Telegram Web Link
❖ ሐዋርያ ቶማስም ሰምቶ ጸለየ ጋኔኑንም ከእርሷ እንዲወጣ አዘዘው ያንጊዜም በእሳትና በጢስ አምሳል ከሴቲቱ ላይ ወጥቶ ተበተነ ከዚህ በኋላ በክርስቶስ መስቀል በላይዋ አማተበ ሥጋውንና ደሙንም አቀበላት ወደ ዘመዶቿም አሰናበታት።
ልዩ የሆነች በረከቱም በሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ላይ ትደር ለዘላለሙ አሜን።
                     

📌 መጋቢት 14 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ (ጋኔን ያደረባት ሴትን ፈውሶ አሕዛብን ያሳመነበት)
2.ቅዱስ አባ ባጥል ትሩፈ ምግባር (ባንድ ወቅት ከእስክንድርያ ዝሙትን ለማጥፋት የተጋደሉ ጻድቅና አረጋዊ አባት)
3.ቅዱስ ሲኖዳ (ሺኖዳ) ሰማዕት
4.ቅዱስ ቄርሎስ ሊቀ ዻዻሳት

📌 ወርኀዊ በዓላት
1.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል)
2.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
3.ቅዱስ ሲኖዳ (ሺኖዳ) ሰማዕት
4.ቅዱስ ሙሴ (የእግዚአብሔር ሰው)
5.አባ ስምዖን ገዳማዊ
6.አባ ዮሐንስ ጻድቅ
7.እናታችን ቅድስት ነሣሒት
Forwarded from TIKVAH-ETHIOPIA
#Update

" ምዕመናን #ክርስቲያናዊ_አለባበስ ለብሳችሁ እንድትገኙ እና የአቅማችሁን ያህል እድትለግሱ ጥሪ እናቀርባለን " - ማህበረ ቅዱሳን

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን " ኑ ቸርነትን  እናድርግ " በሚል መሪ ቃል ነገ እሁድ ከቀኑ 7:00 ላይ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በሚሊኒየም አዳራሽ ያካሂዳል።

ገቢ ማሰባሰቢያው በሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ባጋጠመው ማኅበራዊ ቀውስና ድርቅ የተጎዱ ወገኖቻችንን፣ ገዳማትና አብነት ት/ቤቶችን ለመደገፍ የሚውል እንደሆነ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ከአዘጋጆቹ ያገኘው መረጃ ያሳያል።

የመግቢያ ትኬቶች በ100 ብር እየተሸጡ ሲሆን ትኬቶቹን ፦
1. በማኅበረ ቅዱሳን ሕንጻ 4ኛ ወለል (ቤተ አብርሃም)
2. በወረዳ ማዕከላት ጽ/ቤቶች  
3. በማኅበረ ቅዱሳን ንዋያተ ቅድሳት መሸጫ ሱቆች
4. በማኅበረ ቅዱሳን ሕንጻ የዕለት ገንዘብ መሰብሰቢያዎች
5. በአሐዱ ባንክ ሁሉም ቅርንጫፎች
6. በሰ/ት/ቤት ጽ/ቤቶች ማግኘት ይቻላል ተብሏል።

ነገ በመግቢያ በር ላይም ትኬት ማግኘት እንደሚቻል ተገልጿል።

ሁሉም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች / ምዕመናን ነገ ወደ ሚሊኒየም አዳራሽ ሲሄዱ ክርስቲያናዊ አለባበስ እንዲለብሱ እና የአቅማቸውን ያህል እንዲለግሱ ጥሪ ቀርቧል።

@tikvahethiopia
†† እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ዓመታዊ የተአምር በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ †††

††† ከ12ቱ ቅዱሳን ሐዋርያት አንዱ የሆነው ቅዱስ ቶማስ ብዙ መከራን በማሳለፉና የጌታችንን ጐን በመዳሰሱ ይታወቃል::

ቅዱስ ቶማስ እንደ ሌሎቹ ሐዋርያት በእሥራኤል ተወልዶ በዚያውም በሥርዓተ ኦሪት አድጐ ገና በወጣትነቱ የሰዱቃውያንን ማሕበር ተቀላቅሏል:: ሰዱቃውያን ሰው ከሞተ በሁዋላ አይነሳም (አልቦ ትንሳኤ) የሚሉ ናቸው:: መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማስተማር ሲጀምር ግን ቅዱስ ቶማስ ከነበረበት ማሕበር ወጥቶ ጌታችንን ተከተለ:: ጌታችንም ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ ይሆን ዘንድ ሾመው:: የቀደመ ስሙ "ዲዲሞስ" ሲሆን ጌታችን "ቶማስ" ብሎታል::

ቅዱስ ቶማስ ጌታ አልዓዛርን ለማስነሳት በሔደ ጊዜ ሌሎች ሐዋርያት ጌታን "አይሁድ ይገድሉሃል ቅር" ሲሉት እርሱ ግን "እንሒድና አብረን እንሙት" ሲል ፍቅሩን አሳይቷል:: (ዮሐ. 11:16)

ጌታችን ትንሳኤውን ለደቀ መዛሙርቱ በገለጠ ጊዜ ያልነበረው ቶማስ ካላየሁ አላምንም አለ:: ምክንያቱም:-
1.ለጌታችን ከነበረው ፍቅር የተነሳ እውነት አልመስልህ ቢለው::
2.አንድም ሌሎቹ ሐዋርያት "ትንሳኤውን አየን" እያሉ ሲያስተምሩ እኔ ግን "ሰማሁ" ብየ ማስተማሬ ነው ብሎ በማሰቡ ነበር::

ለጊዜው ጌታ ተገልጾ ቢገስጸው "እግዚእየ ወአምላኪየ (ጌታየና አምላኬ)" ብሎ ፍጹም ሃይማኖቱን ገልጿል:: ለፍጻሜው ግን የጌታችንን ጎን (መለኮትን) ይዳስስ ዘንድ ባለቤቱ እንዳደለው ያጠይቃል:: መለኮትን የዳሰሰች ይሕቺ ቅድስት እጁ ዛሬም ድረስ ሕያው ናት:: በሕንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥም በክብር ተቀምጣለች::

ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ሐገረ ስብከት ሲከፋፈሉ ለቅዱስ ቶማስ ሕንድና በዙሪያዋ ያሉ ሃገራት ደረሱት:: ከዚህ በሁዋላ ነው እንግዲህ ዘርዝረን የማንጨርሰውን ተጋድሎ የፈጸመው:: ቅዱሱ በነበረው ፍጹም ትጋት አባቶቻችን "ዘአሠርገዋ ለብሔረ ሕንደኬ (ሕንድን በወንጌል ያስጌጣት)" ሲሉ ያከብሩታል::

ቅዱስ ቶማስ ንጉሥ ሉክዮስንና የሃገሩን ሕዝብ ለማሳመን በችንካር መሬት ላይ ወጥረው ቆዳውን ገፈውታል:: ቆዳውንም እንደ ገና ሰፍተው: አሸዋ ሞልተው አሸክመውታል:: በየመንገዱ የተገፈፈ ገላውን ጨው ቢቀቡት በጎች መጥተው ግጠው በልተውታል:: በዚሕ ምክንያት:-
"ኩሉ የአኪ እንዘ የአኪ ዘመኑ::
አባግዒሁ ለቶማስ እስመ አራዊተ ኮኑ::" ብለዋል ሊቃውንቱ::

በሁዋላ ግን ከፎቅ ወድቃ የሞተችውን የንጉሡን ሚስት በተገፈፈ ቆዳው በማዳኑ ሁሉም አምነው ተጠምቀዋል::

ቅዱሱ ሐዋርያ ልክ እንደ ቅዱስ ዻውሎስ አንዳንዴ በፈሊጥ: ሌላ ጊዜም በመከራ ለወንጌልና ለቤተ ክርስቲያን ተጋድሏል:: ያለ ማቁዋረጥም ከሕንድ እስከ ሃገራችን ኢትዮዽያ ድረስ ለ38 ዓመታት ወንጌልን ሰብኩዋል::

በመጨረሻም በ72 ዓ/ም በሰማዕትነት አርፏል:: መቃብሩና ቅድስት እጁ ዛሬ ድረስ ሕንድ ውስጥ አሉ:: ከኘሮቴስታንቶች በቀር መላው ዓለም ያከብረዋል::

††† ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአገልጋዩ ቅዱስ ቶማስ ጸጋ በረከት ይክፈለን::

††† መጋቢት 14 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ (ጋኔን ያደረባት ሴትን ፈውሶ አሕዛብን ያሳመነበት)
2.ቅዱስ አባ ባጥል ትሩፈ ምግባር (ባንድ ወቅት ከእስክንድርያ ዝሙትን ለማጥፋት የተጋደሉ ጻድቅና አረጋዊ አባት)
3.ቅዱስ ሲኖዳ (ሺኖዳ) ሰማዕት
4.ቅዱስ ቄርሎስ ሊቀ ዻዻሳት

††† ወርሐዊ በዓላት
1.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል)
2.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
3.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
4.ቅዱስ ሙሴ (የእግዚአብሔር ሰው)
5.አባ ስምዖን ገዳማዊ
6.አባ ዮሐንስ ጻድቅ
7.እናታችን ቅድስት ነሣሒት

††† "ደጆች ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ:: በመካከላቸውም ቆሞ 'ሰላም ለእናንተ ይሁን' አላቸው:: ከዚያም በሁዋላ ቶማስን 'ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ:: እጅህንም አምጣና በጐኔ አግባው:: ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን' አለው:: ቶማስም 'ጌታዬ አምላኬም' ብሎ መለሰለት:: ኢየሱስም 'ስላየኸኝ አምነሃል:: ሳያዩ የሚያምኑ ብጹዓን ናቸው' አለው::" †††
(ዮሐ. 20:26-29)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
"ቤተክርስትያንን መርዳት ከፈለክ ሌሎችን ለማረም ከማሰብ በፊት በቅድሚያ እራስን ማስተካከል ይበጃል። እራስህን ካስተካከልክ አንድ የቤተክርስትያን ክፍል ዳነ ወይም ተስተካከለ ማለት ነው። ሁሉም ሰው ይህን ማድረግ ከቻለ ቤተክርስትያን ጤናማ ትሆናለች። ስለዚህ ላስተዋለው ሰው ሌሎች ላይ መፍረድ እጅግ በጣም ቀላል ነው እራስን ማስተካከል ግን ጥረት ይጠይቃል።"

#ቅዱስ_ፓሲዮስ
#ለሰይጣን_ጊዜ_የለኝም

መምህሩ ተማሪዎችን ሊፈትን በአንድ ሰዓት ውስጥ የሚመለሱ ሁለት ጥያቄዎችን አዘጋጀ። ተማሪዎች ራሳቸውን አዘጋጅተው ወደ ፈተና ክፍል ገበተው ወንበር ወንበራቸውን ይዘው ይጠብቃሉ። መምህሩ የፈተና ወረቀቱን ይዞ ገባ። የፈተናውን መመሪያ ተናግሮ የፈተና ወረቀቱን አደለና ሰዓት ይዞ "መጀመር ትችላላችሁ" አላቸው።

የመጀመሪያው ጥያቄ ስለ እግዚአብሔር የምታውቀውን ጻፍ የሚል ነው። ሁለተኛው ጥያቄ ደግሞ ስለ ሰይጣን የምታውቀውን ጻፍ ይላል፡፡ "ለአንዱ ጥያቄ 30 ደቂቃ ነው የተሰጠው ማለት ነው" ብለው ሰዓት ሳያልቅባቸው ሁለቱንም ጥያቄዎች ለመጨረስ ተሎ ተሎ ይጽፋሉ። ፈተና ከተጀመረ 30 ደቂቃ መሙላቱ ሰዓት ያዩ ተማሪዎች ከአንደኛው ጥያቄ ወደ ሁለተኛው አልፈው መስራት ጀምረዋል፡፡ በአእምሮአቸው የመጣላቸውን ሐሳብ በቻሉት ፍጥነት ይጽፋሉ፡፡ መምህሩም ሁሉም ተማሪ የየራሱ መስራቱን እየዞረ ይከታተላል።

"ለማጠናቀቅ አስር ደቂቃ ይቀራችኋል" አለ መምህሩ። መልሰን ጨርሰናል ብለው ያሰቡ ተማሪዎች ግማሾቹ ፈተና ወረቀቱን ለመምህሩ ሰጥተው ሲወጡ፥ ሌሎቹም የመለሱትን ደግመው ያነባሉ፡፡ ያልጨረሱም የቀረችውን ደቂቃ ለመጠቀም ይጣደፋሉ። ከአስር ደቂቃ በኋላ "ሰዓት አልቋል ሁላችሁም መስራት አቁሙ" አለ መምህሩ፡፡ እየዞረም ፈተና ወረቀቱን መሰብሰብ ጀመረ፡፡ አንድ ተማሪ ጋር ሲደርስ ግን አሁንም መልስ እየጻፈ ያገኘውና "ሰዓት አልቋል ሲባል አትሰማም እንዴ?" ብሎ ወረቁትን ተቀበለው፡፡

ሁሉም ተማሪዎች ለሁለቱም ጥያቄ የሚያውቁትን የመለሱ ሲሆን አንዱ ተማሪ ግን ለጥያቄ ቍጥር አንድ (ስለ እግዚአብሔር የምታውቁትን ጻፉ ለሚለው) ብቻ ነው መልስ የሰጠው። መምህሩ በዚህ ተማሪ መልስ ተገርሞ "ለምንድ ነው ለሁለቱንም ጥያቄዎች መልስ ያልጻፍከው?" ብሎ ጠየቀው። እርሱም "#ለሰይጣን_ጊዜ_የለኝም" ስለ እግዚአብሔር ራሱ የማያልቅ ቢሆን እኮ ነው የተሰጠን ሰዓት አልቆ ገና እየጻፍኩ ያስቆምከኝ" አለው ይባላል፡፡

እውነት ነው ነገረ እግዚአብሔር ቢጽፉት፣ ቢናገሩት፣ ቢሰሙትና ቢያዜሙት የማያልቅና የማይሰለች ጥልቅ ምሥጢር ነው። የፈለግነው ያህል ጊዜ ብንሰጠው እንኳን በጅምር እያለን ጊዜው ያልቃል። በቃሉ ፍቅር፥ በምሥጢሩ ተመስጦ ውስጥ ሆነን ወደማያልፈው ዓለም እንሻገራለን፡፡

ይህንን ገንዘብ ለማድረግ ግን ለሰይጣንና ለጉዳዮቹ የሚሆን ጊዜ የለኝም ማለት ይገባል፡፡ ከጊዜ ውጭ የሚሰራ ነገር የለምና ለሰይጣን የሚሆን ጊዜ ከሌለን ከኃጢአት ሁሉ መራቃችን አይደል? ለሰይጣን ጊዜ ላለመስጠት ደግሞ ከእርሱ ጋር መጣላት ነው። መቼም ሰው ለጠላው ነገር የሚሆን ጊዜ አይኖረውም። ምንም ስራ ባይኖረውም እንኳ ከጠላው ጋር ላለመገናኘት ምክንያት ፈጥሮ ይርቅ የለ? ስለዚህ ለሰይጣን ጊዜ እንዳይኖርህ ከእርሱ ጋር ተጣላ። የሚገርመው ከሰይጣን ጋር ስትጣላ ደግሞ ከሰው እና ከእግዚአብሔር ጋር በፍቅር መኖር ትችላለህ፡፡ ከ24ቱ ሰዓት ለሰይጣን የሚሆን ጊዜ ከሌለን መቼም ቢሆን ኃጢአት ሊያሰራን የሚችልበት ዕድል ወይም አጋጣሚ አይኖርም። የተሰጠን ጊዜ ለሰጪው አምላክ መልሰን እንሰጠው ዘንድ ማስተዋሉን ያድለን።

@beteafework      @beteafework
@beteafework      @beteafework
@beteafework      @beteafework
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
          አሜን
"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"         
         ቀናችንን በጸሎት እንጀምር


🛎 ስንክሳር ዘወርኀ መጋቢት ፲፯


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መጋቢት ዐሥራ ሰባት  በዚች ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚወደው በአራተኛውም ቀን ከመቃብር ያስነሣው የከበረ ጻድቅ አልዓዛር አረፈ።

❖ ይህም ጻድቅ ሰው ከእስራኤል ልጆች ውስጥ ነው ማርያና ማርታ የተባሉ ሁለት እኅቶች አሉት፤ ማርያም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሸቱ የቀባችው ናት፤ እነርሱም ለጌታ ደቀመዛሙርቶቹ ናቸው ስለ ምግባራቸውም ጌታችን ይወዳቸዋል ሁሉም ያላገቡ ድናግል ናቸው፤ በሰው ወገን ሁሉ ላይ የተቆረጠና የተወሰነው ሰዎችም ሊጠጡት ያላቸው የሞት ጻዋን የሚጠጣበትና እጁን ለሞት የሚሰጥበት ለዚህ ጻድቅ ጊዜው ሲደርስ እርሱም እጁን በመስጠት አረፈ።

❖ የክብር ባለቤት ጌታችን ግን የሚሠራውን ያውቃልና መጀመርያ  ከሞት አላዳነውም ጠርቶ እስከሚአሥነሣው ድረስ ሙቶ በመቃብር አራት ቀን እንዲኖር በዚህ በአራት ቀንም የጻድቃንን ማደሪያዎችንና የኃጥአንን የሥቃይ ቦታዎች እንዲያይ ተወው እንጂ አላዳነውም ያን ጊዜም ታላቅ ምልክት ትሆናለች።
❖ ከአራት ቀኖችም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እርሱ መጥቶ አልዓዛር አልዓዛር ና ውጣ ብሎ ከመቃብር ውስጥ ጠራው ያን ጊዜ አጆቹና እግሮቹ እንደታሠሩ ሙታኖችንም እንደሚጠቀልሏቸው በሰበን ፊቱ ተጠቅልሎ ወጣ።

❖ እጆቹና እግሮቹ እንደ ተጠቀለሉና እንደ ታሠሩ ከመቃብር የመውጣቱ ምክንያት ሰዎች ሁሉ መሞቱን እንዲረዱ ሌሎችም ይህ በመካከላቸው በስምምነት የሆነ ነው ብለው እንዳያሰቡ፤ ስለዚህም እንደ ገነዙት ሁኖ እንዲወጣ ጌታችን አዘዘው ይችም ምልክት እንድትሆን።
❖ ከሀዲዎችም በመቃብር ውስጥ ሕያው እንደ ነበር ቢያስቡም እጆቹና እግሮቹ ፊቱም እንደ ተጠቀለሉ እንዴት ይወጣ ነበር እኛ የክርስቲያን ወገኖች ግን የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአራት ቀኖች በኋላ አልዓዛርን ያስነሣው እርሱ እንደሆነ እናምናለን፤ እንታመናለንም እርሱ በሥራው ሁሉ ላይ ችሎታ አለውና።
ለጌታችን ለፈጣሪያችን ለመድኃኒታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ከቸር አባቱና ሕይወት ከሆነ መንፈስ ቅዱስም ክብር ስግደት ይሁን ለዘላለሙ አሜን።

🛎 በዚችም ዕለት አናጕንስጢስ ቴዎቅሪጦስ በሰማዕትነት አረፈ፤ ይህም ቅዱስ የሮሜ አገር ሰው ነው፤ ዐላውያንም ለጣዖት እንዲሠዉ ክርስቲያኖችን ይዘው በአስገደዷቸው ጊዜ እርሱንም ከእነርሱ ጋር ያዙት ወደ ንጉሥም አቀረቡት ያንጊዜ የዐሥራ አምስት ዓመት ልጅ ነበር።

❖ንጉሡም በማመጣብህ ሥቃይ ትፈተናለህን ወይስ ለአማልክት ትሠዋለህ አለው፤ ቴዎቅሪጦስም እኔስ ለክብር ባለቤት ለጌታዬ ለፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ እሠዋለሁ አለው፤ ንጉሡም ቴዎቅሪጦስ ሆይ በክፉ አሟሟት እንዳትሞት ለአማልክት መሥዋዕት አቅርብ አለው ።

❖ እርሱም ንጉሥ ሆይ መሥዋዕቴን እንድታይ ና አለው ንጉሡም ወደ ጣዒቱ ቤት እንዲወስዱትና በዚያ እንዲሠዋ አዘዘና እርሱም በበር ቆመ፤ ቅዱሱም በጸለየ ጊዜ ንውጸውጽታ ሁኖ አጽቀላጽዮስ የሚሉት አምላካቸው ወድቆ ተሰበረ ።

❖ ንጉሡም እንደ ዘበተበት አይቶ አፍንጫውን ቆረጠው አሥረው በወህኒ ቤት እንዲአስገቡት አዘዘ፤ በማግሥቱም አውጥተው በብረት ምጣዶች ውስጥ ጨመሩት ደግመው ጥልቅ ግድጓድ ቆፈሩ በውስጡም እንጨት ረብርበው ሥጋው ከመለያያው እስቲቦጫጨቅና ቅልጥሙም ከአጥንቶቹ እስቲፈስ ድረስ ወረወሩት፤ በዚህም ሊአጠቁት አለቻሉም የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከእርሱ ጋር አለና።

❖ ከዚህ በኋላ አማልክቶቻቸው የሚበቀሉት መስሏቸው ከአማልክቶቻቸው ቤት አስገብተው በዚያ ዘጉበት፤ ቴዎቅሪጦስ ግን ከጣዖታቱ ላይ ያለውን ወርቅ ቀጥቅጦ በሥውር ይዞ እየወጣ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች መጸወተው፤ ተመልሶ ሲገባም ደጃፉ እንደ ቀድሞው ራሱ ይዘጋል።

❖ በስምንተኛውም ቀን ንጉሡ መጣ ከደጃፍም ሁኖ አየ አማልክቶቹም ተጥለው ተሰባብረው የከበረ ቴዎቅሪጦስም ሲዘብትባቸው አገኛቸው፤ ዕውነተኛ ቴዎቅሪጦስንም የሆድ ዕቃው እስቲታይ እንዲሰነጣጥቁት አዘዘ፤ ደግመው ወደ ጨዋታ ቦታ እንዲአስገቡትና በላዩ አንበሶችን እንዲአስገቡአቸው አዘዘ፤ አንበሶችም ቁስሎቹን ላሱለት።

❖ ዳግመኛም ሕዋሳቱ እስቲነጣጠል ከሚአጣብቅ ቦታ እንዲአስገቡት መላ አካላቱም ታጥፎ እስቲቆለመም እንዲአሠቃዩት አዘዘ፤ በዚህም ተሸብሮ አላሸነፉትም ንጉሡም ብርታቱን አይቶ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ።
❖ የከበረ ኤጲስቆጶስ ኤሞሬዎስና ህዝብ ሁሉ በጸሎት እየተራዱት ቅዱስ ቴዎቅሪጦስን ተከተሉት በቅዱሳን ሰላምታም ተሳልመውት ተሰናበቱት ባለወግ ወታደርም ሰይፉን አንስቶ አንገቱን ቆረጠው ምስክርነቱንም ፈጸመ አማላጅነቱ።
በረከቱም ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ጋራ ለዘላለሙ ይኑር አሜን።
  
                   
✍️ በዚችም ቀን ደግሞ የታጋዩ የቅዱስ ጊዮርጊስና የሰማዕቱ ተላስስ የኤጲስቆጶስ ዮሴፍ መታሰቢያቸውና የሊቀ ካህናት ኒቆር የሥጋው ፍልሰት ነው።

           

📌 መጋቢት 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አልዓዛር ጻድቅ ሐዋርያ
2.ቅዱስ ቴዎቅሪጦስ አናጉንስጢስ (ሰማዕት)
3.ቅዱስ ተላስስ ሰማዕት
4.ቅዱስ ዮሴፍ ኤዺስ ቆዾስ
5.ቅዱስ ጊዮርጊስ መስተጋድል

📌 ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት (ቀዳሜ ሰማዕት)
2.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዘብዴዎስ)
3.ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ዘቆዽሮስ
4.ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
5.አባ ገሪማ ዘመደራ
6.አባ ዸላሞን ፈላሢ
7.አባ ለትጹን የዋህ
ነፍስ ይማር 👇
Forwarded from TIKVAH-ETHIOPIA
" 2 አገልጋዮች ከነሙሉ ቤተሰቦቻቸው በጥይት ተደብድበው ተገድለዋል " - የአካባቢው ምዕመናን

የደብረ ቅዱሳን ቅዱስ ገ/ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ሁለት አገልጋዮች #ከነሙሉ ቤተሰቦቻቸው መገደላቸውን የማህበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ገለጸ።

በምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት በዶዶላ የደብረ  ቅዱሳን ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን 2 አገልጋዮች ከነሙሉ ቤተሰቦቻቸው ጋር ለጊዜው " ማንነታቸው አልታወቀም " በተባሉ አካላት መገደላቸው ተነግሯል።

የቴሌቪዥን ጣቢያው ፤ ግድያው የተፈፀመው ትናንት መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 3:00 ገደማ መሆኑን የአካባቢው ምዕመናን እንደነገሩት ገልጿል።

በተፈጸመው በዚህ ግድያ የደብረ ቅዱሳን ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን  አገልጋይ የሆኑት አንድ መሪጌታና ዲያቆንን ጨምሮ 5 የቤተሰብ አባሎቻቸው በጥይት ተደብድበው መገደላቸው ተገልጿል።

የቴሌቪዥን ጣቢያው ፥ በዶዶላ ከተማ ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም በርካታ ኦርቶዶክሳውያን መገደላቸውን አስታውሷል።

@tikvahethiopia
"ትህትናን ውደዷት ኃጢአታችሁን የምትሸፍን ናትና፡፡ ሁሉም ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ቢሆንም ከኃጢአቶች ሁሉ መጥፎ የሆነው ግን የልብ ትዕቢት ነው:: ራሳችሁን አዋቂ አድርጋችሁ ከፍ ከፍ አታድርጉ፡፡ ይህን ምታድረጉ ከሆነ ጥረታችሁ ሁሉ ፍሬ አልባ ይሆናል፡፡"

#አባ_እንጦንስ
Forwarded from Bketa @¥
ምኵራብ

የዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት
 
“ቦአ ኢየሱስ ምኵራበ አይሁድ ወመሐረ ቃለ ሃይማኖት፤ ወይቤሎሙ ምጽዋተ አበድር እመሥዋዕት፤ አነ ውእቱ እግዚኣ ለሰንበት ወአቡሃ ለምሕረት፤ እግዚኣ ውእቱ ለሰንበት ወልደ እጓለ እመሕያው፤ ጌታችን ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገባ፤ የሃይማኖት ቃልን አስተማረ፤ ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ፤ የሰንበት ጌታዋ የምሕረት አባቷም እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም
የሰንበት ጌታዋ ነው።” (ጾመ ድጓ)
 
በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሦስተኛውን የዐቢይ ጾም ሳምንት “ምኵራብ” ይባላል። ቀጥተኛ ፍቺው “ኮረብታ፣ ተራራ የሚያህል ታላቅ ሕንጻ፣ ሰቀላ መሰል አዳራሽ” ሲሆን፣ የአይሁድ መካነ ጸሎት ወይም ቤተ መቅደስ በመሆን ያገለግል ነበር። በብሉይ ኪዳን አይሁድ ቤተ መቅደስ ነበራቸው፡፡
 
ናቡከደነጾር ኢየሩሳሌምን በወረረ ጊዜ ግን ቤተ መቅደሱን አፈረሰ፤ ሕዝቡን ወደ ባቢሎን አፈለሰ፤(፪ኛነገ.፳፬-፳፭፣ኤር.፬፥፯:፣፴፱፥፩-፲፣፶፪፥፩-፴) ከዚህ ጊዜ ጀምሮ አይሁድ በሚኖሩባቸው ሥፍራዎች ሁሉ ለጸሎት ቤት ይሠሩ ነበር፡፡ በዚያን ዘመን ቢያንስ ዐሥር አባ ወራዎች/የቤተ ሰብ ኃላፊዎች/ በቦታው ከተገኙ እነዚህን ምኵራቦችን ለመሥራት ይፈቀድላቸው ነበር፡፡ (Talmud Mishnah, Responsa literature, Jewish Encyclopedia, Academic Scholarly Works.)  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም እየተዘዋወረ በሚያስተምርበት ጊዜ ግን ብዙ ምኵራቦች ነበሩ፡፡ በሐዲስ ኪዳንም ለሐዋርያት በብዛት የስብከት ዓውደ ምሕረቶች ሆነው አገልግለዋል።

 
ምኵራበ አይሁድ በውስጡ የብራና የሕግ እና የነቢያት መጻሐፍት ይገኛሉ፡፡ ምእመኑ እንዲሰማቸው ከፍ ባለ መድረክ ላይ በመሆን መምህራንና ካህናት ቆመው መጻሕፍትን ያነባሉ፤ ቃለ እግዚአብሔርንም  ያስተምሩ ነበር። የምኵራብ ሹማምንት አለቆች ጥፋተኛ ሰው ሊቀጡ ሥልጣን ነበራቸው፡፡ አገልጋይ ወይም የሚራዱ ወጣቶችም ልጆችን በማስተማር፣ በማቅረብ በተጨማሪ የአለቆችን ትእዛዝ በመፈጸም ያገለግላሉ፡፡
 
በሰንበት ሕዝብ ሁሉ በምኵራብ ተሰብስቦ ከሕግና ከነቢያት ንባብ፣ ስብከትና ቡራኬ በመቀበል አምልኮታቸውን ይፈጽሙ ነበር፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምኵራብ ተገኝቶ ሕዝቡን አስተምሯል፡፡ ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ ”ወዳደገበትም ወደ ናዝሬት መጣ፤ እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን  ምኵራብ ገባ ሊያነብም ተነሣ” እንዳለ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ፣ መማር፣ መመርመር፣መተርጎም፣ጉባኤ መሥራት አዘውትረው የሚፈጽሙት ተግባር እንደነበር ያስረዳል።(ሉቃ.፬፡፥፲፮)
 
ነገር ግን በምኵራብ ሰዎች ለተለያየ ዓላማ ይሰበሰቡ ነበር፡፡
 
፩. አማናዊ እረኛ ነው ብለው፦
ወልድ ዋሕድ ብለው ሲጠብቁት የነበረው ተስፋ “ደረሰልን፤ ወረደ፤ ተወለደ፤ የዓለም መድኃኒት እርሱ ነው” ብለው አዳኝነቱን አምነው ይከተሉታል። “ነዋ በግዑ ለእግዚብሔር ዘያአትት ወያሴስል ኃጢአተ ዓለም፤ የዓለሙን ኃጢአት የሚያስተሰርይ የእግዚብሔር በግ መሆኑን አውቀው የሚከተሉት አሉ። ”በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል” እንዲል። (ዮሐ.፲፥፬)
 
፪. የቃሉን ትምህርት የእጁን ተአምራት ሽተው፦ ከደዌ ለመፈወስ ይሰበሰባሉ፤ ልብሱን ዳሰው፣ ወድቀው ሰግደው፣ ጥላውን ተጋርደው፣ በእጁ ተዳሰው የሚፈወሱ ነበሩ። (ማር. ፭፥፳፪ እስከ ፍጻሜ)። ጌታችን በዕለተ ሰንበት ሕዝብ በተሰበሰበበት በምኵራብ እንደሚያስተምር ያስረዳናል፤ ”ሰንበትም በሆነ ጊዜ በምኵራብ ያስተምር ጀመር፤…ወደ ምኩራባቸውም ገብቶ ዝም ይሉ ዘንድ ገሠፃቸው፤ እነርሱም ትምህርቱን፣ የቃሉን ግርማ፣ የአነጋገሩን ጣዕምና፣ የአንደበቱን ቅልጥፍና አደነቁ፡፡”  (ማር.፮፥፩) “ወደ ገዛ አገሩም መጥቶ እስኪገረሙ ድረስ በሚገባቸው ያስተምራቸው ነበር።” (ማቴ.፲፫፥፶፬)
 
፫. ምግበ-ሥጋ ፈልገው ደም ግባቱን አይተው:- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከምኵራብ ጉባኤ ትምህርት በኋላ ጥቂቱን አበርክቶ እልፉን ይመግብ ስለነበር ጉባኤውን ይታደማሉ። ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን የምናመልከው ምግበ ሥጋ ስለሰጠን አይደለም። እርሱንማ ለሕዝብም ለአሕዛብም ሳይሰስት የሚመግብ መጋቤ ዓለማት ነው። ክርስቲያን በመብል አይገመትም። “እንግዲህ በመብልም ቢሆን÷ በመጠጥም ቢሆን÷ በልዩ ልዩ በዓላትም ቢሆን÷ በመባቻም ቢሆን÷ በሰንበትም ቢሆን የሚነቅፋችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፡፡” እንዲል፡፡ (ቆላ. ፪፥፲፮ እስከ ፍጻሜ)
 
፬. ለክስ የሚቀርቡ አሉ፦ ከቃሉ ግድፈት ከትምህርቱ ስሕተት የሚፈልጉ ሰቃለያን አይሁድ፣ ሊቃነ ካህናት አምላክነቱን የሚጠራጠሩ አይሁድ የሸንጎውን ጌታ ለሸንጎ ፍርድ ሊያቀርቡት ከግር በግር ይከተሉት ነበር። “ወጸቢሖ ተጋብኡ ሊቃነ ካህናት ወጸሐፍት ወሊቃናተ ሕዝብ ወወሰድዎ ውስተ ዐውዶሙ። ወይቤልዎ እመ አንተሁ ክርስቶስ ንግረነ ገሃደ ወይቤሎሙ እመኒ አይዳእኩክሙ ኢተአምኑኒ፡፡ በነጋም ጊዜ፥ የካህናት አለቆች፥ ጻፎችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ተሰብስበው ወደ ሸንጎአቸው ወሰዱት፡፡ “አንተ ክርስቶስ እንደ ሆንህ በግልጥ ንገረን” አሉት፡፡እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “ብነግራችሁም አታምኑኝም” እንዲል፡፡ (ሉቃ. ፳፪፥፷፮፣ ማቴ.፳፮፥፶፱)
 
ዛሬም በአማናዊቷ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥጋዊ ነገር ብቻ ገዝፎባቸው ቤተ መቅደሱን ለንግድ፣ ንዋያተ ቅድሳትን ለትርፍ ብቻ አሳልፈው የሚሸጡ፣ የሚለውጡ፣ ለክስ የሚፋጠኑ ከምኵራብ ያልወጡ የበጎችን እረኛ አሳልፈው የሚሰጡ አዋልደ ይሁዳ እንዳሉ ግልጽ ነው። “ወረከበ በምኵራብ እለ ይሠይጡ አልህምተ ወአባግዐ ወአርጋበ …፤ በመቅደስም በሬዎችን፣ ላሞችን፣ በጎችን፣ ርግቦችን፣ የሚሸጡትን አገኘ …፤ “ኢትግበሩ ቤተ አቡየ ቤተ ምስያጥ ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ይሰመይ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቦታ አታድርጉት፤ እናንተ ግን የሌቦች ዋሻ አደረጋችሁት፤ ቤቴስ የጸሎት ቤት ይባላል” እያለም የሃይማኖትን ቃል አስተማራቸው፡፡ (ዮሐ.፪፥፲፮፣ማቴ.፳፩፥፲፫)
 
በምኵራብ ይሸጡ፣ ይለውጡ የነበሩትን የገሠፀበት፣ ቤተ መቅደስን የከብት መንጃ የወርቅ መነገጃ ያደረጉ ሰዎችን ከእነ ሸቀጣቸው ከቤተ መቅደስ ያስወጣበት፣ ቤተ መቅደስ የእግዚአብሔር ማደሪያ፣ የመሥዋዕቱ መክበሪያ፣ የጸሎት ሥፍራ ምስካበ ቅዱሳን መሆኗን ያስተማረበት ዕለት ነው። ቃሉ በዚያን ዘመን ተነግሮ ብቻ ያለፈ አይደለም፤ ለእኛ የተነገረን መሆኑን አውቀን የባለቤቱ ጅራፍ ሳይገርፈን ልንመለስ ይገባል። “የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፥ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፡፡” (ዮሐ.፪፥፲፬)
 
ከሚመጣው ጅራፍ ለመዳን እምነት ከተግባር ይዞ መገኘት ያስፈልጋል።” ወንድሞቻችን ሆይ÷ እምነት አለኝ፤ ምግባር ግን የለኝም የሚል ሰው ቢኖር÷ ምን ይጠቅመዋል? በውኑ እምነቱ ልታድነው ትችላለችን? ከወንድሞቻችን÷ ወይም ከእኅቶቻችን÷ የታረዙ ወይም የዕለት ምግብ ያጡ ቢኖሩ÷ ከእናንተም አንዱ …እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው።” እንዳለ። (ያዕ.፪፥፲፬ እስከ ፍጻሜ)
 
የዕለቱ መዝሙር (ከጾመ ድጓ)፦ ቦአ ኢየሱስ ምኩራበ አይሁድ ወመሐረ ቃለ ሃይማኖት፤ጌታችን ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኩራብ ገባ፤ የሃይማኖት ቃልን አስተማረ፤
 
መልእክታት፦(ቆላ.፪፥፲፮ እስከ ፍጻሜ) (ያዕ.፪፥፲፬ እስከ ፍጻሜ)
ወንጌል፦ (ዮሐ.፪፥፲፪-እስከ ፍጻሜ)
(የሐዋ.፲፥፩-፰)
 
ምስባክ፦ “እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ፡፡ ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ፡፡ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ፡፡” ትርጉም “የቤትህ ቅንዓት በልቶኛልና፥ የሚሰድቡህም ስድብ በለዬ ወድቆአልና፡፡ ሰውነቴን በጾም አደከምኋት፡፡  (መዝ.፷፰፥፱)     
 
በምሕረቱ ይታደገን፤ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ አሜን!!!
ምንጭ :-ማኅበረ ቅዱሳን

ይህ በጽ/ጽ/ሐ/ጎ/ቅ/ሚካኤል ቤ/ክ ፍ/ብ/ሰ/ት/ቤት እውቅና የተሰጠው የቴሌግራም ቻናል ነው።
https://www.tg-me.com/finotebirhan12

የዩቲዩብ ቻናላችን
https://youtube.com/@finotebirhan12

የቲክቶክ አካውንታችን https://www.tiktok.com/@finotebirhan?_t=8i8eHwFI3Es&_r=1

የፌስቡክ ገጻችን  https://www.facebook.com/Fbirhan?mibextid=2JQ9oc
2024/09/28 18:15:02
Back to Top
HTML Embed Code: