Telegram Web Link
#ነሐሴ_18

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ዐሥራ ስምንት በዚህች ቀን የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት #አባ_እለእስክንድሮስ አረፈ፣ የከበረና የተመሰገነ ሐዋርያ #ቅዱስ_እንድራኒቆስ መታሰቢያው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_እለእስክንድሮስ

ነሐሴ ዐሥራ ስምንት በዚህች ቀን ቁጥሩ ከአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ እለእስክንድሮስ አረፈ። ይህም አባት ከአርዮስ ወገኖች ብዙ ችግር ደርሶበታል እርሱ ከወገኖቹ ጋር ሁኖ አርዮስን አውግዞ ከቤተክርስቲያን አሳዶት ነበርና።

በታላቁ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ዘመን በኒቅያ ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት አባቶች ሊቃውንት አርዮስን በጉባኤ አውግዘው ከቤተ ክርስቲያን ለይተው በአሳደዱት ጊዜ ወደ ንጉሡ ቈስጠንጢኖስ ጓደኞቹን ይዞ ገብቶ በእለእስክንድሮስና በአትናቴዎስ ላይ ነገር ሠራ ሁለተኛም እለእስክንድሮስ ከካህናቱ ጋር ይቀበለው ዘንድ እንዲያዝለት ንጉሡን ለመነው።

ንጉሡም ልመናውን ተቀብሎ መልእክተኞችን ልኮ አባት እለእስክንድሮስን አስመጥቶ እንዲህ አለው "አትናቴዎስ ትእዛዛችንን በመተላለፍ አርዮስን አልቀበልም ብሏል፤ እኛም አንተን እንዳከበርንህ አንተ ታውቃለህ አሁንም ትእዛዛችንን አትተላለፍ አርዮስንም ከውግዘቱ ፈትተህ ልባችንን ደስ አሰኝ" አለው ።

ቅዱስ እለእስክንድሮስም ለንጉሥ እንዲህ ብሎ መለሰለት "አርዮስን እኮን ቤተክርስቲያን አልተቀበለችውም። ልዩ ሦስትነትን አያመልክምና" ንጉሡም "አይደለም እርሱ በ #ሥሉስ_ቅዱስ ያምናል እንጂ" አለው ቅዱስ እለእስክንድሮስም " #ወልድ በመለኮቱ ከ #አብ#መንፈስ_ቅዱስ ጋራ ትክክል እንደሆነ የሚያምን ከሆነ በእጁ ይጻፍ" ብሎ መለሰለት።

ንጉሥም አርዮስን አስቀርቦ "ትክክለኛ ሃይማኖትህን ጻፍ" አለው አርዮስም በልቡ ሳያምን ' #ወልድ#አብ ጋራ በመለኮቱ ትክክል ነው' ብሎ ጻፈ በሐሰትም የከበረ ወንጌልን ይዞ ማለ። ንጉሡም ቅዱስ እለእስክንድሮስን "አሁን በአርዮስ ላይ ምክንያት አልቀረህም ትክክለኛ ሃይማኖቱን ጽፎአልና በከበረ ወንጌልም ምሎአልና" አለው ።

አባ እለእስክንድሮስም ንጉሡን እንዲህ አለው "በአባትህ በንጉሥ ቈስጠንጢኖስ እጅ የተጻፈ ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ አባቶች በእጆቻቸው የጻፉትን እርሱንና ወገኖቹን ከቤተ ክርስቲያን እንዳሳደዷቸው የአርዮስን ክህደቱንና ውግዘቱን አትናቴዎስ አንብቦታል። ነገር ግን አንድ ሱባዔ በእኔ ላይ ታገሥ በዚህ ሱባዔ በአርዮስ ላይ አንዳች ነገር ካልደረሰ ይህ ካልሆነ ሃይማኖቱ መሐላውም እውነት ነው እኔም ተቀብዬ ከካህናቱ ጋር እቀላቅለዋለሁ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎትም ከእሳቸው ጋራ አንድ ይሆናል።"

ንጉሡም አባት እለእስክንድሮስን እንዲህ አለው "እወቅ እኔ ስምንቱን ቀኖች እታገሥሃለሁ አርዮስን ካልተቀበልከው በአንተ ላይ የፈለግሁትን አደርጋለሁ።" ከዚህም በኋላ ከንጉሡ ዘንድ ወጥቶ ወደ ማደሪያው ሔደ ቤተክርስቲያንን ከአርዮስ መርዝ ያድናት ዘንድ በዚያ ሱባዔ እየጾመና እየጸለየ ወደ #እግዚአብሔር ሲለምን ሰነበተ።

ከዚያም ሱባዔ በኋላ አርዮስ መልካም ልብስን ለበሰ ወደ ቤተክርስቲያንም ገብቶ በመሠዊያው ፊት ከካህናቱ ጋራ ተቀመጠ። ከዚህም በኋላ አባ እለእስክንድሮስ እያዘነና እየተከዘ ገባ ከኀዘኑም ብዛት የተነሣ የሚሠራውን አላወቀም የቅዳሴውንም ሥርዓት ሊጀምር ቆመ። ያን ጊዜ የአርዮስ ሆዱ ተበጠበጠና ወጥቼ ልመለስ አለ ይህንንም ብሎ ወደ መጸዳጃ ቦታ ወጣ። ሊጸዳዳም በተቀመጠ ጊዜ አንጀቱና የሆድ ዕቃው ሁሉ ወጣ በዚያውም ላይ ሞተ።

በዘገየም ጊዜ ሊፈልጉት ወጡ በመጸዳጃውም ቦታ ሬሳውን ወድቆ አገኙት። ለዚህም ለአባት እለእስክንድሮስ ነገሩት እርሱም አደነቀ የከበረች ቤተክርስቲያኑን ያልጣላት ምስጉን የሆነ #ክርስቶስንም አመሰገነው።

ንጉሡም በሰማ ጊዜ አደነቀ ከሀዲ አርዮስም በሐሰት እንደማለና በሽንገላ እንደጻፈ አወቀ። የዚህንም አባት የእለእስክንድሮስን ቅድስናውን ዕውነተኛነቱ ሃይማኖቱም የቀናች መሆኗን የአርዮስንም ሐሰተኛነቱንና ከሀዲነቱን ተረዳ።

አንድ የሆነ #አብ_ወልድ_መንፈስ_ቅዱስንም አመሰገነው መለኮታቸውም አንድ እንደሆነ ታመነ።

ይህም አባት በበጎ ሥራ ጸንቶ ኖረ ለምለም ወደ ሆነ እርጅናም ደርሶ ወደ ወደደው #ክርስቶስ ሔደ የሕይወት አክሊልንም አገኘ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_እንድራኒቆስ

በዚህችም ቀን የከበረና የተመሰገነ ሐዋርያ እንድራኒቆስ መታሰቢያው ነው። ይህንንም ሐዋርያ የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ መረጠው። እርሱም የ #እግዚአብሔርን መንግሥት እንዲሰብኩ ጌታ ከመከራው በፊት ከላካቸው ከሰባ ሁለቱ አርድእት ውስጥ የተቆጠረ ነው።

በጽርሐ ጽዮንም #መንፈ_ቅዱስ በወረደ ጊዜ ከሐዋርያት ጋራ የ #መንፈስ_ቅዱስን ስጦታ ተቀብሎ በብዙ አገሮች ውስጥ ሰበከ። በኒውብያ አገር ላይም ሐዋርያት በአንብሮተ እድ ኤጲስቆጶስነት ሾሙት በውስጧም ሰበከ በጨለማ በድንቁርና የሚኖሩ ብዙዎች አረማውያንንም የክብር ባለቤት ወደሆነ ወደ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሃይማኖት አስገባቸው።

ከዚህም በኋላ ሐዋርያ ዮልዮስን ወሰደው በአንድነትም በብዙ አገሮች ዙረው አስተማሩ። ብዙ ሰዎችንም አጠመቁ ተአምራትንም በማድረግ ከሰዎች ላይ አጋንንትን አባረሩ። ብዙዎች በሽተኞችንም ፈወሱአቸው የጣዖታትንም ቤቶች አፍርሰው የክብር ባለቤት የሆነ የ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አብያተ ክርስቲያናትን አነፁ። አገልገሎታቸውንም በፈጸሙ ጊዜ #ጌታችን ከድካም ወደ ዕረፍት ከኀዘንም ወደ ደስታ ሊወስዳቸው ወደደ።

ከዚህ በኋላ ሐዋርያ እንድራኒቆስ ታመመና ግንቦት ሃያ ሁለት ቀን አረፈ ቅዱስ ዮልዮስም ገንዞ በመቃብር አኖረው።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_18 ና_ዘወርኀ_ግንቦት_22)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_18_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ፊልጵስዩስ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ በቀረውስ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ በጌታ ደስ ይበላችሁ። ስለ አንድ ነገር መልሼ ልጽፍላችሁ እኔን አይታክተኝም ለእናንተ ግን ደኅና ነው።
² ከውሾች ተጠበቁ፥ ከክፉዎችም ሠራተኞች ተጠበቁ፥ ከሐሰተኛም መገረዝ ተጠበቁ።
³ እኛ በመንፈስ እግዚአብሔርን የምናመልክ በክርስቶስ ኢየሱስም የምንመካ በሥጋም የማንታመን እኛ የተገረዝን ነንና።
⁴ እኔ ግን በሥጋ ደግሞ የምታመንበት አለኝ። ሌላ ሰው ማንም ቢሆን በሥጋ የሚታመንበት እንዳለው ቢመስለው፥ እኔ እበልጠዋለሁ።
⁵ በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፥ ከእስራኤል ትውልድ፥ ከብንያም ወገን፥ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ብትጠይቁ፥ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ዮሐንስ 2
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
² እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።
³ ትእዛዛቱንም ብንጠብቅ በዚህ እንዳወቅነው እናውቃለን።
⁴ አውቄዋለሁ የሚል ትእዛዛቱንም የማይጠብቅ ውሸተኛ ነው እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም።
⁵ ቃሉን ግን የሚጠብቅ ሁሉ በእርሱ የእግዚአብሔር ፍቅር በእውነት ተፈጽሞአል። በእርሱ እንዳለን በዚህ እናውቃለን፤
⁶ በእርሱ እኖራለሁ የሚል እርሱ እንደ ተመላለሰ ራሱ ደግሞ ሊመላለስ ይገባዋል።
⁷ ወንድሞች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረቻችሁ አሮጌ ትእዛዝ እንጂ የምጽፍላችሁ አዲስ ትእዛዝ አይደለችም፤ አሮጌይቱ ትእዛዝ የሰማችኋት ቃል ናት።
⁸ ዳግመኛ አዲስ ትእዛዝን እጽፍላችኋለሁ፥ ይህም ነገር በእርሱ በእናንተም እውነተኛ ነው፤ ጨለማው ያልፋልና እውነተኛውም ብርሃን አሁን ይበራል።
⁹ በብርሃን አለሁ የሚል ወንድሙንም የሚጠላ እስከ አሁን በጨለማ አለ።
¹⁰ ወንድሙንም የሚወድ በብርሃን ይኖራል ማሰናከያም የለበትም፤
¹¹ ወንድሙን የሚጠላ ግን በጨለማ አለ፥ በጨለማም ይመላለሳል፥ የሚሄድበትንም አያውቅም፥ ጨለማው ዓይኖቹን አሳውሮታልና።
¹² ልጆች ሆይ፥ ኃጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና እጽፍላችኋለሁ።
¹³ አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጎበዞች ሆይ፥ ክፉውን አሸንፋችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ልጆች ሆይ፥ አብን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ።
¹⁴ አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጐበዞች ሆይ፥ ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም ቃል በእናንተ ስለሚኖር ክፉውንም ስለ አሸነፋችሁ እጽፍላችኋለሁ።
¹⁵-¹⁶ ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።
¹⁷ ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።
¹⁸ ልጆች ሆይ፥ መጨረሻው ሰዓት ነው፥ የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል፤ ስለዚህም መጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ እናውቃለን።
¹⁹ ከእኛ ዘንድ ወጡ፥ ዳሩ ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገንስ ቢሆኑ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉ ከእኛ ወገን እንዳልሆኑ ይገለጡ ዘንድ ወጡ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 20
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁸ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።
²⁹-³⁰ ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ።
³¹ ስለዚህ ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሠጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_18_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ዘዐበያ ለበረከት ወትርኅቅ እምኔሁ። ወለብሳ ለመርገም ከመ ልብስ ወቦአ ከመ ማይ ውስተ አማዑቱ። መዝ.108÷17-18
"መርገምን ወደደ ወደ እርሱም መጣች፤ በረከትንም አልመረጠም ከእርሱም ራቀች።
መርገምን እንደ ልብስ ለበሳት፥ እንደ ውኃም ወደ አንጀቱ፥ እንደ ቅባትም ወደ አጥንቱ ገባች"። መዝ.108÷17-18
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_18_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 15
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁶ አባቱን ወይም እናቱን አያከብርም ትላላችሁ፤ ስለ ወጋችሁም የእግዚአብሔርን ቃል ሻራችሁ።
⁷ እናንተ ግብዞች፥ ኢሳይያስ ስለ እናንተ፦
⁸ ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፥ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤
⁹ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ብሎ በእውነት ትንቢት ተናገረ።
¹⁰ ሕዝቡንም ጠርቶ፦ ስሙ አስተውሉም፤
¹¹ ሰውን የሚያረክሰው ወደ አፍ የሚገባ አይደለም፥ ከአፍ የሚወጣው ግን ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው አላቸው።
¹² በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው፦ ፈሪሳውያን ይህን ቃል ሰምተው እንደ ተሰናከሉ አወቅህን? አሉት።
¹³ እርሱ ግን መልሶ፦ የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል።
¹⁴ ተዉአቸው፤ ዕውሮችን የሚመሩ ዕውሮች ናቸው፤ ዕውርም ዕውርን ቢመራው ሁለቱም ወደ ጉድጓድ ይወድቃሉ አለ።
¹⁵ ጴጥሮስም መልሶ፦ ምሳሌውን ተርጕምልን አለው።
¹⁶ ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ እናንተ ደግሞ እስካሁን የማታስተውሉ ናችሁን?
¹⁷ ወደ አፍ የሚገባ ሁሉ ወደ ሆድ አልፎ ወደ እዳሪ እንዲጣል አትመለከቱምን?
¹⁸ ከአፍ የሚወጣ ግን ከልብ ይወጣል፥ ሰውንም የሚያረክሰው ያ ነው።
¹⁹ ከልብ ክፉ አሳብ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብ ይወጣልና።
²⁰ ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው እንጂ፥ ባልታጠበ እጅ መብላትስ ሰውን አያረክሰውም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን የ #ማርያም ቅዳሴ ወይም የ #ሠለስቱ_ምእት ቅዳሴ ነው። መልካም የታላቁ ሐዋርያ የሊቀ ጳጳስ የ #እለእስክንድሮስ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
በኒቂያ ለተሰበሰቡት ማኅበር አፈ ጉባኤ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት እለ እስክንድሮስ የምሥጢረ ሥጋዌን ነገር በተናገረበት ድርሳኑ እንዲህ አለ።

#እግዚአብሔር ቃል ወደዚህ ዓለም ይመጣ ዘንድ ከንጽሕት #ድንግል_ማርያም ሥጋን ይዋሐድ ዘንድ ምን አተጋው? በጨርቅ ይጠቀለል በበረት ይጣል ዘንድ ከሴት (ከድንግል) ጡት ወተትን ይጠባ ዘንድ በዮርዳኖስ ይጠመቅ ዘንድ ምን አተጋው?

ሕግ አፍራሽ ጲላጦስ ይዘብትበት ዘንድ በመስቀል ይሰቀል ዘንድ በመቃብር ይቀበር ዘንድ በሦስተኛው ቀን ይነሳ ዘንድ ምን አተጋው? በፍዳ ተይዘን የነበርን እኛን ያድነን ዘንድ ለእኛ ብሎ አይደለምን። ኢሳ.7÷17፣ ፊልጵ.2÷9፣ 1ኛቆሮ.1÷21-25

ዳግመኛም የ #ጌታችንን የሕማሙን ነገር በተናገረበት ድርሳኑ ይህ አባት እለ እስክንድሮስ እንዲህ አለ።

በእርሱ ለማይነግር ለዚህ እንግዳ ምሥጢር አንክሮ ይገባል፤ ፈራጅ እርሱን ፈረዱበት፤ ከማዕሠረ ኃጢያት የሚፈታ እርሱን አሰሩት፤ ዓለምን የያዘ እርሱን ያዙት።

ለሰው ሕይወትን ለሚሰጥ ለእርሱ ሐሞትን አጠጡት፤ የሚያድን እርሱ ሞተ፤ ሙታንን የሚያስነሳቸው እርሱ ተቀበረ። ሉቃ.13÷10-17፣ ዮሐ.11÷11፣ ዮሐ.19÷28-30

በሰማይ ያሉ ኃይላት አደነቁ፤ መላእክትም በተደሞ ፈዘዙ በፍጥረት ላይ የተሾመ ሁሉ ደነገጠ፣ ፍጡራንም ሁሉ አደነቁ። ኢሳ.49÷7፣ 1ኛቆሮ.2÷6-10

አይሁድም ገዥው እነሆ አሉ፤ እርሱ ግን ዝም ብሎ መከራ ተቀበለ፤ የማይታየው ታየ፤ በምን ዕዳዬ ነው? አላለም፤ የማይያዘው ተያዘ አላዘነም።

የማይታመመው ታመመ አልተቀበለም፤ የማይሞት እርሱ በፈቃዱ ሞተ፤ ይሁን ብሎ በመቃብር አደረ። ማቴ.27÷29-45፣ 1ኛጴጥ.2÷21-25

ፍጥረት ሁሉ አደነቁ፤ የማይታመም እርሱ ለሰው ብሎ መከራ ተቀብሏልና፤ በመኳንንት በሚፈርድ እርሱ ፈረዱበት፤ የማይታይ እርሱን ራቁቱን ሰቅለው አዩት፤ የማይሞተውን ገደሉት፤ ሰማያዊ እርሱ በመቃብር ተቀበረ። ማር.15÷17-27፣ ቆላ.2÷14-15፣ ዕብ.12÷2፣ ራእ.1÷5-7

#ሃይማኖተ_አበው_ዘቅዱስ_እለእስክንድሮስ
#ነሐሴ_19

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ዐሥራ ዘጠኝ በዚች ቀን የታላቁ #አባ_መቃርስ የሥጋው ፍልሰት ሆነ፣ የደግነት የምጽዋት የፍቅር አባት የሆነው #ደጉ_አብርሃም ጣዖት የሰበረበት፣ የአልዓዛር ልጅ #የቅዱስ_ፊንሐስ መታሰቢያው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ታላቁ_ቅዱስ_መቃርስ

ነሐሴ ዐሥራ ዘጠኝ በዚህች ቀን ሳስዊር ከሚባል አገር ወደ አስቄጥስ ገዳም የታላቁ አባ መቃርስ የሥጋው ፍልሰት ሆነ።

ከዕረፍቱ በኋላ ከሀገሩ ከሳስዊር ሰዎች መጥተው ሥጋውን ሰርቀው ወደ ሀገራቸው ወሰዱት ቤተ ክርስቲያንም ሠርተውለት ሥጋውን በዚያ አኖሩት እስላሞች እስከ ነገሡበት ዘመንም በዚያ ኖረ።

ከዚህም በኋላ ወደ ሌላ ቦታ አፍልሰውት በዚያም ቤተ ክርስቲያን ሠሩለት። ለአባ መቃርስ ገዳም አበ ምኔት ሁኖ አባ ዮሐንስ እስከ ተሾመበት ዘመን ኖረ።

ሊቀ ጳጳሳቱም የከበረች ጾመ አርብዓን ሊጾም ወደ አባ መቃርስ ገዳም በወጣ ጊዜ ፈጽሞ አለቀሰ እንዲህም ብሎ ጸለየ። #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሆይ የከበረ የአባ መቃርስ ሥጋ በዚህ ገዳም በመካከላችን ይሆን ዘንድ እንድትረዳኝ እመኛለሁ።

ከጥቂት ቀኖችም በኋላ አባ ሚካኤል ሔደ ከእርሱ ጋራም ስለ ገዳሙ አገልግሎት አረጋውያን መነኰሳት አሉ ልቦናቸውም በመንፈሳዊ ሁከት ተነሣሥቶ ያመጡት ዘንድ የአባ መቃርስ ሥጋ ወደ አለበት ቦታ ደረሱ።

የአገር ሰዎችም በአዩአቸው ጊዜ በትሮቻቸውንና ሰይፎቻቸውን በመያዝ ከመኰንናቸው ጋራ ተሰብስበው ከለከሏቸው። በዚያቺም ሌሊት በልባቸው ፈጽሞ እያዘኑ አደሩ። አባ መቃርስም በዚያች ሌሊት ለመኰንኑ በራእይ ተገለጠለትና ከልጆቼ ጋራ መሔድን ለምን ትከለክለኛለህ እንግዲህስ ተወኝ ከእሳቸው ጋራ ወደ ቦታዬ ልሒድ አለው።

ያ መኰንንም በጥዋት ተነሣ እየፈራና እየተንቀጠቀጠ የከበሩ አረጋውያን መነኰሳትን ጠርቶ የከበረ የአባ መቃርስን ሥጋ ሰጣቸው። እነርሱም ደስ ብሏቸው ተቀበሉት በመርከብም ተሳፍረው ተርኑጥ ወደሚባል አገር ደረሱ ከእርሳቸውም ጋራ የሚሸኙአቸው ከየአገሩ የመጡ ብዙ ሕዝቦች ነበሩ። በዚያችም ሌሊት በዚያ አደሩ ጸሎትንም አደረጉ ቀድሰውም ለሕዝቡ ሥጋውንና ደሙን አቀበሉ።

ከዚህም በኋላ ተሸክመው ወደ ገዳም ተጓዙ ሲጓዙም ከበረሀው እኵሌታ ደርሰው ከድካማቸው ጥቂት ሊአርፉ ወደዱ። አባ ሚካኤልም የከበረ የአባታችን የአባ መቃርስን ሥጋ የምናሳርፍበትን #እግዚአብሔር እስከ ገለጠልን ድረስ እንደማናርፍ ሕያው #እግዚአብሔርን ብሎ ማለ።

ከዚህም በኋላ የከበረ የአባ መቃርስን ሥጋ የተሸከመ ገመል ወደ አንድ ቦታ ደርሶ በዚያ በረክ አለ። የከበረ የአባ መቃርስ ሥጋ ያለበትንም ሣጥን ይጥል ዘንድ በራሱ ወዲያና ወዲህ ይዞር ጀመረ። አረጋውያን መነኰሳትም #እግዚአብሔር የፈቀደው ያ ቦታ እንደሆነ አወቁ እጅግም አደነቁ #እግዚአብሔርንም አመሰገኑት ያም ቦታ እስከ ዛሬ የታወቀ ነው።

ወደ ገዳሙም በቀረቡ ጊዜ መነኰሳቱ ሁሉም ወጡ ወንጌልና መስቀሎችን ይዘው መብራቶችን እያበሩ እየዘመሩና እያመሰገኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን እስከ አስገቡት ድረስ በታላቅ ክብር በራሳቸው ተሸክመው ወሰዱት።

#እግዚአብሔርም በዚያች ሌሊት ተአምራትን አደረገ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ አባቶቻችን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ይድረሰን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አበ_ብዙሃን_ቅዱስ_አብርሃም

በዚህችም ቀን የሃይማኖት የደግነት የምጽዋት የፍቅር አባት የሆነው ደጉ አብርሃም ጣዖት የሰበረበት እለት ይታሠባል።

በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት የአብርሃም አባቱ ታራ ጣዖትን ይጠርብና ይሸጥ ነበር። ሽጦ ገንዘብ የሚያመጣለት ደግሞ ልጁ አብርሃም ነበር። በዚያ ወራት አብርሃም እውነተኛውን አምላክ ፍለጋ ገብቶ ነበር። አንድ ቀን ጣዖቱን ሊሸጥ ወደ ገበያ እየሔደ የተሸከመውን እንጨት ይመራመረው ገባ። "አሁን ይሔ ምኑ ነው አምላክ!" እያለም ያደንቅ ገባ። መንገድ ላይም ደክሞት ካረፈበት "ለምን አልጠይቀውም" በሚል አናገረው።

"እርቦኛል አብላኝ" አለው:: መልስ የለም:: "እሺ አጠጣኝ" አለው:: አሁንም ያው ነው:: "ባይሆን እሺ አጫውተኝ" አለው:: ጣዖቱ ተራ እንጨት ነውና መልሱ ዝምታ ነበር:: ከዚያ ተነስቶ ወደ ገበያው ሲደርስ "ዐይን እያለው የማያይ: ጀሮ እያለው የማይሰማ አምላክ የሚገዛ" እያለ ይጮህ ጀመር::

ይህን ሲሰሙ አንዳንዶቹ "የታራ ልጅ አብዶ" ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ "እሱ ያቀለለውን ማን ይገዛዋል" ብለውት ሔደዋል:: ከገበያ ሲመለስም ጣዖቱን ተመልክቶ አብርሃም እንዲህ አለ:: "አንተ ቀድሞውን በዕለተ ሠሉስ የተፈጠርክ ዕፅ ነህ" ብሎ ሰባበረው።

ወደ ቤቱ ሲመለስም ሁሉንም ጣዖታት ሠባበራቸው:: ይህ የተደረገው ከ2,000 ዓመታት በፊት በዚህች ቀን ነው። የመንግስተ ሰማያት አበጋዝ የ #እግዚአብሔር ወዳጅ አባታችን አብርሃም በመጨረሻው በውሃ፣ በነፋስ፣ በእሳትና በፀሐይ ተመራምሮ ፈጣሪውን አግኝቷል።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አብርሃም ጸሎት ይማረን በረከቱም ይድረሰን ለዘላለሙ አሜን።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ፊንሐስ_ካህን

በዚህች ቀን የአልዓዛር ልጅ የፊንሐስ መታሰቢያው ነው። ካህኑ ፊንሐስ የብሉይ ኪዳን ዘመን አገልጋይ: ከነገደ ሌዊ: የሊቀ ካህናቱ የአሮን የልጅ ልጅ ነው:: አባቱም ሊቀ ካህናቱ አልዓዛር ነው:: ፊንሐስ እሥራኤል ከግብጽ ሲወጡ ሕጻን የነበረ ሲሆን አድጐ በመጀመሪያ ካህን፤ አባቱ አልዓዛርና አያቱ አሮን ሲያርፉ ደግሞ ሊቀ ካህንነትን ተሹሟል::

አንድ ቀን በጠንቅዋዩ በበለዓም ክፉ ምክር እሥራኤላውያን ከሞዐብ ሴቶች ጋር በኃጢአት በመሳተፋቸው #እግዚአብሔር ተቆጥቶ ነበር:: ያጠፋቸው ዘንድም መቅሰፍት ተጀምሮ ሳለ ፊንሐስ ወንድና ሴት: በደብተራ ኦሪቱ አንጻር የማይገባውን ሲሠሩ አያቸው::

ለፈጣሪው ቀንቶ በአንድ ጦር ሁለቱንም በአንድ ላይ ጥሏቸዋል:: ያን ጊዜ ጌታ "አስተንፈስካ ለነፍስየ" ብሎታል:: መቅሰፍቱም ተከልክሏል:: በዚህም ምክንያት ካህኑ ፊንሐስ የ300 ዓመት ዕድሜ ተጨምሮለት: #እግዚአብሔርን ሲያገለግል ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፏል:: (ዘኁ. 25፥7, መዝ. 105፥30)

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ አባቶቻችን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ይድረሰን ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_19 እና #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_19_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ቆሮንቶስ 7
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹³ ያላመነ ባል ያላት ሚስትም ብትኖር ይህ ከእርስዋ ጋር ሊቀመጥ ቢስማማ፥ አትተወው።
¹⁴ ያላመነ ባል በሚስቱ ተቀድሶአልና፥ ያላመነችም ሚስት በባልዋ ተቀድሳለች፤ አለዚያ ልጆቻችሁ ርኵሳን ናቸው፤ አሁን ግን የተቀደሱ ናቸው።
¹⁵ የማያምን ግን ቢለይ ይለይ፤ ወንድም ቢሆን ወይም እኅት እንዲህ በሚመስል ነገር አይገዙም፤ እግዚአብሔር ግን በሰላም ጠርቶናል።
¹⁶ አንቺ ሴት፥ ባልሽን ታድኚ እንደ ሆንሽ ምን ታውቂአለሽ? ወይስ አንተ ሰው፥ ሚስትህን ታድን እንደ ሆንህ ምን ታውቃለህ?
¹⁷ ብቻ ለእያንዳንዱ እግዚአብሔር እንደ ከፈለለት እያንዳንዱም እግዚአብሔር እንደ ጠራው እንዲሁ ይመላለስ። እንዲሁም በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እደነግጋለሁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ያዕቆብ 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹¹ ወንድሞች ሆይ፥ እርስ በርሳችሁ አትተማሙ። ወንድሙን የሚያማ በወንድሙም የሚፈርድ ሕግን ያማል በሕግም ይፈርዳል፤ በሕግም ብትፈርድ ፈራጅ ነህ እንጂ ሕግን አድራጊ አይደለህም።
¹² ሕግን የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ነው፤ እርሱም ሊያድን ሊያጠፋም የሚችል ነው፤ በሌላው ግን የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?
¹³ አሁንም፦ ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህ ከተማ እንሄዳለን በዚያም ዓመት እንኖራለን እንነግድማለን እናተርፍማለን የምትሉ እናንተ፥ ተመልከቱ፥ ነገ የሚሆነውን አታውቁምና።
¹⁴ ሕይወታችሁ ምንድር ነው? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፍዋለት ናችሁና።
¹⁵ በዚህ ፈንታ። ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም ይህን ወይም ያን እናደርጋለን ማለት ይገባችኋል።
¹⁶ አሁን ግን በትዕቢታችሁ ትመካላችሁ፤ እንደዚህ ያለ ትምክህት ሁሉ ክፉ ነው።
¹⁷ እንግዲህ በጎ ለማድረግ አውቆ ለማይሠራው ኃጢአት ነው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 18
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁹-¹⁰ ጌታም ሌሊት በራእይ ጳውሎስን፦ እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥ ማንም ክፉ ሊያደርግብህ የሚነሣብህ የለምና አትፍራ፥ ነገር ግን ተናገር ዝምም አትበል፤ በዚህ ከተማ ብዙ ሕዝብ አሉኝና አለው።
¹¹ በመካከላቸውም የእግዚአብሔርን ቃል እያስተማረ ዓመት ከስድስት ወር ተቀመጠ።
¹² ጋልዮስም በአካይያ አገረ ገዥ በነበረ ጊዜ፥ አይሁድ በአንድ ልብ ሆነው በጳውሎስ ላይ ተነሡ፥ ወደ ፍርድ ወንበርም አምጥተው፦
¹³ ይህ ሕግን ተቃውሞ እግዚአብሔርን ያመልኩት ዘንድ ሰዎችን ያባብላል አሉ።
¹⁴ ጳውሎስም አፉን ሊከፍት ባሰበ ጊዜ፥ ጋልዮስ አይሁድን፦ አይሁድ ሆይ፥ ዓመፅ ወይም ክፉ በደል በሆነ እንድታገሣችሁ በተገባኝ፤
¹⁵ ስለ ቃልና ስለ ስሞች ስለ ሕጋችሁም የምትከራከሩ ከሆነ ግን፥ ራሳችሁ ተጠንቀቁ እኔ በዚህ ነገር ፈራጅ እሆን ዘንድ አልፈቅድምና አላቸው።
¹⁶ ከፍርድ ወንበርም ፊት አስወጣቸው።
¹⁷ የግሪክ ሰዎችም ሁሉ የምኩራብ አለቃ ሶስቴንስን ይዘው በወንበሩ ፊት መቱት፤ በእነዚህም ነገሮች ጋልዮስ ግድ የለውም ነበር።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_19_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ክነፈ ርግብ በብሩር ዘግቡር። ወገበዋቲሃኒ በሐመልማለ ወርቅ። አመ አዘዘ ሰማያዊ ንጉሥ ላዕሌሃ። መዝ. 67÷13
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_19_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³⁸ ማርያምም፦ እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ አለች። መልአኩም ከእርስዋ ሄደ።
³⁹ ማርያምም በዚያ ወራት ተነሥታ ወደ ተራራማው አገር ወደ ይሁዳ ከተማ ፈጥና ወጣች፥
⁴⁰ ወደ ዘካርያስም ቤት ገብታ ኤልሳቤጥን ተሳለመቻት።
⁴¹ ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ፤ በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት፥
⁴² በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ አለች፦ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፥ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው።
⁴³ የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?
⁴⁴ እነሆ፥ የሰላምታሽ ድምጽ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና።
⁴⁵ ከጌታ፤ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን #ማርያም ቅዳሴ ነው። መልካም የእመቤታችን የትንሣኤዋና የዕርገቷ በዓል ሰሞን እና መልካም ዕለተ ሰንበት ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2024/09/24 13:20:59
Back to Top
HTML Embed Code: