Telegram Web Link
ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት ….. እኔ የቀጠልኩት
(ክፍል አምስት ………. ሜሪ ፈለቀ)

«እኔ ደስ የሚለኝ ጓደኛሞች ብንሆን ነው።» አልኩት እቤቱ ይዞኝ የሄደ ቀን

«እረፊ! እኔ አንዴ ልብስሽን አውልቄ ጭንቅላቴ ውስጥ ስዬሻለሁ። ጓደኛሞች እንሁን ብልሽ ውሸቴን ነው። ገና ሳይሽ የቀሚስሽን ሶስት ትንንሽዬ ቁልፎች ፣ ቀጥሎ ዚፑን …….. ወደታች ባወልቀው ወይ ወደላይ የቱ ይፈጥናል? አስቤ ጨርሻለሁ!» የገረመኝ ክፍት አፍነቱ አይደለም። እሱን እየለመድኩት ማፈር ትቻለሁ፣ በዛ ላይ ሌላ ሰው ሲያወራው የሚያሳፍረኝን ነገር እሱ ሲያወራው አለው የሆነ ልከኛ ወሬ የሚያስመስለው ድምፀት። በትክክል ቀሚሴ ከጀርባው የዚፑ መጨረሻ ማጅራቴ ጋር ትንንሽዬ ሶስት ቁልፎች መኖራቸው ነው። ከላይ ደርቤ የነበረውን ኮት ካወለቅኩት 5 ደቂቃ አይልፍም ነበር። ገርሞኝ አፍጥጬ ሳየው። <ነግሬሻለሁኮ> አይነት ፊቱን እና ትከሻውን ሰበቀ።

ቤቱ <እንደማንኛውም ፊልሞች ላይ እንደምናያቸው የሀብታም ፎቆች> ከሚባሉት በይዘትም በስፋትም በጥራትም በሶስት ክፍል ቤት እናትና አባቴን ጨምሮ ለስምንት ላደግኩት እኔ (በዝህችም ጥበቷ ክረምት ላይ የአክስት ልጅ ፣የአጎት ልጅ ፣ የክርስትና ልጅ ፣ የአበልጅ ………… የልጅ ብዛት ቤቷን እንደጉንዳን ይወራታል።) አፌን ከፍቼ የምፈዝበት አይነት ነው። አልተገረምኩም። እንደዛ ዓይነት ቤት እንዳለው ነግሮኛል። የገረመኝ እሱም ያልነገረኝ ሁለት የቤቱ ክፍሎች ናቸው። አንደኛው የአንድ ትልቅ ትምህርት ቤት ላይብረሪ የሚያክለው ሰፊው የቤቱ ውስጥ ላይብረሪ ነው። መሃከሉ ላይ ሰፋ ያለ ኮምፒውተሮችን የተሸከመ ጠረጴዛ በአራት ምቹ ወንበሮች ተከቦ ተንጣሏል። አትርገጡኝ የሚለውን የመሬቱን ምንጣፍ ጫማውን አውልቆ ሲገባ አውልቄ ተከተልኩት። የሆነ የተቀደሰ ቦታ የሚገባ ነው የሚመስለው። ከምን ጀምሬ የቱን እንደምነካ ግራ ገባኝ። በቋንቋ ፣ በይዘት፣ በፀሃፊው ስም ……… በስርዓት ተደራጅተው ነው የተቀመጡት። እስካሁን ያላየሁበትን መጀነን ፊቱ ላይ አገኘሁት።

«ምን ያህሉን አንብበሃቸዋል?»

«ቢያንስ 35%! አማርኛዎቹ በቁጥር ነው የቀሩኝ።» አማርኛዎቹጋ ሄጄ ያነበብኳቸውን ለመቁጠር ሞከርኩ። ያው እንደማንኛውም ማንበብ እንደሚችል ኢትዮጵያዊ <ፍቅር እስከመቃብር> እና <ዴርቶጋዳ> ን ሁለት ብዬ ከሀምሳ የማይበልጡ መፅሃፍትን በዓይኔ ቆጠርኩ። እንግሊዘኛውን ያው ተውኩት።

ሌላኛው ክፍል የወንበሩ ቁጥር ከማነሱ ውጪ በሲኒማ ቤት ቅርፅ የተሰራው ፊልም ማሳያ ክፍል ነው።

«ዶክመንተሪ ፊልሞች እወዳለሁ። ማየት ከፈለግሽ መርጬ ልጋብዝሽ?»

«በኢቲቪ ከታዩት <የጀግናው ሰራዊታችን ፍዳ ዶክመንተሪ፣ የታላቁ ኢህአዲግ ወደር የለሽ ትዕግስት፣ ህገመንግስቱን ለመናድ የታጠቁት ሀይሎች ሴራ …..> ምናምን ከሚሉት ውጪ ዶክመንተሪ ማየቴንም እንጃ። ወይም አይቼ ሊሆን ይችላል። ዶክመንተሪ ይሁን ዶክመንቴሽን ወይም ጥናታዊ ፅሁፍ ልዩነታቸው ምን እንደሆነ ስለማላውቅ እኔእንጃ!» ፈገግ ብቻ ነው ያለው። ብዙ ሰዎች እነሱ በብዙ የሚያውቁትን ነገር የማያውቅ ሰው አለማወቁን ሲነግራቸው የሚስቁትን <ከእኔ በላይ ላሳር> ዓይነት ሳቅ አልሳቀም። በአንደኛው ጥግ ለዓይን እሩቅ ሆነው ከኔ ቁመት በጣም በላይ ከተቆለሉት የሸክላ ሲዲዎች ውስጥ አንዱን እያነሳ

«ከቆዩት ውስጥ ልጋብዝሽ! » ብሎ «night and fog» የሚለውን መረጠ። ማጫወቻው ላይ አድርጎ ሲዲውን የምትጫነዋን ቀጭን አናቷ ድርብ ብረት ሲዲው ላይ ለቆት መብራቱን አጠፋፍቶ እጄን ይዞኝ ከፊት ለፊት ካሉት ወንበሮች መደዳ አስቀመጠኝ። በሹክሹክታ

«የሚጠጣ ምን ትፈልጊያለሽ? መብላት የምትፈልጊውስ ነገር?»

«ፈንድሻ ቢኖር፣ ከዛ ደግሞ ኮካ!» ያልኩት ለጨዋታ ነበር። በስልኩ መልእክት ላከ። አስር ደቂቃ ሳይሆን ቅድም ጓዳ ያየኋት ሴት ያዘዝኩትን ይዛ መጣች።


**
የዛን እለት ………. መጀመሪያ ያየሁት እለት ……… ጤንነት እንደጎደለው ሰው ያየኝ ቀን ላግባሽ ያለኝ እለት…….. እንደእኔ ሀሳብ ጥዬው በሄድኩ፣ እንደእኔ እምነት <ልክ ካልሆነ ሰው> ጋር ተጨማሪ ደቂቃ ባላባከንኩ ፣ እንደእኔ ልምድ ከአፉ የሚወጡት ቃላት አርባ ክንድ ከእርሱ ባራቁኝ ፣ እንደ እኔ አስተዳደግ ይሄ ሰው የብዙ የህይወት መርሆቼ ፉርሸት ነበር። ተጎለትኩ አላልኳችሁም? ለሰዓታት ስለተለያዩ የማህበረሰባችን ምሰሶ አስተሳሰቦች እና እምነቶች ስናነሳ እና ስንጥል ለሰዓታት ተጎለትኩ።

«አልተሳሳትኩም አየሽ! መልክ ብቻ አይደለሽም ታስቢያለሽ!» አለኝ በመሃል

«ደሞ ይሄ ምን ማለት ነው?»

«ቆንጆ ሴት ሳይ ከራሴ ጋር አስይዛለሁ። እወራረዳለሁ። ይህችኛዋ መልክ ብቻ ናት፣ ይህችኛዋ ግድ የለህም ከመልኳ ጀርባ አሪፍ ጭንቅላት አለ፣ ውይይይ ይቺኛዋ ደግሞ የራሷ ሀሳብ የላትም የሰዎችን ጭንቅላት ተውሳ ነው የምታስበው ……… ዓይነት ውርርድ! አንዳንዱ እምነትሽን ብትጠይቂ የሚናድብሽ ስለሚመስልሽ በፍርሃት ያለምክንያታዊነት ሙጭጭ ከማለትሽ ውጪ ታሰላስያለሽ!»

«የሴት ቁንጅና ላንተ በምንድነው የሚለካው?»

«ቁንጅናውን ለምንድነው የምፈልገው? የሚለው ነዋ የሚወስነው? የውስጥ ውበት ምናምን ብዬ እንድዋሽሽ አትጠብቂ! የፊዚካል ውበት አድናቂ ነኝ። አልጋ ላይ ይዣት ለመውደቅ ከምጣደፍባት ሴት ሀሳቧ መንፈሷ አይነት ዝባዝንኬ ትዝ አይለኝም። ችግሩ ከተኛኋት በኋላ የማወራው ስለሚጠፋኝ ቶሎ እንድትለየኝ እፈልጋለሁ። ምናልባት ግን በሌላ ጊዜም ላገኛት እፈልግ ይሆናል። ከወዳጄ ጋር ተማክረን (ወዳጄ ያለው ታች ቤቱን መሆኑን ለማሳየት በእጁ ወደታች ጠቆመኝ) እሷ ትሻለናለች ተባብለን ላገኛት እችላለሁ። የምታሰላስል፣ የምትጠይቅ ሴት ግን ደስ ትለኛለች። ከእራት እስከአልጋ ሳትሰለቸኝ ጊዜ ሰጣታለሁ። አብሮ እስከመኖርም አይከፋኝም። »

የሆነ ……… እየጠሉ የሚወዱት፣ እየፈሩ የሚደፍሩት፣ እንደሚፋጅ እያወቁ የሚሞክሩት ፣ መሸሽ እየፈለጉ የሚቀርቡት ፣ እየረገሙ የሚመርቁት ፣ በአንዴ ልክም ስህተትም የሚሆን ፣ ሲኦልም ገነትም ዓይነት ስሜት ያለው፣ ህመምም እርካታም ዓይነት ስሜት ያለው ……… በቃ በየትኛውም ጎራ የማያቅፉት አይነት ሰው ነበር። የዛን ቀን እቤቴ ከሸኘኝ በኋላ

«ደውዪልኝ!» ብሎ ስልኩን ሰጥቶኝ ሄደ። እኔው ራሴ ያላወቅኩት እብደት ውስጤ መኖሩን ያወቅኩት <ላግባሽ> ያለኝን ደግሜ ከነአመክንዮዎቹ ሳስብ ራሴን ሳገኘው ነው። የሆነ ቀን <ለምንድነው የምደውልለት?> የሚለውን ሳላስብበት ደወልኩለት። ስልኩን እንዳነሳ እኔ መሆኔን ሲያውቅ

« ከሰው ጋር ነኝ በኃላ ልደውልልሽ?» አለኝ። በስልኩ ውስጥ በሹክሹክታ የምታወራ ሴት ድምፅ ሰማሁ።

«እሺ ይቅርታ!» ብዬው ስልኩን ዘጋሁት። ከዛ በራሴ ተናደድኩ። መደወል አልነበረብኝም!! የሆነ ክብሬን ዝቅ ያደረግኩ አይነት ስሜት ተሰማኝ። <ምን አስቤ ነው የደወልኩለት?> ራሴን በወቀሳ ስቀጣ ቆይቼ ከሰዓታት በኋላ ደወለ።

«ከሰው ጋር ነበርኩ።» አለኝ ስልኩን እንዳነሳው

«አወቅኩኝ።» አልኩኝ
«ደብሮሽ ባልሆነ?» ብሎ ድክም ብሎ ሳቀ። ጭራሽ ደበረኝ። ዝም አልኩ። «ኦህህህ አግቢኝ ያልኩሽን አስበሽበታል ማለት ነው። (በእርግጠኛነት ነው የሚያወራው) አሰብሽው እንጂኮ ታዲያ ለእኔ አልነገርሽኝም። ከማንም ጋር ብሆን በእኔ የመናደድ መብት የለሽም» ወሬ ውስጥ ሳቅ ይሰማል? እንደሱ ነው የሰማሁት። «ነገ እራት ልጋብዝሽ?» አለ

«ነገ? » ብዬ ላለመሄድ የምሰጠውን ሰበብ ሳስብ ሳቁ አቋረጠኝ

«እሺ ቅድም ምን ልትዪኝ ነበር የደወልሽው?»

«እኔ እንጃ? ላዋራህ? እኔ እንጃ ለምን እንደደወልኩ!» አሁንም ሳቅ ባጀበው የወሬ ለዛው።

«ነገ አስራ ሁለት ሰዓት ላይ መጥቼ ፒክ አደርግሻለሁ። እሺ ካልሽ ማለት ነው! ከሴት ጋር ነበርኩ። አብሬያት ሆኜ ሌላ ሴት ላላወራ ቃል ገብቼላታለሁ። ቃሌን ደግሞ የምጠብቅ ሰው ነኝ።»

«አሁን እኔን ስታወራ ቃልህን እያፈረስክ አይደለም?»

«አይደለም! ፊዚካሊ አብረን ስንሆን ነው ውላችን …… ይቅርብሽ ዲቴሉ አትወጂውም። አይጠቅምሽምም! ካንቺምጋ ብሆን ለሚኖሩን ህጎች ቃሌን እጠብቃለሁ። የማልጠብቀውን ቃል አልገባልሽም። እራት እንብላ?»

«እሺ» አልኩት። ምንም አስቤ አይደለም። እራት ከእርሱ ጋር ለመብላት ካለመፈለጌ መፈለጌ ስላየለ ብቻ እሺ አልኩት።

ድጋሚ <ላግባሽ> የሚለውን ነገር ለተወሰኑ ቀናት አላነሳቸውም። በትዳር ዙሪያ ያሉንን ሀሳቦች ግን ማውራት አላቆምንም። ለምሳሌ የሆነኛው ቀን

«ቆይ ሁለት ሰዎች ተጋብተው ወይም ሳይጋቡ ለመኖር ዋነኛው መስፈርት ምንድነው?»

«ፍቅር ዋነኛው ነው። ነገር ግን ፍቅርን የሚያጠነክሩት ……… መከባበር፣ አንዱ የአንዱን ስሜትና ሃሳብ ለመረዳት የሚሄድበት ርቀት፣ መደጋገፍ ……. ብዙ ነገሮች አሉ።»

ፍቅር የሚባል ነገር ስላለመኖሩ ረዥም ማብራሪያ ከሰጠኝ በኋላ

«ይሁንልሽ ፍቅር የምትዪው ስሜት አለ እንበል እና መገለጫው ምንድነው? ሚስተር አፍቃሪ እንዳፈቀረሽ በምን ታውቂያለሽ? አበባ ይዞልሽ የሚመጣ? በ24 ሰዓት 26 ጊዜ የሚደውል? ስለፍቅሩ ስድስት ልብ ወለድ መፅሃፍ የሚወጣው ዲስኩር የሚዘበዝብ? የሚያቅፍሽ? የሚስምሽ? ራቁትሽን ስትሆኚ የማታፍሪው? በየሰርግ ውልደት ግብዣ ላይ ይዞሽ በኩራት የሚዞር? ምን አለ ከዚህ ሌላ? ከዚህ የተለየ የፍቅር ማሳያ ነው የምትዪው ካለ እ?»

ለደቂቃዎች የእውነት ከነዚህ በተጨማሪ አንድ ሰው ፍቅሩን የሚገልፅበት ነገር ያለ እንደሆነ አሰብኩ። ከአፌ የወጣው ግን ሌላ ጥያቄ ነበር።

«አንተ ግን በ42 ዓመት ዘመንህ ፍቅር ይዞህ ያውቃል? ወይም እሺ እንዴት ላስቀምጠው? የጓደኝነት ስሜት መጠቃቀም ሲደመር የወሲብ ስሜት መጠቃቀም ሲደመር ወይ ሳይደመር የቁስ መጠቃቀም ያልከውን የተቃራኒ ፆታ ትስስር ዓይነት ኖሮህ ያውቃል?»

ፊቱ ድንገት እንደመዳመን ዓይነት ሆነ ። «ማናት? መቼ? እንዴት ? ለምን የሚል ጥያቄ አስከትለሽ እንዳትጠይቂኝ። አዎ ኖሮኝ ያውቃል።» አለኝ በደፈናው። ለማውራት አፌን ሳሟሽ «እስከመቼውም የማልነግርሽ ድሮ አለኝ። አትልፊ። ማውራት አልፈልግም!»

የማይተነበይ አይነት ሰው ነው። ሲያወራ ካለመሰልቸቱ እና በእውቀት ላይ ከተመሰረቱት ምክንያታዊ ጨዋታዎቹ በተጨማሪ መኪና አቁሞ ዝናብ ላይ ቆሞ አፉን ከፍቶ ዝናብ እየተደበደበ የዝናብ ጠብታ የሚጠጣ ንቅል ነው። ልክ እንደልከኛ ነገር «ይህቺ ሁለተኛ ሚስቴ ነበረች።» ብሎ እራት እየበላን በአጠገባችን ከሌላ ወንድ ጋር እራት ለመብላት የምትገባን ሴት የሚያስተዋውቀኝ ልክ ያልሆነ ሰው ነው። <እገሌ የፃፈው ገፀባህሪ በፍፁም እንዲህ ሊያደርግ አይችልም። ደራሲው ገፀባህሪውን በደንብ አልተረዳውም።> ብሎ የሚሟገት ንክ ነው። ባጠቃላይ በእኔ ዓለም፣ በእኔ እምነት ፣ በእኔ ባህል፣ በእኔ ልምድ ፣ በእኔ አስተዳደግ አይደለም ባል ብለው ሊመርጡት ለአንድ ቀን እንግዳ አድርገው ሊመርጡት ጤንነቱ የሚያጠራጥር ዓይነት ሰውኮ ነው። እንደሚፋጅ እያወቅኩ ካልነካሁት ብዬ የነካሁት እሳት

«ቤቴን ላሳይሽ?» ሲለኝ እንቢ ለማለት ወይም ለመሽኮርመም ሀሳቡም አልመጣልኝም። ወደእርሱ ዓለም እየተሳብኩ እንደሆነ ያኔ ገባኝ። እሱ ሲያደርገው ወይም ሲያወራው እብደት ወይም ብልግና ሲመስለኝ የነበረው ነገር እኔ ውስጥም ያለ ግን ልኖረው ያልደፈርኩት ልክነት መሆኑ የገባኝ ዶክመንተሪ ፊልሙን አይተን ከጨረስን በኋላ መብራቱን ሲያበራው ሞቆት ይሁን እኔን መፈታተን ፈልጎ የለበሰውን ሸሚዝ አውልቆ ከላይ ፈርጣማ ሰውነቱን ሳየው ልነካው መመኘቴን መደበቅ አቅቶት ሳላዘው እጄ ሲዘረጋ ነው.........

………….. አልጨረስንም.........

@wegoch
@wegoch
@paappii
ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት ….. እኔ የቀጠልኩት
(ክፍል ስድስት ………. ሜሪ ፈለቀ)

የዛን ቀን …….. እንኳን ዶክመንተሪ ፊልሙን አይተን ስንጨርስ በሙቀቱ ወዝቶ ቅባት የተቀባ የመሰለውን ጠይም ፈርጣማ ደረቱን እጄ ሲንቀለቀል ሄዶ የነካው ቀን……… እጄን ደረቱ ላይ በእጁ ደግፎ እንዳላንቀሳቅሰው ይዞት

«እርግጠኛ ነሽ?»

«ቨርጅን አይደለሁምኮ።»

«አውቃለሁ!! በኋላ የፀፀትሽ ምክንያት መሆን አልፈልግም።» እያለኝ ትንፋሹ ከንፈሬጋ ደርሷል። አሁን ማን ይሙት ሀሳቤን መቀየር እንኳን ብፈልግ የቱን ሀሳቤን እንደምቀይር አስተካክዬ ማስታወስ እችል ነበር? እየሳመኝ እያቋረጠ ያወራል። አንዳንዱን ቃል እየሳመኝም እያወራም ነው ልበል? ወይም መስሎኝ ነው።

« ለምን እፀፀታለሁ?» አልኩኝ ከንፈሬን ነፃ ባደረገልኝ ቅፅበት። ደረቱ ላይ ይዞት የነበረውን እጄን አንስቶ እንደዋልዝ ዳንስ አሽከርክክሮ በጀርባዬ እያዞረኝ

«የሴት ልጅ ክብሯ እግሯ መሃል ነው ብለው ነግረዋችኋል።r (ቅድም የቆጠራቸውን ሶስት ቁልፎች እየፈታ አንገቴ ስር ነው የሚያወራው) አብዛኛዋ ሴት እግሯን ከፍታ ስትዘጋ ከክብሯ የሆነኛውን ያህል እንደገመሰች ነው የሚሰማት። (በቃላቱ በየመሃል አንገቴን ይስመኛል።) ፈልጋ እንኳን አድርጋው ዝቅ ያለች ስሜት ይሰማታል። ራሷን ትጠላለች።» ዚፑን ከፍቶ ቀሚሴን ወደታች እያወለቀው። ከትንፋሼ እና ከምውጠው ምራቅ ጋር እየታገልኩ

«ወሬህን ማቆም አትችልም?»

«አፋችን ስራ ካልያዘ (እንደቅድሙ ደግሞ ወደፊቱ አዙሮኝ ክንፈሬን እየሳመኝ) ብናወራበትሳ! (ሳቅ ባለበት ለዛው ነው የሚያወራው።)»

«ቢያንስ ወሬው (ከንፈሩ አቋረጠኝ) ከሰዓቱጋ የሚሄድ (እጁ አጓጉል ቦታ ደርሶ አቋረጠኝ) »

«እኔ የኔ ፍቅር፣ ወድጄሽ ፣ ሞቼልሽ …… አይነት ቃላቶች አልችልም። » እጁም ከንፈሩም ሰውነቴ ላይ መርመስመሳቸውን አላቆሙም።

«እና ዝም ማለት አይቻልም?»

«እንዴ? ምን በወጣን? ቅጣት ነው የምንወጣው? አልተጣላን ለምን ዝም እንባባላለን?(መሬቱ ላይ እየተዋደቅን) መኝታ ቤት ይሁንልሽ?»

«አልፈልግም! ወሬህ ግን እየረበሸኝ ነው።»

«ያለመድሽው ነገር መሆኑን እርሺውና (ለከንፈሩ ስራ ሰጥቶት መለስ ይልና) ራንደም ወሬ አውሪኝ። ምግብ እያበሰልሽ ስለውሎሽ ማውራት እንደምትችዪው ፣ ፊልም እያየሽ ስለተዋናዩ ጫማ አስተያየት እንደምትሰጪው ፣ መፅሃፍ እያነበብሽ ፋታ ወስደሽ ሻይ ፉት እንደምትዪው ……..»

«እና ስለሶቅራጠስም ቢሆን እያወራን እናልብ?»

ከተጋባን ከዓመታት በኋላ አንዲት የተረገመች ቀን ላይ አፌ የማይገባውን ለፍልፎ እሱን ሌላ ጭራቅ ሰው እስካደረገው ቀን ድረስ ሁሌም እንዲህ ነበር። የጦፈ ልፋታችን መሃል ስላነበብነው መፅሃፍ እንጨቃጨቃለን ወይም ቀን ላይ ስራ ቦታ ስለገጠመው ደንበኛው ያወራኛል ወይም ትምህርት ቤት ስለገጠመችኝ ደም አፍዪ የተማሪ ወላጅ ወይም ደግሞ አዲስ ወጥቶ ስላየነው ዶክመንተሪ ፊልም ……. ብቻ ከልፋታችን ጋር የማይገናኝ ወሬ እያወራን እናልብ ነበር። አፌ ከአዕምሮዬ ጋር ሳይማከር እስከዘባረቀበት እስከዛች ቀን ድረስ……

የወደፊቱ የትዳር ህይወቴን ሲኦልነት የሚገልፁ <ማሳያ ትኩሳቶች> እያወቅኩ እና ፍንጣሪውን እየተለማመድኩ ሰንብቼ ነው ያገባሁት። ሶስት ዋና ዋና ምክንያቶች እና ሌሎች ፍርፋሪ አባሪ ምክንያቶች ነበሩኝ። አንዱ ከሌላኛው ጋር በቀጥታም በጓሮም ይጋመዳል። ብያችሁ አልነበር። አንደኛውን ነገርኳችኋ?

ሁለተኛው እሱ ወደህይወቴ ሳይመጣም በፊት ይናድብኛል የምለው ጠንካራ የተገነባ የኑሮ ዘይቤ አልነበረኝም። ለቤተሰቦቼ አምስተኛ ልጅ ነኝ። እንዳለመታደል ሆኖ ከእኔ በላይ የተወለዱት ታላላቆቼ በትምህርታቸው ጎበዝ ፣ በዓመላቸው በትምህርት ቤትም በጎረቤትም በቤትም የተመሰገኑ ሲሆኑ እግዚአብሄር እኔጋ ሲደርስ ዓመሉን ዘለለኝ።

አሁንም እንዳለመታደል ሆኖ እውቀት በሂሳብ እና እንግሊዝ ውጤት የሚገለፅ ሆነና በእሱም አልታደልኩም። እንደው ለምኑም ሳትሆን ከምትቀር ብሎ ነው መሰለኝ ለዓይን ማራኪ አድርጎ ሰራኝ። ከታላላቆቼ የተለየሁ በመሆኔ እንደጥፋት፣ እንደእርግማን ታየብኝ። በልዩነቴ ምክንያት ስቀጣ አደግኩ። ቀኔን ሲያከብድብኝ ታናናቼም ቤተሰቦቼ እንደሚሉት የእኔን አርአያ ተከትለው ትምህርቱን እርግፍ አድርገው ትተው ቦዘኔዎች ሆኑ። ለእነርሱም ጥፋት እኔ ተቀጣሁ።

የአብዛኛዎቻችን ወላጆች ልጅ አዋቂ እንዲሆን ከበላ ፣ትምህርት ቤት ከተላከ፣ የሚያድርበት ማደሪያ ካለው፣ ካልታረዘ በቃ የተቀረው አድጎ አዋቂ፣ ሀላፊነት ተቀባይ ለመሆን የልጁ የራሱ ሀላፊነት እንደሆነ ያስባሉ።

አባትሽ ትምህርት ቤት ሲጠራ «አንቺ መቼም ሰው አትሆኚም! ሁሌም እንዳዋረድሽኝ» የሚልሽ ተደጋጋሚ ወቀሳ ሰው እንዳትሆኚ ወደታች እንደሚጎትትሽ አያስተውልም።

አጎትሽ ድንገት ከአምስት ዓመት አንዴ መጥቶ «ውይ እቴቴ በዝህችኛዋስ አላደለሽም! ትልልቆቹን ይባርክልሽ እንጂ እቺ መቼም ሰው አትሆንም!» ብሎ ለእናትሽ ባዘነ ሙድ ሲነግራት አንቺ ይዘሽው የምታድጊው ከንቱነት እያቀበለሽ እንደሆነ አይገነዘቡልሽም።

አፏ የማያርፍ አክስትሽ «እቴትዬ ይህቺኛዋስ ደህና አማች ታመጣልሽ እንደው እንጂ ትምህርቱስ አልሆናትም!» ስትልሽ እናትሽ አብራ ትስቃለች እንጂ በማንም ፊት የማትረቢ እንደሆንሽ እያመንሽ ራስሽን እንደምትቀጪ አትገነዘብም!

ወላጆች ልጆቻቸውን በዱላ ሲቀጡ የሚታያቸው ዱላው ደም አለማፍሰሱ ነው። ወይም አጥንት አለመስበሩ፣ እዛ ደረጃ ካልደረሰ ልጁ እየተቀጣ እንጂ እየተጎዳ አይደለም። ትምህርት እየሰጡት ነው።

ዱላው ሰውነቱ ላይ ሊያርፍ በተዘረጋ ቁጥር ከሰውነቱ መሸማቀቅ ጋር በዘመኑ ሁሉ አብሮት የሚጓዝ በራስ ያለመተማመን እያሳጨዱት እንደሆነ አያውቁም። ሰውነቱ ላይ ባረፈው ዱላ ልክ ፈሪ እና ሸምቃቃ ልጅ እያፈሩ እንደሆነ አያውቁም! ሲቀጠቅጡት ያሳደጉትን ልጅ አድጎ በሰዎች ፊት መብቱን አንገቱን ሳይደፋ የሚጠይቅ ኩሩ ባለመሆኑ ይወቅሱታል። ከነዛ የዱላ ሰንበሮች ጋር በራስ መተማመኑ መክሰሙን አያስተውሉም። የዱላው ቁስል አይደለም ከልጁ ጋር አብሮ የሚኖረው ስሜቱ ነው። ፍርሃቱ፣ አንገት መድፋቱ፣ እንዳያስረዳ እንኳን <ዝም ጭጭ!> ተብሎ የዋጠው የመጠየቅ እና የመናገር መብቱ፣ ሰቀቀኑ ………… ያ ነው አብሮት የሚያድገው።

ሁል ጊዜ ለራሴ ሳይሆን ለእነርሱ ስል ጥሩ ልጅ ለመሆን እሞክራለሁኮ፣ ለአባቴ ጎበዝ ተማሪ ሆኜ ውርደቱ እንዳልሆን ፣ ለእማዬ ጨዋ ልጅ ሆኜ ሰው እንድሆንላት ፣ ለዘመዶቻችን ከታላላቆቼ እኩል ሆኜ ላኮራቸው። ለራሴ ስል ሳይሆን ለእነርሱ ስል እሞክራለሁ። ያለመታደል ሆኖ ውጤት እንጂ ትግል አይቆጠርማ? እፎርሻለሁ። አስረኛ ክፍል ደርሼ በእነሱ መለኪያ ሰው ያለመሆኔን ተቀብዬ ሙከራዬን ትቼ በራሴ ዓለም መኖር እስከጀመርኩበት ጊዜ ድረስ ሞክሬያለሁ።

መኖሬን ቀጥዬ የረባ ውጤት ሳላመጣ የሆነ መዋዕለ ህፃናት አስተማሪ ሆኜ እየሰራሁ። ሁሌም ልደበቀው የማልችለው ሀሳብ ጭንቅላቴ ጓዳ አለ። የሆነ ቀን ቤተሰቦቼን ማኩራት፣ በሙሉ አፋቸው « የእኔ ልጅ እኮ!» ሲሉኝ መስማት። እንግዲህ ሌላኛው ምክንያቴ ይሄ ነው። እናቴ «የልጄ ሰርግ ነው!» ብላ ለዘመዶቿ በኩራት መጥሪያ እንድትልክላቸው ፣ አባቴ «በመጨረሻም ልብ ገዛች! ልጄኮ ምን የመሰለ ባል አገባች መሰላችሁ!» እያለ ለወዳጆቹ እንዲያወራ ፣ ታላላቆቼ በትምህርታቸው ቁልል ያላደረጉላቸውን አድርጌ «ድሮምኮ ልጄ!» መባል።
ሶስተኛው ምክንያቴ እሱ ራሱ ነው። በ34 ዓመት ካገኘሽው ጋር ተጠቃለዪ የምትባዪበት እድሜሽ ነው። ያገኘሁት ሰው ቢያንስ ከዚህ በፊት እንደማውቃቸው ወንዶች ጅል አይደለም። ከአዎ እና አይደለም ውጪ የተለመደ እኝኝ የሚያወራ ወንድ ጅል ነው የሚመስለኝ። አዲስ እንደዛ አይደለም። የሚወደድ እና የሚጠላ ባህሪ ቢኖረውም አንድ ነገር ልዩ ያደርገዋል። አይሰለችም። ሁሉም ቀን ከእርሱ ጋር አድቬንቸር ነው።

«ከተጋባን ሰርግ እፈልጋለሁ! ትልቅ ሰርግ!» አልኩት የሲኒማ ክፍሉ ወለል ላይ እርቃናችንን እንደተጋደምን

«done!»

«በቁስ የምትደሰቺ ሴት ከሆንሽ አንቀባርሬ አኖርሻለሁ። አላልከኝም?»

«አዎ»

«ለራሴ ምንም እንድታደርግልኝ አልፈልግም! የሆነ ቀን ላይ ለእናት እና አባቴ ቤት እንድትገዛልኝ ብቻ ነው የምፈልገው። ከፈለግክ ከ8 ዓመት በኋላ የምታካፍለኝን ውርስ ሰርዘው።»

«እሺ!» አለ በምን አገባኝ ትከሻውን ሰብቆ

«በቃ እንጋባ! ሚዜዎችህን አዘጋጅ ለዘመዶችህ ለጓደኞችህ ንገራቸው።»

«እኔ ዘመድም ጓደኛም የለኝም። ሚዜ ብለሽ አታስጨንቂኝ። ሰርጉን የሚታደም የኔ ወገን የለም። » እያለኝ እየሰራሁት ያለሁት እብደት እንደሆነ ጠርጥሪያለሁ።

«የምርህን ነው? እንዴት አንድ ዘመድ አይኖርህም? ጓደኛስ? ቢያንስ የስራ ባልደረቦች አሉህ አይደል?»

«ዘመድ ጓደኛ የለኝም! የስራ ባልደረቦች አሉኝ ግን የግል ህይወታችንን አንነጋገርም! እና ማንንም ሰው ለግሌ ጉዳይ እንዲህ አድርጉልኝ ብዬ አልጠይቅም!»

............. ..... አልጨረስንም …………………..

@wegoch
@wegoch
@paappii
ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት ….. እኔ የቀጠልኩት
(ክፍል ሰባት ………. ሜሪ ፈለቀ)

ሰርጉ የራሴ ሆኖ ፣ በሰው ሰራሽ ፋብሪካ የተመረተ ሮቦት ይመስል ዘመድ አልባ ባል ላገባ የተዘጋጀሁት እኔ ሆኜ ሳለሁ፣ ሰርጉ ላይ ሚዜ እንኳን የሚሆን ጓደኛ የሌለው ባል ለማግባት ራሴ አምኜ ………. ምን ይሉ ይሆን ብዬ የምጨነቀው ለቤተሰብ ፣ ሰርጉ እንከን እንዳይኖረው ቁጭ ብድግ የምለው ለታዳሚው ……ሙሽራዋ ግን እኔው …… ቀኑ መሆን የነበረበት የኔ

«ለምን ራስሽን አትሆኝም?» አለኝ አዲስ የሰርጉ ውጥረት ቀልቤን ሲነሳኝ አይቶ

«ይሄ ነገር ስለሚባል ነው አይደል የምትሉት? ራስህን መሆን እኮ …… የምትወደው ራስህ ሲኖርህ ነው! እኔን መሆን እንዴት እንደሚያስጠላ ብታውቅ <ራስሽን ሁኚ> አትለኝም! ራሴን አልወደውም አዲስ! የማልወደውን ራሴን እንድሆን አትንገረኝ! እኔን መሆን ይቀፋል! ሌላን ሰው መልበስ ይሻለኛል። ያ ሰው ማን እንደሆነ ሳታውቁ <ራስህን ሁን> እያላችሁ አትምከሩት! የማነቃቂያ ንግግራችሁ ማስዋቢያ ወይም ንግግር ማሳመሪያ ብቻ ነው። መጀመሪያ ራሱ የሚወደው ማንነት ይኖረው እንደሆነ ጠይቁት እስኪ!! ራሱን ሲሸሽኮ ነው ሌላ ሰው የሚሆነው! » እየጮህኩ እና ስሜታዊ ሆኜ እያወራሁ እንደሆነ የገባኝ አዲስ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከራከርበት ሀሳብ ሰጥቼው በመከራከር ፈንታ በጣም ረጋ ብሎ ሁለቱን እጆቼን ሲይዘኝ ነው

« ቤተሰብ ፣ ማህበረሰብ፣ እኔ ፣ ሀይማኖት ……… ብቻ ምንም በዙሪያሽ ባይኖር ፣ ማንም ካንቺ ምንም ባይጠብቅ ፣ ማንንም ማስደሰት ወይም የማንንም expectation ማሟላት ባይኖርብሽ ………. ምን አይነት ሰው ነው መሆን የምትፈልጊው? ምን ማድረግ ነው የምትፈልጊው የነበረው?»

« ደስተኛ ሴት መሆን ብቻ ነበር የምፈልገው!! ማንም ሳያዋክበኝ ፣ ማንም < ሴት መሆን ያለባት፣ ወጣት መሆን ያለበት፣ ቆንጆ መሆን ያለበት፣ የእቴቴ ልጅ በመሆንሽ መሆን ያለብሽ፣ የዳግም እህት በመሆንሽ መሆን ያለብሽ፣ ክርስቲያን መሆን ያለበት ……… > እያለ የኑሮ ዘይቤዬን ሳያሰምርልኝ ከህሊናዬ እና ከአምላኬ ጋር ሰላሜን እየጠበቅኩ ራሴን መፈለግ ብቻ ነው የምመኘውኮ! ራሴን ማግኘት!! ፍለጋዬን ገና ድሮ ስላጠፉብኝ ማን እንደሆንኩ እንኳን አላውቀውምኮ!!» አሁንም እየጮህኩ ነው የማወራው። እስከዛሬ ለራሴ ራሱ ለማስረዳት በውል የቸገረኝን መሻቴን ሳብራራ ራሴን አገኘሁት። ለደቂቃ ያህል ዝም ካለኝ በኋላ

«ሰርጉን መሰረዝ ትፈልጊያለሽ? ማንንም የማታዪ የማትሰሚበት ቦታ ሄደሽ ከራስሽ ጋር ብቻ ጊዜ እያሳለፍሽ ራስሽን መፈለግ ትፈልጊያለሽ? ያን ላሳካልሽ እችላለሁ። ነገር ግን ሁሉንም ከኋላሽ የመተው አቅሙ አለሽ?»

«አቅሙ የለኝም! አልፈልግምም! አየህ ወፍ መብረር እችላለሁ ብላ የፈለገችበት ዝም ብላ አትበርም። ስደተኛ ወፎች የሚባሉትን ታውቃቸዋለህ? ተፈጥሯዊው የአየር እና ወቅት ለውጥ የኑሮ ዘይቤያቸውን እነርሱ ወደፈለጉበት ሳይሆን ምግብ ወደሚገኝበት፣ መኖሪያቸውን በረዶና ንፋስ ሳያፈርስባቸው ወደሚኖሩበት አቅጣጫ እንዲበሩ ያስገድዳቸዋል። አየህ ህብረተሰብ ቤተሰብ ሀይማኖት ባህል ምናምን የማይዛት ወፍ እንኳን ተፈጥሮ በሆነ መልኩ ያጥራታል። ወደድንም ጠላንም የምትታሰርበት ሸምቀቆ እንደግለሰቡ ከመጥበቁ እና ከመላላቱ ውጪ ሁላችንም በአንደኛው ገመድ ተጠፍንገናል። ምክንያቱም የዚህ ማህበረሰብ አካል ነና! የምንኖረው ከዚሁ ማህበረሰብ ጋር ነዋ! የምንኖረው ለዚሁ ማህበረሰብ ነዋ! እንደአለመታደል ሆኖ አንዳንዶቻችን የታሰርንበት ገመድ አንቆ ሊገድለን አንገታችን ሰልሎ እንኳን ለማምለጥ አቅሙ የለንም!» አይኔ ይሁን እንጃ ያዘነልኝ መሰለ? የሆነ ውሳኔ ለመወሰን ያመነታ መሰለ። ግንባሩ ላይ ስሜቶቹ ተቁነጠነጡ።

«እሺ በተወሰነ መልኩ ውጥረትሽን ከቀነሰልሽ ስራ ቦታ ያሉ ሰዎችን ሚዜ እንዲሆኑልኝ ጠይቃቸዋለሁ። የተወሰኑትንም ሰርጉን እንዲታደሙ የጥሪ ወረቀት እሰጣቸዋለሁ። ይሄ የሚያቀልልሽ ነገር አለ?»

«አዎ በጣም! በጣም እንጂ! በጣም ብዙ ነገር ያቀልልኛል። አመሰግናለሁ!» እንደህፃን ልጅ መጨፈር ቃጣኝ። ማድረግ የፈለግኩት ከንፈሩን መሳም ነበር ግን ጉንጩ ላይ አረፍኩ። ሰርጌ ሳምንታት እየቀሩት የማገባውን ሰውኮ በጭራሽ አላውቀውም! እሱ ላይ ስልጣንና መብቴ ምን ድረስ እንደሆነ እንኳን አላውቅም።

«የሰውን ልጅ ልወቀው ብለሽ እድሜሽን አትፍጂ ይልቅ ያንን ኢነርጂ ራስሽ ላይ አውዪው። እመኚኝ ራስሽን ለማወቅ የምታደርጊው ፍለጋ በራሱ እንኳን እድሜ ልክ ይፈጃል እንኳን የውስጥ ሀሳቡን ልታውቂ የማትችዪውን ሌላ ሰው ማወቅ» ይለኛል ላውቀው እንደምፈልግ ስነግረው።

«እውነት ነው የሰው ልጅ ሙሉ በሙሉ ልታውቀው የምትችለው ፍጡር አይደለም። ግን ሁሉም ሰው የማይቀየሩ ወይም ቢቀየሩም ሙሉ በሙሉ የማይጠፉ መሰረታዊ የሆነ የማንነት ምሰሶ አለውኮ!»

«አትሳሳቺ! ፐርሰናሊቲ ካዳበርሽው የሚያድግ፣ ከተውሽው የሚሞት፣ ወይም በማህበረሰብ ሚዛን ጥሩ ወይም መጥፎ ከሆኑት ፅንፎች ከሌላው ሰው የሚቀዳ ነው። ሰው ማሰብ ካላቆመ በቀር ይቀየራል። እንደቁስ እዚህጋ አስቀምጬሃለሁ እና ከዝህችው አንተነትህ ፈቅ እንዳትል ልትዪው አትችይም! ያስባላ! ሰዎች ባላቸው የተለያየ ግንኙነት የሚጣሉት ለምን ይመስልሻል? በአብዛኛው በጊዜ ሂደት የሚመጣውን የዛኛውን ሰው ማንነት መቀበል ስለሚያቅታቸው ነው። ወንድ እና ሴት ይጋቡ እና ከአስር ዓመት በኋላ ይለያያሉ። ለምን ብትያቸው <ሳገባው የነበረው ዓይነት ሰው አይደለም> ትልሻለች ወይም ይልሻል። ከዓመታት በፊት የተመቸው ነገር ተመችቶት እንዲቀጥል ትጠብቃለች። የሌላን ሰው ለውጥ መቀበል አንወድም! ወደ ራሳችን ብናይ ግን በነዛ ዓመታት ራሳችንም ተለውጠናልኮ! ለምን ነገ ሊቀየር የሚችል እኔነቴን ለማወቅ ጊዜ ታባክኛለሽ? አወቅኩት ብለሽ ስታስቢ ተቀይሬ ብታገኚኝ ጊዜና ጉልበትሽን አባከንሽ ማለትም አይደል?»

ተውኩት። ያለፈውን የእምነት መሰረቱን ለማወቅ መቆፈሬን ተውኩት። ዛሬ ላይ ብቻ አተኮርኩ። አብሬው ስሆን ያለው አዲስ ላይ ብቻ አተኮርኩ። ዛሬ የትናንታችን ውጤት መሆኑን ልቤ እያወቀ ትናንትን ከእኔና ከእርሱ መሃከል አሽቀንጥሬ ጣልኩት። ትናንት ምን ያህል ቢገፉት አራሙቻውን በጣጥሶ ዛሬ ላይ የመንገስ አቅም እንኳን እንዳለው ልቤ እያወቀ። ትናንትን እንደአሮጌ ሸማ አጣጥፌ የማልከፍተው ያረጀ ሳጥን ውስጥ ቆልፌ ከአዲስ ጋር አዲስ ኑሮ ጀመርኩ።

ሽማግሌዎቼን ራሴ መርጬ አስላኩኝ። ሰርጌ ደመቀ። «አሁን ደመቅሽ የኛ ልጅ !» ተባለልኝ። በቤተሰባችን ታሪክ ያልታየ የተባለለትን ደማቅ ሰርግ ደገሰልኝ። «የማታ ትዳር ሰጣት » ተባለልኝ። ቆማ ቀረች ያለኝ ዘመድ አዝማድ «እንኳንም ታግሰሽ ጠበቅሽ! ትዕግስት ፍሬዋ …..» እያለ አገላብጦ ሳመኝ። «ውለዱ ክበዱ !» ተባልንልን! ላለመውለድ ላለመክበድ ፈርሜ እንደገባሁ አያውቁም! የቤተሰብ ቅልቅል፣ መልስ አንጃ ግራንጃውን « ቤተሰቦቹ እዚህ ሀገር አይደሉም!» እያልኩ ስዋሽ ከረምኩት። አዲስ ዝም ብሎ አላለፈኝም። በየመሃሉ ሀሳብ ከመስጠት አይቦዝንም። ግን ባይዋጥለትም ለእኔ ከማዘን ውጪ ቀኔን አላበላሸብኝም።

«ኸረ ተይ ሰዎች በህይወትሽ ውስጥ ያላቸውን ስልጣን ገደብ አበጂለት? ቤተሰቦችሽም ቢሆኑ ህይወትሽን የሚያማስሉበት ገደብ አለው። ዛሬ ለእነሱ ብለሽ ሰርግ ደገስሽ፣ አገባሽ፣ ዋሸሽ …… አያቆምምኮ አንቺ የማስቆም ሀሳብ ከሌለሽ» ብሎኝ ነበር የቅልቅሉ ቀን።
እኔም የተገላገልኩ መስሎኝ ነበር። ገና መጀመሪያው መሆኑ የገባኝ አግብቼ ብዙም ሳልቆይ ሁሉም በየፊናው <ሴት ልጅ ጠቢብ ናት። ያዝ ቆንጠጥ ማድረግ ልመጂ> አይነት የጨዋ የሚመስል ግን ሀብቱ በእጅሽ እያለ ስረቂው አይነት ምክር መምከር ሲጀምሩ፣ <ገንዘብ አይሰጥሽም እንዴ? ይሄን ያህል ሀብት ላይ እየዋኘሽ መዋዕለህፃናት የምታስተምሪው ለምንድነው?> ዓይነት ጥያቆዎች ሲጠይቁኝ ፣ <እንዴ እስከመቼ ነው? ለምን የግልሽ ስራ እንዲከፍትልሽ አትጠይቂውም?> እያሉ በእኔ ባል ገንዘብ ምን ቢከፍትልኝ እንደሚያዋጣኝ ትርፍ እና ኪሳራውን እያሰሉ እንቅልፍ ሲያጡብኝ ፣ በአመቱ «ምንድነው የምትጠብቂው ሁሉ እያላችሁ ልጅ የማትወልዱት ለምንድነው?» እያሉ ሲነተርኩኝ ነው። ………. ገደብ እንደሌለው ገባኝ! እድሉን ከሰጠኋቸው ከባሌ ጋር የማደርገውን የአልጋ ልፊያ ፖዝሽን እንምረጥልሽ እንደሚሉኝ ገባኝ።

በተጋባን በወራት ውስጥ አዲስ ለቤተሰቦቼ በሀሳባቸው እንኳን ሽው ብሎ ሊያውቅ የማይችል ትልቅ ዘመናዊ ቤት ገዛልኝ። አባቴ ስምንት ልጅ ወልዶ ያሳደገበትን የቀበሌ ቤት ያስረከበ ቀን ቀበሌ ለሚሰሩት ለእያንዳንዳቸው እየዞረ « ህልም የመሰለ ቤት ልጄ ገዛችልኝ! ልጅ ማለት እንዲህ ነውይ!» እያለ የቤቱን ፎቶ ሲያሳያቸው ዋለ። ትምህርት ቤት በተጠራ ቁጥር «አንቺ መቼም እኔን ከማዋረድ የተሻለ ስራም የለሽ። ደግሞ ምን አጥፍተሽ ነው?» ያለኝን እልፍ ቀን በዝህች አንድ ቀን ሙገሳ አጣፋሁት!! እማዬ ቤቴን መርቁልኝ ብላ ጎረቤቶቿን እና ገጠር ያሉ ዘመዶቿን ሁላ ሳይቀር ጠርታ አዲሷ ቤቷ ውስጥ ከአንድ ክፍል ወደሌላው ክፍል ሽር ብትን እያለች «እልልልልልልል እንደው ልጄ በመድከሚያዬ ማረፊያዬን እንዳሳመርሽልኝ ትዳርሽን ያሳምርልሽ!» እያለች ስትመርቀኝ ዓለሜ የሞላ መሰለኝ። በቃ ከዚህ በኋላ ለእነርሱ ኩራት ለመሆን መንፈራገጤን የማቆም መስሎኝ ነበር።

«ራስሽ ለማቆም ካልወሰንሽ ማብቂያ የለውም! የሆነ ቦታ መወሰን ካልቻልሽ ሁሌም እነሱን ለማስደሰት ብቻ ነው የምትኖሪው።» የሚለኝ የአዲስ ቃል እየቆየ ነው የሚገባኝ። ምንም ቢጠይቁኝ <እንቢ> <አልችልም> ማለት ሲያቅተኝ። ሁሌም «የእኔ ልጅኮ!» ለመባል የማይቻለውን ለመቻል ስዳክር፣ እየቆየ <ይሄን አሁን ማድረግ አልችልም! ጊዜ ስጡኝ> ስል ማኩረፍ ሲዳዳቸው፣ አለፍ ሲልም <ቤተሰብሽን እንኳን ለመርዳት ካልቻልሽ እያዩ የማይበሉት ሀብት ለጉራ ካልሆነ ምን ይሰራል?> አይነት ወቀሳ ጣል ሲያደርጉ ሳልፋቸው፣ ለቤተሰብ እና ለዘመድ ከማደርገው መቶ ነገር ይልቅ አንድ ያላደረግኩት ሲቆጠርልኝ ፣ ላደረግኩት እልፍ ነገር ከመመስገን ይልቅ ላላደረግኩት አንድ ነገር ዓመቱን ሙሉ ስረገም ……. ዘግይቶም ቢሆን ገባኝ። የተባረኩኝ ልጅ ወይም ጥሩ እህት መሆኔን ለእነሱ ለማስመስከር ስዳክር ጉልምስናዬ ላይ መድረሴ ሳያንስ ራሴን ለማስደሰት ሳልኖር ላረጅ መሆኑን አወቅኩ። ማድረግ ከምችለው በላይ ራሴን ላለማስጨነቅ ወሰንኩ። የምችለውን በእነሱ ለመሞገስ ሳይሆን ለነሱ ማድረግ በመቻል ውስጥ ስላለው እርካታ ስል አደርጋለሁ።

አዲስ ገንዘብን በተመለከተ ስግብግብ የሚባል ሰው አይደለም። ያለምክንያት ግን ሽራፊ ሳንቲም አያወጣም። አንደኛውን የባንክ አካውንቱን በሁለታችን ስም አድርጎታል። ከ50 ሺህ ብር በላይ ማውጣት ስፈልግ ግን የግድ እሱ መፈረም አለበት። በራሴ ምክንያት ከፍ ያለ ገንዘብ አውጥቼ አላውቅም። ሁሌም በቤተሰብ ምክንያት ነው። ካላሳመነው አይስማማም። ካሳመነው ዝም ይላል። አንዳንዴ ሲመስለኝ ባይዋጥለትም ለእኔ ብሎ ያልፈኛል።

ከቤተሰቦቼ አዙሪት ውጪ ትዳሬ እንደተለመዱት የትዳር አይነቶች ቅርፅ ሳይዝ ቀጠለ። በፍቅር ወይም በተለመደው የትዳር ህግ ሳይሆን የሚተዳደረው ራሳችን በተስማማንባቸው ህጎች ነው። ያልፃፍናቸው ግን የተስማማንባቸው ብዙ ህጎች አርቅቀናል። በትንሹ ሀኒ፣ ቤቢ፣ ማሬ ውዴ የሚሉትን የቁልምጫ ቃላቶች ካለመጠቀም ጀምሮ ልጅ እስካለመውለድ ድረስ........ያለፈ ህይወታችንን (አንደኛው አካል ፈቃደኛ ሆኖ መናገር እስካልፈለገ ድረስ) ለመቆፈር ምንም አይነት እርምጃ ካለማድረግ እስከ አንደኛው አካል ትዳሩን ለቆ ለመሄድ በፈለገው ጊዜ መብቱ እንደሚከበርለት። ብዙ ህጎች …….. ሁለታችንም ያልገባን ወይም ማመን ያልፈለግነው ህግን የሚጥስ ስሜት መኖሩን ነው። ሳላውቀው፣ ሳላሰላ፣ ምንም አይነት ሂሳብ ሳልሰራ ህግ ጣስኩ።

ዛሬ ላይ ለምቀጣው ቅጣቴ ሁላ ጥፋቴ ያ ነበር………. አብሬው ስኖር ያወቅኩትን አዲስ በአዕምሮዬ ትግል የልቤን ስሜት አሸንፌ አለመውደድ አቃተኝ። በእያንዳንዷ ቀን አፍኜ እስከማልይዘው ድረስ ፍቅሩ ልቤ ውስጥ ተቆለለ። መቼ እንደሆነ አላውቅም ብቻ ግን የሆነኛው ቀን ላይ እሱ ልብ ውስጥ ለመቀመጥ ምንም ነገር መስዋዕት የማደርግ አቅመ ቢስ ሆኜ ራሴን አገኘሁት። ይኸው ነበር ጥፋቴ! እንዳገባው ለራሴ ለማሳመን ምክንያቶችን የደረደርኩለትን ሰው እንዳላጣው የትኛውን ምክንያት እንደማደረጅ ቸገረኝ።

«ምንድነው?» አለኝ የሆነ ቀን ማታ ልንተኛ ወደአልጋችን ሄደን እየተሳሳምን አቋርጦኝ።

«ምኑ?» አልኩት ግራ ገብቶኝ

«አሁን የሳምሺን መሳም! ልክ ያልሆነ ነገር አለው።» አለኝ።

ያለው ገብቶኛል። <አዎ ፍቅር አለበት> ብለው ደስ ይለኝ ነበር። ምላሹ ምን እንደሚሆን ልቤ አስቀድሞ አውቆ ነው መሰለኝ ፈራሁት። ባሌን ፣ አብሬው ኑሮ የምጋራውን አጋሬን፣ አቅፌው የምተኛውን ፍቅሬን፣ ምንም የማልደብቀውን የልብ ጓደኛዬን ……….. ማፍቀሬ በደል ሆነብኝ። ስለየትኛውም ስሜቴ ይዳኘኛል ብዬ የማላፍረውን ባሌን ፍቅሬን ዋሸሁት። ከንፈሮቹ እሱ እንደሚለው ከስሜት መጠቃቀም ልቀው መለኮታዊነት ያለበት ዓለም ውስጥ እንደሚከቱኝ መንገር አፈርኩ።

........ አልጨረስንም……………..

@wegoch
@wegoch
@paappii
ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት ….. እኔ የቀጠልኩት
(ክፍል ስምንት ………. ሜሪ ፈለቀ)

ጥፋቴ ማፍቀሬ ነበር አላልኳችሁም? የትኛው ዓመት ፣ መቼ ላይ እንዳፈቀርኩት እንኳንኮ አላውቅም! ቀስ በቀስ ……. መሰረቱን ሲጥል ….. ግድግዳውን ሲገነባ ….. ጣራውን ሲከድን …… ቀለም ሲቀባባባ ፣ ወለሉን ሲያሳምር …… ገዝፎ ገዝፎ ተሰርቶ አልቆ …… በአራተኛው ዓመት በራሴ ላይ ማዘዝ የማልችል ሆኜ ሽምድምድ ካልኩ በኋላ ነው ከእንቅልፉ እንደባነነ ሰው የማደርገው ጠፍቶኝ ጥፋት እንዳጠፋ ህፃን ባየሁት ቁጥር ልቤ ከአቃፊዋ ካላመለጥኩ ትል የጀመረችው:: ሰርቆ መች ከመቼ ተነቃብኝ እንደሚል ሌባ ..

መሰረቱን ሲጥል

በተጋባን በሆኑ ወራቶች ውስጥ የሆነ ቅዳሜ ከሰዓት ሁሌም ላይብረሪ ሲቀመጥ እንደሚያደርገው ስልኩን አጠፋፍቶ እያነበበ ነበር። ሁሌም ማንበብ ሲጀምር በስርዓቱ ወንበሩ ላይ ተቀምጦ መፅሃፉን ጠረዼዛው ላይ አስቀምጦ ነው።
ከሆነ ሰዓት በኋላ ተነስቶ እየተንጎራደደ ማንበብ ይጀምራል። ይቆይና ደግሞ ምንጣፉ ላይ ቁጭ ብሎ መደርደሪያውን ተደግፎ ያነባል። ቀጥሎ በደረቱ ምንጣፉ ላይ ይተኛል። ወይም በጀርባው። ሁሌም ቅደም ተከተሉ ይለያያል እንጂ እንዲህ ይመሳቀላል። የዛን ቀን ራሴን አሞኛል ብዬው ምንጣፉ ላይ ተቀምጦ እግሮቹ ላይ አስተኝቶኝ እያነበበ ፀሃይ ስትጣደፍ ገባች

«የሆነ ሰውዬ እየፈለገህ ነው! » አለች።

ተከታትለን ወደሳሎን ገባን። ቤታችን እኔን ብሎ የሚንጋጋው የእኔ ዘመድ እንጂ ማንም ሰው እሱን ፈልጎት መጥቶ አያውቅም። ከሰውየው ጋር እንደተያዩ እንደሚግባቡ ያስታውቃሉ።

«ህሊና በጣም ታማለች። ስልክህን ደጋግሜ ብደውል አታነሳም። ይቅርታ የነፍስ ጉዳይ ባይሆንብኝ እቤትህ ድረስ መጥቼ አልደፍርህም!» አለው ሰውየው።

አዲስ ምንም ቃል አልተነፈሰም። ዞር ብሎም አላየኝም። ሊያስረዳኝም አልሞከረም። ከነቱታው በሲሊፐር ዋሌቱንና ጃኬት ብቻ አንስቶ ወጣ! ህሊና ማናት? ስልኩን እንኳን አልያዘም! እንዲህ አለት ልቡን የነቀነቀችው ማናት? እህቱ? ሚስቱ? እናቱ? ልጁ? አላውቅማ!! ስለእርሱ ከግምት ውጪ የማውቀው የለማ!! ብቻ ማንም ትሁን ቀናሁባት! የዛን ቀን ማታ ምንም ቢፈጠር ከቤቱ ውጪ የማያድረው ሰው እቤት አልመጣም አደረ። ምኑ ልትሆን እንደምትችል እያንዳንዱን ምርጫ እያሰላሁ መኝታ ቤቱን በእርምጃዬ ስመትር ነጋ!! ጠዋት የዛለ ሰውነቱን እየጎተተ መጣ!

«ማናት?»

«ህፃን ልጅ ናት! ታማ ነው።»

«እኮ ማን ናት? ምንህ ናት? ከቀድሞ ትዳርህ ልጅ አለህ?»

«ያልነገርኩሽ እንጂ የዋሸሁሽ ነገር የለም! ልጅ ኖሮኝ ለምን ዋሽሻለሁ?»

«አላውቅም አዲስ! አላውቅህምኮ! ምንም ስላንተ የማውቀው ነገርኮ የለም።»

«እኔ ያለፈ ታሪኬ ውስጥ የለሁም! እኔ ይሄ ዛሬ የምታዪው አዲስ ነኝ። ድሮዬ ውስጥ አትፈልጊኝ። ማወቅ ኖሮብሽ ያልነገርኩሽ ምንም የለም! የምዋሽበት ምንም ምክንያት የለም! ራስሽን አታድክሚ! ብሎኝ ልብሱን አወላልቆ አልጋ ውስጥ ገባ! «ይልቅ ነይ ተኚ! በኃላ አስረዳሻለሁ»

ከእንቅልፉ ሲነሳ ህሊና የተኛችበት ሆስፒታል ወሰደኝ። የ12 ዓመት ህፃን ናት። ማታ እቤት የመጣው ሰውዬ አጠገቧ ነበረ። ከህፃኗ ጋር ሲጫወት ሳየው የሆነ የማላውቀው ሰው ነው። ግራ መጋባቴ ገብቶት ይሆን ሰውየው አዲስን በፈገግታ እያየ ። «መቼም እሱ ባይኖር እነዚህ ህፃናት ምን ይውጣቸው እንደነበር? ቅድም ስታቃስት ሁሉ ነበር አሁን እሱን ስታይ ዳነች።» አለኝ።

«ልጅ መውለድ አልፈልግም ማለት ልጅ አልወድም ማለት አይደለም። እነዚህ ወላጆቻቸው ያለሃላፊነት ወልደው ለቁር እና ለጠኔ የዳረጓቸው፣ ያለጥፋታቸው የተቀጡ ህፃናት ናቸው።» አለኝ እየወጣን። የመገረም አስተያየቴ ምን ማለት እንደሆነ ገብቶት።

«ለምን አልነገርከኝም?»

«ምን ብዬ? ደግሞስ ምን ይጠቅምሽ ነበር? ወላጅ የሌላቸውን ልጆች የሚረዳ መልካም ሰው ነው የሚለውን ካባ እንድትደርቢልኝ? ነውር አይደል? ምርጫ ባጡ ህፃናት ሆድ ውዳሴ መሰብሰብ ነውር አይደል?»

ዝም አልኩ!! በምቾት የተቀመጠበት ልቤ ውስጥ መሰረቱን አስፍቶ ቁልል አለ። ደሞ የሆነኛው ቀን ከስራ ደወለልኝና

«ፀዲ ታማ ብር ፈልጋ ጠይቃኝ ነበር። በዚህ ጉዳይ አውርተን ባናውቅም ሳልነግርሽ መስጠቱ ምቾት ስላልሰጠኝ ልንገርሽ ብዬ ነው። ይደብርሻል?» አለኝ

ፀዲ የመጀመሪያ ሚስቱ ናት። አሁን እሷ አግብታ ወልዳለች። የሆነ ቀን ሞል እቃ እየገዛን ልጇን በእጇ ይዛ ተገናኝተን አስተዋውቆኛል። የዛን ቀን

«ይገርማልኮ መቼም የሰው ልጅ ይቀየራል። አዲስ የሰርግ ግርግር ተመችቶት ደግሶ አገባ? ማመንኮ ነው የሚያቅተው? » እያለች ስታበሽቀው፣ እየሞላበት ያለበት ልቤ ውስጥ ገዘፈ። <ለእኔ ብሎ ነው ያደረገው!> ብዬ ማመን ፈለግኩ።

«አትስጣት ይደብረኛል ብልህ አትሰጣትም?» አልኩት።

«እሰጣታለሁ። አትስጣት የምትዪበት በቂ ምክንያት ካለሽ እናውራበት!» ሁሌም ይኸው ነው ፊት ይሰጠኝና ደግሞ ይኮሳተርብኛል። ያቀብጠኝና ደግሞ ይገፋኛል።

«አይ ዝም ብዬ ነው። ታገኛታለህ?» ድምፄ እሱ ላይ ስልጣን ስለሌለኝ ከመቅዘዝ ውጪ ምርጫ እንዳልነበረኝ አሳበቀብኝ።

«አዎ ሄጄ ነው ብሩን የማቀብላት። ታማለችኮ! (ትዝብት ያለበት አይነት ለዛ) መጥቼ ልውሰድሽ አብረን እንሂድ?» ይኸው ደግሞ ሲያቀብጠኝ። መጥቶ ይዞኝ እየሄደ

«ለምንድነው ያላመንሽኝ? ከፀዲጋኮ ተበቃቅተን ነው በምርጫችን የተለያየነው። ለምን የምመለስ መሰለሽ?»

«እኔ እንጃ! ዛሬም ላይ ግን ሲቸግራት የምትጠራህ ሰው ነህ! ምንም ማሰብ አልነበረብኝም? የእኔና ያንተ ትዳር እኮ በህግ እንጂ በፍቅር የቆመ አይደለም። ህግ ያለፍቅር አቅም ያጣል።»

«አብረሽኝ ደስተኛ አይደለሽም? እኔኮ ደስተኛ ነኝ ሌላ ሴትጋ የምሄድበት ምክንያት የለኝም። ለምን ታወሳስቢዋለሽ? አንቺጋ ጎድሎብኝ ሌላ ሴት የምፈልገው ጉድለት የለኝም።»

ይኼኛው ሁለት አይነት ስሜት ሰጠኝ። ደስተኛ መሆኑ ደስ አለኝ። አታወሳስቢው ያለበት ድምፅ ማስጠንቀቂያ መሰለኝ። እናም ላለማወሳሰብ ዝም አልኩ። በየሆነ ጊዜው የሚያስገርመኝ ባህሪውን አውቃለሁ። ላልወደው አልችልም ነበር። ግን ዝም አልኩ።

«ለምንድነው ይሄን ያህል ኢሞሽናልይ ከሰዎች ጋር መቆራኘትን የምትፈራው? ታዝናለህ ግን እንዳዘንክ ማንም እንዲያውቅብህ አትፈልግም፣ ትራራለህኮ ግን ድክመት ስለሚመስልህ ትሸፍነዋለህ፣ ትወዳለህ ግን መሸነፍ ስለሚመስልህ ትደብቀዋለህ።» አልኩት የሆነ ቀን እሁድ ህፃናቶቹጋ ውለን እየተመለስን።

«ሁሉም በድርብቡ ጥሩ ነው! ኢሞሽን በገዛ እጅሽ ነፃነትሽን በሸምቀቆ መጠፍነግ ነው። ለሀሴትሽ የተደገፍሽው ሰው የነገ ሀዘንሽ ምክንያት እንዲሆን ስልጣን እየሰጠሽው ነው። ማንም ሉጋም እንዲያበጅልኝ አልፈልግም። ተደግፌህ ጥለኸኝ ስትሄድ ወድቄ ተሰበርኩ ብለሽ ማንንም መውቀስ መብት የለሽም። የሰው ልጅ ይቀየራል። ሁሌ ላንቺ ደስታ ምክንያት ለመሆን ሲል ድጋፍሽ ሆኖ ተገትሮ አይቀርም። ይሄዳል። ማወቅ ያለብሽ በህይወትሽ ውስጥ ሰዎች ይመጣሉ። ይሄዳሉ። አብረሻቸው ስትሆኚ ጥሩ ጊዜ አሳልፊ! ሲሄዱ ተንቀሳቀሺ!! ያስተሳሰራችሁ መጠቃቀም ሲሳሳ ኢ,ሞሽን የምትዪው ብን ይላል። »
በተደጋጋሚ በየጨዋታው በኢሞሽን መጠለፍ እንደማይፈልግ እያስረገጠ ይነግረኛል። በቃ ምንም ስሜት የለውም እንዳልል እያንዳንዱ ድርጊቶቹ ለእኔ የሚታዩኝ በፍቅር ተጠቅልለው ነው። ምንም ስሜት የሌለው ሰው ከአራት አመት በኋላ እንኳን የሚስቱን ፀጉር ያጥባል? ምንም ስሜት የሌለው ሰው <ዛሬ የበላሁት ምግብ አልተስማማኝም መሰለኝ። አስመለሰኝኮ> ስለው በደቂቃ ቢሮ ድረስ መጥቶ ደህና መሆኔን ቼክ ያደርጋል? እሺ ምንም ስሜት የሌለው ሰው ከደረጃ ወድቄ እጄ የተሰበረ ቀን የታሸገውን እጄን ደረቱ ላይ አድርጎ ሳይንቀሳቀስ ያድራል? እሺ ምንም ስሜት የሌለው ሰው አራት ዓመት ሙሉ ነፍስ ከስጋዬ የሚያስቃትተኝ ፍቅር ይሰራል? እሺ ምንም ስሜት የሌለው ሰው <አይንሽ ላይ እንባ ሳይ ቀኔ ይበላሻል!> ይላል? እሺ ምንም ስሜት የሌለው ሰው <ጠዋት ሳትስሚኝ ሄጄ ሰራተኞቹ ላይ ተቀየርኩባቸውኮ! ለምን ሳትስሚኝ ሄድሽ?> ይላል።

ከዛ ደግሞ ዓለሜን ድብልቅልቁን ያወጣውና እኔ ከቀኑ ብጎድል ምንም እንደማይጎድልበት ይሆናል። በቃ ምንም እንደሆንኩ። የሆነኛው የህይወቱን ቀኖች አካሂያጅ ብቻ እንደሆንኩ። ምንም እንደማልመስለው። በዚህ ሁሉ ውስጥ የእኔ ነፍስ አንዲት ቀን ብቻ ተሳስቶ «ወድሻለሁኮ» እንዲለኝ ትፀልያለች። በስህተት እንኳን! ከፈለገ አይድገመው። አንዴ ብቻ! እሺ እሱ አይበለኝ እኔኮ «የእኔ ፍቅር » እንድለው እፈልጋለሁ። እሱ አይበለኝ ለምን እኔ የሚነድ ፍቅሬን መግለፅ እከለከላለሁ? ጠዋትኮ ስሜህ ወጥቼ ማታ እስክመለስ እንደቲንኤጀር እቅበጠበጣለሁ> ልለው እፈልጋለሁኮ። መስማት የማይፈልገው ነገር መሆኑን አውቃለሁ። ከአፌ እንዳያመልጠኝ ተጠነቀቅኩ፣ እቅፉ ውስጥ ሆኜ የምትደልቅ ልቤ የምታሳብቅብኝ ይመስል ተሳቀቅኩ!

ከአራት ዓመት በኋላ እንደለመድነው የቀን ውሏችንን እያወራን መኝታችን ላይ እየለፋን የሞላው ስሜቴ ገነፈለ፣ ያባበልኩት ፍቅሬ አመፀ

«እኔ ከዚህ በላይ ማስመሰል አልችልም! ከአቅሜ በላይ ነው የምወድህ!» እያልኩት እናቱ ናፍቃው እንዳገኘ ህፃን መንሰቅሰቅ ጀመርኩ።

................. አልጨረስንም……………………………

@wegoch
@wegoch
@paappii
ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት ….. እኔ የቀጠልኩት
(ክፍል ዘጠኝ ………. ሜሪ ፈለቀ)

«እኔ ከዚህ በላይ ማስመሰል አልችልም! ከአቅሜ በላይ ነው የምወድህ!» እያልኩት እናቱ ናፍቃው እንዳገኘ ህፃን መንሰቅሰቅ ጀመርኩ።

የሚያስለቅሰኝ ምኑ እንደሆነ ለራሴ ምክንያት መስጠት አልቻልኩም። ፍቅሩ፣ ፍርሃቴ፣ ሳልናገር መታፈኔ ……… አላውቅም። እንደህፃን ድምፅ አውጥቼ እዬዬ ማለት ጀመርኩ። እሱ መጀመሪያ እየከወነ ያለውን ልፋት በቀስታ አቆመ።

«አውቃለሁኮ! » አለ ለእኔ ይሁን ለራሱ የተናገረው በማያስታውቅ አወራር። <አውቃለሁኮ!> ያለበት አባባል <አውቄልሻለሁኝኮ! ፍቅርሽ ገብቶኛል፣ ተረድቼሻለሁ።> ዓይነት አይደለም። የሆነ የቁጭት ዓይነት፣ የብስጭት ዓይነት ነበር። …….. መንሰቅሰቄ ሲብስበት በጎኑ ተኝቶ ደረቱ ላይ አጣብቆ አቅፎኝ ዝም አለ። የሳጌ ድምፅ ከፍ ሲልበት እቅፉን ጠበቅ ያደርገዋል። እንደማባበል ዓይነት። ደቂቃዎች ካለፉ በኃላ ………….. ለቅሶዬን ያለከልካይ ካስነካሁት በኃላ………. እንባዬ ደረቱን ካራሰው በኋላ ………. ከዚህ ሁሉ ደቂቃ በኋላ ጭንቅላቴን ከደረቱ ወደ ክንዱ አሸጋግሮ ቀና አለ። ባላቀፈኝ እጁ ፀጉሬን ከግንባሬ ላይ አሸሸው፣ በእንባ የተጨማለቀ ፊቴን ጠራረገ ፣ የስስት ይሁን የፍቅር ይሁን መግለፅ በማልችለው ስሜት ዓይኔን ፣ ጉንጬን ፣ አፍንጫዬን፣ አገጬን ፣ ግንባሬን ፣ አንገቴን ……… ፊቴ ላይ ስማቸውን ሁላ የማላውቃቸውን ቦታዎቼን በቀስታ እና በተመስጦ ሳማቸው። ከንፈሬን ስሞኝ እንደማያውቀው ፤ ተሰምቶኝ እንደማያውቀው እና የእርሱ እንዳልሆነ አሳሳም እየሳመኝ አቋርጦ

«ልትዪኝ ፈልገሽ ያላልሺኝን፣ ልትነግሪኝ ፈልገሽ ያልነገርሽኝን ንገሪኝ፣ ማድረግ ፈልገሽ የቆጠብሽውን አድርጊኝ! » ይሄን ያወራበትም ድምፀት የእርሱ አልነበረም። የሆነ ፊልሞች ላይ ያለ ያፈቀረ ሰውዬ ድምፀት ነበር።

«ያ ማለት በፈለግኩት ቁልምጭ መጥራትንም ጭምር ያካትታል? (ፈገግ እንደማለት ብሎ በጭንቅላቱ ንቅናቄ አዎ አለኝ) እሺ እያደረግንም እንዴት እንደማፈቅርህ ማውራትንም ይጨምራል?»

«የፈለግሽውን! ያለምንም ገደብ!»

ለምን ብዬ አልጠየቅኩም። ሊሰማው የማይፈልገውን ሁሉ በነፃነት እንድለፈልፍ ለምን ነፃነቱን እንደሰጠኝ የምጠይቅበት ማሰቢያ እንዳይኖረኝ ፍቅሩ አቃቂሎኛል። ነገርኩት። ምንም ነገር በዝህች ምድር ላይ ቀርቶብኝ እሱን እንደምመርጥ ነገርኩት፣ ከእርሱ ጋር እስከሁሌውም የመኖር ልዋጭ ከሰጠኝ እናት መሆንን በሱ ፍቅር ለመለወጥ እንደማላመነታ ነገርኩት፣ አብሬው እየኖርኩ ሁላ አቅፌው እየተኛው ሁላ እቅፉ ውስጥ ሆኜ ሁላ እንደምሳሳ ነገርኩት፣ እኔ እንደማፈቅርህ አፍቅረኝ ብዬ አልልህም ምላሹን አልጠብቅም ግን የእኔ ብቻ ሁንልኝ አልኩት፣ አንተ አታፍቅረኝ እኔ ግን በፍቅርህ ስለተሸነፍኩ እንድፈራህ አታድርገኝ አልኩት………. አልኩት …….. ብዙ ነገር አልኩት። በማውቀው የፍቅር ቁልምጭ ሁላ ጠራሁት። እየደጋገመ ያን የእርሱ ያልሆነውን አሳሳም ከመሳም ውጪ ምንም ነገር አላለኝም። ለብዙ ደቂቃ ያለከልካይ ባለኝ አቅምና ችሎታ ሁላ ፍቅሬን ደስኩሬ ሳበቃ የእርሱ ያልሆነ ዓይነት ፍቅር ሰራን …… ምንም ወሬ የሌለው፣ ግን ያለወሬ ወሬ ያለው፣ በጣም ለስላሳ አይነት ነገር ……. በወሬው ምትክ ብዙ መሳም ያለው….. በዓይኖቼ ውስጥ አድርጎ ልቤጋ የሚያደርሰው ዓይነት አስተያየት በየመሃሉ ያየኛል። በሰዓቱ ያልገባኝ ሀዘን እና ስስት ዓይኑ ውስጥ ነበረ። ስንጨርስ እንደቅድሙ ደረቱ ላይ አጥብቆ አቀፈኝ።

ደስ ሊለኝ ነበር የሚገባው አይደል? በምትኩ ነፍሴ ድረስ የዘለቀ የሚያርድ ፍርሃት ነበር የተሰማኝ። አቅፎኝ አስባለሁ። ያስባል። ከብዙ ሀሳብ በኋላ እንቅልፍ ወሰደኝ። ስነቃ ስንተኛ እንደነበረው። የራስጌው መብራት እንደበራ ፣ የምበር ይመስል አጥብቆ እንዳቀፈኝ ፣ዓይኖቹ እንዳፈጠጡ ነው።

«እንቅልፍ አልወሰደህም?»

«አዎ! አልተኛሁም! አሁንማ ነጋ!»

«ምን እያሰብክ ነው?»

«አንቺን!»

«እቅፍህ ውስጥ ሆኜ ስለእኔ ምን ያሳስብሃል?»

አልመለሰልኝም። ተነስቶ ገላውን ተጣጥቦ ሳይስመኝ ቀድሞኝ ወጥቶ ወደስራ ሄደ። ቀኑን ሙሉ መብላትም ማሰብም ልጆቹን ማስተማርም በትክክል ማሰብም ሳይሆንልኝ አሞኛል ብዬ አስፈቅጄ ወደቤት ተመለስኩ። ከስራ እስኪመለስ ጓጓሁም ፈራሁም። የጠዋቱን ሳይሆን የማታውን አዲስ ቢመልስልኝ ፀለይኩ። እየደጋገምኩ <ምናለ ባልነገርኩት?> እላለሁ። ደግሞ መልሼ <አልችልም ነበር> እላለሁ። የሆነኛው እኔ አዲስን ላላገኘው እንደሸኘሁት ነግሮኛል። የሆነኛው እኔ ያን ማመን ስላልፈለገ ጥሩ ጥሩውን ሰበብ ይጎነጉናል። ያልበላሁት ምግብ ሊያስመልሰኝ ያቅለሸልሸኛል። እጄን ያልበኛል። ስቀመጥ ስነሳ ውዬ መጣ። ሲገባ እንደሌላው ቀን አልሳመኝም። ያ የምፈራው አዲስ ሆነ። ጠበቅኩት ከአፉ የሆነ ነገር እንዲወጣ። ምንም ቃል ሳይተነፍስ እራት ቀርቦ በላን።

«ውሎህ ጥሩ ነበር።»
«የተለመደው ዓይነት»

ደሞ የማወራው እፈልግ እፈልግና
«ዛሬኮ አሞኝ ጠዋት ነው አስፈቅጄ የመጣሁት።»

አሞኛል ስለው አጠገቤ ዘሎ ደርሶ የሚነካካኝ አዲስ ምንም ስሜት በሌለው ቀና ብሎ እንኳን ሳያየኝ

«ምነው? ጠዋት ደህና አልነበርሽ?»

እራቱን ሲጨርስ ወደ ላይብረሪው ሄደ። መኝታዬ ላይ ተኝቼ ከአሁን አሁን መጣ ብዬ ስጠብቀው እና በሃሳብ ስባዝን እንቅልፍ ይዞኝ ሄደ። ለሊት 10 ሰዓት ስባንን አጠገቤ የለም። ተነስቼ ላይብረሪው ስሄድ እዛም የለም። ክፍሎቹን እየከፋፈትኩ የሆነኛው ሌላ ክፍል ተኝቶ አገኘሁት። ማልቀስ አማረኝ። እሪሪሪሪ ብዬ ማልቀስ ……. የመብራት መብሪያ እና ማጥፊያ ቀጭ ሲል የሚነቃ ንቁ ሰውዬ በሩን ከፍቼ ስገባ እንዳልነቃ ሰው ረጭ ብሎ የተኛ መሰለ። በሩን መልሼ ዘግቼለት ወጣሁ። ይሄ ቂል ልቤ ደግሞ <አምሽቶ እንዳይረብሽሽ ነው ሌላ ክፍል የተኛው> ይለኛል። ሄጄ አልጋዬ ላይ ተገላበጥኩ እና ነጋልኝ። የተኛበት ሄጄ

«አውራኝ ምንድነው ያደረግኩህ? ማፍቀሬ ሃጥያት ነው? ቆይ እሺ ደግሞስ ላፍቅርህ ብዬ መሰለህ ያፈቀርኩህ? ለየትኛው በደሌ ነው የምትቀጣኝ? ታውቅ ነበርኮ አይደል እንዳፈቀርኩህ? አፌ ላወራቸው ቃላት ነው የምትቀጣኝ?»

ጥያቄም አልነበረም። ልመና ነበር። መጨረሻ ላይ ከአፉ የወጣው ቃል።

«እንፋታ!» የሚል ነበር። ራሴን የምስት መሰለኝ። የሰማሁትም ቃል እኔ ጆሮጋ ሲደርስ አበላሽቼ ሰምቼው መሰለኝ

«ምን? እንፋታ አይደለም አይደል ያልከው?»

«ነው! እንፋታ ነው ያልኩሽ!» ቃላቶቹን ሁሉ ሲላቸው በጭካኔ ነበር።

«እህህ ቆይ ምንድነው ያደረግኩህ? ንገረኝ ምንድነው ምክንያትህ?»

«ምክንያቴን ልነግርሽ አልችልም! »

« በእኔ መፈቀር የዚን ያህል የሚያስጠላ ነገር ነው? ፍቺን የሚያስመርጥ ነው? በመነጋገር ታምን የለ? የማንነጋገረው ነገርኮ ኖሮ አያውቅም! እሺ ፍታኝ ግን ቢያንስ ምክንያቱን እንኳን ማወቅ የለብኝም?»

ተነስቶ ከአልጋው እየወረደ ያሳዘንኩት በሚመስል ሁኔታ በሚያባብል ድምፅ
«ላንቺ ምክንያቴን ለማስረዳት መቼም አልነግርሽም ያልኩሽን ድሮዬን ማስረዳት አለብኝ። እሱን ማድረግ ደግሞ አልፈልግም። ምክንያቱ ለእርሱ በቂ ቢሆን ነው ብለሽ አስቢው። ደግሞ ውላችን አንደኛው አካል መፋታት ከፈለገ……… » ሳይጨርስ ጮህኩኝ እንባ ያነቀው ጩኸት ፣ እልህ ያነቀው ንዴት

«ውል ህግ አትበልብኝ። ውልና ህግ ብቻውን የሰውን ህይወት ቢመራ ዛሬ ያንተ መጫወቻ አልሆንም ነበር።» ጥዬው ወጣሁ።
ከዛ ቀን በኋላ እንደፈለገው እንዲሆን ተውኩት። ጭራሽ ሊያየኝ አለመፈለጉን አከበርኩለት። እኔ ግን በየቀኑ አለቅኩ። በ50 ኪሎሜትር ርቀት ዓይነት እየገፋኝ በ100 ኪሎሜትር ዓይነት ርቀት ወደእርሱ እወነጨፋለሁ። ሁሉ ነገር አቃተኝ። በሳምንታት ውስጥ እያየሁት ሰውነቴ ቀነሰ። መልበስ፣ መብላት፣ መስራት፣ መተኛት …….. ሁሉ ነገር ታከተኝ። ከሳምንታት በኋላ ስለእርሱ ላወራው የምችለው ሰው ትዝ አለኝ። ፀዲ! የመጀመሪያ ሚስቱ! ያኔ ብር ልናቀብላት እቤቷ ሄደን አልነበር?

«እመኚኝ አንቺ ከምታውቂው የተለየ ስለእርሱ የማውቀው ነገር የለም። እኔ የመጀመሪያው ስለሆንኩ የማውቀው ነው የሚመስላችሁ?» ስትለኝ በብዙ ቁጥር የጠራችኝ ከማን ጋር ደርባ እንደሆነ ሳስብ ሁለተኛ ሚስቱ ልክ እንደእኔ ግራ ሲገባት መጥታ አዋርታት እንደነበር ነገረችኝ።

«እኔ ሳገባውም በፍቅሩ ጧ ብዬ ነው ያገባሁት። እንደምታውቂው ነገረ ስራውን ላትወጂው አትችዪም። አስብ የነበረው ፍቅሩን መግለፅ ስለማይችል እንጂ ያፈቅረኛል ብዬ ነበር። ስህተቴ የነበረው ታውቂያለሽ < ብልህ ሴት ወንድን ልጅ ትቀይራለች> በሚል እሳቤ ነው ያደግኩት እና ከትዳር በኋላ ይቀየራል የሚለው እምነቴ ነበር። ተጋብተን መኖር ከጀመርን በኋላ ግን የሚያደርግልኝን የሚያደርገው በባህሪው ጥሩ ሰው ስለሆነ እንጂ በፍቅር አለመሆኑን አወቅሁ። በዛ ላይ ለማያፈቅረኝ ሰው ስል እናት የመሆን ስጦታን መዝለል ልቀበለው አልቻልኩም። የሆነ ቀን እንደምለየው እርግጠኛ ስሆን ተነጋገርን እና ተፋታን!!»

ስለእርሱ ሳወራ ከሚገባው፣ እሱን አብሮ ኖሮ ከሚያውቀው ሰው ጋር ስለእርሱ ማውራት የሆነ ደስ የሚል ስሜት ስለሰጠኝ ከእኔጋር የተፈጠረውን ስነግራት።

«በቃ?» ብላ ጮኸች

«አዎ በቃ!»

«የሆነ ነገርማ አለ። እንደምታፈቅሪው ስለነገርሽው እንፋታ አይልም አዲስ! ሳንጋባ በፊት ጀምሮ እስከምንለያይ ድረስ እንደማፈቅረው በየቀኑ እነግረው ነበር። ከእርሱ ምንም ምላሽ አታገኚም እንጂ ያንቺን ስሜት አይከለክልሽም! Come on ሰውየውኮ አዲስ ነው። የሰው ልጅ ሀሳቡን ሳይበርዝ በነፃነት መግለፅ አለበት ብሎ የሚያምን ሰው ነው። ያመነውን ደግሞ እንደሚኖር ታውቂያለሽ።»

«በእናቴ እምልልሻለሁ ያልነገርኩሽ ነገር የለም። ከዚህ የተለየ ያደረግኩት ምንም ነገር አልነበረም።!»

«ሰብለን ከፈለግሽ ጠይቂያት (ሁለተኛ ሚስቱ ናት) እሷም እንዳንቺ ከገባች በኋላ ነው በፍቅር የበሰለችው። ምላሹን እንደማታገኝ ተስፋ ቆርጣ ፍቺ እስከፈለገች ቀን ድረስ እንደምትወደው ነግራዋለች። ምንም ሊገባኝ አልቻለም። ohhh my God ማሰብ እንኳን አልችልም! ምናልባት የራሱን ስሜት እንዳይሆን መሸሽ የፈለገው? » ብላኝ የሆነ ግኝት እንዳገኘ ሰው ጮኸች።

…………. አልጨረስንም ……………………….

@wegoch
@wegoch
@paappii
Forwarded from Sunset Hiking
#Sunsethiking is hosting a day hike to " Lake Dembel(Ziway)"

💡Hiking Date :- May 22, 2021 (Ginbot 14, 2014)

💵 Hiking Cost:- 874.99 ETB only

🛫Departure: Piasa (Taitu Hotel)
@1:00 Am LT

🎉🎊Package includes🎋🎊

🚣‍♀️ Boat trip
🚍 Transportation
🌲 Bottled water
🌺 Guide + scout
🍂 photography 📷
💐 Breakfast
🏖 lunch
🧜‍♂️ Swimming
🐠 Eating fish(self sponsered)


💦Sanitizer & facemask mandatory!
☘️walking hour: 3 hour (up to 5 km of walking)
Hiking Level: Medium !

for more join the
🎸@sunsethiking👣
🏓@sunsetphotography📸
🍿@sunsethikers

🎫 tickets available at
@Paappii ( +251922303747)
አከራዬ ጋሽ ፋንቱን ፈጣሪ እጄ ላይ ጣላቸው።
ለዛን ቀን ባለቤታቸው እትዬ ዘነቡ ቤተስክያን ሄደው ነበር። እጅግ ሲበዛ አማኝ ናቸው። ከዓመታት በፊት የዓለም ዱብ ዱብ በቃኝ ብለው ቆረቡ ።
ጋሽ ፋንቲሽ ቁረቡ ቢባሉ ወይ ፍንክች እቴ!
ሰው እንዴት ሲሸመግል ፍንዳታነት ይብስበታል። በተለይ አመሻሽ ላይ አንድ ሁለት ብለው ሲመጡ ሀገር ምድሩን በብልግና ይሳደባሉ ። ደግሞ በዛ ላይ ፖለቲካ አይፈሩም... ብልፅግና ን ሙሽልቅ አድርገው ይራገማሉ ። የሰከሩ ጊዜ መንግስትን መራገም ብቻ ሳይሆን ግቢያቸው የበቀሉ የዳማከሴ ችግኞችን እየነቃቀሉ "ይኸው ችግኝ ነቀልኩኝ.. .ምናባህ ታመጣለህ? " እያሉ የሆነ ሰውዬን ይሞሸልቃሉ ። ከዛሬ ነገ ይታሰራሉ ብዬ ብጠብቅም ዝንባቸውን እሽ የሚል አንድ ደህንነት እንኳ የለም (ሼባ አስሮ ማን ይቀልባል? ")- ብለው ንቀዋቸው ነው መሰል !
መንግስት ባያስራቸውም እኔ ግን ትልቅ ጅራፍ ገመድኩላቸው ።
አይናለምን (-የቤት ሰራተኛቸው ነች) ...መቀመጫዋን እንደ ጠንቋይ ድቤ ሲነርቱት እጅ ከፉ ያዝኳቸው። አይናለም የኔን ማየት ስታይ ከበረንዳው ዘላ ወደ ማጀት ገባች (በረረች ብል ይቀለኛል)
ጋሼ ፈገግ ብለው "ልጄ መቼም የወንድ ልጅን ነገር ታውቀዋለህ። ይሄ የራስ ዳሽን ተራራ የሚያህል መቀመጫዋን ስትንጥብኝ አልቻልኩም...አቀለለችኝ" አሉ ።
"ኸረ ያለ ነው አባባ...ትንሽ ግን አመታቱን ከበድ አደረጉት ። ታይሰን እንኳ ይሄን ያህል ቡጢ የሚሰነዝር አይመስለኝም " ብዬ አጫወትኳቸው።
"ኸረ የሷ የጉድ ነው። እንዲህስ ተነርቶ መቼ ይተነፍሳል ? አሁንማ ስፋቱ ብሶበት አንተ የተከራያሀትን ክፍል ሊያክልልህ ነው" አሉኝ ።
በርግጥ ጋሼ ሀቅ አላቸው። ምፕንግስት የአይናለም መቀመጫን ቢያየው አዲስ የፓርክ ፕሮጀክት ይነድፍበት ነበር።
ከዛች ቀን በኋላ ደረት አነፋፌን ላየው ግቢው የኔ የሆነ ነበር የሚመስለው።
እንደ በፊቱ ጋሼ ፊቴን ሲያዩ ቤት ኪራይ ጨምር ይሉኛል የሚል ስጋት የለብኝም። አንዳንዴ እንደውም ማለዳ ላይ በራቸውን ቆፍቁፌ ራሱ "ሰላም አደሩ?" እላቸዋለሁ ።
ለዓመት ያህል እንኳን ቤት ኪራይ ጨምር ሙዚቃህን ቀነስ አድርግ የሚል ግልምጫ እንኳ የለም።
አንድ ቀትር ላይ ግን እትዬ መጡ.. .
የቤቷን ደረጃ እንደ ኤሊ ተንቀራፈው ወጥተው
"ልጄ" ሲሉ ጠሩኝ።
"አቤት ማዘር ..."
"እኔ ምልህ ኑሮ እኮ ደመና ጠቀሰ ...ጢያራ ተሳፍረህ ካልሆነ መልኩ አልታይ ብሏል " አሉኝ። ይህች የዘፈን ዳርዳርታ ቤት ኪራይ ጨምር ሊሉ እንደሆነ ነፍስያዬ ሹክ አለችኝ።
"መንግስታችን ፓርክ ውስጥ ለሚያረባቸው አንበሶች መኖ ብሎ ይሆን ሁሉ ነገር የጨመረብን?" አሉኝ ለጥቀው።
"እንጃ ይሄ የኑሮ ውድነት ለአሳ ነባሪ እንጅ ለአንበሳ መኖ ነው ብለው ነውን?"
ቂ....ቂ...ቂ
እትዬ ተፍለቀለቁ።
"መቼም ትረዳኛለህ.. .ዛሬ አንድ ሺህ ብርም ዋጋ የላት ...ባይሆን ቀጣይ ወር ላይ የበፊቱ ኪራይ ላይ ሺህ ተሁለት ጨምርባት " አሉኝ።
"ማዘር እኔ ዘንዳም እኮ ነው ኑሮ የጨመረው "
"አይ አንተ ትሻላለህ.. . ከቢሮ ስራ በተጨማሪ እንደ ደብተራ ግጥም ምናምን ሞጫጭረህ ትሸጥ የለም ? ራድዮ ላይ እኮ ስትተርክ ሰምቼህ አውቃለሁ "
"ግድየለም ማዘር...እርሶ ብቻዎትን ከሚጨናነቁ... ስለዚህ ጉዳይ አባባን ያማክሯቸው። እሳቸው ይጨምር ካሉ ምን ገዶኝ? " ብዬ መለስኩላቸው።
"ይሁና.. ." እንደ ኤሊ እየተንቀራፈፉ የወጧትን ደረጃ እንደ ጥንቸል ብር ብለው ወረዷት (ንዴት እኮ ነው!)
በነጋታው ከስራ መልስ ቦርሳዬን አንግቼ ወደ ግቢ ስገባ እትዬን በረንዳ ላይ ቡና ሲያፈሉ አገኘኋቸው ።
"እስቲ ሚካኤል አንዴ ትመጣ? " አሉኝ.. .ተጠጋኋቸው ።
"ሽማግሌው ባንተ ጉዳይ ምን እንደነካው አላውቅም ... ተይው ብሎኛል " አሉኝ።
እጅግ አመስግኛቸው ወደ ቤቷ ጀርባ መጓዝ ስጀምር.. .
"ይሄ ምናምንቴያም ደብተራ ባሌን ምን እንዳስነካብኝ እንጃ! " የሚል ማጉረምረም ሰማሁ ።

(ሚካኤል .አ)

@wegoch
@wegoch
@paappii
ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት ….. እኔ የቀጠልኩት
(ክፍል አስር ………. ሜሪ ፈለቀ)

«የእናቱን ለቀናት የቆየ የሚሸት ሬሳ ታቅፎ ከጎሮሮው የማይወጣ ጩኸት ጮኸ። ድምፁ ከጉሮሮው እንደማይወጣ ቢያውቅም በሆነ ተዓምር የሆነ ሰው እንዲደርስለት ተመኘ። በማይሰማ ድምፅ ሊደርስለት የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ ስላወቀ አይኞቹን ጨፍኖ <አምላኬ ሆይ እባክህ ድረስልኝ? እባክህ ድረስልኝ? እባክህ? ……… > እያለ በልቡ የፀለየውን ባይሰማው እንኳን እንባውን አይቶ እንዲራራለት እራሱ እግዚአብሔር ቢያጠራቅመው ለአንድ ክረምት የሚበቃውን እንባ አነባ። እግዚአብሔር ግን ለልቡም ፀሎት ለዓይኑም እንባ መልሱ ዝም ነበር! ዝም!! » የመጨረሻዎቹ ቃላት ላይ ድምፁ እየቀነሰ፣ እየሻከረ መጣ። ከመጀመሪያው ዓረፍተ ነገር በኋላ አልፃፍኩም። ጣቶቼ አደጋ ከደረሰባቸው የእርሱ ጣቶች በላይ ተንቀጠቀጡ።

«ስንት ዓመቱ ነበር?» አልኩት ቀና ብዬ

«አስራ ሁለት» አለኝ። ስሜቱ መረበሹ በግልፅ እያስታወቀበት አስተካክሎ መግፋት የለመደውን ዊልቸር እየገፋ ላይብረሪ ውስጥ ወዲህ ወዲያ እያለ። የህይወት መርሆቹ እና የሚያስብበት ጥግ፣ ሀሳብን የሚገልፅበት መንገድ ሁሌም ሲያስገርመኝ <አንተኮ መፅሃፍ መፃፍ ነበረብህ!> እለዋለው። ሁሌም መልሱ ተመሳሳይ ነበር። <መስራት ሲደክመኝ ወይ ማቆም ስወስን …… በደንብ ጊዜ ሲኖረኝ እፅፋለሁ። አንድ መፅሃፍ ይኖረኛል። እሱም የራሴ ባዮግራፊ ነው የሚሆነው።>

ከቀናት በፊት ከተለመደው የፊዚዮቴራፒ ህክምናው እየተመለስን ድንገት የሆነ መገለጥ እንደበራለት ሰው።

«አሁን ጊዜው አይመስልሽም?» አለኝ። ቀጠል አድርጎ ግራ በመጋባት ለጥያቄ የተሰናዳ አፌን ከመክፈቴ በፊት « መፅሃፌን ለመፃፍ?»

«ጣቶችህ አሁንም ቢሆን ይቀራቸዋል። ዶክተሯን አልሰማሃትም? 100 ፐርሰንት እስኪሆን ጫና እንዳታበዛበት ብላሃለችኮ!»

«አውቃለሁ! እኔ እየነገርኩሽ አንቺ ትፅፊልኛለሽ ብዬ ነበር ተስፋ ያደረግኩት!!»

«መቼ እንጀምር?»

ሚስጥር ማወቅ ነው ያጓጓኝ። እንጂ ከእርሱ ትናንትጋ ራሴው ተላትሜ አዙሪት እንደሚሆንብኝ አላሰብኩም። ሚስጥር ማወቅ የሆነ የመለኮታዊነት ዓለም ተቋዳሽ የመሆንን ስሜት ስለሚፈጥር ይመስለኛል ደስ የሚለው። ስለሆነሰው ከአምላክ ውጪ ማንም ሰው አያውቀውም ብለን የምናስበውን ማወቅ …………

ያቺ ባለፈው የመጣችው ሴት ማንናት? ያቺ ድሮዬ ውስጥ ነበረች ያላት ሴት ምን አይነት ነበረች? በቃ ስለእርሱ ማወቅ። እሱ ድሮዬ ውስጥ አትፈልጊኝ ይለኛል እንጂ ድሮ ቢቀብሩት እንኳን አራሙቻውን በጣጥሶ ዛሬን የማነቅ ጉልበት እንዳለው አውቃለሁ። አንዳንድ ድሮ ይብሱኑ ክስተቱ ከሆነበት ጊዜ ይልቅ ዛሬ ላይ ይበረታል።

«አንቺ ብትሆኚ ታሪክሽን ከምንድነው የምትጀምሪው?»

«ከጡዘት! በህይወቴ ውስጥ ወሳኙ ነው ከምለው ምእራፍ! ከዛ ታሪኩን ወደፊትና ወደኋላ አጫውተዋለሁ። ሲጀመር ግን አንባቢን ሰቅዞ ከሚይዝ ቦታ ነው የምጀምረው።»

«ዝግጁ ስሆን እነግርሻለሁ።» ካለኝ ከቀናት በኋላ ነው ላይብረሪው ውስጥ የተከሰትነው። የምለው ጨነቀኝ። ያለፈውን ለማወቅ ከመጓጓቴ በላይ ገና ሳልጀምረው ልቤ ቀዘቀዘ።

«ለምን አሁን?» አልኩት ጭንቅላቴ ያሰበውን አፌ ሳያስፈቅደኝ

«ለምን አሁን ምን?»

«ለምን አሁን እንዳውቅ ፈለግክ? እንደዛ ላውቅህ ስቧችር ድሮዬ ውስጥ አትፈልጊኝ ብለኸኝ እኔን ግን በድሮህ እየቀጣኸኝ እንደዛ ስለምንህ ዝም ብለህ…….. ዛሬ ለምን?»

በረዥሙ ተነፈሰ እና እየመሰለው ምንም እንዳልመሰለው ሲሆን የሚያመጣትን ፈገግታ ፈገግ ብሎ
«መፃፉን ብትቀጥዪ ታውቂው የለ?»

«እሺ በቃ ወይ ደስ ከሚለው ህይወቱ እንጀምር?» አልኩት።

«ኦኬ! ደስ ከሚለው? ደስ ከሚለው ሆኖ አሁንም ጡዘት ያለበት? » እንደማሰብ ብሎ

« ሰውነቱ ከመቀዝቀዙ የተነሳ ለሰዓታት የተኛበት አንሶላ እንኳን ሳይሞቅ ድጋሚ ተመልሳ በሩን ከፍታ ገባች። እንደቅድሙ በሩን አላባበለችውም። ሆነ ብላ በሩን አስጩኻው ገብታ <ምንድነው ያደረግኩህ? ንገረኝ ምንድነው ጥፋቴ?> (ከዚህ በኋላ ያለውንም አልፃፍኩትም። አቁሜ ግን ቀና ማለት አቅቶኝ እየሰማሁት ነው።) <እንፋታ!> ሲላት ራሱን ሰማው»

ከተቀመጥኩበት ዘልዬ ተነሳሁ። «ይሄ ነው ደስ የሚለው ዘመኑ? ……. እሺ በቃ እኔ ለመፃፍ ዝግጁ አይደለሁም።!» ብዬ ከላይብረሪ ወጣሁ። ማልቀስ ካቆምኩ እጅግ ሰንብቼ ነበር። ማልቀስ አማረኝ።

እሱ የደስታው ጡዘት ብሎ የጀመረበት ታሪካችን የእኔ የመድቀቅ ጡዘት ነበርኮ! በቃ አለም ሁላ ከእርሱ ጋር በአሻጥር ትሰራ ይመስል ቀስ በቀስ የመኖር ማገሮቼ የምላቸው ሲመዘዙ ዓቅም አጥቼ ከማየት ውጪ ምርጫ አጥቼ ተምዘግዝጌ የወደቅኩበት ጡዘት ……

የዛን እለት

«እንዴት ቻልሽው? እንዴት ረሳሽው?» አልኳት ፀዲን

« የማትክጂው ሀቅ <ሰዎች ከአጋራቸው ጋር የሚያስተሳስራቸው የስሜት መጠቃቀም ሲጎድል ለዛ ሰው ያላቸው ስሜት ይጎድላል > የሚለው ነገሩ ልክ ነው። (ሳቅ አለች እዚህጋ የድሮውን በማስታወስ ዓይነት) የሆነ ጊዜ ላይ የተከራከርሽውን ፍልስፍናውን ሁሉ በራስሽ ላይ prove ስታደርጊለት ራስሽን ታገኚዋለሽ። ያለምንም ምላሽ ማፍቀር ይደክማል። የሆነ ቀን ራስሽን ሲደክምሽ ታገኚዋለሽ። ከፍ ሲልም በተጎዳሽው ልክ ስትጠዪው ራስሽን ታገኚዋለሽ።!»

«ይቅርታ አድርጊልኝና the most romantic የምትዪውን ቅፅበት ንገሪኝ? እባክሽ እንደድፍረት አትውሰጂብኝ በቃ ጭንቅ ብሎኝ ነው»

«ኸረ ችግር የለውም በናትሽ ይገባኛል!» ብላ እጄን ስትይዘኝ እንባዬን እንዴት ቁም ልበለው? ደንግጣ አቀፈችኝ። ከሳጌ ጋር እየተናነቅኩኝ አስሬ «ይቅርታ!» እላታለሁ።

«ወይኔ ፀደይ! አዲስ ምንድነው ያደረግከው?» አለች የሆነ ጣሪያው ላይ ሆኖ የሚሰማት ትንሽዬ አምላክ ይመስል። አባብላኝ ስታበቃ።

«የመጨረሻ የምንለያይ ቀን (እሩቅ የተጓዘ ፈገግታ ፈገግ አለች) <ለነበረን የሚታወሱ ትዝታዎች በጣም ነው የማመሰግነው። ለምትወልጃቸው ልጆች የምትገርሚ እናት እንደምትሆኚ አውቃለሁ! ካስፈለግኩሽ የልጅ ልጆች ወልደሽም ቢሆን አስታውሰሽ ከደወልሽልኝ የምችለውን አለሁ። ከእኔ ጋር ላሳለፍሽው ምርጥ ጊዜ እስካሁን ሰጥቼሽ ለማላውቀው ስጦታዎች ምትክ እና ለወደፊት ህይወትሽ መጀመሪያ ይሆንሻል።> ብሎ ንብረቱ ቢሰላ የሚያወጣውን እኩሌታ ገንዘብ የሰጠኝ።» ዝም ስትል ቀጣዩን እየጠበቅኩ እንደሆነ ገብቷት እንደመባነን ዓይነት« that was the most romantic day I ever had with him» ብላ ጨረሰችው።

«አላውቅም! ውላችሁን ስላፈረስሽ ንብረቱን ያልተካፈልሽ ነበር የመሰለኝ!»

«አዲስ ጥሩ ነገር ሰራሁ ብሎ አይነግርሽም! ራስሽ ካልደረስሽበት በቀር! ጥሩ ስለሆነ እንድትወጂው አይፈልግም ራሱን ስለሆነ እንድትቀበዪው ነው የሚፈልገው። ሲመስለኝ ለማንም ሰው ደስታ ሀላፊነት መውሰድ አይፈልግም። ችግሩ ደስታው አይደለም። ቀጥሎ ለሚመጣው ሀዘን ራሱን ተወቃሽ ማድረግ ስለማይፈልግ ይመስለኛል። ለደስታው ሰበብ የሆንኩትን ሰው የሆነ ቀን ለሀዘኑ ሀላፊ ነኝ ብሎ ስለሚያምን ይመስለኛል።»

«ደስተኛ ነሽ?» የሚለው ጥያቄ ከአፌ ከወጣ በኋላ ስላለፈው ይሁን ስለአሁኑ ህይወቷ የጠየቅኳት ራሴው ግራ ገባኝ።
«ውይ በጣም! ከአዲስ ጋር ያሳለፍኩትን ግዜ እወደዋለሁ። እንደሰው ብዙ ያደግኩበት እና የተማርኩበት ጊዜዬ ነው። ስላገባሁትም! ስለፈታሁትም! በሁለቱም ውሳኔዬ ደስተና ነኝ!! አሁን ደግሞ እንደምታዪው {ብላ ከባል እና ሁለት ልጆቿ ጋር የተነሳችውን ፎቶ አሳየችኝ} በጣም! ባሌን እወደዋለሁ! አዲስ በሰጠኝ ስጦታ ነው የራሳችንን ቢዝነስ ጀምረን የምንኖረው። {ሳቅ ብላ } ህይወት ደስ ይላል። »

ስታወራኝ አዲስ እሷ ውስጥ ምን እንደሳበው ለማወቅ አልተቸገርኩም። ሽራፊ አዲስ ውስጧ አለ። የቀለለ ስሜት እንዲሰማኝ ልታስቀኝ ስትሞክር ቆይታ ወደቤቴ ተመለስኩ።

«የአዲስ ሚስቶች ማህበር ነገርማ መመስረት አለብን! ብታዪ አሁን እኔና ሰብሊ በጣም ጓደኛሞች ነን። የሆነ ቀን አብረን ሻይ መጠጣት እንችላለን!» ብላ እንደቀልድ ያወራችውን አሰብኩት። ከእነርሱ ጋር ሻይ መጠጣት አልነበረም ፍላጎቴ! ፍቅር በዚህ ልክ ያቃቂላል? የሚስቶቹን ታሪክ እየሰማሁ ከራሴ ጋር በማነፃፀር መፍታት ያልቻልኩትን እዚህም እዛም የተበታተነ አመክንዮ አጋጭቼ ራሴን ለማፅናናት ነው። እቤት እንደተመለስኩ የጣልኩትን ሰውነቴን ሰብስቤ አፋፍሼ በቁሟ ያለች ሴት ለመምሰል ተጣጥቤ ለባበስኩ።

አራቱን ዓመት አብረን ስንኖር ምን ብለብስ እንደምደምቅለት አስቤው አላውቅም። ልብሴን አይቶ አያውቅም! ሁሌም እኔን ነው የሚያየው የነበረው። አሁን ግን እኔን ማየት አቁሟል። የልብስ ምርጫውንም አላውቅም! አንዱን ሳነሳ አንዱን ስጥል ቆይቼ የሆነ ቀሚስ ለበስኩ። እራት ላይ ተቀብቼ የማላውቀውን ቀይ ሊፒስቲክ ተቀብቼ ተገኘሁ። ለወጉ እልሉን ፊቴ አስቀምጠዋለሁ እንጂ ከሁለት ጉርሻ በላይ ማላመጥ ካቃተኝ ሰንብቻለሁ።

«ደህና ዋልክ?»

«ደህና! ቀንሽ እንዴት ነበር?» ቀና እንኳን ብሎ አላየኝም። እንዲያየኝ ስለፈለግኩ ብቻ

«ዛሬ ፀዲን አገኘኋት!» አልኩት። ባለመገረም ቀና ብሎ አይቶኝ ዓይኖቹ ለውጦቼን በአንድ አሰሳ ካዳረሱት በኋላ ተመልሶ ወደ እህሉ እያጎነበሰ

«ጥሩ ጊዜ አሳለፋችሁ?» አለኝ።

«እ!» አልኩኝ ልቤ ዝቅ እያለብኝ። በልቶ ሲጨርስ ተነስቶ ወደላይብረሪው ሄደ። ወደመኝታ ቤቴ ገብቼ ጉልበቴን አቅፌ ለሰዓታት አለቀስኩ! ሰው ለምን አልወደደኝም ተብሎ ይለቀሳል? ቂልነት እየመሰለኝም ማልቀሴን አላቆምም!! በየቀኑ የማልበላውን እራት ለመብላት የማያየውን መዘነጥ እየዘነጥኩ እቀርባለሁ። የተለመደውን እይታ ገርቦኝ የራሱን እራት በልቶ ወደላይብረሪው ከዛም ወደአንዱ እኔ የሌለሁበት ክፍል ይሄዳል። ለቀናት ለሳምንታት…… የሆነኛው ቀን ወንድሜ በጠዋት ሲበር እቤቴ መጣ። ያየኝ ሰው ሁሉ <ምነው ደህና አይደለሽም?> የሚለኝን አይነት የሰውነት መቀነስ ሾቄ፣ በትክክል ማሰብ ስላቃተኝ ትምህርት ቤት መሄዱን ትቼ፣ ሰኞ እና ቅዳሜ ተምታተውብኝ፣ ጥቅምትና ሀምሌ ተሳክረውብኝ ፣ ቀንና ማታው ተምታቶብኝ ……….. “ ምነው እህቴ ደህና ነሽ ግን?» የሚል ሰላምታ አልነበረም ከአፉ የወጣው።

«እንዴት በቤተሰቦችሽ ትጨክኛለሽ? ጎዳና ቢወጡ ኩራትሽ የሚሆን ነው የሚመስልሽ?» በሚል ወቀሳ ነው የተቀበለኝ። የራሴ ችግር ያለብኝ አይመስላቸውም፣ የራሴ መከፋት ያለብኝ እንደሆነ አያውቁም፣ እኔ በቃ የሆነ የተንጣለለ ቤት ውስጥ የምኖር የኤቲኤም ማሽን ብቻ ነኝ ለእነሱ ሲቸግራቸው እንጂ ቸግሮኝ ይሆን ትዝ የማልላቸው፣ ሲከፋቸው እንጂ ከፍቶኝ ይሆን የማልታወሳቸው፣ ልደርስላቸው እንጂ ግዴታ ያለብኝ ሊደርሱልኝ እሩቃቸው ነኝ። አባቴ ድሮ የተወውን ቁማር በስተእርጅና አዲስ ካፈራቸው ወዳጆቹጋ ሲቆምር ቤቱን አስበልቶ ነው ልክ የእኔ ጥፋት ይመስል በየተራ እየመጡ የሚያስጨንቁኝ።

«ምናገባኝ! ገዝቼ የሰጠሁትን ቤት አላወጣሁበትም ብሎ አይደል በማይረባ ገንዘብ ያስያዘው? እንዴ ቆይ እሺ በምን እዳዬ ነው የቁማር ብር የመክፈል ግዴታ እንዳለብኝ የምታስቡት?»

«ምንም ቢሆንኮ ቤተሰቦችሽ ናቸው።» ያለበት አባባል። ውስጡ ምንአይነቷ ክፉ ነሽ የሚል ቅላፄ ነበረው። ትቼ ነበርኮ! የማልችለውን ለመቻል መጋጋጥ አቁሜ ነበር። ያኔ ያጎበዘኝ አዲስ ነበር። አሁን ግን ግራ ገባኝ የምርም ዝም ብላቸው እንዴት ይኖራሉ? በዛ ላይ ታናሽ እህቴ ስራም ሳይኖራት ለልጁ ወተት እንኳን ከማይገዛ ወንድ ወልዳ እቤት እነሱጋ ናት። በየወሩ ለቀለብ የምቆርጥላቸው ከአዲስ ጋር ተነጋግረን በጋራ ከምንጠቀመው አካውንት ነው። ጭራሽ አባቴ ሲቆምር ቤቱን አሲዞ ስለተበላ 400 ሺህ ብር ካልሰጠኸኝ ብዬ ልጠይቀው? አይሆንም!! ያውም አሁን!!

«አሁን ምንም ማድረግ አልችልም! የዛን ያህል ብር ከየትም ላመጣ አልችልም!» አልኩት። የሆነ እኔጋ ያስቀመጠውን ብር የከለከልኩት እንጂ እርዳታዬን የፈለገ አይመስልም አበሰጫጨቱ። ጥሎ ከቤቴ ወጣ!! የዛን ቀን እራት ሳልቀርብ ተውኩት። አቅም አነሰኝ። የራሴን ስቃይ እየዛቅኩ ስባዝን፣ የቤተሰቤን ሁኔታ እያሰላሰልኩ ስተክን በሬ ተንኳኳ! ከሳምንታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደመኝታ ቤታችን መጣ! ሁሉም ነገር ረጭ አለብኝ!! እረሳሁት! ድካሜን እረሳሁት! ስቃዬን እረሳሁት! ቤተሰቦቼን እረሳኋቸው! እሱ ስጎድልበት ሊፈልገኝ መጣኣ!!

«ደህና ነሽ? እራት ላይ ቀረሽ?» አለኝ በሩ ላይ እንደቆመ። ልለው የምፈልገው ብዙ ነው ጭንቅላቴ ውስጥ የሚራወጠው። <ግድ ይሰጥሃል? ብቀርብም ባልቀርብም ጠረጴዛውን ከከበቡት ወንበሮች ለይተህ አታየኝም ብዬ እኮ ነው የቀረሁት፣ ዓለም ካንተ ጋር አብራ ዞራብኝ ነው፣ ምግብ አልወርድ ብሎኝ ነው> ብዙ ልለው አስባለሁ። አንዲት ቃል ከአፌ ከወጣች ለቅሶዬ እንደሚቀድመኝ ስላወቅኩ ዝም አልኩ። ዋጥ!!

«ፀሃይ ዛሬ አሞሽ እንደዋለ ነገረችን፣ እህልም እየበላሽ እንዳልሆነ፤ ሀኪም ቤት ልውሰድሽ?» <ህመሜኮ አንተ ነህ ሀኪም ምን ይፈይድልኛል? > ማለት እፈልጋለሁ። ከአፌ የሚወጣ ቃል ግን የለም። አጠገቤ ደርሶ አልጋው ላይ ሲቀመጥ ማሰቢያዬ ተንገዳገደ። እጁን ግንባሬ ላይ አድርጎ «ታተኩሻለሽኮ! ሀኪም ቤት እንሂድ?» ደግሞ ተነስቶ አንደኛውን መስኮት እየከፈተ «ቤቱኮ ታፍኗል! ንፋስ ገብቶበት ያውቃል?»

ፊቴን አዞርኩ። ትራሴ ውስጥ ሸፈንኩት። ትንፋሽና ሳጌን ውጬ መዋጥ የማልችለውን እንባዬን ፈቀድኩለት። ለተወሰነ ደቂቃ እንደቆመ ይሰማኛል። ከዛ ቀስ ብሎ በሩን ዘግቶት ወጣ!! እኔም በነፃነት እሪታዬን አስነካሁት። በሚቀጥለው ቀን እራት ስላልሄድኩ ይመጣል ብዬ ጠበቅኩት። ሲመጣ እንደትናንቱ ዝም አልልም! እንዲህ እለዋለው! እንዲያ እለዋለሁ ! እያልኩ ጠበቅኩት! አልመጣም! ከቀናት በኋላ እጅግ በጣም በጠዋት ቀሰቀሰኝ።

«ሰዎች ሊያናግሩሽ መጥተዋል!» እንዲህ ሲጨነቅ አይቼው አላውቅም!! ቁምሳጥኔን ከፍቶ የምደርበው ልብስ እንደመፈለግ አደረገው።

«ማነው በዚህ ጠዋት የሚፈልገኝ?» በደመነፍስ ሲሊፐሬን አጥልቄ ያቀበለኝን ጋውን ለብሼ ወደሳሎን እየሄድኩ የመጡትን ሰዎች ሳያቸው ሳይነግሩኝ በፊት ገባኝ!! አባቴ!! እናቴ እንደትናንት ደውላ አባትሽ ደምግፊቱ ተነስቶበታል ሲነጋ መጥተሽ እዪው ብላኝ ነበር። እሱን ዞሬ አየሁት! መልሼ እነሱን አየሁ! እግሬ መቆም አቃተው! ዘሎ እጆቹን ከስሬ ሲያነጥፋቸው፣ እጁ ላይ ራሴን ስጥል፣ አይኔ ከመከደኑ በፊት ከጉሮሮው የማይወጣ ጩኸት እያማጣ ሊጮህ ሲታገል አየዋለሁ። ስቃይ ያለበት ፊት

........ አልጨረስንም..........

@wegoch
@wegoch
@paappii
ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት ….. እኔ የቀጠልኩት
(ክፍል አስራ አንድ ………. ሜሪ ፈለቀ)

እሱን ዞሬ አየሁት! መልሼ እነሱን አየሁ! እግሬ መቆም አቃተው! ዘሎ እጆቹን ከስሬ ሲያነጥፋቸው፣ እጁ ላይ ራሴን ስጥል፣ አይኔ ከመከደኑ በፊት ከጉሮሮው የማይወጣ ጩኸት እያማጣ ሊጮህ ሲታገል አየዋለሁ። ስቃይ ያለበት ፊት……….

ሰከንዶች ወይ ደቂቃ አላውቅም እጁ ላይ ምንያህል እንደቆየሁ ግን እንደነበርኩ መሬቱ ላይ ስለሆነ የነቃሁት ብዙም ጊዜ እንዳልሄደ ገምቻለሁ። የረጠበ ፎጣ ደረቴና ግንባሬ ላይ አድርጎልኝ እሱ ቁና ቁና እየተነፈሰ ነቃሁ። ተጠርቶ ይሁን ማወቅ ያልቻልኩት ጎረቤት ያለው ሰውዬ ተሸክመው ወደ መኪናው እንዲወስዱኝ ይወተውታል። መርዶ ሊያረዱኝ የመጡት ሰዎች ይተረማመሳሉ። ፀሃይ ፀሎት ይሁን ወቀሳ ያልለየለት ማልጎምጎም ለአምላክም ለእኛም ታሰማለች። መተንፈስ አቅቶት ሲጨነቅ እሱን ያየው የለም። የተንተራስኳቸው እግሮቹ ይንቀጠቀጣሉ፣ ፎጣ የያዙት እጆቹ ይንቀጠቀጣሉ። ግንባሩ ላይ ላቡ ኩልል እያለ ነው። ማንም አላስተዋለም! የሚያወራው አይሰማኝም ግን አፉ ይንቀሳቀሳል። እኔን አፋፍሰው መኪና ውስጥ ካስገቡኝ በኋላ እሱ እላዩ ላይ አስተኝቶኝ ከጎረቤት የመጣው ሰውዬ እየነዳ ወደሆስፒታል ሄድን። መርዶ ነጋሪዎቹ ወደቤት ተመለሱ።

«እኔኮ ደህና ነኝ! ነቅቻለሁኮ!» እለዋለሁ እየደጋገምኩ ባለኝ አቅም የእሱ ሁኔታ ጨንቆኝ። አፉ ይንቀሳቀሳልኮ ግን ቃል አይዋጣውም። ሆስፒታል እንደደረስን ያስመልሰው ጀመር። የታመመው ማን እንደሆነ ግራ እስኪገባ እርሱ ብሶ ቁጭ አለ። በላይ በላዩ እየተነፈሰ ማስመለስ ቀጠለ። ነፍሱ ካልወጣው ብላ እየታገለችው ነው የሚመስለው። ፊቱ ላይ የተገታተሩት ደምስሮቹ ካጠመቀው ላብ ጋር ሲኦልን ያየ ነው የሚመስለው። እኔ ተወስጄ ጉሉኮስ እየተሰጠኝ ዶክተሩ ስለራሴ እየጠየቀኝ ሁላ እሱ ምን ሆኖ እንደሆነ ነው የምጠይቀው።

«panic አድርጎ ነው።» ይሉኛል። እንዲህ የሚባል ነገር ስለመኖሩ ራሱ ዛሬ ነው የምሰማው። ሰዎች ሲደነግጡ በተለይም በህይወታቸው ከዚህ በፊት ገጥሟቸው የነበረ አስፈሪ ወይም አስደንጋጭ አጋጣሚ ከነበር ተመሳሳይ ነገር ሲገጥማቸው ሊፈጠር ይችላል። አንዳንድ ሰዎች ለምሳሌ መድረክ ላይ ሲወጡ ፓኒክ የሚያደርጉ አሉ ……………. በተደጋጋሚ የሚያጠቃቸው ሰዎችም አሉ። ………… ያለማቋረጥ እየጠየቅኩ ስላስቸገርኩ አብራራልኝ። ከሰዓታት በኋላ የራሱን ህክምና ጨርሶ እኔ ወደተኛሁበት ክፍል መጣ………… ፊቱ ጥላሸት መስሎ፣ ከጣረሞትጋ ሲታገል የቆየ አይነት መስሎ ፣ ከፍ ያለው ትከሻው ወርዶ ፣ ቀና ያለው አንገቱ አቀርቅሮ ………… የእርሱ ባልሆነ አረማመድ የእርሱ ያልሆነ አመጣጥ መጥቶ አልጋው ጫፍ ላይ ተቀመጠ። የሆነ ነገር እንደተፈጠረ ቢገባኝም ምን ብዬ እንደምጠይቅ ግራ ገባኝ!


«ምግብ ስለማትበዪ አቅም ጨርሰሽ ነው አሉኝ!» አለኝ ሞገስ በራቀው ቀሰስተኛ ድምፅ ቀና ብሎ ሊያልቅ የደረሰውን ጎሉኮስ እያየው።

«አዎ እኔ ደህና ነኝ! አንተ ደህና ሆንክ?»

«ደህና እሆናለሁ! ትንሽ ማረፍ አለብኝ። ወንድምሽ እየመጣ ነው! ትንሽ እረፍት ካደረግሽ በኋላ ወደ ቤት ይወስድሻል።» አለኝ

«አንተስ?»

«ወደቤት ልሂድ!» በሚያቃጥል እጁ ፊቴን ነካካኝ። መልሶ ጉሉኮስ ያልተደረገበትን እጄን አንስቶ በመዳፉም በአይበሉባውም እያገላበጠ ሳመው። ዓይኖቼን ተራ በተራ ሳማቸው፣ በሹክሹክታ ነገር «ምንም አትሁኚ!» አለኝ። መርበትበቱ በፍፁም የእርሱ አይደለም። «ምንም አልሆንኩምኮ ደህና ነኝ!» አልኩት!!…………………የስንብት እንደሆነ ልቤ ነግሮኛልኮ ላለማመን ታገልኩ እንጂ …………………. ለደቂቃ ከንፈሬን ከሳመኝ በኋላ። ተነስቶ አሁንም ድጋሚ «ምንም እንዳትሆኚ!» ብሎኝ ወጣ!! ልቤ ተከትሎት ሄደ……. ስንብት እንደሆነ ነፍሴ አውቃለች። ሆድ ባሰኝ!! ተከትዬው ሄጄ አትሂድብኝ ማለት አማረኝ። ……

የአባቴን ለቅሶ እንኳን አልመጣም! ቀብር የለ፣ ሳልስት የለ፣ ……. «አዲስ የት ነው? እንዴት ቀብር እንኳን ይቀራል? ምን አይነት ሰው ነው?» ሲሉኝ መልስ አጣሁ። ሀዘኔን አከበደብኝ። የአባቴን ለቅሶ እንኳን በነፃነት እርሜን እንዳላወጣ አሳቀቁኝ። <እንዴት የሚስቱን አባት ለቅሶ አይመጣም?> አይነት አስተያየታቸው አንገበገበኝ። አዲስ የለም! እንኳን ለቅሶ እቤትም የለም! ከአስራ ሁለተኛው ቀን በኋላ ወደ ቤት ልሂድ ብዬ ስነሳ እናቴ ተከትላኝ ከቤት ወጥታ
«ምንድነው ጉዱ? ከባልሽ ጋር ሰላም አይደላችሁም እንዴ? ደግሞስ ምንም ቢሆን ሀዘን ሀዘን አይደል እንዴ? እንዴት ይቀራል?» ስትለኝ መከፋት፣ ንዴት፣ የአባዬ ሀዘን፣ የአዲስ ህመም……… ሁሉም የእስከዛሬ ጥርቅም ግንፍል ብሎ ተዘረገፈ።

«ዛሬ ለቅሶ ቀረ ብላችሁ ለመውቀስ ጊዜ ነው ሰላም መሆናችን የሚያስጨንቃችሁ? ትዳርሽ እንዴት ነው ብለሽ ጠይቀሽኝ ታውቂያለሽ? ደስተኛ ነሽ ወይ ብለሽ ጠይቀሽኝ ታውቂያለሽ? ንገሪኝ እስኪ እናቴ ደህና መሆኔን ለመጠየቅ ወይም ናፍቀሽኝኮ ብለሽ የደወልሽልኝ መቼ ነው? ብር ያለው ሰው ስላገባሁ የናንተ ፍቅርና መጠየቅ የማያስፈልገኝ፣ የሆነ ነገር ስትፈልጉ ብቻ የምትደውሉልኝ፣ ደበረኝ ስላችሁ ምን ጎድሎሽ ነው የሚደብርሽ አትቅበጪ የምትሉኝ፣ እናቱ የሞተችበት እና እናቱ ገበያ የሄደችበት እኩል ያለቅሳሉ እያላችሁ መከፋቴን ቅንጦት የምታደርጉብኝ። ለወቀሳ ሲሆን እና መሃን ነው ያገባችው ባል እያላችሁ ከእህቶችሽ ጋር ለማማት ጊዜ ግን ትዝ እላችኋለሁ።»

ደነገጠች። እንዲህ ተናግሬም ስለማላውቅ ዝም አለች። እንደልጅነቴ ውስጧ ክትት አድርጋ አቀፈችኝ እና «ወይኔ ልጄን!» አለች በቁጭት! «እኔ ልብሰልሰልልሽ!» በቁጭት ማልቀስ ስትጀምር እኔ ብሼ ተገኘሁ። አይኔ ሊፈርጥ እስኪደርስ ተነፋርቄ ወደቤቴ ተመለስኩ። አዲስ አልመጣም!! አሁን ሀሳብ ያዘኝ! ምን ሆኖ ነው? የት ብዬ ልፈልገው? የዛን ቀን የሆነውን እያሰብኩ የሆነ ነገር ሆኖ ቢሆንስ ብዬ ተጨነቅኩ። ስልኩ ዝግ ነው። ቢያንስ እንዴት ስልኩን ለስራ ሲል ክፍት አያደርግም? ስራ ቦታዎቹ በሙሉ ዞርኩ። ሁሉምጋ ለተወሰነ ጊዜ እንደማይመጣ ነግሯቸው ሀላፊነት እና ስራ አከፋፍሎ እንደሄደ ሰማሁ። ቢጨንቀኝ ፀዲጋ ተመልሼ ሄድኩ። ሰብለምጋ ደወልን! በፍፁም እንዲህ አይነት ባህሪ እንደማያውቁበት ቤቱን እንደቤተክርስቲያን የሚሳለም ሰውዬ ለሁለት ሳምንት ከቤቱ የሚጠፋበት ምክንያት ማሰብ አቃታቸው።

ቤተሰቦቼጋ እየተመላለስኩ ብጠይቃቸውም ባሌ ቤቱን ለቆ ከጠፋ ሰነባበተ ብዬ የምናገርበት አቅም አጣሁ። በአባዬ ሞት እማዬ ተሰብራ ስለነበር ቤቷ አይኗ እያየ በጥጋበኛ ቁማርተኛ ሲወሰድባት ዝም ብዬ ማየት ስላቃተኝ ብሩን በጊዜ ገደብ እንድንከፍላቸው ወንድሜ ተስማምቶ መጣ። በ18 ወር ቀስ እያልኩኝ ልከፍላቸው። አዲስ ይመለስልኛል ብዬ አስቤ ከመጣ እና ከጠየቀኝ አስረዳዋለሁ። ካልጠየቀኝ እሰየው ብዬ ወስኜ ነው።

ከአንድ ወር ከሁለት ሳምንት በኋላ ወደቤት ተመለሰ። ሌላ ሰው ሆኖ መጣ! ያ ሆስፒታል የተሰናበተኝ ሰውዬ አይደለም። ያ በፍቅሩ እየጨስኩ ሳልነግረው ሳለ በልዝቡ የሚወደኝ ሰውዬም አይደለም። ያ መጀመሪያ ሳቀው ጤንነት እንደጎደለው ሰው እንጋባ ያለኝ ሰውዬም አይደለም። ያ በመሃል እያለሁ እንደሌለሁ የሚቆጥረኝም ሰውዬ አይደለም። ሌላ ሰውዬ! አዲስ ሰውዬ ሆኖ ተመለሰ።
ሳየው በደስታ ጦዤ ስጠመጠምበት ልክ ምንም እንዳልተፈጠረ፣ ትናንት እዚሁ እንደነበረ ሁሉ፣ ጭራሽ <ምን ሆነሻል?> በሚል ግራ መጋባት እንደዝምብሎ አስተቃቀፍ ለእቅፌ ምላሽ ሰጥቶ ከቅድም የቀጠለው ውሎ እንደሆነ ነገር ቤት ውስጥ ይንቀሳቀስ ጀመር። ስር ስሩ እየተከተልኩ።

«ምን ሆነህ ነው? እሺ ቆይ በደህናህ ነው ይሄን ያህል ቀን? የት እንደነበርክ አትንገረኝ ቢያንስ ደህና ሆነህ መሆኑን አትነግረኝም?» እለዋለሁ።

«ደህና ነኝ አልኩሽ አይደል? ከራሴ ጋር ጊዜ መውሰድ ፈልጌ ነው!!»

«እና እንደዛ ብለህ አትናገርም? ትጨነቃለች ብለህ አታስብም?»

እያፏጨ እቤት ውስጥ ከወዲያ ወዲህ ይላል። ስለምንም ስለማንም ግድ እንደማይሰጠው። የማላውቀው ሰውዬ ነው። ንዴትም፣ መከፋትም ከዛ ደግሞ ያልገባኝ መዋረድም አይነት ስሜት ተሰማኝ። ትንሽዬ እልህም ነገር። ትቼው ወደመኝታ ቤት ገባሁ። ምን ማሰብ እንዳለብኝ ግራ ገባኝ። በምንም መንገድ ይሄን ሰው ማወቅ እንደማልችል ተረድቻለሁ። <አወቅኩት ብለሽ ስታስቢ ተቀይሬ ብታገኚኝ> ያለኝ ይሄንን መሆኑ ነው? እኔ ግን መንቀሳቀስ ቸገረኝ፣ ወዴት ልንቀሳቀስ? በቃ አዲስ ከህይወቴ ወጥቷል ብዬ ልንቀሳቀስ? ይሂድ? ይቁም የማውቀው እንኳን የለኝምኮ። ልሂድስ ብል ወዴት ነው የምሄደው? እናቴጋ? ግራ ገባኝ! ያለኝ አማራጭ የሚሆነውን ዝም ብሎ ማየት ነበር። የሚሆነው ግን ለመረዳት የቸገረ ነበር።ሌላኛውን መኝታ ቤት በቋሚነት እንድታሰናዳለት ለፀሃይ ትዕዛዝ ሰጠ። ጠዋት ከእንቅልፉ ይነሳል ልክ ምንም ዓይነት ነገር በመሃከላችን እንደሌለ የአዘቦት ቃለምልልስ እናደርጋለን። ጓደኛውን ቻው እንደሚል አይነት <ደህና ዋዪ> ብሎኝ ይወጣል። ምሳ ይመጣል። ስራ ቦታ ስለዋለው ውሎ ያወራል። ተመልሶ ይሄዳል። ማታ ይመጣል። አሁንም ልክ እንደ ትክክለኛ ነገር የቀን ውሎውን ወይም የሆኑ ፍልስፍናዎቹን፣ ወይም ስለገጠመው አዲስ ነገር ሲያወራ ይቆያል። እራቱን በልቶ ላይብረሪ ይሄዳል። ከዛ ወደራሱ መኝታ ቤት!!

እሺ ምን ላስብ? አብረን ነን? ወይስ አብረን አይደለንም? ተጣልተናል ወይስ ሰላም ነን? ልክ ያልሆነ ነገር እየሰራ ያለው እሱ ሆኖ ለማውራት እና ለመጠየቅ የምፈራው እኔ መሆኔስ ምን ይሉታል? ከብዙ እንዲህ ዓይነት ልክ የሚመስሉ ልክ ያልሆኑ ቀናት በኋላ ላይብረሪ ተቀምጦ ላወራው ሄድኩኝ።

«እስከመቼ ነው እንዲህ እንድንሆን ያሰብከው? ምነድነው? ምንድነን እኔና አንተ?»

«ምን ሆንን? ምን መሆን ነበረብን? የአኗኗር ዘይቤዬ ላይ አንዳንድ ለውጦች አድርጊያለሁ። አንዳንዱ ካንቺ ያኗኗር ሁኔታጋ ላይሄድ ይችላል። ያው እንደምታውቂው እኔ ማንንም በማስገደድ አላምንም! የግድ መስማማት የለብሽም!» በአዲስ ሰውነት ውስጥ የሆነ ጋጠወጥ ባለጌ ሰውዬ እያናገረኝ መሰለኝ።

«ምን ማለት ነው? »

«ማለትማ ራሴ ላይ ለውጥ ማድረግ ያስፈልገኝ ነበር። ያንን ነው ያደረግኩት! የሰው ልጅ በየሆነ ጊዜው ራሱን upgrade ማድረግ ያለበት አይመስልሽም?»

«upgrade እስከገባኝ ድረስ ወደመሻሻል ነው። ወደመዝቀጥ አይደለም።»

«ኑሮውን የሚኖረው ባለቤቱ አይደል? እየተሻለው ይሆን እየባሰበት የሚያውቀውም ባለቤቱ ነው። እንደቁስ ተጠቃሚው ቼክ አድርጎ በልፅጓል ወይም ቆርቁዟል የሚል ሰርተፊኬት የምንጠብቀውኮ ኑሯችን ሁሉ ለራሳችን ሳይሆን ለሰው ስለሆነ ነው። እኛ ለራሳችን የሚመቸንን ሳይሆን ሰዎች የሚመቻቸውን እኛን ነው የምንኖረው።»

« ፍልስፍናህን ተወው እና ማወቅ ያለብኝን ንገረኝ! ምንህ ነኝ? ምንስ ሆነን ነው እንድንኖር የምትፈልገው?»

«ምርጫውን ላንቺ ሰጥሻለሁ! ምንድነው ሆነሽ መኖር የምትፈልጊው? የራሴን ፍላጎት ደግሞ እነግርሻለሁ። አንድ መኝታ ቤት መተኛትም ምንም አይነት ስሜታዊ መነካካት አልፈልግም። ከዛ በተረፈ አብሮ መውጣት መግባቱ አይጎረብጠኝም። የግድ ካልተዋሰብን አብሬህ መኖር አልፈልግም ካልሽ እሱም ምርጫው ያንቺ ነው።» የሆነ ጋጠወጥ ሰውዬማ የአዲስን ሰውነት ተውሶ ነው እንጂ አዲስ እንዲህ ባለጌ አይደለም። ……………..

........ .. አልጨረስንም.....................

@wegoch
@wegoch
@paappii
ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት ….. እኔ የቀጠልኩት
(ክፍል አስራ ሁለት…….. ሜሪ ፈለቀ)

«ዝናቡ ፀቡ ከምሽቱ ጋር ይሁን ከእርሱ ጥበቃ ጋር አይገባውም። የጠቆረው ሰማይ እያፏጨ ያለቅሳል። ……… »

«የመብረቁ ብልጭታ ምናምን ምናምን ብለህ አትቀጥልማ?» ከት ብሎ ሳቀ

በድጋሚ ሌላ ቀን ባዮግራፊውን ልንፅፍ ተቀምጠን ነው ከምን እንደምንጀምር ላልቆጠርነው ጊዜ የምንጀምር የምንሰርዘው። ዛሬ ባልተለመደ ሁኔታ ጥሩ ሙድ ላይ ነው።

«why not?» አለው አይደል እየሳቀ የሚያወራበት ድምፁ?

«come on you are better than this! ሰማዩ የአህያ ሆድ ሲመስል፣ ፀሃይዋ ብርቱካንማ ሆና ስትንቀለቀል አይነት ጅማሬ አንተ ብትሆን ይስብሃል? ተረኩን እያስኬድከው ባለታሪኩ ያለበትን ቦታና ሁኔታ ከታሪኩ ስሜት ጋር ተያያዥነት ካለው ሳለው። ካለዚያ ግን ምንድነው ዝናቡ፣ መብረቁ ? ዝናብ ከሆነ ሰማዩ እንደሚጠቁርና መብረቅ እንደሚኖር አንባቢው የማያውቀውን እውነት እየደጋገሙ ማደናቆር ነው።»

«አንቺ የራስሽን ባዮግራፊ ብትፅፊ ከምን ትጀምሪያለሽ?»

«ህምምም ካንተ በፊት ለመፃፍ የሚበቃ ታሪክ የለኝም! (አይኑን አሸንቁሮ አየኝ) ምናልባት በየመሃሉ አስተዳደጌን እጠቅስ ይሆናል እንጂ …… ስለዚህ በእርግጠንኝነት የምጀምረው ከሆስፒታል በዊልቸር ይዤህ ስገባ ነው።»

በመገረም እያየኝ «ምን ያህል እንደተለወጥሽ ግን ይታወቅሽ ይሆን? ከሰባት ዓመት በፊት ሬስቶራንት ያገኘኋት ለሰው መኖር የደከማት ምስኪን ሴት፣ ምን እንደምትፈልግ ግራ የገባት ሴት ድምጥማጧ ነው የጠፋውኮ!»

«thanks to you! ሰው ካንተ ጋር ኖሮ ካልተቀየረኮ ፍጥረቱ መመርመር አለበት!"

"Is that a good thing or bad?"

"Honestly both. የሚገርመኝ ሰው እንዴት ሁለቱንም perfect ይሆናል? እጅግ በጣም ደግ ደግሞ እጅግ በጣም ጨካኝ! እጅግ በጣም ሚዛናዊ ከዛ ደግሞ በውስን ነገሮች ላይ ሚዛነ ቢስ! ሁለት ተቃራኒ ፅንፍ ድንቅፍ ሳይልህ ትመታለህኮ!! ከሁለት አንዱ ተፅዕኖ ስር አለመውደቅ ከባድ ነው::"

" ተፅዕኖ አንድ ነገር ነው:: ለውጥ ግን ምርጫ ነው:: በየቀን ተቀን ውሎሽ ውስጥ ጫና በሚያሳድርብሽ ብዙ አይነት ግለሰብ እና መረጃ ተከበሽ ነው የምትውዪው ... ለየትኛው እንደምትሳቢ የምትመርጪው አንቺ ነሽ!! ለምሳሌ በፈጣሪ ላይ ባለሽ እምነት የእኔ አለማመን ያመጣብሽ ለውጥ የለም:: እምነትሽን መለወጥ ምርጫ ውስጥ የሚገባ መሰረትሽ ስላልነበረ:: ... .. አየሽ ለውጥሽ በምርጫሽ ነበር:: ይህችን ምድር ከተቀላቀልን ጀምሮ በህይወታችን በሚያልፉ ሰዎች እና በምናገኛቸው መረጃዎች እና በሚያጋጥሙን ክስተቶች ተፅዕኖ ስር ነን። ምን ያህሉ ናቸው ለለውጥ የተጠቀምንባቸው? ያገኘናቸው መረጃዎች በሙሉ እውቀት ቢሆኑን፣ ያወቅናቸው እውቀቶች በሙሉ ደግሞ ቢለውጡን አስበሽዋል? እንዲለውጡን የፈቀድንላቸው ብቻ ናቸው የሚለውጡን።»

« 100% ለውጥ በእጃችን ነው ማለት የማያስችሉን አጋጣሚዎች የሉም?። ለምሳሌ በህይወታችን የሚገጥሙን አንዳንድ መጥፎ ክስተቶች ባላሰብነው አቅጣጫ ይቀይሩናል። ፈሪ ወይም ደፋር፣ ደካማ ወይም ጠንካራ ያደርግሃል።»

«አየሽ እራስሽ አመጣሽው! ተመሳሳይ የህይወት መሰናክል አንዱን ሰው ትሁት ሲያደርገው ሌላውን ክፉ ያደርገዋል። ተመሳሳይ ገጠመኝ አንዱን ሰው ሲያስተምረው አንዱን ሰው ይገድለዋል። ሰካራም አባት ኖሯቸው አንዱ ልጅ እንደአባቱ ሰካራም ሌላኛው በተቃራኒው መጠጥ የማይደርስበት ዋለ። ሰካራሙ <ከአባቴ ምን ልማር? የማውቀው ስካሩን ነው። የተማርኩት ያንን ነው> ሲል ያኛው <ከአባቴ የተማርኩት ሰካራምነት ምን አይነት ከንቱ አባት እና ባል እንደሚያደርግ ስለሆነ ከመጠጥ በብዙ ራቅኩኝ> እንዳለው ነው። ምርጫ አይደለም?»

ፈዝዤ እያየሁት በጭንቅላቴ ንቅናቄ ልክ ነህ ካልኩት በኋላ እኔ የራሴን ምርጫ እያሰላሰልኩ ነበር። ለምን በእርሱ ክፋት መንገድ መጓዝ መረጥኩ? እርሱን ከነጭካኔው ትቼው ያልተበረዘ ልቤን ይዤ መውጣት አልችልም ነበር?

«እንሞክር ደግሞ?» አለኝ ጥዬው በሃሳብ መንጎዴን ሲያስተውል።

«እሺ ግን ያልገባኝ ያንተ ታሪክ ሆኖ ለምንድነው በአንደኛ መደብ መፃፍ ያልፈለግከው? <እርሱ> እያልክ ስትፅፈው እሩቅ ነው! ውስጥህ ያለ ሰው አይመስልም!»

«አንቺ እንድትፅፊው የምፈልገው ክፍል ስላለ!» ልፅፍ እየነካካሁ የነበረውን ኮንፒውተር አቁሜ አየሁት። ቀጠል አድርጎ «ስንደርስበት እነግርሻለሁ።»

«እንደዛም ቢሆን በተለያየ ምእራፍ ያንተን ባንተ አፍ እኔ እንድሞላው ያሰብከውን ታሪክ ደግሞ በእኔ አፍ መፃፍኮ ይቻላል። ምቾት እንደሰጠህ እሺ!» ብዬ ለመፃፍ አጎነበስኩ።

«እኩዮቼ የትምህርት ቤት የቤት ስራቸውን ወላጆቻቸው እያገዟቸው በሚሰሩበት ሰዓት እኔ እሷን ፍለጋ ከአንዱ መጠጥ ቤት ወደሌላ መጠጥ ቤት እዳክራለሁ። እኩዮቼ በሞቀ አልጋ ውስጥ በዳበሳና በተረት ሲተኙ እኔ እናቱ የምትጠጣበት መጠጥ ቤት ደጅ ላይ ተቀምጬ ዝናቡ ያረጠበው ልብሴ እላዬ ላይ ተጣብቆ እጠብቃታለሁ። ትልቅ መሆንን የምመኘው እንዲህ ባሉ አመሻሾች ላይ ነው። ሁሌም መጠጥ ቤቱ እና ሰዎቹ ይለያያሉ እንጂ ሂደቱ ተመሳሳይ ነው። አቅሏን አጥታ ሰክራ መረበሽ ስትጀምር እየጎተቱ ያስወጧታል። እንደዘመናይ እመቤት አጊጣ ከቤትዋ ስትወጣ ላያት የምሽቷ መጨረሻ ከመጠጥ ቤቱ ተጎትቶ መባረር አይመስልም። <የፈረደበት ልጅ! ና በል ውሰዳት! ምስኪን! ምፅ!> ይሉኛል ሲያዩኝ። ይሄኔ በጣም ትልቅ ብሆን ከመጠጥ ቤቱ አፋፍሼ ራሴ ይዣት ብወጣ ነውኮ ምኞቴ ………… ማንም ባይጎትትብኝ!! ማንም ባያዋርድብኝ! እንደ እኩዮቼ እናቶች <የእገሌ እናት> ብለው ቢጠሩልኝ፣ ደግሞ መጣች ብይሉብኝ። ያ ነበር ምኞቴ ……….

ማታ ስተኛ ተንበርክኬ <ትልቅ ሰው አድርገኝ> ብዬ የህፃን ፀሎት እፀልያለሁ። ትልቅ ብሆን መጠጡን እቤቷ እገዛላታለሁ። ትልቅ ብሆን መጠጥ ቤት መጠጣት ስትፈልግ እስክትጠጣ ጠብቄ ማንም ጫፏን ሳይነካት በፊት ይዣት እገባለሁ። በትንሽዬ ሀሳቤ ከምንም እንደማልጠብቃት አውቃለሁኮ ግን እቤት ተኝቼ ብጠብቃት የምትመጣ አይመስለኝም። አንድ ምሽት እንቅልፍ ጥሎኝ ባልመጣላት መንገድ ላይ ወድቃ የምትቀር ይመስለኛል። ለራሴ ይሁን ለራs4 አባቴ እሱ በብዙ እድሜው፣ በትልቅ አካሉ፣ በተከማቸ ልምዱ እና በዳበረእውቀቱ ሊጠብቃት ያልቻለውን ሚስቱን <እናትህን አደራ> ብሎኝ ሌላ ሚስት አግብቶ መኖር ከጀመረ ሶስት ዓመት አለፈው።

የተለመደ ቀኗ እንዲህ ነው። ጠዋት ስትነሳ ከእንባዋ ጋር ትምህርት ቤት ትሸኘኛለች። <ልጄን ልጠብቅህ ሲገባ ጠበቅከኝ! ይሄ የተረገመ አባትህ ትቶን ባይሄድ !> እያለች ትንሰቀሰቃለች። ከትምህርት ቤት ስመለስ ጭሰቶቿን አንዱን ከአንዱ አምታታ ስባ ራሷን አታውቅም። የምበላው አይኖርም። አንዳንዴ እንግዳ ይኖራታል። እንዲህ ባለ ቀን መኝታ ቤቴ ውስጥ ትዘጋብኝና ትረሳኛለች። የሚርበው ልጅ እንዳላት ትረሳኛለች። በሩን እየቀጠቀጥኩ ካስቸገርኳት ከቤት አስወጥታ ውጪ ትጥለኛለች። የመጠጥ ሰዓቷ እስኪደርስ እጠብቃትና እከተላታለሁ። የባሰባት ቀን «ሂድ አባትህጋ! ምን አድርጊ ነው የምትለኝ? ለምን በፀፀት ታበስለኛለህ? የአባትህ አይበቃኝም? ሂድ ጥሎ መሄድ ከዘርህ ነው ሂድ አንተም!» ትለኛለች።
አባቴ ምን እንደበደላት አላውቅም! በምን ምክንያት እንደተለያዩ እንኳን በዛን የልጅነት ጭንቅላቴ ማገናዘብ አልችልም ነበር። የአባቴን በደል እኔ እየከፈልኩ እንደሆነ ነበር የሚሰማኝ። የሱ ልጅ ስለሆንኩ ብቻ ለሱ በደል መቀጣጫ እንዳደረገችኝ። በልጅነት ትንሽዬ ልቤ የሱን በደል ልክሳት ታገልኩላት። እንደሱ ጥያት አልሄድም ብዬ ልጅነቴን ጣልኩ። የእሷን በደል ትቼ የአባቴ ዘር እንዳልሆንኩ ፣ ትቶ መሄድ በደሜ እንደሌለ ላሳያት በጥንጥዬ አቅሜ ባዘንኩላት። አልቆጠረችልኝም።

የሆነኛው ቀን በቃኝ! ደከመኝ! እናቱን የሚጠብቅ ልጅ ሳይሆን እናቱ የምትጠብቀው ልጅ መሆን አማረኝ!! ልጅ መሆን አማረኝ። እንደልጅ መባባል፣ እንደእኩዮቼ ትምህርት እንዴት ነበር መባል፣ እንደእኩዮቼ ምሳ ምን ይታሰርልህ መባል ……. እኩዮቼን መሆን አማረኝ!! ጠዋት እንደተለመደው አገላብጣ እየሳመችኝ ከእንባዋ ጋር ፀፀቷን ስታጥብ ቆይታ

«ልጄ እወድሀለሁኮ! ጠልቼህኮ አይደለም! ወድጄ አይደለም!» እያለች አገላብጣ ስማ ላከችኝ። የማላስታውሰውን ያህል ሰዓት ተጉዤ አባቴ ቤት ሄድኩ።

ከሶስት ቀን በኋላ ግን ከጭንቅላቴ አውጥቼ ልረሳት አቃተኝ። ጥፋት ያጠፋሁ መሰለኝ። የአባቴ ዘር መሆኔን ያረጋገጥኩላት መሰለኝ። እንቅልፍ አልተኛ ምግብ አልበላ አለኝ። የሆነኛው መጠጥ ቤት ደጅ ጎትተው ሲጥሏት፣ እቤት መድረስ አቅተት መንገድ ላይ ስትወድቅ፣ ስትንገዳገድ አንድ መኪና ሲድጣት፣ ደሞ እኔ ልጠብቃት እንዳልመጣሁ ስታውቅ አባቴ ጥሏት ሲሄድ እየተንከባለለች እንዳለቀሰችው ስታለቅስ………. የማስበው ሁሉ የከፋ የከፋውን ሆነ። በነገታው ለአባቴም ለእንጀራ እናቴም ሳልናገር ተመልሼ ወደ ቤት መጣሁ። በሩን ባንኳኳ አልመልስ ስትልኝ በጓዳ መስኮት ዘልዬ ገባሁ። ሳሎን ተዘርራለች። እናቴ ተስፋ እንደቆረጥኩባት ስታውቅ በራሷ ተስፋ ቆርጣ ሄዳለች። አምላክን ለመንኩት! <አንዴ መልስልኝና እስከሁሌው እጠብቃታለሁ! አንዴ ብቻ መልስልኝ!> አልኩት አልሰማኝም! » ጣቶቼ ኪቦርዱ ላይ እየተንቀለቀሉ እንባዬ ታፋዬ ላይ ይንዥቀዥቃል። ዝም አለ። ዝም አልኩ። ለደቂቃዎች ምንም አላወራንም……… የምፈልገውኮ አቅፌው እሪሪሪ ብዬ ማልቀስ ነው። ግን ከተቀመጥኩበት አልነሳም።

አልጨረስንም!!.............................

@wegoch
@wegoch
@paappii
ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት ….. እኔ የቀጠልኩት
(ክፍል አስራ ሶስት…….. ሜሪ ፈለቀ)

«ሁሉም ሰውኮ አንድ የሆነ ስስ የሆነበት ጎን አለው። ሰዎች ስስ ጎንህን ማወቃቸው ሁሌም መጥፎ ነገር አይደለም። በእርግጥ አንዳንድ ሰዎች ድክመትህን ለመጥፎ ቀን አንተን ለመጣያ ጥይት አድርገው ሊጠቀሙበት ያስቀምጡታል። ለማን ምን ልንገር የሚለው ይመስለኛል እንጂ የሚወስነው ………..» ከአፌ ነጥቆኝ ቀጠለ

«ሁሉም ድክመትሽን የነገርሽው ሰው ድክመትሽን በነገርሽው ሰዓት ይረዳኛል ያልሽው፣ ወዳጄ ያልሽው፣ ያዝንልኛል ያልሽው፣ የኔ ነው ያልሽው…….. ሰው ነው የሚሆነው። አብዛኞቻችን ስንወዳጅ እንለያየን ወይም እንጣላለን ብለን አስበን አይደለም እና ቁስልሽን ቀምሞ አንቺኑ የሚጥልበት ጥይት እንደሚያደርገው የምትረጂው በሆነ ነገር ሳትስማሙ ስትቀሩ እና ስትለያዩ ነው። አየሽ እኔ ደግሞ ትዳርን ጨምሮ ምንም አይነት በሰዎች መሃል ያለ መስተጋብር አንድ ቀን እንደሚፎርሽ አውቃለሁ። ያ ማለት ሳትለያዪም ሚስቴ ያልሻት ሴት ድክመትን ያወቀችው ቀን የተጠቃች ሲመስላት መጀመሪያ የምትመዘው ያንን ስስ ጎንሽን ነው። በዛ ላይ ሰው ምፅ ሲልልሽ እንደሚቀፈው በዚህ ምድር ቀፋፊ ነገር አለ?» አለኝ። የጀመርነውን ባዮግራፊ መፃፍ በመሃል አቁመን ነው ይሄን የምናወራው። ቡና ጠጥተን መጻፍችንን ቀጠልን።

«< ምፅ ! ያላደለው ልጅ! ኖራውም ሞታም ጦስ ሆነችበት። የእናቱን እሬሳ አቅፎ ሲያለቅስ ሰይጣን አጊንቶት ነው!> ይላሉ ሲያዩኝ። የተያዘው አንደበቴ ብቻ ሳይሆን ጆሮዬም የተደፈነ ይመስላቸዋል። የእናቴን ሬሳ ካገኘሁበት ቀን በኋላ ማውራት አቃተኝ። አጋንንት ለክፎት ነው ብለው የአባቴ እህት እና እንጀራ እናቴ በየፀበሉ ይዘውኝ ዞሩ። ዲዳ የሆንኩበትን ምክንያት በየፀበሉ፣ በየመንገዱ <ምን ሆኖ ነው?> ላላቸው ሁሉ ሲያብራሩ አብሬያቸው መሆኔን ይዘነጉታል። እንደገና መሽተት የጀመረው የሬሳዋ ሽታ አፍንጫዬን ያፍነኛል ፣ የተገታተረ ደረቅ ሰውነቷ እጄን ይሻክረኛል፣ ትንፋሽ ያጥረኝና እሰቃያለሁ። <እናቱ ሞታ እሬሳዋን ……..> ማብራራታቸውን ይቀጥላሉ። የሚሰማቸው ሰው <ምፅ ምስኪን!> ይላቸዋል። ምፅ የሚል ሀዘኔታ ሰውነቴን ያሳክከኝ ጀመር። አንድ ዓመት! አንድ ዓመት ሙሉ መናገር አልቻልኩም። የተፀበልኩት ፀበል፣ መስዋእት የቀረበለት አዋቂ፣ ፈዋሽ የተባለ ፀላይ…… ማናቸውም አላዳኑኝም። ማናቸውም ያልገባቸው ካለመናገሬ በላይ መዳን የምፈልገው ጭንቅላቴ ውስጥ ተስሎ ካለው ምስሏ ነበር። በእያንዳንዱ ቀን መስማትም እያቆምኩ እየመሰለኝ ጠዋት ስነሳ ድምፅ መስማቴን እፈትሻለሁ።

በአመቱ አባቴ በጥቆማ አንድ ዶክተር ጋር ወሰደኝ። የተፈጠረውን ነገር ከአባቴ ከሰማ በኋላ የሚፈጠር ነገር መሆኑን አብራራልን። አንደኛው psychogenic mutism ከሚባሉት ውስጥ ነው። ልጆች በተለያየ trauma ውስጥ ሲያልፉ ይከሰታል። ገና አፉን እንደሚፈታ ህፃን ሀ ሁ ብዬ ድምፅ ማውጣት መማር ጀመርኩ። ለወራት ህክምና ስከታተል ቆይቼ ለመጀመሪያ ቀን ቃላት ሰካክቼ ያወራሁ ቀን በቃላት መተንፈስ የፈለግኩት የነበረው።

« ጥያት ባልሄድ ኖሮ አትሞትም ነበር።» የሚለውን ነበር።

አስተካክዬ መናገር የጀመርኩ ቀን መቃብሯ ላይ ሄጄ ስለእሷ ማለት የፈለግኩትን ሁሉ በቃሌ እያልኩኝ አለቀስኩላት። ለሰዓታት አለቀስኩ። የሆነ ነገር ቀለለኝ። የሬሳዋ ሽታ ከአፍንጫዬ ላይ የጠፋ መሰለኝ። እንደማንኛውም ልጅ ማንኛውም ዓይነት የልጅ ህይወት ለመቀጠል ትምህርቴን ካቆምኩበት ቀጥዬ መማር ጀመርኩ።

«እንረፍና እንቀጥል?» ዝም አለ። ዊልቸሩን እየገፋሁ ወደሳሎን መጣን። የሚጨንቅ ዝምታ ዝም አለ። እየደጋገምኩ <ደህና ነህኣ?> እለዋለሁ። ማለት የምፈልገው ብዙ ነበር። ያዘንኩለት ሳልመስል ማዘኔን እንዴት ነው የምነግረው? ይሄን ሁሉ ትናንቱን አውቄ ቢሆን ኖሮ የሆነውን ሁሉ መካኋናችንን ያስቀርልን ነበር? የተወኝን ፣ የገፋኝን፣ የጠላኝን ያስቀርልን ነበር?

«የዛን ቀን እንደምወድህ ባልነግርህ ኖሮ ነገሮች ይቀየሩ ነበር? ያለፉትን መጥፎ ነገሮች ያስቀሩልን ነበር?» አልኩት

«አላውቅም! ማንም ሰው ያለምንም ምላሽ እና ጥበቃ ለዘለዓለሙ አይወድም! (አይወድም የሚለውን በእጁ የትምህርተ ጥቅስ ምልክት ሰርቶ ነው የገለፀው) የጊዜ ጉዳይ እንጂ የሆነ ቀን ትነግሪኝ ነበር። ምላሹንም ትጠብቂ ነበር።»

«እና የዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ መንስኤ እኔ እንደምወድህ መንገሬ ነው?»

«አይደለም። ባትነግሪኝም አውቀው ነበር።»

« እና እሺ ምንድንነበር? ምላሹን ስጠኝኮ አላልኩህም ነበር። ያለምንም ጥበቃኮ ወድጄህ ነበር።» አልኩኝ ድምፄ ሁላ ያኔ ወደነበረው ስሜቴ ሄዶ

«የምታስቢው ዓይነት ሰው ሳልሆንልሽ ስቀር ደግሞ የመጥላትን ጥግ ጠልተሽኝም ነበር።»

«ያንን ነበር prove ማድረግ የፈለግከው? ምንም ዓይነት ሰው ብትሆን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አፈቅርህ እንደነበር?»

«አይደለም!»

«እኮ እሺ ምንድነው?»

«በቃ አንቺ የሌለሽበትን ህይወት መኖር ነበር የፈለግኩት! አንቺ ወደህይወቴ ሳትመጪ በፈቀድኩት መንገድ የማዝዘው ሀሳብና ስሜቴን መልሼ መቆጣጠር ብቻ ነበር የፈለግኩት!» ጮኸብኝ። መጀመሪያ ደነገጥኩ ከዛ ግን ደስ የሚል ስሜት ተሰማኝ። ብዙ ልጠይቀው ፈለግኩ ግን ያ ድሮ እፈራው የነበረውን ዓይነት ፍርሃት ፈራሁት። ዝም አልኩ።

…………….

የዛኔ! ሌላ ሰው ሆኖ ከተመለሰ በኋላ

«ምርጫውን ላንቺ ሰጥሻለሁ! ምንድነው ሆነሽ መኖር የምትፈልጊው? የራሴን ፍላጎት ደግሞ እነግርሻለሁ። አንድ መኝታ ቤት መተኛትም ምንም አይነት ስሜታዊ መነካካት አልፈልግም። ከዛ በተረፈ አብሮ መውጣት መግባቱ አይጎረብጠኝም። የግድ ካልተዋሰብን አብሬህ መኖር አልፈልግም ካልሽ እሱም ምርጫው ያንቺ ነው።» ካለኝ በኋላ

የተኳኋነው እብደት ነው። የአዋቂም የጤናም ያልሆነ እብደት…………….

ምርጫው ያንቺ ነው እንዳለኝ መረጥኩ። አዲሱ አዲስ እስኪበርድለት መታገስ፣ እንደፈለገው ሆኖ የድሮው አዲስ እንዲመለስልኝ ተስፋ ሳልቆርጥ ልጠብቀው ወሰንኩ። አልተመለሰም!! እቤት ሲመጣ እንደእህቱ ነገር ፣ እንደ ጎረቤቱ ነገር፣ እንደ ቤት ደባሉ ነገር ….. አለመቅረብም አለመራቅም የሆነ አኳኋን መሆኑን ቀጠለ። ከህይወቱ ሹልክ ብዬ እንድወጣለት ግን በራሴ እንድወጣለት እንጂ እሱ ውጪ እንደማይለኝ አውቄያለሁ። ብዙ እንደእነዚህ ያሉ የተጃጃሉ ውላቸው ያልለየ ቀኖች ካሳለፍን በኋላ የሆነ ቀን ማታ ላይብረሪ ቁጭ ብለን እያነበብን

«እኔ የምልሽ? በየወሩ ለአቶ ጌትነት የሚል አካውንት ብር የሚላከው ለማንነው? ማነው ሰውየው?» አለኝ። አባቴ ቤቱን በቁማር አስይዞት እንደነበር እና እሱን እየከፈልኩ እንደሆነ አስረዳሁት።

«ታዲያ ቢያንስ ልታሳውቂኝ አይገባም ነበር? እኔ ምን አግብቶኝ ነው የአባትሽን ቁማር ቅሌት የምሸፍነው? ከዛሬ በኋላ ከገንዘቤ ላይ በዚህ ሰበብ ቤሳቤስቲን እንዲነሳ አልፈልግም።» አለኝ

የዛን ቀን ያቺን ሰዓት ለመጀመርያ ጊዜ እልህና ፍቅሬ ፣ ፍቅርና የጥላቻ ዘር ውስጤ ተሳከረ

አልጨረስንም ...........

@wegoch
@wegoch
@paappii
ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት ….. እኔ የቀጠልኩት
(ክፍል አስራ አራት…….. ሜሪ ፈለቀ)

«ታዲያ ቢያንስ ልታሳውቂኝ አይገባም ነበር? እኔ ምን አግብቶኝ ነው የአባትሽን ቁማር ቅሌት የምሸፍነው? ከዛሬ በኋላ ከገንዘቤ ላይ በዚህ ሰበብ ቤሳቤስቲን እንዲነሳ አልፈልግም።» አለኝ

የብዙ ሰዎች ባህሪ መሰለኝ። እየተገፋን እና በፍቅር የወደቅንለት ሰው በማይገባን መልኩ ክፋትና ጥላቻ እያሳየን ያየነውን መመዝበር አምነን ልባችንን ከመሰበር እንደመጠበቅ ይልቅ እዛው እንቆያለን። ምክንያቱም ከሰውየው እውነተኛ የሚታይ ባህሪ ይልቅ ሰውየው ነው ብለን በልባችን የሳልነውን ምስል እናምናለን። ከዛም አንዴም አይደለም ሁለቴም አይደለም። እየደጋገመ በማይገባን መንገድ ክፉውን እሱነቱን ያሳየንና ልባችንም ተሰብሮ ፣ ሞራላችንም ደቆ፣ ከክብራችንም አንሰን ፣ በፍቅር ልባችን ውስጥ የተሳለውንም ምስል በአውሬ ተክተን ………… ያኔ እናምናለን። በዜሮ አማራጭ እና በሚያነክስ ልብ እንለያያለን።

«በየወሩ የሚቆረጠው ብዙ ብር ስላልሆነ ነበር ያልነገርኩህ። ድሮም ቢሆን ከ50 ሺህ ብር በታች የሆነ ገንዘብ እንዳሳውቅህም ግድ ሰጥቶህ አያውቅም፤ ጠይቀኸኝም አታውቅም ነበርኮ! እውነት ለማውራት ብሩ የሚከፈልበት ምክንያትም አሳፍሮኝ ነበር ያልነገርኩህ።»

«እሱ ድሮ ነዋ! ድሮ አልሽውኮ እራስሽም! ራሴ ላይ ለውጥ አድርጌያለሁ አልኩሽ አይደል? ይኸኛው አዲስ ግድ ይለዋል። አንቺን እንጂ ቤተሰብሽን የማኖር ግዴታ የለብኝም።»

«ምን አድርጌህ ነው ግን ቆይ እንደዚህ የጠላኸኝ? ለምንድነው ክፉ እንደሆንክ ልታሳየኝ የምትፈልገው? ምንድነው ሀጥያቴ? ልወቀው በደሌንና እንድተውህ አይደል የምትፈልገው እተውሃለሁ። ምክንያትህን ብቻ ንገረኝ! እንዳምን ላደረግከኝ ማንነትህ በፍቅር ከመውደቅ ውጪ ምንድነው የበደልኩት? ጠልተኸኝም፣ ገፍተኸኝም ደግሞ <ምን በድዬ ነው?> እያልኩ እራሴን ስጠይቅ እንድኖርም ፈርደህብኝ አላሳዝንህም?» አልኩት ላለማልቀስ ከራሴ ጋር ግብ ግብ እየፈጠርኩ

« አንቺ ነው ብለሽ ጭንቅላትሽ ውስጥ ስለሳልሽው ሰው ተጠያቂ አይደለሁም። ራሴን ስለመሆን እንጂ ሰዎች የሚስሉትን ምስሌን ስለመሆን ግድ የለኝም።» ብሎኝ ጭራሽ ስለጠየቅኩትም የሆነ ያጠፋሁ ነገር አስመስሎት ያነብ የነበረውን መፅሃፍ የመወርወር ያህል ጠረጴዛው ላይ ጥሎት እየተበሳጨብኝ ወጣ!

ሲጀምር ፍቅሩን ፣ገላውን፣ ትንፋሹን ፣ እቅፉን …….. ራሱን ነበር የከለከለኝ እንጂ በንግግር የሚያስከፋኝን ወይም የሚጎዳኝን ነገር ተናግሮ አያውቅም ነበር። ሳይናገር ግን እንድፈራው ያደርገኝ ነበር። ራሱን ከኔ በማራቅ ፍቅርን ስለከለከለኝ ተስፋ ቆርጬበት ጥዬው የምሄድ ነበር የመሰለው ይመስለኛል። በዚህኛው ጊዜ <ይወደኛል! ያሳለፈው የሆነ መራራ ህይወት ፍቅርን እንዲፈራ አድርጎት ነው!! ምን ያህል እንደማፈቅረው ሲያውቅ ይመለስልኛል።> የሚል ሰበብ ነበር ለራሴ የምሰጠው። እየገፋኝ እና እንደሌለሁ እየቆጠረኝ እንኳን ስር ስሩ ከማለት ውጪ የሱን ልብ ልረታበት የምችልበት ምንም መላ ላመጣ ባልችልም በሆነኛው ተዓምር ብቻ የፍቅሬ ልክ እንዲገባው ተስፋ አደረግኩ። አልገባውም ወይም እንዲገባው አልፈለገም! ይሄኛው መንገድ እንዳልሰራ ሲያውቅ ንግግራችንንም በጥላቻ ይለውስብኝ ያዘ። ምን ያህል እንድተወው እንደፈለገ ቢገባኝም እዚህኛው ነጥብ ላይ ሰበቤ ብዙ ነው። <ይወደኛል> የሚለውን <ሊያየኝ አይፈልግም> በሚለው ተክቼዋለሁ።

የዋሁ ልቤ በልቤ የተሸከምኩትን ፣ በፍቅሩ የታመምኩለትን ፣ እኔ ራሴን ስስትበት ፓኒክ ያደረገውን፣ በልግስናው ከማንም የማላወዳድረውን ፣ ለታይታ የማይኖረውን ፣ ያ < እንባሽን ከማይ ሳምንት ፀሃይን ባላይ> የሚለኝን ፣ እንደእኔ ዓይነት ባል የታደለች ሴት የለችም ብዬ የምጎርርበትን ፣ ከነግራ ማጋባቱ የማብድለትን ………… ያን አዲስ ምስሉን ከልቤ ሳይሸረሽረው፤ ክፋቱ በዝቶ መልካም ትዝታዎቼን ሳያጠፋብኝ ፤ እንዳፈቀርኩት ማቄን ጨርቄን ሳልል እብስ ብዬ መጥፋት ያምረዋል። ሌላኛው ልቤ ደግሞ ከጭንቅላቴ ጋር ይማከር እና ከዛስ? ይለኛል።

ከዛስ? በዚህ እድሜዬ እናቴ ቤት ልገባ? ምን ቤት አላት? ቤት ገዛሁልሽ ብያት ከቀበሌ ቤቷ አስወጥቻታለሁ። ሟች ባሏ ያስያዘባትን ቤት እዳ እከፍልልሻለሁ ብያት ከዚህ በኋላ ልከፍልላት አልችልም። ትቼው የነበረውን ማስተማር እቤት እየዋልኩኝ ስብሰከሰክ ከመዋል ብዬ ድጋሚ የጀመርኩት ቢሆንም ደመወዜ እንኳን የቤቱን እዳ ሊከፍል ቤት እንኳን ብንከራይ የቤት ኪራይ አይሸፍንም! ምንስ ብዬ ነው አሁን የምነግራት? ከቤቷ ወጥታ የት ትኖራለች? የአባዬ የጡረታ ብር አይደለም የቤት ኪራይ ሊከፍልላት ብቻዋን እንኳን ብትሆን የቀለብ አይችላትም እንኳን የታናሼ እና የልጇ ሆድ ተጨምሮ። ታናሽ እህቴንስ ምንድነው የምላት? በቃ ከዛሬ በኋላ ልጅሽን የምታደርጊውን አድርጊው ልረዳሽ አልችልም ነው የምላት? አንዳንዴ ምናልባት እንደመጀመሪያ ሚስቱ ጥዬው ብሄድም ባዶ እጄን አይሰደኝም ብዬ አስብ እና ከእርሷ ጋር በሰላም ተከባብረው እንደተለያዩ ሳስበው እጣዬ እንደሁለተኛ ሚስቱ አጨብጭቦ በባዶ እጅ መቅረት ሊሆን እንደሚችል እጠረጥራለሁ። (ሰብለ ፍታኝ ስትለው ትነዳው ከነበረ መኪና ውጪ ምንም ሳይሰጣት ነው የፈታት።) እኔ ደግሞ እሱጋ ያለኝን ቦታ እንኳን ለይቼ አላውቀውም። ይጠላኛል? ይወደኛል? እንደምንስ ይሆን የሚያየኝ?

ከዛ በኋላ የተኳኋነው እብደት ነው። የአዋቂም የጤናም ያልሆነ እብደት……………. አልኳችሁ አይደል?

ይሄን ሁሉ ሀሳብ ደምሬ ቀንሼ እና አባዝቼ ደግሞ እልህ ይይዘኛል። በየቀኑ በቃላት ሊገፋኝ በጣረ ቁጥር ፍቅሬ ከክምሩ ትንሽ በትንሽ እየተናደ …….. ንዴት እና ቁጣ በምትኩ ትንሽ በትንሽ እየተቆለሉ ………. ንዴት እና ፍቅሬ እኩል መጠን ላይ ሲደርሱ ጥላቻ እና እልህ ተወለዱ። አንድ ብለው መሰረታቸውን አኖሩ ……… እፈራው ነበር። ለካንስ እፈራው የነበረው ስለማፈቅረው ነበር። የምፈራው የነበረው እንዳላጣው ስለምንሰፈሰፍ ነበር። ልክ ፍቅሬ መጉደል ሲጀምር የምፈራው ነገር እኩል እየቀነሰ መጣ።

ሁለት ወር የሰውየውን ብር መክፈል ሲያቅተኝ ሰውዬው ለእማዬ ማስጠንቀቂያ ላከ። ከዚህ በላይ መሸሽ የምችለው ሀቅ ስላልነበረ እማዬንም ሁሉንም ሰብስቤ እውነቱን ነገርኳቸው። ሁሉንም ጥቃቅን ነገር ባላወራቸውም አዲስ ደስተኛ ስላልሆነ እንዳልከፍል እንደከለከለኝ ነገርኳቸው። በወንድሞቼ ዓይን ስወርድ ታየኝ። እማዬ ግን ገባት። እንደውም ለብቻዬ ጠርታ ደህና መሆኔን ጠየቀችኝ። ከወንድሞቼጋ ተጋግዘን ልናኖራት ቤት ተከራየንላት። እቃዎቿን ስትሸጥ አይኗን ማየት ስለከበደኝ አላገዝኳትም። መከፋቴን፣ ማፈሬን ፣ ማነሴን የምነግረው ሰው ስላልነበረኝ መኝታ ቤቴን ዘግቼ ተንሰቀሰቅኩ። ቤቷን የለቀቀች ቀን ግን የሆነችውን መሆን ሳየው ቤቷን ለማጣቷ ሰበቡ አባቴ ቢሆንም ላተርፍላት ባለመቻሌ ራሴን ጠላሁት። <ልጄ ዓለሜን እንዳሳየሽኝ ድመቂ > ብላ የመረቀችኝ እናቴ ዓለሜ ያለችውን ቤቷን ራሴ የቀማኋት መሰለኝ። ከታናሽ እህቴ ጋር እና ከልጇ ጋር አንድ መኝታ ቤት ያለው ኮንዶሚንየም ነበር የተከራየንላት። በህይወቴ የተመኘሁት አንድ ነገር ለቤተሰቦቼ ኩራት መሆን ነበር። በቃ ሌላ ምኞትም ህልምም አልነበረኝም:: እስከማስታውሰው ለራሴ በሆንኩት ብዬ አጥብቄ የተመኘሁት የለኝም::

«እንዲህ ያለው ቅሌትስ በዘርም አይድረስ! በመምሻ እድሜዋ አሳይቶ ነሳት!» እያሉ ጎረቤቶቿ ከንፈራቸውን መጠጡላት።
2024/09/22 22:33:52
Back to Top
HTML Embed Code: