Telegram Web Link
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
[ የማይሰለች ተጋዳይ ፤ የክብር ኮከብ ! ]

" እንግዲህ ከሰው ተለይቶ ወደ ጫካ ገባ ፤ በዚያም ኖረ። በበጋው ፡ ሓሩር ፡ በክረምቱ ፡ ቍር ፡ እየተሠቃየ ፡ ኖረ ። በሰውነቱ ላይ ፡ ልብስን ፡ አልለበሰም ፡ ዕራቁቱን ፡ ነበረ እንጂ ራቁቱን ፡ በብርድ ፡ ላይ ፡ ቆሞ ፡ ይጸልይ ነበር ፤ ወገቡንም ፡ በማቅ ፤ በሠንሰለት ታጥቆ ነበር ። ከዚያ ፡ ጫካ ፡ ቅዝቃዜ ፡ የተነሣም ፡ ሰውነቱ ፡ አልቆ አጥንቱ ፡ ደርቆ ፡ ነበር።

ሰውነቱንም ፡ በእግዚአብሔር ፡ ፊት ፡ ዕራቁትሽን ፡ ትቆሚአለሽና ፡ እወቂ ፥ ጽኚ በርቺ ፡ ጨክኚ ፡ ይላት ፡ ነበር ፤ እንደዚህ ፡ ባለ ፡ ሥራ ፡ በጾምና ፡ በጸሎት ፡ በስግደትና ፡ በብዙ ፡ ትጋት ፡ ቀንም ፡ ሌሊትም ፡ ጽሙድ ፡ ሆኖ ፡ ኖረ።

ያለ ዕረፍት ብዙ ፡ ጸሎትን ፡ ይጸልይ ፡ ብዙ ፡ ስግደት ይሰግድ ነበር ። ሥጋው እስኪደርቅ : ቍርበቱም ፡ ከአጥንቱ እስኪጣበቅ ፡ ድረስ ከእንጨት ፡ ፍሬና ሥራ ሥር ፡ ወይም ፡ ከአትክልት ፡ ወይም ገዳማውያን ፡ ከሚመገቡት ፡ ከሌሎች ፡ ፍሬያት ፡ ምንም፡ ምን ፡ የሚመገበው አልነበረውም : ለሥጋውም ፡ ምንም ፡ ምን ፡ ምክንያት ፡ አልሰጠም።

መላእክትም : ዘወትር : ይጎበኙት ፡ ነበር ፤ በሥራውም ፡ በቃሉም፡ እንደነሱ ፡ ነበርና ፤ በገድልና ፡ በትሩፋት ፡ የሚመስለው : ማነው ፡ምድራዊ : ምግብ : የተመገበበት : ጊዜ : የለም ፤ ውሃን አልጠጣም ፤ ምንም ፡ ምን ፡ ልብስ ፡ አልለበሰም ፤ ፈጽሞ ፡ ለሥጋው አላደላም ።

በእውነትም ፡ አቡነ ፡ ገብረ : መንፈስ : ቅዱስ : መላእክትን : መሰለ ፤ በዚህ ፡ በኃላፊው ፡ ዓለም ፡ ለመብል ፥ ለመጠጥ ፥ አላሰበም። ስለ ፡ እግዚአብሔር ፡ ብሎ ፡ ተራበ ተጠማ ። "

[ ገድለ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ]

       †         †         †
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬
🕊

[ † እንኳን ለጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

🕊 † አቡነ ገብረ ሕይወት † 🕊

† ጻድቁ የተወለዱት ግብፅ [ንሒሳ አካባቢ] ሲሆን አባታቸው ስምዖን እናታቸው አቅሌስያ ይባላሉ:: አባታችን ገብረ ሕይወት የጻድቃን አለቃ: የቅዱሳን የበላይ: ተጋድሎአቸውና ድንቅ ተአምራቸው እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ቅዱስ ሰው ናቸው::

የጻድቁን ክብር መናገር የሚችል ምን አንደበት ይኖራል?
- እንደ ምንስ ባለ ብራና ይጻፋል?
- ዜናቸውንስ ለመስማት የታደለ እንደ ምን ዓይነት ሰው ይሆን?

አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስ ለ ፭፻፷፪ [562] ዓመታት በዚህች ዓለም ሲኖሩ :-
- እህል ያልቀመሱ [ምግባቸው ምስጋና ነውና]
- ልብስ ያልለበሱ [ጠጉር አካላቸውን ይሸፍን ነበርና]
- ሐዋርያዊ ሆነው ከግብፅ እስከ ኢትዮዽያ ብዙ ነፍሳትን ያዳኑ አባት::
- ሃገራችንን አስምረው: አስራት እንድትሆናቸውም ተቀብለው ምድረ ከብድ አካባቢ አርፈዋል::

ጻድቁ ገብረ መንፈስ ቅዱስም : ገብረ ሕይወትም ይባላሉ:: በ፭፻፷፪ [562] ዓመታት ሕይወታቸው እንደ ሐዋርያት ከምድረ ግብፅ እስከ ኢትዮዽያ ወንጌልን ሰብከዋል:: በዚህም በሚሊየን [አእላፍ] ለሚቆጠሩ ነፍሳት የድኅነት ምክንያት ሆነዋል::

ጻድቁ እንደ ሰማዕታትም ከከሃዲ ሰዎች ብዙ መከራን ተቀብለዋል:: እንደ ባሕታውያን ለብዙ መቶ ዓመታት ሰው ሳያዩ ቆይተዋል:: ለየት የሚለው ግን የጽድቅ ሕይወታቸው ነው:: ከእልፍ አዕላፍ አጋንንት ጋር ተዋግተው ድል ማድረግ ችለዋልና::

የንሒሳው ኮከብ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ለኢትዮዽያ ልዩ ፍቅር አላቸው:: ስለ ሃገሪቱና ሕዝቧ ፍቅር ሲሉ ለ ፻ [100] ዓመታት በደብረ ዝቋላ መከራን ተቀብለዋል:: ምሕረትን ሲለምኑ ሥጋቸው አልቆ በአጥንታቸው ቁመው ነበርና ሃገራችን አሥራት ሆና ተሰጠቻቸው::

ስለዚህም ነው በሃገሪቱ ውስጥ ከ፳፻ [2,000] በላይ የጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳማትና አድባራት ዛሬም ድረስ ያሉት:: በ8ኛው ክ/ዘመን አካባቢ የተወለዱት አባታችን ያረፉት በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን አካባቢ ነው:: ፍጥረታትን ሁሉ አዘው መጋቢት ፭ [5] ቀን ሲያርፉ ግሩማን መላእክት ገንዘው አካላቸውን ሠውረዋል::

ሥላሴን የተሸከመ አካላቸው በጐልጐታ ተቀብሯል የሚሉም አሉ::
"ሰላም ለመቃብሪከ ዘኢተከሥተ ለባዕድ::
ከመ መቃብሩ ለሙሴ ወልደ ዮካብድ::
ዜና መቃብሪከሰ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጸማድ::
ቦ ዘይቤ በኢየሩሳሌም አጸድ::
ወቦ ዘይቤ ኀለወ በከብድ::" እንዲል::

† የጻድቁ በዓል ጥቅምት ፭ [5] ቀን የሚከበረው ብዙ ጊዜ መጋቢት ፭ [5] ዐቢይ ጾም ውስጥ ስለሚውል ተውላጥ [ቅያሪ] ሆኖ ነው::

† ቸር አምላክ ከጻድቁ ዋጋና በረከት ይክፈለን::

🕊

[ † መጋቢት ፭ [ 5 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጻድቅ [አባ ገብረ ሕይወት]
፪. ቅዱስ አባ ሰረባሞን [በምድረ ግብፅ ምንኩስናን ካስፋፉ ታላላቅ ቅዱሳን አንዱ]
፫. አባ ግርማኖስ ጻድቅ [ሶርያዊ]
፬. ቅድስት አውዶክስያ ሰማዕት [ከከፋ የኃጢአት ሕይወት ተመልሳ ለቅድስና የበቃች እናት]
፭. ቅዱሳን ስምዖንና ሚስቱ አቅሌስያ [የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ወላጆች]

[ † ወርሐዊ በዓላት ]

፩. ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
፪. ቅዱስ ዻውሎስ ሐዋርያ
፫. ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮዽያዊ
፬. ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ

" ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል:: ጻድቅን በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል:: ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ውሃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላቹሃለሁ ዋጋው አይጠፋበትም::" † [ማቴ.፲፥፵፩] [10:41]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬
💖                    🕊                     💖
🕊

[ † እንኳን ለቅዱስ ቴዎዶስዮስ ተአማኒ ሰማዕት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


🕊  †  ቅዱስ ቴዎዶስዮስ  †   🕊

† በሃገረ ኒቅያ በእመቤታችን እና በአምላክ ልጇ የሚያምኑ ፫፻፲፰ [318] ቱ ቅዱሳን ሊቃውንት ተሰብስበዋል:: ከእነዚህ አንዱ ቅዱስ ቴዎዶስዮስ እንደሆነ በትውፊት ይታመናል:: የጉባዔውስ ነገር እንደምን ነበር ቢሉ :-

የሊብያው ሰው አርዮስ ጌትነት ገንዘቡ የሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ክዶ ሊያስክድ ሲሯሯጥ በፈቃደ እግዚአብሔር: በጻድቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ጥሪ: ፳፻፫፻፲፰ [2348] ምሑራን ከመላው ዓለም ተሰበሰቡ::

ጥሪው የተላለፈው በወርኀ ሚያዝያ ሲሆን በመንገድ ችግር ሁሉም ተጠቃለው ኒቅያ የገቡት መስከረም 21 ቀን ነበር:: ከተሰበሰበው ብዙ ሰው መካከል የአበውን ደቀ መዛሙርት ሳንቆጥር ሃይማኖታቸው የቀና: ምግባራቸው የጸና ፫፻፲፰ [318]ቱ አበው ሊቃውንት ተገኙ::

እነዚህ አባቶች "ሊቃውንት" ሲባሉ እንዲሁ በእውቀት ብቻ የበሰሉ እንዳይመስሉን:: ፫፻፲፰ [318]ቱ አበው እኩሎቹ በዘመነ ሰማዕታት እጅና እግራቸውን የተቆረጡና ለሃይማኖታቸው ብዙ ዋጋ የከፈሉ ናቸው::

እኩሎቹ ደግሞ በገዳማዊ ሕይወት ያጌጡ: ፍቅረ ክርስቶስ በውስጣቸው የሚነድ: የመንፈስ ቅዱስ ቤት ናቸው:: እስኪ እናውቃቸው ዘንድ የጥቂቶችን ማንነት በስምና በመገለጫ እንመልከት :-

፩. ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ [በዘመነ ሰማዕታት ለ፳፪ [22] ዓመት ሲቆራርጡት ኖረው በጉባኤው ላይ የተገኘው ያለ እጅ: እግር: ጀሮ: ከንፈር: ቅንድብ ነው]

፪. ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ [ስለ ቀናች እምነት ለ፶ [50] ዓመታት የተጋደለና ለ፲፭ [15] ዓመታት በስደት የኖረ ነው]

፫. ቅዱስ እለእስክንድሮስ ሊቅ [ከሰማይ ብርሃን ይወርድለት የነበረ አባት ነው]

፬. ቅዱስ ቴዎዶስዮስ [በምድረ ቆረንቶስ መከራን የተቀበለ]

፭. ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ [በጸሎቱ አጋንንትን ያንቀጠቀጠ: ነፍሳትን ከሲዖል የቀማና ከከዊነ እሳት የደረሰ አባት ነው]

፮. ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘአርማንያ [ስለ ቀናች እምነት መጸዳጃ ጉድጓድ ውስጥ ለ፲፭ [15] ዓመታት ተጥሎ የኖረ ሰማዕት ነው]

፯. ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሜራ [ከሕፃንነቱ የተቀደሰ: በበርሃ የተጋደለ: በዘመነ ሰማዕታት ብዙ መከራን የተቀበለ አባት ነው]

፰. ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን [በደግነቱ ሙታንን ያስነሳ: ወንዝን በጸሎቱ ያቆመ: በንጽሕና የተጋደለ አባት ነው]

፱. ቅዱስ ሶል ጴጥሮስ [ቅዱሱን ንጉሥ ያጠመቀ: ቁስጥንጥንያን በወንጌል ያበራ ሊቅ ነው]

፲. ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ [ስለ ቀናች እምነቱ ብዙ ግፍ የደረሰበትና በስደት ያረፈ አባት ነው]

ለአብነት እንዲሆኑን እነዚህን አነሳን እንጂ ፫፻፲፰ [318] ቱም ሊቃውንት ስለ ቤተ ክርስቲያን ተግተው የተጋደሉ: ብዙ ዋጋም የከፈሉ አባቶች ናቸው::

በወቅቱ ታዲያ ቤተ ክርስቲያንን የበጠበጡ ብዙ መናፍቃን ቢኖሩም የአርዮስ ግን ከመጠኑ አለፈ:: የእርሱ ኑፋቄ [ፈጣሪያችንን ፍጡር ማለቱ] መነሻው ከእርሱ በፊት ነው:: መናፍቃን ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ቤተ ክርስቲያንን ሲያውኩ መኖራቸው ግልጽ ነው::

በተለይ ደግሞ ቢጽ ሐሳውያንና ግኖስቲኮች የወለዷቸው እሾሆች አባቶቻችንን እንቅልፍ ነስተው ነበር:: የሚገርመኝ በዘመኑ እንደ ነበሩ መናፍቃን ኃይለኝነት የእኞቹ ከዋክብት ሊቃውንት ባይኖሩ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ያሳስብ ነበር::

ግን እግዚአብሔር ለሁሉ እንደሚገባ ያዘጋጃልና አበው ብርቱ መናፍቃንን በብርቱ መንፈሳዊ ክንድ እያደቀቁ ከጐዳና አስወገዷቸው:: የዛሬውን ደካማ ትውልድ ደግሞ የአርዮስ ልጆች ፪ [2] [3] ጥቅስ ይዘው ሲያደናብሩት ይውላሉ::

ሐረገ መናፍቃን በርጉም ሳምሳጢ ጳውሎስ: በመርቅያንና በማኒ ይጀምራል:: በእርግጥ አርጌንስ እና የግብጹ ቀሌምንጦስም ተቀላቅለዋቸዋል:: ርጉም ሳምሳጢ ድያድርስን በኑፋቄ ወልዶታል:: ድያድርስ ሉቅያኖስን: ሉቅያኖስ ደግሞ አርዮስን ወልደዋል::

ይህ አርዮስ እጅግ ተንኮለኛ በመሆኑ ልክ እንደ ዘመኑ መሰሎቹ ግጥምና ዜማ እየጻፈ በየመንገዱ እያደለ: በየቤቱ እየሰበከ ብዙዎችን በኑፋቄው በከለ:: በመጀመሪያ ተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ [አስተማሪው] መከረው:: ባይሰማው ከአንዴም ሁለት ጊዜ አወገዘው::

ቆይቶ ሰነፉ ጳጳስ አኪላስ ቢፈታውም ሊቁ ቅዱስ እለእስክንድሮስ እንደ ገና አወገዘው:: እንደ አርዮስ ሐሳብ መድኃኒታችን ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ አይደለም [ሎቱ ስብሐት!] ማለት ክርስትናን ከሥሩ ፈንቅሎ መጣል ነው::

ስለ ክርስቶስ እግዚአብሔርነት ብሉይም ሐዲስም እየመሰከሩ [ኢሳ.፱፥፮, መዝ.፵፮፥፭, ፸፯፥፷፭, ዘካ.፲፬፥፬, ዮሐ.፩፥፩, ፲፥፴, ራዕይ.፩፥፰, ሮሜ.፱፥፭] አርዮስና የዛሬ መሰሎቹ አንዲት ጥቅስ ይዘው ክርስትናን ከመሠረቱ ለመናድ መሞከራቸው በእርግጥም ከሰይጣን መላካቸውን ያሳያል::

በወቅቱም በመወገዙ "ተበደልኩ" ብሎ የጮኸው አርዮስ ከሁለቱ አውሳብዮሶች ባልንጀሮቹ [ዘቂሣርያና ዘኒቆምድያ] ጋር ሆኖ ወደ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ሔዶ ከሰሰ:: ቅዱሱ ንጉሥም የጉዳዩን ክብደት ተመልክቶ የዓለም ሊቃውንት ይሰበሰቡ ዘንድ አዘዘ::

ከሚያዝያ ፳፩ [21] እስከ መስከረም ፳፩ [21] ተጠቃለው ገቡ:: በ፫፻፳፭ [325] ዓ/ም [በእኛው በ፫፻፲፰ [318] ዓ/ም] ለ፵ [40] ቀናት የሚቆይ ሱባኤን ያዙ:: ሱባኤውን ሲጨርሱም በአራቱ ፓትርያርኮች [እለእስክንድሮስ: ሶል ጴጥሮስ: ዮናክንዲኖስና ኤዎስጣቴዎስ] መሪነት: በእለእስክንድሮስ ሊቀ መንበርነት: በአትናቴዎስ ጸሐፊነት ጉባኤው ተጀመረ::

በጉባኤው ሙሉ ስልጣን በሰማይ ከፈጣሪ: በምድር ከንጉሡ የተሰጣቸው አበው አርዮስን ተከራክረው ከነ ጀሌዎቹ ምላሽ አሳጡት:: ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ: ሥግው ቃል: ራሱም እግዚአብሔር መሆኑን አስረዱት::

በጉባኤው መጨረሻም :-

፩. አልመለስም በማለቱ አርዮስን አወገዙ::
፪. ጸሎተ ሃይማኖትን "ለመንግስቱም ፍጻሜ የለውም" እስከሚለው ድረስ ተናገሩ::
፫. ፍትሐ ነገሥትን ሥጋዊና መንፈሳዊ ብለው አዘጋጁ::
፬. ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እንደሚገባ አደራጁ::
፭. በስማቸው የሚጠራ አንድ ቅዳሴን ደረሱ::

ይህ ሁሉ ሲሆን መድኃኒታችን ክርስቶስ 319ኛ ሆኖና ገሊላዊ ጳጳስን መስሎ ሁሉን አከናውኖላቸዋል:: አባቶችም ሥራቸውን ከጨረሱ በኋላ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስን ባርከው ወደየ ሃገረ ስብከታቸው ተመልሰዋል:: ለክብረ መንግስተ ሰማያት በቅተዋል:: እኛም እነሆ "አባቶቻችን:
መምሕሮቻችን:
መሠረቶቻችን:
ብርሃኖቻችን:
ምሰሶዎቻችን" እያልን እናከብራቸዋለን::
ቅዱስ ቴዎዶስዮስ የቆረንቶስ ጳጳስ ሲሆን በዘመነ ሰማዕታት ብዙ መከራን አሳልፎ ከሰማዕታት ተቆጥሯል:: ነገር ግን አልተሰየፈም ነበርና እስከ ጉባኤ ኒቅያ ቆይቶ የጉባኤው ተሳታፊ ሆነ::

ከጉባኤው በኋላ ቅዱስ ቴዎዶስዮስ ወደ ሃገሩ ቆረንቶስ ተመልሶ : ሕዝቡን ሲመክር ቆይቶ በዚህች ቀን በመልካም ሽምግልና አርፏል::

† አምላከ ቅዱሳን ሊቃውንት በጸሎታቸው እኛንም: ቤተ ክርስቲያናችንንም ከክፉ ጠላት ይጠብቅልን::

🕊

[ † መጋቢት ፮ [ 6 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ቴዎዶስዮስ ተአማኒ [ዘቆረንቶስ]
፪. ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ሰማዕት [ አማሌቃውያን የገደሉት ]
፫. አባ ዘሩፋኤል ጻድቅ
፬. አባ እንጦንስ ገዳማዊ
፭. አባ አርከሌድስ ገዳማዊ
" በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም ፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ " [ ኤፌ.፬፥፪ ]

[ † ወርኀዊ በዓላት ]

፩. ቅድስት ደብረ ቁስቋም
፪. አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
፫. አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
፬. ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
፭. ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
፮. ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
፯. ቅድስት ሰሎሜ
፰. አባ አርከ ሥሉስ
፱. አባ ጽጌ ድንግል
፲. ቅድስት አርሴማ ድንግል

† "እውነት እላቹሃለሁ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል:: በምድርም የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል:: ደግሞ እላቹሃለሁ . . . ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና::" † [ማቴ. ፲፰፥፲፰]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬
💖                    🕊                     💖
🕊

✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞

መጋቢት ፯ [ 7 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

✞ ሰማዕትነት በቅዱስ ቴዎዶጦስ ሕይወት ✞


🕊  †  ቅዱስ ቴዎዶጦስ  †  🕊

በ፫ [3] ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ጊዜው ለክርስቲያኖች ሁሉ ፍጹም የመከራ ከመሆኑ የተነሳ "ዘመነ-ሰማዕታት" ሲባል በወቅቱ ከ፵፯ [47] ሚሊዎን በላይ ክርስቲያኖች ተጨፍጭፈዋል::

የዘመኑ ክርስቲያኖች ለመሞት የሚያደርጉትን እሽቅድምድም እያዩ አሕዛብ "ወፈፌዎች" እያሉ ይጠሯቸው ነበር:: [ዓለም እንዲህ ናትና!] እብዶቹ ጤነኞችን "እብድ" ማለታቸውኮ ዛሬም አለ::
[ለነገሩ "ግደልና ጽደቅ" ከሚል መመሪያ በላይ ጤና ማጣት አይኖርም)]

ታዲያ በወቅቱ አንድ ቴዎዶጦስ የሚሉት ወጣት በምድረ ግብጽ ይኖር ነበር:: ወጣቱ እጅግ ብርቱ ክርስቲያን ነበርና እንደ ዘመኑ ልማድ ተከሦ በነፍሰ ገዳዮች ፊት ቀረ:: ክሱ አንድ ብቻ ነው:: "ክርስቶስን አምልከሃል" የሚል::

ከሥጋ ሞት ለማምለጥ ደግሞ መንገዱ ያው አንድ ብቻ ነው:: ፈጣሪውን ክርስቶስን ክዶ ለአሕዛብ አማልክት [ አጋንንት ] መገዛት:: ቅዱስ ቴዎዶጦስ በገዳዮቹ ፊት ቆሞ ተናገረ :-
"እኔ ክርስቲያን ክርስቶሳዊ የክርስቶስ ነኝ:: ምንም ብታደርጉኝ ከክርስቶስ ፍቅር ልትለዩኝ አትችሉም"[ሮሜ.፰፥፴፭] አላቸው::

እነሱ ግን ነገሩ እውነት አልመሰላቸውምና ሊያሰቃዩት ጀመሩ::
- ገረፉት
- አቃጠሉት
- ደበደቡት
- ሌላም ሌላም ማሰቃያዎችን በእርሱ ላይ ተጠቀሙ:: የሚገርመው ግን እሱ ሁሉን ሲታገሥ ገዳዮቹ ግን ደከሙ::

በመጨረሻም ወደ ገዢው ዘንድ አቅርበው "ብዙ አሰቃይተነዋል:: ግን ሊሳካልን አልቻለም" በሚል ሰይፍ [ሞት] ተፈረደበት:: በአደባባይ ሊሰይፉት ሲወስዱት ግን ትንሽ አዘኑለት መሰል ጨርቅ አምጥተው "ፊትህን ሸፍን" አሉት:: [ያኔ ትንሽም ቢሆን ሰብአዊነት ሳይኖር አይቀርም]

ቅዱስ ቴዎዶጦስ ግን ገዳዮቹን በመገረም እየተመለከታቸው ተናገረ:- "እኛ ክርስቲያኖች ሞትን አንፈራም:: ሞት ለእኛ ወደ ክርስቶስ መሸገጋገሪያ ድልድያችን ነውና የምንፈራው ሳይሆን የምንናፍቀው ነው::" "ኢትፍርሕዎሙ [አትፍሯቸው]" [ማቴ.፲፥፳፰]

ይህን ብሎ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ጌታውን አመሰገነ:: ፊቱ ላይ ደስታ እየተነበበ ጨካኞቹ አንገቱን ሰየፉት:: በብርሃን አክሊልም ቅዱሳን መላእክት ከለሉት::
- መሠረታዊው ነገር ቅዱስ ቴዎዶጦስ ለምን አልፈራም? ነው::

አጭር መልስ ካስፈለገን ቅዱሱ ያልፈራው ከልቡ ክርስቶሳዊ በመሆኑ ነው:: ትኩረት እንድንሰጠው የሚያስፈልገው ግን የሰማዕታት ምስጢራቸው :-

፩. በጽኑ የክርስትና መሠረት ላይ መመሥረታቸው
፪. ዕለት ዕለት የክርስቶስን ፍቅር መለማመዳቸው
፫. ከወሬ [ንግግር] ይልቅ ተግባርን መምረጣቸው
፬. በንስሃ ሕይወት መመላለሳቸው
፭. ሥጋ ወደሙን የሕይወታቸው ዋና አካል ማድረጋቸው
፮. ከእነሱ የቀደሙ ቅዱሳንን ዜና ሕይወት ከልብ ማንበባቸው
፯. በቃለ እግዚአብሔር መታነጻቸው . . . መጠቀስ የሚችሉ መገለጫዎቻቸው ናቸው::

" ዛሬስ "

ዓለማችን ከጠበቅነው በላይ ነፍሰ በላነቷ እየጨመረ ነው:: ዛሬ የክርስትና ጠላቶች ከጉንዳን በዝተዋል::
- የራሳችን ማንነት
- ክርስትናችን በአፋችን ላይ ብቻ መሆኑ
- እረኞችና በጐች መለያየታቸው . . . ሁሉ እኛ ልናርማቸው የሚገቡ ናቸው::
- አሸባሪዎች
- አሕዛብ
- የመዝናኛው ዓለም
- ሰይጣን አምላኪ ዝነኞች [Celebrities]
- ሚዲያው
- ማሕበራዊ ድረ ገጾችና መሰል ነገሮች ደግሞ ልንጠነቀቅባቸው የሚገቡና እኛን ውስጥ ለውስጥ በልተው የፈጁን የሰይጣን መሣሪያዎች ናቸው::

ስለዚህም ከዛሬ ጀምረን ባለ መታወክ ክርስትናችንን ከአፋችን ወደ ልባችን: ከብዕራችን ወደ አንጀታችን እንድናወርደው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አደራ ትላለች::

ዛሬ ነገሮችን ረስተን ሌሎች አላስፈላጊ ነገሮችን ከጀመርን እጅግ አሳፋሪ መሆኑ አይቀርም:: በጐውን ጐዳና ተከትለን በሃይማኖትና በፍቅረ ክርስቶስ ከጸናን ግን ማንም ቢመጣም ፈጽሞ አንናወጥም::

ይልቁኑ

"አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን:
ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው:: ስለዚህም ምድር ብትነዋወጥ: ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም::" [መዝ.፵፮፥፩] እያልን ከቅዱስ ዳዊት ጋር እንዘምራለን::

" ለዚህ ደግሞ ደመ ሰማዕታት ይርዳን:: በረከታቸው ይድረሰን:: የጌታ ፍቅርም አይለየን "


🕊  † ጻድቁ ንጉሥ ቴዎድሮስ †  🕊

በሃገራችን ታሪክ በጣም ተወዳጅ ከነበሩ ነገሥታት ጻድቁ ቴዎድሮስ ቅድሚያውን ይወስዳል:: በርግጥ በርካቶቻችን የምናውቀው ስለ ሃገሩ ፍቅር ራሱን የሰዋውን ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስን [1845-1860] ነው:: በበጎ ሥራውና በቅድስና ሕይወቱ የተመሠከረለት ግን ዛሬ የምናስበው ቀዳማዊው ነው::

ቀዳማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ የደጉ ዐፄ ዳዊት [ግማደ መስቀሉን ያመጡት] እና የተባረከችው ሚስታቸው ፅዮን ሞገሳ ልጅና የጻድቁ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ታላቅ ወንድም ነው:: በኢትዮዽያ ለ፫ [3] ዓመታት [ከ1396-1399] ብቻ ነግሦ እያለ እንደ ንጉሥ ሳይሆን-

- ከጠዋት እስከ ማታ ድሃ እንዳይበደል ፍርድ እንዳይጉዋደል ይታትር የነበር::
- ጾምና ጸሎትን የሚያዘወትር::
- ወገቡን ታጥቆ ነዳያንን የሚያበላ::
- ለአብያተ ክርስቲያናትም የሚጨነቅ ደግ ሰው ነበር::

- ስለዚህም በሕዝቡ እጅግ ተወዳጅ ነበር:: በነገሠ በ፫ [3] ዓመቱ ዐርፎ በዝማሬና በለቅሦ ሥጋውን ተሸክመው ሲሔዱ ወንዝ ተከፍሎላቸዋል:: ከመቃብሩም ላይ ጸበል ፈልቁዋል::

ዘለዓለም ሥላሴ ደግ መሪና ሰላማዊ ዘመንን ያድሉን::

🕊

[ † መጋቢት ፯ [ 7 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ጻድቁ ኢትዮዽያዊ ንጉሥ ዐፄ ቴዎድሮስ
፪. ቅዱስ ቴዎዶጦስ ሰማዕት
፫. ቅዱስ ፊልሞን ሰማዕት
፬. ቅዱስ አብላንዮስ ሰማዕት

[ † ወርሐዊ በዓላት ]

፩. ሥሉስ ቅዱስ [ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ]
፪. አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
፫. አባ ሲኖዳ [ የባሕታውያን አለቃ ]
፬. አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
፭. አባ ባውላ ገዳማዊ
፮. ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
፯. ቅዱስ አግናጥዮስ [ ለአንበሳ የተሰጠ ]

" ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ:: ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና:: ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው:: ስለዚህ ባ ለሥልጣንን የሚቃወም የእግዚአብሔርን ሥርዓት ይቃወማል:: . . . ለሁሉ እንደሚገባው አስረክቡ:: ግብር ለሚገባው ግብርን: ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን: መፈራት ለሚገባው መፈራትን: ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ::" [ሮሜ.፲፫፥፩-፰]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬
💖                    🕊                     💖
#ሥላሴ አንድ ሲሆኑ ሦስት፤ ሦስት ሲሆኑ አንድ ናቸው።
ሥላሴ፤ በሥም፤ በአካል፤ በግብር፤ ሦስት ናቸው።
#የስም_ሦስትነታቸውም፤ አብ፤ ወልድ፤ መንፈስ ቅዱስ ነው ። (ማቴ 28፥19)
#የአካል_ሦስትነታቸው፤ አብ የራሱ የሆነ አካል አለው፤ ወልድ የራሱ የሆነ አካል አለው፤ መንፈስ ቅዱስ የራሱ የሆነ አካል አለው። (ማቴ 3፥ 16-17)
#የግብር_ሦስትነታቸውም፤ አብ አባት፤ ወልድ ልጅ፤ መንፈስ ቅዱስ ሰራፂ ነው
አብ ወልድን ወለደ ማለት ከአካሉ ከባሕርይው ተገኘ ማለት ነው።

#አብ_መንፈስ_ቅዱስን አሰረጸው ማለት ከአካሉ ከባሕርይው ተገኘ ማለት ነው። ለምሳሌ የነፍስ ልብነቷ ሕይወቷን እንዳስገኘው ነው። መንፈስ ቅዱስ ከአብ ሰረጸ ሲባል አብን አህሎ መስሎ ከአብ ተገኘ ማለት ነው። (ዮሐ 15፥16)
አምላካችን ሥላሴ በመለኮት፤ በአገዛዝ፤ በሥልጣን፤ ይህን ዓለም በመፍጠርና በማሳለፍ ደግሞ አንድ ናቸው። ያለፈው ሺህ ዘመን በፊትህ እንደ ትላንት ቀን የሆነ፤ የሚመጣውም ሺህ ዘመን በፊትህ እንደ ነገ የቀረበ እድሜን ሰጪ፣ ጸጋን አዳይ የሆንከው ጌታ ልዑል እግዚአብሔር ሆይ እናመሰግንሃለን። የነቢያት ትንቢት፣ የሐዋርያት ስብከት፣ የሊቃውንት ትምህርት፣ የዘማርያን ቅኔ፣ የምእመናን መገዛት፣ የሰማዕታት ኅልፈት፣ የጻድቃን አኗኗር፣ የደናግል ንጽሕና አንተን አይገልጥህምና
የሞትክልን ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ እናሰግንሃለን፡፡ የስደተኞች አገር፣ የእንግዶች ማረፊያ፣ የሐዘንተኞች
መጽናናት፣ የደካሞች ብርታት አጽናኝ ጌታ እግዚአብሔር
መንፈስ ቅዱስ ሆይ እናመሰግንሃለን ለዘለዓለሙ አሜን
ክብር ፣ኃይል፣ ምስጋና ለአምላካችን ለሥላሴ ይገባል 🙏

        
#ሰናይ___ቀን🙏

አጫጭር ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶች
      •➢ 👇  ለማግኘት // 👇

@Enatachn_mareyam  
@Enatachn_mareyam
🕊

[ † እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ማትያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †


🕊  ሐዋርያው ቅዱስ ማትያስ  🕊

† በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ ከእመቤታችን በቀር ከቅዱሳን ሐዋርያት የሚበልጥ አልተነሳም:: "ሐዋርያ" ማለት "ፍንው: ልዑክ: የተላከ: የጽድቅ መንገደኛ" እንደ ማለት ነው:: በምሥጢሩ ግን "ባለሟል" ብለው ሊቃውንቱ ተርጉመውታል::

ይህስ እንደምን ነው ቢሉ :-

¤የፍጥረታት ሁሉ ጌታ: የክብር ባለቤት መድኃኔ ዓለም ከድንግል ማርያም ተወልዶ: አድጐ: ተጠምቆ: ጾሞ: ከገዳመ ቆረንቶስ ሲመለስ ቀዳሚ ሥራው ያደረገው ደቀ መዛሙርቱን መጥራት ነበር::

ከተከተሉት የ፭ [5] ገበያ ሕዝብ መካከል "ወሐረየ እምሰብአ ዚአሁ አሠርተ ወክልኤተ ሐዋርያተ" እንዲል በመጀመሪያ ፲፪ [12] ቱን ሐዋርያት መረጠ::

† እሊህም :-

፩. ዼጥሮስ የተባለ ስምኦን
፪. እንድርያስ [ወንድሙ]
፫. ያዕቆብ ወልደ ዘብዴዎስ
፬. ዮሐንስ [ወንድሙ]
፭. ፊልዾስ
፮. በርተሎሜዎስ
፯. ቶማስ
፰. ማቴዎስ
፱. ያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ
፲. ታዴዎስ [ልብድዮስ]
፲፩. ናትናኤል [ቀናተኛው ስምዖን] እና
፲፪. ማትያስ [በይሁዳ የተተካ] ናቸው:: [ማቴ.፲፥፩] [10:1]

† እነዚህን ፲፪ [12] አርድእቱን ከጠራ በሁዋላ ለ፫ [3] ዓመታት ከ፫ [3] ወራት ከዋለበት ሲማሩ ይውሉ ነበር:: ሌሊት ደግሞ ምሥጢር ሲያስተረጉሙ ያድሩ ነበር::

ጌታ እንደሚገባ ካስተማራቸው በሁዋላ ከፍ ያለ ኃላፊነትን ሾማቸው:: ለዓለም እረኞች: የእርሱም ባለሟሎች ሆኑ:: እጅግ ብዙ መከራ እንደሚገጥማቸው ነገራቸው:: [ማቴ.፲፥፲፮] (10:16), [ዮሐ.፲፮፥፴፫] (16:33) በዚያው ልክ ክብራቸውንም አከለላቸው:: [ማቴ.፲፱፥፳፰] (19:28)

ሥልጣናቸው ደግሞ እስከዚህ ድረስ ሆነ:: "በምድር ያሠራችሁት በሰማይ የታሰረ ይሆናል: በምድር የፈታችሁት በሰማይ የተፈታ ይሆናል::" [ማቴ.፲፰፥፲፰] (18:18) "ይቅር ያላችሁዋቸው ኃጢአታቸው ይቀርላቸዋል: ያላላቹሃቸው ግን አይቀርላቸውም::" [ዮሐ.፳፥፳፫] (20:23)

የመንግስተ ሰማያትን መክፈቻ [ማቴ.፲፮፥፲፱] (16:19): እረኝነትን [ዮሐ.፳፩፥፲፭] (21:15) ተቀበሉ:: ጌታ በንጹሕ አንደበቱ ሐዋርያቱን እጅግ ሲያከብራቸው "ጨው: የዓለም ብርሃናት" [ማቴ.፭፥፲፫] (5:13) አላቸው:: ወንድሞቹም ተባሉ:: [ዮሐ.፯፥፭] [7:5] ከዚህም በሚበልጥ በሌላ ክብር አከበራቸው::

ከዚህ ሁሉ ነገር በሁዋላ በጌታ ሕማማት ጊዜ ገና ነበሩና አንዳንዶቹ ፈርተው ተበተኑ:: ተመልሰው ግን በጽርሐ ጽዮን ሲጸልዩ ሰንብተው የጌታን ትንሳኤ ተመለከቱ:: እጆቹን: እግሮቹንም ዳስሰው ሐሴትን አደረጉ::

ለ ፵ [40] ቀናት መጽሐፈ ኪዳንን: ትምሕርተ ኅቡዓት: ሌላም በፍጡር አንደበት የማይነገር ብዙ ምሥጢራትን ተምረው: ጌታ ሊቀ ዽዽስናን ሹሟቸው ዐረገ::

ለ ፲ [10] ቀናት በእመ ብርሃን ሥር ተጠልለው ሲጸልዩና በአንድ ልብ ሲተጉ ሰንብተው መንፈስ ቅዱስ ወረደላቸው:: በአንዴም ከፍርሃት ወደ ድፍረት ተመልሰው ፍጹማን: ብርሃናውያን ሆኑ:: ፸፩ [71] ልሳናትን ነስተው በአንዲት ስብከት ብቻ 3ሺ ነፍሳትን ማረኩ:: [ሐዋ.፪፥፵፩] (2:41)

ቅዱሳን ሐዋርያት በኅብረት ለአንድ ዓመት ያህል በኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ እየተመላለሱ አስተምረው ብዙ እሥራኤላውያንን ወደ ክርስትና ማርከዋል:: ከዚህ በሁዋላ ግን እንደ ትውፊቱ ዓለምን በእጣ ለ ፲፪ [12] ተካፈሏት::

ይህ ሲሆን መንፈስ ቅዱስ አብሯቸው ነበርና ለእያንዳንዳቸው እንደሚገባቸው አሕጉረ ስብከቶች ደረሷቸው:: እነርሱም ደቀ መዛሙርቶቻቸውን አስከትለው ለታላቁ መንፈሳዊ ዘመቻ ወረዱ::

በሔዱበት ቦታም ከተኩላ: ከአንበሳና ከነምር ጋር ታገሉ:: በጸጋቸውም አራዊትን [ክፉ ሰዎችን] ወደ በግነት መልሰው ለክርስቶስ አስረከቡ:: በየሃገሩ እየሰበኩ ድውያንን ፈወሱ:: ለምጻሞችን አነጹ:: እውራንን አበሩ:: አንካሶችን አረቱ:: ጐባጦችን አቀኑ:: ሙታንንም አስነሱ:: እልፍ አእላፍ አሕዛብንም ወደ መንጋው ቀላቀሉ::

ስለዚህ ፈንታም ብዙዎቹ በእሳት ተቃጠሉ:: ቆዳቸው ተገፈፈ:: በምጣድ ተጠበሱ:: ደማቸው በምድር ላይ ፈሰሰ:: ከአንድ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በቀር ሁሉም ይህችን ዓለም በሰማዕትነት ተሰናበቱ:: ጨው ሆነው አጣፍጠዋልና: ብርሃንም ሆነው አብርተዋልና እናከብራቸዋለን:: "አባቶቻችን: መምሕሮቻችን: ጌቶቻችንና ሊቆቻችን" እንላቸዋለን::

ቅዱስ ማትያስ ስም አጠራሩ ይክበርና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተሰቦቼ ብሎ ከመረጣቸው ፻፳ [120] ቅዱሳን አንዱ : ፫ [3] ዓመት ከ፫ [3] ወር ከጌታችን እግር ቁጭ ብሎ የተማረ: በይሁዳ ፈንታ ከ፲፪ [12]ቱ ሐዋርያት ይቆጠር ዘንድ መንፈስ ቅዱስ የመረጠው ሐዋርያ ነው::

ቅዱሱ ሐዋርያ በዕጣ በደረሰው ሃገረ ስብከቱና በሌሎቹም ዓለማት ለወንጌል አገልግሎት ብዙ ደክሙዋል:: በተለይ የሰውን ሥጋ ወደሚበሉ ሰዎች ሃገር ገብቶ ወንጌልን ቢሰብክላቸው ዓይኖቹን አውጥተው ከብዙ ስቃይ ጋር ለ ፴ [30] ቀናት ሣር አብልተውታል::

እሱ ግን በትእግስትና በፈጣሪው ኃይል ድንቅ ተአምር አድርጐ አሳምኖ አጥምቋቸዋል:: ከብዙ ተጋድሎና ቅድስና በሁዋላም በዚሕች ቀን በመልካም ሽምግልና አርፏል::

† አምላከ ቅዱሳን ሐዋርያት ቸርነቱን ያብዛልን:: በምልጃቸው ከክፉ ጠብቆ ከበረከታቸው ይክፈለን::

🕊

[ † መጋቢት ፰ [ 8 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ [ከ፲፪ [12] ቱ ሐዋርያት]
፪. ቅዱስ አርያኖስ ሰማዕት [በዘመነ ሰማዕታት ብዙ ክርስቲያኖችን ያሳድድ የነበረና ጌታ በንስሃ የጠራው]
፫. ቅዱስ ዮልዮስ ሊቀ ዻዻሳት

[ † ወርሐዊ በዓላት ]

፩. ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
፪. ኪሩቤል [አርባዕቱ እንስሳ]
፫. አባ ብሶይ [ቢሾይ]
፬. አቡነ ኪሮስ
፭. አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን

" . . . እንዲህም ብለው ጸለዩ:: 'አቤቱ ልብን ሁሉ የምታውቅ አንተ ከእነዚህ ከሁለቱ የመረጥከውን አንዱን ግለጥ?' . . . ዕጣ አጣጣሉአቸው ዕጣውም በማትያስ ላይ ወጣ:: ከዐሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋርም ተቆጠረ::" † [ሐዋ.፩፥፳፬]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬
💖                    🕊                     💖
2024/11/18 14:57:55
Back to Top
HTML Embed Code: