Telegram Web Link
Forwarded from Bketa @¥
"የአባት ምክር ለልጅ"

በዚህ ከደግነት- ክፋት፣ ከጥጋብ - ቸነፈር፣ ከሐሴት - መከራ፣ ከጤንነት - በሸታ፣ ከደህንነት - አደጋ በነገሰበት ፣ ውጥንቅጥ ዓለም ውስጥ የምትኖር ልጄ ሆይ፦
- በዕለት ተዕለት ሕይወትህ ውስጥ ትግዕስት፣ እርጋታና ማስተዋል አይለይህ፣ ለጠብ፣ ለግጭት፣ ለኩርፊያና ለጥል ከመቸኮል ይልቅ ከነዚህ ችግሮች ውስጥ በሰከነ መንፈስ ጸጋና በረከትን ፈልግ፣

- ልጄ ሆይ! በዚህ ዓለም የሁካታና ጥድፊያ ባሕር ውስጥ ሰምጠህ እንዳትቀር አብዝተህ ተጠንቀቅ፡፡ በተቻለ መጠን መንፈስህን ከሚያውኩ ሰዎችና ሁነቶች ራቅበል፣

- ልጄ ሆይ! ጓደኛ፣ ወዳጅ፣ ዘመዴ ያልከው ባስቀመጥከው ቦታ ባታገኘው እንደነብር በድንገት ተቆጥተህ እላፊ ነገር ውስጥ ዘለህ አትግባ! ትርፍ ንግግር ሁሌም ቢሆን ሕሊናን ከማቆሸሽ ያለፈ ውጤት ከቶም የለውም፡፡ ይልቅስ ነገሮች ሁሉ ለበጎ ናቸው የሚባለውን የአባቶች ብሂል አስታውስና ነገሩን ናቅ አድርገህ እለፈው፣

- ልጄ ሆይ! ብዙ ሰዎች ከገንዘብ ፍቅር ይበልጣል ወይም ከፍቅር ገንዘብ ይበልጣል እያሉ ጉንጭ አልፋ ክርክር ሲገጥሙ ታዝበህ ይሆናል፡፡ እኔ ግን እልሃለሁ! ፍቅርም ገንዘብም ለአንተ አስፈላጊ ናቸው፡፡ አየህ ፍቅር ልክ እንደችግኝ ነው፡፡ ስትንከባከበው ያድጋል፣ ይፋፋል፡፡ ከተውከው ይጠወልጋል፡፡ እናም ገንዘብህን በአግባቡ የፍቅር ችግኝህን ለመንከባከብ አውለው፣

- ልጄ ሆይ! ገንዘብ አገኘሁ ብለህ በዚህ ዓለም እንደምታያቸው ዓለማውያን ግዙፍ ቤት ገንብተህ፣ ቤትህንም ከፍ ባለ አጥር ክበህ፣ በአጥሩም ላይ የኤሌክትሪክ ሸቦ ጎንጉነህ፣ ከጎረቤት ከወዳጅ ዘመድ ርቀህ የድንጋይ ክምር ውስጥ መሽገህ መኖር ሊያጓጓህ ይችላል፡፡ ሰው ነህና መጓጓትህ፣ መመኘትህ ምንም ነውር የለውም፡፡ እኔ ግን እልሃለሁ አሁንም አብዝተህ አስተውል! አፍ የሚችለውን እጅ ይመጥነዋል እንዲሉ ለሁሉ ነገር መጠን፣ ልክ፣ ገደብ አለው፡፡በርሜል ውስጥ የተጠራቀመ ውሃ ከሞላ መፍሰሱ አይቀርም፡፡ ሞልቶ የሚፈስ ቅንጦትና መብለጭለጭ በእኔ ይሁንብህ አያጓጓህ፤ ተወው። ይልቁንም ሁልጊዜም ሞልቶ ከተረፈ ብቻ ሳይሆን ካልተረፈህም ትንሽዬ ጥሪትህ ለሌሎች ማካፈልን ልመድ፡፡

- ልጄ ሆይ! በዚህ ከንቱ ዓለም ልግስና የመንፈስ ሐሴት ነው፡፡ የሰውነት ጸጋና ክብርን መጎናጸፊያም መንገድ ነው፡፡ በመንገዱም ትመላለስበት ዘንድ እነሆ አባታዊ ምክሬን እለግስሃለሁ፡፡ የልብህን መሻት ፈጣሪ ይፈጽምልህ ዘንድ በዘውትር ጸሎቴ አልረሳህም፡፡

አባትህ
/ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተገኘ/
††† እንኳን ለቅዱሳኑ የአስከናፍር ቤተሰብ ዓመታዊ በዓለ ዕረፍት በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ አስከናፍር †††

††† ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት አስከናፍር የሚባል ደግ ክርስቲያን ማርታ የምትባል በሃይማኖትና ምግባር የምትመስለውን ሴት አግብቶ ይኖር ነበር:: እንደ ሕጉና ሥርዓቱ በሥጋ ወደሙ ተወሥነው እንግዳ ቢቀበሉ: ነዳያንን ቢያበሉ እግዚአብሔር ጸሎታቸውን ሰምቶ አርቃድዮስና ዮሐንስ የሚባሉ ልጆችን ሰጣቸው::

አስከናፍርና ማርታ ልጆቻቸውን ጥበብ መንፈሳዊን (ቃለ እግዚአብሔርን) አስቀድመው አስተምረው : ሥጋዊ ጥበብን እዲማሩላቸው ቢልኩዋቸው መንገድ ላይ መርከብ ተሰብሮባቸው ብዙዎቹ ሲሞቱ ወንድማማቾች ግን የመርከብ ስባሪ ወደተለያየ ቦታ አድርሷቸዋል::

አርቃድዮስና ዮሐንስ "ወደ ዓለም አንመለስም" ብለው መነኑ:: ወላጆቻቸው የሆነውን ሰምተው በጭንቅ ሃዘንና ለቅሶ ለብዙ ጊዜ ኑረዋል:: ከዘመናት በሁዋላ ግን የልጆቻቸውን መኖር በራዕይ የተረዱት አስከናፍርና ማርታ ሃብት ንብረታቸውን ለነዳያን አካፍለው ወደ በርሃ መንነው ሔደዋል::

ጥበበኛ እግዚአብሔር አራቱንም አገናኝቷቸው ለብዙ ዓመታት በአንድ ገዳም ውስጥ ተጋድለዋል::
በዚሕች ዕለትም አራቱም ወደ ሰማያዊው ሠርግ ተጠርተዋል::

††† ቸር አምላክ ከቅዱሱ ቤተሰብ በረከት ይክፈለን::

††† መጋቢት 19 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አስከናፍር : ሚስቱ ማርታ : ልጆቹ አርቃድዮስና ዮሐንስ
2.ቅዱስ አርስጥቦሎስ ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት-የቅዱስ ዻውሎስ ደቀ መዝሙር)
3.ሰባቱ ቅዱሳን ሰማዕታት (ከተለያየ ቦታ ተሰብስበው በክርስቶስ ስም የሞቱ)

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
3.አቡነ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ
4.አቡነ ስነ ኢየሱስ
5.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም

††† "እንግዲህ ወንዶች በሥፍራ ሁሉ አለ ቁጣና አለ ክፉ አሳብ የተቀደሱትን እጆች እያነሱ እንዲጸልዩ እፈቅዳለሁ:: እንዲሁም ደግሞ ሴቶች በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ:: እግዚአብሔርን እንፈራለን ለሚሉት ሴቶች እንደሚገባ መልካም በማድረግ እንጂ በሽሩባና በወርቅ: ወይም በዕንቁ: ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ::" †††
(1ጢሞ. 2:8)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
          አሜን
"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"         
📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
         ቀናችንን በጸሎት እንጀምር

🛎 ስንክሳር ዘወርኀ መጋቢት ፳

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወለድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መጋቢት ሃያ በዚች ቀን በእስክንድርያ ከተሾሙ አባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሃምሳ ሰባተኛ የሆነ የከበረ አባት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤል አረፈ።

ይህም አባት በሹመቱ ወራት ብዙ ኀዘንና መከራ ደረሰበት ጎሕ በሚባል አገር የተሾመ የዚህን የኃላፊውን ዓለም ክብር የሚወድ አንድ ክፉ ኤጲስቆጶስ ነበረ፤ በሀገረ ስብከቱም ውስጥ ደነውስር በሚባል አገር ያሉ ምእመናን የቤተ ክርስቲያናቸውን ሕንፃዋን አደሱ ሊአከብሩዋትም በፈለጉ ጊዜ የአገር ታላላቆች ከእርሳቸው ሊባረኩ ወደው ሊቀ ጳጳሳቱና በአገሩ ዙሪያ ያሉትን ኤጲስቆጶሳት ልኮ እንዲአስመጣቸው ይህን ክፉ ኤጲስቆጶስ ለመኑት እርሱ ግን እምቢ አላቸው ልመናቸውን መቀበል አልወደደም።
❖ እነርሱም በራሳቸው ፈቃድ ይህ ክፉ ኤጲስቆጶስ ሳይፈቅድ ሊቀ ጳጳሳቱንና ኤጲስቆጶሳቱን ሁሉ ልከው አስመጡአቸው፤ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤልና ኤጲስቆጶሳቱ ሁሉ በመጡ ጊዜ ምሳ አዘጋጅላቸዋለሁ ብሎ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትቶአቸው ሔደ፤ ማርታ ማርታ ብዙ በማዘጋጀት ብዙ ትደክሚያለሽ ግን ጥቂቱ ይበቃል ያለውን የጌታችንን ቃል አላሰበም።
❖ የቍርባን ጊዜ ሊያልፍ ስለሆነ ሊቃውንቱና ኤጲስቆጶሳቱ የቅዳሴውን ሥርዓት ይጀምር ዘንድ ሊቀ ጳጳሳቱን ለመኑት ግድ ባሉትም ጊዜ በሊቀ ጵጵስና ማዕረግና ክብር ተሠይሞ ተነሣ እርሱ ለሁሉ አባት የሆነ ሥልጣኑም ከሥልጣናቸው በላይ ነውና የቅዳሴውንም ሥርዓት ጀመረ።

❖ ያ ክፉ ኤጲስቆጶስም በሰማ ጊዜ በልቡ ሰይጣን አደረበትና ተቆጥቶ መጣ፤ መሥዋዕቱንም ከመቅደስ ገብቶ ከጻሕሉ ውስጥ ነጥቆ ወደ ምድር ወረወረው ሊቀ ጳጳሳቱም ሌላ መሥዋዕት አምጡ ብሎ አዘዘ አምጥተውለትም ቀድሶ ለሕዝቡ ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸውና አሰናበታቸውም፤ በማግሥቱም ይህ አባት አባ ሚካኤል ሕዝቡን ሰበሰበ ከእርሱ ጋራ ያሉትንም ኤጲስቆጶሳት ካህናቱንና የምእመናንን አንድነት ሰብስቦ ይህን ክፉ ኤጲስቆጶስ ከሹመቱ ሽረው በእርሱ ፈንታ ሌላ ኤጲስቆጶስ ሾሙ።
❖ ይህም ለአስቆሮቱ ሰው ለይሁዳ ሁለተኛው የሆነ የምስርን አገር ወደ ሚገዛ ስሙ አሕመድ ወልደ በጥሎን ወደተባለው ሹም ሔደ ይህን አባት አባ ሚካኤልን እንዲህ ሲል ነገር ሠራበት፤ በሊቀ ጳጳሳቱ ዘንድ ብዙ የወርቅና የብር ገንዘብ እንዳለ እንዲሁም አብያተ ክርስቲያናት የወርቅና የብር ንዋየ ቅድሳትን የተመሉ እንደሆኑ መኰንን ሆይ ዕወቅ አለው።
❖ መኰንኑም ይህን አባት ወደርሱ አስቀርቦ ንዋየ ቅድሳቱን እንዲሰጠው ፈለገ እርሱም ሥጋዬን እንደፈለግህ አድርግ ነፍሴ ግን በእግዚአብሔር እጅ ናት በሎ ከለከለው፤ እጆቹንና እግሮቹን አሥረው በእሥር ቤት እንዲጥሉት አዘዘ በእሥር ቤትም ከአንድ ዓመት በላይ ኖረ በእሥር ቤት ውስጥ በኖረበት መጠን ከለምለም እንጀራና ከጨው ከበሰለ አተር በቀር ሳይበላ ሁል ጊዜ ይጾም ነበር።
❖ ከዚህም በኋላ አንድ ጸሐፊ ምእመን ዮሐንስ የሚባል መጥቶ ለዚህ ለከበረ አባት አባ ሚካኤል ዋስ ሆነው ለመኰንኑ አባ ሚካኤል ሃያ ሽህ የወርቅ ዲናር እንዲሰጠው ሁኖ ከወህኒ ወጥቶ ወደ ቤቱ ሔደ ጥቂት ቀን ተቀመጠ ታላላቆች ምእመናንና የአስቄጥስ ገዳም መነኰሳት ዐሥር ሽህ የወርቅ ዲናር ሰበሰቡ ደግሞ የእስክንድርያ አገር ሰዎች ከምድራቸው አንዱን ለዐሥር ሽህ ዲናር ሸጡ ሃያ ሽህ እስከሚሞላ ሰበሰቡ፤ ሊቀ ጳጳሳቱም ለመኰንኑ ይህን ሃያ ሽህ የወርቅ ዲናር ሰጠው መኰንኑም ዐሥር ዐሥር ሽህ የወርቅ ዲናር እንደ ግብር ሁኖ በየዓመቱ እንዲከፈል ጽፎ አስፈረመው።
❖ጊዜውም ሲቀርብ ይህ አባት አባ ሚካኤል ከምእመናን ሊለምን ተነሥቶ ወጣ በልበይስ ወደተባለም አገር ደርሶ አንዲት ቀን ዋለ ወደርሱም አንድ ምስኪን ድኃ መነኰሴ ገባ፤ ከሊቀ ጳጳሳቱም ቡራኬ ተቀብሎ ተመልሶ በበር አጠገብ ከረድኡ ጐን ቆሞ አትዘን በልብህም አትተክዝ ከዛሬዪቱ ዕለት እስከ አርባ ቀኖች ትድናለህ በላይህ ያለውን የዕዳ ደብዳቤ ትቀበላለህና ለመኰንኑ ምንም አትሰጠውም ብለህ ለአባት ሊቀ ጳጳሳት ንገረው አለው ያ ረድኡም እንዳለው ነገረው ድኃውን መነኲሴ ፈለጉት ግን አላገኙትም።
❖ አርባ ቀኖችም ሳይፈጸሙ ያ መኰንን በክፉ አሟሟት ሞተ በእርሱ ፈንታም ልጁ ተሾመ ለዚህም አባት ያንን የዕዳ ደብዳቤ መለሰለት ይህም አባት ድኃው መነኰስ ትንቢት እንደ ተናገረ ደብዳቤውን ተቀብሎ ቀደደው ከዕዳም ዳነ፤ ይህም አባት በታላቅ መከራና በኀዘን በሹመቱ ዘመን ሃያ ዘጠኝ ዓመት ከኖረ በኋላ በፍቅር በሰላም አረፈ።
በረከቱም ከእኛ ጋራ ለዘላለሙ ትኑር አሜን።

🛎 በዚችም ዕለት የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጻድቅ ሰው አልዓዛርን ከሞተ በኋላ በአራተኛው ቀን ከሙታን ለይቶ አስነስቶት ነበርና ስለዚች ምልክት ገናናነት ብዙዎች አመኑበት። ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቸር አባቱና ሕይወት ከሆነ መንፈስ ቅዱስ ጋር ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።

                  
✍️ በዚችም ዕለት የተመሰገነችና የከበረች ተጋዳይም የሆነች አስጠራጦኒቃ ስለ ክርስቶስ ምስክር ሁና ሞተች፤ የዚች ቅድስት አባቷ ጣዖት አምላኪ ነው እርሷ ግን በክብር ባለቤት በክርስቶስ የምታምን ናት ሥጋዋም እስቲከሣና እስቲደርቅ መልኳም እስቲለወጥ ድረስ በሥውር ትጾማለች ትጸልያለችም።
❖ ዐሥራ አምስት ዓመት በሆናት ጊዜ እናትና አባቷ ምን ያከሣሻል አሏት እርሷም እኔስ ኃጢአቴን ይቅር ይለኝ ዘንድ የክብር ባለቤት ወደሆነ ወደ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ እጸልያለሁ አለቻቸው።
❖ አባቷም በሰማ ጊዜ ወደ ጢባርዮስ ሒዶ የልጁን ሥራ ነገረው እርሱም ወታደሮች ልኮ ወደ ርሱ አስመጣት፤ ለጣዖትም እንድትሰግድ መኰንኑ አባበላት እምቢ በአለችም ጊዜ ወደ ወህኒ ቤት አስገቧት እናቷም ክርስቲያናዊት ናት እየመጣች በክብር ባለቤት በክርስቶስ እምነት ታበረታታት ነበር።
❖ ከዚህ በኋላ የብረት የሆነ የሰሌዳ ክርታስ ይሠሩላት ዘንድ በእሳትም አግለው ክንዶቿ ከወገቦቿ ጋራ አንድ እስቲሆኑ እንዲአጣብቋት አዘዘ ይህንንም በአደረጉባት ጊዜ ያንን የብረት ክርታስ ሰብራ በደኅና ወጣች ሕዝቡም ይህን አይተው በክብር ባለቤት በክርስቶስ አራት ሺህ ሰባት መቶ ያህል አምነው በሰማዕትነት ሞቱ የሰማዕታትንም አክሊል ተቀበሉ።
❖ ሁለተኛም ደግመው ከእሥር ቤት አስገቧት ጥፍሮች ያሉት የብረት በሬ ሠሩላት ሆዷን ያስወጓት ዘንድ ሊሰቅሏትም ወደርሷ አቀረቡት ይህንንም በአደረጉባት ጊዜ በጌታ ኃይል በሬው ወዲያና ወዲህ ተከፈለ ሕዝቡም ይህን በአዩ ጊዜ በክብር ባለቤት በጌታችን ዘጠኝ መቶ ሰማንያ አምስት ያህል ሰው አምነው በሰማዕትነት አረፉ።
❖ ከዚህም በኋላ መርዝን ከተመሉ እባቦች ጉድጓድ ውስጥ ጨመሩዋት በጸለየችም ጊዜ እንደ ትቢያ ሆኑ፤ ሁለተኛም አራት ሰዎች የሚሸከሙትን ከባድ ደንጊያ አምጥተው በአንገቷ ላይ ሰቀሉ በጸለየችም ጊዜ ደንጊያው ወደ ሦስት ተከፈለ፤ ብዙዎች አረማውያንም በክርስቶስ አምነው በሰማዕትነት አረፉ።
"እውነተኛ ሐሴት ትፈልጋላችሁን? እንግዲያውስ ለድሆች መጽውቱ፤ ክርስቶስን ወደ ቤታችሁ ጥሩት፡፡ ይህን ስታደርጉ ማዕዱ ቢነሣም ሐሴቱ አይነሣም፤ ይቀጥላል እንጂ፡፡ በተለይ ደግሞ በዚህ በወርሐ ጦም ይህን አብዝታችሁ አድርጉት።"

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
Channel photo updated
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
          አሜን
"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"         
📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
         ቀናችንን በጸሎት እንጀምር

🛎 ስንክሳር ዘወርኀ መጋቢት ፳፩

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መጋቢት ሃያ አንድ በዚች ቀን አምላክን ለወለደች ለቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም የበዓሏ መታሰቢያ ነው።
ጸሎቷና በረከቷ የተወዳጅ ልጅዋ ቸርነትም ከእኛ ጋራ ለዘላለሙ ይኑር አሜን።

                        
    
  🛎 በዚችም ዕለት የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ለይቶ ወደ አስንሳው ወደ አልዓዛር ቤት ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ሔደ በዚያም ምሳ አዘጋጂለት ማርታም ምግብ በማቅረብ ታገለግላቸው ነበር፤ ሁለተኛዋ ማርያም ግን እግሮቹን ሽቱ እየቀባች በጸጕሩዋ ታሸው ነበር፤ ጌታችንም አመሰገናት እርሷ ከመቀበሪያዬ ጠብቃዋለች በማለት ስለ ቅርብ ሞቱ አመለከተ።

❖ ዳግመኛም ድኆች ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉ እኔ ግን ከእናንተ ጋራ አልኖርም አለ በዚህም ተሰቅሎ የሚሞትበት ጊዜ ቅርብ መሆኑን ያመለክታል ለርሱም ክብር ከሃሊነት ገንዘቡ ስለሆነ ምስጋና ይገባዋል ለዘላለሙ አሜን።
                  
✍️ በዚችም ቀን አልዓዛርን ሊገሉት የካህናት አለቆች ተማከሩ ገናና ስለሆነች ምልክት በእርሱ ምክንያት ብዙዎች በጌታችን የሚያምኑ ሁነዋልና። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።
በዚችም ዕለት የማቱሳላ ልጅ የላሜህ መታሰቢያው ነው፤ እርሱም አንድ መቶ ሰማንያ ሁለት ዓመት ኑሮ ኖኀን ወለደው ከወለደውም በኋላ አምስት መቶ ስልሳ አምስት አመት ኖረ፤ በድምር ሰባት መቶ አርባ ሰባት ዓመት ኖረ፤ እግዚአብሔርንም አገልግሎት በሰላም አረፈ። የፈጣሪው በረከት ከእኛ ጋራ ለዘላለም ይኑር አሜን።
      
📌 በዚችም ቀን ደግሞ የከበሩ ሰማዕታት የቴዎድሮስና የጢሞቴዎስ መታሰቢያቸው ነው በረከታቸው ከእኛ ጋራ ለዘላለሙ ትኑር አሜን።

                   

1.ቅዱሱ ቤተሰብ (አልዓዛር ማርያና ማርታ)
2.አባታችን ላሜኅ (የማቱሳላ ልጅ-የጻድቁ ኖኅ አባት)
3.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሰማዕት
4.ቅዱስ ጢሞቴዎስ ሰማዕት

📌 ወርኀዊ በዓላት
1.ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም
2.አበው ጎርጎርዮሳት
3.አቡነ ምዕመነ ድንግል
4.አቡነ አምደ ሥላሴ
5.አባ አሮን ሶርያዊ
6.አባ መርትያኖስ ጻድቅ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
          አሜን
"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"         
📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
         ቀናችንን በጸሎት እንጀምር

🛎 ስንክሳር ዘወርኀ መጋቢት ፳፪

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መጋቢት ሃያ ሁለት በዚችም ቀን የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ ገብቶ ቤተ መቅደሱን በአህያ ግልገል ተቀምጦ በመዞር ሆሣዕና እያሉ እንዲአመሰግኑት አድርጓል።

   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
        ጥንተ በዓለ ሆሳዕና
   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ ይህም ስለርሱ እየአንዳንዳቸው በዘመናቸው ነቢያት የተናገሩት ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው፤ ያዕቆብም በክርስቶስ ስለ ተመሰለው ስለ ልጁ ይሁዳ አህያውን በዘይት ዕንጨት ላይ ያሥራል ውርንጫውንም በወይን አረግ አለ፤ ዘካርያስም የጽዮን ልጅ አትፍሪ እነሆ ንጉሥሽ በአህያ ግልገል ተቀምጦ ይመጣል አለ።
❖ ኢሳይያስም ንጉሥሽ ጻድቅ የዋህ የሆነ ይመጣል ዋጋውም ከእርሱ ጋራ ነው ሥራውም በፊቱ የተገለጠ ነው በአህያ ግልገልም ላይ ይቀመጣል አለ፤ አብርሃምም የሰሌን ዝንጣፊ ይዞ መሠውያውን በዞረ ጊዜ ይቺን ዕለት ተድላ ደስታ የሚደረግባት የእግዚአብሔር በዓል ብሎ ጠራት።
❖ ዳዊትም ከሕፃናትና ከልጆች አንደበት ምስጋናን አዘጋጀህ አለ፤ ሰሎሞንም የሕፃናት አንደበታቸው የተቃናች ሆነች አለ ሁለተኛም ልጆችና ሽማግሌዎች በኢየሩሳሌም ይጫወታሉ ምርጕዛቸውም በእጃቻቸው ውስጥ ነው አለደግሞ መትከያዎችሽን አስፍተሽ ድንኳኖችሽን ዘርጊ ያለም አለ።
❖ ይህንንም የትንቢት ነገር ለመፈጸም በከበረ ወንጌል እንደተጻፈ ጌታ በአህያዋና በውርንጭላዋ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፤ ወደ ኢየሩሳሌም ሊገባ በቀረበ ጊዜ የደብረ ዘይት አጠገብ ከምትሆን ቤተ ፋጌ ደረሰ ደብረ ዘይት ወደሚባል ቢታንያም በደረሰ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከ፤ ወደ ፊታችሁ ወዳለ አገር ሒዱ፤ በገባችሁም ጊዜ ሰው ያልተቀመጠበት ያህያ ግልገል ታገኛላችሁ ፈትታችሁ አምጡልኝ፤ ለምን ትፈቱታላችሁ የሚል ሰው ቢኖር ጌታው ይሻዋል በሉ፤ የተላኩትም በሔዱ ጊዜ እንደነገራቸው አገኙ፤ የአህያውንም ግልገል ፈቱ ጌቶቹም ለምን ትፈቱታላችሁ አሏቸው።
❖ ጌታው ይሻዋል አሉ፤ ወደ ጌታ ኢየሱስም ይዘውት ሔዱ ልብሳቸውንም በአህያው ግልገል ላይ ጐዘጐዙ ጌታንም አስቀመጡት፤ ቅጠል ቆርጠው በመንገድ ላይ የጐዘጐዙ ብዙዎች ናቸው፤ ልብሳቸውንም በመንገድ ላይ ያነጠፉ አሉ፤ በፊትም በኋላ ይሔዱ የነበሩት በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ መድኃኒት ነው ብለው አሰምተው ተናገሩ፤ በእግዚአብሔር ስን የምትመጣ የአባታችን የዳዊት መንግሥትም የተባረከች ናት።

❖ ጌታ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ገባ ሕዝቡም ሁሉ አዩት በመሸም ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ አርድእት ጋር ወደ ቢታንያ ወጣ፤ በነጋውም ከቢታንያ በወጣ ጊዜ ተራበ፤ በሩቅም ቅጠል ያላትን በለስ አየ፤ በርሷ ፍሬ ያገኝ እንደሆነ ሊያይ ሔደ ወደርሷም በደረሰ ጊዜ ከቅጠል ብቻ በቀር ያገኘው የለም የበለስ ወራቱ አልነበረምና፤ ለዘላለም ካንቺ ፍሬ የሚበላ አይኑር አላት ደቀ መዛሙርቱም ሰሙ፤ ወደ ኢየሩሳሌም ደርሶ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ በምኲራቡም ግቢ የሚገበያዩትን ያስወጣ ጀመረ የለዋጮችንም ሰደቃቸውን ገለበጠ ርግብ የሚሸጡትንም ወንበራቸውን ።
❖ ወደ ምኲራብ ለንግድ ገንዘብ ይዘው እንዳይገቡ ከለከለ፤ ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ይሁን የሚል ጽሑፍ ያለ አይደለምን እናንተ ግን የሌቦችና የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት ብሎ አስተማራቸው፤ ዮሐንስም እንዲህ አለ አልዓዛርን ከሙታን ለይቶ ካስነሳው በኋላ፤ በነጋውም እሑድ ለበዓል የመጡ ሰዎች ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመጣ በሰሙ ጊዜ፤ የሰሌን ዛፍ ዝንጣፊ ይዘው ከኢየሩሳሌም ፈጥነው ወጡ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ከአርያም የተገኘ መድኃኒት የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው እያሉ እየጮኹ ተቀበሉት።
❖ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የአህያ ግልገል አገኘ፤ ተቀመጠበትም እንደ ተጻፈ እንዲህ ሲል፤ የጽዮን ልጅ አትፍሪ እነሆ ንጉሥሽ በአህያ ግልግል ተቀምጦ ይመጣል፤ አስቀድሞ ግን ደቀ መዛሙርቱ ይህን ነገር አላወቁም ነበር ጌታ ሳይሰቀል፤ ጌታ በተሰቀለ ጊዜ ይህ የተጻፈ ስለ እርሱ እንደሆነ ያን ጊዜ አወቁት እንጂ እንዲህም አደረጉለት፤ አልዓዛር አልዓዛር ብሎ ከሙታን ለይቶ እንዳስነሣው ባስነሣው ጊዜ ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎች መሰከሩለት፤ ስለዚህም ሕዝቡ አመኑበት፤ ያደረገውን ተአምራት ሰምተዋልና የሕፃናቱንም ምስጋና ደግሞ አልዓዛርን ማስነሣቱን።
❖ የካህናቱ አለቆችና ፈሪሳውያን ግን እርስ በርሳቸው የምታገኙት ረብሕ ጥቅም እንደሌለ አታውቁምን እነሆ ሰው ሁሉ አመነበት አሉ፤ ማቴዎስና ማርቆስ የሰሌንን ነገር አላወሱም ሌሎች ከእጨንቶች ቅጠሎችን እየቆረጠ በመንገድ ውስጥ ጐዘጐዙ አሉ እንጂ፤ ሉቃስም ቅጠልን ወይም ሰሌንን አላወሳም ሲሔዱ ልብሳቸውን በመንገድ ላይ ይጐዘጒዙ ነበር አለ እንጂ፤ ዮሐንስ ግን ለብቻው ከኢየሩሳሌም ከሰሌን ዛፍ ላይ ዘንባባ ቆርጠው ያዙ አለ፤ ሰሌንም በኢየሩሳሌም አልነበረም ጌታችን ሕፃን ሁኖ ሳለ ወደ ግብጽ በወረደ ጊዜ ከእናቱ ቡርክት ቅድስት ከሆነች ከእመቤታችን ድንግል ማርያም ጋር እስሙናይን ከሚባል አገር ደረሱ ከዚያም ሰሌን አገኙ።
❖ ጌታችንም ከሥርዋ ተነቅላ ሒዳ በደብረ ዘይት ላይ እንድትተከል አዘዛት ያንጊዜ ወደ አየር ወጥታ በረረች ሒዳም በዚያ በደብረ ዘይት ተተከለች ከእርስዋም ወስደው የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ተቀበሉት፤ ጌታችንም የሆሣዕናን ዑደት በአሳየ ጊዜ የአይሁድ ወገን ቅናት ይዟቸው በሚገድሉት ገንዘብ ምክንያት ፈለጉ፤ ለእርሱም ምስጋና ይሁን በእኛ ላይም ይቅርታው ቸርነቱ ይደረግልን ለዘላለም አሜን።

🛎 በዚችም ዕለት የከበረው መንፈሳዊ አባት የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ አባ ቄርሎስ አረፈ፤ ይህም አባት የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በመማር ያደገና እጅግ አዋቂ ምሁር ሆነ፤ ከእርሱ በፊት የነበረ ኤጲስቆጶስ አባ በርኪሶስ በአረፈ ጊዜ ይህን አባት መርጠው ለኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ  አድርገው ሾሙት፤ በተሾመም ጊዜ ከመናንያንና ከአርዮሳውያን ተኵላዎች በመልካም አጠባበቅ ሕዝቡን ጠበቀ።
❖ የኤጲስቆጶሳት ጉባኤ በሰርድቄ በተሰበሰበ ጊዜ ይህ አባት ከዚያ ደርሶ አርዮሳውያንን ተከራከራቸው ምላሽ አሳጥቶም አውግዞ አሳደዳቸው አካክዮስንም ከቂሣርያ ሀገረ ስብከቱ መንበር አሳደደው፤ አካክዮስም ወደ ታናሹ አርዮሳዊ ወደ ሆነው ቆስጠንጢኖስ ሒዶ ከማኀበሩ ስለ ደረሰበት ውግዘትና ስደት ይልቁንም ከዚህ አባት ቄርሎስ የደረሰበትን ሁሉ በመናገር ከሰሰው፤ ስለዚህም አርዮሳዊ ንጉሥ ይህን አባት ከኢየሩሳሌም አሳደደው ሌሎችንም ብዙዎች ኤጲስቆጶሳትን ከሀገረ ስብከት መንበራቸው አሳደዳቸው።
❖ ይህም አባት ቄርሎስ ወደ ተርሴስ ከተማ ሒዶ ከአገሩ ኤጲስቆጶስ ከስልዋኖስ ጋራ ተገናኘ፤ እርሱም ተራዳው ጥቂት ቀኖችም ከእርሱ ዘንድ አስቀመጠው፤ በሉክያኖስ ስብሰባ በሆነ ጊዜም ይህ አባት ከተሰበሰቡት ውስጥ አንዱ እርሱ ነው አካክዮስንም ደግመው አወገዙት ረገሙትም ዳግመኛ ወደ ንጉሥ ሒዶ በዚህ በቅዱስ ቄርሎስ ነገር ሠራበት ንጉሡም ወታደሮች ልኮ ከዚያም ካለበተረ አሳደደው።
Forwarded from Bketa @¥
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

አሜን

✍️"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"
📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

ቀናችንን በጸሎት እንጀምር


📌 ስንክሳር ዘወርኀ መጋቢት ፳፫


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መጋቢት ሃያ ሦስት በዚች ቀን የዮናኪር ሴት ልጁ የወለደችው ታላቅ ነቢይ ዳንኤል አረፈ።
❖ ናቡከደናጾርም ኢየሩሳሌምን በወረራት ጊዜ አባታቸው ዮናኪር አናንያን አዛርያንና ሚሳኤልን ሦስቱን ልጆቹን የልጁን ልጅ ዳንኤልንም ወሰዳቸው ከእንርሱም ጋር ከእስራኤል ልጆች ብዙ ሰዎች ተማረኩ፤ ይህም ዮናኪር የንጉሡ የኢዮአቄም ልጅ ነው፤ ኢሳይያስ ለሕዝቅያስ ንጉሥ ትንቢት እንደተናገረ የቤተ መንግሥቱንና የቤተ እግዚአብሔርን ዕቃ ሁሉ ናቡከደነጾር ወደ ባቢሎን ወሰደ።



❖ ይህ ዳንኤል ያን ጊዜ በዕድሜው ታናሽ ነበር ፍጹም የሆነ ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ የእግዚአብሔር መንፈስም አድሮበት በባቢሎን አገር ትንቢት ሲናገር ኖረ፤ ምርኮ በሆነ በአራተኛው ዓመት ናቡከደነጾር የምታስፈራ ራእይን አየ ከእንቅልፉም በነቃ ጊዜ ያቺን ሕልም ረሳት፤ በባቢሎን የሚኖሩትን ሁሉን ጥበበኞች ሰበሰባቸው ከእርሳቸውም ያቺን ራእይና ትርጓሜዋንም እንዲነግሩት ፈለገ እንርሱ ግን ያቺን ራእይና ትርጓሜዋን ሊያውቋት አልቻሉም።

❖ የባቢሎንን ጥበበኞች ሁሉ እርሱንና ባልንጀሮቹ ሠለስቱ ደቂቅን ይገድሏቸው ዘንድ ንጉሥ አዘዘ፤ ዳንኤልም ይህን ነገር ሰምቶ የዘበኞችን አለቃ ስለ ምን እንዲህ ያለ ትእዛዝ ከንጉሥ ዘንድ ታዘዘ ብሎ ጠየቀው፤ እርሱም ንጉሥ ስለ አያት ራእይ ነው የባቢሎንና የግብጽ ጠቢባን ሁሉ እርሷን ራእዩን ትርጓሜዋንም ሊነግሩት አልተቻላቸውምና ብሎ መለሰለት።

❖ ዳንኤልም የዘበኞቹን አለቃ እኔ ለንጉሥ ሕልሙን እንደምነግረውና ፍቺውንም እንደምተረጕምለት ስለ እኔ ንገርው እሊህንም ተዋቸው አለው፤ከዚህ በኋላም ዳንኤልም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ ባልንጀሮቹ ሠለስቱ ደቂቅም ከእርሱ ጋር የንጉሡን ሕልም ፍቺዋንም ይገለጥላቸው ዘንድ በአንድነት ማለዱ፤ እግዚአብሔርም ገለጠላቸው ዳንኤልም ወደንጉሥ ገብቶ ሕልሙንና ፍችዋን ነገረው፤ ከእርሱ በኋላም ስለሚነሡ ነገሥታት ከእንርሱም ከየአንዳንዳቸው የሚሆነውንም ገለጠለት።



❖ የዳንኤል ቃል ናቡከደነጾርን ደስ አሰኘው በፊቱም ሰገደ ብዙ እጅ መንሻንም ሰጠው ታላቅ ክብርንም ሰጥቶ በባቢሎን ጠቢባን ሁሉ ላይ አለቃ አድርጎ ሾመው።

❖ ከዚህም በኋላ ናቡከደነጾር ሌላ ሕልም አየ ያንንም ተረጐመለት እንዲህም ብሎ አስረዳው ስለታበይክ እግዚአብሔር ከሰው መካከል አውጥቶ ከአራዊት ጋራ በዱር ሰባት ዓመት ያኖርህ ዘንድ አለው፤ እንደ እንስሳም ሣር ትበላለህ ከሰባት ዓመትም በኋላ ወደ መንግሥትህ ይመልስሃል በማለት ይህም ተፈጸመበት።

❖ ናቡከደነጾር ከሞተ በኋላ መልአክ በግድግዳ ላይ የጻፋትን ለልጁ ለብልጣሶር ተረጐመለት በቤተ እግዚአብሔር ዕቃ በጠጣ ጊዜ ጽሑፉ የተቆጠረ የተመጠነ የተመዘነ እንደሆነ ትርጓሜውም ዙፋኑንና መንግሥቱን እግዚአብሔር ለሌላ የሰጠው መሆኑን ገለጠለት፤እንዲህም አለው ቢመዝንህ ጐደሎ ሆነህ አገኘህ መንግሥትህንም ለፋርስ አሳልፎ ሰጠ ትንቢቱም ተፈጸመች፤እግዚአብሔርም እስከ ዓለም ፍጻሜ የሚነግሡትን ነገሥታት በራእይ አሳየው የሐሳዊ መሲሕንም መገለጥ አሳየው።

❖ ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔርነቱን ክብር ልዕልናውን ጌትነቱን አሳየው፤ የክበር ባለቤት ክርስቶስን ወደ ዓለም መምጣቱን ትንቢት ተናገረ ሱባኤዎችንም ወሰነ እንዚያ ሱባኤዎችም በተፈጸሙ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጣ፤ ክርስቶስ ይመጣል ይገድሉታልም ለኢየሩሳሌምም መዳኛዋ ይሆናታል ብሎ ትንቢት እንደ ተናገረ።

❖ የክብር ባለቤት ከሆነ ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት በኋላ ኢየሩሳሌም እንደምትጠፋ ቤተ መቅደስም እንደሚፈርስ የተናገረው ትንቢት ሁሉ ተፈጸመ፤ በባቢሎን አገርም ቤል የሚባል ጣዖት ነበረ ምግብንም ሁልጊዜ ዐሥራ ሁለት ጫን በሚፈጅ ቻል ዐሥራ ሁለት መስፈሪያ ስንዴ አርባ በግ ሰባት ፊቀን የወይን ጠጅ እያወጣጡ ይሰጡት ነበር፤ ንጉሡም ሁልጊዜ ይሰግድለታል ቤል ጣዖትም ከንጉሡ ቤት የሚሰጡትን የሚበላና የሚጠጣ ይመስለው ነበር ።

❖ ንጉሡም ዳንኤልን ለቤል የማትሰግድ ለምንድን ነው አለው፤ ዳንኤልም ንጉሡን እኔስ ሰማይንና ምድርን ለፈጠረ ፍጥረቱንም ሁሉ በሕያውነት ለሚያኖር አምላክ እንጂ የሰው እጅ ለሠራው ጣዖት አልሰግድም አለው፤ ንጉሡም ቤል ሕያው ያልሆነ ይመስላሃልን በየነጋታው እንዲበላ እንዲጠጣ አታይምን አለው፤ ዳንኤልም በንጉሡ ሳቀበት ንጉሥ ሆይ ይበላል ይጠጣል እያሉ አያታሉህ ይህ ውስጡ ጭቃ ላዩ ናስ ነው ምንም ምን አይበላም አይጠጣም አለው።

❖ ንጉሡም ተቆጣ የጣዖቱንም ካህናት ጠራቸው እውነት ነውን ቤል አምላክ አይበላም አይጠጣምን አላቸው፤ ሁልጊዜ የምንሰጠውን በዕውነት ይበላል ይጠጣል አሉት።



❖ ከዚህም በኋላ በመሸ ጊዜ ከጣዖቱ ዘንድ መብሉንና መጠጡን ሁሉ ንጉሡ እየተመለከተ ካህናቱ አስቀምጠው ወጡ፤ የጣዖቱ ካህናትም ከወጡ በኋላ ዳንኤል አመድ አምጡ ብሎ አዘዘ አመጡለትም፤ ንጉሡም ከዚያ ሁኖ እያየ በጣዖቱ ቤት ውስጥ ነሰነሰው።

❖ ንጉሡም በቁልፉ ከዳንኤል ጋር በአንድነት ቈለፉት አተሙትም ወደ ማደሪያቸውም ሔዱ፤ የጣዖቱ ካህናት ግን ከምድር በታች ውስጥ ለውስጥ መግቢያ ቀዳዳ ነበራቸው ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋራ በሌሊት በዚያ ገብተው በሉ ጠጡ በመጡበትም ተመለሱ፤ በማግሥቱም ንጉሡ መጥቶ የጣዖቱን ቤት ከፈተ ራሱ ከአኖረው መብሎች ምንም አላገኘም ንጉሥም ቤል ሆይ ፈጣሪዬ ዳንኤልን ያሳፈርከው አንተ ገናና ነህ ብሎ ጮኸ።

❖ ዳንኤልም ሳቀ ለንጉሡም የወንዶችና የሴቶችን የልጆችንም ፍለጋቸውን በአመድ ላይ አሳየው፤ ንጉሡም የጣዖቱን ካህናት ይዞ መረመራቸው እነርሱም ውስጥ ለውስጥ ተሠውረው የሚገቡበትንና የሚወጡበትን ለንጉሡ አሳዩት፤ ያን ጊዜ ንጉሡ ተቆጥቶ የጣዖቱን ካህናት ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋራ ገደላቸው ጣዖቱንም ለዳንኤል ሰጠው፤ ዳንኤልም ሰበረው ምኲራቡንም አፈረሰ።



❖ ከዚህ በኋላ ደግሞ የባቢሎን ሰዎች የሚአመልኩትና የሚሰግዱለት ታላቅ ዘንዶ ነበር ንጉሡም ዳንኤልን ይህንንስ አምላክ አይደለም ትለዋለህን እነሆ ሕያው ነው ይበላል ይጠጣል ናስ ነው ትለው ዘንድ አትችልምና ስገድለት እንጂ አለው፤ ደንኤልም ለንጉሡ እንዲህ ብሎ መለሰለት እኔስ በሕያውነት ከሚኖር ከእግዚአብሔር በቀር ለሌላ አልሰግድም ግን ያለ ሰይፍና ያለ በትር ይህን ከይሲ እገድለው ዘንድ አሰነሰብተኝ አለው፤ ንጉሥም አሰናበትኩህ አለው።
❖ ዳንኤልም ጠጉርና አደሮ ማር ወስዶ እንደ እንቁላልም አድበልብሎ በእሳት አጋለው በሞራም ጠቅልሎ ለከይሲው አጐረሰው በዋጠውም ጊዜ ሆዱ ተሰንጥቆ ሞተ ዳንኤልም የባቢሎን ሰዎች ሆይ አምላካችሁን ተመልከቱ አላቸው፤ፐየባቢሎን ሰዎችም በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቆጡ ወደ ንጉሡም ተሰብስበው አይሁዳዊው ዳንኤል ነግሦአልን እነሆ ቤልን ሰበረው ካህናቶቹንም ገደላቸው ከዚያም ደግሞ ዘንዶውን ገደለው አሁን እርሱን ዳንኤልን እንድንገድለው ካልሰጠህን አንተን ቤተ ሰብህንም እንገድላለን አሉት።

❖ ንጉሡንም እጅግ በአስጨነቁት ጊዜ ስለ ዳንኤል አዘነ ግን ዳንኤልን ሰጣቸው እነርሱም በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ጣሉት በዚያም ሰባት ቀን ኖረ፤ ከረኀብ ጽናትም የተነሣ እንዲበሉት በሌላ ጊዜ የሚሰጧቸውን በእነዚያ ቀኖች ምንም ምን አልሰጧቸውም ነበር፤ እግዚአብሔርም መልአኩን ወደ እንባቆም ላከው እርሱም በኢየሩሳሌም ውስጥ ለአጫጅዎች ምሳ ተሸክም ሲሔድ በራስ ጠጉሩ ተሸከመው፤ ወስዶም ዳንኤል በአለበት ጉድጓድ ውስጥ አኖረው።

❖ ዳንኤልም ተመግቦ እግዚአብሔርን አመሰገነው በዕንባቆምም ቃል ተረጋጋ በዚያችም ሰዓት እግዚአብሔር የላከው መልአክ ወደ አገሩ ወደ ኢየሩሳሌም መልሶ አደረሰው፤ በሰባተኛዪቱ ቀንም ስለ ዳንኤል እያለቀሰ ንጉሡ ወደ ጕድጓድ መጣ ዳንኤል ሙቶ አንበሶች የበሉት መስሎት ነበርና፥ ወደ ጕድጓዱም ሲመለከት ዳንኤልን አየው አንበሶችም እንደ ድመቶች እግሮቹን እየላሱ ከእግሮቹ በታች እጥፍጥፍ ብለው ተኝተው ነበር።

❖ ንጉሡም እግሮቹን እስከሚልሱ እንደ ድመቶች አንበሶችን ያገረመለትና ያሰገዛለት የዳንኤል አምላክ ታላቅ ነው ብሎ ከፍ ባለ ድምፅ ጮኸ፤ በዚያን ጊዜ ዳንኤልን ከጕድጓድ እንዲያወጡት እነዚያንም የዳንኤልን ጠላቶች ይዘው ለአንበሶች ወደ ጕድጓድ እንዲጥሉአቸው ንጉሥ አዘዘ ወዲያው እነዚያ አንበሶች በንጉሡ ፊት በሏቸው፤ ዳንኤልም የእስራኤል ልጆች ወደ ኢየሩሳሌም እስከ ሚመለሱበት ጊዜ በባቢሎን ኖረ እርሷም ሰባ ዘመን ናት ከዚያም በኋላ በሰላም

በፍቅር አረፈ በጸሎቱ የምትገኝ በረከቱ ከእኛ ጋራ ለዘላለሙ ትኑር አሜን።




📌 መጋቢት 23 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳንኤል (የስሙ ትርጏሜ እግዚአብሔር ፈራጅ ነው ማለት ነው)

2. የአቡነ ፊሊጶስ ፍልሰተ ዐፅማቸው



📌 ወርኀዊ በዓላት
1.ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት

2.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት

3.ቅዱስ ሰሎሞን ንጉሠ እስራኤል

4.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ

5.አባ ሳሙኤል

6.አባ ስምዖን

7.አባ ገብርኤል
👆ትናንትና መለቀቅ የነበረበት ስንክሳር ነበር በጊዜው ስላለቀቅን በጣም ይቅርታ
✥••┈┈┈••●◉ ✞ ◉●••┈┈┈••✥

የአምላክ እናት በዘይቱን ማርያም ከመጋቢት 24 ጀምሮ ለ3 ዓመታት የተገለጠችበት የበረከት በዓል
✥••┈┈┈••●◉ ✞ ◉●••┈┈┈••✥

❖ በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን በእኛ አቈጣጠር ከ1960 ዓ.ም. ላይ ከመጋቢት 24 ጀምሮ በካይሮ ባለችው በዘይቱን ማርያም የብርሃን እናቱ የቅድስት ድንግል ማርያም መገለጥ ይታሰባል።

❖ የአምላክ እናት በዘይቱን ማርያም የመጀመሪያው መገለጧ የተደረገው መጋቢት 24 ሲኾን ብርሃንን ለብሳ በጉልላቱ ላይ ተገልጣ በታየች ጊዜ ወደ 250,000 የሚጠጉ የሚያምኑም የማያምኑም ሕዝቦች ተሰብስበው በታላቅ ደስታና ምስጋና ያን አስደናቂ መገለጥ ይመለከቱ ነበር፡፡

❖ ከአንድ ሳምንት በኋላ ሚያዝያ 1 በድጋሚ በታላቅ ብርሃን ታጅባ በታላቅ ግርማ ተገለጠች፤ ከዚያም በኹለት ሳምንት በሦስት ሳምንት ልዩነት በታላቅ ብርሃን እየታጀበች በመገለጥ እስከ 1963 ዓ.ም. ድረስ ለሦስት ዓመታት ታይታለች፡፡

❖ ንግሥታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በቤተ ክርስቲያኑ ጉልላት ላይ ስትገለጥም ለ2 ሰዓታት ከዚያ የበለጠ ሰዓትም ትታያቸው ነበር፤ መላእክትም በአርአያ ብሩሃን አርጋብ ዙሪያዋን ክንፋቸውን ዘርግተው ሲመላለሱ ይታዩ ነበር፤ ሌላው አስደናቂ የነበረው ክስተት እንደ ዕንቊ ፈርጥ የመሰሉ አስደናቂ ብርሃናት በዙሪያዋ ይፈስሱ ነበር።

❖ ይልቁኑ እጅግ አስደናቂ ቀይ ሕብረ ብርሃናማ ደመና በዙሪያዋ ከብቧ ነበር፤ ልዩ መዐዛ ያለው ዕጣንም በእጅጉ ይሸት ነበር፤ የታመሙትም በእንዲኽ ባለ ክብር በምትገለጥ ጊዜ ከሕመማቸው ይፈወሱ ስለነበር ኹሉም የታመመ ይመጣ ነበር፡፡

❖ ይኽ የተገለጸችበት የዘይቱን ማርያም ቤተ ክርስቲያን እመቤታችን ጌታን ይዛ በተሰሰደች ጊዜ ያረፈችበት የተቀደሰ ቦታ እንደነበር የኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ያስተምራሉ፡፡

❖ በዚያን ጊዜ የነበሩት የግብጽ ፓትርያርክ በቅድስና ሕይወታቸው በጣም የታወቁት አቡነ ቄርሎስ ነበሩና ከብፁዓን አባቶች ጋር የእመቤታችን መገለጽ አማናዊ መኾኑን በዐይናቸው በማየት በጸሎት በሱባዔ በመታገዝ አረጋግጠው ሚያዝያ 26 በይፋ መገለጧን የሚያረጋግጥ ጽሑፍን ጽፈዋል፡፡ ይኽ መገለጧ በመላው ዓለም በመሰማቱ የሮም ቤተ ክርስቲያን ልዑካንን በዚኽ ጉዳይ ወደ እስክንድርያ በመላክ አረጋግጣለች፡፡

❖ ይኽነን በግብጽ በዘይቱን ማርያም የመገለጧን ነገር ምስክርነት በጊዜው የግብጽ ፕሬዝዳንት የነበሩት ጀማል አብደል ናስር ጭምር ያረጋገጡ ሲኾን በግብጽ ቴሌቭዥን በዜና አውታሮች ኹሉ ሲተላለፍ ነበር፡፡

❖ ይኽነን መገለጧን በሚሊየን የሚቈጠሩ የኮፕቲክ ክርስቲያኖችም፣ ካቶሊኮች፣ ሙስሊሞች፣ አይሁዶች፣ ኢአማንያን ጭምር አይተው ምስክርነታቸው ሰጥተዋል።

❖ የመገለጧን 50ኛ ዓመት ግንቦት 4 2010 ዓ.ም. ላይ የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓልን ፓፕ ታዎድሮስ 2ኛ ሥርዐተ ቅዳሴውን ራሳቸው በመምራት ያከበሩ ሲኾን እጅግ ብዙዎች ካህናትና የግብጽ ክርስቲያኖች በዓሉን አድምቀውት ነበር፡፡

❖ ጥንት የነበሩት የኢትዮጵያ ሊቃውንት የእመቤታችንን መገለጥ ይጽፉ ነበር፤ አባ ጽጌ ድንግልም አስቀድማ በደብረ ምጥማቅ በታላቅ ክብር ተገልጻ ለምእመናን የታየችው የአምላክ እናት ለርሱም ትገለጽለት ዘንድ በማሕሌተ ጽጌ መጽሐፉ ላይ

✍️“አመ ትበርቂ በደብረ ምጥማቅ ኀምሰ ዕለታተ። ትእምርተ ገጽኪ ይርአይ እስከ ይትነሣእ ዘሞተ። ሚ መጠነ ማርያም ታሥተፌሥሒ ትፍሥሕተ። ኅድጊሰ ጽጌ ፍቅርኪ በጊዜ ንቃሑ መዓልተ። ብፁዕ ዘርእየኪ በሕልሙ ሌሊተ”
👉የፊትሽን መልክ ያይ ዘንድ የሞተ ሰው እስኪነሣ ድረስ በደብረ ምጥማቅ ለዐምስት ቀናት ያኽል በተገለጽሽ ጊዜ ማርያም ምን ያኽል ደስ ታሰኚ ኖሯል፤ በቀን የታየው የፍቅርሽ አበባ ይቅርና ሌሊት በሕልሙ ያየሽ ምስጉን ነው በማለት ተማፅኗታል፡፡

❖ የእመቤታችን ታማኝ ወዳጅ አባ ጽጌ ድንግል በተመስጦ በመኾን እጅግ ድንቅ የኾነችውን የአምላክን እናት ሥዕል ካየ በኋላ ይኽነን የምስጋና ቃላት ለርሷ ያቀርባል

✍️“ሥዕልኪ ጽግይተ ላሕይ ዘከመዝ ትኤድም በዓለም እፎ ይሤኒ በሰማይ ላሕየ ገጽኪ ማርያም። ሐሤተ ትእምርትኪ እጽገብ አስተርእዪኒ በሕልም። እስመ አውዐየኒ ነደ ፍቅርኪ ፍሕም። አጥፍኦቶ ዘኢይክል ዝናም”
👉ማርያም ሥዕልሽ በዓለም እንዲኽ የምታበራ ከኾነ በሰማይ የፊትሽ መልክ ምን ያምር! አንቺን ከማየት የሚገኘውን ደስታ እጠግብ ዘንድ በሕልም ተገለጪልኝ፤ ዝናብ ሊያጠፋው የማይቻለው የፍቅርሽ እሳት አንድዶኛልና ብሏል፡፡

✍️ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም ይኽነን መገለጧን በእንዚራ ስብሐት መጽሐፉ ላይ
✍️ “ኦ ንግሥት ይገንዩ ለኪ ነገሥት ወለኪ ንግሥታት ይትቀነያ ወኪያኪ የአኲታ ወለስምኪ ይገንያ። ወለኪ ይሰግዳ ወለክብርኪ የሐልያ። ጢሮስ ወሲዶና ሰብአ ግብጽ ወኢትዮጵያ ። ፊንቂ ወሮምያ ማሮን ወአርማንያ። በሥነ ጸዳልኪ ይትፌሥሓ ወበላሕይኪ ይትሐሠያ”
👉ንግሥት ሆይ ነገሥታት ለአንቺ ያገለግላሉ፤ ንግሥታትም አንቺን ያመሰግናሉ፤ አንቺንም ያሞግሳሉ፤ ለስምሽም ያጐነብሳሉ፤ ለአንቺ የጸጋ ስግደትን ይሰግዳሉ፤ ለክብርሽም ምስጋናን ያቀርባሉ፡፡ ጢሮስና ሲዶና የግብጽና የኢትዮጵያ ሰዎች፣ ፊንቄና ሮምያ፣ ማሮንና አርማንያ በወጋገንሽ ውበት ደስ ይሰኛሉ፤ በደም ግባትሽም እሰይ ይላሉ በማለት ገልጦታል፡፡



✍️ የመልክአ ማርያም ደራሲም የአምላኩን እናት ቅድስት ድንግል ማርያምን ፊቷን ለማየት ሽቶ በናፍቆት ኾኖ
✍️ “ሰላም ለመልክእኪ ዘተሠርገወ አሜረ። ዘያበርህ ወትረ ፍቅርትየ አንቲ እንተ ታበድሪ ፍቅረ። አርእዪኒ ገጸ ዚኣኪ ማርያም ምዕረ። ዘኢይሰምዖ ካልእ እንግርኪ ነገረ”
👉ኹልጊዜ (ዘወትር) የሚያበራ ፀሓይን ጌጥ ላደረገ መልክሽ ሰላምታ ይገባል፤ ፍቅርን የምትመርጪ (የምታስቀድሚ) አንቺ ፍቅረኛዬ ማርያም ሌላ የማይሰማው ነገርን እነግርሽ ዘንድ አንድ ጊዜ ያንቺን ፊት ግለጪልኝ በማለት ተማፅኗታል፡፡

❖ የአምላክ እናት ሆይ አስቀድመሽ በደብረ ምጥማቅ በኋላም በዘይቱን ማርያም ተገልጠሽ በረከትን እንዳትረፈረፍሽላቸው ዛሬም ለእኛ ለምንወድሽ ለልጆችሽ ትገለጪልን ዘንድ እንማፀንሻለን፤ በዓለም ላይ የመጣውን መቅሠፍት ከልጅሽ አማልደሽ አርቂልን እኛ ልጆችሽንም በቃል ኪዳንሽ ጥላ ከጥፋት ሠውሪን።



📌 ምንጭ
✍️ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
Forwarded from Bketa @¥
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መጋቢት ፳፭ በዚች ቀን ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ የከበረና የተመሰገነ ሐዋርያ አንሲፎሮስ አረፈ።
  
❖ ይህም ከእስራኤል ልጆች ከቢንያም ነገድ ነው ወላጆቹም የኦሪትን ሕግ የሚጠብቁ ናቸው እርሱም ሥራዎቹን በአየ ጊዜ ትምህርቶቹንም በሰማ ጊዜ ጌታችንን ተከተለው፤ ድንቅ የሆኑ ተአምራቶችን እየተመለከተ ጥቂት ቀን ተቀመጠ ጌታችንም በሀገረ ናይን የመበለቲቱን ልጅ በአስነሣው ጊዜ ከዚያ ነበረ።

❖ ይህን አይቶ ወዲያውኑ አመነ ሌላ ምልክት አልሻም ብልጭ ብልጭ ሲል የነበረ የአይሁድ የሕግ ፋና ትቶ ወደ ዕውነተኛ ፀሐይ ወደ ጌታ ኢየሱስ ቀርቦ ደቀ መዝሙሩ ሆነው እንጂ።

❖ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከዐረገ በኋላ በጽዮን አዳራሽ አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ከሐዋርያት ጋራ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ተቀብሎ ሐዋርያትንም በመከተል በብዙ አገሮች ውስጥ አስተማረ።

❖ ሐዋርያትም በሀገረ አቴና ኤጲስቆጶስ አድርገው ሾሙት በውስጥዋም ወንጌልን በመስበክ ብዙዎችን አሳመነ የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው በትምህርቱና በምክሩ ዕውቀት እንዲአድርባቸው አደረጋቸው በትምህርቱም ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ ፈወሳቸው።
❖ ተጋድሎውንም በፈጸመ ጊዜ በሰላም አረፈ በድል አድራጊነትም የክብር አክሊል ተቀበለ፤ መላ ዘመኑ ሰባ ዓመት ነው በአይሁድ ሕግ ሃያ ዘጠኝ ዓመት በክርስትና ሕግ አርባ አንድ ዓመት ኖረ።
እነሆ የከበረ ሐዋርያ ጳውሎስም በመልእክቶቹ አስታውሶታል ሰላምታም አቅርቦለታል።
በጸሎቱ የምትገኝ በረከቱ ከእኛ ጋራ ለዘላለሙ ትኑር

📌 መጋቢት ፳፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1. ቅዱስ አንሲፎሮስ ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት)

📌 ወርሐዊ በዓላት
1. ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
2. ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
3. ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
4. ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
5. አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)
6. ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ
  ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
    ዘመነ ሐጋይ (በጋን)
  ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ አምላካችን እግዚአብሔር ሁሉን ስነ ፍጥረት የፈጠረ ለሰው ልጆች ጥቅም ነው፤ ጌታ አዝማናትን ወሮችን ሳምንታትን ቀኖችንና ሰዓታትን ፈጥሮ ወስኖ ሰጥቶናል::

❖ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጥንታዊት እንደ መሆኗ ሁሉ ነገሯ በሥርዓት ይፈፀማል፤ በራሷ የዘመን ቀመር ስሌት መሠረትም አንድ ዓመት በአራት ወቅቶች ይከፈላል::

📌  አባታችን ሊቁ ቅዱስ ያሬድም እነዚህን ወቅቶች መሠረት አድርጎ መንፈሳዊ ድርሰቶችን ደርሷል፤ እነዚሕ አዝማናት (ወቅቶች)

⓵ ዘመነ ክረምት (ከሰኔ 26 እስከ መስከረም 25)
⓶ ዘመነ መፀው (ከመስከረም 26 እስከ ታኅሣሥ 25)
⓷ ዘመነ ሐጋይ (ከታኅሣሥ 26 እስከ መጋቢት 25)
⓸ ዘመነ ፀደይ (ከመጋቢት 26 እስከ ሰኔ 25) መሆናቸው ይታወቃል::

ዘመነ ሐጋይ (በጋን) የባረከ አምላክ ዘመነ ፀደይ (መከርን) እንዲባርክልን የንስሐ ጊዜም እንዲያደርግልን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን::
2024/09/28 20:17:24
Back to Top
HTML Embed Code: