Telegram Web Link
የጳጉሜን አስጎብኚ እና የጉዞ  ወኪል አ.ማ ዋን ራይድ በሚል የሜትር ታክሲ አገልግሎት መጀመሩን ገለጸ።


በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ የሚገኘው የጳጉሜን አስጎብኚ እና የጉዞ  ወኪል አ.ማ  በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ የሚደረገውን ርብርብ የሚያግዘውን የሜትረ ታከሲ አገልግሎት  ዋን ራይድ  በሜል መጠሪያ  ወደ  ሥራ መግባቱን   በማብሰር   ጋዜጣዊ   መግለጫ  ሰጥቷል።

ዋን  ራይድ  በሌሎች መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ያልተሞከሩ አዳዲስ አገልግሎቶችን ይዞ መምጣቱን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተጠቆመ ሲሆን አሽከርካሪዎችም ሆነ ተሳፋሪዎች የሚመርጡት የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ለመሆን በከፍተኛ ትኩረት እንደሚሠራ ተገልጿል።

በተለይ ከደኅንነት ስጋት ነጻ የሚያደርጉ አሠራሮችን ይዞ የመጣው ዋን ራይድ ከኅዳር 10 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎቱን መስጠት እንደሚጀምር ተጠቁሟል።

ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጣትን በልዩ ትኩረት እንደሚያየው የተነገረለት ዋን ራይድ ሥራ መጀመሩን ምክንያት በማድረግ የወደቁትን አንሱ አረጋውያን መርጃ ማእከል እና ተስፋ አዲስ የሕጻናት ካንሰር ማእከልን አገልግሎት ለማገዝ የሚረዳ የአንድ ሳምንት የምሳ ወጪ እንደሚሸፍን ተነግሯል።በተጨማሪም ከዓመታዊ ገቢው 1 % ለበጎ አድራጎት ተግባር እንደሚያውልም ተገልጿል።

በመጨረሽማ አርቲስት መሠረት መብራቴን ብራንድ አምባሳደር አድርጎ በመምረጥ የፊርማ ሥነ ሥርዓት ያከናወነ ሲሆን ከማኅበረ ቅዱሳን እና ከአሐዱ ባንክ ጋር በጋራ መሥራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል።
በተመሳሳይም ዋን ራይድ  ከማኅበረ ቅዱሳን እና ከአሐዱ ባንክ ጋር በጋራ መሥራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል።

የጳጉሜን አስጎብኚና የጎዞ ወኪል አ.ማ በቱሪዝሙ ዘርፍ ከፍተኛ ድርሻ እየተወጣ የሚገኝ ሲሆን በኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባለ ሀብቶች በቱሪዝምን እና ተያያዥ ዘርፎች አግልግሎት ለመስጠት በ2009 ዓ.ም በ80 ሚሊዮን ብር ካፒታል እና በ1388 ባለአክሲዮኖች ተቋቁሞ አግልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ድርጅት ነው።
https://youtu.be/P0ONtiUqeMw?si=whf4LOY_wiWNLRDa

አንቅዕተ ማኅሌት

አንቅዕተ ማኅሌት አንቅዕተ ውዳሴ
ምግባቸው ምስጋና ልብሳቸው ቅዳሴ
ዘወትር ይቀኛሉ ለቅድስት ሥላሴ /፪/

ዐይኖቻቸው ብዙ ክንፎቻቸው ስድስት የሥላሴን መንበር የሚሸከሙት
ሱራፌል ኪሩቤል መገብተ ስብሐት /፪/
          አዝ.....
ሰአሉ ለነ አርባዕቱ እንስሳ ገጸ ሰብእ ወገጸ አንበሳ
ገጸ ላሕም ወገጸ ንስር /፪/
          አዝ.....
ዘወትር አይለዩም ከመንበሩ ዙሪያ ያመሰግናሉ ብለው ሃሌ ሉያ
ይሏታል ድንግልን እኅትነ ነያ /፪/
          አዝ.....
ኪሩቤል ሱራፌል ምሉዓነ ግርማ ምስጋናቸው ሲፈስ ድምፃቸው ሲሰማ
ልብን ይመስጣል የምስጋናው ዜማ /፪/
          አዝ.....
ሰአሉ ለነ አርባዕቱ እንስሳ ገጸ ሰብእ ወገጸ አንበሳ
ገጸ ላሕም ወገጸ ንስር /፪/
የእግዚአብሔር ሠረገላዎች
(መጽሐፈ ስንክሳር)

ለቅድስት ሥላሴ ምስጋና ይድረስና እኛ የሰው ልጆች በተለይም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ እንዲረዱን ቅዱሳን መላእክትን ፈጥረውልናል፡፡ (ዕብ.፩፥፲፬) በዚህ ዓለም ስንኖር ተስፋ ከሚሆነን፣ ፍርሃትን እንድናስወግድ ከሚረዳን የአምላክ ስጦታ መካከል የነገረ መላእክት ነገር ነው፡፡

ቅዱሳን መላእክት አይደለም እኛን በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል የተፈጠርን የሰው ልጆችን ቀርቶ ፀሐይን፣ ከዋክብትን፣ አዝርእትን፣ አትክልትን፣ እንስሳትን፣ አራዊትን፣ ከሰማይ በታች ከምድር በላይ የተፈጠረውን ሁሉ የሚጠብቁ ናቸው፡፡ መቼም የሚጠብቀን አምላክ እንደማይተኛና በሥራችን ሁሉ፣ በዚህ ዓለም ያለ የነፍስም የሥጋም እንቅፋት እንዳይመታን ይጠብቁን ዘንድ ምድራውያን ያይደሉ ሰማያውያን ጠባቂዎች አገልጋዮቹን ቅዱሳን መላእክትን እንደሚያዝልን ከማወቅ በላይ ምን የሚያስደስትና ፍርሃትን የሚያስወግድ ነገር ይኖራል፡፡ (መዝ.፺፥፲፩)

እግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክትን በዕለተ እሑድ ሲፈጥር በነገድ ፻ (አንድ መቶ) በአለቃ ፲ (ዐሥር) አድርጎ በሦስቱ ሰማያት አስፍሯቸዋል፡፡ ሦስቱ ሰማያት የሚባሉትም ኢዮር፣ ራማ እና ኤረር ናቸው፡፡ ኢዮር ዐራት፣ ራማ ሦስት፣ ኤረርም እንዲሁ ሦስት ከተሞች አሏቸው፡፡ በአጠቃላይ የመላእክት ከተሞች ዐሥር ናቸው፡፡ ከእነዚህ ቅዱሳን መላእክት መካከል ኪሩቤል ይገኙበታል፤ አለቃቸው ኪሩብ ሲባል ሰማያቸው ኢዮር ከተማቸው ሁለተኛው ነው፡፡
‹‹ኪሩቤል›› የሚለው ስም  የነገደ መላእክቱ ሁሉ (የብዙ ቁጥራቸው መጠሪያ) እንጂ፣ የአንዱ መልአክ መጠሪያ ‹‹ኪሩብ›› ነው፡፡ ኪሩብ ማለት መልአክ፣ የመልአክ ስም፣ ሥዕሉ ምስሉ ነገዱ 4ት 4ት ገጽ ካላቸው ከአራቱ ጸወርተ መንበር አንዱ ሲሆን፣ ፍችው መሸከምን፣ መያዝን ይገልጣል፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ገጽ ፭፻፵፬)

ነገደ ኪሩቤል የካህናት የቀሳውስት አምሳል ናቸው፡፡ ሁለተንተናቸው በዓይን የተመላ ነው፡፡  ነቢዩ ቅዱስ ሕዝቅኤል እንደነገረን ለእያንዳንዳቸው አራት አራት ፊት አላቸው፡፡  (ሕዝ. ፩፥፮) ከቀኝ ወደ ግራ፣ ከፊት ወደ ኋላ ሳይንቀሳቀሱ አራቱን አቅጣጫ መመልከት ይችላሉ፡፡ ሲሔዱም እንዲሁ እግዚአብሔር ወደ አዘዛቸው ቀጥ ብለው፣ እንደ ሰው አቅጣጫ መቀየር ሳያስፈልጋቸው መንጎድ ይችላሉ፡፡
ኪሩቤል መንበሩን የሚሸከሙ የእግዚአብሔር ሠረጋዎቹ ናቸው፤ (ወእሉ እሙንቱ ሠረገላሁ ለእግዚአብሔር) እንዲል፡፡ ነቢዩ ቅዱስ ሕዝቅኤል እንደተመለከታቸው ዙፋኑን ተሸክመው እግዚአብሔር ለወደደው ይገለጻሉ፡፡  እነርሱንም፡- ‹‹ኪሩባውያን አፍራሱ፤ ፈረሶቹ ናቸው›› ሲል መጽሐፍ ይገልጻቸዋል፡፡ ዙፋኑን ተሸከሙ ሲባልም እግዚአብሔርን የመሸከም ኃይል ኑሯቸው ከወዲያ ወዲህ ይዘው መራመድ ማለት አይደለም፡፡ እግዚአብሔር መገለጽ ሲፈቅድ ዙፋኑን እንደፈቀደ (በወደደው) ተሸክመው ስለሚታዩ ነው፡፡

መሐሪና ይቅርባይ የሆነ አምላካችን እግዚአብሔር ኪሩቤልን ስለ ሁሉ የሰው ፍጥረት ይለምኑት ዘንድ የቅርብ ባለሟሎቹ አድርጎ ሾሟቸዋል፡፡ ለእኛ ለሰው ልጆችም ሆኑ ለመላው ፍጥረት በእግዚአብሔር ዘንድ የሚለምኑልንን ኪሩቤልን በዓለሙ ሁሉ በስማቸው አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነጹላቸው እና በኅዳር ስምንት ቀንም መታሰቢያቸውን እንድናደርግ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አዘውናል፡፡

የቅዱስ እግዚአብሔርን መንበር የሚሸከሙ ኪሩቤል በተለይም እኛ ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ ከመለያየት ይልቅ ሰውን ሁሉ በፍቅርና በትዕግሥት የምንሸከምበትን ኃይሉን ያድሉን ዘንድ፣ ከአምላካችንም ያስታርቁን ዘንድ በረከታቸው ከእኛ ጋር ትኑር፤ ለዘላለሙ አሜን!
 
ምንጭ፡- መጽሐፍ ቅዱስ፣ መጽሐፈ ስንክሳር፣ የአንቀጸ ብርሃን አንድምታ ትርጓሜ /መ/ር ኃይለ ማርያም ዘውዱ / ፣ ምሥጢረ ሰማይ / መ/ር ማዕበል ፈጠነ/
“ሰላምየ አኀድግ ለክሙ ወሰላመ አቡየ እሁበክሙ፡- ሰላሜን እተውላችኋለሁ፥ የአባቴ ሰላምም እሰጣችኋለሁ” (ዮሐ.14፡27)

የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ

ሀገራዊ ሰላምን፣ መረጋጋትንና አንድነት ማስፈንን አስመልክቶ በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ በተላለፈው ውሳኔ መሠረት ከቋሚ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ፤

ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነትና ደኅንነት የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ቀዳሚ ተልእኮዎች ናቸው፡፡ በሃገራችን ሰላምን ለማስፈን ቅድስት እናት ቤተ ክርስቲያን ከቀድሞ ጀምሮ ብዙ ጥረት ስታደርግ ኑራለች፡፡ አሁንም ሊኖራት የሚገባውን ተግባራዊ ሚና መወጣት ይኖርባታል፡፡

በተለይም ሰላም በመንፈሳዊ፣ በማኅበራዊ፣ በግለሰብ፣ በተቋም፣ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ክበብ ውስጥ ያለውን የተሣሠረ ሁለንተናዊ ትርጉም ከግምት ውስጥ ያስገባ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡

ለሰላም መደፍረስና መታጣት ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን በማንሳትና ያስከተሉትን የሰው ልጅ እልቂት፣ ሞትና ስደት፣ የአብያተ ክርስቲያናትና የመንፈሳዊ ቅርሶች ውድመት፣ የካህናትና የሊቃውንት ስደትና መከራ፣ የቋሚና የተንቀሳቃሽ ንብረቶች ውድመት፣ የቤተ ክርስቲያን አንድነት መናጋት፣ በዜጎች መካከል ጥላቻ መስፋት፣ መተማመን መጥፋት፣ የኑሮ ዋስትና ማጣት፣ በስጋት መኖር፣ የማያባራ መከፋፈል፣ የሰብአዊ ክብር ማጣት፣ የመብት ጥሰት፣ የኑሮ ውድነትና የሕዝቦች መፈናቀል በአደባባይ እየታዩ ያሉ ሰብኣዊ ሰቆቃዎች ናቸው፡፡
“ብፁዓን ገባርያነ ሰላም እስመ እሙንቱ ውሉደ እግዚአብሔር ይሰመዩ፡- የሚያስታርቁ ብፁዓን ናቸው፣ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና” (ማቴ.5፡9) በማለት ጌታችን ያስተማረው ትምህርት የቤተ ክርስቲያን መመርያ ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያን የሰላምና የአስታራቂነት ድርሻ፣ የሃገር አንድነትና የሕዝብን ሰላም ለመጠበቅ በታሪኳ ያደረገችው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም፡፡

የቤተ ክርስቲያን ታላቅነት፣ የአበውን ተቀባይነትና የሊቃውንቷን ሰላምን የማስፈን ክሂሎት፣ ችግርን የመፍታት ጥበብ አሁንም ተጠናክሮ መተግበር ይኖርበታል፡፡

የሰላምን ወሳኝ ሚና ከግምት ውስጥ በማስገባትና ተገቢውን ትኩረት በመስጠት የሰላምና የዕርቅ ሰነድ በማዘጋጀት የመሪነት ተሳትፎ እንድትፈጽም ገለልተኛና ሰውን ማእከል በማድረግ ታገለግላለች፡፡

ካህናትና መላው አገልጋዮች የሰላም ልዑካን እንዲሆኑ፤ ሰላምን ግንባር ቀደም ሐዋርያዊ ተልእኮዋ አድርጋ ትንቀሳቀሳለች፡፡

በሃገራዊ የሰላምና የዕርቅ ጥረቶች አዎንታዊ ተጽዕኖ ለመፍጠር የሚያስችል ይፋዊ ውክልና እንዲኖራት፣ በሥነ ምግባርና በግብረ ገብነት ትምህርት የራስዋን ኃላፊነት እንድትወጣ፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሃገራዊም ሆነ በራስዋ መዋቅር በሰላም ዙርያ አስተዋጽኦዋን ለማሳደግና የሚጠበቅባትን ለመወጣት ትችል ዘንድ የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በሚገባ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

ለቤተ ክርስቲያን መመርያዋ ጽድቅን፣ እምነትን፣ ፍቅርን አጥብቀህ ተከተል ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ያዘዘው መመሪያ ነው፡፡ (፪ኛ ጢሞ. ፪፡ ፳፪)

ሰላምን ሳታዳላ በሩቅም በቅርብም ላሉት ትሰብካለች፡፡
• “ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ” እንዲል (ኤፌ.፪፡፲፯)፡፡
ለቤተ ክርስቲያን ሰላም መሣርያዋ፣ ሕይወቷ፣ ጸሎቷ፣ ቀኖናዋና ዶግማዋ ነው፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ሰላም ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህ “ሰላም ከሌላችሁ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር የለም” በማለት የሰው ልጅ ሰላማዊ እንዲሆን ታስተምራለች፡፡
ጥላቻን አጥብቃ ትቃወማለች፡፡ “ጥልን በመስቀሉ ገደለ” የሚለውን መልእክት እንደ ሰንደቅ የምትጠቀምበት መለያዋ ነው፡፡ ስለዚህ በሰዎች መካከል የተከሰተውን ጥላቻ በተሰጣት መንፈሳዊ ጥበብ ማስወገድ ተልእኮዋ ነው፡፡

በሰላም ግንባታ ኢትዮጵያውያንን ያለ ልዩነት በማሳተፍ ቤተ ክርስቲያን የሰላም ሚናዋን በጥበብና በማስተዋል በቋሚነት ትሠራለች፡፡

ሰላምን ያሳጡን ጦርነቶችና ግጭቶች ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙና በአጭሩ እንዲቋጩ ጥሪዋን ታስተላልፋለች፤ እምቢ ባዮችንም በማውገዝ ዘላቂ መፍትሔ የሚገኝባቸውን ሂደቶችን ትቅይሳለች፡፡

የሰላም ሰነዶችን በማዘጋጀት አስቸኳይ የሆነ ሃገራዊ የሰላም ንቅናቄ በፍጥነት እንዲጀመርና በዚህም ውስጥ ውጤት ሊያመጣ የሚችል ሥልት ተቀይሶ ወደ ሥራ እንዲገባ ማድረግ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡

ቤተ ክርስቲያን የራስዋ የሰላም ከፍተኛ ልዑክ ኖሯት በመዋቅሯ ሁሉ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ የሰላም ሥምሪት ለማድረግ የሚያስችል ንቅናቄ ታደርጋለች፡፡

በሃገራዊ የሰላም ጥረቶች፣ የውይይትና የምክክር መድረኮች ባለድርሻ እንድንሆን ከሚመለከተው ጋር ተቀራርቦ መሥራት የሚቻልበትን አሠራር ትዘረጋለች፡፡

በማኅበራዊ ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የቤተ ክርስቲያን የሰላም ጥሪ ተቀባይነት እንዲኖረው በትጋት ትሠራለች፡፡

በሰብአዊ ድጋፍና በእርዳታ ማስተባበር ለወገኖቻችን መድረስ እንዲቻል ልጆቿን አስተባብራ ትንቀሳቀሳለች፡፡

በመግቢያችን እንደተጠቀሰው “ፈኑ እዴከ አንሥእ ኃይለከ” ብለው የለመኑ ነቢያትን የሰማ እግዚአብሔር አምላካችን ጸሎታችንን እንደሚሰማን ከልባችን በማመን በእርሱ ያለንን ትምክህታችን ይህ በመሆኑ ከጽኑ ተስፋና ፍቅር ጋር እንድንፈጽመው አደራ እንላለን፡፡

በተጨማሪ ይህንን መንፈሳዊ ሥርዓትና መደበኛ የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ሁሉም በቅንነት እንዲረዳው በጥብቅ እናሳስባለን፡፡

ዓለማውያን ምሁራን ሃገሮቻቸውን ለመጠበቅ፣ የሕዝባቸውን አንድነት ለማስቀጠል፣ የተረጋጋና እርስ በርሱ የሚተማመን ማኅበረሰብን ለማጽናት በሕግ የሚያስቀጡ “የጥላቻ ንግግርን” የሚያስቀር አዋጅ ያወጣሉ፡፡ ሃገራችንም የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃን የሚከለክል አዋጅ አላት፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ጥላቻንና ሐሰተኛ ትርክቶችን ታወግዛለች፡፡

የአሁኑ ጸሎተ ምኅላ የሚደረገው አለመግባባት በምክክር፣ በውይይት፣ በመደማመጥ እንዲፈታ፤ መከራን በመረዳዳት እንድንሻገር፣ እንደየ ኃላፊነታችን የሚጠበቅብንን ለመወጣትና የሕዝባችንን ጥያቄ ለመመለስ እንድንችል፣ ችግራችን ሁሉ ተፈትቶ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ከሃሊው አምላክ እንዲያግዘን በአንድነት ለመጮኽ ነው፡፡

ስለዚህ ይህ ዓላማው መንፈሳዊ ብቻ የሆነ የጾም፣ የጸሎትና የምኅላ አዋጅ መሆኑን ተረድታችሁ የሚድያ፣ የትምህርትና የፍትሕ፣ መሰል ተቋማት በሚያስፈልገው ሁሉ እንድትተባበሩን በዚሁ አጋጣሚ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም አባታዊ ማሳሰቢያን እናቀርባለን፡፡

በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያን በታሪክም ሆነ በትውልድ የሚያኮራ ውጤታማ ሥራን እንድትሠራና ከቃል ወደ ተግባር እንድትሸጋገር ለማድረግ ይህ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ ይቀድስ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!!!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ሕዳር 11 ቀን 2016 ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

አፈጻጸም ፦

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

ሀገራዊ ሰላምን፣ መረጋጋትንና አንድነትን ለማስፈን የታወጀውን የጾምና የጸሎተ ምኅላው አፈጻጸም በቅደሱ ሲኖዶስ በተወሰነው መሠረት ከዚህ በመቀጠል አቀርባለሁ፡፡

ቀደም ሲል ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት በመላው ዓለም ለሚገኙ ሕዝበ ክርስቲያን የታወጀውን አዋጅ አስተላልፈዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ያለፈውን በይቅርታና በምህረት ዘግተን በእውነተኛ ንሥሓ ልቅሶና በምህላ፣ በጾምና በጸሎት ወደ ፈጣሪ እንድንቀርብ፣ በመካከላችንም ፍቅርና አንድነት እንዲመጣ ይኽንን ጾመ ነቢያት ወይም የገና ጾም በልዩ ሁኔታ እንድንጾም መንፈሳዊ አዋጅ ተላልፏል፡፡

ይኽ ጥንታዊ የአዋጅ ጾም ሁለት አበይት ታሪኮችን የያዘ ነው፡፡ የመጀመሪያው ክፍል ቅዱስ አብርሃም ሶርያዊ የተባለ ጻድቅ አባት በጸሎት፣ በጾምና በምኅላ ተራራን ከመሬት ከፍ በማድረጉ ኃይለ ጸሎቱና ክብረ አምለኩ የሚዘከርበት ነው፡፡ በሁለተኛው ክፍል ነቢያት የጌታችንን ሰው መሆን እያፈለጉ፣ ድህነትንና ሰላምን በመሻት መጾማቸው ይዘከራል፡፡ (፩ኛ ጴጥ ፩፡፲) እኛም ይኽንን አብነት አድርገን ታላቋ ቤተ ክርስቲያን፣ ኃላፊነቷን እንድትወጣ ስለችግራችን፣ ስለሀገር ሰላምና ስለ ሕዝቡ ደኅንነት በአንድነት ሆነን ወደፈጣሪያች እንድንጮኽ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በጥቅምት ወር ፳፻፲ወ፮ ዓ/ም ወስኖ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

ሀገራችን እንድትፈወስ፣ የወገን በወገን ደም መፋሰስ እንዲቀር፣ ያለፈውን በይቅርታና በንሥሓ ዘግቶ ለወደፊቱ ብሩህ ዘመንን እንዲመጣ በንሥሓና በፍጹም ለቅሶ፣ በቁመትና በሰጊድ፣ በሰፊሕና በአንቅአድዎ፣ ወደፈጣሪ እንድንቀርብ የምልኣተ ጉባኤውን ውሳኔ መሠረት በማድረግ ቋሚ ሲኖዶስ በኅዳር ወር ፳፻፲ወ፮ዓ/ም የሚከተለውን ዝርዝር አፈጻጸም አውጥቷል፡፡
፩ኛ. የጾሙ የመጀመሪያ ሳምንት ከቅዳሜ ኅዳር ፲፭ እስከ ኅዳር ፳፩ ቀን ፳፻፲ወ፮ ዓ/ም በሁሉም የሀገራችን ክፍልና ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ባለችበት በመላው ዓለም የንሥሓ፣ የጾም፣ የጸሎትና የምኅላ ሳምንት እንዲሆን፤

፪ኛ. በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ በአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ በአጥቢያ አለቆችና በገዳም አበምኔቶች መሪነት ሁሉም ዲያቆናት፣ ቀሳውስት፣ መነኰሳት፣ ሰባክያንና ሊቃውንት በሙሉ በየመዐርጋቸው ልብሰ ተክህኖና ወጣት የሰንበት ትምህርት ቤት ዩኒፎርማቸው ለብሰው፣ ሁሉም ምእመናን ጋር በአንድነት በዐውደ ምህረት ጸሎተ ምኅላውን እንዲያደርሱ፤

፫ኛ. በላው ሕዝበ ክርስቲያን ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ እናቶች አባቶች አረጋውያን ሁሉ የቻለ በቤተ ክርስቲያን፣ ያልቻለ በያለበት ሆኖ የተጣላ ታርቆ፣ በፍቅርና በአንድነት፣ በእውነተኛ ንሥሓና ጸጸት በምኅላው እንዲሳተፍ፤ በማእከል የሚደረገው ጸሎተ ምኅላ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ መሪነት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በተገኙበት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ገዳም ሆኖ በመገናኛ ብዙኀን የቀጥታ ሥርጭት ለመላው ዓለም እንዲተላለፍ፤

፬ኛ. በመጀመሪያው የሱባኤ ቀን ኅዳር ፲፭ ቀንና፣ በሰባተኛው ቀን ኅዳር ፳፩ ቀን በጸሎተ ምኅላው በሚደረግበት ጊዜ ታቦቱ ከመንበሩ ተነሥቶ በዐውደ ምኅረት በቀሳውስት እንዲከብር ሆኖ፤ በሁሉም የምኅላው ቀናት ሥዕለ ማርያም፣ ወንጌልና መስቀል ወጥቶ በአራቱ መዐዝን ሥርዓተ ጸሎተ ምኅላው ከጸሎተ ወንጌል ጋር በየቀኑ በነግህና በሠርክ የሥራ ሰዓትን በማይነካ ሁኔታ እንዲፈጸም፤

፭ኛ. በየዕለቱ የሚነበቡት የወንጌል ክፍሎችን ስለ ሰላም፣ ስለንሥሓና ጸጸት፣ ስለ ፍቅርና አንድነት፣ ስለ በጎነትና መደማመጥ፣ ስለመሰማማትና ጥላቻን ስለማራቅ እንዲሆን፤

፮ኛ. በሰፊህና በአንቀዓድዎ፣ በሰጊድና በአስተብርኮ፣ ምኅላው ከደረሰና፣ ጸሎተ ወንጌል ደርሶ ዕለቱ ወንጌል ከተነበበ በኋላ በአንድነት የንሥሓ መዝሙር በመዘመር፣ ሕዝበ ክርስቲያን ስለሀገራቸውና ስለሰው ልጆ ደኅንነት እያሰቡ ወደቤታቸው እንዲሄዱ፤

፯ኛ. ከመጀመሪው ሳምንት በኋላ እስከ በዓለ ልደት ድረስ የሰርክ ምህላ ሳይቋረጥ መደበኛው ሥርዓተ ጾምና ጸሎት እንዲቀጥል፣ የቤተ ክርስቲያንን ታላቅነት፣ የአበውን ተቀባይነት በሚገለጽ፣ በቀጣይም ሁሉም ኦርቶዶክሳውያን በመንፈሳዊ ጽናት የሰላም ልዑካን ሆነው እንዲቀጥሉ በሚያደርግ ሁኔታ እንዲፈጸም፤

፰ኛ. አስቀድሞ የደረሰውንና፣ እየደረሰብን ያለው ችግር የጦርነትና የግጭት ብቻ ሳይሆን የረሀብ፣ የድርቅ፣ የኑሮ ውድነት፣ የመፈናቀልና የስደት ጭምር ስለሆነ ከጸሎትና ምኅላችን ጎን ለጎን መረዳዳትና መተዛዘን፣ ርኅራሄና መደጋገፍ አብሮ እንዲፈጸም፤

፱ኛ. ይኽንኑ መልእክት መላው ዓለም እንዲውቀው፣ በተለይም የኦሬንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በጸሎት እንዲያስቡን፣ የጸሎታችንና የምኅላችን መነሻ ምክንያቱ የሀገራችን ወቅታዊ ችግር ቢሆንም የምንጸልየው ለመላው ዓለም መሆኑ ተገልጾ በደብዳቤ እንዲላክ እንዲደረግ፣ በማለት ቅዱስ ሲኖዶስ ጥብቅ መመሪያ አስተላልፏል፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን በእንባና በንሥሓ የምናቀርበውን ጸሎተ ምኅላችንን በምህረቱ ተቀብሎ ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን፣ ሕዝባችንን ይጠብቅልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ቅዱስ ሲኖዶስ
‹‹እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ነኝ›› (ኢያ.፭፥፲፫)

በቅድስና፣ በውዳሴ፣ በኅብረ ቀለም በመላእክት ዝማሬ በደመቀው በዓለመ መላእክት ውስጥ ቅዱሳን መላእክት በነገድ ተከፍለው ይኖራሉ፡፡ እነርሱም የዘወትር ምግባራቸው እንዲያውም ምግባቸው ፈጣሪን ማመስገን ነው፡፡ ስፍራ ቁጥር የሌላቸው መላእክቱም በሦስቱ የመላእክት ከተሞች ኢዮር፣ ራማ እና ኤረር በአላቃቸው ስር ሆነው ዘወትር አምላክን ያገለግላሉ፡፡ ለዚህም ድንቅ ሥራው ክብረ ምስጋና ይድረሰውና፣ በኢዮር ከተማ የኃይላት አለቃ አድርጎ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤልን ሾሞታል፤ ይህም የሆነበት ኅዳር ፲፪ ቀን የከበረ በዓል ነው፡፡ ስለዚህ የዚህን የከበረና የገናና መልአክ በዓሉን እንድናደረግ ቅዱሳን አባቶች ሥርዓት ሠሩልን፡፡

የስሙ ትርጓሜ ‹‹ማን እንደ እግዚአብሔር›› የሆነው የመላእክት ሁሉ አለቃ ቅዱስ ሚካኤል፣ እንደ አምላክ ኃያል፣ ቸርና ርኅሩኅ ነው፤ በቅዱሱ መጽሐፍ ላይ ይህንን ነገር ራሱ መልአኩ ለነቢዩ ኢያሱ እንዲህ ሲል ገልጾለታል፤ ‹‹እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ነኝ›› (ኢያ.፭፥፲፫)

ሊቀ መለእክት ቅዱስ ሚካኤል፣ ለእኛ ሰዎች አምላጅ ሲሆን ለቅዱሳና ሰማዕታት ደግሞ አጋዣቸው የሆነው ነው፤ በሕይወታቸውና በተጋድሏቸውም እስከ መጨረሻው ይረዳቸዋል፤ እዚህ ላይ አንድ ታሪክ እናንሣ፡፡

እግዚአብሔርን የሚወድ ስሙ ዱራታዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፡፡ የሚስቱም ስም ቴዎብስታ ነው፡፡ እነርሱም ሁልጊዜ ያለማቋረጥ የዚህን የከበረ መልአክ የቅዱስ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ያደርጉ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ በሀገር ውስጥ ችግር በሆነ ጊዜ ገንዘባቸው አለቀ፡፡ ለቅዱስ ሚካኤልም ለበዓሉ መታሰቢያ የሚያደርጉትን እስኪያጡ ድረስ ቸገራቸው፡፡ ዱራታዎስም ሸጦ ለመልአኩ በዓል መታሰቢያ ያደርገው ዘንድ የእርሱንና የሚስቱን ልብስ ይዞ ወጥቶ ሄደ፡፡
የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም በታላቅ መኮንን አምሳል ለዱራታዎስ ተገለጠለትና ወደ ባለ ጸጎች ሄዶ በእርሱ ዋስትና በአንድ ዲናር አንድ በግ እንዲወስድ፣ ሁለተኛም ወደ ባለ ስንዴ ዘንድ ሄዶ በእርሱ ዋስትና ስንዴን እንዲወስድ፣ ዳግመኛም ወደ ዓሣ አጥማጅ ዘንድ ሄዶ አንድ ዓሣ እንዲወስድ፣ ነገር ግን ወደ ቤቱ ሳይርስ የዓሣውን ሆድ እንዳይቀድ አዘዘው፡፡ ዱራታዎስም እንደታዘዘው አደረገ፡፡ ወደ ቤቱም በተመለሰ ጊዜ ቤቱ ሁሉ በበረከት ተመልቶ አገኘው፡፡ እርሱም እጅግ ተደስቶ የዚህን የክበር መልአክ የመታሰቢያውን በዓል አደረገ፡፡ ጦም አዳሪዎችንና ድኆችን ጠርቶ አጠገባቸው፡፡

ከዚህም በኋላ ለዱራታዎስና ለሚስቱ ቅዱስ ሚካኤል ሁለተኛ ተገለጠላቸው፡፡ ዱራታዎስንም የዓሣውን ሆድ እንድሰነጥቅ አዘው፡፡ በሰነጠቀውም ጊዜ ፫፻ (ሦስት መቶ) የወርቅ ዲናር በዓሣው ሆድ ውስጥ ተገኘ፡፡ ቅዱስ ሚካኤል ዱራታዎስንና ሚስቱን ቴዎብስታን እንዲህ አላቸው፡- ‹‹ከዚህ ዲናር ወስዳችሁ ለባለ በጉ፣ ለባለ ዓሣውና ለባለ ስንዴው ዕዳችሁን ክፈሉ፡፡ የቀረውም ለፍላጎታችሁ ይሁናችሁ እግዚአብሔር አስቧችኋልና በጎ ሥራችሁን፣ መሥዋዕታችሁንና ምጽዋታችሁን አስቦ በዚህ ዓለም አሳመረላችሁ፣ በኋለኛውም መንግሥተ ሰማያትን አጀጋጀላችሁ›› አላቸው፡፡

እነርሱም ይህን ነገር ሲሰሙ ደነገጡ፤ የከበረ ገናናው መልአክም ‹‹ከመከራችሁ ሁሉ ያዳንኳችሁ የመላእክት አለቃ እኔ ሚካኤል ነኝ፤ መሥዋዕታችሁንና ምጽዋታችሁን ወደ እግዚአብሔር ፊት ያሳረግሁ እኔ ነኝ፡፡ አሁንም በዚህ ዓለም ከበጎ ነገር እንድታጡ አላደርጋችሁም›› አላቸው፡፡ ይህንንም ከነገራቸው በኋላ ወደ ሰማያት ወጣ፤ እነርሱም በፍርሃትና በክብር ሰገዱለት፡፡››

የኃይላት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ከበዓሉ ረድኤት በረከት ይክፈለን፤ ጥበቃውና አማላጅነቱ ሁላችንም ይጠብቀን፤ አሜን!

ምንጭ፡- ድርሳነ ቅዱስ ሚካኤል፣ ስንክሳር ዘወርኃ ኅዳር
የምሕላና የጸሎት መርሐ ግብርን በተመለከተ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት የተሰጠ ማሳሰቢያ።
*

ቅዱስ
ሲኖዶስ ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት ከኅዳር 15 አስከ21 ቀን 2016 ዓ.ም  የሚካሔደው የምህላና የጸሎት መርሐ ግብር ከላይ በተጠቀሱት ሰባት ቀናት ከማለዳው 12:00 ሰዓት እስከ ጠዋቱ 1:00 ሰዓት በምሽት መርሐ ግብር ደግሞ  ከምሽቱ 12:00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 1:00 ሰዓት ድረስ የሚከናወን ሲሆን  ሕዝበ ክርስቲያኑ በየ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ በመገኘት በመርሐ ግብሩ ላይ እንዲሳተፍ እየገለጸ አጠቃላይ መርሐ ግብሩ ቀደም ሲል በተሰጠው መግለጫ መሰረት የሚፈጸም መሆኑን ያስታውቃል።

                 የቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት

ምንጭ: EOTCPR
‹‹የእግዚአብሔር ሰው›› (፩ኛሳሙ.፱፥፮)

ውድ የዚህ ጽሑፍ አንባብያን! ዘመነ ክረምቱን/ዘመነ ጽጌን እግዚአብሔር ረድቶን ብዙ ተምረንበት አልፏል፡፡ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ወቅቶችን ከፋፍላ ነገረ እግዚአብሔርን፣ ነገረ ማርያምን እና ነገረ ቅዱሳንን ታስተምራለች፤ ትዘክራለች፡፡ ከፊታችን ኅዳር ፲፭ ቀን ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ ፳፰/፳፱ ድረስ ደግሞ ዘመነ ነቢያትን የምንዘክርበት፣ ‹‹ጾመ ነቢያት›› ብለን ከጾም ጋር አገናኝተን ስለ ነቢያትና ነቢይነት፣ እንዲሁም ስለ ትንቢት ዓላማና ምክንያቱ ቤተ ክርስቲያን ብዙ የምታስተምርበት ወቅት ነው፡፡ እኛም ‹‹የእግዚአብሔር ሰው›› በሚል ርእስ ስለ ነቢያት ምንነትና ማንነት ይህችን ጽሑፍ ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡

በመጽሐፈ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንደተጠቀሰው ነቢይ ማለት ‹‹የእግዚአብሔር ሰው›› ማለት ነው፤ ነቢይ ለአንድ፣ ነቢያት ለብዙ፣ ነቢይት ለሴት መጠሪያዎች ናቸው፡፡ (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ገጽ ፻፵፩) በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላትም በሌሎች መጻሕፍትም እንደምንረዳው

፩ኛ. ነቢይ ማለት ቃልን ከእግዚአብሔር ተቀብሎ ለሕዝብ የሚናገር፤
፪ኛ. የእግዚአብሔር ሰው፤
፫ኛ. ባለ ራእይ /ራእይ የሚያይ/፤
፬ኛ. የእግዚአብሔር ባሪያ አገልጋይ፤
፭ኛ. ኃላፍያትን፣ መጻእያትን በእርግጠኝነት የሚያውቅ የሚናገር….ወዘተ ማለት ነው፡፡

ነቢያት ለብዙ ቁጥር ሲሆን ትርጉሙ አይለወጥም፡፡ በጥቅሉ ሀብተ ትንቢት የተሰጣቸው ወደ ፊት የሚሆነውን፣ የሚከሰተውን ሁሉ በእርግጠኝነት የሚናገሩ፣ የሚናገሩትም ‹‹እግዚአብሔር እንዲህ ይላል›› እያሉ ነው፡፡ (፩ኛሳሙ.፱፥፮፣አሞ.፩፥፫፣መክ.፫፥፰) እግዚአብሔርም የሚገለጥላቸውና የሚያናግራቸው በራእይ፣ በሕልም፣ በመልአክ አማካኝነት ነው፡፡ (ዘኁ.፲፪፥፮፣ዳን.፲፥፲፩፣፣ዕብ፣ ፩፥፩)
የነቢያት ሥራ

ትንቢት ይናገራሉ፤ ሕዝቡን ይመክራሉ፤ ያስተምራሉ፤ ይገሥፃሉ እንዲሁም ያጽናናሉ፡፡ ‹‹አጽናኑ፥ ሕዝቤን አጽናኑ›› እንዳለ፡፡ (ኢሳ.፵፥፩) በእግዚአብሔር ውሳኔ ስለ ሚፈጸሙ ድርጊቶች ስለ መንግሥታት፣ ስለ ስለ ሕዝቡ፣ ስለ ኀጢአት፣ ወደ ፊት ስለሚፈጸሙ ክስተቶች ወዘተ በምሳሌ ወይም በድርጊት ይገልጹ ነበር፡፡ (ኢሳ.፭፥፩፣ኤር.፩፥፲፱) ስለዚህ ነቢይ ማለት አፈ እግዚአብሔር፣ መምህር፣ ሰባኪ ማለትም ነው፡፡ ስያሜውም መንፈሰ ትንቢት ላደረባቸው፣ ራእይን የማየት ጸጋ ለተሰጣቸው እውነተኛ ነቢያት የሚሰጥ ስያሜ ነው፡፡

የነቢያት አከፋፈል

ነቢያት ብዙ ወገን ናቸው፡፡ ቀደምት ነቢያት ደኃርት ነቢያት፣ ዐበይት ነቢያት ደቂቀ ነቢያት፣ እውነተኛ ነቢያት ሐሰተኛ ነቢያት፣ ወንድ ነቢያት ሴት ነቢያት፣ የቃል ነቢያት የጽሑፍ ነቢያት ወዘተ እየተባሉ ይከፈላሉ፡፡

ከአዳም እስከ ዳዊት ያሉትን ነቢያት ብዙ ጊዜ ቀደምት ነቢያት እያሉ ይጠሯቸዋል፡፡ በአጠቃላይ አበው ቅዱሳን ነቢያትን በአራት ከፍለን እንማራቸዋለን፡፡

፩. ዐሥራ አምስቱ አበው ነቢያት
፪. አራቱ ዐበይት ነቢያት፤
፫. ዐሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት እና
፬. ካልአን ነቢያት ናቸው፡፡
፩. ዐሥራ አምስቱ አበው ነቢያት
ዋና ዋናዎቹ አባታችን አዳም፣ ሴት፣ ሔኖስ፣ ቃይናን፣ መላልኤል፣ ያሬድ፣ ሄኖክ፣ ማቱሳላ፣ ላሜህ፣ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ፣ ሙሴ፣ ሳሙኤል ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ በየወገናቸው ሀብተ ትንቢት ተሰጥቷቸው ኃላፍያትን፣ መጻእያትን ሲናገሩ፣ ሕዝቡን ሲመክሩ፣ ሲያሰተምሩ፣ ሲያስጠነቅቁ፣ ሲያጽናኑ የነበሩ አበው ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል፡- የመጀመሪያዎቹን ዐሥሩን አበው ከአዳም እስከ ኖኅ ያሉትን ብንወስድ፣ በደብር ቅዱስ ሆነው ልጆቻቸውን ሲመክሩ፣ ከደቂቀ ቃኤል እንዳይደባለቁ፣ ቅድስናቸውን እንዲጠብቁ፣ በደቂቀ ቃኤል ምክንያት ምድሪቱ በማየ አይኅ እንደምትጠፋ አስቀድመው እንደተናገሩ በገድለ አዳምና በመጽሐፈ ቀሌምንጦስ ላይ በሰፊው ተጽፎ እናገኘዋለን፡፡

፪. አራቱ ዐበይት ነቢያት
ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤልና ዳንኤል ናቸው፡፡

፫. ዐሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት
ሆሴዕ፣ አሞጽ፣ ሚክያስ፣ ዮናስ፣ ናሆም፣ አብድዩ፣ ሶፎንያስ፣ ሐጌ፣ ኢዩኤል፣ ዕንባቆም፣ ዘካርያስና ሚልክያስ ናቸው፡፡ ዓበይትና ደቂቅ መባላቸው በምሥጢር ሳይሆን በይዘት ሰፊና አነስ ያለ ትንቢት ከመናገር አንጻር ነው፡፡

፬. ካልኣን ነቢያት
ኢያሱ፣ ሶምሶን፣ ዮፍታሔ፣ ጌዴዎን፣ ዳዊት፣ ሰሎሞን፣ ኤልያስ፣ ኤልሳዕ ወዘተ ናቸው፡፡

ነቢያት በከተማና በዘመን ጭምር ይከፈላሉ፡፡ ለምሳሌ በከተማ የይሁዳ፣ የሠማርያ፣ የባቢሎን ምርኮ ነቢያት ወዘተ እየተባሉ ሲከፈሉ፣ በዘመን ደግሞ
✍️ ከአዳም እስከ ዮሴፍ የዘመነ አበው ነቢያት፤
✍️ ከሙሴ እስከ ሳሙኤል የዘመነ መሳፍንት ነቢያት፤
✍️ ከዳዊት እስከ ዘሩባቤል የዘመነ ነገሥት ነቢያት፤
✍️ ከዘሩባቤል እስከ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ የዘመነ ካህናት ነቢያት እየተባሉ ይጠራሉ፡፡

ነቢያት የሚከፈሉበት ሌላው አከፋፈል ደግሞ የጽሑፍ ነቢያትና የቃል ነቢያት ሲሆን የጽሑፍ ማለት የተናገሩት የትንቢት ቃል በጽሑፍ የሰፈረ፣ የተጻፈ ሲሆን ከኢሳይያስ እስከ ነቢዩ ሚልክያስ ያሉትን ዐሥራ ስድስቱን ነቢያት የሚያመለክት ነው፡፡ እነዚህም አራቱ ዐበይትና ዐሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት ያልናቸው ናቸው፡፡

የቃል ነቢያት የሚባሉት ደግሞ ትንቢት ተናግረዋል፤ ግን የተናገሩት ትንቢት በጽሑፍ ያልሰፈረ ያልተጻፈ ለማለት ነው፡፡ እንደ ምሳሌ የሚወሰዱት ነቢዩ ጋድ፣ ኤልያስ፣ ኤልሳዕ፣ ናታን፣ ወዘተ፡፡

ሌላኛው አከፋፈል ደግሞ ወንድ ነቢያትና ሴት ነቢያት የምንለው ሲሆን ከላይ በተለያየ መልኩ የገለጽናቸው ወንድ ነቢያት ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ በርካታ ሴት ነቢያትም መኖራቸውን እንረዳለን፡፡ ከእነዚህም መካከል የሙሴ እኅት ማርያም (ዘፀ.፲፭፥፳) የሰፊዶት ሚስት ዲቦራ (መሳ.፬፥፬)፣ በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት የነበረችው ሕልዳና (፪ኛነገ.፳፪፥፲፬)፣ ነቢይት ሐና (ሉቃ.፪፥፴፮)፣ የፊልጶስ አራት ደናግል ሴት ልጆች ወዘተ ሴት ነቢያት ናቸው፡፡(የሐዋ.ሥ. ፳፩፥፱፣ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት)

እነዚህ ሁሉ የጠቀስናቸው ሀብተ ትንቢት ያደረባቸው፣ አፈ እግዚአብሔር ሆነው የእግዚአብሔርን ቃል ለሕዝቡም ለነገሥታቱም ሲያድረሱ፣ ሲያስተምሩ፣ ሲመክሩ፣ ሲዘክሩ፣ ሲያጽናኑ አልፎም ሲገሥፁ የነበሩ ነቢያት ሲሆኑ እውነተኞች ነቢያት ናቸው፡፡ ያናገራቸውም መንፈስ ቅዱስ ሲሆን የተናገሩት ሁሉ የተፈጸመላቸው ናቸው፡፡ ከዚሁ ጋር አብሮ የሚታየው ሌላኛው ዓይነት አከፋፈል እውነተኛ ነቢያትና ሐሰተኛ ነቢያት ተብሎ ነው፡፡

ውድ አንባብያን! ሐሰተኛ ነቢያት በዘመናችን እንደ አሸን የፈሉበት ዘመን በመሆኑ ስለ ሐሰተኛ ነቢያት መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ሐሰተኛ የሚባሉትስ ከምን አንጻር ነው? የሚለውን በክፍል ሁለት እናዳርሳችኋለን፤ ቸር እንሰንብት!
ቅዱስ ሲኖዶስ ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት ከኅዳር 15 አስከ21 ቀን 2016 ዓ.ም የሚካሔደው የምህላና የጸሎት መርሐ ግብር ከላይ በተጠቀሱት ሰባት ቀናት ከማለዳው 12:00 ሰዓት እስከ ጠዋቱ 1:00 ሰዓት በምሽት መርሐ ግብር ደግሞ ከምሽቱ 12:00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 1:00 ሰዓት ድረስ የሚከናወን ሲሆን ሕዝበ ክርስቲያኑ በየ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ በመገኘት በመርሐ ግብሩ ላይ እንዲሳተፍ እየገለጸ አጠቃላይ መርሐ ግብሩ ቀደም ሲል በተሰጠው መግለጫ መሰረት የሚፈጸም መሆኑን ያስታውቃል።

የቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት
2024/09/30 22:29:09
Back to Top
HTML Embed Code: