Telegram Web Link
"ድንግል ሆይ አንገታቸውን እንደሚያገዝፉ እንደ ዕብራውያን ሴቶች ልጆች በዋዛ ያደግሽ አይደለም፤ በንጽሕና በቅድስና በቤተ መቅደስ ኖርሽ እንጂ፤ ድንግል ሆይ ምድራዊ ኅብስትን የተመገብሽ አይደለም፤ ከሰማየ ሰማያት የበሰለ ሰማያዊ ኅብስትን ነው እንጂ፤ ድንግል ሆይ ምድራዊ መጠጥን የጠጣሽ አይደለም፤ ከሰማየ ሰማያት የተቀዳ ሰማያዊ መጠጥን ነው እንጂ፤ ድንግል ሆይ ከአንቺ አስቀድሞ ከአንቺም በኋላ እንዳሉ ሴቶች መተዳደፍን የምታውቂ አይደለም፤ በንጽሕና በቅድስና ያጌጥሽ ነሽ እንጂ፤ ድንግል ሆይ የሚያታልሉ ጐልማሶች ያረጋጉሽ አይደለም የሰማይ መላእክት ጐበኙሽ እንጂ እንደተነገረ ካህናትና የካህናት አለቆች አመሰገኑሽ እንጂ....."

(አባ ሕርያቆስ - ቅዳሴ ማርያም)
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"         
         ቀናችንን በጸሎት እንጀምር


🛎 ስንክሳር ዘወርኀ ታኅሣሥ ፬

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ታኅሣሥ አራት በዚች ቀን የሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ወንድም የተመሰገነ ቅዱስ ሐዋርያ እንድርያስ በምስክርነት አረፈ።

❖ ለዚህም ቅዱስ ይሰብክ ዘንድ ዕጣው በልዳ ሀገር ወጣ ከእርሷም ብዙዎች በቅዱስ ጴጥሮስ ትምህርት አምነው ነበር አንደበቱ የሚጥም በሥራው ሁሉና በአምልኮቱ የተወደደ ያማረ ደቀ መዝሙሩ ፊልሞና አብሮት ነበር ሐዋርያ እንድርያስም ከፍ ካለ ቦታ ላይ ወጥቶ ጣዕም ባለው አንደበቱ ከቅዱሳት መጻሕፍት እንዲአነብ አዘዘው።

❖ የጣዖታት ካህናትም የሐዋርያ እንድርያስን መምጣት በሰሙ ጊዜ አማልክቶቻቸውን ይረግሙ እንደሆነ ሊጣሏቸው ሽተው የጦር መሳሪያቸውን ይዘው መጡ።

❖ በዚያንም ጊዜ ፊልሞና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከወርቅና ከብር የሰው እጅ ሥራ የሆኑ የአሕዛብ አማልክቶቻቸው አፍ አላቸው አይናገሩም፣ ዐይን አላቸው አያዩም፣ ጆሮ አላቸው አይሰሙም፣ አፍንጫ አላቸው አያሸቱም፣ እጅ አላቸው አይዳስሱም፣ እግር አላቸው አይሔዱም፣ በጉሮሮአቸውም አይናገሩም፣ የሚሠሩአቸውና የሚአምኑባቸው ሁሉ እንደእነርሱ ይሁኑ እያለ ሲያነብ ሰሙት።

❖ ስለ ቃሉ ጣዕምና ስለ ንባቡ ማማር ልባቸው ከክህደት ማሠሪያ ተፈታ ወደ ቤተ ክርስቲያንም ገብተው ከሐዋርያ እንድርያስ እግር በታች ሰገዱ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም አመኑ እርሱም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት አስተምሮ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው ከእሳቸውም ጋር ጣዖትን ከሚያመልኩ ውስጥ ብዙዎች አምነው ተጠመቁ።
❖ በዚያ ወራትም እንዲህ ሆነ በልዳ አገር አቅራቢያ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ቄስ ነበረ ለእርሱም አንድ ልጅ አለው እርሱም ከባልንጀራው ጋር ሲጫወት በድንገት ገደለው የሟች አባትም ልጄን የገደለ ልጅህን አሳልፈህ ስጠኝ ሲል ቀሲስ ዮሐንስን ያዘው ቀሲስ ዮሐንስም የሀገር ሰዎችን ሔጄ ሐዋርያ እንድርያስን እስከማመጣው ዋስ ሁኑኝ እርሱ የሞተውን ያነሣልኛልና ብሎ ለመናቸው እነርሱም በተዋሱት ጊዜ ቀሲስ ዮሐንስ ወደ ሐዋርያ እንድርያስ ሒዶ ችግሩን ሁሉ ነገረው።
❖ ሐዋርያ እንድርያስም ቀሲስ ዮሐንስን እንዲህ አለው ከእኔ ዘንድ የሚጠመቁ ብዙ ሕዝቦች ስላሉ ከአንተ ጋር እሔድ ዘንድ አይቻለኝም ግን ደቀ መዝሙሬ ፊልሞና አብሮህ ይሒድ እርሱ የሞተውን ያስነሣልሃል አለው።
❖ ሐዋርያ እንድርያስም ከቄሱ ጋር ሒዶ የሞተውን ያስነሣለት ዘንድ ፊልሞናን አዘዘው ወደ ከተማውም ሲቀርቡ ቄሱንና ፊልሞናን ሰዎች በከተማው ውስጥ ሁከት ሁኗልና አገረ ገዥው እንዳይገድላችሁ ወደ ከተማ አትግቡ አሏቸው። ፊልሞናም እንዲህ አለ እኔ የመምህሬን ትእዛዝ መተላለፍ አልችልም የሞተውን ለማንሣት እሔዳለሁ እንጂ መኰንኑ ቢገድለኝም መምህሬ እንድርያስ መጥቶ እኔንም አስቀድሞ የሞተውንም ያስነሣናል።

❖ ሲገባም መኰንኑን ኒቆሮስን ተገናኘውና ፊልሞና እንዲህ አለው ሀገርን ለምን ታጠፋለህ የሾሙህ ከክፉ ነገር ሁሉ ሀገርን ልትጠብቅ አይደለምን መኰንኑም ይህ ሰው ነፍሰ ገዳይ ይመስላል አለ ወታደሮችንም ይዛችሁ ሰቅላችሁ ግረፉት አላቸው ወታደሮችም ይገርፉት ዘንድ ይዘው ሰቀሉት።
❖ ፊልሞናም ኒቆሮስ የተባለውን መኰንን እንዲህ አለው የበደልኩት በደል ሳይኖር ለምን ሰቅለህ ትገርፈኛለህ እኔ ታናሽ ብላቴና ስሆን ደቀ መዝሙሩን እኔን ሰቅለው ሲገርፉኝ ይመለከት ዘንድ ለመምህሬ እንድርያስ ማን በነገረው አለ፤ ወደ ወታደሮችም ፊቱን መልሶ እንዲህ አላቸው ከውስጣችሁ የሚራራና የሚያዝንልኝ የለምን በመሰቀልና በመገረፍ እንዳለሁ ሒዶ ለመምህሬ እንድርያስ ስለ እኔ ይነግረው ዘንድ አለ ከቃሉ ጣዕም የተነሣ ወታደሮች ተሰብስበው መጥተው አለቀሱ።

❖ በዚያንም ጊዜ አዕዋፍ ሁሉ መጥተው እኛን ላከን ብለው ተናገሩት ድምቢጥ ቀርባ እኔ በአካሌ ቀላል ነኝና እኔን ላከኝ አለችው አንቺስ አመንዝራ ነሽ ከወገንሽ በመንገድ አንዱን ያገኘሽ እንደሆነ ከርሱ ጋር ትጫወቺአለሽ ፈጥነሽ አትመለሽም አላት ከዚህም በኋላ ቁራ ቀርቦ እኔን ላከኝ አለው ፊልሞናም እንዲህ አለው አንተም በቀድሞ ዘመን በተላክህ ጊዜ ለአባታችን ኖኅ የመልእክቱን መልስ አልመለስክም አለው።

❖ ፊልሞና ግን ርግብን ጠርቶ እንዲህ አላት እግዚአብሔር የዋሂት ብሎ ስም ያወጣልሽ ከአዕዋፍ ሁሉ የተመረጥሽ ወገን አንቺ ለአባታችን ኖኅ በመርከብ ውስጥ ሳለ መልካም ዜና አድረሰሽለታልና አባታችን ጻድቅ ኖኅም ባርኮሻልና አሁንም ወደ ልዳ ከተማ ወደ መምህሬ እንድርያስ ሔደሽ ንገሪው ሰቅለው እየገረፉኝ ነውና ወደ እኔ ወደ ደቀ መዝሙሩ ፊልሞና ይመጣ ዘንድ።
❖ በዚያን ጊዜ ርግብ ሒዳ ለሐዋርያ እንድርያስ ነግራ የመልእክቱን መልስ ይዛ ተመለሰች የተባረከች ርግብም ለፊልሞና መምህርህ እንድርያስ እኔ እመጣለሁና አይዞህ በርታ ብሎሃል አለችው።

❖ በዚያንም ጊዜ ርግብ በሰው ቋንቋ ለፊልሞና ስትነግረው ኒቆሮስ መኰንን ሰማት እጅግም አደነቀ ፈጥኖ ተነሥቶም ራሱ በእጁ ፊልሞናን ፈትቶ ከተሰቀለበት አወረደው ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም አመነ።
❖ ሰይጣን ግን ቀና በመኰንኑ ሚስት ልቡና አድሮ አሳበዳትና ልጅዋን ገደለች አገልጋዮቹም ሒደው የሆነውን ሁሉ ለመኰንኑ ነገሩት ፊልሞናም አትፍራ አይዞህ አለው።
❖ ከዚህም በኋላ ርግብን ጠርቶ ወደ መኰንኑ ቤት ሒጂ እንዳይሸበሩ በጸጥታ እንዲቆዩ ንገሪያቸው አላት ርግቢቱም ሒዳ ፊልሞና እንዳዘዛት ለሕዝቡ ነገረቻቸው ሕዝቡም ርግቢቱ በሰው ቃል ስትናገር በሰሙ ጊዜ እጅግ አድንቀው ፊልሞና ወዳለበት ተሰበሰቡ።

❖ በዚያንም ጊዜ ሐዋርያ እንድርያስ ደረሰ አስቀድሞ የሞተውን ያስነሣው ዘንድ ደቀ መዝሙሩ ፊልሞናን አዘዘው እርሱም ክብር ይግባውና ወደ ጌታችን በመጸለይ ከሞት አስነሣው ሁለተኛም ወደ መኰንኑ ቤት ሔዱ ሐዋርያ እንድርያስም የመኰንኑን ልጅ እናቱ የገደለችውን አስነሣው የመኰንኑንም ሚስት አዳናት ከእርሷ የወጣውንም ያንን ጋኔን ይዞ በሰው ሁሉ ፊት ምድርን ከፍቶ ወደ ጥልቅ አዘቅት አሰጠመው።

❖ ከዚህም በኋላ ሐዋርያ እንድርያስ ርግብን ጠርቶ ዕድሜሽ ስንት ነው አላት እርሷም ስምንት ዓመት ነው አለችው፤ እርሱም ለደቀ መዝሙሬ ስለታዘዝሽ ወደ ዱር ሒጂ ለዓለም ሰዎች ከመገዛት ነጻ ሁኚ አላት ወዲያውኑ ሔደች ሕዝቡም ይህን ድንቅ ሥራ አይተው አምነው ሁሉም የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቁ።

❖ ከዚህም በኋላ ከእርሳቸው ዘንድ ወጥቶ አክራድ አክሲስ አክሳስያ ሴኒፎሮስም ወደ ተባሉ አገሮች ሒዶ አስተማረ ከሐዋርያ በርተሎሜዎስም ጋር ተገናኝቶ ጋዝሪኖስ ወደ ሚባል አገር በአንድነት ሔዱ የሀገር ሰዎች እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ እስከተመለሱ ድረስ ረዳት ከተደረገላቸው ገጸ ከልብ ጋር ገብተው ወንጌልን ሰበኩ ድንቅ ተአምራትንም አደረጉ።

❖ ከዚህም በኋላ ሐዋርያ እንድርያስ ወደ ሌሎች አገሮች ሒዶ አስተማረ በፍጻሜውም ወደ አንዲት አገር ገብቶ ቅዱስ ወንጌልን ሰበከ የዚያች አገር ሰዎች ግን እጅግ የከፉ ስለሆኑ ትምህርቱን አልተቀበሉትም።
❖ ከቅዱስ ሐዋርያ እንድርያስም ድንቅ ተአምራትን ስለአዩ ያመኑ አሉ ያላመኑ ግን ወደእነርሱ እንዲመጣና እንዲገድሉት በቅዱስ እንድርያስ ላይ ክፉ ምክርን መክረው በተንኩል ወደርሱ መልእክተኞችን ላኩ መልእክተኞችም ወደ ቅዱስ እንድርያስ ሲደርሱ ማራኪ የሆነ ትምህርቱን ሰሙ ፊቱንም ብርሃን ሁኖ አዩትና ክብር ይግባውና በጌታችን አመኑ ደቀ መዝሙሮችም ሆኑት ወደላኳቸውም አልተመለሱም።
❖ ሁለተኛም በእሳት ሊአቃጥሉት ተማከሩና ተሰብስበው ወደርሱ ሔዱ እርሱ ግን የልባችሁን ክፋት ትታችሁ ትድኑ ዘንድ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እመኑ ይህ ካልሆነ ግን ለእኔ ያላችኋት ይቺ እሳት እናንተን ትበላለች አላቸው።
❖ ቃሉንም ባልሰሙ ጊዜ ከሰማይ እሳት ወርዳ እንድታቃጥላቸው ክብር ይግባውና ጌታችንን ለመነው ወዲያውኑ እሳት ወርዳ አቃጠለቻቸው በዚያች አገር አውራጃዎች ሁሉ ዜናው ተሰማ እጅግም ፈርተው ብዙዎች ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ።

❖ የጣዖታት አገልጋዮች ግን ይህን ሁሉ ድንቅ ተአምራት አይተው አላመኑም ቅዱስ ሐዋርያ እንድርያስን ሊገድሉት ፈለጉት እንጂ።
❖ ከዚህም በኋላ ተሰብስበው መጡና ቅዱስ ሐዋርያ እንድርያስን ይዘው ወሰዱት ታላቅ ግርፋትንም ገርፈው በከተማው ሁሉ ራቁቱን አዙረው ከወህኒ ቤት ጨመሩት በማግሥቱ የሚሰቅሉትን ሰው ልማዳቸው እንዲሁ ነውና ሰው ሊገድሉ በሚሹ ጊዜ ወስደው በእንጨት ላይ ይሰቅሉታል እስከሚሞትም ድረስ በደንጊያዎች ይወግሩታል።
❖ በዚያችም ሌሊት የተመሰገነ ሐዋርያ አባታችን እንድርያስ እንደ ፊተኞቹ እሳት ወርዳ እንድትበላቸው ክብር ይግባውና ጌታችንን ክርስቶስን ለመነው ክብር ይግባውና ጌታችንም ተገለጠለትና ከዚህ ዓለም የምትለይበት ጊዜ ደርሷልና አትዘን አለው ሰላምታም ሰጥቶት ከእርሱ ተሠወረ የተመሰገነ የሐዋርያ እንድርያስም ልቡናው ፈጽማ ደስ አላት።
❖ ንጋትም በሆነ ጊዜ ወስደው በዕንጨት ላይ ሰቀሉት እስከ ሞተ ድረስም በደንጊያዎች ወገሩት አማንያን ሰዎችም መጥተው ሥጋውን ወስደው ገንዘው ቀበሩት ከእርሱም ታላላቅ የሆኑ አስደናቂዎች ተአምራት ተገለጡ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ በሐዋርያ እንድርያስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

               አርኬ
✍️ ሰላም ለከ ረድአ ኢየሱስ ኬንያ። እንተ ሰበከ ወንጌሉ ወመሀርከ በኒቆምድያ። እዜምር ለከ ወእየብብ በሃሌ ሉያ። አንቅሐኒ እምኀኬትየ እንድርያስ ሐዋርያ። ከመ በእዴከ ነቅሐት እሙታን ልድያ

🛎 በዚችም ቀን የቅዱሳን የአባ ጻዕ፣ የአባ ያዕቆብ፣ የዘካርያስ፣ የስምዖን፣ የታዖድራና የታውፍልዖ መታሰቢያቸው ነው። በረከታቸውም ከእኛ ጋር ተኑር ለዘላለሙ አሜን።

📌 ታኅሣሥ 4 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
2.አባ ጻዕ
3.አባ ያዕቆብ
4.ቅድስት ታዖድራ

📌 ወርኀዊ በዓላት

1.ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ
2.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
3. ዮሐንስ ዘሐራቅሊ (ሰማዕት)
††† እንኳን ለቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ †††

††† ቅዱሱ ሐዋርያ ተወልዶ ያደገው በቤተ ሳይዳ አካባቢ ሲሆን የሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ትንሽ ወንድም ነው:: አባቱም ዮና ይባላል:: ገና ከልጅነቱ ጀምሮ አሣ ማጥመድን ከትልቅ ወንድሙ ተምሯል:: እድሜው ከፍ ባለ ጊዜ ኦሪትን ተምሮ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ሆኗል::

ከእርሱም እያገለገለ ለ6 ወራት ተምሯል:: በወቅቱ ከወንጌላዊው (ወልደ ዘብዴዎስ) ዮሐንስ ጋር ቅርብ ባልንጀራም ነበር:: ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ ያን ድንቅ ምሥጢረ ሥላሴ ከተመለከቱትም አንዱ ነው::

ጌታ ከጾም (ከገዳመ ቆረንቶስ) በተመለሰ ጊዜ እንድርያስ መንፈስ ቅዱስ አነሳስቶት ተከትሎታል:: መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ "ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘያዐትት ኃጢአተ ዓለም - የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ እነሆ" ማለቱን ሰምቶ ቅዱስ እንድርያስ ጌታን ተከተለ::

በዚህም የመጀመሪያው የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመባል በቃ:: (ዮሐ. 1:47) ሊቁ ማር ገላውዴዎስም እመቤታችንን ሲያመሰግናት:-
"ለሐዋርያ እንድርያስ ቀዳማዊ ማርያም ሃይማኖቱ::
(ለመጀመሪያው ሐዋርያ ለእንድርያስ ሃይማኖቱ ማርያም አንቺ ነሽ)" ብሏል:: (መልክዐ ስዕል)

ቅዱሱ ሐዋርያ ስሉጥ (ፈጣን) አገልጋይ እንደ ነበርም ወንጌል ይነግረናል:: (ዮሐ. 6:9, 12:22) ለ3 ዓመታት ከ3 ወራት ከጌታ እግር ሥር ተምሮ: በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሎ ምን ሃገረ ስብከቱ ልዳ ብትሆን ብዙ አሕጉረ ዓለምን ሰብኳል::

ሐዋርያው ከጌታ ጋር በመርከብ ውስጥ ተነጋገረና ቅዱስ ማትያስን ሰውን ከሚበሉ ሰዎች እጅ አዳነ:: ቅዱስ እንድርያስ 30 ቀናት የሚፈጅ የባሕር ላይ ጉዞ ለማድረግ ከአርድእቱ ጋር ወደ ወደብ ቢሔድም መርከበኞች ሁሉ አናሳፍርም በማለታቸው የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወጣት መርከበኛ መስሎ ሐዋርያውንና አርድእቱን የሠላሳውን ቀን መንገድ በሰዓታት ልዩነት እንዲጨርሱ አድርጓል::

ቅዱስ እንድርያስም እንዲሁ ሰው መስሎት ለጌታችን ስለ ጌታችን ሰብኮለታል:: መርቆታልም:: መርከበኛው ጌታችን መሆኑን ሲያውቅም ደንግጦ አልቅሷል::

¤"ሶበ አእመረ ኪያሁ ወጠየቀ አምሳሎ::
ዘተናገርኩ በድፍረት ምስሌከ ኩሎ::
ሥረይ ሊተ ጌጋይየ ወኅድግ ይቤሎ::" እንዲል "ማረኝ?" ብሎታል:: ጌታችንም "አይዞህ እኔ ካንተ ጋር ነኝ" ብሎታል::

እንድርያስ ማለት "ተባዕ" (ደፋር: ብርቱ) ማለት ነው:: ድፍረት ሥጋዊ: ድፍረት መንፈሳዊ አለና:: "ድፍረት ሥጋዊ" በራስ ተመክቶ ሌሎችን ማጥቃት: ለጥቃትም ምላሽ መስጠት ነው::

"ድፍረት መንፈሳዊ" ስለ ክርስቶስ: ስለ ቀናችው ሃይማኖት ሲሉ በራስ ላይ መጨከን: ራስን አሳልፎ መስጠት: መከራንም አለመሰቀቅ ነው:: ይሕንንም አበው "ጥብዓት" ይሉታል::

ቅዱስ እንድርያስም ለጊዜው በቤተ እሥራኤል መካከል ደፋር የነበረ ሲሆን ለፍጻሜው ግን እስከ ሞት ደርሶ ስመ ክርስቶስን በድፍረት ገልጧልና "ተባዕ (ደፋር)" ይለዋል::
"ዘኢያፍርሃከ ምንተ መልአከ ዓመጻ ጽኑዕ::
አንተኑ እንድርያስ ተባዕ" እንዲል:: (መልክዐ ዓቢየ እግዚእ)

የቅዱስ እንድርያስ ሃገረ ስብከቱ ልዳ (ልድያ) ናት:: ይህቺን ሃገር: አስቀድሞ ሊቀ ሐዋርያቱ (ትልቅ ወንድሙ) ቅዱስ ጴጥሮስ አስተምሮባታል:: ቅዱስ ጴጥሮስ ወደ ሮም ሲዘልቅ ቅዱስ እንድርያስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ገብቶ ብዙ ደክሞባታል::

በቀደመው ዘመን ልዳ እንደ ዛሬው ትንሽ ሃገር አልነበረችም:: ቅዱሱ ሐዋርያ ወደ ቦታው ገብቶ: ስመ ክርስቶስን ሰብኮ ብዙዎችን ቢያሳምንም የጣዖቱ ካህናት ግን ተበሳጩ:: በእርግጥ እነርሱ የሚያጥኗቸው ድንጋዮች አማልክት እንዳልሆኑ ጠንቅቀው ያውቃሉ::

ነገር ግን ከብረው: ገነው: ባለ ጠጐችም ሆነው የሚኖሩበት ሐሰት እንዲገለጥ አይፈልጉምና እውነትን ከመቀበል ሐዋርያቱን ማሳደዱን ይመርጡ ነበር:: አሁንም የልዳ ከተማ ሕዝብ ማመናቸውን ሲሰሙ በቁጣ ሠራዊት ሰብስበው: ጦርና ጋሻን አስታጥቀው: ሐዋርያውን ያጠፉ ዘንድ እየተመሙ መጡ::

ቅዱስ እንድርያስ ይህንን ሲያውቅ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል "ጥዑመ-ቃል" የሚባለውን ቅዱስ ፊልሞናን (ኅዳር 27 ቀን ያከበርነውን ማለት ነው) ጠርቶ የቅዱስ ዳዊትን መዝሙር ገልጦ ምዕራፍ (113:12) ላይ ሰጠውና "ጮክ ብለህ አንብብ" አለው::

††† ቅዱስ ፊልሞናም በቅዱስ መንፈሱ ተቃኝቶ ያነብ ጀመር::
"አማልክቲሆሙ ለአሕዛብ ዘወርቅ ወዘብሩር::
ዓይን ቦሙ ወኢይሬእዩ::
እዝን ቦሙ ወኢይሰምዑ::
አንፍ ቦሙ ወኢያጼንዉ . . .
የአሕዛብ አማልክት ከወርቅና ከብር የተሠሩ ናቸው::
ዓይን አላቸው: ግን አያዩም::
ጆሮ አላቸው: ግን አይሰሙም::
አፍንጫ አላቸው: ግን አያሸቱም . . ." አለ::

በፍጻሜውም "ከማሁ ለይኩኑ ኩሎሙ እለ ገብርዎሙ / የሚሰሯቸው ሁሉ እንደ እነርሱ ይሁኑ" ብሎ ጸጥ አለ:: ይህንን የሰሙት ካህናተ ጣዖትና ሠራዊታቸው የልባቸው መታጠቂያ ተፈታ:: በደቂቃዎችም የመንፈስ ቅዱስ ምርኮኛ ሆነው በቅዱስ እንድርያስ ፊት ሰገዱ::

እርሱም አጥምቆ ወደ ምዕመናን ማኅበር ቀላቀላቸው:: አንድ ጊዜ ደግሞ ከልዳ አውራጃዎች በአንዱ እንዲህ ሆነ:: በጨዋታ ላይ ሳሉ የክርስቲያኑ ልጅ የአሕዛቡን ቢገፈትረው ወድቆ ሞተ::

የሟቹ አባትም የገዳዩን አባት ዮሐንስን (ቀሲስ ነው) "ልጅህን በፈንታው እገድለዋለሁ" አለው:: ቀሲስ ዮሐንስ ግን "ለመምሕሬ ለእንድርያስ እስክነግር ድረስ ታገሠኝ" ብሎ ሒዶ ለሐዋርያው ነገረው::

በወቅቱ ቅዱስ እንድርያስ የወንጌል አገልግሎት ላይ ስለ ነበር ቅዱስ ፊልሞናን ላከው:: ፊልሞና ወደ አካባቢው ሲደርስ ሁከት ተነስቶ አገረ ገዢው ሕዝቡን ይደበድብ ነበርና ቀርቦ ገሠጸው:: "የተሾምከው ሕዝቡን ልታስተዳድርና ልትጠብቅ ነው እንጂ ልታሰቃይ አይደለም" ስላለው አገረ ገዥው ቅዱሱን አሰቀለው::

ተሰቅሎም ሳለ ይገርፉት ነበርና አለቀሰ:: ምክንያቱም ቅዱስ ፊልሞና ሕጻን ነበርና:: በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሲያለቅሱለት ቁራ: ወፍና ርግብ ቀርበው አጽናኑት:: ከእነርሱም መርጦ ርግብን ወደ ቅዱስ እንድርያስ ላካት::

ርግብ በሰው ልሳን ስትናገር የሰማት አገረ ገዢው ተገርሞ ቅዱሱን ከተሰቀለበት አወረደው:: ሰይጣን ግን በብስጭት በመኮንኑ ሚስት አድሮ ልጁን አስገደለበት:: በሃዘን ላይ ሳሉም ቅዱስ እንድርያስ ደረሰ::

በመኮንኑ ሚስት ያደረውን ሰይጣንን ወደ ጥልቁ አስጥሞ የሞተውን አስነሳው:: መጀመሪያ የሞተውን ሕጻን ደግሞ ፊልሞና አስነሳው:: በእነዚህ ተአምራትም መኮንኑ: ሕዝቡና ሠራዊቱ በክርስቶስ አምነው ተጠመቁ::

ቅዱስ እንድርያስ በእድሜው የመጨረሻ ዘመናት ከልድያ ወጥቶ በብዙ አሕጉራት አስተማረ:: ስሟ ባልተጠቀሰ አንዲት ሃገር ውስጥ ግን በእሳት ሊያቃጥሉት ሲሉ እሳት ከሰማይ ወርዳ በላቻቸው::

ድጋሚ ሌሎች ይዘው አሰሩት: ደበደቡት አሰቃዩት:: በሌሊትም ጌታ መጥቶ አጽናናው:: ታኅሣሥ 4 ቀን በሆነ ጊዜም ወደ ውጭ አውጥተው: ወግረውና ሰቅለው ገድለውታል::
¤እኛም እንደ አባቶቻችን:-
"እዜምር ለከ ወእየብብ በሃሌ ሉያ::
አንቅሃኒ እምሐኬትየ እንድርያስ ሐዋርያ::
ከመ በእዴከ ነቅሐት እሙታን ልድያ::" እያልን ቅዱሱን እንጠራዋለን:: (አርኬ ዘታኅሣሥ 4)††† አምላከ ቅዱስ እንድርያስ ከሞተ ልቡና አንቅቶ ለክብሩ ያድርሰን:: ከበረከቱም ያድለን::

††† ታኅሣሥ 4 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
2.አባ ጻዕ
3.አባ ያዕቆብ
4.ቅድስት ታኦድራ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ
2.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
3.ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ (ሰማዕት)

††† "ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሲናገር ሰምተው ጌታ ኢየሱስን ተከተሉት:: ጌታ ኢየሱስም ዘወር ብሎ: ሲከተሉትም አይቶ:- "ምን ትፈልጋላችሁ?" አላቸው:: እነርሱም:- "ረቢ ወዴት ትኖራለህ?" አሉት:: ትርጓሜው "መምህር ሆይ!" ማለት ነው:: "መጥታችሁ እዩ" አላቸው:: መጥተው የሚኖርበትን አዩ:: በዚያም ቀን በእርሱ ዘንድ ዋሉ:: አሥር ሰዓት ያህል ነበረ:: ከዮሐንስ ዘንድ ሰምተው ከተከተሉት ከሁለቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበረ::" †††
(ዮሐ. ፩፥፴፯-፵፩)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
5•­3- ØÈ- s #%  +u--- 16k
ASR by NLL APPS
ስንክሳር ዘወርሃ ታህሣሥ አራት(፬)
https://www.tg-me.com/SinkisarZekidusan2
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
                  አሜን
"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"         

         ቀናችንን በጸሎት እንጀምር

📌 ስንክሳር ዘወርኀ ታኅሣሥ ፭

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ታኅሣሥ አምስት በዚች ቀን የኬልቅዩ ልጅ ታላቅ ነቢይ ኖሆም አረፈ።

❖ ከስምዖን ነገድ የሆነ ይህ ጻድቅ ነቢይ ከነቢይ ሙሴ በትንቢቱ ዐሥራ ሰባተኛ ነው፤ በካህኑ ዮዳሄ በነገሥታቱ በኢዮአስ በአሜስያስ በልጁ በኦዝያን ዘመን ትንቢት ተነገረ ስለ ክህደታቸውና ጣዖታትን ስለ ማምለካቸውም የእስራኤልን ልጆች ገሠጻቸው።
❖ እግዚአብሔርም ምንም መሐሪና ይቅር ባይ ምሕረቱም የበዛ ቢሆን ካልተመለሱ ጠላቶቹን ይበቀላቸው ዘንድ እንደ አለው ለሚቃወሙትም የፍርድ ቀን እንደሚጠብቃቸው በትንቢቱ ገለጠ።
❖ ዳግመኛም ስለ ከበረ የወንጌል ትምህርትና ስለ ሐዋርያት እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ የምሥራች የሚናገሩ ሰዎች እግራቸው እነሆ በተራራ ላይ ቁሟል ሰላምንም ይናገራሉ።
❖ ስለነነዌም ውኃና እሳት ያጠፉአት ዘንድ እንዳላቸው ትንቢት ተናግሮ እንደቃሉ ሆነ ከዕውነት መንገድ ተመልሰው በበደሉ ሰዎች ላይ እግዚአብሔር በውስጧ ታላቅ ንውጽውጽታ አድርጎ እሳትም አውርዶ እኩሌታዋን አቃጥሏልና።
❖ በንስሐ ጸንተው ወደ እግዚአብሔር የተመለሱትን ግን ከክፉ ነገር ከቶ ምንም ምን አልደረሰባቸውም፤ የትንቢቱንም ወራት ሲፈጽም እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ነቢይ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

             አርኬ
✍️ሰላም ለከ ሰባኬ ምጽአቱ እምሲና። ዘበድልቅልቅ ፍና። ለዝ አምላክ እንተ ርኢኮ በዐይነ ሕሊና። አስተብቊዖ ናሆም ወሰአሎ እምፀበለ እግሩ ደመና። ዲበ ሕማምየ ይነፍንፍ ጥዒና።

📌 በዚችም ቀን የቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት መታሰቢያው ነው በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

📌 በዚችም ቀን ደግሞ ከሮም አገር ቅድስት አውጋንያ በሰማዕትነት አረፈች፤ የዚችም ቅድስት የአባቷ ስም ፊልጶስ ነው እርሱም የእስክንድርያ አገር ገዥ ነበር ጣዖትንም ያመልካል ስሙ መምድያኖስ የሚባል የሮም ንጉሥም ለጣዖት የሚሰግድ ነው ይቺም ቅድስት አውጋንያ በእስክንድርያ ከተማ ተወለደች እናቷም ክርስቲያን ስለሆነች በሥውር የክርስቲያን ሃይማኖትን አስተማረቻት።
❖ በአደገችም ጊዜ ታላላቆች መኳንንት አጯት አባቷም ይህን በነገራት ጊዜ አባቴ ሆይ መጀመሪያ ወደ እስክንድርያ ገዳም እንድገባና እንድጎበኝ ተራሮችን በማየት ዐይኖቼ አይተው ደስ ይለኝ ዘንድ ፍቀድልኝ አለችው አባቷም ሰምቶ ሁለት ጃንደረቦችን ጨምሮ የወደደችውን ታደርግ ዘንድ ፈቀደላት።
❖ በወጣችም ጊዜ የመነኰሳቱን ገዳማት ሁሉ ዞረች ስሙ ቴዎድሮስ የሚባል ጻድቅ ደግ ኤጲስቆጶስ ወደሚኖርባትም ቤተ ክርስቲያን ደረሰች ቀረብ ብላም በልቧ ያለውን ሁሉ ነገረችው ከጃንደረቦቿም ጋር ተጠምቃ በዚያ መነኰሰች በወንድ አምሳልም ሁና ስሟን አባ አውጋንዮስ አሰኘች እርሷ ሴት እንደሆነች ማንም አላወቀም።
❖ ወደ አባቷም ባልተመለሰች ጊዜ በቦታው ሁሉ ፈለጋት ሲአጣትም በርሷ አምሳል ጣዖት ሠርቶ ማታና ጧት እየሰገደላት ኖረ።
❖ አንድ ዓመትም ከኖረች በኋላ የዚያ ቦታ አበ ምኔት አረፈ መነኰሳቱም መረጧትና አበ ምኔት አድርገው ሾሟት እግዚአብሔርም አጋንንትን ታስወጣ ዘንድ የዕውራንን ዐይኖች ትገልጥ ዘንድ ደዌውን ሁሉ ታድን ዘንድ ሀብተ ፈውስን ሰጣት።
❖ ከዚህም በኋላ ሰይጣን በአንዲት ሴት ልብ ክፉ አሳብ አሳደረባት ከአዳነቻት በኋላ ወንድ መስላታለችና ገዳምህንና ምንኩስናህን ትተህ ለኔ ባል ሁነኝ ብዙ ገንዘብ አለኝና አለቻት።
❖ አባ አውጋንዮስ የተባለችው ቅድስቷም እናቴ ሆይ ከእኔ ዘንድ ሂጂ ሰይጣን በከንቱ አድክሞሻል አለቻት በአሳፈረቻትም ጊዜ ወደ እስክንድርያ ገዥ ሒዳ እንዲህ አለችው እኔ ወደ ዕገሌ ቦታ በሔድኩ ጊዜ ሊደፍረኝ ሽቶ ወጣት መነኵሴ በሌሊት ወደእኔ መጣ ወደ አገልጋዮቼም ስጮህ ከእኔ ዘንድ ወጥቶ ሸሸ።
❖ መኰንኑም በሰማ ጊዜ ይኸውም የቅድስት አውጋንያ አባቷ የሆነ መነኰሳቱን ሁሉ አሥረው ያመጧቸው ዘንድ አዘዘ በአደረሷቸውም ጊዜ እንዲአሠቃያቸው ለሌላ መኰንን አሳልፎ ሰጣቸው ከሥቃይም ጽናት የተነሣ ከእርሳቸው የሞቱ አሉ።
❖ የመነኰሳቱንም መጐሳቈል በአየች ጊዜ መኰንን አባቷን እንዲህ አለችው ጌታዬ ሆይ ምሥጢሬን ዕውነቱን እነግርህ ዘንድ የምፈልገውንም እንዳትከለክለኝ ማልልኝ አለችው፤ በማለላትም ጊዜ ወደ ሥውር ቦታ ወስዳ ምሥጢርዋን ሁሉ ገለጠችለትና ልጁ አውጋንያ እርሷ እንደሆነች አስረዳችው፤ መኰንኑም አይቶ በእውነት አንቺ ልጄ አውጋንያ ነሽ እኔም በአምላክሽ አመንኩ አላት።
❖ በዚያንም ጊዜ መነኰሳቱን ይፈቷቸው ዘንድ በመሠቃየት የሞቱትንም ይቀብሩአቸው ዘንድ አዘዘ ወዲያውኑ ከቤተሰቦቹ ሁሉ ጋር ተጠምቆ ሁሉም ክርስቲያን ሆኑ።
❖ የእስክንድርያ ሰዎችም የሃይማኖቱን ጽናት በአዩ ጊዜ በወንጌላዊው ማርቆስ ወንበር ላይ ሊቀ ጳጳሳት አድርገው ሾሙት ክብር ይግባውና የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ሃይማኖት እያስተማረ ብዙ ዓመታትን ኖረ።
❖ ከዚህም በኋላ በእርሱ ላይ ሌላ ከሀዲ መኰንን ተነሥቶ ይህን ሊቀ ጳጳሳት ፊልጶስን በሥውር ይገድሉት ዘንድ ጭፍሮቹን ላከ በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ ቁሞ ሲጸልይ ገደሉት የሰማዕታትንም አክሊል አገኘ።
❖ የሮሜ ሊቀ ጳጳሳትም የቅድስት አውጋንያን ዜና በሰማ ጊዜ ወደርሱ ወስዶ እርሱ በሠራው ገዳም ላይ እመ ምኔት አድርጎ ሾማት የመነኰሳይያቱም ብዛት ሦስት ሽህ ሦስት መቶ ነው እነዚያንም ከእርሷ ጋር የኖሩ ሁለት ጃንደረቦች በሁለት አገሮች ላይ ኤጲስቆጶስነት ሾማቸው።
❖ ከዚህም በኋላ ሌላ ከሀዲ መኰንን በተሾመ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነፍሷን ለሞት አሳልፋ እስከ ሰጠች ድረስ ቅድስት አውጋንያን ይዞ በጽኑ ሥቃይ አሠቃያት የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበለች።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቷ ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።
📌 በዚችም ቀን ደግሞ ከአስዩጥ አውራጃ ሻው ከሚባል ከተማ ቅዱስ ፊቅጦር በሰማዕትነት አረፈ።
❖ የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም መርመር የእናቱ ማርታ ይባላል እነርሱም ያለ ፍርሀት እግዚአብሔርን የሚያመልኩት እውነተኞች ጻድቃን ናቸው ነገር ግን ልጅ አልነበራቸውምና ክብር ይግባውና ጌታችንን እየለመኑ ኖሩ ለድኆችም ምጽዋትን ይሰጡ ነበር።
❖ እግዚአብሔርም ልመናቸውን ተቀበለ ይቺ የተባረከች ማርታም ይህን ሊቅ ፊቅጦርን ፀንሳ ግንቦት ዘጠኝ ቀን ወለደችው እግዚአብሔርን በመፍራትም ሠርተው ቀጥተው አሳደጉት።
❖ ሃያ ዓመትም ሲሆነው አባቱ ወደ ንጉሥ አቀረበውና ንጉሡም በአባቱ ፈንታ ምስፍና ሾመው አባቱ በዕድሜው ሸምግሎ ነበርና።
❖ ከጥቂት ወራትም በኋላ ጣዖታትን የማያመልኩ ክርስቲያኖችን ሁሉ ይገድል ዘንድ የንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ መልእክት ወደ እንጽና አገር መኰንን ደረሰ።
❖ መኰንኑም ክርስቲያኖችን እየፈለገ ወደ ሻው ከተማ ደረሰ ያን ጊዜ ክብር ይግባውና ክርስቶስን እንደሚአመልከው ክፉዎች ሰዎች ይህን ቅዱስ ፊቅጦርን ወነጀሉት ያን ጊዜም እንዲአመጡት አዘዘና በአመጡት ጊዜ ለጣዖታት እንዲሠዋ አስገደደው እምቢ በአለውም ጊዜ በወህኒ ቤት እንዲአሥሩት አዘዘ።
❖ በዚያም እያለ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ወደ ሰማይ አወጣው የወህኒ ቤት ጣባቂዎችም በአጡት ጊዜ ተሸበሩ ከሰባት ቀኖችም በኋላ አግኝተውት ወደ መኰንኑ ወሰዱት መኰንኑ ግን ራራለትና ወደ ንጉሡ ሰደደው ንጉሡም እግዚአብሔርን ከማምለክ ይመልሰው ዘንድ በማባበል ብዙ ሸነገለው።
❖ መመለስም በተሳነው ጊዜ አውጣኪያኖስ ወደሚባል መኰንን ሰደደው፤ እንዲህም ብሎ አዘዘው እነሆ ፊቅጦርን ወደአንተ ልኬዋለሁ ያንተን ምክር ከሰማ ለአማልክት ይሠዋ ካልሰማህ ግን ግደለው እንጂ አትራራለት።
❖ ከዚህም በኋላ ወደ መኰንኑ ሊወስዱት እጆቹንና እግሮቹን አሠሩ በአፉም የብረት ልጓም አግብተው በመርከብ አሳፈሩት የእግዚአብሔርም መልአክ ወርዶ ከማሠሪያውም ፈትቶ ወደ መኰንኑ አደረሰው ቅዱስ ፊቅጦርም መኰንኑንና ከሀዲውን ንጉሥ ሊረግም ጀመረ መኰንኑም ተቆጣ ጽኑዕ ሥቃይንም አሠቃይቶ በወህኒ ቤት አሠረው።
❖ በዚያም ሳለ ክብር ይግባውና መድኃኒታችን በብርሃን ሠረገላ ላይ ሁኖ ተገለጠለትና ቃል ኪዳን ሰጠው ከዚያችም ቀን ጀምሮ ድንቅ ተአምራትን በማድረግ ብዙ በሽተኞችን የሚፈውስ ሆነ።
❖ መኰንኑም ይህን ሰምቶ ተቆጣ ወደርሱ አስመጣውና ይመልሰው ዘንድ ደግሞ ሸነገለው ቅዱስ ፊቅጦር ግን የረከሱ አማልክቶቹን ረገመ በዚያንም ጊዜ በፈረስ ጅራት ላይ አሥረው የአንድ ቀን መንገድ ያህል እንዲጐትቱት ከዚያም ከውሽባ ቤት እሳትማንደጃ ውስጥ እንዲጨምሩት አዘዘ እንዲህም መልካም ተጋድሎውን ፈጸመ።
❖ ሥጋውን ግን ከዚያ ውሽባ ቤት አላወጡትም በመሰላል ወርደው በአማሩ ልብሶች ገንዘው በሽቱዎች አጣፈጡት እንጂ በላዩም ቤተ ክርስቲያንን ሠሩ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
           

📌 በዚችም ቀን የፊንጦስ፣ የሐናንያ፣ የባርክዮስ፣ የዮሐንስ፣ የተጋዳይዋ የቅድስት አውጋንያ አባት የፊልጶስ መታሰቢያቸው ነው። በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

📌 በዚችም ቀን የሰማዕት ቅዱስ ኤላው ትሮስ መታሰቢያው ነው በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
   
📌 በዚችም ቀን ለእግዚአብሔር ሕግ የሚቀና ገድለኛ የሆነ ንጹሕ ድንግል ቅዱስ አባት አባ ገብረ ናዝራዊ አረፈ።
❖ የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ በወገን የከበሩ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ናቸው አባቱም የቤተ ክርስቲያንን ሕጓንና ሥርዓቷን የሚጠብቅ ካህን ነው እናቱም ፈጣሪዋን የምትወድ ደግ ሴት ናት።
❖ ይህም ቅዱስ በተወለደ ጊዜ በዕውቀት እግዚአብሔርን በመፍራት በመማር አደገ ከዚህም በኋላ ዲቁናን በተሾመ ጊዜ የብሉይና የሐዲስ መጻሕፍትን የሚያነብ ሆነ በኦሪትም ውስጥ የሰንበትን ቀን የሻረና ሥራ የሠራባት በሞት ይቀጣ የሚል አገኘ።
❖ ከወንጌልም ውስጥ እንዲህ የሚል አገኘ ከእነዚህ ትእዛዛት ታንሳለች ብሎ የሚያስተምር አንዲቱን የሻረ ለሰውም እንዲህ ብሎ የሚያስተምር በመንግሥተ ሰማይ የተለየ ይሆናል የሚያደርግና የሚያስተምር ግን እርሱ በመንግሥተ ሰማይ ታላቅ ይሆናል ዳግመኛም መድኃኒታችን አባትና እናቱን ያልተወ ሰውነቱንም ለመከራ አሳልፎ ያልጣላት ሊአገለግለኝ ደቀ መዝሙሬም ሊሆነኝ አይችልም ያለውን አስተዋለ።
❖ ከዚህም በኋላ ወደ አቡነ ጎርጎርዮስ ሔደ እርሱም ጽጋጃ በሚባል ገዳም የአቡነ አኖሬዎስ ልጅ ነው በዚያም መነኵሶ በጾም በጸሎት በስግደት እየተጋ ኖረ።
❖ ከዚህም በኋላ ቅስና ተሾመ ከዚያም ወደ ትግራይ አገር ሔዶ ከአባ ያዕቆብ ጋር ተገናኝቶ በቅዱሳት መጻሕፍት ቃሎች ተነጋገሩ።
❖ ከዚህም በኋላ ሀሳቡን ገለጠለት አባ ያዕቆብም እንዴት ይቻላል አለው አባ ገብረ ናዝራዊም እግዚአብሔር ይረዳኛል አለ ከአባ ያዕቆብም ጒልት ተቀብሎ እርስበርሳቸው በእግዚአብሔር ፈቃድ ተለያዩ።
❖ ከዚህም በኋላ ተስፋፍቶ ገዳምን ሠራ ብዙ ሰዎችም ወደርሱ ተሰብስበው መነኰሳትን ሆኑ ስለ ሰንበታትና በዓላትም አከባበር እንደሚገባ ሥርዓትን ሠራ፤ ለመነኰሳትም ከመድኃኒታችን ከልደቱና ከጥምቀቱ በዓል ከሰንበታትና ከበዓለ ሃምሳ በቀር በየሰሞኑ ሁሉ እስከ ማታ ያለ ማቋረጥ መጾም እንደሚገባቸው ሥርዓትን ሠራ።
❖ ዳግመኛም የሌላውን ገንዘብ እንዳይነኩ እንዳይረግሙ በሕያው እግዚአብሔርም ስም እንዳይምሉም ለልጆቹ ይህን ሁሉ ያስተምራቸው ነበር።
❖ ለእርሱ ግን ለሚጸልየው ጸሎት ልክ የለውም ነቢይ ዳዊት እግዚአብሔርን ሁልጊዜ አመሰግነዋለሁ፤ ምስጋናውም ዘወትር በአፌ ውስጥ አለ ያለውን አስቦ ዳግመኛም ትእዛዝህን በማሰብ እጫወታለሁ ሕግህን እሻለሁ ትእዛዞችህንም አስተምራለሁ ቃልህንም አልረሳም ያለውን አስቦ።
❖ ዳግመኛም ከሰባውና ደም ካለው ጣዕም ካላቸውም መብሎች ሁሉ ይከለከላል የጌታውን መከራ ለነፍሱ ያሳስባታልና ዕንባው ያለ ማቋረጥ ይፈስ ነበር ያለ ማቋረጥም ይሰግዳል ያመሰግናልም እንግዳና መጻተኛውን ይቀበላል በጽዮን ዘር በኢየሩሳሌም ቤቶች ያሉት ብፁዕ ነው ያለውን የነቢይ ቃል አስቦ ድኆችንና ችግረኞችን ይጉበኛቸዋል።
❖ ለዚህም አባት ትሩፋቱ ብዙ ነው ደጋግ ተአምራትንም በማድረግ በሰው ልቡናም ተሠውሮ ያለውን በማወቅ ብዙ የተለያዩ ሀብቶች ተሰጥተውታል ለልጆቹም የቀናች ሃይማኖትን አስተማራቸው በእርሷም እንዲጸኑ አዘዛቸው ከዚህም በኋላ በሸመገለ ጊዜ እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ አባት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

📌 ታኅሣሥ 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅድስት አውጋንያ ተጋዳሊት
2.አባ ገብረ ናዝራዊ ንጹሕ
3.ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት
4.ቅዱስ ፊልዾስ
5.ቅዱስ ናሆም ነቢይ

📌 ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
2.ቅዱስ ዻውሎስ ብርሃነ ዓለም
3.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
Daniel:
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለእናታችን "ቅድስት አውጋንያ" : "አባ ገብረ ናዝራዊ" እና "ቅዱስ ፊቅጦር" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+*" ቅድስት አውጋንያ "*+

=>ይህቺ ቅድስት ወጣት ስም አጠራሯ በእውነት የከበረ ነው:: ዜና ሕይወቷ ሲሰማ ጣዕመ ነፍስን ያድሳልና:: በፈጣሪ ረዳትነት ልጀምር:: እናንተም በእግዚአብሔር አጋዥነት ተከተሉኝ::

+ቅድስት አውጋንያ የ3ኛው መቶ ክ/ዘ የክርስትና ፍሬ ናት:: በትውልዷ ሮማዊት ስትሆን አባቷ ፊልዾስ ይባላል:: ሥራውም የጦር መሪ: የሃገርም አስተዳዳሪ ነው:: በስም ያልተጠቀሰች እናቷ ደግሞ ክርስቲያን ነበረች::

+ዘመኑ አስከፊ ሰለ ነበር (ለክርስቲያኖች ማለቴ ነው) ክርስትናዋን ደብቃ: አልባሌ (አሕዛባዊ) መስላ ትኖር ነበር:: ቅድስት አውጋንያን ስትወልድ ግን ጨነቃት:: እንዳታስጠምቃት የእርሷም ሆነ የሕጻን ልጇ እጣ ፈንታ ሞት መሆኑ ነው::

+ምክንያቱም ባሏ ፊልዾስ ክርስትናን ፈጽሞ የሚጠላ ጣዖት አምላኪ ነበርና:: ከዚያም አልፎ ሰዎች ለጣዖት እንዲንበረከኩም ያስገድድ ነበር:: ስለዚህ እናት ልጇን ሳታስጠምቅ: ግን በፍጹም የክርስትና ትምሕርትና ሥርዓት አሳደገቻት::

+ቅድስት አውጋንያም ጾምን ጸሎትን: ትሕትናን: ትእግስትን የተመላች ወጣት ሆነች:: ግን ምሥጢረ ጥምቀትን ታገኝ ዘንድ ዘወትር ፈጣሪዋን ትማጸን ነበር::

+በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉም አንድ መልካም አጋጣሚ ተፈጠረ:: መኮንኑ አባቷ (ፊልዾስ) በምድረ ግብጽ እስክንድርያ አገረ ገዥ ሆኖ በመሾሙ ጉዋዛቸውን ጠቅልለው ወረዱ:: ምንም ይህ ለቅድስት አውጋንያ መልካም አጋጣሚ ቢሆንም ሌላ ፈተናን አመጣባት::

+አባቷ ለአረማዊ መኮንን ሊድራት መሆኑን ሰማች:: አሁን ግን መቁረጥ ያስፈልግ ነበርና ወሰነች:: ወደ አባቷ ገብታም "አባቴ! አንድ ነገር ላስቸግርህ:: አንተ ለምትለኝ ሁሉ እታዘዛለሁ:: ግን ከሠርጌ ቀን በፊት ለአንዲት ቀን በዱር ውስጥ ተናፍሼ: ተዝናንቼ እንድመጣ ፍቀድልኝ?" አለችው::

+ምን እንዳሰበች ያልጠረጠረ አባቷም ከ2 ጃንደረቦች ጋር እንድትሔድ አደረገ:: በርሃ አካባቢ ሲደርሱም ቅድስት አውጋንያ እውነቱን ለ2ቱ ጃንደረቦች ተከታዮቿ ነገረቻቸው::

+"እኔ ወደ በርሃ የምሔደው ክርስቲያን ልሆን: ደግሞም ልመንን ነውና ካላሰኛችሁ ተመለሱ" አለቻቸው:: 2ቱም ግን በአንድ ቃል "ሞታችንም: ሕይወታችንም ከአንቺ ጋር ነው" ብለዋት አብረው ገዳም ገቡ::

+እንደ ደረሱም ምሥጢራቸውን ለአንድ ጻድቅ መነኮስ ተናግራ እንዲያጠምቃት ጠየቀችው:: መነኮሱም 3ቱንም ካጠመቃቸው በሁዋላ ቅድስት አውጋንያ "አመንኩሰን" ብትለው "ልጄ! ይሔ የወንዶች ገዳም ነውኮ" አላት::

+"አባ! ግድ የለህም! እኔ ራሴን እሰውራለሁ" አለችው:: ከዚያም ሥርዓተ ገዳምን አስተምሮ ስሟን "አባ አውጋንዮስ" ብሎ ከማሕበረ መነኮሳቱ ቀላቀላት:: *አውጋንያን *ታኦድራ *አንስጣስያ . . . የመሳሰሉ ስሞች በቀላል መንገድ ወደ ወንድ ስምነት *አውጋንዮስ *ቴዎድሮስ *አንስጣስዮስ . . .በሚል መቀየር ይችላሉና::

+ከዚህች ዕለት ጀምራ ቅድስት አውጋንያ በአባ አውጋንዮስነቷ ተጋድሎን ጀመረች:: ቀን ቀን ወንዶች መነኮሳት የሚሠሩትን ከባድ ሥራ ሁሉ ስትሠራ ትውልና ሌሊት በትጋት ስትጸልይ ታድራለች:: ለ1 ዓመት ያህል በፍጹም ተጸምዶ ገዳሙን አገለገለች::

+በነዚህ ጊዜያት የመጡባትን ፈተናዎችም ታገሰች:: ዓለምን የናቀችለት: የአባቷን ቤተ መንግስት የተወችለት ክርስቶስ ኃይሏ ነበርና:: በዚያ ሰሞንም የገዳሙ አበ ምኔት በማረፉ መነኮሳትን የሚመራና የሚናዝዝ ሌላ አበ ምኔትን ለመምረጥ ሱባኤ ገቡ::

+ከሱባኤ ወጥተው ሲሰበሰቡ ግን ያመጡት የመንፈስ ቅዱስ መልእክት የሚገርም ነበር:: የሁሉም ዓይን ወደ አባ አውጋንዮስ ተወረወረ:: እርሷ ምሥጢሯን (ሴትነቷን) ታውቃለችና ደነገጠች:: ምርጫው ግን የመንፈስ ቅዱስ ነበርና ግድ ብለው በእነዛ ሁሉ መነኮሳት ላይ እረኛ ሁና ተሾመች::

+በእርግጥ እርሷ ሴት በዚያውም ላይ ወጣት ናት:: ግን እውነተኛ የክርስቶስ ወዳጅ ነበረችና በፍጹም ትጋት መነኮሳትን አስተዳደረች:: ጸጋው ቢበዛላት የተጨነቀውን ታረጋጋ: የታመመውን እጇን እየጫነች በጸሎቷ ትፈውስ ነበር:: በዚህም መነኮሳቱ ደስ ተሰኙ::

+እርሷ ግን ስለዚህ ፈንታ ብዙ ፈተናዎችን በአኮቴት ታሳልፍ ነበር:: ስም አጠራሯም ከበርሃ ወጥቶ ወደ ከተሞች በመግባቱ ድውያን እየመጡ ከእርሷ ዘንድ ይፈወሱ ነበር:: አንድ ቀን ግን ያልተጠበቀ ፈተና መጣባት::

+አንዲት ሰይጣን ያደረባትን ሴት ካዳነቻት በሁዋላ: መልኩዋ እጅግ ውብ ስለ ነበር የዝሙት ጥያቄን አቀረበችላት:: (ሴቷ ለሴቷ ማለት ነው) ለእርሷ ወንድ መስላታለችና:: ቅድስት አውጋንያ ግን ገሥጻ ሰደደቻት:: በዚህ የበሸቀችው ያቺ ክፉ ወጣት ወደ ከተማ ሒዳ ለሃገረ ገዢው ፊልዾስ (የቅድስቷ አባት) ክስ አቀረበች::

+እርሱ (ፊልዾስ) አውጋንያ ከጠፋችበት ቀን ጀምሮ በስሟ ጣዖት አሠርቶ የሚሰግድ ሆኖ ነበር:: ወጣቷ "በገዳም ያሉ መነኮሳት: በተለይ አውጋንዮስ የሚሉት መሪያቸው አስገድዶ ከክብር ሊያጐድሉኝ ሲሉ አመለጥኩ" ብላ በሃሰት በመክሰሷ ገዳሙ እንዲመዘበር: መነኮሳቱም እንዲገረፉ መኮንኑ ፊልዾስ አዘዘ::

+በግርፋቱ መካከልም ብዙ መነኮሳት ሞቱ:: የእነርሱ ስቃይ ያንገበገባት ቅድስት አውጋንያ ግን አባቷን ለብቻ ወስዳ አስምላ ማንነቷን ገለጸችለት:: የናፈቃት ልጁን ሲያገኝ ደስ ብሎት መነኮሳቱን እንዲተዉ አዘዘ::

+ለብቻ ከልጁ ጋር ተቀምጦም ያለፈውን ነገር ሁሉ ነግራ ስለ ሰማያዊ ሕይወት አስረዳችው:: በስሟ የተቀረጸውን ጣዖትም ሰብራ አባቷን አስጠመቀችው:: እርሱም መንኖ ለዓመታት ኖረ:: ከዚያም ዻዻስ ሆኖ ተሹሟል::

+በዚህች ቀንም ስለ ክርስቶስ አንገቱን ተሰይፏል:: ቅድስት አውጋንያ ግን ከግብጽ ወደ ሮም ሒዳ የደናግል ገዳምን መሠረተች:: በሥሯም አምላክ 3,300 ደናግልን ሰበሰበላት:: እነርሱን ስታጽናና: ስትመክር: ስትመራ ለዓመታት ኑራ በአካባቢው ገዢ ሃይማኖቷን እንድትክድ ተጠየቀች::

+"እንቢ" በማለቷ እርሷም እንደ አባቷ በዚህች ቀን ተሰይፋ ሰማዕት ሆናለች:: አብረዋት የመነኑ 2ቱ ጃንደረቦችም ዻዻሳት ሆነው ቤተ ክርስቲያንን አገልግለዋል::

<< *ድንግል: *መናኝ: *ፈዋሽ: *ናዛዥ: *አበ ምኔት: *እመ ምኔት: *ጻድቅትና *ሰማዕት ለሆነች ለእናታችን ቅድስት አውጋንያ ክብር ይገባል! >>

+"+ አባ ገብረ ናዝራዊ +"+

=>እኒህ ጻድቅ በ14ኛው መቶ ክ/ዘ የነበሩ ኢትዮዽያዊ ናቸው:: ጻድቁ ትግራይ (ገዳማቸው ያለበትና) ሽዋ አካባቢ በደንብ ይታወቃሉ:: የእርሳቸው የቆብ አባት የሆኑት አባ ጐርጐርዮስ የታላቁ አኖሬዎስ (የደብረ ጽጋጋው) ልጅ ናቸው::

+አባ ገብረ ናዝራዊ በምናኔ በየገዳማቱ ሲጋደሉ ከኖሩ በሁዋላ በምክረ አበው ራሳቸው ገዳምን መሥርተዋል:: ብዙ ደቀ መዛሙርትንም ሰብስበው ገዳሙ ታላቅ ሆኗል:: በወቅቱ ከገዳመ ዋሊ (ዋልድባ) ቀጥሎ ጥብቅ ሥርዓት የነበረበት ታላቅ ገዳምም ሆኖ ነበር::
+ለዚህም ምክንያቱ አባ ገብረ ናዝራዊ ፍጹም ተሐራሚ በመሆናቸው ማንኛውም መነኮስ ከአንድ ማዕድ ውጪ እንዲቀምስ የማይፈቅዱ ስለ ነበር ነው:: ከታላቁ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ቀጥሎም ሰንበትን አክብሮ በማስከበር ጻድቁ ትልቁን ቦታ ይይዛሉ::+በተለይ ቀዳሚት ሰንበት እንድትከበር ታግለዋል:: በበጐ አበ_ምኔትነታቸውም ብዙ ፍጹማንን ለሃገራችን አፍርተዋል:: ራሳቸው የበሰለ ነገር ወደ አፋቸው ሳያስገቡ 24 ሰዓት በዳዊት መዝሙር ይደሰቱ ነበር::

+ላባቸው እስኪንጠፈጠፍም ይሰግዱ ነበር:: ሐዋርያዊ ግብርን ለመፈጸምም ወንጌልን እየሰበኩ ያለቻቸውን ነገር ይመጸውቱ ነበር:: ዛሬ የጻድቁ ዕረፍታቸው ነው::

+"+ ቅዱስ ፊቅጦር ዘሻው +"+

=>ይህ ቅዱስ ከታላላቅ ሰማዕታት አንዱ ነው:: ሻው ማለት ሰማዕትነትን የተቀበለባት ቦታ ስትሆን "ፊቅጦር ካልዕም" ይባላል:: ከክርስቲያን ወላጆቹ የወረሰውን በጐነት አጽንቶ በቅን መንገድ ኑሯል::
+ምንም ወጣት: የሃገር አስተዳዳሪ: ሃብታምና መልከ መልካም ቢሆንም ይህ ሁሉ ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየው አልቻለም:: (ሮሜ. 8:35) ዘመነ ሰማዕታት በደረሰ ጊዜም ክብሩን ንቆ: ስለ ክርስትና ብዙተ ሰቃይቶ: በዚህች ቀን ከነ ተከታዮቹ ሰማዕት ሆኗል:: ጌታም ቃል ኪዳንን ገብቶለታል::

=>አምላከ ቅዱሳን የወዳጆቹን ምሥጢረ ቅድስና አይሰውርብን:: በረከታቸውንም ያብዛልን::

=>ታሕሳስ 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅድስት አውጋንያ ተጋዳሊት
2.አባ ገብረ ናዝራዊ ንጹሕ
3.ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት
4.ቅዱስ ፊልዾስ ሰማዕት
5.ቅዱስ ናሆም ነቢይ

ወርኀዊ የቅዱሳን  በዓላት
1.ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
2.ቅዱስ ዻውሎስ ብርሃነ ዓለም
3.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
4.ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮዽያዊ
5.ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ



=>+"+ ነገር ግን ለበጐ ነገር ጥበበኞች: ለክፉትም የዋሆች እንድትሆኑ እወዳለሁ:: የሰላምም አምላክ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል:: የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን:: +"+ (ሮሜ. 16:19)

✞✞✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞✞✞
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
          አሜን
"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"         

         ቀናችንን በጸሎት እንጀምር

📌 ስንክሳር ዘወርኀ ታኅሣሥ ፮

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ታኅሣሥ ስድስት በዚች ቀን የቀሲስ ሰማዕት የቅዱስ እንጣልዮስ መታሰቢያው ነው በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

📌 በዚችም ቀን ቅዱስ አባት የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት የአባ አብርሃም ሶርያዊ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ስልሳ ሁለተኛ ነው።

📌 ታኅሣሥ 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅድስት አርሴማ ድንግል
2."119" ሰማዕታት (ማሕበሯ)
3.ቅዱስ ስምዖን ጻድቅ (ጫማ ሠፊው)
4.አባ አብርሃም ሶርያዊ
5.ቅዱስ እንጣልዮስ ሰማዕት

📌 ወርሐዊ በዓላት
1. ቁስቋም ማርያም
2. ማርያም ዕንተ እፍረት
2024/10/01 05:00:40
Back to Top
HTML Embed Code: