Telegram Web Link
ቅዱስ አብሮኮሮስ ሐዋርያ
(Saint Prochorus The Desciple)

=>በዘመነ ሐዋርያት ዝነኛ ከነበሩ ቅዱሳን አንዱ ቢሆንም አሁን እየተዘነጋ ነው:: ቁጥሩ ከ72ቱ አርድእት ሲሆን የዮሐንስ ወንጌላዊ ደቀ መዝሙር ሆኖ የሰኔ ጐልጐታን ምሥጢር ጽፏል:: ከአርድእት ባለ ረዥም ዕድሜ እና ከዕርገተ ክርስቶስ በሁዋላ ለ80 ዓመታት ያስተማረ ደግ ሐዋርያ ነው::

<< እጅግ አርጅቶ ወደ ወደደው ክርስቶስ የሔደው ጥር 20  ነውና በረከቱ ይደርብን !! >>


❇️ዝክረቅዱሳን (ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት)❇️

" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
https://www.tg-me.com/zikirekdusn
እንኳን ለእመቤታችን ንጽሕት ድንግል ወላዲተ አምላክ ማርያም ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

† ዕረፍተ ድንግል †

††† እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድመ ዓለም በአምላክ ልቡና ታስባ ትኖር ነበር:: ከነገር ሁሉ በፊት እግዚአብሔር እናቱን ያውቃት ነበር::

*ዓለም ተፈጥሮ: አዳምና ሔዋን ስተው: መርገመ ሥጋና መርገመ ነፍስ አግኝቷቸው: በኃዘን ንስሃ ቢገቡ "እትወለድ እም ወለተ ወለትከ - ከ5 ቀን ተኩል (5500 ዘመናት) በሁዋላ ካንተ ባሕርይ ከምትገኝ ንጽሕት ዘር ተወልጄ አድንሃለሁ" ብሎ ተስፋ ድኅነት ሰጠው::

*ከአዳም አንስቶ ለ5500 ዓመታት አበው: ነቢያትና ካህናት ስለ ድንግል ማርያም ብዙ ሐረገ ትንቢቶችን ተናገሩ:: መዳኛቸውን ሱባኤ ቆጠሩላት:: ምሳሌም መሰሉላት:: ከሩቅ ዘመን ሁነውም ሊያገኟት እየተመኙ እጅ ነሷት::
"እምርሑቅሰ ርእይዋ: ወተአምኅዋ" እንዲል::

††† የድንግል ማርያም ሐረገ ትውልድ
*ከአዳም በሴት
*ከያሬድ በሔኖክ
*ከኖኅ በሴም
*ከአብርሃም በይስሐቅ
*ከያዕቆብ በይሁዳና በሌዊ
*ከይሁዳ በእሴይ: በዳዊት: በሰሎሞንና በሕዝቅያስ ወርዳ ከኢያቄም ትደርሳለች::

*ከሌዊ ደግሞ በአሮን: አልዓዛር: ፊንሐስ: ቴክታና በጥሪቃ አድርጋ ከሐና ትደርሳለች::

*አባታችን አዳም ከገነት በወጣ በ5,485 ዓመት ወላዲተ አምላክ ንጽሕና ሳይጐድልባት: ኃጢአት ሳያገኛት: ጥንተ አብሶ ሳይደርስባት ከደጋጉ ኢያቄም ወሐና ትወለዳለች:: (ኢሳ. 1:9, መኃ. 4:7) "ወኢረኩሰት በምንትኒ እምዘፈጠራ" እንዳለ:: (ቅዱስ ቴዎዶጦስ ዘዕንቆራ)

ከዚያም ከእናት ከአባቷ ቤት ለ3 ዓመታት ቆይታ ወደ ቤተ መቅደስ ትገባለች:: በቤተ መቅደስም ለ12 ዓመታት ፈጣሪዋን እግዚአብሔርን እያመሰገነችና እያገለገለች: እርሷን ደግሞ መላእክተ ብርሃን እያገለገሏት: ሕብስት ሰማያዊ ጽዋዕ ሰማያዊ እየመገቧት ኑራለች:: 15 ዓመት በሞላት ጊዜ አረጋዊ ዮሴፍ ያገለግላት ዘንድ ወደ ቤቱ ወሰዳት::

*በዚያም መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ዜና ድኅነትን ነግሯት አካላዊ ቃልን በማሕጸንዋ ጸነሰችው:: ነደ እሳትን ተሸከመችው: ቻለችው:: "ጾርኪ ዘኢይትጸወር: ወአግመርኪ ዘኢይትገመር" እንዳለ:: (ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ለብሐዊ)

*ወልደ እግዚአብሔርን ለ9 ወራት ከ5 ቀናት ጸንሳ: እንበለ ተፈትሆ (በድንግልና) ወለደችው:: (ኢሳ. 7:14) "ኢየሱስ" ብላ ስም አውጥታለት በገሊላ ለ2 ዓመታት ቆዩ::

*አርዌ ሔሮድስ እገድላለሁ ብሎ በተነሳበት ወቅትም ልጇን አዝላ በረሃብ እና በጥም: በላበትና በድካም: በዕንባና በኃዘን ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት ከገሊላ እስከ ኢትዮዽያ ተሰዳለች:: ልጇ ጌታችን 5 ዓመት ከ6 ወር ሲሆነው: ለድንግል ደግሞ 21 ዓመት ከ3 ወር ሲሆናት ወደ ናዝሬት ተመለሱ::

*በናዝሬትም ለ24 ዓመታት ከ6 ወራት ልጇን ክርስቶስን እያሳደገች: ነዳያንን እያሰበች ኑራለች:: እርሷ 45 ዓመት ልጇ 30 ዓመት ሲሆናቸው ጌታችን ተጠምቆ በጉባኤ ትምሕርት: ተአምራት ጀመረ:: ለ3 ዓመታት ከ3 ወራትም ከዋለበት እየዋለች: ካደረበትም እያደረች ትምሕርቱን ሰማች::

*የማዳን ቀኑ ደርሶ ልጇ ክርስቶስ ሲሰቀልም የመጨረሻውን ፍጹም ሐዘን አስተናገደች:: አንጀቷ በኃዘን ተቃጠለ:: በነፍሷም ሰይፍ አለፈ:: (ሉቃ. 2:35) ጌታ በተነሳ ጊዜም ከፍጥረት ሁሉ ቀድማ ትንሳኤውን አየች:: ለ40 ቀናትም ሳትለይ ከልጇ ጋር ቆየች::

*ከልጇ ዕርገት በሁዋላ በጽርሐ ጽዮን ሐዋርያትን ሰብስባ ለጸጋ መንፈስ ቅዱስ አበቃች:: በጽርሐ ጽዮንም ከአደራ ልጇ ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ለ15 ዓመታት ኖረች:: በእነዚህ ዓመታት ሥራ ሳትፈታ ስለ ኃጥአን ስትማልድ: ቃል ኪዳንን ከልጇ ስትቀበል: ሐዋርያትን ስታጽናና: ምሥጢርም ስትገልጽላቸው ኑራለች::

*ዕድሜዋ 64 በደረሰ ጊዜ ጥር 21 ቀን መድኃኒታችን አእላፍ ቅዱሳንን አስከትሎ መጣ:: ኢየሩሳሌምን ጨነቃት:: አካባቢውም በፈውስ ተሞላ:: በዓለም ላይም በጐ መዓዛ ወረደ:: እመ ብርሃን ለፍጡር ከዚያ በፊት ባልተደረገ: ለዘለዓለምም ለማንም በማይደረግ ሞገስ: ክብርና ተአምራት ዐረፈች:: ሞቷ ብዙዎችን አስደንቁአል::
"ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ::
ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኩሉ::" እንዲል::

*ከዚህ በሁዋላ መላእክት እየዘመሩ: ሐዋርያቱም እያለቀሱ ወደ ጌቴሴማኒ: በአጐበር ሥጋዋን ጋርደው ወሰዱ:: ይሕንን ሊቃውንት:-
"ሐራ ሰማይ ብዙኃን እለ አልቦሙ ሐሳበ::
እንዘ ይዜምሩ ቅድሜኪ ወመንገለ ድኅሬኪ ካዕበ::
ማርያም ሞትኪ ይመስል ከብካበ" ሲሉ ይገልጡታል::

*በወቅቱ ግን አይሁድ በክፋት ሥጋዋን እናቃጥል ስላሉ ቅዱስ ገብርኤል (ጠባቂ መልአክ ነው) እነርሱን ቀጥቶ: እርሷን ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ወስዶ በዕጸ ሕይወት ሥር አኑሯታል:: በዚያም መላእክት እያመሰገኗት ለ205 ቀናት ቆይታለች::

*ቅዱስ ዮሐንስ መጥቶ ለሐዋርያቱ ክብረ ድንግልን ቢነግራቸው በጐ ቅንአት ቀንተው በነሐሴ 1 ሱባኤ ጀመሩ:: 2ኛው ሱባኤ ሲጠናቀቅም ጌታ የድንግል ማርያምን ንጹሕ ሥጋ ሰጣቸው:: እየዘመሩም በጌቴሴማኒ ቀብረዋታል::

*በ3ኛው ቀን (ነሐሴ 16) እንደ ልጇ ባለ ትንሳኤ ተነስታ ዐርጋለች:: ትንሳኤዋንና ዕርገቷንም ደጉ ሐዋርያ ቅዱስ ቶማስ አይቶ: መግነዟን ተቀብሏል:: ሐዋርያቱም መግነዟን ለበረከት ተካፍለው: እንደ ገና በዓመቱ ነሐሴ 1 ቀን ሱባኤ ገቡ::

*ለ2 ሳምንታት ቆይተው: ሁሉንም ወደ ሰማይ አወጣቸው:: በፍጡር አንደበት ተከናውኖ የማይነገር ተድላ: ደስታና ምሥጢርንም አዩ:: ጌታ ራሱ ቀድሶ ሁሉንም አቆረባቸው:: የበዓሉን ቃል ኪዳን ሰምተው: ከድንግል ተባርከው ወደ ደብረ ዘይት ተመልሰዋል::

††† ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን: ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኚልን:: አእምሮውን: ለብዎውን: ጥበቡን በልቡናችን ሳይብን አሳድሪብን:: †††

††† ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሊቅ †††

††† ለዚህ ቅዱስ አባት ብጹዕ መባል ተገብቷል:: ክቡር: ምስጉን: ንዑድ ሰው ነውና:: በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን በቂሣርያ ቀዸዶቅያ የተወለደው ቅዱሱ ሰው ለደሴተ ኑሲስ ብርሃኗ ነው:: አባቱ ኤስድሮስ: እናቱ ኤሚሊያ: ወንድሞቹ ቅዱሳን "ባስልዮስ: ዼጥሮስ: መክርዮስና መካርዮስ" ይባላሉ::

የተቀደሰች እህቱም ማቅሪና ትባላለች:: ከዚህ የተባረከ ቤተሰብ ለቅድስና ያልበቃ አንድም ሰው የለም:: ሊቁ ቅዱስ ጐርጐርዮስም ከማር በጣፈጠ ዜና ሕይወቱ እንደ ተጻፈው:-
*በልጅነቱ ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምሯል::
*ሥጋውያን ጠቢባንን ያሳፍር ዘንድም የግሪክን ፍልሥፍና በልኩ ተምሯል::
*በታላቅ ወንድሙ ቅዱስ ባስልዮስ መሪነት ገዳማዊ ሕይወትን ተምሯል::
*በመንኖ ጥሪት ተመስግኗል::
*ተገብቶትም በኑሲስ ደሴት ላይ ዻዻስ ሆኗል::
*እርሱ ሲሔድ በከተማው የነበሩ ክርስቲያኖች 11 ብቻ የነበሩ ሲሆን እርሱ ሲያርፍ ክርስቶስን የማያመልኩ ሰዎች ቁጥር 11 ብቻ ነበር::
*ቅዱስ ጐርጐርዮስ ፍጹም ሊቅ ነበርና ከቁጥር የበዙ ድርሳናትን ደርሷል::
*ታላቁን ጉባኤ ቁስጥንጥንያን (በ381 ዓ/ም) መርቷል:: ብዙ መናፍቃንንም አሳፍሯል::

ከንጽሕናው የተነሳ መላእክት ያቅፉት: እመ ብርሃንም ትገለጥለት ነበር:: ለ33 ዓመታት እንደ ሐዋርያት ኑሮ በዚህ ቀን ድንግል ጠራችው:: ቀድሶ አቁርቦ: ሕዝቡን አሰናብቶ: የቤተ መቅደሱን ምሰሶ እንደ ተደገፈ ዐርፎ ተገኝቷል:: በዝማሬና በፍቅር ቀብረውታል::
††† ቅድስት ኢላርያ †††

††† "ኢላርያ" ማለት "ፍሥሕት (ደስ የተሰኘች)" እንደ ማለት ነው:: ከተባረኩ ቅዱሳት አንስት ትልቁን ሥፍራ ትይዛለች:: ማን እንደ እርሷ!

ቅድስት ኢላርያ ማለት:-
*የታላቁ ንጉሠ ነገሠት: የደጉ ዘይኑን (Emperor Zenon) የበክር ልጅ
*በ6ኛው መቶ ክ/ዘመን የተወለደች
*ትምሕርተ ሃይማኖትን: ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የተማረች
*ምድራዊ ንግሥናን ንቃ ፍቅረ ክርስቶስን የመረጠች
*የአባቷን ቤተ መንግስት ትታ ከሮም ግዛት ወደ ግብጽ (ገዳመ አስቄጥስ) የወረደች:
*ስሟን ከኢላርያ ወደ ኢላርዮን ቀይራ በወንዶች ገዳም የመነኮሰች
*ራሷን በፍጹም ገድል ቀጥቅጣ ከወንዶቹ በላይ በሞገስ ከፍ ከፍ ያለች
*ትንሽ እህቷን ጨምሮ በርካቶችን የፈወሰች
*በእርሷ ምክንያት ለግብጽና በመላው ዓለም ለሚገኙ ገዳማት ብዙ ቸርነት በዘይኑን የተደረገላት ታላቅ እናት ናት::

ቅድስት ኢላርያ ማንም ሴት መሆኗን ሳያውቅባት: አባ ኢላርዮን እንደ ተባለች በዚህች ቀን ዐርፋለች:: ቤተ ክርስቲያንም እነሆ ላለፉት 1,400 ዓመታት: ቅድስቲቱንና የተባረከ አባቷን ዘይኑንን: ስለ በጐነታቸውና ውለታቸው ታስባቸዋለች::

††† የእመቤታችን ድንግል ማርያም ጣዕሟ: ፍቅሯ: ጸጋዋና በረከቷ ይደርብን:: †††

††† ጥር 21 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
1.በዓለ አስተርዕዮ ማርያም (እመቤታችን ከእረፍቱዋ በሁዋላ ለደቀ መዛሙርት በዚሁ ቀን ተገልጣ ነበር)
2.ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ (ታላቅ ሊቅና ጻድቅ)
3.ቅድስት ኢላርያ እናታችን (የዘይኑን ንጉሥ ልጅ)
4.ቅዱስ ኤርምያስ ነቢይ
5.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ
6.ቅዱስ ኒቆላዎስ ሰማዕት
7.አባ ፊቅጦር

††† ወርሐዊ በዓላት
1.አባ ምዕመነ ድንግል
2.አባ አምደ ሥላሴ
3.አባ አሮን ሶርያዊ
4.አባ መርትያኖስ
5.አበው ጎርጎርዮሳት

††† "ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን::
እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን::
አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነስ::
አንተና የመቅደስህ ታቦት::
ካህናቶችህ ጽድቅን ይልበሱ::
ቅዱሳንህም ደስ ይበላቸው::
ስለ ባሪያህ ስለ ዳዊት. . ."
(መዝ. 131:7)

††† "ወዳጄ ሆይ! ተነሺ::
ውበቴ ሆይ! ነዪ::
በዓለት: በንቃቃትና በገደል መሸሸጊያ ያለሽ ርግብ ሆይ!
ቃልሽ መልካም: ውበትሽም ያማረ ነውና:
መልክሽን አሳዪኝ::
ድምጽሽንም አሰሚኝ::"
(መኃ. 2:13)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

https://www.tg-me.com/zikirekdusn
እንኳን አደረሳችሁ


በረከቱ ይደርብና የቅዱስ ገላውዴዎስና የቅድስት እምነ ጽዮን ፍሬ አቡነ ቀውስጦስ ሰማዕተ ጽድቅ ጥር 21  ዕረፍቱ

ዝክረ ቅዱሳን (ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት)

" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
https://www.tg-me.com/zikirekdusn
✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞

ጥር 22 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

++ አባ እንጦንስ ++

=>በቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ "ታላቁ / ዓቢይ / THE GREAT" የሚል ስም የሚሰጣቸው አባቶች የተለዩ
ናቸው::
አንድም እጅግ ብዙ ትሩፋቶችን የሠሩ ናቸው:: በሌላ
በኩል ደግሞ በተመሳሳይ ስም ከሚጠሩ ሌሎች ቅዱሳን
እንለይበታለን::

+ገዳማዊ ሕይወት ጥንቱ ብሉይ ኪዳን ነው::
በቀዳሚነትም በደብር ቅዱስ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ደቂቀ
ሴት እንደ ጀመሩት
ይታመናል:: ሕይወቱ በጐላ: በተረዳ መንገድ የታየው ግን
በታላቁ ጻድቅ ሄኖክ: ከዚያም በቅዱሱ ካህን መልከ
ጼዴቅ
አማካኝነት ነው::

+ቀጥሎም እነ ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ: እነ ኤልሳዕ ደቀ
መዝሙሩ ኑረውበታል:: በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ሙሉ
ሕይወቱን በገዳም
(በበርሃ) ያሳለፈው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ
ቅድሚያውን ይይዛል::

+ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ
በገዳመ ቆረንቶስ ለ40 ቀናት በትሕርምት ኑሮ ገዳማዊ
ሕይወትን
ቀድሷል: አስተምሯል:: በዘመነ ስብከቱም ያድርባት
የነበረችው የደብረ ዘይቷ በዓቱ (ኤሌዎን ዋሻ) በራሷ
ለዚህ ሕይወት
ትልቅ ማሳያ ናት::

+ከጌታ ዕርገት በኋላም ክርስቲያኖቹ የዓለም ሁካታ
ሲሰለቻቸው: አንድም በንጹሕና በተሸከፈ ልቡና
ለፈጣሪያቸው መገዛትን
ሲሹ ከከተማ ወጣ እያሉ ይኖሩ እንደ ነበር የታሪክ
መዛግብት ያሳያሉ:: አኗኗራቸውም በቡድንም: በነጠላም
ሊሆን ይችላል::

+ዋናው ነገር ግን በጾምና በጸሎት መትጋታቸው ነው::
ይሕም ሲያያዝ እስከ 3ኛው መቶ ክ/ዘመን ደረሰ:: በዚህ
ዘመን
ግን አባ ዻውሊ የሚባል አንድ ንጹሕ ክርስቲያን ይሕንን
ሕይወት ወደ ሌላ ደረጃ ከፍ አደረገው::
ለ80 ዓመታት ሰው ሳያይ ተጋድሎ 'የባሕታውያን አባት'
ተባለ:: ደንብ ያለው ተባሕትዎም ጀመረ::

+ይህ ከሆነ ከ20 ዓመታት በኋላ ደግሞ አባ እንጦንስ
የሚባሉ ደግ ክርስቲያን ይህንን ገዳማዊ ሕይወት በሌላ
መንገድ
አጣፈጡት:: በቅዱስ ሚካኤል አመንኳሽነት ገዳማዊ
ሕይወት በምንኩስና ተቃኘ:: ስለዚህም አባ እንጦንስ
የመነኮሳት አባት ተባሉ::

+እርሳቸውም ሕይወቱን ለማስፋፋት ከተለያዩ አሕጉር ደቀ
መዛሙርትን እየተቀበሉ አመንኩሰዋል:: ቅዱሳን የአባ
እንጦንስ
ልጆችም ወደየ ሃገራቸው ተመልሰው: ሕይወቱን በተግባር
አሳይተው ገዳማዊነትን አስፋፍተዋል::

+"+ አባ እንጦንስ +"+

+አባ እንጦንስ የመነኮሳት ሁሉ አባታቸው: ለገዳማውያን
ሁሉም ሞገሳቸው ናቸው:: እንዲያውም ብዙ ጊዜ "ኮከበ
ገዳም:
ማኅቶተ ገድል (የበርሃው ኮከብ: የተጋድሎ መብራት)"
ተብለውም ይጠራሉ::

+ቤተ ክርስቲያን ለጀማሪዎች ትልቅ ትኩረት ትሰጣለች::
ለምሳሌ:- አባ ዻውሊን (የካቲት 2 የሚከበሩ)
ለብሕትውና
መሠረትን ስለ ጣሉ "አበ ባሕታውያን" ብላ ታከብራለች::
አባ እንጦንስን ደግሞ "አበ መነኮሳት (የመነኮሳት አባት):
ቀዳሚሆሙ ለመነኮሳት (ለመነኮሳት ቀዳሚና ጀማሪ)
ስትል ትጠራቸዋለች::

+አባ እንጦንስ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ለሚነሱ ቅዱሳን
መነኮሳት ሁሉ መንገድን ይጠርጉ ዘንድ ብዙ መከራን
በትዕግስትና
በአኮቴት ተቀብለዋል:: ላለፉት 1,700 ዓመታት እንደ
ሻማ እየቀለጡ ያበሩ አበው ቅዱሳን ሁሉ የአባ እንጦንስ
ልጆች ናቸው::

+ከምጥ የከፋ የዲያብሎስ ፈተናን ተቀብለው ከመንፈሳዊ
አብራካቸው ቅዱሳኑን ወልደዋል:: የመነኮሳት አለቃ
የሆኑትን
ታላቁን መቃርዮስን ጨምሮ በርካቶችን አመንኩሰው
ለቅድስና አብቅተዋል::

+አባ እንጦንስ ግብጻዊ ሲሆኑ የተወለዱት አቅማን
በምትባል ቦታ አካባቢ ነው:: ጊዜውም በ252 ዓ/ም
ነው:: የተባረኩ
ወላጆች ለቅዱሱ እንጦንስና አስከትለው ለወለዷት ሴት
ልጃቸው አስቀድመው ፍቅረ ክርስቶስን: አስከትለውም
ሃብት
ንብረታቸውን አውርሰው ዐርፈዋል::

+በዚህ ጊዜ የአባ እንጦንስ እድሜ አፍላ ወጣትነት ላይ
ነበር:: በልጅነት ጊዜአቸውም አባ እንጦንስን ሲስቁ:
ሲጫወቱ:
አልያም ሲቀልዱ አየሁ የሚል ሰው አልነበረም:: ፍጹም
ቁም ነገረኛና ታዛዥ: በዚያ ላይም አስተዋይ ነበሩና ሙሉ
ጊዜአቸውንም ከቅዱስ ቃሉ በመመገብ: በትምሕርትና
በማስቀደስ ያሳልፉ ነበር::

+ዘወትርም ዜና ሐዋርያትን እያነበቡ በመንፈሳዊ ቅናት
ይቃጠሉ ነበር:: በጊዜው የምናኔ ሕይወት ጐልቶ ባለ
መገለጡ አባ
እንጦንስ የሚያደርጉት ይጨንቃቸው ነበር:: ሲጸልዩም
"አበው ሐዋርያት ይሕንን ክፉ ዓለም ንቃችሁ ጌታችሁን
የተከተላችሁበት ጥበብ እንደ ምን ያለ ነው!" እያሉ
ይደነቁ ነበር:: መሻታቸውን ያወቀ ጌታም ምሥጢርን
ገለጠላቸው::

+አንድ ቀን በቅዳሴ ላይ ወንጌል ሲነበብ ካህኑ ስለ
ምናኔ የሚጠቅሰውን ክፍል አነበበ:: ለአንድ ባለ ጠጋ
ሕግጋትን
ከነገረው በኋላ "ፍጹም ልትሆን ከወደድክስ ያለህን ሁሉ
ሸጠህ ተከተለኝ" (ማር. 10:17) የሚለውን ጥቅስ
ሲሰሙ
ተገርመው "ጌታ ሆይ! ይህንን የተናገርኸው ለእኔ ነው"
ሲሉ አሰቡ:: በቀጥታም ሃብታቸውን ለአካባቢው ሰው
አካፍለው:
እህታቸውን ከደናግል ማኅበር ደምረው እርሳቸው ወደ ዱር
ሔዱ::

+ከዚህች ቀን ጀምረው አባ እንጦንስ ከ80 እስከ መቶ
ለሚገመቱ ዓመታት ከአጋንንት ጋር በጦርነት ነበር
የኖሩት::
በንጹሕ አምልኮታቸውና በቅድስናቸው የቀና ጠላት
ሰይጣን በብዙ ጐዳና ፈተናቸው:: አቅም ቢያጥረው
አራዊትን መስሎ
ታገላቸው::

+በዚህ አልሳካ ቢለው የእሳት ሰንሰለትን አምጥቶ
ገረፋቸው:: በሞትና በሕይወት መካከል ጥሏቸው ሔደ::
ወድቀው
ያገነኟቸው ሰዎች ለዘመዶቻቸው ሰጥተዋቸው አገገሙ::
ልክ ሲነቁ ግን ፈጥነው ወደ በርሃ ተመለሱ::

+ሰይጣን በርሃው የቅዱሳን ማደሪያ እንዳይሆን ሰግቷልና
ጨክኖ ታገላቸው:: ግን አልቻላቸውምና ተረታ:: አምላከ
ኃያላን
ክርስቶስ ከቅዱሱ ጋር ነበርና:: ከዚህ በኋላ ግን ጸጋው
በዝቶላቸው ድውያንን የሚፈውሱና ሰይጣን
የማይቀርባቸው ሰው
ሆኑ::

+በረዥም ዘመነ ቅድስናቸውም:-
1.ብዙ አርድእትን ከመላው ዓለም ሰብስበው:
አስተምረው: ምናኔ ከግብጽ ማዶ በመላው ዓለም
አስፋፉ::
2.በደመና እየተጫኑ ብዙ አሕጉራትንም እየዞሩ ሰበኩ::
በዚህም አሕዛብን ወደ እምነት: ኃጥአንን ወደ ንስሃ
መለሱ::
3.ጊዜው ዘመነ ሰማዕታት ነበርና ወደ አደባባይ ሒደው
ከሃዲዎችን ገሠጹ:: ማንም ደፍሮ ግን አልገደላቸውም::

+እነዚህንና ሌሎች ተግባራትን እየሠሩ በቅዱስ ሚካኤል
እጅ መነኮሱ:: እርሳቸውም ብዙዎችን አመነኮሱ::
አርጅተው እንኳ
ከተጋድሎ ያላረፉት አባታችን የጣመ ነገር ቀምሰው:
ገላቸውን ታጥበው አያውቁም:: በ372 ዓ/ም በዚህች ቀን
ሲያርፉም
ዕድሜአቸው 120 ደርሶ ነበር::

+የአባ እንጦንስን በዓል ለማክበር የምትሹ ቤተ
ክርስቲያናቸው ጎንደር ከተማ ከቀሃ ኢየሱስ በላይ
ይገኛል::

<< ለአባታችን እንጦንዮስ / እንጦንስ / እንጦኒ ክብር
ይገባል:: >>

+" ቅዱስ ዑራኤል "+

+በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ከ7ቱ ሊቃነ
መላእክት አንዱ የሆነው ቅዱስ ዑራኤል:-
1.ድንግል ማርያም በአካለ ሥጋ እያለች ወደ ሰማይ
አሳርጉዋታል:: በሠረገላ ብርሃን ጭኖ: በክንፎቹም
ተሸክሞ: አስቅድሞ
ገነትን ቀጥሎም ሲዖልን አስጐብኝቷታል:: በዚህም
ምክንያት እመ ብርሃን ስለ ኃጥአን የምታለቅስ:
የምትለምንና የምትማልድ
ሆናለች:: ለምናም አልቀረች የምሕረት ቃል ኪዳን
ተቀብላለች::
2.ቅዱሱ መልአክ እመ ብርሃንን በስደቷ ጊዜ ወደ
ኢትዮዽያ መርቶ አምጥቷታል:: በክንፉ ተሸክሞ: በ4
አቅጣጫ አዙሮ
አሳይቶ አሥራት እንድትቀበል አድርጉዋል::
3.ጌታችን በተሰቀለ ጊዜ ደሙን በጽዋዕ አድርጐ
በኢትዮዽያ ወንዞች ላይ አፍስሷል::
4.ለብዙ ቅዱሳን (አባ ጊዮርጊስን ጨምሮ) ጽዋዐ ልቡናን
አጠጥቷል::

✞አምላከ ቅዱሳን ስለ ወዳጆቹ በጐ ምኞታችንን
ይፈጽምልን:: ከበረከታቸውም ያድለን::

✞ጥር 22 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=

1.ቅዱስ አባ እንጦንስ (የመነኮሳት አባት-የበርሐው
ኮከብ /ልደቱና ዕረፍቱ)
2.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላዕክት (ለተጠሙ ጽዋዓ
ልቡናን የሚያጠጣ: ምሥጢር ገላጭ መልዐክ)
3.ቅዱስ ሚናስ ኤዺስ ቆዾስ

ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ
3.ቅዱስ ደቅስዮስ (የእመቤታችን ወዳጅ)
4.አባ እንጦንስ አበ መነኮሳት
5.አባ ዻውሊ የዋህ

++"+ እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ::
መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ:: ነፍሱን ሊያድን የሚወድ
ሁሉ
ያጠፋታል:: ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ
ያገኛታል:: +"+ (ማቴ. 16:24)

✞✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር
† እንኳን ለቅዱስ ጢሞቴዎስ ሐዋርያ: እና ጻድቅ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ጢሞቴዎስ ሐዋርያ †††

††† ይህ ቅዱስ ሐዋርያ አንድ የቤተ ክርስቲያናችን መብራት ነው:: ወደ ክርስትና የመጣው በ40ዎቹ ዓ/ም አካባቢ ሲሆን አሳምኖ ለቅድስና ያበቃው ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ዻውሎስ ነው::

በጊዜውም በነበረው ትጋትና ተጋድሎ ፍሬ አፍርቷል:: ሆዱንም እጅግ ያመው ነበር:: ቅዱስ ዻውሎስ ሲጠራው "የምወድህ ልጄ" እያለ ነበር:: በኤፌሶንም ዽዽስናን ሹሞ 2 መልዕክታትን ልኮለታል:: ቅዱስ ጢሞቴዎስ ቤተ ክርስቲያንን ለብዙ ዘመናት አገልግሎ በሰማዕትነት ዐርፏል::

ከሐዋርያው ቅዱስ ጢሞቴዎስ በረከትን እንሳተፍ ዘንድ ጊዜ ካለን ቅዱስ ዻውሎስ ለልጁ ጢሞቴዎስ ከላካቸው መልዕክቶች ጥቂት እናንብብ::

††† ቴዎዶስዮስ †††

††† በዚህ ስም የሚጠሩ ብዙ አበው አሉ:: ሰማዕታትም: ጻድቃንም: ሊቃውንትም: ነገሥታትም ተጠርተውበታልና:: ዛሬ የምናከብረውም ቴዎዶስዮስ ዘየዓቢ (ታላቁ) የሚባል ሲሆን ይህን የምንለው ከትንሹ ቴዎዶስዮስ (የልጅ ልጁ ነው) ለመለየት ነው::

ታላቁ ቴዎዶስዮስ በሮም የነገሠው በ370 ዓ/ም አካባቢ ሲሆን ከነ ቤተሰቡ ክርስቲያን ነበር:: እነዚህ ነገሮቹ ደግሞ በቤተ ክርስቲያን እንዲታሰብ አድርጐታል:-
1.በዓለም ታሪክ ክርስትና በሮም ግዛት ሁሉ ብሔራዊ ሃይማኖት እንዲሆን አውጇል::
2.የቤተክርስቲያንን ትልቁን 2ኛ ጉባኤ ቁስጥንጥንያን በ381 (373) ዓ/ም አሰናድቷል::
3.ከበጐነቱ የተነሳ የተቀደሱ ልጆችን አፍርቷል:: ሙሽራው ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ: ቅዱስ አኖሬዎስ: ቅዱስ አርቃዴዎስ እና ቅድሰት ታኦድራ ልጆቹ ሲሆኑ አቡነ ኪሮስ ትንሽ ወንድሙ ናቸው::

ጻድቁ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ በ390 ዓ/ም አካባቢ ዐርፏል::

††† አምላከ ቅዱሳን ስለ አባቶቻችን ሲል ይማረን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::

††† ጥር 23 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ጢሞቴዎስ (ሐዋርያና ሰማዕት-የቅዱስ ዻውሎስ ደቀ መዝሙር)
2.ቅዱስ ጌርሎስ ሰማዕት
3.ቅዱስ አትናቴዎስ ሰማዕት
4.ጻድቅ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ (ዘቁስጥንጥንያ)

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዳዊት ልበ አምላክ
2.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
3.ቅዱስ ሰሎሞን ንጉሠ እሥራኤል
4.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
5.አባ ሳሙኤል
6.አባ ስምዖን
7.አባ ገብርኤል

††† "መድኃኒታችን እግዚአብሔር: ተስፋችንም ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳዘዘው ትእዛዝ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ዻውሎስ: በእምነት እውነተኛ ልጄ ለሆነ ለጢሞቴዎስ::
ከእግዚአብሔር ከአባታችን: ከክርስቶስ ኢየሱስም ከጌታችን: ጸጋና ምሕረት: ሰላምም ይሁን . . ." †††
(1ጢሞ. 1:1)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
2024/09/25 19:23:37
Back to Top
HTML Embed Code: