Telegram Web Link
††† እንኳን ለጻድቅ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ዘጉጉቤን ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ዘጉጉቤን †††

††† በኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ መካከለኛው ዘመን (በተለይ ከ13ኛው እስከ 15ኛው መቶ ክ/ዘመን ድረስ ያለው) የብርሃን ዘመን ይባላል:: ምክንያቱም ዘመኑ
*ክርስትና ያበበበት::
*መጻሕፍት የተደረሱበት::
*ስብከተ ወንጌል የተስፋፋበት::
*ገዳማዊ ሕይወት የሠመረበት ወቅት በመሆኑ ነው::

ለዚህ ትልቁ አስተዋጽኦ ደግሞ:-
¤አቡነ ተክለ ሃይማኖት::
¤አቡነ ኤዎስጣቴዎስ::
¤አባ ሰላማ ካልዕ::
¤አቡነ ያዕቆብ::
¤ቅዱሱ ንጉሥ ዘርዓ ያዕቆብ::
¤አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ::
¤አቡነ መድኃኒነ እግዚእን የመሰሉ አበው መነሳታቸው ነው::

በተጨማሪም:-
¤12ቱ ንቡራነ ዕድ::
¤7ቱ ከዋክብት::
¤47ቱ ከዋክብት::
¤5ቱ ከዋክብት የሚባሉ አበው አስተዋጽኦም ልዩ ነበር:: ከእነዚህ መካከልም የ7ቱ እና የ47ቱ ከዋክብት አስተማሪ: የአበው 3ቱ ሳሙኤሎች (ዘዋልድባ: ዘጣሬጣና ዘቆየጻ): የሌሎችም እልፍ አእላፍ ቅዱሳን አባት የሆኑት አባ መድኃኒነ እግዚእ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ::

ጻድቁ ቅዱሳኑን ሰብስበው: አስተምረው: አመንኩሰው: መርቀው ሰደው: ሃገራችንን እንዲያበሩ በማድረጋቸው እንደ አባ ኢየሱስ ሞዐ እርሳቸውም "ወላዴ አእላፍ ቅዱሳን" ይባላሉ::

ከእነዚህ ቅዱሳን የጻድቁ ፍሬዎች አንዱ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ናቸው:: ጻድቁ አንዳንዴ "አፍቀረነ እግዚእ" እየተባሉም ይጠራሉ:: ትርጉሙም "ጌታ ወደደን" እንደ ማለት ነው::

ያፍቅረነ እግዚእ የነበሩት በ14ኛው መቶ ክ/ዘ ሲሆን ቁጥራቸው ከ7ቱ ከዋክብት ነው:: ጻድቁ ከልጅነት ጀምሮ በሥርዓቱ ከማደጋቸው ባሻገር እጅግ የተማሩ እንደነበሩም ይነገርላቸዋል::

ለምናኔ ከወጡ በሁዋላ ከኖሩባቸው ቦታዎችም 3ቱ ተጠቃሽ ናቸው:: የመጀመሪያውና ትልቁን ሥፍራ የሚይዘው ደግሞ ደብረ በንኮል ነው:: ጻድቁ በዚህ ገዳም ከታላቁ ቅዱስ አባ መድኃኒነ እግዚእ ሥርዓተ ገዳምን : ትኅርምተ አበውን : ተጋድሎተ ቅዱሳንን አጥንተው ለመዓርገ ምንኩስና በቅተዋል::

በገዳሙም ለተወሰነ ጊዜ አገልግለው ወደ ጣና አካባቢ ከአቡነ ያሳይና ከአባ ሳሙኤል ዘዋሊ ጋር መጥተዋል:: የመምጣታቸው ምክንያትም ስብከተ ወንጌልን ለማዳረስና ገዳማትን ለመመሥረት ነው::

ሶስቱ ቅዱሳን ለተወሰነ ጊዜ ከቆዩ በሁዋላ አቡነ ሳሙኤል ወደ ዋልድባ ሲሔዱ አቡነ ያሳይ ደግሞ ማንዳባን አቀኑ:: ያፍቅረነ እግዚእም ጌታ ባዘዛቸው መሠረት ጣና ውስጥ ገዳም አቅንተው ኑረዋል:: ይህ ገዳማቸው ዛሬም ድረስ በስማቸው ይጠራል::

ጻድቁ አፍቀረነ እግዚእ 3ኛው የሚታወቁበት ገዳም ማኅበረ ዴጌ (ጻድቃነ ዴጌ) ሲሆን ገዳሙ በአክሱም ዙሪያ ይገኛል:: እርሳቸው 3ሺ ቅዱሳን የተሠወሩበትን ገዳም በማገልገላቸውም ዛሬም ድረስ በአካባቢው የታወቁ ሆነዋል::

በተረፈም አክሱም አካባቢ ሌሎች ገዳማትን እንዳቀኑም ይነገርላቸዋል:: ጻድቁ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ለብዙ ዘመናት በተጋድሎ : በስብከተ ወንጌልና ገዳማትን በማስፋፋት ከኖሩ በሁዋላ በዚህች ቀን ዐርፈው ለክብሩ : ለርስቱ በቅተዋል::

††† አምላከ ቅዱሳን በጻድቁ አማላጅነት ይቅር ብሎ በረከታቸውን ያሳድርብን::

††† ጥር 19 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ጻድቁ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ (አፍቀረነ እግዚእ ዘጉጉቤ - ጣና ውስጥ - ከሰባቱ ከዋክብት አንዱ)
2.አባ ባሱራ
3.ቅድስት ኔራ
4.ቅድስት በርስጢና
5.አባ ዝሑራ

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላዕክት
2.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
3.አባ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ (ታቦታቸው ጎንደር ከተማ ቀበሌ 09 አካባቢ ይገኛል)
4.አቡነ ስነ ኢየሱስ
5.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም

††† ቅዱሳንን ታስቡ ዘንድ ቸል አትበሉ::

††† "እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና::
ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና::
ለዘለዓለምም ይጠብቃቸዋል . . .
ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ::
በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ::
የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል::
አንደበቱም ፍርድን ይናገራል::
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው::
በእርምጃውም አይሰናከልም::" †††
(መዝ. 36:28-31)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
St. Abahor (Pihour) St. Bisoura (Pisoura) and their Mother Ampira (Asra).
††† እንኳን ለቅዱሳን አክሎግ ቀሲስ: መርምሕናም: ወዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ አክሎግ ሰማዕት †††

††† ቤተ ክርስቲያን ካፈራቻቸው ዓበይት ሰማዕታት አንዱ ይህ ቅዱስ ነው:: "አክሎግ" ማለት "በእግዚአብሔር ዘንድ ጣፋጭ (ተወዳጅ)" ማለት ነው:: እውነትም ጥዑም ዜና: ጣፋጭ ሕይወት ያለው አባት ነው:: "መልአክ ስምን ያወጣል" የሚባለው እንዲህ ላለው ነውና::

እርሱ የወላጆቹ ፍሬ ነው:: በ3ኛው መቶ ክ/ዘ የነበሩ ወላጆቹ ለልጃቸው ያወረሱት ሞልቶ የተረፈ ሃብታቸውን አልነበረም:: ይልቁኑ ፍቅረ ክርስቶስን: ምሥጢረ መጻሕፍትን: ክርስቲያናዊ ስምን ነው እንጂ::

ቅዱስ አክሎግ ገና ከልጅነቱ ወደ ት/ቤት ገብቶ: ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምሮ: ሐዲስ ኪዳንን በሙሉ: መኀልየ ነቢያትን: መዝሙረ ዳዊትን አክሎ በቃሉ አጠና:: ቅዱስ ቃሉ ለእርሱ እውቀት አልነበረም: ሕይወት እንጂ:: ሳይሰለች ያነበው: በሕይወቱም ይተረጉመው ነበርና::

በዚህ ንጹሕ ሕይወቱም ፈጣሪውን አስደስቶ ብዙ ተአምራትን ሠርቷል:: ከዚያም ተጋድሎውን ቀጥሎ በትሕርምት ኑሯል:: ቀሲስ ሆኖ ሲሾምም ቅዱሳን መላእክት "ይገባዋል!" ሲሉ 3 ጊዜ ጮሁ:: በጽድቅ ጸንቶም ዘመናት አለፉ::

በዘመነ ሰማዕታትም ነጭ በነጭ ለብሶ ብዙ መከራን ተቀበለ:: በዚህች ቀንም ከብዙ ተከታዮቹ ጋር ደሙ ፈሷል:: ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን "ጻድቅ: ንጹሕ: ድንግል: ባሕታዊ: ቀሲስ ወሰማዕት" ብላ ታከብረዋለች:: ጌታም "ስምህን ያከበረውን: የተሰየመውን እምርልሃለሁ" ብሎታል::

††† ቅዱስ መርምሕናም ሰማዕት †††

††† ሰማዕቱ በቤተ ክርስቲያን ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ዐበይት ቅዱሳን አንዱ ነው:: በየአብያተ ክርስቲያናቱ ከሚሳሉ ቅዱሳንም አንዱ ነው:: ሃገሩ አቶር (በፋርስ አካባቢ) ሲሆን አባቱ ሰናክሬም የሚባል ንጉሠ ነገሥት ነው::

እናቱ ምንም ክርስቲያን ብትሆንም ስለ ፈራች ሁለቱን ልጆቿን (መርምሕናምና ሣራን) ክርስትናን አላስተማረቻቸውም:: ሁለቱም ወጣት በሆኑ ጊዜም ከንጉሥ አባታቸው ጋር ይወጡ ይገቡ ነበርና እናታቸው በሐዘን ጸለየች:: ወዲያውም ወጣቷ ሣራ በለምጽ ተመታች::

የሚፈውሳት ጠፋ:: መርምሕናም ግን ጐበዝ ወጣት ነውና 40 የጦር አለቆችን ይመራ ነበር:: በዚያው በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ቅዱስ መርምሕናም 40 ተከታዮቹን ይዞ ለአደን ወደ ዱር ሲወጣ ከአባ ማቴዎስ ገዳማዊ ጋር ተገናኘ::

ጻድቁ ለብዙ ዓመታት በበርሃ የኖሩ አባት ናቸው:: አካላቸው በጸጉር ስለ ተሸፈነ ደንግጦ ሲሸሽ "ልጄ አትፍራ! እኔም እንዳንተ የክርስቶስ ፍጡር የሆንኩ ሰው ነኝ" አሉት::

እርሱ ግን "ደግሞ ክርስቶስ ማነው?" ሲል ጠየቃቸው:: አባ ማቴዎስም ምሥጢረ ክርስትናን ከመሠረቱ አስተምረው የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት ነገሩት::

ቅዱስ መርምሕናም ግን "ክርስቶስ አምላክ እንደ ሆነ አምን ዘንድ እህቴን አድንልኝ" አላቸው:: "አምጣት" ብለውት አመጣት:: ጻድቁ ጸሎት አድርሰው መሬትን ቢረግጧት ውኃን አፈለቀች:: "በእምነት: በስመ ሥላሴ ተጠመቁ" አሏቸው::

ቅዱሱ: እህቱ ሣራና 40 የጦር አለቆች ተጠምቀው ሲወጡ ሣራ ከለምጿ ነጻች:: ፈጽሞም ደስ አላቸው:: ወደ ቤተ መንግስት ተመልሰውም ቅዱስ መርምሕናም ከእናቱ: ከእህቱና ከ40 ተከታዮቹ ጋር ክርስቶስን ሊያመልኩ ጀመሩ::

ንጉሡ ሰናክሬም ግን ነገሩን ሲሰማ ተቆጣ:: እነርሱም ወደ ተራራ ሸሹ:: ንጉሡ "ልጆቼ! መንግስቴን ውረሱ" ብሎ ቢልክባቸውም እንቢ አሉ:: ስለ ተበሳጨም ቅዱስ መርምሕናምን: ቅድስት ሣራንና 40ውን ቅዱሳን በሰይፍ አስመታቸው::

ሥጋቸውን በእሳት ሊያቃጥሉ ሲሉ ግን መነዋወጥ ሆኖ ብዙ አረማውያን ሞቱ:: ንጉሡም አብዶ አውሬ (እሪያ) ሆነ:: ያን ጊዜ አባ ማቴዎስ ከበርሃ ወጥተው ንጉሡን ሰናክሬምን ፈወሱት::

እርሱም አምኖ የልጆቹና የ40ውን ሥጋ በክብር አኖረ:: በሃገሩ አቶርም የእመ ብርሃን ማርያምን ቤተ መቅደስ አነጸ:: በክርስትና ኑሮም ዐረፈ:: እርሱ ከተቀበረ በኋላ ግን የከለዳውያን ንጉሥ መጥቶ አቶርን ወረራት::

ንግሥቲቱን (የቅዱሳኑን እናት) ከሕፃኑ ልጇ ጋርም ገደለ:: በኋላም "ለጣዖት ስገዱ" ማለቱን የሰሙት የቅዱስ መርምሕናም ወታደሮች ደርሰው በምስክርነት ተሰየፉ:: ቁጥራቸውም 170,000 ሆነ::

††† ቅዱስ ዮሐንስ ጻድቅ (ወንጌሉ ዘወርቅ) †††

††† ቅዱሱ "ወንጌሉ ዘወርቅ" እየተባለ የሚጠራው ከሌሎች "ዮሐንስ" ከሚባሉ ቅዱሳን ለመለየት ቢሆንም ዋናው ምክንያት ግን እድሜ ልኩን የሚያነበው: ከእጁ የማይለየውና አቅፎት የሚተኛ በወርቅ የተለበጠ ወንጌል ስለ ነበረው ነው::

የቅዱስ ዮሐንስ ታሪኩ በሆነ መንገድ ከመርዓዊ (ሙሽራው) ገብረ ክርስቶስ እና ከቅዱስ ሙሴ ሮማዊ ጋር ተመሳሳይነት አለው::
ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
በሮም ግዛት ሥር የሚኖሩ አጥራብዮስና ብዱራ የሚባሉ ደጋግ ክርስቲያኖች ነበሩ:: እግዚአብሔር በቀደሰው ትዳር የሚኖሩና ነዳያንን የሚዘከሩ ነበሩና ይህንን ቅዱስ ወለዱ:: ስሙን ዮሐንስ ብለው: እንደሚገባም አሳድገው: ምሥጢረ መንግስተ ሰማያትን እንዲረዳ ለመምህር ሰጡት:: ቅዱስ ዮሐንስ ከመምህሩ ዘንድ ቁጭ ብሎ መጻሕፍተ ቤተ ክርስቲያንን ተማረ::

ለወላጆቹ ቅንና ታዛዥ ነበርና አባቱ "ልጄ! የምትፈልገውን ጠይቀኝ:: ምን ላደርግልህ ትወዳለህ?" አለው:: ቅዱስ ዮሐንስ ዘንድሮ እኛን የሚያምረን ሁሉ አላሰኘውም:: አባቱን "ቅዱስ ወንጌልን ግዛልኝ: በወርቅም አስለብጠው" አለው:: አባትም የተባለውን ፈጸመ::

ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ከዚህ ዓለም ተለይቶ እስካረፈባት ቀን ድረስ ቅዱስ ዮሐንስና የወርቅ ወንጌሉ ተለያይተው አያውቁም:: ሁሌም ያለመታከት ያነበዋል:: ሲቀመጥም ሲነሳም: ሲሔድም ሲተኛም አብሮት ነበር::

ቅዱስ ዮሐንስ ወጣት በሆነ ጊዜ ወላጆቹ ይድሩት ዘንድ ተዘጋጁ:: ልብሰ መርዐም (የሙሽራ ልብስ) አዘጋጁ:: በዚያው ሰሞን ግን አንድ እንግዳ መነኮስ ወደ ቤታቸው መጥቶ ያድራል:: በዚያች ሌሊት መነኮሱ በጨዋታ መካከል ስለ ቅዱሳን መነኮሳት ተጋድሎና ክብር ነገረው:: የሰማው ነገር ልቡናውን የማረከው ቅዱስ ዮሐንስ ከዚያች ቀን ጀምሮ ወደ ፈጣሪው ይለምን ነበር::

አንድ ቀን ግን ያ መነኮስ በድጋሚ መጥቶ አደረ:: ቅዱስ ዮሐንስ መነኮሱን ወደ ገዳም እንዲወስደው ቢጠይቀው "አይሆንም: አባትህ ያዝንብኛል" አለው:: ቅዱሱ ግን "በእግዚአብሔር ስም አማጽኜሃለሁ" ስላለው ሁለቱም በሌሊት ወጥተው ወደ ገዳም ሔዱ::

አበ ምኔቱ "ልጄ! የበርሃውን መከራ አትችለውም: ይቅርብህ" ቢለውም "አባቴ! አይድከሙ:: ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር አይለየኝም'' ስላላቸው እንደሚገባ ፈትነው አመንኩሰውታል:: ቅዱስ ዮሐንስ ከመነኮሰ በኋላ በጾም: በጸሎት: በስግደትና በትሕርምት ያሳየው ተጋድሎ በርካቶችን አስደነቀ::

ለሥጋው ቦታ አልሰጣትምና በወጣትነቱ አካሉ ረገፈ:: ቆዳውና አካሉም ተገናኘ:: ሥጋውን አድርቆ ነፍሱን አለመለማት:: በእንዲሕ ያለ ሕይወት ለ7 ዓመታት ከተጋደለ በኋላ በራዕይ "ወደ ወላጆችህ ተመለስ" እያለ 3 ጊዜ አናገረው::
ቅዱስ ዮሐንስ ወደ አበ ምኔቱ ሔዶ ቢጠይቀው "ራዕዩ ከእግዚአብሔር ነው" ብሎ ወደ ቤተሰቦቹ አሰናበተው::
ቅዱስ ዮሐንስ በላዩ ላይ የነበረችውን ልብስ በመንገድ ለነዳይ ሰጥቶ: በፈንታው ቆሻሻ ጨርቅ ለብሶ ከወላጆቹ በር ላይ ለመነ:: "እባካችሁ አስጠጉኝ" አላቸው:: ወላጆቹ በጭራሽሊለዩት አልቻሉም:: ነገር ግን አሳዝኗቸዋልና በበራቸው አካባቢ ትንሽ ቤት ሠሩለት::

በዚያች በዓት ውስጥ እንዳስለመደ በትጋት ለ7 ዓመታት ተጋደለ:: በእነዚህ ዓመታት እንኳን ሌላው ሰው ወላጆቹም ቢሆኑ ፍርፋሪ ከመስጠት በቀር አይቀርቡትም ነበር:: ምክንያቱ ደግሞ "ይሸተናል" የሚል ነበር:: በመጨረሻም መልአከ እግዚአብሔር ከሰማይ ወርዶ "ከ7 ቀናት በኋላ ታርፋለህ" አለው::

እናቱን ጠርቶ "አንድ ነገር ልለምንሽ" አላት:: "እሺ" አለችው:: "ከሞትኩ በኋላ በለበስኳት ጨርቅ እንድትገንዙኝ: በበዓቴ ውስጥም እንድትቀብሩኝ" አላትና የወርቅ ወንጌሉን አውጥቶ ሰጣት:: ያን ጊዜ አባቱም ደርሶ ነበርና ደነገጡ::

የወርቅ ወንጌሉን ለዩት:: ልጃቸውን ግን መለየት አልቻሉምና እያለቀሱ ስለ ልጃቸው የሚያውቀው ካለ እንዲነግራቸው ለመኑት:: እርሱም "ልጃችሁ ዮሐንስ እኔ ነኝ" አላቸው::

በዚያ ቅጽበት ወላጆቹ የሰሙትን ማመን አልቻሉም:: በፍጹም ዋይታ እየጮሁ አለቀሱ:: ለቅሷቸውን የሰሙ ሁሉ ተሰበሰቡ:: ለ7 ቀናት እኩሉ እያለቀሰ: እኩሉ እየተባረከ በዓቱን ከበው ሰነበቱ:: በ7ኛው ቀን መልአኩ መጥቶ በክብር ነፍሱን ተቀበለ::

እናቱ የልጇን አደራ ረስታ (እሷስ መልካም አደረግሁ ብላ ነው) ለሠርጉ ባዘጋጀችው የወርቅ ልብስ ገነዘችው:: ወዲያው ግን በጽኑ ታመመች:: አባት ግን ፈጠን ብሎ በዚያች ጨርቅ ገንዞ በበዓቱ ውስጥ ቀበረው:: ያን ጊዜ እናት ፈጥና ዳነች:: ከቅዱሱ መቃብርም ብዙ ተአምራትና ፈውስ ተደርጓል::

††† ቸሩ እግዚአብሔር ከወዳጆቹ በረከት ያሳትፈን፡፡

††† ጥር 20 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ (ሰማዕትና ጻድቅ)
2.ቅዱስ መርምሕናም ሰማዕት (ቅዳሴ ቤቱ)
3.ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ (ቅዳሴ ቤቱ)
4.አባ አብድዩ ጻድቅ
5.ቅዱስ ብሕኑ ሰማዕት
6.ቅዱስ አብሮኮሮስ ሐዋርያ (የወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር)
7.አባ ኖሕ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር
2.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሊቀ ሠራዊት
3.ቅዱስ አሞንዮስ
4.ቅዱስ ካሌብ ንጉሠ ኢትዮጵያ
5.ቅድስት ሳድዥ የዋሂት

††† "እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ: የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ: በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ:: በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሱ:: የመዳንንም ራስ ቁር: የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ:: እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው:: በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ:: በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ::" †††
(ኤፌ. ፮፥፲፬)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
ቅዱስ አብሮኮሮስ ሐዋርያ
(Saint Prochorus The Desciple)

=>በዘመነ ሐዋርያት ዝነኛ ከነበሩ ቅዱሳን አንዱ ቢሆንም አሁን እየተዘነጋ ነው:: ቁጥሩ ከ72ቱ አርድእት ሲሆን የዮሐንስ ወንጌላዊ ደቀ መዝሙር ሆኖ የሰኔ ጐልጐታን ምሥጢር ጽፏል:: ከአርድእት ባለ ረዥም ዕድሜ እና ከዕርገተ ክርስቶስ በሁዋላ ለ80 ዓመታት ያስተማረ ደግ ሐዋርያ ነው::

<< እጅግ አርጅቶ ወደ ወደደው ክርስቶስ የሔደው ጥር 20  ነውና በረከቱ ይደርብን !! >>


❇️ዝክረቅዱሳን (ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት)❇️

" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
https://www.tg-me.com/zikirekdusn
እንኳን ለእመቤታችን ንጽሕት ድንግል ወላዲተ አምላክ ማርያም ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

† ዕረፍተ ድንግል †

††† እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድመ ዓለም በአምላክ ልቡና ታስባ ትኖር ነበር:: ከነገር ሁሉ በፊት እግዚአብሔር እናቱን ያውቃት ነበር::

*ዓለም ተፈጥሮ: አዳምና ሔዋን ስተው: መርገመ ሥጋና መርገመ ነፍስ አግኝቷቸው: በኃዘን ንስሃ ቢገቡ "እትወለድ እም ወለተ ወለትከ - ከ5 ቀን ተኩል (5500 ዘመናት) በሁዋላ ካንተ ባሕርይ ከምትገኝ ንጽሕት ዘር ተወልጄ አድንሃለሁ" ብሎ ተስፋ ድኅነት ሰጠው::

*ከአዳም አንስቶ ለ5500 ዓመታት አበው: ነቢያትና ካህናት ስለ ድንግል ማርያም ብዙ ሐረገ ትንቢቶችን ተናገሩ:: መዳኛቸውን ሱባኤ ቆጠሩላት:: ምሳሌም መሰሉላት:: ከሩቅ ዘመን ሁነውም ሊያገኟት እየተመኙ እጅ ነሷት::
"እምርሑቅሰ ርእይዋ: ወተአምኅዋ" እንዲል::

††† የድንግል ማርያም ሐረገ ትውልድ
*ከአዳም በሴት
*ከያሬድ በሔኖክ
*ከኖኅ በሴም
*ከአብርሃም በይስሐቅ
*ከያዕቆብ በይሁዳና በሌዊ
*ከይሁዳ በእሴይ: በዳዊት: በሰሎሞንና በሕዝቅያስ ወርዳ ከኢያቄም ትደርሳለች::

*ከሌዊ ደግሞ በአሮን: አልዓዛር: ፊንሐስ: ቴክታና በጥሪቃ አድርጋ ከሐና ትደርሳለች::

*አባታችን አዳም ከገነት በወጣ በ5,485 ዓመት ወላዲተ አምላክ ንጽሕና ሳይጐድልባት: ኃጢአት ሳያገኛት: ጥንተ አብሶ ሳይደርስባት ከደጋጉ ኢያቄም ወሐና ትወለዳለች:: (ኢሳ. 1:9, መኃ. 4:7) "ወኢረኩሰት በምንትኒ እምዘፈጠራ" እንዳለ:: (ቅዱስ ቴዎዶጦስ ዘዕንቆራ)

ከዚያም ከእናት ከአባቷ ቤት ለ3 ዓመታት ቆይታ ወደ ቤተ መቅደስ ትገባለች:: በቤተ መቅደስም ለ12 ዓመታት ፈጣሪዋን እግዚአብሔርን እያመሰገነችና እያገለገለች: እርሷን ደግሞ መላእክተ ብርሃን እያገለገሏት: ሕብስት ሰማያዊ ጽዋዕ ሰማያዊ እየመገቧት ኑራለች:: 15 ዓመት በሞላት ጊዜ አረጋዊ ዮሴፍ ያገለግላት ዘንድ ወደ ቤቱ ወሰዳት::

*በዚያም መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ዜና ድኅነትን ነግሯት አካላዊ ቃልን በማሕጸንዋ ጸነሰችው:: ነደ እሳትን ተሸከመችው: ቻለችው:: "ጾርኪ ዘኢይትጸወር: ወአግመርኪ ዘኢይትገመር" እንዳለ:: (ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ለብሐዊ)

*ወልደ እግዚአብሔርን ለ9 ወራት ከ5 ቀናት ጸንሳ: እንበለ ተፈትሆ (በድንግልና) ወለደችው:: (ኢሳ. 7:14) "ኢየሱስ" ብላ ስም አውጥታለት በገሊላ ለ2 ዓመታት ቆዩ::

*አርዌ ሔሮድስ እገድላለሁ ብሎ በተነሳበት ወቅትም ልጇን አዝላ በረሃብ እና በጥም: በላበትና በድካም: በዕንባና በኃዘን ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት ከገሊላ እስከ ኢትዮዽያ ተሰዳለች:: ልጇ ጌታችን 5 ዓመት ከ6 ወር ሲሆነው: ለድንግል ደግሞ 21 ዓመት ከ3 ወር ሲሆናት ወደ ናዝሬት ተመለሱ::

*በናዝሬትም ለ24 ዓመታት ከ6 ወራት ልጇን ክርስቶስን እያሳደገች: ነዳያንን እያሰበች ኑራለች:: እርሷ 45 ዓመት ልጇ 30 ዓመት ሲሆናቸው ጌታችን ተጠምቆ በጉባኤ ትምሕርት: ተአምራት ጀመረ:: ለ3 ዓመታት ከ3 ወራትም ከዋለበት እየዋለች: ካደረበትም እያደረች ትምሕርቱን ሰማች::

*የማዳን ቀኑ ደርሶ ልጇ ክርስቶስ ሲሰቀልም የመጨረሻውን ፍጹም ሐዘን አስተናገደች:: አንጀቷ በኃዘን ተቃጠለ:: በነፍሷም ሰይፍ አለፈ:: (ሉቃ. 2:35) ጌታ በተነሳ ጊዜም ከፍጥረት ሁሉ ቀድማ ትንሳኤውን አየች:: ለ40 ቀናትም ሳትለይ ከልጇ ጋር ቆየች::

*ከልጇ ዕርገት በሁዋላ በጽርሐ ጽዮን ሐዋርያትን ሰብስባ ለጸጋ መንፈስ ቅዱስ አበቃች:: በጽርሐ ጽዮንም ከአደራ ልጇ ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ለ15 ዓመታት ኖረች:: በእነዚህ ዓመታት ሥራ ሳትፈታ ስለ ኃጥአን ስትማልድ: ቃል ኪዳንን ከልጇ ስትቀበል: ሐዋርያትን ስታጽናና: ምሥጢርም ስትገልጽላቸው ኑራለች::

*ዕድሜዋ 64 በደረሰ ጊዜ ጥር 21 ቀን መድኃኒታችን አእላፍ ቅዱሳንን አስከትሎ መጣ:: ኢየሩሳሌምን ጨነቃት:: አካባቢውም በፈውስ ተሞላ:: በዓለም ላይም በጐ መዓዛ ወረደ:: እመ ብርሃን ለፍጡር ከዚያ በፊት ባልተደረገ: ለዘለዓለምም ለማንም በማይደረግ ሞገስ: ክብርና ተአምራት ዐረፈች:: ሞቷ ብዙዎችን አስደንቁአል::
"ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ::
ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኩሉ::" እንዲል::

*ከዚህ በሁዋላ መላእክት እየዘመሩ: ሐዋርያቱም እያለቀሱ ወደ ጌቴሴማኒ: በአጐበር ሥጋዋን ጋርደው ወሰዱ:: ይሕንን ሊቃውንት:-
"ሐራ ሰማይ ብዙኃን እለ አልቦሙ ሐሳበ::
እንዘ ይዜምሩ ቅድሜኪ ወመንገለ ድኅሬኪ ካዕበ::
ማርያም ሞትኪ ይመስል ከብካበ" ሲሉ ይገልጡታል::

*በወቅቱ ግን አይሁድ በክፋት ሥጋዋን እናቃጥል ስላሉ ቅዱስ ገብርኤል (ጠባቂ መልአክ ነው) እነርሱን ቀጥቶ: እርሷን ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ወስዶ በዕጸ ሕይወት ሥር አኑሯታል:: በዚያም መላእክት እያመሰገኗት ለ205 ቀናት ቆይታለች::

*ቅዱስ ዮሐንስ መጥቶ ለሐዋርያቱ ክብረ ድንግልን ቢነግራቸው በጐ ቅንአት ቀንተው በነሐሴ 1 ሱባኤ ጀመሩ:: 2ኛው ሱባኤ ሲጠናቀቅም ጌታ የድንግል ማርያምን ንጹሕ ሥጋ ሰጣቸው:: እየዘመሩም በጌቴሴማኒ ቀብረዋታል::

*በ3ኛው ቀን (ነሐሴ 16) እንደ ልጇ ባለ ትንሳኤ ተነስታ ዐርጋለች:: ትንሳኤዋንና ዕርገቷንም ደጉ ሐዋርያ ቅዱስ ቶማስ አይቶ: መግነዟን ተቀብሏል:: ሐዋርያቱም መግነዟን ለበረከት ተካፍለው: እንደ ገና በዓመቱ ነሐሴ 1 ቀን ሱባኤ ገቡ::

*ለ2 ሳምንታት ቆይተው: ሁሉንም ወደ ሰማይ አወጣቸው:: በፍጡር አንደበት ተከናውኖ የማይነገር ተድላ: ደስታና ምሥጢርንም አዩ:: ጌታ ራሱ ቀድሶ ሁሉንም አቆረባቸው:: የበዓሉን ቃል ኪዳን ሰምተው: ከድንግል ተባርከው ወደ ደብረ ዘይት ተመልሰዋል::

††† ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን: ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኚልን:: አእምሮውን: ለብዎውን: ጥበቡን በልቡናችን ሳይብን አሳድሪብን:: †††

††† ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሊቅ †††

††† ለዚህ ቅዱስ አባት ብጹዕ መባል ተገብቷል:: ክቡር: ምስጉን: ንዑድ ሰው ነውና:: በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን በቂሣርያ ቀዸዶቅያ የተወለደው ቅዱሱ ሰው ለደሴተ ኑሲስ ብርሃኗ ነው:: አባቱ ኤስድሮስ: እናቱ ኤሚሊያ: ወንድሞቹ ቅዱሳን "ባስልዮስ: ዼጥሮስ: መክርዮስና መካርዮስ" ይባላሉ::

የተቀደሰች እህቱም ማቅሪና ትባላለች:: ከዚህ የተባረከ ቤተሰብ ለቅድስና ያልበቃ አንድም ሰው የለም:: ሊቁ ቅዱስ ጐርጐርዮስም ከማር በጣፈጠ ዜና ሕይወቱ እንደ ተጻፈው:-
*በልጅነቱ ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምሯል::
*ሥጋውያን ጠቢባንን ያሳፍር ዘንድም የግሪክን ፍልሥፍና በልኩ ተምሯል::
*በታላቅ ወንድሙ ቅዱስ ባስልዮስ መሪነት ገዳማዊ ሕይወትን ተምሯል::
*በመንኖ ጥሪት ተመስግኗል::
*ተገብቶትም በኑሲስ ደሴት ላይ ዻዻስ ሆኗል::
*እርሱ ሲሔድ በከተማው የነበሩ ክርስቲያኖች 11 ብቻ የነበሩ ሲሆን እርሱ ሲያርፍ ክርስቶስን የማያመልኩ ሰዎች ቁጥር 11 ብቻ ነበር::
*ቅዱስ ጐርጐርዮስ ፍጹም ሊቅ ነበርና ከቁጥር የበዙ ድርሳናትን ደርሷል::
*ታላቁን ጉባኤ ቁስጥንጥንያን (በ381 ዓ/ም) መርቷል:: ብዙ መናፍቃንንም አሳፍሯል::

ከንጽሕናው የተነሳ መላእክት ያቅፉት: እመ ብርሃንም ትገለጥለት ነበር:: ለ33 ዓመታት እንደ ሐዋርያት ኑሮ በዚህ ቀን ድንግል ጠራችው:: ቀድሶ አቁርቦ: ሕዝቡን አሰናብቶ: የቤተ መቅደሱን ምሰሶ እንደ ተደገፈ ዐርፎ ተገኝቷል:: በዝማሬና በፍቅር ቀብረውታል::
††† ቅድስት ኢላርያ †††

††† "ኢላርያ" ማለት "ፍሥሕት (ደስ የተሰኘች)" እንደ ማለት ነው:: ከተባረኩ ቅዱሳት አንስት ትልቁን ሥፍራ ትይዛለች:: ማን እንደ እርሷ!

ቅድስት ኢላርያ ማለት:-
*የታላቁ ንጉሠ ነገሠት: የደጉ ዘይኑን (Emperor Zenon) የበክር ልጅ
*በ6ኛው መቶ ክ/ዘመን የተወለደች
*ትምሕርተ ሃይማኖትን: ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የተማረች
*ምድራዊ ንግሥናን ንቃ ፍቅረ ክርስቶስን የመረጠች
*የአባቷን ቤተ መንግስት ትታ ከሮም ግዛት ወደ ግብጽ (ገዳመ አስቄጥስ) የወረደች:
*ስሟን ከኢላርያ ወደ ኢላርዮን ቀይራ በወንዶች ገዳም የመነኮሰች
*ራሷን በፍጹም ገድል ቀጥቅጣ ከወንዶቹ በላይ በሞገስ ከፍ ከፍ ያለች
*ትንሽ እህቷን ጨምሮ በርካቶችን የፈወሰች
*በእርሷ ምክንያት ለግብጽና በመላው ዓለም ለሚገኙ ገዳማት ብዙ ቸርነት በዘይኑን የተደረገላት ታላቅ እናት ናት::

ቅድስት ኢላርያ ማንም ሴት መሆኗን ሳያውቅባት: አባ ኢላርዮን እንደ ተባለች በዚህች ቀን ዐርፋለች:: ቤተ ክርስቲያንም እነሆ ላለፉት 1,400 ዓመታት: ቅድስቲቱንና የተባረከ አባቷን ዘይኑንን: ስለ በጐነታቸውና ውለታቸው ታስባቸዋለች::

††† የእመቤታችን ድንግል ማርያም ጣዕሟ: ፍቅሯ: ጸጋዋና በረከቷ ይደርብን:: †††

††† ጥር 21 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
1.በዓለ አስተርዕዮ ማርያም (እመቤታችን ከእረፍቱዋ በሁዋላ ለደቀ መዛሙርት በዚሁ ቀን ተገልጣ ነበር)
2.ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ (ታላቅ ሊቅና ጻድቅ)
3.ቅድስት ኢላርያ እናታችን (የዘይኑን ንጉሥ ልጅ)
4.ቅዱስ ኤርምያስ ነቢይ
5.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ
6.ቅዱስ ኒቆላዎስ ሰማዕት
7.አባ ፊቅጦር

††† ወርሐዊ በዓላት
1.አባ ምዕመነ ድንግል
2.አባ አምደ ሥላሴ
3.አባ አሮን ሶርያዊ
4.አባ መርትያኖስ
5.አበው ጎርጎርዮሳት

††† "ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን::
እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን::
አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነስ::
አንተና የመቅደስህ ታቦት::
ካህናቶችህ ጽድቅን ይልበሱ::
ቅዱሳንህም ደስ ይበላቸው::
ስለ ባሪያህ ስለ ዳዊት. . ."
(መዝ. 131:7)

††† "ወዳጄ ሆይ! ተነሺ::
ውበቴ ሆይ! ነዪ::
በዓለት: በንቃቃትና በገደል መሸሸጊያ ያለሽ ርግብ ሆይ!
ቃልሽ መልካም: ውበትሽም ያማረ ነውና:
መልክሽን አሳዪኝ::
ድምጽሽንም አሰሚኝ::"
(መኃ. 2:13)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

https://www.tg-me.com/zikirekdusn
እንኳን አደረሳችሁ


በረከቱ ይደርብና የቅዱስ ገላውዴዎስና የቅድስት እምነ ጽዮን ፍሬ አቡነ ቀውስጦስ ሰማዕተ ጽድቅ ጥር 21  ዕረፍቱ

ዝክረ ቅዱሳን (ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት)

" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
https://www.tg-me.com/zikirekdusn
✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞

ጥር 22 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

++ አባ እንጦንስ ++

=>በቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ "ታላቁ / ዓቢይ / THE GREAT" የሚል ስም የሚሰጣቸው አባቶች የተለዩ
ናቸው::
አንድም እጅግ ብዙ ትሩፋቶችን የሠሩ ናቸው:: በሌላ
በኩል ደግሞ በተመሳሳይ ስም ከሚጠሩ ሌሎች ቅዱሳን
እንለይበታለን::

+ገዳማዊ ሕይወት ጥንቱ ብሉይ ኪዳን ነው::
በቀዳሚነትም በደብር ቅዱስ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ደቂቀ
ሴት እንደ ጀመሩት
ይታመናል:: ሕይወቱ በጐላ: በተረዳ መንገድ የታየው ግን
በታላቁ ጻድቅ ሄኖክ: ከዚያም በቅዱሱ ካህን መልከ
ጼዴቅ
አማካኝነት ነው::

+ቀጥሎም እነ ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ: እነ ኤልሳዕ ደቀ
መዝሙሩ ኑረውበታል:: በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ሙሉ
ሕይወቱን በገዳም
(በበርሃ) ያሳለፈው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ
ቅድሚያውን ይይዛል::

+ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ
በገዳመ ቆረንቶስ ለ40 ቀናት በትሕርምት ኑሮ ገዳማዊ
ሕይወትን
ቀድሷል: አስተምሯል:: በዘመነ ስብከቱም ያድርባት
የነበረችው የደብረ ዘይቷ በዓቱ (ኤሌዎን ዋሻ) በራሷ
ለዚህ ሕይወት
ትልቅ ማሳያ ናት::

+ከጌታ ዕርገት በኋላም ክርስቲያኖቹ የዓለም ሁካታ
ሲሰለቻቸው: አንድም በንጹሕና በተሸከፈ ልቡና
ለፈጣሪያቸው መገዛትን
ሲሹ ከከተማ ወጣ እያሉ ይኖሩ እንደ ነበር የታሪክ
መዛግብት ያሳያሉ:: አኗኗራቸውም በቡድንም: በነጠላም
ሊሆን ይችላል::

+ዋናው ነገር ግን በጾምና በጸሎት መትጋታቸው ነው::
ይሕም ሲያያዝ እስከ 3ኛው መቶ ክ/ዘመን ደረሰ:: በዚህ
ዘመን
ግን አባ ዻውሊ የሚባል አንድ ንጹሕ ክርስቲያን ይሕንን
ሕይወት ወደ ሌላ ደረጃ ከፍ አደረገው::
ለ80 ዓመታት ሰው ሳያይ ተጋድሎ 'የባሕታውያን አባት'
ተባለ:: ደንብ ያለው ተባሕትዎም ጀመረ::

+ይህ ከሆነ ከ20 ዓመታት በኋላ ደግሞ አባ እንጦንስ
የሚባሉ ደግ ክርስቲያን ይህንን ገዳማዊ ሕይወት በሌላ
መንገድ
አጣፈጡት:: በቅዱስ ሚካኤል አመንኳሽነት ገዳማዊ
ሕይወት በምንኩስና ተቃኘ:: ስለዚህም አባ እንጦንስ
የመነኮሳት አባት ተባሉ::

+እርሳቸውም ሕይወቱን ለማስፋፋት ከተለያዩ አሕጉር ደቀ
መዛሙርትን እየተቀበሉ አመንኩሰዋል:: ቅዱሳን የአባ
እንጦንስ
ልጆችም ወደየ ሃገራቸው ተመልሰው: ሕይወቱን በተግባር
አሳይተው ገዳማዊነትን አስፋፍተዋል::

+"+ አባ እንጦንስ +"+

+አባ እንጦንስ የመነኮሳት ሁሉ አባታቸው: ለገዳማውያን
ሁሉም ሞገሳቸው ናቸው:: እንዲያውም ብዙ ጊዜ "ኮከበ
ገዳም:
ማኅቶተ ገድል (የበርሃው ኮከብ: የተጋድሎ መብራት)"
ተብለውም ይጠራሉ::

+ቤተ ክርስቲያን ለጀማሪዎች ትልቅ ትኩረት ትሰጣለች::
ለምሳሌ:- አባ ዻውሊን (የካቲት 2 የሚከበሩ)
ለብሕትውና
መሠረትን ስለ ጣሉ "አበ ባሕታውያን" ብላ ታከብራለች::
አባ እንጦንስን ደግሞ "አበ መነኮሳት (የመነኮሳት አባት):
ቀዳሚሆሙ ለመነኮሳት (ለመነኮሳት ቀዳሚና ጀማሪ)
ስትል ትጠራቸዋለች::

+አባ እንጦንስ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ለሚነሱ ቅዱሳን
መነኮሳት ሁሉ መንገድን ይጠርጉ ዘንድ ብዙ መከራን
በትዕግስትና
በአኮቴት ተቀብለዋል:: ላለፉት 1,700 ዓመታት እንደ
ሻማ እየቀለጡ ያበሩ አበው ቅዱሳን ሁሉ የአባ እንጦንስ
ልጆች ናቸው::

+ከምጥ የከፋ የዲያብሎስ ፈተናን ተቀብለው ከመንፈሳዊ
አብራካቸው ቅዱሳኑን ወልደዋል:: የመነኮሳት አለቃ
የሆኑትን
ታላቁን መቃርዮስን ጨምሮ በርካቶችን አመንኩሰው
ለቅድስና አብቅተዋል::

+አባ እንጦንስ ግብጻዊ ሲሆኑ የተወለዱት አቅማን
በምትባል ቦታ አካባቢ ነው:: ጊዜውም በ252 ዓ/ም
ነው:: የተባረኩ
ወላጆች ለቅዱሱ እንጦንስና አስከትለው ለወለዷት ሴት
ልጃቸው አስቀድመው ፍቅረ ክርስቶስን: አስከትለውም
ሃብት
ንብረታቸውን አውርሰው ዐርፈዋል::

+በዚህ ጊዜ የአባ እንጦንስ እድሜ አፍላ ወጣትነት ላይ
ነበር:: በልጅነት ጊዜአቸውም አባ እንጦንስን ሲስቁ:
ሲጫወቱ:
አልያም ሲቀልዱ አየሁ የሚል ሰው አልነበረም:: ፍጹም
ቁም ነገረኛና ታዛዥ: በዚያ ላይም አስተዋይ ነበሩና ሙሉ
ጊዜአቸውንም ከቅዱስ ቃሉ በመመገብ: በትምሕርትና
በማስቀደስ ያሳልፉ ነበር::

+ዘወትርም ዜና ሐዋርያትን እያነበቡ በመንፈሳዊ ቅናት
ይቃጠሉ ነበር:: በጊዜው የምናኔ ሕይወት ጐልቶ ባለ
መገለጡ አባ
እንጦንስ የሚያደርጉት ይጨንቃቸው ነበር:: ሲጸልዩም
"አበው ሐዋርያት ይሕንን ክፉ ዓለም ንቃችሁ ጌታችሁን
የተከተላችሁበት ጥበብ እንደ ምን ያለ ነው!" እያሉ
ይደነቁ ነበር:: መሻታቸውን ያወቀ ጌታም ምሥጢርን
ገለጠላቸው::

+አንድ ቀን በቅዳሴ ላይ ወንጌል ሲነበብ ካህኑ ስለ
ምናኔ የሚጠቅሰውን ክፍል አነበበ:: ለአንድ ባለ ጠጋ
ሕግጋትን
ከነገረው በኋላ "ፍጹም ልትሆን ከወደድክስ ያለህን ሁሉ
ሸጠህ ተከተለኝ" (ማር. 10:17) የሚለውን ጥቅስ
ሲሰሙ
ተገርመው "ጌታ ሆይ! ይህንን የተናገርኸው ለእኔ ነው"
ሲሉ አሰቡ:: በቀጥታም ሃብታቸውን ለአካባቢው ሰው
አካፍለው:
እህታቸውን ከደናግል ማኅበር ደምረው እርሳቸው ወደ ዱር
ሔዱ::

+ከዚህች ቀን ጀምረው አባ እንጦንስ ከ80 እስከ መቶ
ለሚገመቱ ዓመታት ከአጋንንት ጋር በጦርነት ነበር
የኖሩት::
በንጹሕ አምልኮታቸውና በቅድስናቸው የቀና ጠላት
ሰይጣን በብዙ ጐዳና ፈተናቸው:: አቅም ቢያጥረው
አራዊትን መስሎ
ታገላቸው::

+በዚህ አልሳካ ቢለው የእሳት ሰንሰለትን አምጥቶ
ገረፋቸው:: በሞትና በሕይወት መካከል ጥሏቸው ሔደ::
ወድቀው
ያገነኟቸው ሰዎች ለዘመዶቻቸው ሰጥተዋቸው አገገሙ::
ልክ ሲነቁ ግን ፈጥነው ወደ በርሃ ተመለሱ::

+ሰይጣን በርሃው የቅዱሳን ማደሪያ እንዳይሆን ሰግቷልና
ጨክኖ ታገላቸው:: ግን አልቻላቸውምና ተረታ:: አምላከ
ኃያላን
ክርስቶስ ከቅዱሱ ጋር ነበርና:: ከዚህ በኋላ ግን ጸጋው
በዝቶላቸው ድውያንን የሚፈውሱና ሰይጣን
የማይቀርባቸው ሰው
ሆኑ::

+በረዥም ዘመነ ቅድስናቸውም:-
1.ብዙ አርድእትን ከመላው ዓለም ሰብስበው:
አስተምረው: ምናኔ ከግብጽ ማዶ በመላው ዓለም
አስፋፉ::
2.በደመና እየተጫኑ ብዙ አሕጉራትንም እየዞሩ ሰበኩ::
በዚህም አሕዛብን ወደ እምነት: ኃጥአንን ወደ ንስሃ
መለሱ::
3.ጊዜው ዘመነ ሰማዕታት ነበርና ወደ አደባባይ ሒደው
ከሃዲዎችን ገሠጹ:: ማንም ደፍሮ ግን አልገደላቸውም::

+እነዚህንና ሌሎች ተግባራትን እየሠሩ በቅዱስ ሚካኤል
እጅ መነኮሱ:: እርሳቸውም ብዙዎችን አመነኮሱ::
አርጅተው እንኳ
ከተጋድሎ ያላረፉት አባታችን የጣመ ነገር ቀምሰው:
ገላቸውን ታጥበው አያውቁም:: በ372 ዓ/ም በዚህች ቀን
ሲያርፉም
ዕድሜአቸው 120 ደርሶ ነበር::

+የአባ እንጦንስን በዓል ለማክበር የምትሹ ቤተ
ክርስቲያናቸው ጎንደር ከተማ ከቀሃ ኢየሱስ በላይ
ይገኛል::

<< ለአባታችን እንጦንዮስ / እንጦንስ / እንጦኒ ክብር
ይገባል:: >>

+" ቅዱስ ዑራኤል "+

+በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ከ7ቱ ሊቃነ
መላእክት አንዱ የሆነው ቅዱስ ዑራኤል:-
1.ድንግል ማርያም በአካለ ሥጋ እያለች ወደ ሰማይ
አሳርጉዋታል:: በሠረገላ ብርሃን ጭኖ: በክንፎቹም
ተሸክሞ: አስቅድሞ
ገነትን ቀጥሎም ሲዖልን አስጐብኝቷታል:: በዚህም
ምክንያት እመ ብርሃን ስለ ኃጥአን የምታለቅስ:
የምትለምንና የምትማልድ
ሆናለች:: ለምናም አልቀረች የምሕረት ቃል ኪዳን
ተቀብላለች::
2.ቅዱሱ መልአክ እመ ብርሃንን በስደቷ ጊዜ ወደ
ኢትዮዽያ መርቶ አምጥቷታል:: በክንፉ ተሸክሞ: በ4
አቅጣጫ አዙሮ
አሳይቶ አሥራት እንድትቀበል አድርጉዋል::
3.ጌታችን በተሰቀለ ጊዜ ደሙን በጽዋዕ አድርጐ
በኢትዮዽያ ወንዞች ላይ አፍስሷል::
4.ለብዙ ቅዱሳን (አባ ጊዮርጊስን ጨምሮ) ጽዋዐ ልቡናን
አጠጥቷል::

✞አምላከ ቅዱሳን ስለ ወዳጆቹ በጐ ምኞታችንን
ይፈጽምልን:: ከበረከታቸውም ያድለን::

✞ጥር 22 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=

1.ቅዱስ አባ እንጦንስ (የመነኮሳት አባት-የበርሐው
ኮከብ /ልደቱና ዕረፍቱ)
2.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላዕክት (ለተጠሙ ጽዋዓ
ልቡናን የሚያጠጣ: ምሥጢር ገላጭ መልዐክ)
3.ቅዱስ ሚናስ ኤዺስ ቆዾስ

ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ
3.ቅዱስ ደቅስዮስ (የእመቤታችን ወዳጅ)
4.አባ እንጦንስ አበ መነኮሳት
5.አባ ዻውሊ የዋህ

++"+ እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ::
መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ:: ነፍሱን ሊያድን የሚወድ
ሁሉ
ያጠፋታል:: ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ
ያገኛታል:: +"+ (ማቴ. 16:24)

✞✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር
2024/09/30 19:24:33
Back to Top
HTML Embed Code: