Telegram Web Link
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ኅዳር_16_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ቆሮ 9
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁵ እንግዲህ እንደ በረከት ሆኖ ከስስት የማይሆን ይህ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ አስቀድመው ወደ እናንተ መጥተው፥ አስቀድማችሁ ተስፋ የሰጣችሁትን በረከት አስቀድመው እንዲፈጽሙ ወንድሞችን እለምን ዘንድ እንዲያስፈልገኝ አሰብሁ።
⁶ ይህንም እላለሁ፦ በጥቂት የሚዘራ በጥቂት ደግሞ ያጭዳል፥ በበረከትም የሚዘራ በበረከት ደግሞ ያጭዳል።
⁷ እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፥ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም።
⁸-⁹ በተነ፥ ለምስኪኖች ሰጠ፥ ጽድቁ ለዘላለም ይኖራል ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ እግዚአብሔር፥ ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ፥ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል።
¹⁰ ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል ያበረክትላችሁማል፥ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል፤
¹¹ በእኛ በኩል ለእግዚአብሔር የምስጋና ምክንያት የሚሆነውን ልግስና ሁሉ እንድታሳዩ በሁሉ ነገር ባለ ጠጎች ትሆናላችሁ።
¹² የዚህ ረድኤት አገልግሎት ለቅዱሳን የሚጎድላቸውን በሙሉ የሚሰጥ ብቻ አይደለምና፥ ነገር ግን ደግሞ በብዙ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይበዛል፤
¹³ በዚህ አገልግሎት ስለ ተፈተናችሁ፥ በክርስቶስ ወንጌል በማመናችሁ ስለሚሆን መታዘዝ እነርሱንና ሁሉንም ስለምትረዱበት ልግስና እግዚአብሔርን ያከብራሉ፥
¹⁴ ራሳቸውም ስለ እናንተ ሲያማልዱ፥ በእናንተ ላይ ከሚሆነው ከሚበልጠው ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሣ ይናፍቁአችኋል።
¹⁵ ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
² በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤
³ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ፤
⁴ የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ።
⁵ እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።
⁶ እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤
⁷ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።
⁸ በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤
⁹ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት።
¹⁰ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል ያጸናችሁማል ያበረታችሁማል።
¹¹ ለእርሱ ክብርና ኃይል እስከዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 14
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²³ በየቤተ ክርስቲያኑም ሽማግሌዎችን ከሾሙላቸው በኋላ ጦመውም ከጸለዩ በኋላ፥ ላመኑበት ለጌታ አደራ ሰጡአቸው።
²⁴ በጲስድያም አልፈው ወደ ጵንፍልያ መጡ፥
²⁵ በጴርጌንም ቃሉን ከተናገሩ በኋላ ወደ አጣልያ ወረዱ፥
²⁶ ከዚያም ስለ ፈጸሙት ሥራ ለእግዚአብሔር ጸጋ አደራ ወደ ተሰጡበት ወደ አንጾኪያ በመርከብ ሄዱ።
²⁷ በደረሱም ጊዜ ቤተ ክርስቲያኑን ሰብስበው እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ያደረገውን ሁሉ ለአሕዛብም የሃይማኖትን ደጅ እንደ ከፈተላቸው ተናገሩ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ኅዳር_16_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"እግዚኦ በኃይልከ ይትፌሣሕ  ንጉሥ። ወብዙኀ ይትኀሠይ በአድኅኖትከ። ፍትወተ ነፍሱ ወሀብኮ"። መዝ 20፥1-2።
"አቤቱ፥ በኃይልህ ንጉሥ ደስ ይለዋል፤ በማዳንህ እጅግ ሐሤትን ያደርጋል። የልቡን ፈቃድ ሰጠኽው፥ የከንፈሩንም ልመና አልከለከልኸውም"። መዝ 20፥1-2።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ኅዳር_16_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ሉቃስ 14
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁷ የታደሙትንም የከበሬታ ስፍራ እንደ መረጡ ተመልክቶ ምሳሌ ነገራቸው እንዲህ ሲል፦
⁸ ማንም ለሰርግ ቢጠራህ በከበሬታ ስፍራ አትቀመጥ፤ ምናልባት ከአንተ ይልቅ የከበረ ተጠርቶ ይሆናልና አንተን እርሱንም የጠራ መጥቶ፦
⁹ ለዚህ ስፍራ ተውለት ይልሃል፥ በዚያን ጊዜም እያፈርህ በዝቅተኛው ስፍራ ልትሆን ትጀምራለህ።
¹⁰ ነገር ግን በተጠራህ ጊዜ፥ የጠራህ መጥቶ፦ ወዳጄ ሆይ፥ ወደ ላይ ውጣ እንዲልህ፥ ሄደህ በዝቅተኛው ስፍራ ተቀመጥ፤ ያን ጊዜም ከአንተ ጋር በተቀመጡት ሁሉ ፊት ክብር ይሆንልሃል።
¹¹ ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፥ ራሱንም የሚያዋርድ ከፍ ይላል።
¹² የጠራውንም ደግሞ እንዲህ አለው፦ ምሳ ወይም እራት ባደረግህ ጊዜ፥ እነርሱ ደግሞ በተራቸው ምናልባት እንዳይጠሩህ ብድራትም እንዳይመልሱልህ፥ ወዳጆችህንና ወንድሞችህን ዘመዶችህንም ባለ ጠጎች ጎረቤቶችህንም አትጥራ።
¹³ ነገር ግን ግብዣ ባደረግህ ጊዜ ድሆችንና ጕንድሾችን አንካሶችንም ዕውሮችንም ጥራ፤
¹⁴ የሚመልሱት ብድራት የላቸውምና ብፁዕ ትሆናለህ፤ በጻድቃን ትንሣኤ ይመለስልሃልና።
¹⁵ ከተቀመጡትም አንዱ ይህን ሰምቶ፦ በእግዚአብሔር መንግሥት እንጀራ የሚበላ ብፁዕ ነው አለው።
¹⁶ እርሱ ግን እንዲህ አለው፦ አንድ ሰው ታላቅ እራት አድርጎ ብዙዎችን ጠራ፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ _ቄርሎስ_ቅዳሴ ነው። መልካም የነቢያት (የገና) የጾም ጊዜና በዓል ለሁላችን ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ለዝክረ_ስምኪ

#እመቤቴ_ኪዳነ_ምህረት_ሆይ በብርሃናዊው ኮከብ ለተመሰለው ስም አጠራርሽ ሰላምታ ይገባል፤ በጨለማ ለሚኖሩ ሕዝቦች ብርሃኑን አብርቶላቸዋልና።

#የቃል_ኪዳኗ_እመቤቴ_ሆይ የአምላክ ቃል ኪዳኑ መዛግብት በዕለተ ዓርብ የተገኘውን የደኅነታችን ተስፋ ያስገኘሽ ዕውነተኛ መዝገብ ነሽ እኮን። አባታችን ቀዳማዊ አዳም በጭንቅና በሀዘን ከገነት ወጥቶ በተሰደደ ጊዜ ከልቡናው ኅዘን ተረጋግቶብሻልና።

#መልክአ_ቅድስት_ኪዳነ_ምህረት
#ኅዳር_17

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ኅዳር ዐሥራ ሰባት በዚህችም ዕለት የከበረ አባት #ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ የሥጋው ፍልሰት ሆነ፣ #የቅድስት_ወለተ_ጴጥሮስ እረፍቷ ነው፣ #የአቡነ_ሲኖዳ_ዘደብረ_ጽሙና የእረፍታቸው መታሰቢያ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ

ኅዳር ዐሥራ ሰባት በዚህችም ዕለት የዓለሙ ሁሉ መምህር የሆነ የከበረ አባት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የሥጋው ፍልሰት ሆነ።

ይህም አባት ከእስክንድርያ አገር ሰዎች ወገን ነው የአባቱም ስም አስፋኒዶስ የእናቱም ስም አትናሲያ ነው እሊህም እጅግ ባለጸጎች ነበሩ ይህንንም ልጃቸውን በመልካም አስተዳደግ አሳደጉት ትምህርትንና ጥበብንም ሁሉ አስተማሩት እርሱ ወደ አቴና ሒዶ በመምህራን ቤት ተቀምጦ ትምህርትን ሁሉ ተምሮ በዕውቀቱ ከብዙዎች በላይ ከፍ ከፍ ብሏልና። ከዚህም በኋላ ገና በታናሽነቱ መነኰሰ የዚህንም የኃላፊውን ዓለም ጣዕም ንቆ ተወ ከእርሱም ቀድሞ በዚሁ ገዳም ቅዱስ ባስልዮስ መንኵሶ ነበር በአንድነትም ተስማምተው ብዙ ትሩፋትን ሠሩ ወላጆቹም በሞቱ ጊዜ ከተውለት ገንዘብ ምንም ምን አልወሰደም ለድኆችና ለምስኪኖች ሰጠ እንጂ ከዚያም በምንኵስና ሥራ በመጠመድ ፍጹም ገድልን እየተጋደለ ኖረ።

በዚያም ገዳም ሶርያዊ ጻድቅ ሰው ስሙ ሲሲኮስ የሚባል መነኰስ ነበረ እርሱም ወደፊት የሚሆነውን በ #መንፈስ_ቅዱስ ያይ ነበር በአንዲት ሌሊትም ለጸሎት እየተጋ ሳለ ቅዱሳን ሐዋርያትን ጴጥሮስንና ዮሐንስን አያቸው ወደ ዮሐንስ አፈወርቅ ገብተው ጴጥሮስ መክፈቻ ሰጠው ወንጌላዊ ዮሐንስም ወንጌልን ሰጠው እንዲህም አሉት በምድር ያሠርከው በሰማይ የታሠረ ይሆናል በምድርም የፈታኸው ደግሞ በሰማያት የተፈታ ይሆናልና በውስጥህ #መንፈስ_ቅዱስ ያደረብህ አዲስ ዳንኤል ሆይ የክብር ባለቤት ከሆነ ከታለቅ መምህር #ኢየሱስ_ክርስቶስ ዘንድ ወደ አንተ ተልከናልና ዕወቅ እኔም የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻ የተሰጠኝ ጴጥሮስ ነኝ ።

ሁለተኛውም እኔም በመጀመሪያው ስብከቴ በከበረ ወንጌል ቃል አስቀድሞ ነበረ ያልኩ ይህም ቃል በጠላት ላይ የእሳት ሰይፍ የሆነ ዮሐንስ ነኝ ። ለአንተም ከክብር ባለቤት #ጌታ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ዘንድ ወገኖችህ ምእመናንን በቀናች ሃይማኖት ታሳድጋቸው ዘንድ ዕውነተኛ አእምሮ ደግሞ ተሰጥቶሃል ።

ጻድቅ ሲሲኮስም ይህን ራእይ በአየ ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ ቸር ታማኝ እረኛ ሁኖ እንደሚሾም ዐወቀ። ከዚህም በኋላ በቅዱስ ዮሐንስ ላይ የ #መንፈስ_ቅዱስ ጸጋ በላዩ ወርዶ አደረበትና ብዙ ድርሳናትንና ተግሣጻትን ደረሰ ዲያቆን ሁኖ ሳለም የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍት ብሉያትንና ሐዲሳትን ተረጐመ ። በአንዲት ሌሊትም ቅዱስ ዮሐንስ ሲጸልይ የ #እግዚአብሔር መልአክ በድንገት እንደ በረድ ነጭ በሆነ ልብስ ተገለጠለት ቅዱስ ዮሐንስም ሲያየው ደንግጦ በምድር ላይ ወደቀ መልአኩም አርአያውን ለውጦ እንደ ሰው ሁኖ ታየው ወዳጄ አዲስ ዳንኤል ሆይ አትፍራ ተነሣ አለው የቅዱስ ዮሐንስም ልቡ ተጽናንቶ ጌታዬ አንተ ማነህ ግርማህ አስፈርቶኛልና አለው የ #እግዚአብሔር መልአክም ትሠራው ዘንድ የሚገባህን ልነግርህ ወዳንተ የተላክሁ ነኝ።

አሁንም #እግዚአብሔር አምላክ ያዘዘህን ለመሥራት ልብህን አበርታ ቃልህ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ በአራቱ ማእዘን ይደርሳልና እልፍ አእላፋትም ትምህርትህን ተቀብለው ትእዛዝህን ሰምተው ወደ ፈጣሪያቸው #እግዚአብሔር ተመልሰው ይድናሉና በ #እግዚአብሔር መንግሥትም ውስጥ የጸና የብርሃን ዐምድ ትሆናለህና። እነሆ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ወደ አንተ ይመጣል ከእርሱም ጋራ ሁሉም ካህናትና ዲያቆናት በየማዕረጋቸው የሚያዝህንም አድርግ የ #እግዚአብሐር ትእዛዝ ነውና ልትተላለፍ አይገባህም አለው። ከዚህም በኋላ ያ መልአክ ለአባ ፊላትያኖስ ተገልጦ ቅዱስ ዮሐንስን ቅስና እንዲሾመው አዘዘው በማግሥቱም ሊቀ ጳጳሳቱ መጣ ከርሱ ጋራም ካህናት አሉ ይህን ቅዱስ ዮሐንስንም ይዞ ቅስና ሾመው።

የቍስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳትም በአረፈ ጊዜ ንጉሥ አርቃድዮስ ልኮ አስመጥቶ ቅዱስ ዮሐንስን በቍስጥንጥንያ ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾመው አባቶቻችን ሐዋርያት እንደሚአደርጉት በሊቀ ጵጵስናው ሥራ ላይ ጸና ሕይወትነት በአላቸው ትምህርቶችና ተግሣጾች ሕዝቡን ሁልጊዜ የሚአስተምር ሆነ።

ከኤጲስቆጶሳትም ሆነ ከመንግሥት ወገን ሕግን የሚተላለፉትን ሁሉ ይገሥጻቸዋል ማንንም አይፈራም ፊት አይቶም አያደላም። የንጉሥ አርቃድዮስ ሚስት አውዶክስያም ገንዘብ ወዳጅ ስለሆነች የአንዲት ድኃ መበለት ቦታዋን በግፍ ወሰደች ያቺ መበለትም ወደ ቅዱስ ዮሐንስ መጥታ ንግሥት አውዶክስያ ቦታዋን እንደነጠቀቻት ነገረችው እርሱም የደኃዋን ቦታዋን መልሺላት ብሎ ከብዙ ምክር ጋር እንድትመልስላት ንግሥት አውዶክስያን ለመናት እርሷ ግን እምቢ በማለት አልታዘዘችለትም ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብታ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን እንዳትቀበል አውግዞ ለያት።

ቍጣንና ብስጭትንም ተመልታ ስለ ክፉ ሥራቸው ከሹመታቸው እርሱ የሻራቸውን ኤጲስቆጶሳት ሰበሰበች እነርሱም ንግሥቲቱን ስለ ተቃወመ ስደት እንደሚገባው በእርሱ ላይ ተስማምተው ጻፉ እርሷም አጥራክያ ወደ ሚባል ደሴት ሰደደችው ። ከዚያም በደረሰ ጊዜ የዚያች ደሴት ሰዎች በክፉ ሥራ ጸንተው የሚኖሩ ከሀድያን ሁነው አገኛቸው ቅዱስ ዮሐንስም አስተማራቸው ገሠጻቸውም በፊታቸው ስለ አደረጋቸው ድንቆች ተአምራት ወደ ቀናች ሃይማኖት አስገባቸው።

የሮሜ ንጉሥ አኖሬዎስና ሊቀ ጳጳሳቱ ዮናክኒዶስ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ስደት በሰሙ ጊዜ እጅግ አዘኑ በንጉሥ አርቃድዮስ ላይም በመቆጣት እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጽፈው ላኩ ከዚህ ከክፉ ሥራ ተጠበቅ ትእዛዛችንንም ተቀብለህ የከበረ ዮሐንስን ከስደቱ ከአልመለስከው በአንተና በእኛ መካከል ሰላም አይኖርም። መልእክታቸውንም በአነበበ ጊዜ እጅግ አዘነ ሚስቱንም አግዶ ልኮ ቅዱስ ዮሐንስን ከስደቱ መለሰው በተመለሰ ጊዜም የቍስጥንጥንያ ሰዎች በመመለሱ ታላቅ ደስታ አደረጉ። ከጥቂት ቀኖች በኋላም ንግሥቲቱ ወደ ክፋቷ ተመልሳ ሁለተኛ ወደ አጥራክያ ደሴት ሰደደችውና በዚያው አረፈ።

ንጉሥ አኖሬዎስና ሊቀ ጳጳሳት ዮናክኒዶስም በሰሙ ጊዜ መልእክትን ላኩ ሊቀ ጳጳሳቱም የከበረ ዮሐንስን ከስደቱ እስከምትመልሰው ድረስ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን እንዳትቀበል አውዶክስያን አወገዛት። ከዚህም በኋላ የከበረ ዮሐንስን ይመልሱት ዘንድ ንጉሥ ላከ ግን ሙቶ አገኙት ሥጋውንም ተሸክመው ወደ ቊስጥንጥንያ ከተማ አደረሱት። የከበረ ዮሐንስም በተሰደደበት አገር እንደ አረፈና ሥጋውንም ወደ ቍስጥንጥንያ ከተማ እንደአመጡ ወደ አባ ዮናክኒዶስ መልእክት ጽፈው አስረዱት። ሁለተኛም የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብታ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን እንዳትቀበል ልኮ አውድክስያን አወገዛት እየለመነችውም ስምንት ወር ያህል ኖረች በብዙ ልመናም ፈታት።

ነገር ግን ጭንቅ በሆነ ደዌ #እግዚአብሔር አሠቃያት ያድኗት ዘንድ ገንዘቧን ለባለ መድኃኒቶች ጥበበኞች እስከ ሰጠች ድረስ ግን አልዳነችም ወደ ቅዱስ ዮሐንስ መቃብርም ሔዳ በእርሱ ላይ ያደረገችውን በደል ይቅር ይላት ዘንድ እየሰገደችና እያለቀሰች ለመነችው እርሱም ይቅር አላት ከደዌዋም ፈወሳት። #ጌታችንም ከሥጋው ታላላቅ ድንቆች ታአምራትን ገለጠ።
ስለርሱም እንዲህ ተባለ በአንዲት ዕለትም ከንጉሥ አርቃዴዎስ ጋር ተቀምጦ ሳለ ንጉሡ እንዲህ አለው አባቴ ሆይ ስለ አንድ ቃል እንድታስረዳኝ እለምንሃለሁ። ይህም ቃል ከብዙ ጊዜ ጀምሮ በልቤ ውስጥ ይመላለሳል ወንጌላዊ ቅዱስ ማቴዎስ ቅድስት ድንግል እመቤታችን #ማርያምን የበኵር ልጅዋን እስከ ወለደች ድረስ ዮሴፍ አላወቃትም ስለምን አለ ወንዶች ሴቶችን እንደሚአውቋቸው ዮሴፍ አወቃትን አለው።

የከበረ ዮሐንስም ንጉሥ ሆይ እንዲህ አትበል እንዲህ አንተ እንደምትለው አይደለም የከበረች ድንግል #እመቤታችንስ የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በሆድዋ ውስጥ በነበረ ጊዜ የእርሱ ኅብረ መልክ በሚለዋወጥ ጊዜ ከእርሱ ጋር መልኳ ይለወዋወጥ ነበር። በንጹሕ ብርሌ ውስጥ ውኃ በጨመሩ ጊዜ ውኃ መስሎ እንደሚታይ ወይን ጠጅም ቢጨምሩ ያንኑ መስሎ እንደሚታይ ወይም ከውስጡ በተጨመረው ቀይም ቢሆን ቀልቶ እንደሚታይ ቅጠልያም ቢገባበት ቅጠልያ መስሎ እንደሚታይ ። #ድንግልም በሆድዋ ውስጥ የልጅዋ መልክ በሚለዋወጥ ጊዜ ከእርሱ ጋራ መልኳ ይለዋወጥ ነበር። እንደ ሮማን አበባ የምትቀላበት ጊዜ አለ እንደናርዶስም የምታብለጨልጭበት ጊዜ አለ የለመለመ ቅጠል የምትመስልበትም ጊዜ አለ ከወለደች በኋላ ግን አልተለወጠችምና ዮሴፍ በአንድ በቀድሞው ኅብረ መልኳ ተወስናለት መልኳን ተረዳ ማለት ነው አለው። በዚያን ጊዜ በንጉሥ አዳራሽ ውስጥ ከወርቅ የተሠራ የእመቤታችን አምላክን የወለደች የድንግል #ማርያም ሥዕል ነበረችና አፈ ወርቅ ዮሐንስ ልሳነ ወርቅ ዮሐንስ አፈ በረከት ዮሐንስ መልካም ተናገርክ የሚል ቃል ከእርሷ ወጣ ።

ንጉሡና ከእርሱ ጋር ያሉት በሰሙ ጊዜ እጅግ አደነቁ #እግዚአብሔርንም አመሰገኑት በዚያን ጊዜ ንጉሥ አዝዞ ወርቅ ሠሪ አስመጥቶ ለከበረ ዮሐንስ የወርቅ ልሳን አሠርቶ ለሚያየው ሁሉ መታሰቢያ ምልክት ሊሆን አምላክን ከወለደች ከእመቤታችን ከድንግል #ማርያም ሥዕል ዘንድ ሰቀለው። ቅዱስ ዮሐንስንም ከዚያች ቀን ወዲህ ልሳነ ወርቅ ብሎ ጠራው አፈ ወርቅም ተብሎ እስከዛሬ ተጠራ።

የአርቃዴዎስም ልጅ ታናሹ ቴዎዶስዮስ በነገሠ ጊዜ መልክተኞችን ልኮ የቅዱስ ዮሐንስን ሥጋ ብዙ በመዘመርና በማመስገን በታላቅ ክብር ወደ ቊስጥንጥንያ አፍልሶ አስመጣው ይህም ከዕረፍቱ በኋላ በሠላሳ አምስት ዓመት ነው። በሌላ በቅብጢ መጽሐፍ በግንቦት ወር ሃያ ሁለት ቀን እንደ ደረሰ ይናገራል በሮማውያን መጽሐፍ ግን በየካቲት ወር ሃያ ሁለት ቀን ተባለ የዕንቊ ፈርጾች ባሉት የዕብነ በረድ ሣጥን ውስጥ አድርገው ወደ ቤተ መቅደስ አስገቡት ከሥጋውም ታላላቅ የሆኑ ድንቆች ተአምራት ተገለጡ ።

ሁለተኛም የእስክንድርያ ግጻዌና የሀገረ ቅፍጥ ኤጲስቆጶስ አባ ዮሐንስ የጻፈው ግጻዌ የመለካውያንም ግጻዌ በዚች በኅዳር ዐሥራ ሰባት ቀን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳረፈባት ተባበሩ። ሁለተኛም ደግሞ የመለካውያን ግጻዌ ዮሐንስ አፈወርቅ ዐይሉል በሚባል ወር በዐሥራ አራት እንዳረፈ ይናገራል ይህም በ #መድኃኒታችን#መስቀሉ በዓል መስከረም ዐሥራ ሰባት ቀን ነው ። ስለዚህም ራሱን ለማስቻል ወደ ኅዳር ዐሥራ ሰባት ቀን ለወጡት። የቀደሙ መጻሕፍት ግን ዕረፍቱ ግንቦት ዐሥራ ሁለት ቀን እንደሆነ ያወሳሉ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ በከበረ አባት ጸሎት ይማረን ለዘለዓለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ወለተ_ጴጥሮስ

በዚህችም ዕለት ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ አረፈች። አባቷ ባሕር አሰግድ እናቷ ደግሞ ክርስቶስ አዕበያ ይባላሉ። ትውልዷ ከዳሮ /ምስራቅ ኢትዮጵያ/ ወገን ነው። ወንድሞቿ ዮሐንስና ዘድንግል በንጉሥ ሱስንዮስ ጊዜ ታላላቅ ባለስልጣናት ነበሩ። እናት አባቷ በህግ በስርዓት ካሳደጓት በኋላ ሥዕለ ክርስቶስ የሚባል የስስኑዮስ የጦር አበጋዝ ቢትወደድ አግብታ 3 ልጆች መውለድዋን ገድሏ ይናገራል። ይህ ቢትወደድ ይኖርበት የነበረው ግንብ ቤት ፍራሽ እስከ አሁን ድረስ በጋይንት ስማዳ ይታያል።

ወለተ ጴጥሮስ ከቢትወደድ ሥዕለ ክርስቶስ ጋር በሰላም በመኖር ላይ እያለች ንጉሡ አጼ ሱስንዮስ የተዋሕዶ ሃይማኖቱን ቀይሮ በሮማውያን ሀሰተኛ መምህራን በመታለል ካቶሊክነትን ተቀብሎ የኢትዮጵያ ህዝብም ካቶሊክ እንዲሆን ዐወጀ። በዚህ ዐዋጅ የተነሣ በንጉሡ ደጋፊዎችና የቀደመ ሃይማኖታችንን አንለቅም ባሉት እውነተኛ የተዋህዶ ምዕመናን መካከል ታላቅ ጠብ ሆነ።

የንጉሡ ሠራዊትም በተዋሕዶ ምእመናን ላይ ዘመቱ። ቢትወደድ ሥዕለ ክርስቶስ ከዘመቻ ሲመለስ የጳጳሱን የአቡነ ስምዖንን ልብስ እንደግዳይ ሰለባ ለንጉሡ ይዞለት መጣ። ይህንን የሃይማኖቷን መናቅ የአባቶቿን መደፈር የተመለከተችው ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ እንደዚህ ካለው ከሀዲ ጋር በአንድ ቤት አብሮ መኖር አያስፈልግም ብላ ቆረጠች። ከዚህም በኋላ ከቤቱ የምትወጣበትን ዘዴ ያለ እረፍት ማሰላሰል ጀመረች። ከዚያም ወደገዳሙ ለመድረስ እንዲረዷት ከጣና መነኮሳት ጋር መላላክ ጀመረች። የጣና ቂርቆስ ገዳም አበምኔት አባ ፈትለ ሥላሴም ወለተ ጴጥሮስን ይዘዋት እንዲመጡ ሁለት መነኮሳትን ላኩ። በዚያ ጊዜ ልጆቿ ሁሉ ሞተውባት ነበር። ወለተ ጴጥሮስ ከመነኮሳቱ ጋር መጥፋቷን ያወቀው ቢትወደድ ሥዕለ ክርስቶስ ይዘው ያመጡለት ዘንድ አያሌ ሠራዊት ከኋላዋ ሰደደ። ነገር ግን ወለተ ጴጥሮስና ሁለቱ መነኮሳት በ #እግዚአብሄር ረዳትነት በዱር ውስጥ ተሰዉረዉባቸዉ ሊያገኟቸው አልቻሉም። ይህ ተሰዉረዉበት የነበረዉ ቦታ እስከዛሬ ድረስ "ሳጋ ወለተ ጴጥሮስ" ይባላል። በኋላ ዘመንም በስሟ ቤተ ክርስቲያን ተሰርቶበታል።

ከዚህ በኋላ ወደ ደብረ ዕንቁ ገዳም ገብታ ስርዓተ ምንኩስናን ተምራ መነኮሰች። ታላቁ ገድሏ የተጀመረውም ከዚህ በኋላ ነው። ወለተ ጴጥሮስ ከምንኩስናዋ በኋላ በመላ ሀገሪቱ እየተዘዋወረች ሕዝቡ በተዋሕዶ እምነት እንዲፀና፣ በጸሎተ ቅዳሴም ጊዜ ሃይማኖቱን የለወጠው የንጉሡ የሱስንዮስ ስም እንዳይጠራ ትመክር ጀመር። ብዙ ሰዎችም በምክሯ ተስበው በሃይማኖታቸው እየጸኑ ሰማዕትነትን መቀበል ያዙ።

ይህንን የወለተ ጴጥሮስን ተጋድሎ የሰማው ንጉሥ ሱስንዮስ ተይዛ ለፍርድ ትቀርብ ዘንድ ብዙ ወታደሮች በየአካባቢው አሰማራ። በመጨረሻም በሰራዊቱ ተይዛ በሱስንዮስ ፊት ቀረበች። መሳፍንቱ መኳንንቱና ለእንጀራቸው ሲሉ ሃይማኖታቸውን የለወጡ ሊቃውንት በተሰበሰቡበት ትመረመር ጀመር።

ከሳሽዋ " ንጉሡን ካድሽ፣ #እግዚአብሔርን ካድሽ፣ ትዕዛዙን እምቢ አልሽ፣ ሃይማኖቱን ዘለፍሽ፣ ሌሎች ሰዎችም ሃይማኖቱን እንዳይቀበሉ ልባቸውን አሻከርሽ" ሲል ከሰሳት። ወለተ ጴጥሮስ ግን እንደ አምላኳ እንደ #ኢየሱስ_ክርስቶስ በከሳሾቿ ፊት ዝም አለች። ንጉሡም ርቃ እንዳትሄድ ነገር ግን ከቅርብ ዘመዶቿ ጋር እንድትኖር /የቁም እስር/ ፈረደባት።

ሃይማኖት ተንቃ፣ ቤተ ክርስቲያን ተዋርዳ የመናፍቃን መጨዋቻ ስትሆን ማየት የሃይማኖት ፍቅርዋ ያላስቻላት ወለተ ጴጥሮስ በግዞት መልክ ከተቀመጠችበት ቦታ ጠፍታ ዘጌ ገዳም ገባች። አብርዋትም ወለተ ጳውሎስና እህተ ክርስቶስ የተባሉ እናቶች ነበሩ። በዚያም በገዳሙ የነበሩ መነኮሳት እና የአካባቢው ምእመናን በተዋሕዶ ሃይማኖታቸው እንዲጸኑ እየመከረች ጥቂት እንደቆየች የሚያሳጧትና የሚከሷት ስለበዙ ቦታውን ለቃ ወደ ዋልድባ ገዳም ገባች። ዋልድባ ገብታ ሱባዔዋን ከፈጸመች በኋላ በገዳሙ የነበሩትን አባቶችና እናቶች በእምነታቸው ጸንተው እንዲቆዩ ትመክራቸው ጀመር።
አጼ ሱስንዮስ የወለተ ጴጥሮስን ተጋድሎ፣ መነኮሳትንና ምእመናንን በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ፣ የካዱትም ከክህደታቸው እንዲመለሱ ማድረጓን ሲረዳ ብዙ ወታደሮችን ይልክባት ነበር። በዋልድባ እያለችም የንጉሡ ሰራዊት ሊያስኖሯት ስላልቻሉ ወደ ጸለምት አመራች። በጸለምት የወለተ ጴጥሮስ ትምህርት እንደ ሰደድ እሳት ተስፋፋ። ምእመናን እየውደዷትና እየተቀበሏት እራሳቸውን ለሰማዕትነት አዘጋጁ። ይህንን የሰማው ሱስንዮስ ይቺ ሴት እኔ ብተዋት እርሷ አልተወችኝም፣ አለና የጸለምቱን ገዥ ባላምባራስ ፊላታዎስን ወለተ ጴጥሮስን ይዞ እንዲያመጣለት አዘዘው።

ወለተ ጴጥሮስ በጸለምቱ ገዥ ተይዛ ወደ ሱስንዮስ መጣች። አስቀድመው ሃይማኖቷን እንድትለውጥ ሊያግባቧት ሞከሩ። እርሷ ግን ጸናች። ሦስት የካቶሊክ ቀሳውስት መጥተው ስለሃይማኖትዋ ተከራከሯት። ወለተ ጴጥሮስ ግን የሚገባቸውን መልስ ሰጥታ አሳፈረቻቸው። በየቀኑ የካቶሊክ ቀሳውስት ሃይማኖቷን ትታ ካቶሊክ እንድትሆን በምክርም በትምህርትም ለማታለል ሞከሩ። ይሁን እንጂ ወለተ ጴጥሮስ በተዋሕዶ ዓለት ላይ ተመስርታ ነበርና ፍንክች አላለችም።

በመጨረሻ አንዱ የካቶሊክ ቄስ "እርሷን እቀይራለሁ ማለት በድንጋይ ላይ ውኃ ማፍሰስ ነው" ሲል ለንጉሡ አመለከተ። ሱስንዮስ ይህንን ሲሰማ ሊገላት ቆረጠ። አማካሪዎቹ ግን "አሁን እርስዋን ብትገል ህዝቡ ሁሉ በሞቷ ይተባበራል፣ ስለ ሃይማኖቱ እንደ እርሱዋ መስዋዕት ይሆናል። ደግሞ ሰው ሁሉ ካለቀ በማን ላይ ትነግሣለህ? ይልቅስ ታስራ ትቀመጥ።" ብለው መከሩት። ንጉሡም ገርበል ወደተባለው በርሃ ሊልካት ወሰነ።

መልክዐ ክርስቶስ የተባለው ዋነኛ የካቶሊኮች አቀንቃኝ ወደ ሱስንዮስ ፊት ቀርቦ "ንጉሥ ሆይ በፊትህ ሞገስን ካገኘሁ ክረምቱ እስኪያልፍ ድረስ ከእኔ ጋር ትክረም። እኔ እመክራታለሁ። የፈረንጆቹ መምህር አልፎኑስም ሁልጊዜ መጽሐፉን ያሰማታል። ይህ ሁሉ ተደርጎ አሻፈረኝ ካለች ያንጊዜ ግዞት ትልካታለህ" ሲል ለመነው ንጉሡም ተስማማ።

መልክዐ ክርስቶስ ወለተ ጴጥሮስን የካቶሊኮች ጳጳስ ወደሚኖርበት ጎንደር አዘዞ ወሰዳት። ሁለቱ ተከታዮቿ ወለተ ክርስቶስ እና እኅተ ክርስቶስ አብረዋት ሰነበቱ። ወለተ ጳውሎስ ዘጌ ቀርታለች። አልፎኑስ ሜንዴዝም ዘወትር እየሄደ የልዮንን ክህደት ያስተምራት ነበር። ንጉሡም የወለተ ጴጥሮስን ወደ ካቶሊክነት መቀየር በየጊዜው ይጠይቅ ነበር፣ የሚያገኘው መልስ ግን ሁልጊዜ አንድ ነው "በፍጹም"። ክረምቱ አለፈ። ኅዳርም ታጠነ። ወለተ ጴጥሮስም በትምህርትም በማባበልም ከተዋሕዶ ሃይማኖቷ ንቅንቅ አልል አለች። ስለዚህ ወደ ስደት ቦታዋ ገርበል በርሃ በሱስንዮስ ወታደሮች ተጋዘች። ወለተ ጴጥሮስ ብቻዋን ገርበል ወረደች። በእርጅና ላይ ያለችው እናቷ ይህንን ስትሰማ አንዲት አገልጋይ ላከችላት። ቆራጧ ተከታይዋ እኅተ ክርስቶስም ወዲያው ወደ እርሷ መጣች።

ገርበል በርሃ ለሦስት አመት ስትኖር ብዙ ጊዜ ትታመም ነበር። ስለዚህ መከራውን ሁሉ ስለሃይማኖቷ ቻለችው። ከግዞቱ ከተፈታች በኋላ ደንቢያ ውስጥ ጫንቃ በተባለ ቦታ ተቀመጠች። በስደቱ ምክንያት ቆባቸውን አውልቀው የነበሩ አያሌ መነኮሳትም ስደቱ መለስ ሲል በዙሪያዋ ተሰበሰቡ፡ በገዳማቸዉም ፀንተዉ እንዲኖሩ ትመክራቸዉ ነበር። በኋላም ወደ ጣና ቂርቆስ ተጉዛለች። ከዚያም ምጽሊ ወደተባለው ደሴት ሄዳ በዙርያዋ አያሌ መነኮሳትን ሰብስባ ለሃይማኖታቸዉ እንዲጋደሉ መከረቻቸዉ። ነገር ግን መከራ ያልተለያት ወለተ ጴጥሮስ መዝራዕተ ክርስቶስ የተባለው ሰው ካቶሊክ ያልሆኑ ምእመናንን አስገድዶ የሚያስጠምቅበትን ደብዳቤ ይዞ ወደ አካባቢው መምጣቱን ስለሰማች መነኮሳቱን መክራና አስተምራ ወደ እየበረሃው ከሰደደች በኋላ እርሷም እንደገና ስደት ጀመረች። ተመልሳ ወደ ምጽሊ የመጣችው አገር ሲረጋጋ በ፵፱ አመቷ ነው።

ከስደት ስትመለስ መኖርያዋ ያደረገችው መንዞ የተባለውን ቦታ ነው። በዚያ ቦታ ላይ በጸሎትና በስግደት ተጠምዳ ኖረች። በምጽሊ ገዳም አብሯት የነበረው የደብረ ማርያም አበምኔት አባ ጸጋ ክርስቶስም መጽሐፈ ሐዊን ይተረጉምላት ነበር።

አጼ ሱስንዮስ ምላሱ ተጎልጉሎ ከ #እግዚአብሔር ቅጣቱን ሲቀበልና የተዋሕዶ ሃይማኖት ስትመለስ አቡነ ማርቆስ ግብጻዊ ጵጵስና ተሹመው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ከመንገድ ላይ ጠብቃ ቡራኬ ተቀበለች። ስለሃይማኖቷ ብላ ከባሏ መለየትዋ እና መከራ መቀበሏ እስከ ግብጽ ድረስ መሰማቱን ጳጳሱ ነግረዋታል።

ከዚያም በመንዞ ገዳም አቋቁማ በተጋድሎ
ተቀመጠች። ያቋቋመችው ገዳም የወንዶችም የሴቶችም ነበር።

የተዋሕዶ ሃይማኖት በዐዋጅ ከተመለሰችና አጼ ፋሲል ከነገሠ በኋላ ንጉሡን ለማግኘትና ወንድሞቿንና ዘመዶቿን ለማየት ወደ ጎንደር መጣች። ንጉሡም በታላቅ ክብር ተቀበላት። በየቀኑም ሳያያት አይውልም ነበር። ወደ እርስዋ ሲገባም አደግድጎ ነበር። ይህም ስለሃይማኖትዋ ጽናትና ስለቅድስናዋ ክብር ነው።

ወለተ ጴጥሮስ በተጋድሎና በምንኩስና ኖራ በ፶ አመቷ በቆረቆረችው ገዳም ዐረፈች። መታሰቢያዋም ኅዳር ፲፯ ቀን ይከበራል። የተከታይዋ ወለተ ክርስቶስ በዓል ደግሞ ኅዳር ፯ ቀን ይውላል። በሃይማኖት ጸንቶ መጋደል ወንድ ሴት አይልም። ቤተ ክርስቲያናችን እንደነ ወለተ ጴጥሮስ ያሉ አያሌ ልጆች አሏት። የዛሬዎቹ እህቶችና እናቶችም በምግባር ታንፆ በሃይማኖት ጸንቶ በእምነት መጋደልን ከእነዚህ እናቶች ሊቀስሙ ይገባል።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት ወለተ ጴጥሮስ ጸሎት ይማረን በረከቷም ይደርብን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ሲኖዳ_ዘደብረ_ጽሙና

በዚህችም ቀን አቡነ ሲኖዳ ዘደብረ ጽሙና የእረፍታቸው መታሰቢያ ነው፡፡ ሲኖዳ ማለት ‹‹ታማኝ›› ማለት ነው፡፡ ትውልድ ሀገራቸው ጎጃም ሲሆኑ የሸዋ ባላባት ልጅ ናቸው፡፡በጎጃም ደብረ ዲማህ አጠገብ ደብረ ፅሞና በተባለው ቦታ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ያመልኩት የነበረውን ትልቅ ዘንዶ አቡነ ሲኖዳ በ #መስቀል ባርከው ከሁለት ሰንጥቀውታል፡፡ ሰዎቹንም አስተምረው አሳምነው አጥምቀው የ #እመቤታችንን ቤተ ክርስቲያን ሠርተውላቸዋል፡፡ ጻድቁ የሊቀ ሰማዕታት የቅዱስ ጊዮርጊስ ዓይነት ገድል አላቸው፡፡ ለዘንዶ ምግብ እንዲትሆን ግብር ሆና የተሰጠችውን ሴት ልጅ ከጫካ አግኝተው ዘንዶውን በመስቀላቸው አማትበው ገድለው ልጅቷን አድነዋታል፡፡

በዘመናቸው ነግሦ የነበረው ‹‹ሕዝበ ናኝ›› የተባለው ንጉሥ በሰዎች ወሬ ‹‹ንግሥናዬ ለሌላ ይሰጣል ትላለህሳ›› በማለት ጻድቁን እጅና እግራቸውን አስሮ ካሠቃያቸው በኋላ እጃቸውን አስቆረጣቸው፡፡ ነገር ግን ለአቡነ ሲኖዳ እመ ብርሃን የብርሃን እጅ ተከለችላቸው፡፡ በጌቴሴማኒ ያለችው ቅዱስ ሉቃስ የሳላትና ስርጉት የተባለችው የ #እመቤታችን ሥዕል በየጊዜው እየተገለጠች ታነጋግራቸው ነበር፡፡ ንጉሡ በስደትና በግዞት ብዙ እያሠቃያቸው ሳለ መልአክ መጥቶ ዕለተ ዕረፍታቸውን ነግሯቸው እሳቸውም ደቀ መዛሙርቶቻቸውን ጠርተው ከተሰናበቷቸው በኋላ ነው ንጉሡ በኅዳር 17 ቀን አንገታቸውን ያሰየፋቸው፡፡ ከአንገታቸው ውኃ፣ ደምና ወተት ፈሷል፡፡

ጻድቁ በሐይቅ ደሴት የተቀበሩ ቢሆንም ቀድሞ በሚያገለግሉበት በድፍን ምስራቅ ጎጃም ድርቅና ርኃብ ስለሆነ በደብረ ፅሞና ገዳም ይኖሩ የነበሩት አባ መቃርስ ዐፅማቸውን አፍልሰው በማምጣት በደብረ ዲማህ አጠገብ በስማቸው በተሰራው በደብረ ፅሞና ቤተ ክርስቲያን በክብር ሲያሳርፉት ወዲያው ዝናብ ጥሎ ድርቁም ጠፍቷል፡፡ ዐፅማቸውን ተሸክማ ያመጣችው በቅሎም ወልዳለች፡፡
ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ሲኖዳ ለማይወልዱ መካኖች እጅግ ልዩ ቃልኪዳን ነው የተሰጣቸው፡፡ መቃብራቸውን እየዞሩ እምነታቸውን እየተቀቡ ገድላቸውን እየታሹ የማይወልዱ መካኖች የሉም፡፡ ከሩቅም ሆነው በስማቸው ተስለው እምነታቸውን ተቀብተው የሚወልዱ በጣም ብዙዎች ናቸው፡፡

የጻድቁ ሌላኛው በስማቸው የተሰየመውና እጅግ ተአምረኛው ታቦታቸው ዛሬም አቡነ ሲኖዳ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከአ.አ 180 ኪ.ሜ ርቆ ከጣርማ በር አልፎ ሞላሌ ከተማ ውስጥ ይገኛል፡፡ በሰሜን ሸዋ በሚገኘው በዚህ ቤተ ክርስቲያናቸው ውስጥ በዘመናችንም በጣም በርካታ ተአምራት ይደረጋሉ፡፡ ለጻድቁ የተሰጠችውን የስዕለት በግ ጅብ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ገብቶ ሊበላ ሲል ቀንዱን ነክሶ ደርቆ ሞቶ ሲገኝ በጉ ግን ምንም አልሆነም፡፡ አቃቢቷም እንዲሁ ከትልቁ ተራራ ሥር በትልቅ ቅል ውኃ ቀድተው ሲመለሱ ገመዱ ተበጥሶ ቅሉ ከነውኃው ከትልቁ ገደል ገብቶ ድንጋይ ላይ ቢያርፍም ቅሉ ሳይሆን ድንጋዩ ነው የተሰበረው፡፡ የአካባቢው ነዋሪም ‹‹በጉ ጅብ ገደለ፣ ቅሉ ድንጋይ ሰበረ›› እያሉ ጻድቁን ያወድሷቸዋል፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር_17_እና_ግንቦት#ከገድላት_አንደበት#ነገረ_ቅዱሳን_አንስት (መዝገበ ሃይማኖት አፕሊኬሽን))
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ኅዳር_17_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ፊልጵስዩስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህ የደረሰብኝ በእውነት ወንጌልን ለማስፋት እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ።
¹³ ስለዚህም እስራቴ ስለ ክርስቶስ እንዲሆን በንጉሥ ዘበኞች ሁሉና በሌሎች ሁሉ ዘንድ ተገልጦአል፥
¹⁴ በጌታም ካሉት ወንድሞች የሚበዙት ስለ እስራቴ ታምነው የእግዚአብሔርን ቃል እንዲነግሩ ያለ ፍርሃት ከፊት ይልቅ ይደፍራሉ።
¹⁵ አንዳንዶች ከቅንአትና ከክርክር እንኳ ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብኩታል፤
¹⁶ እነዚህ ወንጌልን መመከቻ ለማድረግ እንደ ተሾምሁ አውቀው በፍቅር ይሰብካሉ፥
¹⁷ እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ መከራን ሊያመጡብኝ መስሎአቸው፥ ለወገናቸው የሚጠቅም ፈልገው በቅን አሳብ ሳይሆኑ ስለ ክርስቶስ ያወራሉ።
¹⁸ ምን አለ? ቢሆንም በሁሉ ጎዳና፥ በማመካኘት ቢሆን ወይም በቅንነት ቢሆን፥ ክርስቶስ ይሰበካል ስለዚህም ደስ ብሎኛል።
¹⁹ ወደ ፊትም ደግሞ ደስ ይለኛል፤ ይህ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ መሰጠት ለመዳኔ እንዲሆንልኝ አውቃለሁና፥
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁰ ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው፥ መላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል፤
¹¹ ከክፉ ፈቀቅ ይበል፥ መልካምንም ያድርግ፥ ሰላምን ይሻ ይከተለውም፤
¹² የጌታ ዓይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና፥ ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው ተከፍተዋል፥ የጌታ ፊት ግን ክፉ ነገርን በሚያደርጉ ላይ ነው።
¹³ በጎንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው?
¹⁴ ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብፁዓን ናችሁ። ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ አትናወጡም፥
¹⁵ ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።
¹⁶ በክርስቶስ ያለውን መልካሙን ኑሮአችሁን የሚሳደቡ ሰዎች ክፉን እንደምታደርጉ በሚያሙበት ነገር እንዲያፍሩ በጎ ሕሊና ይኑራችሁ።
¹⁷ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲህ ቢሆን፥ ክፉ ስለ ማድረግ ሳይሆን በጎ ስለ ማድረግ መከራን ብትቀበሉ ይሻላችኋልና።
¹⁸ ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፥
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 16
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁴ ከትያጥሮን ከተማም የመጣች ቀይ ሐር ሻጭ እግዚአብሔርን የምታመልክ ልድያ የሚሉአት አንዲት ሴት ትሰማ ነበረች፤ ጳውሎስም የሚናገረውን ታዳምጥ ዘንድ ጌታ ልብዋን ከፈተላት።
¹⁵ እርስዋም ከቤተ ሰዎችዋ ጋር ከተጠመቀች በኋላ፦ በጌታ የማምን እንድሆን ከፈረዳችሁልኝ፥ ወደ ቤቴ ገብታችሁ ኑሩ ብላ ለመነችን፤ በግድም አለችን።
¹⁶ ወደ ጸሎት ስፍራም ስንሄድ፥ የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት ለጌቶችዋም እየጠነቈለች ብዙ ትርፍ ታመጣ የነበረች አንዲት ገረድ አገኘችን።
¹⁷ እርስዋ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፦ የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባሪያዎች ናቸው ብላ ትጮኽ ነበር።
¹⁸ ይህንም እጅግ ቀን አደረገች። ጳውሎስ ግን ተቸገረና ዘወር ብሎ መንፈሱን፦ ከእርስዋ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ አለው፤ በዚያም ሰዓት ወጣ።
¹⁹ ጌቶችዋም የትርፋቸው ተስፋ እንደ ወጣ ባዩ ጊዜ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው ወደ ገበያ በሹማምት ፊት ጐተቱአቸው፤
²⁰ ወደ ገዢዎችም አቅርበው፦ እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ከተማችንን እጅግ ያናውጣሉ።
²¹ እኛም የሮሜ ሰዎች ሆነን እንቀበላቸውና እናደርጋቸው ዘንድ ያልተፈቀደልንን ልማዶች ይናገራሉ አሉ።
²² ሕዝቡም አብረው ተነሡባቸው፥ ገዢዎቹም ልብሳቸውን ገፈው በበትር ይመቱአቸው ዘንድ አዘዙ፤
²³ በብዙም ከደበደቡአቸው በኋላ ወደ ወኅኒ ጣሉአቸው፥ የወኅኒውንም ጠባቂ ተጠንቅቆ እንዲጠብቃቸው አዘዙት።
²⁴ እርሱም የዚህን ዓይነት ትእዛዝ ተቀብሎ ወደ ውስጠኛው ወኅኒ ጣላቸው፥ እግራቸውንም በግንድ አጣብቆ ጠረቃቸው።
²⁵ በመንፈቀ ሌሊት ግን ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩ እግዚአብሔርን በዜማ ያመሰግኑ ነበር፥ እስረኞቹም ያደምጡአቸው ነበር
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ኅዳር_17_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"እግዚአብሔር ያፈቅሮሙ ለጻድቃን። እግዚአብሔር የዐቅቦሙ ለፈላስያን። ወይትዌከፎሙ ለዕቤራት ወለእጓለ ማውታ"። መዝ.145፥8-9።
"እግዚአብሔር የወደቁትን ያነሣል፤ እግዚአብሔር ዕውሮችን ጥበበኞች ያደርጋቸዋል፤ እግዚአብሔር ጻድቃንን ይወድዳል፤ እግዚአብሔር ስደተኞችን ይጠብቃል፤ ድሀ አደጎችንና ባልቴቶችን ይቀበላል፤ የኃጢአተኞችንም መንገድ ያጠፋል"። መዝ.145፥8-9።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ኅዳር_17_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 10
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁶ እነሆ፥ እኔ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ።
¹⁷ ነገር ግን ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ በምኩራቦቻቸውም ይገርፉአችኋልና ከሰዎች ተጠበቁ፤
¹⁸ ለእነርሱና ለአሕዛብም ምስክር እንዲሆን፥ ስለ እኔ ወደ ገዥዎች ወደ ነገሥታትም ትወሰዳላችሁ።
¹⁹ አሳልፈውም ሲሰጡአችሁ፥ የምትናገሩት በዚያች ሰዓት ይሰጣችኋልና እንዴት ወይስ ምን እንድትናገሩ አትጨነቁ፤
²⁰ በእናንተ የሚናገር የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ፥ የምትናገሩ እናንተ አይደላችሁምና።
²¹ ወንድምም ወንድሙን፥ አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፥ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ ይገድሉአቸውማል።
²² በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።
²³ በአንዲቱ ከተማም መከራ ቢያሳዩአችሁ ወደ ሌላይቱ ሽሹ፤ እውነት እላችኋለሁና፥ የሰው ልጅ እስኪመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተማዎች አትዘልቁም።
²⁴ ደቀ መዝሙር ከመምህሩ፥ ባሪያም ከጌታው አይበልጥም።
²⁵ ደቀ መዝሙር እንደ መምህሩ፥ ባሪያም እንደ ጌታው መሆኑ ይበቃዋል። ባለቤቱን ብዔል ዜቡል ካሉት፥ ቤተሰዎቹንማ እንዴት አብዝተው አይሉአቸው!
²⁶ እንግዲህ አትፍሩአቸው፤ የማይገለጥ የተከደነ፥ የማይታወቅም የተሰወረ ምንም የለምና።
²⁷ በጨለማ የምነግራችሁን በብርሃን ተናገሩ፤ በጆሮም የምትሰሙትን በሰገነት ላይ ስበኩ።
²⁸ ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ።
²⁹ ሁለት ድንቢጦች በአምስት ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ያለ አባታችሁ ፈቃድ በምድር ላይ አትወድቅም።
³⁰ የእናንተስ የራሳችሁ ጠጉር ሁሉ እንኳ ተቈጥሮአል።
³¹ እንግዲህ አትፍሩ ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ።
³² ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤
³³ በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ።
³⁴ በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም።
³⁵ ሰውን ከአባቱ፥ ሴት ልጅንም ከእናትዋ፥ ምራትንም ከአማትዋ እለያይ ዘንድ መጥቻለሁና፤
³⁶ ለሰውም ቤተ ሰዎቹ ጠላቶች ይሆኑበታል።
³⁷ ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤
³⁸ መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም።
³⁹ ነፍሱን የሚያገኝ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም ስለ እኔ የሚያጠፋ ያገኛታል።
⁴⁰ እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።
⁴¹ ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል።
⁴² ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ_ቅዳሴ ነው። መልካም የቅድስት ወለተ ጴጥሮስና የአቡነ ሲኖዳ የዕረፍታቸው በዓልና የነቢያት (የገና) ጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ኅዳር_18

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ኅዳር ዐሥራ ስምንት በዚህች ዕለት #ሐዋርያው_ቅዱስ_ፊልጶስ#ቅዱሳት_ደናግል_አጥራስስ_እና_ዮና#ቅዱስ_ኤላውትሮስና_እናቱ_እንትያ በሰማዕትነት አረፉ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ፊልጶስ_ሐዋርያ

ኅዳር ዐሥራ ስምንት በዚህች ዕለት ከአባቶቻችን ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ቅዱስ ሐዋርያ ፊልጶስ በሰማዕትነት የሞተበት መታሰቢያው ነው።

ይህም እንዲህ ነው ዕጣው ወደ አፍራቅያና ወደ አውራጃዋ ሁሉ በወጣ ጊዜ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስም በውስጧ ሰበከ። ልቡናንም የሚያስደነግጥ ድንቆች ታምራቶችንም አደረገ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አመኑ #እግዚአብሔርንም ወደ ማወቅ ከመለሳቸው በኋላ ወደሌሎች ብዙ አገሮች ወጣ እያስተማረ ሰዎችን ወደ ሃይማኖት ሲጠራ ኖረ ።

ከዚህም በኋላ ወደ ሌላ አገር ሒዶ የከበረ ወንጌልን ሰበከላቸው ብዙዎቹም ክብር ይግባውና በ #ጌታችን አመኑ ያላመኑት ግን ይገድሉት ዘንድ ተማከሩ በንጉሥም ዘንድ ተወዳጅነትን ያገኙ ዘንድ ከዚህም በኋላ ቅዱስ ሐዋርያ ፊልጶስን ይዘው አሠሩት ጽኑዕ ሥቃይንም አሠቃዩት እርሱም ይስቅባቸውና ከዘላለም ሕይወት ለምን ትርቃላችሁ የነፍሳችሁንስ ድኅነት ለምን አታስቡም ይላቸው ነበር እነርሱ ግን ብዙ ካሠቃዩት በኋላ ዘቅዝቀው ሰቀሉት ነፍሱንም በ #እግዚአብሔር እጅ ሰጠ።

ሥጋውንም በእሳት ሊአቃጥሉ በወደዱ ጊዜ የ #እግዚአብሔር መልአክ ከእጆቻቸው መካከል ነጠቃቸው እነርሱም ወደርሱ እየተመለከቱ ወስዶ ከኢየሩሳሌም አገር ውጭ አግብቶ ሠወረው ይህንንም ድንቅ ተአምር አይተው ሁሉም በታላቅ ድምፅ የቅዱስ ፊልጶስ አምላክ አንድ ነው እያሉ ጮኹ አሠቃይተው ስለገደሉትም ተጸጽተው አዘኑ ክብር ይግባውና በ #ጌታችንም አመኑ ።

የቅዱስ ሐዋርያ ፊልጶስንም ሥጋ ይመልስላቸው ዘንድ ለመኑት ሰውን የሚወድ ቸር ይቅር ባይ #ጌታችንም ልመናቸውን ተቀብሎ የሐዋርያ ፊልጶስን ሥጋ መለሰላቸውና እጅግ ደስ አላቸው ሁሉም ክብር ይግባውና ወደ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሃይማኖት ገቡ ከሐዋርያውም ሥጋ ታላላቅ የሆኑ ድንቆች ተአምራት ተገለጡ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባታችን ሐዋርያ ቅዱስ ፊልጶስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳት_ደናግል_አጥራስስና_ዮና

ዳግመኛም በዚህች ቀን ቅዱሳት ደናግል አጥራስስና ዮና በሰማዕትነት አረፉ። አጥራስስ ግን ጣዖታትን ለሚያመልክ ንጉሥ እንድርያኖስ ልጁ ናት እርሱም ከሰው ወገን ማንም እንዳያያት አዳራሽ ሠርቶ ለብቻዋ አኖራት እርሷ ግን ስለዚህ ዓለም ኃላፊነት የምታስብ ሆነች እውነተኛውንና የቀናውን መንገድ ይመራት ዘንድ በቀንና በሌሊት #እግዚአብሔርን ትለምነው ነበር።

ወደ ፍላጽፍሮን ልጅ ወደ ድንግሊቱ ዮና ላኪ እርሷም የ #እግዚአብሔርን መንገድ ትመራሻለች የሚላትን ራእይ አየች ከእንቅልፏም ስትነቃ በልቧ ደስ አላት ወደ ዮና ድንግልም ላከች እርሷም ፈጥና መጣች ለዮናም ሰላምታ ሰጠቻትና ከእግርዋ በታች ሰገደችላት የ #እግዚአብሔርንም ሃይማኖት ታሰተምራትና ትገልጥላት ዘንድ ለመነቻት።

ድንግል ዮናም የ #እግዚአብሔር ልጅ ሰው የሆነበትን ምክንያት #እግዚአብሔር አዳምን ከፈጠረበት ጊዜ በመጀመር ልትነግራት ጀመረች አዳም እንደበደለና ከተድላ ገነት እንደ ወጣ በኖኅም ዘመን የጥፋት ውኃ መጥቶ ኃጢአተኞችን ሁሉ እንደደመሰሰ የ #እግዚአብሔርን ሕግ የጠበቁ ስምነት ሰዎች ብቻ እንደ ቀሩ ከዚህም በኋላ ዳግመኛ ሰዎች በምድር ላይ በበዙ ጊዜ እንደበደሉና ጣዖትን እንዳመለኩ #እግዚአብሔርም ለአብርሃም እንደተገለጠለትና መርጦ ወዳጅ እንዳደረገው ከእርሱም ጋር ቃል ኪዳንን እንዳጸና እስራኤልንም ከግብጽ አገር እንዳወጣቸው የሰውንም ወገን ጠላት ሰይጣንን ከማምለክ ለእርሱም ከመገዛት ያድነው ዘንድ የ #እግዚአብሔር ልጅ መምጣቱንና ከእመቤታችን ከቅድስት #ድንግል_ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው መሆኑን ነቢያት እንደሰበኩ ነገረቻት።

ሁለተኛም ስለ ከበረ ስሙ መከራ በመቀበል ለሚደክሙ ሰማያዊ ሀብት የዘላለም መንግሥትን #እግዚአብሔር ስለ ሚሰጣቸው አስረዳቻት። አጥራስስም የዮናን ትምርቷን ሰምታ እጅግ ደስ አላት በሕያው #እግዚአብሔር ልጅ በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም አመነች።

እሊህ ደናግልም ሌሊትና ቀን በተጋድሎ ተጠምደው በአንድነት ተቀመጡ የአጥራስስም አባቷ ይህን አያውቅም ከሌሊቶችም በአንዲቱ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስን አዩት እናቱን እመቤታችን ቅድስት #ድንግል_ማርያምንም አዩአት። #እመቤታችንም ወደ ልጅዋ #እግዚአብሔር እንደ ቁርባን አቀረበቻቸውና እርሱም ባረካቸው።

ከዚህም በኋላ ንጉሥ ወደ ጦርነት ሒዶ በተመለሰ ጊዜ ወደ ልጁ አጥራስስ ገብቶ ልጄ ሆይ ወደ መሞሸሪያሽ ከመግባትሽ በፊት ለአምላክ አጵሎን ዕጣን ታሳርጊ ዘንድ ነዪ አላት። አጥራስስ ድንግልም አባቴ ሆይ ነፍስህና ሥጋህ በእጁ ውስጥ የሆነ የፈጠረህን በሰማይ ያለ አምላክን ትተህ ነፍስ የሌላቸው የረከሱ ጣዖታትን ለምን ታመልካለህ ብላ መለሰችለት።

ንጉሥም እንዲህ ያለ ነገር ከቶ ያልሰማውን ከልጁ አፍ በሰማ ጊዜ አደነቀ በልጁ ላይ ምን እንደደረሰ ልቧንም ማን እንደለወጠው ጠየቀ የፍላጽፍሮን ልጅ ድንግል ዮና የልጁን ልብ እንደ ለወጠች ነገሩት።

ንጉሡም በእሳት ያቃጥሏቸው ዘንድ አዘዘ በወርቅና በብር በተጌጠ የግምጃ ልብሶችን እንደ ተሸለሙ አወጧቸው እነርሱ የነገሥታት ልጆች ስለሆኑ አላራቆቿቸውም ታላላቆችና ታናናሾች ሁሉም ሰዎች ስለ እሳቸው እያዘኑና እያለቀሱ ወጡ ነፍሳቸውንም እንዳያጠፉ ለንጉሥ ይታዘዙ ዘንድ ለመኗቸው እነርሱ ግን ከበጎ ምክራቸው አልተመለሱም።

በዚያንም ጊዜ ጉድጓድ ቆፈሩላቸውና በውስጡ እሳትን አነደዱ ነበልባሉም እጅግ ከፍ ከፍ አለ ያን ጊዜ አንዷ ከሁለተኛዋ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው ወደ እሳት ውስጥ ተወረወሩ ፊታቸውንም ወደ ምሥራቅ መልሰው በመቆም ረጅም ጸሎትን ጸለዩ ከዚህም በኋላ ነፍሳቸውን በ #እግዚአብሔር እጅ ሰጡ እሳቱም እንደውኃ የቀዘቀዘ ሆነ ምእመናንም ሥጋቸውን አነሡ ተጠጋግተውም ልብሳቸውንም ቢሆን ወይም የራሳቸውን ጠጉር እሳት ምንም ምን ሳይነካቸው አገኟቸው ። የመከራውም ወራት እስቲፈጸም በታላቅ ክብር በአማረ ቦታ አኖርዋቸው ከዚህም በኋላ ቤተ ክርስቲያን ሠርተውላቸው ሥጋቸውን በውስጥዋ አኖሩ ከእርሳቸውም ታላላቅ የሆኑ ድንቆች ተአምራት ተገለጡ ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእሊህ በቅዱሳት ደናግል ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ኤላውትሮስና_እናቱ_እንትያ

በዚህችም ዕለት ከሮሜ አገር ቅዱስ ኤላውትሮስና እናቱ እንትያ በሰማዕትነት አረፉ። ይህም ቅዱስ #እግዚአብሔርን ከሚፈራ አንቂጦስ ከሚባል ኤጲስቆጶስ ዘንድ አደገ ዐሥራ ሰባት ዓመትም በሆነው ጊዜ ዲቁና ተሾመ ደግሞ በዐሥራ ስምንት ዐመቱ ቅስና ተሾመ ከዚህም በኋላ በሃያ ዓመቱ አላሪቆስ ለሚባል አገር ጵጵስና ተሾመ።

በዚያንም ወራት ንጉሥ እንድርያኖስ ወደ ሮሜ አገር መጣ ስለ ኤላውትሮስም ሰምቶ ወደርሱ ያመጣው ዘንድ ፊልቅስን አዘዘው ፊልቅስም በሔደ ጊዜ ቅዱሱን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የ #እግዚአብሔርን ቃል ሲያስተምር አገኘው። ፊልቅስም ትምርቱን በሰማ ጊዜ አመነና በክብር ባለቤት በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስም ተጠመቀ።
ኤላውትሮስንም ወደ ንጉሥ እንድርያኖስ በአደረሱት ጊዜ ለአማልክት ሠዋ አንተ ነጻነት ያለህ ስትሆን ለተሰቀለ ሰው ለምን ትገዛለህ አለው ። ኤላውትሮስም ነጻነትማ ሰማይና ምድርን በፈጠረ በ #ጌታ_ኢየሱስ_ክርስቶስ #መስቀል ነው ንጉሡም መንኰራኩር ካለው የእሳት ማንደጃ ውስጥ ጨምረው እንዲአቃጥሉት አዘዘ በጨመሩትም ጊዜ እሳቱ ጠፋ መንኩራኩሩም ተቆራረጠ። ንጉሡም አይቶ አደነቀ የሚያደርገውንም አጥቶ ከወህኒ ቤት ጨመረው ርግብም ከገነት መብልን አምጥታለት በልቶ ጠገበ ። ቆሊሪቆስ የሚባለውም መኰንን አይቶ በቅዱስ ኤላውትሮስ አምላክ አምኖ በሰማዕትነት ሞተ የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበለ።

ከዚህም በኋላ ፈረሶችን አምጥተው በሠረገላ ላይ እንዲጠምዷቸው ቅዱስ ኤላውትሮስንም ከሠረገላው በታች አሥረው ሕዋሳቱ እስኪሰነጣጠቅ ፈረሶችን እንዲአስሮጡአቸው እንድርያኖስ አዘዘ። በዚያንም ጊዜ የ #እግዚአብሔር መልአክ ወረደ ከማሠሪያውም ፈትቶ ወደ ከፍተኛ ተራራ ወሰደው በዚያም #እግዚአብሔርን እያመሰገነ ከአራዊት ጋር ተቀመጠ ።

እንድርያኖስም አራዊትን ያድኑ ዘንድ ወታደሮቹን በአዘዘ ጊዜ በዚያ ተራራ ውስጥ ቅዱስ ኤላውትሮስን አግኝተው ከዚያ ወደ ንጉሥ እንድርያኖስ ወሰዱት። ንጉሡም ለአንበሳ እንዲሰጥ አዘዘ አንበሶችም የፊቱን ላብ ጠረጉለትና እግሮቹን ሳሙ ከዚህም በኋላ ተመልሰው ከአረማውያን መቶ ሃምሳ ሰው ገደሉ እንድርያኖስም አይቶ ቁጣን ተመላ ሁለት ወታደሮችን ከእንትያ እናቱ ጋር በጦር እንዲወጉት አዘዘ እርሷንም ብዙ ከአሠቃይዋት በኋላ የልጅዋን አንገት እንዳቀፈች ከእርሱ ጋር ወጓት ነፍሳቸውንም በ #እግዚአብሔር እጅ ሰጡ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር_18)
2025/01/07 18:58:16
Back to Top
HTML Embed Code: