Telegram Web Link
+ቅዱስ አግናጥዮስ የተወለደው በክርስቶስ አምላካችን መዋዕለ ስብከት (በ30 ዓ/ም አካባቢ) እንደ ሆነ ይታመናል:: በትውፊትም በማቴ. 18:1 ላይ ያለው ሕጻን እርሱ ነው ይባላል::+ሐዋርያት ከመካከላቸው ማን እንደሚበልጥ ሲጠይቁት አንድ ሕጻንን (አግናጥዮስን) ከመሃል አቁሞ "ካልተመለሳችሁ: እንደዚህም ሕጻንካልሆናችሁ ከቶውንም ወደ እግዚአብሔር መንግስት አትገቡም" ብሏቸዋል::

+ከጌታ ዕርገት በሁዋላም ሐዋርያት ለወንጌል ሲፋጠኑ ሕጻኑ ቅዱስ አግናጥዮስ እየተከተለ አገልግሏል: ተምሯል:: ኢየሩሳሌም በጥጦስ አስባስያኖስ ቄሣር በጠፋችበት ዓመት (በ70 ዓ/ም) ቅዱሱ የአንጾኪያ ሊቀ ዻዻሳት ሆኖ ተሹሟል::

+ከዚህ በሁዋላም ለ2 እና 3 አሠርት ዓመታት ከወንጌላዊ ዮሐንስ ጋር አብሮ ወንጌልን ሰብኩዋል:: የዚህ ቅዱስ ተጋድሎ ጫፍ የደረሰው ከ100 ዓ/ም በሁዋላ ሁሉም ሐዋርያት ሰማዕት በመሆናቸውና ትልቁን ኃላፊነት እርሱ በመሸከሙ ነው:: የወቅቷን ቤተ ክርስቲያን ከቅዱሳኑ ቀሌምንጦስ ዘሮምና ፖሊካርፐስ ዘሰርምኔስ ጋር ሆኖ እስከ ደም ጠብታ ጠብቁዋል::

+ከዚህ በሁዋላ ቅዱስ አግናጥዮስ ለዘመናት ወንጌልን እየሰበከ በሕይወቱና በትምሕርቱ አስተማረ:: ብዙ መልእክቶችን (ድርሳናትንም) ጻፈ:: በመጨረሻው ግን በጠራብሎስ ቄሣር ተይዞ: በብረት ሰንሰለት ታስሮ: ከአንጾኪያ (ሶርያ) ወደ ሮም (ጣልያን) ተወሰደ::

+ደሙ እስኪፈስም ገረፉት:: ዛሬ በሮም ከተማ ግማሽ አካሉ ፈርሶ በሚታየው ስታዲየም (በአባቶቻችን አጠራር ተያጥሮን) እንዲገደል ተወሰነበት:: በወቅቱ ባደረገው ንግግርም ቄሣሩና ሕዝቡ ድፍረቱን አደነቁ:: በመጨረሻም ለአንበሳ እንዲሰጥ ተደርጐ በዚህች ቀን ሰማዕት ሆነ::

+" ቅድስት አስቴር "+

=>ይህቺ ቅድስት እናት:-
*እሥራኤል በባቢሎን ምርኮ ሳሉ የነበረች
*አባቷ አሚናዳብ ባለ መኖሩ በአጐቷ መርዶክዮስ እጅ ያደገች
*እጅግ ውብ በመሆኗ የአርጤክስስ ሚስት (ንግሥት) ለመሆን የበቃች
*ራሷን መስዋዕት አድርጋ ወገኖቿን አይሁድን ከሞት ያተረፈች
*ለመርዶክዮስ ክብርን: ለአማሌቃዊው ሐማ ደግሞ ስቅላትን ያስፈረደች እና
*እግዚአብሔር ሞገስ የሆናት እናት ናት::
*ዛሬ ዕረፍቷ ነው::

=>አምላከ ቅዱሳን ወዳጆቹን ባጸናበት ቅዱስ መንፈሱ እኛንም ያጽናን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::

=>ታሕሳስ 24 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
2.ቅዱሳን ጸጋ ዘአብና እግዚእ ኃረያ
3.ቅዱስ አግናጥዮስ ሐዋርያ
4.ቅድስት አስቴር
5.አባ ፊሎንጐስ ሊቀ ዻዻሳት
6.አባ ዻውሊ ጻድቅ
7.ጻድቃን ቅዱሳን ዘከዲህ

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
2.አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ ዘክብራን
3.ቅዱስ አጋቢጦስ (ጻድቅ ኤዺስቆዾስ)
4.ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
5."24ቱ" ካኅናተ ሰማይ (ሱራፌል)
6.ቅዱስ አባ ሙሴ ጸሊም (ኢትዮዽያዊ)
7.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ

=>+"+ ንግሥቲቱም አስቴር መልሳ:- 'ንጉሥ ሆይ! በአንተ ዘንድ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆነ: ንጉሡንም ደስ ቢያሰኘው: ሕይወቴ በልመናዬ: ሕዝቤም በመሻቴ ይሰጠኝ:: እኔና ሕዝቤ ለመጥፋትና ለመገደል: ለመደምሰስም ተሸጠናልና:: +"+ (አስቴር. 7:3)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
እንኩዋን ለ5ቱ "ቅዱሳን መቃብያን" እና "ቅዱስ ዮሐንስ ከማ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

+*" 5ቱ መቃብያን "*+

=>እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን: 22ቱን ሥነ ፍጥረትን ፈጥሮ አዳምን ገዢ አደረገው:: አክሎም በነፍስ ሕያው አድርጐ: በመንፈስ ቅዱስ አክብሮ: ነቢይና ካህን አድርጐ: ካንዲት ዕፀ በለስ በቀር በፍጥረት ሁሉ ላይ አሰለጠነው::

+አባታችን አዳም ግን ስሕተት አግኝቶት ከገነት ወጣ:: መከራና ፍዳም አገኘው:: በሁዋላም ለ100 ዓመት አልቅሶ ንስሃ ገባ:: ጌታም ንስሃውን ተቀብሎ "ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ" የሚል ተስፋ ድህነትን ሰጠው::

+ስለዚህም ምክንያት ለ5,500 ዓመታት ትንቢት ሲነገር: ሱባኤ ወደ ታች ሲቆጠር: ምሳሌም ሲመሰል ኖረ:: ከደግ ፍጥረት አዳም እስከ ኖኅ ድረስ: የሴት ልጆች እግዚአብሔርን በንጽሕና ሁነው በደብር ቅዱስ አመለኩ::

+ትንሽ ቆይተው ግን ስለተቀላቀሉ ከቃየን ልጆች ጋር በማየ ድምሳሴ ጠፉ:: በጻድቅ ሰው ኖኅ የተጀመረው ትውልድም እግዚአብሔርን ለመዘንጋት ጊዜ አልፈጀበትም:: ነገር ግን ከሴም ዘር ቅንና ጻድቅ ሰው አብርሃም ተገኘ::

+ከእርሱም ይስሐቅ: ከዚያም ያዕቆብ ደጋጉ ተገኙ:: ያዕቆብም "እሥራኤል" ተብሎ በልጆቹ "ሕዝበ እግዚአብሔር" የተባለ ነገድ ተመሠረተ:: በተስፋይቱ ምድር በከነዓን እንዳይኖሩም ረሃብ ምድረ ግብጽ አወረዳቸው::

+በዚያም ለ215 ዓመታት በጭንቅ የባርነትን ሕይወትን አሳለፉ:: እግዚአብሔርም ስለ ወዳጁ አብርሃም ሲል እሥራኤልን አሰባቸው:: የዋሕና ጻድቅ ሰው ሙሴን አስነስቶ እሥራኤልን ከግብጽ ባርነት አዳናቸው::

+ይኸውም በጸናች እጅ: በበረታችም ክንድ: በ9 መቅሰፍት: በ10ኛ ሞተ በኩር: በ11ኛ ስጥመት ግብጻውያንን አጥፍቶ ነው:: በየመንገዱም ጠላቶቻቸውን እየተበቀለላቸው ነው:: ከዚህ ዘመን ጀምሮም እሥራኤል በመሳፍንትና በካህናት የሚተዳደሩ ሆኑ::

+አስቀድሞ ሙሴ በምስፍና: አሮን በክህነት መሯቸው:: ቀጥሎም በቅዱስ ሙሴ ኢያሱ: በአሮን አልዓዛር ተተኩ::

+ከዚህ በሁዋላ ለ300 ዓመታት ያህል መሣፍንት እየተቀያየሩ አስተዳደሩዋቸው:: ሲበድሉ ጠላት እየገዛቸው: ሲጸጸቱ በጐ መሥፍን እየመጣላቸው ከነቢዩ ሳሙኤል ደረሱ::

+በዚህ ጊዜም ሕዝቡ እንደ አሕዛብ ሥርዓት ንጉሥ በመፈለጋቸው ክፉው ሳዖል ለ40 ዓመት ገዛቸው:: ቀጥሎ ግን እንደ አምላክ ልብ የሆነ ቅዱስ ሰው ዳዊት ነግሦላቸው እሥራኤል ከፍ ከፍ አሉ:: ከቅዱስ ዳዊት እስከ ሮብዓም ቆይተው ግን እሥራኤል ከ2 ተከፈሉ::

+10ሩ ነገድ በሰማርያ ሲኖሩ ግፍን ስላበዙ ስልምናሶር ማርኮ አሦር አወረዳቸው:: ባሮችም አደረጋቸው:: 2ቱ ነገድ ደግሞ ከብረው: ገነው በኢየሩሳሌም ቢኖሩም እነርሱም አመጸኞች ነበሩና ናቡከደነጾር ወስዶ የባቢሎን ባሪያ አደረጋቸው::

+እግዚአብሔር ግን እንደ ነቢያቱ ቃል 70ው ዘመን ሲፈጸም በኃይል ወደ ርስታቸው መለሳቸው:: በዚያም ዘሩባቤል የሚባል ደግ ንጉሥ ነግሦላቸው: ቤተ መቅደስ ታንጾላቸው ኖሩ:: ክፋታቸው ግን ማብቂያ አልነበረውምና ከዘሩባቤል በሁዋላ ቅን ንጉሥን ማግኘት አልቻሉም::

+እግዚአብሔር ግን ምሕረቱንና መግቦቱን አይተውምና አልዓዛርን የመሰሉ ደጋግ ካህናትን እያስነሳ ሰው እስከሚሆንባት ቀን ድረስ አቆይቷቸዋል:: በዚህም ምክንያት ይህ ዘመን "ዘመነ ካህናት" ተብሏል::

+በዚህ በዘመነ ካህናት ውስጥ ደግሞ በጐነታቸው የታወቀላቸው: ግን ደግሞ መከራው የበዛባቸው እሥራኤላውያን ነበሩ:: ብዙ ጊዜ የሚጠሩት "መቃብያን" በሚል ስም ነው::

+በያዕቆብ እሥራኤል: በዔቦር ዕብራውያን: በይሁዳ አይሁድ: በፋሬስ ፈሪሳውያን: በሳዶቅ ሰዱቃውያን እንደተባሉት ሁሉ እነዚህም በአባታቸው በመቃቢስ ምክንያት መቃብያን ተብለዋል:: ታሪካቸው ሰፊና በመጽሐፈ መቃብያን የተጻፈ ሲሆን እኛ ግን በአጭሩ አንዷን የታሪክ ዘለላ ብቻ እንመለከታለን::

+በዘመኑ መቃቢስ የሚባል ደግ ሰው 5 (3) ወንዶች ልጆችን (መቃብያንን) ወልዶ ነበር:: እነዚህም በመልክ ይህ ቀራችሁ የማይባሉ: በጠባይ እጅግ የተመሰገኑ: በኃይላቸው ጽናትም የተፈሩ ነበሩ::

+በተለይ 3ቱ ከግሩማን አራዊት አንበሳና ድብ ታግለው ያሸነፉ: በጦርነትም ጠላትን ያንበረከኩ ነበሩ:: ታዲያ ይህ ሁሉ የተሰጣቸው ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ያውቁ ነበርና ፈጣሪያቸውን በንጹሕ ልብ ያመልኩት ነበር::

+በዘመኑ ደግሞ ሞዐባውያንና ሜዶናውያን አካባቢውን ያስገብሩ ነበር:: በተለይ የሞዐቡ ንጉሥ ጺሩጻይዳን ከክፋቱ ብዛት 70 ጣዖታት በወንድና በሴት ምሳሌ አስቀርጾ ያመልክ ነበር:: ከዚያም አልፎ ሕዝቡን "አምልኩ" እያለ ያውክ: ይቀጣ: ይገድልም ነበር::

+ቅዱሳን መቃብያን ይህንን ሲሰሙ ወደ እርሱ ገሰገሱ:: ምንም እንኩዋ ሊያጠፉት ኃይል ቢኖራቸውም አላደረጉትም:: ይልቁኑ ቀርበው ዘለፉት እንጂ::

+እርሱም "ጣዖትን አናመልክም" ስላሉ ለአንበሳ ጣላቸው:: አንበሶቹም ለቅዱሳኑ ሰግደው የንጉሡን ወታደሮች ፈጇቸው:: እርሱም 3ቱን ወደ እሥር ቤት ጣላቸው:: በዚህ ጊዜ 2ቱ ወንድሞቻቸው መጥተው ተቀላቀሉ::

+ቀጥሎም 5ቱንም አስወጥቶ በሰይፍ አስመታቸው:: ከተገደሉ በሁዋላም ወደ ውሃ ጥሏቸው: በእሳት አቃጥሏቸው ነበር:: ባይሳካለት ስለ ተቆጣ ሳይቀበሩ እንዲጣሉ አዘዘ:: ከ14 ቀናት በሁዋላም የቅዱሳኑ አካል እንደ መብረቅ እያብለጨለጨ ተገኝቶ በክብር እንዲቀበር ሆኗል::

<< ቀሪው ታሪካቸው በመጽሐፈ መቃብያን የተጻፈ አይደለምን !! >>

+*" አባ ዮሐንስ ከማ "*+

=>ቅዱስ ዮሐንስ ከማ በዘመነ ጻድቃን (በተለይም በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን) ከተነሱ አበው አንዱ ነው:: ቅዱሱ ድንቅ ሕይወት ስለ ነበረው በዜና አበው በስፋት ተጠቅሷል:: መጽሐፈ ስንክሳር "ከማ" የሚለውን ቃል "ከማ ብሒል ካም - 'ከማ' ማለት 'ካም' ማለት ነው" ይላል::

+"ካም" የሚለው ቃል ደግሞ ብዙ ጊዜ መልካቸው ጠቆር ላሉ ሰዎች የሚሰጥ ስም ነው:: ምናልባት የድሮ የኢትዮዽያ ግዛት በነበረው ደቡብ ግብጽ የነበረ አባት እንደ መሆኑ የዘር ሐረጉ ከኢትዮዽያ የተመዘዘ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል::

+ቅዱሱ በስፋት የሚታወቀው በድንግልና ሕይወቱ ነው:: መልካም ቤተሰቦቹ በሥርዓት አሳድገው "እንዳርህ" አሉት:: እንቢ ቢላቸው ብቸኛ ልጃቸው ነውና ፈጽሞ ሊያዝኑበት ነው:: ደስታውን ለቤተሰቦቹ ሰውቶ በተክሊል ተዳረ::

+እርሱ የሚሻው በድንግልና መኖርን ነውና ጥበበኛ እግዚአብሔር ሚስቱ የተቀደሰች እንድትሆን አደረጋት:: በሠርጋቸው ምሽት ቅዱስ ዮሐንስ ከማ መልከ መልካሟን ሙሽራ በድንግልና ይኖሩ ዘንድ ቢጠይቃት በደስታ አነባች::

+ምክንያቱም እርሷም ያገባችው ቤተሰብን ለማስደሰት እንጂ ፈቃዷ በድንግልና መኖር ነበርና:: 2ቱም ስላደረገላቸው ፈጣሪን እያከበሩ የድንግልና ሕይወት ተጋድሎን ቀጠሉ:: ቅዱሳኑ በአንድ አልጋ ላይ እየተኙ: አንዲት ምንጣፍን እያነጠፉ: አንድ ልብስንም በጋራ ለብሰው እያደሩ ድንግልናቸውን ጠበቁ::

+አምላከ ድሜጥሮስም ቅዱስ መልአኩን ልኮላቸው በመካከላቸው ያድር: ክንፉንም ያለብሳቸው ነበር:: ክብራቸውን ይገልጥ ዘንድም በቤታቸው መካከል ታላቅ ዛፍን ያለ ማንም ተካይነት አበቀለ::
+በዚህ ጊዜ ግን ቅዱስ ዮሐንስ ከማ ድንግሊቱን ሚስቱን "የከተማ ኑሮ ይብቃን: ወደ በርሃ እንሒድ" አላት:: እርሷም "ፈቃድህ ፈቃዴ ነው" ስላለችው እርሷን ወደ ደናግል ገዳም አስገብቶ እርሱ ወደ ገዳመ አስቄጥስ ተጉዋዘ::+ቅድስቲቱ አስቀድማ ጸጋው በዝቶላት ነበርና ድውያንን ትፈውስ ነበር:: የገዳሙ እመ ምኔት ሆና መርታ በክብር አረፈች:: ቅዱስ ዮሐንስ ከማም በቅዱስ መልአክ መሪነት መጀመሪያ ወደ አባ ዳሩዲ ሔዶ መነኮሰ::

+በመጨረሻም በቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ገዳም ጐን ማደሪያን አነጸ:: በዚያም በመቶ የሚቆጠሩ ደቀ መዛሙርትን አፍርቶ በአበ ምኔትነት አገለገለ:: ለእመቤታችንና ለቅዱስ አትናቴዎስ ልዩ ፍቅር የነበረው ቅዱሱ ከበርካታ የቅድስና ዘመናት በሁዋላ በዚህች ቀን በክብር ዐርፎ ተቀብሯል::

=>አምላከ ቅዱሳን ይራዳን: ይባርከን: ይቀድሰን:: ከወዳጆቹ በረከትም ያሳትፈን::

=>ታሕሳስ 25 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱሳን 5ቱ መቃብያን
2.ቅዱስ ዮሐንስ ከማ (እና የተቀደሰች ሚስቱ)
3.ቅዱስ ዳንኤል መነኮስ
4.ቅዱስ ኒቆላዎስ መኮንን

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
2.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
3.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
4.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
5.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)
6.ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ
7.ታላቁ አባ ቢጻርዮን ገዳማዊ

=>+"+ ቃሌን የሚጠብቅ: በትዕዛዜም ጸንቶ የሚኖር: በረከቴን የሚያገኝ: በእኔ ዘንድ የሚከብር እርሱ ነው::
ቃሌን የሚጠብቅ: በትዕዛዜም ጸንቶ የሚኖር ሰው ሁሉ ከምድር የተገኘውን ድልብ ይበላል:: ቅን ልቡና ያላቸው ደጋጎች ነገሥታት ወደ ገቡበት ወደ ገነትም ገብቶ ይኖራል:: +"+ (መቃ. 12:43)

   <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

https://www.tg-me.com/zikirekdusn
<<< በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ >>>

<<< ታሕሳስ 26 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት >>>

+" ቅድስት አንስጣስያ "+

=>እስኪ ዛሬ በጥቂቱ የተባረኩ (ቡሩካት) እናቶቻችን
እንዘክር:: "ቅድስት" የሚለው ቃል ለሁሉም ቅዱሳት
እናቶች ቢሰጥም
ቅሉ ለድንግል ማርያም ሲሰጥ ግን ትርጉሙ ይለያል::
እርሷ 'ቅድስተ ቅዱሳን: ንጽሕተ ንጹሐን: ቡርክት
እምቡሩካን:
ኅሪት እምኅሩያን ናትና::

+ከሰው ልጆችም ሁሉ ትበልጣለች:: ይቅርና የሰው ልጅን
ንጹሐን መላእክትንም በንጽሕናና በቅድስና
ትበልጣቸዋለች:: እርሷ
እመ ብርሃን: የአምላክ እናቱ: የሰውነታችን መመኪያ
ናትና::

+እመቤታችንን "ቅድስት" ስንል "ጽንዕት: ንጽሕት: ክብርት:
ልዩ" ማለታችን ነው:: 1."ንጽሕት" ትባላለች:: ሌሎች
ሰዎች (ቅዱሳን) ቢነጹ ከገቢር: ከነቢብ ኃጢአት ነው
እንጂ ከኃልዮ ኃጢአት አይደለም:: እርሷ ግን ከነቢብ:
ከገቢር:
ከኃልዮ ንጽሕት ናት::

"ለመኑ ተውኅቦ ተደንግሎ ኅሊና: ለመላእክትሂ
ኢተክህሎሙ-ኃጢአትን ከማሰብ መጠበቅ ከሰው ልጆች
ለማን ተሰጠው: ይህስ
ለመላእክትም አልተቻላቸውም" እንዲል:: (ተአምረ
ማርያም)

2."ጽንዕት" እንላታለን:: ሴቶች ቢጸኑ ለጊዜው ነው እንጂ
በኋላ በጊዜው ተፈትሆ አለባቸው:: እመቤታችን ግን
ቅድመ
ጸኒስ: ጊዜ ጸኒስ: ድኅረ ጸኒስ: ቅድመ ወሊድ: ጊዜ
ወሊድ: ድኅረ ወሊድ ድንግል ናትና::
"ጽንዕት በድንግልና አልባቲ ሙስና" እንዳላት:: (ቅዱስ
ያሬድ) ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስም "ወትረ ድንግል ማርያም-
ማርያም
ዘለዓለማዊት ድንግል ናት" እንዳለ:: (መጽሐፈ ቅዳሴ)

3.ድንግልን "ክብርት" እንላታለን:: ሌሎች ሴቶች ቢከብሩ
ጻድቃን ሰማዕታትን: ነቢያት ሐዋርያትን ወልደው ነው::
እመቤታችንን ግን የምናከብራት "ወላዲተ አምላክ-
የአምላክ እናቱ" ብለን ነውና::

4.እመቤታችንን "ልዩ" እንላታለን:: ከእርሷ በቀር እናት ሁና
ድንግል: እመቤት ሁና አገልጋይ የሆነች: በድንግልና
ወልዳ ወተትን (ሐሊበ ድንግልናዌን) ያስገኘች ሌላ ሴት
የለችምና::

+የእመ ብርሃን ይቆየንና ደግሞ ሌሎች ቅዱሳት
እናቶቻችንን እንመልከት:: እናቶቻችን ስናከብር
የምንጀምረው በቅድስት
ሔዋን ነው:: ብዙ ጊዜ የእናታችን ሔዋን ጥፋቷ እንጂ
በጐ ነገሯ: ደግነቷ: ንስሃዋ አይነገርላትም:: ሆኖም
እናታችን
ቅድስት ሔዋን ክብር የሚገባት ሴት ናት::

*ክርስቶስ ሰው የሆነ እርሷንና ልጆቿን ለመቀደስ ነውና::
"ከመ ይስዓር መርገማ ለሔዋን ዲበ ዕፅ ተሰቅለ"
እንዲል::
(ድጉዋ)

+ቀጥሎ በብሉይ ኪዳን እነ ሐይከል: እድና: ሣራ: ርብቃ:
አስኔት: ሲፓራ: ሐና: ቤርሳቤህን የመሰሉ እናቶቻችን
በበጐው
መንገድ ፈጣሪን ደስ አሰኝተዋል:: በዘመነ ሥጋዌም
ቅዱሳቱ ሐና: ኤልሳቤጥ: ማርያም: ሶፍያ: ሰሎሜ: ዮሐና
እና 36ቱ
ቅዱሳት አንስት በጐነታቸው ያበራል::

+ከዚያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ለ2,000 ዓመታት የተነሱ
አእላፍ ቅዱሳት እናቶቻችንን ግን ዘርዝረን አንዘልቃቸውም::
በቅድስናቸው አራዊትን ያሰገዱ: ነገሥታትን ያንቀጠቀጡ:
አጋንንቸትን የረገጡ: በዘንዶ ላይ የተጫሙ ብዙ እናቶችን
ቤተ
ክርስቲያን አፍርታለች::

+ዛሬም ቢሆን በበርሃና በከተማ በጐውን ጐዳና የተከተሉ
ብዙ እናቶች እንዳሉን እናውቃለን:: አንድም እናምናለን::
ግን
ግን በከተሞች የምንመለከተው ሥርዓቱን የለቀቀው
የበርካታ እህቶቻችን አካሔድ ለሃገርም ለቤተ
ክርስቲያንም ትልቅ ስጋት
ነው:: ክብርና ነውር የማይለይበት ዘመን ይመስላል::

+ይህንን እያነበባችሁ ያላችሁ እህቶቼ! አንድ ነገር
ልንገራችሁ:: በመልካቸው ብዙዎችን ያጋጩ: አጊጠው
በመታየታቸው ብዙዎችን ያሰናከሉ: ለብዙ ምዕመናንም
የጥፋት ምክንያት የሆኑ ብዙ ሴቶች በታሪክ ነበሩ::

+የሚያሳዝነው ግን ዛሬ ያሉት ከመሬት በታች ነው:: አፈር
በልቷቸዋል:: ስም አጠራራቸውም ጠፍቷል:: በጣም
የሚያሳዝነው
ደግሞ ዛሬ በዘለዓለማዊው እሳት እየተቃጠሉ በሲኦል:
በጥልቁ ውስጥ አሉ::

+እናም ወገኖቼ! ይህን አውቀን እንንቃ:: ይህ ዓለም
ጠፊም: አጥፊም ነውና:: እድሜአችን ቢረዝምና ከዚህ
በኋላ ለ100
ዓመታት ብንኖርም እርሱም ማለቁ አይቀርምና::
ምርጫችን ዘለዓለማዊው ሕይወት ይሁን ትላለች ቅድስት
ቤተ ክርስቲያን::

+" ቅድስት አንስጣስያ "+

+ይህች ቅድስት እንደ በርካቶቹ ቅዱሳት እናቶቻችን ሁሉ
የዘመነ ሰማዕታት ፍሬ ናት:: በቀደመችው ታናሽ እስያ
አካባቢ
ተወልዳ: የነገሥታት ዘር በመሆኗ ያደገችው በቤተ
መንግሥት ነው:: አባቷ ከክቡራኑ አንዱ ቢሆንም ሙያው
ጣዖትን ማምለክ
ነበር::

+ጊዜው የመከራ በመሆኑ ብዙ ሴቶች የሚኖሩት
ክርስትናቸውን ደብቀው ነው:: ከእነዚህ መካከል አንዷ
ደግሞ የቅድስት
አንስጣስያ እናት ናት:: ማንን እንደምታመልክ አረሚ ባሏ
አያውቅም ነበር::

+አንስጣስያን በወለደች ጊዜም በድብቅ አስጠመቀቻት::
ከሕጻንነቷ ጀምሮም ፍቅረ ክርስትና እንዲያድርባት ነገረ
ሃይማኖትን
አስተማረቻት:: ቅድስት አንስጣስያ ወጣት በሆነች ጊዜ
ግን ከውበቷ የተነሳ ተመልካቿ በዛ:: እርሷ ግን ይህ ሁሉ
የዓለም
ኮተት አይገባትም ነበር::

+በፈጣሪዋ ፍቅር ከመጠመዷ የተነሳ ለመሰል ነገሮች
ትኩረት አልነበራትም:: ትጾማለች: ትጸልያለች: ነዳያንና
እሥረኞችን
ትጐበኛለች:: በዚህም ዘወትር ደስ ይላት ነበር:: ነገር ግን
አባቷ ባላሰበችው ጊዜ ለአንድ አረማዊ አጋባት:: በጣም
አዘነች: ግን ተስፋ አልቆረጠችምና መፍትሔ ፈለገች::

+ድንግልናዋን እንዳያረክስ በጫጉላዋ ቀን ታመምኩ ብላ
ተኛች:: ከዚያ በኋላም አንዴ በልማደ አንስት: አንዴ
በሕመም
እያመካኘች አላስቀርብ አለችው:: እርሱ የጦር አለቃ
በመሆኑ ወደ ጦርነት ሲሔድ እርሷ ታጥቃ ስለ ቀናች
እምነት የታሠሩ
ክርስቲያኖችን ታገለግል ነበር::

+ቁስላቸውን እያጠበች: አንጀታቸውን በምግብ እየደገፈች
ደስ ታሰኛቸውም ነበር:: ባሏ ሲመለስ ግን ይህንን
በመስማቱ
ድጋሚ እንዳትወጣ ቆልፎባት ወደ ጦርነት ተመለሰ::
ፈጽማ ስላዘነችበትም እግዚአብሔር በጠላቶቹ እጅ
አሳልፎ ሰጠውና ሞተ::

+እርሷም ከነ ድንግልናዋ ቀሪ ሕይወቷን ስትመራ
መከራው ወደ እርሷ ደረሰ:: ተይዛ ቀርባ በአረማውያን እጅ
ብዙ
ተሰቃየች:: በዚህች ቀንም ስለ ክርስቶስ ተገድላ ክብረ
ሰማዕታትን ተቀዳጀች::

ቅዱስ አቦሊ ጻድቅ

+ቅዱሱ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የክርስቶስን ሕማማት
ለመሳተፍ ሲተጉ ከኖሩ ጻድቃን አንዱ ነው:: መሉ ጊዜውን
በበርሃ
ሲያሳልፍ ብዙ ተጋድሎን ፈጽሟል:: በተለይ ሲጸልይ
እግሩን ከዛፍ ላይ አስሮ: ቁልቁል ከባሕር ውስጥ ሰጥሞ
ነው:: ዛሬ
ቤተ ክርስቲያን ዕረፍቱን ታስባለች::

=>አምላከ ቅዱሳን ጸጋውን: ክብሩን ያድለን:: ከወዳጆቹ
በረከትም አይለየን::

=>ታሕሳስ 26 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅድስት አንስጣስያ ሰማዕት
2.ቅዱስ አቦሊ ጻድቅ
3.ቅድሰት ዮልያና ሰማዕት

=>በ 26 የሚከበሩ ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
2.አቡነ ሐብተ ማርያም ጻድቅ
3.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
4.ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን
5.ቅዱስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን

++"+ ለእናንተም ጠጉርን በመሸረብና ወርቅን
በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጐናጸፍ በውጭ የሆነ
ሽልማት አይሁንላችሁ::
ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ
የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ
ለብሶ የተሰወረ
የልብ ሰው ይሁንላችሁ:: +"+ (1ዼጥ. 3:3)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
2024/10/01 09:36:46
Back to Top
HTML Embed Code: