Telegram Web Link
ጥር 29
ወበዛቲ ዕለት አዕረፈ አብ ክቡር አረጋዊ፡ ወሰማዕተ ጽድቅ አቡነ ታዴዎስ ዘጽላልሽ፡፡ በዚህች ዕለት ኢትዮጵያዊው ፃድቅ አቡነ ታዴዎስ አረፉ

#አቡነ_ታዴዎስ_ዘጽላልሽ

ትውልድ ሀገራቸው ጽላልሽ (ዞረ) ነው። አባታቸው ሮማንዮስ እናታቸው ማርታ ይባላሉ። አባታቸው ሮማንዮስ ቄስ ነው። የአቡነ ተክለ ሃይማኖት አጎት ናቸው።
በእናታቸው ማኅፀን ሳሉ በጽላልሽ ረሀብ ፀንቶ ነበር። እሳቸው ግንቦት ፳፫ ቀን በመንፈቀ ሌሊት በልብሰ ብርሃን ተጠቅልለው ተወለዱ። ቤታቸው በበረከት ተመላ። ለሀገሬው ዝናብ ዘንቦለት ህዝቡ ከፃድቁ እናትና አባት የተመፀወቱትን ከፍለው ዘሩ።

አቡነ ታዴዎስ በተወለዱ በ፵ ቀናቸው ሐምሌ ፪ ቀን ሲጠመቁ የተዘራው እህል አንድ ሳይቀር አፍርቶ ተገኝቷል።

ዕድሜአቸው ለትምህርት ሲደርስ ለሊቀ ካህናቱ ለሕይወት ብነ ሰጥተዋቸው ሲማሩ አደጉ። አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዳሞት (ወላይታ) ተሻግረው መተሎሚን አስተምረው “በእግዚአብሔር ቸርነት በአንተ ፀሎት መተሎሚን በሃይማኖት ወልጄዋለሁ። በምግባር አሳድጌዋለሁና እህትህን ይዘህ በቶሎ ና፤” ብለው ላኩባቸው።
እህታቸው ትቤጽዮን ትባላለች። የመተሎሚን ወንድም ዝግናን አግብታ አባ ኤልሳዕን ወልዳለች። ከባሏ ተጣልታ ነበርና እሷን ከባሏ አስታርቀው እሳቸው አቡነ ተክለሃይማኖትን እያገለገሉ ፱ አመት ኖረዋል።

በኋላ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ አባ በጸሎተ ሚካኤል ሲሄዱ እሳቸውም ወደ ጽላልሽ ተመልሰው ስለነበር አፄ ይኩኖ አምላክ እንድትመክረኝ እንድትገስፀኝ ከቤቴ ተቀመጥ ብለው ከቤተመንግስት አስቀመጣቸው።
ሰይጣን ለፀብ ለምቀኝነት አያርፍምና ጠላ ቤቷን ክፉ የሚገድል ሽታ አሸተታትና ሞተች። አባ ታዴዎስ ወንዝ ገብተው ሲፀልዩ ሙቷ ተነሥታለች። ከዚህ በኋላ ውዳሴ ከንቱ ይሆንብኛል ብለው ወደ ደብረ ሊባኖስ ተመለሱ።

አቡነ ተክለሃይማኖት ወደ ጽጋጋ (ጅጅጋ) ሂድ አሏቸው። ለምን ቢሉ? አባ አኖሬዎስ ሄደው ሲያስተምሩ ያገሬው ሰዎች ደብድበው አስረዋቸው ነበርና እሳቸውን ለማሰወፈታት ነበር።
የአካባቢው ንጉስ መዩጥ ይባላል። በነፋስ ሰረገላ ተጭነው ሄደው ከፊቱ ወርደው ሲቆሙ ደንግጦ ከሰማይ መላእክት ነህ ወይስ ከሰው ወገን? ቢላቸው። እኔ ከሰው ወገን ነኝ አሉት። ክርስትናንም አስተማሩት ጋኔን ከእሳት ላይ ጥሎት ሲሰቃይ የሚኖር ልጅ ነበረው አድነውለታል።
ይህን አይቶ አምኖ ሕዝቡም እንዲያምኑና ክርስትናን እንዲቀበሉ አዋጅ ነገረ።

እንደ ሐዋርያው ታዴዎስ ፳፭ ግመል በመርፌ ቀዳዳ በተአምራት አሳልፈው በማሳየታቸው አፍጃል የሚባል ያንድ ባለጠጋ ልጅ በምትሐት እንደሚያደርጉት አድርጎ በመናገሩ ከግመሎቹ አንዲቱ ረግጣው ሞተ፤ ይህን ሙሳ የሚባል ልጅም በተቀበረ በሦስተኛው ቀን «አልዓዛርን ከሙታን በአስነሳው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ልጄ ና ተነስ» ብለህ ይህንን መቋሚያዬን ወስደህ ከመቃብሩ ላይ አኑር ብለው በአፍጃል ሰጥተውት እንዳሉት ቢያደርግ አፈፍ ብሎ ተነስቷል።
ይህን አይተው ህዝቡ ሁሉ አምነዋል። ከዚህ በኋላ ሙሳን ሙሴ ብለው ሊቀ ካህናት አድርገው ፲፪ አብያተ ክርስቲያናት አሳንፀው አኖሬዎስን ይዘው ተመልሰዋል።

አቡነ ተክለሃይማኖትም ከንጉሱ ተማክረው ሊቀካህናት ዘጽላልሽ ብለው ሾመዋቸዋል።
ንጉስ ዓምደ ጽዮን ፍቅረ ዝሙት አድሮበት የአባቱን ቅምጥ ቢያገባት ሄደው ገሰፁት። በዚህ የተናደደች የንጉሱ ሚስት የኋሊት አሳስራ ከጥልቅ ገደል አሰጣለቻቸው።
በዚህ ጊዜ የመቶ ሃያ አመት አረጋዊ ነበሩ።

የታዘዘ መልአክ ገብረ እግዚአብሔርና ውቢት የተባሉ ደጋግ ሰዎችን አስነስቶ ስጋቸውን ወስደው ከበዓታቸው ቀብረው የተሰጣቸውንም ቃል ኪዳን በዳግማዊ አፄ ዳዊት ዘመን በህዝቡ ፊት መስክረዋል።
ንጉስ ዳዊትም ዜና ገድላቸውን አጽፈዋል፤ ስጋቸውንም ወደ ከተማቸው በክብር አፍልሰው በተቀደሰ ስፍራ አኑረውታል።

የፃድቁ አባታችን እረድሄት በረከት ይደርብን አሜን!!!
† እንኳን ለቅዱሳት አንስት ሶፍያ ወአዋልዲሃ: ኦርኒ ወማኅበራኒሃ እና ለሊቁ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

† ቅድስት ሶፍያና ልጆቿ †

† በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ታዋቂ ከሆኑ የእናቶቻችን ስሞች "ሶፍያ" ቀዳሚው ነው:: ቃሉ በጥሬው ሲተረጐም "ጥበብ (ጥበበ ክርስቶስ) Wisdom of God" ማለት ነው:: ከጻድቃንና ከሰማዕታት ወገን በዚህ ስም የተጠሩ እናቶች አሉ::

ከእነዚህ መካከል አንዷ የሆነችው በዕለቱ የምናስባት እናት ቁጥሯ ከሰማዕታት ነው:: ዋናው ዘመነ ሰማዕታት ከመጀመሩ በፊት የነበረችው ቅድስት ሶፍያ ከሕግ ትዳር 3 ሴቶች ልጆችን አፍርታለች::

ስማቸውንም:- ጲስጢስ (ሃይማኖት) : አላጲስ (ተስፋ) : አጋጲስ (ፍቅር) ስትል ሰይማቸዋለች:: እንደሚገባም በሥርዓቱ አሳድጋ እድሜአቸው 9 : 10 እና 12 ሲደርስ ለሰማያዊ ሙሽርነት አጭታቸዋለች::

በዘመኑ "ክርስቶስን ካዱ" የሚል መሪ ተነስቶ ነበርና ቅዱሳቱ በመድኃኒታችን አምነው : ጣዖትን ዘልፈው አንገታቸውን ሰጥተዋል:: ክብረ ሰማዕትን : ሃገረ ክርስቶስንም ወርሰዋል::

††† ቅድስት ኦርኒ ሰማዕት †††

††† "ኦርኒ" ማለት በምሥራቃውያን ልሳን "ሰላም" ማለት ነው:: ቅድስቲቱ አርበኛ የዘመነ ሐዋርያት የቤተ ክርስቲያን ፍሬ ስትሆን ተወልዳ ያደገችውም በቀድሞው የሮም ግዛት ውስጥ ነው::

ምንም ዛሬ ያለ ትውልድ ቢዘነጋት ቅድስት ኦርኒ ተወዳዳሪ የሌላት ሰማዕት : ሐዋርያዊት : ድንግል ናት:: እርሷ ውበቷን : ንግሥናዋን : ክብሯን : ሃብቷን : ወጣትነቷንና ያላትን ሁሉ ስለ ፍቅረ ክርስቶስ ሰውታለችና ክብርት ናት::

በ1ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ከሮም ቤተ መንግስት የተወለደችው ቅድስት ኦርኒ እስከ ወጣትነቷ ድረስ ክርስቶስን ልታውቀው አልተቻላትም ነበር:: ምክንያቱ ደግሞ ንጉሡ አባቷ ጣዖትን ማምለኩ ነበር::

ንግሥት እናቷ ምንም ክርስቲያን ብትሆንም ስለ ክርስትና ልትነግራት አልደፈረችም:: ይህን ብታደርግ የሚደርስባትን መከራ ታውቃለችና:: ግን ደግሞ ውስጥ ውስጡን ትጸልይላት ነበርና ፈጣሪ መንገዱን ሊከፍት ጀመረ::

መምለኬ ጣዖት አባቷ ሰው እንዳያያት ቤተ መንግስት ሠርቶ : 12 ሞግዚቶችን መድቦ ጣዖት ከፊቷ አቁሞ ለዘመናት ዘጋት:: የሚገርመው ግን መልኳን እንዳያይ በበር ሆኖ የሚያስተምራት ፈላስፋ ተቀጥሮ ነበርና የዚህ ሰው ማንነቱ ነው::

መምለኬ ክርስቶስ ደግ ሰው ነበርና ፈሊጥን ይሻላት ገባ:: በዚህ መካከል ቅድስት ኦርኒ ራዕይን ታያለች:: የቤቷ መስኮቶች ተከፍተው ሳሉ በስተምሥራቅ ነጭ ርግብ : የዘይት (የወይራ) ዝንጣፊ ይዛ ገብታ : ከማዕዷ ላይ ጥላው ወጣች::

እርሷን ተከትሎ ቁራ በምዕራብ ገባ:: እባቡን ማዕዷ ላይ ጣለው:: በ3ኛው ደግሞ ንስር ገብቶ አክሊል ትቶላት ወጣ:: ቅድስቲቱም እየገረማት አረጋዊ መምህሯን "ተርጉምልኝ" አለችው::

††† እርሱም:-
"•ርግብ=ጥበብ (መንፈስ ቅዱስ)
•ዘይት=ጥምቀት
•ቁራ=ክፉ ንጉሥ
•እባብ=መከራ
•ንስር=ድል ነሺነት (ልዑላዊነት)
•አክሊልም=ክብረ ሰማዕታት ነው" ብሎ ተርጉሞ : ክርስቲያን ሆና ይህ ሁሉ እንደሚደረግ ነግሮ ተሰናበታት::

እርሷም ስትጸልይ ቅዱስ መልአክ ተገልጦ አጽናናት:: ያጠምቃትና ያስተምራት ዘንድም ሐዋርያው ቅዱስ ጢሞቴዎስን ልኮላታል:: ሐዋርያውም የቤተ መንግስቱን ግድግዳ ሰንጥቆ ገብቶ : ለሰማያዊ ሙሽርነት የሚያበቃ ትምህርትና ጥምቀትን ሰጥቷት ሔዷል::

ቅድስት ኦርኒም የአባቷን ጣዖታት ቀጥቅጣ ሰብራ ከአባቷ ጋር ተጣላች:: እርሱም "እገድላታለሁ" ብሎ በእንስሳት ጅራት ላይ ጸጉሯን ሲያስር እንስሶቹ ደንብረው : እጁን ገንጥለው መሬት ላይ ጥለው ገደሉት:: ቅድስት ኦርኒ ግን ጸሎት አድርሳ አባቷን ከሞት አስነሳችው:: እጁንም ቀጠለችለት::

በዚህ ምክንያት በዚያች ዕለት ብቻ አባቷና 30,000 የከተማው አሕዛብ አምነው ተጠምቀዋል:: ቅድስት ኦርኒ ግን ኃይለ መንፈስ ቅዱስ ታጥቃ ክርስትናን ሰበከች:: ብዙም ተሰቃየች:: ንጉሡ ዳኬዎስ : ልጁና ሌሎች 2 ያህል ነገሥታት በእሳት : በአራዊት : በግርፋትና በጦር ፈትነዋታል::

እርሷ ግን ሁሉን በኃይለ ክርስቶስ ድል ነስታለች:: ሙታም የተነሳችበት ጊዜ አለ:: በመጨረሻም በዚህች ቀን ወደ ሰማያዊ ርስት (ገነት) ተመስጣለች:: በዘመነ ስብከቷ ካሳመነቻቸው ባሻገር 130,000 የሚያህሉ ሰዎች ለሰማዕትነት እንዲበቁም ምክንያት ሆናለች::

††† ቅዱስ ጐርጐርዮስ ታኦሎጐስ †††

††† ቅዱሱ:-
•የዘመነ ሊቃውንት ፍሬ:
•የእንዚናዙ ኤጲስ ቆጶስ:
•የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ:
•የጉባዔ ቁስጥንጥንያ (በ381 ዓ/ም) 3ኛ ሊቀ መንበር:
•ባለ ብዙ ድርሳን:
•የቂሣርያ (ቀጰዶቅያ) ኮከብ:
•ብሩህ ገዳማዊ:
•መልካም እረኛ የነበረ አባት ነው::
መጽሐፈ ቅዳሴውን ጨምሮ በጻፋቸው ብዙ መጻሕፍትና በስብከቱ ከሊቃውንት ወገን "ታኦ(ዎ)ሎጐስ" ተብሎ የተጠራ እርሱ ብቻ ነው:: ትርጉሙም በግዕዙ "ነባቤ መለኮት" ማለት ነው:: በአማርኛም "አንድነትን : ሦስትነትን የተናገረ (ያመሠጠረ) እንደ ማለት ነው:: ቅዱሱ ዛሬ ዕረፍቱ ነው::

††† አምላከ ቅዱሳን ከበረከታቸው ይክፈለን፡፡
በመጽናታቸውም ያጽናን፡፡

††† እንዲህ ኃጢአታችን ጽዋዑን ሞልቶ በተረፈበት በዚህ ዘመን አንዲት ሰዓትም ውድ የሆነች የንስሃ ዕድሜ ናት:: እግዚአብሔር ግን ደግ ነውና ይሔው ጥርን አስፈጸመን:: ባይገባን ነው እንጂ በዚሕች ወር ውስጥ ሚሊየኖች በደዌ የአልጋ ቁራኛ ሁነዋል::

ሚሊየኖችም ለንስሃ ሳይበቁ እንዲሁ አንቀላፍተዋል (ሙተዋል):: እስኪ እርሱ አምላካችን ቀሪውን ዘመን ደግሞ ለንስሃና ለመልካም ሥራ ባርኮ ይስጠን::

††† ወርኀ ጥርን በቸር ያስፈፀመ አምላከ ቅዱሳን ወርኀ የካቲትን እንዲባርክልን እንለምነው::

††† ጥር 30 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅድስት ሶፍያና ሦስቱ ሰማዕታት ልጆቿ (ጲስጢስ አላጲስና አጋጲስ)
2.ቅድስት ኦርኒ ሰማዕት ( (በ5 ነገሥታት እጅ የተሰቃየች : የሐዋርያው ጢሞቴዎስ ተከታይና ወደ ብሔረ ሕያዋን የተነጠቀች እናት)
3.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
4.አባ አክርስጥሮስ
5.አምስቱ ደናግል ሰማዕታት (ጤቅላ: ማርያ: ማርታ: አበያ: ዓመታ)
6.ጻድቃነ ዴጌ (የተሠወሩበት)
7.አባ ሚናስ ሊቀ ጳጳሳት
8."130,000" ሰማዕታት (የቅድስት ኦርኒ ማኅበር)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ማርቆስ ዘአንበሳ
2.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
3.አባ ሣሉሲ ክቡር

††† "ለእናንተም ጠጉርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጐናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ:: ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ::" †††
(፩ጴጥ. ፫፥፫)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ለተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ዼጥሮስ እና ለ150ው ቅዱሳን ሊቃውንት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ዼጥሮስ ሰማዕት †††

††† የቅዱሳን ሰማዕታት መነሻቸው ቅዱስ እስጢፋኖስ ሲሆን ፍጻሜአቸው ደግሞ ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ዻዻሳት ነው::

ይህ ቅዱስ የሚታወቀው "ተፍጻሜተ ሰማዕት (የሰማዕታት መጨረሻ)" በሚለው ስሙ ነው:: ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
የቅዱሱ ሃገረ ሙላዱ ግብጽ ናት:: ዘመኑም 3ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ወላጆቹ ካህን ቴዎድሮስና ቡርክት ሶፍያ ልጅ አጥተው ሐምሌ 5 ቀን ወደ ፈጣሪ ቢማጸኑ በራዕይ ዼጥሮስ ወዻውሎስ ተገልጠው ብሥራትን ለሶፍያ ነገሯት:: በወለደችው ጊዜም በራዕዩ መሠረት "ዼጥሮስ" አለችው::

ሰባት ዓመት በሆነው ጊዜም ለቤተ እግዚአብሔር ሰጥተው በሊቀ ዻዻሳቱ ቅዱስ ቴዎናስ እጅ አደገና በወጣትነቱ ሊቅ: ጥዑመ ቃልና በጐ ሰው ሆነ:: ዲቁናና ቅስናን ተሹሞ ሲያገለግል ቅዱስ ቴዎናስ በማረፉ ቅዱስ ዼጥሮስን የግብጽ 17ኛ ፓትርያርክ አድርገው ሾሙት::

ዘመኑ ደግሞ እጅግ ጭንቅ ነበር:: ክርስቲያኖች በተገኙበት ስለሚገደሉ: አብያተ ክርስቲያናትም ስለ ተቃጠሉ የቅዱሱ መከራ የበዛ ነበር:: ለ14 ዓመታት በፍጹም ትጋት ከመንጋው ጋር ተጨነቀ::

አርዮስን (ተማሪው ነበር) አውግዞ ለየው:: ከጌታ ጋርም ብዙ ጊዜ ተነጋገረ:: ብዙ ተአምራትንም ሠራ:: በዚህ ሁሉ ጊዜ አንድም ቀን በመንበረ ዽዽስናው ላይ አልተቀመጠም:: በሁዋላ ግን ጨካኙ ንጉሥ እንዲገደል አዘዘ::

ሕዝቡ "ከእሱ በፊት እኛን ግደሉን" በማለታቸው ሁከት እንዳይነሳ ቅዱስ ዼጥሮስ ተደብቆ ሔደና በፈቃዱ ለወታደሮች ተሰጠ:: በዚያች ሌሊትም የእርሱ ደም የግፍ ማብቂያ እንዲሆን እያለቀሰ ጮኸ:: ከሰማይም "አሜን! ይሁን!" የሚል ቃል መጣ:: ያን ጊዜ የእርሱ አንገት ተሰየፈ:: ዘመነ ሰማዕታትም አለፈ::

††† የቅዱሳንን ዝክር ከማንበብ ባለፈ በስማቸው መጸለይ (ዘፀ. 32:13): በምጽዋትም ማሰብ (ማቴ. 10:41) ይገባል::

††† ወርኀ የካቲትን ይባርክልን!

††† የካቲት 1 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1."150"ቅዱሳን ሊቃውንት ዻዻሳት (በቁስጥንጥንያ ተሠብሥበው መናፍቃንን ያወገዙበት: ትምሕርተ ቤተ ክርስቲያንን ያፀኑበት /ጉባዔ ቁስጥንጥንያ/ በ381 ዓ/ም::
ከወቅቱ ቅዱሳን ሊቃውንት እነዚህ ይጠቀሳሉ:-
*ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘኑሲስ
*ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘእንዚናዙ
*ቅዱስ ጢሞቴዎስ ዘአልቦ ጥሪት
*ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም)
2.ቅዱስ ዼጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት (ቅዳሴ ቤቱ)
3.ታላቁ ቴዎዶስዮስ ጻድቅ (ንጉሠ ቁስጥንጥንያ)

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ልደታ ለቅድስት ድንግል ማርያም እግዝእትነ
2.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
3.ቅዱስ ሚልኪ ቁልዝማዊ
4.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላዕክት
5.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና

††† "ስለዚህ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያንን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ዻዻሳት አድርጎ ለሾመባት: ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ:: ከሄድሁ በሁዋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ እኔ አውቃለሁ:: ስለዚህ 3 ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሰጽ እንዳላቁዋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ::" †††
(ሐዋ. 20:28)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ለታላቁ ገዳማዊ አባ ጳውሊ እና ለጻድቁ አባ ለንጊኖስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ታላቁ ቅዱስ ጳውሊ †††

††† በቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ "ታላቁ /ዐቢይ/ THE GREAT" የሚል ስም የሚሰጣቸው አባቶች የተለዩ ናቸው። አንድም እጅግ ብዙ ትሩፋቶችን የሠሩ ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ በተመሳሳይ ስም ከሚጠሩ ሌሎች ቅዱሳን እንለይበታለን።

ገዳማዊ ሕይወት ጥንቱ ብሉይ ኪዳን ነው። በቀዳሚነትም በደብር ቅዱስ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ደቂቀ ሴት እንደ ጀመሩት ይታመናል። ሕይወቱ በጐላ በተረዳ መንገድ የታየው ግን በታላቁ ጻድቅ ሄኖክ ከዚያም በቅዱሱ ካህን መልከ ጼዴቅ አማካኝነት ነው።

ቀጥሎም እነ ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ እነ ኤልሳዕ ደቀ መዝሙሩ ኑረውበታል። በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ሙሉ ሕይወቱን በገዳም (በበርሃ) ያሳለፈው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቅድሚያውን ይይዛል።

ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ በገዳመ ቆረንቶስ ለአርባ ቀናት በትሕርምት ኑሮ ገዳማዊ ሕይወትን ቀድሷል፤ አስተምሯል። በዘመነ ስብከቱም ያድርባት የነበረችው የደብረ ዘይቷ በዓቱ (ኤሌዎን ዋሻ) በራሷ ለዚህ ሕይወት ትልቅ ማሳያ ናት።

ከጌታ ዕርገት በኋላም ክርስቲያኖቹ የዓለም ሁካታ ሲሰለቻቸው አንድም በንጹሕና በተሸከፈ ልቡና ለፈጣሪያቸው መገዛትን ሲሹ ከከተማ ወጣ እያሉ ይኖሩ እንደ ነበር የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ። አኗኗራቸውም በቡድንም በነጠላም ሊሆን ይችላል። ዋናው ነገር ግን በጾምና በጸሎት መትጋታቸው ነው። ይህም ሲያያዝ እስከ ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ደረሰ። በዚህ ዘመን ግን አባ ጳውሊ የሚባል ንጹሕ ክርስቲያን ይህንን ሕይወት ወደ ሌላ ደረጃ ከፍ አደረገው። ለሰማንያ ዓመታት ሰው ሳያይ ተጋድሎ "የባሕታውያን አባት" ተባለ። ደንብ ያለው ተባሕትዎም ጀመረ።

ይህ ከሆነ ከሃያ ዓመታት በኋላ ደግሞ አባ እንጦንስ የሚባሉ ደግ ክርስቲያን ይህንን ገዳማዊ ሕይወት በሌላ መንገድ አጣፈጡት። በቅዱስ ሚካኤል አመንኳሽነት ገዳማዊ ሕይወት በምንኩስና ተቃኘ። ስለዚህም አባ እንጦንስ የመነኮሳት አባት ተባሉ።

እርሳቸውም ሕይወቱን ለማስፋፋት ከተለያዩ አሕጉር ደቀ መዛሙርትን እየተቀበሉ አመንኩሰዋል። ቅዱሳን የአባ እንጦንስ ልጆችም ወደየ ሃገራቸው ተመልሰው ሕይወቱን በተግባር አሳይተው ገዳማዊነትን አስፋፍተዋል።

አንድ ቀን ቅዱስ እንጦንስ (የመነኮሳት ሁሉ አባት) እንዲህ ሲል አሰበ። "በውኑ በበርሃ ለበርካታ ዘመናት በመኖር ከእኔ የሚቀድም (የሚበልጥ) ሰው ይኖር ይሆን?"
ይህንን ሃሳቡን ገና ሳይጨርሰው ቅዱስ ሚካኤል ወደ እርሱ ዘንድ ደረሰ።

"እንጦንስ ሆይ! ከእኔ የሚቀድም የበርሃ ሰው ይኖር ይሆን ብለህ አስበሃል። በእርግጥም ከአንተ ሃያ ዓመታትን ቀድሞ ወደ በርሃ የገባ፣ በቅድስናው ፈጣሪውን ያስደሰተ፣ ዓለም ከነ ክብሯ የእግሩን መረገጫ ያህል እንኳ የማትመጥነው በጸሎቱና በምልጇው ዓለም የምትጠበቅለት ሞገስን የተሞላ አንድ ሰው በበርሃ ስላለ ሒድና ተመልከተው።" ብሎት ተሠወረው።

ቅዱስ እንጦንስም ከሰማው ነገር የተነሳ እየተደነቀ ተነሳ። እርሱ ካለበት በርሃ በራቀ መንገድም ለቀናት ተጉዞ አንድ በዓት (ዋሻ) በር ላይ ደረሰ። በበሩ አካባቢ የሰውና የአራዊት ኮቴ ተመልክቶ በሩን ጸፋ (ቆፈቆፈ)። በውስጥ ያለው አረጋዊ ሰው ግን ትልቅ ድንጋይ ገልብጦ በሩን አጠበቀው። ለሰማንያ ዓመታት ሰውን አይቶ አያውቅምና ሰይጣን ሊያታልለኝ መጥቷል ብሎ አስቧል። ቅዱስ እንጦንስ ግን "ኃሠሥኩ እርከብ ጐድጐድኩ ይትረኃው ሊተ - ሽቻለሁና ላግኝ፤ ደጅ መትቻለሁና ይከፈትልኝ።" ሲል አሰምቶ ተናገረ።

ቅዱሱ ገዳማዊም ሰው መሆኑን ሲያውቅ በሩን ከፈተለትና ወደ ዋሻው አስገባው። መንፈሳዊ ሰላምታንም ተለዋወጡ። ሲመሽም ቅዱስ እንጦንስ ሽማግሌውን ገዳማዊ "ስምህ ማን ነው?" ቢለው "ስሜን ካላወክ ለምን መጣህ?" ሲል መለሰለት።

ያን ጊዜ ቅዱስ እንጦንስ ቀና ብሎ ሰማይን ሲመለከት ምሥጢር ተገለጠለትና "ቅዱስ ጳውሊ ሆይ! ከአንተ ጋር ያገናኘኝ ፈጣሪ ይክበር፤ ይመስገን።" ሲል ፈጣሪውን ባረከ። ቅዱስ ጳውሊም መልሶ (በጸጋ አውቆት) "አባ እንጦንስ ሆይ! እንኳን ደህና መጣህ።" አለው። ሁለቱም ደስ ብሏቸው ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ ተጨዋወቱ።

ቤተ ክርስቲያን ለሁሉም ዓይነት የቅድስና ሕይወት የመጀመሪያ የምትላቸው አላት። ለምሳሌ፦
የመጀመሪያው ሐዋርያ ቅዱስ እንድርያስ፣
የመጀመሪያው ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ፣
የመጀመሪያው ባሕታዊ (ገዳማዊ) ቅዱስ ጳውሊ እና የመጀመሪያው መነኮስ ቅዱስ እንጦንስን ማንሳት እንችላለን።

ቅዱስ ጳውሊ የተወለደው በሰሜናዊ ግብጽ በእስክንድርያ ከተማ ሲሆን ዘመኑም ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው። ወላጆቹ ባለጸጐች ነበሩ። ቅዱሱንና ታላቅ ወንድሙን አባ ጴጥሮስን ወልደዋል። ሁለቱ ክርስቲያን ወንድማማቾች ገና ወጣት ሳሉ ወላጆቻቸው ሞቱባቸው። ሃዘናቸውን ፈጽመው ሃብት ሲካፈሉ ግን መስማማት አልቻሉም።

ምክንያቱ ደግሞ ትልቁ ጴጥሮስ ደህና ደህናውን እቃ ወስዶ መናኛ መናኛውን ለትንሹ ለጳውሎስ (ጳውሊ) መስጠቱ ነበር። ስለዚህ ነገር ተካሰው ወደ ፍርድ ቤት ሲሔዱ ግን መንገድ ላይ አንድ ባለጸጋ ሙቶ ደረሱ።

ቆመው ሳሉም ቅዱስ መልአክ ሰው መስሎ ጳውሊን "ይህ ሰው ባለጸጋ ነው። በገንዘቡ የሰጠውን ፈጣሪ ሲበድልበት ኑሮ እነሆ ተሸኘ። በሰማይም አስጨናቂ ፍርድ ይጠብቀዋል።" ሲል ነገረው።

በዚያች ቅጽበት የወጣቱ ጳውሊ ሐሳብ ተለወጠ። ወደ ወንድሙ ተመልሶ "ወንድሜ ሆይ! ሁሉ ንብረት ያንተ ይሁን።" ብሎት ከአካባቢው ጠፋ። በመቃብር ሥፍራ ለሦስት ቀናት ያለ ምግብ ጸልዮ የእግዚአብሔር መልአክ ሰው ወደ ማይደርስበት በርሃ ወሰደው።

በዚያም ምንጭ ፈለቀችለት። እየጾመ ይጸልይ ይሰግድ ገባ። ሁሌ ማታ ግማሽ ሕብስት ከሰማይ እየወረደለት ቅዳሜና እሑድ መላእክት እያቆረቡት ለሰማንያ ዓመታት ኖረ። (አንዳንድ ምንጮች ግን ለዘጠና ዓመታት ይላሉ።) ከቅዱስ እንጦንስ ጋር የተገናኙትም ከዚህ በኋላ ነው።

ከቅዱስ እንጦንስ ጋር በነበራቸው የሁለት ቀናት ቆይታም ቅዱስ ጳውሊ ብዙ ትንቢቶችን ተናግሯል። በዚህች ቀን ሲያርፍም መቃብሩን አናብስቱ ቆፍረዋል። ቅዱስ እንጦንስም በክብር ቀብሮታል። ለሰማንያ ዓመታት የለበሳት የዘንባባ ልብሱም ሙት አስነስታለች።

††† ጻድቅ፣ ቡሩክ፣ ቀዳሚው ገዳማዊ፣ መላእክትን የመሰለና የባሕታውያን ሁሉ አባት ለተባለ ለቅዱስ ጳውሊ ክብር ይገባል!

††† አባ ለንጊኖስ †††

††† ጻድቁ ከኪልቅያ እስከ ሶርያ ከሶርያ እስከ ግብጽ ድረስ በተጋድሎ የተጓዙ አባት ናቸው። በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽም የደብረ ዝጋግ (ግብጽ፤ እስክንድርያ) አበ ምኔት ሆነው አገልግለዋል።

ሙታንን አስነስተው ሃይማኖታቸውን ጠብቀው ብዙ ተአምራትን ሠርተው በዚህች ቀን ዐርፈዋል። ከድንቅ ነገራቸው ሰይጣን የእርሳቸውን የምንኩስና ቆብ ዐይቶ ደንግጦ መሸሹን እንጠቅሳለን።
"ኀበ ኢኀሎከ ሶበ ቆብዓከ ርዕየ
ሰይጣን ተኃፊሮ እፎኑመ ጐየ።" እንዲል።
(አርኬ)

††† አምላክ በበረከታቸው ይባርከን።
የካቲት ፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አባ ጳውሊ ገዳማዊ (የባሕታውያን ሁሉ አባት)
፪.ቅዱስ አባ ለንጊኖስ ሊቀ ምኔት (ደብረ ዝጋግ)
፫.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
††† ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
፪.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ
፫.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ (የሃይማኖት
ጠበቃ)
፬.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ
፭.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
፮.አባ ሕርያቆስ ዘሐገረ ብሕንሳ

††† "የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ። ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ። በድንጋይ ተወግረው ሞቱ። ተፈተኑ፤ በመጋዝ ተሰነጠቁ፤ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ። ሁሉን እያጡ፣ መከራን እየተቀበሉ፣ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ። ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ በዋሻና በምድር ጉድጓድ ተቅበዘበዙ።" †††
(ዕብ ፲፩፥፴፭-፴፰)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

Dn Yordanos Abebe
Audio
"" መንፈስ ቅዱስን የሰደበ ኀጢአቱ አይሠረይለትም! "" (ማቴ. ፲፪:፴፩)

(የካቲት 1 - 2016)

ዝክረቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት

"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::
       አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር
በዩቲብለመከታተል👉
https://www.youtube.com/@ZikereKedusan
በቴሌግራም👉
https://www.tg-me.com/zikirekdusn
† እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ አጋቦስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ አጋቦስ ሐዋርያ †††

††† ከ72ቱ አርድዕት አንዱ የሆነው ቅዱሱ ሐዋርያ ሃብተ-ትንቢት የተሠጠውና በዘመነ ሐዋርያት (በቀላውዴዎስ ቄሳር ጊዜ) በዓለም ላይ ከባድ ረሃብ እንደሚሆን ትንቢት የተናገረና በርካታ ክርስቲያኖችን ከረሃብና ከሞት የታደገ ትልቅ ሐዋርያ ነው:: (ሐዋ. 11:27)

በቅዱስ ጳውሎስ ላይ የሚደርሰውን መከራ በመናገሩም "ሐዋርያ ትንቢት" ተብሏል:: በአገልግሎቱ ከአይሁድና ከአረማውያን ብዙዎችን ወደ ክርስትና በመሳቡ የተበሳጩ አይሁድም በዚህች ቀን ገድለውታል:: በተቀደሰ ሥጋው (መቃብሩ) ላይ ብርሃን ሲወርድ ያየች አይሁዳዊት ሴትም በክርስቶስ አምና ተሰውታለች::

††† የአባታችን በረከት ይደርብን::

የ††† ካቲት 4 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አጋቦስ ነቢይ: ሐዋርያና ሰማዕት
2.አባ ዘካርያስ ትሩፈ ምግባር

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ ሐዋርያ ወልደ ነጎድጓድ
2.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
3.ቅድስት ሶፊያ ሰማዕት
4.ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ

††† "በዚያም ወራት ነቢያት ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ወረዱ:: ከእነርሱም አጋቦስ የሚሉት አንድ ሰው ተነስቶ በዓለም ሁሉ ታላቅ ራብ ሊሆን እንዳለው በመንፈስ አመለከተ:: ይህም በቀላውዴዎስ ቄሣር ዘመን ሆነ::
ደቀ መዛሙርትም እያንዳንዳቸው: እንደ ችሎታቸው መጠን አዋጥተው በይሁዳ ለሚኖሩት ወንድሞች እርዳታን ይልኩ ዘንድ ወሰኑ::
እንዲህም ደግሞ አደረጉ:: በበርናባስና በሳውልም እጅ ወደ ሽማግሌዎቹ ሰደዱት::" †††
(ሐዋ. ፲፩፥፳፯)

††† "ስለ እኛ ትጸልዩ ዘንድ ይገባቹሃል: ለሁሉ መልካም ነገርን እንደምትወዱና እንደምትሹ እናምናለን::" †††
(ዕብ. ፲፫፥፲፰)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

Dn Yordanos Abebe
2024/09/25 11:25:03
Back to Top
HTML Embed Code: