Telegram Web Link
Daniel:
✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ ታኅሣሥ ፩ (1) ❖

✞✞✞ እንኩዋን ለታላቁ ነቢይ "ቅዱስ ኤልያስ" :
"ቅዱስ ዼጥሮስ ዘጋዛ" እና "ቅድስት ቤርሳቤህ"
ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+*" ታላቁ ቅዱስ ኤልያስ "*+

=>ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ
ቀጥላ ቅዱስ ኤልያስን ታከብራለች:: "ርዕሰ ነቢያት - የነቢያት ራስም" ትለዋለች:: እርሱ ሰማይን የለጐመ:
እሳትን ያዘነመ: ፍጥረትንም በቃሉ ያዘዘ አባት ነውና::
ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

+ቅዱሱ ትውልዱ (ነገዱ) ኢዮርብዓም ነጥሎ
ከወሰዳቸው እሥራኤል (10ሩ ነገድ) ሲሆን አባቱ
"ኢያስኑዩ" : እናቱ ደግሞ "ቶና (ቶናህ)" ይባላሉ:: በጐ
አምልኮ ነበራቸውና እግዚአብሔር ማሕጸነ ቶናህን ቀድሶ
ይህንን ቅዱስ ፍሬ ፈጠረ::

+ቅዱስ ኤልያስ በተወለደ ቀን በቤታቸው ብርሃን ተሞልቶ
ታይቷል:: ብርሃን የለበሱ 4 ሰዎች (መላእክት)
መጥተውም በእሳት ሰፋድል (መጐናጸፊያ) ሲጠቀልሉት
ወላጆቹ በማየታቸው ደንግጠው ለነቢያትና ለካህናት ነገሯቸው::

+ካህናቱ ግን ነገሩ ቢረቅባቸው "ምን ዓይነት ፍጥረት
ይሆን? በእሥራኤል ይነግሥ ይሆን! ወይስ ነቢይ
ይሆን?" ብለውም አድንቀዋል:: ቅዱስ ኤልያስ ከልጅነቱ
ጀምሮ ኮስታራ: ቁም ነገረኛ: ንጽሕናንም የሚወድ
እሥራኤላዊ ነው::

+ወቅቱ (ከክርስቶስ ልደት 900 ዓመት በፊት) ሕዝቡና
ነገሥታቱ የከፉበት: እግዚአብሔር ተክዶ ጣዖት
የሚመለክበት ነበር:: ድሮ በኢሎፍላውያን እጅ የነበሩት
ጣዖታት (ዳጐንና ቤል) በዚያ ዘመን ወደ እሥራኤል
ገብተው ነበር::

+ቅዱስ ኤልያስ ግን በዚህ ክፉ ትውልድ መካከል
ሆኖም ሥርዓተ ኦሪትን የጠነቀቀ: የንጽሕናና የአምልኮ ሰው ነበር::

+በዚያ ወራትም እግዚአብሔር ለነቢይነት ጠራው::
እርሱም "እሺ" ብሎ ታዞ የእግዚአብሔርን የጸጋ ጥሪ
ተቀበለ::

ቅዱሱ ብዙ ጊዜ ለጉዳይ ካልሆነ ከሰው ጋር መዋል:
ማደርን አይወድምና መኖሪያውን በተራሮችና በዱር
አደረገ::

+በተለይ ደብረ ቀርሜሎስ ለእርሱ ቤቱ ነበር:: በዚህ
ሕይወቱም ከመልከ ጼዴቅ ቀጥሎ:-

1.ለድንግልና (ድንግል ነበርና)
2.ለብሕትውና (ብቸኛ ነበርና)
3.ለምንኩስና (ተሐራሚ ነበርና) በብሉይ ኪዳን መሠረትን
የጣለ ነቢይ ይባላል::

+መቼም በብሉይ ኪዳን የቅዱስ ኤልያስን: በዘመነ
ክርስቶስ የመጥምቁ ዮሐንስን: በዘመነ ሊቃውንት ደግሞ
የአፈ ወርቅ ዮሐንስን ያህል ደፋርና መገሥጽ አስተማሪ
አልነበረም:: በጊዜው ደግሞ አክአብና ኤልዛቤል የሚባሉ
ክፉ ባልና ሚስት በእሥራኤል ላይ ነግሠው ሕዝቡን
ጣዖት አስመለኩት::

+ይባስ ብለው ደግሞ በወይኑ እርሻ አማካኝነት
ኢይዝራኤላዊው ናቡቴን በሃሰት ምስክር ደሙን
አፈሰሱት:: ናቡቴም "የአባቶቼን ርስት አልሸጥም:
አልለውጥም::" በማለቱ እንደ ሰማዕት ይቆጠራል::

+ኤልያስ ግን ይህንን ሲሰማ ወደ አክአብና ኤልዛቤል
ቀርቦ "የናቡቴ ደም በእናንተ ላይ አይቀርም:: የአንቺንም
ደም ውሻ ይልሰዋል" አላቸው:: በዚህ ምክንያትም
ኤልዛቤል ልትገድለው ብትፈልገውም እርሱ
የእግዚአብሔር ነውና አላገኘችውም::

+በዚህ ብስጭትም ይመስላል አንድ ሺህ ነቢያትን
ሰብስባ "ፍጇቸው" አለች:: 900ው ሲታረዱ አንድ
መቶውን ግን ቅዱስ አብድዩ በዋሻ ውስጥ ደብቆ
እየመገበ አተረፋቸው:: በእሥራኤል ውስጥ ግን ዓመጻና
ኃጢአት እየተስፋፋ ሔደ:: የእግዚአብሔርን ስጦታ
እየተመገበ ሕዝቡ ለቤል (ለበዓል) ሰገደ::

+ይህን ጊዜ ግን ቅዱስ ኤልያስ እንዲህ አለ:-
"ሕያው እግዚአብሔር አምላከ ኃይል: ዘቆምኩ
ቅድሜሁ: ከመ ኢይረድ ጠል በእላ መዋዕል ዘእንበለ
በቃለ አፉየ::" ብሎ ዝናም ከሰማይ እንዳይወርድ
ከለከለ::

ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት ሰማይ ዝናም ለዘር ጠል
ለመከር ከመስጠት ተከለከለ::

+ሕዝቡ በኃጢአቱ ምክንያት ተጐዳ:: እርሱን ቁራ
ይመግበው: ምንጭ ፈልቆለት ይጠጣ ነበር:: ይሔው
ቢቀርበት ጸለየ:: እግዚአብሔርም ከፈለገ ኮራት ወደ
ሰራፕታ እንዲወርድ አዘዘው:: በዚያም የነቢዩ ዮናስ እናት
እንጐቻ ጋግራ ብታበላው ቤቷ በበረከት ተሞላ::

+ልጇ ሕጻኑ ዮናስ ቢሞትም በጸሎቱ አስነሳላት::
ቀጥሎም 7 ጊዜ በትጋት ጸልዮ ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት
የዘጋውን ሰማይ ከፍቶታል:: ሕዝቡም ዕለቱኑ ከበረከቱ
ቀምሰዋል::

+ከዚያ አስቀድሞ ግን ከኤልዛቤል 850 ነቢያተ ሐሰትና
ካህናተ ጣዖት ጋር ተወዳድሮ አሸንፏቸዋል:: መስዋዕት
ሰውተው የእርሱን ብቻ እሳት ከሰማይ ወርዳ
በልታለታለችና ሕዝቡ 850ውን ሐሰተኛ ነቢያት በወንዝ
ዳር በሰይፍ መትተዋቸዋል::

+ይሕንን የሰማች ኤልዛቤልም ትገድለው ዘንድ
አሳደደችው:: "አቤቱ ከአባቶቼ አልበልጥምና ውሰደኝ!
ብቻየን ቀርቻለሁና" ብሎ ቢጸልይ እግዚአብሔር ለጣዖት
ያልሰገዱ ሰባት ሺህ ሰዎችን እንዳተረፈ: እርሱንም ወደ
ብሔረ ሕያዋን እንደሚወስደው ብሥራትን ነገረው::

+ደክሞት ተኝቶ ሳለም ቅዱስ መልአክ (ሚካኤል)
ቀስቅሶ ታየው:: እንጐቻ ባገልግል: ውሃ በመንቀል
አቅርቦ "ብላ! ጠጣ!" አለው:: በላ: ጠጣ: ተኛ:: እንደ
ገና ቀስቅሶ አበላው:: በ3ኛው ግን "ብላዕ እስከ ትጸግብ
እስመ ርሑቅ ፍኖትከ - ጐዳናህ ሩቅ ነውና
እስክትጠግብ ብላ" አለው::

+ኤልያስም ለ40 ቀናት ያለ ምግብ ተጉዟል:: ከዚያ
በሁዋላም ምድራዊ ሕብስትን አልተመገበም::
እግዚአብሔር አክአብና ኤልዛቤልን ከተበቀላቸው
በሁዋላም ቅዱስ ኤልያስ በክፋተኞች ላይ 2 ጊዜ እሳትን
አዝንሟል::

+የሚያርግበት ጊዜ ሲደርስም ደቀ መዝሙሩን ኤልሳዕን
"የምትሻውን ለምነኝ" ቢለው "እጥፍ መንፈስህን"
አለው:: 3 ጊዜ ሊያስመልሰው ሞከረ:: ቅዱስ ኤልሳዕ
ግን በብርታት ተከተለው:: ዮርዳኖስን ከፍለው ከተሻገሩ
በሁዋላ ግን ቅዱስ ኤልያስን ሠረገላ እሳት ወርዶ
ነጠቀው:: ለኤልሳዕም እኩሉን ግምጃውን ጣለለት::

+ዛሬ ቅዱስ ኤልያስ በብሔረ ሕያዋን ያለ ሲሆን በዘመነ
ሐሳዌ መሲሕ መጥቶ በሰማዕትነት ከቅዱስ ሔኖክ ጋር ያርፋል:: (ራዕይ)
¤ለተጨማሪ ንባብ ( ከ1ነገ. 17-2ነገ. 2, እና ዕርገተ ኤልያስን ያንብቡ::)

<<ነቢዩ ኤልያስ በእውነት ታላቅ ነው!>>

+"+ ቅዱስ ዼጥሮስ ዘጋዛ +"+

=>ይህ ቅዱስ በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን በታናሽ እስያ
አካባቢ የተወለደ ሲሆን የክቡራኑ የመሣፍንት ልጅ ነው::
በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አድጐ የቁስጥንጥንያ ንጉሥ
ትንሹ ቴዎዶስዮስ ወደ ቤተ መንግስቱ ወሰደው::

+በዚያም "አገረ ገዥ ላድርግህ" ብሎ ቢጠይቀው
"ትንሽ ቆየኝማ" ብሎት ጠፍቶ በርሃ ገብቶ መነኮሰ::
ቅዱስ ዼጥሮስ በምንኩስና ሲጋደል: ካለበት በርሃ
መጥተው በግድ ወስደው: የጋዛ (አሁን የፍልስጤምና
እሥራኤል ደንበር) ዻዻስ አደረጉት::

+ከደግነቱ የተነሳም በቅዳሴ ጊዜ ሥጋ ወደሙ ሲለወጥ
ያየው ነበር:: መላእክትም ያጫውቱት ነበር:: ሕዝቡ
ሲያጠፉ በየዋሕነት ዝም ቢላቸውም ቅዱስ መልአክ ገሥጾታል::

+የፋርስ ነገሥታት አጽመ ሰማዕታትን ሲያቃጥሉም እርሱ
የቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድን አጽም ይዞ ተሰዷል:: ለብዙ
ዘመናት በቅድስና ኑሮም በዚህች ቀን ዐርፏል::

+"+ ቅድስት ቤርሳቤህ +"+
=>ይህቺ እናት አስቀድማ የኦርዮ ሚስት: ቀጥሎ ደግሞ
የልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ሚስትና የሰሎሞን እናት
ለመሆን በቅታለች:: ቁጥሯ ከደጋግ እናቶቻችን ሲሆን
የድንግል ማርያም ቅድመ አያትም ናት:: አንዳንድ
ሊቃውንት ደግሞ ስሟን "ቤትስባ (ቤተ ሳባ)" :
ትውልዷንም ከኢትዮዽያ ያደርጉታል::=>አምላከ ኤልያስ በምልጃው ለሃገራችንና ለሕዝቧ
ርሕራሔውን ይላክልን:: ከቅዱሳኑም በረከትን ይክፈለን::

=>ታሕሳስ 1 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ኤልያስ ርዕሰ ነቢያት
2.ቅዱስ ዼጥሮስ ዘጋዛ
3.ቅድስት ቤርሳቤህ (ቤትስባ)
4.ናቡቴ ኢይዝራኤላዊ
5.አባ ዮሐንስ ሊቀ ዻዻሳት

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ልደታ ለማርያም ድንግል እግዝእትነ
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
4.ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር
5.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላእክት

=>+"+ ለእስራኤል ሁሉ ሥርዓትንና ፍርድን አድርጌ
በኮሬብ ያዘዝኩትን: የባሪያየን የሙሴን ሕግ አስቡ::
እነሆ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ
ነቢዩን ኤልያስን እልክላቹሃለሁ:: መጥቼም ምድርን
በእርግማን እንዳልመታ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ
ልጆች: የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል:: +"+ (ሚል. 4:4)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር>>>
õ-3• ØEñ5 + ¤ ØÈ- s #%
ASR by NLL APPS
ድርሳን ዘቅዱስ ራጉኤል ዘወርሃ ታህሣሥ
https://www.tg-me.com/SinkisarZekidusan2
በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ከቋሚ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

በስመአብ፣ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን፡፡

በወቅታዊ ጉዳዮች ከቋሚ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

“ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን” ሮሜ 8፡35-36

ቤተ ክርስቲያን ልዩ ልዩ ጸዋትወ መከራን፣ ሞትንና ስደትን፣ የመቀበል ታሪኳ ዛሬ የተጀመረ ባይሆንም በአሁኑ ጊዜ የሰው ልጅ ይኽንና መሰል መተኪያ የሌለው ሕይወት የሚያጠፋና ሥጋት ላይ የሚጥሉ ተፈጥሮአዊ፣ ሰብዓዊ ክብሩን የሚያራክስ ተግባራት እንዳይደገሙ ለማድረግ በሚጥርበት ዓለም ችግሩ በተለይም በሀገራችን እየተባባሰ መቀጠሉ እጅግ ያሳስበናል፡፡

በአርሲ ዞን በሹርካ ወረዳ ሶሌ ሚካኤል፣ በዲገሎ ማርያም፣ በሮቤ እንደቶ ደብረ ምጥማቅ ማርያም አብያተ ክርስቲያናት ላይ በተለያዩ ጊዜያት ሠላሳ ስድስት፣ እንዲሁም በሶሌዲገሉና ጢጆለቡ በተባሉ ቀበሌዎች ሃያ ስምንት ኦርቶዶክሳዊያን ከየቤታቸው ተለቅመው ሰማዕትነትን ሲቀበሉ ከእነዚህም ሰባቱ ሴቶችና ሃያ አንዱ ወንዶች ናቸው፡፡ በዚህ ጥቃት የሰባ ዓመት አዛውንትና የሃያ ስምንት ቀን ጨቅላ ሕጻናት ይገኛሉ፡፡ ከጥቂት ቀናት በፊትም በዲገሉ ማርያም ቤተክርስቲያን አምስት ምእመናን ሰማዕት ሲሆኑ የሦስት ምእመናን ቤት ተቃጥሏል። በሮቤ አንዲቶ ደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም አጥቢያ በዓለ ድንግል ማርያምን አክብረው በመመለስ ላይ የነበሩ ሦስት ኦርቶዶክሳዊያን ጨለማን ተገን ባደረጉ ገዳዮች ሰማዕትነት የተቀበሉ መሆኑን ከሀገረ ስብከቱ ሪፖርት ደርሶን ከሐዘናችን ገና ሳንጽናና ይባስ ብሎ በማዕከላዊ ጐንደር ሀገረ ስብከት የጐንደር ዓቢየ እግዚእ ኪዳነ ምሕረት የአቋቋም መምህር የሆኑት መምህር ፍሥሐ አለምነው ባልታወቀ ግለሰብ በድንጋይ ተወግረው መገደላቸው እና ኅዳር 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሌሊቱ 11፡00 ላይ የማዕከላዊ ጐንደር ዞን ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት በኲረትጉሃን ዘርዓዳዊት ኃይሉ ባልታወቁ ግለሰቦች በጥይት ተመተው መገደላቸው በእጅጉ ከማዘናችንም በላይ የጉዳዩን አሳሳቢነት የሚያረጋግጥ አድራጐት ሆኗል፡፡

በዚህ መግለጫ በቅርብ የተፈጸመውን ለማቅረብ ተሞከረ እንጅ ተመሳሳይ ግድያና፣ ስደት፣ የንብረት ውድመትና መፈናቀል የየዕለት ዜናችን ከሆነ ሰንብቷል፡፡ ለአብነትም ያህል በወለጋ፣ በጐንደር፣ በጐጃም፣ በወሎ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በመሳሰሉት እየተፈጸመ ያለው ድርጊት መንግሥትና ሕገ መንግሥት ባለበት ሀገር፣ የውጭ ወራሪና ድንበር ተሻጋሪ ጠላት ሳይኖርብን፣ እርስ በርሳችን በምናደርገው መጠፋፋት፣ ሃይማኖት ተኮር ጥላቻዎች፣ የንፁሐን ሕይወት መቀጠፉና የሀገርን ሀብት መውደሙ እኛንም ሆነ በመላው ዓለም መፍቀሬ ሰብእ የሆኑ የሰብዓዊ ክብር አስጠባቂ ተቋማትን ሳይቀር ማሳዘኑ ቀጥሏል፡፡

ይህ ሁኔታ በታሪክ ከመመዝገቡ በላይ የዜጎች በሕይወት የመኖር፣ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የመሥራት፣ የአካልና የንብረት ደኅንነታቸው መጠበቅ፣ የሃይማኖትና የእምነት ነፃነት መከበር፤ የዜጎች ሁለንተናዊ ደኅንነት የመጠበቅና የማስጠበቅ ግዴታ ያለባቸውን አካላት በሙሉ በምድርም ሆነ በሰማይ ተጠያቂ የሚያደርግ ጉዳይ ነው፡፡ እየተፈጠረ ባለው አስከፊ መከራ፣ በጭካኔ የተሞላ ድርጊት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ማጣት የዜጎችን ሕይወት፣ አካልና ንብረት፣ የእምነት ተቋማትን፣ መተኪያ የሌላቸው የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ቅርሶችና መስሕቦችን ሲያወድም፣ በሀገር ሁለንተናዊ ደኅንነትና በሕዝቦች ትሥሥር ላይ የፈጠረው አለመተማመን በቀላሉ የማይመለስ አደጋ ነው፡፡

ይኽ እንደተጠበቀ ሆኖ ከተከሰተው ረሀብ፣ ድርቅ፣ የኑሮ ውድነትና ሥራ አጥነት በተጨማሪ በየቦታው በተፈጠሩ አለመረጋጋቶችና ግጭቶች ምክንያት በርካቶች ቀያቸውን ለቀው፣ መነኰሳት ገዳማትን ትተው ተሰደዋል፤ ወላድ እናቶች፣ ሕሙማንና አረጋውያን በሕክምና እጦት እያለቁ ነው፣ ሕፃናትና ወጣቶች ከጤናማ እድገትና ከትምህርት ገበታ ተደናቅፈዋል፣

በመሆኑም

፩. ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ከግጭትና ከጦርነት፣ ከርስ በርስ መገዳደል ወጥተው በውይይትና በምክክር፣ በኃላፊነትና በተጠያቂነት ስሜት የታላቋን ሀገር መልካም ስምና ክብር እንዲሁም የዜጎቿን ሁለንተናዊ ደኅንነት የመጠበቅና የማስጠበቅ ተግባር ቅድሚያ እንዲሰጡ በጥብቅ እናሳስባለን፡፡

፪. በቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ንፁሐን ምእመናንና ተቋማት ላይ ያተኮሩ ጥቃቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ፣ መንግሥትና የሚመለከታችሁ ሁሉ ዋስትና እንድትሰጡ፣ ወንጀል ፈጻሚዎችም ለፍርድ እንዲቀርቡ፣ ድርጊቱንም መላው ዓለም እንዲያወግዘው ቋሚ ሲኖዶስ በአጽንዖት ይጠይቃል፡፡

፫. ከቤተ ክርስቲያን አልፎ የሀገርና የዓለም ሀብት የሆኑ ቅዱሳን መካናት፣ እንደ ዝቋላ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ ደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም፣ አሰቦት ደብረ ወገግ አቡነ ሳሙኤል ገዳም እና አካባቢው፣ ደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ ገዳምና አካባቢው የመሳሰሉ ሁሉ ታላላቅ አድባራትና ገዳማት አደጋ የተጋረጠባቸው በመሆኑ ልዩ ጥበቃ እንዲደረግላቸው እናሳስባለን።

፬. በመጨረሻም በየቦታው የሚያጋጥሙ ተመሳሳይ ጥቃቶችን ለማስቀረት ይቻል ዘንድ የሚመለከታቸው አካላት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ለቅድመ ወንጀል መከላከል ሥራ ቅድሚያ በመስጠት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እያሳሰብን ለቅድመ ወንጀል መከላከል ሥራው መሳካትም በየደረጃው ያላችሁ አህጉረ ስብከት የስጋት መረጃዎችን ለሚመለከተው ሁሉ በማሳወቅ ግዴታችሁን እንድትወጡ በጥብቅ እናሳስባለን፡፡

ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን ለሞቱት የተዋሕዶ ኦርቶዶክሳውያን ወገኖቻችን አስበ ሰማእትታን እንዲከፍልልን፣ ለወገኖቻቸው ሁሉ መጽናናት እንዲሰጥልን፣ ስለስሙና ስለሰብዓዊ ማንነታቸው በመከራና ሥጋት ወስጥ ለሚገኙ ወገኖቻችን ሁሉ ጽናቱንና ብርታቱን እንዲሰጥልን፣ አጥፊዎችን እንዲገስጽልን፣ ስደትና አለመረጋጋትን እንዲያርቅልን፤ የሀገራችንን አንድነትና ሰላም፣ የቅድስት ቤተክርስቲያንን ሕልውና እንዲጠብቅልን የአምላካችን የልዑል እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Forwarded from Bketa @¥
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

አሜን



✍️"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"
📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ



ቀናችንን በጸሎት እንጀምር


🔔 ስንክሳር ዘወርኀ ታኅሣሥ ፪


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ታኅሣሥ ሁለት በዚች ቀን ናቡከደነፆር ከአባታቸው ጋር ለማረካቸው ሦስት ለሆኑ ለይሁዳ ንጉሥ ለኢዮአቄም ልጆች እግዚአብሔር ኃይልን አደረገላቸው።

❖ ንጉሥ ናቡከደነፆር ከአባታቸው ከይሁዳው ንጉሥ ከኢዮአቄም ጋር የማረካቸው አናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ እግዚአብሔር በዚህች ዕለት ታላቅ ተአምር አድርጎላቸዋል፡፡


🔔 በዚችም ቀን ቅዱስ አውክያኖስ በሰማዕትነት አረፈ። እርሱም ሃይማኖቱን ጠብቆ ሰዎች አባለ ዘሩን እስከ ቆረጡት ድረስ ተጋድሎውን የፈጸመ ነው እግዚአብሔርንም አመሰገነው።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።



🔔 በዚችም ቀን ሰባት ሺህ ሠላሳ ሦስት ለሆኑ ሰማዕታት መታሰቢያቸው ነው እሊህም ለቅዱስ ፋሲለደስ አገልጋዮቹና ዘመዲቹ የሆኑ ናቸው ዳግመኛም የአብላፍታንና ከዐረብ ወገን የሆነ የሰማዕት አንበስ የመነኰሰ ናትናኤል መታሰቢያቸው ነው።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።

🔔 በዚችም ቀን በላይኛው ግብጽ ከሚኖሩ ሰዎች ወገን የሆነ ቅዱስ አባት አባ ሖር አረፈ፤ ደግነት ያለው መነኰስ በመሆን ጽኑዕ ገድልን ተጋደለ በአምልኮቱና በተጋድሎው ከቅዱሳን ሁሉ ተለይቶ በብዙዎች ላይ ከፍ ከፍ አለ ለብቻ መኖርን ስለወደደ ወደ በረሀ ወጥቶ በገድል ተጠምዶ ብዙ ዘመናት ኖረ።

❖ የበጎ ሥራ ጠላት የሆነ ሰይጣንም ቀንቶበት በግልጥ ታየውና በበረሀ ውስጥ ግን አንተ ድል ትነሣናለህ በዚህ ሰው የለምና ጽኑ ኃይለኛ ከሆንክ ወደ እስክንድርያ ከተማ ና ብሎ ተናገረው።

❖ አባ ሖርም ይህን በሰማ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኃይል ተማምኖ ወደ እስክንድርያ ከተማ ሒዶ ለእሥረኞችና ለችግረኞች ደካሞች ውኃ የሚቀዳ ሆነ በአንዲት ዕለት ሦስት ፈረሶች በከተማው ውስጥ እየዘለሉ ሲያልፉ አንዱ ፈረስ አንዱን ሕፃን ረገጠውና ወዲያውኑ ሞተ ሰይጣንም በሰዎች ልብ አደረና ይህን ሕፃን ያለዚህ አረጋዊ መነኵሴ የገደለው የለም ብለው አሰቡ አባ ሖርም መጣና ሕፃኑን አንሥቶ ታቀፈው በልቡም በመጸለይ ክብር ይግባውና ወደ እግዚአብሔር ማለደ በመስቀል ምልክትም በላዩ አማተበ የሕፃኑም ነፍስ ተመለሰች ድኖም ተነሣ ለአባቱም ሰጠው ወደ ከተማ ውጭ ሸሽቶ በመሔድ ወደ በዓቱ ገባ ፈልገውም አላገኙትም ጽድቅንና ትሩፋትንም በመሥራት ብዙ ዘመናት በገድል ተጠምዶ ኖረ።


❖ የሚሞትበት ጊዜ ሲቀርብ ብዙዎች ቅዱሳንን ሲጠሩት አያቸው እጅግም ደስ አለው ልጆቹንም ሰብስቦ በምንኲስና ሥርዓት ጸንተው ትሩፋትን እንዲሠሩ አዘዛቸው ክብር ይግባውና ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እርሱ እንደሚሔድ ነገራቸው እነርሱም እጅግ አዘኑ ጥቂት ቀንም ታሞ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ አባት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።


📌 ታኅሳስ 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱሳን ሠለስቱ ደቂቅ (አናንያ: አዛርያ: ሚሳኤል)

2.አባ ሖር ጻድቅ

3.ቅዱስ አውካቲዎስ ሰማዕት

4.አባ አንበስ ሰማዕት

5.7,033 ሰማዕታት (የቅዱስ ፋሲለደስ ማሕበር)

6.ቅዱስ ናትናኤል መነኮስ



📌 ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)

2.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ

3.ቅዱስ አቤል ጻድቅ

4.ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)

5.ቅዱስ ዮሐንስ ነቢይ (መጥምቀ መለኮት)

6.ሊቁ አባ ሕርያቆስ

7.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
Daniel:
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለቅዱሳን "ሠለስቱ ደቂቅ" እና "አባ ሖር ገዳማዊ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

" ታኅሣሥ 2 "

+*" ቅዱሳን ሠለስቱ ደቂቅ "*+

=>አናንያ: አዛርያና ሚሳኤልን እንዲያው በቀድሞው አጠራር ሠለስቱ ደቂቅ (ሦስቱ ሕጻናት) እንላቸዋለን እንጂ ለእኛስ በእድሜም: በጸጋም: በትሩፋትም አባቶቻችን ናቸው::

+ቅዱሳኑ የወቅቱ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአቄም ልጆች ናቸው:: ናቡከደነጾር ኢየሩሳሌምን አቃጥሎ ሕዝቡን ሲማርክ አብረው ተማርከው ባቢሎን ወርደዋል::

+ንጉሡ ከምርኮ ወጣቶች ለቤተ መንግስት ሲመርጥ ሦስቱ ቅዱሳንና ዳንኤል ተመርጠው የምቾት ሕይወት ተዘጋጅቶላቸው ነበር:: ነገር ግን በምግብና በአምልኮ ከአሕዛብ ጋር መተባበርን አልፈለጉምና ምርጫቸው ጾምና ጸሎት ከቆሎ ጋር ሆነ:: ምንም እንኩዋ በቤተ መንግስት ውስጥ ቢኖሩ: ምንም የነገሥታት ልጆች ቢሆኑ ለእነርሱ ከእግዚአብሔር ፍቅር የተሻለ አልነበረምና በጥሬ ቆሎ ተወስነው ኖሩ::

+አምላካቸው ከሃሊ ነውና በውበትም ሆነ በጥበብ በባቢሎን ምድር ከነርሱ የሚደርስ አልተገኘም:: ንጉሡም በባቢሎንና በአውራጃዋ ላይ ሾማቸው:: ስማቸውንም በአማልክቱ ስም ሲድራቅ: ሚሳቅና አብደናጐ አላቸው::

+ከነገር ሁሉ በሁዋላ አሕዛብ ቀንተውባቸዋልና የክፋት አዋጅን አሳወጁ:: ናቡከደነጾር 60 ክንድ ቁመት ያለውን የወርቅ ምስል አቁሞ ስገዱ ቢላቸው አይሆንም በማለታቸው ተቃጥለው እንዲሞቱ እሳት ተፈረደባቸው:: ነበልባሉ ከጉድጉዋዱ ወደ ላይ 49 ክንድ ቢነድም ቅንጣት ያህል ፍርሃት አልጎበኛቸውም::

+ወደ እሳቱም ሲጥሏቸው መልዐከ አድኅኖ ቅዱስ ገብርኤል ደርሶ አዳናቸው:: ከሆነው ነገር የተነሳም አሕዛብ አፈሩ:: ናቡከደነጾር ግን ከዙፋኑ ተነስቶ የቅዱሳኑን አምላክ እግዚአብሔርን ባረከ::

+ከዚያች ቀን በሁዋላ አናንያ: አዛርያና ሚሳኤል በአት አጽንተው: በጾምና በጸሎት ተወስነው ኑረዋል:: ነፍሳቸው ከሥጋቸው ስትለይ ታላቅ ንውጽውጽታ ሆኗል:: ቅዱስ ዳንኤልና ናቡከደነጾር ተሯሩጠው ቢሄዱ ሦስቱም በአንድነት ዐርፈው ተገኝተዋል:: ንጉሡ በእጅጉ ይወዳቸው ነበርና በወርቅ በተለበጠ ሳጥን ቀብሯቸዋል:: ስሞት ከመካከላቸው ቅበሩኝ በማለቱ ዛሬ ድረስ ለበቁ አባቶች የአራቱ መቃብር ባቢሎን ውስጥ ይታያል::

+ቅዱሳን አናንያ: አዛርያና ሚሳኤል (ሲድራቅ: ሚሳቅና አብደናጐ) ያረፉት ግንቦት 10 ቀን ሲሆን ዘመኑም ከክርስቶስ 500 ዓመት በፊት ነው:: ይህቺ ዕለት ደግሞ ናቡከደነጾር ወደ እሳት ሲጥላቸው መልአከ እግዚአብሔር እነርሱን ያዳነበት ቀን ናት::

+አምላካቸው ከአሳት ባወጣቸው በዚህ ቀንም:-
"ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ::
ስቡሕኒ ውዕቱ ወልዑልኒ ውዕቱ ለዓለም::" የሚለውን ምስጋና ፈጣሪ ገልጾላቸው ደርሰውታል:: በእሳቱ ውስጥ ሆነው ተናግረውታል::

+ድርሰታቸው 2 ወገን ሲሆን ባለ ስድስት አንቀጹ ምስጋናቸው ከ600 ዓመት በሁዋላ ክርስቶስ እንደሚወለድ የሚያሳይ ነው:: ሌላኛውና 33 አንቀጾች ያሉት ምስጋናቸው ደግሞ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ለ33 ዓመታት እንደሚመላለስ ያጠይቃል::

+ቅዱሳን ሠለስቱ ደቂቅ ካረፉ ከ900 ዓመታት በሁዋላ (ማለትም ከክርስቶስ ልደት በ400 ዓመታት) ታላቁ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ቤተ ክርስቲያንን አንጾላቸው ነበርና አጽማቸውን ሊያገኝ ተመኘ::

+ወዳጁን ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ጠርቶ "አባ! አጽመ ቅዱሳንን ባቢሎን ወርደህ አምጣልኝ?" አለው:: ቅዱሱ ሐጺር ዮሐንስም በደመና ተጭኖ ባቢሎን ገባ:: በቅዱሳኑ መቃብር ፊትም ሰግዶ አለቀሰ:: ሠለስቱ ደቂቅም "ወዳጃችን! ምን ሆንክ?" አሉት::

+ቅዱሱም መልሶ "ወደ ግብጽ እንሒድ:: አባ ቴዎፍሎስ ይፈልጋቹሃል" አላቸው:: እነሱም "ለቅዱሱ ቴዎፍሎስ እንዲህ በለው:: እግዚአብሔር ዋጋህን ይክፈልህ:: ግን አጽማችን እስከ ዓለም ፍጻሜ ባቢሎንን አይለቅም:: ለክብርህ ግን እንመጣለን::"

+"ለምልክትም ይሆን ዘንድ መብራት ሳታበራ በሌሊት ጠብቀን በለው" ብለው ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ባርከው ሸኙት:: ሐጺርም መጥቶ መልአክቱን አደረሰ:: በዕለተ ቅዳሴ ቤታቸው ቅዱሳን:- ቴዎፍሎስ: ቄርሎስ: ሐጺር ዮሐንስና ሌሎችም ከምዕመናን ጋር በጨለማ ሳሉ ቤተ ክርስቲያኑ ቦግ ብሎ በራ::

+እጅግ የሚደነቅ ብርሃንም ከበባቸው:: በብርሃኑ መካከል ሠለስቱ ደቂቅ ሲያልፉ በጐ መዓዛ ሸተተ:: ሕዝቡም በደስታና በዝማሬ የቅዱሳኑን ቅዳሴ ቤት አክብሯል::

+"+ አባ ሖር ገዳማዊ +"+

=>በዚህ ስም የሚጠሩ ብዙ ቅዱሳን ከጻድቃንም: ከሰማዕታትም አሉ:: ከጻድቃኑ መካክል: በተለይም ከታላላቆቹ አንዱ ቅዱስ አባ ሖር ነው:: አባ ሖር በዘመነ ጻድቃን የነበረና በደግነቱ የሚታወቅ ክርስቲያን ነው::

+በዓለም ያለውን በጐነት ሲፈጽም ድንግልናውን እንደ ጠበቀ ገዳም ገባ:: በዚያም በአገልግሎት ተጠምዶ ዘመናትን አሳለፈ:: ከዚያም መነኮሰ:: ከመነኮሰ በሁዋላ ደግሞ አበውን በማገልገል: በጾምና በጸሎት: በበጐው ትሕርምት ሁሉ የተጠመደ ሆነ:: ግራ ቀኝ የማይል ("ጽኑዕ ከመ ዓምድ ዘኢያንቀለቅል" እንዲሉ አበው) ብርቱ ምሰሶ ሆነ::

+ሰይጣንም አባ ሖርን በብዙ ጐዳና ፈተነው:: ከእርሱ ጋር መታገል ከአቅሙ በላይ ሲሆንበት በገሃድ ተገለጠለት:: "አንተኮ የምታሸንፈኝ በአበው መካከል ስለ ሆንክ ነው:: በበርሃ ብቻህን ባገኝህ ግን እጥልሃለሁ" ሲል ተፈካከረው::

+አባ ሖርም የዳዊትን መዝሙር እየዘመረ ጭው ወዳለ በርሃ ገባ:: በዚያም ሰይጣን ታገለው:: ግን ሊያሸንፈው አልቻለም:: ምክንያቱም ኃያሉ እግዚአብሔር ከጻድቁ ጋር ነበርና:: ሰይጣን እንደ ተሸነፈ ሲያውቅ እንደ ገና ሌላ ምክንያት ፈጠረ::

+አሁንም በገሃድ ተገልጦ ተናገረው:: "በዚህ በበርሃ ማንም በሌለበት ብታሸንፈኝ ምኑ ይደንቃል! ወደ ከተማ ብትሔድ ግን አትችለኝም" አለው:: ቅዱስ ሖር ግን አሁንም ሰይጣንን ያሳፍር ዘንድ በፈጣሪው ኃይል ተመክቶ ወደ ዓለም ወጣ::

+"እግዚአብሔር ያበርሕ ሊተ ወያድኅነኒ: ምንትኑ ያፈርሃኒ - እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው:: የሚያስፈራኝ ማነው!" ሲል (መዝ. 26:1) ይጸልይ ነበር:: በከተማም በነበረው ቆይታ አልባሌ ሰው መስሎ ደካሞችን ሲረዳ: ነዳያንን ሲንከባከብ: ለድሆች ውሃ ሲቀዳ: እንጨት ሲሰብር ይውልና ሌሊት እንደ ምሰሶ ተተክሎ ሲጸልይ ያድራል::

+ሰይጣን በዚህም እንዳላሸነፈው ሲያውቅ ከሰዎች ጋር በሐሰት ሊያጣላው ሞከረ:: ፈረስ ረግጦ የገደለውን አንድ ሕጻን ሲያይ ሰይጣን ሰው መስሎ ወደ አባ ሖር እየጠቆመ "እርሱ ነው ረግጦ የገደለው" አላቸው:: የሕጻኑ ወገኖች ቅዱሱን ሲይዙት አባ ሖር "ቆዩኝማ" ብሎ የሞተውን ሕጻን አንስቶ ታቀፈው::

+ጸልዮ በመስቀል ምልክት አማተበበትና "እፍ" ቢልበት ሕጻኑ ከሞት ተነሳ:: ለወላጆቹም ሰጣቸው:: ይሕንን ድንቅ የተመለከቱ የእስክንድርያ ሰዎችም ይባርካቸው ዘንድ ሲጠጉት ተሰውሯቸው በርሃ ገባ:: ውዳሴ ከንቱን ፈጽሞ ይጠላት ነበርና::

+ጻድቁ አባ ሖር ቀሪ ዘመኑን በበርሃ አሳልፎ በዚህች ቀን በክብር ዐርፏል::

=>አምላከ ጻድቃን ቅዱሳን ከነደደ እሳት: ከዲያብሎስ ክፋትም ይሰውረን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::
=>ታሕሳስ 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱሳን ሠለስቱ ደቂቅ (አናንያ: አዛርያ: ሚሳኤል)
2.አባ ሖር ጻድቅ
3.ቅዱስ አውካቲዎስ ሰማዕት
4.አባ አንበስ ሰማዕት
5.7,033 ሰማዕታት (የቅዱስ ፋሲለደስማሕበር)
6.ቅዱስ ናትናኤል መነኮስ

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)
2.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
3.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
4.ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
5.ቅዱስ ዮሐንስ ነቢይ (መጥምቀ መለኮት)
6.ሊቁ አባ ሕርያቆስ
7.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ

=>+"+ ናቡከደነፆርም መልሶ:- 'መልአኩን የላከ: ከአምላካቸውም በቀር ማንንም አምላክ እንዳያመልኩ: ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን: የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን: በእርሱ የታመኑትን ባርያዎቹን ያዳነ: የሲድራቅና የሚሳቅ የአብደናጎም አምላክ ይባረክ::' +"+ (ዳን. 3:28)

✞✞✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞✞✞
Audio
ስንክሳር ዘወርሃ ታህሣሥ ሁለት(፪)
https://www.tg-me.com/SinkisarZekidusan2
Forwarded from Sintu.D
በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ውስተ ቤተመቅደስ

ስታድጊ በቤተመቅደስ
በቅዱስ በእግዚአብሔር መንፈስ
አጊጠሽ በትህትና
ተውበሽ በቅድስና
ምግብሽ የሰማይ መና
ከምድር አደለምና
አካላዊ ቃል መርጦሻል
ትውልዱ ብፅዕት ይሉሻል

እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ ለገባችበት ዓመታዊ በዓል አደረሰን አደረሳችሁ
††† እንኳን ለእግዝእትነ ማርያም (#በዓታ): አቡነ ዜና ማርቆስ ጻድቅ እና ቅዱስ ፋኑኤል ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም †††

††† ከነገደ ይሁዳ የሚወለድ ቅዱስ ኢያቄም የሚባል ደግ ሰው ከነገደ ሌዊ (አሮን) የተወለደች ሐና የምትባል ደግ ሴት አግብቶ በሕጉ ጸንተው: በሥርዓቱ ተጠብቀው ይኖሩ ነበር:: ነገር ግን በዘመኑ ሰዎች "ልጅ የላችሁም" በሚል ይናቁ ነበር::

ኦሪታውያን ልጅ የሌለውን "ኅጡአ በረከት-ከጸጋ እግዚአብሔር የራቀ" ነው ብለው ያምኑ ነበር:: ኢያቄምና ሐና ልጅ እንዲሰጣቸው ሲያዝኑ: ሲጸልዩ ዘመናቸው አልፎ አረጁ:: እነሱ ግን የሚያመልኩት የአብርሃምና ሣራን አምላክ ነውና ተስፋ አልቆረጡም::

የለመኑትን የማይነሳ ጌታ በስተእርጅናቸው ድንቅ ነገርን አደረገላቸው:: አንድ ቀን እርግቦች ከጫጩቶቻቸው ጋር ሲጫወቱ የተመለከተች ቅድስት ሐና ፈጽማ አለቀሰች:: "እንስሳትና አራዊትን: እጽዋትን ሳይቀር በተፈጥሯቸው እንዲያፈሩ የምታደርግ አምላክ ምነው ሐናን ድንጋይ አድርገህ ፈጥረሃታልን?" ብላ አዘነች::

ይህን የተመለከተ ቅዱስ ኢያቄም ወደ ተራራ ወጥቶ ሱባኤ ያዘ:: ለ40 ቀናትም ሲጸልይና ሲማለል ቆየ:: በ40ኛው ቀን ሁለቱም ሕልምን ያልማሉ::
እርሱ:-
*ነጭ ርግብ ሰማያትን ሰንጥቃ ወርዳ: በሐና ቀኝ ጀሮ ገብታ: በማሕጸኗ ስትደርስ አየ::

እርሷ ደግሞ:-
*የኢያቄም በትር አብቦ: አፍርቶ: ጣፋጭ ፍሬውን ሰው ሁሉ ሲመገበው ታያለች:: ቅዱስ ኢያቄም ከሱባኤ እንደ ተመለሰ ያዩትን ተጨዋውተው "ፈቃደ እግዚአብሔር ይሁን" አሉ:: ለ7 ቀናትም በጋራ እግዚአብሔርን ሲለምኑ ሰነበቱ::

በ7ኛው ቀን (ማለትም ነሐሴ 7) መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ክንፉን እያማታ ወደ እነርሱ ወረደ:: "ዓለም የሚድንባት: የፍጥረት ሁሉ መመኪያ የሆነች ልጅ ትወልዳላችሁ" ብሏቸው ተሠወራቸው:: እነርሱም ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑ::

እንደ ሥርዓቱም አብረው አድረው እመ ብርሃን ተጸነሰች::
"ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተጸነስኪ . . .
ድንግል ሆይ! ኃጢአት ባለበት ሥጋዊ ፍትወት የተጸነስሽ አይደለም" እንዳለ ሊቁ:: (ቅዳሴ ማርያም)

††† "ለጽንሰትኪ በከርሥ::
እንበለ አበሳ ወርኩስ::
ወለልደትኪ እማሕጸን ቅዱስ . . ."
"ድንግል ሆይ! መጸነስሽ ያለ በደል (ያለ ጥፋት) ነው: የተወለድሽበት ማሕጸንም ቅዱስ ነው . . ." (መጽሐፈ ሰዓታት፣ ኢሳ. 1:9)
"ኢያቄም ወሐና ወለዱ ለነ ሰማየ::
ሰማዮሙኒ አስረቀት ለነ ፀሐየ::"
"ኢያቄምና ሐና ሰማይን ወለዱልን::
ሰማያቸው ደግሞ ፀሐይን አወጣችልን (ወለደች-አስገኘችልን)"

የዓለማችን ወላጆች ነቢያት ሐዋርያትን: ጻድቃን ሰማዕታትን ወልደው ከብረዋል: ተመስግነዋል:: ኢያቄምና ሐና ግን ፍጥረት ሁሉ በአንድነት ቢሰበሰብ በእግሯ የረገጠችውን ትቢያ እንኳ መሆን የማይችል: የሰማይና የምድር ንግሥት: የእግዚአብሔርን እናት: እመቤታችን ማርያምን ወለዱልን::

ኢያቄም ወሐና ለእግዚአብሔር የሥጋዌ አያቶቹም ተባሉ:: ቅዱሳኑ እስኪያረጁ ድረስ በመካንነት አዝነው ፀልየዋል:: ንጽሕናቸውና ደግነታቸው ተመስክሮላቸው ድንግል ማርያምን አግኝተዋል::

እመቤታችን ነሐሴ 7 ቀን ተጸንሳ ግንቦት አንድ ቀን ተወልዳለች:: ከአዳም ስሕተት በኋላ ያለ ጥንተ አብሶ የተወለደች የመጀመሪያዋ ሰው ድንግል ማርያም ሆናለች:: (ኢሳ. 1:9)

††† የእመቤታችን የዘር ሐረግ:-
*አዳም-ኖኅ-አብርሃም-ይስሐቅ-ያዕቆብ=
*በእናቷ:-
ሌዊ-ቀዓት-እንበረም-አሮን-ቴክታና በጥሪቃ-ሔኤሜን-ዴርዴን-ቶና-ሲካር-ሔርሜላና ማጣት-ሐና::

*በአባቷ በኩል:-
ይሁዳ-ፋሬስ-ሰልሞን-ቦኤዝ-እሴይ-ዳዊት-ሰሎሞን-ሕዝቅያስ-ዘሩባቤል-አልዓዛር-ቅስራ-ኢያቄም ይሆናል::

ለጨለማው ዓለም የብርሃን መቅረዝ ሆና ትጠቅመን ዘንድ: አንድም ትንቢቱና ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም: በሊባኖስ ተራራ ከ2,023 ዓመታት በፊት ተወልዳለች::

ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና ድንግል እመ ብርሃንን ከወለዱ በኋላ ለ3 ዓመታት እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ: ነዳያንንም ሲጠግኑ ኖሩ:: በእነዚህ ዓመታትም ቅድስት ሐና ድንግል ማርያምን ከእቅፏ አውርዳት አታውቅም::

ቅዱሳን መላእክትም ዘወትር እየመጡ ያጫውቷት ይንከባከቧትም ነበር:: 3 ዓመት በሞላት ጊዜም በቅድስት ሐና አሳሳቢነት ብጽዓታቸውን (ስዕለታቸውን) ይፈጽሙ ዘንድ ተዘጋጁ::

እንደ ሥርዓቱ የሚዘጋጀውን (መባውን) ይዘው ወደ ቤተ መቅደስ ሲደርሱ አበው ካህናትና የመቅደሱ አገልጋዮች ሁሉ ሊቀበሏቸው ወጡ:: ሕዝቡ: ሊቃነ ካህናት ቅዱሳን ዘካርያስና ስምዖን: ኢያቄም ወሐና ከድንግል ማርያም ጋር ቆመው ሳሉም ሊቀ መላእክት ፋኑኤል ከሰማይ ወርዶ ረቦ ታየ::

ከቅዱስ ዘካርያስ ጀምሮ ሁሉም ሰው ሕብስትና ጽዋዑን ለመቀበል ቀረበ:: ግን መልአኩ ራቀ:: ድንግል ማርያም በቀረበች ጊዜ ግን ከመሬት አፈፍ አድርጐ አንስቶ: ክንፉን ጋርዶ ሰማያዊውን ማዕድ መገባት:: በዚህ ደስ የተሰኙ ካህናትና ሕዝቡ እየዘመሩ በታኅሣሥ ሦስት ቀን ወደ ቤተ መቅደስ አስገብተዋታል::

አማናዊት መቅደሰ መለኮት ድንግል ማርያም ወደ ኦሪቱ ቤተ መቅደስ በገባችበት ዕለት ጸሎታችን እንድትሰማን እንደ ሊቃውንቱ:-
"ማርያም አንቲ ሰዋስው ዘምድረ ሎዛ::
ዲቤኪ ትዕርግ ጸሎትየ ከመ ጼና ሠናይ መዓዛ::
ኀበ ለነፍስየ ታሰስል ትካዛ" እንላለን:: (አርኬ)

††† አቡነ ዜና ማርቆስ ጻድቅ †††

††† አባ ዜና ማርቆስ በሃገራችን በተለይ በደቡብ ምድረ ጉራጌ ስመ ጥር ሐዋርያዊ ጻድቅ ናቸው:: ምድረ ሽዋ ደግሞ እርሳቸውን ጨምሮ የብዙ ቅዱሳን መፍለቂያ ናትና ክብር ይገባታል:: ነቢየ ጽድቅ ዳዊት "ትውልደ ጻድቃን ይትባረኩ-የጻድቃን (የቅኖች) ትውልድ ይባረካል" (መዝ. 111) ያለው ነገር በምድረ ዞረሬ (ጽላልሽ) ተፈጽሟል::

ሦስት ወንድማማች የተባረኩ ካህናት በስፍራው ነበሩ:: ስማቸው ጸጋ ዘአብ: እንድርያስና ዮሐንስ ይባላል:: ከእነዚህ መካከልም ጸጋ ዘአብ: እግዚእ ኃረያን አግብቶ ኮከበ ከዋክብት ተክለ ሃይማኖትን ሲወልድ ካህኑ ዮሐንስ ደግሞ ዲቦራ የምትባል ደግ ሴት አግብቶ ዜና ማርቆስን ወልዷል::

የአቡነ ዜና ማርቆስ ጽንሰታቸው ሚያዝያ 30 በብሥራተ ማርቆስ ወንጌላዊ ሲሆን ልደታቸው ደግሞ ኅዳር 24 ቀን በበዓለ ሱራፌል ካህናተ ሰማይ ነው:: ዘመኑም 13ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው::

ዜና ማርቆስ በተወለዱ በ40 ቀናቸው አጐታቸው ቀሲስ እንድርያስ (የ72 ዓመት ሽማግሌ ናቸው) ሊያጠምቁ ቀረቡ:: ሕጻኑ ዜና ማርቆስ ግን ከእናታቸው እቅፍ ወርደው 3 ጊዜ "እሰግድ ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ" እያሉ ቢሰግዱ የመጠመቂያው ገንዳ ውኃ ፈላ::

ይህንን የተመለከቱት ካህኑ ደንግጠው ወጥተው ሲሮጡ ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላእክት ተገልጦ "አትፍራ! ይልቁኑ ከጠበሉ ራስህን ተቀባ" አላቸው:: እንዳላቸው ቢያደርጉ ራሰ በራ ነበሩና ጸጉር በቀለላቸው::

ሕጻኑ ዜና ማርቆስ ግን 5 ዓመት ሲሞላቸው ወደ ጉባኤ ቤት ገብተው በአጭር ጊዜ ብሉይ ከሐዲስ ጠነቀቁ:: ዲቁናን ተቀብለው ወደ ቤታቸው ሲመለሱም ሽፍቶች አግኝተው: በትራቸውን ቀምተው: አንገላተው ሰደዋቸዋል::
ወዲያው ግን ያቺ በትር እባብ ሁና ሽፍቶችን አጥፍታቸዋለች:: ጻድቁ ለቤተሰብ እየታዘዙ: ንጽሕናቸውንም እየጠበቁ ኑረው 30 ዓመት ሲሞላቸው ወላጆቻቸው ግድ ብለው ማርያም ክብራ ለምትባል ወጣት አጯቸው::

እሳቸው ግን በሠርጉ ሌሊት ከጫጉላ ቤት ጠፍተው በርሃ ገቡ:: ከዚያም በቅዱስ መልአክ መሪነት ሃገረ ምሑር ደረሱ:: በቦታውም ጣዖትን ሰባብረው: ተአምራትንም አድርገው: ሕዝቡን ወደ ክርስትና መለሱ:: መስፍኑ አውጊት ግን ተፈታተናቸው: አሠራቸው: አሥራባቸው::

በጦር እወጋለሁ ሲል ግን መሬት ተከፍታ ከነ ተከታዮቹ ውጣዋለች:: ከ5 ዓመታት በኋላ ግን ማልደው: ከሰጠመበት አውጥተው አጥምቀውታል:: ቀጥለውም ምድረ ጉራጌ ወርደው: ሕዝቡን አሳምነው አጥምቀዋል::

የአዳልን ሕዝብና ንጉሡን አብደልማልን አስተምረው ያጠመቁም እርሳቸው ናቸው:: ድል አሰግድ የሚባለውን መስፍንም ያሳምኑ ዘንድ ጠንቅዋዮቹን ድል አድርገው አጥፍተዋል::

ጻድቁ ዜና ማርቆስ ከዚህ ሐዋርያዊ ሥራቸው በተጨማሪ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ምንኩስናን ከተቀበሉባት ቀን ጀምረው በጾም: በጸሎትና በሰጊድ ኑረዋል:: ፀሐይን በምድረ ጉራጌ እስከ ማቆም ደርሰውም ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል::

አእላፍ ደቀ መዛሙርትን ሲያፈሩ 200 አንበሶች በቀኝ: 200 ነብሮች በግራ ይከተሏቸው ነበር:: ደብረ ብሥራትን ጨምሮም ገዳማትን አንጸዋል:: በመጨረሻም የምሕረት ቃል ኪዳንን ከፈጣሪ ዘንድ ተቀብለው ታኅሣሥ ሦስት ቀን በ140 ዓመታቸው ዐርፈዋል::

††† የእመቤታችን ድንግል ማርያም ጣዕሟ: ፍቅሯ: ጸጋዋና በረከቷ ይደርብን::

††† ታኅሣሥ 3 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም
2.ብጹዓን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱሳን ካህናት ዘካርያስና ስምዖን
4.ቅዱስ ፋኑኤል ሊቀ መላእክት
5.አቡነ ዜና ማርቆስ ጻድቅ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ጻድቅ (ዘደብረ በንኮል)
2.አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
3.ቅዱስ ቄርሎስ ሊቅ (ዓምደ ሃይማኖት)

††† "ድንግል ሆይ! አንገታቸውን እንደሚያረዝሙ እንደ እብራውያን ሴቶች ልጆች በዋዛ ያደግሽ አይደለሽም:: በቅድስናና በንጽሕና በቤተ መቅደስ ኖርሽ እንጂ::
ድንግል ሆይ! ምድራዊ ሕብስትን የተመገብሽ አይደለም:: ከሰማየ ሰማያት የበሰለ ሰማያዊ ሕብስትን እንጂ::
ድንግል ሆይ! ምድራዊ መጠጥን የጠጣሽ አይደለም:: ከሰማየ ሰማያት የተቀዳ ሰማያዊ መጠጥን እንጂ::" †††
(ቅዳሴ ማርያም)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Audio
ስንክሳር ዘወርሃ ታህሣሥ ሦስት(፫)
https://www.tg-me.com/SinkisarZekidusan2
õ  a ܓ -F5 ¨ Õ  %- ¥5¨ Õ
ASR by NLL APPS
ገድለ አቡነ ዜና ማርቆስ ከምዕራፍ አሥር https://www.tg-me.com/SinkisarZekidusan2
2024/10/01 07:26:12
Back to Top
HTML Embed Code: