይሆንልኝ ገባኝ። ልጄን ለማሚ ልሰጣት እንደሆነ ስነግረው "በፍፁም!" ብሎ በጣም ተጣላን።

"ልጄ ናት በልጄ ላይ የመወሰን መብት አለኝ!" አለኝ

"ያ ማለት ሰይጣንህ ሲመጣ እየወረወርካት ማለት ነው? ይቅር አልማር? ከዛ ቁጭ ብዬ ልጄን ላሳድግ? ያውም ባሻህ ጊዜ እየጠፈጠፍከኝ?" ይሄ ድክመቱ ነው!! ብቻ ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ ተስማማ ግን ለሚቀጥሉት ብዙ ቀናት የፀብ እርሾ ሆነ። 'ልጄን ቀማሽኝ' የሁል ጊዜ ፀብ ሁለት ነጥብ ሆነ::

መስከረም መጥቶ ትምህርት ሊጀመር ሲል ፀግዬ 6 ወሯ ነበር። ለማንም ስለእሱ አንዲት ነገር ተናግሬ አላውቅም። ልጄን እያጠባሁ ወስጄ ለእናቴ ሰጥቻት ተመለስኩ። ከመሳሳቴ የተነሳ ብዙ ጊዜ ሀሳቤን ልቀይር ዳዳኝ።

'ለምን ትምህርቱ ራሱ ጥንቅር ብሎ አይቀርም ልጄን ለምን አርፌ አላሳድግም እኔ ከሌሎች ሴቶች በምን ተለይቼ ነው ዓላማ ቅብርጥሶ እያልኩ የምጋጋጠው? ወይም ለምን ልጄ ከፍ ብላ ትምህርት ቤት ስትገባ ከዛ አልማርም?' ብዙውን አሰብኩ

የጡቴ ወተት ሞልቶ ማጅራቴን ህመሙ እያሰቃየኝ ከሀዋሳ አርባምንጭ እንባዬን እየዘራሁ ልጄን ትቼ ተመለስኩ። እንደዛ እንደምሆን ገብቶት ስለነበር ፈቃድ ወስዶ ምግብ ሰርቶ ቤቱን አስተካክሎ ጠበቀኝ። እሱን ሳገኘው ጭራሽ ማን ይቻለኝ ? በነገታው ተመልሼ አልፈልግም በቃ ልጄን ስጡኝ የምል ነበር የመሰለኝ። ለቀናት አለቀስኩ:: እየደወልኩ መንሰቅሰቅ ስራዬ ሆነ ..
ሁለቱን ባሎቼን ላስማማ እያሸማገልኳቸው ነው
(ክፍል ሰባት)

ይሄ ሁሉ ሲሆን በጌታ ነን 🤣🤣 በጌታ ፍቅር ጥላ ስር ሆነን ነው የምንፋቀረውም የምንቧቀሰውም። ቸርች እናስመልካለን። የምሬን የምፀልይለትስ “ጌታ ሆይ ቁጣውን እንዲገታ እርዳው” ብዬ እሱ በተቃራኒው “ጌታ ሆይ ዱላዬን የምትችልበት ፀጋ ስጣት!” እያለ እየፀለየ ይሁን እንጃ አይደለም ተመትቼ ጮክ አድርገው ተናግረውኝ ቤት የማምስ ልጅ ዝም አልኩ ......... ውርድ አልኩ.....

"ትቼለትለሁ የእኔን ጉዳይ ትቼለታለሁ የእኔን ታሪክ
መላ አለው እንዴት እንደሚያደርግ ያውቃል
ዘዴ አለው እንዴት እንደሚያደርግ ያውቃል"

የሚለው የሊሊ መዝሙር እየዘመርኩ ስነፋረቅ አመሻለሁ። ዛሬም ድረስ ስሰማት እንባዬ ይመጣልኮ

ጎበዝ ተማሪ ከመሆን ውጪ ለሌላ ምንም ምርጫ ጭንቅላቴ ዝግ ነው። ገና ትምህርት ቤት እንደገባ ህፃን ቦረቅኩ ሰው በማትስ ይወሰወሳል? በቃ በትምህርት ጠፋሁ ...... ከሱ ውጪ ጓደኞች ኖሩኝ። Bilen ቢዬ መጣች ...... ሳልነግራት ገባኋት። እሱን እንዴት እንደምወደው ማውራት ከጀመርኩ የሚሰማኝ ሁሉ ጤንነት አይመስለውም። ጓደኞቼን አስተዋወቅኩት ወደዱት። እያደር እየዋለ ግን በአጠገቤ ዝንብ ራሱ ብታልፍ ጾታዋን ማጣራት ጀመረ። እንዴት እንደምወደው እንዴት እንደማይገባው ይነደኛል። ወንድ አይደለም እኔ አይቼው እሱ አይቶኝ ነገር አከተመ። ችግሩ ትምህርት ቤት ውስጥ አንድ ነጠላ ማገር በህይወቷ ዝንፍ ያለባት የማልመስል ተጫዋች ነኝና ወንዱም ሴቱም ይቀርበኛል። እቤት ስመጣም ቆንጆ ነገር ይቀርብልኛል። "ቅድም አብሮሽ ሲገለፍጥ የነበረው ልጅ አስተያየቱን አልወደድኩትም ሁለተኛ አብረሽው እንዳላይሽ"

ቆዩኝማ መሆን የነበረበትኮ ተቃራኒው ነው። እኔ ነኝ መቅናት የነበረብኝ። ቁመቱ ሜትር ከ83 ሰውነቱ ገራሚ አይኖቹ ጥርሱ ከንፈሩ (ልጆቼን አይታችሁ መስክሩኣ?) የትም ቦታ ሄደን ሲያወራኮ ሴቶቹ አፉ ውስጥ ሊገቡ ትንሽ ነው የሚቀራቸው ሲቀልድ ሲያምርበት ሲኮሳተር ግርማ ሞገሱ ሲደመጥ (እየቀለድኩ አይደለም! አሁን ይሄንኑ ታሪክ እየነገራችሁ ያለው እሱ ቢሆን ተከርብታችሁ እንዲህ እየወደደሽ ቢቀጠቅጥሽ ምናለበት ቻዪው ነበር የምትሉኝ!! ፍቅርንማ እሱ ያውራት) የትም ብወስደውኮ ኩራቴ ነው:: ሁሉም ሰው ይወደዋል። እሺ በዚህ ላይ ፍቅር ችሎበት ..... በዚህ ላይ ስለምንም ርእስ ቢነሳ በሃሳብ መከራከር ችሎበት.... በዛ ላይ ጉዳዩ ላይ ጉድ አርጎኝ (ከዛኛው እሱ ውጪ ሌላው ነገሩ እኮ በምድር የሌለ ሰው ነው።)

የተለወጠው ነገር ልጄን ለማሚ ሰጥቻት ከመጣሁ በኋላ በጣም ተሰብሬ ስለነበር ድጋሚ እንዳይሰብረኝ ራሱን ይፈራው ነበር። ሲናደድ መማታቱን ትቶ ጥሎኝ ይወጣ ጀመር። እንደመፍትሄ የወሰድነው ያንን ነው። ከዛ ግን ትምህርት ቤት መዋሌ ለኔ ሳቅ ሲጨምርልኝ ለሱ ስጋት ሆነበት። አስተማሪዎቼን የክፍል ተማሪዎችን በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ ያውቃቸዋል።

አንድ ቀን የሆነ ርእስ ተሰጥቶን በግሩፕ በተማሪ ፊት ከግሩፑ ሁለት ሰው ወጥቶ present ሊያደርግ አሳይመንት ተሰጠን። ከኛ ግሩፕ እኔና ሙሄ የሚባል ጓደኛዬ ተመረጥን። በደስታ ተቀብለን ተዘጋጀን!! የሚቀርብ ቀን 60 የማይሞላ ተማሪ ፊት ወጥቶ ለማቅረብ ፈራሁ። እኔ ሜሪ ሰው ፊት መቆም ፈራሁ ....... በ10 ዓመቴ በሺዎች ፊት ቆሜ ግጥም ያነበብኩ ልጅ ........ ማንንም ፈርቼ የማላውቅ ልጅ እጄን ሲያልበኝ አገኘሁት ........ የምወደው ነገርኮ በሰዎች ፊት ቆሞ ያን ሁሉ ጆሮ መያዝ ነበር .... የዛን ቀን ፍቅሬን ላለማጉደል ራሴ እየጎደልኩ እንደሆነ ገባኝ። "ደህና ነሽኣ?" ይለኛል ሙሄ መቶ ጊዜ ..... ይግባው አይግባው አላውቅም " ፈሪ ሆኛለሁ ማለት ነው!" አልኩት

"አንቺ? እኮ አንቺ ... በይ አትቀልጂ ..." ብሎኝ የሱን ፓርት ቀጠለ

የሆነው ሆነና ጨርሰን ስንወጣ አስተማሪያችን ለባሌ "ሚስትህ በራስ መተማመኗ ምናምን ...." ብሎ አዳንቆ ነግሮታል። ያለፉትን ዓመታት ምርጥ ከሚባሉት ትምህርት ቤቶች ውስጥ በአንደኛው ስለተማርኩ ጥሩ መሰረት ነበረኝ። ...... እና ባልዬ ሊኮራብኝ ሲገባ (የትኛው ሰይጣን ሹክ እንዳለው መድሃንያለም ብቻ ነው የሚያውቀው) አቴንሽን ፍለጋ ሆነ ብዬ ሰበብ እየፈለግኩ ተማሪ ፊት እንደምቆም ነገረኝ። ከተፈጠረው ነገር ጋር ተደማምሮልኝ የዛን ቀን ፀቡን እኔው ጀመርኩት። ልክ ከሆነ ነገር እንደነቃ ሰው ሁሉም ነገር ዛሬ እንደተገለጠልኝ ነገር። ..... የተዋበች ቡጢዬን ቀምሼ ባበጠ ፊቴ ትምህርት ቤት ገባሁ። ወድቄ ነው አልኩ። ... ለመጀመሪያ ጊዜ ባሌ መታኝ ብዬ ለሰው ተናገርኩ። ለቢዬ !! ምሳ እየበላን ብቻችንን ቁጭ ብለን ነገርኳት። እቤት ስመጣ ግን ከፋኝ!! እሱን ማንም በዛ መንገድ እንዲያውቅብኝ አልፈልግማ!! ማንም እሱን ከዛ ማንም ከሚያውቀው ተወዳጅ ስብዕናው እንዲያወርደው አልፈልግም!!

አንዳንዴ ምልክት ኖሮኝ ትምህርት ቤት እገባለሁ:: ሙሄ "እሺ ዛሬስ ምንላይ ወድቀሽ ነው?" ይለኛል:: ቢዬ ታውቃለች:: .... የልጄ ናፍቆት ሊያስነቅለኝ ይደርሳል:: እንዲያም ሆኖ ዓመቱ አለቀ::

ማትሪክ ሰኞ ልፈተን ቅዳሜ እሱ ታመመ። ቅዳሜ ለሊት ሀኪም ቤት ሄድን። እጄ ላይ ያለው ገንዘብ 1000 ብር አይሞላም። ለሊት 6 ሰዓት ገደማ ነው። አሁኑኑ መተኛት አለበት ሰርጀሪ መደረግ አለበት ተባልኩ። የሆስፒታሉ በረንዳ ላይ በቂጤ ዘጭ ብዬ ተቀመጥኩ።

"ለምን? ምን አድርጊ ነው የምትለኝ? ለምንድነው አንዱን በአንዱ የምትጭንብኝ? እላይ ሆነህ ሙድ ነው የምትይዝብኝኣ? ለመሆኑ ትሰማኛለህ ግን?" ከሰው ጋር እንደሚያወራ ሰው ከእግዜሩ ጋር ጭቅጭቅ ጀመርኩ። ገንዘብ ልጠይቀው የምችለው ብቸኛ ሰው በዛ ሰዓት ቢዬ ብቻ ነበረች። ደወልኩላት!! ከእናቷ ጋር ሲመጡ ሳያቸው ላለማልቀስ ታገልኩ። ተኛ። ሆስፒታል እያደርኩ ፈተናዬን ተፈተንኩ።

ከሆስፒታል ሲወጣ ብር ስላልነበረኝ እናቴ ለሰርጌ የሰጠችኝን ወርቆች ሸጬ የሚደረገውን ሁሉ አደረግኩ። ሳድግ እንዳየሁት ሰው ከታመመ በግ ይታረዳል:: ወግ ነው ብዬ በግ ገዝቼ አሳረድኩ:: (እራሴው እንባባባባ ብል ይሻለኝ ነበር) ሲሻለው በቀረኝ ብር ለልጄ የሆነ የሆነ ነገር ገዝቼ ልጄጋ ሄድኩ። አንዳንዴ ምኑም አይገባኝም። ወርቆቼን እንደሸጥኳቸው ሲያውቅ እኔ ለሱ ብዬ የምሄደው ርቀት ሳይሆን የታየው "ለምን አልነገርሽኝም" ብሎ መቀወጥ ነበር። ደከመኝ። ልቤ ዛለ ...... የምር ደከመኝ። ..... ምን ባደርግ ደስተኛ እንደሚሆን አላውቅም:: ያስቆጣዋል ብዬ የማስበው ነገር ምንም ሳይመስለው ያልፋል:: ጭራሽ ያልጠበቅኩት ነገር እብድ ያደርገዋል:: ክረምቱን ልጄጋ ከሱ ተለይቼ አሳለፍኩ። እዛ እያለሁ ውጤት መጣ።

ውጤቴ መጣ። ከትምህርት ቤቱ ከፍተኛውን ውጤት አምጥቼ አለፍኩ። ቅብርር ያለ ውጤት አምጥቼ። ውጤቴን ያየልኝ እሱ ነበር። በስልክ እየነገረኝ አላስጨረስኩትም ሳቅና ለቅሶዬ ተደባለቀብኝ። ነፍስ ዘራሁ ነገር..... አለሁኝ አልኩ.... ለእናቴ ስነግራት እልልልልልልል አለች። አባቴ ውጤቴን ሲሰማ አቀፈኝ። በቃ ዝም ብሎ ለደቂቃዎች አቀፈኝ። ምንም ሳይናገር ሁሉንም አለኝ። .... ልጄ ይህቺ ናት ያለ መሰለኝ...... ኮራሁብሽ ያለ መሰለኝ..... ከዛ በኃላ ምንም ዳገት የሚወጣ አቅም እንዳለኝ አመንኩ:: .... ትችያለሽ አልኳት ራሴን!!!

የዛኔ ልክ ውጤት ሲመጣ ነበር የትምህርት ምርጫችንን የምንሞላው።

"አባ በቃ ሙላልኝ እና አስገባ!" አልኩት ምክንያቱም የትና ምን እንደምፈልግ ያውቀዋል። እኔን
የሚያውቀኝ በሙሉ ያውቃል ህግ መማር እንደምፈልግ። ከተማ የመጀመሪያ ምርጫ ሀዋሳ ሁለተኛ አዲስ አበባ

ወደ እሱጋ ተመልሼ መጣሁ:: አቃቤ ህግ ነሽ ወንጀለኛ መቅጫ ብቻ ሊጠቅመኝ ይችላል ብዬ የማስበውን በሙሉ መፅሃፍ ከላይብረሪ እያወጣሁ ማንበብ ሆነ ስራዬ እዚህ ወቅት ላይ ምንም ተጨማሪ ፈጣሪዬን የምጠይቀው ነገር አልነበረኝም።

አዳራሽ ውስጥ ተቀምጠን በፕላዝማ ምድባችን ሲነገር ስሜ ብቅ አለ አርባምንጭ ዩንቨርስቲ FBE Faculty ...... ተማሪው አብሮኝ “WHAT?” አለ.... ዓይኔን ማመን አቃተኝ...

እግሬ እንዴት እየረገጠልኝ እቤት እንደደረስኩ አላውቅም። ለመጀመሪያ ጊዜ እሱ ከልቤ ግምስ ሲል ታወቀኝ። ለመጀመሪያ ጊዜ ልለየው እንደምችል አሰብኩ። በቃ ለመጀመሪያ ጊዜ ሞልቶ ከጠበበው ልቤ ሲቀነስ ታወቀኝ።

"እንኳን ደስ ያለህ እዚሁ ነው የደረሰኝ" አልኩት ማታ ሲመጣ

"እማ እርቀሽኝ እንድትሄጂ ስላልፈለግኩ ነው። ....ስለማፈቅርሽ አንቺን ላለማጣት ......." እንባው ለመጀመሪያ ጊዜ የማንም ሰው እንባ ዓይነት ሆነብኝ።

"አላሳዝንህም? ቢያንስ ህግ እንደምማር አምኜ ያን ሁላ መፅሃፍ በፍቅር ሳነብ 'እማ ተይ የሞላሁልሽ ሌላ ነገር ነው እንዲህ አትልፊ አትለኝም?' ልቤ እንደሚሰበር መገመት ከባድ ነበር? አላሳዝንህም? የ5ተኛ ክፍል አስተማሪዬ እንኳንኮ ህግ መማር እንደምፈልግ ያውቃል። እንዴት አንተ ከአይንህ እንዳታጣኝ ህልሜን ትቀማኛለህ? እስቲ ራስህን ጠይቅ የእውነት ትወደኛለህ? እኔስ ራሴን ነጥቀኸኝ... ህልሜን ነጥቀኸኝ ... ከዛም ዝም ብዬ ማፍቀሬን ልቀጥል?"
......
.....
.....
................ አልጨረስንም.................

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Meri feleke
ሁለቱን ባሎቼን ላስማማ እያሸማገልኳቸው ነው
(ክፍል ስምንት)

'ጊቢ ግቡ' እስኪባል ድረስ ምን መወሰን እንዳለብኝ ግራ ገባኝ። ማንም FBE በLAW እንደማይቀይረኝ እያወቅኩ ሞከርኩ። ላለመማርም አስቤያለሁ። ከዛ ልጄን ይዤ የሆነ ቦታ እልም ብዬ መጥፋት ....... ማንም የማያውቀኝ ቦታ ሄጄ ከዜሮ መጀመር። በእኔ እልህ ልጄን ማስከፈል የማይታሰብ ነው። እጅ መስጠትም ምርጫዬ አልሆነም። ልክ ጊቢ ግቡ ሲባል አሁንም አቧራዬን አራግፌ ተነሳሁ ....... እማራለሁ ........ ጥሩ ውጤት አመጣለሁ ..... ለሚጠብቀኝ ሁሉ ኩራት እሆናለሁ ...... ከማንም በላይ ራሴን እና ልጄን አኮራለሁ ........ ቀና ብላ የምትሄድ ሴት እሆናለሁ ....... ህይወቴን ሳሸንፍ የሆነ ቀን ህግ እማራለሁ። ራሴን ሳፅናና "ያውም ህግ መማር የምፈልገው ወንጀል ነክ መፅሃፎች ለመፃፍኣ? እደርስበታለሁ"

እሱን? ግራ ቂጡን ትወጋዋለች ብላችሁ ነው የምትጠብቁትኣ? አልገባችሁም ግራ ቂጤ እስኪጨስ እንደማፈቅረው።

"አምላክ ሆይ እባክህ ለሱ ያለኝን ፍቅር ውሰድልኝ አልችልም ብዙ ነው" ብዬ የምፀልይ ሰገጥ እንደሆንኩ አልገባችሁም። በዚህ ሁሉ ውስጥ እንዴት እንደምወደው ቢያውቅልኝና ድሮ እንደማውቀው 'እሱ' ፍቅራችንን ብንኖረው ስለቴ እንደሆነ አልገባችሁም። በዚህ ሁሉ ውስጥ ለነገ አብሮ ኑሮኣችን መሰረት ይሆነናል ብዬ ከወር ደሞዙ ላይ የሚከፈል መሬት በሊዝ እንደዳስገዛሁት አታውቁማ (ለዛዛ በሉኝ ስትፈልጉ።)

እናም ተውኩለት "ይቅር ብዬሃለሁ" አልኩት "ካንተ አይበልጥብኝም!" አልኩት በአዋቂ ደንብ ቁጭ ብለን አወራን (እኔ 20 ዓመቴ እሱ 25 ነበርን ይሄ ሲሆን ለሚያጠፋቸው ጥፋቶች ለራሴ ከምሰጠው ምክንያት አንዱ 'ስላልበሰለ ነው ወደፊት እንዲህ አይሆንም' የምለው ነገርስ? የሆነች አሮጊት ሴትዬማ ውስጤ ነበረች )

"ይሄን ማሪኝና ሁን ያልሽኝን ልሁን" አለኝ። ከዛም እሱም የማታ ኢኮኖሚክስ MA ሊማር ተመዘገበ።

ጊቢ የገባሁ ቀን አብሮኝ ሄደ። ከዘበኛው የጀመረ በጋሞኛ ሰላምታ እየሰጠ ሚስቱ መሆኔን አበክሮ እየነገረ። ፕሮክተር ነሽ ወጥ ቤት ያልዞረበት የለውም እጄን ይዞ ....... እንዴት እንደሚያወራ ያውቅበታል። ስቆ አያውቅም የሚባል ሰፊ ፊት ማስፈታት ያውቅበታል።

"ባልሽ ግን 'የሜሪ ባል ነኝ' እያለ ራሱን የሚያስተዋውቀው ማነሽ ብሎ ነው የሚያምነው ሴሌብሪቲ ነው እንዴ የምትመስዪው?" ብሎኛል አንዱ የአርክ ተማሪ 'ሚስቴ ናት' ሲል ኩራቱን አይቶት .....

አብረን ዶርም ድረስ ሄድን:: አልጋዬን አንጥፎልኝ። ዶርሚተሪዎቼን ተዋውቆ ሲያስቀን ቆይቶ ወደቤት ተመለሰ።

"ወንድምሽ ነው?" ሲሉኝ የምበሳጨው መበሳጨት

"ባሌ ነው። የልጄ አባት እሺ" እላለሁ:: በነገታው አዳዲስ ልብሶች ገዝቶልኝ መጣ። ግራ ገባኝ ምክንያቱም ብር እንደሌለው አውቃለሁ። ከሁለት ቀን በኋላ እቤት ስሄድ ቴሌብዥኑን እንደሸጠው አየሁ። እኔ እንደሱ 'አልበላ አልጠጣ ብዬ የገዛሁትን ...... እንዴት አትነግረኝም' አላልኩም:: ዶርም የገባሁ ቀን ቱታ እንደለበስኩ ነው የሄድኩት ሴቶቹ ዘንጠው ሲያያቸው ሚስቴ ከነሱ አትነስብኝ ብሎ እንዳደረገው ገብቶኛል አቅፌው አለቀስኩ ብዙ እንደምወደው ነገርኩት.....

እኔ የሀብታም ልጅ አይደለሁም። ግን ቤተሰቦቼ ባላቸው አቅብጠውኝ ነው ያደግኩት። እሱን እስካገባሁበት ሰዓት ድረስ እግሬን ሰራተኛ ያጥበኝ ነበር። ሀብታሞች የሚማሩበት የግል ትምህርት ቤት ነው የተማርኩት። ይሄ ሁሉ ሆኖ ካነበብኳቸውም መፅሃፍት ሆነ መፅሃፍ ቅዱስ ከሚታየው የላይ ለውጥ ራሴን ውስጤን ስለመቀየር እንድጨነቅ ነው አብዝቼ የተማርኩት። ልብስና እህል በፍፁም ብርቄ አይደሉም። ስለእውነቱ ከእኩዮቼ በተሻለ የምፈልገውን በእድሜዬ አጊጫለሁ። እዛ እድሜዬ ላይ ቁሳቁስ የሚያሳስበኝ ሴት አልነበርኩም። ሀብት ካፈራሁ የምመኘው ከእርሱ ጋር ስለምናፈራው ሀብትና እኔና እሱ ከልጆቻችን ጋር ስለምንኖረው ድሎት እንጂ ጊቢ እገሊት የለበሰችው ቀሚስ ግድ የሚሰጠኝ ሴት አልነበርኩም። ለእሱ ግን ለእኔ የሚያስፈልገኝን አለማሟላት ሞቱ ነበር። የቤተሰቤ ቤት የሚናፍቀኝ ...... የማያቸው ሰዎች የሚያስቀኑኝ ይመስለው ነበር ....... ላስረዳው ይቸግረኛል።

ተማሪዎቹ ስልክ ስለነበራቸው የሱን ስልክ ለእኔ ሰጠኝ። 'ስትናፍቂኝ እኔ መጥቼ አይሻለሁ ስልክ እኔ ምንም አያደርግልኝም' አለኝ ስለእውነቱ ለእኔ ከሚያደርግልኝ በላይ ለእርሱ ያደርግለት ነበር።

አንደኛ ሴሚስተር አርባምንጭ ተማሪ በማባረር አንደኛ ነው ብለው አስፈራርተውኝ ስለነበር ድምፄን አጥፍቼ ትምህርት ላይ አደፈጥኩ። ያው በሳምንት ብዙውን ቀን ነው እሱጋ የማድረው ዶርም ያደርኩ ቀን ደግሞ ስለእርሱ እያወራሁ ሳደነቁራቸው አድራለሁ። እሱም በሳምንት ብዙውን ቀን ትምህርት ቤት ጊቢ ይመጣል። ማታ ከክላስ መልስ ጊቢ ውስጥ አቅፎኝ ሲንጎራደድ ትምህርት ቤቱን የገዛ ባለሃብት ነው የሚመስለው። የሚያየን ሁላ ታድለሽ ባልሽ ደስ ሲል እንዲህ ዓይነት ባል ቢኖረኝ' የማይቀናብኝ የለም።

ነፃነቴን በሆነ መልኩ እንደያዘው ባውቅም አልጎረበጠኝም። ለምሳሌ ከጠዋት እስከማታ የለበስኩትን ያገሳሁትን የበላሁትን የሄድኩበትን የፈሳሁትን ፈስ ቁጥር ልክ የሚነግሩት ሰዎች አሉት። አውቃለሁ። ከእሱ ተደብቄ የማደርገው ነገር ስላልነበረ ግድ የለኝም። ቢበዛ 'ዛሬ ለብሰሽ የነበረው ቦዲ ግን አልሳሳም? ደረብ አታደርጊም?' ቢለኝ ነው። ወይም ከጓደኞቼጋ ሻይ ልንጠጣ ወደከተማ ስንወጣ ከየት መጣ ሳንለው ዱብ ብሎ ሰላም ብሎን ይሄዳል። ወይም ስንጨርስ 'ባልሽ ሂሳብ ከፍሎላችሁ ነው የሄደው' እንባላለን ሳናየው

"ይሄ መንፈስ የሆነ ባልሽ ትከሻዬ ላይ ዱብ እንዳይል" ይሉኛል ጓደኞቼ ሙድ ሲይዙ የሆነ ቦታ ስንሄድ

ደስተኛ ሆንኩ። ደሞኮ ብዙ የማልፈጀው ነገሬ ..... በቃ ደስተኛ አደረገኝ ...... የመጀመሪያ ሴሚስተር ውጤት መጣ። ሁሉንም ትምህርት A ሳመጣ ካልኩለስ B አመጣሁ። ካልኩለስ አስተማሪያችን ሴት ናት (ይሄን ፅሁፍ አታየውም ብዬ ተስፋ ላድርግ) ቂጧ ትልቅ የሚያምር ...... ስታስተምረን ፊቷን አዙራ አዳሜ ይቸክልና ልክ ስትዞር ሁሉም በልቡ ኤጭ የሚል አይነት ይመስለኛል። ያልሰራሁት ጥያቄ በጣም ቀላሉን ስለነበር በዛ ላይ ሴት መሆኔ በዛ ላይ ሌሎቹን በሙሉ A ማምጣቴ ይመስለኛል ቢሮ አስጠራችኝ።

"ከባዱን ሰርተሽ ቀላሉን ነው የሳትሽው" አለችኝ

"ካልኩለስ የመጨረሻ ቀን አልነበር? የልጄ ልደት ነበር ፈተናውን ቶሎ ሰርቼ ሀዋሳ መሳፈር ነበረብኝ ስቸኩል መሰለኝ የሳትኩት!" አልኳት

"ልጅ አለሽ?" አለችኝ

"አዎ ሁለት ዓመት ሆናት። ቤተሰቦቼጋ ነው ያለችው እኔና ባሌ እዚህ ነው የምንኖረው ብዬ " ያልተጠየቅኩትን መቀባጠር። ዝም ብልስ ኖሮ?
ደስ ብሏት ስታደንቀኝ ቆየችና ምንም ብፈልግ እንደምታግዘኝ ከጎኔ እንደሆነች እንደምታግዘኝ ምናምን ነገረችኝና

"ባልሽ እዚህ ከተማ ነዋሪ ነው?" አለችኝ ባትጠይቀኝስ እሷስ ቢቀርባት? እኔ ደግሞ ስለእሱ እንኳን ተጠይቄ ሳይጠይቁኝ የፍቅር እስከመቃብርን ትረካ ያህል ክፍሎች ያለመታከት እተርካለሁ።

"አዎ እገሌ ይባላል! እንዴ ታውቂዋለሽኮ የማታ ታስተምሪዋለሽኮ ስላንቺ እንደውም አውርቶልኛል .... ረዥም እንኳን .... ጠይም ቆንጆ ዓይኖቹ ትልልቅ ......" እኔ እለፈልፋለሁ እሷ ስሙን ከሰማች በኋላ ደንዝዛለች። በልፍለፋዬ መሃል አስተዋልኳት አሳዘንኳት ወይም ለራሷ አዘነች ወይም አላውቅም እጄን ጥብቅ አድርጋ ይዛኝ

"አንቺ ብርቱ ሴት ነሽ ምንም ነገር እን
ዳይበግርሽ እሺ? ልብሽን ጠብቂው በናትሽ። አደራ በርቺ" አለችኝ። እንስ ስል ታወቀኝ..... በቃ ቅንስ ...... ኩምሽሽ ።

ስለሷ ያወራነውን ሁሉ ገጣጠምኩት። ብትን ብዬ የምፈነዳ ነገር መሰለኝ። ከምሽቱ 4 ሰዓት ወደከተማ የሚሄደውን የመጨረሻ ታክሲ ይዤ እቤት ደረስኩ። በሩን በርግጄ እንደገባሁ ፈነዳሁ።

"አንተ በእኔ ላይ? ያውም ከአስተማሪዬ ጋር (ያውም ከዛ ቂጥ ጋር ብለው ደስታዬ ነበር?) ወይኔ ሜሪ !!

አበድኩ ሊሰደቡ የሚችሉ ስድቦችን ሁላ ብልግና ስድቦች ሳይቀር ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳደብኩ። ብቻዬን እየተቀነጣጠስኩ ስውረገረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ዝምምምምምም አለ።

...........አልጨረስንም ....

@getem
@getem
@paappii

#Meri feleke
ሁለቱን ባሎቼን ላስማማ እያሸማገልኳቸው ነው
(ክፍል ዘጠኝ)

ከሁሉም ከሁሉም ምኑ ያስጠላል መሰለሽ? ራስሽን ባልሽ ካባለጋት ሴት ጋር ማነፃፀር ...... መድቀቅ የምትጀምሪው እዚህጋ ነው ...... ራስሽን ከሆነ ሰው ጋር ማነፃፀር ስትጀምሪ በራስ መተማመንሽ እየተምዘገዘገ ይፈጠፈጣል። ከዛ በፊት ከማንም በልጣለሁ ወይም ከማንም አንሳለሁ ብዬ ራሴን ከማንም አወዳድሬ አላውቅም እራሴን እንዳለሁ እንደዛ በብዙ እወደዋለሁ። ደግሞ ምናለ ከሆነች ጥፍጥፍ ጋር እንኳን ቢያደርገው ......... ማለት ምንም ንፅፅር ሳያስፈልገው ቆርጥማ ትበላኛለች።

እንደው ለማረጋገጥ አለ አይደል ከወንዱም ከሴቱም 'እገሊት ግን ታምራለችኣ?' ብዬ ጠይቃለሁ? ሴቱ 'ልቅም ያለች ቆንጆ ናት!' ይለኛል። ወንዱ 'ፓ ቂጥዋ ይምጣብኝ!' ይለኛል። (ይኸው በሷ የለከፈኝ ....... ትልቅ ቂጥ ሳይ አንገቴ እስኪጠማዘዝ እየዞርኩ እሸኛለሁ። ሰርች ሳደርግ ራሱ ቂጥ ለማተለቅ የሚረዱ 10 የምግብ ዓይነቶች የሚል ነገር ዓይኔን ይጠልፈዋል።)

የዛን ቀን ማታ እቤት አላድርም ብዬ 6 ሰዓት ጊቢ በሚሄድ የሰራተኞች ሰርቪስ ዶርም ገባሁ። ደጋግሞ የሆነ ጥፋት ባጠፋ ቁጥር የማለቅሰው መጠን እየቀነሰ የህመሜ መጠን እየቀነሰ መጥቷል። ማሪኝ ባለ ቁጥር ይቅርታ ሳደርግለት እንደመጀመሪያው ሁሉ ነገር ይቀጥል ነበር። ሁለታችንም ያልገባን ቀስ በቀስ ፍቅራችንን እየገዘገዘው እንደሆነ ነው። መጀመሪያ ቢላ አንገቴ ላይ ያደረገ ቀን ለሳምንታት ነው ባሰብኩት ቁጥር ያለቀስኩት የዛን ቀን ማልቀስ ብፈልግ ራሱ አላለቀስኩም። ካደረገኝ ሁሉ የከፋ ነው ያልኩት እኮ ይሄንንን ነው። ግን እንባ እንቢ አለኝ። ይልቅስ ለመጀመሪያ ጊዜ እሱ የሌለበት ህይወቴ ምን ሊሆን እንደሚችል ከአሁኑ ጋር ማነፃፀር ጀመርኩ። እሱን መጥላት የምችልበት ጉልበት አይደለም የነበረኝ ራሴን መውደዴን መጨመር የምችልበት ጉልበት አገኝሁ። ..... ዳዴ ማለት ...... ያቺ እሱ ቢሆን የሚወዳት ሴት ብዬ የሆንኳትን ሜሪ አውጥቼ ጣልኳት። እሱ ስለሚሰማው ሳይሆን እኔ ስለምፈልገው ነገር መጨነቅ ጀመርኩ። የዛን ቀን እንቅልፍ በአይኔ ሳይዞር አደረ። ጠዋት ክላስ ቀርቼ ተኛሁ። ስነሳ መከፋቴ ልቤን ቢጫነውም ከሌላው ጊዜ በተለየ በማንም ላይ ያልተደገፈ መነቃቃት ውስጤ ነበር።

"ባልሽኮ ውጪ ተቀምጧል!" አለችኝ ጓደኛዬ ወደዶርም እየገባች

"ተይው ባክሽ ይቀመጥ!" ስል ራሴን ሰማሁት።

ለሳምንታት እንደዛ አደረገ። ሊያዋራኝ አይሞክርም። አይቶኝ ብቻ ይሄዳል። ሲበርድልኝ የሆነ ቀን 'እናውራ' ብዬ ጠራሁት እና ካፌ ተገናኝኝ። (እቤት ከሄድኩ እንደምቀልጥ አውቀዋለሁ።) አንድ ጥያቄ ብቻ ነው የነበረኝ።

"ለማያቅህ ሰው ሁሉ የሜሪ ባል ነኝ ብለህ ሳትጠየቅ የምታወራ ሰው ያውም እንደምታውቀኝ እያወቅክ ለሷ መንገሩ እንዴት አልመጣልህም?"

"አላውቅም እማ! ሁሉም ነገር በአጋጣሚ የተከሰተ ነው። የአንድ ቀን ስህተት ነው። እባክሽ ዲቴሉን እንዳወራ አታድርጊኝ። ላንቺ ማውራቱ ከሰራሁት በላይ ያማል።" አለኝ።

"እንለያይ?" አልኩት። የሰማውን ማመን አቃተው።

"እንለያይ! አባ እንዲህ እንዳፈቀርኩህ እንለያይ! አልጥላህ .... እውነቱን ልንገርህ በፊት እንደምወድህ አሁን አልወድህም! በዚህ ከቀጠልን ግን ጭራሽ ላልወድህ ነው። እኔ መኖር የምፈልገው ካሉን ጥሩ ትዝታዎች ጋር ነው። አንተን ሳስብ ካፈቀርከኝ ፍቅር በልጦ የጎዳኸኝ እንዲያመኝ አልፈልግም። ሳስብህ ፈገግ ማለት ነው የምፈልገው።" አልኩት

"አልችልም። እኔ አንቺን አጥቼ መኖር አልችልም። ቤተሰቤ እኮ አንቺ ነሽ! ማን አለኝ? እንለያይ? ከዛስ? ሰው አልሆንብሽምኮ! እማ እታመምብሻለሁ ተይ!" አለኝ (እሱ እውነት ነው ከኔ ውጪ ቤተሰቤ ብሎ የሚጠያየቀው የለም። ቤተሰቦቹም ከሁለቴ በላይ ደውለውልን አያውቁም። ዛሬም ድረስ የማይገባኝ የተወሳሰበ ግንኙነት ነው ያለው ከቤተሰቡ ጋር። ብቻ እንዲህ ሆንኩ የሚባባለው ቤተሰብ የለውም። ይሄም ሌላኛው ለራሴ ከምሰጣቸው ምክንያቶች አንዱ ነበር። ቤተሰቤ ለእኔ ምን ማለት እንደሆነ አውቃለሁና 'ከኔ ሌላ ማንም የለውም'

"እኔ ደግሞ እንዲህ መኖር አልችልም።"

"ልጃችንስ?"

"እኔ እየሞትኩ ለልጄ እንዴት ነው እናት የምሆናት?" (በዚህ ጉዳይ ያለኝን አቋም ያውቃል። እውነቱን ነው ልጄን ሳላስባት ቀርቼ አይደለም። ባሌ ለልጆቼ ጥሩ አባት ከሆነ መቻል አይከብደኝም ብዬ የማምን ዱዝ እንደሆንኩ ያውቃል።)

"እማ በፍፁም አይሆንም! እኔና አንቺ ገና ነጭ ፁጉር እስክናበቅል አብረን እንሆናለን። ፍቅርን እንወልዳለን (ፍቅር የሁለተኛ ልጃችን ስም ነው።) የፈለግሽውን ጊዜ ውሰጂ ብቻ ተመለሺልኝ .... አትተይኝ" አለኝ

ብዙ ነገር አውርተን። 'እንለያይ' ያልኩት ልጅ ከንፈሩን ስሜው የምለየውስ ነገር? ሸኝቶኝ ልንለያይ ስንል

"ካንተ ውጪ ከሌላ ወንድ ልጅ አልወልድም። ምናልባት ወደፊት ፍቅርን የመውለድ ሃሳብ ከመጣልኝ ትቸገርልኛለህ።" ብዬው ተሳስቀን ተለያየን። የእውነቴን ነበር ከሁለት አባት ልጅ አልወልድም።( እሱ ሌላ ታሪክ ነው ግን የራሴ ምክንያት አለኝ።) በዛ ላይ come on እሱኮ ጣኦቴ ነበር።

ወደ ዶርሜ ተመለስኩ። ከትምህርቴ በተጨማሪ ትምህርት ቤት ውስጥ የማልገባበት መድረክ ነገር የለም። እሱን የማስብበት ጊዜ እንዲኖረኝ አልፈልግም በተጨማሪ እሱ ደስ ስለማይለው ተውኩ እንጂ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ላይ መሳተፍ እወድ ነበር። ብሄር ብሄረሰቦች ቀን ....የሴቶች ቀን ....ኪነጥበብ ምሽት ....ብቻ ምንም ይሁን ...... እንደቀይ ወጥ መሃል ላይ ዱቅ ..... ግጥም ....አጭር ልብወለድ .... ዘፈን መዝፈን ..... መድረክ መምራት .... ብቻ ምንም አልኩ ......የአባቶች ቀንም መድረክ አስመሩኝ ብዬ ከልክለውኝ ነው።

"ትቼለታለሁ የኔን ጉዳይ ..." ያልኩትን ጌታ ራሴ ትቼ

"ይማርሽ ይሉኛል አሜን ይማረኝ
አንተ ልጅ ፍቅርህ እንዳልሄድ ይዞኝ " ማቀንቀኑን ያዝኩት (የምሬን ነውኮ ይሄንኑ ዘፈን ጊቢ ዝግጅት ላይ ዘፍኜዋለሁ)

እኔ መድረክ ዝግጅት ሲኖርብኝ ወፎቹ ይነግሩታል። ይመጣል። ያየኛል። "ዛሬ ታምሪ ነበር" ብሎኝ ይሄዳል። እርግጥ አንዳንዴ "ይሄ ነገር ትንሽ አላጠረም?" ይላል። በሱ እልህ የሃመሮቹን ቆዳ ብለብስ ራሱ ውስጤ ነበር። ወደቤቴ ሳልሄድ ወራት አለፈ። መጥቶ ያላየኝ አንድም ቀን የለም። እንለያይ ካልኩት በኋላ ግን ቢያንስ ሰላም እንባባላለን። 'ምንድነው አንተ እህል አትበላም እንዴ? ከሳህኮ?' 'ምንድነው ሸሚዝህን አትተኩሰውም እንዴ?' ዓይነት ንግግሮች አሉበት። በጠዋት አንድ ቀን አይኔን ስገልጥ ጊቢ ሳየው 'ለመሆኑ ቁርስህን በልተሃል?'ነው መጀመሪያ ከአፌ የወጣው።

ሀቁንኣ የምናወራው? በጣም ከመናፈቄ የተነሳ ብዙ ቀን "በቃ አባ ይቅር ብዬሃለሁ ወደ ቤት እንሂድ" ልለው አስቤ አውቃለሁ። ሰላም ስንባባል አለው አስተቃቀፍ ውስጡ ክትት የሚያደርገኝ ለቅጽበት የሆነውን ሁላ እርስት የሚያስደርገኝ። እልሄ ያንን ያልፍ ነበር።

የሆነ ቀን አስተማሪያችን ቢሮ አስጠራችኝ። ምንም የሚያገናኘን ኮርስ ስላልነበረ እየገረመኝ ሄድኩ። ገና እንደገባሁ ቀለበቴን እጄ ላይ ቼክ ስታደርግ አየኋት::

"አላወለቅኩትም" አልኳት

"እባክሽ አታውልቂው በናትሽ። የልጅሽ አባት ነው። ይቅርታ ልጠይቅሽ ነው የጠራሁሽ። በጉዳዩ መጠየቅ ካለብኝ እኔም ነኝ ጥፋተኛ! እኔም እሱም አስበን ያደረግነው ነገር አይደለም። እናቴ ትሙት ባለትዳር መሆኑን ግን አላውቅም ነበር።" እያለች ነገሩን ስታብራራልኝ
እኔ ያደረጉት ነገር በስዕል መልክ እየተከሰተብኝ ደሜ መንተክተኩን አልክድም። ብዙ መጠየቅ የምፈልገው ነገር ነበር ዲቴሉን ማወቅ ህመም እንጂ የሚሰጠኝ መልስ እንደሌለ ሳውቅ ተውኩት። ከእርሷ ጋር ያወራሁ ቀን ድብዝዝ ብሎ የነበረው ቁጣዬ ፈላ!! ማታ ላይ ሳየው ሀገር ሰላም ብሎ ሲያቅፈኝ። ለነገር ሲሊፐሬን አቀብሉኝ አልኩ። ... ሌላ የማላውቃት ሴትዮ ከውስጤ ወጣች .... እያለቀስኩም እየተሳደብኩም... እየተራገምኩም..... የሆነ የማልወዳት የመንደር ነገረኛ ሴት ነገር ሆንኩ:: ........ ... ዝም አለኝ። በሚቀጥለው ቀን አልመጣም። .......... ማለት ሲቀርብኝ ጠበቅኩትኮ። 'እንለያይ' ብዬው ነበርኮኣ? ምን ሆኖ ይሁን ብዬ ስጨነቅ አደርኩ። በሚቀጥለውም ቀን አልመጣም። ማታ ላይ ማሚ ደወለችልኝ።

"በይ ነይ እቤት እየጠበቅኩሽ ነው!"

"የት ቤት ነው?"

"እቤትሽ!"

"አርባምንጭ ነው?"

"አዎ!" ማሚ ከሀዋሳ ልትመጣ የምትችልበትን ምክንያት ማሰብ ቸገረኝ። .... የሆነ ነገር ሆኖ ቢሆን ግን ድምፅዋ እንዲህ አይረጋጋም::

....................... አልጨረስንም................

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Meri feleke
……… ርዕሱን አላውቀውም………


አተኩሬ አየሁት ፣ አየኝ . . . . ተንጋዶዋል ፣ ተንጋድጄበታለው………

ደብዛዛ ፊት፣ የጨፈነ ግንባር ፣ በሲጋራ ጢስ
የተፈረካከሰ ከንፈር ፣ በሃሳብ የተዳጠ እራስ
ያጨመጨሙ አይኖች ……… ግማሽ ሰው
. . .ግማሽ አካል . .

በድጋሚ አየሁት መንጋደዱ ትክክል ነው ። ቀጥ ብሎ አያውቅም ………

ሁለት መለክያ ውስኪ ይጎነጭና . . .

"ውሃ ልኬ ይሄ ነው " ይለኛል . . .

ሲቅም ፣ ሲያጤስም የውሃ ልኩ ነው . . . ብሎም ያምናል. . .

ማመን እሱ ጋር መሆን ነው ፣ መደረግ ፣ መጨበጥ ልክ እደ ሚጠጣው የውስኪ መለክያ።. . .

መጥመቂያ አፉን ስስመው ፣ ህቅ ፣ ህቅ እያለኝ ይጣፍጠኛል።


"በፀጥታ ነው ማስታውስሽ ፣ ተው እንዳትይኝ ፣ መንፈሴ ሲረበሽ እረሳሻለው ፣ ማስታውስሽ በዚህ መለክያ ውስጥ ነው. . . ." ይለኛል ሳልጠይቀው ፣ ሳልከለክለው. . . .

ብዙ ቀን ይረሳኝና ሊያስታውሰኝ ሲፈልግ. .

"እድትሄጅም ፣ እድትመጪም አልፈልግም ፣ ከመሄድሽ ግን መምጣትሽ የበለጠ ጣፋጭ ነው" ይለኛል።. . . . ስልኩን ዘግቼ እየበረርኩ ሄድለታለው። . .

. . . አይሰክርም ፤ ይሰክራልም። . . .

"ለምን እደምትለዪ ታውቂያለሽ?" ከሶስት መለክያ በኃላ ይጠይቀኛል. . .

እኔጃ . . . .

"አትቆጥቢኝም………"

በቃ እለዋለው እየከፋኝ

"በቃ " . . . ..


ዝም . . . ትካዜ የደኮነ ዝምታ . . .

* * *

በአንደኛው ቀን ላይ ………

" አርግዣለው " አልኩት

"ውለጂው ፣ ጠንካራ ሴት ነሽ ፣ በእውቀትም በገንዘብም አታቀነጭሪውም " ግድ የለሽ ሆኖ ነው የመለሰለኝ . . . ውስጡን ጠልቄ ለማየት ሞከርኩ ያው ነው. . . .

ትቼው ሄድኩ. . . .

. . . ከአራት ወራቶች በኃላ ደወለ. . . .

"አመሽኛል"አለኝ

ሄድኩለት. . . ሳይፈልገኝ ስሄድ ይጠላኛል ፣ እስከሚፈልገኝ ጠብቃለው።

"ልጅሽ አላደገም " ሆድ ፣ ሆዴን እያየ ፈገግ አለ. ,


" ልትነካው ትፈልግ ይሁን ?" መልሱ አዎ እንዲሆን እየተመኘው ጠየኩ. . .

"ሁለ……ቱንም " አለኝ . . . የወጡት ቃላቶች ሲሰባበሩ ወጉኝ . . . እሱንም እያመሙት ነበር. .

"ለምን. . ?"

"ሂጂ በቃ. . !"

"አሁን ነው የመጣሁት እኮ ጌት"

"ድኛለው ፣ ከቆየሽም ያመኛል"

ወጣሁኝ………

* * *

"አደራ ብሰጠው አደራ ልቤን
በልቶ ተገኘ አሉ በጣጥሶ አንጀቴን
የደከመን ገሎ ፉከሬ ምንድነው
ቀን የጣለው ለታ እሱም እንደኔ ነው
እርም የናቴን ስጋ እምልልሀለው
ፍቅር ካልሰጠኽኝ እሞትብሀለው
ያንእምቢ ያንእምቢ ስለመን ከርሜ
ይኽው ተጃጃልኩኝ ደግሜ ደግሜ " . . . ጂጂ እያዜመች እሱ እየሰማት ደረስኩ ጠርቶኝ . .

"ስንት ወር ቀረሽ "

"ሰባት ወሬ ነው "

"ለምን ጂጂን እደምወዳት ታውቂያለሽ ?"

"አይ………"

"በራሷ ውስጥ ነው የበቀለችው. . .ውበት እንዲህ ነው!" ሲጋራውን ተነፈሰው. . . እኔ ሳብኩት. . .

"ለምን እዲህ ሆንክ "

"ምን ሆንኩ " ተረጋግቶ ጥያቄዬን በጥያቄ አጣፋው. . .

ዝም አልኩ ………

"አፈቅርሻለው " . . . ደነገጥኩ አየሁት . . . ብሎኝ አያውቅም . . . ጠጋ አልኩት . . . ሳመኝ . . አይኔን ፣ ግንባሬን ፣ ከንፈሬን . . ጎንበስ ብሎ ሆዴን . . .

"እናቷ ስለምትሆኚ እድለኛ ነች !"

"ወንድ ነው !"


. . . .

"ዛሬ አልሂድ " ጠየኩት . .

"ነገ ነይ ፣ አትቅሪ " አለኝ . . . ተነሳው እጄን ያዘው
. . . .

"ሁለት ደቂቃ ልስማሽ "

"ምን ልንገርህ ?"

"ስሙን ማነው ምትይው?"


"አላወጣሁለትም "

"ዛብሎን . . . በይው "

"ምን ማለት ነው ?"

"መኖሪያ. መኖሪያ ቤት. . . ማለት ነው . . . ሁሉን ሚያኖር ሆኖ ያድጋል . . . አንቺ ስለሆንሽ እናቱ" አለኝ. . .

. . . ሳምኩት. . . .

* * *

ከስራ እደወጣው ቤቱ ሄድኩ . . . ገመድ አንገቱ ላይ ተንጠልጥሎ ዝም ብሎዋል . . .

* * *

ቀበርኩት ፣ አልቅሼ ሳይሆን ታምሜ ቀበርኩት ፣ ቆስዬ ፣ ተለብልቤ ለአፈር ሰጠሁት. . ሳልረዳው ፣ ሳላውቀው ፣ ሳይገባኝ ሸኘሁት . . .


* * *

ከብዙ ዓመታት በኃላ የዛብሎኔ ልጅ ጠየቀኝ

"አያቴ . . "

"ወዬ "

"ወንድ አያቴ . . . ምን አይነት ሰው ነበር?"

"በአባትህ ነው ማውቀው ልጄ " አልኩት!

######
/ትዝታ/
@tiztawe
@wegoch
@wegoch
@wegoch
ሁለቱን ባሎቼን ላስማማ እያሸማገልኳቸው ነው
(ክፍል አስር)

ልታሸንፈኝ የምትችለው እሷ ብቻ እንደሆነች ያውቀዋል። እንዴት ብሎ እንደነገራት አላውቅም። ግን እንዳልኳችሁ ነው ..... ይሄን ታሪክ እንኳን እየነገራችሁ ያለው እሱ ቢሆን እንዴት አንጀት እንደሚበላ ያውቅበታል። 'አንቺ ልዩ ነሽ' ያልሽ ሁላ ክርብት ብለሽ 'ምን ልሁን ነው የምትዪው?' ማለትሽ አይቀርም ነበር። በእርግጥ እንደወሰለተ ነው እንጂ የነገራት ሌላ ጣጣችንን አልነገራትም።

መፅሃፍ ቅዱሱ እንኳን ፍቺን የሚፈቅድበት ብቸኛ ምክንያት ውስልትና መሆኑን እያወቀች። እሱን አልፋ ስለይቅርታ ስትሰብከ አመሸች።

"ውይ አንጀቴን በላው! ሌላ መሄጃ የለኝም .... ጉዴን ልንገርሽና እንደፈለግሽ አርጊኝ ብዬ ነው አንቺጋ የመጣሁት አንቺው አማልጂኝ! ያለእሷ መኖር አልችልም ብሎ እግሬ ላይ ሲወድቅ አንጀቴን በላው! በጣም ነው የሚወድሽ" ብላ ጭራሽ ልትቆጣኝ ሁላ ዳዳት።

ከዛ ግን ለብቻዬ እንዲህ አለችኝ

"ትዳር አንዴ ከገባሽበት በኋላ ያውም ልጅ ካመጣሽ በኋላ በሰበብ አስባቡ ብድግ እያልሽ ወጥቼበታለሁ የምትዪበት አይደለም።" (በሰበብ አስባቡ አይደለምኮ ብዬ የሆነውን ሁሉ ልነግራት እፈልግና እተወዋለሁ። ምናልባት 'መጀመሪያ እረፊ ብዬሽ ነበር' መባልን ፈርቼ? ወይም 'ልክ ነበርሽ እሱን ተከትዬ መምጣት አልነበረብኝም' ማለት ሽንፈት መስሎኝ ወይም አሁንም ለእሱ ያለኝ ፍቅር እርሱን እንዳትጠላብኝ እንድሰስት አድርጎኝ። ዝም ብዬ ሰማሁ ብቻ)

"አግብተሽ ያውም ከልጅ በኋላ ብቻሽን ህይወትን መግፋት ለሴት ልጅ ከባድ ነው። አንቺ ገና ህፃን ነሽ ለዛ አልተዘጋጀሽም! ቅስምሽ ይሰበራል። ምንም አድርጎሽ ውጪ ዝቅ ተደርገሽ የምትታዪው አንቺ ነሽ። ምንም በደል ደርሶብሽ ትዳርሽን ፍቺ ያው ፈት ነሽ! የምታገኚው ወንድ እንኳን ፈት መሆንሽን ሲያውቅ ያጎድልሻል።" አለችኝ (ይሄኛው ምን ማለት እንደሆነ የገባኝ ዘግይቶ ነው።)

ከምክሩ በኋላ በዘይትም በእጅ መጫንም ተፀልዮልን። "በጌታ ስም ትዳራችሁ ካሁን በኋላ የሰይጣን ሴራ መጠቀሚያ አይሆንም። ልጆቼን ልትዋጋ በአየር በባቡር በየብስ ...... የምታንዣብብ በየሱስ ስም የከሸፈ ይሁን" ተብለን ታረቅን።

እኔና እሱ መሃል ሶስተኛ ሰው ገባ! ያ ለእኔ የትዳራችን መፍረስ ጅማሬ ነበር። በዚህ ሁሉ መሃል እያለፍን ሌላ ሰው የማይረዳው የእኔና የእሱ ስሜት አለ። በቃ ለሌላ ሰው የማይገባው ያንን ድንበር አልፈን ተጣልተን እንዲያሸማግለን ሶስተኛ ሰው ስንጠራ መግባባት አቅቶናል።

ክረምቱን ፀጊ መጣች እኛጋ። ሁሉ ሞላልኝ። እሱም ቦረቀ። ሁለቱን ወር እራሱ ፈጣሪ ተገልጦ 'ምን ልስጥሽ?' ቢለኝ

'እያየኸኝ? ከዚህ በላይ ምን እፈልጋለሁ?' ነበር የምለው። ደስታ አልፈጅም ብያችሁ የለ? በቃ ምንም ነገር ከዚህ ደስታ አይበልጥም አልኳ!! የልጄና የአባቷን መፍለቅለቅ እያየሁ ይሄን ቤት ለማቆየት መክፈል ያለብኝን እከፍላለሁ አልኳ!

አልኩ ነው እንግዲህ ........ ትምህርት ሲጀመር ጸግዬን ወደነበረችበት ወሰድኳት። ንትርኩ የተጀመረው ይሄኔ ነው። "ልጄ አብራኝ ትሁን!" አለ። እኔም ልጄ አብራኝ ብትሆን ደስታዬ ልክ የለውም። ግን የሚያስከፍለኝን ደግሞ አውቀዋለሁ። ልጄን እቤት እየተውኩ ምን አይነት ትምህርት ነበር የምማረው? ከዛ ደግሞ እነማሚን በቃ ልጄን ወስጃለሁ ካልኳቸው በኋላ የሆነ ቀን ቢባርቅበት አይ በቃ ደግሞ ትመለስ ልላቸው ነው? በዛ ላይ እዛ የለመደችውን ድሎት በሰዓቱ እኔ አልሰጣትም። የነበረው አማራጭ ሁለት አመት ታግሼ ልጄን በሙሉ አቅሜና ትኩረት ማሳደግ ነበር።

"ለሁለተኛ ጊዜ ልጄን ቀማሽኝ!" የንትርክ ሁለት ነጥብ ሆነ። ይችልበታል! እናም በዚህ ጉዳይ ሁሌ ራሴን እንድወቅስ ..... ራስ ወዳድ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ አደረገኝ። እናም ይሄን ነጥብ አንስቶ ንትርክ ሲጀምር እንደጎዳሁት ስለሚሰማኝ ሁሌ ይቅርታ እጠይቀዋለሁ። እውነታውንኮ ልቤ አሳምሮ ያውቀዋል። ልጄን ባመጣት የሆነ ቀን ትምህርቴን አቆማለሁ። ግን ደግሞ እሱም ልክ ነው ልጁን ነው ከአጠገቡ ያጣው። እሱ እንደአባት ሃላፊነት ወስዶ ቀን ከሌት ልጁን ይንከባከባል ብዬ 100 % እሱን ማመን ልቤ ከበደው። ስለዚህ በራስ ወዳድነቴ ፀናሁ!!

ከዚህ በኋላ ያለው አንድ አመት አዙሪት ነው። እያንዳንዱን ዝርዝር ብፅፍላችሁ ምክንያቱና ሰዎቹ ይቀያየራሉ እንጂ ሂደቱ ያው ነው። አንድ ወር እፍፍፍፍ ብለን እንፋቀራለን ከዛ በሆነኛው ሰበብ እንጣላለን ወይ ይጠልዘኛል ወይ ሞልጬው ወደዶርሜ እመለሳለሁ። በነገታው ትምህርት ቤት ይመጣል እማ አይለመደኝም ይላል። ሁለት ቀን አኮርፋለሁ ከዛ ደግሞ እፍፍፍፍፍፍፍ .......

ደግሞ የሆነ ቀን እኔው ደሙን አፈላዋለሁ። እንፋታ በቃ መዝሙሬ ሆነች። ያብዳል። ይቅርታ እጠይቃለሁ ..... ደግሞ እንታረቃለን።
ለውጡ ምንድነው መሰላችሁ? ያቺ ምስኪኗ ሜሪ ድራሿ ጠፋ! ይህችኛዋ በራሷ የማትተማመን 'ሽቶ ሸተተኝ' ብላ ሀገር ይያዝ የምትል። (እርግጥ ሸቶኝ ነው። ፓንቱ ድረስ የሴት ሽቶ ምን ይሰራል? ) 'ደብዳቤ ሴት ፅፋልህ አልነገርከኝም' ብላ እሪሪሪሪ የምትል ........ ራሴን እያየሁት ሌላ ሰው ሆንኩ። በጣም የምጠላት እና ልሆን የማልፈልጋት መንቻካ ሴት ሆንኩ። በፊት እንዳይናደድ ሰማይ ከምድር የምገለብጥ ልጅ ሲናደድ እሳት ለኩሼለት ሄዳለሁ።

አሁን እንደበፊቱ ሰው ሰማ አልሰማ ችግሬ አይደለም። ይሄኔ ስንጣላም ስንታረቅ ጓደኞቼ ወይም ሰፈር ያውቃሉ። እርግጥ ዶርም ድረስ መጥቶ አንጥፎኝ ያውቃል እና ላያውቁ የሚችሉበት ሁኔታ አልነበረም። ብቻ አቡካካነው። ስንታረቅ ሁሉ እንደነበረ ቢመስለንም አልነበረም።

የሆነ ቀን ከአንዱ የፈረደበት ተማሪ ጋር የሙዝ ገበያ እያወራሁ እየገለፈጥኩ አምሽቼ ወደዶርሜ ገባሁ። መጥቶ ሲያስጠራኝ የነገር ዲዘርት ሊያበላኝ እንደሆነ ሳልጠረጥር ዊን ዊን እያልኩ ተንደርድሬ ወረድኩ። ሁለቱን እጆቼን ጭብጥ አድርጎ እያሳመመ አርገፈገፈኝ። የተፈጠረው ስላልገባኝ የያዘኝ እጁ ስለሚያም ለማስለቀቅ እታገላለሁ።

"ማነው?"

"ማነው ማን?"

"ቅድም አብሮሽ የነበረው? ከዛሬ ጋር ብዙ ጊዜ ነው አብረሽው የነበርሽው! ማነው?" ሲለኝ የፈረደበት ልጅ ትዝ አለኝ

"ኸረ ማንም አይደለም በጌታ ! ከሰው ሰው ጋር እንዳትጣላ?" ዘግይቻለሁ ልጁን ዘመዶቹን የሚያስረሳ ቡጢ ጠብቶት ነው እኔጋ የመጣው።
ልጁ ደግሞ ወሬ አማረልኝ ብሎ ከሰይጣን ጋር እንደተፋጠጠ ሳይገባው "ሜሪ ቀሽት ልጅ ናት" ምናምን ብሎ ዘላብዷል።እኔኮ ብድግ እያልኩ ባምፅም መጽሃፍ ቅዱስ ሳጠና እንደማደጌ እግዜሩን እፈራለሁ። መጀመሪያ የዘፈንኩ ቀን ዝናብ ሲዘንብ በኔ ምክንያት መብረቅ ሊዘንብ ነው ብዬ የፈራሁ ሴትዮ ነኝ። አንድ የሆነ ቆንጅዬ የክፍላችን ልጅ ቸኮሌት ገዝቶ ሰጥቶኝ ስለበላሁ በከፍተኛ የፀፀት መንፈስ የምናዘዝለት ካህን ባገኝ "አባ በድያለሁ በትዳሬ ላይ ማግጫለሁ" ልል ትንሽ የቀረኝ ሴትዮ ነኝ።

የዚን ቀን ዓይኖቹ ሲያስፈሩ
"የሌላ ሆነሽ ከማይ ገድዬሽ ሞታለሁ!" ያለኝን አመንኩት። የንዴት አይደለም። የምሩን እንደሚያደርገው ያስታውቅ ነበር።

የሚያውቀን ሁሉ "አንድ ቀን ይገላታል!" ይላል። የኔ ቤተሰቦች "የሆነ ነገር አድርጎባት!" ነው ብለው ወጥረው ይፀልያሉ። ጭራሽ ከጅምሩ ያልነበሩ የሱ ቤተሰቦች በተቃራኒው ባለቀ ሰዓት መጥተው "ልጃችንማ የሆነ ነገር ሆኖ ነው በሴት ፍቅር እንዲህ አይኮንም ፀበል ይግባ!" ይሉኛል ከነሱ ብሶ
ጓደኞቼ ቢሞቱ እሱን በእኔ ፊት አያሙትም።
ምንም ሆኜ ብመጣ

"ኸረ አርፈሽ
ቁጭ በይ እነሱ ነገ ታርቀው አልጋቸው ላይ ሆነው። 'ይህቺ ወሬኛ እንዲህ አላለች መሰለህ?' ሊባባሉብን ዝም በይ ነገ ይታረቃሉ" ይባባላሉ።

ደግሞ የምራቸውን ነውኮ 'ውይ በቃ ይሄማ የመጨረሻቸው ነው!' ሲባል በነገታው እኛ እፍፍፍፍፍፍ ብለን የሚሪንዳ ቆርኪ ለሁለት ሻወር ለመውሰጃ ይበቃናል። እንላለን። እዚህጋ ብጠየቅ ምን እዛ ትዳር ውስጥ እንዳቆየኝ አላውቅም። በየቀኑ አዲስ ነገር እንደማይፈጠር አውቃለሁኮ ግን በቃኝ አልልም። ምን እንደፈራሁም አላውቅም። ብቸኝነቱን ነው የምፈራው? ፍቺውን? እሱን ማጣቱን? አላውቅም ምናልባት እሱ ናት ያላትን ሜሪ እወዳታለሁ ይመስለኛል። ልዩ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ የሚያደርገኝን ........ ብቻ አላውቅም። ለስድቡ ለምቱ ለሌላው ለእያንዳንዱ ጥፋት የራሴን ምክንያትና ሰበብ እደረድራለሁ። ለውስልትናው ግን ምንም ሰበብ ብሰጠው ልክ አይደለም። ልክ እንዳልሆነ እያወቅኩም አልፈዋለሁ። እንደበፊቱ አያምም ........ እንደመጀመሪያው አይጠዘጥዝም። ግን አዙሪት አለው ተመሳሳይ ሂደት እዞራለሁ!!

ቸርቹን እሱም እርግፍ አድርጎ ተወው ጭራሽ ክለብ ይዞኝ ወጣ። ድሮ በመዝሙር እንዳልተባረክን ሙዚቃ መገባበዝ ያዝን .....በዛኛው ህይወቱ ዲጄ ሁላ ሆኖ የሚያውቅ ቀውጢ እንደመሆኑ ሙዚቃ ምርጫ ሲያውቅበት ..... ማሪንጌ ሬጌ ፖፕ ብለን ጨፈርን። (እነዚን ሁሉ ነገሮች አላውቅም ለምን ብሎ እንዳደረጋቸው። እሱ አንቺን ለማስደሰት ደስ የሚልሽ መስሎኝ ነው የሚለው። )

ከዓመት በኋላ ለክረምት ፀጊ እኛጋ መጣች በድጋሚ። እንደተለመደው ፈንጠዝያችን ተጀመረ። ይሄኛው ክረምት ግን ከአንድ ወር አላለፈም። አሁን ምክንያቱን በማላስታውሰው ምክንያት ንትርክ ጀመርን። ጸቡ እየተጋጋለ ሲሄድ ልጄ ስላለች ዝም አልኩ። አልቀረልኝም አንዴ በጥፊ ሲለኝ ልጄን ነው ያየኋት ፊቷ ላይ የነበረው መሳቀቅ ድንጋጤ ፊቷ አመድ መሰለ። የተመታሁ አልመስልም። የእጁ ምልክት የተሰመረበትን ፊቴን እያሸሁ ልጄን ማባበል ጀመርኩ። ምንም አልተናገርኩም። በቃ ምንም !!!

ጠዋት እሱ ስራ ሲሄድ ቀለበቴን አስቀምጬለት ልጄን ይዤ ሄድኩ። አላለቀስኩም። አልተገረምኩምም። ውስጤ ዝም ነው ያለው። በቃ እንዳከተመ ገባኝ!! ራሴን ስሰማው የገባኝ አሁን እሱ ከህይወቴ ቢጎድል አልጎዳም! ሳላየው ሳምንት ሲሆን የማብድ የሚመስለኝን ባሌን ስለመለየት ሳስብ እርፍት ነው የተሰማኝ። እቤት ስሄድ ለማሚ መፋታት ነው የምፈልገው አልኳት። ገባት! ዝም አለች አልመከረችኝም። ምንም ቢመጣ እቀበላለሁ። ተመርቄ ስራ እይዛለሁ። ልጄን አሳድጋለሁ።

ስመለስ መነጋገር አለብን ብሎ የቀጠረኝ እሱ ነው። ተገናኘኝ!! ምንም ቢፈጠር የቃልኪዳን ቀለበቴን እንደማላወልቅ ያውቃል። የእውነት የሚመስለኝ የነበረው ያ ማለት ቃሌ ነው። ያ ማለት ፍቅሬ ነው። ያ ማለት እኔና እሱ ብቻ ማንም ሳያየን በእግዜሩ ፊት እንደሚስት በህመም በድሎትም ብዬ የገባሁት ቃሌ ነው። (እርግጥ ከገባሁት በላይ ኖሪያለሁኮ ስጠለዝም ሲማግጥም ብዬ የገባሁት የለም)

"እሺ እንለያይ!" አለኝ የምር ማመን አቃተኝ።



....... ....... አልጨረስንም ........

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Meri feleke
ሁለቱ ባሎቼን ላስማማ እያሸማገልኳቸው ነው
(ክፍል 11)

"እሺ እንለያይ!" አለኝ የምር ማመን አቃተኝ።

"ከምርህን ነው? ያ ማለት አትከታተለኝም? የፈለግኩትን እሆናለሁ ማለት ነውኣ? እንደመንፈስ ዙሪያዬ አታንዣብብም። አብሮኝ የታየ ወንድ አትደበድብም? "

"አዎ አጠገብሽ አልደርስም። እንደፈለገሽ ሁኚ ቃሌ ነው። ብቻ እንደማፈቅርሽ እወቂ!" አለኝ

"እንደምታፈቅረኝ ጠርጥሬ አላውቅም። ችግሩ ፍቅርህን የምትገልፅበት መንገድ ልክ አይደለም። 24 ሰዓት ሙሉ አይንህ ስር የምትሆን ከማንም የማትገጥም ሴት እኔ መሆን አልችልም። ስታገኘኝ ያቺን ሴት አልነበርኩም። ስትወደኝ ያቺን ሴት አልነበርኩም። ያንተ ካደረግከኝ በኋላ ሌላ ሴት አድርጌ ልስራሽ ብለህ ትግል ነው የያዝከው። አይሆንም!" አልኩት

"አውቃለሁ" አለኝ። ተለያየን። ተለያየን ስላችሁ መቶ ጊዜ መተቃቀፍ መቶ ጊዜ መሳሳም እንደነበረውም አልደብቃችሁም። ለቅሶም ነበረው ከፈለጋችሁ። ለተወሰኑ ቀናት ማመን አቅቶኝ በየሄድኩበት ድንገት ዱብ ይል እንደው ብዬ እፈልገዋለሁ። የለም። ማታ ትምህርት ቤት ሲገባ ድንገት ከሆነ ሰው ጋር ካየኝ ፈነዳ ብዬ ብጨነቅም የለም። አልከፋኝም። ይልቅስ ነፃነት ተሰማኝ። በቃ ተለያይተናል። የምጠቀመው እሱ የሚሰራበት ባንክ ስለሆነ የሆነ ቀን ስሄድ የለም። ጓደኞቹን ስጠይቃቸው ስራ መልቀቁን ሰማሁ። የሆነ ቀን የጋራ ጓደኛችን ትምህርቱን ለሴሚስተር ዊዝድሮ ሞልቶ አዲስ አበባ ለእረፍት መሄዱን ነገረኝ። ጣዖቴ እንደነበረው ባሌ ሳይሆን እንደሰው አዘንኩ። እንዴት ስራ ይለቃል? እንዴት ትምህርቱን ያራዝማል?

ከአንድ ሴሚስተር በኋላ ባሌን ከተማ አየሁት። በጣም ከስቶ ጠቁሮ አምስት ወር ሳይሆን 5 ዓመት ያልተያየን ነበር የመሰለኝ።

"በየሱስ ስም ደህና ነህ?" አልኩት ደንግጬ ሳየው

"ደህና ነኝ!" አለኝ። "እቤት ሄጄ ነበር። ከቤተሰቤጋ ከሀ ለመጀመር እየሞከርኩ ነው። ቢያንስ አሁን ጴንጤ ስላልሆንኩላቸው ደስተኛ ናቸው!" አለኝ። ደስ አለኝ ያ የህይወቱ ጉድለት እንደሆነ አውቅ ነበር።

"አሪፍ አደረግክ!" አልኩት። እኔም የማውቃትን ደብዳቤ ፅፋለት አጊንቼ የተጣላሁትን ሴት ስም ጠቅሶ (የድሮ ፍቅረኛው ነበረች። ቤተሰቦቹ የሚወዷት ፍቅረኛው ነበረች።) ከሷጋ እንደሆነ ነገረኝ። እውነት ነው በቃ ተለያይተናል። እርግጠኛ ሆንኩ። ከዛን ቀን በኋላ እሷም ተከትላው መጥታ ኖሮ አብረው ከተማ አየኋቸው። ያ ማለት እቤቴ ሌላ ሴት እየኖረች ነው። አልጋችን ላይ ከሌላ ሴት ጋር እየተኛበት ነው። ያ ማለት በይፋ ትዳራችን ፈርሷል ማለት ነው። አልተናደድኩም። ጭራሽም አልቀናሁም። በቃ ለሱ ያለኝን ነገር ጨርሻለሁ። ወይም መሰለኝ።

መመረቂያዬ እየደረሰ ባለበት ጊዜ ውስጥ በባለጌ አይን ያየኝ ከነበረ ልጅ ጋር ባለግኩ። ዌል የባለግኩ የመጀመሪያ ቀን ቁጭ ብዬ ሳለቅስ አደርኩ። ትዳሬ እንደፈረሰ እያወቅኩ እንኳን የሆነ ሀጢያት የሰራሁ የረከስኩ ዓይነት መሰለኝ። ለምን እንዳለቀስኩ እንኳን አላውቀውም። ብቻ የዛን ቀን ነው ቃሌን ያፈረስኩ የመሰለኝ:: ..... የካድኩት አይነት......... የሆነ ቀን ከልጁ ጋር ወክ እያደረግኩ ስልክ ተደወለለት።

"እገሌ ነህ?"

"አዎ ነኝ ማን ልበል?"

"የሜሪ ባል ነኝ (ባልሽ ነው አንቺ አለኝ ዞር ብሎ ጥጋበኛ ነው ለራሱ። ደነገጥኩ)

"እኔ ሜሪ ከባሏ መለያየቷን ነው የማውቀው!" አለው መልሱ ድምፁን ላውድ አድርጎት እሰማዋለሁ

"እገልሃለሁ እናትህ ሆድ ብትገባ የምታመልጠኝ እንዳይመስልህ እገድልሃለሁ።" ይለዋል። ወላ አጠገባችን ያለ መሰለኝ ተንቀጠቀጥኩ። እሱ ምንም አልመሰለውም።

"ስትገለኝ ዝም ብዬ እሞትልሃለሁ እንዴ?" ይለዋል። ሲያብድ ይሰማ

እንደዛ ከደነፋ ከቀናት በኋላ የተመራቂ ተማሪዎች ፓርቲ አዘጋጅተን ዝግጅቱ የነበረው ከተማ ነበር። ልንመረቅ ሁለት ወር ነበር የቀረን። እኔን ብሎ ደግሞኮ ተተራማሽ። መግቢያ ትኬት ምናምን እየሸጥኩ ስተራመስ ከርሜ የፓርቲው ቀን ጠዋት ከጓደኞቼጋ ጫማ ልንገዛ ከተማ ስንወጣ አገኘሁት። ምንም እንዳላደረገ ...... እንደዛ እንዳልደነፋ (ማለት ሁኔታውኮ የዛን ቀን ሳይገለው የሚያድር አይመስልም ነበር።)

"እንዴት ነሽ እማ?" አላለም?

"ደህና!" አልኩት ግራ ገብቶኝ። ሁኔታው የሰማሁትን እንድጠራጠር አደረገኝ።

"ዛሬ ፓርቲ አላችሁኣ??"አለኝ ደነገጥኩ። እየተከታተለኝ እንደሆነ ገባኝ ግን ዝግጅቱ የነበረው ማታ ከ2 ሰዓት ጀምሮ ስለነበር ቢያንስ ቺኩን ትቶ አይመጣም ብዬ ተረጋጋሁ።

"ይመችሽ ፈታ በይ!! ይገባሻል!!" ብሎኝ እንደሰላማዊ ሰው ቻው ብሎኝ ሄደ። የምር ግራ ተጋባሁ። ቀልቤ አልተመቸውም። ቢሆንም ሀገር ሰላም ብዬ ቀሽ ቋ ብዬ ፓርቲውጋ ሄድኳ!!

እስከሆነ ሰዓት ድረስ ድንገት ከመጣ ብዬ በር በሩን እያየሁ አልተረጋጋሁም። ልክ ማታ 5 ሰዓት ሲያልፍ ተነፈስኩ። የዳንስ ወለሉ ላይ ከኔ ሌላ ማን አለ አልኳ!! ከአንድ የክፍሌ ልጅ ጋር ቅንጥስ ውልቅ እያልኩ ስደንስ ልጁ ድንገት እንደጅብራ ግትር ቀጥ አለብኝ። ምን ሆኖ ነው ብዬ አይኑን ተከትዬ ያየውን ሳይ ባሌ እየገባ ነበር። (ልጁ ግን ባሌን ያየ ሳይሆን ይሄ ነጩ የበረዶ ድብ ፊቱ ቀጥ ብሎ የቆመበት ነበር የሚመስለው .....እኔ ክው ልበልለት።) እዛ መሃል ግርግር ከተነሳ የተማሪውን ቀልብ እንስብና የተማሪው ምላስ ላይ መክረሜ ነው ብዬ ፈራሁና ቀስ ብዬ እንዳማረብኝ ወደሱ ሶምሶማ (በሂል ሶምሶማ ግን ኢማጅኑልኝማ ) አጠገቡ ስደርስ እጄን ለቀም አድርጎ መራመድ ጀመረ ወደ ውጪ በሩን እስክናልፍ ዝም አልኩት። ምክንያቱም አዳራሽ ውስጥ ኮሽ ካለ ነገር ተበላሽ። ከዛ ልክ ስንወጣ እጄን መንጭቄ ፊን ፊን አልኩ ........ ተረስቶኝ ነበራ!!

"እኔን ለማስቀናት ሆነ ብለሽ ነው እንዲህ የምታደርጊው?" አላለም? የምር የምለው ጠፋኝ?

አንተ ማነኝ ብለህ ነው የምታስበው? ምን ልሁን ነው? አታፍርም ሴት እቤትህ አስተኝተህ ልታስቀኚኝ ስትል? እኔና አንተ ተለያይተኛል። ረስተህ ከሆነ ራስህን አስታውሰው? የትም ከመሄድ ምንም ከማድረግ አትከለክለኝም" እሪሪሪሪ አልኩ (ቆይ ለምስሉ በደንብ እንዲገለፅላችሁ ድመት ዝሆን ፊት ስትውረገረግ ማለት ነው ላየኝ )

አንዴ በቦክስ ሲጠጣኝ ብዙ እስካሁን ስያሜ ያላገኙ ሁላ ከለሮች ታዩኝ። በቃ የሆኑ የቀለሞች ድብልቅ .... ሀምራያዊ ..... ብርቱጓዴ .... ምናምን በስንት እጅ መጫን ቢባል በዘይት በፀሎት ያላወራሁትን ልሳን ሁላ ሳልናገር አልቀረሁም። ጥምልምል ብዬ መሬቱ ላይ ከመውደቄ በፊት ቀለበኝ። የመታኝ አይኔጋ ነበር!! ከዓይኔ ስር የቀለበቱ ፈርጥ ቀዶኝ ስለነበር ደሙ ወደላይ ተፈነጠቀ። አቅፎ ይዞኝ እሪሪሪሪ የፈራሁት አልቀረም አንዳንድ እያለ የተወሰነ ተማሪ ተሰበሰበ። ደግነቱ ያው ውስጥ ሙዚቃ ስለነበረ ሊያጨስ ... ሊሳሳም ... አየር ሊወስድ ... ዜድ ሪፖርት ሊያወጣ .... ምናምን ከወጣው ተማሪ ውጪ ውስጥ አይሰማም። የለበሰው ነጭ ቲሸርት ቀይ ጠቃጠቆ ሰራ 'እሺ ልቀቃት?' 'አልለቅም።' ዝም ሲሉት 'እርዱኝ እንጂ እየደማችኮ ነው።!' አልኮል ሲሰጡት በሁለቱም እጆቹ ወደላይ ተሸክሞኛል እንዴት ያድርግልኝ? ሊያደርጉልኝ ሲሉ 'አትንኳት እኔ ነኝ ያደማኋት ራሴ ነኝ የማደርግላት!' የሚያየው ሰው ግራ ገባው።

በልብሱ ደሜን ከፊቴ ላይ ይሞዥቀዋል። በዛ ላይ እንባው ደግሞ እኔን መልሶ ያወራኛል። "እማ እኔኮ እንዲህ ላደርግ አይደለም የመጣሁት የነበረው ምዬ ነበርኮ አልነካትም ብዬ ምዬ ነበርኮ !" ደግሞ በዚህ ሁሉ መሃል መሳምም አለው። ጉንጬን
ከነደሜ አንገቴን ይስመዋል። ከሰከንድ በፊት 'ምንዓይነቱ ነው?' ሲሉ የነበሩት 'ምፅ ምፅ ሲያሳዝን' አላሉም?

........ አልጨረስንም ......

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Meri feleke
ሁለቱን ባሎቼን ላስማማ እያሸማገልኳቸው ነው!!
ክፍል 12
(የመጨረሻ ክፍል)

ጉንጬን ከነደሜ አንገቴን ይስመዋል። ከሰከንድ በፊት 'ምንዓይነቱ ነው?' ሲሉ የነበሩት 'ምፅ ምፅ ሲያሳዝን' አላሉም? በዚህ መሃል ማን መጣ ያ ያባለገኝ ልጅ ባልየው ልክ ሲያየው አወቀው መሰለኝ እኔን እንዳይለቅ እኔ ሆንኩበት ዝም እንዳይል እሱ ሆነበት። በቃ ቆንጆ ቲያትር ተፈጠረ።

"አንተ እናትህ ..... አገኝሃለሁ!!" ያኛው ለራሱ አንድ ሁለት ብሏል መደንፋት።

"ማነኝ ነው የምትለው?" የነበረው ተማሪ የተፈጠረው ሳይገባው ያኛውን ይይዛል ይመስለኛል። እኔ ለራሴ ምንም እንዳልል ልሳን ላይ ነኝ የባሌንና የልጁን ድምፅም መለየት እራሱ እየቸገረኝ ነበር። ፖሊስ መጥቶ እኔ ወደሆስፒታል እሱ ወደፖሊስ ጣቢያ ሄድን። አይኔ ስር ስቲች ተደረግኩ። (ይሄ ምልክት አሁንም ድረስ አይኔ ስር አለ። አዳሜ እየገባሽ ፎቶዬን ዙም አድርጊ አሉሽ!)

እና ከዚህ በኋላ ፍቅር ተወለደ ነው የምትዪው? አላችሁኣ? ግድ የላችሁም እንቀጥል። እኔኮ የብዙ ሰው ህይወት የኖርኩ ነው የሚመስለኝ የምላችሁ ለዚህ ነው።

በነገታው ማሚ እኔጋ ስትደውል ስልኬን አላነሳሁላትም አንድ ጓደኛዬጋ ስትደውል የተፈጠረውን ነገረቻት። እኔ መስማቷን እንኳን ከማወቄ ማሚ መጥታለች። ማታ አሳድረውት ፖሊሶቹ ለቀውት ነበር እሱን። ማሚ ቀወጠችው። ሴቶች ጉዳይም አይደለች? ደዋወለች። አሳሰረችው። እኔጋ ስትመጣ ግን ከፍቷት ነው የደረሰችው።

"ምነው?" ስላት

"ባልሽ ምን እንዳለኝ ታውቂያለሽ? "

"ምን አለሽ?" (ምንም ቢል የምገረም ይመስል)

ልጄን ይገድላታል ብላ ስትቀውጠው። "ሞታም ቢሆን ዘግይተሽ ነው የደረስሽውኮ ታዲያ አንቺ አታስጥያትም ማሚ በሷና በኔ መሃከል አትግቢ!" ብሏት ነው የምትብሰከሰከው። ትምህርት ቤት በዶርሜም አካባቢ ሆነ በክላሴ አካባቢ ብቻ እኔ ባለሁበት አቅራቢያ እንዳይገኝ ታገደ እና ከቀንት በኋላ ተለቀቀ። ሁሉም እንደነበረ ቀጠለ። ማሚም ተመለሰች። እኔም ትምህርቴን ቀጠልኩ። ከዛ ልጅጋም እንደነበረ (ምን እንደነበረ መድሃንያለም ይወቀው ) የነበረውን ቀጠልን። የሆነ ቀን ስልክ ደወልኩለት ለልጁ

"ና በናትህ ወክ እናድርግ!" አልኩት ስልኩን እንዳነሳ

"ገምቺ የት እንደሆንኩ?"

"እኔንጃ የት ትሆናለህ? መሽቷልኮ!"

"እቤትሽ ከባልሽ ጋር !" ቀልድም መሰለኝ።

"አንተ በማይቀለድ ነገር አትቀልድ!"

"እግዚአብሄርን የምሬን ነው።" ጠላታችሁ ክው ይበል። (አሁንም እማጅኑልኝ ያባለግኩት ልጅና ባሌን አንድ ቤት።)

"ይገድልሃል!! እየቀለድኩ አይደለም ይገድልሃል!" አልኩት

"እየጠበቅኩት ነው!.... ተፋጠን ነው ዛሬ የምናድረው!! ነገ ጊቢ ስመጣ ደውልልሻለሁ።" ይለኛል እየሳቀ

"እኔ አንተን ብሆን እዛች ቤት አላድርም።"
ስልኩን ዘግቼው ምን ማሰብ እንዳለብኝ ግራ ገባኝ። ምንድነው ሁለቱን አንድ ቤት የሚያሳድራቸው? ወይ አንደኛው አጋች አንደኛው ታጋች ሆነው ካልሆነ በቀደም እኔ እየደማው እናቶቻቸውን በብልግና ሲቀባበሉ የነበሩ ሰዎች አንድ ቤት ማደር? ይሄ በዓለምም የትኛው ልብ ወለድ ውስጥም የለም። ይሄ የተከሰተው እኔ ቤት ብቻ ነው። እንደ ቅዠትም እንደዱካክም እንደመባነንም እንልክፍትም ሲያደርገኝ አደርኩ።

በነገታው እንዳለውም ደወለልኝ። የምናወራው ጉዳይ አለ ብሎኝ ተያይዘን ፀጥ ያለቦታ ሄድን። ከትናንት ወዲያ ነገር ይኸው ራሱ ጉድ ወድጄሻለሁ ብሎኝ ነበርኮ ዛሬ መጥቶ "ከባልሽ ጋር ታረቂ!" ብሎኝ እርፍ!! ለልብወለድነት ሁላ አይሆንም አላልኳችሁም? የእውነት ዞረብኝ! ተጋድለው እሁድ ፖሊስ ፕሮግራም ላይ ቀርቤ "ሁለቱንምኮ እወዳቸው ነበር .... ጌታ ለእኔ ባይላቸው ነው ..... ፎሊስ ምን ታደርገዋለህ? " ምናምን ብዬ ቃሌን ሰጠሁ ስል አጅሬዎቹ ፍቅር በፍቅር ሆነው አይዞህ ሲባባሉብኝ ነው ያደሩት!

"ማንም ሰው እንዲህ አይወድም ሜሪዬ ግፍ ነው። በስመአብ እኔ እንዲህ ዓይነት ፍቅር አይቼ አላውቅም!! የትኛውም ወንድ ወንድነቱን ውጦ ከሚስቱጋ ያለ ወንድ አስታርቀኝ አይልም። የመጨረሻ ይወድሻል።"

"ሚስቱ አይደለሁም! ሚስትህ አይደለችም ስትለው የነበርከው አንተ አይደለህ እንዴ?"

"ለሱ አሁንም የሚወዳት ሚስቱ ነሽ!! ሜዬ አሁን አንቺን አጥቶ መኖር ምን ማለት እንደሆነ በጣም ተምሯልኮ አንድ እድል ስጪው!" በአንድ ለሊት ሚኒ ባሌን ሆኖ ብቅ አለልኝ። ስለሌላ ሰውም እያወራ ወይም እሱም ሌላ ሰው ነው የመሰለኝ ሳቅኩኝ

"በቀደም መስሎኝ በቦክስ ያነጠፈኝ .....ይታይሃል ? ፊቴ ገና አልጎደለም። ተለውጧል? ቆይ ምን ቢልህ ነው?"

"እንዴ እሱማ በቃ ቀንቶ ነው። ደግሞ የዛን ቀን የመጣው እኔን ሊጣላ እንጂ ካንቺጋ ሊጣላ አልነበረም። ከወንድ ጋር ሲያይሽ ደሙ ፈልቶ ነው በዛ ላይ አንቺ አጋጋልሽ! " (ወንዶችኮ ግን አትስማሙ።)

"እ........ሺ?" ደንቆኝ ነው የማየው። "የምልህ ቆይ አንተ በቀደም ወድጄሻለሁ ስትለኝ አልነበር? "

"እግዚአብሄርን ነው የምልሽ እሱ የሚወድሽን እሩቡን አልወድሽም። ደሞ ሀጥያት ነው እንደዛ እየሆነልሽ እያወቅኩ ለራሴ አላዳላም።"

ነግሬአችኋለሁኮ ከኔጋ አብረው ሲያለቅሱ የቆዩ ጓደኞቼ እሱ መጥቶ "እሷ ማለት ለእኔ የህይወቴ ካስማ ብሎ ..." እትት ብትት ሲል በግልምጫ የሚያፈርጡኝ ሰው ነኝ። የሚገርመኝ ያጠፋው እሱ ከሆነ ጥፋቱን አያስተባብልም። የሚናገርበት መንገድ ግን በቃ ለመኮነን አይመችም። የተፈጠረውም እንደዛ ነው። በጉልበት የሚሆን ነገር እንደሌለ ሲገባው ቢያንስ የተሻለ ብሎ ያሰበው መንገድ ይመስለኛል ልጁን ጠርቶ ማናገር ነው። ከዛ ያው ጠርቶ አጥምቆ ላከልኝ። ከቺኩጋ ተጣልቶ ትታው ሄዳለች።

ብቻ ለሌቱን ሙሉ ሲባባሉ ያደሩትን ሲነግረኝ እኛም ልናድር ሆነ። የታሸገ ነገር ሰጥቶኝ ተለያየን። ገብቼ ስከፍተው ቀለበቴ ነበር።

እዚህጋ የተሰማኝን ወይም የሚቀጥለውን እርምጃ እንዴት እንደተራመድኩ ምክንያቴን ልፅፍላችሁ የምሬን አሰብኩትኮ። አላውቅም! ምናልባት እዚህኛው ጊዜ ላይ ቡረቃም ህመምም ስለሌለው ይሆናል ትዝ አይለኝም ምን አስቤ እንደነበር። ኤጭ በሉና ተዘጋጁ አንዴ .......

የሆነ ቀን ልንመረቅ አንድ ወር ሲቀረን ይመስለኛል። እሱም የተወሰነ ኮርስ እየቀረው አብሮኝ ተመራቂ ነበር። ብድግ ብዬ ብቻ ቀለበቴን አደረግኩት። ተነስቼ እቤት ሄድኩ። በቃ ሄድኩ አልኩኮ .......

ምንም እንዳልተፈጠረ...... ይቅርታ የለ ...... መወቃቀስ የለ ....... ልክ ትናንት ተገናኝተን እንደነበር ሁላ ጨዋታ ጀመርን:: ስገባ ሲያየኝ የነበረው ፈንጠዝያ እንዳለ ሆኖ ...... ወላ

"ቺኳ ጎበዝ ናት አንተ ቤቴን አሪፍ አድርጋ ነው የያዘችው!" ሁላ አይነት ወሬ ነበረው። የገዛነውን መሬት እንደሸጠው ነገረኝ ሚስት ሚስት አልሰራራኝም። ይመችህ አልኩት።

"አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው እሱን የወደድሽው ሎቲ የሚያደርግ ወንድ አትወጂም አልነበር?"
(ሲቆይ ጆሮዬን ልበሳልሽ ከወደድሽ ብሎኛልኮ)

"አንተ ግን በጣም ከሳህኮ እህል አታበላህም ነበር እንዴ?" (እኔምኮ ከስቻለሁ ከዛ በላይ የሚከሳ ቀሪ ስጋ ስላልነበረኝ እንጂ)

"በቃ እስክንመረቅ ለምን አብረን አንሆንም?"

"እንዲህኮ ደስ ስንል" ምናምን ተባብለን ወደ ዶርም ተመለስኩ።

ምንም ሳይጨመር ሳይቀነስ በቃ እንዲህ ነው የሆነው። ዶርም ስመለስ ሁሉም ሊበላኝ በጣም የገረመኝ ማሚ ታብዳለች ብዬ ስጠብቃት።

"እንኳን ነገር አበረድሽ ቢያንስ ተረጋግተሽ ተመረቂ! እኔማ በእልህ ከአሁን አሁን የሆነ ነገር አደረጋት ብዬ
ሌት ተቀን አምላኬን ስወተውት ነው የማድረው!" አለችኝ። እንደባልና ሚስት ሳይሆን እንደ ፍቅረኞች ነገር ሆንን ..... ያለፀብ አለቀ እና ልንመረቅ አንድ ቀን ሲቀረን አብረን አደርን!!

በነገታው እነማሚ መጡ ልጃችን ልታስመርቀን መጣች። ተመረቅን!! እንደማንኛውም ተመራቂ ተማሪ ፊታችን እስኪገረጣ ፎቶ ስንነሳ ዋልን!! እንዳሰብኩት በማእረግ ባልመረቅም በሚያኮራ ውጤት ተመረቅኩ። በምወዳቸው ሁሉ ተከብቤ ያ የናፈቅኩት ቀን ሆነ!! በሚቀጥለው ቀን ቤተሰቦቼን ሸኝቼ ዶርም ተመለስኩ። ለማንም ምንም ሳልል እቃዬን ሸካክፌ ወደአዲስ አበባ ......... ለማሚ ያለሁበትን ለማንም እንዳይናገሩ አስጠነቀቅኩ። ብዙም ሳልቆይ የግል ዩንቨርስቲ ማስተማር ስራ ጀመርኩ።

በወሩ ደወልኩለት።

"ማወቅ ስላለብህ ልንገርህ ብዬ ነው። ፍቅርን አርግዣለሁ!" አልኩት። ደስ አለው። እብድ ናት በሉኝ በማርገዜ ደስታዬን ብታዩት። ከእርሱ ውጪ ከሌላ ወንድ ልጅ መውለድ አልፈልግማ!!

"የት ነሽ?" ቦረቀ። "ላግኝሽ? We can fix this eko ልጆቻችንን አብረን እናሳድጋለን አይደል? "

"ልጆቻችንን እናሳድጋለን። እኔና አንተ ግን አንድ ላይ ሆነን አይደለም። ልጅህን መጥተህ እንድታይ ስወልድ አሳውቅሃለሁ። በልጆችህ ህይወት ውስጥ እንደፈለግክ ሁን አባታቸው ነህ። በእኔ ህይወት ውስጥ ግን አይደለም።" አልኩት።

happily divorced

እና ዛሬ ላይ ለልጆቼ ሳወራላቸው እንዲህ ነው የምላቸው

"እንዳባታችሁ ያፈቀረኝ ወንድ የለም! ወደፊትም አይኖርም። እንዳባታችሁም ደግሞ የጎዳኝ ወንድም የለም። ....... አባታችሁ ጣኦቴ ነበር። በምድር ላይ ትልቁን ስጦታዎቼን እናንተን ሰጥቶኛል። በእናንተ ደግሞ ደስተኛ ሴት አድርጎኛል። መልካም ነገር ብቻ ይግጠመው።"

................ጨርሰናል ........

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Meri feleke
[መደነቃቀፋችን ዳንስ መስሎን ነበረ]
የስልኬ ሙዚቃ ማጫዎቻ ላይ ሙሉ ቀን እየተደጋገመ ሲዘፍን የዋለው የBen E.King 'stand by me' የሚል ዘፈን ነው። ሁልጊዜ ለምን እንደዛ እንደማደርግ አይገባኝም ፤ አንድ ሙዚቃ ደጋግሜ አደምጣለሁ። አንዳንዴ ለተከታታይ ቀናት ሌላ ዘፈን ሳልቀላቅል ካለማቋረጥ የምሰማቸው ዘፈኖች አሉ፤ ከወደድኩት ነገር ላይ ቶሎ መላቀቅ የሚከብደኝ ለዛ ነው በቃ ከያዝኩ እንደዚ ነኝ ስወድ አፍናለሁ ስወድ አስጨንቃለሁ፤ ለራሴ ራሱ የሚረብሸኝ ባህርዬ ነው እና አዲስ ለሚተዋወቁኝ ሁሉ መጀመሪያ የምናገረው ነገር "ስወድ አስጨንቃለሁ.....ስወድ ችግር አለብኝ"ን ነው። ዘፈኑ ደግሞ አሁን እንዲህ እየተስረቀረቀ ሩቅ ልውሰድሽ ይለኛል፤ ረስቼዋለሁ ትቼዋለሁ ወዳልኩት ትናንት አጅቤሽ ካልሄድን እያለ ያባብለኛል ....
"አሻቅበን ያየነው ሰማዩ ተገምሶ ላያችን ቢደፋ ፣ ወይ ደግሞ _ ግዙፍ ተራራ ተንዶ ከውቅያኖስ ገብቶ ቢጠፋ፣
ማልቀስ እርም ነው ለኔ _አንዲት ዘለላ እንባ እንኳ 'ካይኔ ጠብ አትል አትፈስ፣
አንተ አጠገቤ እስቆምክ ከጎኔ እስካለህ ድረስ፣" አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው በአብሮነታችን ውስጥ የነበሩ እንደቀልድ ያለፍናቸው ፤ በእብደታችን ያሸበረቁ በሳቅ ያከበብናቸው በኩርፊያ ያጀብናቸው አያንዳንዱ ቅፅበታት እጅግ ውብ ቢሆኑም ልክ ናቸው ብዬ የማስብበት ዘመን አልፏልና ድጋሚ በጨረፍታም ላስባቸው አልፈልግም። በርግጥ አንዳንዴ ከነዚህ ቀናቶቻችን ጥቂት የእብደት ስራችን የጎላባቸውን
እያነሳሁ ለወዳጆቼ ስነግራቸው ( በትንሹ፤ ስለ ምሽት ባሌት ዳንሳንችን፣ ፀጉሬን ሰብስቦ በስርአት ስለሚያያይዝበት ሻጤ። በአብዛኛው ደግሞ ስለ ፍትወት፤ የቃምነው ጫት ገረባ ላይ ስለምንፈፅመው ሩካቤ፣ ማዕዳችንን ገፍተን ስላጧጧፍነው ወሲብ፣ ዝናብ እየዘነበ ጭቃ ላይ ስላደረግነው ፣ ምናምን) ወይ 'ያማችኋል ግን?' ወይም 'እብድ ናችሁ? ' ካልሆነ ደግሞ 'ይሄ ልክ አይደለም ! '
ይሉኛል። የምንወደው እብደት ውስጥ አብረን እንዋኝ እንደነበር፤ ነፃነት እና እውነት ከሰሩት እብደት በላይ ልክነት እንደሌለ ጨምሬ ልነግራቸው ፈልጌ በቸልታ ትከሻዬን ሰብቄ እተወዋለሁ። ግን እንደዛ ያሉኝ ዕለት አመሻሽ ላይ ናፍቆኛል ልቤ እስኪርድ ናፍቆኛል አለ አይደል የኔና የእርሱ አለም በራሳችን ህግ ተከልሎ በእብደታችን የቆመ ፍፁም ሌላ ፕላኔት ነበርና ማንም የሰራነውን አለም ልክ አይደለም ቢለን የምንሰማ አይነት አልነበርንም፤ አንዳችን ላንዳችን እስካለን
ድረስ የምንፈራው ምንም ነገር አልነበረም። "ምሽቱ በመጣ ጊዜ፤ ምድር ፅልመት ስትለብስ፣ ድቅድቅ ጨለማው መሃል ጨረቃ ብቻ ተግታ ብርሃኗን ለእኛ ስትለግስ፣ ፍፁም ልፈራ አልችልም _
አንተ አጠገቤ እስቆምክ ከጎኔ እስካለህ ድረስ፣" ከሆነ ጊዜ በፊት ወደ ኋላ ተመልሼ አመሻሻችን እንዴት እንደነበር ሳጤን ከሰርክ እለት ዑደታችን ( ስንራኮት ከዋልንበት ከእርሱ ቤት ወደ ቤቴ ሲሸኘኝ) በመንገዳችን አሳብረን የምናልፈው የኡሪዎች ኳስ ሜዳ ነበር፤ ልክ እዛ ስንደርስ ከላያችን የምታበራ ጨረቃ ጥላችንን ፍንትው አድርጋ ስታሳየን ከጥላዎቻችን ጋር የደነስንበት በምሽት ከደመቀ ውበቷ ላይ ቅርፁን ቀይሮ ብርሃኗ ዜማ ሆኖ በጆሮዎቻችን ተንቆርቁሮ እንደነበር አስቤ አውቃለሁ።
በፊት ላይ ሲናፍቀኝ ከሁሉ ከሁሉ በግድግዳው እና በአልጋው ክፍተት መካከል ከፀጉሬ ሾልካ የወደቀች የአንዲት የሻጤ ነገር ያሳስበኝ ነበር። ስለ እርሷ ያልተመለሱ ብዙ ጥያቄዎች ነበሩኝና ባገኘውና ብጠይቀው እወድ ነበር። ከኔ በኋላ ቤቱን እና ገላውን የጎበኘች እንስት ከአልጋ ተንሸራቶ በዚያ በኩል መሬት ያረፈ የውስጥ ሱሪዋን እጇን ሰዳ ስታስስ የፀጉሬ ሁለት ዘለላ
የተተበተበበት ያን ሻጤ ያገኘች እለት ምንድነው የሚሰማት? ምንስ ነው
የምታስበው? እርሱም ከእኔ ጋር እንደለመደው ፍቅር ሲሰሩ የተንጨፋረረ ፀጉሯን ከጉዳያቸው በኋላ ሰብስቦ ሊያስይዝላት አልጋቸው ላይ የተበታተ የፀጉሯን ማያያዣ ሲያስስ አንዱን ተሳስቶ ገፍቶ በቀደመው ክፍተት ቢልከው፤ አልጋ ስር የተገናኙ ሁለት ሻጤዎች እንደ ባለቤቶቻቸው በጣውንትነት ስም ይጠራሩ ይሆን? የየራሳቸውን የውድቀት ታሪክ እና የሴቶቹን እንዝህላልነት እያነሱ ይወያዩ ይሆን? ወይስ... ለየባለቤታቸው ወግነው ቀጫጫ ሽቦ አካላቸውን ለድብድብ ያነሳሉ? ወይስ... እዛው ባሉበት ብዙ ቀናትን አሳልፈው ቤት አፀዳለሁ በሚል ሰበብ አልጋ በምትጎትት ሶስተኛ ሴት እጅ ከወዳደቁበት ተነስተው የወረሳቸው ትቢያ እፍፍ ተብሎላቸው ድጋሚ አናት ላይ ይወጣሉ? እና የናፈቀኝ እለት ወይስ ...... ወይስ ... ወይስ እያልኩ ስለ ጥቃቅኗ ነገር ሁሉ በጥልቅ የማስበው እና የምብከነከነው ከእለታት ድሮ ቀን በወጣች ደንጋዛ እና ፈዛዛ ጨረቃ ደነስን ያልነው መደነቃቀፍ፣ በሌላ ጥንት በሚመስል ቀን ከፀጉሬ የወደቀ ወልጋዳ ሽቦ ምናምን የገዘፈ ጥቅም ኖሯቸው ሳይሆን ከእርሱ ጋር የነበሩኝን ቅንጣቶች በሙሉ ከቋጥኝ አግዝፌ ስለማይ ነበር።
አሁን ላይ ዛሬን በአሁን መለካት ሳይሆን በነገ መስፈር ስለለመድኩ እንደ ጥንቱ
ስወድ አላስጨንቅም፣ አሁን Ben E.King ሳምንት ሙሉ ልብ በሚበላ ብሉዝ ቢለምነኝ እንኳ የሚያንኳኳውን የትዝታ በር ለመክፈት የምጥር አይነት
አይደለሁም። ዘንድሮ ከተረት እና ከኩሸት የቻልኩትን ያህል ተምሪያለሁና ይሄ ይሄ ትዝ ሲለኝ የምለው "የሁሉንም ነገር ዋጋ በሰአቱ መረዳት ብንችል ህይወት እንዴት ውብ ይሆን ነበር" ነው። የማዝነው የማይገባቸውን ዋጋ ሰጥተን ላጡን እና ላጣናቸው ስናላዘን ስለተላለፉን ቀናት ነው።

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Elssa Mulugeta
ልጅ ስትወልድ ነው ቤተሰቦችህን የምታመሰግነው ከቤ :)
ህፃናት ቤትህን ሲያምሱት ህወሀት ማረኝ ትላለህ። ለምሳሌ ልጅህ የቤትህን ቴሌቪዥን ኩባያ ወርውሮ ሊሰብርብህ ይችላል ። ነገ ወሳኝ ስብሰባ አለኝ ብለህ በክብር ያኖርከውን የሱፍ ጃኬት ባሊ ውስጥ ነክሮ ሲያንቦራጭቅ ልታገኘው ትችላለህ ። ውዷ ባለቤትህ ናፍቃህ እቅፍ አድርገሀት ጉያህ ከመክተትህ ቅናት ያንገበገበው ፈልፈላህ ስኒ ወርውሮ ግንባርህን ይገምስሀል 😄 በተለይ ወንድ ልጅ ራሱን የቻለ ወያኔ ነው። ልጄን ቅዱስ ብዬ ከምጠራው ጌታቸው ረዳ ብዬ ለምን አልሰየምኩትም የሚል ቁጭት አንገብግቦኝ ያውቃል። ሌላው ልጅ ስትወልድ የምትረዳው የሴቶችን አስማት ነው። ሴት ልጅ ምትሀተኛ ናት። ሚስትህ የውጭውን ስራ ሰርታ ቤት ተፍተፍ ብላ ልጅህን እንደፀባዩ ስትይዝልህ የሴት ልጅን ተፈጥሮ ታደንቃለህ። ብዙ ወንዶች በባህሪያችን ስልቹ ነን። 10 ደቂቃ ልጅህን አቅፈህ ተቀምጠህ ትግል ሲጀምርልህ ትማረራለህ። አንዳንዴ ረዥም ገመድ አዘጋጅቼ ከጠረጴዛ ግርጌ ልሰረው ወይ ልትል ትችላለህ ።
ቢሆንም...ቢሆንም...ወንድም መላ አለው። ልጄ ሲረብሽ ጊልዶና ሳንቾ ትዝ ይሉኛል። ጊልዶ የሚደብረኝን ያህል መርቄው አውቃለሁ። የጊልዶ ባዶ ...ባዶ ሙዚቃ ቅንብሮች ልጄን ያስጨፍሩታል። የኤልያስ መልካ አጥንት እየወቀሰኝ ሳንቾን እከፍትለታለሁ። ሙዚቃው እስኪፈፀም የሰላም አየር እምጋለሁ። ሙዚቃው ሲፈፀም Phase 2 ጦርነት በይፋ ቤቴ ውስጥ ይጀመራል። ህወሀት ማነው ቅዱሴ ያንሰራራል። የቤቱ ህገመንግስት ተጣሰ ይለኛል። ወልቃይት ....(ወይኔ ጨለልኩ በቃ !)... አንተ የተቀመጥክበት ቦታ የኔ ነው ብሎ ያንባርቃል። እየተንጫነጭኩ ቦታዬን አስረክባለሁ ።
ከልጅህ ጋር ትንሽ ከተጎራበጥክ ባለቤትህ በግልምጫ ታነሳሀለች። ያልሰከነ ቡና ልትቀሳልህ ትችላለች...እንደ ጣና ሀይቅ በቀጠነ ሽሮም ልትመታ ትችላለህ። This is life brother!
....ፈጣሪ ላያስችል አይሰጥም ብለህ ስትማረር ብትውልም የልጅህ አንገት ስር ገብተህ ስትስመው አመፁን ትረሳዋለህ። ሌላ ልጅ መድገም ሁሉ ያምርሀል። ህፃናት ገነትን በአንገታቸው ይዘው ይዞራሉ። በስራ እየጦዝክ በመሀል ልጅህ ይናፍቅሀል። ብጥብጡ.. .አመፁ...ረብሻውም ለካ አንድ መሳጭ የህይወት ሂደት ነው አባዬ ! እየከነፍክ ቤትህ ትገባለህ.. .የሶስተኛው ዙር ጦርነት መለከት ይነፋል :)

@getem
@getem
@paappii

#mikael aschenaki
Forwarded from WORDS
“Express your love, we can't read minds. “

@words19
ዜማና ሰውነት
[ግዕዝ፤አሃዱ]
ሰዎች"እንዴት ነው ሰብራህ የሄደችው ?" ብለው ሲጠይቁኝ " ልቤ እስከሚያነክስ" ብዬ ከመለስኩላቸው ረጂም ጊዜ ቢያልፍም ድንገት ቀና ስል የጠራ የመስከረም ሰማይ አይቼ ናፈቀችኝ ።
ለእንቁጣጣሽ በፈካ ቢጫ አደይ ያቆጠቆጠ አረንጓዴ መስክ ላይ ይሄን ብራ ሰማያዊ ሰማይ ደርበን የተራከብን ነን። በሚያሳሳ የመስከረም ቀን መኻል
አፍላነት ያቀጣጠለው፤ ነፋስ ስሞ ያበረደው ገላችን ላይ ጣል ያደረግነው፤ የተጋፈፍነው ሰማይን ነው። ሽቅብ ያየሁበትን አይኔን ቶሎ ሰበርኩ እንጂ ባተኩር ከጭኗ የተላቀቀ የጠይምነቷን ባዘቶ ጉም ሰርቶ አየው ነበር። ሁሉ እንደዛሬ ስላይደለ ልብ ብዬ ባየው ህመሙ ነፍሴ ላይ ያረብባል እንጂ። በልጅነት ቀናቷ ድንግል ልቧን እና ነፍሷን የገረሰስኩ ተቀዳሚ ግዕዟ ነኝ። ማለት የመጀመሪያውን መሳም የትኛውም መሳም እንደማይሽረው፤ የመጀመሪያው ዜማ ድንቅነት በሌሎች እንደማይሸፈነው፤ በልቧ ቅኝት ላይ ተደላድዬ የተፃፍኩ ማንም የማይሰረዘኝ ዜማዋ ነኝ። ለመጣ ለሄደው ሳትሰለች የምትነግረኝ ገድሏ ከአንደበቷ የምወጣ ብቸኛ ተረኳ መሆን ትምክተኛ አድርጎኝ፤ ልታቅፈኝ የዘረጋቻቸው እጆቿ አየር ላይ
እንደተንከረፈፉ ትቻት ስነጉድ፤ በማንም ያልተሳሙ ለጋ ከንፈሮቿ ሊስሙኝ ሲተጉ
ስገፋ ተስፋ ቆረጠችና ያልቃል ብዬ ያልገመትኩትን ለኔ ያላትን ፍቅር ለሌላ አጋርታ አገኘኹዋት። በኔ ግዕዟ ላይ እዝል ደርባ የምታዜም ሆነች። ፀፀት ልቤን ሲበላኝ እስከዛሬ ትምክህት የሸበበው አንደበቴን ከፍቼ እንደምወዳት
ነገርኳት። ሁለተኛ ፍቅሯ ከኔ እንደማይበልጥባት አውቃ ይሁን የዘመናት ህልሟ ስለሆንኩ ብቻ ግን መውደዴን ስነግራት ደስ አላት አቅፋኝ አለቀሰች። "ሁሌም አለሁልህ "አለችኝ።
ፍቅሬ በእኔ በግዕዟ እና በሁለተኛዋ እዝሏ ዜማ የምትንገላታ አሳዛኝ አራራይ
ሆነች። በዚህ ዜማ የታመምን ሶስት ሰዎች ነበርን። ከእርሱ ጋር አሸብሽባ
እንደምትመጣ እያወኩ በቅዳሴዋ ልዘምም ደፋ ቀና ስል ከጠይም ገላዋ ላይ የሚነሳ የእዝሏ ጠረን፣ ከሴትነቷ የሚተን የእርሱ ጢስ ዜማዬን እና አቋቋሜን ቢያዛባውም። በ"የኔ ነበረች፤ ሁሌም የኔ ነች። " እምቢተኝነት በቅኝት መኻል ሽብርክ የሚል ልቤን ታቅፌ ወረቧ ላይ ከርሚያለሁ። አሁን ይሄን እኔ እና እርሷ የተጋፈፍነውን የመስከረም ብራ ሰማይ ቀና ብዬ ባይ በተመሳሳይ ቀን እኔ ጋር ከመምጣቷ በፊት ከእዝሏ ጋር የነበራትን ወረብ በበራሪ ኮከብ እንደ ስዕል አስቀምጦ ያሳየኛል። ግን አይኔን አቅንቼ ሰማዩን ሳይ ትዝ ባለችኝ ቅፅበት አንገቴን መልሼ እጄን ደረቴ ላይ አጣምሬ የልቤ ድሪቶ ውስጥ ቀበርኳት። ቢሆንም እኔ ምንም የልቤ ስርቻ ውስጥ እንደመነኛ ልጥላት ብሞክር በእርሷ ልብ ውስጥ ግን ያለኝን ቦታ አውቃለሁ፤ ብዙ ሁለተኞች ያልሻሩኝ የሁሉ ነገር አሃዱዋ ተቀዳሚ ግዕዟ ነኝ። [እዝል፤ ተደራቢ]
ትዝ የምትለኝ በእኩለ ሌሊት ነቅቼ ሲጋራዬን ለኩሼ ያጨስኩ ቀን ነው። ከሁሉ ከሁሉ የምትወደው ከንፈሬን ነው። ከንፈሬ ላይ ባለችው ጥቁር ነቁጥ ሁሉ ሳትቀር ትቀና ነበር "ማርያም ለምን ሌላ ቦታ አልሳመችህም?" ብላ ታኮርፈኛለች። ሌሊት እንዳልቀሰቅሳት ተጠንቅቄ ተነስቼ ወንበር ስቤ ተቀምጬ
ሲጋራዬን ስለኩስ ከእንቅልፏ ትነቃለች። በቅጡ ያልተከፈቱ አይኖቿን ገርበብ
አድርጋ " ጭሱን ከአፍህ ልውሰድ?" ትለኛለች። ቀጥላ ከመኝታዋ ተነስታ ጭኔ
መሃል ትንበረከክ እና አጭሼ የምተነፍሰውን ጭስ ከአፌ አንደ ወፍ ትቀበላለች። የዛኔ ከንፈሮቻችን ተጋጥመው ቅጡ በማይገባን ወረብ ቆመን መወዛወዝ እንጀምራለን።
ሁሉም እንደሚያውቀው ከኔ ቀድሞ በገጠማት ዜማ ያልተደሰተች ዘማሪ ነች እኔ አፍላነቷ ጎትቶ ከቀሚሷ ስር ከገላዋ ላይ ያዋለኝ እዝሏ ተደራቢ ዜማዋ ነኝ።
አለ አይደል በግዕዝ የጋለ እሳቷን አቀዝቅዤ አረጋጋታለሁ። ቀልበ ቢስ ቀልቃላ እና ሃይለኛ ቅላፄዋን ዳብሼ ገርቼ እመልስላታለሁ። የመጀመሪያዋ ነውና ለግዕዟ ያላትን ስሜት በአንዴ አውጥተሽ ጣይ ባልላትም። በኔ እርጋታ አገግማለች። ፍቅር ከጀመርን ከጥቂት ጊዜ በኹዋላ በወረባችን መኻል የቀደመ ትትርናዋን ችላ ብላ ሁሉ ነገሯ ሲቀየርብኝ ግራ ገባኝ ። ቆይቼ አስቸጋሪ ግዕዟን አስጣልኳት ያልኳት እርሷ የቀደመ ቅላፄዋን ሳትተው በእኔ ላይ ደርባ ማዜም መጀመሯን አወኩኝ ። ይህን ሳውቅ እውነቱን በልቤ ደብቄ ሸፋች ልቧን ላረጋጋ ርቃኗን አስተኝቼ ከላይ እስከ ታች በከንፈሬ እየዳበስኩ በእንባዬ አርጥቤ አጠብኳት። እንዲህ ሳደርግ በሃይለኛ እና እምቢተኛ የሚማረክ እርሷነቷ ለኔ መለማመጥ
ትኩረት መስጠት ተሳነው። እናም ያኔ የጀመርነው ለስላሳ ቅኝት ዜማችን
ተቆራረጠ። አሁን ዛሬ ላይ ስለ እርሷ ሳስብ ሃዘን በልቤ ያልፋል ። በህይወቷ ከተጣባት ጠንካራ ግዕዝ ላሳርፋት የጣርኩ ለስላሳ እዝሏ ብሆንም እዚያና እዚህ የሚረግጥ አሳዛኝ አራራይ ነፍሷ ግን ያን እንድታደርግ አልፈቀደም። ከብዙ ጊዜ በኹዋላም ቢሆን እኔ ላይ ካደረገችው ክህደት ይልቅ ለቅብዝብዝ እርሷነቷ እና በዚህ ምክንያት ለሚበላሹ ዜማዎቿ የማዝን ተደራቢ ዜማዋ እዝሏ ነኝ። [አራራይ፤ አሳዛኝ] ሰዎች በሰራኹዋቸው ነገሮች በሙሉ ይበሳጫሉ። ይበሳጩና ያዝናሉ።
የበደልኳቸው እንኳን ትንሽ ተበሳጭተውብኝ ቀጥሎ የሚያደርጉት ነገር ቢኖር ለእኔ ማዘን ነው። እኔነቴ ሰው ጨክኖ ጆሮ እንደ ማይነፍገው አሳዛኝ ዜማ ነው፤ እንደ አራራይ። ስለ ዜማ ሳስብ ስለ ሁለቱ የቀድሞ ፍቅረኞቼ አስባለሁ። የመጀመሪያው ግዕዜ
ነው ...... ልጅነቴን በጥበቃ የጨረሸ፤ የኮራብኝ፤ የተጀነነብኝ፣ ደጅ ያስጠናኝ፣
ያስለመነኝ፣ እልህ ያጋባኝ ፣ የፈተነኝ። ሁለተኛው ደግሞ እዝሌ ነው ......የደረብኩት ፣ ያረጋጋኝ ፣ያበረደኝ ፣የወደደኝ። ስለምነው የከረምኩት ግን የገፋኝ። በኋላም ከሚያሳርፈኝ ጋር እፎይ ማለቴን ሲያይ ስመኘው የኖርኩት ፍቅር ካልሰጠሁሽ ብሎ ፊቴ ቆመ። አመታት እርሱን የኔ በማድረግ ምኞት አልፈው በመጨረሻ ፊቴ ሲቆም አይሆንም ማለት አቅቶኝ፤ እዝሌንም በቃኸኝ ግዕዜን አግኝቻለሁ ብዬ እንዳልለው የምጠለልበት የምሰክንበት ጥጋቴ ነውና እንዳላጣው ፈርቼ በሁለት ቢላ የምበላ ሆንኩኝ ። ሁለቱንም በተለያዩ ምክንያቶች ሳላስባቸው ውዬ አላውቅም። ባስታወስኳቸው ቁጥር ግን ሃዘን ይከበኛል። ሁለቱም በመቅበዝበዝ እና በመንገብገብ ያበላሸኹዋቸው የህይወቴ ዋና ዋና ዜማዎች ናቸው። በእርግጥ ከነርሱ በኋላም ያማረብኝ ቅላፄ የተዋጣልኝ አቋቋም የለም ግን እንደ ሁለቱ ያበላሸሁት የለም። አሁን ላይ ከግዕዜና ከእዝሌ የተረፈኝን አራራይ ዜማ ለራሴ ወስጄ ሌት ተቀን እህህ እላለሁ።
ሁሉን የእኔ ይሁን የሚል ልጅነቴን ለተከተለ ደመነፍሴ ፣ በሁለት ዜማ አንድ ቅኝት ለናፈቀ ለጋነቴ ፣ ለባተልኩት ፣ ለባከንኩት ፣ ከሁሉ ከሁሉ በአንድ እለት ግዕዝም እዝልንም ለተቀበለ ሴትነቴ በአራራይ ዜማ እህህ እላለሁ ። በመጨረሻ የገባኝ ግን ሁሉ በአሳዛኝ ዜማ እንደሚቋጭ ነው ፤ ህይወት የሚባል ውብ ነገርም ቢሆን

@wegoch
@wegoch
@paappii

#elssa mulugeta
Forwarded from Sunset Hiking
#Sunsethiking is hosting a day hike to "DAMOCHA"

Damocha Mountain is an eroded volcanic crater with a jagged rim surrounding the valley floor far below. The valley features a drainage stream that comes out just to the right of the museum and provides an easy, well-worn route past the lower peaks that hide the real summit (from the vantage point of the park). This trail ends at a tiny mountain village.

📅Hiking Date :- Aug 15, 2021 (Nehase 9), 2013).

💵 Hiking #Cost:- 675 ETB only

🛫Departure: Piasa (Taitu Hotel)

Departure Time - 12:30 Am LT

🎉🎊Package includes🎋🎊
🚍 Transportation
🌲 Bottled water
🌺 Guide + scout
🍂 photography 📷
💐 Breakfast
🏖 lunch

NB.
🚫 Sanitizer & facemask mandatory!

👉 walking hour: 5 hour (up to 20 km of walking)

suitable for: HARD, basic skill required

for more join the

🔸channel @sunsethiking🍁
🔻📷 @sunsetphotography🍁

🎫 tickets available at
@Paappii ( +251922303747)
2024/09/23 10:33:58
Back to Top
HTML Embed Code: