Telegram Web Link
... ድግግሞሽን ማን ያስቀራታል? 'የሆነ ወቅት' የሚባል ነገር የላትም። ከተኖረ ይደጋገማል...

.. ደግሞ የአንደኛው ክፍል ድግግሞሽ ይደበዝዛል... ይረሳል...ይቻላል ... ይተዋል...ይታለፋል። መተው እንዴት እድለኝነት ነው?! መርሳት ምን ያህል ፈውስ ነው?! ማለፍን የሚያክል ...?

... "በቃ ቻለው! ትሰማለህ? ለምን ቻል አታደርገውም?" ማለትን የለመደባቸው ሊታዘንላቸው በተገባ! መቻልን በቀመሱና እንዲህ ሲሉ ባልተሰሙ!

... በሞኝነትህ ሰምን ችለህ የነበርከው ሰውዬ 'መቻል'ን ስትረዳ ሐሳብ ማገላበጥ ሲያቃጥል!... ብስብስ ሐሳብህን ከመቻል መጋዘንህ እየቀናነስክ ስትበላና መዋጥ ሲሳንህ፥ ሲያበግን! (ኢሄን ነገር ምንም አይፍቀው። አኝከው ሲለቁት ከተወጠረበት ሄዶ ይለጠፋል። ደሞ ሌላ ቀን ለተራው አሳስቦ ይተኛል! ተቻችሎ...)

..<መቻል አስተማሪን ማን አስተማረው?>
ገርሞኝም አላባራ!
(አዌ እሜ)
@awezeru
@awezeru
@wegoch
@wegoch
አልወዳትም እንጂ አልጠላትም...

ሞታ የለቅሶ ድንኳኗ ውስጥ የተነጠፈው ፍራሽ ላይ ተቀምጬ ሊቀብሯት በሳጥን አሽገው ጥጉ ላይ አስቀምጠዋት ሲላቀሱ የማስበው

'አልወዳትም እንጂ አልጠላትም' .... የሚለውን ነው... በሃሳቤ መሃል ከቤተሰብ ወይ ከወዳጅ አንዱ ሲያፈጥብኝ

"ወይኔ እህቴን .. ወይኔ እህቴን ... ትተሺኝ አትሂጂ .." እሪታዬን አቀልጠዋለሁ ... እንባዬ ይተባበረኛል::

እህቴ ናት ... አዎ የሞተችው እህቴ ናት ... ብዙ መለስተኛ ክፉ ነገሮች አድርጌባት አውቃለሁ ...

ለምሳሌ ለሰርጏ ሰዓታት ሲቀሯት የሙሽራ ልብሷን በእስኪሪብቶ ቀለም ቡራቡሬ እንዳደረግኩባት አይነት ትንንሽዬ ክፋቶች ...... ግን አልጠላትም!!!

ባሏን ከማባለግና ሰርጏን ከማበላሸት የትኛው ትልቅ ክፋት ነው?

"ካላንቺ እንዴት ልኑረው?" እያለ ወገቡን ተደግፎ ድንኳን ውስጥ ይዝረከረካል ባሏ ... እኔ ሰልችቶኝ እስካቆምኩበት ቀን ድረስ እኮ ከሚስቱጋ ከተኛበት ቀስቅሼ የማባልገው ሰውዬ ነበር!! .. እሺ ከኔና ከሱ ማናችን የባሰ ክፉ ነበርን ለሷ?

አያችሁ አልወዳትም እንጂ አልጠላትምኮ ...

ኦው የምርቃቷ ቀን የጫማ ሂሏን የሰበርኩባትን መቼም እንደክፋት አትቆጥሩብኝም ... ምርቃት የምታክል ክፋት !

ያስቃምኳት... ያሰከርኳት ... ያስጨስኳት .... ያጣበስኳት ... ይሄ መቼም ከውለታ እንጂ ከተንኮል ከተቆጠረ ... ደግ ነገር የለም ማለት እኮ ነው...ሆ!!

"እህቴ መካሪዬ ... " ... እናቴ አየችኛ ... ለቀስተኛውን ተቀላቅዬ የፈረደበት ዓይኔን ላስጨንቀው ...

እህቴ ክፉ ሴት ሆና አይደለም!! በተቃራኒው ከማውቃቸው ሰዎች ለፍፅምና የቀረበች መልካም ሴት ናት .... የማልጠላት ለዛ ነው ...

የማልወዳት በዚህ ፍፅምናዋ እሷ በፍሬም የተቀመጠች ሞዴል ሆና ቤተሰቦቼ እኔን በሷ አምሳል ጠፍጥፈው ሊሰሩኝ እያቦኩ የሚጠፈጥፉኝ ሁሌም በጅምር ያለሁ ቡኮ የሸክላ ጭቃ መሆኔ ነው ....

እሷ በትምህርቷ አንደኛ ስትወጣ 'እህትሽን አየሻት?' ያቦኩኛል .. ጎበዝ ተማሪ አድርገው ሊቀርፁኝ ሲጀምሩ እሷ በሆነኛው እስፖርት አሸንፋ ዋንጫ ይዛ ትመጣለች .....

ደሞ የጀመሩትን አፍርሰው ያቦኩኛል ... እስፖርተኛ እንድሆን ሊቀርፁኝ ይጀምራሉ ... ገና ቅርፅ ሳልይዝ እሷ በሆነኛው በጎ አድራጎት ተሳትፋ ስሟ ይወደሳል ... ደሞ ያፈርሱኛል ... ይጠፈጥፉኛል ..

'እህትሽን አየሻት?'

በተሳሳተ መንገድ አትረዱኝ 🤷🏽 ክፉ መስራት ፈልጌ አይደለም .... እኔ እሷን መሆን ብዙ ሞክሬ ያልተሳካልኝ ነገር ስለነበር ... የክፋት ሙከራዬ እሷን ወደ እኔ ማውረድ ነበር::.... ትዳር ባይኖራት ..... ባትመረቅ ... የክፋት ክፋቱ እሷ ማምለጫ አታጣም ነበር!! ....

ከሞት ማምለጫ የለውም እንጂ ህምምም... አሁንም በተሳሳተ መንገድ አትረዱኝ በመሞቷ አልተደሰትኩም:: በመሞቷ ከማንም በላይ የምጎዳው እኔ ነኝ...

ግማሹን ዘመኔን እኔ እሷን ለመምሰል ስጋጋጥ ... የቀረውን እሷ እኔን እንድትሆን ስጋጋጥ ነው በመሃል አየር ላይ በትናኝ የሞተችው .... እና አሁን ምን ልስራ? ማንን ልምሰል?

በሞቷም ልከተላት? ራሷን ብቻ ሳይሆን ያቺ በፍሬም የተቀመጠችልኝን ሞዴሌን ይዛት ነው የተቀበረችውኮ ..... ከኔ በላይ ማን ሊያለቅስላት ይችላል?

"እህቴ ... ምሳሌዬ ..... ወዮዮዮዮዮዮ ኡኡኡኡኡኡኡኡ" .... አብርዶ የነበረው ለቀስተኛ ማርሹን ጨምሮ እርርርርሪሪሪሪሪሪሪሪሪሪ.....

"አይዞሽ! አይዞሽ ኤድዬ" ... ጀርባዬን ቸብ ቸብ ያደርጉኛል ...

እሷ ራሷን ሆና .. የምትፈልገውን አድርጋ ... የራሷን የህይወት መንገድ ሮጣ በ30 ዓመቷ ሞተች ... ቢያንስ ኖራለችኣ?

እኔ እሷን ስመስል ... እሷ እኔን እንድትመስል ተንኮል ስፅፍ 30 ዓመት .... ኖርኩ ነው የሚባለው?

ማነው የሞተው? እኔ ወይስ እሷ?

"ኤድዬ እህትሽን ትሰናበቻታለሽ?" ወደ ቀብር ሊንቀሳቀሱ ነው ... እናቴን አየኃት በተከፈተው ሳጥን ጠርዝ ላይ ድግፍ ብላ እህህህህ ትላለች ...

እሷን ነው የምሰናበተው ራሴን?

"ቆይ ትንሽ ደቂቃ" አልኩኝ ...... ፊቷን የማይበት ጉልበት እያሰባሰብኩ ... (ነፍስም ባይኖረውም... ባታየኝም) ጥፋተኝነት ሲሰማኝ ፊቷን እፈራዋለሁ

.....

"ጫማዬን የሰበርሽው አንቺ ነሽኣ?"

"አዎ... በምን አወቅሽ?" አላያትም.... በግድ አጠገቤ መጥታ እንዳያት ታስገድደኛለች

"ለምን? "

"እኔ እንጃ I guess ቀንቼ ነው" (ትስቅብኛለች)

"We talked about this አይደል እንዴ? Remember? አንቺ ዶክተር መሆን አትፈልጊም.. እኔ ነኝ የምፈልገው... እኔ ዘፋኝ መሆን አልፈልግም አንቺ ነሽ የምትፈልጊው... መሆን በማትፈልጊው ነገር ለምን ትቀኚብኛለሽ? እነ ማሚ እንዲበጠብጡሽ ለምን ትፈቅጅላቸዋለሽ?"

"አላውቅም!" (ታቅፈኛለች ... ጭንቅላቴን ያጣበበውን ብስጭት ... ቅናት ... ተንኳል .. ሀዘን ... ስብራት ... ታሪክ ... ባወራላት ደስ ይለኛል.... እየመጣ ያንቀኛል .... ለምን እንደሆነ በማይገባኝ ምክንያት ሽንፈቴን አምኖ መቀበል ይመስለኛል)

"በደም እህትሽ እንዳልሆንኩ ታውቂያለሽ? አንቺም እንደነሱ እያወቅሽ ነው ወይስ አታውቂም?" ይሄን ያልኳት እሷን መጉዳት ፈልጌ ይሁን መልሱን ፈልጌው አላውቅም::

ፊቷ ላይ መልሱን አገኘሁት:: አታውቅም!! በደቂቃዎች ቀድማኝ የተወለደች መንታ እህቷ መሆኔን ነው የምታውቀው::

"ኤድዬ እህትሽን መሰናበት ከፈለግሽ እየጠበቅንሽ ነው::"

"እሺ"

...... አልጨረስንም...........

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Meri feleke
አልወዳትም እንጂ አልጠላትም ....#2

"ከእኔና ከርሷ ምረጥ ብትባል?"

"ደሞ ጀመረሽ .... ተይ ኤዱ እረፊ.... "

"ንገረኝ... ምን መስማት እንደምፈልግ ታውቃለህ!! ... ንገረኝ!!" እጮሃለሁ ... በጥፍሬ ቆዳውን እጫነዋለሁ .... ሚስቱ(እህቴ) ሰውነቱ ላይ ምንም ምልክት እንድታገኝበት አይፈልግምኣ ...

"አንቺ!!.. አንቺ ትበልጫታለሽ!" ይለኛል:: ከሚስቱ ንፁህ ልብ እና ከእኔ እብድ ጭን መሃል እየዋለለ ... ቃላቶቹ አፉን ለቀው ሲወጡ ይጎመዝዙታል..... ያስታውቅበታል:: .....

ፍቅር ይሁን ተንኮል አልጋው ላይ የምሰራው አይገባኝም ..... ፍቅር የያዘኝ በውጊያችን መሃል ከሚነግረኝ ቃላቶች ነው .... የሰውነታችን ግብ ግብ ብዙም አይስበኝም ....

እሱ ከህሊናው ይልቅ ግለቱ ያሾረዋል!! ... እኔ ከህሊናዬ ይልቅ ቅናቴ ያነደኛል:: ... ሁለታችንም ፀፀት አለብንኮ .... እንደ vampire diaries ቫምፓየሮች ... let us shut it down! ብለን የምንዘጋው የህሊና ማስቀመጫ ሳጥን የለንም ...

ነገሩ አንደኛው ስሜት ሌላኛውን የመደፍጠጥ ጉልበቱ ነው .... እሱ ፀፀቱን በደምስሩ የሚንቀለቀል ግለቱ ይበልጥበታል:: እኔ ቅናቴና እሷን ለመብለጥ ያለኝ ፉክክር ፀፀቴን በብዙ እጥፍ ያስከነዳል:: ... ወጥረን እንዋጋለን!!

እኔ እሷ መሳተፏን እንኳን በማታውቀው ውግያ ማሸነፌ ሲነገረኝ ..... የምን ፀፀት ... የምን ህሊና... የምን ሲኦል .....

"ለእሷ እንዲህ አድርገህላት ታውቃለህ?"

"አዎ"

"አልፈልግም በቃ አቁም!! .... አልፈልግም አልኩ እኮ " እጮሃለሁ ....

"እሷ ግን እንዳንቺ አትጣፍጠኝም!" (ውሸቱን እንደሆነ አውቃለሁ .... ቢሆንም ደስ ይላል)

"እሺ አታቁም .... ቀጥል" እላለሁ ፈገግ ብዬ
.....
.....
....

አንድ ቀን ሀቅ አመለጠው ..."እውነቱን ልንገርሽ ... አልጋ ላይ ትበልጫታለሽ .... ልቧ ግን ይበልጥሻል:: ንፁህ ሴት ናት እሷ!"

"ውረድልኝ ወደዛ .... እላዬ ላይ ዘጥ ዘጥ እያልክ ስለንፁህነት በሙሉ አፍህ ታወራኛለህ?"

አስጠላኝ ..... ሲደውል አላነሳለትም .... በየቀኑ የሚፀፀትበትን ውጊያ ለመዋጋት ለምን እንደሚለምነኝም አይገባኝም ..... !!!

.....
.....
...
"አይዞሽ ኤዱ አይዞሽ.." ይለኛል የእህቴን ሬሳ ልሰናበት በቆምኩበት የሚንዠቀዠቅ እንባዬን እያየ

'የምርህን ነው ግን እንዲህ እየተንፈራፈርክ የምታለቅስላት?' ልለው ያምረኝና ... እኔስ የምሬን ነው? ለምንድነው የማለቅሰውስ? ... ምናልባት እሱም ከቅንዝራምነቱ አስበልጦ አይወዳት ይሆናል እንጂ ይወዳታልኮ .... እኔም ከቅናቴ አያይልም እንጂ.... እህቴኮ ናት!!

አለቀስኩ ..... ምርር ብዬ እየተንገፈገፍኩ አለቀስኩ ... ለሷ ይሁን ... ለራሴ... ለሀጢያቴ ... ለፀፀቴ ..... ብቻ ድንኳኑ ገና አሁን ሞቷን የተረዳ ይመስል በለቅሶ ግልብጥብጡ እስኪወጣ እሪሪሪሪሪሪሪ አልኩ .....

"ገደልሽ ..... ገደልሽኝ ...... ገደልሽኝ" ደጋግሜ የምለው ይሄን ነው ...... ያደረግኳትን ሁሉ በሞቷ ተበቀለችኝ ....

......

የሙሽራ ቀሚሷን ካበላሸሁባት በኃላ ... ለወራት አኩርፋኝ ነበር .... ሌላ የተገኘውን ቀሚስ ሚዜዎቿ ተከራይተው ተሞሽራ አለፈ:: ....

"ትጠይኛለሽ?" አለችኝ ከወራት በኃላ እቤት መጥታ ...

"አልጠላሽም!" አልኳት

"ታዲያ ለምንድነው ሀዘኔን ማየት የምትፈልጊው? እኔ ምንድነው የበደልኩሽ?"

"ምንም! ...... አላውቅም!! ምናልባት አንቺን ከምወድሽ በላይ ራሴን እጠላዋለሁ መሰለኝ .... አላውቅም!!"

"ኤዱዬ በስመአብ ወልድ .... !!(አማተበች) እሺ ለምን አታወሪኝም? ልስማሽ ንገሪኝ!"

"መናገር እንደማይሆንልኝ ታውቂያለሽ!"

አቅፋኝ ብዙ ቆየችና "እሺ እኔ ምን ላድርግልሽ? ኤድዬ ለኔኮ ያው መንታ እህቴ ነሽ.... ከአንድ ማህፀን አለመውጣታችን it doesn’t matter at all... እንዲህ አድርጊ በይኝ ላንቺ ጥሩ ስሜት ከሰጠሽ አደርጋለሁ::"

"ማሸነፍሽን ተይኝ!!" አልኳት ሳላስበው .... ግራ ገባት .... "አየሽ .... የሰርግ ቀንሽን አበላሽቼብሽ እንኳን ምንም እንዳላደረግኩኝ .... ጭራሽ ታዝኚልኛለሽ .... እኔ ልጥልሽ እታገላለሁ .... አንቺ ሳትታገዪ ሁሌም ታሸንፊኛለሽ .... ተይ በቃ .... እንደ እኔ ክፉ መሆን ባትችዪ እንኳን መልካም አትሁኚልኝ!!"...

በጣም ግራ ተጋብታ ስታየኝ ቆይታ

"ኤዱዬ እባክሽ ሳይካትሪስትጋ ሂጂ .... ቢያንስ ስትተነፍሺ ይወጣልሻል:: ቁጣሽ ይበርዳል!!" አለችኝ ...... አልሰማችኝም ..... ያልኳት አንዱም አልገባትም ..... አሁንም በለጠችኝ!!! ለዛ ነው የማላወራው .... ለማንም አይገባም ....
......
.....
....

"ገደልሽኝ .... ገደልሽኝ ..... " እሪታዬን ማቆም አቃተኝ ..... ድምፄ እየተዘጋ መጣ ..... አባቴ መጥቶ ከወደቅኩበት አነሳኝ .....

"ልቀቀኝ .... ልቀቀኝ!" ብዬ የጮህኩት ምንም የማክበር ለዛ በሌለው ቁጣ ነው .... ደንግጦ እጁን አሸሸ.... ራሴን ፈራሁት ... እሱም የፈራኝ ይመስላል ...... እንዳልፈነዳ እና እንዳልፈጀው ....
......
.....
.....

ለመጨረሻ ጊዜ 'አባ' ብዬ የጠራሁት ቀን 17 ዓመቴ ነበር ..... እንባ እና ንፍጤ ፊቴ ላይ ተለዋውሰው .... እንደ አባት መከታ እንዲሆነኝ ዓይን ዓይኑን እያየሁ ... ባለፈው እህቴ ከትምህርት ቤት ስትመለስ መንገድ ላይ ጎረምሳ በጥፊ መቷት ... እያለቀሰች ስትነግረው ደም ስሩ ተገታትሮ እየፈላ ሄዶ ልጁን አሩን እንዳበላው .... 'እኔ አባትሽ እያለሁ' እንዲለኝ .....የእኔማ ይብሳል .... ይገድላቸዋል.... የገዛ ቤቱ ... ልጁ ተደፍራ ... አለቀላቸው ....

"አባ ..." መናገር አቅቶኝ እንሰቀሰቃለሁ .... ሲጨነቅ ቆይቶ

"ይሄን ጉድ ለማንም እንዳትናገሪ የኔ ልጅ !!" አለኝ ... የቱን ጉድ እንደሆነም በደንብ አልገባኝም ... እኔ በአራት ጎረምሳ መደፈሬ? ወይስ ከደፋሪዎቹ አንዱ አብሮን የሚኖረው የሱ ወንድም ልጅ መሆኑ? እቤቱ መሆኑ? ....

"የኔ መደፈር ነው የሚያሳስብህ ስምህ?" አልኩት ተናግሬው በማላውቀው ቁጣ

"መደፈር ብለሽ ጭራሽ ነገሩን አታጋኚው .... ድንግል የነበርሽ ነው የሚመስለው:: ሲጀመር ክፍልሽ ድረስ አራት ጎረምሳ ምን ስታደርጊ አስገባሽ?"

እንባዬ ደረቀ ..."ቤቱ ነውኮ .... ወንድሜ ነውኮ .... እህቴ ናት ብሎ ነው ለጏደኞቹ ያስተዋወቀኝ....ሰላም ልንልሽ ነው ብለው ነው የገቡት ... ውጡ ልበላቸው? ይሄ ይሆናል ብዬ አስባለሁ?" ማስረዳት ቸገረኝ.....

"ወንድምሽ አይደለም:: ልጄ ... ነገሩን የባሰ አፀያፊ እያስመሰልሽው ነው:: ... በደም እንደማትዛመዱ ታውቂያለሽ!! ቀድሞውኑ እንደ እህትሽ ስብስብ ብለሽ ብትቀመጪ ......"

ከዛ በኃላ ያወራውን ብዙም አልሰማሁትም ....
"እሱ ወንድሜ ካልሆነ ... እሷስ በምን በኩል እህቴ ሆነች? አይደለችም!" አልኩት .....

........ አልጨረስንም ..........

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Meri feleke
አልወዳትም እንጂ አልጠላትም .....#3

እንድትሞት በጭራሽ አልፈልግም ነበር:: ስለምወዳት አይደለም !!!.... በቁሟ ልበልጣት .... ላሸንፋት ነበር ትግሌ ..... ሞቷማ ኪሳራዬ ነው::

የሞቷ ቀን ማታ በሬን አንኳኳች ........ ደፈራርሰው ያበጡ ዓይኖቿ .... የተንጨባረረው ፀጉሯ ....የሚንቀጠቀጡ እግሮቿ ... የሆነ ነገር እንደተፈጠረ ገባኝ::

"ትዳሬን? ኤዱዬ ፍቅሬን? እንዴት እንደምወደው እያወቅሽ? ምን ብበድልሽ ነው እንዲህ የከፋሽብኝ? እስኪ ንገሪኝ እኔ ምንድነው ያደረግኩሽ?" ከንፈሯ ይንቀጠቀጣል..... እንባዋ ይከታተላል ..... አሳዘነችኝ .... ማታ አልጋቸው ላይ ሲዋደቁ የእኔን ስም እንደጠራባት ነገረችኝ ... ፈገግታዬ አመለጠኝ::

"ይሄን ነው prove ማድረግ የፈለግሽው? ከኔ የተሻልሽ መሆንሽን ከባሌ ጋር ተኝተሽ ነው ማረጋገጥ የምትፈልጊው?" እየተናደደች መጣች ..." .... ጤነኛ አይደለሽም ..... ይሄ በሽታ ነው!..... " ደሞ ምልስ ትልና አሳዛኝ ትሆናለች ... "እንዴት ክፉ ነሽ ግን በማሪያም?...." ኩርምት ብላ ትንሰቀሰቃለች ........

ዝም ብዬ እሰማታለሁ:: .... ስታለቅስ... ምን ያህል ክፉ ሴት እንደሆንኩ ቃላት እየቀያየረች ስትነግረኝ... ስትናደድ ... አንድ ሰዓት ያህል ዝም ብዬ ሰማኃት ...

ለምንድነው የመሸነፍ እንጂ የድል ስሜት የማይሰማኝ ታዲያ? ..... በክፋት መብለጥ የለም ይሆናል....

"ታውቂያለሽ ወንድምሽ ከደፈረኝ በኃላ አብሬው የተኛሁት ወንድ ባልሽ ነው!!" አልኳት .... (አታውቅም... እንደማታውቅም አውቃለሁ:: .... ፊቷ የሆነ ነገር የፈነዳበት ይመስል ተመሰቃቀለ::)

"ቤተሰቦችሽ እኔ ለተደፈርኩት ... እህትሽ ከሰማች ትጎዳለች ... እንዳትሰማ ብለው ተጠነቀቁልሽ:: ... አስበሽዋል? እኔ እሳት ውስጥ ሆኜ እየነደድኩ .... ሙቀቱ አንቺን እንዳይነካሽ እየከሰልኩ ዝምም ጭጭጭጭ ብዬ ስነድ?"

ዝም አለች:: ክው ብላ ደርቃ ከአፌ የሚወጡት ቃላት የሆኑ የሞት ፍላፃዎች ይመስሉ እየተንቀጠቀጠች ትጠብቃቸዋለች .....

ሁሌም እንደዛ ነበር ... የሆነ የተረገመ ቀን እቤታችን የመጣች እንግዳ

"በስመአብ ቁልጭ እናትሽ አይደል እንዴ? ነፍሷን ይማረው ፀጉሯን እንዲህ ማስያዝ ትወድ ነበር እሷም!" ብላ የማውቅ የመሰላትን ቦንብ ከማፈንዳቷ ቀን በፊት

'ውይ ልጄ ደረቅ ዳቦ አትወድምኮ' ተብሎ እኔ ደረቅ ዳቦ ስበላ ለእህቴ እንቁላል መሰራቱን በክፉ ተርጉሜው አላውቅም ነበር::

'እሷ ጎበዝ ተማሪ ስለሆነች' ተብሎ እሷ የግል ትምህርት ቤት ስትማር እኔ የመንግስት መማሬን ጉብዝናዋ የሰጣት ሽልማት ነው ብዬ ከማሰብ ዘልዬ አላውቅም....

'እሷ ቆንጆ ስለሆነች ጎረምሳ አያስኬዳትም' በሚል የሚያመላልሳት መኪና ሲከራዩላት ... እኔ ጥፍጥፍ መሆኔን አምኜ ከሷ ትምህርት ቤት የሚርቅ ትምህርት ቤቴን መንገድ በእግሬ እየፈጨሁ ለእህቴ ጥበቃ ከመደሰት ያለፈ የተሰማኝ አልነበረም::

እህቴ ናታ.... በመልክም በባህሪም በጭራሽ የማንመሳሰል መንታ እህቴ ....

"እናቴ ማናት?" ብዬ ጎፈላሁ እንግዳዋ ከሄደች በኃላ ..... 13 ዓመቴ ነው:: እናቴ(አሳዳጊዬ) እህቴ እንዳትሰማ እሽሽሽሽ አስብላኝ

"ይሄን ነገር ግን በፍፁም እህትሽ እንዳትሰማ... እንዴት እንደምትወድሽ ታውቂያለሽ አይደል? ቃል ግቢልኝ በፍፁም ለእህትሽ እንዳትነግርያት .... " ብላ መርዶዬን ነገረችኝ .... እናቴ የኛን ቤት ተከራይታ የምትኖር የቡና ቤት ሴት እንደነበረችና እኔን ስትወልድ እንደሞተች ነገረችኝ .....

አሳዳጊዎቼ ልጅ የመውለድ ተስፋቸው ባዶ መሆኑን በዶክተርም በጥበቃ ብዛትም ባረጋገጡበት ወቅት የእኔ እናት እንደ ተዓምር ከማን እንዳረገዘች የማታውቀውን ልጅ ልታስወርድ ዱብ ዱብ ስትል ነው አሳዳጊዎቼ በደስታ እኔን ሊያሳድጉኝ ቃል ገብተውላት እናቴ የወለደችኝ .... ቆይ ....!!!! እህቴ ከእኔ ጋር ግብ ግብ የጀመረችው ገና ሳላውቃት
ሳታውቀኝ ... በእናቴ ሆድ ሆኜ ነው...

ለዓመታት ልጅ አልሸከም ያለው የአሳዳጊዬ ማህፀን ልክ እናቴ ሆድ እኔ መደላደል ስጀምር እህቴን ቋጠረ:: .... ውድድሩ ተጀመረ....

"በቃ አሁን የራሳችንን ልጅ ስላገኘን ልጅሽን የማሳደግ ፍላጎታችንን ትተነዋል" ብለዋት እንደነበር አድጌ ያቺ እንግዳ ናት የምትነግረኝ ... እናቴ በማላውቀው ምክንያት ልትወልደኝ ወሰነች.... ስትወልደኝ ሞተች:: አሳዝኛቸው.... ወይም ልውሰዳት ያለ ዘመድ ስለጠፋ... አልያም እግዜሩን ፈርተው ለፅድቅ ትሆነናለች ብለው ... አላውቅም:: ወሰዱኝ...... በወሩ እህቴ .... መንታዬ ተወለደች::

ቤተሰብ ያጣሁት እኔ .... የኖርኩት ህይወት ሁሉ እንክትክት ብሎ የውሸት ካብ ሆኖ የተናደብኝ እኔ .... የተዋሸሁት እኔ .... "እሷ ከሰማች ይከፋታል..." ተብሎ የምትጠበቀው እሷ ....

"ለምን አልነገርሽኝም? እንዲህ ሁሉ ስትሆኚ ምናለ ብትነግሪኝ? ይሄ ጅብ እንዴት እህቱ ላይ እንዲህ ያደርጋል?" አለችኝ መልሳ ወንድሜ የምትለው የአጎቷ ልጅ ከጏደኞቹጋ ያደረገኝን ስነግራት ... ባሏን እንዳባለግኩባት ረስታው አቅፋኝ ለእኔ መንገብገብ ጀመረች .....

"ቤተሰቦችሽ ሁሉም ነገር በደም ካልተገመደ ዋጋው አይታያቸውም ..... በደም ስለማንገናኝ እህቱ አልነበርኩም ..... ደም ስላልፈሰሰኝ ደፈረኝ እንዳልል ዝም አስባሉኝ .... ስህተት ነው ተባለለት .... ድሮም የጀመረችው ነው ተባለና የሱን አውሬነት በእኔ ጥፋት ከደኑለት ..... እሽሽሽሽሽሽ ዝም በይ ተባልኩ::"

አሁንም ልክ እንደ ቅድሙ መንሰቅሰቅ ጀመረች .....

"በህይወቴ አንድ ነገር ይሁንልሽ ብሎ ፈጣሪ ቢጠይቀኝ ምን እንደምሻ ታውቂያለሽ?" አልኳት ....

"ምንድነው?" አለችኝ ማድረግ የምትችለው ነገር ቢሆን አሁኑኑ የምታሳካልኝ በሚመስል ጉጉት

"አንቺን እንዲያደርገኝ .... አንቺን መሆን"

ዝምምምምም አለች::..... አሳዘንኳት .... ዝምምምም አለች .....

"እሺ እኔ ምን ላድርግ? እነአባቢን ልጣላቸው? ያ ደስ ይልሻል? ወይም እኔን እንደሚወዱኝ እንዲወዱሽ ልንገራቸው? ስራ ልተው? ስራ ባይኖረኝ ደስ ይልሻል? አብርሽን ብቻ ተይልኝ አትበይኝ .... እሱን አልችልም.... ኤዱዬ እሱን ከራሴ በላይ እወደዋለሁ:: ሌላ የፈለግሽውን ላድርግልሽ እንዳሸነፍሽኝ ከተሰማሽ..." አለችኝ ..........

አዎ በክፋት አይበለጥም ......... ይኸው አሁንም በዝረራ አሸነፈችኝ ....

"ውጪልኝ!!" አልኳት በቀስታ ..... "ውጪልኝ .... ከህይወቴም ከቤቴም ውጪልኝ ... " እያልኳት ለራሴ 'በቃኝ' እላለሁ ..... ርቄ እሄዳለሁ ... ሁላቸውንም የማላይበት .... ሁሉንም ከኃላዬ ጥዬ ብንንንንንን ብዬ እሄዳለሁ ....

......... አልጨረስንም ..........

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Meri feleke
አልወዳትም እንጂ አልጠላትም.....#4

'ከቤቴ ውጪልኝ' የሚለውን ዘላ 'ከህይወቴ ውጪልኝ' ያልኳትን ሰምታኝ መሰለኝ....... የሞተችው......

"ኤዱዬ የኔ ከህይወትሽም ከቤትሽም መውጣት አንቺን አያስተካክልሽም!! Let us make this right!! ላግዝሽ?" አለችኝ ....

"የቱን? የቱን ነው የምናስተካክለው?" አልኳት "ያንቺ እህት አለመሆኔን? ንገሪኝ ከየት እንጀምር? ገና ሳልወለድ ቤተሰቦችሽ ከከዱኝ? ወይስ ለ13 ዓመት እማ አባ ያልኳቸው ቤተሰቦቼ ሳይሆኑ የወለደችኝ ሌላ ሴት መሆኗን እንዴት ነው የምናርመው? ከየት እንጀምር ንገሪኝ? .... ጥፋት ሳጠፋ 'ዘር ከግንዱ ይመዘዛል' እየተባልኩ .... በራሴ መንገድ ስጏዝ 'እንደእህትሽ ብትሆኚ ምናለ?' እየተባልኩ ማደጌን ምኑጋ እናቅናው ?" ......

እንዲህ ለማንም አውርቼ አላውቅም.... የተሰማኝን ህመም ሁሉ መዋጥ እንዳለብኝ ተነግሮኝ ነው ያደግኩት.... ጭጭ... እሽሽሽሽሽ ተብዬ ... እየታመሙ መሳቅ ለምጄ ነው ያደግኩት ....

"ወንድሜ ስለው ያደግኩት ወንድ ከጏደኞቹ ጋር የደፈረኝን ምኑጋ እናቅናው እህቴ? ንገሪኝ ?.... እኔ .... እኔ መቃናት አልችልም!! .... የእኔ ህይወት የቱምጋ አይቃናም!! .. "

"ወደኃላ ተመልሶ ቢቃና .... ሀ ብዬ ሌላ ሰው ሆኜ መፈጠር ነው የምፈልገው.... ያንቺ እህት ሳልባል... አንቺ በምታገኚው ፍቅር ሳልቀና ... ባንቺ ጉብዝና ራሴን ሳልለካ.... እንዳንቺ ቆንጆ ለመሆን ሳልመኝ.... ባጠቃላይ ካንቺ ሳያወዳድሩኝ 'እኔን' የሚወዱኝ ቤተሰቦች ልጅ ሆኜ መፈጠር ነው የምፈልገው ..... ክፉ ... ቀናተኛ ... ሳልሆን ...."

ከተቀመጠችበት ሳትነሳ ብዙ ቆየች.... እኔ ህመሜን ብዙ አወራሁ .... ከቤቴ ስትወጣ ....

የኔን ሸክም ሲደመር የጥፋተኝነት ስሜት ሲደመር ባሏ ከእህቷጋ የባለገባት ሚስት የልብ ስብራት ... ይሄን ሁሉ ተሸክማ ከአንገቷ አቀርቅራ .... የጎበጠች መሰለኝ ...

"ኤድዬ ህመምሽን ስላልታመምኩልሽ ይቅርታ!!" ብላኝ ወጣች .... እኔ 30 ዓመት ቀስ በቀስ የጠጣሁትን ጎምዛዛ ክፋትና በደል ... በአንድ ቀን ጋትኳት .... ከበዳት!!
....
.....
...

የቀብር ቦታው ላይ ሬሳዋን ወደ ጉድጏዱ ሲነዱት እያየሁ ...ምናለ አቅፌያት ቢሆን? 'ያንቺ ጥፋት አይደለም' ብያት ቢሆን? ምናለ ዝም ብዬስ ቢሆን? .... ምናለ..... ምናለ.... እያልኩ እንሰቀሰቃለሁ:: .....
.....
.....

ከቤቴ ከወጣች በኃላ ለሰዓታት ከተቀመጥኩበት ሳልነሳ ስልኬ ጠራ!!

"እህትሽ አርፋለች!"

ምንም አልጠየቅኩም:: እስከአሁንም ድረስ የደወለልኝ ማን እንደሆነ አላውቅም:: ... ስልኩንም ከዘጋሁ በኃላ ለሰዓታት እዛው ተቀመጥኩ:: ድጋሚ ስልኬ ጠራ:: ጏደኛዋ ናት::

"ኤዱ የት ነሽ?" አለችኝ በማልቀስ በሻከረ ድምፅ .... 'እንዴት እህትሽ ሞታ ለቅሶ ቦታ የለሽም' የሚል ድምፀት ባለው ቃና

"ምን ሆና ነው?" የሚል ጥያቄ ነው ከአፌ የወጣው....

"ወየው ጉዴ አልሰማሽም? (ለቅሶ አስከትላ) ምን እንዳጋጠማት ምን አውቄ? ራሷን ነው ያጠፋችው::" አለችኝ ...... ስልኩን ዘጋሁት .... እስኪነጋ ከተቀመጥኩበት አልተነሳሁም:: ..... ፀሀይዋ ብቅ ስትል ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ለቅሶዋ ላይ ተገኘሁ:: ስገባ ነጠላ ትከሻዬ ላይ አደረጉልኝ.... ምፅ ምፅ እያሉ ደግፈው ወንበር ላይ አስቀመጡኝ ...... ግራ ገባኝ ....

ሲያፈጡብኝ አለቅሳለሁ .... እንባዬ ይተባበረኛል ..... እስከቀብሯ ቀን ድረስ ሲያለቅሱ ከማልቀስ .... ሲያፈጡብኝ 'ጨካኝ' ላለመባል አይኔን ከማስጨነቅ ያለፈ የሚሰማኝንም ስሜት ለይቼ አላወቅኩትም::

አፈሩን ሲያለብሷት ልቤን ሞት ተጫነው:: ዝም ጭጭ .... ያለ ስሜት ተሰማኝ:: አብሬያት ጉድጏድ ውስጥ የገባሁ ስሜት .... አፈሩ እኔ ላይ የሚጫን ስሜት .... ራሴን ልስት አይነት ስሜት ይሰማኝና ተስተካክዬ ለመቆም እሞክራለሁ .. .... የሚሰማኝ ዝምታ ብቻ ሆነ ... ከዛ .... ጨለማ!!!!

እንደሞት ያለ ጨለማ ........

"ምን ሆኜ ነው?" አልኩኝ አይኖቼን ስገልጥ ሆስፒታል እንዳለሁ ገብቶኝ:: ...... አጠገቤ የእህቴ ጏደኛ እና እናቴ (አሳዳጊዬ) ነበሩ:;

"ቀብር ቦታ ራስሽን ስተሽ ነው" አለችኝ ጏደኛዋ .... ፊታቸው ላይ የሆነ የጉጉት ስሜት አየሁ..... ስለነቃሁ የመደሰት ግን ያስደሰታቸው መንቃቴ ብቻ ሳይሆን ሌላ ነገር እንዳለ ገባኝ

"ምንድነው?" አልኩኝ ወደ እናቴ ዞሬ ..... ከአፌ
እስኪወጣ ስትጠብቀው የቆየ ቃል ይመስል ቅብል አድርጋ

"ምን ማለቷ ነው? ምንድነው?" ብላ የሆነ ፖስታ ሰጠችኝ

"ምንድነው?" አልኩ እየተቀበልኩኝ

"እህትሽ ከመሞቷ በፊት ያስቀመጠችልሽ ደብዳቤ ነው! ምን ማለቷ ነው? ከሁላችን መርጣ ለምንድነው ላንቺ የፃፈችው? የፃፈችው ምኑን አልገባኝም!" አለችኝ

"ለእኔ ከሆነ የተፃፈው ለምን አነበባችሁት?" አልኩኝ ፖስታው ላይ ለኤደን ብቻ የሚል ፅሁፍ እያየሁ .,,......

.......... አልጨረስንም............

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Meri feleke
አልወዳትም እንጂ አልጠላትም ....#5
(የመጨረሻ ክፍል)

"ኤደን ምን ይሰማሻል?"

"ምንም"
(ዝም ተባብለን ሰዓቴ አልቆ እመለሳለሁ::)

በሌላኛው ቀንም ........

"ኤደን ዛሬስ ለማውራት ዝግጁ ነሽ?"

"አይደለሁም!! ማውራት አልፈልግም!"
(ዝምምምምም..... ሰዓቱ ያልቃል)

ደግሞ በሌላኛውም ቀን

"ኤደን ዛሬስ ለመጀመር ዝግጁ ነሽ?"

"ምኑን?"

" ማውራት ትፈልጊያለሽ?"

"እኔ ምንም የማድረግ ፍላጎት የለኝም!!"

(የምፈልገው አንድና አንድ ነገር .... የቀብሯ ቀን ጭልጥ አድርጎ የወሰደኝ ጨለማ ለዘለዓለሙ እንዲወስደኝ ነው)

በሌላኛው ቀን አልጠየቀኝም:: ገብቼ ስቀመጥ ሰላምታ ሰጥቶኝ ዝም አለ::

"ዛሬ አትጠይቀኝም እንዴ?"

"ምኑን?"

"ዝግጁ መሆን አለመሆኔን?"

"ነሽ?"

"አይደለሁም!"

"ጥሩ!! ዝግጁ እስክትሆኚ ድረስ የሚሰማሽ እዚህ መጥቶ መቀመጡ ከሆነ ዝም በይ... ማውራት ሲሰማሽ አውሪ.... ማልቀስ ሲሰማሽ አልቅሺ.... መጮህ ሲሰማሽ ጩሂ ..... ሰዎች ሀዘናቸውን በተለያያየ መንገድ ነው የሚያስተናግዱት.... የተለያየ ጊዜ ይወስድባቸዋል::"

"ሀዘን አይደለም የሚሰማኝ!!"

"እሺ!! ምንድነው የሚሰማሽ?"

"ምንም!!! ዝም ... ፀጥ .... ያለ ስሜት!!"

ለብዙ ቀናት ተመላለስኩ .... እሄዳለሁ:: እቀመጣለሁ:: ሰዓቴ ያልቃል:: እመለሳለሁ::

"ዛሬ አሻንጉሊትሽን የት ትተሻት መጣሽ?" አለኝ

"ሰጥቻት መጣሁ:: ..... 'ያውልሽ' ብዬ መቃብሯ ላይ ወርውሬላት መጣሁ:: ትውሰደው .... " እንባዬ ከወራት በኃላ ላስቆመው እንዳልችል ሆኖ ይንጠኝ ገባ ...... ማልቀስ ማቆም እፈልጋለሁ:: .. አቃተኝ.... የቀብሯ ቀን እንደሆነው ራሴን የምስት መሰለኝ .... ጨለማው ናፈቀኝ... ግን አልመጣም... አልወሰደኝም.... ደብዳቤዋን ከኪሴ አውጥቼ ሰጠሁት::

"አየህ በዝህች ሁለት መስመር ደብዳቤ እንዳልሞትም እንዳልኖርም አስራኝ ሞተች:: አንብበውማ! ጮክ ብለህ አንብበው!!"

" አንቺ ደግሞ በተራሽ የእኔንም ደርበሽ ኑሪልኝ:: የከፈልኩትን ዋጋ እንዳታከስሪኝ .... ደስ ተሰኝተሽ ኑሪና ዋጋዬን ክፈዪ!! .... ፖኒን ትቼልሻለሁ::" ጮክ ብሎ አነበበው .... ቤተሰቦቻችን እንዳልገባቸው ሁሉ እሱም አልገባውም..... የሆነው ሳይገባቸው ነው 'ጭንቅላቷ ተቃውሷል' ብለው ሳይካትሪስት የቀጠሩልኝ....

"ፖኒ ያቺ አሻንጉሊት ናት!" እንደገባው ራሱን ነቀነቀ.... "በጣም ልጅ ሆነን ለሁለት አንድ አሻንጉሊት ተገዛልን:: እሷ ስም አወጣችላት:: አልተቃወምኩም:: .... የሆነ ቀን እኔ ስጫወት ደርሳ ካልወሰድኩ አለች ... ተደባደብን ... አባታችን መጥቶ አሻንጉሊቷን ከእኔ ቀምቶ ለሷ ሰጣት ... ቀን ቀን በአሻንጉሊቷ መጫወት የምትችለው እሷ መሆኗን አወጀ:: ከፈለግኩ ማታ እሷ ስትተኛ መጫወት እንደምትችል... ያውም እሷ ከፈቀደችልኝ..... ነገረኝ:: ምርርርርርር ብዬ አለቀስኩ::...... ያስለቀሰኝ ከአባታችን ለሷ ማገዝ በላይ የሷ መደሰት ነበር:: እንዳለመታደል ሆኖ ሁሌም እሷ ስትተኛ ጠብቄ ለመጫወት እቀመጥና እንቅልፍ ቀድሞ ስለሚጥለኝ ያልፈኛል::.... ምን ማለቷ ነው? ስትሞት ትታልኝ የምትሞተው?"

"ምን ማለቷ ይመስልሻል አንቺ?"

"እኔ ምን አውቅላታለሁ? ህይወትሽን የቀማሁሽ እዛጋ ነው ... ከዛ ጀምሪ ማለቷ? ያውልሽ ይስፋሽ ማለቷ? እኔ ምን አውቅላታለሁ ምን አድርጊ እንደምትለኝ? ቆይ እሷ ራሷን እንደክርስቶስ ነው የምታየው? ማነኝ ብላ ነው የምታስበው ህይወቷን ስትሰጠኝ ..... በቃ ሞተችልኝ ብዬ በደስታ የምኖር ነው የመሰላት? ደሞ ቆይ ክርስቶስኮ ለአንድ ሰው አልሞተም .... ለዓለም ህዝብ ነው የሞተው... ክርስቶስ ለአንተ እንደሞተልህ ብታውቅም ስላላመንከው እኔ አሁን የሚሰማኝ አይነት ሸክም አይሰማህም .... ሌላ የሆነ ሰው አምኖ እንደሚያገለግለው ታውቃለህ ... እሷ ምን አስባ ነው ለአንድ ለእኔ ህይወት ከፍላ ... ከዛ በደስታ እንድኖርላት የምትፈልገው? ቆይ የቱጋ ሀ ብዬ መኖር እንድጀምርላት ነው? ቆይ አንተ ስታስበው ጤነኛ ሆኜ ራሱ መኖር የምችል ይመስልሃል?"

"አዎ ይመስለኛል!!"

"እኮ እንዴት?" ..... እስከዛሬ ያላወራሁበትን ሰዓታት ጨምሬ ለፈለፍኩ::

"ራስሽን ይቅር በማለት ትጀምሪያለሽ!!"

"ሌላ 30 ዓመት መኖር ቢሰጥሽም መኖር አትጀምሪም አትለኝም ታዲያ?"

"ሳይኖሩ ከመሞት መኖር ጀምሮ መሞቱ አይሻልም ታዲያ? ...... "
......
.....
"ለራሴ ስል መኖር አልፈልግም..... ለሷ ስል ደግሞ መሞት አልፈልግም"

.....

"ሁለቱን ለማስታረቅ ነው ከራስሽ መታረቅ ያለብሽ..... "

................. ጨርሰናል................

(አላለቀም ብትሉም አልቋል..... አልቋል ብትሉም እንደዛው)

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Meri feleke
ሙስተጃብ ነኝ
<<ሽቶ በእንጀራ !>>
.
"አንተ ቆሽሸህ የለህ እንዴ ?"
አለችኝ እማዬ በመሃል የምታንጎራጉረውን ዜማ አቁማ። ዝም አልኳት። ሆን ብዬ
ነው መልስ ያልስጠኋት። ማንጎራጎሯን እንዳታቋርጥብኝ። ደስ ሲላት ሁሌም
እንደዚህ ነው የሚያደርጋት። ፍንክንክ ብላ ድምፆን ሳታወጣ ማንጎራጎር ! ከእሷ
ውጪ ሰምቼው የማላውቀው ደስ የሚል ዜማ ነው ሁሌም የምታንጎራጉረው።
ቋሚ ግጥም ግን የለውም። እንዳስፈላጊነቱ በየጊዜው እንዳስደሰታት ነገር
ትለዋውጠዋለች መሰለኝ። ይሄንም ያወኩት ሆን ብዬ ተከታትያት ከስንት ሙከ
በኋላ የሆነ ቀን የአባዬን ስም 'ታዴዋ' ብላ ስታንጎራጉር ስለያዝኳትና እንዲሁም
ሌላ ጊዜ በዛው ዜማ የእኔን ስም አስገብታ ስታንጎራጉር በመስማቴ ነው። ድምፆን
አውጥታ ስለማትለው ምን እንደምትል አይሰማም። ከልጅነቴ ጀምሮ ብሰማው
ሁሌ ስለማይገኝ ነው መሰለኝ እስከአሁን ድረሶ ያልሰለቸኝ ዘፈን የእናቴ ብቻ
ነው።
"ተነስ እስኪ ማሙሼ እግርህ ልሽህ ?"
አለቺን ወሃ ከባልዲው ቀድታ እየከለበሰቺብኝ።
"እንቢየው አልነሳም። ጀርባዬን ካሸሺኝ ይበቃል እግሬን እራሴ አሸዋለሁ..."
አልኳት ከቀድሞ በባሰ አንገቴን ጉልበቶቼ ስር እየቀበርኩት። የብረት ሳፋው ከፍ
ያለ ስለሆነ ከወገቤ በታች ያለውን ሰውነቴ በሙሉ ሸፍኖልኛል።
"ጉድ ጭራሽ ደርሰህልኝ እኔ እናትህንም ማፈር ጀመርክ ?"
አለቺኝ እማዬ ከሳቋ ጋር እየታገለች እንደ አዲስ።
"ቆይ እኔ እናትህ ምን የማላውቀው አዲስ ነገር አወጣህና ነው የምታፍረኝ...."
ከቅርብ ጊዜ በኋላ ሆን ብላ እኔን ማሳፈር ያስደስታት ጀምሯል። ብቸኛ መዝናኛው
ሳይሆን አይቀርም። ከዓመት ከምናምን በፊት በመጀመሪያ 'ከአሁን በኋላ ገላዬ
እራሴ ነኝ የምታጠበው' ስላት ደስ ብሏት 'ኡፍፍፍ ገላገልከኝ' ብላ ነበር። ለሷ
አዝኜ መስሏት። ጭራሽ የዛኑ ቀን ማታ አባዬ ከስራ ገብቶ 'ቡና አፊይልኝ ሲላት...'
'እስኪ እንደ ልጅህ እራስህን ቻል...' ብላ ምሳሌ ሁላ አድርጋኝ ነበር። ኋላ ኋላ
ገላዬን ለመታጠብ የእሷን ከጓዳ መውጣት በተደጋጋሚ ስጠባበቅ በመታዘቧ
ነበር ጉዳዩ ለእሷ የማዘን ሳይሆን የመጎርመስና የማፈር መሆኑ የገባት።
ይሄንንም ለአባዬ ነግራው የዛኑ ቀን አስቃብኛለች። ከዛ በኋላ እኔ ገላዬን
በታጠብኩ ቁጥር ፣ የእማዬ ቋሚ መዝናኛዋ ሆንኩኝ።
"እሰይ ከአሁን በኋላ እኮ እያሳፈርሺኝ አትስቂብኝም..."
አልኳት እኔም በተራዬ ቀና ብዬ እየሳኩባት።
"ምን ስለተገኘ ?"
የእጆቿን አረፋ በውሃ እያወረደች ጠየቀቺኝ።
"እህ ዛሬ ሄደን የምናየው አባዬ የገዛው አዲሱ ቤታችን እኮ ሻወር ቤት አለው።
በሩን ቆልፌ ነው የምታጠበው...."
ስላልጠበቀች ነው መሰለኝ እማዬ ከልቧ ነበር በመልሴ የሳቀችው።
"እሱን እናየዋለን አባትህ ሳይመጣ በል ቶሎ ተለቅልቀህ ውጣ..."
ብላ እየተጣደፈች ወደ ሳሎን ወጣች።
እንደለመደችው አሁን ያልኳትንም ለአባዬ ልትነግረው እኮ ነው።

ከእማዬ ጋር ቤቱን እየተዟዟርን አየነው። ግቢው ሰፊ ነው። ክፍሎችም ብዙ
አሉት። የቀድሞ ሁለት ክፍል ቤታችን አብራን ብትመጣ እዚህ አንድ ክፍል ቤት
ውስጥ ተብቃቅታ ትኖር ነበረ።
"ይሄ ሳሎኑ ነው"
አለን አባዬ እሱም ከእኛ እኩል የክፍሉን ዙሪያውን እንደ አዲስ እየቃኛ።
"በጣም ሰፊ ታድዬ። ግን ምን ልንከትበት ነው..."
አለች እማዬ እየተከዘች።
"ቤት ያስገዛን አምላክ ለዕቃ ይከለክለናል ብለሽ ነው..."
የእማዬ ፊት ወዲያው ብርሃን ሆነ። አባዬ ወደ ቀጣዩ ክፍል ሲሄድ እኛም
ተከተልነው። በሩን ከፍቶ እየገባ...
"ይሄ ደግሞ የእኔ አንቺ መኝታ ክፍላችን ነው..."
አባዬ ከእኔ ተደብቆ እማዬ ሲጠቅሳት ያዝኩት። እሷም ፈገግ አለችለት። እኔን
ብቻ ከፋኝ። 'የእኔ አንቺ እኮ ብቻ ነው..' ያለው ? ከዚህ በኋላ የተኛው መስዬ
እማዬና አባዬ ተኝተው ሲያወሩ ፣ ሲስቁ ፣ ሲላፉ ፣ መስማትና ማየቱ ሊቀርብኝ
ነው ማለት ነው። አዲሱ ቤታችንን ልጠላው ነው እንዴ !
"ያ ደግሞ የውስጥ ሻወራችን ነው..."
አለ አባዬ። ቀና ብዬ ሳየው...
"ይሄ ግን የሶስታችንም ነው..."
አለኝ ፈገግ ብሎ። እማዬም በሳቅ እያጀበችው...
"ታዲያ የማሙሼስ ክፍል የታለ ?"
"እሱ ከዋናው ቤት ውጪ ጓሮ ነው ክፍሉ..."
አለ በሌላ አቅጣጫ ወደ ውጪ እየወጣ። ተከተልነው። ድንገት ግን እማዬ ጥያቄ
አነሳ...
"ያ ምንድን ነው ?"
አለች ከጎረቤት ጋር በሚለየን የግንብ አጥር መሃል የተተወችውን የቆርቆር በር
አይታ።
"እ ይሄ እንገነበዋለን። ቤቱን የሸጠልን ሰውዬ ከጎረቤቶቹ ጋር በጣም ይቀራረቡ
ስለነበር ለቡናም ሆነ ለአደጋ ጊዜ በቶሎ ለመጠራራት የተዉት በር ነው። እኛ
እንኳን ስለማያስፈልገን በግንብ እናሳጥረዋለን...."
አለ አባዬ ለእኔ የተመደበውን ክፍል እየከፈተ።
"እንደሱስ ከሆነ ቢሆንም ችግር የለውም። ለእኛም ሊጠቅመን ይችላል..."
"ምን ይጠቅመናል ? ከጎረቤት ጋር በሩቁ ነው። አጉል መቀራረብ ትርፉ መዘዝ
ነው..."
አለ አባዬ ወደ ውስጥ እየገባ። እኔም ተሽቀዳድሜ እማዬን ገፍቼያት ገባው።
ከክፍሌ ጋር ተፋጠጥኩ። ሰፊ ነው። ፍርሃት ፍርሃት አለኝ። ብቻዬን የሚውጠኝ
መሰለኝ።
"ለእሱ የሚሆን ከውስጥ አንድ ክፍል ብናገኝለት ጥሩ ነበር..." አለች እማዬ
ፍርሃቴን ከፊቴ ያነበበችው ይመስል።
"ከየት ይመጣል ? ሻወር ውስጥ አናሳድረው ነገር..."
አባዬ ከእነሱ መራቄን በጉጉት ሲጠባበቅ የኖረ መሰለኝ።
"ወይ ሳሎን ቢነጠ...."
አላስጨረሳትም።
"ልጅሽ እኮ ጎርምሷል ፀዲ። ለሳሎን ለሳሎን ተሰብስቦ ለማደርማ የድሮ
ቤታችንስ ምን አለን !? ትፈራለህ እንዴ ጎረምሳው ?"
አለኝ ቁልቁል እያየኝ።
አንገቴን 'አይይይ...' በሚል ነቀነኩለት። ቆይ ከጉዳዩ የበለጠ እያስፈራሩ
'ትፈራለህ እንዴ ?' ብሎ መጠየቅ ምን የሚሉት ነገር ነው።
"እና ወደድሺው?"
አለ አባዬ የእማዬን አይን እያየ።
"በጣም ነዋ ታድዬ..."
አለች እማዬ። 'ታድዬ' ያለችው እንደሁል ጊዜው አባዬን እያቆላመጠችው ይሁን
'ዕድለኛ ነኝ' ለማለት ፈልጋ ግራ ገብቶኝ ነበር።

ከቀናት በኋላ እቃችንን ጭነን አዲሱ ቤታችን ገባን።
በገባን ቀን ማታውኑ ሳሎን ቁጭ ብለን እያወራን በር ተንኳኳ። አባዬ ተነስ ክፈት
ሲለኝ...
"ቆይ እሱ ይፈራል.."
ብላ እማዬ ተነስታ ወጣች። ከቆይታ በኋላ....
"ሰላም ለዚህ ቤት እንዴት አመሻችሁ ?" የሚሉ ሰዎችን አስከትለ ተመለሰች።
አንድ ሴትና ወንድ ከእማዬ ኋላ ተከትለው ወደ ሳሎን ገቡ። አባዬ ከተቀመጠበት
ተፈናጥሮ ተነሰ።
"ብናመሽም ጎረቤታችንን ሳንጠይቅ አናድርም ብለን ነው የመጣነው አለች..."
ሴቷ እየሳቀች። ሰውዬውም አንገቱን በፈገግታ ነቀነቀላት።
"ታድዬ ተዋወቃችው..."
አለች እማዬ እየሳቀች።
"ታደለ..." አለ አባዬ እጁን እየዘረጋ...
"ማሪቱ..." አለች ሴትዬዋ የአባዬን እጅ እየጨበጠች...
"ተስፋዬ.. " አለ ሰውዬውም ተራውን ጠብቆ እራሱን እያስተዋወቀ። እኔንም
ሁለቱም እያገላበጡ ሳሙኝ። የሴትየዋ ሽቶ ቤቱን አወደው።
"ተቀመጡ .. ተቀመጡ..."
አለች እማዬ ያመጡትን የጠርሙስ አረቄ እየተቀበለቻቸው።
"በሉ ተጫወቱ መጣው..." ብላ እማዬ ሁላችንንም ቦታ ቦታ አሲዛን ወጣች።
አልቆየችም ተመልሳ መጥታ "ማሙሼ ና እስኪ አንተ የምታግዘኝ ነገር..."
አለቺኝ። ወሬ ለመስማት አሰፍስፌ ስለነበር እየተነጫነጭኩ ወጣሁ። ከቆይታ
በኋላ እኔና እማዬ እራት ይዘን ስንገባ አባዬና እንግዳዎቹ ለረዥም ጊዜ
የሚተዋወቁ ይመስል የሞቀ ወሬ ይዘዋል። እኛም ቦታ ቦታችንን እንደያዝን....
"ፀዲዬ ስለ ድሮ ጎረቤታቸው ጥሩነት እያጫወቱኝ ነበር። እና እኛስ ከእሱ
እናንሳለን እንዴ በ
ጉርብትና ?"
እማዬ እንደማፈር እያለች....
"በቆይታ ያዩን የለ..."
"እየው በበቂ ሁኔታ አየነው እኮ እንክብካቤያችሁ..." አለች ሴትየዋ እየሳቀች።
"እንግዲህ ዋናው እሷ ነች። እኔ እንኳን ብዙ ጊዜዬን ፊልድ ነኝ..." አለ ሰውዬው
ፈገግ እያለ።
"አንተ ልጅ እየበላህ አይደለም እኮ..." ብላ ሴትየዋ በትልቁ አንስታ ወደ አፌ
ሰደደችው ፣ ትንሽ ከተግደረደርኩ በኋላ አባዬ በፊቱ 'የጉረስላት' ምልክት
ሲያሳየኝ ፣ ጎረስኩ። አዎ ለመጀመሪያ ጊዜ ሽቶ በእንጀራ ጎረስኩ !
ከምግቡ በኋላ ቡና ተፈላ ተጠጣ። የመጣው አረቄ ተከፈተ ጠጡ። እኔም ተኛ
ተባልኩ !

ከጊዜያት በኋላ ሰፈሩን ለመድነው። ከመጤነት ኗሪ ሆንን። ከአባዬ ውጪ ሰፈሩ
ላይ እኔም ጓደኛ ፣ እማዬም ጎረቤቶች አፈራን። ሆኖም እኔ አንድ ነገር መልመድ
ተሳነኝ። ብቻዬን ውጪ ያለ ክፍል መተኛት። የሆነ ቀን ደግሞ የበለጠ ፍርሃቴን
የሚጨምር ነገር ሰማሁ። ጓደኛዬ ድንገት ወደ አንድ ግዙፍና አንድ አይኑ የጠፋ
ሰውዬ እያሳየኝ...
"ታውቀዋለህ ?" አለኝ።
"አረ እኔ ማን ነው እሱ ? አልኩት።
"የእናንተን ቤት የሸጠላችሁ ነዋ..."
"አረ እኔ አላውቀውም...."
"ደግሞ እናንተ ግቢ ከጀርባ ወደ ጎረቤት የሚያስገባ የቆርቆር በር አለ
አይደል ?"
"አዎ። በምን አወክ በፊት ትገባ ነበር ?"
"አረ እማዬና አባዬ ሲያወሩ አንዴ ሰምቼ ነው ተደብቆ በዛ በር ይገባል...." ሲሉ።
"እኮ ቡና እንዲጠጣ ሲጠሩትና በዛ ላይ ደግሞ...."
"አረ እኔ የሰማሁት ግን ሌላ ነው እሱ...."
"ምንድን ነው እሱ ?"
ብለው ብሰራው ፣ ላወጣጣው ብሞክር እንቢ አልናገርም አለኝ። ከዛች ቀን በኋላ
የባሰ እንቅልፍ አጣሁ። ትንሽ ኮሽታ ያባንነኝ ጀመር። ሰውዬው የሚመጣብኝ
መሰለኝ። ይባስ ብሎ በሳምንቱ የቆርቆሮ አጥሩ ከስር ተቦደሰ። እማዬና
ጎረቤታችን ማሪቱ ቀለል አድርገው 'ውሻ ቀዶት ነው...' አሉ። 'ሰውዬው መጥቶ
ቢሆንስ ?" ልላቸው አልኩና '
"የቱ ?" ቢሉኝ ምን ልላቸው ነው ብዬ ተውኩት።
"ይሄ ነገር እኮ ቢገነባ ይሻል ነበር..." አለ አባዬ ማታ ላይ ቡና እየጠጡ
ስለአጥሩ ስለተፈጠረው ነገር እማዬ ስትነግረው። ደስ አለኝ።
"አዎ እኔንም የቆርቆሮ ድምፁ እየረበሸኝ ነው..."
አልኩ ... ትንፋሼን አሰባስቤ...
"ዝም በል እስኪ አንተ። አንተ ስለፈራህ እኛ ከጎረቤት ጋር መቆራረጥ አለብን
እንዴ ?!"
እማዬ ተቆጣቺኝ።
"ባይሆን ታድዬ ነገ እረፍት ነኝ አላልክም ? ስለዚህ እንደነበረ ጠግነው..."
በንጋታው አባዬ መዶሻውን ፣ መጋዝና ሚስማር ይዞ ወጣ። ደንበኛ አናፂ ሆነ።
እማዬ ካለችው የማይሆነው ነገር የለም እኮ። ገና በሩን ለመንቀል አንድ ሁለቴ
እንደመታው ጎረቤታችን ማሪቱ በር ከፍተው ወጥተው ወደ እኛ እየመጡ።
ከእሳቸው ቀድሞ ሾቶዋቸው እኛ ጋር ደረሰ። ድንገት አባዬን ሲያዩት እንደ
መገረም እያሉ....
"እንዴ እንዴ አንተው ገባህበት ?"
"ምን ላድርግ ብለሽ ነው ? ባልሽ ቢኖር ያግዘኝ ነበር..."
"ወይ ማገዝ እሱ የእራሱን ድርሻስ መች ተወጣና ?"
አባዬ ግራ ገባው መሰለኝ ፈገግ አለ።
"ውሻ የቀደደው እንድፈን ብለን ገና ከመንጋቱ እንግዲህ አናጺ ሆንን....."
"ጅብ እንዳይገባ መሆኑ ነው ?"
ብለው በእራሳቸው ንግግር ይስቁ ጀመር። አባዬ አብሯቸው ይስቅ ጀመረ። ከዛ
በኋላ አባዬ ሲያወራ እሳቸው ሲስቁ ፣ እሳቸው ሲያወሩ አባዬ ሲስቅ ቆዩ። እማዬም
ከገበያ ስትመጣ በአባዬ ስራ ደስ ተሰኘች። እኔ ብቻ እንደተከፋሁ ቀረሁ !

የሆነ ቀን ጠዋት ከእንቅልፌ ስነሳ አባዬና እማዬ እየተጨቃጨቁ ነው። ከክፍሌ
ሳልወጣ በሩ ላይ ተለጥፌ እሰማቸው ጀመር።
"አንተ ልክ ነበርክ እሺ አሁን በግንብ ይታጠር ማለቴ ቆይ ምንድን ነው ጥፋቱ
ታዴ ?"
ጆሮዬ ተጠራጠርኩ። እማዬ የቆርቆሮው አጥር በግንብ ይቀየር ብላ አባዬን
እየለመነችው ነበር።
"ብር የለማ አሁን እጄ ላይ። ቆይ አንቺ ምንድን ነው እንዲህ ያማረረሽ ?"
አባዬ እየተቆጣ ነው።
"በቆርቆሮው ስር ውሻ አልፎ እየገባ ነው እኮ ?"
እማዬ ድምፆ በሳግ ታፍኗል።
"ታዲያ እሱን እንደባለፈው እጠግነዋለኋ..."
"ሁሌ ስትጠግን ልትኖር ነው ? እኔ እኮ ባለፈው በግንብ ይገንባ ስትለኝ ጠግን
ማለቴ ስህተት እንደሆነ ገብቶኝ ነው ዛሬ ስህተቴን ማረሜ.... "
በቀዳዳ ሳይ የእማዬ አይን በእንባ ተሞልቷል። አሳዘነቺኝ። የክፍሌን በር ከፍቼን
ወጣሁ።
"አዎ እማዬ እውነቷን ነው። እኔ እራሱ ማታ ማታ የምሰማው የቆርቆር ድምፅ
እያስፈራኝ ነው...."
አልኩኝ ገና ከእንቅልፌ እንደተነሳሁ እያስመሰልኩ።
"ዝም በል እስኪ አንተ። እና አንተ ስለፈራህ እኛ ከጎረቤት ጋር መቆራረጥ አለብን
እንዴ ?!"
አባዬ ተቆጣኝ። በጩህትም...
"የእሱስ ይሁን እሺ ልጅነት ነው። ቆይ አንቺ ምን አጣሁ ነው የምትይው ?"
ሁለታችንም በቆምንበት ጥሎን ወጣ። እማዬ በረዥሙ ከተነፈሰች በኋላ ድምፆን
ቀንሳ የሆነ ነገር አጉተመተመች። ሰምቼያት ነበር።
"ጠረንህን ነዋ ያጣሁት። ይሄ ያህል አፍንጫ የሌለኝ መሰለው..." ነበር ያለቺው።
ደነገጥኩ። እሷም እንደ'ኔ አባዬን እየዋሸችው ነበረ ? እኔ ማታ ማታ መፍራት
ካቆምኩ ቆይቻለሁ። ምክንያት ነበረኝ። የሆነ ቀን ለሊት የቆርቆሮውን ድምፅ
ሰምቼ ሁሌ ጭንቅላቴ ውስጥ ተቀምጦ የሚረብሸኝን አስፈሪውን የቤታችንን
ሻጭ ለማየት ቀስ ብዬ የክፍሌን በሩን ከፍቼ ወጣሁ። በጨለማ ውስጥ
ደነዘዝኩኝ። አባዬ በቆርቆሮ አጥሩ ስር ሾልኮ ወደ ጎረቤት ግቢ ሲገባ አይቼው
ፈዝዤ ቀረሁ። እማዬም የእሱ ጠረን ናፍቋት እቅፉ ብትገባ ፣ የማሪቱን ሽቶ
(ጠረን)ስባው አርፋ ኖሯል !
ከዛች ቀን በኋላ እናቴ ስታንጎራጉር ሰምቼያት አላውቅም !

@wegoch
@wegoch
@paappii
የምፈልጊውን ፍቅር በማልፈልጊው ሰው በኩል ስታገኚው ምን ይሰማሻል? የማትፈልጊውን ፍቅር ደግሞ ከምትፈልጊው ሰው ስታገኚውስ? ወይ ደግሞ ልብሽ በስስትና በፍቅር ሙልት ብሎ ከምታፈቅሪው ሰው... እፍኝ የማይሞላ ውዳቂ የፍቅር አፀፋ ስታገኚና ከምታከብሪው ከምትወጂው ልታስቀይሚው ከማትፈልጊው እንዲሁም እንደፍቅረኛ ሳይሆን እንደ ወንድም ወይም እንደምሳሌ ከምትቆጥሪው ሰው ደግሞ ልብሽን የሚያጨናንቅ በመስዋትነት የታጀበ ውድ ፍቅር ሲዘንብልሽ ምን ታደርጊያለሽ?

የተዘበራረቀ አለም! ነው ወይስ ለኔ ብቻ ነው የተዘበራረቀው?........... እንደሚያስፈልገኝ የምረዳው "ከለታት አንድ ቀን...." ተብሎ የሚነገር ነገር ከሆነ ቦሀላ ነው. ይፈልገኝ ይሆን እንዴ ብዬ ያሰብኩት ሰው ጭራሽ "የት ነው ይችን ልጅ የማውቃት!?" የሚል ምድብ ውስጥ መድቦኝ ባይ

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Magi
ወግ መፃፍ ለምን እንዳቆምኩኝ...
... (ሚካኤል. አስጨናቂ )
ነገሩ እንዲህ ነው! :)
አንድ ቀን ሚስቴ እንደ ሲኦል እሳት የሚፋጅ ፍርፍር ሰራችልኝ...ያፈላችው ሻይ የጣናን ቱሪስት በጀልባ አንሳፎ ወደ ደሴት ለመውሰድ የተዘጋጀ በሚመስል ሰፊ ኩባያ አቀረበችልኝ ምናምን የሚል ቀደዳ የታከለበት ፅሁፍ ሞነጫጭሬ ነበር ። ፌስቡክ ላይ በሽ ላይክና ኮመንት ሸቅዬበትም ነበር ።
አንድ ወግ ፀሀፊ በምናቡ በሚፈጥራቸው ካራክተሮች ሰክሮ ብዙ ሊቀላምድ ይችላል ።
ብዙ ሊበጠረቅም ይችላል ። ይሄን ህዝብ ለማሳቅ ብብቱ ውስጥ ገብቶ የሚኮረኩረው ቀለም መጣል የግድ ነው ። የተፃፈው ሁሉ የወግ ፀሀፊው ታሪክ የሚመስለው ብዙ አንባቢ ደግሞ አለ ። ባለቤቴ ከነሱ ውስጥ አንዷ ነች። አንዳንዴ ስናደድ አንቺ የንግድ ፍቃድ ያወጣሽ ላይሰንስድ ሰገጤ ነሽ እላታለሁ።
አትሰማኝም!
ስለማትሰማኝም ነው ቀን ላይክ የሸቃቀልኩበት ፅሁፌ በዛኑ ዕለት ምሽት ጦሱን ይዞ ከተፍ ያለው ።
ሀገር ሰላም ብሎ.. .አንድ ሁለት ቡትሌ አረቄውን ልፎ ወደ ጎጆው ለመግባት የተጣደፈው አባት አስፈሪው የሚስቱ ቁጣ ተቀበለው።
"እናት ፍርፍር ነገር ካለ ራቴን ስጭኝ " ርቦኝ ነበረ...
"አንተ ?!... ቆይ ቆይ ... ፍርፍር ስትል?
ከመቼ ጀምሮ ነው እዚህ ቤት እንደ ሲኦል የሚፋጅ ፍርፍር በልተህ የምታውቀው?
የአባቴ አምላክ ሲኦል ያንቦራጭቅህና! "
"ማሬ"
"ማርህን ጎዣም ፈልግ !"
"እናቴ ወግ እኮ ነው። የኔ ታሪክ ሳይሆን የገፀ ባህሪው ..."
"አይ ...አይ እንግዲህ አትሞላፈጥብኝ። የቤትህን ታሪክ እያወጣህ አደባባይ አትበትን።"
እየተንቀራፈፈች ከተቀመጠችበት ሶፍ ላይ ተነሳች።
"ገፀ ባህሪይ ይላል እንዴ? ይልቅ ባህሪህን አስተካክል... Stupid! "...ወደ ጓዳዋ ገብታ የሽንኩርት ቢላዋን አነሳች።
ታድያ ይሄ አጋጣሚ ተከስቶ ሳምንት ሳይሞላው ማስጠንቀቂያውን ዘንግቼ...
"ውሽማዬ የሰራችልኝ የቂጣ ጭብጦ
ከስሯ እንዳልጠፋ አስቀረኝ ጨብጦ😊 " የሚል ግጥም ፃፍኩኝ። ግጥሙን ባለቤቴ ቡና እያፈላችልኝ ጋደም ብዬ ነበር የፃፍኩት።
ላይክና የሳቅ ሪአክት ገፄን አጨናነቀው ። (ላይኩ ብዙ አይደለም...300 ላይክ ብርቅ ስለሚሆንብኝ ነው ...ይ )
አቦል ቡናው ደርሶ ... ጀበናዋ ከከሰል ማንደጃው ተነስታ ክበቧ ላይ ተቀመጠች።
ባለቤቴ ቡናው እስኪሰክን ብላ ስልኳን ስትጎረጉር ቆየችና እዛው እያየኋት ፊቷን አመድ ወረሰው። አጠገቤ ሆረር ፊልም እየተረፀ ይሆን እንዴ? ብዬ ሳሎኔን ለመቃኘት ሁሉ ዳዳኝ!
ቆመች !
አባጅፋር ከነ ቡልኳቸው ላዬ ላይ የተከመሩ ይመስል ከበደችኝ። ከሻሿ ስር አፈንግጠው ያሉ ቡናማ የፀጉር ዘለላዎቿን አየኋቸው።
"ምነው? "
ተንደርድራ ጓዳዋ ገባችና ብረቱ እንደ አዲስ አበባ ኑሮ የሚከብደውን የእንቁላል መጥበሻዋን አንስታ አሽቀነጠረችው። ራሴን ገመሰኝ።
"ምን ሆነሻል ሴትዮ?"
" ጭራሽ እኔን ሴትዮ ! የውሽማህ ቂጣ ነዋ ያጠገበህ.. . "
"የምን ውሽማ? " ...
" ከስሯ የማያርቅ የቂጣ ጭብጦ የምትሰራልህ ጭማሪ ሚስትህን ነዋ !"
"እንዴ.. . ይሄ እኮ ገፀባህሪይ.. .. "
ባለቤቴ አላስጨረሰችኝም.. .
" ባህሪህን ማስተካከል ካልቻልክ ይህችን ያዝበት.. . "
ሰፊው የአጥሚት ኩባያ ሀማስ እንዳስወነጨፈው ሮኬት ተምዘግዝጎ ወደ ግንባሬ አቅጣጫ ተወነጨፈ.. .. :)

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Mikael aschenaki
#ቅንድል_ዲጂታል_መፅሔት

ቅፅ2- ቁጥር9
በነፃ ለማንበብ 👇የታችኛውን pdf ይጠቀሙ፡፡
ሁለቱን ባሎቼን ላስማማ እያሸማገልኳቸው ነው!!
(ሜሪ ፈለቀ)

ግርምታችሁን እና እርግማናችሁን ከማዥጎድጎዳችሁ በፊት ትንፋሽ እየሰበሰባችሁ ከመጀመሪያው ልጀምርላችሁና ሁለቱንም ላስተዋውቃችሁ።

የመጀመሪያው ባሌ “ባለቤቴ ነው ተዋወቂው!” ብዬ ያስተዋወቅኳት ጓደኛዬ “ወየው በፈጣሪ ባልሽ ሲያምር አጣብሺኝ!” ያለችለት ውብ ነው።

የገዛ እናቴ ልክ እንደጠበስኩት ስታውቅ “ውይ ልጄ የልጁን ህይወት አታበልሺ አጉል ታደርጊዋለሽ !ይቅርብሽ በሞቴ!!” ብላ የለመነችለት ስነስርዓታም ነው።

የቤተክርስቲያናችን ፓስተር ጠርቶኝ “ሜሪ ሰይጣን አንቺን ተጠቅሞ ልጁን ከጌታ ቤት ሊያስኮበልል እየተጋ ነው።” ያለለት የቸርቻችን ዓይን የሆነ አገልጋይ ነው።

እሱስ ብትሉ? መጀመሪያ እጄን የጨበጠ ቀን “ሜሪ እባላለሁ!” ስለው

"ሜሪ ....ሜሪ ? " ብሎ ሰይጣንን ራሱን የጨበጠ ይመስል እንዴት እጄን አሽቀንጥሮ እንደጣለው። የጨበጠኝን እጁን ልብሱ ላይ ሁላ ቢጠርገው ደስ የሚለው ይመስለኛል።

እሱ ለከተማውም ለቸርቹም አዲስ ነበር። እኔ ደግሞ ከቸርቹም ከወሬውም ገለል ለማለት ክረምት ስለነበር ሁለት ወር አዲስአበባ ከርሜ መመለሴ ነው። ጫፉን እንኳን ያልነካሁትን ቀድሞ የነበረውን ፓስተር በዝሙት ጣለችው ተብዬ ተወንጅዬ መሆኑ ነው። ቢችሉ እንደጌታ ቢሰቅሉኝ ደስ ይላቸው ነበር። ያው ጫፉን አልነካሁትም አልኳችሁ እንጂ ከንፈሩን ነክቼዋለሁ። ከንፈርና ጫፍ ይለያያል አይደል? እኮ!! 🤷🏽🤷🏽 ነገሩ ውስብስብ ሆኖ አይደለም ሲያወሳስቡት እንጂ። ስለፓስተሩ በኃላ እመለስላችኋለሁ።

ስለዋናዬ ላውጋችሁ። ክረምቱን ጨርሼ እንደተመለስኩ እቤት ከምላሳቸው ላይ የሱን ስም እንዴት ላውርደው? ቸርች ውስጥ የማይገባበት የለውም። ይሰብካል ..... ይዘምራል(ውብ ድምፅ ድክመቴ ነውኮ ደግሞ) ........ ፒያኖ ይጫወታል....... ወላ ኤሌክትሮኒክስ ነገር ሲበላሽ ይጠጋግናል ........ ቸርቹን ያፀዳል የማያደርገው የለውም። በቃ ምንም ይሁን

እነማሚ ....ቸርች አዲስ የመጣው .... ልጅ እንዲህ ብሎ .... እንዲያ ብሎ .... ሳላየው ብዙ ሰማሁ:: የተዋወቅን ቀን ደግሞ እሱም ሳያየኝ ብዙ እንደሰማ ገባኝ። ያው ክፉ ክፉውንም ቢሆን......

ወንድሜ አጠገቡ ነበረ “እህቴ ናትኮ!” ይለዋል

“ሜሪ ያንተ እህት ናት?” አባባሉ ይህቺ አጋንንት እንዴት ብላ ከእናንተ ቤተሰብ ተፈጠረች? እንዴት ነው መልዓክና ሰይጣን ተስማምታችሁ አንድ ቤት የምትኖሩት? አይነት ለዛ ነው። የለመድኩት ነገር ስለሆነ ስቄ ለወንድሜ ምግቡን አቀብዬ ተመለስኩ።

ከዛ በኋላ እኔ አልደረስኩበትም። ስለእውነቱ ጭራሽ በሀሳቤም በልቤም የለም። ለራሴ በአንድ ፓስተር ከንፈር ጦስ ሳቢያ መፅሃፍ ቅዱስ ላይ ያሉ ክፉ ሴቶች መንፈስ ሁላ ስም (የኤልዛቤል መንፈስ የደሊላ መንፈስ ሲወጋ የሚውለው የሴቶች መንፈስ ብዛት ) እየተጠቀሰልኝ እጅ በመጫን ፀሎት ብዛት ሌላ አገልጋይጋ መድረሻ እጅም እግርም ፍላጎትም የለኝም።

ከወንድሜጋ ሁሌ እሁድ ከቸርች በኋላ እቤት ይመጣሉ። እሱ ማውራት ሲጀምር እቤት አፉን የሚከፍት የለም። ፀጥ ብለው ይሰሙታል። ስለምንም ርእስ ይነሳ ይቀዳል የቸርቹ ወሬ ብዙም ስለማይጥመኝ አልሳተፍም። ድንገት በሆነ ሰበብ ወደሳሎን ብቅ ካልኩ በገዛ ቤቴ ይገላምጠኛል። ወይ በነገር ይተናኮሳል። ቤቴ ነው ብዬ አልፈዋለሁ።

“ቸርች ለምንድነው የማትመጪው?” አለኝ የሆነ ቀን ኮስተር ብሎ ውጪ ተቀምጬ የማነብበት መጥቶ

“ለምንድነው የምመጣው?”

“ለመፀለይ ..... ጌታን ለማምለክ ..... ጌታን ለመፈለግ .... ወንድሞች በህብረት ቢቀመጡ መልካም ነው እነሆም ያማረ ነው!!”

“ዌል ወንድም አይደለሁም እንደምታየው!”

“የምሬን ነው!” አለ ፈገግ ብሎ:: ‘ጥርስህኮ ሲያምር በየሱስ ስም! ምን ሆነህ ነው ሁሌ የምትኮሳተረው?’ ልለው ነበር። ያው በደህና አያይብኝም ብዬ ዋጥኩት

“ሲገባኝ ቸርች የምትሄደው ሸክምህን ለማራገፍ ነው። ፈራጅ በየመንገዱ ሞልቷል። ለምን ብዬ ቸርች ሄጄ የፈራጆቼን አይን እያየሁ ራሴን እኮንናለሁ? አምላክ ፍቅር ነው እኔ እስከገባኝ። ፍቅርን ፍለጋ የምሄድበት ቸርች ገና እግሬ ሲረግጥ ዘማዊት ናት ትወገር የሚሉ አይኖች እና እኛ ካንቺ የተሻልን ፃድቃን ነን ብለው የሚመፃደቁ ሰዎች ጋር ተቀላቅዬ ራሴን ለምን አሳንሳለሁ? Am ok where I am now. “

ዝም አለኝ። ሁለታችንም ዝም ከምንል ብዬ ቀጠልኩለት

"ታውቃለህ ያቺ ዘማዊት ሴት መፅሃፍ ቅዱስ ላይ ስትዘሙት አጊንተናት ነው ብለው ወደእየሱስ ያመጧት? ህም ሁሌ የሚገርመኝ ነገር ከሆነኛው ሰውዬጋ ነውኣ ስታመነዝር ያዩዋት? እሱን 'በል ሱሪህን ታጠቅና አምልጥ ብለውት ነው እሷን ብቻ ይዘዋት የመጡት? ለምን እሷን ብቻ ኮነኗት? ምናልባት ሰውየው ወዳጃቸው ነው? አልያም ክብሩ የማይነካ ስም ያለው ሰው ነው? ለሁለት ባጠፉት ጥፉት እሷ ብቻ እንድትወገር ለምን ተፈለገ?"

ብዙ ዝም አለኝኛ "የሚወራው ግን እውነት ነው?" አለኝ

"አይገርምህም ግን ማንም ሰው እውነት ነው ወይ ብሎ ጠይቆኝኮ አያውቅም! ቤተሰቤን ጨምሮ የተፈጠረውን እንኳን ሳያውቁ ነው ሲወጉ የሚውሉት" ድክም ብሎ ሳቀ

"እውነት ነው ግን?"

"ግማሹ እውነት ነው። እውነት የሆነው ክፍል 'የሆነ ነገር ነበራቸው' የሚለው ነው። 'በሷ ምክንያት ነው ከአገልግሎት የታገደው!' የሚለውም እውነት ነው። እርግጥ 'አሳሳተችው' የተባለውም እውነት ነው ያው የተሳሳተው ምን ድረስ ነው የሚለውን ነው ልክ ያልሆኑት።"

እንደሆነ ተዓምር ያየኛል። ...... ፈገግ ይላል። እሱ እንደሚለው ይሄን ቀን ነው ነፍሴን የወደዳት ....

"ፓስተር የመጣ ጊዜ እኔ ዼንጤነቱን እርግፍ አድርጌ ትቼው ነበር:: ... ማሚ በስንት ጉቦ የሆነ ቀን ይዛኝ ስትመጣ ... ሸበላ .. ወጣት ... ሲናገር የሚጣፍጥ አዲስ ፖስተር እየሰበከ ነው:: ከጏደኞቼጋ ነበር የመጣነው:: ተያየን ... 'በየሱስ ስም ይሄ ዼንጤ ብሆን ራሱ ሲኦል ደርሶ መልስ ትኬት ያስቆርጠኛል' አልኳቸው:: 'በፍፁም አይደረስበትም ... ፓስተርኮ ነው!' ተባባልን:: ከዛ በብር አስያዝን ... እጠብሰዋለሁ ብዬ!! ... ያው አባቢ ፓስተር ስለሆነ መግባባት ጊዜ አልፈጀብኝም:: ... እንዳልኩትም ጠበስኩት:: ችግሩ እሱ የምሩን የጌታ ሰው ነው.... ልክ የደፈርኩት አስመስለው የሚያወሩት (ልክ ልፉ ነገር አስመስለው) ... እሱ እወድሻለሁ ካለኝ በኃላ ራሱ ንሰሃ የሚገባ ነው የሚመስለኝ::"

ድክም ብሎ እየሳቀ ይሰማኛል:: .... ይኼኛው ዼንጤው እሱ አይደለም:: ሰው የሆነው እሱ ነው:: ከቤት እየወጡ ቼክ እያደረጉ ስላስቸገሩን ወክ እያደረግን ወሬውን ቀጠልኩለት::

"ከዛማ በቃ ... የሆነ ቀን ስሞኝ .... በፀፀት አለንጋ ሲዠለጥ ከረመ:: ... እኔ ብሬን በላሁ:: እሱ አመረረ ... ጭራሽ በቅድስና ፍቅራችንን እንድንኖር እንጋባ አለ:: ... ከዛ እውነቱን ነገርኩት:: ... መልቀቂያ አስገብቶ ወደአዲስ አበባ መሄዱን ሰማሁ.... ከዛ እዛም እንዳያገለግል መታገዱን ሰማሁ !! ከዛ የማውቀው ታሪክ የለም:: ... ምን እንዳላቸውም አላውቅም:: ብቻ በኔ ምክንያት መሆኑን ነግሯቸዋል!! .... "

ሳናውቀው ብዙ መንገድ ተጏዝን!! .... ስንመለስ እጁን ትከሻዬ ላይ ጣል አድርጎ .... እብድ እንደሆንኩ እየነገረኝ ነበር::

"ይቅርታ በጣም! በሰማሁት ልዳኝሽ አይገባም ነበር::" አለኝ እቤት ልንደርስ አካባቢ

"እሺ ይኸው እኔ እውነቱን ነግሬህ የለ? ምንድነው
የሰማኸው?"

"ካንቺ በጣም መጠንቀቅ እንዳለብኝ:: ካለበለዚያ እንደምታባልጊኝ " እየሳቀ ነው...

ማሚ በሩጋ ቆማ እየጠበቀችኝ ነው:: ..... አስተያየቷ 'ደሞ በምን አገኘሽው?" አይነት ነው::

........ አልጨረስንም......

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Meri feleke
ሁለቱን ባሎቼን ላስማማ እያሸማገልኳቸው ነው !!
(ክፍል ሁለት)

የሳመኝ ቀን "በናትህ ይሄን ነገር በምስክር ፊት አድርግልኝ" ብለው ደስ ባለኝ። ስሜ መራራ ነዋ። ሳመችው እንጂ ሳማት አይባልልኝማ! እርግጥ የሳመኝ እለት ያልኳችሁ ቀን ማለት በዋዛ የተገኘ እንዳይመስላችሁ

"ጌታ ሆይ ይሄ ሰው በወንድምነት ይሁን በባልነት ፍቅር የሚወደኝ መለየት የምችልበት ፀጋ ስጠኝ! .... ወይ ምልክት ነገር አሳየኝ! ..... ቢያንስ በህልሜ አንድ ጋቢ ለሁለት ስንለብስ ምናምን ....... አለ አይደል የሆነ ምልክት በቃ ...... እኔ ልጅህ በውዝግብ ስንገላታ በቤትህም እንደሚገባህ እያገለገልኩህ አይደለም! (ይሄኛው በእርግጥ ለራስህ ስትል ባሪያህን አስባት አይነት ልምምጥ ነው። ውለታዬ አለብህ በዚህ እንኳን ክፈለኝ አይነት ሰፋጣም ነው።) ብዬ ፆም ፀሎት ልይዝ ትንሽ ሲቀረኝ ነው ያው ምልክት መሆኑ ነው መሳሙ!!

ከምልክቱ አስቀድሞ ከወራት በፊት
ሲሊፐር ያጠለቁ እግሮቼ የቸርቹን በር አልፈው ሲገቡ ራሴን አገኘሁት። ከቤት የወጣሁት ቁምጣዬን ሆዴን በሚያሳይ አላባሽ ለብሼ ከእግዜሩ የተጣላሁበት የወንድሜ መቃብር ጋር ለመሄድ ነበር። እንደለመድኩት

"የማይሰማ ፀሎት ለምን እፀልያለሁ? ወይም ቁልጭ አድርገህ በዚህ ጉዳይ አትፀልዩ ምናምን ብለህ ህግ ብታወጣ ጥሩ ...... በደፈናው ብቻ አንኳኩ ...... ብቻ ፀልዩ አልክ ...... ከዛ ግን የማትሰማው ፀሎት ብዛቱ ....." እያልኩ ከራሱ ከፈጣሪ ጋር እየተነታረኩኝ በእግሬ እስኪደክመኝ ከተጓዝኩ በኋላ ነው ድንገት አቅጣጫዬን ወደቸርቹ ያዞርኩት ......... ገባሁ።

ለወራት ያላዩኝ አስተናጋጆች በፈገግታ ሰላም እያሉኝና አለባበሴን እየገላመጡ ክፍት ቦታ አሳዩኝ። እሱ መድረኩ ላይ አይኑን ጨፍኖ ፒያኖውን እየመታ ይዘምራል።

ከተደረገልኝ በጎነትህ
አንዳችም ለእኔ የማይገባ ነበር
በቸርነትህ አድርገሃልና እደነቃለሁ
አብዝቼ ተመስገን እላለሁ ......

እያለ በሚጣፍጥ ድምፁ ይዘምራል:: ህዝቡ ቆሞ ግማሹ እጁን ወዳፈጣሪ አንስቶ .... ግማሹ ወሬ እያየ ግማሹ ጨፍኖ አብሮት ይዘምራል። መግባቴን ያወቀ ይመስል አይኖቹን ገልጦ አየኝ። ተያየን!! ፈገግ ብሎ አይኖቹን ጨፍኖ ማስመለኩን ቀጠለ። ያስተዋለ ሰው ምላስ ማሟሻ ሆኜ መክረሜን እያወቅኩት ሳቅ ብዬ ተቀመጥኩ። የዛን ቀን ስንወጣ ሲንደረደር መጥቶ አቀፈኝ (በጌታ ፍቅር ነው ይህኛው)

"ስለመጣሽ ደስ ብሎኛል። ሳይሽ በጣም ነው ደስ ያለኝ" አለኝ ወደጆሮዬ ጠጋ ብሎ "ምንም እንኳን ቸርች ለመምጣት አስበሽ ባትመጪም!" አለኝ። አለባበሴን መሆኑ ገብቶኛል።

ከዛን ቀን በኋላ የጌታ ፍቅር ይሁን የሱ ፍቅር መጀመሪያ ሰሞን ባልለየሁት ምክንያት ቸርች እመላለሰው ጀመር። በሳምንት እሮብና እሁድ መደበኛ የቸርቹ ፕሮግራም አልበቃ ብሎኝ ...... አርብ የአገልጋዩች ፕሮግራም ...... ቅዳሜ የወንድሞች ፕሮግራም ...... ማክሰኞ የማለዳ ፀሎት ..... ብቻ ምንም ይሁን እሱ ካለ እኔ አለሁ!!

ፕሮግራሞቹ ሲያልቁ እስከቤት መንገድ እያራዘምን ወክ እያደረግን የባጥ የቆጡን እናወራለን። ጠዋት ተነስቶ ትምህርት ቤት ድረስ ሸኝቶኝ ይመለሳል። የማነባቸውን መፅሃፍቶች ተከራይቶልኝ ይመጣል:: ... አንብቦ ነው የሚሰጠኝ... እኔ አንብቤ ስጨርስ መፈጠራችንን ለማያውቀው ደራሲ ሂስ እንሰጣለን.... እንከራከራለን....

ማታ በየቀኑ ደብዳቤ ይፅፍልኛል... እኔም እፅፍለታለሁ ... ጠዋት ስንገናኝ ደብዳቤዎቹን እንቀባበላለን:: ከሰዓት ከስራ የሚወጣበት ሰዓት ከኔ ጋር ስለማይዛመድ ከሱጋር ሳይክሌን እየገፋሁ በእግሬ 40 ደቂቃ የሚወስድብኝን መንገድ በሳይክል በ10 ደቂቃ እልሰዋለሁ።

ደጋግመን የሄድንባቸው መንገዶች ኮቴያችንን ሰምተው እስኪያውቁት .... በየመንገዱ ያሉ የንግድ ቤት ዘበኞችና ቋሚ የኔቢጤዎች እንደወዳጅ ሰላምታ መስጠት እስኪጀምሩ ...... ቤተኞቼም የኔና የእሱን አብሮ መውጣትና መግባት ከመልመዳቸው የተነሳ እሱ የአጥሩን በር ሲያንኳኳ 'ሜሪ መጥቷል!' ብለው መጥራት እስኪለምዱ ..... ከዚህን ያህል የጊዜ ለውጥ በኋላ ነበር የሳመኝ። (መፀለይ ይነሰኝ?) እንደጠጣ ሰው ጀብረር አድርጎኝ ነበር አሳሳሙ ሳልዋሻችሁ (ቤተኞቼ አንድም እሱን ስለሚያምኑት 'የጌታ ሰው' ስለሆነ ... ሁለትም ለወትሮው በየቀኑ የሆነ ጥፋት የማጠፋ የነበርኩትን ልጅ ስላለዘበላቸው ... በተጨማሪም ወደ ቸርች ስለተመለስኩላቸው .... ከእርሱ ጋር መውጣት መግባቴ ብዙም አልጎረበጣቸውም)

ይሄ በሆነ በጥቂት ቀን "የስራ እድገት አጊንቼ ሌላ ሀገር ልሄድ ነው አለኝ!" እንዴት እንደሚነግረኝ አፉ ላይ ቃላቶቹን ሲያንገዋልላቸው ቆይቶ

"እኔስ? ስምንት ወር ሙሉ እጅህን ተመርኩዤ ሀዘኔን የረሳሁት እኔስ? ትተኸኝ ስትሄድ ምን ልስራ? በቀን ሁለቴ የማይህ እኔስ አንተ የሌለህበትን ቀን እንዴት ልለፍ? ምን ልስራ? አንተ ሳትኖር ማነኝ? ንገረኝ ምን ልሁን?"

እንደሚሄድ እርግጠኝነት ነበረው ድምፁ ስለዚህ 'ቅርልኝ' ልለው አቅሙ አልነበረኝም። ምን ያህል በፍቅር ሙክክ ብዬ እንደበሰልኩ የገባኝ የዛን ቀን ነው። ለወትሮ በሰው ፊት ማልቀስ ያውም ለማልቀስ ምክንያት በሆነኝ ሰው ፊት ማልቀስ ሽንፈት የሚመስለኝ እኔ ....... በሱ ፊት ተዝረከረኩ።

"በቃ አልሄድም እቀራለሁ::" አለኝ "በቃ አንቺ ትምህርትሽን እስክትጨርሺ የትም አልሄድም ይቅር !" አለኝ አቅፎ እያባበለኝ። አዲሱ ስራው አዲስ በተከፈተው የአቢሲንያ ባንክ ማናጀር ሆኖ ነው የሚሄድ የነበረው። ገና እንደተመረቀ ነው አሁን የሚሰራውን ስራ አጊንቶ የጀመረው። በአንድ አመቱ አሁን ያገኘው እድገት ለእሱ ምን ያህል ትልቅ ነገር መሆኑን አውቃለሁ። 'ትቼልሻለሁ' ሲለኝ የባሰ ሙክክ ከማለት ውጪ ምርጫ ነበረኝ? እኔ ደግሞ አስራ ሁለተኛ ክፍልን ገና መጀመሬ ነበር። ተስማማን!! በሆነ መልኩ ራስ ወዳድ እንደሆንኩ ገባኝ።

"ይዘኸኝ ሂድ!" አልኩት በነገታው ጠዋት ትምህርት ቤት ሊሸኘኝ እንደመጣ እስክነግረው ጓጉቼ እላዩ ላይ እየተንጠለጠልኩ ምን እንዳልኩ ገብቶታል። ግን ማመን አልፈለገም።

"የት ነው ይዤሽ የምሄደው? የምትዪው የማስበውን ከሆነ.... አይሆንም!!" አለኝ ኮስተር ብሎ

"ለምንድነው የማይሆነው?"

"ስለምወድሽ ነው የማይሆነው!! ...የኔ ሚስት በስነስርዓት ለቤተሰቦቿ ሽማግሌ ልኬ .... ቸርች ቆሜ በጌታ ፊት ቃል ገብቼላት .... በቤተዘመድ ተመርቀን ..... ነው የማገባሽ! በፍፁም እንደወመኔ ብድግ አድርጌ ይዤሽ አልሄድም። ትምህርትሽን በጥሩ ውጤት ትጨርሻለሽ .... እንደህልምሽ ህግ ትማሪያለሽ ..... ስትመረቂ ከፈለግሽ የምርቃትሽ ቀን ሰርጋችንን ማድረግ እንችላለን።" አለኝ ኮስተር ብሎ ቀጠል አድርጎ "አንቺ ግን የምርሽን ነው?"

"እሱማ የምሬን ነው። ቆይ ምንድነው ያልከውን ሁሉ ከማድረግ የሚያግደኝ? ሰሞኑን ሽማግሌ ትልካለህ .... ከዛ ቸርች ሄደን ቃል እንገባባለን.... ይዘኸኝ ትሄዳለህ .... አንተም ስራህን እኔም ትምህርቴን ..."

"እ እ አይሆንም አልኩ አይሆንም!" አለኝ ከአፌ ቀምቶ "እብድ እኮ ነሽ ..."

ማታ ምን አቅብጦኝ እንደሆነ ሳላውቅ ለማሚ ነገርኳት። በቤቴኮ 'እንዴት ያለ የተባረከ ልጅ ነው::' ብላ እንድታሞግስልኝ ነበር:: ቦንብ ማፈንዳቴ አልታወቀኝም። ከዛን ቀን በኋላ እሱ እኛ ቤት በምንም ሰበብ ቢሆን እንዳይመጣ ለእርሱም ለወንድሜም ማስጠንቀቂያ ተሰጠ። ትምህርት ቤትም ሆነ ቸርች ወይ ማሚ ወይ አባቴ ሆኑ የሚያደርሱኝ። ቸርች
የምሄድባቸው ቀናት ተወሰኑልኝ። እሱም ቸርች ማስጠንቀቂያ ደረሰው። አንድ ሳምንት ሳናገናኝ አለፈ። ... እንደዛ እንደመልዓክ የሚያዩት ቤተኞቼ .... ሲያዩት ሁላ የሞት መንፈስ እንዳዩ ይሸሹት ጀመር ... ማሚ ጭራሽ ተከርብታ 'ባንተ ተመስሎ ልጄን ከአላማዋ ሊያሰናክል ያለ መንፈስ ወጋሁ!!" ብላዋለች🤣 ለትምህርት ቤት ሁላ ማንም ቢጠራኝ እንዳያስጠሩኝ መልእክት ተላለፈ። በርቀት መድረክ ላይ ብቻ አየዋለሁ።

(ምንም አልገቡኝም:: ቀላሉ መንገድ ከኔጋር ማውራት ነበርኮ ... እውነቱንኮ ነግሬያቸዋለሁኝ... )

ከዛ ግን ያቺ እንቢ ባዩዋ እኔ ሁሉንም "የራሳችሁ ጉዳይ!" አለች ከትምህርት ቤት አሞኛል ብዬ አስፈቅጄ ስራ ቦታው ስበር ደረስኩ ሲያየኝ ሊጮህ ሁላ ዳዳው በደስታ ከመሬት አንስቶ አየር ላይ አሽከረከረኝ።

"የማብድ መስሎኝ ነበር::" አለኝ ፀጉሬን.. አንገቴን .. ጉንጬን ... ከንፈሬን ... እየሳመ... እንደሌላው ቀን ለሚያየው ሰው ሁላ ሳይጨነቅ

"አሁንስ ይዘኸኝ አትጠፋም?" አልኩት

ፈገግ ብሎ "መቼ?" አለኝ

........ አልጨረስንም ......

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Meri feleke
ሁለቱን ባሎቼን ላስማማ እያሸማገልኳቸው ነው!!
(ክፍል ሶስት)

ሁለተኛውን ባሌን እስክተዋወቀው ሰዓት ድረስ ዓለሜ ሁሉ እሱ ነበር (የመጀመሪያው ባሌ) ትምህርቴ .... ትዳሬ .... ፍቅሬ .... ቤተሰቤ ... ጓደኛዬ .... ወንድሜ ....... ይሄን ሁሉ ከኋላዬ ትቼ እርሱን መርጫለሁኛ!!

እንዲህ ነበር የሆነው
«ይዘኸኝ ጥፋ!» ያልኩት ቀን ከተማ ይዞኝ ሄዶ ቀለበት ገዛን። ማንም በሌለበት ቸርች ሄድን። ልክ እኔና እሱ ሙሽራ እንደሆንን ... የቸርቻችን ፓስተር እያጋቡን እንደሆነ አስመስለን መድረኩ ፊት ቆምን።

"ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን በወደደበት መውደድ በፍፁም ልቤ ልወድሽ በህመምሽ በጤናሽ በማግኘት በማጣት....." ብሎ ቃል ገባልኝ! በእንባው ቃሉን አተመልኝ።

"ሚስት ለባሏ እንደምትገዛው ልገዛልህ! በጤናም በህመምህ በማግኘት በማጣትህ ልኖርልህ ....." ብዬ ቃል ገባሁለት። የደስታ እንባዬን እያነባሁ ቃሌን አተምኩለት።

'Now you can kiss the bride' የሚለውን ክፍል የኛ ቸርች ፓስተሮች የማይሉት ቢሆንም እኛ ለራሳችን ብለን ተሳሳምን።

'just married' ብለን መኪና ጀርባ ላይ ባንለጥፍም ወደ እሱ ቤት እንዲያደርሰን ለያዝነው ባለላዳ ሹፌር 'ተጋብተን መምጣታችን ነው!' ብለን ነግረነዋል። እንደሙሽሪት ወግ ከነዩኒፎርሜ ወደላይ ተሸክሞ አቅፎኝ ወደተከራየባት አንድ ክፍል ቤት (አንድ ክፍል ቤት ለማለት እንኳ ይከብዳል። አንድ አልጋ ቢባል ይቀላል። ክፍሏ ከመጥበቧ የተነሳ ያለማጋነን በሩን ከፍተን አልጋው ጋር ላይ ነው ያረፍነው። ላለመሳሳት ሀሳብ ኖሮን ቢሆን እንኳን ክፉኛ ፈታኝ ነበር።) ልብሶቻችንን ምኑጋ እንዳወለቅነው ሳናውቅ ተጣመድን!! (ብዙም አታስቡት የመጀመሪያዬ አይደለም። የመጀመሪያው አይደለም። ሁለታችንም አሳምረን ያወራነው ጉዳይ ስለሆነ ቀጥታ ወደስራ) ካላብን በኋላ የምንጠፋበትን ቀን እስክንቆርጥ ደብዳቤ እየተፃጻፍን ትምህርት ቤት ደጅ ያለ ሱቅ ልናስቀምጥ ተነጋግረን ወደቤት ሄድኩኝ። አባቢ ትምህርት ቤት ሊያመጣኝ ሄዶ ገና በጠዋቱ 'አመመኝ' ብዬ መውጣቴ ተነግሮት ስለነበር እሳት ለብሰው ነገር ጎርሰው ሲንጎራደዱ ጠበቁኝ። ልቤ አብጧል:: ፍቅር ጠግቤ ነዋ የመጣሁት

"አዎ እሱጋ ነበርኩ" አልኩ

"ምን ልሁን ነው የምትዪው?" ማሚ ቀወጠችው።

"ማግባት ነው የምፈልገው። ላገባው ነው የምፈልገው። አስገድዳችሁ ከሱ ልትለዩኝ አትችሉም!" ደሞኮ እያለቀስኩ ነው ምኑ እንደሚያስለቅሰኝ ባላውቅም

"እንዴት እንደማልችልማ አሳይሻለሁ። ትዳር? አንቺኮ ህፃን ነሽ? ጌታ ሆይ ልጄን ምንድነው ያስነካብኝ?"

"18 ዓመት ሞላሁ::" አልኩ ፍርጥም ብዬ። ይሄኔ በምንም የማልሸነፍበት ግትርናዬ ላይ መድረሴን ስታውቅ መውረግረጓን ትታ ተቀመጠች። እስከዛ ምንም ያላለው አባቴ

"ህልምሽስ? ትምህርትሽስ?" ሲለኝ ሃሳቤ ሊከፈል ምንም አልቀረውም። አባቴ ኩራቱ እንደሆንኩ አውቃለሁ። ልጄ ህግ ተምራ ወነጀል ነክ መፅሃፍ መጻፍ ነው የምትፈልገው ብሎ ሲጎርርብኝ በእርግጠኝነት ነው። ትምህርት ቤት በየተርሙ ውጤት ሊያይልኝ ይሄድ የነበረው እሱ ነው። 'ሜሪ በትምህርቷ ጎበዝ ናት!' ብለው ውጤቴን ይዘረዝሩለትና በመደዳ ያጠፋሁት ጥፋት ሲነገረው 'እኔ እቆጣታለሁ ትታረማለች!' ይልልኛል። ስንወጣ ግን ለጥሩ ውጤቴ እጋበዛለሁ እንጂ ለጥፋቴ ቁጣም ሆነ ተግሳፅ አያዘንብብኝም። ልጁ ከነረባሽነቴ ኩራቱ ነኝ!! በፊት ወንድሜ በህይወት እያለ ወደቤት ሲገባ የሚጠራው የሱን ስም ነበር። ከሱ ሞት በኋላ 'ሜሪ' እያለ ነው ወደቤት የሚገባው

"እማራለሁ። እሱ እንዳልማር አይከለክለኝምኮ!" ድምፄ ወደማባበል ሄደ። "እማራለሁ። ተመርቄ አኮራሃለሁ። እሱን አጥቼ ግን መማር አልችልም።" በቃ አባቴ ከዚህ በኋላ አልተናገረም። ማሚ ቀጠለች።

"ትዳር እንደምታስቢው ቀላል አይደለም ልጄ!" ልምምጥ ..... ከዛ ደግሞ ቁጣም ታደርገዋለች።

"አይሆኑ ሆነን ያን ሁሉ ብር እየከፈልን ያስተማርንሽ ለከንቱ ነው? ሽሮ እየበላሁ ስጋ የቋጠርኩልሽ ሰው እንድትሆኚልኝ እንጂ ማንንም አግብተሽ የትም እንድትቀሪ ነው?" ደግሞ ድምፅ አውጥታ ታለቅሳለች:: ሆዴ ቡጭቡጭ ከማለቱ ደግሞ እልህ ይይዛታል መሰለኝ(የእኔ እናት አይደለች)

"እስኪ ልብ እዚህ ቤት አስተዳዳሪው ይለያል። እኔ በህይወት እያለሁማ እንዲህ አይደፍረኝም። "

በተዘባረቀ ስሜት ከረምኩ። ከሱጋር በደብዳቤ መገናኘታችንን ቀጠልን። እሱም የቢሮ ፕሮሰሱን እየጨራረሰ ሳለ የሆነ ቀን እቤት ጠዋት ማሚ ከእንቅልፌ ቀስቅሳ

"እውነቱን ንገሪኝ እርጉዝ ነሽ?" አለችኝ። አበድኩባት::

"ምንድነውሱ? ከየት ያመጣሽው ነው?" ብዬ እየቀወጥኩት ፔሬዴ መምጫውን ቀን እቆጥራለሁ።

"ማታ በህልሜ አይቻለሁ::" ብላ ገገመች። በፍፁም ብዬ ገገምኩ። እንደለመድኩት ከትምህርት ቤት ጠፍቼ ልመረመር ከሱጋ ሄድን። አርግዣለሁ!!

ደስታም ድንጋጤም ብቻ መላው ያለየለት ስሜት ተተራመሰብን። እዛው የሆስፒታሉ አግዳሚ ላይ እንደህፃን ልጅ ውስጡ ጥቅልል አድርጎ አቅፎኝ ለአንድ ሰዓት ተቀመጥን። ብቻ እየደጋገመ

"እኔ አለሁልሽ አይደል?" ይለኛል። ምንም ቃል ከአፌ ባያወጣም ግራ የገባው ስሜት ነበር የሚሰማኝ።

ከዚህ ብዙም ባልራቀ ቀን ጨርቄን ማቄን ብዬ ሁለታችንም ከዛ በፊት ረግጠነው ወደማናውቀው ከተማ ሄድን። እንደማንኛውም መደበኛ የዘመናችን ትዳር አንድ ፍራሽ ... ሁለት ብርጭቆ ... አንድ ድስት .... አንድ መጥበሻ ... አንድ ጭልፋ ..... ቢላ ...... ብለን ቤት ተከራይተን መኖር ጀመርን። በእርግጥ አንዳንዴ እቤት ውልብ ይሉብኝና ከሆርሞኑ ጋር ተደርቦ እነፋረቃለሁ።

እናቴ መጥፋቴን ስታውቅ የምትለውን አስባለሁ አባቴ እንዴት አዝኖብኝ ይሆን እላለሁ። ባሌ ግን እናቴም አባቴም ወንድሜም ፍቅረኛዬም ጓደኛዬም ሆነ።

የአራት ወር እርጉዝ ሆኜ ነው አዲሱ ባሌ የመጣው። በዓል ሆኖ እሱ ዶሮ እያረደልኝ። አጠገቡ ቆሜ እያየሁት ነው። ከጎናችን ያለው ተከራይ አሁን በውል የማላስታውሰውን ነገር ያወራኛል። እመልስለታለሁ። ባሌ ሲናደድ አየሁት ምክንያቱ ስላልገባኝ ወሬዬን አላቆምኩም:: ደግሞ መገልፈጤስ? ጨርሰን ስንገባ ደም የነካካውን ቢላ እና ሞረድ እያጣጠብኩ

"አባ ምን ሆንክ?" አልኩት

"ባለትዳር አይደለሽ እንዴ? ከላጤ ጋር ምንድነው እንዲያ መሆን?" ሲለኝ ሳቄን ለቀቅኩት እሱ መሳቄ ይባስ አናደደው

"አባ አንደኛ ባለትዳር እንደሆንኩ ያውቃል። እርጉዝም እንደሆንኩ። በዛ ላይ አንተን ከመውደድ የሚተርፍ ልብ ኖሮኝ ነው ሌላ ሰው ታስብበታለች ብለህ የምትቀናው?"

አንድ ሁለት አንድ ሁለት መመላለስ ጀመረ። እኔም በፍቅር ማባበሌን ትቼ በቁጣ መመላለስ ጀመርኩ።

ይሄኔ የሆነ ሌላ የማላውቀው ሰው ሆነ። ሌላ ፈጡር !!! ድምፁ ሻከረ። ደምስሩ ተገታተረ። ከመቼው ዘሎ አጠገቤ እንደደረሰ ሳላውቅ አጥቤ ያሰቀመጥኩትን ቢላ አንስቶ አንገቴ ላይ አደረሰው። ሰውነቴ በደነ። እንባዬ እጁና ቢላው ላይ ተንጠባጠበ። አሰፈሪ ህልም አይቶ እንደባነነ ህፃን ሰውነቴ ተርበተበተ። በዛች ደቂቃ ሁሉ ነገር ፀጥ አለብኝ:: 'አባ' ብዬ የምጠራው ባሌ ውስጥ ሌላ የማላውቀው ሰው አለ:: .....

በርትታችሁ እዚህ ድረስ ከዘለቃችሁ .........አልጨረስንም!!........

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Meri feleke
ሁለቱን ባሎቼን ላስማማ እያሸማገልኳቸው ነው!!
(ክፍል አራት)

በሚንቀጠቀጡ እጆቼ ደመነፍሴን ቢላ አንገቴ ላይ ያደረገ እጁን ለቀም አድርጌ ያዝኩት። ያዝኩት እንጂ እንዲያሸሽልኝ ልገፋው ወይ ራሴን ላሸሽ አቅሙ አልነበረኝም። የአቅሜ ጥግ ሳጌ ድምፁ እንዳይሰማ አፍኜ እንባዬን ማዝነብ ብቻ ነበር። እጁ አንገቴ ላይ ቢላዋ መደገኑን እጆቼ ሲይዙት ገና ያወቀ ይመስል ደነገጠ። በጣም ቀስ ብሎ እጁን አወረደው ........ ቢላውን ወረወረው ........ በጣም ቀስ ብሎ መሬቱ ላይ ተቀመጠ። አንገቱን ወደመሬቱ ደፍቶ እንባው መሬቱ ላይ ተንጠባጠበ። ይሄኔ 'ዋጥ አድርጋት' ተብሎ ታፍኖ እንደተገረፈ ህፃን "ህእእ ህእእእ ......" ብዬ ድምፄን አውጥቼ ማልቀስ ጀመርኩ።

ይሄኛው ሌላ ሰውዬ ነው። የእኔ ባል እንኳን ቢላዋ አንስቶ አንገቴ ላይ ሊያደርግ እጅሽን ይቆርጥሻል ብሎ ሽንኩርት የሚከትፍልኝ ...... ትልልቅ አይኖቹ እያለቀሱ ሲያስቸግሩት

"እማ ቆይ ወጥ ያለሽንኩርት ቢሰራ ምን ይሆናል?" የሚለኝ

"እሺ አንተ ነጭ ሽንኩርቱን ላጥልኝ ሽንኩርቱን እኔ ልጠዋለሁ" ስለው ሊልጥ ይታገልና

"እማ ቆይ ወጥ ውስጥ ነጭሽንኩርት ባይገባ ምን ይሆናል?" የሚለኝ።

"እህ? እና ያለሽንኩርት ያለነጭሽንኩርት ዘይት ላይ በርበሬ አድርገን እናቁላላ? "

"አንቺ ከምትቃጠዪብኝ አይሻልም?" እያለ የሚያባብለኝ። ሁሉ ነገር ከእሱ ሲወዳደር የሚያንስብኝ የኔ ባል ይሄ ነው።

የኔ ባል በቀደም በእግር እየሄድን ከእርግዝናው ጋር ተያይዞ በመጣ ደም ማነስ አዙሮኝ ስወድቅ እንደህጻን በእጆቹ አቅፎ ሀኪም ቤት ያደረሰኝ።

"አባ መራመድ እችላለሁ እኮ!" ስለው

"እኔ ምን እሰራለሁ?" የሚለኝ ዶክተሩን

"ደም ማነስ እንዴት አዙሮ ይጥላታል? ደግመህ መርምርልኝ ካለበለዚያ የሆነ ነገር ብትሆንብኝ እጣላሃለሁ!" ብሎ የሚቀውጠው

"ፈሳሽ ነገር በብዛት መውሰድ አለባት!" ብሎ ሲለው። ያለ የሌለ የጁስ መዓት እያስጠጣኝ በሽንት ብዙት የረጋ እንቅልፍ የማያስተኛኝ

ለእኔ ከሆነ ምንም የሚያደርግ የትም የሚሄድልኝ።

የኔ ባል ገና ለከተማው አዲስ ሆነን እንደመጣን አንዱ ቸርች ይዞኝ ሄዶ "ባለቤቴ ናት የሚያምር ድምፅ አላት እኔም እሷም ጌታን ማገልገል እንፈልጋለን ብሎ ኮስተር ብሎ ሲያወራ (ማስፈራቱ ግርማሞገሱ ደግሞ ) ከሳምንታት በኋላ አብሬው ማስመለክ የጀመርኩት ......

ከእግዜር ጋር ያለኝን ፀብ በሚገባኝ ጣፋጭ ቃል አይኔን ከሰዎች ላይ እና ካልተደረገልኝ ነገር ላይ አንስቼ ትልቁ አምላክ ላይ እንዳደርግ ያስተማረኝ መምህሬ .......

እንኳን እኔ ወንድሜ እጁን ይዞ ፒያኖ ያስተማረው። ወንድሜ ምን መሆን ትፈልጋለህ ቢባል "እሱን" የሚልለት የሚያስቀና ስብእና ያለው (ያሸነፈኝ ምን ሆነና?)

የኔ ባል
ጎረቤት ዶሮ ወጥ ተሰርቶ አይቼ ከስራ ሲመጣ እያለቀስኩ "ወጥ ሰርተው እንብላ እንኳን ሳይሉኝ ወደቤት አስገቡት!" ብዬ ስነግረው በአንድ እርምጃ የሰው ቤት ገብቶ

"እንዴት ሚስቴ እርጉዝ መሆኗን እያወቃችሁ ወጣችሁን ከለከላችኋት?" ብሎ የሚጣላልኝ። በሰው ዶሮ ወጥ 'እሷ የምትወደው እግር ነው' ብሎ መርጦ ይዞልኝ የሚመጣ ...

የኔ ባል "መንገድ ላይ ጮክ ብሎ መዘመር አማረኝ" ስለው እንዘምራለና ታዲያ ብሎ በሰው ሀገር መንገድ ላይ ቀውጢ አምልኮ ፈጥረን ሰው ከመንገዱ የምናሰናክል .....

"አባ ደከመኝ ትንሽ እንረፍ!" ስለው እሽኮኮ ካላደረግኩሽ ብሎ የሚያስቸግር ...

መንገድ እየሄድን በሃሳብ ተውጬ የሆነኛው መንገድ ላይ የተንጠለጠለ ሙዝ ላይ ሳፈጥ የሰው ማሳ ገብቶ ያልበሰለ ሙዝ ሰብሮ ከጠባቂው ጋር ግብ ግብ የሚገጥምልኝ ....

የኔ ባል ሁለት ልጆች አንድ ሴትና አንድ ወንድ ወልደን ስማቸውን አውጥተን ስናረጅ ምን እንደምንሰራ አቅደን። ፀጉራችን ነጭ ሆኖ ጥርሳችን አልቆ ምን እየተባባልን እንደምንፎጋገር አውርተን የጨረስን ....

የኔ ባል "ባንተ ድምፅ ሲሆንኮ ሲጣፍጠኝ" ስለው ቁጭ ብሎ መፅሃፍቶች የሚያነብልኝ።

ሰው ውጪ ምሳ ልጋብዝህ ሲለው ሚስቴ ብቻዋን ናት ብሎ የሚመጣልኝ ...

የእኔ ባል ብዙ ነው ...... በእያንዳንዱ በሚያደርጋቸው ጥቃቅን ነገር ሁላ ሳይቀር ከምንም እንዳላወዳድረው ሆኖ ልቤን የሞላ ነው
.....
ይሄኛው የኔ ባል አይደለም:: እንዴት ሁለት ማንነት አንድ ስጋ ውስጥ ይቀመጣል???
.....
.....

ለሰዓት ያህል ከተቀመጥንበት እሱ ቀድሞ ተነሳ

"ሄጄ አምሳሉን (ስራ በመስራት የምታግዘን ልጅ ናት) ልጥራትና እሷ ወጡን ትስራው በቃ ወይም ይቅር በቃ ስጋ ገዝተን ጠብሰን እንብላ .....አይሻልም ? ..... አንቺ ተነሺ በቃ አረፍ በይ እ?" ሊወጣ መንገድ ከጀመረ በኋላ

"የትም አትሄጂብኝምኣ?" አለኝ እግሬ ስር መጥቶ ጉልበቴን እያሻሸ

"ልሂድ ብል የት እሄዳለሁ?" አልኩት ሳላስበው። በዛ ቁመቱ ዝርፍጥ ብሎ ስሬ ቁጭ አለ። በእርግዝናው ሳቢያ ማበጥ የጀመሩ እግሮቼን ከጫማው ላይ አንስቶ ሁሌን እንደሚያደርገው እያሸልኝ

"እማ እባክሽ ማሪኝ!" አለኝ እንባው ጠብ ሲል እግሬ ላይ ያርፋል:: እሺም ..እንቢም ... ሙግትም ... ትግልም ... የለኝም ብቻ ፀጥ !!

"እማ እባክሽ አትተይኝ! ???ይቅር በይኝ!??" ከማልቀስ ውጪ መልስ አልሰጠውም:: ሁሉም ነገር ግልብጥብጥ ብሎብኛል የተፈጠረው ቅፅበት ህልም ቢሆን ..... እሱን ክፍል ብቻ መደምሰስ ብችል ከጭንቅላቴ ውስጥ ..... ለምን? እንዴት? ጭንቅላቴ ውስጥኮ ብዙ ጥያቄ ይንከላወሳል።

እንዴት አንድ የዚህኛውን እሱን ምልክት ይሄን ያህል ጊዜ አላየሁበትም? ግን አፌን ለቆ የሚወጣ ምንም ቃል የለም። ልጅ ልኮ የምትሰራልንን ሴት አስጠርቷት አመት በአል አስመስላው ሄደች እንደነገሩ እራታችንን ቀማመሰን በጊዜ ተኛን። እኔና እሱ ኩባያ የምንለውን አስተኛነት (ለምን እንደዛ እንዳልነው አላስታውስም) ጀርባዬን ሰጥቼው በጎኔ በእጆቹ በሃል ታቅፌ ጀርባዬና ደረቱ ተጣብቀው .... እጥፍ ያለ ጉልበቱ መሃል እግሮቼን አጥፌ ተኛኝ። ማልቀሴን ማቆም አቃተኝ:: ሳጌ እንዳያመልጠኝ እታገላለሁ።

እያለቀሰ ነው። ሳጉን እንዳልሰማው ውጦታል። እንባዬ ክንዱን ሲያርሰው ይሞቀዋል:: እንባው አንገቴ ስር ሲያርሰኝ ይሞቀኛል። አልቅሼ እንባዬ ሲያልቅ ነው መሰለኝ ...

"ምን ያህል እንደማፈቅርህ ህቅ ህቅ (ሳጌ ያቋርጠኛል) አልገባህም ማለት ነው?" አልኩት ዞሬ

"እማ እባክሽ ማሪኝ?" አንገቴን ፀጉሬን እጄን በእንባ የራሱ ጉንጮቼን አይኖቼን ይስማቸዋል። ለደቂቃዎች ምላሳችን ላይ እንባችን ጨው ጨው እያለን ስንሳሳም ቆይተን ደረቱ ላይ እንቅልፍ ይዞኝ ሄደ።

በነገታው ለሱ ሳልነግረው ከቤት ወጥቼ እናቴጋ እቤት ስልክ ደወልኩ። የተፈጠረው ነገር ለሱ ያለኝን ፍቅር አልነበረም የቀነሰው። እኔኑ ራሴኑ ነበር በሆነ መጠን የሸረፈኝ። ምክንያቱም ከትናንት በፊት የነበረችው ሜሪ ለማንም ብላ ማንንም የምትፈራ ሴት አልነበረችም።

በስልኩ ውስጥ የእናቴን ድምፅ ስሰማ:: ማውራት አቃተኝ!!! እንባ እና ህቅታ ብቻ ....

......... አልጨረስንም እንግዲህ.......

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Meri feleke
ሁለቱን ባሎቼን ላስማማ እያሸማገልኳቸው ነው!!
(ክፍል አምስት)

"ማሚ" ከማለቴ እናቴ በስልኩ እልልታዋን አቀለጠችው። ፀሎት አይሉት ወሬ
"ጌታ ሆይ ምን ይሳንሃል? ጸሎቴን ሰማኸኝ እልልልልል ...... ልጄ? ደህና ነሽ?"

"ደህና ነኝ!" እያልኳት እሪታዬን እለቀዋለሁ

"ምን ሆነሽ ነው? የት ነው ያለሽው ?አሁኑኑ ልምጣ ?"

"ምንም አልሆንኩም! ናፍቃችሁኝ ነው።"

ስለእሱ ላወራት አልችልም። እሱን ከማሳማው ያን ቢላ አንገቴ ላይ ድጋሚ ባገኘው ይቀለኛል። እሱን እንድትጠላብኝ አልፈልግማ!! ልጇን ያደረጋትን እንጂ ልጇ ለሱ ያላት ገደብ የለሽ ፍቅር አይገባትማ! ግን የእናት ሆዷ ነግሯታል።

"እሺ ይሁን እንዴት ሆንሽ? ትምህርትሽን እየተማርሽ ነው? "

"አይደለም ማም እርጉዝ ነኝ። በዚህ ዓመት አልማርም። ልጄን ከወለድኩ በኋላ እማራለሁ!"

ዝም አለች። ወደፊቴን አስባው ልቧ ዝሎባት መሰለኝ ዝም አለች። ከወለዱ ኋላ ያለውን አቀበት አይታው ነው መሰለኝ ዝም አለችልኝ። የምትለው የማታጣው እናቴ ዝም

"ማም ?"

"ወዬ? እስኪ ይሁን ብቻ አንቺ ደህና ሁኚ!..... እሱ አሁን አጠገብሽ አለ? (አባባሏ ይሄ እንትን .... ብላ የሆነ ስድብ የመቀጠል ነገር ነው። )ምንም ባልላትም ጠምዳዋለች።

"የለም ስራ ነው!"

"ይሁን እንደምትዪው ..... በወጉ ሽማግሌ ላክ በዪው ..... ሳትወልጂ በስነስርዓቱ ተደግሶ ቃልኪዳን ትፈፅማላችሁ። በምንም ሁኔታ ቢሆን ልጄን እንደማልተውሽ ማወቅ አለበት።"

"ማሚ እሱኮ ከእናንተ እንድጣላ አይፈልግም ለምን እንደጠላት ታዪዋለሽ? ምርጫዬን የመረጥኩት እኔ ነኝ እሱ እንደውም ሁሌ ደውዪላቸው ነው የሚለው።" (ደግሞ የምሬን ነው። በከፋኝ ቁጥር ለምን አትደውይላትም ነበር የሚለው)

"እሱን እንኳን ተይው .... የውልሽ ልጄ ወንድ ልጅ ብቻሽን ሲያገኝሽ እና መሄጃ እንደሌለሽ ሲያውቅ ጥሩ አይደለም። ያኔ ከርሱ ውጪ ምርጫ የሌለሽ ንብረቱ ነሽ። ያን ክፍተት አትስጪው ...... አይደላደል ..... ተንከባክቦ በፍቅር ካላኖረሽ አማራጭ ያለሽ መሆንሽን ሲያውቅ እንደሚገባሽ ያከብርሻል!!"

የኔ ባል ይለያል ብዬ እንዴትም ላስረዳት አልችልም። እናቴ አንድም በህይወቷ ሴትነትን ከፍ አድርጋ የምትኖር ሁለትም ሴቶች ጉዳይ የምትሰራ ያውም በከፍተኛ ሃላፊነት ደረጃ ላይ ያለች ሴት ናት።

"What happen to ስታስተምሩ ያሳደጋችሁኝ 'ሚስት ለባሏ ትገዛ?'"

"ሚስት ለባሏ ትገዛ ሲል ለባልም ሚስቱን ነፍስን እስከመስጠት ባለ የክርስቶስ ፍቅር የመውደድን ሀላፊነት እንደሰጠው አትርሺ!" አለችኝ ኮምጠጥ ብላ።

"ማሚዬ እንደዛ ይወደኛል።" አልኳት ለእሷ ... ለራሴ መልሼ ግን 'እንደዛ ይወደኛል?' ብዬ አሰብኩ። ያልጠየቀችኝ ነገር የለም።

"ለመሆኑ ቤቱን በትክክል ያስተዳድራል?" ምን ማለቷ እንደሆነ አውቃለሁ። ገንዘብ ይሰጥሻል ወይ ነው?

"ማሚ ደሞዙን አምጥቶ ለእኔ ነው የሚሰጠኝ (የምሬን ነው። ሙሉውን ደሞዝ አምጥቶ ለእኔ ነበር የሚሰጠኝ። ልክ አባቴ ለእናቴ እንደሚያደርገው። በወር የሚያስፈልገንን ፅፌ አዘጋጃለሁ። ለሱ የኪስ ብር እሰጠዋለሁ። የሚደረገውን ሁሉ እኔ ነኝ የማደርገው። )

"እሺ ጉዳዩ ላይ እንዴት ነው?"

"ማሚ ኸረ በጌታ ?" ለቅሶዬን አስትታ አስፈገገችኝ

"እህህ የምሬን ነው። ከዚህ ሰው ጋርኮ ነው የምታረጂው። ትዳር እኮ ቆይ ለጉዳዩ ለጉዳዩ ጊዜ ወጣ ብዬ ልምጣ አይባልበትም!"

መጨረሻ ላይ አባቴን ላወራው እንደምፈልግ ስነግራት። እሷ ሰበብ ብትነግረኝም አባቴ ሊያናግረኝ እንዳልፈለገ ገባኝ። ዝምተኛው አባቴ በዝምታው ሊቀጣኝ ፈልጓል። ሁሌም እንደዛ ነው። ጥፋት ሳጠፋ ተቆጥቶኝ አያውቅም። በዝምታ ነው የሚቀጣኝ። ጥፋቴን እስካርም ወይም ይቅርታ እስክጠይቅ ድረስ አያዋራኝም። ይሄኛውን ግን ለማረም ዓመታት ሊፈጅብኝ ይችላል። እሱ የሚስላትን ልጁን ሆኜ ላሳየው ብዙ ይፈጃል እና በዝምታው የሚቀጣኝ እስከዛ ከሆነ?......

የዛን ቀን ማታ ከስራ መጥቶ ወክ እያደረግን ለእናቴ እንደደወልኩ ልነግረው ፈራሁት። ምኑ እንዳስፈራኝ አላውቅም። ካፈቀርኩት ጀምሮ ከሱ ጋር ሳልማከር አድርጌ የማውቀው ነገር ባለመኖሩ ስለደበቅኩት? 'ግን እናቴጋ ለመደወል የግድ ከእርሱ ጋር መማከር አለብኝ?' እላለሁ ለራሴ ነገሩን ለማቅለል።

"አባ ዛሬ ማሚጋ ደወልኩኮ!" መገረምም መደንገጥም ፊቱ ላይ እያየሁ ምንም እንዳልመሰለው ለመሆን ጣረ ሁለታችንም እየተቀየርን እንደሆነ አሰብኩና ፈራሁ። መደባበቅ እየጀመርን ነው። ፈራሁ!!

"ቆንጆ አደረግሽ! ምን ተሰማሽ? ደስ አለሽ? ማሚ ምን አለች? ደህና ናቸው?" ስሜቱን ለመደበቅ በጥያቄ ያጣድፈኛል። ያለችኝን ነገርኩት

"ደስ ይላል እማ!" አለኝ ማንን ሽማግሌ እንደሚልክ ምናምን ሰርጋችን ላይ ማን እንደሚጠራ ምናምን ማውራት ጀመርን!!

ስለሰርጋችን ማውራቴ ትቼው ልሄድ አለማሰቤን ስለነገረው ይመስለኛል ቀለል አለው። እኔ ግን ከፋኝ !! እኔ እና እሱ መሰለኝ እየተባባልን ስሜታችንን አንገማመትም:: ይነግረኛል አውቃለሁ። እነግረዋለሁ ያውቃል።

"ቤተሰቦችህጋ ትደውላለህ?" አልኩት።

"አላውቅም!" አለኝ ከቤተሰቡ ጋር ለረዥም ዓመታት ተገናኝቶም ደውሎም አያውቅም።

ማውራት የማይፈልገው አጀንዳ ነው። እሱ ጴንጤ ከሆነ በኋላ ምንም አይነት መጠያየቅ ተጠያይቀው አያውቁም። ትዳራችን ላይ የሚያመጣው መዘዝ አለ ብዬ አስቤውም ስለማላውቅ ትኩረት ሰጥቼው የማውቀው ነገር አልነበረም።

ከዚህ ክስተት በኋላ ከዋነኛው ባሌጋ የምናነባቸው መፅሃፍት ውስጥ እንዳሉት ፍቅረኛሞች የሚያስቀና ትዳራችንን ቀጠልን። መፅሃፍቶቹ ውስጥ ያሉ ባለትዳሮችም ሆነ በገሃዱ አለም ያሉ ባለትዳሮች ሳይነግሩሽ የሚዘሏቸው ጥቃቅን የሚመስሉ ከባባድ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ምስር ወጥ ለመስራት ከወጡ ሙሉ ሂደት ምስሩን መልቀም እንደሚያደክም አይነግሩሽም ....... እርጉዝ ሆነሽ እንጣዬ ስታደርጊ ልጄን እየነካው ይሆን? የሚለው ሀሳብ ከስሜት እንደሚያወጣ አይነግሩሽም። (ምነው እማ? ሲለኝ በመሃል ልጁን ትነካው እንደሆነ ሃሳብ መጥቶልኝ ስለው አቋርጠን ለሰዓታት በሳቅ መዛላችንስ?)

የሰርጋችን ቀን ተወሰነ። ሽማግሌ ተላከ። ሆዴ እየገፋ ሲመጣ ደም ማነሴ እየጨመረ መጣ። ስለሚያዞረኝ ድንገት እንዳልወድቅ እርሱ እንደህፃን እጄን ይዞኝ ካልሆነ በቀር ከቤት አልወጣም። የሆነ ቀን እንጀራ የሚጋግሩልኝ ሴትዮ 'ምጣዱ ተሰበረ' ሲሉኝ። አብሪያቸው ምጣድ ላጋዛ ገበያ ሄድኩ።(ይሄንንም አይነግሩሽም በነገርሽ ላይ)

ገበያው መሃል ጎንበስ ብዬ ቀና ስል አዙሮኝ ወደቅኩ። እኔ እቤት ሳልደርስ ወሬው ባሌጋ ደርሷል። ሲመጣ እጅ እግሩ እየተንቀጠቀጠ ደባብሶ ደህና መሆኔን ካረጋገጠ በኋላ ..... ልቡ በአፉ ልትወጣ እስኪደርስ ደንግጧል። ከዛ ያልገባኝ የድንጋጤው ብዛት ወደ ቁጣ ተቀየረ።

"አትውጪ አላልኩሽም? አይቀርም? ለምን ሰው የሚልሽን አትሰሚም? የሆነ ነገር ሆነሽ ቢሆንስ? " (ያ ደባሉ ባሌ መጣ) ረስቼው ነበር እና አላስተዋልኩትም።

"በቃ ምንም አልሆንኩምኮ ! በጣም አካበድክ" ከተኛሁበት ብድግ አልኩ እሱ በሚናገርበት ድምፅ ጮክ ብዬ (ምላሴ ቢያርፍስ ?)

አንዴ በጥፊ ሲያልሰኝ እኔ ከሲኖትራክ ልውደቅ ሲኖትራኩ በኔ ላይ ይሂድ አላውቀውም! ብቻ ስሜቱ እንደዛ ነው። የሰው ጥፊማ እንዲህ ጭው አይልም።
አመንኩ። ይሄ የአንድ ቀን ስህተት አይደለም። ባሌ ሁለት ነው። እሺ ምን የሚሉት ነው? ፍቅር ነው ጥላቻ? በምነኛው ዘርፍ ልቀበለው? ነፍሱ እስክትወጣ ስለሚያፈቅረኝ የሆነ ነገር ሆነሽብኝ ቢሆን ኖሮስ ብሎ ተናዶ እርጉዝ ሚስቱን እሱ በነፃ በአንድ ሲኖትራካዊ ጥፊ የሆነ ቦታ ደርሶ መልስ ትኬት የሚያስቆርጠኝን ባሌን በምን ዘርፍ ልመዝግበው? ለሁለት ባል እያወቅኩት ልሞሸር?


........... አልጨረስንም ባይዘዌያችሁ ላይ......

@wegoch
@wegoch
@paappii
2024/09/23 12:12:46
Back to Top
HTML Embed Code: