Telegram Web Link
† እንኳን ለቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያዊ †††

††† ልደት †††

††† መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራልና ተክለ ሃይማኖትን
የወለዱት ደጋጉ: ጸጋ ዘአብ ካህኑና እግዚእ ኃረያ ናቸው::
እርሱ በክህነቱ: እርሷ በደግነቷ: በምጽዋቷ ጸንተው ቢኖሩ
እግዚአብሔር ጣፋጭ ፍሬን ሰጥቷቸዋል::

በዳሞቱ ገዢ በሞተለሚ አደጋ ቢደርስባቸው ቅዱስ
ሚካኤል: ጸጋ ዘአብን ከሞት: እግዚእ ኃረያን ከትድምርተ
አረሚ (ከአረማዊ ጋብቻ) አድኗቸዋል:: በኋላም የቅዱሱን
መወለድ አብስሯቸዋል::

ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የተጸነሱት መጋቢት 24 ቀን
በ1206 ዓ/ም ሲሆን የተወለዱት ደግሞ ታኅሣሥ 24 ቀን
በ1207 ዓ/ም ነው:: በተወለዱበት ቀንም ብዙ ተአምራት
ተገልጸዋል:: ቤታቸውም በበረከት ሞልቷል::

††† ዕድገት †††

የጻድቁ የመጀመሪያ ስማቸው "ፍሥሃ ጽዮን" ይሰኛል::
ይሕንን ስም ይዘው: አባታቸው ጸጋ ዘአብን ተከትለው
አድገዋል:: በተለይ ቅዱሳት መጻሕፍትን (ብሉያት:
ሐዲሳትን) ተምረዋል:: በሥጋዊው ጐዳናም ብርቱ አዳኝ
እንደ ነበሩ ይነገራል:: ዲቁናም ከወቅቱ ጳጳስ አባ ጌርሎስ
ተቀብለዋል::

††† መጠራት †††

አንድ ቀን ፍሥሃ ጽዮን ለአደን ወጥቶ ሲያነጣጥር ድንገት
ከሰማይ አስደንጋጭ ድምጽ ተሰማ:: የክብር ባለቤት
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አእላፍ መላእክት እያመሰገኑት
በሚካኤል ክንፍ ተቀምጦ ወረደ::

የወጣቱን አዳኝ ፍርሃቱን አርቆ ጌታችን ተናገረ:: "ከዛሬ
ጀምሮ ስምህ ተክለ ሃይማኖት (ተክለ ሥላሴ) ይሁን::
ከዚህ በኋላ አራዊትን ሳይሆን ነፍሳትን ታድናለህ:: ዘወትር
ካንተ ጋር ነኝ" ብሎ በግርማ ዐረገ:: ቅዱስ ተክለ
ሃይማኖት ከዚህ ጊዜ በኋላ ሰዓትን አላጠፉም::
ንብረታቸውን ለነዳያን በትነው በትር ብቻ ይዘው ቤታቸው
እንደ ተከፈተ ወደ ምናኔ ወጡ::

††† አገልግሎት †††

ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከጳጳሱ ቅስና ተቀብለው የወንጌል
አገልግሎትን ጀመሩ:: በመጀመሪያ ስብከታቸው እዚያው
ሽዋ (ጽላልሽ) አካባቢ ብቻ በ10ሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን
አሳምነው አጠመቁ:: ያን ጊዜ ኢትዮጵያ 2 መልክ ነበራት::

1ኛ. ዮዲት (ጉዲት) በፈጠረችው ጣጣና በእስላሞች
ተጽዕኖ ወደ ደቡብ አካባቢ ያለው ነዋሪ አንድም ሃይማኖቱን
ክዷል: ወይም በባዕድ አምልኮ ተጠምዷል::
2ኛው ደግሞ በዛግዌ ነገሥታት ጥረት ክርስትናና ምናኔ
ተነቃቅቶ ነበር::

ግማሹ ሃገር በጨለመበት ወቅት የደረሱት ሐዲስ ሐዋርያ
አባ ተክለ ሃይማኖት በወጣት ጉልበታቸውና በኃይለ
መንፈስ ቅዱስ ብዙ ቦታዎችን አደረሱ:: ሕዝቡን:
መሣፍንቱን ወደ ሃይማኖት መልሰው: ማርያኖችን
(ጠንቋዮችን) አጥፍተዋል::

††† ገዳማዊ ሕይወት †††

††† ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በወንጌል ብርሃን ኢትዮጵያን
ከማብራታቸው ባለፈ ገዳማዊ ሕይወትንም አስፋፍተዋል::
እርሳቸው ከሁሉ የተሻሉ ሳሉም በ3 ገዳማት በረድዕነት
አገልግለዋል::

እነዚህም በአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ለ12 ዓመታት:
በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ ገዳም ለ7 ዓመታት: በደብረ
ዳሞ ከአቡነ ዮሐኒ ጋር ለ7 ዓመታት: በአጠቃላይ ለ26
ዓመታት አገልግለዋል::

በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ከመነኮሱ በኋላም ወደ ምድረ ሽዋ
(ዞረሬ) ተመልሰው በአንዲት በዓት ውስጥ ለ22 ዓመታት
ቆመው ጸልየዋል:: በተሰበረ እግራቸውም 6 ጦሮችን
በግራና በቀኝ ተክለው ለ7 ዓመታት ጸልየዋል::

††† ስድስት ክንፍ †††

ኢትዮጵያዊው ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት
ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት
ተባርከዋል:: ጻድቁ ምድረ እሥራኤል የገቡት በየመንገዱ
መንፈሳዊ ዘርን እየዘሩ: እያስተማሩና እያሳመኑ ነበር::

ከወቅቱ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤል ጋርም ተገናኝተው
ቡራኬን ተሰጣጥተዋል:: ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ በኋላ
ነው:: ጻድቁ እመቤታችንና ጌታችን ከጽንሰታቸው እስከ
ዕርገታቸው የረገጧቸውን ቦታዎች ሲመለከቱ በፍጹም
ተደሞ እንባቸው ይፈስ ነበር::

ምክንያቱም እግዚአብሔር ስላበቃቸው ተክለ ሃይማኖት
የሚያዩት ቦታውን አልነበረም:: በገሃድ:-
*በቤተ መቅደስ ብስራቱን
*በቤተ ልሔም ልደቱን
*በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን
*በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን
*በቤተ አልዓዛር ተአምራቱን ይመለከቱ ነበር::

የጉብኝታቸው የመጨረሻ ክፍል ወደ ሆነው ቀራንዮ
ደርሰው ጌታቸውን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ቢመለከቱት
ከዓይናቸው ይፈስ የነበረው ቁጡ እንባ መልኩን ቀየረና
ዓይናቸው ጠፋ::

በዚያች ቅጽበት ስም አጠራሯ የከበረ እመቤታችን ድንግል
ማርያም ፈጥና ደርሳ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ወደ ሰማይ
አሳረገቻቸው::

††† በዚያም:-
*የብርሃን ዐይን ተቀብለው
*6 ክንፍ አብቅለው
*የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው
*ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው
*ከ24ቱ ካህናተ ሰማይም ተደምረው
*ሥላሴን በአንድነቱና ሦስትነቱ ተመልክተው
*"ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ ይደሉ" ብለው መንበረ
ጸባኦትን አጥነው ወደ መሬት ተመልሰዋል::

††† ተአምራት †††

የቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ተአምራት እንደ ሰማይ ከዋክብት
የበዛ ነው::
*ሙት አንስተዋል
*ድውያንን ፈውሰዋል
*አጋንንትን አሳደዋል
*እሳትን ጨብጠዋል
*በክንፍ በረዋል
*ደመናን ዙፋን አድርገዋል::

ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው ደብረ ሊባኖስን
መሥርተዋል:: በዚያም ሴትና ወንድ መነኮሳት እንደ
ሕጻናት አብረው ኑረዋል:: በዘመናቸው ሰይጣን
ታሥሯልና::

††† ዕረፍት †††

††† ጻድቅ: ሰማዕትና ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ብርሃን
ሆነው: መከራን በብዙ ተቀብለው: እልፍ አእላፍ ፍሬን
አፍርተው: በተወለዱ በ99 ዓመት: ከ8 ወር: ከ1 ቀናቸው
ነሐሴ 24 ቀን በ1306 ዓ/ም ዐርፈዋል:: ጌታ: ድንግል
ማርያምና ቅዱሳን ከሰማይ ወርደው ተቀብለዋቸዋል:: 10
ትውልድ የሚያስምር ቃል ኪዳንም ተቀብለዋል::

††† በዚህ ዕለት አባታችን ተክለ ሃይማኖት ለ22 ዓመታት
የቆሙበት ቀኝ እግራቸው መሠበሩንና በአንድ እግራቸው
ለ7 ዓመታት ቆመው መጸለያቸውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን
ታስባለች::

††† ጥር 24 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1አቡነ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት
2.ቅድስት ማርያ ግብጻዊት
3.ታላቁ አባ ቢፋ
4.አባ አብሳዲ ቀሲስ
5.ቅዱሳን ጻድቃነ ሐውዚን

††† ወርኀዊ በዓላት
1.አቡነ ዘዮሐንስ (ዘክብራን ገብርኤል-ጣና)
2.ቅድስት እናታችን ክርስቶስ ሠምራ
3.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ
4.ቅዱስ ሙሴ ጸሊም
5.ቅዱስ አጋቢጦስ
6.ሃያ አራቱ ካህናተ ሠማይ

††† "በድካም : አብዝቼ በመገረፍ : አብዝቼ በመታሠር :
አትርፌ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ:: በድካምና በጥረት :
ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት : በራብና በጥም : ብዙ
ጊዜም በመጦም : በብርድና በራቁትነት ነበርሁ . . .
የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ
የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው::" †††
(፪ቆሮ ፲፩፥፳፫)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
† እንኳን ለቅዱሳን አርባ ዘጠኝ አረጋውያን ሰማዕታት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

††† አረጋውያን ሰማዕታት †††

††† ሰማዕትነት በክርስትና ለሃይማኖት የሚከፈል የመጨረሻው ዋጋ (መስዋዕትነት) ነው:: ሰው ለፈጣሪው ሰውነቱን ሊያስገዛ: ሃብት ንብረቱን ሊሰጥ ይችላል:: ከስጦታ በላይ ታላቅ ስጦታ ግን ራስን አሳልፎ መስጠት ነው::

ራስን መስጠት በትዳርም ሆነ በምናኔ ውስጥ ይቻላል:: የመጨረሻ ደረጃው ግን ሰማዕትነት ነው:: "አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዝ ዓለም: ወተዓገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግስተ ሰማያት" እንዳለው ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ሰማዕትነት ማለት መራራውን ሞት ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ሲሉ መታገስ ነው::

እርሱ ቅሉ መድኃኒታችን ክርስቶስ የሰማይና የምድር ጌታ ሲሆን ኃፍረተ መስቀልን ታግሦ ሙቶልን የለ! በዓለም ያሉ ብዙ እምነቶች ስለ መግደል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያስተምራሉ:: ክርስትና ግን መሞትን እንጂ መግደልን የሚመለከት ሕግ የለውም::

እርሱ ባለቤቱ "ጠላቶቻችሁን ውደዱ: የሚረግሟችሁን መርቁ: ስለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ" ብሎናልና:: (ማቴ. 5:44) ነገር ግን
ዕለት ዕለት ራሳችንን በሃይማኖትና በምግባር ካልኮተኮትነው ክርስትና በአንድ ጀምበር ፍጹም የሚኮንበት እምነት አይደለምና በፈተና መውደቅ ይመጣል::

በተለይ የዘመኑ ክርስቲያን ወጣቶች ልናስተውል ይገባናል:: የቀደሙ ሰማዕታት ዜና የሚነገረን እንድንጸና ነውና::

የእነዚህ ሰማዕታት ቁጥራቸው 49 ሲሆን አባ ቢስዱራ የሚባል ጻድቅ ሰው 50ኛ ሁኖ ይመራቸው ነበር:: መኖሪያቸው ገዳመ አስቄጥስ (ግብጽ) ሆኖ ዘመኑ 5ኛው መቶ ክ/ዘ ነበር::

ሃምሳውም ሙሉ ዘመናቸውን በምናኔና በቅድስና ፈጽመው በስተእርጅና ደግሞ ሰማዕትነት መጣላቸው:: በ430ዎቹ አካባቢ
የዚያን ጊዜ በርበር ይባሉ የነበሩት አረማውያኑ (የዛሬዎቹ አሕዛብ አባቶች) "ሃይማኖት ካዱ" እያሉ ሰይፍን መዘዙባቸው::

በጊዜው አባ ቢስዱራ በማረፉ ሃላፊነቱን የወሰዱት አባ ዮሐንስ ከአርባ ስምንቱ ባልንጀሮቻቸው ጋር ተስማምተው በበርበር እጅ ሰማዕትነትን ተቀብለዋል:: ከንጉስ ቴዎዶስዮስ (ትንሹ) ተልኮ የነበረ አንድ ክርስቲያንም በፍቅረ ክርስቶስ ተስቦ ከወጣት ልጁ ጋር ተሰይፏል:: የብርሃን አክሊልም ለሃምሳ አንዱም ወርዷል::

††† አምላከ ቅዱሳን ከተከፈተ ገነት : ከተነጠፈ ዕረፍት በቸርነቱ ያድርሰን::

††† ጥር 26 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አርባ ዘጠኝ አረጋውያን ሰማዕታት (ግብጽ ገዳመ አስቄጥስ ውስጥ)
2.ቅድስት አንስጣስያ (በ5ኛው መቶ ክ/ዘ ከቁስጥንጥንያ ወደ ግብጽ ወርዳ ፡ ንግሥናን ንቃ በበርሃ ስትጋደል የኖረች ቅድስት
እናት ናት::)
3.ቅዱስ ዮሴፍ (መፍቀሬ ነዳያን)
4.አባ ጽሕማ (ከተስዓቱ ቅዱሳን)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
2.አቡነ ሐብተ ማርያም ኢትዮጵያዊ
3.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
4.አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን

††† "ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ: ወይስ
ጭንቀት: ወይስ ስደት: ወይስ ራብ: ወይስ ራቁትነት: ወይስ ፍርሃት: ወይስ ሰይፍ ነውን? 'ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን:: እንደሚታረዱ በጐች ተቈጠርን' ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው:: በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን::" †††
(ሮሜ. ፰፥፴፭-፴፰)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
+*" ቅዱስ አብርሃም ርዕሰ አበው "*+

=>የሃይማኖት: የደግነት: የምጽዋት: የፍቅር አባት የሆነው አብርሃም በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት አባቱ ታራ ጣዖትን ይጠርብና ይሸጥ ነበር:: ሽጦ ገንዘብ የሚያመጣለት ደግሞ ልጁ አብርሃም ነበር::

*በዚያ ወራት አብርሃም እውነተኛውን አምላክ ፍለጋ ገብቶ ነበር:: አንድ ቀን ጣዖቱን ሊሸጥ ወደ ገበያ እየሔደ የተሸከመውን እንጨት ይመራመረው ገባ:: "አሁን ይሔ ምኑ ነው አምላክ!" እያለም ያደንቅ ገባ:: መንገድ ላይም ደክሞት ካረፈበት "ለምን አልጠይቀውም" በሚል አናገረው::

*"እርቦኛል አብላኝ" አለው:: መልስ የለም:: "እሺ አጠጣኝ" አለው:: አሁንም ያው ነው:: "ባይሆን እሺ አጫውተኝ" አለው:: ጣዖቱ ተራ እንጨት ነውና መልሱ ዝምታ ነበር:: ከዚያ ተነስቶ ወደ ገበያው ሲደርስ "ዐይን እያለው የማያይ: ጀሮ እያለው የማይሰማ አምላክ የሚገዛ" እያለ ይጮህ ጀመር::

*ይህን ሲሰሙ አንዳንዶቹ "የታራ ልጅ አብዶ" ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ "እሱ ያቀለለውን ማን ይገዛዋል" ብለውት ሔደዋል:: ከገበያ ሲመለስም ጣዖቱን ተመልክቶ አብርሃም እንዲህ አለ:: "አንተ ቀድሞውን በዕለተ ሠሉስ የተፈጠርክ ዕፅ ነህ" ብሎ ሰባበረው::

*ወደ ቤቱ ሲመለስም ሁሉንም ጣዖታት ሠባበራቸው:: የመንግስተ ሰማያት አበጋዝ: የእግዚአብሔር ወዳጅ: የሕዝብና የአሕዛብ አባት የሆነው አብርሃም እግዚአብሔርን አምልኮ: ጣዖታትን ሰብሮ ወደ ከነዓን ከወጣ በሁዋላ ብዙ ችግርን አሳልፏል:: በረሃብ ምክንያት ከአንድም 2 ጊዜ ወደ ግብጽና ፍልስጥኤም ተሰዷል:: በዚያ ግን ፈጣሪው አክብሮታል::

*2ቱ ነገሥታት (ፈርኦንና አቤሜሌክ) ሣራን እንነካለን ቢሉ ተግሣጽ ደርሶባቸዋል:: ነቢይ ነውና በአብርሃም ጸሎት ተፈውሰዋል:: ቅዱስ አብርሃም ከደግነቱ የተነሳ በኬብሮን (በተመሳቀለ መንገድ) ላይ ድንኩዋን ሠርቶ እንግዳ ይቀበል ነበር:: ምሥክር ሳይይዝም እህል አይቀምስም ነበር::

*ሰይጣን ከፍቶ ለ3 ቀናት እንግዳ ቢያስቀርበት ያለ ምግብ ለ3 ቀናት ቆይቷል:: በፍጻሜውም ሥላሴ በእንግድነት መጥተውለት በክብር ላይ ክብር: በጸጋ ላይ ጸጋ: በጣዕም ላይ ጣዕም ተጨምሮለታል:: እርሱ የሥላሴን እግር ያጥብ ዘንድ: በጀርባውም ይሸከማቸው ዘንድ አድሎታልና:: ሥላሴም በቤቱ ተስተናግደው: ልደተ ይስሐቅን አክብሥረውታል:: ጻድቁ ሰውም በፈጣሪው ፊት ስለ ሰዶምና ገሞራ ለምኗል::

*አብርሃም በአምልኮው ፍጹም ነውና የሚወደውን ልጁን ይስሐቅን ለመስዋዕት አቅርቧል:: በዚህም የነቢያት: የሐዋርያት: የነገሥታት: የካህናት አባት: ሥርወ ሃይማኖት (የሃይማኖት ሥር) ተብሏል:: ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ አያቱም ተብሏል::

*አንድ ቀን እግዚአብሔር መላእክቱን "ብየ አርክ አብርሃም በዲበ ምድር - በምድር ላይ ወዳጄ አብርሃም አለ" አላቸው:: ያን ጊዜ 99ኙ ነገደ መላእክት ፈጣሪያቸውን አመሰገኑ:-
>"አብርሃም አርከ እግዚአብሔር (አብርሃም የእግዚአብሔር ወዳጅ)"
>"አብርሃም ብእሴ እግዚአብሔር (አብርሃም የእግዚአብሔር ሰው)"

>"አብርሃም ገብረ እግዚአብሔር (አብርሃም የእግዚአብሔር አገልጋይ)"
>"አብርሃም ምዕመነ እግዚአብሔር
(አብርሃም የእግዚአብሔር ታማኝ)
>"አብርሃም ፍቁረ እግዚአብሔር (አብርሃም የእግዚአብሔር ተወዳጁ ነው) እያሉ አሰምተው ተናግረዋል::

*አባታችን አብርሃም በክብር: በቅድስናና በሞገስ ከዘፍጥረት እስከ ዮሐንስ ራዕይ ድረስ ተጠቅሷል:: ፈጣሪ በስሙ ለቅዱሳን ተለምኗል:: ስለ ክብሩም በሲዖል ውስጥ እንኩዋ ማረፊያን ሠርቶለታል:: አጋንንትም ሊቀርቡት አልተቻላቸውም:: ያረፈውም ከክርስቶስ ልደት 1,900 ዓመታት በፊት ነው:: እድሜውም 175 ዓመት ነበር::

*ፍቅሩን የተረዱ ሊቃውንት ድንግል ማርያምን "ሐይመቱ (ድንኩዋኑ): ተናግዶቱ (እንግድነቱ) ለአብርሃም" ሲሉ አመስግነዋታል:: ሊቁም:-
"አብርሃም ፍጹም በሒሩት ወበአምልኮ:
እግዚአብሔር አዕበየከ ወባረከከ ባርኮ:
እስከ ሰመየከ ዲበ ምድር አርኮ::" ብሎ በምሥጢር ገልጾታል::

=>አምላከ ቅዱሳን በእነርሱ ላይ የበዛች ፍቅሩን ለእኛም ያድለን:: ፍሬ ትሩፋት: ፍሬ ክብር እንድናፈራም ይርዳን:: ክብራቸውንም አያጉድልብን::

    <ወስብሐት ለእግዚአብሔር>
† እንኳን ለጌታችን አማኑኤል ክርስቶስ ዓመታዊ የተአምር በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

ተአምረ እግዚእ

††† "ተአምር" የሚለውን ቃል በቁሙ "ምልክት" ብሎ መተርጐም ይቻላል:: መሠረታዊ መልዕክቱ ግን ነጮቹ በልሳናቸው Miracle የሚሉት ዓይነት ነው:: ከተፈጥሮ ሕግ ውጪ (በላይ): ከፍጡራንም ችሎታ የላቀ ነገር ሲሠራ (ሲፈጸም) ተአምር ይባላል::

ተአምር የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ነው:: እርሱ ዓለምን ከመፍጠሩ ጀምሮ እያንዳንዷ ተግባሩ ለእኛ ተአምራት ናቸው:: ስለዚህም ነው "ኤልሻዳይ - ከሐሌ ኩሉ - ሁሉን ቻይ" እያልን የምንጠራው::

እግዚአብሔር ፍጡራኑን ይወዳልና እርሱ ለወደዳቸውና ደስ ላሰኙት ተአምራት ማድረግን ሰጥቷል:: በብሉይ ኪዳን እነ ሙሴ ባሕር ሲከፍሉ: መና ሲያዘንሙ: ውሃ ሲያፈልቁ (ኦሪትን ተመልከት) እነ ኤልያስ ሰማይን ሲለጉሙ: እሳትን ሲያዘንሙ: ሙታንን ሲያስነሱ (1 ነገሥት) እንደ ነበር ይታወቃል::

እንዲያውም በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ የተአምር መጽሐፍ ነው ብሎ ለመናገርም ያስደፍራል:: በሐዲስ ኪዳንም መድኃኒታችን ብዙ ተአምራትን ሠርቶ ለሐዋርያቱ የተአምራት ጸጋውን ሰጥቷቸዋል:: (ማቴ. 10:8, 17:20, ማር. 16:17, ሉቃ. 10:17, ዮሐ. 14:12)

እነርሱም በተሰጣቸው ሥልጣን ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል:: (ሐዋ. 3:6, 5:1, 5:12, 8:6, 9:33-43, 14:8, 19:11)

††† ተአምራተ እግዚእ †††

††† ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ብዙ ተአምራትን ሰርቷል:: እያንዳንዱ ግን ቢጻፍ ዓለም ለራሷ ባልበቃች ነበር:: ከእነዚህ መካከልም አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው በዚህ ዕለት በ7 እንጀራ እና በጥቂት ዓሣ ሴቶችና ሕፃናትን ሳይጨምር 4,000 ሰዎችን በቸርነቱ አበርክቶ አጥግቡዋል:: ደቀ መዛሙርቱም 7 ቅርጫት ማዕድ አንስተዋል::

ጌታችን በከሃሊነቱ የተራቡትን ሲያጠግብ እንዲሁ አይደለም:: በጊዜው የነበሩ አይሁድ ጠማሞች ነበሩና እነሱን ምላሽ በሚያሳጣ መንገድ ነበር እንጂ:: አይሁድ ላለማመን ብዙ ጥረት ነበራቸውና::

በዚህ ዕለትም እንጀራውን አበርክቶ ሲያበላቸው:-
1.ጊዜው አመሻሽ ላይ ነበር:: ምክንያት:- ጧት ላይ ቢሆን ከቤታችን የበላነው ሳይጐድል ብለው ከማመን ይርቁ ነበርና::

2.ከውሃ ዳር አድርጐታል:: መታጠቢያ ብናጣ በደንብ ሳንበላ ቀረን እንዳይሉ::

3.ሳር የበዛበት ቦታ ላይ አድርጐታል:: ምክንያቱም መቀመጫ ብናጣ በደንብ ሳንበላ ቀረን እንዳይሉ::

4.ከከተማ አርቆ ምድረ በዳ ላይ አድርጐታል:: ያማ ባይሆን "ፈጣን: ፈጣን ደቀ መዛሙርቱ ተሯሩጠው እየገዙ አቀረቡለት" ባሉ ነበርና::

††† ለመድኃኒታችን ክርስቶስ አምልኮና ምስጋና ይሁን!
አማኑኤል አምላካችን ጣዕመ ፍቅሩን ያሳድርብን::

††† ጥር 28 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ቀሌምንጦስ ሰማዕት (ስለ ሃይማኖት 7 ጊዜ ሙቶ የተነሳ, 7 አክሊል የወረደለት)
2.ቅዱስ አካውህ መነኮስ
3."800" ሰማዕታት
4.ቅዱስ ዮሴፍ አይሁዳዊ (የእመቤታችን ወዳጅ)
5.ቅድስት ሳቤላ

††† ወርሐዊ በዓላት
1.አባቶቻችን አብርሃም: ይስሐቅና ያዕቆብ
2.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ
3.ቅዱስ እንድራኒቆስና አትናስያ
4.ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ

††† "ጌታ ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ:- ሕዝቡ ከእኔ ጋር እስከ አሁን ሦስት ቀን ውለዋልና የሚበሉት ስለ ሌላቸው አዝንላቸዋለሁ:: በመንገድም እንዳይዝሉ ጦማቸውን ላሰናብታቸው አልወድም' አላቸው::
ደቀ መዛሙርቱም:- 'ይህን ያህል ሕዝብ የሚያጠግብ ይህን ያህል እንጀራ በምድረ በዳ ከወዴት እናገኛለን?' አሉት:: ጌታ ኢየሱስም:- 'ስንት እንጀራ አላችሁ?' አላቸው:: እነርሱም:- 'ሰባት: ጥቂትም ትንሽ ዓሣ' አሉት::
ሕዝቡም በምድር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ:: ሰባቱንም እንጀራ: ዓሣውንም ይዞ አመሰገነ:: ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ:: ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ:: ሁሉም በሉና ጠገቡ:: የተረፈውንም ቁርስራሽ ሰባት ቅርጫት ሙሉ አነሱ:: የበሉትም ከሴቶችና ከልጆች በቀር አራት ሺህ ወንዶች ነበሩ::" †††
(ማቴ. 15:32)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
† እንኳን ለቅዱሳን ጻድቃነ ዴጌ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

† ጻድቃነ ዴጌ †

† እነዚህ ጻድቃን ኢትዮዽያውያን ባይሆኑም ያበሩት በሃገራችን ነው:: ቅዱሳኑ በቁጥር 3,000 : በዜግነት ሮማውያን ናቸው:: ከሺህ አዝማናት በፊት ከሮም ግዛት ተሰባስበው እንደ ተስዓቱ ቅዱሳን ወደ ኢትዮዽያ (አክሱም) መጥተዋል::

ቀጥለውም እዛው አካባቢ ወደሚገኝ ገዳም ገብተዋል:: ይህ ቦታ ለአክሱም ቅርብ ሲሆን በዘመነ ሐዋርያት የቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊ በዓት ነበር:: የሐዋርያው በትረ መስቀልም እስካሁን አለች::

ጻድቃነ ዴጌ ሕጋቸው አንዲት : እርሷም ፍቅር ናት:: ለዘመናት በፍቅረ ክርስቶስ ታሥረው : ፍቅርን ለብሰው : በፍቅር ኑረዋል:: ሁሌም በ29 የጌታችንን ስም እየጠሩ ጽዋ ጠጥተዋል:: ስለ ፍቅራቸውም ጌታችን 3,001ኛ ሆኖ : ነዳይ መስሎ አብሯቸው ጠጥቷል::

በመጨረሻም 3ሺው በአንድነት ተሠውረዋል::

††† ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን:: እኛንም በወዳጆቹ ጸሎት ይማረን:: . . .አሜን!

††† ጥር 29 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ጻድቃን ቅዱሳን ማሕበረ ዶጌ (ዴጌ ጻድቃን)
(አክሱም አካባቢ በቁጥር ወደ 3,000 ሲሆኑ ከመድኃኔ ዓለም ጋር ማሕበር ይጠጡ የነበሩና በአንድ ላይ የተሠወሩ ቅዱሳን ናቸው)
2.አባ ገብረ ናዝራዊ ዘቃውንት (ኢትዮዽያዊ)
3.ቅድስት አክሳኒ ፈላሲት
4.ቅዱስ ሰርያኮስ ሰማዕት
5.አባ እስጢፋኖስ ገዳማዊ
6.ከድሮዋ ሮም የተነሱ ቅዱሳት አንስት

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅድስት አርሴማ ሰማዕት
2.ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ እናታችን
3.ቅዱስ ዼጥሮስ ተፍፃሜተ ሰማዕት
4.ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ
5.ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ

††† "ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ::
በእርስዋም ለዘለዓለም ይኖራሉ::
የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል::
አንደበቱም ፍርድን ይናገራል::
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው::
በእርምጃውም አይሰናከልም::" †††
(መዝ. 36:29)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
2024/09/25 17:26:48
Back to Top
HTML Embed Code: