Telegram Web Link
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ኅዳር_26_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ቆሮ 6
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ አብረንም እየሠራን የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ እንዳትቀበሉ ደግሞ እንለምናለን፤
² በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ በመዳንም ቀን ረዳሁህ ይላልና፤ እነሆ፥ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤እነሆ፥ የመዳን ቀን አሁን ነው።
³ አገልግሎታችንም እንዳይነቀፍ በአንዳች ነገር ማሰናከያ ከቶ አንሰጥም።
⁴ ነገር ግን በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን፤
⁵ በብዙ መጽናት፥ በመከራ፥ በችግር፥ በጭንቀት፥ በመገረፍ፥ በወኅኒ፥ በሁከት፥ በድካም፥ እንቅልፍ በማጣት፥
⁶ በመጦም፥ በንጽህና፥ በእውቀት፥ በትዕግሥት፥ በቸርነት፥ በመንፈስ ቅዱስ፥ ግብዝነት በሌለው ፍቅር፥ በእውነት ቃል፥
⁷ በእግዚአብሔር ኃይል፥ ለቀኝና ለግራ በሚሆን በጽድቅ የጦር ዕቃ፥ በክብርና በውርደት፥
⁸ በክፉ ወሬና በመልካም ወሬ ራሳችንን እናማጥናለን፤ አሳቾች ስንባል እውነተኞች ነን፤
⁹ ያልታወቁ ስንባል የታወቅን ነን፤ የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን፤ የተቀጣን ስንሆን አንገደልም፤
¹⁰ ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፤ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፤ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው።
¹¹ እናንተ የቆሮንቶስ ሰዎች ሆይ፥ አፋችን ለእናንተ ተከፍቶአል ልባችንም ሰፍቶላችኋል፤
¹² በእኛ አልጠበባችሁም በሆዳችሁ ግን ጠቦባችኋል፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁶-⁷ በዚህም እጅግ ደስ ይላችኋል፥ ነገር ግን በእሳት ምንም ቢፈተን ከሚጠፋው ወርቅ ይልቅ አብልጦ የሚከብር የተፈተነ እምነታችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ፥ ለምስጋናና ለክብር ለውዳሴም ይገኝ ዘንድ አሁን ለጥቂት ጊዜ ቢያስፈልግ በልዩ ልዩ ፈተና አዝናችኋል።
⁸-⁹ እርሱንም ሳታዩት ትወዱታላችሁ፤ አሁንም ምንም ባታዩት በእርሱ አምናችሁ፥ የእምነታችሁን ፍፃሜ እርሱም የነፍሳችሁን መዳን እየተቀበላችሁ፥ በማይነገርና ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ይላችኋል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 20
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁸ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።
²⁹-³⁰ ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ።
³¹ ስለዚህ ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሠጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ኅዳር_26_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"እስመ ተዘከረ ዘይትኃሠሥ ደሞሙ። ወኢረስዐ አውያቶሙ ለነዳያን። ተሣሃለኒ እግዚኦ ወርኢ ዘከመ የሐሙኒ ጸላእትየ"። መዝ 9፥12-13
"ደማቸውን የሚመራመር እርሱ አስቦአልና፥ የድሆችንም ጩኸት አልረሳምና። አቤቱ፥ እዘንልኝ፥ ጠላቶቼም የሚያመጡብኝን መከራ እይ፥ ከሞት ደጆች ከፍ ከፍ የምታደርገኝ"፤ መዝ. 9፥12-13
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ኅዳር_26_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 21
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² ከዚህም ሁሉ በፊት እጃቸውን በላያችሁ ይጭናሉ ያሳድዱአችሁማል፤ ስለ ስሜም ወደ ምኵራብና ወደ ወኅኒ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ ወደ ነገሥታትና ወደ ገዥዎችም ይወስዱአችኋል፤
¹³ ይህም ለምስክርነት ይሆንላችኋል።
¹⁴ ስለዚህ እንዴት እንድትመልሱ አስቀድማችሁ እንዳታስቡ በልባችሁ አኑሩት፤
¹⁵ ወደረኞቻችሁ ሁሉ ሊቃወሙና ሊከራከሩ የማይችሉትን አፍና ጥበብ እሰጣችኋለሁና።
¹⁶ ወላጆችም ስንኳ ወንድሞችም ዘመዶችም ወዳጆችም አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ ከእናንተም አንዳንዱን ይገድላሉ፤
¹⁷ በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።
¹⁸ ከራሳችሁም አንዲት ጠጉር ስንኳ አትጠፋም፤
¹⁹ በመታገሣችሁም ነፍሳችሁን ታገኛላችሁ።
²⁰ ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ።
²¹ የዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ፥ በመካከልዋም ያሉ ከእርስዋ ፈቀቅ ይበሉ፥ በገጠር ያሉም ወደ እርስዋ አይግቡ፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ የሚቀደሰው የ #ቅዱስ_ዮሐንስ_ወልደ_ነጎድጓድ ነው። መልካም የአቡነ ሀብተ ማርያም፣ የአቡነ ኢየሱስ ሞዐ የዕረፍት በዓል፤ የአቡነ ሰላማ የልደት በዓል፣ የናግራ ሰማዕታት መታሰቢያ በዓልና የነቢያት (የገና) የጾም ጊዜ። ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"#ሰላም_ለዘበናግራን_ሰማዕታት_ሰላም_ለአቡሆሙ_ኂሩት። ሰላም ለቀሳውስት ወለዲያቆናት ወለመነኰሳት ወለመበለታት። ሰላም ለአእሩግ ወለሕፃናት ሰላም ለእድ ወለአንስት። ሰላም ለኵሎሙ እለ በናግራን ሰማዕታት እለ ቦኡ ሀገረ እንተ ትመስል ኢየሩሳሬም እንተ በሰማያት፤ ወደቂቃ ይመስሉ ከዋክብተ ብሩሃነ፤ አድባሪሃ ቅዱሳን ወከዋክብቲሃ ይጸንሑ እስከ አርያም፤ ለቀበላሁ ለወልደ ማርያም"። ትርጉም፦ #በናግራን_ሰማዕታት_ለኾኑ፤ ለአባታቸውም #ኂሩት_ሰላምታ_ይገባል። ለቀሳውስትና ለዲያቆናት ለመነኰሳትና ለድኾች ሴቶች ሰላምታ ይገባል፤ ለሽማግሎችና ለሕፃናት ሰላምታ ይገባል፤ ለወንዶችና ለሴቶች ሰላምታ ይገባል። በሰማያት ያለች ኢየሩሳሌምን ወደ ምትመስል አገር የገቡ በናግራን ላሉ ሰማዕታት ኹሉ ሰላምታ ይገባል፤ ልጆቿም ብሩሃን ከዋክብትን ይመስላሉ፤ ተራሮቿም የተቀደሱ ናቸው፤ ከዋክብቷም የማርያምን ልጅ ክርስቶስን ለመቀበል እስከ ሰማይ ድረስ ደጅ ይጠናሉ። #ሊቁ_አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ_በተአምኆ_ቅዱሳን_ላይ

                      
"#ሰላም_እብል_ስነክሙ መአድመ። #ከዋክብተ_ናግራን_ሰማዕት ዘአብራህክሙ ዓለመ። ዓራቄ ኩኑነ ወመስተሳልመ። በቅድመ አምላክ ፈታሒ አመ ኃጢአትነ ቆመ። በእንተ ስሙ ዘከአውክሙ አርእይዎ ደመ። ትርጉም፦ ዓለምን ያበራችኍ #የናግራን_ከዋክብት_ሰማዕት_ሆይ ላማረ ደም ግባታችኍ ሰላም እላለኊ፤ ኃጢአታችን #በፈራጅ_አምላክ ፊት በቆመ ጊዜ አስታራቂና አስማሚ ኹኑን! በስሙ ያፈሰሳችኹትን ደም አሳዩት!። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የኅዳር_26
ጻድቁ አቡነ ተክለ ሐይማኖትን ያመነኮሷቸው አባት አቡነ ኢየሱስ ሞዓ የነበሩበት ዘመን(ዓ.ም) ስንት ነው?
Anonymous Quiz
21%
ከ1292-1356 ዓ.ም
48%
ከ1210-1292 ዓ.ም
19%
ከ1250-1308 ዓ.ም
12%
ከ1215-1299 ዓ.ም
የናግራን ሰማዕታት አባታቸው የአቡነ ኂሩት የባለቤታቸው ስም ማን ይባላል?
Anonymous Quiz
25%
ቅድስት ዮስቴና
35%
ቅድስት ኪልቅያ
24%
ቅድስት ድማሕን
16%
ቅድስት ታቱስብያ
ጻድቁ አቡነ ሐብተ ማርያም የተወለዱበት ቀን መቼ ነዌ?
Anonymous Quiz
25%
ሰኔ 26
35%
ግንቦት 26
22%
ሚያዝያ 26
18%
መጋቢት 26
ጻድቁ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ የጣና ሐይቅ ቅዱስ እስጢፋኖስ ገዳምን በአበምኔትነት ለስንት ዓመት አገለገሉ?
Anonymous Quiz
42%
ለ40 ዓመት
22%
ለ42 ዓመት
22%
ለ48 ዓመት
14%
ለ45 ዓመት
በአይሁድ ንጉስ ፊንሐስ በግፍ ለተገደሉት የናግራን ሰማዕታት እግዚአብሔር እንዲበቀልላቸው የላከው የኢትዮጵያዊው ቅድስ ማን ይባላል?
Anonymous Quiz
20%
ቅዱስ አጼ ገብረ መስቀል
33%
ቅዱስ አጼ ዘርዐ ያዕቆብ
31%
ቅድስ አጼ ካሌብ
16%
ቅዱስ አጼ ገላውዴዎስ
#ኅዳር_27

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ኅዳር ሃያ ሰባት በዚህች ቀን አባታችን #አቡነ_ተክለ_ሐዋርያት ዕረፍታቸው ነው፣ ሕዋሳቱ የተቆራረጠ #ቅዱስ_ያዕቆብ_ዘግሙድ በሰማዕትነት አረፈ፣ ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ #ቅዱስ_ፊልሞና_ሐዋርያ ዕረፍቱ ነው፣ በንሑር ከሚባል አገር #ቅዱስ_ጢሞቴዎስ በሰማዕትነት አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ተክለ_ሐዋርያት

ኅዳር ሃያ ሰባት በዚህች ቀን አባታችን አቡነ ተክለ ሐዋርያት በክብር አርፈዋል።

አባታቸው የእናርዕት አገረ ገዥ የነበሩት እንድርያስ ሲሆኑ እናታቸው ደግሞ እሌኒ ይባላሉ፡፡ የትውልድ ሀገራቸው ሸዋ ሲሆን በዚሁ የምትገኘውን ታላቋን የደብረ ጽሙናን ገዳም የመሠረቱ ሲሆን በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን የነበሩ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ገና በእናታቸው ማኅፀን ሳሉ አጋንንትን እያቃጠሉ ያጠፏቸው ነበር፡፡ የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርት ተምረው ከጨረሱ በኋላ ገና በድቁና እያገለገሉ ሳለ 40 ቀን በማክፈል ይጾሙና ይጸልዩ ነበር፡፡

አባታችን የመነኮሱትና ብዙ ተጋድሎአቸን ፈጽመው ወደ ሰማይ ተነጥቀው #ሥላሴን እስከማየት የደረሱት በደብረ ሊባኖስ ነው፡፡ ያመነኮሷቸውም ሁሉን በስውር ያለውን የሚያውቁት አቡነ ዮሐንስ ከማ ናቸው፡፡ አባታችን ማታ ማታ ከባሕር ውስጥ ገብተው ሲጸልዩ እያደሩ በቀን 30 ፍሬ አተር ብቻ እየተመገቡ ይጾሙ ነበር፡፡ ስውራን የሆኑ ቅዱሳን አባታችም እየተገለጡላቸው ምሥጢራትን ይነግሯቸዋል፡፡ ከስግደታቸውም ብዛት የተነሣ የአባታችን ሁለት የእጆቻቸው አጥንቶች ተሰበሩ፡፡ ከቁመታቸውም ብዛት የተነሣ እግሮቻቸው አበጡ፡፡ ስምንት ስለታም ጦሮችን ያሉበትን የብረት ሰንሰለት በወገባቸው ታጥቀው ሁለት ሁለቱን በፊት በኋላ በቀኝ በግራ አድርገው ታጠቁ፡፡ እነዚህም ጦሮች ከልደት፣ ከጥምቀትና ከትነሣኤ በዓል በቀር ከወገባቸው ላይ አያወጧቸውም ነበር፡፡

በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ሲቀመጡ፣ ሲነሡና ሲሰግዱ ጦሮቹ ሰውነታቸውን ሲወጓቸው በዚያን ጊዜ የ #ጌታችንን በጦር መወጋቱንና መከራውን ያስባሉ፡፡ በታመሙም ጊዜ "ኃጢአተኛ ሰውነቴ ሆይ ስለአንቺ የተቀበለውን የ #ክርስቶስን መከራ አስቢ" እያሉ ሰውነታቸውን ይጎስማሉ፡፡ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ነጥቆ ወስዶ ከገነት ዕፅ አምጥቶ አባታችንን ካሸተታቸው በኋላ ግን ርሃብና ጥም የሚባል ነገር ጠፍቶላቸዋልና ምድራዊውን ነገር ለመቅመስ የሚጸየፉ ሆኑ፡፡ ጻድቁ ቅስና እንዲሾሙ የገዳሙ አበምኔት ግድ ቢሏቸውም አባታችን ግን እምቢ ስላሉ "ለጳጳሱ መልእክት አድርስልኝ" ብለው በዘዴ ልከዋቸው ጳጳሱም በመንፈስ ተረድተው ቅስና ሾመዋቸዋል፡፡

ጻድቁ በአቡነ አትናቴዎስ መቃብር ላይ ሄደው አጥብቀው ይጸልዩ በነበረበት ወቅት ብርሃን ይወርድላቸው እንደነበር እግዚእ ክብራ የተባለች አንዲት ትልቅ ጻድቅ እናት ትመለከት ነበር፡፡ አባታችን ሁልጊዜ "ሦስት ነገሮችን እፈልጋለሁ እነርሱም ከሐሜት ስለመራቅ፣ ክፉ ነገርን ከማየት ስለመራቅና ከንቱ ነገርን ከመስማት ስለመራቅ ናቸው" እያሉ ይናገሩ ነበር፡፡ አቡነ ተክለ ሐዋርያት የታላቁን አባት የአቡነ አትናቴዎስን መቃብር ለማየት በሄዱ ጊዜ ቆመው ሲጸልዩ ከእግራቸው በታች ጸበል ፈልቆ በጽዋ ውኃ ሲፈስ አገኙት፡፡ ውኃውንም ወስደው ቦታውን ላሳየቻቸው ለእግዚእ ክብራ ሰጧት፡፡ እርሷም መካን ለነበረችው ገረዷ ሰጠቻትና ገረዷም በጻድቁ ጸሎት የፈለቀውን ውኃ ጠጥታ ልጅ ወለደች፡፡ ይህ አባታችን ያፈለቁት ጸበል ዛሬም ድረስ ሲፈስና ሕሙማንን ሲፈውስ ይገኛል፡፡

ጸድቁን የታዘዘ መልአክ መጥቶ ወደ በረሃ እንዲገቡ ስለነገራቸው ወደ ምድረ ሐጋይ ሄደው በዚያ ታላቅ በረሃ ውስጥ ለ41 ዓመታት ጽኑ ተጋድሎን ተጋድለዋል፡፡ ባሕር ውስጥ በሚገኝ ዋሻ ውስጥም ገብተው ብዙ ዘመን በጸሎት ኖረዋል፡፡ ሰዎች የአባታችንን የእግራቸውን እጣቢ ሕመምተኞች ላይ በረጩት ጊዜ በላያቸው ላይ ያደረባቸው ርኩስ መንፈስ እየጮኸ ይወጣል፡፡ ቅዱሳን መላእክት ዘወትር እየመጡ አባታችንን ይጎበነኟቸዋል፡፡ #እመቤታችን ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን አስከትላ እየመጣች ትጎበኛቸዋለች፡፡ ብዙ ተጋድሎ ባደረጉበት ዋሻ ውስጥም ሳሉ #መድኃኔዓለም_ክርስቶስ ተገልጦላቸው በቦታው ላይ ታላቅ ቃልኪዳን ሰጥቷቸዋል፡፡ መላእክትም ወደ ሰማይ አሳርገዋቸው በ #ሥሉስ ቅዱስ መንበር ፊት አቁመዋቸው ታላቅ ምሥጢርን አይተዋል፡፡

አቡነ ተክለ ሐዋርያት ለ #መድኃኔዓለም ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ትልቅ ክብር ያላቸው አባት ናቸው፡፡ አንድ በከባድ በሽታ ይሠቃይ የነበረ ሰው "ነፍሴ ከሥጋዬ ሳትለይ ፈጥናችሁ ወደ ቤተ ክርስቲያን ውሰዱኝና የ #ጌታችንን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ልቀበል" ብሎ ቤተሰቦቹን ለመነ፡፡ ቤተሰቦቹም ወደ ቤተ ክርስቲያን ወስደውት ቅዱስ ሥጋ ክቡር ደሙን ከተቀበለ በኋላ ከሆዱ ውስጥ ዥንጉርጉር ደምና ሐሞት ከመግል ጋር ወጣ፡፡ በዚህም ጊዜ ካህናቱ ስለ ሥጋ ወደሙ ክብር ብለው በዕቃ ተቀበሉት፡፡ ሽታው ግን ቤተ ክርስቲያኑን አናወጸው፡፡ በዚህም ጊዜ አባታችን ተክለ ሐዋርያት #መድኃኔዓለም_ክርስቶስ ስለእኛ ብሎ በዕለተ ዐርብ መራራ ሐሞትና ከርቤ መጠጣቱን አስበው ከሰውየው ሆድ ውስጥ የወጣውን ደም የተቀላቀለበትን መግልና ሐሞት ስለ ሥጋ ወደሙ ክብር ብለው በቤተ ክርስቲያኑ በተሰበሰቡት ሰዎች ፊት አንሥተው ጠጡት፡፡ ይህም የሆነበት ዕለት እሁድ ነበርና አባታችን እዚያው ቤተ ክርስቲያኑ ዋሉ፡፡ #መድኃኔዓለም_ክርስቶስም አባታችን ወዳሉበት መጥቶ "ወዳጄ ተክለ ሐዋርያት ሆይ ሰላምታ ይገባሃል፡፡ በሰው ሁሉ ፊት እንዳከበርከኝ እኔም በምድራውያንና በሰማያውያን መላእክት ሁሉ ፊት አከብርሃለሁ" ካላቸው በኋላ ሌላም ብዙ ቃልኪዳን ገባላቸው፡፡ ሰባት አክሊላትንም ካቀዳጃቸው በኋላ ዕጣ ክፍላቸው ከመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር መሆኑን ነግሯቸዋል፡፡

ከዚህም በኋላ አባታችን ወደተለያዩ የሀገራችን ገዳማት በመሄድ ከቅዱሳን በረከትን ከተቀበሉ በኋላ በየሄዱባቸው ገዳማት 40 ቀንና 40 ሌሊት ይጾማሉ፡፡ ከሰንበት በቀርም ምንም ምንመ አይቀምሱም፡፡ ሰንበትም በሆነ ጊዜ የዕንጨቶችን ፍሬ ብቻ ይመገባሉ፡፡ አባታችን ከዋልድባ ገዳም ወጥተው ወደ ደባብ ገዳም በመሄድ በዚያ አርባዋን ቀን ከጾሙ በኋላ #ጌታችን ተገለጠላቸውና "ተነሥተህ ወደ አልተጠመቁ አሕዛብ አገር ሂድ በዚያ በአንተ እጅ የሚጠመቁና የሚድኑ ብዙ አሕዛብ አሉና በስሜ አስተምር" አላቸው፡፡ አባታችንም ተነሥተው "ሀገረ ጽልመት" ወደሚባል ወዳልተጠመቁ አሕዛብ አገር ሄደው የአገሪቱን ንጉሥና ሕዝቡንም በጠቅላላ አስተምረው በተአምራቶቻቸው አሳምነው አጥምቀዋቸዋል፡፡ በዚያም ሀገር ለአሕዛብ እየጠነቆለ የሚኖር አንድ መሠርይ ነበርና አባታችንን አግኝተውት አስተምረው በላዩ ያለበትን ርኩስ መንፈስ አውጥተውለት አጥምቀውታል፡፡

አባታችን የ #እግዚአብሔርን ወዳጅ የሊቀ ነቢያትን መቃብር ያሳቸው ዘንድ #ጌታችንን በለመኑት ጊዜ #ጌታችን በሌሊት ተገልጦላቸው ወስዶ የ ቅዱስ ሙሴን መቃብር አሳይቷቸዋል፡፡ የአባታችን በትራቸው እንደሙሴ በትር ተአምር ትሠራ ነበር፡፡ ሕመምተኞች በትሯን አጥበው የእጣቢውን ውኃ ሲጠጡት ፈጥነው ከሕመማቸው ይፈወሱ ነበር፡፡ በ #ጌታችን የጥምቀት በዓል ቀን አባታችን ተክለ ሐዋርያት ጸሎት በማድረግ ሰዎችን ሲያጠምቁ #መንፈስ_ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሳቸው ላይ ይታይ ነበር፡፡ በቆሙበትም ቦታ የብርሃን ምሰሶም እስከ ሰማይ ድረስ ደርሶ ተተክሎ ታይቷል፡፡ አባታችን ቅዱሳት ገዳማትን ለመሳለም ከአንዱ ቦታ ወደ አንዱ ቦታ የሚዘዋወሩት በብርሃን
ሰረገላ ነበር፡፡ በደመናም ተጭነው ሲሄዱ ያዩአቸው ቅዱሳን አሉ፡፡ የመለኮትን ቃል ወንጌልን ሲጸልዩ ቅዱሳን መላእክት መጥተው በክንፋቸው ይጋርዷቸው ነበር፡፡ የአቡቀለምሲስን ራእይ በጸለዩ ጊዜ ራሱ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊው መጥቶ በአጠገባቸው ይቆም ነበር፡፡

አባታችን የዕረፍታቸው ጊዜ በደረሰ ሰዓት የብርሃን እናቱ #እመቤታችን ቅዱሳን ሚካኤልንና ገብርኤልን ሰማዕቱን ቅዱስ ጊዮርጊስን አስከትላ መጥታ "የጳውሎስ አበባ የጴጥሮስ ፍሬ የልጄ ተክል ወዳጄ ተክለ ሐዋርያት ሆይ ሰላምታ ይገባሃል" አለቻቸው፡፡ ዳግመኛም "እነሆ የተመኘኸውን ታገኘዋለህና፣ ጊዜው ቀርቧልና ጽና በርታ እኔንና ልጄን የለመንከንን ነገር አስብ" ብላቸው ተሰወረች፡፡ አባታችን በተደጋጋሚ #እመቤታችንንና #ጌታችንን ስለ ስሙ ብለው ሰማዕት ይሆኑ ዘንድ ይለምኑ ስለነበረ ነው #እመቤታችን ይህንን የነገረቻው፡፡

ከዚህም በኋላ የንጉሡ የዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ባለቤት አባታችንን "ስለ #ክርስቶስ ብለሁ መጥተው አስትምሩን ምከሩን" ብላ ለመነቻቸውና አባታችን ሄደው መከሯት፡፡ ልጃቸውን ገላውዴዎስን አስተምረው ባረኩት፡፡ ለንጉሡ ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብም ብዙ ምሥጢርን ነገሩት፡፡ ንጉሡም በአቅራቢያው የ #እመቤታችን ታቦት ካለችበት ቦታ ሦስት ወር ከእርሱ እንዲቀመጡ ለመናቸው፡፡ እሳቸውም በዚያ ሲቆዩ የንጉሡ ወታደሮች በፈረስ ግልቢያና በድብደባ እየተገዳደሉ አይተው አዘኑ፡፡ "ይህ የአረመኔዎች ሥራ ነው" ብለው ሕግንና ሥርዓትን ሊያስተማሯቸው አስበው ወደ ንጉሡ ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ እንዲያናግራቸው መልእክተኛ ላኩበት፡፡ ንጉሡም "ዛሬ አይመቸኝም" አላቸው፡፡ አባታችንም መልአክተኛውን ስለ ሰዎቹ በከንቱ መሞትና ሌላንም መልእክቶችን ላኩለት፡፡ መልእክተኛውም የመዘምራን አለቃ ደብተራ ስለነበር አባታችንን "እኔ እያለሁ ለአንተ ነቢይነትን ማን ሰጠህ?" ብሎ በክፉ ቃል ተናገራቸውና ሄዶ ከንጉሡ ጋር በክፉ ወሬ አጣላቸው፡፡ ወደ ንጉሡ ገብቶ "ንጉሥ ሆይ ይህ መነኩሴ ጻድቅ ነኝ ይላል፣ አንተን ግን ይሰድብሃል ባንተ ላይም ብዙ ዘለፋ ይናገራል…" አለው፡፡ ንጉሡም በጣም ተቆጥቶ አባተችን አስመጥቶ "ለምን ይዘልፉኛል?" አላቸው፡፡ አባታችንም ዘለፋ ሳይሆን ሊሆን የማይገባውን ነገር ሁሉ ነገሩት፡፡ ይልቁንም ስለሴቶቸና ስለፍርድና መሥራት ስለማይገባው ነገር ሁሉ ሲናገሩት ንጉሡም ደፍረው ስለተናገሩት በኃይል ይደበድቧቸው ዘንድ አዘዘ፡፡ ከአፍና አፍንጫቸውም ደም እንደውኃ እስኪርድ ድረስ ደበደቧቸውና አሠሯቸው፡፡

ዳግመኛም ንጉሡ ቢያስመጣቸው ደግመው ስለጥፋቱ ገሠጹት፡፡ አሁንም ጽኑ ድብደባን አደረሱባቸውና አሠሯቸው፡፡ በዚያም ብዙ አሠቃዩአቸው፡፡ በዚህም ጊዜ #እመቤታችን ለአባታችን ተገልጣላቸው "እነሆ የልጄን ትእዛዝ ፈጸምህ የተመኘኸውን አገኘህ፣ ነገር ግን ሁለት የትዕግስት በር ይቀርሃል እርሱን ከፈጸምክ ልጄ ከዚህ ከኃላፊው ዓለም ያሳርፍሃል" አለቻቸው፡፡ አባታችንም #እመቤታችንን "ሰማዕትነት ስጪኝ ያልኩሽ በክርስቲያናዊ እጅ ነውን? ነገር ግን አማላጅነትሽ ሰማዕትነትን ለመፈጸም ያጽናኝ" አሏት፡፡

ከዚህም በኋላ የንጉሡ ጭፍሮች አባታችንን በጠጠር ጎዳና ላይ እየጎተቷቸው ብዙ አሠቃዩአቸው፡፡ የንጉሡ ስምንት ጭፍሮች በመቀጣጠብ "ንጉሡ መቼ እሞታለሁ" ብሎሃል እያሉ በመሾፍ አባታችንን ወደ ዱር ወስደው በአቅማቸውን ያህል በኃይል ደበደቧቸው፡፡ የ #መንፈስ_ቅዱስ ኃይል ባያጸናቸው ኖሮ በአንደኛው ሰው ዱላ ብቻ ነፍሳቸው በወጣች ነበር፡፡ በእሥርም 8 ወር ከተቀመጡ በኋላ ከዚህ ዓለም በሞት የሚያርፉበት ጊዜ ስለደረሰ ቅዱሳን መላእክት ከእሥር ቤት ነጥቀው ወስደው ወደ ሰማይ አሳረጓቸውና በ #ሥሉስ ቅዱስ ፊት አቆሟቸው፡፡ በዚያም ለሦስት ሳምንት ቆዩ፡፡ #ጌታችንም ለአባታችን ብዙ የሕይወትን ምሥጢር ነገራቸው፡፡ እንደጸሐይ የምታበራዋን የምድርን ማዕዘነ ዓለም የምታክል ሰማያዊት ሀገር ርስት አድርጎ ሰጣቸው፡፡ "ስምህን ከሚጠሩ ልጆችህ፣ የገድልህን መጽሐፍ ከጻፉ ካጻፉ ከሰሙ፣ ዝክርን ካዘከሩ በጸሎትህ ከተማኑ ልጆችህ ጋር የምትኖርባት ዕድል ፈንታህ ናት" አላቸው፡፡

አባታችንም #ጌታችንን "አቤቱ ፈጣሪዬ ሆይ ይህን ቃልኪዳን የሰጠኸኝ አንተን የሚያስደስት ምን ነገር አደረኩልህ በቸርነትህ ነው እንጂ" አሉት፡፡ #ጌታችንም "ዕድል ፈንታህ ጽዋ ተርታህ እውነተኛ የእኔ ምስክር ከሚሆን ጊዮርጊስና ወዳጄ ከሚሆን ከዮሐንስ ጋራ ይሁን" አላቸው፡፡ ዳግመኛም #ጌታችን ሰባት አክሊትን አቀዳጃቸውና "አንዱ ስለ ድንግልናህ ነው፣ አንዱ ሃይማኖትህን ለማስተማር ከአንዱ ሀገር ወደ አንዱ አገር ስለሄድክ ነው፣ አንዱ ቅዱሳንን ለመጎብኘት እየተዘዋወርክ ከቅዱሳን ጋራ ስለተነጋገርክበት ነው፣ አንዱ ስለየዋህነትህ ኃላፊ ዓለምን ስለመናቅህ ነው፣ አንዱ ስለተወደደ ክህነትህ ነው፣ አንዱ ታግሰህ ስለመጋደልህ ነው፣ አንዱም ደምህን ስለማፍሰስህ ነው" አላቸው፡፡ #ጌታችን ይህን ቃልኪዳንና ክብር ከሰጣቸው በኋለ "ከዚህ ከሚጠፋው ዓለም አሳርፍሃለሁ" አላቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ከተነጠቁበት ከሦስት ሳምንት በኋላ ተመልሰው ከእሥር ቤቱ ሆነው ያዩትን ሁሉ ለአንድ ወዳጃቸው ለሆነ ቄስ ተክለ ኢየሱስ ነገሩት፡፡

ዳግመኛም አባታችን በእሥር ቤት ሳሉ በመላአክት እጅ ተነጥቀው ወደ ሰማይ ከተወሰዱና ከ #ጌታችን ቃልኪዳን ከተቀበሉ በኋላ የብርሃን እናቱ ክብርት #እመቤታችን እንዳነጋገረቻቸው ተናገሩ፡፡ " #እመቤታችን_ማርያም 'ዘርዐ ያዕቆብን ይቅር በልልኝ፣ ኃጢአቱንም ተውለት፣ በልጄ ፊት ቀርበህ 'ግፌን ተመልከትልኝ' አትበል እርሱ ዘወትር ስሜን ይጠራልና፣ ስለ ድንግልናዬም የሚያስተምር ነውና' አለኝ፡፡ እኔም የእመ ብርሃንን ርኅራኄ አደነቅሁና ' #እመቤቴ_ሆይ! አንቺ እያዘዝሽኝ ወድጄ ነውን የምመረው! እኔ ኃጢአተኛ ለምን ይቅር አልልም ይቅር እላለሁ እንጂ ነገር ግን የአንቺ ጸሎት ሁላችንንም ይማረን' አልኋት፡፡"

አቡነ ተክለ ሐዋርያት በመጨረሻ ዘመናቸው በንጉሡ አደባባይ ኅዳር 27 ቀን ሲያርፉ ቅዱሳን መላእክት መጥተው ገንዘው ቀብረዋቸዋል፡፡ በመካነ መቃብራቸውም ላይ ብርሃን ተተክሎ ታይቷል፡፡ ንጉሡ ዘርዐ ያዕቆብም በመካነ መቃብራቸው ላይ ብርሃን መውረዱንና ብዙ ተአምራት ማድረጉን በሰማ ጊዜ እጅግ አደነቀ፡፡ ብዙ ምልክትም አገኘ፡፡ አባታችን ሰማዕትነትን ይቀበሉ ዘንድ ተመኝተው ራሳቸው ለምነዋልና መደብደብ መሠቃየታቸው በ #እግዚአብሔር ፈቃድ ነው፡፡ ንጉሡም መነኮሳት ልጆቻቸውንም ጠርቶ የአባታችንን ሥጋ በክብር እንዲያፈልሱ ነገራቸው፡፡ ርስት ጉልት የሚሆን መሬት ሰጣቸው፡፡ ነገር ግን ዐፅማቸው ከመፍለሱ በፊት ንጉሡ በሞት ስላረፈ ልጁ በእደ ማርያም በአባቱ ትእዛዝ መሠረት የአባታችንን ዐፅም ከ13 ዓመት በኋላ ወደ ደብረ ጽሞና በክብር አፍልሶታል፡፡ ታቦታቸው ደብረ ሊባኖስ አውራጃ አጋት #መድኃኔዓለም ይገኛል፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጻድቁ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ያዕቆብ_ዘግሙድ

ዳግመኛም በዚህች ቀን ለፋርስ ንጉሥ ለሳፎር ልጅ ለንጉሥ ሰክራድ ከጭፍሮቹ ውስጥ የሆነ ሕዋሳቱን የተቆራረጠ ቅዱስ ያዕቆብ በሰማዕትነት አረፈ።

ይህም ንጉሥ ሰክራድ እጅግ ይወደው ነበር ስለ መንግሥቱ ሥራ ሁሉ ከእርሱ ጋር ይማከር ነበርና ስለዚህም የቅዱስ ያዕቆብን ልቡና አዘንብሎ ፀሐይንና እሳትን እንዲአመልክ አደረገው ።
በሃይማኖቱም ከንጉሡ ጋር እንደተስማማ የተቀደሱ እናቱ ሚስቱና እኅቱ በሰሙ ጊዜ እንዲህ ብለው ጽፈው ወደርሱ ላኩ የቀናች የ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስን ሃይማኖት ትተህ የፍጡራንን ጠባይ ለምን ተከተልክ እሊህም ፀሐይ ጨረቃ ከዋክብት እሳት ናቸው ዕወቅ ከዛሬ ጀምሮ በንጉሥ ሃይማኖት ከኖርክ እኛ ከአንተ የተለየን ነን።

የመልእክታቸውንም ጽሑፍ በአነበበ ጊዜ መሪር ልቅሶን አለቀሰ በዚህም የጥፋት ምክር ጸንቼ ብኖር ከቤተ ሰቦቼና ከወገኖቼ የተለየሁ መሆኔ ነው ። ደግሞስ በ #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ፊት እንዴት እቆማለሁ አለ ከዚህም በኋላ የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍቶች ማንበብ ጀመረ የንጉሡን አገልግሎትም ተወ ለንጉሡም ወዳጅህ ያዕቆብ እነሆ አገልግሎትህን አማልክቶችህንም ማምለክ ተወ ብለው ነገሩት።

ንጉሡም ልኮ ወደርሱ አስቀርቦ አገልግሎትህን ለምን ተውክ አለው ቅዱስ ያዕቆብም እንዲህ አለ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በከበረ ወንጌል በሰው ፊት ያመነብኝን ሁሉ እኔም በሰማያዊ አባቴ ፊት አምነዋለሁ በሰው ፊት የካደኝንም በአባቴ ፊትና በመላእክት ፊት እክደዋለሁ ብሏልና ስለዚህ አገልግሎትህን ፍቅርህን አማልክቶችህንም ማምለክ ትቼ ሰማይና ምድርን ፀሐይን ጨረቃን ከዋክብትን የሚታየውንና የማይታየውን ለፈጠረ ለሕያው #እግዚአብሔር ልጅ ለ #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ የምሰግድ ሆንኩ።

ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ ደሙ እንደ ውኃ በዝቶ እስቲፈስ ታላቅ ግርፋትን እንዲገርፉት አዘዘ እርሱ ግን ከበጎ ምክሩ አልተመለሰም ዳግመኛም ሕዋሳቱን በየዕለቱ እንዲቆርጡ አዘዘ የእጆቹንና የእግሮቹን ጣቶች ሃያውን ቆረጡ ክንዶቹንና እግሮቹን እስከ ጭኖቹ ድረስ ወደ አርባ ሁለት ቁራጭ በየጥቂቱ ቆረጡት ። በሚቆርጡትም ጊዜ ሁሉ #ጌታዬና_ንጉሤ_ኢየሱስ_ክርስቶስ እንደ ዕንጨት ቅርንጫፍ ሰውነቴን በይቅርታህ ገናናነት ተቀበል የወይን አታክልት ያለው በየሦስት ዓጽቅ ሲቆርጡለት ዓጽቆቹ በዝተው ይበቅላሉ ይሰፋሉ በሚያዝያ ወር አብቦ ያፈራልና እያለ የሚዘምርና የሚያመሰግን ሆነ ።

ደረቱና አካሉ እንደ ግንድ ድብልብል ሆኖ በቀረ ጊዜ ነፍሱን ለመስጠት እንደ ደረሰ አውቆ በዚያን ጊዜ በዓለም ውስጥ ያሉትን ሰዎች ሁሉንም ይምራቸው ዘንድ #እግዚአብሔርን ለመነው እንዲህም አለ ለእኔ ግን ወደ አንተ የማነሣው አካል አልቀረልኝም ሕዋሳቶቼ ተቆርጠው በፊቴ የወደቁ ስለሆነ አሁንም ነፍሴን ተቀበላት አለ ።

በዚያንም ጊዜ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ተገልጾ አረጋጋው አጸናውም ያን ጊዜ ነፍሱ ደስ አላት ነፍሱንም ከመስጠቱ በፊት ወታደሩ በፍጥነት መጥቶ የከበረች ራሱን በሰይፍ ቆረጠ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ ሥጋውንም ምእመናን ሰዎች ወስደው በመልካም አገናነዝ ገነዙትና በንጹሕ ቦታ አኖሩት ። እናቱ ሚስቱና እኅቱ በሰማዕትነት እንደሞተ በሰሙ ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው ወደ ቅዱስ ያዕቆብም ሥጋ መጥተው ተሳለሙት አለቀሱለትም የከበሩ ልብሶችንም በላዩ አኖሩ ጣፋጮች የሆኑ ሽቱዎችንም ረጩበት ።

በደጋጎች ነገሥታት በአኖሬዎስና በአርቃዴዎስ በሌሎችም ዘመን አብያተ ክርስቲያን ታነፁ ገዳማትና አድባራትም ተሠሩ የሰማዕታትንም ሥጋ በውስጣቸው አኖሩ ታላላቆች ድንቆች ተአምራትም ከእሳቸው የሚታዩ ሆኑ ። የፋርስ ንጉሥም ሰምቶ በቦታው ሁሉ የሰማዕታትን ሥጋ ያቃጥሉ ዘንድ አዘዘ በሚገዛውም አገር ውስጥ ምንም ምን እንዳይተው አማንያን ሰዎችም መጥተው የቅዱስ ያዕቆብን ሥጋ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት ከዚያም ወደ ሀገረ ሮሀ ከሀገረ ሮሀም የከበረ ኤጲስቆጶስ ጴጥሮስ ወደ ግብጽ አገር ወደ ብሕንሳ ከተማ ወሰደው ። በዚያም ጥቂት ጊዜ ኖረ ከርሱ ጋርም መነኰሳት ነበሩ ከቀኑ እኩሌታም ሲጸልዩ የቅዱስ ያዕቆብ ሥጋ ከብዙ የፋርስ ሰማዕታት ሥጋ ጋር በአለበት ሰማዕታት አብረዋቸው ዘመሩ ባረኳቸውም ቅዱስ ያዕቆብም #እግዚአብሔር እንዳዘዘ ሥጋዬ በዚህ ይኑር አለ ከዚህም በኋላ ተሠወሩ ።

ከዚህም በኋላ የከበረ ኤጲስቆጶስ ጴጥሮስ ወደ አገሩ ሊመለስ በወደደ ጊዜ ሥጋዬ በዚህ ቦታ ይኑር ያለውን የቅዱስ ያዕቆብን ቃል ተላልፎ የቅዱስ ያዕቆብን ሥጋ ወሰደ በዚያንም ጊዜ አስቀድሞ ወደ አመለከተው ቦታ ከእጆቻቸው መካከል ተመለሰ ከሥጋውም ታላላቅ የሆኑ ተአምራት ተገለጡ ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ሰማዕት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ፊልሞና_ሐዋርያ

በዚህችም ዕለት ከሰባ ሁለቱ አርድእት የአንዱ የፊልሞና የዕረፍቱ መታሰቢያው ነው።

ቅዱስ ፊልሞና ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ሲሆን ብዙ ጊዜ "ጥዑመ - ቃል (አንደበቱ የሚጣፍጥ)" ተብሎ ይጠራል። በዘመነ ሐዋርያት በጣም ልጅ በመሆኑ እየተሯሯጠ ለአበው ይታዘዝ ነበር።

#ጌታን አምኖ ተከትሎ ለሦስት ዓመት ከሦስት ወር ተምሮ፣ ከቅዱስ መንፈሱ ነስቶ፣ ከቅዱስ እንድርያስ ጋር ለስብከት ወጥቷል። ሃገረ ስብከቱም ልዳ ነበረች። እርሱ ሲያነብ (ሲያስተምር) ሰው ሁሉ በተመስጦ ይሰማው ነበር። ሊገድሉት የመጡ ወታደሮች እንኳ በተደሞ መግደላቸውን ይረሱት ነበር።

አንዳንድ ቀን ደግሞ ወፎችና ርግቦች ያደምጡት፣ ያወሩትም ነበር። ይህቺ ቀን ለቅዱስ ፊልሞና ዕለተ ዕረፍቱ ናት።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሱ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ጢሞቴዎስ_ሰማዕት

በዚህችም ቀን በንሑር ከሚባል አገር ቅዱስ ጢሞቴዎስ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ቅዱስ ከታናሽነቱ ጀምሮ #እግዚአብሔርን የሚፈራ ሁልጊዜ በጾም በጸሎት ተጠምዶ የሚኖር ነው ስሟ ሞራ የሚባል ሚስት አለችው እርሷም የአጎቱ ልጅ ናት በሥራዋ ሁሉ ደስ የምታሰኘው መልካም ሴት ናት።

እንደዚህም በፍቅርና በስምምነት ሲኖር ከከሀዲ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ዘንድ የጣዖታት ቤቶች ይከፈቱ ዘንድ አብያተ ክርስቲያናት እንዲዘጉ ትእዛዝ ወጣ። ቅዱስ ጢሞቴዎስም ይህን ሰምቶ እጅግ ደስ አለው። እርሱ ስለ #ክርስቶስ ፍቅር ደሙን ያፈስ ዘንድ ይህን ዘመን ይጠብቀው ነበርና ለሚስቱም ሊሠራው ያሰበውን ነገራት እርሷም የ #እግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን አለች።

ከዚህም በኋላ መንገዱን ያቀናለት ዘንድ ወደ #እግዚአብሔር ጸለየ #ጌታችንም በዚያች ሌሊት በሕልሙ ተገልጾለት ወዳጄ ጢሞቴዎስ ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን እነሆ ከጻድቃኖቼ ቁጥር ውስጥ ቆጥሬሃለሁ አሁንም ተነሣ ሚስትህንም ይዘህ ወደ ብህንሳ ከተማ ሒዳችሁ ጣዖታትን በሚያመልኩ ሁሉ ሕዝብ ፊት በስሜ ታመኑ አለው። በነቃ ጊዜም ለሚስቱ ነገራት እርሷም ይህንኑ የሚመስል ሕልሟን ነገረችው።

ከዚህም በኋላ ተነሥተው በአንድነት ሔዱ ወደ መኰንኑ ወደ ቊልቊልያኖስም ደረሱ መሰንቆና እንዚራ እያስመታ ለጣዖታቱ በዓልን ሲያከብር አገኙት ያንጊዜ ወታደሮቹ ይዘው በመኰንኑ ፊት አቆሙት ሚስቱም ተከተለችው መኰንኑም ለጣዖት መስገድን እያግባባ በርኅራኄ ቃል ተናገረው ቅዱሱ ግን እርሱንና የረከሰች ሃይማኖቱን ሰደበ ስለዚህም መኰንኑ ተቆጥቶ ከሚስቱ ጋር ወደ ወህኒ ቤት እንዲአስገቡት አዘዘ።

ከጥቂት ቀኖች በኋላም ከሚስቱ ጋር አውጥተው ደማቸው እንደ ውኃ እስቲፈስ በአለንጋዎች እንዲገረፉአቸው አዘዘ ያለ ርኅራኄም ገረፏቸው ሚስቱም በዚህ ሥቃይ ምስክርነቷን ፈጸመች።
2024/12/29 07:58:57
Back to Top
HTML Embed Code: