Telegram Web Link
ቅድስት አንስጣስያን በድብቅ ያጠመቃት ማን ነው/ናት
Anonymous Quiz
42%
ባሏ
11%
እህቷ
30%
እናቷ
17%
አባቷ
እንኩዋን ለሰማዕቱ "አባ አብሳዲ" እና ለጻድቁ "አባ በግዑ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

+"+ ቅዱስ አባ አብሳዲ +"+

=>ቅዱሱን የመሰሉ አባቶች "መስተጋድላን" ይባላሉ በግእዙ:: ለሃይማኖታቸው እስከ ደም ጠብታና እስከ መጨረሻዋ ህቅታ ድረስ መጋደላቸውን የሚያሳይ ነው:: መጋደል ጐዳናው ብዙ ዓይነት ነው::

+ከራሱ ጋር የሚጋደል አለ:: ከዓለም ጋር የሚጋደልም አለ:: የቅዱሳኑ ተጋድሎ ግን በዋነኝነት ከ2 አካላት ጋር ነው:: በመጀመሪያ ፍትወታት እኩያትን (ኃጣውዕን) ከሚያመጡ አጋንንት ጋር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ "ሃይማኖቸታችሁን ካዱ: ለጣዖትም ስገዱ" ከሚሉ ከሃድያን ጋር የሚደረግ ትግል ነው::

+በተለይ 2ኛው እስከ ሞት የሚያደርስ ውሳኔን ይጠይቃል:: የዚህን ቅዱስ ሕይወት ለመረዳት ግን አንድ ነገርን ልብ እንድትሉልኝ እፈልጋለሁ::

+ያለንበት ዘመን ክርስትና በራድ (ቀዝቃዛ) በመሆኑ የቀደሙ አባቶች የጸና ተጋድሎ አንዳንዴ ግራ ሲያጋባን ተመልክቻለሁ:: ቅዱሳኑ ሁሌም አንድ ነገርን እያሰቡ ይኖራሉ:: ይኼውም በዘመኑ በርካቶቻችን የረሳነው: ወይም ማስታወስ የማንፈልገው ነገር ይመስላል::

+ሰማያዊው አምላክ ከዙፋኑ ወርዶ በተዋሐደው ሥጋ በቃል ሊገለጽ የማይችል መከራን ስለ እኛ ተቀብሏል:: ክርስትና ማለት ቀራንዮን በልብ ውስጥ መሳል ነው:: ፍቅረ መስቀሉን: የጌታንም ውለታ የሚያስብ ማንኛውም ሰው: የትኛውም ዓይነት መከራ ቢመጣበት አይታወክም::

+ቅዱሳኑም የፍቅራቸውና የትእግስታቸው ምሥጢር ይኼው ነው:: ጌታችን "የሚወደኝ ቢኖር የሞቱን መስቀል ተሸክሞ ይከተለኝ" (ማቴ. 16:18) እንዳለው ቅዱሳኑ ይህንን ቃል በቃል ሲፈጽሙት እነሆ እንመለከታለን::

+"+ ቅዱስ አባ አብሳዲ +"+

=>ቅዱሱ ሰማዕት ተወልዶ ያደገው በምድረ ግብጽ : በ3ኛው መቶ ክ/ዘ ነው:: እንደርሱ በቅድስና ያጌጠ ባልንጀራም ነበረው:: ስሙም ቅዱስ አላኒቆስ ነበር::

+እኒህ ክርስቲያኖች በዚያ የመከራ ዘመን ግራ ቀኝ ሳይሉ ትምሕርተ ቤተ ክርስቲያንን ጠንቅቀው ተምረዋል:: በጐውን ጐዳና አጽንተው በመገኘታቸውም መንፈስ ቅዱስ 2ቱንም በአንዴ ለእረኝነት ጠራቸው::

+ዽዽስና ከዚህ በፊት እንደ ተመለከትነው እዳ (ኃላፊነት) እንጂ ምድራዊ ክብርን ማጋበሻ መንገድ: ወይም የሥጋ ድሎትን መፍጠሪያ ዙፋን አይደለም:: ያም ሆኖ ምርጫው የመንፈስ ቅዱስ ሲሆን ደስ ያሰኛል::

+በእርግጥም የክርስቶስን መንጋ እንደሚገባ መምራትና በለመለመው የወንጌል መስክ ማሰማራት የሚያስገኘው ክብር በሰማያት ታላቅ ነው:: ያም ቢሆን ግን ከብዙ መከራ በሁዋላ እንጂ እንዲሁ በዋዛ አይደለም:: የእግዚአብሔር ጸጋውና መንግስቱ ያለ መከራ አትገኝምና::

+ቅዱሳኑ አባ አብሳዲና አባ አላኒቆስም ይህንን ኃላፊነት የተረዱ ነበርና ታጥቀው ሥራቸውን ጀመሩ:: እንደ ሐዋርያት ሥርዓትም ያላመነውን ማሳመን: ያመነውን በሃይማኖቱ ማጽናት: የጸናውን ደግሞ ለምሥጢራተ ቅድሳት (ሥጋ ወደሙ) ማብቃት የዘወትር ተግባራቸው ነበር::

+ቅዱሳኑ በዚህ ተጋድሏቸው ሳሉ ዜናቸው በየቦታው ተሰማ:: ነገር ግን ይህ ዝናቸው የወለደው መከራን ነበር:: በጊዜው አውሬው ዲዮቅልጢያኖስ ክርስቲያኖችን ከዋሉበት አላሳድር: ካደሩበትም አላውል ብሎ ነበር::

+ለክፋቱ እንዲመቸው በየሃገሩ ጨካኝ መኮንኖችን ሾመ:: በምድረ ግብጽም 2 ገዢዎችን ሲያኖር አንዱ አርያኖስ (በሁዋላ አምኖ ሰማዕት ሆኗል): 2ኛው ደግሞ ሔርሜኔዎስ ይባላሉ::

+እነዚህ መኩዋንንት ግብጽን ለ2 ተካፍለው: በሥራቸው ገዥዎችን ሹመው በግፍ ተግባራቸው ክርስቲያኖችን ይቀጡ ገቡ:: የስቃይ ተራው ደግሞ የ2ቱ ቅዱሳን (አባ አብሳዲና አባ አላኒቆስ) ነበርና ተከሰሱ::

+ለፍርድ ይቀርቡ ዘንድም አርያኖስ በማዘዙ ወታደሮች መጡ:: ነገሮችን አስቀድሞ የሚያውቀው ቅዱስ አብሳዲም ምንም ስለ ክርስቶስ ለመሞት ቢቸኩልም መንጋውን እንዲሁ ሊበትን ግን አልወደደም::

+ስለዚህም ወታደሮችን "እባካችሁ ሕዝቡን ልሰናበት : አንድ ቀን ታገሱኝ" አላቸው:: ወታደሮቹ ከፊቱ የሚታየው ግርማው ደንቁዋቸው ነበርና ፈቀዱለት:: ቅዱሱም ከሕይወቱ የቀረችውን 24 ሰዓት ይጠቀምባት ዘንድ ምዕመናን ልጆቹን ሁሉ ጠራ::

+ቅዳሴ ቀድሶ : ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ፈትቶ ለሁሉም አቀበላቸው:: (በጊዜው የማይቆርብ ክርስቲያን አልነበረምና)

+ከቅዳሴ መልስም የተፈጠረውን ሁሉ ነግሮ ወደ ክርስቶስ ሊሔድ እንደ ናፈቀ ነገራቸው:: ሊያስቀሩት እንደማይችሉ ሲረዱ ፈጽመው አዘኑ:: እርሱም በቀናችው እምነት እስከ ሞት ድረስ እንዲጸኑ አስተምሯቸው ከባልንጀራው ቅዱስ አላኒቆስ ጋር በወታደሮች እጅ ወደቀ::

+እነርሱም ቅዱሳኑን ወስደው በመኮንኑ አርያኖስ ፊት ለፍርድ አቀረቧቸው:: አርያኖስም የአባ አብሳዲ የፊቱ ግርማ ቢስበው ላለመግደል ወስኖ ሊያባብለው ወሰነ:: "አንተ ክቡር ሰው ነሕና ለንጉሡ ታዘዝ : ለጣዖትንም እጠን" አለው::

+ቅዱስ አላኒቆስ ግን "ክብሬ ክርስቶስ ነውና ፈጣሪየን በምንም ነገር አልለውጠውም" ሲል እቅጩን ነገረው:: እንደማያሳምነው ሲረዳም ከአባ አላኒቆስ ጋር ያሰቃዩአቸው ዘንድ አዘዘ::

+በምስክርነት አደባባይም በመንኮራኩር (አካልን የሚበጣጥስ ተሽከርካሪ ብረት ነው) አበራዩአቸው:: እግዚአብሔር ግን አዳናቸው:: እንደ ገና እሳት አስነድደው እዚያ ውስጥ ጨመሯቸው:: እሳቱም ግን ሊበላቸው አልቻለም::

+በመጨረሻም መኮንኑ አንገታቸው ይሰየፍ ዘንድ አዘዘ:: ከመሰየፋቸው በፊትም ቅዱሳኑ ጸሎትን አደረሱ:: አባ አብሳዲ ነጭ የቅዳሴ ልብሱን ለብሶ: ወደ ሰይፍ ቀረበ:: ወታደሮች ደግሞ ሁለቱን ቅዱሳን እንደታዘዙት ሰየፏቸው:: በክብርም ዐረፉ::

+"+ አባ በግዑ ጻድቅ +"+

=>እኒህ አባት በመካከለኛው ዘመን የሃገራችን ታሪክ ሰፊ ቦታን ይዘው ይገኛሉ:: ተጋድሏቸውን የፈጸሙት በደብረ ሐይቅ ነው:: ጻድቁ ብዙ ጊዜ የሁዋለኛው ዘመን ሙሴ ጸሊም ይባላሉ:: ብዙ የሕወታቸው ጐዳና ተመሳሳይ ነው::

+ልክ ቅዱስ ሙሴ ጸሊም ከኃጢአት ከሽፍትነት ሕይወት እንደ መጣው ሁሉ አባ በግዑም አስቸጋሪ ሰው እንደ ነበሩ ይነገርላቸዋል:: ከዚያ የከፋ የኃጢአት ኑሮ እግዚአብሔር ሲጠራቸው ግን ክሳደ ልቡናቸውን አላደነደኑም:: "እሺ" ብለው ንስሃ ገቡ እንጂ::

+ከዚያም በደብረ ሐይቅ (ወሎ) በፍጹም ተጋድሎ ኑረዋል:: ያዩ ሁሉም ፍጹም ያደንቁ ነበር:: ስትበላ: ስትጠጣ የኖረችውን ሰውነት ራሳቸውን ውሃ ለዘመናት በመከልከል ቀጥተዋታል:: ስለዚህም "ውሃ የማይጠጣው አባት" ይባሉም ነበር:: ጻድቁ ሲያርፉ ፈጣሪያቸው አክብሯቸዋል::

=>አምላከ አበው ቅዱሳን አሠረ ፍኖታቸውን ይግለጽልን:: ከበረከታቸውም ያድለን::

=>ታሕሳስ 27 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አብሳዲ ሰማዕት
2.አባ አላኒቆስ ሰማዕት
3.አባ በግዑ ጻድቅ
4.አባ ፊልዾስ

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
2.አቡነ መብዓ ጽዮን ጻድቅ
3.ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ)
4.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
5.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
6.ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት
7.ማር ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት
=>+"+ መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ ዘጠና ዘጠኙን በበርሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሔድ ከእናንተ ማን ነው? ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል:: ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጐረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ 'የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ' ይላቸዋል:: እላችሁአለሁ: እንዲሁ ንስሃ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሃ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል:: +"+ (ሉቃ. 15:3-7)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
https://www.tg-me.com/zikirekdusn
#ሰማዕት ሊሆኑ ከመሄዳቸው በፊት ምእመኑን #ያቆረቡ አባት
Anonymous Quiz
21%
#አባ_በግዑ
33%
#አባ_አላኒቆስ
18%
#አባ_አብሳዲ
29%
ለ እና ሐ
ከተጋድሎ ብዛት #የጌታችንን_ሥጋ_ና_ደም ለመቀበል በቃሬዛ የወሰዱት #ቅዱስ_አባት
Anonymous Quiz
32%
#አባ_በግዑ
37%
#አባ_ይሥሐቅ
22%
#አባ_አብሳዲ
9%
#አባ_አላኒቆስ
እንኩዋን ለቅዱስ "አምላካችን አማኑኤል" : "ዕለተ ማርያም" እና "ዕለተ ጌና ስቡሕ" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ

+*" ቅዱስ አማኑኤል "*+

=>የክርስትና ሃይማኖት እጅግ ብዙ ምሥጢራትን ያካትታል:: ታላቅ መዝገብ ነውና:: ሰዎች እናልፋለን:: ዓለምም ታረጃለች እንጂ ምሥጢረ ክርስትና አያረጅም:: እዚህ ቦታ ላይ ይጠናቀቃልም አይባልም::

+"አማኑኤል" የሚለውን ስም መረዳት የሚቻለው በአንድ መንገድ : እርሱም ምሥጢረ ሥላሴንና ምሥጢረ ሥጋዌን ጠንቅቆ በመማር ነው:: ምሥጢራት ደግሞ በእምነት ለማይኖር: በትሕትናም ለማይቀርብ የሚገለጡ አይደሉም::

+እግዚአብሔር አንድም ነው: ሦስትም ነው:: ጊዜ ሣይሠፈር: ዘመንም ሳይቆጠር እግዚአብሔር በስም: በአካል: በግብር ሦስትነቱ: በባሕርይ: በሕልውና: በመለኮትና በሥልጣን አንድነቱ የጸና አምላክ ነው::

+ከዓለም መፈጠር በፊት ስለ ነበረው ነገር የሚያውቅ ራሱ ሥላሴ ብቻ ነው:: ዓለምን ከፈጠረ በሁዋላም ምሥጢረ ሥላሴ (መለኮት) ብለን የምንማረው ትምሕርት እንድንና እንጠቀም ዘንድ እርሱ የገለጠልንን ያህል ብቻ ነው::

+ይኼውም በየጊዜው እርሱ ለወደዳቸውና ደስ ላሰኙት ቅዱሳኑ የገለጠው ምሥጢር ነው:: ከዚህ አልፈን በሥጋዊ አዕምሯችን ጌታን "እንመርምርሕ" ብንለው ግን ፍጻሜአችን ሞት: ማደሪያችንም ገሃነመ እሳት መሆኑ አይቀርም::

+ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና እግዚአብሔር በአንድነቱና ሦስትነቱ ሳለ ይህንን ዓለም ፈጠረ:: እግዚአብሔር ዓለምን ለምን ፈጠረ ቢሉ:- ስሙን ቀድሰን ክብሩን እንድንወርስ ነው:: ከዚህ የተረፈውን ምክንያት ግን ራሱ ባለቤቱ ያውቃል::

+እግዚአብሔር በሁዋለኛው ዘመን ሰው የሆነበት ምሥጢር እኛን ለማዳን ቢሆንም ይሔው ተግባሩ ዓለም ሳይፈጠር ያሰበው እንጂ በአዳም ውድቀት ምክንያት ድንገት የታሰበ አይደለም::

+እግዚአብሔር አዳምን በ7 ሃብታት አክብሮ በገነት ቢያኖረው "አትብላ" የተባለውን ዕፀ በለስ በላ:: በዚህም ከፈጣሪው ተጣልቶ: በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ: በርደተ መቃብር ርደተ ገሃነም ተፈረደበት:: በሁዋላ ግን ንስሃ ስለ ገባ "ከ5 ቀን ተኩል (5,500 ዘመን) በሁዋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ" የሚል ቃል ኪዳንን ሰጠው::

+ከዚህ በሁዋላ ለ5,500 ዘመናት ጊዜ ወደ ታች ይቆጠር ጀመር:: ስለ እግዚአብሔር ሰው መሆንና ዓለምን ማዳንም ትንቢት ይነገር: ሱባኤ ይቆጠር: ምሳሌም ይመሰል ገባ::

+ከአዳም እስከ ሙሴ (ዘመነ አበው) ምሳሌያት ይበዛሉ:: ከሙሴ እስከ ዳዊት (ዘመነ መሣፍንት) ምሳሌያቱ እየጐሉ መጥተዋል:: ከልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት እስከ ቅዱስ ሚልክያስ ድረስ (በዘመነ ነቢያት / ነገሥት) ግን ትንቢቶች ስለ ክርስቶስና ስለ ማደሪያ እናቱ እንደ ጐርፍ ፈሰዋል::

+ነቢያትም የመሲህን መምጣት እየጠበቁ በጾም: በጸሎትና በትሕርምት ኑረዋል:: እንባቸውንም አፍሰው ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶላቸዋል:: መድኅን ክርስቶስም ተወልዶ አድኗቸዋል::

+"አማኑኤል" የሚለው ቃል ከእብራይስጥ ልሳን (ከጽርዕ የሚሉም አሉ) በቀጥታ የተወረሰ ሲሆን ትርጉሙም "እግዚአብሔር ምስሌነ - እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ" እንደ ማለት ነው:: (ኢሳ. 7:14, ማቴ. 1:22) ምሥጢሩ ግን ከዚህ የሠፋ ነው::

+"አማኑኤል" ማለት "እግዚአብሔር ከሥጋችን ሥጋን: ከነፍሳችን ነፍስን ነስቶ በፍጹም ተዋሕዶ እኛን መሰለን" ማለት ነው:: በሌላ አነጋገርም "አምላክ ሰው ሆነ: ሰውም አምላክ ሆነ" እንደ ማለት ነው::

+ይሕንን ሲያደንቁ ቅዱሳን ሊቃውንት "ወዝንቱ ስም ዓቢይ: ወኢይደሉ ፈሊጦቶ-ይህ ስም ታላቅ ነው:: ወደ ሁለት ሊከፍሉት (ሊለዩት) አይገባም" ብለው ምሥጢረ ተዋሕዶን አስረድተዋል:: (ሃይ. አበ. ዘሳዊሮስ)

+ስለዚህም ከሦስቱ አካላት አንዱ ወልድ እኛን ያድን ዘንድ በተለየ አካሉና በከዊነ ቃልነቱ ፍጹም የድንግል ማርያምን ሥጋ ተዋሕዶ የሰውነትንም: የአምላክነቱንም ሥራ ሠርቶ አድኖናል::

+በማሕጸነ ድንግል ከተቀረጸባት ደቂቃ ጀምሮም ፍጹም ተዋሕዶን ፈጽሟልና መቼም መች አምላክም: ሰውም ነው እንጂ ወደ ሁለትነት: ማለትም አምላክን ለብቻ: ሰውን ለብቻ አናደርግም::

+ስለዚህም ዛሬም: ዘወትርም እግዚአብሔር ቃል የተዋሐደው ሥጋችን በዘባነ ኪሩብ ሲሠለስና ሲቀደስ ይኖራል:: እርሱ ጌታችን እስከዚህ ድረስ ወዶናልና::

+ፈጣሪያች በሦስትነቱ:- ሥላሴ (አብ: ወልድ: መንፈስ ቅዱስ): በአንድነቱ:- እግዚአብሔር: ኤልሻዳይ: አልፋ: ወዖ: ቤጣ: የውጣ: ኦሜጋ . . . እያልን እንደምንጠራው ሁሉ በሥጋዌው ምክንያት:- አማኑኤል: መድኃኔ ዓለም: ኢየሱስ: ክርስቶስ እያልን እንጠራዋለን::

+*" ዕለተ ጌና "*+

=>ከሳምንታት በፊት ጀምረን የክርስቶስን የማዳን ሥራ ለመገንዘብ እየሞከርን ቆይተናል:: በተለይ ታኅሳስ 7 ቀን "ስብከት" በሚል ስለ እግዚአብሔር ሰው መሆን ትንቢት መነገሩን: ምሳሌ መመሰሉን: ሱባኤ መቆጠሩን ተመልክተን ነበር::

+ቀጥለን ደግሞ ታኅሳስ 14 ቀን "ብርሃን" በሚል አምላካችን እንደ ምን ባለ ጥበቡ ብርሃኑን እንደ ሰጠን: አንድም ወደን ወደ ጨለማ በገባን ጌዜ ሥጋችንን ተዋሕዶ ብርሃን እንደ ሆነልን ለማየት ሞክረናል::

+ታኅሳስ 21 ቀን ደግሞ በበደላችን ምክንያት የነፍሳችንን እረኛ አጥተን ነበር:: ለእኛው በደል እርሱ ክሶ ድጋሚ መልካም እረኛችን ሆኖ በሥጋ ማርያም መለገለጡን አየን:: የዛሬው በዓል ዕለተ ጌና ደግሞ ማሠሪያው ነው::

+"ጌና" ማለት በቁሙ "ዕለተ ልደት ስቡሕ: ማለትም አምላክ ሰው የሆነበት ምስጉን ቀን" እንደ ማለት ነው:: ይህ ቀን ሁሌም በየዓመቱ "አማኑኤል (ጌና)" እየተባለ ይከበራል:: ምክንያቱ ደግሞ ጌታ የተጸነሰ መጋቢት 29 ቀን በመሆኑና ከዚህ ቀን 9 ወር ከ5 ቀናት ብንጨምር ይህ ዕለት ታሕሳስ 29 ቀን ይመጣል::

+ነገር ግን በ4ኛው ዓመት ዘመነ ዮሐንስ ዻጉሜን 6 ስትሆን 9 ወር ከ6 ቀን ስለሚሆን ቀኑን እንዳይለቅ በዘመነ ዮሐንስ ዕለተ ልደቱ ለክርስቶስ ታሕሳስ 28 ቀን ይከበራል:: ያም ሆኖ በዘመነ ዮሐንስ ታኅሳስ 28ን አክብረናል ብለን 29ን አንተወውም:: እርሱም ይከበራል::

+በዚያው ልክ ደግሞ በ3ቱ አዝማናት (በማቴዎስ: በማርቆስና በሉቃስ) ልደቱ በ29 ነው ብለን 28ን አንሽረውም:: "ጌና-አማኑኤል-ዕለተ ማርያም" እያልን እናከብረዋለን እንጂ:: ብዙ ጊዜም በተለምዶ በዓለ ልደትን "ጌና" በማለት ፈንታ "ገና" የምንል ብዙዎች አለን::

+ግን አበው ባቆዩልን ትውፊት "ጌና" ልደቱን የሚመለከት ሲሆን "ገና" ግን ባሕላዊ ጨዋታውን የሚመለከት ቃል ነው::

+*" ዕለተ ማርያም "*+

=>ዳግመኛ ይህ ቀን ዕለተ ማርያም ይባላል:: "ማርያም" የሚለው ቃል ብዙ ትርጉምን ያዘለ የእናታችንና የእመቤታችን: የተስፋችንና መመኪያችን: የድንግል እመ ብርሃን ስም ነው::

+ክርስቶስ ተጸነሰ-ተወለደ ስንል ለዚህ ሁሉ ምሥጢር ማካተቻና የድኅነታችን መጀመሪያ: የመመኪያችን ዘውድና የንጽሕናችን መሠረት ድንግል ማርያም ናትና ከፈጣሪ ቀጥሎ ታላቅ ክብር: ምስጋና: ስግደትና ውዳሴ ለእርሷ ይገባታል:: መድኅናችን ክርስቶስ ያዳነን በእርሷ ምክንያት ነውና::

+ሠለስቱ ምዕት (318ቱ ቅዱሳን ሊቃውንት) ይህንን ምሥጢር ሲያደንቁ እንዲህ ብለዋል:-
*በሥጋ ማርያም ጌታ ተጸነሰ
*በሥጋ ማርያም ጌታ ተወለደ
*በሥጋ ማርያም ጌታ አደገ
*በሥጋ ማርያም ጌታ ተጠመቀ::

*በሥጋ ማርያም ጌታ አስተማረ
*በሥጋ ማርያም ጌታ ተሰቀለ
*በሥጋ ማርያም ጌታ ሞተ
*በሥጋ ማርያም ጌታ ተነሳ
*በሥጋ ማርያም ጌታ ዐረገ
*በሥጋ ማርያም ጌታ በአባቱ ቀኝ ተቀመጠ
*በሥጋ ማርያም ጌታ ዳግመኛ በሕያዋንና ሙታን ላይ ይፈርድ ዘንድ ከመለኮቱ ኃይል ጋር ይመጣል:: (መጽሐፈ ቅዳሴ)

+በዚያውም ላይ ለዘለዓለም ድኅነት የምንመገበው የጌታ ሥጋና ደም መለኮት የተዋሐደው የድንግል ማርያም ሥጋና ደም ነው::

<< ለድንግል ማርያም ክብርና ውዳሴ ከስግደት ጋር ይሁን !!! >>

=>የድንግል ማርያም ልጅ አማኑኤል ክርስቶስ በርሕራሔው ይማረን:: ከበረከተ ልደቱም ያሳትፈን::

=>ታሕሳስ 28 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.አማኑኤል አምላካችን
2.በዓለ ጌና ስቡሕ
3.ዕለተ ማርያም ድንግል
4."174" ሰማዕታት (የቅዱስ ዻውሎስ ማሕበር)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱሳን (አብርሃም: ይስሐቅና ያዕቆብ)
2.ቅዱስ እንድራኒቆስና ሚስቱ ቅድስት አትናስያ
3.ቅድስት ዓመተ ክክርስቶስ
4.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ
5.ቅዱስ አባዲርና ቅድስት ኢራኢ

=>+"+ የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ! ከእርስዋ የተጸነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ:: ልጅም ትወልዳለች:: እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ:: በነቢይ ከጌታ ዘንድ:-
'እነሆ ድንግል ትጸንሳለች:: ልጅም ትወልዳለች:: ስሙንም አማኑኤል ይሉታል::'
የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኗል:: ትርጉዋሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው:: +"+ (ማቴ. 1:20)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
እንኩዋን ለዓለም ሁሉ ጌታ "ኢየሱስ ክርስቶስ" ዓመታዊ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

"+" ልደተ ክርስቶስ "+"

=>ዓለማትን: ዘመናትን: ፍጥረታትን ሁሉ የፈጠረ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ: ወልደ አምላክ ነው:: የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጁ ሲሆን ራሱም እግዚአብሔር ነው:: በባሕርየ ሥላሴ መበላለጥ የለምና ወልድ ክርስቶስ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ትክክል ነው እንጂ አይበልጥምም: አያንስምም::

+እርሱ ቅድመ ዓለም የነበረ: ማዕከለ ዓለም ያለና ዓለምን አሳልፎ የሚኖር ጌታ ነው:: ቀዳማዊና ደኃራዊው: አልፋና ኦሜጋ እርሱ ነው:: (ዮሐ. 1:1, ራዕ. 1) ሁሉ በእጁ የተያዘ ነው::

+እርሱ እውነተኛ አምላክ (ሮሜ. 9:5): የዘለዓለም አባት: የሰላምም አለቃ ነው:: (ኢሳ. 9:6) ቅድመ ዓለም ሲሠለስ: ሲቀደስ ኑሮ ይህንን ዓለም ፈጠረ:: እርሱ ሁሉን ያስገኛል እንጂ ለእርሱ አስገኝ የለውም::
< አንድ ክርስቲያን ከሁሉ አስቀድሞ ሊያውቀው የሚገባ መሠረተ እምነት ይሔው ነው !! >

+መድኃኒታችን ክርስቶስን በዚህ መንገድ የማያምንና የማያመልክ ሁሉ እርሱ ክርስቲያን አይደለም:: ምንም ሥጋችንን ተዋሕዶ ብዙ የትሕትና ሥራዎችን ቢሠራም: ቢሰቀል: ቢሞትም እርሱ እግዚአብሔር ነውና ፍጹም አምላክ ፍጹምም ሰው ብለን ልናመልከው ይገባል::

+እንደ አርዮስ: ንስጥሮስና ልዮን የማይገቡ ነገሮችን መናገር ጐዳናው የሞት: መዳረሻውም ገሃነመ እሳት ነው:: እንኩዋን የክብር ባለቤት መድኅን ክርስቶስ ላይ በፍጡር ላይ እንኩዋ የማይገባ ነገርን የተናገረ ሁሉ የገሃነም ፍርድ አለበት::

<< ለእርሱ የዓለም ፈጣሪ: ጌታና ቤዛ ለሆነው መድኅን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዘለዓለም ምስጋና: ጌትነት: ውዳሴና አምልኮ ይሁን !! >>

+እግዚአብሔር አዳምን በ7 ሃብታት አክብሮ በገነት ቢያኖረው "አትብላ" የተባለውን ዕፀ በለስ በላ:: በዚህም ከፈጣሪው ተጣልቶ: በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ: በርደተ መቃብር ርደተ ገሃነም ተፈረደበት:: በሁዋላ ግን ንስሃ ስለ ገባ "ከ5 ቀን ተኩል (5,500 ዘመን) በሁዋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ" የሚል ቃል ኪዳንን ሰጠው::

+ከዚህ በሁዋላ ለ5,500 ዘመናት ጊዜ ወደ ታች ይቆጠር ጀመር:: ስለ እግዚአብሔር ሰው መሆንና ዓለምን ማዳንም ትንቢት ይነገር: ሱባኤ ይቆጠር: ምሳሌም ይመሰል ገባ::

+ከአዳም እስከ ሙሴ (ዘመነ አበው) ምሳሌያት ይበዛሉ:: ከሙሴ እስከ ዳዊት (ዘመነ መሣፍንት) ምሳሌያቱ እየጐሉ መጥተዋል:: ከልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት እስከ ቅዱስ ሚልክያስ ድረስ (በዘመነ ነቢያት / ነገሥት) ግን ትንቢቶች ስለ ክርስቶስና ስለ ማደሪያ እናቱ እንደ ጐርፍ ፈሰዋል::

+ነቢያትም የመሲህን መምጣት እየጠበቁ በጾም: በጸሎትና በትሕርምት ኑረዋል:: እንባቸውንም አፍሰው ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶላቸዋል::

*"+" ልደተ ክርስቶስ እምድንግል "+"*

=>"ጊዜው ሲደርስ አንባ ይፈርስ" እንዲሉ አበው መደኃኒታችን የጥልን ግድግዳ ያፈርስ ዘንድ: ከኃጢአትና ከሞት ቁራኝነት ይፈታን ዘንድ: ለሰዎች ቤዛ ይሆን ዘንድ: ትንቢተ ነቢያትን ይፈጽም ዘንድ: በቀጠሮ (በ5 ቀን ተኩል) ወደዚህ ዓለም መጣ::

+የሰማይና የምድር ጌታ በእንግድነት በመጣ ጊዜም እርሱን ለመቀበል በተገባ የተገኘች ንጽሕት ሙሽራ ድንግል ማርያም ሆነች:: ከእርሷ በቀር ለዚህ ክብር ሊበቃ የሚቻለው ፍጥረት: እንኩዋን ኃጢአት ካደከመው የሰው ልጅ ከንጹሐን መላእክት ወገን አልተገኘም::

+በጊዜውም መልአከ ትፍሥሕት ቅዱስ ገብርኤል መጋቢት 29 ቀን ወደ ድንግል ወርዶ የአምላክን ሰው የመሆን ዜና ከውዳሴና ከክብር ጋር ነገራት:: (ሉቃ. 1:26) ድንግልም ለ9 ወራት ከ5 ቀናት ሰማይና ምድር የማይችሉትን መለኮትን ተሸከመች::

+ልክ ሙሴ በደብረ ሲና እንዳያት ዕጽ ድንግል ማርያምንም ባሕርየ መለኮቱ አላቃጠላትም:: ስለዚህም ነገር "ወላዲተ አምላክ: ታኦዶኮስ: ንጽሕተ ንጹሐን: ቅድስተ ቅዱሳን: ንግሥተ አርያም: የባሕርያችን መመኪያ . . ." እያልን እንጠራታለን::

+ግሩም ድንቅ ጌታን ጸንሳ ዘጠኝ ወራት እስኪፈጸሙ ድረስ ብዙ ተአምራትን ሠራች:: መላእክተ ብርሃን እየታጠቁ አገለገሏት: አመሰገኗት:: ልጇን አምላክ: እርሷን እመ አምላክ እያሉ ተገዙላት::

+ከዚያም በሮሙ ቄሣር በአውግስጦስ ዘመን ሰው ሁሉ ይቆጠር ዘንድ አዋጅ ወጥቷልና እመ ብርሃን ማርያም ከቅዱሳኑ ዘመዶቿ ዮሴፍና ሰሎሜ ጋር ወደ አባቷ ዳዊት ከተማ ወደ ቤተ ልሔም ሔደች::

+በዚያም ሳሉ የምትወልድበት ጊዜ ቢደርስ በፍጹም ድንግልና እንደ ጸነሰችው ሁሉ በፍጹም ድንግልና ወለደችው:: (ኢሳ. 7:14, ሕዝ. 44:1) ተፈትሖም አላገኛትም:: ልማደ አንስትም አልጐበኛትም:: ምጥም አልነበረባትም::

+ድንግል ማርያም ክርስቶስን በወለደች ጊዜ ልጇ አምላክ: እርሷም የአምላክ እናት መሆኗ ይታወቅ ዘንድ:-

1.የብርሃን ጐርፍ ፈሰሰ:
2.99ኙ ነገደ መላእክት ወርደው "ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም" እያሉ ዘመሩ:
3.ትጉሐን እረኞች በቅዱስ ገብርኤል መሪነት መጥተው ክብሩን ተካፈሉ:
4.በሰማይም ልዩ ኮከብ ድንግልና ልጇ ተስለውበት ዝቅ ብሎ ታየ:
5.ቅድስት ሰሎሜም በድፍረት የድንግልን ሆድ ዳስሳ እጇ ቢቃጠል እንደ ገና በተአምራት ድኖላታል::

+በጊዜውም በምሥራቅ የፋርስ: የባቢሎንና የሳባ ነገሥት አስቀድሞ ከበለዓም: በሁዋላም ከዠረደሸት በተረዱት መሠረት ኮከቡን በማየታቸው ታጥቀው ተነሱ::

+ከምሥራቅ አፍሪቃና ከእስያም በተመሳሳይ ኮከቡን በማየታቸው 12 ነገሥታት በየግላቸው 10 10 ሺህ ሠራዊትን እየያዙ ድንግልንና ንጉሥ ልጇን ፍለጋ ወጡ::

+12ቱ ነገሥታት ከነ ሠራዊታቸው ሲሔዱ ስንቃቸው በማለቁ 9 ነገሥታት ተስፋ ቆርጠው ተመለሱ:: 3ቱ ግን በፍጹም ጥብዓት ከ30ሺ ሠራዊት ጋር በኮከብ እየተመሩ ኢየሩሳሌም ደረሱ::

+እነዚህም መሊኩ የኢትዮዽያ (የሳባ ንጉሥ ተወራጅ): በዲዳስፋና መኑሲያ (ማንቱሲማር) ደግሞ የፋርስና የባቢሎን ነገሥታት ናቸው:: ወደ ኢየሩሳሌም ሲደርሱም ሔሮድስና ሠራዊቱ ታወኩ::

+እነርሱ ግን የቤተ ልሔምን ዜና ከጠየቁ በሁዋላ በጐል ድንግል ማርያምን: ክርስቶስን: ዮሴፍና ሰሎሜን አገኙ:: ለ2 ዓመታት እነርሱን ፍለጋ ደክመዋል: ተንከራተዋልና ደስታቸው ወሰን አጣ::

+በእመቤታችንና በልጇ ፊት በደስታ ዘለሉ:: "አንፈርዓጹ ሰብአ ሰገል" እንዲል:: ወርቁን: እጣኑንና ከርቤውንም ገብረው: በግንባራቸው በፊቱ ሰገዱ:: 3 ጊዜም እየወጡ እየገቡ ቢመለከቱት በኪነ ጥበቡ አንዴ እንደ ሕጻን: በ2ኛው እንደ ወጣት: በ3ኛው እንደ አረጋዊ ሆኖ ታይቷቸው ፈጽመው አድንቀዋል::

+ወደ ሃገራቸው ሲመለሱም "ወአስነቀቶሙ ሕብስተ ሰገም" እንዲል የገብስ ዳቦ ጋግራ ድንግል ለሰብአ ሰገል ሰጠቻቸው:: እነርሱም ይህንን እየተመገቡ የ2 ዓመቱን መንገድ በ40 ቀን ሲጨርሱት ዳቦው ግን ያ ሁሉ ሺህ ሰው ተመግቦት አላለቀም:: ተአምራትንም ሠርቷል::

<< የልደቱ ነገር እንዲሁ ተተርኮ የሚያልቅ አይደለምና ይቆየን:: የከርሞ ሰውም ይበለን:: >>

+*" ቅዱስ ላል-ይበላ ንጉሥ "*+

=>በ12ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ ላይ በሃገራችን የነገሠው ቅዱስ ላሊበላ:-
+በብሥራተ መልአክ ተወልዷል:
+ቅዱሳት መጻሕፍትን ገና በልጅነቱ አጥንቷል:
+የንጉሥ ዘር ቢሆንም በጾምና ጸሎት: በትሕርምት አድጉዋል::

+በወንድሙ ቢገረፍም ቂም አልነበረውም:
+ስለ ወዳጆቹ ፍቅር መርዝ ጠጥቷል:
+በዙፋን ላይ የኢትዮዽያ ንጉሥ ሆኖ ቢቀመጥም እርሱስ አ
ኗኗሩ ገዳማዊ ነበር:
+ከተባረከች ሚስቱ ቅድስት መስቀል ክብራ ጋር አንዲት ማዕድ ብቻ በቀን ይቀምሱ ነበር:: ለዛውም ለምለሙን ለነዳያን ሰጥተው እነርሱ የሚበሉት የእንጀራውን ቅርፍት (ጠርዝ) ብቻ ነበር::

+በአካለ ሥጋ ወደ ሰማያት ተነጥቆ ብዙ ምሥጢራትን አይቷል:
+በምሳሌውም ሃገረ ሮሃን (ላስታን) ገንብቷል:
+ዛሬም ድረስ ምስጢር የሆኑት ፍልፍል አብያተ መቃድስ የእጆቹ ሥራዎች ናቸው::

+ሥራውን ከፈጸመ በሁዋላ መንግሥቱን ለቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አውርሶ: በመንኖ ጥሪትና በቅድስና ኑሮ አርፏል:: ጌታችን ስምህን ያከበረ: ዝክርህን የዘከረ: ከቤትህ ያደረውን: ከርስተ መንግስተ ሰማያት አካፍለዋለሁ ሲል ቃል ኪዳን ገብቶለታል:: ይህቺ ዕለት ቅዱሱ ንጉሥ የተወለደባት ናት::

=>እኛን ስለ ወደደ ሰው የሆነ ጌታ ፍቅሩን ይሳልብን:: ከድንግል እናቱና ከልደቱ በረከትም ያሣትፈን::

=>ታሕሳስ 29 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ልደተ ክርስቶስ ስቡሕ
2.ታኦዶኮስ (ድንግል ማርያም)
3.ቅዱስ ኢያሱ ነቢይ (ልደቱ)
4.ቅዱስ ላሊበላ (ልደቱ)
5.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ (ልደታቸው)
6.ጻድቅ አቃርዮስ (ንጉሠ ሮሃ)
7.ቅዱስ ቆሪል ገመላዊ
8.ሰብአ ሰገል
9.ዮሴፍና ሰሎሜ
10.ቅዱሳን ሰማዕታተ አክሚም

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዼጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት
2.ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ
3.ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ኢትዮዽያዊት
4.ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ
5.ቅድስት አርሴማ ድንግል

=>"+"+" እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራቹሃለሁና አትፍሩ:: ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት: እርሱም ክርስቶስ: ጌታ የሆነ ተወልዶላቹሃልና:: "+"+" (ሉቃ. 2:10)


<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
2024/10/01 11:30:04
Back to Top
HTML Embed Code: