Telegram Web Link
የማኀበረ ቅዱሳን ዋና ማእከል ምዕራፍ ሁለት የሕንጻ ግንባታ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተከናወነ

ማኅበረ ቅዱሳን ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን በኹለንተናዊ አቅሟ እንድትጠናከር ለማድረግ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። አገልግሎቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ የመጣው ማኅበሩ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ማስፈጸም የሚችሉ ማእከላት በማቋቋም ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ላይ ይገኛል።

ማኅበሩ ዘመኑ የሚጠይቀውን የአገልግሎት መንገድ በመከተል በዘመናዊ አሠራር ቤተ ክርስቲያንን ማገዝ የሚችሉ በርካታ አሠራሮችን ወደ ተግባር እያስገባ ሲሆን ለዚህ ተግባር የሚያግዙ የሰው ኃይል እና የግብዓት ማሟላት ላይ በትኩረት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ አሁን ግባታውን ለመጀመር በዝግጅት ላይ የሚገኘው የምዕራፍ ሁለት የማኅበሩ ሕንጻ ማስፋፊያ ነው።

ማኅበሩ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ የተነገረለት አዲሱ የማኅበሩ ሕንጻ የመሬት ወለልን ጨምሮ 14 ወለሎች እንደሚኖረው የተነገረለት ሲሆን ኅዳር 15 ቀን 2016 ዓ.ም ግንባታውን ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተከናውኗል።
የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ለማስፈጸም ከፈተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ 25 ተተኪ መምህራን ተመረቁ።

በማኅበረ ቅዱሳን እና ደብረ ከዋክብት አቡነ አረጋዊ ወገብረ ክርስቶስ ቤተ ከርስቲያን ፈለገ ሰላም ሰ/ት/ቤት ትብብር ከቤንች ሸኮ፣ ሸካ እና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች ሀገረ ስብከት የመጡ 25 ሠልጣኞች በዛሬው ዕለት ተመርቀዋል።

ለ15 ተከታታይ ቀናት የተለያዩ ሥልጠናዎችን ሲወስዱ የቆዩት መምህራኑ በዛሬው ዕለት የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ አርያም መንግሥቱ ዘለዓለም እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተመርቀዋል።

በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት መልአከ አርያም መንግሥቱ ዘለዓለም  በጠረፋማ አካባቢ ያሉ ምእመናንን ለማስተማር እና ያላመኑትን በማሳመን ለማስጠመቅ የሚደረገውን ጥረት ሁሉም የቤተክርስቲያን ባለድርሻ አካላት  በባለቤትነት ሊያግዙ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ዛሬ የተመረቁት ሠልጣኞች የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት እና ቀኖና ተረድተው እንዲያገለግሉ ለማድረግ የሚችሉ ትምህርቶችን መስጠት መቻሉን ገልጸው የደብሩ አስተዳደር ከሰንበት ትምህርት ቤቱ እና ከምእመናን ጋር በመሆን በቀጣይ 72 ሠልጣኞችን ከተለያዩ አካባቢዎች ተቀብለው ለማሠልጠን ቃል ገብተዋል።

የማኅበረ ቅዱሳን የሕዝብ ግንኙነት እና ትብብር አገልግሎት ማስተባበሪያ ምክትል ኃላፊ መጋቤ ብርሃናት ቀሲስ ሙሉቀን ብርሃኑ እንደገለጹት ማኅበረ ቅዱሳን 2014 እና 2015 ዓ.ም ሐዋርያዊ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በሠራው ሥራ 86,582 ኢ አማንያንን በማስጠመቅ የቤተ ክርስቲያን ልጅነት እንዲያገኙ አድርጓል ብለዋል።

ም/ኃላፊው እንደገለጹት ዛሬ የተመረቁት ሠልጣኞች በቤንችኛ፣ ካፊ ኖኖ እና ሸኮኛ ቋንቋዎች ሐዋርያዊ አገልግሎት እንደሚሠጡ ተናግረዋል።
በመጨረሻም ማኅበረ ቅዱሳን የደብረ ከዋክብት አቡነ አረጋዊወ ገብረ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ጽ/ቤት እና የፈለገ ሰላም ሰ/ት/ቤት የሠልጣኞቹን ምግብ ትራንስፖርት እና አስፈላጊ ወጪዎችን በመሸፈን ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋናውን ያቀርባል ብለዋል።

በዚህ ሥልጠና ላይ የተካፈሉት ከደቡብ ቤንች ወረዳ10 ተሳታፊዎች ፣ ከሰሜን ቤንች ወረዳ 5 ተሳታፊዎች፣ ከጊዲ ቤንች ወረዳ 7 ተሳታፊዎች፣ ከሼይ (ሸዋ) ቤንች ወረዳ 3 ተሳታፊዎች መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በ2016 ዓ.ም ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚገቡ እንዲሁም በማሻሻያ መርሐ ግብር ለተካተቱ ተማሪዎች የሽኝት እና የአደራ መርሐ ግብር ተከናወነ።

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/በሰ/ማ/መ የአገር አቀፍ ሰ/ት/ቤቶች አንድነት እና ማኅበረ ቅዱሳን በጋራ በመሆን በ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስደው ወደ ክፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ነጥብ ላመጡ እና በማሻሻያ መርሐ ግብር ለተካተቱ ተማሪዎች የሽኝት እና የአደራ መርሐ ግብር አዘጋጅተዋል።

ኅዳር 16 ቀን 2016 ዓ.ም በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ አዳርሽ ውስጥ በተከናወነው መርሐ ግብር ላይ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንዲሁም በርካታ ተማሪዎች በተሳታፊነት ታድመዋል።

በዕለቱ ንግግር ያደረጉት የአገር አቀፍ ሰ/ት/ቤቶች አንድነት ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት ዲ/ን ስንታየሁ ምስጋናው እንደተናገሩት ተማሪዎች ከዓለማዊ ትምህርታቸው ጎን ለጎን መንፈሳዊ ዕውቀትን እና ሕይወት መማር እናደለባቸው አሳስበው በሚሄዱበት ሁሉ መልካም ነገር እንዲገጥማቸው መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ የሆኑት ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም መልእክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚሄዱበት ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን እና ሃይማኖታቸውን ማወቅ እንዲችሉ ማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤ አገልግሎትን አዘጋጅቶ እንደሚጠብቃቸው በመግለጽ በትምህርታቸው እንዲበረቱ አደራ ብለዋል።

ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት  ሊቀ ጳጳስ እና የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት በመርሐ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት ተማሪዎች እምነትን እውነትን እና ዕውቀትን መያዝ እንደሚገባቸው አባታዊ ምክራቸውን የገለጹ ሲሆን ከፍተኛ ውጤት ላመጡ  የተፈጥሮ ሳይንስ እና የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች የላፕቶፕ ስጦታ እንዲሁም ለልዩ ተሸላሚዎች የማበረታቻ ስጦታን አበርክተዋል። በተጨማሪም ለሁሉም ተማሪዎች የውዳሴ ማርያም ስጦታ ሰጥተዋል።
2024/09/30 20:20:27
Back to Top
HTML Embed Code: