Telegram Web Link
🕊

[ † እንኳን ለጻድቁ አባታችን ቅዱስ ጐርጐርዮስ ረዓዬ ኅቡዓት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †


🕊 † ቅዱስ ጐርጐርዮስ ረዓዬ ኅቡዓት † 🕊

† ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሃገሩ ሮሃ [ሶርያ አካባቢ] ሲሆን ረዓዬ ኅቡዓት [ምሥጢራትን የተመለከተ] ይባላል:: ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ :-
ቅዱሱ ተወልዶ ባደገባት ሃገር ይህ ቀረው የማይባል ኃጢአተኛ ሰው ነበር:: ታዲያ ምንም ኃጢአተኛ ሰው ቢሆን እመቤታችን ድንግል ማርያምን በፍፁም ልቡ ይወዳት ነበርና በመዳን ቀን ጥሪ ለንስሐ አበቃችው::

ከዚያች ዕለት ጀምሮም ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰው : ንጹሕ የቤተ ክርስቲያን መስዋዕት : ጽኑዕ የበርሃ ምሰሶ ሆነ:: ድንግል እመቤታችንም ከነሥጋው ወደ ሰማያት ወስዳ ገነትና ሲዖልን አሳይታ : ከአዳም : ኖኅ : አብርሃም : ሙሴ : ዳዊትን ከመሰሉ ቅዱሳን ጋር አስተዋውቃ : ከዚህም በላይ የሆነና በሰብአዊ አንደበት የማይነገር ብዙ ምሥጢር አሳይታ ወደ ምድር መልሳዋለች::

ቅዱስ ጐርጐርዮስ በሰማይ [በገነት] በነበረው ቆይታ ክብረ ቅዱሳንን ተመልክቶ አድንቋል:: በተለይ በፍጹምነት ድንግልናቸውን የጠበቁ ቅዱሳንና ቅዱሳት ደናግል አኗኗራቸው ከአምላክ እናት : ከሰማይ ንግሥት : ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ጋር መሆኑን አይቷል::

"የለበሱት ልብስም በፍጡር አንደበት ተከናውኖ ሊነገር የሚቻል አይደለም" ይላል:: የደናግል ፊታቸው ከፀሐይ ፯ [7] እጅ ያበራልና ግርማቸው ያስፈራል::

ቅዱሱ ሰው በዚያው በሰማይ ሳለ ደግሞ ይህንን ተመለከተ:: አንድ አረጋዊ : ጽሕሙ ተንዠርግጐ : የብርሃን ካባ ላንቃ ለብሶ ይመጣል:: ቅዱሳን መላእክት በፊት በኋላ : በቀኝ በግራ ከበውት ሳለ እግዚአብሔርን ሊያመሰግን ጀመረ::

"እግዚኦ እግዚእነ : ጥቀ ተሰብሐ ስምከ በዲበ ምድር [አቤቱ ጌታችን : በምድር ሁሉ ስምህ የተመሰገነ ሆነ]" ሲል . . . መላእክቱ በዝማሬ አጀቡት:: በዚህ ጊዜም ታላቅ መናወጥ ሆነ:: ደናግሉም የቅዱሱን ሽማግሌ በረከቱን ተሳተፉ::

ይህ አመስጋኝ ሽማግሌ ልበ-አምላክ : ጻድቅ : የዋህና የእሥራኤል ንጉሥ የሆነው ዳዊት ነበር:: በምን ታወቀ ቢሉ :- በበገናው:: አንድም እመቤታችን "አባቴ ዳዊት!" ብላ ስትጠራው ጐርጐርዮስ ሰምቷልና::

በመጨረሻም እመቤታችንን በፍጹም ክብርና ግርማ ተመልክቷት ሐሴትን አድርጓል:: እመ-ብርሃንም "ተወዳጅና ንጹሕ ሰው ነህ" ስትል ቅዱስ ጐርጐርዮስን አመስግናዋለች:: ስለዚህ ዓለምም እንዲህ የሚል መልእክትን ልካለች::

"ልጆቼ ሆይ! ከብርሃን ጨለማን : ከደግነት ክፋትን : ከጽድቅ ይልቅ ኃጢአትን . . . ምነው መምረጣችሁ? እኔ ስለ እናንተ በየቀኑ እየለመንሁ እነሆ አለሁ:: ወደ ጨለማ ገሃነም እንዳትወርዱ እባካችሁ ንስሐ ግቡ !"

ቅድስት ድንግል ማርያም ይህንን ለቅዱሱ ሰው ነግራው : ቅዱስ ዳዊትን አስከትላ : በግሩማን መላእክት ታጅባ ወደ ውሳጤ መንጦላዕት [የእሳት መጋረጃዎች ወደ ተተከሉበት ድንኳን] ገባች:: በዚያም ተመሰገነች::

ለዛም አይደል ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ:- "ይዌድስዋ መላእክት ለማርያም በውስተ ውሳጤ መንጦላዕት : ወይብልዋ : በሐኪ ማርያም ሐዳስዩ ጣዕዋ::" ሲል ያመሰገናት::

ቅዱስ ጐርጐርዮስም ከሰማይ ቆይታ መልስ ያየውን ሁሉ ጽፎ ለአበው ሰጥቷል:: ስለዚህም ረዓዬ ኅቡዓት [ምሥጢራትን ያየ] ይሰኛል:: ቅዱሱ ተረፈ ዘመኑን በተጋድሎ ፈጽሞ በዚህች ቀን አርፏል::

† የቅዱሱ እመቤት ድንግል እመ ብርሃን መዓዛ ፍቅሯን ታብዛልን::

🕊

[ † መጋቢት ፪ [ 2 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ጐርጐርዮስ ረዓዬ ኅቡዓት [ዘሃገረ ሮሃ]
፪. አቡነ መክፈልተ ማርያም ጻድቅ [ኢትዮጵያዊ]
፫. አባ መከራዊ ዘሃገረ ኒቅዮስ [አረጋዊ: ጻድቅ: ጳጳስና ሰማዕት]

[ † ወርኀዊ በዓላት ]

፩. ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
፪. ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ
፫. ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
፬. ቅዱስ አቤል ጻድቅ
፭. ቅዱስ አባ ጳውሊ ገዳማዊ [ታላቁ]
፮. ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
፯. አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ

" ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው:: ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ:: ስለዚህ ግን የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ ምሕረትን አገኘሁ::" † [፩ጢሞ. ፩፥፲፭]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬
💖                    🕊                     💖
🕊

[ † እንኳን ለአባታችን ቅዱስ ቆዝሞስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †


🕊 † ቆዝሞስ ሊቀ ጳጳሳት  †  🕊

† "ጳጳስ" ማለት "አባት - መሪ - እረኛ" ማለት ነው:: በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ በሐዲስ ኪዳን የመንፈሳዊ ስልጣን ደረጃዎች በጥቅሉ ፫ [3] ናቸው:: እነሱም ዲቁና: ቅስና: ጵጵስና ሲሆኑ በሥራቸው ወደ ፱ [9] ያህል ክፍሎች አላቸው:: ከእነዚህም ከፍተኛው ስልጣን ጵጵስና ነው::

ጵጵስና ማለት የክርስቶስን መንጋ እንደ ባለቤቱ አድርጐ መጠበቅ ማለት ነው:: ሥልጣኑ በምድር "ሸክም: ዕዳ" ሲሆን በሰማይ ግን "ክብር" ነው:: ማንም በሥጋው ላይ ካልጨከነ በቀር ጵጵስናን አይመኝም::

ቅዱስ ጳውሎስ "ሠናየ ግብረ ፈተወ - ማንም ጵጵስናን ቢመኝ መልካም ሥራን ተመኘ" [፩ጢሞ.፫፥፩] [3:1] ማለቱን ይዞ "ሹሙኝ" ማለት ወደ ማይጠፋ እሳት የሚያስጥል ከባድ ውሳኔ ነው:: ምክንያቱም አንድ ክርስቲያን የሚጠየቅ በራሱ ኃጢአት ሲሆን አንድ ካህን ደግሞ ስለ ልጆቹ ይጠየቃል:: የከፋው ግን የጳጳሱ ነው::

አንድ ጳጳስ ቢጾም ቢጸልይም እንኳ ለድኅነቱ በቂ አይደለም:: ምክንያቱም በመንበሩ ላይ ያስቀመጠው መንጋውን እንጂ ራሱን እንዲያድን አይደለምና:: ጌታ እንዳለ መልካም እረኛ "ይሜጡ ነፍሶ ቤዛ አባግኢሁ - መልካሙ እረኛ ስለ በጐቹ ቤዛ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ነው::" [ዮሐ.፲ [10] ስለዚህም ክህነት [ጵጵስና] ሐዋርያዊ አገልግሎት ከባድም ኃላፊነት ነው::

አባቶቻችን ሐዋርያትና ተከታዮቻቸው ሐዋርያውያን ታላላቅ የጵጵስና መንበሮችን መሥርተው: ትምሕርቱን ከነ ወንበሩ አስተላልፈዋል:: ከእነዚህ መንበረ ጵጵስናዎች አራቱ የበላይ ናቸው::

እነዚህም የቅዱስ ጴጥሮሱ የሮም: የቅዱስ ዮሐንሱ የአንጾኪያ: የቅዱስ ማርቆሱ የእስክንድርያና የቅዱስ ጳውሎሱ የኤፌሶን መናብርት ናቸው::

እነዚህ መንበሮችም ከክርስቶስ ዕርገት እስከ ፬፻፵፫ [፬፻፶፩] [443 (451] ዓ/ም: ጉባኤ ኬልቄዶን ድረስ በአንድነት ቆይተው ተለያይተዋል:: ከእነዚህ መናብርት መካከል የእስክንድርያው [የግብጹ] እና የአንጾኪያው [የሶርያው] ዛሬም ድረስ በተዋሕዶ እምነት የጸኑ ናቸው::

የእኛ ቤተ ክርስቲያንም ሐዋርያዊት እንደ መሆኗ ሐዋርያትን መስለው: ሐዋርያትን አህለው የተነሱ አበው ጳጳሳትን በየጊዜው በበዓላት ታስባለች: ታከብራለች::

በተለይ ደግሞ የእስክንድርያና የአንጾኪያ በርካታ አባቶችን እናከብራለን:: እነርሱ ለቀናች ሃይማኖትና ለመንጋው ሲሉ ብዙ መከራን በአኮቴት ተቀብለዋልና:: ከእነዚህም መካከል አንዱ ቅዱስ ቆዝሞስ የእስክንድርያ [የግብጽ] ፶፰ [58] ኛ ሊቀ ጳጳሳት የነበረ አባት ነው:: ዘመኑ እስልምና የሰለጠነበት ነበርና በዚያ ጊዜ እረኝነት [ጵጵስና] መመረጥ እንደ ዛሬው ዘመን ሠርግና ምላሽ አልነበረም:: በከሃዲዎች እሳትና ስለት መከራን ለመቀበል መወሰን እንጂ::

ከ6ኛው መቶ ክ/ዘመን በኋላ በዓለማችን ከተነሱ ሊቃነ ጳጳሳት ለግብጻውያኑ ቤተ ክርስቲያን ልዩ ቦታ አላት:: ምክንያቱም በወቅቱ በጎቻቸውን [ምዕመናንን] ለመጠበቅ ከግብጽ ከሊፋዎች የግፍ ጽዋዕን ጠጥተዋልና:: ከነዚህም አንዱ የእመቤታችን ፍቅር የበዛለትና በዚህ ቀን ያረፈው ቅዱስ ቆዝሞስ ነው::

† አምላከ ቅዱሳን ሊቃውንት በጸሎታቸው እኛንም: ቤተ ክርስቲያናችንንም ከክፉ ጠላት ይጠብቅልን::

🕊

[ † መጋቢት ፫ [ 3 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ አባ ቆዝሞስ [የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት]
፪. አባ በርፎንዮስ ክቡር

[ † ወርኀዊ በዓላት ]

፩. በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ
፪. ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫. ቅዱሳን ሊቃነ ካህናት አበው [ዘካርያስና ስምዖን]
፬. አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
፭. አቡነ ዜና ማርቆስ
፮. አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ዘደብረ በንኮል

" ነገር ግን ወንድሞች ሆይ! እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን: መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምናቹሃለሁ:: ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ:: እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና:: በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግርም ተንኮል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉ::" † [ሮሜ ፲፮፥፲፯]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬
💖                    🕊                     💖
የሳምንት 1 ዘወረደ ቻሌንጅ ከዕለታዊ መንፈሳዊ ምግባራት መከታተያ ጋር

1)በዚህ ጾም ከጌታ ዘንድ ምን መቀበል እንደምንፈልግ እናስቀምጥ
2)ማስወገድ የምንፈልጋቸውን ልማዶች/ኃጢአቶችን ለይቶ በማውጣት እግዚአብሔር ድል መንሳትን እንዲሰጠን መለመን

3)በ7ቱ የጸሎት ሰዓታት መጸለይ

4)ይህንን ወቅት በጽሞና እንዳናሳልፍ ከሚያደርጉን የሚያዘናጉ ነገሮች ታቅበን በአንጻሩ የሚያግዙ መጻሕፍትን ማንበብ: መዝሙራትን ማዳመጥ የመሳሰሉትን ማድረግ
41,64 በአቅማችን መስገድ

5)በቤተክርስቲያን በመገኘት የዕለቱን ወንጌል መማር

6)የማቴዎስ ወንጌል 4:1-11 ማስታወሻ በመያዝ ማጥናት
*እነዚን ሁሉ ከምጽዋት ጋር
*ዕለታዊ የመንፈሳዊ ምግባር መከታተያውን ከታች ያገኙታል::
አንደበት ይጹም : ዓይን ይጹም : ጆሮ ይጹም
🕊

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን።

መጋቢት ፬ [ 4 ] [ ድርሳነ መስቀል ]

[ ✞ እንኩዋን ለታላቁ ነቢይ : ጠቢብና የእሠራኤል ንጉሥ "ቅዱስ ሰሎሞን" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞ ]


🕊  † ቅዱስ ሰሎሞን ንጉሠ እሥራኤል †  🕊

-  መፍቀሬ ጥበብ::
¤ ጠቢበ ጠቢባን::
¤ ንጉሠ እሥራኤል::
¤ ነቢየ ጽድቅ::
¤ መስተሣልም [ ሰላማዊ ] . . . እየተባለ የሚጠራው ቅዱስ ሰሎሞን የታላቁ ነቢይና ንጉሥ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት እና የቅድስት ቤርሳቤህ [ ቤትስባ ] ልጅ ነው:: ከ፫ [3] ሺ ዓመታት በፊት የተወለደው ቅዱስ ሰሎሞን እስከ ፲፪ [ 12 ] ዓመቱ ድረስ በቤተ መንግሥት ከአባቱ ጋር አድጉዋል::

ቅዱስ ዳዊት ፸ [ 70 ] ዘመን በሞላው ጊዜ የአካሉን መድከም አይቶ : አዶንያስ በጉልበት እነግሣለሁ ቢልም አልተሳካለትም::

እግዚአብሔር ሰሎሞንን መርጧልና ገና በ፲፪ [12] ዓመቱ ነገሠ:: ልበ አምላክ አባቱ ዳዊት ነፍሱ ከሥጋው ከመለየቷ በፊት መከረው:: "ልጄ ሆይ! ልብህን ስጠኝ:: ፈጣሪህንም አምልክ" አለው::

ቅዱስ ሰሎሞን እንደ ነገሠ በገባዖን ለእግዚአብሔር መስዋዕትን አቀረበ:: ጌታም ተገልጾ "ምን ትፈልጋለህ?" አለው:: ሰሎሞንም ልክ እንደ አባቱ ማስተዋልን : ልቡናን ለመነ:: በዚህም ጌታ ደስ ስለተሰኘ "አልቦ እምቅድሜከ : ወአልቦ እምድኅሬከ - ከአንተም በፊት : ከአንተም በሁዋላ እንዳንተ ያለ ጠቢብና ባለጠጋ ሰው የለም : አይኖርም" ብሎት ተሠወረ:: ቅዱስ ሰሎሞን ለ፵ [40] ዓመታት በእሥራኤል ላይ ነገሠ::

ግሩም በሆነ ፍትሑ : በልዩ ጥበቡ ዓለም ተገዛለት:: እግዚአብሔር የመረጣት የእኛዋ ንግስተ ሳባ / አዜብ / ማክዳም ትፈትነው ዘንድ ሒዳ ምኒልክን [እብነ_መለክን] ጸነሰች:: በሁዋላም ታቦተ ጽዮንና ሥርዓተ_ኦሪት መጣልን::

ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን ድንግል ማርያም ከእነሱ ዘር እንደምትወለድ ነግሮት ነበርና ያበጀሁ መስሎት ሴቶችን አብዝቶ ነበር::

- ነገር ግን :-

¤ አንደኛ ሰው [ሥጋ ለባሽ] ነውና::
¤ ሁለተኛ ደግሞ ከብዙ ሴቶች መካከል ከአንዷ እመ ብርሃን ትገኛለች መስሎት ነበር:: ነገሩ መንገድ ስቶበት ከአሕዛብ [ከፈርዖን ልጅ] ጋር በመወዳጀቱ ለጣዖት አሰገደችው:: እግዚአብሔር እጅግ አዘነ::

በራዕይ ተገልጦ "ስለ ወዳጄ ስለ ዳዊት ስል በአንተ ላይ ክፉን አላደርግም" አለው:: ታላቁ ነቢይ ሰሎሞን ይህንን ሲሰማ ወደ ልቡ ተመለሰ:: ማቅ ለብሶ : አመድ ነስንሶ በፍጹም ልቡ አለቀሰ:: ንስሃ ገባ:: መፍቀሬ ንስሃ ጌታችንም ንስሃውን ተቀበለው::

የይቅርታው መገለጫም ተወዳዳሪ የሌላቸውን ፭ [ 5 ] መጻሕፍት ገለጠለት:: ተናገራቸው:: ጻፋቸው:: እሊሕም :-

፩. መጽሐፈ ጥበብ
፪. መጽሐፈ ተግሣጽ
፫. መጽሐፈ መክብብ
፬. መጽሐፈ ምሳሌ
፭. መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ናቸው::

ቅዱስ ሰሎሞን ልዩ የሆነውን ቤተ መቅደስ በመስራቱም ይደነቃል:: ደጉ ንጉሥ : ጠቢብና ነቢይ ሰሎሞን በዚህች ዕለት በ፶፪ [52] ዓመቱ ዐርፎ ወደ ፈጣሪው ሔዷል:: [እንደ ድርሳነ መስቀል ኢትዮጵያዊ ትውፊት]

ከመፍቀሬ ጥበብ ቅዱስ ሰሎሞን በረከት ይክፈለን፡፡

🕊

[ † መጋቢት ፬ [ 4 ] የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት ]

፩. መፍቀሬ ጥበብ ቅዱስ ሰሎሞን

[ † ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጉዋድ [ወንጌላዊው]
፪. ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
፫. ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
፬. ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ [ሰማዕት]

" የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ:: ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ : ፀሐይ : ጨረቃና ከዋክብትም ሳይጨልሙ . . . አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ : ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ::
ሰባኪው:- "ከንቱ : ከንቱ : ሁሉ ከንቱ ነው" ይላል::
"
[መክ.፲፪፥፩-፱]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬
💖                    🕊                     💖
2024/11/18 17:48:02
Back to Top
HTML Embed Code: