Telegram Web Link
#ነሐሴ_23

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሃያ ሦስት በዚች ቀን በእስክንድርያ አገር ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ሠላሳ ሺህ ሰዎች በሰማዕትነት ሞቱ፣ ሰማዕቱ #ቅዱስ_ድምያኖስ ዕረፍቱ ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#የግብፅ_ሰማዕታት

ነሐሴ ሃያ ሦስት በዚች ቀን በእስክንድርያ አገር ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ሠላሳ ሺህ ሰዎች በሰማዕትነት ሞቱ።

ይህም እንዲህ ነው ንጉሥ መርትያኖስ አባታችን ዲዮስቆሮስን ወደ ደሴተ ጋግራ በአጋዘው ጊዜ ብዙ ዘመናት በእስክንድርያ አገር ሁከትና ብጥብጥ ሆነ።

መርትያኖስም በሞተ ጊዜ በርሱ ፈንታ ልዮን ነገሠ እርሱም አብሩታርዮስ የተባለውን መለካዊ ከሮማውያን ወገን ለእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ሾመ ይህም መለካዊ በኬልቄዶን ጉባዔ የሚያምን ነው ስለዚህም ከጥቂት ግብዞች ሰዎች በቀር የእስክንድርያ ሰዎች አልተቀበሉትም።

ያልተቀበሉትም ሰዎች አስቀድሞ አባታችን ዲዮስቆሮስ ከሾማቸው ቀሳውስት ሥጋውንና ደሙን የሚቀበሉ ሆኑ። ከዚህም በኋላ በቃሉ ለሚያምኑ ባልንጀሮቹ ጉባኤ አደረገላቸውና የክርስቶስ መለኮቱ ከትስብእቱ ተቀላቀለ የሚል አውጣኪን አወገዘው ።

አብሩታርዮስም ይህን ማድረጉ የእስክንድርያን ሰዎች ሸንግሎ ወደ ከፋች እምነቱ ሊስባቸው ወዶ ነው እንጂ ስለዚህ ነገር አባ ዲዮስቆሮስ አውጣኪን አስቀድሞ አውግዞታል። የአባታችን የዲዮስቆሮስ ሃይማኖት እንደ ባስልዮስና ጎርጎርዮስ እንደ ቅዱስ ቄርሎስ ቃል ከሥጋ ጋር ከተዋሐደ በኋላ አንድ አካል፣ አንድ ባሕርይ ብለው እንደሚያምኑ የሚያምን ነውና።

ከጉባኤውም በኋላ የሰበሰባቸው የአብሩታርዮስ ተባባሪዎቹ ወደየቦታቸው ተመለሱ። እርሱም ራሱ አብሩታርዮስ በቤቱ ውስጥ ተገድሎ ተገኘ ለባልንጀሮቹም የአባታችን ዲዮስቆሮስ ደቀ መዛሙርት ወይም የአውጣኪ ባልንጀሮች ወይም ሌቦች ገንዘቡን ለመውሰድ የገደሉት መሰላቸው ይህም እውነት ይመስላል።

የአብሩታርዮስም ባልንጀሮች ወደ ንጉሥ እንዲህ ብለው መልእክትን ላኩ እነሆ የዲዮስቆሮስ ወገኖች የንጉሥን ትእዛዝ በማቃለል ደፍረው የሾምከውን ሊቀ ጳጳሳት ገደሉት። በዚያንም ጊዜ ወንድሞቻችን የእስክንድርያ ሰዎች በላያቸው ጢሞቴዎስን ሊቀ ጵጵስና ሾሙት።

እሊህ መናፍቃንም ከዚህ በኋላ ሁለተኛ እንዲህ ብለው ወደ ንጉሥ መልእክትን ላኩ። እነሆ አብሩታርዮስን የገደሉት ሰዎች አሁንም ያለ ንጉሥ ፈቃድ ደፍረው ሊቀ ጳጳሳት ሾሙ።

ንጉሡም በሰማ ጊዜ ከሁለቱ መልእክቶች የተነሣ እጅግ ተቆጣ። ሰይጣንም በልቡ አድሮ ጭፍሮቹን ልኮ ሃይማኖታቸው ከቀና ወንድሞቻችን ክርስቲያኖች ታላላቆችና ታናናሾች ሠላሳ ሺህ ሰዎች ተገደሉ ጢሞቴዎስንም ወደ ደሴተ ጋግራ አጋዘው በዚያም ሰባት ዓመት ኖረ።

ከአባታችን ዲዮስቆሮስ ደቀ መዛሙርት አንዱ የገደለውስ ቢሆን ስለ አንድ ሰው ፈንታ ሠላሳ ሺህ ሰው መግደል ይገባልን ስለዚህ ከሰይጣን ሥራ እንደሆነ ይታወቃል።

ከዚህ ከከፋ ዕልቂት በኋላም ወንድሞቻችን የሆኑ የዲዮስቆሮስ ደቀ መዛሙርት አብሩታርዮስን እንዳልገደሉት ንጉሡ ተረዳ እጅግም አዘነ ጢሞቴዎስንም ከተሰደደበት መልሶ በመንበረ ሢመቱ አኖረው ታላቅ ክብርንም አከበረው። መንጋውንም እያበረታ ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖረ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ድምያኖስ

ዳግመኛም በዚህች ዕለት ሰማዕቱ ቅዱስ ድምያኖስ ዕረፍቱ ነው፡፡ ይህንንም ቅዱስ የአንጾኪያ አገር መኮንን ይዞ ብዙ አሠቃየው፡፡

በኋላ ቅዱስ ድምያኖስ በእምነቱ መጽናቱን ሲያውቅና ማሠቃየትም በሰለቸው ጊዜ አንገቱን በሰይፍ ቆረጠውና ሰማዕትነት ፍጻሜው ሆነ፡፡ የክብር አክሊንም ተቀዳጀ፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእሊህ ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኅ_ነሐሴ_23)
#ነሐሴ_24

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሃያ አራት በዚህችም ቀን ታላቅ የከበረ ሐዲስ ሐዋርያ #አባታችን_ተክለሃይማኖት አረፈ፣ የከበረች #ቅድስት_ክርስቶስ_ሠምራ የዕረፍቷ መታሰቢያ ነው፣ የክርስቶስ የመርዓስ ኤጲስቆጶስ #ቅዱስ_አባት_ቶማስ_አረፈ

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ጻድቁ_አቡነ_ተክለሃይማኖት

ነሐሴ ሃያ አራት በዚህችም ቀን ታላቅ የከበረ ሐዲስ ሐዋርያ የትሩፋትም መምህር የሆነ አባታችን ተክለሃይማኖት አረፈ። የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም ጸጋ ዘአብ የእናቱ ስም እግዚእ ኀረያ ነው እሊህም ቅዱሳን ለኢትዮጵያ የሃይማኖት ብርሃንን ላበሩ ካህናት ከወገኖቻቸው የሆኑ ናቸው። እግዚእ ኀረያም መካን ስለሆነች ልጅን ይሰጣቸው ዘንድ ወደ #እግዚአብሔር እያዘኑ ሲጸልዩ ኖሩ።

በዚህም ነገር እያሉ የዳሞት ገዥ ሞተለሚን ሰይጣን አነሣሣው የሸዋን አውራጃዎች እስከ ጅማ እስከ ገዛ ድረስ። የሀገር መኳንንቶችም በየተራቸው ሚስቶቻቸውን ይሰጡታል። ከማረከውም ደምግባት ያላቸውን ሴቶች ያገኘ እንደሆነ ቁባቶች ያደርጋቸዋል።

በዚያም ወራት ወደ ጽላልሽ ደርሶ ብዙ ክርስቲያኖችን ገደለ ከእርሳቸውም የሚበዙትን ማረከ ጸጋ ዘአብም ከግድያ ፍርሃት የተነሳ ሸሸ አንድ ወታደርም ተከተለው እርሱም ወደ ባሕር ተወርውሮ ገባ በ #እግዚአብሔርም ፈቃድ በባሕሩ ውስጥ ተሸሸገ።

ሚስቱን እግዚእ ኀረያንም ወታደሮቹ ማረኳት ወደ ሞተለሚም አደረሷት ባያትም ጊዜ ውበቷንና ላህይዋን አደነቀ በልቡም እጅግ ደስ ብሎት ብዙ ሽልማትን ጌጥን ሰጥቷት በሽልማትና በጌጥ ሁሉ ሸለማት አስጌጣትም የጋብቻ ሥርዓትንም ማዘጋጀት ጀመረ ለሠርጉም እንዲሰበሰቡ ወደመኳንንቶቹ ሁሉ ላከ።

እግዚእ ኀረያም ይህን በሰማች ጊዜ ከአረማዊ ጋር አንድ ከመሆን ያድናት ዘንድ በብዙ ልቅሶ ወደ #እግዚአብሔር ጸሎትን አደረገች። ያን ጊዜም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በብርሃናዊ ክንፉ ተሸክሞ ከዳሞት አገር ወደ ምድረ ዞራሬ አድርሶ ወዲያውኑ ወደ ቤተ መቅደስ አስገብቶ በሴቶች መቆሚያ አቆማት። ባሏ ጸጋ ዘአብም ከማዕጠንት ጋራ በወጣ ጊዜ እንደተሸለመች ቁማ አያት አድንቆ በልቡ ይቺ ሴት ምንድን ናት ወደዚህስ ማን አመጣት አለ።

የማዕጠንቱንም ሥራ ጨርሶ ወጣ በጠየቃትና በመረመራት ጊዜ እርሷ ሚስቱ እግዙእ ኀረያ እንደሆነች አገኛት እርሷም ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው #እግዚአብሔር ያደረገላትን ነገረችው።

ከዚህም በኋላ የ #እግዚአብሔር መልአክ በአንዲት ሌሊት ተገለጠላቸው የዜናው መሰማት በዓለሙ ሁሉ የሚደርስ የተባረከ ልጅ ይወልዱ ዘንድ እንዳላቸው ነገራቸው አበሠራቸው።

ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ይህ ቅዱሱ ተፀንሶ በታኀሣሦ ወር በሃያ አራት ተወለደ በጸጋ ዘአብና በእግዚእ ኀረያ ቤታቸው ታላቅ ደስታ ሆነ ከዘመዶቻቸውና ከጐረቤቶቻቸው ጋራ ደስ አላቸው።

ለክርስትና ጥምቀትም በአስገቡት ጊዜ ፍሥሓ ጽዮን ብለው ሰየሙት። ሕፃኑም አደገ ድንቅ ተአምራትንም እያደረገ ዕውቀትንና ኃይልንም ተመልቶ በመነፈስ ቅዱስ ጸና።

ከዚህም በሗላ ዲቁና ይሾመው ዘንድ አባ ጌርሎስ ወደ ተባለ ጳጳስ ወሰዱት በዚያንም ዘመን በዛጔ መንግሥት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ብንያሚን ነበር። ወደ ጳጳሱም በአደረሱት ጊዜ ይህ ልጅ የተመረጠ ዕቃ ይሆናል ብሎ ትንቢት ተናገረለት። የዲቁና ሹመትንም ተቀብሎ ወደ ሀገሩ ተመለሰ።

ጐልማሳ በሆነ ጊዜ አራዊትን ሊያድን ወደ ዱር ሔደ። ቀትር ሲሆንም የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ መልኩ የሚያምር ጐልማሳ አምሳል በቅዱስ ሚካኤል ክነፍ ላይ ተገለጠለትና እንዲህ አለው ወዳጄ አትፍራ እንግዲህ የኃጢአተኞችን ነፍስ ወደ ሕይወት የምታጠምድ ትሆናለህ እንጂ አራዊትን የምታድን አትሆንም ስምህም ተክለ ሃይማኖት ይሁን እንደ ኤርምያስና እንደ አጥማቂው ዮሐንስ እኔ ከእናትህ ማኀፀን መርጬ አከብሬሃለሁና እነሆ በሽተኞችን ትፈውስ ዘንድ ሙታንንም ታሥነሣ ዘንድ ሥልጣንን ሰጠሁህ ርኩሳን አጋንንትንም ከሁሉ ቦታ ታሳድዳቸዋለህ።

ወደ ቤቱም በተመለሰ ጊዜ ገንዘብን ሁሉ ለድኆችና ለምስኪኖች በተነ ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጠፋ ለሰው ምን ይጠቅመዋል እያለ ቤቱን እንደ ተከፈተ ትቶ ምርኩዙን ይዞ በሌሊት ወጣ።

ከዚህም በኋላ ወደ ጳጳስ ሔዶ የቅስና ሹመት ተቀብሎ ለሸዋ አገር ሁሉ ወንጌልን መስበክ ጀመረ። ዐሥራ ሁለት ሽህ ሦስት መቶ ነፍስ ያህል አጠመቀ ለጣፆት የሚሠውበትን ሁሉ ሻረ በውስጡ የሚኖሩ አጋንንት እስከሸሹ ድረስ ዐፀዶቻቸውን ሁሉ ቆረጠ።

ሁለተኛም ወደ ዳሞት ምድር ሔዶ ብዙ ሟርተኞችንና አስማተኞችን ጠንቋዮችን አሳመነ ከሀዲ ሞተለሚም ብዙ ወራት ተቃወመው በጉማሬ ማጥመጃ ውስጥ በመጨመር ብዙ ጊዜ ወደ ገደል ወረወረው እርሱ ግን በደኀና ይመለሳል ደግሞ ሊወጋው ጦር ወረወረ ጦሩም ተመልሶ እጁን ወግቶ ተጠመጠመበት በተሠቃየም ጊዜ አባታችንን ለመነው እርሱም የክብር ባለቤት በሆነ በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አሳምኖ አዳነው የተጠመጠመበትንም ጦር ፈታለት ቀናውን መንገድ የሚያጣምሙ ሟርተኞችንም አጠፋቸው።

ከዚህም በኋላ በክብር ባለቤት #ጌታችን ስም ያደረገውን ድንቅ ተአምራቱን አይተው የአገር ሰዎች ሁሉም ከንጉሣቸው ጋራ አመኑ የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው ቤተ ክርስቲያንም ሠርቶላቸው የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት አስተማራቸው በቀናች ሃይማኖትም አጸናቸው ከዚህም ሁሉ ጋራ በጾም በጸሎት በስግደት ሁልጊዜ ያለ ማቋረጥ ተጠምዶ ይጋደል ነበር።

ዜናውንም ሰምተው ወደርሱ የሚመጡትን የነፍሳቸውን ድኀነት ያስተምራቸዋል የክብር ባለቤት የሆነ #ጌታችን_ኢየሱስን በማመን ያጸናቸዋል።

ከዚህ በኋላ በኤልያስ ሠረገላ ተቀምጦ ወደ አምሐራ ሀገር ሔደ በገድል ተጸምዶ ወደሚኖር መነኰስ ወደ አባ በጸሎተ ሚካኤል በአንዲት ቀን ደርሶ በዚያ እንደባሪያ ሲያገለግል ኖረ በአንድነት የሚኖሩ መነኰሳትንም ያገለግላቸው ነበር የሞተውንም እስከማንሳት ድረስ ከደዌያቸው ይፈውሳቸው ነበር።

በዚያም ዐሥራ ሁለት ዓመት ከሆነው በሗላ ሐይቅ በሚባል ቦታ ወደሚኖር ወደ ኢየሱስ ሞዓ የ #እግዚአብሔር መልአክ እንዳዘዘው ሔዶ ከእርሱም የምንኲስና ልብስ ቀሚስና ቅናትን ተቀበለ። ከዚያም ወደ ደብረ ዳሞ ሔዶ ለአቡነ አረጋዊ አራተኛ ከሆነ ከአባ ዮሐኒ ዘንድ ቆብንና አስኬማን ተቀበለ። ሁለተኛም ወደ ኢየሩሳሌም ሒዶ ከከበሩ ቦታዎችና ከሊቀ ጳጳሳቱ ቡራኬን ተቀበለ።

በዚያም ወደ ሸዋ ምድር ተመልሶ የአባቱ ወንድም ልጅ የሆነ አባ ዜና ማርቆስን አገኘው በወግዳ በረሀም በአንድነት ኖሩ ከዚያም ግራርያ ወደ ሚባል አገር ሒዶ በኮረብታ መካከል ዋሻ አዘጋጅቶ ተቀመጠ በቀንም በሌሊትም ከዚያ አይወጣም ነበረ ከጥቂት ቅጠልም በቀር እህልን አይቀምስም መጠጡም ጥቂት ውኃ ነው።

ብዙ ወንዶችና ሴቶች ወደርሱ መጥተው መነኲሳቶች ሆኑ በአንድ ቤት ውስጥ በአንድ መኝታ ላይ ተኝተው ያድራሉ እርስበርሳቸውም አይተዋወቁም እነርሱም እንደ ሕፃናት ናቸው በጸሎትና በቅዳሴ ጊዜም በአንድነት ይቆማሉ በዘመኑ ሰይጣን ሰለ ታሠረ ወንዱ ሴቷን ሴት እነደሆነች አያውቅም እንዲሁም ሴቷ ወንዱን ወንድ እንደሆነ አታውቅም።

በዚህም በኋላ መጠጊያ ሠርቶ በፊቱ በሗላው በቀኙ በግራው የተሳሉ ፍላጻዎችን ተከለ ይህንም ማድረጉ በመደገፍና በመተኛት እንዳያርፍ ነው በዚያም እግሩ ከቅልጥሙ እስቲሰበር ሰባት ዓመት ቆመ። በዚያም ወራት ምንም የዕንጨት ፍሬ ወይም ቅጠል ሳይቀምስ ውኃም ሳይጠጣ ኖረ።
ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርቶስ ወደርሱ መጣ ከእርሱም ጋራ እመቤታችን #ቅድስት_ድንግል_ማርያም ደግሞ የከበሩ ነቢያትና ሐዋርያት ሁሉም ሰማዕታትና ጻድቃን የጳጳሳት አለቆች የመላእክት አለቆችም ከሠራዊቶቻቸው ጋራ አሉ።

#መድኃኒታችንም እንዲህ አለው ወዳጄ ሆይ አንተ በመከራዬ መሰልከኝ እኔም በመንግሥቴ ከእኔ ጋራ እንድትመስለኝ አደርግሃለሁ። እነሆ የዚህ ዓለም ድካምህ ተፈጸመልህ በእኔ ዘንድም የምቀበለው ሆነ ከእንግዲህስ መንግሥተ ሰማያትን ትወርስ ዘንድ ና። እነሆ ስምህን ለሚጠራ መታሰቢያህን ለሚያደርግ ገድልህን ለሚጽፍ ለሚያነበውና ለሚሰማውም ቤተ ክርስቲያንህን ለሚሠራ በስምህ መባ ለሚሠጥ ለድኆችም በስምህ ለሚመጸውት በመታሰቢያህም ቀን ለሚቆርብ ስለ አንተ በጎ ሥራ ለሚሠራ ሁሉ እኔ እስከ ዐሥር ትውልድ እምርልሃለሁ።

አባታችንም እጅግ ደስ አለው ለ #ጌታችንም ሰገደ #ጌታችንም ከእርሱ ዘንድ በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ። ከዚህም በኋላ አባታችን በንዳድ በሽታ ታመመ ዕድሜውም ዘጠና ዘጠኝ ዓመት ከስምንት ወር ከአንድ ቀን ሆኖት በለመለመ ዕርጅና አረፈ። በመዘመርና በማመስገን አክብረው ገንዘው በዋሻው ውስጥ ቀበሩት።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባታችን በአቡነ ተክለ ሐይማኖት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።


✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ክርስቶስ_ሠምራ

በዚህች ቀን ደግሞ ኢትዮጵያዊት የሆነች ተጋዳይ የከበረች ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ የዕረፍቷ መታሰቢያ ነው፡፡ በሸዋ ከፍለ አገር በቡልጋ አውራጃ ልዩ ስሟ ቅዱስ ጌዬ የተባለች አገር ነበረች ይህችም የእናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ የትውልድ አገሯ ናት። በዚህም አገር በወርቅና በብር በሐር እና በልዩ ልዩ ልብስ በወንድና በሴት አገልጋዮች በፈረስና በበቅሎ የከበረ አንድ ስሙ የታወቀ ሰው ነበር። የዚህ ሰው ስሙ ቅዱስ ደረሳኒ ሲሆን የሚስቱም ስም ቅድስት ዕሌኒ ይባላል ሁለቱም ባልና ሚስቱ እግዚአብሔር የሚፈሩ ደጋግ ሰዎች ስለነበሩ በጎ ሥራቸው በዓለም ሁሉ የታወቀ ነበር። እሊህም ሰዎች በእግዚአብሔር ዘንድ የተመረጠችና የከበረችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራን ወልደው በደም ግባቷና በጠባይዋ እየተደሰቱ አሳደጓት ከዚያም የእግዚአብሔርን ሕግጋትና ሥርዓቶችንም ሁሉ አስተማሯት። ባደገችና ለአቅመ ሔዋን በደረሰች ጊዜ የንጉሥ ባለሟል የሆነ ትውልዱ፤ ነገዱ ከአባ ፃሠርጓ ወገን የሆነ ለኢየሱስ ሞዓ ልጅ ለሠምረ ጊዮርጊስ በሕግ አጋቧት። እሱም በዚህ ዓለም ገንዘብ በጣም የከበረ ከመሆኑም በላይ በይበልጥ መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰው ነበረ። ከደም ግባቷ የተነሣ ሙሽራይቱ ማለት እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራን እጅግ አድርጎ ወደዳት። አሟቷ ኢየሱስ ሞዐም ይህች ብላቴና "በታላቅ ቁም ነገር የተመረጠች ነች" በማለት ትንቢት ይናገርላታል ስለዚህ እንደ እመቤቱ አድርጐ ያከብራት ነበር። ከዚህም በኋላም ለሕጋዊ ባሏ ለሠምረ ጊዮርጊስ ዓሥራ አንድ ልጆች ወለደችለት ከነዚህም መካከል ዘጠኙ ወንዶች ሁለቱ ሴቶች ነበሩ። ልጆችዋንም ሕገ እግዚአብሔርን እያስተማረች በክብር በሥርዓት አሳደገቻቸው።

በዚያን ዘመን የእግዚአብሔር ባለሟል የሚሆን ዓፄ ገብረ መስቀል የሚባል የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ነበር። እርሱም ዝናዋን ሰምቶ ሥነ ምግባሯን ተመልክቶ ይልቁንም በሷ ላይ ያደረውን ኃይለ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ስለገለጸለት እጅግ አድርጐ ይወዳትና ያከብራት ነበር። ከዕለታት ባንድ ቀን በጸሎትሽ አስቢኝ በማለት በራሱ በንጉሡ ቤተ መንግሥት ከሚያገለግሉ አገልጋዮች ወይም ሠራተኞች መካከል እንዲያገለግሏት 174 አገልጋዮች ላካላት። ዳግመኛም ፈረስና በቅሎ ከነሥራታቸው እንደዚሁም ለነሥታት ሚስቶች የሚገባ ከሐርና ከወርቅ የተሠራ ልብስና የወርቅ ጫማ ላከላት። ነገር ግን እሷ ይህን ሁሉ ክብር አልፈለገችም ይልቁንም ለዓላማየ ዕንቅፋት ወይም ከንቱ ውዳሴ ይሆንብኛል በዚያውስ ወርቁ ጌጡ ልብሱ ተሸጦ ለነዳያን ይመጸወታል ለቤተ ክርስቲያን መባዕ ይሰጣል እኒህን አገልጋዮች ግን ምን አደርጋቸዋለሁ በማለት ወደ እግዚአብሔር እያመለከተች ቆየች።

ከአገልጋዮችዋ መካከል ምግባሯ የከፋ የምታናድዳትና የምታበሳጫት አገልጋይ ነበረች። #እግዚአብሔርም አገልጋይዋን ቀሰፋት ብፅዕት ክርስቶስ ሠምራም ደንግጣ ካለችበት ቤት ውስጥ ወደ ሌላው ክፍል ገባችና ወደ ሰማይ አቅንታ "ወይኔ ወዮልኝ ወዮታ አለብኝ የካህን ሚስት ስሆን ነፍስ ገዳይ ሆኛለሁና። ሰውስ ምን ይለኛል ለነፍሴስ ምን እመልስላታለሁ ከእግዲህ ከክርስቲያን ወገን ልቆጠር አይገባኝም በደሌንስ እንደምን አድርጌ ልሸሸሽጋት እችላለሁ" እያለች አለቀሰች።

ከዚህ በኋላ እንዲህ ስትል ለ #እግዚአብሔር ብፅዓት አደረገች "አቤቱ ይህችን በእኔ እጅ የሞተችውን አገልጋይ ነፍስዋን ከሥጋዋ አዋህደህ ብታሥነሣልኝ ልጆቼን ቤቴን ንብረቴን ትቼ ባለ ዘመኔ ሁሉ አንተን እከተላለሁ። አንተን ከመከተል ከቶ ወደኋላ አልልም። ለሰውነቴ ጌጥ ወይም ግርማ ሞገስ የሚሆናት ወይም የሚሞቃት ልብስ ከቶ አልለብስም ሥጋዬን የሚያረካ ምግብም አልመገብም። አቤቱ ጌታዬ ሆይ ጸሎቴን ስማኝ ልመናዬም በፊትህ ፈጥኖ ይድረስ አቤቱ ፊትህን ከኔ ከባሪያህ አትመልስ"። እንዲህ እንዲህ እያለች በልቅሶና በኀዘን ለብዙ ሰዓት ከጸለየች በኋላ ድካም ተሰማትና ዕረፍት አደረገች። ከዚህ በኋላ ቤተሰቦችዋ እስዋ ወዳለችበት ክፍል መጥተው "እመቤታችን ሆይ ሙታ የነበረችው አገልጋይሽ በ #እግዚአብሔር ኃይልና በአንቺ ጸሎት ተነሥታለችና ደስ ይበልሽ" አሏት። በዚህ ጊዜ ፈጥና ተነሥታ ደስ እያላት ሙታ የነበረችው አገልጋይ ካለችበት ቦታ ደረሰችና ሕይወት አገኘቻት ከዚያም ቃሏን ከፍ አድርጋ "ልመናዬን ቸል ያላለ ቸርነቱንም ከኔ ከባሪያው ያላራቀ ፈጣሪ ይክበር ይመስገን" ብላ በታላቅ ምስጋና #እግዚአብሔር አመሰገነች።

ከዚህ በኋላ አስቀድሞ ከአፏ የወጣውን ከአንደበቷ የተነገረውን ቃል አስባ ልብሰ ምንኵስናዋን ማለት ቆቧን ቀሚሷን አጽፏን መታጠቂያዋን አዘጋጀች። ቤተሰቦቿና አገልጋዮቿም "እመቤታችን ሆይ ይህ የምታዘጋጂው የምናኔ ልብስ ለምንሽ ነው ወይስ ለማን ነው የምታዘጋጂው" አሏት። እርሷም " ሃይማኖት ያስተማሩኝ አባቴ ልብስ አልቆባቸዋል ሲሉ ሰምቼ ለሳቸው ነው የማዘጋጀው" አለቻቸው።

ከዚህም በኋላ ከዕለታት ባንደኛው ቀን እናታችን ክርስቶስ ሠምራ አገልጋዮቿን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንሄድ ዘንድ ተዘጋጁ አለቻቸውና እነሱም አሺ በጎ ብለው አጅበዋት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄዱ። ከዚያም እንደደረሱ "በሉ እንዲህ እኔ ከዚህ ጥቂት እቆያለሁና እናንተ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ ለኔ ይህች አንድዲት አገልጋይና ይህ ሕፃን ልጅ ብቻ ይበቁኛል አለቻቸው። በዚያኑ ጊዜ አገልጋዮቿ እጅ እየነሱ ወይም እየተሰናበቱ ወደቤታቸው ተመለሱ። ከዚያም ከዳዊት መዝሙር "ልቤ ጽኑ ነው አቤቱ ልቤ ጽኑ ነው #እግዚአብሔርን ፈጽሜ አመሰግነዋለሁ #እግዚአብሔር የደህንነቴ መብራት ስለሆነ ምን ያስደነግጠኛል #እግዚአብሔር የሕይወቴ መተማመኛ ነው ምንስ ያስፈራኛል የሚለውን እየጸለየች የሚያልፈን ዓለም በማያልፈው ዓለም ለመተካት ወይም ለመለወጥ አውጭኝ እግሬ ብላ ገሠገሠች። ያ በልስላሴና በእንክብካቤ የኖረ እግር ከመንገዱ ብዛት እንደዚሁም ከቅርቅፍቱና ከእንቅፋቱ የተነሣ ፈለግ ሲያወጣ ሥጋውን እየቆረጠች ስትጥለው ደሙ እንደጒርፍ ውሃ ይወርድ ነበር። ያች የተከተለቻት አገልጋይ ግን ከእመቤቷ እግር እየተቆረጠ የሚወድቀውን የአካል ቊራጭ እያነሳች በልብሷ
ትቋጥረው ነበር። በዚህ ዓይነት ችግርና ፀሐይ ሐሩር የብዙ ጐዳና ጉዞ ተጉዛ ከአሰበችበት አገር ደረሰች። በደብረ ሊባኖስ አቅራቢያ ወይም አካባቢ ስትደርስ የራስ ፀጒራን ይዛው በነበረ ምላጭ ላጨች ልብሷንም አውልቃ ለነዳያን አከፋፈለች የያዘችውንም ገንዘብ በመንገድ ላይ ላገኘችው ሁሉ መፅውታ ጨረሰች። ከዚያም አስቀድማ ያዘጋጀችውን ልብስ ምንኵስና ማለት ቀሚስዋን አጥልቃ አጽፋን ተጐናጽፋ ቆቧን ደፍታ ደብረ ሊባኖስ ከሴቶች ገዳም ደረሰች። የገዳሙ መነኰሳትም በታላቅ ክብር ተቀብለው ወደበዓታቸው አስገቧት ...

እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ለሳጥናኤል ምሕረት እንደለመነች፦ ከዕለታት በአንድኛው ቀን እናታችን ክርስቶስ ሠምራ ጓንጉት በምትባል ደሴት ውስጥ ዓርብ ዕለት ከቀኑ በስድስት ሰዓት ላይ ስለሰው ልጆች ስትጸልይ ሣለ። ዓለሙ ሁሉ ከንቱ እንደሆነና የሰውም ልጅ ሕይወት እንደጥላ ኃላፊ ጠፊ መሆኑን ፈጽማ ተመለከተች። ነቢዩ ዳዊት "ሰው ከንቱ ነገርን ይመስላል ዘመኑ ወይም ሕይወቱ እንደጥላ ያልፋል" ሲል ተናግሯልና። ዳግመኛም "ሰው ክብር እንኳ ቢሆን ሊኖር አይችልም እንደሚጠፋ ወይም ማስተዋል እንደሌለው እንስሶች መሰለ... አለ ክቡር ዳዊት። ስለዚህም ሁሉ ነገር አቤቱ ማራቸው ይቅርም በላቸው መፃተኛዋ ባሪያህንም ኃጢአቷን አታስብባት እያለች ወደፈጣሪዋ መሪር ዕንባን አለቀሰች። ያን ጊዜ #ጌታ_ኢየሱስ_ክርስቶስ በታላቅ ግርማ ወደስዋ መጣ። በታላቅ ግርማ ሆኖ ባየችውም ጊዜ ደነገፀች ከእግሩ ሥርም ወደቀች። ከዚህ በኋላ ነውር በሌለባቸው ንዑዳት ክቡራንና ንጹሐን በሆነ እጆቹ አነሣት። ቀጥሎም "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ አትደንግጭ ነገር ግን የልብሽን ሃሳብ ንገሪኝ" አላት። እስዋም "አቤቱ ባሪያህንስ በባለሟልነት ካሠለጠንካት አባታችን አዳምን በአርአያህና በአምሣልህ ስለምን ፈጠርከርው። በእንጨት መስቀልስ ላይ ለምን ተሰቀልክ ስለአዳምና ስለልጆቹ አይደለምን?" አለችው። "አዋን ስለነሱ ስል ተሰቅያለሁ" አላት። "እግዲያውስ መሰቀልህ ወይም የተሰቀልከው ስለነሱ ከሆነ ከአቤል ጀምሮ እስከ ዛሬ የሞቱን ከዛሬም በኋላ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የሚሞቱትን አቤቱ ማራቸው ይቅርም በላቸው" አለችው። "አንተ ቸር ይቅር ባይ መዓትህ የራቀ ምሕረትህ የበዛ ነህና ከአንተ ሌላ አምላክ የሌለ እውነተኛ አምላክ ነህ ሁሉ ይቻልሃልና የሚሣንህ ነገር ከቶ የለምና ዓለም በጠቅላላዋ በእፍኝህ አትሞላም" በማለት እያለቀሰች ለመነችው። በዚያ ጊዜ #ጌታ መልሶ "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ እስኪ አንቺ ራስሽ ፍረጅ አዳም ከነልጆቹ ከሠራው ኃጢአት እና እኔ በጰንጤናዊው በጲላጦስ ዘመን በቀያፋና በሐና አደባባይ በዕለተ ዓርብ ከተቀበልኩት ሕማማተ መስቀል ቢመዘን የትኛው ይመዝን ይመስልሻል?" አላት። ይህንም ባላት ጊዜ ደነገጠችና ከመሬት ላይ ወደቀች። በዚህ ጊዜ ቅዱሳት በሆኑ እጆቹ ከወደቀችበት አነሣትና "እንግዲህ ይህን ሁሉ መከራ የተቀበልኩ ለማን ወይም በማን ምክንያት ይመስልሻል" አላት።

#ጌታም "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ እስኪ የልብሽን ሃሳብ ወይም ፍላጐትሽን ንገሪኝ" አላት። በዚህን ጊዜ "አቤቱ ፈጣሪየ ፈቃድህስ ቢሆን የአዳም ልጆች ከሥቃይ ከኵነኔ ይድኑ ዘንድ ዲያብሎስን ይቅር ትለው ወይም ትምረው ዘንድ እለምንሃለሁ። የኃጥእን መመለሱን እንጂ ጥፋቱን አትወድምና" አለችው። "የምለምንህ ወይም ማረው የምልህ ዲያብሎስን ወድጄው አይደለም ነገር ግን እርሱ ከተማረ በአዳም ልጆች ላይ ሥቃይና ኵነኔ ሊኖር አይችልም ብየ በመገመት እንጂ። የነሱ ሥጋ ሥጋየ እንደሆመኑ መጠን የኔም ሥጋ ሥጋህ ነውና" አለችው። ይህንም ባለችው ጊዜ ጌታ ፍግግ ብሎ "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ሌሎች ካንቺ በፊት የነበሩ ካንቺም በኋላ የሚነሱ የማያስቡትን እጅግ የሚያስደንቅ ልመና አቀረብሽ" አላት። ይህንም ካለ በኋላ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ጠርቶ "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ዲያብሎስን ማርልኝ ስትል ልመና አቅርባለችና እሺ ካላት ታወጣው በንድ ወደሲዖል ይዘሃት ሂድ" ብሎ አዘዘው። በዚህ ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል እሺ ብሎ ሰግዶ እጅ ነሥቶ ወደሲዖል ይዞአት ሄደ። አብረው በሚጓዙበትም ጊዜ "እንግዲህ ዲያብሎስ ከታረቀ ወይም ከተማረ የሰው ልጆች ሁሉ ያርፋሉ" እያለች ለመላእክት አለቃ ለቅዱስ ሚካኤል ታሳስበው ነበር። ይህን አምላክነትን ሲሻ ከክብሩ የተዋረደ ዲያብሎስ ምሕረት ለማግኘት ይሻ መስሏት ነበርና።

ከሲዖል አፋፍ በደረሱም ጊዜ የተመለከተችው ሥቃይ ተነግሮ የማያልቅ ነው ሰዎች ከሰዎች ጋር እንደውሻ ይናከሱ ነበር። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል "ምሕረት የሚፈልግ ከሆነ እስኪ በይ ዲያብሎስ ብለሽ ጥሪው" አላት። በዚህ ጊዜ በመላእክት ቋንቋ ሦስት ጊዜ "ሣጥናኤል ሣጥናኤል ሣጥናኤል" በማለት ጠራችው። ዲያብሎስም "ከዚህ በብዙ ሠራዊት ላይ ነግሼ ከምኖርበት አገር ማን ነው እሱ የሚጠራኝ" እያለ በታላቅ ቃል አሰምቶ ተናገረ። ከዚህም በኋላ "ለብዙ ዘመን ስፈልግሽ ወይም ሳድንሽ ቆይቼ ነበር ዛሬ ግን ከምኖርበት ቤቴ ድረስ መጣሽን" አላት። እርሷም "ጌታ ይቅርታ አድርጓልሃልና ከዚህ ከሥቃይና ከመከራ ቦታ ከወገኖችህ ጋራ ና ፈጥነህ ውጣ" አለችው። ይህንም በለችው ጊዜ ልቡ እንደ እሳት ነደደ አፈፍ ብሎ ተረማምዶ በግራ እጁዋን ይዞ ከሲዖል ረግረግ ውስጥ ወረወራት። በዚያን ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል የእሳት ሰይፍ ይዞ ከኋላ ከኋላዋ ይከተላት ነበርና ይህን ምሕረት የሌለው ዕቡይ ዲያብሎስ በያዘው ሰይፍ ቢቀጣው የሲዖል ደጃፍ ተከፈተች። በዚህ ሰዓት ታላቅ ጨኸትና ውካታ ወይም መደበላለቅ ሆነ በሲዖል ያሉ የሰዎች ነፍሳት እንደንብ ከበቧት ወይም ሠፈሩባት። በዚያን ጊዜ በቅዱስ ሚካኤል ክንፍና በስዋም በተሰጣት ክንፈ ረድኤት ከሲዖል የወጡት ነፍሳት ቁጥር ዓሥር ሺህ ያህል ነበር። እነዚህ ከመከራ ያመለጡ ከሥቃይ የወጡ ነፍሳትን ባየች ጊዜ እጅግ አድርጋ ተደሰተች ከደስታዋም ብዛት የተነሣ የእናቱን ጡት እየጠባ እንደሚዘል እምቦሳ ጥጃ በመካከላቸው ትዘል ነበር።

ከዚህም በኋላ ወደ ፈጣሪዋ ሄዳ "አቤቱ ፍርድህ ከቶ እንደዚህ ነውን?" እያለች አደነቀች። #ጌታም "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ዲያብሎስን ድል አድርገሽ ጥቂት ምርኮን አገኘሽን" አላት። እስዋም "አዋ #ጌታዬ በኃይልህና በቸርነትህ አገኘሁ" አለችው። ከዚህ በኋላ #ጌታ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ቅዱስ ሚካኤል ጠርቶ "እሊህን ነፍሳት ዓለም ሳይፈጠር ወደ አዘጋጀሁላት ወደ ክርስቶስ ሠምራ መኖሪያ ቦታ ውሰዳቸው" አለው። በዚህ ጊዜ "አቤቱ ፈጣሪየ የእኔ መኖሪያየ ወዴት ነው?" አለችው። #ጌታም "መኖሪያሽ ከእናቴ ከድንግል #ማርያም ጋራ ነው እነሆ በትረ ማርያም ብየ ሰየምኩሽ መቀመጫሽን ወይም ደረጃሽን ከእርስዋ ቀጥሎ ሁለተኛ አደረግሁልሽ የባለሟልነት ግርማ አጐናጸፍኩሽ አንቺን የሚወዱ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው" አላት። ይህንም ባላት ጊዜ ፈጽማ ደስ ተሰኘች ወደ ኋላዋም መለስ ብላ ብትመለከት ለዓይን የሚያንፀባርቁ ዓሥር አክሊላት አየች። በየአንዳንዳቸው አክሉል ላይ ዐራት ከዋክብት አሉባቸው የእሊህ ከዋክብት ቊጥራቸው ሲደመር አርባ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ከስዋ ጋራ የነበረውን መልአክ "እሊህ በላያቸው ብርሃናውያን ከዋክብት ያሉባቸው አክሊላት ለማን የተዘጋጁ ናቸው ሰውነቴ እጅግ አድርጋ ወዳቸዋለችና" አለችው። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም "ላንቺ ቢሆን ደስ አይልሽምን?" አላት። እርስዋም "አዎን ጌታየ ለኔ ቢሆን እወዳለሁ" አለችው። "እንግዲያስ ላንቺ የተዘጋጁ ናቸው" አላት።
"በምን ሥራዬ ለኔ ተሰጡኝ" አለችው። "ዐሠርቱ ቃላት ኦሪትን ስድስቱን ቃላተ ወንጌል ጠብቀሽ ቤትሽን ጥለሽ ይህን ዓለም ንቀሽ አጥቅተሽ የ #ክርስቶስን ቀምበር ተሸክመሽ ፈጣሪሽን ስለተከተልሽው ነው" አላት። ይህንንም በአላት ጊዜ እጅግ አድርጋ ተደሰተች ሁሉን ማድረግ የሚችል #እግዚአብሔርንም ፈጽማ አመሰገነች።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም እኛንም በቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ቶማስ_ዘመርዓስ

ዳግመኛም በዚህች ቀን የ #ክርስቶስ ምስክሩና ሐዋርያው የሆነ የመርዓስ ኤጲስቆጶስ ተጋዳይ ቅዱስ አባት ቶማስ አረፈ። የዚህንም አባት ትሩፋቱንና ገድሉን ሰው ተናግሮ ሊፈጽመው አይችልም እርሱ አስቀድሞ በጾም በጸሎት በስጊድ ቀንና ሌሊትም በመራራት ተጠምዶ የሚኖር ነው ። ከዚህም በኃላ መርዓስ ለሚባል አገር ኤጲስቆጶስ ይሆን ዘንድ የክብር ባለቤት #ጌታችን መረጠው መንጋውንም እንደ ሐዋርያት ጠበቀ ። ከሀዲ ዲዮቅልጥያኖስም በነገሠ ጊዜ ክርስቲያኖችን ያሠቃያቸው ዘንድ ከመኳንቶቹ አንዱ ወደዚያች አገር ደረሰ እርሱም ቅዱስ ቶማስን ወደርሱ ያቀርቡት ዘንድ ጭፍሪቹን ላከ እነርሱም እየደበደቡ በምድር ላይ እየጎተቱ ወሰዱት ደሙም እንደውኃ ፈሰሰ ።

ከዚህም በኃላ መኮንኑ ቅዱስ ቶማስን ለአማልክት ስገድ አለው ቅዱሱም እንዲህ ብሎ መለሰለት እኔ ከሕያው #እግዚአብሔር ልጅ ከ #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ በቀር ለረከሱ ጣዖታት የሚሰግድ ሁሉ የተረገመ ነውና ።

መኰንኑም ተቆጥቶ እጅግ የበዛና ዕፁብ ድንቅ የሆነ ሥቃይን አሠቃየው የነዳጅ ድፍድፍና አፍልተው በላዩ በአፉና በአፍንጫው ውስጥ ጨመሩ እንዲህም እያደረጉበት እስከ ብዙ ዘመናት ኖረ።

የእሊህ ከሀዲያን ልባቸው እንደ ድንጊያ የጸና ስለሆነ ቅዱስ ቶማስ ቶሎ እንዲሞት አልፈለጉም። ሌሎች ብዙዎች ሰዎችን ያሰፈሩአቸው ዘንድ የክብር ባለቤት #ክርስቶስንም ይክዱት ዘንድ የሥቃዩን ዘመን አስረዘሙ እንጂ።

እርሱ የክብር ባለቤት በሆነ በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ኃይል የጸና ነውና ማሠቃየቱን ከሀድያን በተቸነፉ ጊዜ ስለ ስሕተታቸውም ይዘልፋቸው ስለነበር ስለዚህ በጨለማ ቦታ ጣሉት በዚያም ሃያ ሁለት ዓመት ኖረ።

ከሀድያንም በየዓመቱ ወደርሱ ገብተው ከሕዋሳቱ አንዱን ይቆርጣሉ። በዚያም ቦታ አፍንጫውን ከንፈሮቹን ጆሮዎቹን እጆቹንና እግሮቹን ቆረጡ መንጋዎቹም ያረፈ መስሏቸው በየዓመቱ መታሰቢያውን ሲያደርጉ ኖሩ። ነገር ግን አንዲት ክርስቲያናዊት ሴት በጣሉት ጊዜ ስለአየችው ቦታውን ታውቅ ነበር እርሷ በሌሊት ወደርሱ ተሠውራ በመሔድ ትመግበዋለች ። ጻድቅ ቁስጠንጢኖስም እስከ ነገሠና የቀናች የ #ክርስቶስን ሃይማኖት ክብር እስከ ገለጠ ድረስ እንዲህ ሲሠቃይ ኖረ።

ይህም ንጉሥ #ክርስቶስን በመታመን የታሠሩ እሥረኞችን ሁሉ በሀገሮች ሁሉ በወህኒ ቤት ያሉትን ይፈቷቸው ዘንድ አዘዘ።

ይችም ሴት ሒዳ ስለ ቅዱስ ቶማስ ከእርሱ የሆነውን ሃያ ሁለት ዓመት ተጥሎ እንደኖረ ለካህናቱ ነገረቻቸው በውስጡ ወደሚኖርበትም ቦታ መራቻቸው። እነርሱም አንሥተው ተሸከሙት እየዘመሩና እያመሰገኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን አደረሱት በቤተ መቅደሱም ፊት ለፊት በወንበሩ ላይ አስቀመጡት ምእመናንም ሁሉ ወደርሱ እየመጡ ከእርሱ ይባረኩና የተቆረጡ ሕዋሳቱን ይሳለሙ ነበር።

ንጉሥ ቂስጠንጢኖስም የከበሩ የሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ኤጲስቆጶሳትን የአንድነት ጉባኤን በኒቅያ አገር በሰበሰበ ጊዜ ይህ የከበረ ቶማስ ከእሳቸው አንዱ ነው።

ንጉሡም ወደ እንርሱ ገብቶ ሰላምታ ሰጣቸውና ከእርሳቸውም ቡራኬ ተቀበለ። የዚህ የቅዱስ ቶማስን ተጋድሎውን በነገሩት ጊዜ ወደርሱ ቀርቦ ሰገደለት ሕዋሰቱም ከተቆረጡበት ላይ ተሳለመው አዝኖና እጅግም አድንቆ ሕዋሳቱን ዳሠሠው ፊቱንና ዐይኖቹን አሻሸው።

ከሀዲ አርዮስንም ተከራክረው ከረቱ በኃላ አውግዘው ለይተው ከወገኖቹ ጋር ከቤተ ክርስቲያን አሳደዱት። ከዚህም በኃላ #መንፈስ_ቅዱስ እንደ አስተማራቸውና እንደመራቸው የሃይማኖትን ትምህርት በአንደበታቸው ተናገሩ ሕግና ሥርዓትን ሥጋዊና መንፈሳዊ ፍርድንም ሠሩ።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ቶማስ ወደ መንበረ ሢመቱ ሔደ ካህናቱንና መንጋዎቹን ሁሉ ሰብስቦ አነበበላቸው እርሱንም እንዲአስተውሉት እንዲጠብቁትም በመጠበቅም እንዲጸኑ አዘዛቸው። ጥቂት ዘመናትም ከኖረ በኃላ በሰላም በፍቅር አረፈ የሹመቱም ዘመን አርባ ዓመት ነው በዚህም #እግዚአብሔርን አገለገለው።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ቶማስ ጸሎት ይማረን። በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኅ_ነሐሴ_24 እና #ገድለ_ቅድስት_ክርስቶስ_ሠምራ)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_24_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሮሜ 8
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³⁵ ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን?
³⁶ ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው።
³⁷ በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።
³⁸ ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥
³⁹ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ እንግዲህ እኔ፥ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ የክርስቶስም መከራ ምስክር ደግሞም ሊገለጥ ካለው ክብር ተካፋይ የሆንሁ፥ በመካከላቸው ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ፤
² በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤
³ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ፤
⁴ የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ።
⁵ እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 20
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁸ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።
²⁹-³⁰ ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ።
³¹ ስለዚህ ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሠጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_24_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"እስመ በእንቲአሁ ይቀትሉነ ኵሎ አሚረ። ወኮነ ከመ አባግዕ ዘይጠብሑ። ንቃህ እግዚኦ ለምንት ትነውም"። መዝ 43፥22-23
"ስለ አንተ ሁልጊዜም ተገድለናል፥ እንደሚታረዱም በጎች ሆነናል። አቤቱ፥ ንቃ፤ ለምንስ ትተኛለህ? ተነሥ፥ ለዘወትርም አትጣለን"። መዝ 43፥22-23
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_24_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 10
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁶ እነሆ፥ እኔ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ።
¹⁷ ነገር ግን ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ በምኩራቦቻቸውም ይገርፉአችኋልና ከሰዎች ተጠበቁ፤
¹⁸ ለእነርሱና ለአሕዛብም ምስክር እንዲሆን፥ ስለ እኔ ወደ ገዥዎች ወደ ነገሥታትም ትወሰዳላችሁ።
¹⁹ አሳልፈውም ሲሰጡአችሁ፥ የምትናገሩት በዚያች ሰዓት ይሰጣችኋልና እንዴት ወይስ ምን እንድትናገሩ አትጨነቁ፤
²⁰ በእናንተ የሚናገር የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ፥ የምትናገሩ እናንተ አይደላችሁምና።
²¹ ወንድምም ወንድሙን፥ አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፥ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ ይገድሉአቸውማል።
²² በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።
²³ በአንዲቱ ከተማም መከራ ቢያሳዩአችሁ ወደ ሌላይቱ ሽሹ፤ እውነት እላችኋለሁና፥ የሰው ልጅ እስኪመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተማዎች አትዘልቁም።
²⁴ ደቀ መዝሙር ከመምህሩ፥ ባሪያም ከጌታው አይበልጥም።
²⁵ ደቀ መዝሙር እንደ መምህሩ፥ ባሪያም እንደ ጌታው መሆኑ ይበቃዋል። ባለቤቱን ብዔል ዜቡል ካሉት፥ ቤተሰዎቹንማ እንዴት አብዝተው አይሉአቸው!
²⁶ እንግዲህ አትፍሩአቸው፤ የማይገለጥ የተከደነ፥ የማይታወቅም የተሰወረ ምንም የለምና።
²⁷ በጨለማ የምነግራችሁን በብርሃን ተናገሩ፤ በጆሮም የምትሰሙትን በሰገነት ላይ ስበኩ።
²⁸ ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ።
²⁹ ሁለት ድንቢጦች በአምስት ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ያለ አባታችሁ ፈቃድ በምድር ላይ አትወድቅም።
³⁰ የእናንተስ የራሳችሁ ጠጉር ሁሉ እንኳ ተቈጥሮአል።
³¹ እንግዲህ አትፍሩ ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ።
³² ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤
³³ በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ።
³⁴ በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም።
³⁵ ሰውን ከአባቱ፥ ሴት ልጅንም ከእናትዋ፥ ምራትንም ከአማትዋ እለያይ ዘንድ መጥቻለሁና፤
³⁶ ለሰውም ቤተ ሰዎቹ ጠላቶች ይሆኑበታል።
³⁷ ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤
³⁸ መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም።
³⁹ ነፍሱን የሚያገኝ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም ስለ እኔ የሚያጠፋ ያገኛታል።
⁴⁰ እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።
⁴¹ ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል።
⁴² ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ሠለስቱ_ምዕት_ቅዳሴ ነው። መልካም የአባታች የአቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ የእናታችን የቅድስት ክርስቶስ ሠምራና የቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ የዕረፍታቸው በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_25

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሃያ አምስት በዚች ቀን #ቅዱስ_እንድርያኖስ በሰማዕትነት ሞተ ከእርሱም ጋር የነበሩ ሃያ አራቱ ባልንጀሮቹ በሰማዕትነት ሞቱ፣ ቅዱሱ አባት #አባ_ቢጻርዮን አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_እንድርያኖስ

ነሐሴ ሃያ አምስት በዚህች ቀን ቅዱስ እንድርያኖስ በሰማዕትነት ሞተ ከእርሱም ጋር የነበሩ ሃያ አራቱ ባልንጀሮቹ በሰማዕትነት ሞቱ። ይህም እንድርያኖስ ከመክስምያኖስ መኳንንቶች አንዱ ነበር እርሱም የጐልማሶች አለቃ ነበረ። ለጣዖት መስገድን እምቤ ስለአሉ ንጉሡ ምእምናንን ሲአሠቃያቸው ቅዱስ እንድርያኖስ የሰማዕታትን የልባቸውን ቆራጥነትና በመከራቸው ላይ መታገሣቸውን ተመልክቶ አደነቀ።

እንዲህም አላቸው ይህን ያህል ስትታገሡ ምን ታገኛላችሁ ቅዱሳን ሰማዕታትም የሚጠብቀንን ተሰፋ ለመናገር አንደበታችን አይችልም አሉት ስለ ዓለም ድኅነትም #ክርስቶስ መከራ እንደ ተቀበለ ከብሉይና ከሐዲስ መጽሐፍ ነገሩት።

እንድርያኖስም በሰማ ጊዜ ጽሕፈትን ወደ ሚያውቁ ብልሆች ሰዎች ሔደና እኔ ከዛሬ ጀምሮ ክርስቲያን ነኝ ስሜን ከገድለኞቹ ጋራ ጻፉ አላቸው።

ለንጉሥ መክስምያኖስም እንዲህ እንዳለ በነገሩት ጊዜ ጠርቶ እንድርያኖስ ሆይ አበድክን አለው እንድርያኖስም ከቀድሞው እብደቴ ተመለስኩ እንጂ እኔ አላበድኩም ብሎ መለሰለት።

ንጉሡም ሰምቶ ወደ ወህኒ ቤት ከንጹሐን ሰማዕታት ጋራ እንዲጨምሩት አዘዘ። ከአገልጋዮቹም አንዱ ሒዶ ለሚስቱ እንጣልያ ነገራት በሰማችም ጊዜ ደስ እያላት ወደ ወህኒ ቤት ሔደች ሃያ አራቱ ቅዱሳን ሰማዕታት የታሠሩበትን ማሠሪያቸውን ሳመች በሥቃዩ እንዲታገሥ የባሏን ልብ ያጽናኑ ዘንድ ለመነቻቸው። እርሱንም እንዲህ አለችው ላህይህ ደምግባትህም ርስትህም ጥሪትህም አያስትህ ሁሉም ከንቱ ነውና ነገር ግን በእርሱ ዘንድ የማያልፍ መንግሥትን ትወርስ ዘንድ የክብር ንጉሥ #ክርስቶስን ተከተለው ይህንንም ብላ ወደቤቷ ገባች።

ከዚህም በኃላ እንድርያኖስ ለፍርድ እንደ ሚአቀርቡት በአወቀ ጊዜ ሊሰናበታት ወደ ሚስቱ ሔደ መምጣቱንም ሰምታ የሸሸ መሰላት ደጇንም ዘግታ በውስጥ ሁና እንዲህ እያለች ዘለፈችው ትላንት ሰማዕት ተብለኽ ዛሬ #ክርስቶስን ካድከውን እንድርያኖስም ሰምቶ የሃይማኖቷን ጽናት አደነቀ እንዲህም አላት እኅቴ ሆይ እንድስናበትሽ ክፈችልኝ አላት።

በሰማችም ጊዜ ከፈተችለት ከዚህም በኃላ ሁሉን እያነጋገራት እስከ እሥር ቤት ወሰዳት እንጣልያም ከዚያ በደረሰች ጊዜ የታሠሩትን ቅዱሳን ተሳለመቻቸው ቁስላቸውንም አጠበች።

ከዚህም በኃላ ንጉሡ ቅዱሳኑን ከእሥር ቤት እንዲአመጧቸው አዘዘ በመጡም ጊዜ ከሥቃይ ብዛት የተነሣ እንደደከሙ አያቸው። እንድርያኖስንም በፊቱ አቁሞ ለአማልክት ሠዋ አለው ቅዱሱም እርሱንና የረከሱ አማልክቶቹን ረገመ ንጉሡም የሆድ ዕቃው እስኪፈስስ ሆዱን እንዲደበድቡት አዘዘ በዚያን ጊዜም የእንድርያኖስ ዕድሜው ሃያ ስምንት ዓመት ነበር።

ከዚህም በኃላ እንድርያኖስን ከባልንጀሮቹ ሰማዕታት ጋራ ወደ እሥር ቤት መለሱት እንጣልያም መጥታ የቅዱሳንን ደማቸውን ጠራረገችላቸው። እሊህ ቅዱሳንም እንድርያኖስን እንዲህ ብለው ተሳለሙት እንድርያኖስ ሆይ ስምህ ተሳለሙት በሕይወት መጽሐፍ ተጽፎአልና ደስ ይበልህ ።

ንጉሡም መሰፍ አምጥተው የቅዱሳኑን ሁሉ ጭናቸውን በድጅኖ ይሰብሩ ዘንድ አዘዘ እንጣልያም የእንድርያኖስን እጆቹንና እግሮቹን በመስፍ ላይ ለማኖር ቀደመች ነፍሱንም በ #እግዚአብሔር እጅ እስከ ሰጠ ድረስ የእንድርያኖስን ዐጥንቶቹን ወታደሮች ቀጠቀጡ የቅዱሳኑንም ሁሉ ጭናቸውን ሰብረው ወደ እሳት ወረወሯቸው እሳቱ ግን ከቶ አልነካቸውም ።

ምእመናንም መጥተው በጭልታ ወደ ሌላ ቦታ ወሰዱአቸው የመከራውም ወራት እስቲያልፍ ሠወሩአቸው። እንጣልያም የእንድርያኖስን የእጁን ቁራጭ ወስዳ በትርአሷ ውስጥ አኖረችው።

ከዚህም በኃላ የሀገሩ ገዥ እንጣልያን ሊአገባት ወደደ በአወቀችም ጊዜ የባሏን የእጅ ቁራጭ ይዛ በመርከብ ሸሸች የቅዱሳኑ ሥጋ ወዳለበትም ደርሶ ወደ እነርሱ ይቀበሏት ዘንድ ለመነች #ጌታችንም ልመናዋን ተቀብሎ አሳረፋት ከእነርሱም ጋራ ተቀበረች።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሰማዕታት አማላጅነት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ቢጻርዮን

በዚህችም ቀን ቅዱሱ አባት አባ ቢጻርዮን አረፈ። የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ #እግዚአብሔርን የሚፈሩ ምእመናን ነበሩ። በአደገም ጊዜ የምንኵስና ልብስን ለብሶ #እግዚአብሔርን ሊአገለግል ወደደ ዓለምንም ንቆ ወደ አባ እንጦንስ ሔደ ለእርሱም ደቀ መዝሙር ሆኖ ብዙ ዘመናት አገለገለው።

ከዚህም በኃላ ወደ አባ መቃርስ ሒዶ ቅዱሳን አረጋውያን መነኰሳትንም አገለገላቸው። በአስቄጥስም ገዳም ይዘዋወር ነበር በቤት ውስጥም አያድርም ነበር። ምንጣፍና ልብስ እስኪአጣ ድረስ ምንም ምን ጥሪት አልነበረውም መነኰሳቱም የማቅ ጨርቅ ይሰጡት ነበር። ወገቡንም ታጥቆ በመነኰሳቱ መንደር ይዞር ነበር በቤቶቻቸውም ደጃፍ እያለቀሰ ይቀመጥ ነበር።

የማያውቀውም ወደርሱ በደረሰ ጊዜ አባቴ ሆይ ምን ያስለቅስሃል ይለው ነበር። እርሱም ንብረቴን ስለዘረፉኝ እንዳልሞት ሸሸሁ ከወገኔም ክብር ተለይቼ በጉስቁልና ወደቅሁ ይለው ነበር። የቃሉንም ምልክት የማያውቅ የጠፋውን ገንዘብህን #እግዚአብሔር ይመልስልህ ብሎ ካለው ይሰጠው ነበር። እርሱም ተቀብሎ ይሔድና ለሌለው ይሰጥ ነበር።

የቃሉን ምልክት የሚያውቅ ግን በፈቃደ ነፍስ የሚሠሩ ትሩፋትን ሰይጣን ከሰዎች የማረካቸው መሆኑን ልብ ብሎ ያስተውል ነበር። አባቶችም ጭንቅ የነበረ ተጋድሎውን ስለርሱ ይናገሩ ነበር። እርሱ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ከቶ ሳይተኛ ቁሞ ኖሮአልና ።

በምንኩስናውም ወራት ብዙ ጊዜ በየአርባ ቀን ጾመ እነሆ እንዲህ እየተጋደለ ድንቆችንም እያደረገ ኀምሳ ሰባት ዓመታት ኖረ። ቅዱሳን አባ ዱላስና አባ ዮሐንስም ከተአምራቱ ተናገሩ እነርሱ ከርሱ ጋር ወደ ኤርትራ ባሕር ዳርቻ ሔዱ። እጅግም በተጠሙ ጊዜ እንደተጠሙ አውቆ ወደ #እግዚአብሔር ጸለየ መራራውንም ውኃ ጣፋጭ አድርጎላቸው ጠጥተዋል።

በሁለተኛም ጊዜ ወደ ፈሳሽ ውኃ ደርሶ መሸጋገሪያ አጣ ወደ #ጌታችንም ጸለየ ያን ጊዜም እንደ የብስ በባሕሩ ላይ ሔደ። በአንዲት ቀንም የከበሩ አባቶች በጸሎታቸው ያድኑት ዘንድ ጋኔን ያደረበትን ሰው ወደ አስቄጥስ ገዳም ሰዎች አመጡ አባቶችም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ እርሱ ከከንቱ ውዳሴ ስለሚሸሽ ብንነግረው ይህን ጋኔን የያዘውን አያድነውም ።

አባ ቢጻርዮን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለጸሎት ወደሚቆምበት ቦታ ያንን ጋኔን ያደረበትን ሰው አስተኙት። አባ ቢጻርዮንም በገባ ጊዜ ያን ጋኔን ያደረበትን ሰው ተኝቶ አገኘውና ቀሰቀሰው እጁንም ይዞ ተነሥ አለው ያን ጊዜም ድኖ ተነሣ አእምሮውም ተመለሰ። ያዩትም እጅግ አደነቁ ለሚፈሩት ስለሚሰጠው ጸጋውም #እግዚአብሔርን አመሰገኑት።

የዚህም ቅዱስ ተአምራቶቹ ከነገርናችሁ የበዙ ናቸው #እግዚአብሔርንም አገልገሎ በሰላም አረፈ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን። በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኅ_ነሐሴ_25)
2024/09/24 13:17:36
Back to Top
HTML Embed Code: