Telegram Web Link
#ነሐሴ_20

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሃያ በዚች ቀን መጻሕፍትን የተረጐመ #አባ_ሰላማ አረፈ፣ በከሀዲው ንጉሥ ዳኬዎስ ዘመን የነበሩ ከኤፌሶን ሀገር #ቅዱሳን_ሰባቱ_ደቂቅ አረፉ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ሰላማ_ካልዕ (#መተርጉም)

ነሐሴ ሃያ በዚች ቀን መጻሕፍትን የተረጐመ አባ ሰላማ አረፈ።

እኒህ ታላቅ ደግ ሰው የነበሩት በሃገራችን ኢትዮዽያ ከ1340 እስከ 1380 ዓ/ም ነው:: በትውልድ ግብጻዊ ቢሆኑም ለኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ውለታን ውለዋል:: በዘመኑ ዻዻስ ሁነው ቢመጡም እንደ ሌሎቹ ዻዻሳት በቤተ መንግስት አካባቢ ሥራ ፈትተው መቀመጥን አልፈለጉም::

ወዲያው እንደ መጡ የግዕዝ ልሳንን ልቅም አድርገው ተማሩ:: ቀጥለው ኢትዮዽያውያን ሊቃውንትን ሰብስበው ቅዱሳት መጻሕፍትን ይተረጉሙ ገቡ:: አሥራው መጻሕፍትን (81ዱን) ጨምሮ ብዙ መሠረታዊ መጻሕፍትን መተርጐም ችለዋል::

ይህም ሥራ አድካሚ በመሆኑ ከ30 ዓመታት በላይ ጊዜን ወስዷል:: ከተረጐሟቸው መጻሕፍትም፦ #ስንክሳር#ግብረ_ሕማማት#ላሃ_ማርያም#ፊልክስዩስ(መጽሐፈ መነኮሳት)፣ #መጽሐፈ_ግንዘት፣ድርሳን ዘቅዱስ #ያዕቆብ_ዘሥሩግ. . . ይጠቀሳሉ::

አቡነ ሰላማ በስብከተ ወንጌል አገልግሎታቸውና በገዳማዊ ሕይወታቸው ይታወቁ ነበር:: በተጨማሪም በየቦታው እየዞሩ ይናዝዙ: ያጠምቁም ነበር:: በወቅቱ ልክ እንደ ስማቸው ሰላም እንዲሰፍን ይተጉ ነበር:: መሣፍንቱን: ነገሥታቱን እያስታረቁ ለቤተ ክርስቲያን በአንድነት እንዲቆሙ አድርገዋል::

ጻድቁ አቡነ ፊልዾስን ጨምሮ ቅዱሳንን ገንዘውም ቀብረዋል:: በቀደመ ስማቸው #አባ_ፊቅጦር የሚባሉት ካልዕ (2ኛው) ሰላማ በ1380 ዓ/ም ከ40 ዓመታት ትጋት በኋላ ዐርፈዋል:: ሲጠሩም:- #መተርጉም (መጻሕፍትን የተረጐሙ)፣ #ብርሃነ_አዜብ(የኢትዮዽያ ብርሃን)፣ #መጋቤ_ሃይማኖት ተብለው ነው::

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_ሰባቱ_ደቂቅ

በዚህችም ቀን በከሀዲው ንጉሥ ዳኬዎስ ዘመን የነበሩ ከኤፌሶን ሀገር ሰባቱ ደቂቅ አረፉ። እሊህም ሰባቱ ደቂቅ ከንጉሥ ዳኬዎስ ጭፍሮች ውስጥ በመዛግብቱ ላይ የሾማቸው ነበሩ። አምልኮ ጣዖትንም በአወጀ ጊዜ ጣዖትን በማምለክ ሥራ አልተሳተፉም። እሊህንም ቅዱሳን በንጉሥ ዘንድ ወነጀሏቸው ይዞም አሠራቸው።

ከዚህም በኋላ ወደ ሌላ ቦታ ለመሔድ በፈለገ ጊዜ እስከ ሚመለስ ድረስ ፈትቶ ለቀቃቸው ምናልባት ከምክራቸው ቢመለሱ ብሎ በልቡ አስቦ። ከዚህም በኋላ እሊህ ቅዱሳን ለረከሱ ጣዖታት እንዳይሰግዱ የጭፍራነት ሥራቸውን ትተው በተራራ ውስጥ ወደአለ ዋሻ ሒደው በዚያ ተሠወሩ።

የዋሻውን አፍ ዘጉ ከእሳቸውም ጋራ በንጉሥ ዳኬዎስ ስም የተቀረጸ ብር ነበር። ከእርሳቸውም አንዱም አንዱ በየተራቸው ወጥቶ ምግባቸውን ገዝቶ ወደእሳቸው ይመለስ ነበር። ዳኬዎስም ከሔደበት እንደተመለሰ በሰሙ ጊዜ የዋሻውን ደጃፍ ዘግተው ተኙ።

የእሊህንም ቦታቸውን የሚያውቅ አማኒ የሆነ ከጭፍሮች ውስጥ አንድ ሰው ነበረ ወደ ከተማ ሲወጡ ያገኛቸው ዘንድ ጠበቃቸው ባልመጡም ጊዜ ተነሥቶ ወደ ዋሻቸው ሔደ። ዋሻዋንም ከውስጥ እንደ ዘጓት ሁና አገኛት እነርሱም በረሀብ የሞቱ መሰለው ታላቅም የደንጊያ ሠሌዳ አምጥቶ ከእሳቸው የሆነውን ገድላቸውን ጽፎ በቀዳዳ ወደ ዋሻው ውስጥ አስገባው።እሊህም ቅዱሳን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ሦስት መቶ ሰባ ሁለት ዘመናት አንቀላፉ ዳኬዎስም ሙቶ እስከ ቴዎዶስዮስ ብዙ ነገሥታት ነገሡ።

በዚህም ምእመን ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ዘመን ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዎች ተነሥተው ብዙዎች ተከተሏቸው። በዚያንም ጊዜ እሊህን ቅዱሳን ሰባቱን ደቂቅ እግዚአብሔር አነቃቸው ትንሣኤ ሙታን መኖሩን ግልጽ ያደርግ ዘንድ።

ከዚህም በኋላ ከእርሳቸው አንዱ ምግባቸውን ሊገዛ የከሀዲ ዳኪዎስንም ወሬ ይሰማ ዘንድ ብር ይዞ ወጣ ወደ ከተማም በገባ ጊዜ የከተማዋ ሁኔታ ተለወጠበት። በከተማውም በር መስቀሎችን አየ በየቅጽሮቿም የክብር ባለቤት የሆነ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም ስሙን ያለ መፍራት ሲጠሩ ሰማ አንዱንም ሰው ይች አገር ኤፌሶን አይደለችምን ብሎ ጠየቀ እርሱም አዎን ናት አለው።

ያንንም ብር አውጥቶ ለባለ ሱቁ ሰጠው ምግባቸውን ይሸጥለት ዘንድ ባለ ሱቁም ያን ብር ተመለከተው የንጉሥ ዳኬዎስም ስም ተቀርጾበት አገኘውና ያንን ሰው ይዞ በአንተ ዘንድ የተሸሸገ መዝገብ አለ ይህ ምልክት ከአንተ ተገኝቷልና አለው።

እንዲህም ሲጣሉ ወደእርሳቸው ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ እንዲህም ብለው ጠየቁት አንተ ከወዴት ነህ ከዚች አገር ነኝ አላቸው።ማንን ታውቃለህ አሉት እርሱም ዕገሌንና ዕገሌን አላቸው ከዘመን ብዛት የተነሣ የጠራቸውን ሰዎች የሚያውቃቸው የለም።ስለዚህም በእርሱ ላይ ተቆጥተው ወደ ዳኞችና ወደ ኤጲስቆጶስ አባ ቴዎድሮስ ወደ ንጉሥ ቴዎዶስዮስም አቀረቡት።

ንጉሡና ኤጲስቆጶሱም ከአንተ የሆነውን እውነቱን ንገረን ከወዴት አገር ነህ አሉት። እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው እኛ ሰባታችን የከሀዲ ንጉሥ ዳኬዎስ ጭፍሮች ነን እርሱም ወጥቶ ወደ ሌላ አገር በሔደ ጊዜ ከአንዷ ዋሻ ውስጥ ገብተን የዋሻዋን በር ዘግተን ተኛን። እነሆ ስንነቃ የምንመገበውን ምግብ እገዛ ዘንድ ላኩኝ።

ንጉሡና ኤጲስቆጶሱ በሰሙ ጊዜ ተነሥተው ወደዚያ ዋሻ ከእርሱ ጋራ ሔዱ ከእርሳቸውም ጋራ ብዙ ሕዝቦች አሉ ቅዱሳኑንም ተቀምጠው አገኙአቸው። የዘመኑም ቁጥር በውስጡ የተጻፈበትን በከሀዲው ንጉሥ በዳኬዎስ ዘመን የሆነውን ሠሌዳውን ወድቆ አገኙት ዘመኑም ሦስት መቶ ሰባ ሁለት ዓመት እንደሆነ ታወቀ።

ንጉሡና ኤጲስቆጶሱ ከሕዝቡ ሁሉ ጋር አደነቁ ምስጉን እግዚአብሔርንም አመሰገኑት ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉትም ይህን ድንቅ ሥራ አይተው ትንሣኤ ሙታን እንዳለ አመኑ። እሊህ ሰባቱ ደቂቅንም በጠየቋቸው ጊዜ ከእርሳቸው የሆነውን ሁሉ ነገሩአቸው።

ከዚህም በኋላ ተመልሰው ተኙ። ነፍሳቸውንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጡ። ንጉሥም የወርቅ ሣጥን ሠራላቸው በሐር ልብሶችም ገንዘው በመልካም ቦታ አኖሩዋቸው። ከሥጋቸውም ብዙዎች ድንቆችና ተአምራት ተገለጡ።

ስማቸውም:- መክሲማኖስ፣ ታሙኪሮስ፣ መርዳዲሞስ፣ ዮሐንስ፣ ቈስጠንጢኖስ፣ አዝሚና ዲዮናስዮ ነው።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የእሊህም ቅዱሳን በረከታቸው ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን!

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_20 እና #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_20_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ቆሮንቶስ 15
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³¹ በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ ባለኝ በእናንተ ትምክህት እየማልሁ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ዕለት ዕለት እሞታለሁ።
³² እንደ ሰው በኤፌሶን ከአውሬ ጋር ከታገልሁ፥ ሙታንስ የማይነሡ ከሆነ፥ ምን ይጠቅመኛል? ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ።
³³ አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል።
³⁴ በጽድቅ ንቁ ኃጢአትንም አትሥሩ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉና፤ አሳፍራችሁ ዘንድ ይህን እላለሁ።
³⁵ ነገር ግን ሰው፦ ሙታን እንዴት ይነሣሉ? በምንስ ዓይነት አካል ይመጣሉ? የሚል ይኖር ይሆናል።


³⁷ የምትዘራውም፥ ስንዴ ቢሆን ከሌላም ዓይነት የአንዱ ቢሆን፥ ቅንጣት ብቻ ነው እንጂ የምትዘራው የሚሆነውን አካል አይደለም፤
³⁸ እግዚአብሔር ግን እንደ ወደደ አካልን ይሰጠዋል ከዘሮችም ለእያንዳንዱ የገዛ አካሉን ይሰጠዋል።
³⁹ ሥጋ ሁሉ አንድ አይደለም፥ የሰው ሥጋ ግን አንድ ነው፥ የእንስሳም ሥጋ ሌላ ነው፥ የወፎችም ሥጋ ሌላ ነው፥ የዓሣም ሥጋ ሌላ ነው።
⁴⁰ ደግሞ ሰማያዊ አካል አለ፥ ምድራዊም አካል አለ፤ ነገር ግን የሰማያዊ አካል ክብር ልዩ ነው፥ የምድራዊም አካል ክብር ልዩ ነው።
⁴¹ የፀሐይ ክብር አንድ ነው የጨረቃም ክብር ሌላ ነው የከዋክብትም ክብር ሌላ ነው፤ በክብር አንዱ ኮከብ ከሌላው ኮከብ ይለያልና።
⁴² የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው። በመበስበስ ይዘራል፥ ባለመበስበስ ይነሣል፤
⁴³ በውርደት ይዘራል፥ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል፥ በኃይል ይነሣል፤
⁴⁴ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፥ መንፈሳዊ አካል ይነሣል። ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ።
⁴⁵ እንዲሁ ደግሞ፦ ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ።
⁴⁶ ነገር ግን አስቀድሞ ፍጥረታዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም።
⁴⁷ የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው ከሰማይ ነው።
⁴⁸ መሬታዊው እንደ ሆነ መሬታውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው፥ ሰማያዊው እንደ ሆነ ሰማያውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው።
⁴⁹ የዚያንም የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን።
⁵⁰ ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እላለሁ፦ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፥ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ያዕቆብ 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹¹ ወንድሞች ሆይ፥ እርስ በርሳችሁ አትተማሙ። ወንድሙን የሚያማ በወንድሙም የሚፈርድ ሕግን ያማል በሕግም ይፈርዳል፤ በሕግም ብትፈርድ ፈራጅ ነህ እንጂ ሕግን አድራጊ አይደለህም።
¹² ሕግን የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ነው፤ እርሱም ሊያድን ሊያጠፋም የሚችል ነው፤ በሌላው ግን የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?
¹³ አሁንም፦ ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህ ከተማ እንሄዳለን በዚያም ዓመት እንኖራለን እንነግድማለን እናተርፍማለን የምትሉ እናንተ፥ ተመልከቱ፥ ነገ የሚሆነውን አታውቁምና።
¹⁴ ሕይወታችሁ ምንድር ነው? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፍዋለት ናችሁና።
¹⁵ በዚህ ፈንታ። ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም ይህን ወይም ያን እናደርጋለን ማለት ይገባችኋል።
¹⁶ አሁን ግን በትዕቢታችሁ ትመካላችሁ፤ እንደዚህ ያለ ትምክህት ሁሉ ክፉ ነው።
¹⁷ እንግዲህ በጎ ለማድረግ አውቆ ለማይሠራው ኃጢአት ነው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 23
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²² የሻለቃውም፦ ይህን ነገር ለእኔ ማመልከትህን ለማንም እንዳትገልጥ ብሎ ካዘዘ በኋላ ብላቴናውን አሰናበተው።
²³ ከመቶ አለቆቹም ሁለት ጠርቶ፦ ወደ ቂሣርያ ይሄዱ ዘንድ ሁለት መቶ ወታደሮችንና ሰባ ፈረሰኞችን ሁለት መቶም ባለ ጦር መሣሪያዎችን ከሌሊቱ በሦስተኛው ሰዓት አዘጋጁ አላቸው።
²⁴ ጳውሎስንም ወደ አገረ ገዡ ወደ ፊልክስ በደኅና እንዲያደርሱት የሚያስቀምጡበትን ከብት ያዘጋጁ ዘንድ አዘዛቸው።
²⁵ ደብዳቤም ጻፈ እንዲህ የሚል፦
²⁶ ከቀላውዴዎስ ሉስዮስ ወደ ክቡር አገረ ገዡ ወደ ፊልክስ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን።
²⁷ ይህን ሰው አይሁድ ይዘው ሊገድሉት ባሰቡ ጊዜ ከጭፍሮቹ ጋር ደርሼ አዳንሁት፥ ሮማዊ እንደ ሆነ አውቄ ነበርና።
²⁸ የሚከሰስበትንም ምክንያት አውቅ ዘንድ አስቤ ወደ ሸንጎአቸው አወረድሁት፤
²⁹ በሕጋቸውም ስለ መከራከር እንደ ከሰሱት አገኘሁ እንጂ ለሞት ወይም ለእስራት የሚያደርስ ክስ አይደለም።
³⁰ በዚህም ሰው አይሁድ ሴራ እንዲያደርጉበት ባመለከቱኝ ጊዜ ያን ጊዜውን ወደ አንተ ሰደድሁት፥ ከሳሾቹንም ደግሞ በፊትህ ይከሱት ዘንድ አዘዝኋቸው። ደኅና ሁን።
³¹ ወታደሮቹም እንደ ታዘዙት ጳውሎስን ይዘው በሌሊት ወደ አንቲጳጥሪስ አደረሱት፤
³² በነገውም ከእርሱ ጋር ይሄዱ ዘንድ ፈረሰኞችን ትተው ወደ ሰፈር ተመለሱ።
³³ እነዚያም ወደ ቂሣርያ ገብተው ደብዳቤውን ለአገረ ገዡ በሰጡ ጊዜ ጳውሎስን ደግሞ በፊቱ አቆሙት።
³⁴ ካነበበውም በኋላ የወዴት አውራጃ እንደ ሆነ ጠየቀው፤ የኪልቅያ ሰው መሆኑንም ባወቀ ጊዜ፦
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_20_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ነጽረኒ ወስምዐኒ እግዚኦ አምላኪየ። አብርሆን ለአዕይንትየ ከመ ኢይኑማ ለመዊት። ወከመ ኢይበሉኒ ጸላእትየ ሞዕናሁ"። መዝ 12፥3 ወይም መዝ 44፥9-10።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_20_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 22
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²³ በዚያን ቀን፦ ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ ቀረቡ፥
²⁴ እንዲህም ብለው ጠየቁት፦ መምህር ሆይ፥ ሙሴ አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ሲሞት ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ አለ።
²⁵ ሰባት ወንድማማች በእኛ ዘንድ ነበሩ፤ ፊተኛውም ሚስት አግብቶ ሞተ፥ ዘርም ስለሌለው ሚስቱን ለወንድሙ ተወለት፤
²⁶ እንዲሁ ደግሞ ሁለተኛው ሦስተኛውም፥ እስከ ሰባተኛው ድረስ።
²⁷ ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ሞተች።
²⁸ ሁሉ አግብተዋታልና በትንሣኤ ቀንስ፥ ከሰባቱ ለማናቸው ሚስት ትሆናለች?
²⁹ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ።
³⁰ በትንሣኤስ እንደ እግዚአብሔር መላእክት በሰማይ ይሆናሉ እንጂ አያገቡም አይጋቡምም።
³¹-³² ስለ ትንሣኤ ሙታን ግን፦ እኔ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ የሚል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እናንተ የተባለውን አላነበባችሁምን? የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም።
³³ ሕዝቡም ይህን ሰምተው በትምህርቱ ተገረሙ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #እመቤታች_የማርያም ቅዳሴ ነው። መልካም የእመቤታችን የትንሣኤዋና የዕርገቷ በዓል ሰሞን። ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_21

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሃያ አንድ በዚህች ቀን #ቅድስት_ኄራኒ ሰማዕትነት የተቀበለችበት፣ #የንግሥተ_ሳባ እና #ንግሥት_ዕሌኒ የተወለዱበት ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ኄራኒ_ሰማዕት

ነሐሴ ሃያ አንድ በዚህች ቀን ቅድስት ኄራኒ የስሟ ትርጓሜ ሰላም ፍቅር የሆነ ለንጉሥ ሉክያኖስ ልጁ ምስክር ሁና ሞተች ። እርሱም አባቷ ያማረ አዳራሽን ሠራላት መስኮቶቹንም ስምንት አደረገ ቅጽሩንም በዙሪያው ዐሥራ ሁለት አደረገ ማዕድንም ሠራላት። የወርቅና የብር የሆኑ ሣህኖችና ጽዋዎችንም አዘጋጀላት የሚያስተምራትም አንድ ሽማግሌ ሰው አደረገላት።

ከዚህም በኋላ በዚያች አዳራሽ ውስጥ አኖራት የሚያገለግሏትም ሦስት አገልጋዮችን በእርሷ ዘንድ አድርጎ ደጃፎችን በላይዋ ዘጋ መምህርዋም በውጭ ሆኖ ያስተምራታል።

ዕድሜዋም ሰባት ዓመት ሆናትና ያን ጊዜ ራእይን አየች በማዕዷ ላይ ርግብ ስትቀመጥ በአፍዋም የወይራ ቅጠል አለ ። በማዕዱም ላይ አኖረችው ሁለተኛም ንስር መጣ ከእርሱ ጋር አክሊል አለ በማዕዷ ላይም አኖረው ። ደግሞ ቊራ መጣ ከእርሱ ጋራ ከይሲ አለ በማዕዷ ላይም አኖረው ። ደነገጠችም ለመምህርዋም ነገረችው እርሱም እንዲህ ብሎ ተረጐመላት ርግብ የሕግ ምልክት ናት የዘይቱም ቅጠል የክርስትና ጥምቀት ናት፣ ንስርም ድል አድራጊነት ነው አክሊልም ለሰማዕታት የሚሰጥ ክብራቸው ነው ። ቊራ የንጉሥ ምሳሌ ነው ከይሲውም መከራ ነው አንቺም የክብር ባለቤት በሆነ #ክርስቶስ ስለ ስሙ ትጋደዪ ዘንድ አለሽ አላት።

ከዚህም በኋላ ይጐበኛት ዘንድ አባቷ ወደርሷ መጣና ልጄ ሆይ ከመንግሥት ታላላቆች ለአንዱ ላጋባሽ እኔ እሻለሁ አላት እርሷ ግን ከልቡናዬ እስተምመክር ሦስት ቀኖችን አባቴ ሆይ ታገሠኝ ብላ መለሰችለት።

አባቷም በሔደ ጊዜ በጣዖታቱ መሠዊያ ፊት ተነሥታ ቆመችና ስለጋብቻ የሚሆነውን ይገልጡላት ዘንድ ለመነቻቸው እነርሱም ምንም ምን ከቶ አልመለሱላትም።

ከዚህም በኋላ ዐይኖቿን ወደ ሰማይ አቅንታ የክርስቲያን አምላክ ሆይ ወደምትፈቅደው ምራኝ ብላ ጸለየች ያን ጊዜ የ #እግዚአብሔር መልአክ መጥቶ እንዲህ አላት። እነሆ ነገ ከጳውሎስ ደቀ መዛመርት አንዱ ወደዚች አገር ይመጣል እርሱም የክርስትና ጥምቀትን ያጠምቅሻል።

በማግሥቱም ያ ሐዋርያ መጥቶ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃት። በሦስተኛውም ቀን እንደቀጠረቻቸው አባቷና እናቷ መጡ እርሷም እንዲህ አለቻቸው እኔ ሰማይና ምድርን በፈጠረ በሕያው #እግዚአብሔር ልጅ በ #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ የማምን ክርስቲያን ነኝ።

አባቷም ሰምቶ በእርሷ ላይ ተቆጣ ወደ ከተማው መካከልም አውጥተው በጐዳና ላይ እንዲጥሏትና በፈረሶች እግር እንዲአስረግጧት አዘዘ። ወታደሮችም ንጉሥ አባቷ እንዳዘዘ አደረጉባት ግን ምንም ምን ክፉ ነገር ከቶ አልደረሰባትም። ይህንንም ድንቅ ሥራ አባቷና እናቷ በአዩ ጊዜ የክብር ባለቤት በሆነ በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አመኑ መንግሥታቸውንም ትተው ለርሷ ወደተሠራው አዳራሽ ሔደው በውስጡ ተቀመጡ።

በጐረቤታቸው ያለ ንጉሥም ዜናቸውን በሰማ ጊዜ ወደ ርሳቸው መጥቶ ወደ መንግሥታቸው እንዲመለሱ ተናገራቸው። እነርሱም አልፈለጉም እርሱም መንግሥታቸውን ያዘ ቅድስት ኄራኒንም ይዞ አሠቃያት ከዚያም አንበሶችን፣ እባቦችን በላይዋ ሰደደ ምንም አልቀረቧትም ። ሁለተኛም በመጋዝ መገዛት በአንገቷም ውስጥ ታላቅ ደንጊያ አሥሮ ከባሕር ጣላት የክብር ባለቤት #ጌታችንም ከዚህ ሁሉ አድኖ ያለ ጥፋት በጤና አሥነሣት።

ከዚህም በኋላ እርሷን ያጠመቀ ሐዋርያን አባቷ ጠርቶ ከቤተሰቦቹ ሁሉ ጋር ተጠመቀ ቊጥራቸውም ሦስት መቶ ሆነ ከዘመዶቹና ከሀገር ሰዎችም ብዙዎች ተጠመቁ።

ከዚህም በኋላ ከሀዲው ንጉሥ ኑማርያኖስ የቅድስት ኄራኒን ዜናዋን ሰማ ወደርሱም አስቀርቦ ቀላኒካ ወደሚባል አገር ወሰዳት ። በዚያም ጽኑ ሥቃይን አሠቃያት በበሬ አምሳል በተሠራ የነሐስ በርሜል ውስጥ ዘጋባት የክብር ባለቤት #ጌታችንም ያንን በሬ ሰብሮ ቅድስት ኄራኒን ያለ ጥፋት በጤና አወጣት።

ከዚህም በኋላ ኑማርያኖስ ሙቶ በርሱ ፈንታ ሳፎር ነገሠ እርሱም የቅድስት ኄራኒን ዜና በሰማ ጊዜ ወደ ርሱ አስቀርቦ በእጁ ውስጥ በአለ በታላቅ ጦር ወጋትና ነፍሷን አሳለፈች የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም ከሞተ አስነሣት።

ንጉሥ ሳፎርም በአየ ጊዜ እጅግ አደነቀ ሰገደላትም በ #ጌታችን_ኢየሱስም አመነ ። ከእርሱም ጋራ ከሀገር ሰዎች ብዙ ወገኖች አመኑ ቁጥራቸውም ሠላሳ አንድ ሺህ ሆነ።

ከዚህም በኋላ በዚያች አዳራሽ ውስጥ አባቷና እናቷ አረፉ እርሷን ግን አምላካዊት ኃይል ተሸከመቻት ወደ ኤፌሶን አገርም አድርሳት በዚያ ታላላቅ የሆኑ ድንቆች ተአምራቶችን አደረገች።

በፋርስ ነገሥታት በመቄዶንያ፣ በቀላኒካና በቊስጥንጥንያ ነገሥታት ፊት በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስም ከመሰከረች በኋላ ወደ ወደደችው #ክርስቶስ ሔደች ። የድልና የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበለች ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቷ ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ንግሥተ_ሳባ

ይህቺ ኢትዮዽያዊት ንግሥት ከ3 ሺ ዘመናት በፊት የነበረች ደግ እናት ናት። በሥጋዊ ደረጃ ከታንዛንያ እስከ የመን ያስተዳደረች ስመ ጥር ንግሥት ስትሆን በመንፈሳዊው ደረጃ ደግሞ #እግዚአብሔር የቀባውን ሰው ፍለጋ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዛለች።

ከዚያውም አምልኮተ #እግዚአብሔርን ከሥርዓተ ኦሪት ጋር አምጥታለች። ድንግልናዋን ለታላቁ ንጉሥ ሰሎሞን ሰጥታ ቀዳማዊ ምኒልክን ወልዳለች።

ይህቺ ንግሥት በጌታችን (በፈጣሪ) አንደበትም ተመስግናለች። (ማቴ. 12፥42) በስምም ሳባ፣ አዜብና ማክዳ ተብላ ትታወቃለች። ዛሬ ዕለተ ልደቷ ነው::

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ዕሌኒ_ንግሥት

በዚህች ቀን የጻድቅ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ እናት ቅድስት ዕሌኒ ተወለደች። ይቺም ቅድስት በፊት የአንድ ነጋዴ ሰው ሚስት ነበረች እርሱም በነገረ ሠሪ ንጽሕት ሁና ሳለች ወደ ባሕር ጣላት። የክብር ባለቤት በሆነ በ #ጌታችን ፈቃድም ሮሐ ከሚባል አገር ደርሳ የበራንጥያ ንጉሥ ቊንስጣ አገኛት። ውበቷንና ደም ግባቷንም አይቶ አገባት። ለክርስቲያን ነገሥታት መጀመሪያቸው የሆነውን ቈስጠንጢኖስን ወለደችው ምግባርንና ሃይማኖትን በማስተማር በመልካም አሳደገችው።

ልጇም በነገሠ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ሒደሽ የክብር ባለቤት የሆነ የ #ክርስቶስን_መስቀል ግለጪ የከበሩ ቦታዎችንም ሥሪ የሚላትን በሕልሟ አይታ እንዴት እንዳየች ይህን ለልጇ ነገረችው እርሱም ከብዙ ሠራዊት ጋራ ሰደዳት። በደረሰችም ጊዜ የክብር ባለቤት ስለሆነ ስለ #ጌታችን_መስቀል መረመረች አዳኝ የሆነ #መስቀሉንም ሁለቱ ወንበዴዎች ከተሰቀሉባቸው መስቀሎች ጋራ አገኘችው። የክብር ባለቤት የ #ክርስቶስ_መስቀል የትኛው እንደሆነ ታውቅ ዘንድ በወደደች ጊዜ ከራሱ በላይ ይህ የናዝሬቱ #ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ ነው የሚል በእንጨት የተቀረጸበት ጽሑፍ ያለው እንደሆነ የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ ቅዱስ መቃርስ ነገራት።

ከዚህ በኋላ ከእርሱ ምልክት ታይ ዘንድ ፈለገች የሞተ ሰውም አግኝታ መስቀሎችን በበድኑ ላይ አኖረች አልተነሣም። ከዚህ በኋላ ሦስተኛውን #መስቀል በላዩ አኖረች። ያን ጊዜ ምውት ተነሣ ሃይማኖቷም ጸና ደስታዋም በዛ።
ከዚህ በኋላም ዜናቸው በመስከረም ወር በዐሥራ ሰባት የተጻፈ በከበሩ ቦታዎች ውስጥ አብያተ ክርስቲያናትን ትሠራ ዘንድ ጀመረች። ለአባ መቃርስም በከበሩ ቦታዎች ሁሉ አብያተ ክርስቲያናትን እንዲሠራ ብዙ ገንዘብ ሰጠችው።

ከዚህ በኋላ ወደ ልጇ ተመልሳ የሆነውን ሁሉ ነገረችው የከበረ #መስቀል በመገኘቱ እጅግ ደስ አለው።

ይቺም ቅድስት በጎ ገድሏን ከፈጸመችና #እግዚአብሔርንም ከአገለገለች በኋላ ስለ ካህናትም ልብስና ቀለብ ለአብያተ ክርስቲያናትና ለገዳማት ብዙ ጉልቶችና ርስቶችን ለድኆችና ለምስኪኖችም እንዲሁ ከሠራችና ከተከለች በኋላ በሰላም ግንቦት ዘጠኝ ቀን አርፋለች መላ ዕድሜዋም ሰማንያ ሆነ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_21_እና_ግንቦት_9)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_21_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ቆሮንቶስ 7
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁵ ስለ ደናግልም የጌታ ትእዛዝ የለኝም፥ ነገር ግን የታመንሁ እሆን ዘንድ ከጌታ ምሕረትን የተቀበልሁ እንደ መሆኔ ምክር እመክራለሁ።
²⁶ እንግዲህ ስለ አሁኑ ችግር ይህ መልካም ይመስለኛል፤ ሰው እንዲህ ሆኖ ቢኖር መልካም ነው።
²⁷ በሚስት ታስረህ እንደ ሆንህ መፋታትን አትሻ፤ በሚስት አልታሰርህ እንደ ሆንህ ሚስትን አትሻ።
²⁸ ብታገባ ግን ኃጢአት አትሠራም ድንግሊቱም ብታገባ ኃጢአት አትሠራም፤ ነገር ግን እንዲህ በሚያደርጉ በሥጋቸው ላይ መከራ ይሆንባቸዋል፥ እኔም እራራላችሁ ነበር።
²⁹ ዳሩ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፥
³⁰ የሚያለቅሱም እንደማያለቅሱ፥ ደስ የሚላቸውም ደስ እንደማይላቸው፥
³¹ የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና።
³² ነገር ግን ያለ አሳብ ልትኖሩ እወዳለሁ። ያላገባው ጌታን እንዴት ደስ እንዲያሰኘው የጌታን ነገር ያስባል፤
³³ ያገባው ግን ሚስቱን እንዴት ደስ እንዲያሰኛት የዓለምን ነገር ያስባል፥ ልቡም ተከፍሎአል።
³⁴ ያልተጋባች ሴትና ድንግል በሥጋም በነፍስም እንዲቀደሱ የጌታን ነገር ያስባሉ፤ የተጋባች ግን ባልዋን እንዴት ደስ እንድታሰኘው የዓለምን ነገር ታስባለች።
³⁵ ይህንም ለራሳችሁ ጥቅም እላለሁ፤ በአገባብ እንድትኖሩ ሳትባክኑም በጌታ እንድትጸኑ ነው እንጂ ላጠምዳችሁ ብዬ አይደለም።
³⁶ ዳሩ ግን ማግባት ወደሚገባው ዕድሜ በደረሰ ጊዜ ስለ ድንግልናው ያፈረ ሰው ቢኖር፥ የወደደውን ያድርግ፤ ኃጢአት የለበትም፤ ይጋቡ።
³⁷ ሳይናወጥ በልቡ የጸና ግን ግድ የለበትም፥ የወደደውን እንዲያደርግ ተፈቅዶለታል፤ ድንግልናውንም በልቡ ይጠብቅ ዘንድ ቢጸና፥ መልካም አደረገ።
³⁸ እንዲሁም ድንግልን ያገባ መልካም አደረገ ያላገባም የተሻለ አደረገ።
³⁹ ሴት ባልዋ በሕይወት ሳለ የታሰረች ናት፤ ባልዋ ቢሞት ግን በጌታ ይሁን እንጂ የወደደችውን ልታገባ ነጻነት አላት።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ዮሐንስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹-² በእኛ ስለሚኖርና ከእኛ ጋር ለዘላለም ስለሚሆን እውነት፥ እኔ ሽማግሌው በእውነት ለምወዳቸውና እኔ ብቻ ሳልሆን እውነትን የሚያውቁ ሁሉ ደግሞ ለሚወዱአቸው ለተመረጠች እመቤትና ለልጆችዋ፤
³ ከእግዚአብሔር አብና ከአብ ልጅ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም በእውነትና በፍቅር ከእኛ ጋር ይሆናሉ።
⁴ ትእዛዝን ከአብ እንደ ተቀበልን ከልጆችሽ በእውነት የሚሄዱ አንዳንዶችን ስለ አገኘኋቸው እጅግ ደስ ብሎኛል።
⁵ አሁንም፥ እመቤት ሆይ፥ እርስ በርሳችን እንድንዋደድ እለምንሻለሁ፤ ይህች ከመጀመሪያ በእኛ ዘንድ የነበረች ትእዛዝ ናት እንጂ አዲስ ትእዛዝን እንደምጽፍልሽ አይደለም።
⁶ እንደ ትእዛዛቱም እንሄድ ዘንድ ይህ ፍቅር ነው፤ ከመጀመሪያ እንደ ሰማችሁ፥ በእርስዋ ትሄዱ ዘንድ ትእዛዙ ይህች ናት።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 16
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹³ በሰንበት ቀንም ከከተማው በር ውጭ የጸሎት ስፍራ በዚያ መሆኑን ስላሰብን ወደ ወንዝ አጠገብ ወጣን፤ ተቀምጠንም ለተሰበሰቡት ሴቶች ተናገርን።
¹⁴ ከትያጥሮን ከተማም የመጣች ቀይ ሐር ሻጭ እግዚአብሔርን የምታመልክ ልድያ የሚሉአት አንዲት ሴት ትሰማ ነበረች፤ ጳውሎስም የሚናገረውን ታዳምጥ ዘንድ ጌታ ልብዋን ከፈተላት።
¹⁵ እርስዋም ከቤተ ሰዎችዋ ጋር ከተጠመቀች በኋላ፦ በጌታ የማምን እንድሆን ከፈረዳችሁልኝ፥ ወደ ቤቴ ገብታችሁ ኑሩ ብላ ለመነችን፤ በግድም አለችን።
¹⁶ ወደ ጸሎት ስፍራም ስንሄድ፥ የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት ለጌቶችዋም እየጠነቈለች ብዙ ትርፍ ታመጣ የነበረች አንዲት ገረድ አገኘችን።
¹⁷ እርስዋ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፦ የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባሪያዎች ናቸው ብላ ትጮኽ ነበር።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_21_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"አዋልደ ንግሥት ለክብርከ። ወትቀውም ንግሥት በየማንከ። በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኊብርት"። መዝ 44፥9።
“የንጉሦች ሴት ልጆች ለክብርህ ናቸው፤ በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች።” መዝ 44፥9።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_21_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 25
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ አሥር ቆነጃጅትን ትመስላለች።
² ከእነርሱም አምስቱ ሰነፎች አምስቱም ልባሞች ነበሩ።
³ ሰነፎቹ መብራታቸውን ይዘው ከእነርሱ ጋር ዘይት አልያዙምና፤
⁴ ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮአቸው ዘይት ያዙ።
⁵ ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ሁሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ።
⁶ እኩል ሌሊትም ሲሆን፦ እነሆ፥ ሙሽራው ይመጣል፥ ትቀበሉት ዘንድ ውጡ የሚል ውካታ ሆነ።
⁷ በዚያን ጊዜ እነዚያ ቆነጃጅት ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ።
⁸ ሰነፎቹም ልባሞቹን፦ መብራታችን ሊጠፋብን ነው፤ ከዘይታችሁ ስጡን አሉአቸው።
⁹ ልባሞቹ ግን መልሰው፦ ምናልባት ለእኛና ለእናንተ ባይበቃስ፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ አሉአቸው።
¹⁰ ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፥ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ፥ ደጁም ተዘጋ።
¹¹ በኋላም ደግሞ የቀሩቱ ቈነጃጅት መጡና፦ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ፥ ክፈትልን አሉ።
¹² እርሱ ግን መልሶ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ አላውቃችሁም አለ።
¹³ ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ።
¹⁴ ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደ ሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #እመቤታች_የማርያም ቅዳሴ ነው፡፡ መልካም በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ልመናዋ ክብሯዋ የልጇም ቸርነት በሁላችን ላይ ለዘለዓለም በእውነት ይደርብንና አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች ክብርት #እመቤታችን ያደረገችው ተአምር ይሕ ነው።

ብዙ ንብ ያለው አንድ ሰው ነበረና ከሰው ሁሉ ይልቅ ፈጽሞ ንቡ ይበዛለት ዘንድ ይወድ ነበር። ወደ አንዲት ስራየኛ ሴት ሒዶ ንቤ ይበዛልኝ ዘንድ ማርም ሰምም ከሰው ሁሉ ይልቅ ይበዛልኝ ዘንድ የምሠራውን ሥራ እንድትመክሪኝ እለምንሻለሁ አላት። ያችም ሰራየኛ ሴት እኔስ #ሥጋውን _ደሙን በተቀበልህ ጊዜ ካፍህ አውጥተህ በዚያ ቀፎ ወስጥ ጨምረው። ብዙ ንብ ሰምና ማርም ይሆንልሃል ብዬ እመክርሃለሁ አለችው። በሁለተኛውም ቀን ወደ ቤተ ክርስትያን ሒዶ #ሥጋውን_ደሙን ተቀብሎ እንደ ነገረችው አደረገና ካፉ አውጥቶ በንቡ ውስጥ ጨምሮ አንዲት ሰዓት እልፍ አለ።

ሁለተኛም ንብ ወዳለበት በተመለሰ ጊዜ ሥጋውን ካስቀመጠበት ከዚያ ቀፎ ውስጥ እጅግ ፍጹም ብርሃንና የ #እመቤታችን ሥዕል በዚያ ቀፎ ውስጥ በንቦች መካከል ተቀምጣ አየ። በደረቷም ከፀሐይና ከጨረቃ የሚያበራ ልጅ ታቅፋ ነበር። ይሕን ምልክት ባየ ጊዜ ጽኑዕ ፍርሃት ፈራና ወደ ቄስ ሒዶ ያደረገውን ሁሉ በቀፎ ውስጥም ያየውን ነገረው፤ ቄሱ ግን ነገሩን አልተቀበለውም ነበር። ነገር ግን ያሳየህን ተመልከት እይ ብሎ አንድ ዲያቆን ከእርሱ ጋራ ላከ። ዲያቆኑም ሒዶ ያ ሰው እንደተናገረው አይቶ በፍጹም ፍርሃት ተመልሶ ያየውን ለቄሱ ነገረው።

ቄሱም ይሕን ነገር ሰምቶ ሕዝቡ ሁሉ በፍጹም ተድላ ደስታ ይሰበሰብ ዘንድ አዘዛቸውና ወደዚያ ቦታ ደረሱ። ያም ቄስ ወደዚያ ቀፎ ቀረበና ያን ፍጹም ብርሃን አይቶ #ድንግል ንጽሕት እመቤታችንም ሕፃኑን አቅፋ በብዙ ንቦች መካከል አይቶ ፈጽሞ ፈራ። ቀፎውንም ተሸክመው ወስደው በታቦቱ ላይ ያኖሩት ዘንድ አዘዘ ያችንም ሥዕል አውጥቶ በመንበሩ ላይ አስቀመጣት። እስከ ፍታቴ ድረስ ይቀደስ ዘንድ አዘዘ ሥዕሊቱም ተመልሳ በታቦቱ ላይ ባለ ሥጋው አደረች። ቅዳሴው እንደ ታዘዘ ተፈጸመ።

ይችም ምልክት ባራቱ ማዕዘን ሁሉ ተረዳች። የሰሙም ሁሉ አደነቁ። #እግዚአብሔርን አምሰገኑት አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች ክብርት #እመቤታችንንም አመሰገኗት።

ልመናዋ ክብሯም በእኛ ለዘለዓለም በእውነት ይደርብን።
#ደብረ_ጥሉል_አቡነ_አብራኒዮስ ገዳም!

በዐፄ ሱስንዮስ ዘመን የነበረውን የቤተ ክርስቲያንን ጥፋት ላለማየት ሳይወለዱ በእናታቸው ማኅፀን 7 ዓመት ከ6 ወር የቆዩት አቡነ አብራኒዮስ ነሐሴ 21 ቀን በዓመታዊ የዕረፍት በዓላቸው ታስበው ይውላሉ፡፡ አባታቸው ወልደ ክርስቶስ እናታቸው ወለተ ትንሣኤ የሚባሉ ደጋግ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ የተወለዱት በ1624 ዓ.ም ምሥራቅ ጎጃም አካባቢ ልዩ ስሙ እነብሴ ይሁን እንጂ ተጋድሏቸውን ያደረጉትና ገዳማቸውን የገደሙት በዛሬዋ ኤርትራ ውስጥ ነው፡፡ ገዳሙ ኤርትራ ውስጥ ዞባ ድባርዋ ደቂ ድግና በተባለ አካባቢ ይገኛል፡፡ የገደሙት ጻድቁ በ1705 ዓ.ም ነው፡፡

አቡነ አብራኒዮስ የተፀነሱት በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል አብሳሪነት ነው፡፡ ነገር ግን ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ጻድቁ በዐፄ ሱስንዮስ ዘመን የነበረውን የቤተ ክርስቲያንን ጥፋት ላለማየት ሳይወለዱ በእግዚአብሔር ፈቃድ በእናታቸው ማኅፀን 7 ዓመት ከ6 ወር ተቀምጠዋል፡፡ በዚህም ወቅት እሳት ልትጭር ከጎረቤቷ የመጣች አንዲት ሴት የአቡነ አብራኒዮስ እናት ‹‹የማትወልጂው ምን ሆነሽ ነው?›› ብላ ስትናገር ጻድቁ በእናታቸው ማኅፀን ሆነው ‹‹…ለምን ክፉ ትናገሪያለሽ?› ብለው መልስ ሰጥተዋታል፡፡ ይህም ቅዱሳን ልክ እንደ ነቢዩ ኤርምያስ ገና በእናታቸው ማኅፀን ሳሉ እንደሚመረጡ አንድ ማሳያ ነው፡፡

በርካታ ምእመናንን በሰማዕትነት ከገደሉ በኋላ በመጨረሻም ዐፄ ሱስንዮስ በመቅሰፍት ተመተው ሊሞቱ ሲሉ ‹‹ሃይማኖት ይመለስ፣ ፋሲል ይንገሥ›› ብለው የቤ/ክ ሰላም መልሰው ንስሓ ገብተው ሞቱ፡፡ አቡነ አብራኒዮስም ይህ የቤ/ክ የመከራ ዘመን ሲያልፍና ሃይማኖት ሲመለስ ተወለዱ፡፡ ገና በ5 ዓመታቸው ከጥንቆላ መጻሕፍት በቀር ሁሉንም የቤ/ክ መጻሕፍትንና ምሥጢራትን ሁሉ ተምረው ዐወቁ፡፡ በ12 ዓመታቸው መነኮሱ፡፡ ዲቁና ሲሾሙም ጳጳሱ ‹‹ገና ሕፃን ነው፣ አሁን አልሾመውም›› ሲሉ የሰማይ መላእክት ‹‹ይባዋል›› ብለው መስክረውላቸዋል፡፡

በልጅነታቸውም መነኮሳቱ ወደ ጫካ ሔደው ዕንጨት እንዲሰብሩ ሲያዟቸው ጌታችን ግን ለአቡነ አብራኒዮስ ኃይል ሰጥቷቸው በነፋስ ሠረገላ እየሔዱ የ6 ሰዓቱን የእግር መንገድ እሳቸው ግን ዕንጨቱን ሰብረው በቶሎ ይመለሱ ነበር፡፡ ይህም ሲታወቅባቸው ውዳሴ ከንቱን ንቀው ከዚያ ገዳም ወጥተው ወደ አቡነ ተጠምቀ መድኅን ዘንድ ሔዱ፡፡ በዚያም በታላቅ ተጋድሎ ከኖሩ በኋላ አቡነ ተጠምቀ መድኅን ‹‹በአንተ ምክንያት ብዙ ነፍሳት ይድናሉ፣ ክፍልህ በዚያ ነው›› ብለው አሁን ገዳማቸውን ወደገደሙበት ቦታ (ኤርትራ) ላኳቸው፤ ሲመጡም ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል እየመሯቸው እንደመጡ ገድላቸው ይናገራል፡፡ ጻድቁ ወደዚህ ገዳም ሲመጡ በፊት ይቀመጡባት የነበረችው ትልቅ ድንጋይ በተኣምር ከመሬት 7 ክንድ ከፍ ብላ አብራቸው መጥታለች፡፡ ድንጋይዋ ዛሬም ድረስ በገዳማቸው በክብር ስለተቀመጠች ምእመናን እየዳሰሷት ይባረኩባታል፣ መካኖች ይወልዱባታል፣ ሕሙማን ይፈወሱባታል፡፡

አቡነ አብራኒዮስ በቅዳሴ ጊዜ ጌታችንን በዕለተ ዐርብ እንደተሰቀለ ሆኖ ይመለከቱት ስለነበር በኀዘን በተመስጦ ሆነው ይቆዩም ስለነበር ሕዝቡም ‹‹በቅዳሴ ሰዓት ይተኛል›› እያሉ ያሟቸው ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ ጻድቁ ወደ አካለ ጉዛይ በመሔድ በዘንዶ ላይ አድሮ ይመለክ የነበረውን ሰይጣን በጸሎታቸው አጥፍተው ዘንዶውን ገድለው ሕዝቡንም አስተምረው በንስሓ መልሰው አጥምቀዋቸዋል፡፡ ወደ ታላቁ ገዳም ደብረ ቢዘንም ሲሔዱ 6400 አጋንንትን አግኝተው በጸሎታቸው አጥፍተዋቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አቡነ አብራኒዮስ ‹‹ሰዳዴ አጋንንት-አጋንንት አባራሪ›› ተብለዋል፡፡

አቡነ አብራኒዮስ ወደ ሌላ ቦታ ሔደው ሰለዳዋ የምትባል ቦታ ላይ ሆነው ሳለ አንድ ሰው ወደ ገዳማቸው ገብቶ አንዲትን ዛፍ ሲቆርጥ በመንፈስ ቅዱስ መነጽርነት አዩት፡፡ ቆራጩም ሰው ‹‹ተው አትቁረጥ›› የሚል የአባታችንን ድምፅ ሰማ፣ በአካል የሉም ብሎ እምቢ አለ፣ ነገር ግን በመቅሠፍት ተመቶ ወዲያው ሞተ፡፡ በአንድ ዕለትም ልጃገረዶች እየዘፈኑ ሲሔዱ ብዙ አጋንንት በዘፈናቸው ተደስተው አብረዋቸው ሲጨፍሩ አባታችን በመንፈስ ተመልክተው ለልጃገረዶቹ ዘፈን የአጋንንት መሆኑን እንዳስተማሯቸው ገድላቸው ይናገራል፡፡

ለአቡነ አብራኒዮስ ክብርት እመቤታችን ተገልጻ ‹‹ቤተ ክርስቲያን በስሜ አንጽልኝ›› አለቻቸው፡፡ እርሳቸውም ውብ አድርገው በእመቤታችን ስም አነጹ ነገር ግን ፍጻሜውን ሳያዩ በዕለተ ቀኗ ነሐሴ 21 ቀን ዐረፉ፡፡ በዕረፍታቸውም ወቅት ጌታችን ተገልጦ ታላቅ ቃልኪዳን ሲሰጣቸው ‹‹...ዋስ እፈልጋለሁ፣ ዋስ ስጠኝ›› አሉት፡፡ ጌታችንም ‹‹ሐዋርያት፣ ሰማዕታት፣ ከአንተ በፊት የነበሩ ጻድቃን ያልጠየቁኝን አንተ እንዴት ጠየከኝ?›› አላቸው፡፡ እርሳቸውም ‹‹አምላኬ ሆይ! አንተ መሐሪና በጽድቅ ፈራጅ ቃልህም የማይለወጥ እንደሆንክ አውቃለሁ›› አሉት፡፡ ጌታችም ፍግግ ብሎ ‹‹ይሁን የምትሻውን አላሳጣህም›› በማለት ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን በላይ የሆነች ክብርት እመቤታችንንና ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስን ዋስ አድርጎ ቃልኪዳን ከገባላቸው በኋላ ነሐሴ 21 ቀን 1713 ዓ.ም በሰላም ዐረፉ።

የታላቁ ጻድቅ አቡነ አብራኒዮስ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን!!!
✞ ✞ ✞
#ነሐሴ_22

#ነቢዩ_ሚክያስ

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሃያ ሁለት በዚህች ቀን ታላቅ ነቢይ የሞራት ልጅ ሚክያስ አረፈ። ይህም ነቢይ በይሁዳ ነገሥታት በኢዮአታም፣ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን ትንቢት በመናገር አስተማረ።

ስለ #ጌታችን መውረድም እንዲህ አለ። እነሆ #እግዚአብሔር ከልዑል መንበሩ ወደዚህ ዓለም ይወርዳል ።

ሁለተኛም ስለ ልደቱ እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ የኤፍራታ ዕጣ የምትሆኚ አንቺም ቤተ ልሔም የእስራኤል ነገሥታት ከነገሡባቸው አገሮች አታንሺም ወገኖቼ እስራኤልን የሚጠብቃቸው ንጉሥ ከአንቺ ይወጣልና ።

ስለ ምኵራብ መቅረት፣ ስለ ቤተክርስቲያን በዓለም ሁሉ መታነፅ ትንቢት ተናግሯል። ዳግመኛም ስለ ሕገ ወንጌል መሠራት ሕግ ከጽዮን የ #እግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣል አለ። የትንቢቱም ወራት ሲፈጸም ወደ በጎ ሽምግልና ደርሶ ወደ ወደደው #እግዚአብሔር ሔደ።

የትንቢቱም ዘመን ከ #ጌታችን መምጣት በፊት በስምንት መቶ ዓመት ነው። ማርታ በምትባልም ቦታ ተቀበረ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኅ_ነሐሴ)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_22_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሮሜ 11
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁵ ወንድሞች ሆይ፥ ልባሞች የሆናችሁ እንዳይመስላችሁ ይህን ምሥጢር ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ፤ የአሕዛብ ሙላት እስኪገባ ድረስ ድንዛዜ በእስራኤል በአንዳንድ በኩል ሆነባቸው፤
²⁶ እንደዚሁም እስራኤል ሁሉ ይድናል፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፦ መድኃኒት ከጽዮን ይወጣል ከያዕቆብም ኃጢአተኛነትን ያስወግዳል።
²⁷ ኃጢአታቸውንም ስወስድላቸው ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው።
²⁸ በወንጌልስ በኩል ስለ እናንተ ጠላቶች ናቸው፥ በምርጫ በኩል ግን ስለ አባቶች ተወዳጆች ናቸው፤
²⁹ እግዚአብሔር በጸጋው ስጦታና በመጥራቱ አይጸጸትምና።
³⁰ እናንተም ቀድሞ ለእግዚአብሔር እንዳልታዘዛችሁ፥ አሁን ግን ከአለመታዘዛቸው የተነሣ ምሕረት እንዳገኛችሁ፥
³¹ እንዲሁ በተማራችሁበት ምሕረት እነርሱ ደግሞ ምሕረትን ያገኙ ዘንድ እነዚህ ደግሞ አሁን አልታዘዙም።
³² እግዚአብሔር ሁሉን ይምር ዘንድ ሁሉን በአለመታዘዝ ዘግቶታልና።
³³ የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፤ ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፥ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም።
³⁴ የጌታን ልብ ያወቀው ማን ነው?
³⁵ ወይስ አማካሪው ማን ነበር? ወይስ ብድራቱን ይመልስ ዘንድ ለእርሱ አስቀድሞ የሰጠው ማን ነው?
³⁶ ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ጴጥሮስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁹ ከእርሱም ይልቅ እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን፤ ምድርም እስኪጠባ ድረስ የንጋትም ኮከብ በልባችሁ እስኪወጣ ድረስ፥ ሰው በጨለማ ስፍራ የሚበራን መብራት እንደሚጠነቀቅ ይህን ቃል እየጠነቀቃችሁ መልካም ታደርጋላችሁ።
²⁰ ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤
²¹ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 7
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁵¹ እናንተ አንገተ ደንዳኖች ልባችሁና ጆሮአችሁም ያልተገረዘ፥ እናንተ ሁልጊዜ መንፈስ ቅዱስን ትቃወማላችሁ፤ አባቶቻችሁ እንደ ተቃወሙት እናንተ ደግሞ።
⁵²-⁵³ ከነቢያትስ አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን ነው? የጻድቁንም መምጣት አስቀድሞ የተናገሩትን ገደሉአቸው፤ በመላእክት ሥርዓት ሕግን ተቀብላችሁ ያልጠበቃችሁት እናንተም አሁን እርሱን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት ገደላችሁትም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_22_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ወገሠፀ ነገሥተ በእንቲአሆሙ። ወኢትግሥሡ መሲሐንየ። ወኢታሕስሙ ዲበ ነቢያትየ"። መዝ 104፥14-15።
“የቀባኋቸውን አትዳስሱ፥ በነቢያቴም ክፉ አታድርጉ ብሎ፥ ሰው ግፍ ያደርግባቸው ዘንድ አልፈቀደም፥ ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ።” መዝ 104፥14-15።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_22_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 2
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹-² ኢየሱስም በይሁዳ ቤተ ልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰብአ ሰገል፦ የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።
³ ንጉሡ ሄሮድስም ሰምቶ ደነገጠ፥ ኢየሩሳሌምም ሁሉ ከእርሱ ጋር፤
⁴ የካህናትንም አለቆች የሕዝቡንም ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ ክርስቶስ ወዴት እንዲወለድ ጠየቃቸው።
⁵-⁶ እነርሱም፦ አንቺ ቤተ ልሔም፥ የይሁዳ ምድር፥ ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሽም፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መስፍን ከአንቺ ይወጣልና ተብሎ በነቢይ እንዲህ ተጽፎአልና በይሁዳ ቤተ ልሔም ነው አሉት።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #እመቤታችን_ማርያም ወይም የ #ቅዱ_ዮሐንስ_ወልደ_ነጎድጓድ ቅዳሴ ነው። መልካም የነቢዩ የቅዱስ ሚክያስ የዕረፍት በዓል። ለሁላችን ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2024/09/24 15:31:25
Back to Top
HTML Embed Code: