Telegram Web Link
እንኩዋን ለቅዱሳን ጻድቃን ወገዳማውያን "አባ ዮሐንስ" : "አባ ዘካርያስ ወአባ ዮሐንስ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

+*" አባ ዮሐንስ ዘአስቄጥስ "*+

=>ገዳማዊ ሕይወት ጥንቱ ብሉይ ኪዳን ነው:: በቀዳሚነትም በደብር ቅዱስ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ደቂቀ ሴት እንደ ጀመሩት ይታመናል:: ሕይወቱ በጐላ: በተረዳ መንገድ የታየው ግን በታላቁ ጻድቅ ሄኖክ: ከዚያም በቅዱሱ ካህን መልከ ጼዴቅ አማካኝነት ነው::

+ቀጥሎም እነ ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ: እነ ኤልሳዕ ደቀ መዝሙሩ ኑረውበታል:: በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ሙሉ ሕይወቱን በገዳም (በበርሃ) ያሳለፈው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቅድሚያውን ይይዛል::

+ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ በገዳመ ቆረንቶስ ለ40 ቀናት በትሕርምት ኑሮ ገዳማዊ ሕይወትን ቀድሷል: አስተምሯል:: በዘመነ ስብከቱም ያድርባት የነበረችው የደብረ ዘይቷ በዓቱ (ኤሌዎን ዋሻ) በራሷ ለዚህ ሕይወት ትልቅ ማሳያ ናት::

+ከጌታ ዕርገት በሁዋላም ክርስቲያኖቹ የዓለም ሁካታ ሲሰለቻቸው: አንድም በንጹሕና በተሸከፈ ልቡና ለፈጣሪያቸው መገዛትን ሲሹ ከከተማ ወጣ እያሉ ይኖሩ እንደ ነበር የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ:: አኗኗራቸውም በቡድንም: በነጠላም ሊሆን ይችላል::

+ዋናው ነገር ግን በጾምና በጸሎት መትጋታቸው ነው:: ይሕም ሲያያዝ እስከ 3ኛው መቶ ክ/ዘመን ደረሰ:: በዚህ ዘመን ግን አባ ዻውሊ የሚባል አንድ ንጹሕ ክርስቲያን ይሕንን ሕይወት ወደ ሌላ ደረጃ ከፍ አደረገው:: ለ80 ዓመታት ሰው ሳያይ ተጋድሎ "የባሕታውያን አባት" ተባለ:: ደንብ ያለው ተባሕትዎም ጀመረ::

+ይህ ከሆነ ከ20 ዓመታት በሁዋላ ደግሞ አባ እንጦንስ የሚባሉ ደግ ክርስቲያን ይህንን ገዳማዊ ሕይወት በሌላ መንገድ አጣፈጡት:: በቅዱስ ሚካኤል አመንኩዋሽነት ገዳማዊ ሕይወት በምንኩስና ተቃኘ:: ስለዚህም አባ እንጦንስ የመነኮሳት አባት ተባሉ::

+እርሳቸውም ሕይወቱን ለማስፋፋት ከተለያዩ አሕጉር ደቀ መዛሙርትን እየተቀበሉ አመንኩሰዋል:: ቅዱሳን የአባ እንጦንስ ልጆችም ወደየ ሃገራቸው ተመልሰው: ሕይወቱን በተግባር አሳይተው ገዳማዊነትን አስፋፍተዋል::

+አባ እንጦንስ አባ መቃርስን: አባ መቃርስ አባ ዮሐንስን ወልደዋል:: አባ ዮሐንስም የታላቁ ገዳመ አስቄጥስ አበ ምኔት ሆነው በጸጋ አገልግለዋል:: አስቄጥስ በምድረ ግብጽ የሚገኝ: በስፋቱና ብዙ ቅዱሳንን በማፍራቱ ተወዳዳሪ የሌለው የዓለማችን ቁጥር አንድ ገዳም ነው::

+ሕይወተ ምንኩሰናም ወደ መላው ዓለም የተስፋፋ በዚህ ገዳም መናንያን አማካኝነት ነው:: በዚህ ገዳም ላይ የሚሾሙ አበው ደግሞ በብዛት መንፈስ ቅዱስ ያደረባቸውና አባታቸውን ቅዱስ መቃርስ ታላቁን የመሰሉ ናቸውና ኃላፊነቱ እጅግ ከባድ ነው::

+በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን በምድረ ግብጽ ተወልደው ያደጉት አባ ዮሐንስ ከመነኑባት ዕለት ጀምረው በፍጹም ተጸምዶና ተጋድሎ ለፈጣሪያቸው ስለ ተገዙ የታላቁ ገዳም አበ ምኔት ሊሆኑ ተገባቸው::

+በአበ ምኔትነት ዘመናቸውም መንጋውን ይጠብቁ ዘንድ ብዙ ደከሙ:: በተለይ ቅዱስ ቃሉን ያስተምሩ ዘንድ ተጉ:: ሕይወተ መላእክትንም ያሳዩ ዘንድ በቃል ብቻ ያይደለ በተግባር ሆነው ከመንፈሳዊ አብራካቸው ብዙ ቅዱሳንን ወለዱ::

+ከዋክብቱ አባ ገዐርጊ: አባ አብርሃም: አባ ሚናስ: አባ ዘካርያስ . . . የአባ ዮሐንስ ፍሬዎች ናቸውና:: ጻድቁ በዘመናቸው ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል:: ከዕረፍታቸው በሁዋላ እንኩዋ መግነዛቸውና የልብሳቸው እራፊ ብዙ ድውያንን ፈውሷል::

+አንድ ጊዜም ለልጆቻቸው መነኮሳት ቤዛ ሆነው በበርበር (አረማውያን) ተማርከዋል:: በዚያም ክፉዎች ባሪያ ቢያደርጉዋቸው እግዚአብሔር ድንቅን ሠርቶ ወደ ገዳማቸው መልሷቸዋል:: ከብዙ ተጋድሎ በሁዋላም በ90 ዓመታቸው በዚህች ቀን ዐርፈው በበዓታቸው ተቀብረዋል::

+"+ አባ ዘካርያስ ገዳማዊ +"+

=>ይሕም ቅዱስ የተነሳው በዚያው በዘመነ ጻድቃን ነው:: ምንም ክርስቲያን ቢሆንም በቀደመ ሕይወቱ ገንዘብ የሚጥመው ነጋዴ ነበር:: በንግድ ሥራውም ሃብታም መሆን ችሎ እንደ ነበር ዜና ሕይወቱ ይናገራል::

+እግዚአብሔር ሁሉም የሰው ልጆች ወደ መንግስተ ሰማያት ቢገቡ መልካም ፈቃዱ ነው:: ያ ብቻ አይደለም:: ለእያንዳንዱ ሰው የድኅነት ጥሪን በተለያየ መንገድ ያቀርብለታል:: ድምጹን ለሰማ ወደ ወንጌል ወደብ ያደርሰዋል::

+አንዳንዴ "እንቢ" ስንለው እንደ በጐ አባትነቱ በተግሣጹ ሊጠራንም ይችላል:: ተግሣጹም በደዌ: በአደጋና በመሰል መንገዶች ሊሆን ይችላል:: ዋናው ቁም ነገር ግን ጊዜው ሳያልፍብን: ቀኑም ሳይመሽብን ድምጹን መስማት: ለቃሉ መታዘዝ: ጥሪውንና ተግሣጹን አለማቃለል ነው::

+አባ ዘካርያስም የቅድስና ሕይወት ጥሪ የደረሰው ለሥጋ ገበያ ሲታትር ነበር:: አንድ ቀን ንብረቱን ይዞ ለንግድ መንገድ ላይ ሳለ ሽፍቶች ያዙት:: ሊያርዱት አጋድመውት ሳለ ግን የገዳመ ዻኩሚስ አበ ምኔት በሥፍራው ነበርና ጮኸባቸው::

+ቅዱሱ አበ ምኔት አካሉ በገድል ያለቀ ቢሆንም ድምጹ እንደ ነጐድጉዋድ ሲመጣ ገዳዮቹ ደንግጠው በረገጉ:: ዘካርያስም ከሞት ተረፈ:: እንደ ገና ሃብቱን ይዞ ወደ ከተማ ሲገባ በሃገረ ገዢው ተይዞ ሞት ተፈረደበት:: ከገንዘቡ መብዛት የተነሳ ዘራፊ መስሏቸው ነበርና:: በዚህ ጊዜም እግዚአብሔር በመኮንኑ ልብ ርሕራሔን ጨምሮ አዳነው::

+በዚያች ሌሊት ግን ነገሮችን ያስተዋለው ዘካርያስ የተፈጠሩት አጋጣሚወች የፈጣሪው ጥሪ እንደ ሆኑ አስተዋለ:: ወዲያውም ለዓይነ ሥጋ የሚያሳሳውን ያን ሁሉ ንብረቱን መጽውቶ በርሃ ገባ:: በደብረ አባ ዻኩሚስም መንኩሶ በዓት ወሰነ::

+ከዚያች ቀን ጀምሮም በፍጹም አምልኮ: በጾምና በጸሎት እግዚአብሔርን እያገለገለ ከርኩሳን መናፍስት ጋር ታገለ:: በእግሩም ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዞ ቅዱሳት መካናትን ተሳለመ:: አንድ ጊዜም ሰይጣን ሰው መስሎ "አባትህ ሳልሞት ልየው እያለህ ነው" አለው:: ውስጡ ግን ፈቃደ ሥላሴ ነበረበትና "እሺ" ብሎ ሒዶ: አባቱን ቀብሮ ተመልሷል::

+ቅዱስ አባ ዘካርያስ ከብቃቱ የተነሳ የሚኖረው ከግሩማን አራዊት ጋር ነበር:: ሁሉንም አራዊትም ይመግባቸው ነበር:: በተለይ ደግሞ ዘንዶዎች ሰውን እንዳይጐዱ አዝዞ እርሱ ይመግባቸው ነበር:: የተጋድሎ ዘመኖቹን ከፈጸመ በሁዋላም በዚህች ቀን በክብር ዐርፏል::

+"+ አባ ዮሐንስ ብጹዕ +"+

=>ይህም ቅዱስ በተመሳሳይ የዘመነ ጻድቃን ቅዱሳን ፍሬ ነው:: "ኢትርአይ ገጻ : ወኢትስማዕ ድምጻ" በሚለው ሕገ ተባሕትዎ ለ40 ዓመታት ተወስኖ ኑሯል::

+ይህም ማለት አንድ ወንድ ከመነነ በሁዋላ ሴቶችን እንዲያይና ከእነርሱም ጋር እንዲያወራ አይፈቀድለትም:: ሴትም ብትመንን ሕጉ ያው ነው:: (ዛሬ እየተደረገ ያለውን ግን ፈጣሪ ይመርምረው)

+አባ ዮሐንስ ብጹዕም እንዲህ ባለ ፈሊጥ: ማለትም በጾምና በጸሎት: ከዓለም ተለይቶ: ከሴት ርቆ: ንጽሕ ጠብቆ ሲኖር አረጀ:: በጊዜው በከተማ የሚኖር አንድ መስፍን ወዳጅ ነበረው:: ይህ መስፍን ዘወትር ወደ ጻድቁ እየመጣ ይባረካል::
+ሚስቱ ግን በረከቱን ሽታ ልታየው ብትሞክርም አልተሳካም:: ሕገ ምናኔ አይፈቅድምና:: በዚህ ነገር ፈጽማ ማዘኗን በጸጋ ያወቀው አባ ዮሐንስ ግን በራዕይ ወደ እርሷ መጣ::+"ሚ ሊተ ወለኪ ብእሲቶ - አንቺ ሆይ! ለምን ካላየሁህ እያልሽ ትዘበዝቢኛለሽ? እኔ ነቢይ ወይ ጻድቅ አይደለሁ" ብሏት ባርኯ ተሠወራት:: እርሷም ደስ ብሏት ለባሏ ነገረችው:: ባሏ ወደ ጻድቁ ሲሔድም ገና ሳይነጋገሩአባ ዮሐንስ ሳቅ ብሎ "ሚስትህ ደስ አላት አይደል?" ብሎታል:: ጻድቁ በ90 ዓመቱ በዚህች ቀን ዐርፎ ተቀብሯል::

=>አምላከ ጻድቃን ቅዱሳን ስለ ወዳጆቹ በጐ ምኞታችንን ይፈጽምልን:: ከበረከታቸውም ያድለን::

=>ታሕሳስ 30 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.አባ ዮሐንስ አበ ምኔት
2.አባ ዘካርያስ ገዳማዊ
3.አባ ዮሐንስ ብጹዕ
4."144 ሺ" ሕጻናት (ሔሮድስ የገደላቸው)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ማርቆስ ሐዋርያ
2.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
3.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
4.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
5.አባ ሣሉሲ ክቡር ጻድቅ

=>+"+ ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን ኑራችሁ: ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ:: እንደሚታዘዙ ልጆች ባለ ማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ:: ዳሩ ግን 'እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ' ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሯችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ:: +"+ (1ዼጥ. 1:13)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
" #ጥር 1 "

<<< እንኩዋን ለቅዱስ "እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት" እና "ለአክሚም ሰማዕታት" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ >>>

+*" ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት ወቀዳሜ ሰማዕት "*+

=>በሕገ ወንጌል (ክርስትና) የመጀመሪያው ሊቀ ዲያቆናትና ቀዳሚው ሰማዕት ይህ ቅዱስ ነው:: ቅዱሱ በመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን አስገራሚ ማንነት ከነበራቸው እሥራኤላውያን አንዱ ነበር:: ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

+የቅዱስ እስጢፋኖስ ወላጆቹ ስምዖንና ማርያም ይባላሉ:: (ሌሎች ናቸው የሚሉም አሉ) ገና ከልጅነቱ ቁም ነገር ወዳድ የነበረው ቅዱስ በሥርዓተ ኦሪት አድጐ እድሜው ሲደርስ ወደ ት/ቤት ገባ:: የወቅቱ ታላቅ መምሕር ገማልያል ይባል ነበር:: ይህ ሰው በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 5:33 ላይ ተጠቅሷል::

+በትውፊት ትምሕርት ደግሞ ይህ ደግ (ትልቅ) ሰው በርካታ ቅዱሳንን (እስጢፋኖስን : ዻውሎስን : ናትናኤልን : ኒቆዲሞስን . . .) አስተምሯል:: በጌታችን መዋዕለ ስብከት ጊዜም ከፈጣሪያችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ እየቀረበ ይጨዋወት ነበር:: በፍጻሜውም አምኗል::

+ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ቅዱስ እስጢፋኖስ ከዚህ ምሑር ዘንድ ተምሮ: ኦሪቱን ነቢያቱን ጠንቅቆ ወጣ:: ወቅቱ አስቸጋሪና ለኃጢአት ሕይወት የተመቸ ቢሆንም ቅዱሱ ግን የመሲህን መምጣት በጸሎትና በተስፋ ይጠባበቅ ነበር::

+በወቅቱ ደግሞ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ የንስሃ ጥምቀትን እየሰበከ መምጣቱን የተመለከተ ቅዱስ እስጢፋኖስ ነገሩን መረመረ:: ከእግዚአብሔር ሆኖ ቢያገኘው የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ሆነ:: ለ6 ወራትም በትጋት ቅዱስ ዮሐንስን አገለገለ::

+ለ6 ወራት ከቅዱስ ዮሐንስ ዘንድ ከተማረ በሁዋላ ለስም አጠራሩ ስግደት ይድረሰውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠመቀ:: በወቅቱ
የተደረገውን ታላቅ ተአምር ልብ ያለው ቅዱስ እስጢፋኖስ
መምሕሩን ቅዱስ ዮሐንስን እንዲያስረዳው ጠየቀው::
"ከእኔ ይልቅ
ከፈጣሪው አንደበት ይስማው" በሚል ላከው:: ቅዱሱም
ከጌታ ዘንድ ሔዶ: እጅ ነስቶ ተማረ:: (ሉቃ. 7:18)
በዚያውም
የጌታ ደቀ መዝሙር ሆኖ ቀረ:: ጌታም ከ72ቱ አርድእት
አንዱ አድርጐት ለአገልግሎት ላከው:: አጋንንትም
ተገዙለት::
(ሉቃ. 10:17)

ቅዱስ እስጢፋኖስ ጌታችን መድኃኔ
ዓለም ከዋለበት እየዋለ: ካደረበት እያደረ ወንጌልን
ተማረ::
ምሥጢር አስተረጐመ:: ጌታ በፈቃዱ ስለ እኛ ሙቶ
ከተነሳ በኋላ ሲያርግ ደቀ መዛሙርቱን በአንብሮ እድ
ባርኳል:: በዚህ
ጊዜም ቅዱሱ እንደ ወንድሞቹ ሐዋርያት ቅስናን
(ዽዽስናን) ተሹሟል:: በበዓለ ሃምሳም መንፈስ ቅዱስ
በወረደ ጊዜ ከ72ቱ
አርድእት የእርሱን ያህል ልሳን የበዛለት:ምሥጢርም
የተገለጠለት የለም:: በፍጹም ድፍረትም ወንጌልን
ይሰብክ ገባ::

በመጀመሪያይቱ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ከማዕድ ሥርዓት
ጋር በተያያዘ ፈተና ሲመጣ በመንፈስ ቅዱስ ምርጫ 7
ዲያቆናት
ሲመረጡ አንዱ እርሱ ነበር:: አልፎም የ6ቱ ዲያቆናት
አለቃ እና የ8ሺው ማሕበር መሪ (አስተዳዳሪ) ሆኗል::
8ሺ ሰውን
ከአጋንንት ፈተና መጠበቅ ምን ያህል ከባድ እንደ ሆነ
ለማወቅ አባቶቻችንን መጠየቅ ነው::

አንድን ሰው
ተቆጣጥሮ
ለድኅነት ማብቃት እንኳ እጅግ ፈተና ነው:: መጽሐፍ
እንደሚል ግን 'መንፈስ ቅዱስ የሞላበት: ማሕደረ
እግዚአብሔር'
ነውና ለእርሱ ተቻለው:: (ሐዋ. 6:5) አንዳንዶቻችን ቅዱስ
እስጢፋኖስ 'ሊቀ ዲያቆናት' ሲባል እንደ ዘመኑ ይመስለን
ይሆናል:: እርሱ በመጀመሪያ ሐዋርያና ካህን ነው::
ዲቁናው ለእርሱ 'በራት ላይ ዳረጐት' ነው እንጂ እንዲሁ
ዲያቆን
ብቻ አይደለም::

ቅዱስ እስጢፋኖስ ከጌታ ዕርገት በኋላ
ለ 1 ዓመት ያህል 8ሺውን ማኅበር እየመራ: ወንጌልን
እየሰበከ
ቢጋደል ኦሪት 'እጠፋ እጠፋ': ወንጌል ደግሞ 'እሰፋ እሰፋ'
አለች:: በዚህ ጊዜ 'ክርስትናን ለማጥፋት መፍትሔው
ቅዱስ
እስጢፋኖስን መግደል
ነው' ብለው አይሁድ በማመናቸው ሊገልድሉት አስበውም
አልቀሩ ገደሉት::

+እርሱ ግን ፊቱ እንደ እግዚአብሔር መልአክ እያበራ
ፈጣሪውን በብዙ ነገር መሰለው:: በመጨረሻውም ስለ
እነሱ ምሕረትን
እየለመነ በድንጋይ ወገሩት:: ደቀ መዛሙርቱም ታላቅ
ለቅሶን እያለቀሱ ቀበሩት::

*"ፍልሠት"*

+ቅዱስ እስጢፋኖስ ካረፈ ከ300 ዓመታት በኋላ
በኢየሩሳሌም የሚኖር አንድ ደግ ሰው ነበር:: ስሙም
ሉክያኖስ ይባል
ነበር:: በተደጋጋሚ በራዕይ ቅዱሱ እየተገለጠ "ሥጋየን
አውጣ" ይለው ነበርና ሒዶ ለዻዻሱ ነገረው:: ዻዻሱም
ደስ ብሎት
ካህናትና ምዕመናንን ሰብስቦ ወደ አጸደ ገማልያል
(የመምሕሩ ርስት ነው) ሔደ::

+ቦታውንም በቆፈሩ ጊዜ ታላቅ መነዋወጥ ሆነ::
መላእክት ሲያጥኑ በጐ መዓዛ ሸተተ:: ዝማሬ መላእክትም
ተሰማ:: ሕዝቡና
ዻዻሱም በቅዱስ እስጢፋኖስ ፊት ሰግደው: በታላቅ
ዝማሬና በሐሴት ዐጽሙን ከዚያ አውጥተው: በጽርሐ
ጽዮን (በተቀደሰችው
ቤት) አኖሩት::

እለ እስክንድሮስ የተባለ ደግ ሰውም ቤተ
ክርስቲያን አንጾለት ወደዚያ አገቡት:: ከ5 ዓመታት
በኋላም
እለ እስክንድሮስ ሲያርፍ በሳጥን አድርገው በቅዱሱ ጐን
ስለ ፍቅሩ አኖሩት::ሚስቱ ወደ ሃገሯ ቁስጥንጥንያ
ስትመለስ
የባሏን ሥጋ መስሏት የቅዱስ እስጢፋኖስን ቅዱስ ሥጋ
በመርከብ ጭና ወሰደችው:: መንገድ ላይ ከሳጥኑ ውስጥ
ዝማሬ ሰምታ
ብታየው ያመጣችው የቅዱሱን ሥጋ ነው:: እጅግ ደስ
አላት: አምላክ ለዚህ አድሏታልና::

እርሷም ወስዳ ለታላቁ
ንጉሥ
ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ አስረከበች:: በከተማውም ታላቅ
ሐሴት ተደረገ::ሥጋውን ሊያኖሩት በበቅሎ ጭነው
ሲወስዱትም በቅሎዋ
በሰው ልሳን ተናግራ ማረፊያውን አሳወቀች:: በዚያም ላይ
ትልቅ ቤተ ክርስቲያን ታንጾለታል:: ቅዱስ እስጢፋኖስ
ሲመቱ
ጥቅምት 17: ዕረፍቱ ጥር 1:ፍልሠቱ ደግሞ መስከረም
15 ቀን ነው::

'' ሰማዕታተ አክሚም ''

+በቤተ ክርስቲያን የሐዲስ ኪዳን ታሪክ አሰቃቂ ጭፍጨፋ
ከተካሔደባቸው አካባቢዎች አንዷ ሃገረ አክሚም ናት::
አክሚም
ማለት የቀድሞ የግብጽ አውራጃ ናት:: በተለይ በ3ኛው
መቶ ክ/ዘመን በርካታ ክርስቲያኖች በፍቅር ይኖሩባት
ነበር::

በከተማዋ ውስጥ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ጥቡዓን:
ታማኞች:ሥጋውን ደሙን የሚቀበሉና ዘወትር ቅዱስ ቃሉን
ለመስማት
የሚተጉ ነበሩ:: ለዚህም ደግሞ ከሊቀ ዻዻሱ አባ
ብኑድያስ ጀምሮ ካህናቱ: ዲያቆናቱ: ንፍቅ ዲያቆናቱ:
መጋቢዎቹ:
አናጉንስጢሶቹ (አንባቢዎቹ): መምሕራኑ: መሣፍንቱም
ሳይቀር ለክርስቶስ ፍቅር የተጉ መሆናቸው አስተዋጽኦ
ነበረው::
በተለይ ግን 2 ወንድማማቾች የነበራቸው ቅድስና
ብዙዎችን ስቧል:: እኒህ ቅዱሳን ዲዮስቆሮስና ሰከላብዮስ
ይባላሉ::

ከባለ ጸጋና ባለ ስልጣን ቤተሰብ ቢወለዱም ክርስትናቸው
አልቀዘቀዘም:: የወጣትነት ስሜት ሳያሸንፋቸውም ወደ
በርሃ ተጓዙ::

+በዚያም በቅድስና ኑረው ለክህነት ማዕረግ በቅተዋል::
ቅዱሳኑ በገዳም ሳሉም መድኃኒታችን ክርስቶስ ተገልጦ
"ወደ ትውልድ ሃገራችሁ አክሚም ተመለሱ:: ክብረ ሰማዕታት
ይጠብቃቹሃል" አላቸው:: እነርሱም ደስ እያላቸው
በፍጥነት ወደ
አክሚም ወጡ::በዚያ ሰሞን የጌና ጾም ተፈጽሞ
የአክሚም ክርስቲያኖች ለበዓለ ልደት ዝግጅት ሲያደርጉ
በጠላት ሠራዊት
ተከበቡ::ይህ ሠራዊት የተላከው ከርጉም
ዲዮቅልጢያኖስ ሲሆን መሪው ደግሞ አርያኖስ ነው::
ዋናው ተልዕኮው
ክርስቲያኖችን ለጣዖት ማሰገድ: እንቢ ካሉ ደግሞ
መግደል ነው:: ክርስቲያኖቹ መከበባቸውን እያወቁ
አልፈሩም:: ታኅሳስ
29 ቀንም ሁሉም የከተማዋ ክርስቲያኖች ወደ ቤተ
ክርስቲያን ተሰበሰቡ::በዚያም ሊቀ ዻዻሱ ሥርዓተ ቅዳሴን
አደረሱ::

ሁሉም
በተመስጦ ይጸልዩ ነበርና የክብር ባለቤት ክርስቶስ
በገሃድ ተገለጠላቸው:: በዓይናቸው እያዩም ሥጋ ወደሙን
አቀበላቸው::
ቅዳሴው ሲጠናቀቅ ግን አርያኖስና ሠራዊቱ ደርሰው
ሁሉንም ክርስቲያኖች ያዛቸው::

+ክርስቶስን ክደው ከመገደል እንዲድኑ ተጠየቁ:: እነርሱ
ግን በአንድ ድምጽ "አይሆንም" አሉ:: በዚያን ጊዜ
ወታደሮቹ
በክርስቲያኖች አንገት ላይ በሰይፍ ይጫወቱ ያዙ::በተራ
አሰልፈው ዻዻሱን: ካህናቱን: ዲያቆናቱን:
አንባቢዎችን:መሣፍንቱን ሳይጨምር ከ16,000 በላይ
ክርስቲያኖች ደማቸው ፈሰሰ:: የቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር
ሞልቶ ደም
ወደ ውጭ 20 ክንድ ያህል ፈሰሰ::

በክርስቲያኖች ላይ
ግፍ ተፈጸመ::አካባቢውም ያለ ወሬ ነጋሪ ቀረ:: ግድያው
ለ3
ቀናት ቀጥሎ ጥር 1 አንድ ቀን ቅዱሳን ዲዮስቆሮስና
ሰከላብዮስ ሲገደሉ ተጠናቀቀ::

✞አምላከ ሰማዕታት ፍቅረ ሃይማኖታቸውን ያሳድርብን::
ከበረከታቸውም ይክፈለን::

✞ጥር 1 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ እስጢፋኖስ ቀዳሜ ሰማዕት (ሊቀ ዲያቆናት)
2.ቅዱሳን ሰማዕታተ አክሚም
3.ቅዱሳን ዲዮስቆሮስ ወሰከላብዮስ
4.ቅዱስ ለውንድዮስ ሰማዕት
5.አባ መቃርስ ሊቀ ዻዻሳት

 በ 01 የሚከበሩ ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ልደታ ለማርያም ድንግል እግዝእትነ
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላዕክት
4.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
5.ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር

✞እስጢፋኖስም ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል
ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር . . . አንዳንዶቹ
ተነስተው
እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር:: ይናገርበት የነበረውንም
ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም:: በዚያን ጊዜ
በሙሴ
ላይ: በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ነገር ሲናገር
ሰምተነዋል የሚሉ ሰዎችን አስነሱ . . . በሸንጐም
የተቀመጡት ሁሉ
ትኩር
ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን አዩት::
(ሐዋ. 6:8-15)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
#የሰማዕታተ_አክሚም በስንት ቀን ይታሰባሉ
Anonymous Quiz
15%
ታሕሳስ 30
56%
ጥር 1
12%
ታሕሳስ 29
18%
ሁሉም
እንኳን ለጻድቅ ሰው "ቅዱስ አቤል" እና "ቅዱስ ቴዎናስ ሊቅ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

("አቤል" ማለት በስዕሉ ከፊት ያለው ወጣት ነው)

+*" ቅዱስ አቤል ጻድቅ "*+

=>እግዚአብሔር አዳምን በ7 ሃብታት አክብሮ በገነት ቢያኖረው "አትብላ" የተባለውን ዕፀ በለስ በላ:: በዚህም ከፈጣሪው ተጣልቶ: በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ: በርደተ መቃብር ርደተ ገሃነም ተፈረደበት:: በሁዋላ ግን ንስሃ ስለ ገባ "ከ5 ቀን ተኩል (5,500 ዘመን) በሁዋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ" የሚል ቃል ኪዳንን ሰጠው::

+አዳምና ሔዋን ከገነት ከወጡ በሁዋላ ወዲያው ሕገ ሰብሳብን (የወንድና የሴት ሥርዓትን) አልፈጸሙም:: ይልቁኑ ለ14 ኢዮቤልዩ (ለ100 (98) ዓመታት) ንስሃ ገቡ: አለቀሱ እንጂ::

+አለቃቀሳቸውም እንደኛ በቤተ ፈት ልማድ ሳይሆን "እግዚአብሔርን ያህል ጌታ: ገነትን ታህል ቦታ በበደላችን አጣን" እያሉ ነበር:: "አልቦቱ ለአዳም ካልዕ ሕሊና ዘእንበለ ብካይ ላዕለ ኃጢአቱ" እንዲል:: (መቅድመ ወንጌል)

+እውነትን እንነጋገር ከተባለ እኛ ለወላጆቻችን አዳምና ሔዋን ተገቢውን ክብር እየሰጠናቸው አይደለም:: አንደበቱን የከፈተ "አስተማሪ" ሁሉ ኃጢአታቸውን እንጂ ክብራቸውን ሲናገር ሰምቼ አላውቅም:: ሌላው ይቅርና ማንም ሰው "ቅዱስ አዳምና ቅድስት ሔዋን" ብሎ ሲጠራቸው ገጥሞኝ አያውቅም::

+የሚገርመው ደግሞ እኛ እልፍ አእላፍ ኃጢአትን ተሸክመን እነርሱን ስለ አንዲቷ ኃጢአታቸው ስንወቅሳቸው መዋላችን ነው:: በእነርሱ ምክንያት ገነት ብትዘጋ: ዳግመኛ የተከፈተችው በፍጹም እንባና ንስሃቸው ነው::

+"ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት" (ቅዳሴ ማርያም) እንዲል:: ጌታን ለሰውነት: ለሞት ያበቃው ፍቅረ አዳም መሆኑን ልንዘነጋ አይገባም::

+በዚያውም ላይ አባታችን ቅዱስ አዳም:-
*በኩረ ኩሉ ፍጥረት
*በኩረ ነቢያት አበው
*በኩረ ሐዋርያት ወአርድእት
*በኩረ ጻድቃን ወሰማዕት
*በኩረ ደናግል ወመነኮሳት የሆነ ደግ ፍጥረት ነው:: ስለዚህም ቅዱሳን አዳምና ሔዋንን ልናከብራቸው በእጅጉ ይገባናል::

+ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ቅዱሳኑ አዳምና ሔዋን ንስሃቸውን ፈጽመው: ተስፋ ድኅነት ከተሰጣቸው በሁዋላ አብረው አደሩ:: በዚያች ሌሊትም ቃየንና ኤልዩድ (ሉድ) ተጸነሱ: በጊዜውም ተወለዱ::

+አሁንም ድጋሚ አብረው ቢያድሩ ቅዱስ አቤልና መንትያው አቅሌማ ተጸንሰው ተወለዱ:: ዓለምም በጊዜው እነዚ 6 ሰዎች ይኖሩባት ነበር:: ምንም እንኩዋ እናታችን ቅድስት ሔዋን ብዙ መንትያዎችን ብትወልድም "ብዙ ተባዙ: ምድርንም ሙሉአት" ያለው የጌታ ቃል ይፈጸም ዘንድ ልጆቻቸውን ማጋባት ነበረባቸው::

+የመጀመሪያው የልጆች ጋብቻም በአቤልና በኤልዩድ: እንዲሁም በቃየንና በአቅሌማ መካከል እንዲሆን ተወሰነ:: አባታችን ቅዱስ አዳም ደግ ነቢይ ነውና ለማራራቅ ሲል ይህንን አደረገ:: ነገር ግን በውሳኔው እንደማይስማማ ቃየን ተናገረ::

+ምክንያቱ ደግሞ የአቤል መንትያ መልኩዋ የኔ ብጤ በመሆኗና የእርሱ መንትያ ኤልዩድ ግን እናቷን ቅድስት ሔዋንን የምትመስል ቆንዦ ስለ ነበረች "እኔ መንትያየን ነው የማገባ" የሚል ነበር::

+አቤል ግን የቱንም ቢሉት ከወላጆቹና ከፈጣሪው ትዕዛዝ የማይወጣ ደግ ሰው ነበር:: በጊዜውም መላእክት ባስተማሩት መሠረት ቅዱስ ሰው አዳም ለልጆቹ እርሻንና እንስሳት እርባታን አስተምሯቸው ነበርና ቃየን በግብርና: አቤል ደግሞ በበግ እረኝነት (እርባታ) ይኖሩ ነበር::

+ቅዱስ ሰው አቤል በቅንነቱና በታዛዥነቱ መንፈሰ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ሆነለት:: ሁሌም ስንጠራው "ጻድቅ" ብለን ነው:: ከጻድቃነ ብሊት (ብሉይ) አንዱ ሲሆን የዚህች ዓለም የመጀመሪያው ሟችና ሰማዕት ለመሆንም በቅቷል::

+በሴት ልጅ መልክ ምክንያት በዚህች ዓለም ጥላቻ "ሀ" ብሎ ጀመረ:: ምንም ሳያደርገው ቃየን ወንድሙ አቤልን ጠላው:: የጥላቻ አባቷ ዲያብሎስ ነውና የእርሱ ዘመድ ሆነ::

+ነገሮች ያላማሩት ቅዱሱ አባታቸው ግን በጐ መፍትሔ ሊሆናቸው: የቀናውንም ሥርዓት ሊያስተምራቸው "ለእግዚአብሔር መስዋዕትን አቅርቡ:: እግዚአብሔር መስዋዕቱን የተቀበለለት ኤልዩድን ያገባል" አላቸው:: "እሺ" ብለው መካነ ምስዋዕ አዘጋጁ::

+አቤል ከንጹሕ ልቡ እንዲህ አሰበ:: "እግዚአብሔር ንጹሐ ባሕርይ ነውና ንጹሕ ነገርን ይወዳል" አለ:: በዚህም ቀንዱ ያልከረከረውን: ጥፍሩ ያልዘረዘረውን: ጠጉሩ ያላረረውን: የ1 ዓመት ነውር የሌለበትን ጠቦት አቀረበ::

+ቃየን ደግሞ ከክፉ ልቡ እንዲህ አሰበ:: "እግዚአብሔር አይበላ: አይጠጣ:: ጥሩ ነገር ብሰጠውስ ምን ያደርገዋል" ብሎ ዋግ የመታውን: ነቀዝ የበላውን እሕል (ሥርናይ) አቀረበ:: እዚህ ላይ አንድ ነገርን ልብ እንበል::

+እግዚአብሔር እንደ ሰው አይበላም: አይጠጣም:: ይህ እውነት ነው:: ግን እግዚአብሔር የአቤልን መስዋዕት የተቀበለው በጉን ፈልጐ: ወይ አቤል ቆንጆዋን ሴት እንዲያገባ አይደለም:: ምክንያቱም አቤል እንደሚገደልና በድንግልናው እንደሚሰዋ እርሱ ያውቃልና::

+ይልቁኑ እግዚአብሔርን የሚያስደስተው የስጦታው ምንነት ሳይሆን የሰጭው ማንነት ነውና እኛ ክርዳድ ሆነን ለእግዚአብሔር ስንዴ ልናቀርብለት አንችልም:: ምክንያቱም እግዚአብሔር ከእኛ ምንም ነገርን አይሻም:: ሰማይና ምድር: ፍጥረታት በሙሉ የእርሱ ናቸውና::

+ንጹሐ ባሕርይ ጌታ ከእኛ አንዲት ነገርን ብቻ ይሻል:: ይህቺም በንጹሕ ልቡና የምትቀርብ ንጹሕ አምልኮ ናት:: በዚህም የምንጠቀመው እኛ እንጂ እርሱ አይደለም::

+2ቱ ወንድማማቾች መስዋዕትን ሲያቀርቡለትም "ወነጸረ እግዚአብሔር ላዕለ አቤል ወላዕለ መስዋዕቱ" እንዲል እግዚአብለሔር ቃየንና መስዋዕቱን ትቶ መጀመሪያ ወደ አቤል: ቀጥሎም ወደ መስዋዕቱ ተመለከተ:: ማለትም አቤልና መስዋዕቱን ወደዳቸው::

+በዚህ ምክንያትም ቃየን ተበሳጨ:: ክፋትን እያሰበ ሲመላለስም ሰይጣን ተገናኝቶ ክፉውን መከረው:: በቁራ ተመስሎ ነፍሰ ገዳይነትን አስተማረው:: በዚህም ወደ ምድረ በዳ ወስዶ በድንጋይ ጭንቅላቱን መትቶ ገድሎት ሔደ::

+በዚህ ምክንያትም አቤል "በኩረ ምውታን - የመጀመሪያው ሟች" ተባለ:: "የዋሕ" የተባለበትም ምሥጢሩ ቂም እንደ ያዘበት: ክፋትን እንዳሰበበት እያወቀ እንደ በግ ተከትሎት መሔዱ ነው::

+ስለዚህም ነገር ለመድኃኒታችን ክርስቶስ ምሳሌው ሆነ:: አባ ሕርያቆስም እመቤታችንን ሲያመሰግናት "የውሃቱ ለአቤል ዘተቀትለ በአመጻ-በአመጻ የተገደለ የአቤል የውሃቱ: የየዋህነቱን ዋጋ የምታሰጭው አንቺ ነሽ" ብሏል::

+ቅዱስ አቤል ከተገደለ ከ28 ዓመታት በሁዋላ ነፍሱ ገነትን ተሳልማለች:: ስለ ቅዱሱ ግፍም እግዚአብሔር የቃየንን ዘሮች በጥፋት ውሃ ደምስሷቸዋል::

+"+ ቅዱስ ቴዎናስ ሊቀ ዻዻሳት +"+

=>ይህ ቅዱስ ሰው ተወልዶ ያደገው በእስክንድርያ (ግብጽ) ሲሆን ዘመኑም 3ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: እርሱ ትምሕርተ ቤተ ክርስቲያንን ተምሮ ጸጋው ቢበዛለት ከምዕመንነት ወደ ዲቁና: ከዲቁና ወደ ቅስና ማዕርግ ተሸጋገረ::
+ቀጥሎም ለታላቅ ሃላፊነት ተመረጠ:: አባ መክሲሞስ ባረፈ ጊዜ የግብጽ 16ኛ ፓትርያርክ ሆነ:: ግን ኃላፊነቱ ሠርግና ምላሽ (የተመቸ) አልነበረም:: ምክንያቱም እርሱ ሊቀ ዻዻሳት ሲሆን ዘመነ ሰማዕታት በመጀመሩ ክርስቲያኖች ተሰደዱ: ተጨፈጨፉ::+አብያተ ክርስቲያናትም ተቃጥለው አለቁ:: በዚሀ ጊዜ ቅዱስ ቴዎናስ እየዞረ ሕዝቡን ያጸና ነበር:: በተለይም የእመቤታችንን ቤተ ክርስቲያን አንጾ ለሕዝቡ ያቆርብ: ያስተምር ነበር::

+በዘመነ ሲመቱ ተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ዼጥሮስን ጨምሮ ብዙ አርድእትን አፍርቷል:: ሥልጣነ እግዚአብሔር ጋርዶት ስለ ነበር አገልግሎቱን ፈጽሞ በዚህ ቀን ዐርፏል::

=>የጻድቅ ሰው አቤል አምላከ የውሃቱን ይስጠን:: የዋሃንን ያብዛልን:: ከበረከቱም ይክፈለን::

=>ጥር 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
2.ቅዱስ ቴዎናስ ሊቀ ዻዻሳት
3.ቅዱስ አላኒቆስ ሰማዕት
4.ቅድስት ሳቤላ ነቢዪት
5.ቅዳሴ ቤታ ለድንግል (በደብረ አባ ሲኖዳ)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ
2.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
3.ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
4.ቅዱስ ዮሐንስ ነቢይ (መጥምቀ መለኮት)
5.ሊቁ አባ ሕርያቆስ
6.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ

=>+"+ እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ: የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው . . . አቤል ከቃየን ይልቅ የሚበልጥን መስዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ:: በዚህም እግዚአብሔር ስለ ስጦታው ሲመሰክር እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ ተመሰከረለት:: ሞቶም ሳለ በመስዋዕቱ እስከ አሁን ይናገራል:: +"+ (ዕብ. 11:1)

    <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
2024/10/01 09:37:44
Back to Top
HTML Embed Code: