Telegram Web Link
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አሁንም በብፁአን አባቶች እና ምእመናን ላይ እየደረሰ ያለው ስቃይና እንግልት መቀጠሉን ገለፀች።

ቤተክርስቲያኗ ከቀናት በፊት በሻሸመኔ ከተማ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተፈፀመው ጥቃት ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ከፍ ማለቱን ገልጻለች።

ቤተክርስቲያኗ የሻሸመኔ ደብረ ስብሐት ቅዱስ ሚካኤል አገልጋይ የነበሩት ቀሲስ ሐረገወይን ከመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት ተመትተው በሕክምና ሲረዱ ቢቆዩም ህይወታቸው ሊተርፍ እንዳልቻለ አሳውቃለች።

በተጨማሪ ቤተክርስቲያኗ ፤ በፓሊሶች ፊት በአጣና ጭንቅላቱን ተቀጥቅጦ በሀዋሳ በፅኑ ህሙማን ክፍል ሕክምና ሲደረግለት የነበረ አያሌው ተረፈ የተባለ ምዕመን በደረሰበት ጉዳት ህይወቱን ማትረፍ ሳይቻል ቀርቶ ማረፉን ገልጻለች።

በጽኑ ሕሙማን ክፍል ሌሎችም ተጎጂዎች እንደሚገኙ የገለፀችው ቤተክርስቲያን የጤናቸው ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን አስረድታለች።

ከሰሞኑ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በሻሸመኔ ከተማ እስካሁን አጠቃላይ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎችን ቁጥር ቤተክርስቲያኗ ይፋ አላደረገችም።

ከዚህ ባለፈ ቤተክርስቲያኗ ፤ በሻሸመኔና አርሲ ነገሌ በሌሎችም ስፍራዎች የቤተክርስቲያን አባቶች፣ ምዕመናን ሰብአዊ ክብራቸው ተጥሶ ዛሬም በየእስር ቤቱ እንደሚገኙ አሁንም እየታሰሩ የሚገኙ መኖራቸውን አሳውቃለች።

መንግስታዊዎቹ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምና የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ዝምታን መምረጣቸው እጅግ እንዳሳዘናት ቤተክርስቲያኗ ገልጻለች።

በሌላ በኩል ቤተክርስቲያኗ ፤ ወደ ከፋ ሸካና  ቤንች ማጂ ሀገረ ስብከታቸው የተጓዙት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ኃይሎች ክልሉን አቋርጠው ወደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እንዳይሄዱ በማገዳቸው ወደ አዲስ አበባ እንደተመለሱ ገልጻለች።

@EotcLibilery
#Update

የሣውላ ከተማ አስተዳደር ፤ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዕውቅና ውጭ የሚንቀሳቀሱ አካላትን " አላስተናግድም " አለ።

" የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር የአከባቢውንና የህዝቡን ሠላም ማስጠበቅ ነው " ያለው የከተማው አስተዳደር ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዕውቅና ውጭ የሚንቀሳቀሱ አካላትን ከተማዋ ተቀብላ አታስተናግድም ብሏል።

የሣውላ ከተማ ከንቲባ አቶ ሙሉቀን ጉጃ ፤ " የደንባ ጎፋ ወረዳ ቤተክህነት በህገወጥ መንገድ ጳጳሳት የሆኑ አካላት ወደ አካባቢያችን እየተንቀሳቀሱ መሆኑን መረጃው ደርሶኛል ሲል በፃፈው ደብዳቤ ገልፆልን መንግስትና የፀጥታ አካላት ቅድስት ቤተክርስቲያንና የአካባቢውን ሠላም በቅርበት እንዲከታተልና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ጠይቀናል " ሲሉ ተናግረዋል።

ከንቲባው ፤ ህብረተሰቡ የሠላም ማስከበር ስራውን አጠናክሮ እንዲያስቀጥል፤ በአከባቢው እንግዳ ነገሮች ሲያጋጥሙ ጥቆማ እንዲሰጥና ከፀጥታ አካላት ጎን በመሆን የተለመደ ተግባሩን እንዲያከናውን ጥሪ አቅርበዋል።

በተጨማሪ ህዝበ ክርስቲያኑ ያለአንዳች የፀጥታ ስጋት በፆመ ነነዌ የጀመረውን ሱባኤ በአርምሞ እንዲያከናውን በመግለፅ የከተማው መንግሥት ከፖሊስ እንዲሁም ከሠላምና ፀጥታ መዋቅሮች ጋር በጋራ በመቀናጀት የአከባቢውን ደህንነት እንደሚያስጠብቁ አረጋግጠዋል።

በከተማዋ ላሉ አቢያተ ክርስቲያናት መንግሰት የተጠናከረ ጥበቃ እንደሚያደርግ ከንቲባው አሳውቀዋል።

tikvahethiopia
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
ያልተቋረጠው የእስከንድሪያው መንበረ ማርቆስ ስልጣነ ክህነት (apostolic succession) ቅብብሎሽ ይሄ ነው ።

1. ማርቆስ
2. አንያኖስ
3. ሜልያስ
4. ክርዳኑ
5. አምብርዮስ
6. ዮስጦስ
7. አውማንዮስ
8. መርክያኖስ
9. ክላውያኖስ
10. አክርጵያኖስ
11. ዮልዮስ
12. ድሜጥሮስ
13. ያሮክላ (ሔራክልስ)
14. ዲዮናስዮስ
15. መክሲሞስ
16. ቴዎናስ
17. ጴጥሮስ (ተፍጻሜተ ሰማዕት)
18. አኪላስ
19. እለእስክንድሮስ
20. አትናቴዎስ
21. ጴጥሮስ 2ኛ
22. ጢሞቴዎስ
23. ቴዎፍሎስ
24. ቄርሎስ
25. ዲዮስቆሮስ
26. ጢሞቴዎስ 2ኛ
27. ጴጥሮስ 3ኛ
28. አትናቴዎስ 2ኛ
29. ዮሐንስ
30. ዮሐንስ 2ኛ
31. ዲዮስቆሮስ 2ኛ
32. ጢሞቴዎስ 3ኛ
33. ቴዎዶስዮስ (ቴውዳስስ)
34. ጴጥሮስ 4ኛ
35. ድምያኖስ
36. አንስጣስዮስ
37. አንድራኒቆስ
38. ብንያሚን
39. ያቃቱ (አጋቶን)
40. ዮሐንስ 3ኛ
41. ይስሐቅ
42. ስምዖን
43. እለእስክንድሮስ 2ኛ
44. ቆዝሞስ
45. ቴዎድሮስ
46. ካኤል (ሚካኤል)
47. ሚናስ
48. ዮሐንስ 4ኛ
49. ማርቆስ 2ኛ
50. ያዕቆብ 1ኛ
51. ስምዖን 2ኛ
52. ዮሳብ 1ኛ (ዮሴፍ)
53. ካኤል (ሚካኤል) 2ኛ
54. ቆዝሞስ 2ኛ
55. ስንትዮ 1ኛ
56. ሚካኤል 1ኛ
57. ገብርኤል 1ኛ
58. ቆዝሞስ 3ኛ
59. መቃርዮስ 1ኛ
60. ታውፋኔዎስ
61. ሚናስ 2ኛ
62. አብርሃም
63. ፊላታዎስ
64. ዘካርያስ
65. ስንትዩ 2ኛ
66. ክርስቶዶሉ (ገብረ ክርስቶስ)
67. ቄርሎስ 2ኛ (ጌርሎስ)
68. ሚካኤል 2ኛ
69. መቃርዮስ 2ኛ (መቃርስ)
70. ገብርኤል 2ኛ
71. ሚካኤል 3ኛ
72. ዮሐንስ 5ኛ
73. ማርቆስ 3ኛ
74. ዮሐንስ 6ኛ
75. ቄርሎስ 3ኛ
76. አትናቴዎስ 3ኛ
77. ገብርኤል 3ኛ
78. ዮሐንስ 7ኛ
79. ታውዳስዮስ 2ኛ
80. ዮሐንስ 8ኛ
81. ዮሐንስ 9ኛ
82. ብንያሚን 2ኛ
83. ጴጥሮስ 5ኛ
84. ማርቆስ 4ኛ
85. ዮሐንስ
86. ገብርኤል 4ኛ
87. ማቴዎስ 1ኛ
88. ዮሐንስ 5ኛ
89. ዮሐንስ 11ኛ
90. ማቴዎስ 2ኛ
91. ገብርኤል 6ኛ
92. ሚካኤል 4ኛ
93. ዮሐንስ 12ኛ
94. ዮሐንስ 13ኛ
95. ገብርኤል 7ኛ
96. ዮሐንስ 14ኛ
97. ገብርኤል 8ኛ
98. ማርቆስ 5ኛ
99. ዮሐንስ 15ኛ
100. ማቴዎስ 3ኛ
101. ማርቆስ 6ኛ
102. ማቴዎስ 4ኛ
103. ዮሐንስ 16ኛ
104. ጴጥሮስ 6ኛ
105. ዮሐንስ 17ኛ
106. ማርቆስ 7ኛ
107. ዮሐንስ 18ኛ
108. ማርቆስ 8ኛ
109. ጴጥሮስ 7ኛ
110. ቄርሎስ 4ኛ
111. ጴጥሮስ 8ኛ
112. ቄርሎስ 5ኛ
113. ዮሐንስ 19ኛ
114. መቃርዮስ 3ኝእ
115. ዮሳብ (ዮሴፍ) 2ኛ
116. ቄርሎስ 6ኛ
117. ባሲልዮስ
118. ቴዎፍሎስ
119. ተክለሃይማኖት
120. መርቆሬዎስ
121. ጳውሎስ
122. ማትያስ

ምንጭ:-ሃይማኖተ አበው አንድምታ ትርጓሜ [ፍቅረ ማርያም ባዘዘው]
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
#Update

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጋር በተገናኘ የተከሰተው ክስተት ዛሬም በተለያዩ አካባቢዎች ውጥረት እንዲፈጠር አድርጎ መቀጠሉን ለማወቅ ተችሏል።

የቤተክርስቲያኗ መገናኛ ብዙሃን  ፤ " በኦሮምያ ክልል ባሉ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ዛሬም ኦርቶዶክሳውያንን የማሰር ተግባር እንደቀጠለ ነው " ብለዋል።

ለአብነት የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት መቀመጫ በሆነችው አምቦ ከተማ የሀገረ ስብከቱ የሚዲያና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አባ ጴጥሮስ ከጠዋቱ 2:00 ሰዓት አካባቢ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ከሚገኘው ማረፊያቸው በጸጥታ ኃይሎች መወሰዳቸውን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባም ትላንት ረቡዕ " በወቅታዊ ጉዳይ ወጣቶችን ታነሳሳላችሁ " ተብለው የቀጨኔ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን የአካባቢ ወጣቶች መታሰራቸውን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ፤ ዛሬ በወለቴ እና በዓለም ገና አካባቢዎች የጸጥታ አካላት በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ ማዋከብ እና ድብደባ እያሳደሩ መሆኑን የቤተክርስቲያኒቱ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

በወለቴ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተክርስቲያን በመሳሪያ የታገዘ ድብደባ እየተፈፀመ መሆኑን የገለፁት የቤተክርስቲያኒቱ መገናኛ ብዙሃን እስከ አሁን ሁለት ሰዎች በፀጥታ ኃይል እንደተመቱ አስረድተዋል።

እስካሁን ግን ከፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል የታየ ምላሽ የለም ሲሉም ወቅሰዋል።

ከዚህ ባለፈ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ወሊሶ ከተማ ምእመናን፣ ወጣቶች በፀጥታ ኃሎች እየታፈሱ መሆኑን የቤተክርስቲያኗ መገናኛ ብዙሃን አሳውቀዋል።

በዚሁ ቀጠና ውጥረት ሊፈጠር የቻለው ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዞ የለያቸው አካላት ወደ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት " ወሊሶ ከተማ " ይመጣሉ መባሉን ተከትሎ መሆኑ ተነግሯል።

tikvahethiopia

@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
"በየቤተ ክርስቲያኑ በር ላይ የፈሰሰውን ደም እረግጠው ገብተው እንዴት ብለው የክርስቶስን ደም ቀድተው ያጠጡን ይሆን?"

ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
ወንድሜ አንተ በመከራ ውስጥ ካለህ የዩናስን ዓሣ ነባሪ አስታውስ። ከፍራቻ ትገላገላለህ። መከራው እግዚአብሔር ጸጋውን ሊያበዛልህ ስለፈለገ ያዘጋጀው ዓሣ ነባሪ እንደሆነ የምታውቅበት ጊዜ ይመጣል። የዚህ ዓለም የባሕር ዓሣዎች ብዙ ስለሆኑ ስትዋጥ እንዳይከፋህ መጠንቀቅ ይኖርብሃል። የመጀመሪያው ባህታዊ ጻድቁ አባ ጳውሊ የተናገረውን መዘንጋት የለብህም "ከመከራ መራቅ የሚወድ ከእግዚአብሔር ይርቃል" ብሏል። በእውነት መከራ የጸሎት ትምህርት ቤት ነው። "በመከራዬ ሳለሁ ወደ አምላኬ ጮኽሁ እርሱም ሰማኝ። በሲኦልም ሆድ ውስጥ ሆኜ ጮኽሁ። ቃሌንም አደመጠ" ዮናስ 2፥3

#አቡነ_ሺኖዳ_ሣልሳዊ
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
"ሆዳችሁ ጠግቦ ከምታቀርቡት አንድ መቶ ጸሎትና ተራራ ከሚያርድ ድምጻችሁ ይልቅ በጾም ውስጥ ሆናችሁ የምታቀርቡት አንድ ጸሎት ተሰሚነት አለው።"

#አቡነ_ሺኖዳ_ሣልሳዊ
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
ጠላት 'ዲያብሎስ' ያልተረዳው ነገር ቢኖር "ክርስቲያን እና ምስማር ሲመቱት (ሲገፉት) መጥበቁን" ብቻ ነው።
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
#የክርስቲያን_መከራ

ለአንድ ክርስቲያን መከራ ለጥቅሙ የሚሰጠው ነው፡፡ ለአንድ ክርስቲያን መከራን መቀበል ማለት ከሰማያዊ ክብር መሳተፍ ነው፡፡ ይህስ እንደ ምን ነው ያልከኝ እንደ ኾነም እንዲህ ብዬ እመልስልሃለሁ ፡- ስንፍናንና ክፉ ፈቃድን የሚያርቅ፣ ዓለማዊ ግብር መውደድን፣ ውዳሴ ከንቱ መውደድን የሚያርቅ ነውና የክርስቲያን መከራ ክብርን ያስገኛል፡፡ ነፍስን የሚረዳ፣ በክብር ላይ ክብርን የሚያስገኝ ነውና የክርስቲያን መከራ የሚያሳዝን መከራ አይደለም ብዬ እነግርሃለሁ፡፡

የቅዱሳኑ ክብራቸው እንዲህ ደምቆ ልናየው የቻልነው ከምን የተነሣ እንደ ኾነ እንመልከተው፡፡ ስላገኛቸው መከራ አይደለምን? ፈቃድህ ከኾነ ገና ከመነሻው አንሥተን እንቍጠራቸው፡፡ አዎ! ከአቤልና ከኖኅ ጀምረን እስኪ እንቍጠራቸው፡፡ እነዚህ ቅዱሳን በዚያ ለመቍጠር እንኳን በሚታክቱ ክፉዎች ሰዎች መካከል እየኖሩ ያለ መከራ ክብርን ማግኘት አልተቻላቸውም፤ እንዲህ እንደ ተባለ፡- “ኖኅም በትውልዱ ጻድቅ ፍጹምም ሰው ነበረ፤ እግዚአብሔርንም ደስ አሰኘው” (ዘፍ.6፥9)፡፡ ተመልከት! ለእኛ አብነት የሚኾኑን እጅግ በጣም ብዙ ሰዎች አሉን፡፡ ብዙ አበውን፣ ብዙ ሕፃናትን፣ ብዙ መምህራንን አብነት አድርገን መከራ እንቀበላለን፡፡ በሰብአ ትካት መካከል ኾኖ መከራ ስለ ተቀበለው ስለ ኖኅ ምን እንላለን? በዙሪያው ስለ ነበረው እንግዳና አስደናቂ ዝናብስ ምን እንናገራለን? ወይስ አብርሃም ከአገር አገር ሲሰደድ መኖሩን፣ ሚስቱን እንደ ቀሙት፣ ጦርነትና ረሃብ እንዳገኘው እናገር ዘንድ ይገባኛልን? ወይስ እጅግ አስጨናቂ ነገሮች ስላገኙት፣ ከቦታ ቦታ ስላሳደዱት፣ ድካሙ ከንቱ ይኾንበት ስለ ነበረው፣ በድካሙ ላይ ሌሎች ሰዎች ይጠቀሙበት ስለ ነበረው ስለ ይስሐቅ ልናገርን? ወይስ ስለ ያዕቆብ ልናገርን? ያዕቆብ ያገኘውን መከራ እዘረዝር ዘንድ አይገባኝም፤ እርሱ ራሱ ለፈርዖን የተናገረውን ምስክር አድርጌ ላቅርብ እንጂ፤ እንዲህ ያለውን፡- “የሕይወቴ ዘመኖች ጥቂትም ክፉም ኾኑብኝ፡፡ አባቶች በእንግድነት የተቀመጡበትንም ዘመን አያህሉም” (ዘፍ.47፥9)፡፡ ወይስ ስለ ዮሴፍ ልናገር ይገባኛልን? ወይስ ስለ ሙሴ፣ ወይስ ስለ ኢያሱ፣ ወይስ ስለ ዳዊት፣ ወይስ ስለ ኤልያስ፣ ወይስ ስለ ሳሙኤል፣ ወይስ ስለ ነቢያት ኹሉ ልናገር ይገባኛልን? እነዚህ ኹሉ በመከራ እንደ ከበሩ አታውቅምን? ሰው ሆይ! ከዕረፍትና ከቅምጥል ሕይወት ክብርን ልታገኘ ትሻለህን? እኔ እነግርሃለሁ፤ በፍጹም አታገኘውም፡፡

ወይስ ስለ ሐዋሪያት ልናገርን? እነዚህስ ከኹሉም በላይ መከራ ተቀበሉ፡፡ ጌታችን ክርስቶስም እንዲህ ብሏልና፡- “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ” (ዮሐ.16፥33)፤ “እናንተ ታለቅሳላችሁ፤ ታዝኑማላችሁ፡፡ ዓለም ግን ደስ ይሏል” (ዮሐ.16፥20)፤ “ወደ ሕይወት የምትወስደው በር እጅግ ጠባብ መንገዷም ቀጭን ናትና የሚገቡባትም ጥቂቶች ናቸው” (ማቴ.7፥14)፡፡ ታዲያ እስኪ ንገረኝ! ጌታችን መንገዷ ጠባብ ናት እያለ አንተ ሰፊውን መንገድ ትፈልጋለህን? ይህስ እንደ ምን ሊኾን ይችላል? በሌላ መንገድ የምትኼድ ከኾነም ወደ ሕይወት አትደርስም፤ እንደ ምርጫህ ምረረ ገሃነም ያገኝሃል እንጂ፡፡

የክርስቲያን መከራ እና ሌሎች #ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ እንዳስተማረው በገብረ እግዚአብሔር ኪደ
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
ብሒላተ አበው ወእመት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ:
በስመ አብ፤ ወወልድ፤ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ከጥር ፳፱ እስከ የካቲት ፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ለ ፫ ተከታታይ ቀናት በመላው ዓለም የታወጀው የነነዌ ፆም እና ምሕላ መጠናቀቅን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ::
++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
በትንቢተ ዮናስ በሰፊው እንደተጠቀሰው የነነዌ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት ላይ ስለአመጹ እና ግብራቸውም በእግዚአብሔር ፊት አጸያፊ በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር ዮናስን “ተነስተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፤ ክፋታቸውም ወደ ፊቴ ወጥቷልና በእርስዋ ላይ ስበክ” በማለት አዘዘው፡፡ ትንቢተ ዮናስ ምዕ ፩ ቁጥር ፪ ዮናስም ድምፁን ከፍ አድርጎ ለነነዌ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ሲሰብክ “የነነዌ ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም አዋጅ ነገሩ፤ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ፡፡ ወሬውም ወደ ነነዌ ንጉሥ ደረሰ፤ እርሱም ከዙፋኑ ተነስቶ መጎናጸፊያውን አወለቀ ማቅም ለበሰ፤ በአመድም ላይ ተቀመጠ፡፡ አዋጅም አስነገረ፤ በነነዌ ውስጥ የንጉሡንና የመኳንንቱን ትእዛዝ አሳወጀ፤ እንዲህም አለ ሰዎችና እንስሶች፤ ላሞችና በጎች አንዳችን አይቅመሱ፣ አይሰማሩ፣ ውኃንም አይጠጡ፤ ሰዎችና እንስሶችም በማቅ ይከደኑ፣ ወደ እግዚአብሔርም በብርቱ ጩኸት ይጩኹ፤ ሰዎችም ሁሉ ከክፉ መንገዳቸውና በእጃቸው ካለው ግፍ ይመለሱ፡፡ እኛ እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ተመልሶ ይጸጸት እንደሆነ ማን ያውቃል፡፡ እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውንም አየ፤ እግዚአብሔርም ያደርግባቸው ዘንድ በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም” ትንቢተ ዮናስ ፫፡ ፭-፲

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ይህን የነነዌ ሰዎች ፆም መነሻ በማድረግ የነነዌ ሰዎችን በምሕረቱ የጎበኘ አምላክ እኛንም በምሕረቱ ይቅር ይለን ዘንድ በየዓመቱ በአዋጅ በመፆም አምላካችንን ስንማጸንበት ኖረናል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባዔ በጥር ፳፮ ቀን ፳፻፲፭ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በወሰነው መሠረት የካቲት ፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም የተጠናቀቀው የነነዌ ፆምና ምሕላ ልዩ በሆነ በመንፈሳዊ የንስሐ ጸሎት በሰላም ተጠናቋል፡፡

በምሕላውም ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ጀምሮ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤ ካህናት፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ አገልጋዮች እና ምእመናን እንደነነዌ ሰዎች ጥቁር ለብሰን ጠዋትና ማታ በጸሎት ፤ በምሕላ፤ ቀን በቅዳሴ እንዲሁም በሰባቱ የጸሎት ጊዜያት ፈጣሪያችንን ስንለምን እና ስንማጸን የቆየንበት ምክንያት በቤተክርስቲያናችን ላይ የመጣው ፈተና እጅግ በጣም ከባድ በመሆኑ ነው፡፡

በዚህ የጾምና የንስሐ ወቅት ምእመናን ልጆቻችን የአባቶቻችሁን ጥሪ ሰምታችሁ፤ የሹመኞችን ማዋክብና እስር ሳትፈሩ ጥቁር ለብሳችሁ ጠዋትና ማታ በጾምና በምሕላ፣ ቀን በቅዳሴ በቤተክርስቲያን ቅጥር እየተገኛችሁ ለአምላካችን ያቀረባችሁትን ጸሎት እና ምሕላ እግዚአብሔር ሰምቶ ለችግራችን መፍትሄ፣ ለሀገራችን ሰላምን እንደሚሰጠን እምነታችን ጽኑ ነው፡፡ እናንተም ምእመናን የቤተ ክርስቲያንን ጥሪ ሰምታችሁ ለሃይማኖታችሁ፣ ለሀገራችሁ አንድነትና ሰላም ያላችሁን ጥልቅ ፍቅር ስለገለፃችሁም ያገኘነው መንፈሳዊ ብርታት ሳንገልፅላችሁ አናልፍም፡፡

በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በእናታችን በቅድስት ድንግል ማርያም እና በቅዱሳን አማላጅነት፣ በመላእክት ተራዳኢነት በፍፁም ፍቅርና አንድነት የያዝነውን ጸሎት እና ምሕላ አጠናቀናል፡፡ ችግራችንን ለአምላካችን በለቅሶ እና በጩኸት ነግረናል፡፡ ከዚህ በኋላ መከራው ቢጸና፣ የመከራው ጊዜ እንኳን ቢረዝም እግዚአብሔር በመከራ ውስጥ ሊያፀናን እና ሊያበረታታን አስቦ በመሆኑ በፍፁም አንናወጽም፡፡ ከእነኚህ መከራዎች በኃላም ታሪክን ጽፈን ሃይማኖታችንን ጠብቀን እና አስጠብቀን በመንፈሳዊ ጽናት እና ተጋድሎ እንሻገራለን፡፡

ጥቃቱ የቤተ ክርስቲያንን እውነት በካዱና በእውነተኛዋ ቤተ ክርስቲያን መካከል ነው፡፡ ይህም የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሃይማኖት፤ ቀኖና እና አስተዳደራዊ ሕግጋትን ጥሰው ሕገወጥ የጳጳሳት ሢመት በመደረጉ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ቅዱስ ሲኖዶስ በሕገ ቤተ ክርስቲያንና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት በጥር ፲፰ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ይህን ጥሰት የፈፀሙትን ግለሰቦች አውግዛ ከቤተ ክርስቲያን ኅብረት የለየቻቸው ቢሆንም ጉዳዩ ከግለሰቦቹ በላይ በመንግሥት ስልጣን ላይ ባሉና ጽንፈኛ በሆኑ ፖለቲከኞች እንዲሁም የሌላ እምነት ተከታዮች ጭምር የሚደገፍ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያንን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈላት ይገኛል፡፡

እየተፈጸመ ያለው ድርጊት በሰማያዊ መንፈሳዊ ዓለምና በምድራዊ ሥጋዊ ዓለም መካከል ስለሆነ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥም የቤተ ክርስቲያን ክብርና ተቋማዊ ልዕልና ተደፍሯል፡፡ የቤተክርስቲያን ቅጥሮች መሣሪያ በያዙ አካላትና በመንግሥት የጸጥታ መዋቅር በኃይልና በጉልበት ተወሯል፡፡ ሊቃነ ጳጳሳት አባቶች ለብዙ ዓመታት ከኖሩበት አህጉረ ስብከት ያለአንዳች የሕግ መሠረት በጸጥታ መዋቅሮች ተባረዋል፡፡ በነጻነት የመንቀሳቀስ መብቶቻቸው ተገድቦም በግዞት ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ተደርገዋል፡፡ ወደ አህጉረ ስብከታቸውም ተመልሰው መግባት እንዳይችሉ እቀባ ተደርጎባቸዋል፡፡ ካህናት አባቶች እና ምእመናንም ያለአንዳች የሕግ መሠረት በየእስር ቤቱ ያለበቂ ምክንያት በሕገወጥ መንገድ ታጉረዋል፡፡ በጸጥታ ኃይል ከመጠን በላይ ከመደብደባቸው የተነሳ የሞት፣ የከባድ እና ቀላል አካል ጉዳት እንዲደርስባቸው ምክንያት ሆኗል፡፡ በአጠቃላይም በመንግሥት ኃይሎች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈፅሞባቸዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ይህ ሁሉ በደል ቢፈጸምባትም ናዛዜ ሕዙናን የሆነው አምላካችን ለቤተ ክርስቲያናችን እና ለሀገራችን መፍትሔ እንዲያመጣልን፣ መንግሥትም ወደ ልቡ ተመልሶ ቤተክርስቲያንን እንዲያከብርና እንዲጠብቅ በሚል ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ይህን ጾም የነነዌ ሰዎች እንዳደረጉት ጥቁር ለብሰን በፍፁም ኃዘን ወደ አምላካችን እንድንጮህ ቅዱስ ሲኖዶስ ትእዛዝ ባስተላለፈበት ማግስት በሻሸመኔ ደብረ ስብሐት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ሕገወጡን ቡድን በኃይል ለማስገባት በመንግሥት የጸጥታ መዋቅሮች በተወሰደ አሰቃቂ እርምጃ እስከ አሁን በደረሰን መረጃ ቁጥራቸው ከ፴ በላይ የሚሆኑ ካህናትን እና አገልጋዮችን ጨምሮ የቤተ ክርስቲያናችን ልጆች ቅጥሯ አይደፈርም፣ ቤተክርስቲያን በተወገዙ ግለሰቦች አትረክስም በሚል ለሃይማኖታቸው ሰማእትነትን ተቀብለዋል፡፡ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ልጆቿም በደረሰባቸው ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት ምክንያት በሕክምና ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ሁሉ በደል በኋላም እስከ አሁን ድረስ የሞቱትን በአግባቡ መቅበርና የተጎዱትን በበቂ ሁኔታ ማሳከም ሳንችል ቀርተናል፡፡ እነዚህ ሰማዕታት በዚህ ኃጢያት በበዛበት ዘመን ለቤተክርስቲያን እስከሞት ድረስ በመታመን ለቤተ ክርስቲያንና ለምእመናን የጽናት ተምሳሌት በመሆናቸው ቤተክርስቲያን ስትዘክራቸው ትኖራለች፡፡ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን በልጆቿ ላይ እየደረሰ ባለው ሞት፤ እርዛት፤ እስራት እና መልከ ብዙ በሆነው መከራ ብታዝንም ለክርስትና እውነተኛነት ምስክሮች የሆኑ አዳዲስ ቅዱሳን ሰማእታትን በማግኘቷም እጅግ ደስ ትሰኛለች፡፡
ጾሙ ከተጀመረም በኋላ ሕዝቡ ወደ አምላኩ እንዳይጮህ እና እንዳይጸልይ ለማወክ የሕዝብ አስተዳዳሪ ሆነው የተሾሙ የመንግሥት ሹማምንት ሊያገለግሉት ኃላፊነት የተቀበሉበትን የሀገሪቱን ሕግ ጥሰው ምእመናን ልጆቻችን ጥቁር ለብሰው ወደ መሥሪያ ቤት እንዳይገቡና በመንግሥት ቢሮዎችም አገልግሎት እንዳያገኙ በተለይም በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እና አንዳንድ በፌዴራል እና በከተማ መስተዳድር ቢሮዎች ጥቁር የለበሱ እና በሀዘን ላይ ያሉ ልጆቻችንን በማሠር ሲያንገላቱ በዓይናቸው ያዩ ምስክሮች አረጋግጠውልናል፡፡ በዚህም ሹማምንት ስልጣናቸውን ቤተ ክርስቲያንን ለማጥቃት እየተጠቀሙበት መሆኑን እና ለቤተ ክርስቲያናችንም ሆነ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ከፍተኛ ንቀት እና ጥላቻ ያላቸው መሆኑን ተረድተናል፡፡

ይህ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየደረሰ ያለው መከራና በደል በዚህ ዘመን በጉልህ የሚጠቀስ የቤተ ክርስቲያን የስደትና የመከራ ጊዜ ነው፡፡ ይህ የቤተ ክርስቲያን የስደትና የመከራ ጊዜ በቤተ ክርስቲያኒቱ የታሪክ መዝገብ እና በመጽሐፈ ስንክሳር ተመዝግቦ ይቀመጣል፡፡ ለትውልድም ይተላለፋል፡፡ ይህ የፈተና ዘመን ያልፋል፤ ነገር ግን በዚህ ታሪክ ውስጥ ከእውነት ጎን የቆማችሁ ስማችሁ በታሪክ እና በወርቅ ቀለም ሲፃፍ በቤተክርስቲያን ላይ መከራ ያበዛችሁ ክፉ ታሪካችሁን ዛሬ በእጃችሁ ጽፋችሁ አልፋችኋል፡፡

በዚህ አጋጣሚ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውጭ ሌሎች የክልል ርዕሳን መስተዳድሮችና ከተሞች በተለይም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፤ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት፤ የሲዳማ ክልላዊ መንግስት፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት፤ የሱማሌ ክልላዊ መንግሥት፤ የቤንሻንጉል ክልላዊ መንግሥት፣ የሐረሪ ክልላዊ መንግሥት፣ የአፋርና ጋምቤላ ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት፤ በጎፋ ዞን የሳውላ ከተማ እና ሌሎች ስማቸውን ያልጠቀስናቸው መንግሥታዊ ተቋማት የቤተ ክርስቲያናችንን ጥሪ በመከተል በአግባቡ ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር የወሰዳችሁ ፍትሐዊ እና ሕጋዊ መፍትሔዎችን እናደንቃለን፣ በቤተ ክርስቲያንም ስም እናመሰግናለን፡፡ እንዲሁም ሀዘናችሁ ሀዘናችን ነው ብላችሁ ከጎናችን የተሰለፋችሁ አኃት አብያተ ክርስቲያናት፤ የሃይማኖት ተቋማት፣ ድርጅቶች እና ጉባኤያት፤ የእስልምና እምነት ተከታዮች፤ በእምነት የማትመስሉን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ስላደረጋችሁልንና ስለምታደርጉልን እርዳታና ትብብር በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም እናመሰግናለን፡፡
ጸሎተ ምሕላውን ስናውጅ መንግሥት ሕግ አክብሮ እንዲያስከብር፣ የቤተክርስቲያኒቱን ክብር እና ልዕልና እንዲያከብር፣ በሃይማኖታችን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን እንዲያቆምና ወደ ውስጡ ማየት እንዲችል ነበር:: ይህ ድርጊት እስከ አሁን ድረስ ግን መንግሥት ለዘመናት ሕጋዊ ተቋም እና የሀገር ባለውለታ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያንን ከመስማት እና ችግሯን ከመቅረፍ ይልቅ የማዋከቡን ሥራ አጠናክሮ ቀጥሎበታል፡፡ በዚህም መንግሥት ችግሮችን ኃላፊነት ተሰምቶት እንዲፈታ ያደርገዋል የሚል እምነት ቢኖረንም አገዛዙ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ልቡ መደንደኑን መመልከታችን በእጅጉ ልባችንን ሰብሮታል፡፡

በተለይም ቤተ ክርስቲያናችን ያወጀችው የ፫ ቀናት ጸሎትና ምህላ በአግባቡ እንኳን ሳይጠናቀቅ ከመንግሥት ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ወቅታዊ የፀጥታ ጉዳይን አስመልክቶ በየካቲት ፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም የተሰጠው የሰልፍ ክልከላ መግለጫ መንግሥት አሁንም ችግሩን ለመፍታት ሳይሆን ቤተክርስቲያኒቱን ለአንዴና ለመጨረሻ ለማውደምና ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማጥፋት የታወጀ አዋጅ መሆኑን በጽኑ እንድናምን አድርጎናል፡፡

በመግለጫውም፡-
፩ኛ. በእምነቱ አባቶች በተመሳሳይ መልኩ ሰልፍ ተጠርቷል በማለት መጥቀሱ የቤተክርስቲያን የመጨረሻው አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዞ የለያቸውን አካላት የእምነቱ ተከታይ ማድረግ ብቻ ሳይሆን መብት ያላቸው ሕጋዊ አካላትና የቤተ ክርስቲያን አባቶች አድርጎ መጥራቱ አሁንም ላይ ማብራርያ ለመስጠት መሞከሩ የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር የሚነካ እና የሚያጠለሽ እንዲሁም ሕግና ሥርዓትን ከማስከበር ይልቅ ለሕገ ወጦች ጠበቃ ሆኖ የሚከራከረው መንግሥት መሆኑን ጭምር ለመረዳት ችለናል፡፡ በመሆኑም ቤተክርስቲያን በመንግሥት የደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ተሰጠ የተባለው መግለጫ የቤተ ክርስቲያናችንን ሕጋዊ መብት የገፈፈ እና ሕገ ወጥ መግለጫ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን አትቀበለውም፡፡
፪ኛ. ጉዳዩን የውጪ እና የውስጥ ጠላቶች የፈጠሩት ነው በማለት የተለመደውን ፖለቲካዊ ቅርፅ ለማስያዝ መሞከርም ቤተክርስቲንያንም ሆነ ሕዝብን መናቅ በመሆኑ የምንቀበለው አይሆንም፡፡ ቤተ ክርስቲያን በተለይ ላለፉት ፬ ዓመታት በሀሰተኛ ትርክት ልጆቿ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል መከራን ሲቀበሉ ችግሮችን በሆደ ሰፊነት ችላ ያለፈችው የሀገር መሠረት እንዳይናጋ፣ ቅጥሯ እንዳይደፈር በማሰብና በሀገር አንድነት ላይ ባላት የማይናወጽ ጽኑ አቋም ምክንያት መሆኑን መንገር ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡ ጉዳዩ ግልፅ የሆነ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ሆኖ እያለና መፍትሄውም በመንግሥት እጅ የሚገኝ ብቻ መሆኑ እየታወቀ የፖለቲካ ቅርፅ ለማስያዝ መሞከር ችግሩን ያባብሰው እንደሆን እንጂ አይፈታውም፡፡

በሰሞኑም ቤተ ክርስቲያናችን በመዋቅር የምትመራ እና ልጆቿም ድምጽዋን አውቀው በአግባቡ የሚሰሟት መሆኑ እየታወቀ ሆነ ተብሎ ቃላት አጠቃቀሙ እንኳን ኦርቶዶክሳዊ ያልሆነ የሀሰት እና ጸብ አጫሪ የሆኑ መልእክቶችን በአደባባይ የተለጠፉ መሆናቸውን ሲታይ ምን ያህል ጉዳዩን ላልተገባ ፖለቲካዊ ጥቅም እንደተፈለገ ለመረዳት ችለናል፡፡ ይህ ተለጠፈ የተባለውም ሕገ ወጥ ጽሑፍ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ያልሆነና ፈጽሞም ሊሆን የማይችል መሆኑን ጭምር ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡

፫ኛ. የትኛውም ሰልፍ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ማድረግ አይቻልም በማለት የተደረገው ክልከላን በተመለከተም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ውስጥ መሠረታዊ መብት ሆኖ የተጠቀሰ እና በሕገ መንግሥቱም አንቀፅ ፴ ላይ በግልጽ የተደነገገ በመሆኑ መንግሥት ራሱ የሚመራበትን ሕገ መንግሥት ማክበርና ማስከበር ይኖርበታል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ላይ ከላይ የተጠቀሰው ከፍተኛ መከራና በደል ምክንያት ከብዙ ሺህ ዓመታት በላይ ጸንታ የመጣችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በእኛ በልጆቿ ዘመን ስትፈርስ ዝም ብሎ መመልከት በጭራሽ የሚታሰብ አይሆንም፡፡

ይህን በደላችንን ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ለማሳወቅ እና መንግሥትም ከሚያደርገው ጣልቃ ገብነትና አፈና ወጥቶ ሕግ እንዲያከብር እና እንዲያስከብር የጠራነው የየካቲት ፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ሰላማዊ ሰልፍም መንግሥት ተገቢውን ጥበቃ በማድረግ እንድናከናውን መፍቀድ አሊያም የጠየቅናቸውን ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎቻችንን በአግባቡ እና አንድ በአንድ መመለስ አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ደግመን ደጋግመን ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥም የሚደርስብንን ሞት፣ መከራና ስደት እኛ አባቶች ከመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ጋር ደስ ብሎን የምንቀበለው እንጂ ቤተ ክርስቲያናችን እና ሀገራችን ስትፈርስ ቆመን የምንመለከት፣ ዝም የሚል አንደበትና የሚሸከም ኀሊና የማይኖረን መሆኑን በአጽንዖት እናሳስባለን፡፡
መንግስት ከአጉል እልከኝነቱ ወጥቶ ከሕገ ወጦቹ ግለሰቦች ጋር በመተባበር በአደባባይ እየፈጸመ ያለውን የሕግ ጥሰት ዛሬን ጨምሮ በቀጣዮቹ ፪/ሁለት/ ቀናት ውስጥ እንዲያቆም እና ሕግ እና ሥርዓትን እንዲያስከብር፣ በኃይል የወረራቸውን መንበረ ጵጵስና እና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ለቆ ለቤተክርስቲያኒቱ ሕጋዊ መዋቅር እንዲያስረክብ፣ ያለአግባብ ያሠራቸውን ካህናት እና ምእመናን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቅ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ለፈፀመው በደል በአደባባይ ይቅርታ እንዲጠይቅ፤ በካህናት እና ምእመናን ላይ ለደረሰው ሞት እና የአካል ጉዳት ተገቢውን ካሳ እንዲክስ እና የወደሙ ንብረቶቿን እንዲጠግን በጥብቅ እንጠይቃለን ፡፡

መንግሥት በዚሁ አካሄድ ሕግ እየጣሰ እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር እና ልእልና እያዋረደ የሚቀጥል ከሆነ ቤተ ክርስቲያን መንግሥት የጣሰውን ሕግ መሠረት በማድረግ መብቷን ለማስከበር እስከአሁን ድረስ ፍጹም ሰላማዊ የሆነውን እንቅስቃሴዋን አድማሱን በማስፋት በየካቲት ፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ለማድረግ ያቀደችውንና ያሳወቀችውን ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ ያለማንም ከልካይነት በራሷ አደባባይ የምታከናውን መሆኑን እያሳወቅን መንግሥትም ድርሻው ሰልፉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ብቻ መሆኑን እያሳሰብን ዛሬም ቢሆን መንግሥት ቆም ብሎ በማሰብ ከእኛ ከአባቶች ጋር ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊና መንፈሳዊ የአስተዳደር ሥርዓታችንን ባልጣሰ መልኩ ለመነጋገር እና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት ካደረገ በውይይት ለመፍታት መንፈሳዊ በራችን ክፍት መሆኑንም እናሳውቃለን፡፡

ከዚህ ውጭ ግን በሁለቱ አባቶች መካከል የተፈጠረ ችግር እየተባለ የሚነገረው ፖለቲካዊ ጨዋታ የመንግሥት እንጂ በሀገሪቱ ሕጋዊ ሰውነት የሌላቸውና ከቤተ ክርስቲያን የተለዩ ግለሰቦች ጋር ማነጻጸር ሕገ መንግሥታዊም ሆነ ሞራላዊ የሕግ መሠረት የለውም፡፡

ስለዚህ ቤተ ክርስቲያናችን የጠራችውን ሰላማዊ እና ሕጋዊ የሆነ የመብት ጥያቄ የማፈን ሂደትን በጥብቅ እንቃወማለን፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን እስከአሁን ባደረጋችሁት ጽናትና ተጋድሎ ሃይማኖታችሁንና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንችሁን እንዳላሳፈራችሁ ሁሉ አሁንም ከስሜታዊነት በወጣ ሁኔታ በከፍተኛ ጽናት እና ጥንካሬ የአባቶቻችሁን ድምጽ ብቻ እንድትሰሙ፣ ቤተ ክርስቲያንን በየአጥቢያችሁ ተደራጅታችሁ እንድትጠብቁ፤ ለአባቶቻችሁ መንፈሳዊ ጥሪ ፈጣን ምላሽ እንድትሰጡ፣ እየመጣው ላለ መከራና ስደት ለመንፈሳዊ ተጋድሎ እንድትዘጋጁና በፍፁም መንፈሳዊ ጨዋነት በአንድነት የመጣብንን ፈተና እንድትወጡ አደራ እያልን አባታዊ መልእክታችንን እያስተላለፍን ሰላማዊ ሰልፉን በተመለከተም በአጭር ጊዜ ውስጥ ዝርዝር መግለጫ የምንሰጥ መሆኑን እያሳውቅን በዚህ ጥቃት መስዋእትነት የከፈሉ እና ያረፉ ልጆቻችንን ነፍሳቸውን በአጸደ ገነት በክብር ያሳርፍልን እያልን ጸሎተ ፍትሐትም በየደረጃው የሚከናወን መሆኑን እያሳወቅን በተለያዬ ጊዜ ዛሬን ጨምሮ በወለቴ እና በሰበታ ከተሞች የደረሰውን የአካል ጉዳት እና ሞት እግዚአብሔር ምህረት እና መጽናናቱን ያድልልን፡፡ እግዚአብሔርም ገድላችሁን፣ ጽናታችሁንና ጸሎታችሁን ይቀበል፤ የቅዱሳን አምላክ ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

“እግዚአብሔር ሀገራችንን ይባርክ”
የካቲት ፪ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም.
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
2024/09/24 18:20:58
Back to Top
HTML Embed Code: