Telegram Web Link
ላፍነው የማልችለው አይነት መከፋት ከፋኝ:: መኖር የምመኝለት ዓላማ ጠፋኝ:: ለቤተሰቤ መሆን አልቻልኩበትም: ወይም መፅናኛዬ የምለው ልጅ እና የራሴ ቤተሰብ የለኝ: ወይም በፍቅሩ እካሳለሁ የምለው ባል የለኝ : ወይም ገና ወጣት ነኝ ነገ የተሻለ ነው የምለው ጊዜ የለኝ : ልደበቅበት የምለው ሙያ እና ህልም የለኝ...... ምንድነው የምኖርበት ዓላማ??

«አምላኬ ሆይ ለምን አሳይተህ ነሳኸኝ? እሺ እኔን ከሆነ መቅጣት የፈለግከው እኔን አትቀጣኝም? ለምን እናቴን? ለምን በስተእርጅና እሷ ትከፋ? ምንድነው ያደረግኩህ ?? ለምንድነው አንድም በህይወቴ የሰመረ መንገድ የሌለኝ??» እግዚዘብሄርን ማማረር ያዝኩ። እናቴን የተከራየችው ቤት አስገብቻት የመጣሁ ቀን .... አዲስ ቀድሞኝ እቤት ገብቶ ነበር:: ... መፍራቴ ትቶኝ የለ??

"በነገርህ ላይ! ምንም እንደማይመስልህ አውቃለሁ ግን እንደው ለጠቅላላ መረጃ እንዲጠቅምህ እናቴ ቤቷን አጥታለች:: .. ዛሬ ኮንዶሚንየም ቤት አስገብቻት መጣሁ::" አልኩት:: ዝም አለ:: ህመሜን እንዴትም ላጋባበት እንደማልችል ባውቅም መከፋቴ ደረቴ ላይ ተነባብሮ ካልወጣሁ ብሎ እያነቀኝ ስለነበር ዝም ማለት አቃተኝ::

"የ48 ዓመት ባሏን እና ጏደኛዋን ባጣች በወራት ውስጥ ቤቷን አጥታ : እቃዋን ሸጣ: በስተርጅናዋ መከፋት ሲሰብራት ብታያት ጥሩ ነበር:: ምንም አይመስልህ እንደው ታውቀው ነበር::" እያወራው ያለሁትኮ ከእናቴ ገንዘቡን ስላስበለጠ እንዲሰማው ላስፀፅተው ነበር:: መከፋቱም ፀፀቱም በእኔው ብሶ እንባዬ ወሬዬንም አደፈራረሰው እና እየሮጥኩ መኝታ ቤቴ ገባሁ:: ህቅ ህቅ ብዬ ተንሰቀሰቅኩ:: .... ለቀናት እየሸሸኝ መሰለኝ ወይም አስጠልቼው እንዳንገጣጠም በተቻለው መጠን ጣረ:: የሆነ ቀን ጠዋት ተገጣጠምን:: አላውቅም ምን እንዳስቆጣኝ ብቻ ግን ውስጤ ያለው እልህ እና ቁጣ ነው::

" ጥላኝ ትሄዳለች ብለህ አትድከም! ስምንት ዓመት እስኪሆን መታገስ አያቅተኝም:: በውላችን መሰረት ግን አንተ ፍቺ ከፈለግክ ይስማማኛል::" አልኩት ልክ እንደእሱ እኔም ለእርሱ ምንም ስሜት እንደሌለኝ ማሳየት ነበርኮ የምፈልገው ግን ድምፄ ልምምጥ እንጂ ቆራጥ ውሳኔዬ እንዳልሆነ አሳበቀብኝ::

ከ8 ዓመት በፊት ፍቺውን የፈለገው እሱ ከሆነ ንብረቱን እኩል የማካፈል ግዴታ አለበት:: ... በልቤ 'እሺ' ቢለኝ የሚለውን ሳስብ ገና ደስ እንደማይለኝ ገባኝ:: እሺ ብሎ ቢፈታኝ ገንዘቡ እሱን ማጣቴን ይክሰዋል? አላውቅም! እሺ አሁንስ እሱ አለኝ ነው የሚባለው?? ምን እንደምፈልግ ሁሉ ግራ ገባኝ:: ሁለቱም ትርጉሙ ያማልኮ .... አንቺ በህይወቴ ውስጥ ከምትኖሪ ግማሽ ልፋቴን ውሰጂና ውጪልኝ መባል ወይም ግማሽ ልፋቴን ከምሰጥሽማ እንዲሁ ጥዕም አልባ ቀን ብኖር ይሻለኛል መባል...... ሁለቱም ያማል:: ... ሁለቱንም በቃሉ አልመለሰልኝም::..... ከጊዜ በኃላ ግን በተግባር ምርጫው ሁለተኛው እንደሆነ አሳየኝ::

ሳምንት ሳምንትን ሲወልድ የጠላሁት ሁሉ መሰለኝ:: ... ንግግራችን እየቀነሰ መጣ:: የሆነ ቀን ምሽት ግን በቁሜ ተኩሶ ልቤን የመታኝ ያህል ተሰማኝ:: ... አምሽቶ ከሴት ጋር መጣ!! አንድ ቤት ከማደራችን ውጪኮ የእኔ እንዳልሆነ አውቃለሁ! የዛን ቀን ግን ሲገባኝ .... ይመለሳል የሚል ተስፋዬ አልሞተም ነበር:: የትኛው ይበልጥ እንዳመመኝ አላውቅም!! እዛው እቤቱ አስቀምጦኝ ሴት ይዞ መጥቶ ክብር የማይገባኝ ምንም እንደሆንኩ የነገረኝ ወይም ለዘለአለም እንደሄደ ማወቄ!! መኝታ ቤት ሆኜ የፀሃይን ያልሆነ የሴት ሳቅ ሰምቼ መኝታቤቴን ከፍቼ ብቅ አልኩ:: ወደእርሱ ክፍል ደረጃውን እየወጡ ነበር:: ... ተከትያቸው ወጥቼ ልጅቷን 'ሚስት እንዳለው ታውቂያለሽ?' ልላት አስቤ ነበር:: ወይም ከእርሱ ጋር 'ምን እያደረግክ ነው?' ብዬ ልጣላ.... ወድያው ጭንቅላቴ ውስጥ የመጣው ብዙ ነበር:: ... ይበልጥ ራሴን ማዋረድ መሰለኝ:: መኝታ ቤቴን ዘግቼው እንኳን የሷ ሳቅ ይሰማኛል:: ... ሆነ ብሎ እንድሰማ እስኪመስለኝ የመኝታ ቤቱን በር አልዘጋውም:: .... ከእነሱ እንዳላየኃቸው እንዳልሰማኃቸው መስዬ መኝታ ቤት ውስጥ ተደበቅኩ ከራሴ ግን የት ልሽሽ??

አዲስ የፈለገውን እና ያመነበትን ነገር የሚያደርግ ሰው ነው:: ነገር ግን የሚኖራቸው መርሆች ያሉት ሰው ነው:: ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ወሲብ ላይ ያለው መርህ ነው::

"በፍቅር ካላመንክ: ልጅ ካልፈለግህ: ወሲብን በፈለግከው ጊዜ ማግኘት ትችላለህ ለምን ትዳርን ትደጋግማለህ? ያውም የዓመት ገደብ እያበጀህ "ብዬው ከመጋባታችን በፊት

"እኔ ሴሰኛ አይነት ሰው አይደለሁም!! በየሄድኩበት ባየኃት ሴት ሁሉ ደሜ አይሞቅም:: ከተለያየ ሴት ጋር መባዘን አይመቸኝም:: ከተመቸችኝ ሴት ጋር ባደርገው ነው ደስ የሚለኝ:: ከወሲብ በተጨማሪ ማሰብ የምትችል አብሬያት ብኖር ደስ የምትለኝ ሴት ስትገጥመኝ በሳምንት ሁለቴ ከቤቷ እየጠራሁ ላሽኮረምማት አልፈልግም:: አብሬያት መኖር ደስ ይለኛል እስክንሰለቻች... ይሄን ስልሽ ለሴክስ ብዬ ብቻ ሴት ቀርቤ አላውቅም እያልኩሽ አይደለም:: ግን ለሴክስ ብቻ አብሬያት እንዳለሁም እያወቅኩ ቢሆን እሷ ከህይወቴ ካልወጣች ከሌላ ሴት ጋር አልሆንም ያ መርሄ ነው::" ብሎኝ ነበር::

ቅናት ቆዳዬን ቆጠቆጠኝ:: ... የሳመኝ ከንፈር የሆነችዋን ሴት እንደሚስማት ማሰብ : ከኔ ጋር የሰራቸውን ፍቅሮች ከሆነችዋ ጋር ሊሰራው እንደሆነ ማሰብ .... ያውም እዚሁ አንድ ደረጃ ወጥቶ አናቴ ላይ.... የማይታክተኝን ለቅሶዬን ተንሰቀሰቅኩት:: ... አልወጣልሽ አለኝ:: ... ... በዛ ምሽት እናቴጋ ሄድኩ:: ስታየኝ ደነገጠች:: 'ባሌ እቤቴ ሴት ይዞ መጣብኝ!' ብዬ ልነግራት አፈርኩ:: 'ተጣላን!' ብቻ ብያት መንሰቅሰቅ ጀመርኩ::

"ባልና ሚስት ይጋጫል... እኔና አባትሽ .." ብላ የግጭት አፈታት ብልሃት ስትመክረኝ አደረች:: በነገታው እሁድ ነበር:: ከእናቴጋ ቤተክርስትያን ሄጄ ከሰዓት አካባቢ ወደ ቤቴ ተመለስኩ:: ሳየው ፍቅሬ ቁጣን አልፎ ጥላቻን ... ጥላቻን አልፎ በቀልጋ መድረሱ ገባኝ.... መናደዴን እንዲያውቅም አልፈለግኩም:: ድምፄ ልናገርበት በፈለግኩት ትክክለኛ ድምፀት ታዘዘልኝ....

"ቢያንስ ስትዳራ መኝታቤትህን ዝጋው ቢበዛ ደግሞ ማታ 5 ሰዓት ላይ ለመንደር የሚሰማ ሳቅ እንደማይሳቅ የምታውቅ ኩል ሴት የምትውልበት ዋል::" ብዬው ለፀሃይ ሲመሽ እራቴን መኝታ ቤት እንድታመጣልኝ እንደምፈልግ ነግሬያት መኝታ ቤት ገባሁ::

...... አልጨረስንም........

@wegoch
@wegoch
@paappii
ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት ….. እኔ የቀጠልኩት
(ክፍል አስራ አምስት…….. ሜሪ ፈለቀ)

ሲመስለኝ ፍቅርም ይረታል። በቁጣ ፣ በክፋት እና በበቀል ይረታል። ወይም ምናልባት እሱን ከማይመስሉ ባህርያት ጋር ግብ ግብ አይገጥም ይሆናል እና ቦታ ይለቃል። ቀስ በቀስ ቁጣ እና መከፋቴ ፍቅሬን እየሸፈነው መጣ። እዚህ ነጥብ ላይ የማስበው ሁሉ በምን መንገድ እኔን ማጣቱ እንዲቆጨው፣ እንዲፀፀት፣ የእግር እሳት እንዲሆንበት እንደማደርገው ነው። በቀል መሆኑ ነው!! በምትኩ በነገረ ስራው የምነደው እኔ ነኝ። ያቺን ከሱሉልታ ፒያሳ የሚሰማ ሳቅ የምታንባርቀውን ሴት እቤቴ ይዟት ከመጣ በኋላ ለሳምንታት ቃላት አልተቀያየርንም። የተያየነውም ለሆኑ ሰከንዶች ያህል ቢሆን ነው። ምግቤን ክፍሌ አስመጣለሁ። ማንበብ የምፈልጋቸውን መፅሃፍት ክፍሌ ይዤ እገባለሁ። (እሱ ከሰጠኝ ስጦታዎች ሁሉ ሳመሰግነው የምኖረው ከማንበብ ጋር በፍቅር እንድወድቅ ስላደረገኝ ነው።) የሆነ ቀን እሁድ ከሰዓት ቢያንስ በወር አንዴ እንደማደርገው ከህፃናቱጋ ላሳልፍ የህፃናት ማሳደጊያ ማዕከሉ ስሄድ እሱ እዛ ነበር። ከህፃናቱጋ ሜዳ ለሜዳ እየተሯሯጠ ይጫወታል። እኔን ሲያዩ ልጆቹ ሰላም ሊሉኝ ወደ እኔ እሮጡ።

ልክ እንደልክ ነገር፣ ትናንት እንዳደረገው የተለመደ ነገር ፤ በመሀከላችን ምንም ፀብ እንደሌለ ነገር በልጆቹ ፊት እቅፍ ነገር አድርጎ ጉንጬን ሳመኝ። ደንዝዤ ባለሁበት ለማላውቀው ጊዜ ያህል ተገተርኩ። ለመጨረሻ ጊዜ የሳመኝን ፣ጭራሽ የነካኝን ጊዜ ለማሰብ ስባዝን እጆቹ እንኳን ቆዳዬን ከነኩት ያኔ ሆስፒታል የተኛሁ ጊዜ ዓመት አለፈው ……… ጠልቼው አልነበር? እንዴት ነው ከንፈሩ ጉንጬ ላይ ሲያርፍ ልቤ ከደረቴ ካላመለጥኩ እያለች የምትደልቀው? መገተሬን ሲያይ መለስ ብሎ አሁንም እንደልክ ነገር ወደጆሮዬ ጠጋ ብሎ

«ልጆቹ እያዩን ነው። ለእነሱ የባልና የሚስት ምሳሌያቸው ፣ የእናት እና የአባት ተስፋቸው ነው። ጨቅላ ጭንቅላታቸው ገና ከጅምሩ በፍቅር ተስፋ እንዲቆርጥ ምክንያት አንሁናቸው!» አለኝ።

ጭንቅላቴ በከንቱነቴ ብስጭት ጦዞ <መጀመሪያስ ምን አስቤ ነው? ምን ዓይነቷ የማልረባ ነኝ በአንድ ጉንጭ መሳም በበደሉ ፈርጥሞ የደደረ ልቤ የሚቀልጥብኝ?> እያለ ያስባል። ከአፌ ማውጣት የቻልኩት ቃል ግን

«እሺ» የሚል ብቻ ነው። ከሰዓቱን በፍቅር እፍ እንዳለ ባል እና ሚስት ስንተውን ከልጆቹ ጋር አሳለፍን።

«እናንተ ለምን የራሳችሁ ልጅ የላችሁም?» አለው አንዱ ተለቅ ያለ ልጅ በልፊያቸው መሃል

«እናንተስ? ይሄ ሁሉ ልጅ የማን ነው? የኛ ልጆች አይደላችሁ?» ብሎ ባኮረፈ አነጋገር ተነጫነጨ።

ልጁ የተከፋበት መስሎት በማባበል አይነት እግሮቹን እያቀፈው
«እኛማኮ ልጆቻችሁ ነን! ሌላ ልጆች ካላችሁ ብዬ ነው! እ? የኛ አባት አይደለህምኮ አይደለም ግን » ብሎ ቀና ብሎ በልምምጥ አየው።
አዲስ ልጁን አንስቶ ተሸክሞት በማላውቀው አዲስ አነጋገር ሲብራራለት እኔ አፌን ከፍቼ እሰማለሁ። ከጨዋታ የተዘናጉትም ህፃናት ገብቷቸው ይሁን አፉ ጣፍጧቸው ይሰሙታል።

«ስለጠየቅከኝ አልከፋኝም እሺ። አንተ ህፃን ልጅ ነህ! ጭንቅላትህ ውስጥ የሚመጣውን ጥያቄ በሙሉ የመጠየቅ መብት አለህ! አዋቂዎች ደግሞ ያንን የመመለስ ግዴታ አለብን! ጥያቄህ ራሳችሁ የወለዳችሁት ልጆች የሏችሁም ወይ? አይደል? እንደሱ ከሆነ የለንም! እናንተ ብቻ ናችሁ ልጆቻችን! (ፈገግ ብሎ በፍቅር ዓይነት እኔን እያየ) እናንተ ትበቁናላችሁ ብለን ነው።»

የዛን ቀን ተመልሼ ወደቤት እየሄድኩ ደብዝዞ የነበረው መከፋቴ አገረሸብኝ። መውደድ ስለማይችል አይደለም። በምርጫው ሊጠላኝ ስለፈለገ እንጂ። አዲስን እስከማውቀው ከህፃናቱ ውጪ ለማንም ሰው የተለየ ፍቅር አያሳይም። ግን ደግሞ ለማንም ሰው ጥላቻን አያሳይም። ስሜት አልባ ይሆናል እንጂ። ላመነበት ምክንያት ማንንም ቢሆን ለመርዳት አያመነታም።ያውም ሰው ስለሆነ ብቻ እንጂ በደም ስለሚጋመድ ወይም ነገ ይጠቅመኛል ብሎ ሳያስብ። ሰውን ከረዳበት ለሚያወጣው ገንዘብም አይጨነቅም። ከቤቱ እና ከመኪናው ውጪ ለየቱም ቁስና ገንዘብ ሌሎች ሰዎች በሚጨነቁት ልክ ግድ ሲሰጠው አይቼ አላውቅም። እኔጋ ሲሆን ብቻ ይለያል ………… እኔን ግን ፈልጎ ነው መግፋት የመረጠው፣ ፈልጎ ነው መበደል የፈለገው፣ ፈልጎ ነው ባልገባኝ ጥፋቴ የሚቀጣኝ። ለምን እንዳልወደደኝ ሳስብ ራሴን መውደድ እቀንሳለሁ።

መጀመሪያውኑም ራስን ስለመውደድ እሱ ነው ያስተማረኝ። ከእርሱ በፊት የረባ የፍቅር ግንኙነት ያልነበረኝ ፣ ቤተሰቦቼን ለማስደሰት ከመዳከር ውጪ ለራሴ ምን እንደምፈልግ እንኳን የማላውቅ ነበርኩ። እሱ የወደደኝ የመሰለኝ ጊዜ ነዋ በእርሱ የመወደድ ዋጋ እንዳለኝ ሳውቅ ራሴን መውደድ የጀመርኩት፣ በራሴ መተማመን መገንባት የጀመርኩት። የሚወደድ ማንነት እንዳለኝ ያሳየኝ እሱ የጠላውን ራሴን መውደድ አቃተኝ። ለሆነ ሰው ማውራት እፈልጋለሁ። ከዛ <ያንቺ ጥፋት አይደለምኮ! አንቺ አሁንም ዋጋሽ ያው ነው እሱ ነው ጥፋተኛው። ቀረበት> እንዲሉኝ። አንደኛ እንደዛ የልቤን የማወራው ጓደኛ የለኝም ሁለተኛ ባወራ እንኳን ለማወራለት ሰው ለፍቅር ያልታደልኩ ዋጋ ቢስ መሆኔን ማውራት ጭራሽ የሚያሳንሰኝ ነው የሚመስለኝ። እሱ እንዳጠፋ ለማውቀው ጥፋት እንኳን በጥፋቱ መንገድ ውስጥ የእኔ ትንሽነት እና መዋረድ ደምቆ ይታየኝና በየቀኑ አንሳለሁ።

ከማሳደጊያው ውሏችን በኋላ በመሀከላችን የነበረው ውጥረት የቀነሰ መሰለ። የጤነኛ አብሮ ነዋሪ ሰዎች ሰላምታ እና ሀሳብ መቀባበል ጀመርን። ስለተፈጠረው ነገር ማናችንም አላነሳንም። እንደውም በቋሚነት ህፃናቱን የምንጎበኝበትን ቀን ልክ እንደበፊቱ <ለልጆቹ ሲባል> ተስማማን። አልፎ አልፎ እራት በአንድ ጠረጴዛ መብላት እና <ቀንህ/ሽ እንዴት ነበር?> አይነት ንግግሮች ጀመርን። አልፎ አልፎም ላይብረሪ ውስጥ ስንገናኝ ስላነበብናቸው መፅሃፍት ማውራት። ስለሚሰማኝ ስሜትም ፣ በትክክል ምን እንደምፈልግም ሳላውቅ በእንደዚህ ያለ ስሙ ያለየለት ኑሮ ወራት ተቆጠሩ። እነዚህ ወራቶች ላይ በተወሰነ መልኩ ነገን አርቄ ሳስብ እሱ የሌለበትን ነገ ማሰብ ጀምሬ ነበር። ባይኖርበትም ግን የሆነ ሰው ሆኜ ያለእርሱ ዋጋ ኖሮኝ አሁንም እንዲያይልኝ እፈልጋለሁ። በተዘዋዋሪ ዋጋዬ ትልቅ መሆኑን ለእርሱው ለራሱ prove ለማድረግ መጋጋጤ ያናድደኛል። ግን ዞሮ ዞሮ ምኞቴ ከዛ አያልፍም።

«የሆነ ሰርግ ተጠርቻለሁ። አብረን እንሂድ?» አለኝ ከእነዚህ ቀናቶች በአንዱ

«እንዴ? አንተ ሰርግ ከመቼ ወዲህ? ማን ቢሆን ነው?»

«እንድሪያስ ሊያገባ ነው።»

ለእኛ ሰርግ ሚዜ የሆነው ሪል ስቴቱን በማናጀርነት የሚሰራለት ሰው ነው። በተለያየ ጊዜ ጎበዝ እና ታማኝ እንደሆነ ነግሮኛል። ቢሆንም አዲስን ሰርግ ሲታደም ማሰብ አስደነቀኝ። የተባለውን ሰርግ ልንሄድ ስንወጣ ልክ ከዛ በፊት ቀሚስ ለብሼ አይቶኝ እንደማያውቅ ሁላ አይኖቹን በልጥጦ እያየኝ

«ቆንጅዬ ሆነሻል!!» አለኝ። ወንድ እንደማታውቅ ልጃገረድ ተሽኮረመምኩ። ባልተረዳሁት ምክንያት የዛን ቀን ደስተኛ ሆንኩ። ችግሩ ደስታሽ አይበርክት ተብዬ ተረግሜያለሁ መሰለኝ ሰርጉ ላይ የማስተምርበት ትምህርት ቤት ባለቤት ተገኝቶ ነበር እና ከአዲስ ጋር አስተዋወቅኩት። እኛ የተቀመጥንበት ጠረጴዛ ላይ ተጋርቶን ተቀመጠ። እና በየመሀሉ ስለትምህርት ቤት እና አንዳንድ ነገሮች እናወራ ነበር። ሰውየው ተጫዋች እና ባየው ነገር ቀልድ መፍጠር የሚችል ዓይነት ስለነበር ሲደመር ከነበረኝ የደስታ ሙድ ጋር ስስቅ እንደነበር አስታውሳለሁ።
የሰርግ ዝግጅቱ ሊያልቅ አካባቢ አዲስ ተነስቶ ወጣ። ሽንቱን ሊሸና ወይም ስልክ ሊያናግር ነበር የመሰለኝ። በጣም ሲቆይብኝ ግራ ገብቶኝ ደወልኩለት ግን አያነሳም። ወጥቼ ሳይ መኪናው ከቆመበት አልነበረም። ያ ድሮ የምፈራው ዓይነት ፍርሃቴ ሆዴን አንቦጫቦጨው። ግራ እየገባኝ ደግሞም እየፈራሁ ምናልባት ከልጆቻችን አንዳቸው የሆነ ነገር ሆነው ይሁን ብዬ አስቤ ለአለቃዬም ይሄንኑ ነገርኩት። <በቃ እኔ ላድርስሽ> ብሎኝ እቤቴ ሸኘኝ። እቤቴ ደጅ ላይ አድርሶኝ ከተሰነባበትን በኋላ ቀና ብዬ ሳይ አዲስ በመስኮት እያየኝ አየሁት። ሳቅኩለት። አልመለሰልኝም። እንደገባሁ እሱ ወዳለበት ክፍል ሄጄ

«ሁሉ ነገር ሰላም ነው? ጥለኸኝ ስትመጣ እኮ መጥፎ ነገር የተፈጠረ መስሎኝ።» አልመለሰልኝም! «ሰርጉ ደብሮህ ነው?»

«ከሰውየው ጋርኮ ፊትለፊቴ ልብሳችሁን ልትጋፈፉ ትንሽ ነበር የቀራችሁ።» ሲለኝ ሳቄን መቆጣጠር አቃተኝ። ቀንቶ ነው ብዬ አስቤ ደግሞ ለእኔ ስሜት ከሌለው ምን ያስቀናዋል? ወይስ ለማንም ሰው ግምት ግድ የሌለው ሰውዬ ሰዎች ለሚያስቡት ግድ ብሎት?

«ቀንተህ አይደለምኣ? እርግጥ አለቃዬ አማላይ ነው ግን በሌላ ነገር የማስበው ሰው አይደለም!» አልኩት። መቀለዴም ነበር።

«ምን ያስቀናኛል? ሳትሳቀቂ እንደፈለገሽ እንድትሆኚ ነው ትቼሽ የመጣሁትኮ » ብሎኝ ኮስተር ብሎ ቁልፉን አንስቶ እየወጣ «እንደዛሬ ደስተኛ ሆነሽ አይቼሽ የማውቅበት ቀን ትዝ አይለኝም። ካስደሰተሽ why not? ደግሞ አብረን አንድ ጣሪያ ስር ኖርን እንጂ ከወረቀት ባለፈ ምንምኮ አይደለንም!» ብሎኝ ልነግረው አፌን መክፈቴን ከቁብ ሳይቆጥረው በቆምኩበት ጥሎኝ ወጣ።

«ደስተኛ ያደረግከኝኮ አንተ ነህ!» ልለው ነበር።
ባስከፋኝ ቁጥር ህመሙ እየቀነሰ መጥቶ ይሆን እኔ እየለመድኩት አላውቅም ብቻ ከቀን ወደቀን ህመሙ ቀንሷል። የዛን ቀን ለለሊት የቀረበ ሰዓት ከሴት ጋር መጣ። ይህችኛዋ ሳቋ ብቻ አይደለም የሚሰማው አልጋው ሁሉ ሲሸበር ይሰማኛል። ሆነ ብሎ እኔ እንድሰማው እሷን ማስጮህ ፈልጎ ካልሆነ በቀር እሱኮ እንዲህ ድብድብ ቀረሽ ልፍያ አይላፋም ነበር! እሷስ ብትሆን ምንድነው ይሄን ያህል ፆሜን አለማደሬን ጎረቤት ካልሰማልኝ ማለት? ከፍቶኛል ግን አላለቀስኩም። ራሴን ጠልቼዋለሁ ግን በዛው ልክ እሱንም ጠልቼዋለሁ። ማነሴ ተሰምቶኛል ግን እሱም አንሶብኛል። አንድ የሆነ ነገሬ ከውስጤ ክፍል ብሎ የወደቀ ዓይነት ስሜት ተሰማኝ። ደሞ የማይበቃቸው ነገርስ?

ከዚህ ቀን በኋላ ያለው ኑሯችን ህፃን ያቦካው ሊጥ ነው። ወይ ተጋግሮ ለእራት አይበቃ ወይ አልቀጠነ ወይ አልወፈረ እጅ ላይ የሚጣበቅ ሊጥ……. መላ ቅጥ የሌለው። እናወራለንም አናወራምም ለማለት የቸገረ። ምንም እንደማይመስለኝ ላሳየው እንፈራገጣለሁ። ምኑም እንዳልሆንኩ ያሳየኛል። ማንም ግን እጅ ላለመስጠት እልህ ዓይነት እንፋታ የሚል የለም። መቆናጠሩን ለመድኩት። እዚህ ወቅት ላይ ነገዬን ያለእርሱ በደብ ማሰብ ጀመርኩ። የሆነኛው ቀን ላይ ስንፋታ ምን ያህል ሀብት እንደምካፈለው ሳሰላ ራሴን ያገኘሁት ቀን በእርግጠኛነት እንደጠላሁት አወቅኩ። እራሴም የማላውቃት ሌላ ሴት ሆንኩ። ከዛ በኋላ ሀሳቤ ሁሉ ከእርሱ ከተለየሁ በኋላ ስለሚኖረኝ ህይወት ሆነ። ትቶ መውጣት የሚለውን ሀሳብ ላላነሳ ከርችሜ ጠረቀምኩት። እንዲህ ልቤ ተሰብሮ፣ እንዲህ ተዋርጄማ ባዶ እጄን ትቼው አልሄድም። ማንም ጉዴንና ውርደቴን ሳያውቅ የተከበረው አዲስ ሚስት እየተባልኩ ያቺን ቀን እጠብቃለሁ። ያኔ ባለብዙ ሚሊየን ሀብት ባለቤት ነኝ። ለእናቴ እንደገና ቤት እገዛላታለሁ። የእህቴን ልጅ አስተምራለሁ። ከዚህ በኋላ የማፈቅርበት ልብ ኖሮኝ ትዳር ስጠኝ ብዬ አልለምንም ግን አምላክ ካልጨከነብኝ አንድ ልጅ ቢሰጠኝ በቃኝ! ሳመነዥክ የምከርመው ሀሳብ እንዲህ ያለውን ብቻ ሆነ። ያ ቀን ሩቅ ሲመስለኝ <ምናለ ወይ በገደልከኝ ወይ በገደልከው?> እላለሁ።

ሴት ማምጣቱን ለመድኩት። ተኝቼ ዙር እቆጥራለሁ። <የዛሬዋ ደግሞ ለቅሶና እንጉርጉሮ l,ieta አታውቅም? እንዴት ያለው አጯጯህ ነው የምትጮኸው?> <የዛሬዋ ደግሞ በአንድ ለሊት ስንት ዙር ነው የምትሄደው እንዴ?> ፣ <የዛሬዋ ደግሞ ምን ብታክል ነው ክፍሉ አብሯት የሚንቀጠቀጠው?> እያልኩ ብዙ ዛሬዎችን ከቆጠርኩ በኋላ ……… ስራ ስሄድ ከውጪ ሲታይ እንዳማረው ዘናጭ ቤቴ ያማርኩ መስዬ ሴሚስተሮች ዘልቄ ……. ለቤተሰቦቼ ብዙ ውሸትን ሳጠግብ ከርሜ ……. ብዙ እሁዶችን እንደሚፋቀሩ ባልና ሚስት ለህፃናቱ ስተውን ባጅቼ ……… ህፃን ያቦካው ዓይነት ኑሮዬን ሳጨማልቅ ሰንብቼ ……..ስሜት አልባ ከሆንኩ በኋላ …….. ለምናፍቀው ቀን አንድ ዓመት ብቻ ከቀረኝ በኋላ አንድ ከሰዓት ስልኬ ጠራ

«ባለቤትሽ መኪናው ተገልብጦ አደጋ ደርሶበታል። ቶሎ ድረሽ!» የሚል። ሆስፒታል ደርሼ በህይወት መኖሩን እስካረጋግጥ ድረስ እንኳን የማስበውን ላውቅ ጭርሱኑ እያሰብኩም እንደነበር እንጃ ……… እንደዛ የጠላሁት ሰው እንዳይሞት መባባቴ ገረመኝ። ለአንድ ወር ሀገር ውስጥ ህክምና ካደረገ በኋላ ከሀገር ውጪ ለህክምና ሄደን ነበር። ሁሉም ተመሳሳይ ውጤት ቢነግሩትም አምኖ ለመቀበል ከበደው። ዶክተርና ሀኪምቤት ቢቀያይርም ውጤቱ ያው ነው።

«በጊዜ እና በፊዚዮቴራፒ እርዳታ እጅህና ሌላው ሰውነትህ ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴው ይመለሳል። እግሮችህ ግን መራመድ አይችሉም።»

…………. አልጨረስንም………

@wegoch
@wegoch
@paappii
ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት ….. እኔ የቀጠልኩት
(ክፍል አስራ ስድስት…….. ሜሪ ፈለቀ)

«ስድስት ዓመት ሙሉ ምን ዓይነት ቀኖች እንደነበሩህ ለአንባቢ ምንም ፍንጭ ሳትሰጥ 20 ዓመትህ ላይ ወደ ሆነ ታሪክ መሄድ ታሪኩን አያጎድለውም?»

«ምንም የሚፃፍ ታሪክ የለውም። ፊልም ቢሆን (በጭንቅላቱ ምስሉን እየከሰተ) ምን ዓይነት ትራንዚሽን መሰለሽ? ማታ 14 ዓመቱ ላይ ተኝቶ ጠዋት 20 ዓመቱ ላይ ሲነቃ የሚያሳይ ሲን ነው የሚሆነው።»

ላይብረሪው ውስጥ ዊልቸሩ ላይ ለሰአታት ከሚቀመጥ በሚል ባስገባነው ሶፋ ላይ እሱ ጋደም ብሎ። እኔ መሬቱ ላይ ተቀምጬ ሶፋውን ተደግፌ ባዮግራፊውን መፃፋችንን እየቀጠልን ነበር። ከምንፅፈው በየመሃሉ የምናወራው ይበልጣል።

«አባትህ? እንጀራ እናትህ? ወንድምህ? ከነርሱጋር የነበረህ ግንኙነት? ትምህርት ቤት? ጓደኛ ? የሆነ የሚወራ የሚወሳ ይኖረዋል። ለህፃን አይደለም ለአዋቂ የሚከብድ ሰቀቀን ያሳለፈ ህፃን እንደማንኛውም ልጄ የተለመደ ዓይነት ዓመታት ሊኖሩት አይችልም መቼም።»

«እነዛ ዓመታት የ trauma ው አካል እንደነበሩ ትልቅ ሰው ከሆንኩ በኋላ ነው ያወቅኩት። ምንም ስሜት ነበር የማይሰማኝ። በቃ ምንም! አድርግ የምባለውን ከማድረግ ውጪ ፀጥ ያለ ህይወት ነበር። አይከፋኝም! አልናደድም! አላለቅስም! ማውራት ብችልም ከማናቸውምጋ አላወራም ነበር። 2 ዓመት ያቋረጥኩትን ትምህርት ቀጥዬ ነበር ብዙም አይገባኝም እንጂ። ቤተሰቦቼን በነዛ ዓመታት አውቃቸው ነበር ማለት ይቸግረኛል። ለእንጀራ እናቴ በእናቱ ሞት ምክንያት በሽተኛ የሆነ፣ አንድ ክፍል ሶስቴ የሚወድቅ ፣አስተውላ ባየችኝ ቁጥር ከንፈሯን የምትመጥልኝ የሆነ ደደብ ልጅ ነኝ። አባቴ ብዙውን ጊዜ ሊያዋራኝ ሞክሮ ፍላጎት እንደሌለኝ በመረዳቱ ከመተው በተጨማሪ በስራ ምክንያት ከቤት ውጪ የሚያሳልፈው ጊዜ ነው የሚበልጠው። ጓደኛ ቅብጠት ነው። በምማርባቸው ክፍሎች ሁሉ በእድሜም በሰውነትም ትልቅ ልጅ፣ በዛ ላይ እንደበሽተኛ የሚቆጠር ማን ጓደኛ ሊያደርገው ፍላጎት ይኖረዋል? ወንድሜ በሁለት ዓመት ቢበልጠኝም በጊዜው ልጅ ነበር።»

«አልገባኝም አባትህ ከእናትህ በኃላ መስሎኝ………»

«ህም የተጋቡት ከእናቴ ከተለየ በኋላ ነው። እንጀራ እናቴ ከእናቴ በፊት ፍቅረኛው ነበረች። የእነሱ ታሪክ ብቻውን ሌላ መፅሃፍ ይወጣዋል። ወንድሜን ወልዳለትም እናቴን ያፈቅራት ስለነበር ለማግባት እናቴን መረጠ። በኋላ ትቷት ቢሄድም።»

«ለአንባቢ ሙሉ ስሜት እንዲሰጥ መካተት አለበት እንደእኔ።» አልኩኝ። ትከሻውን ሰብቆ ዝም አለ። የነገረኝን አሳምሬ ለመፃፍ ሞከርኩ እና ጮክ ብዬ አነበብኩለት። ማስረዳት በማልችለው ምክንያት ያለፈበትን እኔ እንዳውቀው እንጂ መጽሃፍ ሆኖ ስለመታተሙ ብዙም ግድ የሰጠው አልመስልሽ አለኝ። ምንም ከማለት ተቆጥቤ የሚቀጥለውን እሱ እየነገረኝ መፃፍ ጀመርኩ።

«መጀመሪያ እቤት የመጣች ቀን ነው ከማውቃቸው ሰዎች ለስሜቴ የቀረበች እንደሆነች የገባኝ። ቀጥታ መኝታ ቤቴ ገብታ የለበስኩትን ብርድ ልብስ ከላዬ እየገፈፈች።

<ያንተ አቻ ፈረንጅ ስንት ቴክኖሎጂ ለሀገሩ አበርክቷል አጅሬው በ20 ዓመትህ ዘጠነኛ ክፍል እየተማርክም እስከ ጠዋቱ 4 ሰዓት እንቅልፍህን ታገነፋለህ?> አለችኝ።

ማንም ሰው እድሜዬንና የትምህርት ቤት ደረጃዬን ከንፈሩን ሊመጥልኝ እንጂ እንደሷ ያውም ለራሴው ተናግሮ ሰምቼ አላውቅም። አባቴ ዘጠነኛ ክፍል ስገባ በግል እንድታስጠናኝ ብሎ የቀጠረልኝ በእድሜ እኩያዬ የሆነች የዩንቨርስቲ ተማሪ ናት። የዛን ቀን ብርድልብሱን ከላዬ ስትገፍ የዓመታት ሰቀቀኔንም ነበር አብራ የገፈፈችው።

<ማዕረግ እባላለሁ። አስጠኚህ ነኝ I think አባትህ ነግሮሃል። ጊዜዬን አትብላብኝ ሳሎን እየጠበቅኩህ ነው።> ብላ ትታኝ ሄደች።’”

እያወራልኝ የፊቱ ፀዳል ያቺ ሴት ማን እንደነበረች ሳይነግረኝ በፊት አወቅኩ። ዞር ብሎ ሳያየኝ ወቅቱን ከነስሜቱ ወደአሁን ጎትቶ ማውራቱን ቀጠለ።

«ለሳምንታት እሰማታለሁ እንጂ ብዙም አላወራም። በሷ ጣፋጭ ቃላት እና ለዛ ስታወራው ትምህርትም ህይወትም ቀላል ነው። የፊደል እና የቁጥር ሰልፍ ከመሆናቸው ውጪ እምብዛም የማይገቡኝ ፅሁፎች እሷ ስትፈተፍታቸው ትርጉም ነበራቸው። አንድ ቀን ሳሎን እያስጠናችኝ እንደምትፈልገው አልመልስ ስላት <አንተ ግን በዚህ ዓይነት እንዴት ነው ከሰው ጋር ተግባብተህ የኖርከው በአባቢ ሞት? ከአፍህ በሚወጡት ፊደላት ልክ አትከፍልም እኮ ወይም እዳ አይሆኑብህም! ምንድነው? My God! > ብላ ስትጮህ እየሰማች መሆኑን ያላወቅኳት የእንጀራ እናቴ በጣም ሳቀች። አስከትላም። < እንደውም አንቺ ከመጣሽ ጀምሮ እየተሻሻለ ነው። እናቱ ከሞተች በኋላ ጭራሽ ………> ብላ የሆነውን ትነግራት ጀመር። ማዕረግ ያለፈ ህይወቴን መስማቷ መጥፎ ስሜት እንዲሰማኝ አደረገኝ። ተነስቼ ወደ መኝታ ቤት ገባሁ። ከደቂቃዎች በኋላ ወደክፍሌ ስትመጣ ብዙ ለሊት ተኝቼ አልጋ ላይ ሽንቴን መሽናቴን ጨምሮ ምንም ያላወቀችው ገበናዬ እንደሌለ እርግጠኛ ነበርኩ። የተለመደ ነው። ስለእኔ ለጠየቀ ሰው በሙሉ ይነገረዋል። እናቴ መቃብር ላይ ካለቀስኩኝ ቀን በኋላ ግን ምንም ስሜት ሰጥቶኝ አያውቅም ነበር። ሰሚዋ ማዕረግ እስከሆነችበት ቀን ድረስ

<you are brave> አለችኝ መጥታ አልጋዬ ላይ እየተቀመጠች። <ምፅ! ምስኪን> የሚል ሀዘኔታ ነበር የለመድኩት እና ጆሮዬ ደነገጠ።

<ታውቃለህ ? ያልገባህ ነገር ያንተ ጥፋት አልነበረም! ማድረግ የምትችለው ነገር አልነበረም። ራሷን አይደለም ያጠፋችው ያን ታውቃለህ አይደል? አንተ ጥለሃት ስለሄድክ አይደለም የሞተችው! ድራጉን ኦቨርዶዝ ወስዳ ነው።> ልዩነቱን ማወቅ አለማወቄን ለማረጋገጥ አይኔን እያየች <ታውቃለህ እሱንኣ?> ዝም አልኳት <God damit መልስልኝ!> ብላ ስትጮህ ጥያቄዋ ሁሉ ጠፋብኝ እና ዘልዬ ቁጭ አልኩ። የእኔ መደንገጥ አላስደነገጣትም። ጭራሽ ተመቻችታ እየተቀመጠች። ትጮህብኝ ጀመረ።

<ስማኝ? ምናልባት አንተ እዛ ያለመኖርህም ትዝ አላላት ይሆናል። ከለመደችው መጠን ሞቅ ያለ እብደት ፈልጋ ጨምራ የወሰደችው ድራግ ነው የገደላት። አጠገቧ ሆነህም ቢሆን አታድናትም ነበር። ለሷ ሞት ያበረከትከው ምናምኒት አስተዋፅኦ የለም።>

<አጠገቧ ብኖር ተጨማሪ ላትወስድ ትችላለች፣ አጠገቧ ብኖር ስትወድቅ ሀኪም ቤት እወስዳት ነበር፣ አጠገቧ ብኖር ሞታ እንኳን ሳትሸት ትቀበር ነበር። ……….. > መቃብሯ ላይ ካለቀስኩ በኋላ ያላለቀስኩት እንባዬ በዓረፍተ ነገር ታጅቦ እናጠው ጀመር። ጭንቅላቴ ውስጥ ያለውን <ባልተዋት ኖሮ > በሙሉ ነገርኳት። አቅፋ እያባበለችኝ ግን ደግሞ ትቆጣኛለች።

<ቢሆን ኖሮ እያልክ በመላ ምት ስትጃጃል መኖር ነው የምትፈልገው? እኩዮችህ እንደ ዝግምተኛ ሲያዩህ መኖር ነው የምትፈልገው? እስከመቼ ነው ራስህን ስትቀጣ ለመኖር ያሰብከው? ምንም ጥቅም የሌለው ልጅ ሆነህ እዚሁ አልጋ ላይ ማርጀት ነው የምትፈልገው? ያን መከራ በ12 ዓመቱ ተቋቁሞ ያለፈ ልጅ በ20 ዓመቱ እንዲህ ጂል ይሆናል?>
እብድም ግልብም ናት ስታወራ። ከዛ በኋላ ብዙ ነገር ስሜት ይሰጠኝ ጀመር። ቢነኩት ይፈርጥ ይመስል የተድቦለቦለ ሰውነቴ አስጠላኝ። እስፖርት መስራት ጀመርኩ። ትምህርት ቤት ልጆቼ ከሚመስሉ ተማሪዎች ጋር መማሬ ያሳፍረኝ ጀመር። ወንድሜ ዩንቨርስቲ ተማሪ ቢሆንም ሴት በማሳደድ እና ጭፈራ ቤት ለጭፈራ ቤት እንደሚያድር ማወቅ ያሳዝነኝ ጀመር። አባቴ በእኔ ዝምታ ውስጥ ፀፀት እንደሚያንገበግበው አስተውልለት ጀመር። የእንጀራ እናቴ ድንገት እንደባነነ ሰው የመንቃቴ ነገር ደስታ እንዳልሰጣት ማገናዘብ ቻልኩ። የማነባቸው መፅሃፍት እያመጣች ትሰጠኛለች። ለሷ ስል ራሴን ልቀይር በረታሁ። እሷ ማለት ጥቅጥቅ ባለ ጨለማ ዋሻ ውስጥ በርቀት የታየችኝ የብርሃን ፍንጣቂ አይነት ነገር ናት። የድሮው አዲስ የሞተ ይሄኛው አዲስ ማዕረግ ከሞቱ ቀስቅሳው ለማዕረግ የሚኖርላት ነበር። ድጋሚ የመኖር እድሌ ነበረች።

አንደኛ ሴሚስተር ሲያልቅ በትምህርቴም በአካሌም በውስጤም ሌላ ሰው ነበርኩ። ማዕረግ የሞላችበት ሰውነት ያለው ሰው። የአንደኛ ሴሚስተር ውጤቴን አያለሁ ያልኳት ቀን በጠዋት መኝታ ክፍሌ <የታል?> እያለች ገባች። ስታየው ቦረቀችልኝ። ካርዱን ወርውራው ከንፈሬን ለደቂቃ ሳመችኝ። <ወይኔ ጉዴ ለካ ምንም አታውቅም!> ብላ ምንም እንዳልሰራች ነገር <ና እኛ ቤት እንሂድ የማሳይህ ነገር አለ> ብላ እጄን እየጎተተች ወጣች። ታክሲ ተሳፍረን እቤታቸው እስክደርስ ድረስ እኔ የማስበው ቅድም የሳመችኝን ነበር። እሷ የተለየ ነገር እንዳላደረገች ሌላ ወሬ ታወራለች። እቤታቸው ማንም የለም። በሩን ቆላልፋ <የምከፍትልህ ፖርን ነው። ተሽኮርምመህ አማትበህ ምናምን እንዳታፀፅተኝ> ብላኝ ትንፉሽ እንኳን ሰብስቤ ሳልዘጋጅ ከፈተችው። አጉል አጉል የሆነ እያሳየችኝ አጓጉል አደረገችኝ።» እኔ ራሴ ሊከሰት የሚችለውን አስቤ መፃፌን መቀጠል አቃተኝና ሳቅኩ። በሳቁ አጀበኝ።

«እብድ ናት!» አለኝ እየሳቀ።

«መድሃኒት የሆነህ እብደቷ አይደል?»

«exactly!!» (ካለ በኋላ መጥፎውን ትዝታ እንደጫረው እስከአሁን የነበረውን የክፍሉን ድባብ የቀየረ የፊቱን ፀዳል አደበዘዘው)

«እንቀጥል ወይስ ማረፍ ትፈልጋለህ?»

«am good እየፃፍሽ ያለሽውኮ አንቺ ነሽ! ማረፍ ከፈለግሽ የተወሰነኮ መፃፉንም ጣቴን ሳላደክም ላግዝሽ እችላለሁ!»

«እንቢየው! መጻፉንማ ራሴ ነኝ የምፅፈው!»

«<አፈቅርሃለሁ እኮ አንተ ዱዝ!> አለችኝ አጓጉል ባደረገችኝ ማግስት

<አውቃለሁ!> ብዬ መለስኩላት

<ወይኔ ጉዴ! ስንቱን ነው አስተምሬህ የምዘልቀው? ሴት ነኝ! ሴት ልጅ መፈቀሯን በጆሮዋ መስማት ትፈልጋለች።>

<ምርጫኮ አልሰጠሽኝም ነበር። አንቺን አለማፍቀር አልችልም ነበር።>

<ጎበዝ ሆነህ አኩራኝ> አለችኝ ያን ቀልብ የሚነሳ መሳሟን እየሳመችኝ። እብደቷን አበድኩት። ፍቅሯን ለነፍሴ ደርቤ ሞቀኝ። በሷ ውስጥ ነፍስ ዘርቼ ደስታን ቃረምኩ። አልፈልግም ብላ አውጥታ ብትጥለው ይጎዳብኛል ሳልል ስጋዬንም ነፍሴንም ልቤንም ያልሰጠኋት አልነበረም። እሷው እንደአዲስ ያበጃጀችው እኔነቴ ነበር እና ልሰስትባት አልችልም ነበር።

ዘጠነኛን ክፍል እንደጨረስኩ እሷ እናቷ ስለታመመችባት ትምህርቷን ልታቋርጥ ሆነ። አባቴን እሱጋ ስራ እንዲያስገባኝ ለምኜው እኔ ትምህርቴን ተውኩት እና እሷን ማስተማር ጀመርኩ። ለእርሷ መኖር የህይወት ግቤ ስለነበር እሷ የምታገኘው እንጂ እኔ የማጣውን የምቆጥርበት ልብ አልነበረኝም። አባቴ ትምህርቴን መተዌ ባያስደስተውም እንደጤነኛ ልጅ ዳግም ሰው መሆኔ ስላስደሰተው አልተጫነኝም። አኖረችኝ። ኖርኩላት። በአመቱ እናቷም ወደጤንነታቸው ተመለሱ። አባቴ በወቅቱ መጠነኛ የሲሚንቶ ፋብሪካ ነበረው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ስራዎቹን ለምጄ ማሻሻያ ሀሳቦች ማቅረብ ስጀምር አባቴ በደስታ ሲቅበጠበጥ እንጀራ እናቴ በግልፅ በእኔ ስራ ብቃት እምነት እንደሌላት ያለፉትን ዓመታት እና ያለመማሬን እያጣቀሰች መናገር ጀመረች። ማዕረግ ያጎበዘችው ልቤ ለሷ ኩራት ለመሆን የማይረግጠው ቦታ የለም።

<አንተ ዱዝ አፈቅርሃለሁኮ! አንተ ባትኖርልኝ ምን ይውጠኝ ነበር? > እያለችኝ ተመረቀችልኝ። በዛው ዓመት እንደማዕረግ በማዕረግ ባይመረቅም ወንድሜም ተመርቆ ነበር። የሱ ምርቃት ድግስ ቀን የኔ ማዕረግ ውብ ሆና መጥታ ነበር። እንደሁሌውም በህይወት ውስጥ ከሷ ውጪ ዓይኔን የሚስበው ነገር እንዳለመኖሩ አጠገቤ አስቀምጬ አይን አይኖቿን ሳይ መሸ። ለአፍታ ዘወር ብዬ ስመጣ ሳሎን የለችም። ምናልባት ወደ መታጠቢያ ቤት ሄዳ ይሆናል ብዬ ልፈልጋት ስሄድ ሳቋን ሰማሁት። ከወንድሜ መኝታ ቤት ነው። ምን አስቤ ይሁን ሳላስብ አላውቅም እግሬ ወደዛ ተራመደ። ጆሮዬ የገባው

«አንተ እረፍ ልመለስ! ያወቀ እንደሆነ ደግሞ ዲዳ ሆኖ ሀሁ ሳስቆጥረው ልክረም?» የሚለውን ሳቃቸው ያጀበውን ድምፅዋን ነው። ሳቃቸውን ሳይጨርሱ ብቅ ሲሉ መንቀሳቀስ አቅቶኝ እንደቆምኩ ነበር።

አልጨረስንም

@wegoch
@wegoch
@paappii
ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት ….. እኔ የቀጠልኩት
(ክፍል አስራ ሰባት ………. ሜሪ ፈለቀ)

< «አንተ እረፍ ልመለስ! ያወቀ እንደሆነ ደግሞ ዲዳ ሆኖ ሀሁ ሳስቆጥረው ልክረም?» የሚለውን ሳቃቸው ያጀበውን ድምፅዋን ነው። ሳቃቸውን ሳይጨርሱ ብቅ ሲሉ መንቀሳቀስ አቅቶኝ እንደቆምኩ ነበር። > የሚለውን እንደፃፍኩ አቁሜ

« በመድሃንያለም !ውይ ምን ሆና ነው?» አልኩኝ ራሴው ቁዝም ብዬ

«ሰው! ሰው ሆና ነው! የትኛውስ ሰው ቢሆን እንዲህ አይደለም?»

«ይሄ ሰውነት አይደለም!!» ለወሬ እየተቅለበለብኩ ኮንፒውተሩን መሬት ላይ አስቀምጬ በጉልበቴ መሬቱ ላይ ተንበርክኬ ወደእርሱ እየዞርኩ።

«ትክክለኛ ሰውነት ውስጥ ክህደት የለም። ሰውነት ተፈጥሮ ነውኮ እንዴ? ልክ እና ስህተትን በሚያሰላ ህሊና በሚባል ሞተር የሚዘወር ተፈጥሮ ነው። የማንበብህ ብዛት፣ ሀይማኖት፣ የልምድህ ክምችት አልያም ስልጣኔህ ወይም ህግ የሚሰጥህ ነገር አይደለም።»

«ህሊና ከጠቀስቻቸው ዝርዝሮች ተፅዕኖ በላይ አይደለም።»

«በሱ እስማማለሁ። ለዛ ነው ተፈጥሮ ነው ያልኩህ!! በመረጥከው መንገድ ልታሳድገው ወይም ደግሞ ልታዳፍነው ትችላለህ። ለምሳሌ የህሊናህን ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ አልፈህ አንድን ነገር ስታደርግ በደጋገምከው ቁጥር የፀፀትህ መጠን ይቀንሳል። ያ ምናልባት ከዘረዘርኳቸው በአንዳቸው ተፅዕኖ ምክንያት ህሊናህን ላለመስማት ወስነሃል ማለት ነው እናም በሱኛው እሳቤህ ህሊናህን ትከድነዋለህ። በተቃራኒው ደግሞ እግዚአብሔርን በመፍራት ውስጥ በስነስርዓት እና በመልካም ሀሳቦች አዕምሮህን ስታበለፅግ የህሊናህን ቀይ መብራት በደንብ ለማዳመጥ ንቁ ትሆናለህ። በእርግጠኝነት ግን በምንም ተፅዕኖ ህሊናህን ብታዳፍን ሰውን መጉዳት ወይም ክህደት ሰውኛ አለመሆኑን ለመረዳት አትቸገርም።»

«ችግሩ አብዛኛው ሰውኮ ሰውን ለመጉዳት ብሎ አይጎዳም። ከሚጎዳው ሰው እና ከራሱ መምረጥ ሲኖርበት ግን እራሱን ያስቀድማል። ይሄ ደግሞ ትክክለኛ የሰው ስሜት ነው።»

«እና ማዕረግም ራሷን ነው የመረጠችው እያልከኝ ነው?»

«አዎ! ከእኔ ደስታ እና ከራሷ ደስታ መምረጥ ሲኖርባት ራሷን መረጠች ብዬ ነው የማስበው። እስኪ አስቢው ያን አዲስ? አይጨንቅም? ከጠዋት እስከማታው ማዕረግ፣ ደስታው ሀዘኑ ማዕረግ፣ መብላት መጠጣቱ ማዕረግ፣ መስራት ማወቁ ሁሉ ማዕረግ…….. በህይወቱ ከእርሷ ውጪ ምንም ግብ እና ዓላማ የሌለው ፍጡር! አይጨንቅም? በሱ ህይወት ውስጥ ያንን ሁሉ ሆኖ መኖርስ ነፃነትን ማጣት አልነበረም? እሷ ደግሞ በእንደዛ ዓይነት አጥር የማትያዝ ፣ ነፃነቷን የምትወድ ፣ እንደስሜቷ መብረር የምትፈልግ ፣ እሳትም ቢሆን ሞክራ መፈተን የምትፈልግ ዓይነት ነበረች። ከዓመት ዓመት አንድ ዓይነት ቀን ያለው ዱዝ ደስታ ወይስ የራሷን አድቬንቸረስ ቀን መምረጥ ነበረባት። ራሷን መረጠች። »

«አንተ የምርህን ነው? እሺ ንገረኝ ከዛ በኋላ የተፈጠረውን?»

« አልራበሽም? የሆነ ነገር ከበላን በኋላ አንፅፍም?»

«አልራበኝም! ከዛ በኋላ የሆንከውን ካልሰማሁ ደግሞ መብላት አልፈልግም። መፃፉን በኋላ እንፅፈዋለን። ንገረኝ! ከዛስ?» ለወሬ ስቁነጠነጥ ትንፋሼ ፊቱን የሚሞቀው ያህል ቅርበት ላይ እንዳለሁ ያወቅኩት እጁን በአንገቴ አዙሮ ማጅራቴ መጨረሻጋ ያሉትን ድፍት ያሉ ፀጉሮች ሲነካካቸው ነው። (ከግንባርሽ ይልቅኮ ከጀርባሽ ነው ቤቢ ሄር ያለሽ ይለኝ ነበር ድሮ)

«ከምኑ በኋላ?» አለኝ እጁ ምን እንደሚያደርገኝ ስለሚያውቅ ፈገግ ብሎ።

«ከወንድምህ ጋር ከሰማሃት በኃላ……. ከዛ ግን ይሄን እጅህን አሳርፈው እና ነው» ብዬ እጁን አንስቼ ወደቦታው እየመለስኩት።

«አውርቼም፣ መንካት ተከልክዬም? እሺ የሆነውን ላውራሽ ግን እጄ የፈለገበት ይረፍ?»

«የፈለገበት ማለት?»

«ሃሃሃሃ አይዞሽ የማወራውንም እንድትሰሚኝ ስለምፈልግ የሚያደነቁርሽ ቦታ አልከውም! ሙች ከአንገትሽ አላልፍም!»

«ልለፍ ብትልስ……….» ብዬ ሳልጨርስ እጁን የነበረበት መልሶ ወሬውን ቀጠለ።

«ለመጀመሪያ ጊዜ ፓኒክ ያደረግኩት ያኔ ነው። በእርግጥ የሄድኩበት ሆስፒታል ያልተስማማው ምግብ በልቶ ነው ነበር ያለኝ። (ሳቅ ነገር አለ።) ግርግሩ ሰክኖ ሆስፒታል መጣች። <ውጪልኝ ላይሽ አልፈልግም!> ብዬ ስጮህባት አባቴ እንኳን መኖሩን ከምንም ሳትቆጥረው <ተመስገን ቢያንስ ማውራት ትችላለህ> ብላ አጠገቤ እንደደረሰች በጥፊ ነው ያጮለችኝ።» ብሎ ፍርስ ብሎ ሳቀ

«እንዴ?» አልኩኝ ሳላስበው።

«ጥፊዋንም የማጣጥምበት መልስም የምሰጥበት ጊዜ ሳትሰጠኝ እሷ ማውራቷን ስትቀጥል አባቴም እንደእኔ ግራ ገብቶት ነው መሰለኝ ዝም አለ። አስተውሎ ላየን እኔ ቺት አድርጌባት እንጂ እሷን ከወንድሜጋ ይዣት አይደለም የሚመስለው። ስታወራ ግልብ ናት አላልኩሽም?

<ምን ልሁን ነው የምትለው? አንድ ሴት የሌላ ወንድ ከንፈር ሳመችብኝ ብለህ መተንፈስ እስኪያቅትህ ትንፈራፈራለህ? ለሴት ብለህ በራስህ ላይ ተስፋ የምትቆርጥ ጅል ነህ? ገና 24 ዓመትህኮ ነው። ከዚህ በኋላ ሌላ አስር ሴት በህይወትህ ውስጥ ልትመጣ እንደምትችል አታውቅም? እድለኛ ካልሆንክ ደግሞ አስሯም ልብህን ሰብራው ልትሄድ ትችላለች። መጀመሪያ ራስህን ውደድ። ከእኔ ጋር ያሳለፍካቸው አመታት ከምንም እና ከማንም በላይ ራስህን መውደድ ካላስተማሩህኮ አከሰርከኝ! ይሄ ስታነበው የከረምከው መፅሃፍ ምንም ብስለት ካልጨመረልህ ለምንድነው ጊዜህን የምታባክነው? ምን አይነቱ እንከፍ ነው በአባቢ ሞት? ምን ይጠበስ? አዎ ወንድምህን ስሜዋለሁ! እ? ለሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት ጉልበትህን አቅፈህ ስታለቅስ እና ስትጃጃል ልትኖር ነው? ወይስ አሁንም ደግሞ የሆነ ሰው መጥቶ እስኪያነሳህ pause አድርገህ ልትጠብቅ ነው?>

እኔስ የማወራበት አቅሙም ወሬውም አፌ ላይ ስላልነበረ በዛ ላይ እሷ የጭንቅላቴም የአካሌም አዛዥ ስለነበረች ዝም ብዬ ከመስማት ውጪ ምርጫ አልነበረኝም። የገረመኝ አባቴ ደስ ያለው ነበር የሚመስለው። እሷ ያለችውን ማለት ፈልጎ በሆነ ምክንያት ያቃተው እና እሷ የልቡን የተናገረችለት ነበር የሚመስለው። የሆነው እና ያልሆነው ተምታታብኝ። ሀሳቤን እና እውነቱን አወጫበረችብኝ። ጉንጬን እንደመነካካት ነገር አድርጋኝ። ደግሞ እናታዊ በሆነ ሹክሹክታ

<በህይወትህ የሚፈጠር ነገር ሁሉ ያንተ ጥፋት ወይም ሀላፊነት አይደለም። it’s just life! Mess is just one of life’s package! ያንተ ሀላፊነት ወይም ጥፋት የሚሆነው የተፈጠረው ነገር ላይ ሙጭጭ ብለህ እዬዬ ማለት ወይም አቧራህን አራግፈህ መነሳት የቱን መምረጥህ ነው። የተፈጠረው ነገር የእኔ ምርጫ እንጂ ያንተ ጥፋት አይደለም> ብላ አባቴን አልፈራችውም። ከንፈሬን ስማኝ ተነሳች! ያለችው በወቅቱ ይግባኝ አይግባኝ አላውቅም። ቅድም ከወንድሜጋ ተሳስማ ከነበር አሁን እኔን መሳሟ ልክ ይሁን አይሁን ለማስላትም ፋታ አልሰጠችኝም። ከንፈሯ ሲስመኝ ማሰብም አይሆንልኝም። ዝም ብዬ ፈዝዤ ነበር የማያት ……… ደግሞ ወደ መጀመሪያ ቁጣዋ ተመልሳ

<እእ! ራስህን ለመጥላት እኔን ሰበብ እንድታደርግ አልፈቅድልህም! ራስህን ማንሳትህን ሳላረጋግጥ ከህይወትህ ወደየትም አታርቀኝም! እንዳትለፋ! ነገ በተለመደው ሰዓት እንገናኛለን!> ብላኝ ወጣች። እሺም እንቢም አታስብለኝም! በእኔ ላይ አዛዧ ራሷ እንደሆነች ታውቅ ነበር።» ብሎ ስለእርሷ ተመስጦ ሲያወራ አቁሞ የነበረውን መነካካቱን ቀጠለ።
«አሁንም ድረስ ትወዳታለህ?» አልኩት ሳላስበው። ስለእርሷ ሲያወራ ሳቁ ፣ ፈገግታው ፣ ዓይኖቹ ፣ የድምፁ ለዛ ……. የፊቱ ፀዳል …. በፍቅር የተሞላ ነው።

«አልጠላትም! ህይወቴን በሁለቱም ዋልታ የቀየረች ሴት ናት! ያኔ የነበረኝ ስሜት አሁንም መኖሩን ከሆነ ማወቅ የፈለግሽው። የለኝም! ከዛ በኋላ ብዙ ነገር ተፈጥሯል።»

«እሺ ከዛ በኋላ ለሌላ ሴት እንደዛ ሆነህ ታውቃለህ?»

«እንደዛ ይሁን የተለየ አላውቅም! የዝቅታን መጨረሻ፣ የጨለማን ድቅድቅ ፣ የሞትን ያህል ፍርሃት ዓይነት ጭንቅ ስሜት እንዲሰማኝ አድርጋኝ የምታውቅ ሴት አለች።» አለኝ በዓይኖቹ ሙሉ ዓይኖቼን እያየ

«ደስ የሚል ስሜትኮ አይደለም የነገርከኝ ወይም ፍቅር አይደለም።!» አልኩት የሚላት ሴት እኔ መሆኔን ልቤ እየጠረጠረ። ድምፄ ደግሞ ምናባቱ ያልሞሰሙሰዋል? ቅድም ደህና አልነበር?

«እንዳለመታደል ሆኖ ስሜትሽ ከባለቤቱ ካንቺ ይልቅ በስሜት ለተቆራኘሽው ሰው ሲያጎበድድ ደስ የሚል ስሜት አይደለም።» ድምፁን ቀይሮ ወዲያው «አልራበሽም?» አለ

«እንዴ? አልጨረስክልኝምኮ ከዛስ?»

«አያልቅም trust me! እያረፍን ይሻላል።»

«እሺ በነገታው ሄድክ ወይስ ቀረህ? እሱን ንገረኝ።»

«አልገባሽም! ና ብላኝ ልቀር አልችልም። ራሴንኮ አላዘውም ነበር! Ofcource ሄድኩላት። ያውም ላያት እየናፈቀችኝ!»

«oh my God! የዓመታት ፍቅራችሁንኮ ነው ያረከሰችው? ወንድምህን ነው የሳመችው!»

«እሱን የማስብበት ክፍተት አልሰጠችኝም ነበር በሰዓቱ! ወንድሜን ከሳመችው በኋላ ሳመችኝኮ ……. ልኩ እና ስህተቱን አማታችብኝ። ከክብሬ ከኩራቴ ከወንድነቴ በላይ ከእሷ ጋር ያስተሳሰረኝ ስሜት ያይል ነበር። ሁሌም ራስሽን እስከማታዢው ድረስ ከሰው ጋር ያለሽን ግንኙነት ካጠበቅሽው የራስሽ የሆነ ነገር አይኖርሽም! ራስሽን ጨምሮ!!»

«እሺ ከዛስ?»

« ግልብ ናት አላልኩሽም? እውነቱን ነገረችኝ። < አንተ ህይወትህ የተለመደ እና ደባሪ ነው። እኔ ደግሞ unpredictable የሆነ ቀን እንዲኖረኝ ነው የምፈልገው። አልዋሽህም አፈቅርሃለሁ። ታሳዝነኛለህ። ግን ለእኔ ያ በቂ አይደለም። ወንድምህ ደግሞ ነፃ ነፍስ ያለው አደገኛ ነገር ለመሞከር የማያመነታ ደፋር ሆኖ አገኘሁት እና ሳበኝ። ከፈለግክ እመነኝ ካልፈለግክ ተወው ከመሳሳም ውጪ ምንም ያደረግነው ነገር የለም። እንዴት እንደምነግርህ ጨንቆኝ እንጂ እነግርህ ነበር። የሚጠቅምህ እውነቱን ብነግርህ ስለሆነ እውነቱን ልንገርህ አሁን ላይ ከማፈቅርህ በላይ ስለምታሳዝነኝ ነው አብሬህ ያለሁት። ያ ደግሞ ማናችንንም አይጠቅምም። ማንም ሴት ብትሆን ስለምታፈቅርህ እንጂ ያደረግክላት ነገር ይዟት ወይም ብትለይህ ትጎዳለህ ብላ አዝናልህ አብራህ ከሆነች ልክ አይደለም። ፍቅረኛህ አልሆንም። ለመጨረሻ ዛሬ ከምስምህ ውጪ አልስምህም። በየቀኑ ግን አለሁ። በእኔ ምክንያት አይደለም እንድትወድቅ እንድትወላከፍ አልፈቅድልህም።>

ብላኝ የስንብት ያለችኝን መሳም ስማኝ ተለያየን። እንዳለችውም ከቀን ተቀን ህይወቴ አልጠፋችም። በየቀኑ እስፖርት መስራቴን፣ ስራ መግባቴን ፣ በጠዋት መንቃቴን……… በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ታረጋግጣለች። የመጀመሪያዎቹን ሳምንታት አጠገቤ ሆና ላልነካት መታገል ህመም ስለነበር ባትመጣ ሁሉ ደስ ይለኝ ነበር። እንድከፋ ወይም በሷ መሄድ ራሴን እንድጠላ ጊዜ አልሰጠችኝም። ከወንድሜ ጋር ፍቅረኛሞች ሆነው መቀጠላቸውን አልደበቀችኝም። እኔ እንዳላያቸው ወይም እንዳላገኛቸው ስለምትጠነቀቅ ለመቅናትም እድል አልሰጠችኝም። ትኩረቴን ራሴን መስራት ላይ አደረግኩ። ብዙ ማንበብ እና ማሰላሰል ላይ አተኮርኩ። ለዓመታት ጓደኛዬ ሆነች። ከጊዜ በኋላ ከወንድሜ ጋር ተለያይተው ከሌላ ሰው ጋር ሆነች። አብሮ የፍቅር ጊዜ እንዳሳለፈ ወይም ወንድሜን መርጣ ትታኝ እንደሄደች አልያም በሷ ከአዘቅጥ ወጥቼ በሷው የሚያምን ልቤን እንዳጣሁ ……… ብቻ ብዙ እንደተኳኋነ ሰው ሳይሆን ልብ ለልብ እንደሚተዋወቅ ጓደኛ ብዙ አሳለፍን።»

«ቻልከው? ጓደኛ መሆኑን? »

«መሆኑን ሳይሆን ማስመሰሉን ቻልኩት። እሷ በህይወቷ ደስተኛ ነበረች። ጓደኛ ደግሞ ያን ደስታ አይበርዝም።»

«ከዛስ? እሺ?»

«ከዛ ያለው ብዙ ነው! እያረፍን!» ብሎኝ እጁን ከማጅራቴ አንስቶ ጉንጬን እንደመቆንጠጥ አድርጎ የቆነጠጠበትን እጁን ሳመው። ዘልዬ ተነሳሁ።

………………. አልጨረስንም……….

@wegoch
@wegoch
@paappii
ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት ….. እኔ የቀጠልኩት
(ክፍል አስራ ስምንት ………. ሜሪ ፈለቀ)

«ታውቂያለሽ የአዕምሮ ክፍላችን እድገት በ25 ዓመታችን እንደሚያበቃ? ከዛም ውስጥ ከ80% በላዩ የሚያድገው እስከ 5 ዓመት አካባቢ ባለው እድሜያችን ነው። ጥናቶች እንደሚያሳዩት የሰው ልጅ ከ25 ዓመቱ በፊት በሚያዳብረው ልምድ ፣እውቀት ፣ ባህል ፣ ሀይማኖት ……. Whatever ነው የሚቀረፀው። ልክ አለመሆኑን ቢያውቅ እንኳን ለመቀየር ብዙ ጥረት እና ጊዜ ይወስድበታል። ከዛ በኋላ ባለን እድሜ ምንም ያህል እውቀት እና ልምድ ብናዳብር እንኳን ሳናውቀው በsubconscious የአዕምሮ ክፍላችን አማካኝነት አስቀድመን ወዳዳበርነው ልምድ እና እውቀታችን ስንሳብ እንገኛለን።» አለኝ። አደጋው ከደረሰበት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የህፃናት ማቆያውን ሊጎበኝ መጥተን ነው። ለህፃናቱን እኔ እየተመላለስኩ መጠየቅ አላቆምኩም ነበር እና አባታቸው አደጋ እንደደረሰበት አስቀድመው ያውቃሉ። ከበውት <እግዜአብሔርን አጊንተኸው ነው የተመለስከው?> ዓይነት የህፃን ጥያቄ ሁሉ ሲጠይቁት ሲመልስላቸው ነው የዋለው።

«እንዳለመታደል ሆኖ አብዛኛው ወላጅ ስታድግ ሁሉንም የምትረሳ ይመስለዋል እንጂ እያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸው ልጃቸው ውስጥ ልምድ እና ባህሪ ሆኖ የሚቀር አይመስላቸውም። ድሮ እንዲህ ብላችሁኝ ነበር ስትላቸው። <ቂመኛ ነሽ> ነው የምትባለው። 80%ቱ እስከ 5 ዓመት ነው የሚያድገው ነው ያልከው? ሆ! እስከ 5 ዓመትህማ እንኳን የሚናገሩ የሚያደርጉት ትርጉም ሰጥቶህ የምታስታውሰው ሆ!» አልኩኝ ልጆቹ እየቦረቁ ሲጫወቱ እያየኋቸው

«ምናልባት ድርጊቶቹን ትረሻቸው ይሆናል። ስሜቱ ግን አብሮሽ ያድጋል። ፍርሃት፣ ጭንቀት፣ ደስታ፣ በራስ መተማመን፣ ………. በዙሪያሽ የሚከናወኑ ክንውኖች ያሳደሩብሽ ስሜት እሱ አብሮሽ ያድጋል። »

ከህፃናቱጋ ስንመለስ መኪና ውስጥ «መቼ ነው ታዲያ መውጣት በለመደ እግርህ ማለቴ ዊልቸርህ ወደ ስራ የምትመለሰው?» አልኩት። በዊልቸር ሆኖ ማንም ሰው እንዲያየው አይፈልግም ነበር። የእኔን ቤተሰቦች ጨምሮ ከሀኪሞቹ ውጪ ማንም ሰው እንዲጠይቀውም እንዲያገኘውም አይፈልግም። ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ከሀኪም ቤት ውጪ በፍላጎቱ የወጣው።

«ለዛ እንኳን ዝግጁ አይደለሁም!!» አባባሉ በቅርብ ዝግጁ ለመሆንም ሀሳቡ ያለው አይመስልም። «አሁንማ ከሞላ ጎደል የወረቀቱን ስራ አውቀሽዋል። በየቀኑ ቦታዎቹ ላይ መገኘት ነውኮ የቀረሽ!»

«አንድ ወረቀት አንብቦ ለመፈረም አስሬ ጠይቄህ መቶ ጊዜ አንብቤ ምኑን ለመድኩት? ደግነቱ ሰዎችህ ገራሚዎች ናቸው። ታውቃለህኣ በስራህ እንደማከብርህ? ያንተ ጉብዝና አንድ ነገር ነው። ስራውን ቀጥ አድርገው የሚይዙ ብዙ አንተዎች ማፍራት ሌላ ሌቭል ነው።»

«<ውጤታማ የቢዝነስ ሰው እርሱ ቢኖርም ባይኖርም ስራው ሳይጓደል የሚቀጥልበትን የቢዝነስ ተቋም መገንባት የቻለ ነው> ይል ነበር አባቴ። እሱ ነው ብዙውን ያስተማረኝ። ምናልባት ለእኔ ሊተውልኝ ስላሰበ ይመስለኛል የለፋብኝ።»

«ኦኬ! እያልከኝ ያለኸው የሀብትህ ምንጩ የአባትህ ውርስ ነው?»

«ነበር ማለት ይቀላል!! እየፃፍን ብናወራው የሚሻል መሰለኝ። ከመፅሃፉ አንዱ ምዕራፍ አባቴ ነው መሆን ያለበት። (በምናቡ እየሳለ እንደሆነ እያስታወቀበት።) መፅሃፉ 6 ምዕራፍ ይኖረዋል። የመጀመሪያው ምዕራፍ እናቴ ሁለተኛው ምዕራፍ ማዕረግ ሶስተኛው ምዕራፍ አባቴ አራተኛው ምዕራፍ እኔ አምስተኛውም አንቺ ስድስተኛው ምዕራፍም አንቺ ።»

«ኦኦ ! ያንተ ባዮግራፊ ውስጥ እኔ ሁለቴ ምን አደርጋለሁ? የእናትህ እና የማዕረግ ምዕራፍ እስካሁን የመጣንበት ታሪክ ነው። የአባትህንም በሚቀጥለው ምዕራፍ አገኘዋለሁ እሺ! ያልገባኝ ሁሉም ምዕራፍ ውስጥ አንተ አለህ አይደል? ለምን ለብቻው ሌላ ምዕራፍ? እህህ ረስተህ ከሆነ ሁለት ሚስቶች ነበሩህ!»

«ሶስቱ ምዕራፎች አያጠያይቁም። ከሶስቱ በኋላ ነው ያለማንም ሰንሰለት አዲስ ብቻውን አዲስ ሆኖ የቆመው። ያ ነው ትክክለኛው እኔ ብዬ የምለው የህይወት ምዕራፍ! ፀዲ እና ሰብሊ የዚህኛው ምዕራፍ አካሎች ናቸው። ምዕራፍ አምስት ካንቺ ጋር የነበረኝ የህይወት ምዕራፍ ነው። እኔ የምፅፈው። ያንቺ ገፅ ካልገባበት ግን ታሪኩ ይጎድላል። ስድስተኛውን ምዕራፍ የራስሽን ገፅ አንቺ ትፅፊዋለሽ ማለት ነው። ድራፍቱን ከጨረስን በኋላ ባለሙያ እናማክራለን። ግልፅ ሆንኩ አሁን?»

«አዎን! በስሜት ረገድ ከፋፍለው ብትባል በየትኛው ምዕራፍ ነበር ደስተኛ የነበርከው?» አልኩት ምዕራፍ አምስት ቢለኝ እየተመኘሁ

«በአንፃራዊ ምዕራፍ አራት። ግን የሰው ልጅ 100% ደስተኛ ነኝ የሚልበት ምዕራፍ ይኖረዋል? የደስታ የምትያቸው ቅፅበቶች ይኖሩ ይሆናል እንጂ!»

«በህይወት ውስጥ ልንደርስበት የምንሮጥበት ስኬት ሁሉ ግቡ ደስተኛ መሆን አይደል?»

«ይሆናል። ለእኔ ግን ደስተኛ ሆኖ መኖር ከሚለው ይልቅ ትርጉም ያለው ህይወት ኖሮ ማለፍ የሚለው ብልጫ ይይዝብኛል። ከግለሰብ ደስታ አንፃር ካየሽው አንዳንድ ሰው ሆዱ ካልጎደለ፣ አልጋው ከሞቀ ፣ ለአናቱ መጠለያ ካለው ደስተኛ ነው። አንዳንዱ ደግሞ ሊያሳካው የሚያልመው ህልም ይኖረውና እሱጋ ለመድረስ ሲባዝን ባጅቶ ሲሳካለት ደስተኛ ይሆናል። አንዳንዱ ደግሞ ከራሱ ይልቅ ለሌሎች መኖርን የደስታው ምንጭ አድርጎ ይኖራል። ሁሉም ባሰመሩት የደስታቸው ሰበብ ደስተኞች ናቸው እና ከደስታ አንፃር ካየነው ሁሉም ተሳክቶላቸዋል። ስኬት ውጤቱ ነው ብዬ አላምንም መንገዱ እንጂ። እንደእኔ ያ መንገድ በደስታም ይሁን በሃዘን በመውደቅም ይሁን በመነሳት ትርጉም ያለው ሲሆን ጠዋት የምትነቂበት ምክንያት ከሰጠሽ ስኬት ነው።»

ባያብራራልኝም ምን ማለቱ እንደሆነ አውቃለሁ። 316 ህፃናት የሚያሳድግ ተቋም መመስረት እና ማስተዳደር (ያውም እንደወለዳቸው ልጆች የሚጠነቀቅላቸው እና የጎደላቸውን የሚከታተላቸው ሰው ሆኖ)፣ ባጠቃላይ ለ7293 ሰራተኞች ደሞዝ የሚከፍሉ ድርጅቶች ባለቤት መሆን( ያውም እያንዳንዱ ሰራተኛ የሚያከብረው እና በመልካምነት የሚያወሳው አለቃ ሆኖ )ትርጉም ያለው ህይወት ኖሮ ማለፍ ካልተባለ ምን ሊባል ይችላል?

እቤት ደርሰን ብዙም ሳንቆይ ሁለታችንም ላይብረሪ መሄድ ነበር የፈለግነው። ኮምፒውተሬን ይዤ ምዕራፍ ሶስትን ለመቀጠል ጓግቼ ምንጣፉ ላይ ተዘረፈጥኩ። የሆነኛው ሀሳቤ ውስጥ ይሄን ታሪክ ማወቅ የብዙ ጥያቄዬ መልስ ይመስለኛል። ምዕራፍ አምስትጋ የምንደርስበት ሰዓት እረፍት ነስቶ ያጓጓኛል። የተወሰኑ ገጾች ስለአባቱ ባህሪ እና ከእናቱጋ ስለነበረው ግንኙነት ከፃፍን በኋላ የሚቀጥለው አንቀፅ ላይ ስሜቱ ተቀያየረ።

« አብሬው ስራ ስጀምር መጠነኛ የሲሚንቶ ፋብሪካ ነበር የነበረችው። እየቆየ እየተስፋፋ እና ሌላ ቢዝነሶች ላይ መሰማራት ጀመረ። ቀስ በቀስ ብዙ ሃላፊነቶችን ይጥልብኝ ጀመር እናም ውጤታማ በሆንኩለት ቁጥር በሱስ አቅሏን ላጣች ሰካራም እናቴ ጥሎኝ መሄዱ የሚበላውን ነፍሱን ቀስ በቀስ የሚሽርለት ይመስለኛል። አንድ ቀን እኔና እሱ ባር ቁጭ ብለን ቢራ እየጠጣን <ለምንድነው ጥለሃት የሄድከው?> ብዬ ለዘመናት ልጠይቀው እየፈለግኩ ያልቻልኩበትን ጥያቄ ጠየቅኩት። መልሱ መልስ ያልሆነ ግን ሌላ ጥያቄ የማያስነሳ መልስ ነበር። <ምንም ቢሆን አንተን ለመተው በቂ ምክንያት አይሆንም ነበር።> አለኝ። ያላለኝን ብዙ ነገር ሰማሁለት። <አንተ ላይ ምንም አይነት መጥፎ ስሜት የለኝም! አሁን ትልቅ ሰው ሆኛለሁ። ብዙ ነገሮችን ያኔ በምረዳበት መንገድ አልረዳም! በህይወትህ የምትመርጣቸው ምርጫዎች
ትልቅ ሰውም ብትሆን ሁሌ ልክ ላይሆኑ ይችላሉ። ላንተ ልክ ቢሆኑ እንኳን ሌላ ሰው ትጎዳበታለህ!! አሁን ሳስበው አልከፋብህም! ምንም ይሁን ምክንያትህ በጊዜው ላንተ ልክ ነበር።> አልኩት። ትከሻዬን ቸብ ቸብ እያደረገ አባቴ ለመጀመሪያ ጊዜ እንባ ሲታገለው አየሁት። በእኔ ፊት ላለማልቀስ ትቶኝ ወጣ።

ምክንያቱ በእኔ ምክንያት የሚሰማውን ፀፀት ማጠብ ይሁን ወይም ወንድሜ ለሃላፊነት የማይበቃ እንዝህላል በመሆኑ ሲደመር አብሬው እየሰራሁ ብቃቴን ማስመስከሬ አላውቅም። ለሚስቱ የሚገባትን ድርሻ ከፍሎ በአክስዮን መልክ እና በገንዘብ ለወንድሜም ድርሻውን በገንዘብ ከፍሎ ለእኔ ገንዘብ ሳይሆን የቀረውን ስራውን በሙሉ አስረክቦኝ ነበር የሞተው።» መፃፌን ትቼ ስሜቱን ለማንበብ ቀና ስል ገባው።

«ታሞ ነው የሞተው። ቁጭ ብዬ የሱን ሀዘን እያቦካሁ እየጋገርኩ የምተክዝበት ብዙም ጊዜ አልነበረኝም። ስራው እሱ በህይወት እንደነበረው ሁሉ መቀጠል ነበረበት። ያለእርሱ እንዴት እንደምወጣው የማላውቀውን ሀላፊነት ነበር ያሸከመኝ። ሁለተኛ ፍቅረኛዬም ባትሆን ማዕረግ አጠገቤ ነበረች። በየቀኑ ማለት በሚቻል ደረጃ አጠገቤ ነበረች። ስራዬ ላይ አባቴን በሚገባ ተክቼ በየእለቱ ፍሬያማ እየሆንኩ መጣሁ። አባቴ በህይወት እያለ ብዙም ቦታ የማልሰጠው የሚስቱ ጥላቻ ይሄኔ በይፉ መታየት ጀመረ። ወንድሜም የእኔ ስራ በገንዘብ ቢተመን የሚያወጣውን እኩሌታ መጠን በጥሬ ገንዘብ ያገኘ ቢሆንም በየእለቱ እንደጥፋተኛ ይከሰኝ ነበር። እርግጥ ገንዘቡን ለመበተን አንድ ዓመትም አልፈጀበትም ነበር። ከእነርሱ ጋር መኖሩ ምቾት ስለነሳኝ የራሴን ቤት ገዝቼ ወጣሁ። የሆነ ቀን ከማዕረግ ጋር እራት እየበላን።

<አሁንማ የማይደረስብህ ሰው ሆንክኮ! በሰልክ። መቼ ነው ታዲያ የራስህ የሆነች ሴት ከጎንህ የምትኖረው? አሁን ሁሉ አለህ! በዛ ላይ ማንም ሴት አይታ ምራቋን የምትውጥልህ ወንድ ሆነሃል። ለምንድነው ፍቅረኛ የማይኖርህ?> አለችኝ። ልነግራት አስቤው አልነበረም። ብቻ ግን ብዙ ጊዜ ይሄን አጀንዳ አንስታ ስትጠይቀኝ ስቄና ቀልጄ እንደማልፈው ማለፍ አቃተኝ።

<የሴትም የፍቅርም መለኪያዬኮ አንቺ ነሽ። ሳልሞክር ቀርቼ መሰለሽ? ካንቺ ጋር አይደራረሱም! አንቺን የምትሆን ሴት ከየት ላምጣ? ካለች ጠቁሚኝና ዛሬ ነገ ሳልል ላግባት!> አልኳት።

<ሳትዋሽ አሁንም ለእኔ ስሜት አለህ?> አለችኝ

<ላንቺ ያለኝ ስሜት መቼም ጎድሎ አያውቅም!> አልኳት። በሰዓቱ አላውቅም ምን እንዳሰበች አላውቅም ምን እንዳሰብኩ። ሳመችኝ። ተያይዘን ቀለጥን። እነዚህ ጊዜያት ቀኖቼ ሰኞና እሁድ አይለዩም። ጠዋት እስፖርት ሰራለሁ ፣ በቀን ውስጥ ከ16 ሰዓት በላይ ስራ ነኝ፣ ማዕረግን አገኛታለሁ። ይኸው ነበር። ቀንህ ደባሪ እና የሚገመት ነው ብላ የተወችኝ ሴት ያው የተለመደ እና ተመሳሳይ ቀን መኖሬን ሳላቆም የእሷ ስሜት ለምን ተቀየረ ብዬ አልጠየቅኩም። <አሁን በስያለሁ> ያለችኝን አመንኩ እና የበሰለችው ማዕረግ የሰከነ ህይወት ትፈልግ ይሆናል ብዬ ለራሴ ነገርኩት። ምንስ ቢሆን ደግሞ ማዕረግ የእኔ ትሁንልኝ እንጂ ምክንያቷ ምንም ቢሆን ሂሳብ ልሰራ? ያንን ሂሳብ መስራት የሚችል ጭንቅላት ከኖረኝማ ምኑን እሷ አዘዘችብኝ? ወድያው አንድ ላይ መኖር ጀመርን።»

«እህህህ?» አልኩኝ። ሳቅ አለ። <ያልተነካ ግልግል ያውቃል > አይነት

«ከሷ ውጪ የማውቀው ሴት የለም። እንደእርሷ የማውቀውም ሰው የለም። ቢያንስ በሰዓቱ የማስበው እንደዛ ነበር። ፍቅረኛዬ ሳትሆንም በየቀኑ በህይወቴ ውስጥ አለች። ያቀፋት ክንድ የእኔ ቢሆን ስመኝ ፣ የያዛት እጅ ጣቶች የእኔ ቢሆኑ ሳልም፣ ስለፍቅረኞቿ ባወራችልኝ ቁጥር እነርሱን በሆንኩ ስል ሳላስበው የእኔ ሆነች። የእኔ መሆኗን ላክብር ወይስ ምክንያት ላስላ? አይሆንም ነበር። ለሁለት ዓመታት ሳንጋባ አብረን ኖርን! የሷ ያልነበረ ነገር አልነበረኝም። እኔ ፣ ገንዘቤ፣ ቤቴ ኢቭን ስራ ቦታ አብራኝ እንድትውል ስለፈለግኩ ከምትሰራበት ቦታ ለቅቃ አብራኝ መስራት ጀምራ ነበር። ከሁለት ዓመት በኋላ ልንጋባ ሽርጉድ ስንል ነበር የሰርጉ ወረቀት ተበትኖ ባለበት የእንጀራ እናቴ ሽማግሌዎች ይዛ መጥታ እቤት ይቅርታ ጠየቀችኝ። የማላውቀው ደመነፍሴኮ ነግሮኛል በመርዝ የተጠመቀ ይቅርታ መሆኑን። የተደገሰልኝ ሳይገባኝ ይቅርታ ተባብለን ተቃቀፍን። በሽማግሌዎቹ ፊት <ይሄ ይቅርታ አላማረኝም። ይቅርብኝ። ይለፈኝ> ይባል ነበር? ማለት ግን አምሮኝ ነበር። ወዲያው ከማዕረግ ጋር ስለሰርጉ እቅድ ሲወያዩ ያልገባኝ ስሜት ማጅራቴን እያሳከከኝ ነበር።»

አልጨረስንም........

@wegoch
@wegoch
@paappii
ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት ….. እኔ የቀጠልኩት
(ክፍል አስራ ዘጠኝ ………. ሜሪ ፈለቀ)

«ማዕረጌን ከጎኔ አድርጌ የተጋበዝነውን እራት ልንታደም ስንሄድ ዘውድ እንደተደፋለት ልዑል አንገቴን ቀና አድርጌ በኩራት ነበር። ምንም የጎደለኝ ነገር አልነበረም። ማዕረጌ ከጎኔ ነበረቻ!! ከሶስት ሳምንት በኋላ እሷ እንደተመኘችው በሷው አባባል <እልልልልልልል በተባለለት ሰርግ> ወዳጅም ጠላትም ምስክር ሆኖ ባደባባይ የእኔ ልትሆን ነዋ!! ዓለም የእኔ ብቻ ነበረች። የሆነኛው ዓለም በጦርነት ንፁሃን እንደማይሞቱ፣ የሆነኛው ሀገር ህፃናት በርሃብ እንደማይሞቱ፣ የሆነኛው የዓለም ክፍል በተፈጥሮ አደጋ እንደማይተራመስ ……… በቃ ከእኔና ከእሷ ውጪ ሌላ ምንም ዓለም እንደሌለ …… ዓለም በእኔና በእሷ ዙሪያ ብቻ እንደምትዞር …… ዓለሜ እሷ ብቻ እንደሆነች ….. እንደዛ እያደረገኝ ነበር። ፈጣሪን ለሰጠኝ ዓለም እየደጋገምኩ አመሰግነው ነበር።

የሚመጣውን ሰርጋችንን እና እርቁን አስመልክቶ የተወሰነ የማውቃቸው ጎረቤቶች እና ዘመዶችን ያካተተ እራት እንጀራ እናቴ ነበረች ያዘጋጀችው። ወንድሜም ያለወትሮው ብሉልኝ ጠጡልኝ ሲል አመሸ። ለደስታችን ውድ የተባሉ መጠጦች ተከፈቱ። እያስመሰልኩ አልነበረም ውስጤ ልቤን ስልብ የሚያደርግ ፍርሃት ሃሳቤን በየመሃሉ ከመስረቁ ውጪ ደስተኛ ነበርኩ። ማዕረግ ወይን እየጠጣች ነበር እና በመሃል ውሃ መጠጣት ፈልጋ ጠረጴዛው ላይ ያለው ውሃ በማለቁ ላመጣላት ራሴው ተነሳሁ። ወደጓዳ እየሄድኩ ድሮ የእኔ ክፍል ከነበረው መኝታ ቤት ድምፅ ያለው ለቅሶ ሰማሁ እና አንኳኩቼ ገባሁ። የጎረቤታችን ልጅ ናት። ከረሜላ የምገዛላት ሚጢጥዬ ልጅ ነበረች።

<ምነው ሉሲ ምን ሆነሽ ነው እዚህ ተደብቀሽ የምታለቅሺው?> ብዬ ላባብላት አጠገቧ ተቀመጥኩ። ከእናቷ ጋር በወንድ ምክንያት ተጣልታ እንደሆነ ስትነግረኝ በጣም ገርሞኝ።

<ስንት ዓመትሽ ነው?> አልኳት።

<14> አለችኝ። የእውነቷን እያለቀሰች ስለነበር የምላት ግራ ገብቶኝ አቅፌ እያባበልኳት እናቷ ለእርሷ ብላ እንደሆነ እና በዚህ እድሜዋ ወንድ እንዳያታልላት ስመክራት የሆነ ደቂቃ ቆየሁ።

ከዚህ በኋላ የተፈጠረው ዛሬም ድረስ የሆነ መጥፎ ቅዠት ነው የሚመስለኝ። ኮሪደሩ ላይ የእንጀራ እናቴ የሰራተኛዋን ስም እየጠራች ስሰማ እና ሉሲ እሪሪሪሪ ብላ ስትጮህ እኩል ነበር። እየሆነ ያለውን የምረዳበት ምንም ሰከንድ አልነበረም። የእንጀራ እናቴ በሩን በርግዳ ስትገባ ሉሲ እኔ የሆነ ነገር ያደረግኳት ዓይነት እየተንዘፈዘፈች ሄዳ ጉያዋ ተወሸቀች። እሪሪሪሪ እያለች ትጮሃለች። ከሳሎን ሁሉም ሰው እየተሰባበረ ለወሬ ሲመጣ እንጀራ እናቴ ትደነፋለች

<ምን አይነቱ አውሬ ብትሆን ነው ትናንት አይንህ እያየ ያሳደግካትን ህፃን ለማባለግ ሰውነትህ እሺ ያለህ! ቱ!> የቀረው አሟሟቂ ያማትባል፣ በስመአብ ይላል።

<ሉሲ? እንዴ ንገሪያቸው እንጂ ምን እንደተፈጠረ? በስመአብ እንዴት እንደዛ ያደርጋል ብላችሁ ታስባላችሁ?> ብዬ ወደፊት ከመራመዴ ሉሴ ድራማዋን ከወነችው። ሸሽታ እንጀራ እናቴን እየተጣበቀች እና እንባ እና ሳጓን እየደባለቀች
< እንዳልጮህ አፌን አፍኖኝ! ህህ ህህ ወይኔ እናቴ! > የሰዎቹ ፊት ዱላ ሆኖ የሚጋረፍ ቢሆን የሚታይ የሰውነት አካል እስከማይኖረኝ ሰንበር በሰንበር እሆን ነበር። የማዕረግ እይታ ግን ከሁሉም የከፋ ነበር። <ከአውሬ ጋር ነበር የምኖረው?> አይነት እይታ!

<ኸረ ባካችሁ ሰዎች እኔ ምንም አላደረግኩም! ውሸቷን ነው!> ብል ማን ይስማኝ። ወንድሜ

<መጠጡንኮ በላይ በላዩ ስትለው ይህቺን ዓመልህን ስለማውቅ ቀስ በል ብዬህ ነበር።> ብሎ በልግጫ እሳቱ ላይ ጋዝ አርከፈከፈ። በአካባቢው ያልነበረችው የልጅቷ እናት ግርግሩን ከመቀላቀሏ ፖሊስ ካልተጠራልኝ ማንም ከዚህ ንቅንቅ አይልም ብላ ቀወጠችው። ሁሉም ነገር የሆነ በድካም ካለፈ ቀን በኋላ ያለ ቅዠት ነበር የሚመስለኝ።

ፖሊስ ጣቢያ ሄጄ ሳድርም የማስብ የነበረው ማዕረግ ልታየኝ ስትመጣ የሆነውን ሁሉ እንዴት እንደማስረዳት እንጂ የተከሰስኩበትን ምክንያት እንኳን በውል አላሰላሰልኩትም <በስካር መንፈስ የ14 ዓመት ህፃን በመድፈር!> ከአፋቸው ስሰማው ራሱ አንዳች መዘግነን ዘገነነኝ። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ስንት ዓመት ለምታውቀኝ ማዕረግ ማስረዳት ህመምም መዘግነንም ነበረው።

<አታውቂኝም ማለት ነው? ምን ላገኝ ብዬ ነው ህፃን የምደፍረው? እንኳን አስገድጄ ልደፍር ደስታሽ ከስሜቴ ጋር ካልተመጣጠነ ሰውነቴ እንደማይታዘዝልኝ አታውቂም?> አልኳት ልቤ እንክትክት ሲል እየታወቀኝ

<አላውቅም! ማንን ማመን እንዳለብኝ አላውቅም! እሷስ ምን ልታገኝ ትዋሻለች? እንደዛ ሰውነቷ እየተርገፈገፈ ውሸቷን ነው ብዬ ማመን ከበደኝ። አንተን ስለማውቅህ ደግሞ እውነቷን ነው ብዬ ማመን ጨነቀኝ። ጠጥተህ ነበርኮ! አላውቅም ምን ማሰብ እንዳለብኝ!> አለችኝ

<ልብሽን ስሚው! ልብሽ አዲስ ይሄን ያደርጋል ብሎ ያምናል?> አልኳት ድክም ብሎኝ። ያላደረግኩትን ነገር አለማድረጌን ለማሳመን የምሄደው እርቀት ጭራሽ ለጥፋቴ ማስተባበያ እየሰጠሁ ዓይነት ስሜት እንዲሰማኝ እያደረገኝ።

<እሺ ምንድነው የምሆነው? ከተፈረደብህ ምንድነው የሚውጠኝ?> ስትለኝ ለመጀመሪያ ጊዜ የፍርድ ሂደት ላይ መሆኔን አስታወሰኝ።

<እንዴ በፍፁም አይሆንም! ባላደረግኩት ነገር ሊፈረድብኝ አይችልም!>

<አለማድረግህን በምንድነው የምታረጋግጠው? የህክምና ማስረጃዋ መደፈሯን መስክሯል። በቦታው የነበሩ ሰዎች የእንጀራ እናትህን ጨምሮ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ይሄን የሚሽር ምን ማስረጃ ታቀርባለህ?>

<እንዴ? ኸረ በእግዚአብሄር?> ከማለት ውጪ ማለት የቻልኩት የለም።

<ጎበዝ የተባለ ጠበቃ ቀጥሪያለሁ። አላውቅም ሌላ ምን ማድረግ እንደምችል። ከሰዓት መጥቶ ያገኝሃል> ብላ አባብላኝ ስትሄድ ልቤ ወደቀ። እሷ በሙሉ ልቧ ካላመነችኝ ማንንም ማሳመን እንደማልችል ገባኝ። ወደ ፈጣሪ ደጋግሜ አጉተመተምኩ። ምን ብዬም እንደምፀልይ ግራ ገባኝ። <ሌላ ሰው ባያውቅ አንተ ንፅህናዬን ታውቃለህ አይደል እንዴ? በውሸት ሲመሳጠሩብኝ ዝም ብለህ አታይምኣ? አንተ ሁሌም የእውነት ፈራጅ ነህ! በሰው ሳይሆን ባንተ እተማመናለሁ!> አልኩት። ከዚህ በኋላ የነበረው እልም ያለ አስፈሪ ቅዠት ነበር። ከእርሷ ውጪ የማምነውም የምቀርበውም ሰው ስላልነበረ የፍርድ ሂደቱ የሚወስደውን ጊዜ ስላላወቅን ስራዎቹን ውክልና ለእርሷ ሰጠኋት።

<ጥሪ የደረሳቸውን ሰዎች ሰርጉ መሰረዙን ለማሳወቅ በተቻለኝ መጠን ለማዳረስ ሞክሪያለሁ።> ያለችኝ ቀን የእርሷን ህይወት ስላበላሸሁ ራሴን ጠላሁት። ፊቷ ላይ የነበረው መሰበር እኔን አደቀቀኝ። የሆነውን ሳስበው ራስምታት ይለቅብኛል።> » ብሎኝ ራሱን እንዳመመው ነገር የግንባሩን ጠርዞች ይነካካ ጀመር።

«ታርፋለህ? ወይ በቃ ነገ እንቀጥል?» አልኩት ስለእውነቱ ግራ ገብቶኝ እንጂ ልለው የፈለግኩትስ <ምን ጉድ ነው ያሳለፍከው? አንድ ሰው ይሄን ሁሉ መከራ አልፎ እንዴት ይቆማል? ኸረ ይሄ ሁሉስ የአንድ ሰው ህይወት ነው?> ነበር።

«ኖ! እዚህ ምዕራፍ ላይ መመለስ አልፈልግም! ጨርሼው መገላገል ነው የምፈልገው! ይልቅ ልቀመጥ! አስቀምጪኝ !» አለኝ። ሶፋው ላይ እንዲቀመጥ እያገዝኩት የእውነቴን አሳዘነኝ። በእያንዳንዱ ትናንቱ ውስጥ የበደለኝን በደል እየሸረፈው እየሸረፈው ከራሴ ህመም በላይ ለእርሱ መታመም ጀምሬያለሁ።
«በናትህ አትከልክለኝ ልቀፍህ?» አልኩት። አይዞህ መባል ሞቱ ነውኮ አውቃለሁ! ሲታዘንለት የተሸነፈ ነው የሚመስለው ያንንም አውቃለሁ። ግን በቃ አቅፌው ዝም ማለት ፈለግኩ። ራሱ አቀፈኝ! በሱ ህመም እኔ ተባበልኩ። ደረቱ ላይ እንዳቀፈኝ ብዙ የማፅናኛ ቃል ብለው ብዬ አስባለሁ። እንደማይወደው ስለማውቅ ዝም ብዬ ለደቂቃዎች ከታቀፍኩ በኋላ ወደ ፅሁፋችን ተመለስን።

«የትኛው ይበልጥ እንደሰበረኝ አላውቅም። ባላደረግኩት ነገር መከሰሴ ወይስ ምስክሮቹ የራሴው ቤተሰቦች መሆናቸው? ምንስ በደል ብበድላቸው ነው በዚህ መጠን ሊከፉብኝ የቻሉት? እኔ የማውቀው ወንድሜንም ሆነ እንጀራ እናቴን የበደልኩት ትዝ አይለኝም። እነሱ ግን ፍርድ ቤት ቆመው ምለው በውሸት ሲመሰክሩብኝ ዓይናቸው ውስጥ የነበረው የበቀል እርካታ በምንም ልኬት የማልገልፀው ነበር። 7 ዓመት! 7 ዓመት ተፈረደብኝ! ከእውነት ጎን የሚቆመው አምላክ ከእነሱ ጎን ቆመ!»

«እመቤቴ ድረሽ!» አልኩኝ መጻፉን ትቼ

«አዎ! 7 ዓመት የሚለውን ዳኛው ሲናገር ዞሬ ማዕረግን አየኋት። አንጀቷን በአንድ እጇ ደግፋ ድምፁ የማይሰማ ለቅሶ ስታለቅስ አየኋት። እጅ የሰጠ ለቅሶ ፣ ተስፋ የቆረጠ ለቅሶ ፣ ዛሬም ድረስ ጭንቅላቴ ውስጥ ያለ ምስሏ ነው። ለመጨረሻ ጊዜ የተወችልኝ ምስሏ ነው። የፍርድቤቱ የእንጨት ወንበር ላይ ወደኋላ ተደግፋ በቀኝ እጇ የተጣበቀ አንጀቷን ደግፉ ስቅስቅ ብላ የማይሰማ ለቅሷ የምታለቅሰዋ ማዕረግ!! ለመጨረሻ ጊዜ ያየኋት ያኔ ነው። የእስር ቤት የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ከዛሬ ነገ ማዕረግን መጥታ አያታለሁ በሚሉ ናፍቆቶች የተሞላ ስለነበር የእስር ቤቱን ድብርት ፣ አለመመቸት ፣ ምግብ አለመጣፈጥ አላስተዋልኩትም። ብደውል ባስደውል ስልኳ ዝግ ነው። ወር አለፈ። ስራ ቦታ መታሰሬን ማንም እንዳያውቅ ፈልጌ ስለነበር ለማንም እኔ በበኩሌ ምንም አላልኩም! የሷን ደህና መሆን አለማወቅ ሊያሳብደኝ ሲሆን ለእንድርያስ ደወልኩለት። ሊያየኝ እስር ቤት መጥቶ ማዕረግ ስራ ቦታ ብቅ እንደምትል ግን ድባቴ ውስጥ እንደሆነች ነገረኝ። መኖሯ አፅናናኝ። ልታየኝ አለመፈለጓ ደግሞ አመመኝ። ሁለት ወር ሶስት ወር …… ሲለቃት ትመጣልኛለች እንጂ የእኔ ማዕረግ አትተወኝም ብዬ ጠበቅኳት። ቀኑ በጨመረ ቁጥር መጠበቄ እየቀነሰ ፣ ተስፋዬ እየሞተ ፣ በምትኩ ውስጤ ጨለማ እየነገሰ መጣ። ወራት ነጎዱ…….. ውስጤ ፀጥ እያለ፣ ውስን ድምጾች ብቻ ውስጤ እየቀሩ፣ የማዕረግን የመጨረሻ ምስል ጨምሮ በጣም ውስን ምስሎች ብቻ ጭንቅላቴ ውስጥ እየቀረ ከቀን ወደ ቀን እየሞትኩ እንደሆነ ይሰማኝ ጀመር።

ሁለት ድፍን አመት! ልታየኝ አልመጣችም። ስራ ቦታ በጣም አክቲቭ ሆና እየሰራች እንደሆነ ሰማሁ። ደጋግሜ ደወልኩ። ደጋግሜ ደብዳቤ ላኩላት። ልታየኝ አልፈለገችም። በሁለተኛው ዓመት ጎብኚ መጥቶልሃል ተብዬ ስጠራ ልቤ ዘላ ምላሴን ነክታው ነበር የተመለሰችው። በመጨረሻም ልታየኝ መጣች ብዬ!! በምትኩ በቁሜ ልትጨርሰኝ የተከሰተችው የእንጀራ እናቴ ነበረች። እንደወዳጅ ሰላም ካለችኝ በኋላ
<ከሌላ ሰው ከምትሰማው ብዬ ነው ራሴው ልነግርህ የመጣሁት> ብላ የሰርግ ቴንኪው ካርድ አቀበለችኝ። ያየሁትን ከማምን የራሴን ጤንነት አለማመን ተሻለኝ እናም ሰሞኑን ጭንቅላቴ ልክ አይደለም አይደል? የእኔ ማሰቢያ ተናግቶ ነው እንጂ የእኔ ማዕረግ ሰርጋችን በተሰረዘ በሁለት ዓመቱ አትሞሸርም! ያውም ደግሞ መቀመቅ ሊከተኝ ካሴረብኝ ወንድሜ ጋር! በፍፁም!!

<እናትህ ህይወቴን ቀምታኝ እሷ ስትስቅ እኔ ባዶ ቤቴን እና ልጄን ታቅፌ እንባዬን ቁርስ እራት ስበላ ለዓመታት ኖሬያለሁ። እጅ ሳልሰጥ ነው አባትህን የመለስኩት። አንተ ደግሞ በተራህ የልጄን ህይወት ስትቀማው ዝም ብዬ የማይህ ነበር የመሰለህ? ሙትቻ ! እያየሁህ ከሞት ተነስተህ ልትነግስ?> ያለችኝን ሰምቻታለሁ። ምን ያህል እንደምትጠላኝ ድምፅዋም ፊቷም ላይ ይሰማል ይታያል። እግሬን እየጎተትኩ ማዕረግ ከወንድሜ ጉያ በነጭ ቬሎ አጊጣ ያለችበትን ካርድ በእጄ ይዤ ከኋላዬ ትቻት ሄድኩ። የሚቀጥለው ሲዖል ነው። ራሴን የምስት ይመስለኛል ግን አውቃለሁ። ጭንቅላቴን ድቅድቅ ጨለማ ተቆጣጥሮታል። የእናቴ ሬሳ ሽታ እንደገና አፍንጫዬ ላይ ነገሰ። ሁለት ድምፆች ብቻ ጭንቅላቴ ውስጥ ይሰሙኛል።

<አዲስ አንተ ካልሞከርክ እኔ ላግዝህ አልችልም! መናገር ከፈለግክ ታገል። አንተ ብቻ ነህ ራስህን ልታድነው የምትችለው> የሚለው ያኔ ከእናቴ ሞት በኋላ መናገር ሲያቅተኝ ያከመኝ ዶክተር ንግግር እና

<አንተ ደግሞ በተራህ የልጄን ህይወት ስትቀማው ዝም ብዬ የማይህ ነበር የመሰለህ?> የሚለው የእንጀራ እናቴ ድምፅ።

ከጨለማው ሌላ ጭንቅላቴ ውስጥ ያለው ያ ከእጄ የማይጠፋው የወንድሜ እና የማዕረግ ምስል ነው። አዕምሮዬ የእኔ ሳይሆን ቆይቶ ስነቃ ይታወቀኛል። እታገላለሁ። ግን አቅም ያንሰኛል። እንዳለፈው ጊዜ ዲዳ እንዳልሆንኩ አውቃለሁ ግን ምንም ቃል ታዝዞ ከአፌ አይወጣልኝም። የሆነ የማላውቀው ሃይል አስፈሪ ጨለማ ውስጥ የጣለኝ ይመስለኛል። ፍርሃቴ ሰውነቴን ያርደዋል። ቀኑ ቅዳሜ ይሁን ሰኞ፣ ወሩ ሀምሌ ይሁን ጥር ቀኑ ጠዋት ይሁን ውድቅት ለሊት አላውቅም። የሆነ ቀን ጭንቅላቴ ምልስ ሲልልኝ ልብሴ ላይ ሽንቴን ሸንቻለሁ። የዛን ቀን የአዕምሮ ህክምና ሆስፒታል ተወሰድኩ። እጅ ላለመስጠት እታገላለሁኮ ግን ከራሴ ጨለማጋ እንዴት እንደምዋጋ አላውቅበትም። ጨለማው ይዞኝ ሲሄድ ይታወቀኛል። ከምስሎቼ እና ከድምፆቼ ጋር በሚያርድ ፍርሃት ውስጥ ሲነክረኝ ይታወቀኛል። እንዴት ልውጣ? መንገዱ በየት ነው? መሞት እፈልግ እና አስበዋለሁኮ! ከዚህ ስቃይ ሞት ይሻላል እላለሁ። ግን አይሆንልኝም! »

እጆቼ ይፅፋሉ እንጂ እንባ እና ንፍጤ እየተቀላቀለብኝ እየተነፋረቅኩ ነው። እሱም ተመልሶ ይሄን ክፍል ላለማሰብ በሚመስል ቶሎ ለመገላገል ዓይነት እያወራኝ ፊቱ ግን አሁን ከሚያወራልኝ ጨለማ ጋር ግብ ግብ የገጠመ ይመስል በስቃይ ተሸፍኗል።

«ሁሉን ያያል ይሰማል የተባለው ፈጣሪ ሊያድነኝ አልመጣም! ማዕረግ ከሞት ልትቀሰቅሰኝ አልመጣችም! አባቴ ሊታደገኝ የለም! እኔ እና እኔ ብቻ! ቀስ በቀስ የሰላሜ ሰዓት እየረዘመ፣ የትግሉ ሰዓት እየቀነሰ መጣ። እዚህጋ ሌላ ድምፅ ጭንቅላቴ ውስጥ ተጨመረ ድምፁ የአባቴ ነው ቃላቶቹ ግን እኔ የማስባቸው ናቸው። <ይሄን ሁሉ አልፈህማ እዚህጋ እጅ አትሰጥም!> የሚለኝ! በመሃል ረጭ ሲልልኝ <ብቻ አንዴ ከዚህ ስቃይ ልውጣ እንጂ መቼም እዚህ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ አልመለስም> እላለሁ። ወደ ራሴ ስመለስ 11 ወር እንዳለፈኝ አወቅኩ። ሌላ ሰው ሆንኩ። ፍጹም ሌላ ሰው ……. ከዚህ በኋላ ያለውን አዲስ እወደዋለሁ። ማንም ይወደዋል። ምክንያቱም ብዙ ዋጋ ተከፍሎበታል።» ብሎኝ በረዥሙ የመገላገል ትንፋሽ ተነፈሰ። እየተነፋረቅኩ እንደሆነ አሁን ነው ያየኝ። እንደመደንገጥ ብሎ እቅፉ ውስጥ እንድገባ ዘረጋልኝ። ጭራሽ ብሶብኝ አረፍኩት።

«ለምን አልነገርከኝም? ምንአለ ነግረኸኝ ቢሆን?»

«ከዛስ? ነግሬሽ ቢሆን ልታስተካክዪኝ ትሞክሪ ነበር። ዳሜጅ ሆኗል ብለሽ ያሰብሽውን ፓርቴን ልታበጃጂ ትደክሚ ነበር። ከዛ ለማጠፋው ጥፋት ሁሉ እንደሰው በጥፋቴ ሳይሆን ባለፈው ቁስሌ እየዳነሽ ይቅር ትዪኝ ነበር። አይደለም?»

«እሺ ከዚህ በኋላ አስቸጋሪ ወቅት የለኝም በለኝ?»

«አልነበረኝም! አንቺ እስከመጣሽበት የህይወቴ ምዕራፍ!»
«እኔኮ ግን ለትናንት ስቃይህ ያበረከትኩት አንዳችም ነገር አልነበረም። በሙሉ ልቤ ከማፍቀር ውጪ የበደልኩህ አልነበረም። የእናትህን፣ የማዕረግን ፣ የወንድምህን፣ የእንጀራ እናትህን …… ሁሉንም እኔን አስከፈልከኝ። ነግረኸኝ ቢሆን ፍቅሬ አይጎልም እንደውም ይበልጥ አፈቅርህ ነበር።»

«አልገባሽም! እዛ ጨለማ ውስጥ ራሴን ከምመልስ ምንም አደርግ ነበር።» ላለፉት ዓመታት ያላለቀስኩት እንባዬ ሁሉ ይግተለተል ጀመር። ስቃዩ የሱ ሳይሆን የእኔ ይመስል ያባብለኝ ያዘ።

«እሺ ከዛስ?»

«ከዛማ አዲስን ከተበታተነበት እፍ እፍ ብዬ አራግፌ ገጣጥሜ አቆምኩት። እስር ቤት ሶስት ዓመት ከሁለት ወር እንደታሰርኩ በምህረት ተፈታሁ እና ከተበዳይ ቤተሰብጋ እርቅ መፈፀም ግዴታ ስለነበረብኝ ያን አደረግኩ። ወንድሜ እና ማዕረግ ድርጅቶቹን እንዳልሆነ እንዳልሆነ አድርገው በእዳ እና በቋፍ ሁለቱ ጭራሽ ተሽጠው። የቀረኝ እዳ እና ማሽኖች ብቻ ነበሩ።እነርሱ ከሀገር መውጣታቸውን ሰማሁ። ቤቴ ብቻ በእኔ ስም ስለነበር ተከራይቶ ኪራዩ ለእንጀራ እናቴ ገቢ እየሆነ ጠበቀኝ። ቤቴን ሸጬ እዳዎቹን ከፋፍዬ ሀ ብዬ ቢዝነሱን ጀመርኩ። አዲስ አዲስን ሰራሁ። ትናንት እና ትናንት ላይ የነበሩኝን ሰዎች ሁሉ ከማህደሬ ሰረዝኩ። ትንሽ ቢያታግለኝም እንደገና ወደመስመር ገባሁ። እሺ አሁን የምታለቅሺው ለምንድነው?»

«እኔእንጃ! አልወጣልኝማ!»

.......አልጨረስንም…….

@wegoch
@wegoch
@paappii
ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት ….. እኔ የቀጠልኩት
(ክፍል ሀያ ……….)

«ትናንትህ ላይ በበደሉህ ሰዎች ነው ዓለምን በሙሉ እየዳኘህ ያለኸውኮ! በዙሪያህ ያሉ ሰዎች በሙሉ እንደእነሱ ናቸው ማለት አይደለም! በተቃራኒው የሆኑ ሰዎች አሉ። አንተ ያደረግከው ለማንም ምንም እድል አለመስጠትን ነው።» ከምሳ በኋላ ፀሃይ ቡና አፍልታ ሳሎን ቡናችንን እየጠጣን ነው ስላለፉት ውሳኔዎቹ የጀመርነውን የሀሳብ ልውውጥ የቀጠልነው።

«ካለፈው ውድቀትሽ ወይም ስህተትሽ መማር ማለት ታዲያ ምንድነው? ትናንቴን አልደግምም ማለት አይደል? ያለፈውን ስህተትሽን አለመድገም አይደል? ያለፈው ስህተቴ አለልክ ሰዎችን ማመኔ ፣ ያለገደብ ራሴን እስኪያሳጣኝ ከሰው ጋር መቆራኘቴ አይደል? ያንን ነው ያስወገድኩት!! የሰዎችን ስሜት ለውጥ፣ ክፋት ወይም ቅንነት ልትቆጣጠሪ አትችዪም። ልትቆጣጠሪ የምትችዪው የራስሽን ስሜት እና ራስሽን ብቻ ነው። ሰዎች ለምን እንደእኔ አልተሰማቸውም ማለት አትችዪም። በጠበቅሻቸው ልክ ሳይገኙልሽ ሲቀሩ እንዴት ማለት አትችዪም! ምክንያቱም እንዳንቺ ጥበቃ ሳይሆን እንደራሳቸው ስሜት እና እውቀት ነው ህይወታቸውን የሚመሩት። እነሱን መቀየር አትችዪም! አንቺ ስለእነሱ ያለሽን መጠበቅ እና ቅርበት ግን መወሰን ትችያለሽ!! ከማንኛውም የሰው ፍጡር ምንም ባለመጠበቅ ውስጥ እና ባለመተሳሰር ውስጥ ራሴን አትርፊያለሁ።»

«በፍፁም ከማንም ምንም አልጠብቅም ወይም በምንም ማንንም አልደገፍም አልያም ከማንም ጋር በስሜት አልቆራኝም ማለት አትችልም። ያንተም ህይወት ከዛ እጅግ የራቀ ነው። ለምሳሌ ከልጆችህ ጋር ያለህን ቁርኝት እየው! ለእነርሱ የምትሆነውን መሆን ለማንምና ለምንም ስትሆን አይቼህ አላውቅም! ሌላ ምሳሌ እንጥቀስ ቢያንስ በትንሹ ከሰራተኞችህ ጥንቅቅ ያለ ስራ ትጠብቃለህ! አንተ ባትኖር እነርሱ እንደማይኖሩት ሁላ እነርሱ ባይኖሩም ያንተ ቢዝነስ የለም!»

«የሆነ ጊዜ ነግሬሻለሁ መሰለኝ። በህይወት ውስጥ ለደስተኛነት ከመኖር ትርጉም ያለው ህይወት መኖር እንደመረጥኩ። ከዛ የጨለማ ውድቀት በኋላ ስነሳ ባለፈው አንቺ እንዳልሽው ደስተኛ ህይወት ለመኖር ዳከርኩ። እኔ ባለፍኩበት ዓይነት መንገድ ላለፈ ሰው ደስታ ከፍርሃት ጋር የተለወሰ ነው። እዛ የዝቅታ ወለል ላይ ደርሰሽ ካላየሽው ምን እንደምል ብዙም ላይገባሽ ይችላል። የሆኑ የሆኑ ጠርዞች አሉ ፍራሃትሽ የሚፈጥረውን ሀሳብሽን እና እውነታውን መለየት የሚያስቸግርሽ ጠርዝ። እሱ ጠርዝ ላይ መቆም አለብሽ ትግል አይጠቅምሽም። ምክንያቱም ያቺን ጠርዝ ካለፍሽ አለቀ። አዲሱን አዲስ መስራት ስጀምር ማን መሆን እንደምፈልግ እና ምን ዓይነት ህይወት መምራት እንዳለብኝ የራሴን የህይወት መመሪያና መርህ መቅረፅ ነበረብኝ። የማንንም ህይወት መኮረጅ አያዋጣኝም ነበር ምክንያቱም ማንም እኔ ያለፍኩበትን መንገድ አላለፈም። ለውጡ ይሄ ነው ያለማንም እርዳታ ሲሆን ራስሽን የሰራሽው ምርጫ አለሽ ምንና ማን መሆን እንደምትፈልጊ። እናም ደስታን ውስጤ ስፈልገው ከፍርሃቴ ጋር የተለወሰ ነበር እና በምትኩ የምኖርለት እና ትርጉም የሚሰጠኝ ዓላማ ላይ ራሴን ቢዚ ማድረግን ተማርኩ። ስለዚህ ልጆቼን እና ስራን እንደ ዓላማ ነው የምወስዳቸው።»

«በዚህ መጠን ትኩረት እና ጊዜ ለምትሰጠው ዓላማ ታዲያ ምንም ዓይነት የስሜት ቁርኝት የለኝም ማለት ትችላለህ?»

«ራሴን አያሳጣኝ እንጂ ትኩረቴን የማሳርፍበት ዓይነት ቁርኝት አይጎረብጠኝም። ጥያቄው የሚመጣው እኔን ጥያቄ ውስጥ ካስገባ ነው። ከራሴ እና ከምንም ወይም ከማንም መምረጥ ካለብኝ ራሴን ነው የምመርጠው። እውነቱንስ እናውራ ከተባለ ማንስ ራሱን አይደል የሚመርጠው?»

«እንዴ በፍፁም ራስህን የምትሰጥለት ሰው አለ። ኤጭ በምን ላስረዳህ ፍቅርን ታጣጥልብኛለህ እንጂ (ይሁን ቀጥዪ ዓይነት በእጁ እና በጭንቅላቱ ንቅናቄ ምልክት አሳየኝ።) እሺ! አይደለም ፍላጎትህንና ስሜትህን ነፍስህን ብትሰጠው worth የሚያደርግ የፍቅር ልክ አለ» ስለው ከት ብሎ ሳቀ

«መቼም ፍቅር እስከመቃብርን ወይም ሮምዮ እና ጁሌትን አትጠቅሺልኝም! ለስሜት ትስስር ብለሽ ሞትን ከመረጥሽ ቂል ነሽ ነው የምልሽ!! እኔና አንቺ እውነቱን አይደል የምናወራው? እስከሞት ልወድ የምችለው ራሴን ብቻ ነው!!» ብሎኝ ዊልቸሩን አንቀሳቀሰ። ስሜቱ ጥሩ ስላልነበር ለሁለት ቀን መጻፋችንን አቁመን ነበር።

«ለምን ዛሬ ቦታ አንቀይርም? እዚሁ እንፃፍ ወይም ውጪ!» አልኩት
«ውጪ አሪፍ!» አለኝ። ለፀሃይ ሳሩ ላይ ፍራሽ እንድታነጥፍ ነግሬያት ኮምፒውተሬን ላመጣ ወደ ላይብረሪ ሄድኩ። ፍራሹ የተነጠፈበት ዛፍ ስር የጥላው ቅዝቃዜ እና የቅጠሉ ቀዝቃዛ አየር እያጫወተን እሱ ትራስ ደራርቦ ተጋድሞ እኔ ቁጭ ብዬ መፃፍ ቀጠልን።

«ምዕራፍ አምስት!» ብሎ ሊቀጥል ሲል ሳላውቀው ጮህኩ።
«እንዴ? አራትን በአንድ ገፅ ልታልፈው አትችልም! ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉኮ! ከዛ ሁሉ ድቅድቅ ጨለማ በኃላ አዲስን በቃ ሰራሁት ብለህ አንባቢን ልታሳምን አትችልም። ኸረ ደግሞ ፀዲን እና ሰብለን እዚህ ምዕራፍ ውስጥ ልናነባቸው አይገባም? ከቤተሰብህ ጋር እና ከማዕረግ ጋር የነበረህ ታሪክስ እንደዛው በእንጥልጥል ይዘጋል? »
«ኸረ ቆይ እሺ (ከት ብሎ እየሳቀ) የት ሄድኩብሽ አለሁ አይደል?» ብሎ ቀጠለ።

« ለተወሰነ ጊዜ የመረጥኩት መንገድ ራሴን በስራ ቢዚ ማድረግ ነበር። ጎን ለጎን ሙያዊ ድጋፍ ያስፈልገኝ ስለነበር ሳይካትሪስት ጋር ክትትል ማድረግ ነበረብኝ። በትክክል የሚጠቅመኝን ህክምና የሚያደርግልኝ ሳይካትሪስት ማግኘት እጅግ ከባዱ ነበር። አንዳንዶቹ ዝም ብሎ መስማት ይመስላቸዋል መሰለኝ ሙያው ማስታወሻ እና እስክሪብቶ ይዘው ያስለፈልፉኛል። አንዳንዶቹ የሚሰጡሽ ምክር ደግሞ ራሳቸው ምክር እንደሚያስፈልጋቸው ያሳያል። የብዙ ሳይካትሪስት ቢሮ እና ፊት ከጎበኘሁ በኋላ በትክክል ሙያውን የሚያውቅ ፣ ለእኔ የሚያስፈልገኝ ህክምና የቱ እንደሆነ የገባው ዶክተር አገኘሁ። ከጊዜ ወደጊዜ ለውጡን የምገነዘበው ዓይነት ነበር። ከህክምናው ጎን ለጎን ራሴን በማንበብ ጠመድኩ። ንባብ ስልሽ እገሌ የሚባለው ደራሲ እንዲህ ብሎ ፅፏል ወይም እንትን መፅሃፍ ላይ ያለው ገፀባህሪ ምናምን እያሉ ጥቅስ ለማጣቀስ የሚረዳ ማንበብ ሳይሆን ልኖረው የምችለው እና ከራሴ ጋር የማዋህደው እውቀት ፍለጋ ነበር የማነበው። ለምሳሌ ሰዎች ያነባሉ። አንድን ርዕስ ነጥለን ብንወስድ ስለይቅርታ እልፍ ጥቅስ ይጠቅሱልሻል። የማይኖሩትን ህይወት ሊመክሩሽ ይችላሉ። ነገር ግን በህይወታቸው ለመጎዳት ምክንያት የሆናቸውን ሰውጋ ይቅርታ ማድረግ ዳገት ይሆንባቸዋል። ያውቁታል እንጂ እውቀታቸው የእነርሱ አካል አይደለም ወይም አይኖሩትም። ከእውቀቴ ከስሜቴ ከህክምናዬ እና ካለፈው ልምዴ ጨምቄ የመኖሪያ መተዳደሪያዬን ፃፍኩ። በየቀኑ ያን ለመኖር ራሴን አሰለጠንኩ። አዲሱ አዲስ የዚህ ውጤት ነው። አለቀ!!» ብሎ ትንፋሽ ሰበሰበ። የምፅፈውን ገታ አድርጌ

«የተነበበ ሁሉ እኮ ግን አይኖርማ?»

«ያስማማናል። የትኛው እውቀት ብትኖሪው እንደሚበጅሽ የምታውቂው አንቺ ብቻ ነሽ!! የምርጫ ጉዳይ ነው።» አለኝና እንደገና ቀጠለ።
«ስለእነፀዲ ስለእውነት ምን መፃፍ እንዳለበት እንጃ!! ፀዲን መፅሃፍ መደብር ነው ያገኘኋት። እውነተኛ ሀቀኛ ግን የምትፈልገውን ጠንቅቃ የምታውቅ ብልህ ነበረች።በዛ ላይ ታነባለች። ለተወሰነ ጊዜ አብረን ካሳለፍን በኋላ ተጋባን። በጊዜ ብዛት የምትቀይረኝ ይመስላት ስለነበር ብዙ ታገሰችኝ። በተለይ ለልጅ የነበራት ፍቅር ግን በእኔ የምትቀይረው ዓይነት አልነበረም እና መለያየት መረጠች። አሁንም ቢሆን ጓደኛሞች ነን። አብረንም ሳለን ጓደኝነታችን ያመዝን ነበር። ከዚህ የተለየ ይሄ ነው የሚባል የተለየ ዓመታት አልነበረም። ሰብሊ ትለያለች በግልፅ ከስምንት ዓመት በኋላ ስለምትካፈለው ንብረት ብላ እንደምታገባኝ ነግራኝ ነው የተጋባነው። ቀጥተኛነቷን እወደዋለሁ። ጭንቅላቷ ያስባል። በባህል ወግ ሀይማኖት ተፅዕኖ ያልሳሳ ራሷን የሆነ ማንነት ነው ያላት። አልጋ ላይ ጎበዝ ናት! እውነት ለማውራት ለማቴሪያል ያላት ጥማት ትንሽ ከመጭነቁ ውጪ የማትሰለች ዓይነት ነበረች። እየቆየች ከእኔጋር ፍቅር እንደያዛት ነገረችኝ። ምላሹን እንደማታገኝ ስታውቅ ሂሳብ ሰራች። በዛ ላይ ዓለምን እየዞሩ ማየት ህልሟ ነበር። እኔ ደግሞ በተቃራኒው መብላት እና መጠጣት እንኳን እቤቴ የሚያስደስተኝ ሰው ነበርኩ። ሰለቸኋት! እንደሷ የመዞር አባዜ ካለበት አንድ ሀብታም ጋር ተጣብሳ ፈታችኝ።» ትንሽ እንደማሰብ ብሎ

«ስለማዕረግ እስከአሁንም ምንም መረጃ የለኝም። እውነት ለማውራት ማወቅም አልፈልግም። እንጀራ እናቴም ብትሆን ከዘመናት በኋላ ቢሮዬ አፈላልጋኝ እስከመጣችበት ቀን ድረስ የማውቀው ነገር አልነበረም። ይቅርታ ልትጠይቀኝ ነበር የመጣችው (በፌዝ ሳቅ አለ) አንተ ላይ ላደረስኩት በደል እግዜያብሄር ቀጥቶኛል። ልጄ እንኳን ይሙት ይኑር አላውቅም! አለችኝ»

«እና ምን አልካት? ይቅር ብዬሻለሁ አላልካትምኣ?» ያልኩት አስቤው አልነበረም። ከት ብሎ ሳቀብኝ
« የምታምኚው አምላክ ይቅር በሉ ይል የለ? አየሽ ቅድም ያልኩሽን? የምናውቀውን ሁሉ አንኖርም እናወራዋለን እንጂ እኔን ለበደለችኝ በደል አንቺ ስላመመሽ ይቅር መባል እንደሌለባት አሰብሽ።» አለኝ ሳቁን እየቀጠለ
«እግዜር ራሱ ይቅር የሚላት አይመስለኝም። ይልቅ ንገረኝ።»
«አላልኳትም። በተቃራኒው ውስጤን በጥሩ እምነት ሞልቼዋለሁ ብዬ ያመንኩትን የተጠራጠርኩት የዛን ቀን ነው። ያቺ ስትራመድ ሞገሷ መንገዱን የሚቀድላት የምትመስል ሴትዮ የእርሷ ያልሆነ ሰውነት እና አለባበስ አጅቧት ቢሮዬ ሳያት የማላውቀው ጭካኔ ነው የተሰማኝ። ዘበኞች ጠርቼ እንዲያስወጡልኝ ሳደርግ እያለቀሰች እንኳን ልቤ ምንም ርህራሄ አልተሰማውም። ለቀናት ስላየኋት ብቻ ስሜቴ ተረበሸ። ያለችበት ሁኔታ እንዳለችው ስቃይ ከሆነ ነፍሴ ደስታን መቃረም ስለሻተች እንዲያጣሩልኝ አደረግኩ። የማይሆን ባል አግብታ ቤቷን እና ንብሯቷን አሽጧት እንደእናቴ ሰካራም ሆና ከንቱ ህይወት እንደምትኖር ሰማሁ። ከዛ በኋላ ያየኋት ባለፈው እቤቴ ስትመጣ ነው። አደጋ እንደደረሰብኝ ስታውቅ ጮቤ እንደረገጠች አልጠራጠርም። ወይም ሽባ ስሆን የሚራራ ልብ ይኖረኝ ከሆነ ልታረጋግጥ ይሆናል። አላውቅም! ማወቅም አልፈልግም! ሳያት ሲኦል ነው ትዝ የሚለኝ!» አለኝ እየዘገነነው።

የሆነ ነገር ትዝ እንዳለው ሰው ብንን ብሎ። « የሆነ ቀን ቁጭ ብዬ ቴሌቭዥን ሳይ ሉሲን አየኋት። (ሳቅ ብሎ) ተዋናይ ሆና! በቲቪ ባየኋት በወራት ውስጥ ታዋቂ ሾው ላይ ኢንተርቪው ስትሰጥ ያልሆነ ነገር ተናግራ ህዝበ ኢትዮጵያ በስድብ ሲቀባበላት ከረመ። ባጋጣሚ ወሬውን ሰምቼ ፕሮፋይሎቿን ሳጣራ እያለቀሰች ህዝቡን ይቅርታ የጠየቀችበት ቪዲዮ አየሁ። የኛ ህዝብ የሚገመት ስድቡን እና ዘለፋውን ጨመረላት። ላገኛት ፈለግኩ ምናልባት ልጅ ስለነበረች ወይም አሁን አወዳደቋ ተሰምቶኝ፤ እድል ሰጥቻት ለምን ያንን እንዳደረገች መስማት ፈለግኩ። አገኘኋት! ያለችኝን አመንኩ። እሷ የእናቴ እና የእናቷ መጠቀሚያ ብቻ ነበረች። በሰዓቱ አባቷ ታሞ ብዙ ብር ያስፈልጋቸው ነበር። ያን እኔም አውቅ ነበር። አባቷን ለማዳን የሚጠበቅባት ያቺን ድራማ መስራት እንደነበር እና የቀረውን ተንኮል እና ማስረጃ እነርሱ እንደሚጨርሱት አሳመኗት። ያን በማድረጓ ለተወሰነ ዓመትም ቢሆን ለአባቷ እድሜ ቀጥላለታለች። የሚገርመው <አንተን ጎድቼ ባይሆን አባቴን ያተረፍኩት እመርጥ ነበር። ምንም አማራጭ በሌለበት ግን አባቴን በመምረጤ አልተፀፀትኩም! ለደረሰብህ ነገር ግን ይቅርታ!> ነበር ያለችኝ። (ፈገግ አባባሉ ስለሆነች የሚወዳት ልጅ የሚያወራ እንጂ መቀመቅ ስላስወረወረችው ልጅ የሚያወራ አይመስልም ነበር።)»

«ልገምት በህይወቷ ውስጥ የሆነ መልካም ነገር አድርገሃል?» አልኩት ከፈገግታው እየገመትኩ
«በጣም ዲፕረስድ ሆና ነበር። ከሀገር ወጥታ የምትማርበትን መንገድ አመቻችቼላት እንግሊዝ ነው ያለችው።» አለኝ
«ግራ የሆንክ ሰው ነህኮ!» አልኩት
«አውቃለሁ!! አትወጂውም ግን አንድ ሀሳብ አለኝ! ምዕራፍ አምስትን እኔ ልፃፈው! አንቺ ከፃፍሽው አስቢው በየመሃሉ የመልስ ምት ልትሰጪኝ ነው። ከፈለግሽ እኔ ልፃፈውና እያነበብሽ ማውራት እንችላለን!! ከዛ ደግሞ ስላንቺ ላንቺው መተረክ ደስ አይልም። ነፃነቴን አጊንቼ እራሴ ልፃፈው እና አንብቢው።» ልደርስበት የጓጓሁበትን ምዕራፍ ለመፃፍ ስለተከለከልኩ ከፋኝ ግን ደግሞ ነፃነት ያለውን አመንኩለት እና ቅር እያለኝም ቢሆን ተስማማሁ። ኮንፒውተሬን ዘግቼ ዝም ተባብለን ፍራሹ ላይ ጋደም እንዳልን ከንፋሱ ጋር ማውራት ያዝን

@wegoch
@wegoch
@paappii
ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት ….. እኔ የቀጠልኩት
(ክፍል ሀያ አንድ…………….. meri feleke)

ፅፎ እስኪጨርስ እረፍት አጣሁ። አስሬ ላይብረሪ እመላለሳለሁ። ጣቶቹ አሁንም 100% ስላልሆኑ ቀስ ብሎ ነው የሚፅፈው።
«እሺ የፃፍከውን ላንብበውና ትቀጥላለህ?» እለዋለሁ።
«አይሆንም ህፃን አትሁኚ!» ይለኛል።
«ጮክ ብለሽ አታንብቢልኝ! የምትጠይቂኝ ነገር ከሌለ በቀር! ለራስሽ አንብቢው» ብሎኝ ሶፋው ላይ አጠገቡ እንድቀመጥ በእጁ እየመታ አሳየኝ። መስገብገቤ የሆነ እርቦት ውሎ ምግብ እንደሰጡት ርሃብተኛ ነው።

«ከድምፅ ጋር የተለየ ፍቅር አለኝ። ሰውን ሳላየው በድምፁ ብቻ መልክ እስላለሁ። ከድምፁ ቃና ፐርሰናሊቲውን መገመት ደግሞ የበለጠ ደስ ይለኛል። ሬስቶራንት ውስጥ ከጀርባዬ ድምፅዋን ስሰማው ጠይም ጎራዳ ፣ ጥርት ያለቆዳ ያላት ፣ ጥርሷ የሚያምር ፣ ከንፈሯ ስስ ……… ገመትኩ። ድምፅዋ ውስጥ የዋህነት ደግሞ ለዛ ሙሉነት ነበር በመጀመሪያ የሰማሁት። ዞሬ ሳላያት ከውጪ ከመጡ ተለቅ ያሉ ሴት ጋር ስታወራ ድንገት ድምፅዋ ወደ ቁጣ ሲቀየር ግን ቃላቶቿን ደምሬ ስሰማት የሆነች መብረር ፈልጋ ክንፎችዋን የፊጥኝ የተያዘች ነፍስ ያላት ሴት …… እድሉን ብታገኝ እልም ብላ የምትበር ዓይነት። ሲትየዋ ጥለዋት ሲሄዱ ዞሬ አየኋት እና ወንበር ቀይሬ አጠገቧ መጣሁ። መልኳን ከከንፈሯ እና ከቀለሟ ውጪ ብዙ አልሳትኩም። ቀይ ናት የጎራዳ ውብ፣ ቆዳዋ ከመጥራቱ የተነሳ ውሃ ስትጠጣ በረዥሙ አንገቷ ወደሆዷ ሲንቆረቆር ውሃው ኩልል ብሎ የሚታይ የሚመስል። ከንፈሯ ብዙ ስጋ የፈጀ አበባ የመሰለ ፣ ጥርሷ በድዷ ጥቁረት ደምቆ የሚያጥበረብር ፣ ሴት ልጅ ከኋላ የፀጉሯ ማብቂያጋ የተደፉ ሉጫ ፀጉሮች ሲኖሯት ባላውቃት እንኳን እጄን ሰድጄ መንካት ይቃጣኛል። እሷ ደግሞ ወደላይ ባስያዘችው ጥቁር ፁጉሯ ጆሮዋ ስር ድረስ ለጥ ብለው ንካኝ ንካኝ የሚሉ ሉጫ ፀጉሮች ነው ያላት። የዓይኖቿን ውበት ውስጡ በጉልህ የሚነበበው ሀዘን አደብዝዞታል።

ስለስብዕናዋ ግን ሁሉንም ልክ ነበርኩ። ለመነበብ የማትከብድ ያልተወሳሰበች፣ የዋህ፣ ለዛ ሙሉ፣ ልዝብ ያለች ፣ ስርዓት ያላት ግን ደግሞ ግልፅ ነገር፣ ባህልን ባታምንበትም ለቤተሰብ እና ለማህበረሰብ ግምት ብላ የምትኖርበት፣ ሀይማኖትን ግን አምናበት የምትከተል (ብዙ የማውቃቸው ሰዎች ሀይማኖት ያላቸው ሲኦል እና ገነት አለ ስለተባሉ ነው። ከክፋት የሚቆጠቡት ሲኦልን ፍራቻ እንጂ መልካም መሆን ምንም ሽልማት የለውም ክፉ መሆንም ምንም ቅጣት የለውም ቢባሉ ለክፋት የሚግደረደሩ ናቸው። በሰውነት ሰው ስለመሆን ሳይሆን እግዚአብሔር ወይም አላህ ወይም ሌላኛው አምላክ በክፋታቸው ይቀጣናል ፤ በመልካም ስራቸው ይሸልመናል ብለው ስለሚያምኑ ነው ሚዛን የሚሰሩት። እስኪ እውነት እናውራ ከተባለ የብዙ ሀይማኖቶች መደምደሚያ ከሞት በኋላ ያለ ሽልማት ወይ ቅጣት ባይሆን ምን ያህል ሰው ሀይማኖት ይኖረው ነበር? ምን ያህል ሰው ቅዱስ የሚለውን ስራ ለመስራት ይጋጋጣል? ምን ያህሉስ ሰው ወደሀይማኖት ተቋማቱ እየሄደ አቴንዳንስ ያስመዘግብ ነበር?) የሷን ሀይማኖተኝነት የምወድላት ቅጣትን ከመፍራት እና ሽልማትን ከመሻት ባለፈ አምላኳን በየቀን ህይወቷ ታምንበታለች።

እያወራን ሳለ የምትኖርበት ትርጉም ያጣች ጣዕም አልባ ነፍሷን ሰማኋት። ማምለጥ እየፈለገ የታነቀ ስብዕናዋን አየሁት። ሙሉ አደርጋታለሁ ብዬ አስቤ አይደለም። በህይወቴ ውስጥ ከዚህ በፊት የነበሩት ሴቶች ከሰጡኝ የተለየ የምትጨምርልኝም ነገር አለ ብዬ አስቤ አይደለም። እሷ ቤተሰቦቿን የምታስደስትበት ባል ትፈልጋለች። እኔ ደግሞ አጉል ባልከረረ ትስስር ቀኔን የምታጅብልኝ ሴት እፈልግ ነበር። የዛኑ ቀን እንጋባ አልኳት። በዛ ላይ በየቀኑ የምነካው የኋላ ቤቢ ሄር አላት። እያወቅኳት ስመጣ ባወቅኳት በደቂቃዎች ውስጥ እንድታገባኝ መጠየቄ ልክ መሆኑን አወቅኩ። ምንም ነገር ላይ የተሰማትን እና ያመነችበትን አስተያየት ከመስጠት ወደኋላ አትልም። የማታውቀውን ነገር አላውቅም ለማለት አታፍርም! እንደአዋቂ ለመታየት እና እኔን ለማስደመም ቅንጣት አትሄድም። ጠያቂነቷን እወድላታለሁ። ትጠይቃለች። መልሴ ካላሳመናት ለምን አዳር አይሆንም ትጨቃጨቀኛለች። ጭንቅላቴን ስለምትፈትነኝ ከሷ ጋር የማሳልፈውን ጊዜ እወደው ነበር። ገና ሳንጋባ አንድ የኑሮ ህጌን አስፈረሰችኝ። ሰውን እርዳታ መጠየቅ! ልታገባኝ ስትስማማ ሰርግ እፈልጋለሁ አለችኝ። ምክንያቷ ለራሷ ከእገሊት የተሻለ ሰርግ ነበረኝ ለማለት ወይም ሰርግ በራሱ ትርጉም የሚሰጣት ነገር ስለነበረ አልነበረም። በቤተሰቦቿ አይን ለመሙላት ፣ አጎደልኩባቸው ብላ ያሰበችውን ለመካስ ፤ ውርደታቸው ሆንኩ ብላ ያሰበችውን ክብር ልትደርብላቸው፣ በሷ ሰርግ እነርሱን ለማድመቅ ነበር እና እውነት ለማውራት አሳዘነችኝ። ሰው በ34 ዓመቱ የራሳቸውን ህይወት ኖረው ላገባደዱ ቤተሰቦቹ ይኖራል? ማስደሰት አንድ ነገር ነው። እሷኮ የህይወት ግቧም ፣ ስኬቷም ፣ ደስታ ሀዘኗም፣ ህልሟም፣ ትርጉሟም እነርሱ ናቸው። ዘመኗን ሙሉ በፈጠሩባት የትንሽነት እና የከንቱነት ስሜት ለእነርሱ ኖራ ራሷን ፕሩቭ ካላደረገች (የማለፊያ አረንጓዴ መብራት ካላሳይዋት) የራሷን ኖሮ መኖር እንደማይገባት ለራሷ አሳምናለች። እንኳን የራሴን ሰርግ ልደግስ የሰው ሰርግ የማልታደም ሰው ሰርግ ልደግስላት ተስማማሁ። ችግሩ ከእኔ ወገን የሆነ ሰርጌን የሚያጅበኝ ዘመድም ሆነ ጓደኛ አልነበረኝም። ወይም ማንንም በዛ ልክ ማቅረብ አልፈልግም።

የእኔ ሚዜ አልባ መሆን ወይም ዘመድና ጓደኛ አለመኖር ለሰርጉ የነበራትን ደስታ ወደጭንቀት ቀየረባት። ይሄም ለራሷ አልነበረም!! ዘመድ አልባ ባል አገባች ብለው ቤተሰቦቿ እንዳያዝኑባት እንጂ! 34 ዓመት አልጨበጥ ብሏት ስታሳድደው የኖረችውን ህልሟን በሳምንታት ላስቀይራት አልችልም ነበር። በህይወቴ ውስጥ ከምጠላቸው ዋና ዋና ነገሮች ውስጥ አንዱን አደረግኩ። ስራ ቦታ አብረውኝ ብዙ የሰሩ የስራ አጋሮቼን ሚዜ እንዲሆኑኝ ጠየቅኩ። በእርግጥ ከስራ ውጪ ማርስ ላይ ልደር ወይ ጎዳና፣ ሚስት ይኑረኝ ቅምጥ ምንም መረጃ ለሌላቸው ለብልጫዎቹ የስራ ባልደረቦቼ የቅርበት ምልክት አድርገው ስለወሰዱት በደስታ ነበር የተቀበሉኝ። የስራ ህይወቴን እና የግል ህይወቴን ማዳቀል የፈጠረብኝን መወላገድ ድጋሚ ልደግመው ስለማልፈልግ የግል ህይወቴን በአድራሻም በወሬም አርቄ ነው ያኖርኩት የነበረው። ተጋባን!!

መጀመሪያ ላይ ድንበሩን የጠበቀ፤ ያልከረረም ያልላላም፣ ያልሳቀም ያልተኮሳተረም፣ የማያቃጥልም የማይበርድም ዓይነት ትርጉም የነበራቸው ዓመታት ነበረን። እንደአብዛኛዋ ሴት ስም ያለው ቦርሳ መሸመት ፤ አዲስ የወጣ ፋሽን ልብስ እና ጫማ አሳዶ ማጌጥ ፣ አዲስ በተከፈቱ ሬስቶራንቶች መታየት ፣ ፊቷን ሜክአፕ ለመሰራት ጊዜ መፍጀት …….

አታውቅበትም። የመኪና መንጃ ፈቃድ እንኳን ያወጣችው እኔ ጨቅጭቄያት ነው እንጂ ራሴው ነበርኩ የማመላልሳት። ከመሰረታዊ ነገሮች ውጪ ገንዘብ ካወጣች ባትነግረኝም አውቃለሁ። ለቤተሰቦቿ ነው!! ገንዘብ አንዱ የነፃነት በር መሆኑን ባውቅም ከሚያስፈልገኝ ውጪ ባለ ትርፍ ገንዘብ የሚያሳምነኝ ምክንያት ይሁን እንጂ አልሳሳም። ለፍቼ ያመጣሁት ገንዘብ ነውና ሚዛን በማይደፋ ምክንያትም እንዲበተን አልፈቅድም። (ገንዘብ የነፃነት በር ነው ያልኩት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለነፍሳችን አስተዋዕፆ ስላለው ነው። እንደአለመታደል ሆኖ ሀይማኖቶቻችንም ሆኑ ባህሎቻችንን ድህነትን የሚያሞካሹ እና ገንዘብን ልክ ከአምላካቸው ወይ ከስርዓታቸው ወይም
ከደስታቸው የሚያርቅ መዓት አድርገው ይጠምዱታል። ድህነት ውስጥ ደስታ ያለ ሀብት ደግሞ እንቅልፍ አልባ ለሊቶችን ያቀፈ አድርገው ስለነገሩን ሁሌም ገንዘብ ያለው ሰው ለገንዘቡ ሲል በደልን የፈፀመ እንቅልፍ አልባ ምስኪን ይመስለናል። ያለኝን ህይወት እወደዋለሁ። ማድረግ የምፈልገውን ነገር ማድረግ በፈለግኩ ሰዓት ማድረግ መቻሌን እወደዋለሁ። ከማንም ምንም ፈልጌ አላጎበድድም። ከማንም ምንም ስለማልፈልግ ድንበሬ ይከበርልኛል። ሰውኮ እንዲህ ነው …….. በተለይ በኢኮኖሚ እንደተደገፍከው እና የእሱ መኖር እንደሚያስፈልግህ ሲያውቅ ከሱ በምታገኘው ጥቅም ክብርህን ሊገዛህ ይዳዳዋል። በማጣትህ ሽንፈት ይጠቀምበታል። ገንዘብ ይሄን ነፃት ይሰጥሃል። በማንም በምንም ተሸናፊ ያለመሆንን። ከዚያ በተጨማሪ ገንዘብ ስላለኝ ነው ከእስርት ዓመታት በላይ የጭንቅላቴን ውጥረት ማርገብ በፈለግኩ ሰዓት የምሄድበት ዶክተር ያለኝ። ብዙ በተለያዩ ትራውማ እና የአዕምሮ ህመም እየተሰቃዩ አቅሙ ስለሌላቸው መታከም ያልቻሉ ሰዎች አሉና)

ግንኙነታችን ያሰመርኩትን መስመር መች እንዳለፈ አላውቅም። ከአራት ዓመታት በኋላ የሆነ ቀን እንደተለመዱት ምሽቶቻችን ልንተኛ ስንል የከንፈር ብቻ ያልሆነ መሳም ሳመችኝ። ስትስመኝ ወፍራም ከንፈሯን እወደዋለሁ። የዛን ቀን ከተለመደው ስሜት ውጪ ለእኔ መልዕክት ያደረሰ መሳም ሳመችኝ። አስቁሚያት መሳሟ ለውጥ እንዳለው ስነግራት ለውጡ እንዳልተሰማት ነገረችኝ። የዛን ቀን ለመግለፅ የሚከብድ ቅር የሚል ስሜት ተሰማኝ። የሆነ ያልተለመደ ወይም የረሳሁት ቅሬታ!! ከዚህ ስሜት በኋላ ብዙም ባልራቀ ቀን አልጋችን ላይ ጨዋታና ፍቅር ደርበን እየፈተልን

«እኔ ከዚህ በላይ ማስመሰል አልችልም! ከአቅሜ በላይ ነው የምወድህ!» አለችኝ እንደገረፉት የሁለት ዓመት ህፃን ልጅ ህቅ ህቅ እያለች። የሆነ መኪናዬን እየነዳው ተጋጭቶ ኤርባጉ ተነፍቶ ፊቴን ሲጠልዘው ያለው ዓይነት ስሜት ነው የተሰማኝ። ያ ስሜት እንደነበራት ባትነግረኝም አውቀው ነበርኮ የማላውቀው ከአፏ ሲወጣ እኔጋ ሊፈጥር የሚችለውን ስሜት ነበር። እንጂማ ብዙ የማውቃቸው ሴቶች ብለውኛል። የማናቸውም እኔጋ የፈጠረው ስሜት አልነበረም። የተሰማኝ ፍቅር አይደለም። ፍርሃት ነበር።»

(ይሄን ሳነበው ልቤ ዝቅ ሲልብኝ ተሰማኝ!!)

«ማብራራት የሚከብደኝ የማጣት ዓይነት ፍርሃት ፤ ላላስታውሰው ረስቼዋለሁ ያልኩት ድሮዬ ላይ የማውቀው የመለየት ፍርሃት ፤ የዛሬውን አዲስ ከአንድ ጠጠር እና አሻዋ ጀምሬ ከመገንባቴ በፊት ሰውነቴን የወረረኝ መሸነፍ!! የምትፈልገውን እንድታደርግ እና በፈለገችው ቁልምጫ እንድትጠራኝ ፈቅጄላት የመጨረሻዬ እንደሆነ የወሰንኩትን ፍቅር ሰራን። ደረቴ ላይ ሆና የፈገገ ፊቷን ሳትመልሰው እንቅልፍ ወስዷት ምን እንደማደርግ ሳስብ አደርኩ። ከራሴ በላይ እንዳላጣው የምሳቀቅለት ነገር እንዲኖረኝ አልፈልግም!! ከማዕረግ በኋላ ያለው አዲስ ስሜቱንም ውሳኔውንም ለማንም ለመናገር አይደለም ሊፈራ ሁለቴ አያስብም ነበር። አዲስ ፍርሃትን ከላዩ ከገፈፈ ዓመታት ተቆጥረዋል። የተሰማኝን ልነግራት መጨነቄ ይበልጥ ያለሁበትን ሁኔታ እንድጠላው አደረገኝ።

የኑሮ ዋና መርሄን ተፈታተነችው! በስሜቴ ከእኔ ውጪ ማንም አያዝበትም የሚለውን!! አዲሱ አዲስ ስሜቱ ራሱ የሚያዘው ፤ ማንም የማይሰለጥንበት ነው። አልነገርኳትም! በነገታው የእርሷን በቅርቤ መኖር ጠላሁት! ራሴን እንዳላዘው እየሆንኩ እንደሆነ ገባኝ። ትቻት ሌላ ክፍል ተኛሁ። እንቅልፍ ግን አልወሰደኝም። በመሃል በሩን ከፍታ መኖሬን አረጋግጣ ስትመለስ እሰማታለሁ። ሲነጋላት መጥታ

«……… ላፍቅርህ ብዬ ነው ወይ ያፈቀርኩህ? ለምን ትቀጣኛለህ?» ስትለኝ ውስጤ ሲረበሽላት ሰማሁት። ከማዕረግ ውጪ ለማንም ያልሆንኩት መሆን ስሆነው ታወቀኝ። ያ ስሜት ደግሞ ከደስታው በላይ ስቃይ እና ሰቀቀኑ ነው ትዝ የሚለኝ። «እንፋታ» ስላት ራሴን ሰማሁት። ከዛ በኋላ ለሳምንታት ከልቧ ልታወጣኝ እየታገለች መሰለች። አብራኝ መዓድ ብትቀመጥም ብዙ አታወራም!! ያሰብኩት ወይም የተመኘሁት ልክ እንዳልሆነ ፀዲ ስትደውልልኝ ገባኝ! ፀዲ የደወለችልኝ ቀን እራት ላይ ፀዲጋ እንደሄደች ስትነግረኝ የማውቀው ነገር በመሆኑ አልተገረምኩም። የተገረምኩት አድርጋ የማታውቀውን ሜካፕ እና ሊፒስቲክ ፊቷ ላይ ማየቴ ነበር። እቤት ውስጥ በቱታ ወይ በቁምጣ አልያም በኔ ቲሸርቶች እንጂ የማውቃት ቀሚስ ለብሳ አላስታውስም! የእኔን ትኩረት ለመሳብ መሆኑን ሳስብ አሳዘነችኝ። ያንን ግን እሷ እንድታውቀው ማድረግ አልፈለግኩም። በነጋታው ሀኪሜጋ ሄጄ የተፈጠረውን ነገርኩት።

«ወደሃታል! በፍቅር መሸነፍን እንደድክመት የምታይበት የራስህ በቂ ምክንያት አለህ ያን እረዳልሃለሁ! ግን ይህችኛዋ የተለየች ብትሆንስ? ከመስበር ይልቅ የምታጎብዝህ ብትሆንስ? ከእውነቷ የምታፈቅርህ ብትሆንስ? » አለኝ

«ዶክተር ባትሆንስ? ብትሆንስ በሚል ግማሽ እምነት ባትሆን የማጣውን መቋቋም አልችልም።»

«በባትሆን ፍርሃትህ በፍቅር ውስጥ ያለውን ደስ የሚል ህይወት ራስህን እያሳጣኸው ነውኮ! ራስህን እየቀጣኸው ነው!»

«am fine ፍቅር በሚሉት ግማሽ ደስታ ግማሽ ሰቀቀን ያለበት እሳት መጫወት ለጊዜው ምርጫዬ አይደለም። ደስታው ይቅርብኝ እና ሰቀቀኑንም ይዞልኝ ይሂድ!» አልኩት ተነስቼ ቢሮው ውስጥ እየተንጎራደድኩ።

«አዲስ! እንዳንተ በጥንካሬ የማይታለፈውን ያለፈ ሰው አላውቅም። የምትኖራቸው ህጎች እና መርሆች ስለፈወሱህ I appreciate that! ከነዚህ ዓመታት በኋላ እንኳን ይሄን ሁሉ በራስ መተማመንህን እና የገነባኸውን እውቀት የሚከድን ፍርሃት ካነቀህ አሁንም ከትናንት ህመምህ አልዳንክም! ስለሸሸኸው ደግሞ አታመልጠውም! እባክህ አስብበት! ደጋግሜ ከዚህ በፊት እንዳልኩህ እሱን ፋይል ገልጠህ ለማውራት ራስህን አዘጋጅ!» አለኝ

ያን ህመም ቀስቅሼ ላወራ መቼም አልዘጋጅም!! የሬሳ ሽታ፣ የጨለማ ጣር ፣ የሚያደነዝዝ ድምፅ……… ያለበትን ፋይል ከፍቼ መተንፈስ አቅቶኝ መንፈራገጥ የቅርብ ዓመታት እቅዴ ውስጥ አልነበረም!! ወደቤቴ ተመልሼ ላለፉት ሳምንታት እንደተለመደው ዓይነት መግባት መውጣቴን ቀጠልኩ። የሆነ ቀን እራት ላይ ሳትመጣ ቀረች። ፀሃይን እንድትጠራት ስጠይቃት።

«አሟታልኮ ተኝታ ነው የዋለችው! አላስተዋልካትም እንጂ ምንም ደህና አይደለችምኮ! እንደው በማያገባኝ መግባት አይሁንብኝና እንደው በመሃከላችሁ ምን ክፉ ዘልቆ ነው?»

«ገባሽ ፀሃይ! በማያገባሽ ገባሽ!» ብያት ወደመኝታ ቤት ላያት ሄድኩ። ስታለቅስ እንደዋለች ታስታውቃለች። እንፋታ ካልኳት ቀን በኋላ በትኩረት ያየኋት የዚህን ቀን ነው። ከሰውነቷ መክሳት የፊቷ መገርጣት አስደነገጠኝ። አጠገቧ ሄጄ ስነካት ታተኩስ ነበር። እጠይቃታለሁ። አትመልስልኝም! ክፍሏ በታመቀ አየር ተሞልቷል። መስኮቱን እየከፋፈትኩ ሀኪም ቤት እንድወስዳት ደጋግሜ ጠየቅኳት። ቃል አልመለሰችልኝም። ፊቷን አዙራ በትራሷ ተሸፈነች። እራሴን ከመውደዴና ከፍርሃቴ ያየለ ስሜቴ አቅፌ ምን ሆንሽብኝ? ሁላ ልላት እያመነታብኝ ተንጎራደድኩ። ኮቴዬን እየሰማች እስክወጣላት እንደምትጠብቅ ነገር በትራሷ እንደተከለለች ዝም አለች። ይሄኛው አዲስ ስሜቱን መለየት ተቸግሮ አያውቅም ነበር። ዝብርቅርቅ ያለ ስሜት ተሰማኝ። ጠልታኛለች ልታየኝም ልታናግረኝም የማትፈልግበት ደረጃ ደርሳለች። ግን ደግሞ ብትጠላኝ እንዲህ ትጎሳቆል ነበር?»
«ፊቴን አዙሬብህ አልነበረም! (የዛኔው ህመሜ ከማንበቤ ጋር መጣ) ባለቅስም እንደማታዝንልኝ አስቤ ሳታየኝ በትራሱ ተሸፍኜ እያለቀስኩ ነበርኮ!» አልኩት በቀዘቀዘ ድምፅ። እጁን ሰዶ የኋላ ቤቢ ሄሮቼን መነካካት ጀመረ።

«የትኛው ምን አይነት ስሜት እንደሰጠኝ አላውቅም። ብትጠላኝ እና አልፈልግህም በቃ ብላ ጥላኝ ብትሄድ ደስ ይለኛል። ግን ሙሉ በሙሉ ደስ ይለኛል? በእኔ ምክንያት እንዲህ መሆኗ ደግሞ የሚያስጠላ ስሜት ሰጠኝ። ለተከታታይ ቀናት እኔ ያለሁበት ላለመሆን ወሰነች። ፀሃይን ደህና እንደሆነች ስጠይቃት

«ዛሬ ምንም አትል! ቅድም አየር ልትቀበል ብቅ ብላ ነበር» አለችኝ። ልታየኝ አለመፈለጓን አከበርኩላት!!! ከቀናት በኋላ ግን አባቷ ሞተው በለሊት ደውለው መርዶውን ሊነግሯት ሽማግሌዎች እንደሚመጡ ነገሩኝ! ሳሎን ቁጭ ብዬ ስጠብቃቸው ሊነጋጋ ገደማ መጡ! ገና እሷ መርዶውን ሳትሰማ በፊት እጄ እና እግሬ ሲንቀጠቀጥ ይታወቀኛል። ሳሎን ብቅ ከማለቷ ሰዎቹን ስታያቸው የተፈጠረውን አውቃለች መሰለኝ በቁሟ ተገነደሰች። የሚርበተበት ሰውነቴ እንዴት እንደታዘዘልኝ አላውቅም። መሬቱ ላይ ከመውደቋ በፊት እጄ ደረሰ።

እስከዛሬ የሆንኩትን ሁሉንም በአንዴ ሆንኩት። እናቴ ሬሳ ላይ ስደርስ ከአፌ ቃል አልወጣ ብሎኝ ያማጥኩትን ከነሬሳ ሽታው፣ ማዕረግ ወንድሜ ክፍል ስትሳለቅብኝ ያደረግኩትን ፓኒክ ፣ ማዕረግ ወንድሜን እንዳገባች የእንጀራ እናቴ ከነገረችኝ በኃላ የከደነኝ ጨለማ ……. የለም ብዬ ያመንንኩትን እግዜር ለመንኩላት። <እሷ የምታምንህ አምላክ ካለህ ምንም አታድርጋት! ለእኔ ብለህ ሳይሆን ለእርሷ ብለህ ስማኝ ምንም አትሁን!> አልኩት። ሆስፒታል ተሰናብቻት እንደወጣሁ ታክሲ ጠርቼ ዶክተርጋ ሄድኩ።

. አልጨረስምንም .

@wegoch
@wegoch
@paappii
ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት ………. እኔ የቀጠልኩት

(የመጨረሻው ክፍል)

ሜሪ ፈለቀ


«ዶክተር ራሴን ሀኪም ቤት ካገኘሁት አልድንም ይብስብኛል እመነኝ! ትንሽ ቀን አይተኸኝ ከባሰብኝ ቃል እገባልሃለሁ ራሴው ሄዳለሁ» አልኩት። ከህክምና ጣቢያ ህክምናዬን መከታተል እንዳለብኝ ሲነግረኝ
እቤቱ ይዞኝ ሄደ። በዚህ ጊዜ እንዳለፈው ለማላውቀው ጊዜ ያህል ጨለማና ፍርሃቴ ውስጥ አልነከርም!! አስፈሪው ደቂቃ ትንሽ ነው። ያቃተኝ እንቅልፍ ሲወስደኝ የምቃዠውን ቅዠት ነው። የእናቴ ሬሳ ሆኖ ይጀምራል። በእጄ እንደታቀፍኳት ማዕረግ ትሆንብኛለች። ወይም ሚስቴን! በሌላኛው ቀን ደግሞ ልክ የአባቷን ሞት ስትሰማ እጄ ላይ እንደወደቀችው ስትወድቅ እጀምራለሁ። እንደታቀፍኳት ወይ ማዕረግን ወይ እናቴን ትሆንብኛለች። ለቀናት መተኛት ፈራሁ። ዶክተር መድሃኒት አዘዘልኝ። ለሳምንታት እሱጋ ቆየሁ። አሁንም ግን እሱ የሚለውን ፋይል ለመክፈት ዝግጁ አልነበርኩም! እቤቴ ለመመለስ ዝግጁ ስሆን ተመለስኩ። ከተመለስኩ በኃላ የአባቷን ለቅሶ አብሬያት ስላልነበርኩ ታኮርፈለች ብዬ ስጠብቅ ጭራሽ የእኔ ደህንነት አሳስቧት ደህና መሆኔን ትጠይቀኛለች። ትታኝ እንድትሄድ እፈልጋለሁ። ግን ደግሞ ራሷ ጠልታኝ እንድትሄድ እንጂ በእኔ ምክንያት ከሆነችው መሆን ሲደመር ከአባቷ ሀዘን ጋር ሌላ የከባድ ሀዘኗ ሰበብ መሆን አልፈልግም! ያን የማላደርገው ራሴን ላለመጉዳት ይሁን እሷን አላውቅም። ምናልባትም እናቴ እንዳስታቀፈችኝ አይነት ፀፀት ድጋሚ ላለመሸከም ፈርቼም ይሆናል።
ተናግሬ በማላውቃት ለቤተሰቦቿ በምትልከው ገንዘብ ተናገርኳት። የማትደራደርበት ዋልታዋ ስለሆነ ከጠላችኝ በላይ የምትጠላበት ምክንያት ያቀበልኳት ነበር የመሰለኝ። ትጥላኝ ትውደደኝ አላውቅም ግን ትታኝ አልሄደችም። ከሆነ ጊዜ በኋላ ማታ ላይ እራት ልበላ ተቀምጬ ምስቅል እንዳለች ወደሳሎን ገባች። የእናቷን ቤት መወረስ ስትነግረኝ ደነገጥኩ። አላወቅኩም ነበር! ስለእውነት ትኩረት ሰጥቼም ብሩ መከፈል ማቆም አለማቆሙን አላስተዋልኩም! ከእኔ ቃል እና ከእናቷ የእኔን ቃል እንደምታከብር ልገምት አልችልም ነበር። እያለቀሰች ትታኝ ስትገባ ተከትያት መሄድ ፈለግኩ። ለቀናት ሸሸኋት። ይሄ የመጨረሻዋ ይሆናል ብዬ ጥላኝ እንድትሄድ ስጠብቃት የሆነ ቀን ጠዋት ትታኝ እንደማትሄድ ቁርጥ አድርጋ ነገረችኝ። ዓመቱን ጠብቃ ብሯን ተካፍላ እንደምትሄድ ነገረችኝ። ንግግሩም ሀሳቡም የእሷን ስለማይመስል ግራ ገባኝ። ከፈለግክ አንተ ፍታኝ ብላኛለችኮ እንድትሄድ እፈልግ የለ? ለምንድነው በቃ እንፋታ ማለት ያቃተኝ? ለራሴኮ ደጋግሜ እነግረዋለሁ። እሷን አጊንተህ ራስህን ከምታጣ እና እሷን አጥተህ ራስህን ከምታተርፍ የቱ ይበልጥብሃል? ሁለቱንም በራሴ መወሰን አቃተኝ እሷንም ማጣት ፈራሁ ራሴንም ማጣት ፈራሁ። እሷ እንድትወስንልኝ ፈለግኩ። ራሷን ይዛልኝ እንድትሄድ!! ያገባኋትን ቀን ረገምኩ! አብረን ያሳለፍናቸውን ዓመታት ረገምኩ። የሆነ ቀን ያለወትሮዬ እሷን ሳላገባ በፊት አልፎ አልፎ የምሄድበት ባር ሄጄ ስጠጣ ድሮ እንጎዳጎድ የነበረች ኤክስ ተንጎዳጓጄን አገኘኋት። ድንገት የመጣልኝ ሀሳብ ከሷ ጋር ወደቤት መሄድ! ሊፈጠር የሚችለውን አሰላሁ። እንዴት ሴት ይዘህብኝ መጣህ ብላ በተደፈርኩ ትቀውጠዋለች ፣ ምንም ሳይመስላት ታልፋለች ፣ ትቀናለች ፣ ትከሰኛለች ……….. ምንም ሳትል ተነስታ ጥላኝ ትሄዳለች። አንዱ ይሆናል ወይም የቱም አይሆንም ብዬ ሄድኩ። ብቅም አላለችም!! ምንም ዓይነት ከሴት ጋር የመነካካት ፍላጎቱ ስላልነበረኝ ትንሽ እንደተጫወትን ተኛን። በነገታው ከሰዓት ማታ የተፈጠረውን እንዳወቀች የእርሷ ባልሆነ ስርዓት የለሽ ንግግር ነገረችኝ።
እዚህጋ ጥላቻዋ በደንብ ይታይ ነበር። የመከፋት ሳይሆን ከእኔ ከዚህ የተለየ እንደማትጠብቅ ዓይነት ንቀት ያለበት ነበር አነጋገሯ። እንድትጠላኝ አይደል ስፈልግ የነበረው? ደስታ ግን አልተሰማኝም! የዛን ቀን የእረፍቱ ቀን ቢሆንም ዶክተርጋ ደወልኩ። በምልልሳችን መሃል።
«አዲስ! የጥንካሬዬ መሰረት ናቸው የምትላቸውን መርሆችህን ማጣት መጀመርህን እያስተዋልክ ነው? እሷ ከህይወትህ እንድትወጣልህ መፈለግህ አንድ ነገር ነው። ከእርሷ እና ከራሴ ራሴን መረጥኩ አልክ እንጂ እሷንም ራስህንም እያጣህ ነው። ስሜትህን ለመካድ ወይም ለመሸሽ ስትል በጤነኛ ጭንቅላትህ የማታደርጋቸውን ነገሮች እያደረግክ ነው። አልመረጥክም አዲስ!» አለኝ።
ስለእርሷ መሄድ ወይም መቅረት እዚህና እዛ የሚረግጠውን ውል የለሽ ሀሳብ እና ስሜቴን ለማደብዘዝ ስራ እና መፅሃፎቼ ውስጥ አብዝቼ ጠለቅኩ። አብራኝ አትበላም። ላይብረሪም አትመጣም። ከክፍሏ አትወጣም!! አንድ እሁድ ልጆቼ ጋር በሄድኩበት እዛው መጣች። ልጆቼ እሷን ሲያዩ እየተንደረደሩ እናታችን መጣች ብለው ተጠመጠሙባት። በእነርሱ ፊት የተኳረፈ መምሰል ስላልፈለግኩ ጉንጯን ሳምኳት። የሳምኳትን ቦታ በእጇ ዳብሳ ፍዝዝ ብላ ቆመች። ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሳምኳት ነገር። ከልጆቹጋ እየተጫወትኩ ትኩረቴን ከሷ ላይ ማንሳት አቃተኝ። ፍዝዝ ብላ እያየችኝ አይኗ እንባ አቀረረ። ደረስ መለስ የሚለው ፍርሃቴ ተመለሰ። ልጆቹን ማጫወት ትቼ እሷን ማባበል አማረኝ። አሁንም ድረስ አልጠላችኝም። ይሄን ሁሉ አድርጌያትም አልጠላችኝም! የዛን ቀን ተጨማሪ በደል ላልበድላት ለራሴ ቃል ገባሁ! መቆየት እስከፈለገች ጊዜ ትቆይ መሄድ በፈለገች ቀን ትሂድ! አልኩ። ራሴን ረገምኩላትኮ! ከአሁን በኋላ ላልከፋባት ራሴን አስጠነቀቅኩላት!! ማታ ላይ ሻይ ልትወስድ ከክፍሏ ስትወጣ ያለቀሱ አይኖቿ አባብጠው ደፈራርሰዋል። ሳሎን መኖሬን ስታይ እንዳላያት ፊቷን ደበቀችብኝ ግን አይቻታለሁ።»
እያነበብኩ አንገቴ ላይ የሚርመሰመስ እጁን አንድ እጄን ልኬ ያዝኩት። የመከልከል ሳይሆን የመደረብ። የሰርጉ ቀን አጋጣሚ ላይ ስደርስ መጮህ ቃጣኝ።
«የረሳሁትን ሳቋን ተፍለቀለቀች። አውርቶ ሳይጨርስ ይግባባሉ። መቼ ነበር እንዲህ ደስተኛ የነበረችው? እሩቅ!! የማላስታውሰው ቀን ላይ ነበር እንዲህ ስትፍለቀለቅ ያየኋት ! ይሄን ሳቋን ቀምቻታለሁ። በአንድ በኩል ራሴን ረግማለሁ። በሌላ በኩል ደግሞ እንዲህ የተፍለቀለቀችለት ሰው እኔ ብሆን ብዬ አስባለሁ። ሰው እንዴት ሁለት ጠርዝ ላይ ያለ ስሜት እኩል ይሰማዋል? በጣም ስቀርባትም የምትፈጀኝ ስርቃትም የምትፈጀኝ ዓይነት ነገር ናት። መሃል ስሆን ደግሞ እሷን የምጎዳት!! ቀስ ብዬ ወጥቼ ወደቤት ሄድኩ። እቤት ሸኝቷት በሩ ላይ ከመኪናው ስትወርድ አቅፎ ሲሰናበታት አየኋቸው። ፍልቅልቅ ፊቷ አልተለያትም። »
«አንተኮ ቆንጆ ሆነሻል ስላልከኝ ነው እንደዛ ደስ ብሎኝ የነበረው! ለማዕረግ ያልካትን ታስታውሳለህ? ለእኔም የወንድ መለኪያዬ ነበርክኮ አድስዬ! ያንተን ሚዛን ተለካክቶ አይኔን የሚሞላ ማንም አልነበረም! (ለምን ዝም ብለሽ አታነቢም? ዓይነት አየኝ) እሺ ከአሁን በኋላ ዝም ብዬ አነባለሁ!» ብዬው ማንበቤን ቀጠልኩ።

«ውስጤ ያለው ብዙ ስሜት ቢሆንም ጎልቶ የሚሰማኝ ንዴቴ ነው። ማን ላይ እንደተናደድኩ አላውቅም! በትክክል በየትኛው ምክንያት እንደተናደድኩም አላውቅም!! ተነስቼ ወጣሁ። ድብልቅ ያለ አወዛጋቢ ስሜት ናጠኝ። ከሷጋ ለመጨረሻ ጊዜ ከሁለት ዓመት ከምናምን በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ካደረግነው ጉድጉድ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሆነች ሴት ጋር መሆን ፈለግኩ። በትክክል ምን ፈልጌ እቤት እንዲሆን እንደፈለግኩ አላውቅም! አብራኝ ያለችው ሴት የሆነ ነገር ያደረገችኝ ይመስል እንግልት የበዛበት ነገር እያደረግኳት እንደሆነ ገብቶኛል ግን አላቆምም።
የወጠረኝ ደም ሲበርድ የምፀፀት ነበር የመሰለኝ። በምትኩ የሆነ መገላገል አይነት ስሜት ተሰማኝ። የሚራወጥ ጭንቅላቴ እርግት እንደማለት።
«ቀንተሃል! ተናደሃል! በራስህ በሽቀሃል! ያን ግን እየተወጣኸው ያለኸው ትክክለኛ ቦታ አይደለም! በፊት እንደምታደርገው በመፅሃፎችህ ወይም በስራህ ራስህን ልትሸውደው ሞክረህ ሀሳብህ አልሰበሰብ ብሎሃል! ያን በወሲብ እየተካኸው ነው! የቀኑን ውጥረትህን ትቀንስበታለህ እንጂ ቋሚ መፍትሄ አይሆንህም! አንተ ራስህን ልትረዳው ካልፈለግክ እኔ ምንም ላደርግ አልችልም አዲስ መፍትሄው አንተጋ ነው!! ። ራስህን በጊዜያዊ እፎይታ ልትሸውደው አትሞክር! ውጥረት በተሰማህ ቁጥር ያን እፎይታ ፍለጋ በወሲብ ልትወጣው ትሞክራለህ! ስትደጋግመው ልክ እንደማንኛውም ድራግ ነው። የሚሰጥህ እፎይታ መጠን እየቀነሰ ይመጣና ዜሮ ይሆናል። ይሄኔ ውጥረቱ ብቻ ሳይሆን አንተ ባልሆነው ማነነትህ ብስጭትህና ፀፀት ይጨመሩበታል። ወይ ሌላ የምትተነፍስበት ሱስ ትፈልጋለህ ወይም ወደምትሸሸው ጨለማህ ትመለሳለህ!!» አለኝ ዶክተር የሆነ ቀን በሀኪም ለዛ ሳይሆን በአባት ቁጣ!!
በትክክል ሂደቱን ጠብቆ የተከሰተው ያ ነው። ደጋገምኩት! በደጋገምኩት ቁጥር እርካታን ሳይሆን የባሰ ጭንቀትን እያስታቀፈኝ መጣ!! እዚህጋ እሷንም ዘነጋኋት ራሴንም እንደዛው። ከወራት በኋላ ዶክተርጋ ሄጄ
«አሁን ዝግጁ ነኝ የሆንኩትን ሆኜ መዳን እፈልጋለሁ።» አልኩት። ደስ ብሎት ትከሻዬን እየመታ ተቀመጠ። ማውራት የጀመርኩኝ ቀን አስመለሰኝ ሁላ! የእናቴን አልፌ የመጀመሪያ የማዕረግ ክህደቷን አልፌ ሶስተኛው ጋር ስደርስ ተሰምቶኝ የነበረውን ዲቴል ማውራት ያቅተኛል። በየቀኑ ከመጀመሪያው እጀምራለሁ። በየቀኑ ትንሽ እየገፋሁ አቆማለሁ። በዚህ መሃል ለስራ ከከተማ ወጥቼ ስመለስ ነው መኪናዬ የተገለበጠው። እያሰብኩ እንደነበር አስታውሳለሁ ምን እንደሆነ ግን አላውቅም! ከፊቴ የሚመጣ መኪና ጡሩንባውን ሲያስጮኸው ነው እንደመባነን አድርጎኝ መሪዬን ያጠመዘዝኩት።»
«ለእኔኮ ግን እስከመጨረሻው ነገርከኝ አይደል? ያ ማለት?» አልኩት ካለፈው ስቃዩ የመዳን ምክንያት ሆኖት ከሆነ በሚል
«እናያለና!» አለኝ
«እሺ ቆይ በቃ? ከዛ በኋላ ያለውስ?» አልኩት ኮንፒውተሩን እያስቀመጥኩት።
«ከዛ በኋላ ያለውን አንቺ የማታውቂው የለም ራስሽ ትፅፊዋለሽ!» አለኝ በእርግጠኝነት
«እህ! ያንተን ስሜት ግን በትክክል ላሰፍረው አልችልም!»
«come on! ካንቺ በላይ የሚያውቀኝ ሰው የለም። በስሜት ደረጃ ከማንም ጋር መቆራኘት የማልፈልግ ሰው ዊልቸር ላይ ተቀምጬ በአካልም የሰው እርዳታ የምፈልግ ጥገኛ መሆኔ ምን እንዲሰማኝ እንደሚያደርገኝ ካንቺ በላይ የሚረዳ ሰው አለ? »
«የሰውን ድጋፍ ማግኘትኮ ሁሉም ሰው በሆነኛው የህይወቱ ጊዜ የሚገጥመው ነው! አንተ ሰዎችን ትረዳ የለ? ሰዎች ሲረዱህ ውድቀት የሚሆንብህ ለምንድነው?»
«በቃ እኔ ነኛ! (ትከሻውን ምን ላድርግ አይነት እየሰበቀ) በሰው ድጋፍ የምንቀሳቀስ ሰው መሆን ሞቴ ነው! ያን ታውቂያለሽ!! ለዘመናት የለፋሁትኮ በስሜትም በአካልም በገንዘብም ማንንም ያልተደገፍኩ ነፃ ለመሆን ነው» አለኝ የእርሱ ባልሆነ ማባበል ድምፅ! አላውቅም ምን እንዳሰብኩ ማጅራቴ ላይ ያለ እጁን ስቤ ሳምኩት። ሲጠብቀው የነበረ እርምጃ ይመስል አስከትሎ ከንፈሬን ሳመኝ። እየሳመኝ ያወራ ጀመር እንደበፊቱ ወሬው ግን የቀን ውሎአችንን አይነት አይደለም። ጆሮዬን ማመን እስኪያቅተኝ አዲስ በፍቅር ቁልምጫ ስም እየጠራኝ ነው። ደንግጬ ለሰከንድ በርግጌያለሁ ሁላ! ረዥም ሰዓት ከተሳሳምን በኋላ አቁሞ እንደመሳቅ ነገር እያለ
«ንግስቴ እንደምታደርጊኝ ካላደረግሽኝኮ እግሬን አላዘውም!» አለኝ አባባሉ ውስጥ <አየሽ ለዚህ እንኳን ያንቺን እርዳታ መጠየቅ ግድ ሲለኝ?> አይነት የመሰበር ድምፀት አለው። ሶፋው ስላልተመቸን ምንጣፉ ላይ ወርደን ማላብ ጀመርን! ከላይ ሆኜ እያየሁት እሱ በሚጠራኝ የፍቅር ቁልምጫ ሁሉ ልጠራው እፈልጋለሁኮ! ግን ከአፌ አይወጣም! አንዴ ቢለኝ ብዬ አምላኬን የለመንኩትን ቃል አለኝ። «ልትገምቺው ከምትችዪው በላይ እወድሻለሁ!» አለኝ። ስሰማው እፈነጥዛለሁ ብዬ ያሰብኩትን ያህል አላስፈነጠዘኝም! ንግስቴ ፣ ፍቅሬ ፣ ልዕልቴ ……….. ያላለኝ የለውም። ለዓመታት ያላለውን ማካካስ የሚመስል ፍቅር ……. ስንጨርስ አጠገብ ላጠገብ ተኝተን ዝም ተባባልን። ከሴክስ ስሜት ውጪ ያ የተስገበገብኩለት ፍቅር ስጨብጠው ምንም አልመስልሽ አለኝ ብዬ እውነቱን ነው የምነግረው ወይስ እንደዚሁ እንቀጥላለን ? በተጎዳው ላይ ጉዳት መጨመር መሰለኝ! ምናልባት ሽባ ስለሆንኩ ነው የጠላችኝ ይለኛል እያልኩ ሳስብ
«ይሰማኛል ብለሽ ያሰብሽውን ስሜት ውስጥሽ አጣሽው?» አለኝ
«ለምን እንደእሱ አልክ?»
«አውቅሻለሁ እኮ! በደንብ።»
«ታዲያ ካወቅክ?» ብዬ እንዴት መጠየቅ እንዳለብኝ ግራ ሲገባኝ
«ፍቅርሽን ከጨረሽ እንደቆየሽ አውቃለሁ። ከዛ ሁሉ በደል በኋላ ያ ስሜት ሊኖር አይችልም!»
«የበደልከኝንኮ ግን ትቼልሃለሁ!»
«አውቃለሁ! ይቅር ስትዪኝ ላለፍኩት መንገድ አዘንሽልኝ። ፍቅርን እና ሀዘኔታን ነው ያልለየሽው!»
«እሺ ካወቅክ ለምን?»
«ምንም እንዳልቀረብሽ እንድታውቂ!! ከተመኘሽው ምንም እንዳይጎድልብሽ!» አለኝ።
መኝታ ቤታችን ገብተን አቅፌው ተኛሁ። ነጋችንን እንዴት እንደምንኖረው እያሰብኩ እንቅልፍ ወሰደኝ። አይኖቼን ስገልጥ አንዳች ሸክም ከላዬ እንደተነሳ ቅልል ብሎኝ ነበር። አይኖቹን እንደጨፈነ ነው። ተገላብጬ ደረቱ ላይ ተጠግቼ ተኛሁ።
«አዲስዬ ! አዲስዬ!» ልቀሰቅሰው ሞከርኩ «ዛሬ እኔ ስራ ቦታ ደርሼ ልምጣ?» አይመልስልኝም። ቀና ብዬ አየሁት! «አታደርገውም አዲስዬ!!» ራስጌውጋ ያለውን መጠቀም ያቆመውን ያኔ ከባድ ህመም ሲሰማው ይወስድ የነበረውን ከባድ ፔንኪለር እቃ አየሁት!! «አታደርገውም! አዲስ አታደርገውም!» እቃው ባዶ ነው! ተነስቼ ይሰማኝ ይመስል ደረቱን እየደበደብኩ ማልቀስ ጀመርኩ።
መጠርጠር አልነበረብኝም ሲሸነፍልኝ? ያቺን ከዲያቢሎስ ጋር ሲማከር የሚያመጣትን ፈገግታ ፈገግ ካለ በኋላ ድንገት ቅይር ስል መጠርጠር አልነበረብኝም? አውቀው አልነበር ክፉ ሲያስብ? ከምንም ተነስቶ እንደዛ ቅይር እንደማይል እንዴት ጠፋኝ? ይሄን አስቦት ነው ማታ የሆነውን ሁሉ የሆነው! መጠርጠር አልነበረብኝም ፍቅሩን ሲያምንልኝ? መጠርጠር አልነበረብኝም በደሉን ሲያምንልኝ?? እስከሞት ራሴን የምወደው ራሴን ነው ሲለኝ መጠርጠር አልነበረብኝም? ሁሌም አፍቃሪ ሰውነቱ በተገለጠ ማግስት መዘዝ ተከትሎት እንደሚመጣ እንዴት ዘነጋሁት? ከመሸነፍ ሞትን እንደሚመርጥ አውቀው አልነበር? ድምፅ የወጣው ለቅሶ ማልቀስ አቃተኝ። እንባዬ ጉንጬ ላይ እየተንዠቀዠቀ አገላብጬ ሳምኩት። እያለቀስኩ ወደሳሎን ሄጄ ፀሃይን ጎረቤታችንን እንድትጠራ ስነግራት
«ምነው እናቴ? ምን ሆንሽ?» ስትለኝ
«አዲስ አዲስ » ብዬ መጨረስ አቃተኝ።

«በጠዋት ስትነሳ ስጫት ብሎ ይሄን ወረቀት ሰጥቶኝ ነበር ትናንት! ምነው አመመው እንዴ?» አለችኝ ወረቀቱን እያቀበለችኝ።
«እባክሽ ይሄ ከንቱ ሞተ ብለሽ እንባሽን አታባክኚ! ሞት መጥፎ ነገር ነው ያለ ማን ነው? ማን ያውቃል ከህይወት የተሻለስ ቢሆን! በህይወቴ አንድ ቁምነገር ሰርቼ ባልፍ ትይኝ አልነበር? መፃፋችንን ጨርሺው። ልጆቼን አደራ! ስወድሽ ኖሬያለሁ!!»
የሆነ ጊዜ ላይ ስለሞት ያወራኝን አስታወስኩት። ከ80 ዓመት በላይ መኖር አልፈልግም ይለኝ ነበር ሁሌ። ምክንያቱም መዝረክረክ ስለማይፈልግ!
«ሞትን እንደመጥፎ ነገር የምናየውኮ ማንም ከሞት በኋላ ያለውን ህይወት ስለማያውቅ ነው! ሰው ሲሞት በህይወት ያለው ሰው የሚቀርበውን ስለሚያጣ ሞትን ክፉ ነገር አድርጎ ያወራዋል። ለምሳሌ አስቢው በህመም ሲሰቃይ ለነበረ ሰው ሲሞት ማልቀስ ልክ ነው? ሰውየውኮ ስቃይ ላይ ነበር? የምናለቅሰው ሰውየው ስለተገላገለ ነው? ለራሳችን ነው ለሰውየው ነው የምናለቅሰው? ደግሞስ ከሞት በኋላ ያለው ምናልባት ከህይወት የተሻለ ሁላ ቢሆንስ?» ብሎኝ ነበር። ጭራሽ ድምፅ አውጥቼ እያለቀስኩ።
«እሺ ይሁንልህ! የተሻለ ይሁንልህ!» ብዬ በቂጤ መሬቱ ላይ ተዘረፈጥኩ!!


ጨርሰናል!!!

@wegoch
@wegoch
@paappii
2024/09/22 20:39:25
Back to Top
HTML Embed Code: