Telegram Web Link
«13 ዓመትሽ ነበር። አባትሽ ሲሞት 13 ዓመትሽ ነበር። አባትሽ አንቺን ነበር የሚመስለው። መልካችሁ ብቻ መሰለሽ? ቁመትሽ ሳይቀር የሱ ነው። ነገረ ስራሽ የእርሱ ቅጂ መሆንሽ አይጣል ነው።» አለችኝ ለቅሶዋን ገታ አድርጋ። ከዚህ በኋላ የምጠይቃት ነገር ሁሉ ከእርሱ ሞት ጋር የተያያዘ እና የሚያስለቅሳት ስለመሰለኝ ምን ዘልዬ ምን እንደምጠይቃት ግራ ተጋባሁ።

«ኪዳን የዘጠኝ ዓመት ልጅ ነበር። እሱ እንዳንቺ ጠንካራ አልነበረም። (ቅስስ ብላ ነው ይሄን የምታወራው) ክፉ እንዳያይ ጠበቅሽው፤ ክፉ እንዳይነካው ጠበቅሽው። እህትም እናትም ሆንሽው።» ብላኝ ፊቷን አዞረች።

«አንቺስ? እንዴት ነው ከህይወቴ የጎደልሽው? ለምን ተለያየን? ኪዳን አሁን የት ነው?»

አልመለሰችልኝም። ፊቷን ከእኔ መደበቅ ነው የፈለገችው። በእጇ አልጋ ልብሱን ጨመደደችው። ከአባቴ ሞት በላይ ሀዘኗን የሚያበዛ ሌላ ነገር መኖሩ ገባኝ።

«እ? ንገሪኝ ምንድነው የተፈጠረው? » አልኳት

«ኪዳን ካናዳ ነው ያለው። ዶክተር ሆኗል አልሽኝ። አሁንም ትምህርቱን ቀጥሎ የጭንቅላት ቀዶ ህክምና እየተማረ ነው ያለው አልሽኝ መሰለኝ በትክክል ካስታወስኩ።» አለችኝ ፊቷን ሳታዞር

«አንቺስ? ምንም ቢሆን ንገሪኝ እና ታሪኬን የተሟላ አድርጌ ልገጣጥመው።» ልበላት እንጂ በምንም መርፌ የማልሰፋው ብዙ የተቦጫጨቀ ጎዶሎ እንዳለው ገብቶኛል።

«አባትሽ ከሞተ በኋላ (ዝም አለች ለሆነ ሰከንዶች። ተገቢውን ቃል እየፈለገች መሰለኝ) አባትሽ ከሞተ በኋላ አቃተኝ። እናት መሆን አቃተኝ። ያንቺን ፊት በየቀኑ ማየት አቃተኝ። ለአጎታችሁ ትቻችሁ ከተማ መጣሁ። ይኸው ነው!! እኔ የማልረባ እናት ስለሆንኩ ነው የተለያየነው። ራስ ወዳድ ስለነበርኩ ነው ከህይወታችሁ የጎደልኩት።» እያለች ትንሰቀሰቅ ጀመር። የሚሰማኝ ስሜት ተደበላለቀብኝ። ምንም ቢሆን ይቅር ብዬሻለሁ እንዳልኳት አልቀለለኝም። አባታቸው የሞተባቸው ልጆችዋን እንዴት ትታን ትሄዳለች? ልቤ የለመደው ብርድ በረደው። ውስጤ ተከፋባት ግን ደግሞ ከነገረችኝ ታሪክ የተለየ ያልነገረችኝ ምክንያት እንዳለ ይሰማኛል።

«በቃ? ይሄ ብቻ ነው ምክንያትሽ? ለምንድነው ያልነገርሽኝ ሌላ ነገር እንዳለ የሚሰማኝ? እ?» ከዚህ በኋላ የጠየቅኳትን ጥያቄ አንዱንም አልመለሰችልኝም። እቤቴ ይዣት ልሄድ ብለምናትም እንቢ አለችኝ። ልቀየማትም እፈልጋለሁ ልታረቃትም ያምረኛል። እሺ ልጅ ሆኜ ትታኝ ሄደች አሁን እንኳን በሞቷ አፋፍ ላይ ሆና የቀራትን ቀናት ፍቅሯን እንደተራብኩ እንዴት አይገባትም? ያልጠገብኩት እቅፏ እንደሚያስፈልገኝ እንዴት አትረዳም? ልጮህባትም ያምረኛል። ደግሞ እቅፏ ውስጥ ገብቼ ለሰዓታት ጠረኗን መማግም ያምረኛል። ለብዙ ደቂቃዎች ያለምንም ንግግር ዝም ብለን ቆየን። ትቻት ብወጣ ስመለስ የማላገኛት ዓይነት ስሜት እየተሰማኝ ከልክ በላይ ከፋኝ። ከየት መጣ ሳልለው እንባዬ ገነፈለ።

«ምንም አልጠይቅሽም። ምንም አትመልሽልኝ። አጠገቤ ብቻ ሁኚልኝ። የቀረሽ ቀን ቀንድም ቀን ይሁን አንድ ዓመት አብረሽኝ ሁኚ። አንድ ቀንም ቢሆን እማዬ ልበልሽ? አንዲት ሰዓትም ቢሆን ልጅሽ ልሁን?» ብዬ እሪሪሪ ስልባት እሷ ከእኔ ባሰች። በጭንቅላቷ ንቅናቄ እሺ አለችኝ። ከነመድሃኒቶቿ ይዣት ወደ ቤት ተመለስኩ።

ለቀናት ከእሷ ውጪ ስለምንም ነገር ማሰብ አልፈለግኩም። ህመሟ እየፀናባት ስለሆነ ብዙም አትንቀሳቀስም። ምግብ ለመብላትም ታስቸግራለች። ምንም አልጠይቃትም። እሷም ከአባቴ ሞት በፊት ስለነበረን ውብ የልጅነቴ ጊዚያት አንዳንድ ነገር ከማውራት የዘለለ አለመጠየቄ የተመቻት ይመስላል። አብሬያት እተኛለሁ። እሷን ከማጣጣም ውጪ ሌሎች ጥያቄዎቼን እና እውነታዎችን ሆነ ብዬ ችላ አልኩ። እሷ ስለኪዳን እኔ ከነገርኳት ውጪ የምታውቀው መረጃ የለም። እሷ እንደምትለኝ እንደዛ የምወደው እህቱ ከነበርኩ እንዴት ይሄን ሁሉ ጊዜ አይፈልገኝም? የሚለው ሀሳብ በመሃል ይጠልፈኛል። የጎንጥን ሽጉጥ መታጠቅም ልቤ አልረሳውም። አሁን ግን ከእናቴ ውጪ ምንም ነገር ላይ መጠመድ ስላልፈለግኩ ችላ አልኩኝ። ከቀናት በኋላ እናቴ ስትፈራ ስትቸር ቆይታ

«ከሀገሬ ከወጣሁ በኋላ ድጋሚ አልተመለስኩም። ከመሞቴ በፊት ቀዬዬን ብረግጠው ፣ ቤተኞቼን በአይኔ ባያቸው፣ ያ ከርታታ ወንድሜ ምን ላይ እንዳለ ባውቅ፣ ኸረ እንደው ሞቴም እዛ ቢሆን አይከፋኝ። እዛው በአፈሬ ብቀበር። » አለችኝ እንደ እሩቅ ምኞት

ምን ሊፈጠር እንደሚችል ሂሳብ አልሰራሁም። የመጀመሪያው ሀሳቤ የእናቴን ምኞት መሙላት ነው። የሆነኛው ልቤ ውስጥ ግን ናፍቆት አለው። ያ የሳር እርጥበት፣ ያ ቤቴ የሚመስለኝ አረንጓዴ አውድማ …… ልጅነቴ ….. ያደግኩበት መንደር ….. የማላውቀው ግን የማልቆጣጠረው ናፍቆት …….

እናቴ ተቀምጣ ብዙ መጓዝ ስለማትችል የሚመቻት መኪና ተከራየን እና ጎንጥ እየነዳ ከአዲስ አበባ ርቀን ወጣን። ሰው የሚፈልገውን ነገር እንዴት ይፈራዋል? እዛ አውድማ ላይ ስቆም ትውስታዬ እየተግተለተለ የሚመጣ እየመሰለኝ ፍርሃት ያንቀኛል። አውድማው ላይ ስቆም እንዳሰብኩት ትውስታዬ አልመጣም። አውድማው እንደፎቶው አረንጓዴ አይደለም። እናቴ እና ወንድሟ ሲገናኙ የተሰበሰበውን ሰፈርተኛ በእንባ ያራጨ ትእይንት ሆነ። በየቤቱ እየተዞረ የተነገራቸው ይመስል ግልብጥ ብሎ ለመጣው ሰፈርተኛ ሁሉ ጭንቅላቴ ስለማያስታውስ አላውቃችሁም ብሎ ማስረዳት አድካሚ ስለነበር እያቀፉ የሳሙኝን ሁሉ በፈገግታ እያቀፍኩ ስስም ቆየሁ። እናቴ ቀስ በቀስ የትኛው የስጋ ዘመዴ የትኛው ጎረቤት መሆኑን አስረዳችኝ።

መንደሩን ለቅቄ ወንድሜን ይዤ የወጣሁት በ19 ዓመቴ እንደነበር አወቅኩ። የቤቱ ግርግር ሲሰክን እናቴም ድካሟ ጠንቶ ስትተኛ ከቤት ወጥቼ እግሬ ወደመራኝ ዘወር ዘወር ማለት ጀመርኩ። ጎንጥ እየተከተለኝ እንደሆነ ሳውቅ ቆሜ ጠበቅኩትና እኩል መሄድ ጀመርን። የሆነች ትንሽዬ ቤተክርስቲያን አልፈን፣ እጅብ ያሉ ቤቶች ካሉበት አለፍ ብለን የሆነ የፈረሰ ቤትጋ ስደርስ ቆምኩ። ለዘመናት ማንም እንዳልኖረበት የሚያስታውቅ፣ አረም እና ሀረግ የበቀለበት ግድግዳ ፣ የወለቀ በር፣

ደረቴን ደቅቶ ያስቆመኝ የሆነ ነገር ያለ ይመስል ቆምኩ። ጎንጥ ደንግጦ ያዝ አደረገኝ እና «ምነው?» አለኝ። አፌ ቃል አላወጣም። እግሬ የዛለ ስሜት ስለተሰማኝ ዘጭ አልኩ መሬቱ ላይ በቂጤ።

«ይሄ ቤታችን ነበር። አባቴ እዛጋ ነው የሞተው።» አልኩት በጣቴ እየጠቆምኩት።

              አልጨረስንም

@wegoch
@wegoch
@paappii
#የመኖር አካፋይ ፣ የመ ፤ ሞ ፣ ት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል አስራ ሁለት)
(ሜሪ ፈለቀ)


ከተቀመጥኩበት ሳልነሳ ለደቂቃዎች ቆየሁ። ምን ያህሉን እንዳስታወስኩ ባላውቅም ደጁን እያየሁት ምስሎቹ ጭንቅላቴ ውስጥ ቅርፅ እየሰሩ ተደረደሩ። ከቤት ተንደርድሬ ስወጣ በዛ ያሉ መሳሪያ የታጠቁ ወንዶች በድል አድራጊነት እየተወጣጠሩ ጊቢያችንን አልፈው እየወጡ፣ የመጨረሻው ሰውዬ አባቴ በወደቀበት ተራምዶት ሲያልፍ ፣ ዘልዬ አጠገቡ ስደርስ የቱጋ እንደተመታ እንኳን እንዳይለይ ሆኖ ልብሱ በደም ርሶ በእጁ የያዛትን የሲጋራ መለኮሻ መጨበጥ አቅቶት እጁ ሲዝል፣ እሪሪሪ ብዬ ስጮህ  እንኳን መንደርተኛው ባለመሳሪያዎቹን ፈርቶ ስለተሸሸገ ብቅ ያለልኝ ጠፍቶ ባለመሳሪያዎቹ ተመልሰው ቢደፉኝ እንኳን ግድ ሳይለኝ ድምፄ እስኪዛጋ ስጮህ እና ስሳደብ ……… የጎረቤታችን ቤት በእሳት ተያይዞ እየነደደ የእነርሱ ጩኸት ከእኔ ቢብስም ሊረዳቸው ብቅ ያለ አልነበረም። እናቴ እግሯንም ቅስሟንም እየጎተተች ከቤት ውስጥ ብቅ ስትል አባቴ ነፍሱ ወጥታ ነበር። አላለቀሰችኝም። አጠገቡ መሬቱ ላይ ቁጭ ብላ በደም የራሰ ደረቱ ላይ ተኛች። ጩኸቴን አቁሜ አየኋት። አታወራም ፣ አታለቅስም፣ ምንም ስሜት አይታይባትም። ከአባቴ ፊት ይልቅ የሞተ የሚመስለው የእርሷ ፊት ነበር። ብርግግ ብዬ ተነስቼ ወደ ቤት ውስጥ ሮጥኩ።

በቃ እዚህ ድረስ ብቻ ነበር ለጊዜው የታየኝ። ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ሀረግ ወደወረረው ቤት ውስጥ ገባሁ። ደጁ ላይ የበቀሉት አረሞች እሾህ ያላቸው ስለነበሩበት ልብሴን እየያዘኝ ነበር ያለፍኩት። ጎንጥ አንዴ ፊት ፊቴን አንዴ መንገድ መንገዱን እያየ በዝምታ ይከተለኛል። ቤቱ ውስጥ ሳሎን አሮጌ አግዳሚ ወንበር እና የተበታተኑ ቆሻሻዎች አሉ። እንደገመትኩት አንዳንዱ ሰፈርተኛ ቆሻሻውን እያመጣ እዚህ ይጥላል። በቆሻሻ እና በዓይነምድር የሞሉትን ክፍሎች እየዞርኩ ግማቱ እንኳን አልታወቀኝም። ያ ቤት ያደግኩበት ልጅነቴ መሆን አለበት። ነገር ግን አንድም ከልጅነቴ ጋር የተያያዘ ትውስታ አልመጣልኝም። የዛን ቀን የሆነው ግን አንድ በአንድ የአሁን ያህል ሰውነቴን እስኪወረኝ ታወሰኝ። ጭንቅላቴ የፈለገውን መርጦ አንዲት ክስተት ብቻ አስታውሶ ነው ወይስ ቦታው ላይ ስገኝ ሌሎቹንም ትውስታዎቼን አገኛቸዋለሁ? አልገባኝም! ከሆነም ለምን ልጅነቴን አላስታወስኩም?

ዶክተር እንዳለኝ አስፈሪ ገጠመኞቼን ከደበቀበት እያወጣ ሊሆን ይችላል ……. ጭንቅላቴ ራሱ ክፋቱ እንጂ ወይ ሙሉውን ባያስታውሰኝ አልያም እናቴ አውርታ የማትጠግበውን ደጉንም ልጅነቴን ቢያስታውሰኝ ምን ነበረበት?

የዛን ቀን ከሆነው ውስጥ ያላስታወስኩት ይኑር አይኑር የማረጋግጥበት ምንም ማመሳከሪያ የለኝም። ያስታወስኳቸው ምስሎች ግን የጎደለ የሚመስል ትዕይንት የላቸውም።

አባቴ እና እናቴ ሲጨቃጨቁ ሌላኛው ክፍል ከኪዳን ጋር ሆነን እንሰማቸዋለን። እናቴ አባቴ ላይ ትጮሃለች።

«እኔ የምልህን አንዴ ሰምተኸኝ ቢሆን ይሄ ሁሉ አይመጣም!! ያንተ ፉከራ ዛሬ ከምን እንደሚያድንህ እናያለን! እሺ ልጆቼን ምኔ ውስጥ ልደብቃቸው? ሄዳችሁ ባትተነኩሷቸው ዛሬ አሳቻ ሰዓት ጠብቀው መንደራችንን ባልወረሯት ፤ እሺ አሁን ምንድነው የምሆነው?» በበሩ አጮልቄ አያቸዋለሁ። እሷ ወገቧን ይዛ እየተንጎራደደች ነው። እሱ ትልቅዬ መሳሪያ ወደበሩ አነጣጥሮ መንደራችንን ወረሯት የተባሉትን ሰዎች በሩን አልፈው ቢገቡ ሊቀልባቸው ይመስል ይጠብቃል። እናቴ አታቆምም።

«እናንተ የእነሱን መንደር ሄዳችሁ አቃጥላችሁ <ጉሮ ወሸባዬ> እያላችሁ ስትመለሱ እጃቸውን አጣጥፈው የሚቀመጡ ነበር የመሰላችሁ?»

«አንቺ ብዙ የማይገባሽ ነገር አለ አስካል! የአያት የቅድመአያቴን መሬት ካልፈነጨሁበት ሲሉ እኔስ ኑና በላዬ ዘብጡ ብዬ ዘንባባ አንጥፌ እንድቀበላቸው ነው ምኞትሽ?» እየጮኸ ነው እሱም የሚመልስላት። ከውጪ የብዙ ወንዶች ዘፈን ይሁን ፉከራ ያልለየለት ድምፅ እየቀረበ እየቀረበ ይሰማል። በመሃል የሚያወሩት በትክክል ባይሰማም ጮክ ያሉ ድምፆች ትእዛዝ ሲያስተላልፉ ይሰማል። ደግሞ ያጨበጭባሉ። ደግሞ አንዴ ሆ ብለው የደስታ ጩኸት ይጮሃሉ። እናቴ እሮጣ መጥታ ከሽቦ አልጋው ስር እንድንገባ ታደርገናለች።

«ምንም ቢፈጠር እንዳትወጡ! ምንም ብትፈሩ ድምፅ እንዳታሰሙ!» እያለችን መሬቱ ላይ በደረቷ ተደፍታ እያየችን እጇ ይንቀጠቀጣል። ኪዳን ማልቀስ ጀምሯል። ጆሮዎቹን በእጄ ደፍኜ ይዤለት እሹሩሩ እንደማለት እየወዘወዝኩት ወደራሴ አጣብቄ ያዝኩት። ከውጪ የሚሰማው ሁከት መስኮታችን ጋር ደረሰ። እናቴ የመላእክትን ሁሉ ስም በሹክሹክታ እየጠራች ትፀልያለች። አባቴ እኛ ወዳለንበት ብቅ ብሎ

«አንቺም ከእነርሱ ጋር ተሸሸጊ! እነርሱ የሚፈልጉት እኔን ነው!» አላት በትእዛዝ

«ያንተ ሚስትኮ ነኝ አይምሩኝም! እኔን ሲፈልጉ ልጆቼን ካገኟቸው ይገድሉብኛል። እኔን ካገኙኝ ግን ልጆቼን አይፈልጓቸውም በፍፁም አልሸሸግም! የመጣ ይምጣ!» አለች እንጂ ሰውነቷ እየራደ ነው። ላቤ ከጀርባዬ ወደቂጤ ሲወርድ ይሰማኛል። የልቤ ትርታ ሁከተኞቹ ድረስ የሚሰማ ነው የሚመስለው። ብዙም አልቆየም! ድብልቅልቅ ያለ ጩኸት ፣ የበሩ መገንጠል፣ ተኩስ ድብልቅልቁ ወጣ። ሽንቴን እላዬ ላይ ለቅቄ እንዲያ ሰውነቴ የእኔ እስከማይመስለኝ በድኖብኝ ኪዳንን አልለቀቅኩትም። ድንጋጤው በዝቶበት ነው መሰለኝ ትንፋሽ እንደሌለው ሰው ዝም አለ። እናቴ ከአልጋው አጠገብ ተነስታለች ግን አትታየኝም። ፍርሃቴ ሽባ ስላደረገኝ የመነቃነቅም ድፍረቱ አልነበረኝም። ሳሎኑ ውስጥ የተፈጠረው ምን እንደሆነ ባላውቅም ድብልቅልቁ የወጣ ትዕይንት እንደሆነ ከድምፆቹ ያስታውቃል። ከሳሎን ድምፁ እየቀለለ የተወሰኑ ሰዎች ድምፅ ብቻ መሰማት ሲጀምር የእናቴ እሪታ ተከተለ። ነፍስ ከስጋዬ የተላቀቀች መሰለኝ። የሞት ሞቴን ለማየት ስሞክር መኝታ ቤቱ ውስጥ ማንም የለም።

«ሚስትና መሬቴን አለ ይሄ እንከፍ?» የሚል ድምፅ ለመኝታ ቤቱ ቀርቦ ተሰማኝ። ቁጥራቸውን መገመት የሚቸግረኝ ሌሎች ሳቅ ተከተለ። እናቴ ትለምናቸዋለች። የምትለምንበት ድምፅ ሆዴን ረበሸው። መሸነፍ፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ረዳት ማጣት…….. ሆድ የሚደበላልቅ ልመና ነው። የእናቴ ልመና ፍርሃቴን አስዋጠኝ። ምን ሊፈጠር እንደሚችል የማስብበት የብስለት ልክም አልነበረኝም ይሆናል። ኪዳንን ከአልጋው ስር ወደየትም ንቅንቅ እንዳይል አስጠንቅቄው በቀስታ እየተንፏቀቅኩ ገርበብ ያለው የመኝታ ቤት በርጋ ደረስኩ። እግሬ የቆመበት ተተክሎ ቀረ። ልሳኔም የተቆለፈ መሰለኝ። ከእናቴ ጋር ተያየን። መሬቱ ላይ በጀርባዋ ወድቃ የለበሰችው ሻማ ቀሚስ እስከደረቷ ተገልቦ አንደኛው ካኪ የለበሰ ሰውዬ በማሸነፍ ስሜት ቀበቶው ተፈትቶ ወደታች ዝቅ ባለ ሱሪው ቂጡ እየታየ እላይዋ ላይ ይፈነጫል። ሌላኛው ደግሞ የመሳሪያውን አፍ ወደ እርሷ አዙሮ ነውር እያየ ሳይሆን ትክክል ነገር ዓይኑ ስር እየሆነ ይመስል እየገለፈጠ ያያቸዋል። ፊታቸው ከእኔ በተቃራኒ አቅጣጫ ስለሆነ አያዩኝም። ሌላ ማንም የለም ሳሎኑ ውስጥ። አባቴ የት ሄዶ ነው እሷ የሚደርስላት አጥታ የተዋረደችው? አትታገልም! አትንቀሳቀስም! አፉ ብቻ ነበር የሚለምነው። እኔን ስታይ እሱንም ተወችው። በሚያሳዝን አስተያየት አየችኝ። ልመና ያለበት አስተያየት። እንዳያት አልፈለገችም! ልመናዋ ዞር እንድልላት ነው።  ይሄኔ ኪዳን ከየት መጣ ሳልለው አጠገቤ ደረሰ። እየሆነ ያለውን እንዳያይ አይኑን ከደንኩት። ይሄኔ ሌላ አንድ ሰው ከውጪ ገባ። ቀና ቢል ስለሚያየኝ ኪዳንን ይዤ በበሩ ተከልዬ ማጮለቅ ቀጠልኩ። ሰውየው ሲገባ
እናቴ ያቆመችውን ልመና በለቅሶ ታጅባ ቀጠለች። የሰማት አይመስልም። ቢሰማትም ግድ አልሰጠውም። ይልቅ እንደመቆጣት እያለ

« ስንት ነገር እያለብን አንተ እዚህ ወገብህን ታላቅቃለህ? ተነስ ወደዚያ!» ብሎ አምባረቀ። አለቃቸው ነገር ይመስላል።

መሳሪያውን ይዞ የቆመው ሰውዬ «መሬቱን ወስደንበታል። ሚስቱንም እንቅመስለት ብለንኮ ነው!» ብሎ አስቀያሚ ሳቅ እየሳቀ ከእናቴ ላይ መነሳት ሲጀምር ሰውየውን በልቤ አመስግኜ ሳልጨርስ እሱም የአጋንንት ሳቅ የመሰለ ቃጭል ማስካካት አስካክቶ
«እንዲያ ነው …..» ብሎ ሱሪውን መፍታት ሲጀምር ከእኔ የሚበልጥ እልህ እና መጠቃት ሰውነቴ ውስጥ ነደደ። ወዲያው ከውጪ የሆነ ሰው ተጣራ

«ሙሉሰው? ሙሉሰው?» ይሄኔ ሊፈታ የጀመረውን ሱሪ ወደቦታው እየመለሰ በተሸከመው መሳሪያ እነርሱም እንዲወጡ ምልክት አሳይቷቸው ወጣ። መሳሪያ ይዞ በመቆም ሲያጅብ የነበረው ሰውዬ ወዲያው ተከተለው። እናቴ ላይ ሆኖ ሲያሰቃያት የነበረው ግን ቆሞ አዘቅዝቆ እያያት በፀያፍ ንግግር ይዘልፋት ጀመር። እያየኋት እንደሆነ አውቃለች። ፊቷን ወደበሩ አዙራ በስቃይ ታያለች። ከየት በመጣ ጉልበቴ እንደሆነ አላውቅም ኪዳንን ሽክም አድርጌ አልጋው ላይ ወሰድኩት እና በጩኸት እኔ እስክመለስ ንቅንቅ እንዳይል አስጠነቀቅኩት። እየተንሰቀሰቀ በጭንቅላቱ እሺ አለኝ። አልጋው አጠገብ የተቀመጠውን ሳጥን ከፍቼ ከሳጥን ውስጥ አነስ ያለች ቦርሳ አነሳሁ። ጠባብ ዚፕ ኪሱ ውስጥ ያለ ቁልፍ ወስጄ አልጋው እራስጌጋ ያለውን መሳቢያ ከፈትኩ። ከፍቼው ውስጡ ያለውን ሽጉጥ ሳየው ተርበተበትኩ። በሚንቀጠቀጥ እጄ ወጥተው ተበትነው የተቀመጡ ቀለሃዎቹን ሰካክቼ ወደሳሎን ሄድኩ። አንስቼ ሊወጣ የነበረው ሰውዬ ላይ ቀስሬ ስጠጋ እናቴ ከመሬት ብድግ አለች። አልተኮስኩም። ልተኩስ የነበረ ይመስለኛል ግን እጄ እየተንቀጠቀ ያቃተኝ። ሰውየው መርበትበቴን እና ህፃንነቴን አይቶ መሰለኝ ምንም ሳይመስለው በንቀት ወደእኔ ሲመጣ እናቴ ከለለችኝ። ግንድ በሚያክል እጁ ሲገፈትራት ተንገዳግዳ ወደቀች። እጄ መንቀጥቀጡን አቁሞልኝ ልስብ ስል የወደቀችው እናቴ ከየት እንዳገኘችው ያላየሁትን የቡና ዘነዘና አንስታ ጭንቅላቱን ከኋላ መታችው። ሰውየው ተገንድሶ ደሙ እየተንዠቀዠቀ እሱን ዘወር ብላ ሳታይ ዘላ የያዝኩትን ሽጉጥ እየቀማችኝ።

«ለእድሜ ልክ የሚበቃሽን ክፋት አይተሻል። ደግሞ ነፍስ አጥፍተሽ ስትቃዢ ልትኖሪ?» ያለችው ለእራሷ እንጂ ለእኔ አይመስልም። የተቀበለችኝን ሽጉጥ ይዛ የተገነደሰው ሰውዬ አጠገብ ዘፍ አለች። ደንዝዛ በድኗ እየተንቀሳቀሰ ነው የሚመስለው። ሰውየው ደሙ መስመር እየሰራ ወደበሩ ይፈሳል። አይንቀሳቀስም። እሮጬ ወደ ውጪ የወጣሁት አባቴን ፍለጋ መሰለኝ። መሬቱ ላይ ተዘርሮ ያገኘሁት።

እናቴን የአባቴ ሬሳ ላይ ትቻት የፈረጠጥኩት <እንዳትንቀሳቀስ> ያልኩት ኪዳን ፈርቶ ወደሳሎን ቢመጣ የወደቀውን ሰውዬ አይቶ ይደነግጣል ብዬ ነው። ካስቀመጥኩት ቦታ አልተነሳም። የሄድኩት እሱን ልጠብቀው ነበር። አልጋው ላይ አስጨንቄ አቅፌው ስወዘወዝ ምን ያህል ደቂቃዎች እንዳለፉ አላውቅም። ብቻ ወተት እንደሚንጥ ሰው ከፊት ወደኋላ ስናጥ የእናቴ ወንድም እያለቀሰ ገብቶ ኪዳንን ከጀርባ እኔን ከፊት አፋፍሶ ተሸክሞን ወጣ  ……… እዚህ ድረስ ያለው ምስል ምንም ብዥ ሳይል ነው ያስታወስኩት የሚቀጥለው ግን ብዥታ አለው አጎቴ እንደተሸከመን «ወየው ወንድሜን!» እያለ ድምፅ አውጥቶ እያለቀሰ የሆነ መንገድ የሄድን ይመስለኛል። ላስታውሰው ስሞክር ይጠፋብኛል።

እዛው የመኝታ ቤት ውስጥ ቆሻሻ ተሞልቶ የተቀመጠ ማዳበሪያ ላይ ጭብጥ ብዬ ተቀምጫለሁ።

«እያስጨነቅሽኝ እኮ ነው። ምንድነው ያስታወስሽው? ሰውነትሽኮ ያንቺ አይደለም!» ይለኛል ጎንጥ። ከደቂቃዎች በኋላ እሩጫ እና እርምጃ እየደባለቅኩ እናቴጋ ደረስኩ እና ተጠመጠምኩባት። ገባት! እሪሪሪ ብላ ማልቀስ ጀመረች። ስላስታወስኩ  «ምንአልኩህ አምላኬ? ለልጄ አዲስ ህይወት ሰጠህልኝ ብዬ አመስግኜ ሳልጨርስ?» እያለች አምላኳን መውቀስ ጀመረች። የሚሰማኝን ስሜት መለየት ከበደኝ። ከነበሩኝ ጥሩ ቀኖች ተለይቶ አስፈሪ ቅዠት የመሰለ የህይወቴን ክስተት ማስታወስ ሊያሳብደኝ አልነበር የሚገባው? ቁጣ፤ ንዴት፣ ጥላቻ ፣ ፍርሃት ፣ ሀዘን ……. አልነበር ሊሰማኝ የሚገባው? የሚሰማኝ የሆነ ቅዝቅዝ ያለ ፀጥተኛ ስሜት ነው።

«ከእናቶች ሁሉ በላይ እናት ነሽ!!» አልኳት እናቴን እንዳቀፍኳት ብዙ ከቆየሁ በኋላ። አመሻሽ ለእራት ስንሰበሰብ ማስታወስ የቻልኩት ያቺን ቀን ብቻ እንደሆነ ነገርኳቸው። የነገርኳቸው የሆነ አስደንጋጭ ነገር ይመስል ገበታውን የከበበው ሁሉ ረጭ አለ። አጎቴ ሊጎርስ የጠቀለለውን እንጀራ የመወርወር ያህል ትሪው ላይ ጣለው።

«መቼም ከዚህ የባሰ የስቃይ ቀን አለ አትሉኝማ? ምንድነው?» ብዬ ስጮህ

«እንደዛ አይደለም። ለሁላችንም ከባድ የጨለማ ቀን እሱ ነበር። እንደው …… » እያለ ፊደሎቹን አፉ ውስጥ ያውደለድላቸዋል። ከብዙ ንትርክ በኋላ የተፈጠረውን ነገሩኝ።

እንደዚያ ደም ያቃባቸው ፀብ ለዘመናት የከረመ የጎሳ ፀብ ነበር። ለዘመናት ያንተ ጎሳ ገላመጠኝ ፣ ያንተ ጎሳ ድንበሬን አልፎ ሽንቱን ሸና ዓይነት ገለባ ሰበብ እየመዘዙ ሲጣሉ ነበር የኖሩት። የአባቴ ዘመን ከፀቡ ሁሉ የከፋው ነበር። ፀቡ ፖለቲካዊ ይዘት እንዲኖረው ተደረገ። የእነዛ ወገን በቁጥር የምንበልጠው እኛ ብንሆንም ሰፊ ለም መሬት የያዙት እነዛ (የአባቴ ወገኖች) በመሆናቸው የመሬት ይገባኛል ነጠላ ጥያቄ ይዞ ነበር የተነሳው። ሲቀጥል ገበያውን የኛ ሰዎች ይቆጣጠሩት ፣ ሲቀጣጠል በማእከላዊ ደረጃ በአብላጫው ስልጣን ላይ ያሉት  የአባቴ ወገኖች መሆናቸው ሌላ ዘመናዊ የመሰለ የፀብ ድፍድፍ ጋገረ። ፀቡ በከረረ ቁጥር ከላይ ወታደር ይመጣል። ለቀናት ጋብ ይላል። ደግሞ ተመልሶ ይጋጋላል። አባቴ ነው አሉ የእኛን ጎሳ የሚመራው። አጓጉል ጉልበት መለካካት። የእኔ እበልጣለሁ ፉክክሩ ጦዞ ከተማ እስከማቃጠል ዘለቀ። የመጨረሻው ፀባቸው አባቴ ህይወቱን የገበረበት ነው። ራሴን እስክፈራው ድረስ ሰውነቴ ውስጥ የሞቀ ደም እንዲሮጥ ያደረገው መጨረሻው ነው። የእነዛ ጎሳዎች ሽማግሌ ላኩ። ከዚህም ወገን ሽማግሌ ተቀመጠ። ታረቁ!!

የተበደልኩ ዓይነት ስሜት ተሰማኝ። እነርሱ ተጣሉ ከዛ ታረቁ። እኔስ በአስራ ሶስት ዓመቴ አባቴ ሲሞት እናቴ ስትደፈር ያየሁት እኔስ? እኔን ይቅርታ ጠይቀውኛል? እናቴስ? በአንድ ቀን ባሏንም ክብሯንም ያጣችው እናቴስ? ስትደፈር ያየቻትን ልጇን ዓይን እያዩ መኖር ስቃይ ሆኖባት መኖሪያዋን ጥላ የጠፋችው እናቴስ? በቃ! እነሱ እንደቀልድ ታረቁ? ማንም ላጠፋው ቅጣቱን ሳይቀበል ታረቁ! በሰላም ኖሩ! ተጋቡ! ተዋለዱ! የሚባለው የሰው ነፍስ እንዴት ሲናቅ ነው? እኔ እና የዛን ቀን የህይወት ሚዛናችንን የሳትን እኩዮቼስ? ንዴቴ ይንቀለቀል ጀመር። ከነቃሁ ጀምሮ ይሄን ስሜት አላውቀውም! እናቴ ትለምነኝ ጀመር። አጎቴ የፈራው ነገር የደረሰ ዓይነት ተሳቆ ሲያየኝ ቆይቶ ያኔም ልክ እነሱ ታረቁ ተብሎ በሰላም መኖር ሲጀምሩ እንዲህ መሆኔን እና ከዛ በኋላ ህፃንዋ ሜላት ድራሽዋ ጠፍቶ አስፈሪዋ ሜላት ማደግ መጀመሯን ነገረኝ።

          ………………. አልጨረስንም ………..

@wegoch
@wegoch
@paappii
" አንዳንድ ሰው የኔ ብለን ተንከባክበን ምቾት ስንፈጥርለት በምቾት ሰበብ ሌላ ተድላ ለማግኘት ወደ ሌላ ሚያማትር የፍቅር ወንፊት ይሆናል ። "

( ካሊድ አቅሉ )


አስሬ ሰአቴን አያለው በየፌርማታው የሚቆመው ታክሲ ከኔ አርፍዶ መውጣት ጋር ተደምሮ የንዴት ቃሎችን በየሰከንዱ ለራሴ አሰማለው ።  ሳርቤት ጋር አንዲት ቀጠን ያለች ልጅ ወራጅ አለችና ለመውረድ ወደ በሩ ተጠጋች ። መኪናው ቦታ ለመያዝ ፍጥነቱን ሲቀንስ  ጥንዶቹ ለመግባት ወደ በሩ ተጠጉ ።

ልጅትዋ በፍጥነት ወርዳ እረዳቱ   "ሜክሲኮ ናቹ " አለ በስስት የሚተያዩትን ፍቅረኛሞች በጎላ ድምፅ ጠየቀ ። ተጠምጥሞ አንገትዋን ከሳማት ብሃላ "ቤት ስትገቢ ደውይልኝ " ብሎ አፈገፈገ በአካልዋ እሺታዋን ገልፃ ከሃላ መቀመጫ አራተኛ ሆና ተቀላቀለችን ።


ታክሲው ከቅድሙ በተሻለ ፍጥነት ይሄዳል እፎይታ ተሰምቶኝ መድረሴን እያሰብኩ ስንጓዝ አጠገቤ የወንድና የሴት ምልልስ ጆሮዬ ገባ ። 

" ይሄን የሚያህል ፀጉር ለብቻ መያዝ አያስቀጣም ?" ይላል አሁን የተሳፈረችዋን ጉብል

"ሃሃሃ ምን አረግሽ ተብዬ ፈጣሪ አይደል እንዴ የሰጠኝ " አለች አሁን በፍቅረኛዋ የተሸኘችው ወጣት ።

" ወጪውስ እራሱ መከራ እኮ ነው በየሳምንቱ እሱን መሰራት " አለ በተቀደደው ቦይ መፍሰስ የፈለገው ቀጠን እረዘም ያለው ጀንጃኝ

" የምር አስቤው አላውቅም ግን እንዳልከው ከባድ ነው "  አለች የልጁ አቀራረብ እንደመሰጣት በሚያሳይ የሰውነት ንግግር  ።

ፊቴን ወደ መስኮቱ ባዞርም ሁለመናዬ በጆሮዬ መሪነት ከነሱ ዘንድ ነው ። ፊቴን ትንሽ መለስ አድርጌ ልጅትዋን ገረፍ አረኳት ባይኔ ፁጉርዋ ትከሻዬ ላይ ተዘርርዋል ።  " አንተስ አውራት እንጂ ምን ትጠብቃለህ😊 "  ሚለኝ መሰለኝ . . .

መኪናው ዳገቱን ተያይዞታል እነሱም የጋለ ወሬ ላይ ናቸው ። አይ ምስኪኑ  አፍቃሪ የሚወዳትን ልጅ ሸኝቶ መመለሱ ነው ልብዋ አብሮ እንደተጓዘ አውቆ በሆነ አልኩኝ በልቤ ሜክሲኮ መውረጃችንን ጥግ ለመያዝ መኪናው ቦታ ሲፈልግ ስልኩን ወጣ አረገና ሳቅ እያለ
" እስኪ ቁጥርሽን ንገሪኝ ልያዘው"  አለ እንደማይከለከል በተማመነ ቅላፄ

" እእ ይሻላል እሺ 091672 . . .   "
መጨረሻው ነው ብሎ እረዳቱ በሩን ከፈተው ተስፈንጥሬ ወጥቼ ጉዞዬን ቀጠልኩኝ .     .     .    .

" አንዳንድ ሰው የኔ ብለን ተንከባክበን ምቾት ስንፈጥርለት በምቾት ሰበብ ሌላ ተድላ ለማግኘት ወደ ሌላ ሚያማትር የፍቅር ወንፊት ይሆናል ። "

ስልኬን ወጣ አድርጌ ደወልኩና " ማኪ ደርሻለው ይሄው  "  አልኳት እርምጃዬን ጨምሬ ።

ይሄኔ ማኪም ታክሲ ውስጥ ለአንዱ ምላሳም ቁጥርዋን ሰታ መታ ይሆናል እኮ አልኩኝ ፈገግታ ባለው ከራሴ ጋር ምልልስ።

@kalidakelu

@wegoch
@wegoch
@paappii
#የመኖር አካፋይ ፣ የመ ፤ ሞ ፣ ት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል አስራ ሶስት)
(ሜሪ ፈለቀ)

«አባቴም እንደእነሱ መጥፎ ሰው የነበረ ቢሆንስ? የሆነችን ልጅ አባት የገደለ ቢሆንስ? የሆነኛው ሰው ሚስት ስትደፈር ቆሞ አይቶ ቢሆንስ? መቼም ከተማቸውን በእሳት ሊለኩስ  ሲሄድ <የእግዜር እንግዳ> ብለው አልተቀበሉትም! ተታኩሰዋል አይደል? በተኩሱ መሃል የገደላቸው ሰዎች እነሱም የሆነች ህፃን አባት ፣ የፀቡ ግብም አላማም ያልገባት የሆነች ምስኪን ሴት ባል ይሆናሉ።» አልኳት እናቴን ከቀናት ድንዝዝና እና ማሰላሰል በኋላ የሆነ ቀን። ከአሁን አሁን ትጎፈላለች ብሎ በዓነቁረኛ የሚከታተለኝ አጎቴ ዝግንን እያለው

«ውይ በስመአብ!!! እውነትም አባትሽን ዘንግተሽዋል። ምነው ልጄ? እሱ እንደው አንዳንዴ አጓጉል ጀብደኝነቱ ከልክ ያልፋል እንጂ እንዴት ያለ ለሰው አዛኝ እና ደግ ሰው መሰለሽ? አባትሽን መጥፎ ሰው? ኸረ ተይ መንደሬው እንዳይሰማሽ? የሀገሬው ሁሉ አጉራሽ አልባሽ ነበር።» አለኝ።

«ለወገኑ ነዋ! በመሰረቱ ሁለቱም ወገኖች ለየራሳቸው ወገን መከታ ለመሆን አይደል የሌላውን ወገን ሲያጠቁ የኖሩት። እነዛም ወገኖቻቸው የሚመሰክሩላቸው ደግ ሊሆኑ ይችሉ ይሆናልኮ!! ምናልባትም <ማ? የእኔ አባት? እንኳን በሰው በዝንብ ላይ እጁን አያነሳም> የሚሉላቸው ልጆች ይኖሯቸው ይሆናል። ሁሉም ሰው በራሱ እስካልደረሰ በስተቀር ምክንያታዊ እና ልክ ነው። በራሱ ሲደርስ ነው ሚዛናዊነቱን የሚያጣው። ለምሳሌ የእኛዎቹ ተደፈርን ብለው ሲያስቡ ከተማቸው ድረስ ሄደው አጥቅተው ሲመለሱ፣ የሰራነው ልክ አይደለም ብለው ለአንዴ እንኳን ተፀጽተዋል? ምናልባትም ልክ አይደላችሁም ያለ አዋቂ ይኖር ይሆን? እስቲ ለትውልድ የሚሻገር ቁርሾ ከማኖራችን በፊት ሳንጫረስ መፍትሄ እንፈልግ ያለ ይኖር ይሆን? እነዛ ተመሳሳዩን ሲያደርጉ ህመማችንን የምናየው ከእኛ ወገን ስለሆነ አውሬነታቸው እና እንስሳነታቸው ነው የታየን። » አልኩኝ። እናቴ ፈገግ አለች።

«ምነው?» አልኳት

«ኸረ ምንም አለች!» አሁንም ድካም በተጫነው ፊቷ ላይ ፈገግታ እየነገሰ።

«እንዴ አስካል እንዲህማ ፊት አትስጫት!! የአባቷንም ነፍስ መና ማድረግ ነው። ሰው ነውና ምኑንም ያህል ጥፋት ባይጠፋው፣ ህይወቱን ጭምር የገበረው ለዝህች መንደር ነው። ያ መረሳት የለበትም!!» አለ የእውነቱን እየተቆጣ!! ምናልባት ሰው የመሆን የአፈር ልውሳችን ውስጥ ያለ ነገር ይሆን? የእኛ ወገን ቢያጠፋም ( ወይም እናውቃለን አጥፍቷል) ቢሆንም የእኛ ወገን ስለሆነ ጥፋቱ እናኮስስለታለን። ከዛሳ? ከዛማ የእሱን ሀጢያት ደርምሰን የኛ ወገን ላልሆነ እንደርባለን። ከዛማ በንፅፅሮሽ የኛ ወገን ለመልዓክ የቀረበ ፃድቅ አድርገን እናርፈዋለን!! አጎቴ ሰሞኑን ከሚነግረኝ የመንደራችን ታሪክ በብዙ የተረዳሁት ያንን ነው።

«አዛኝቷን ነው የምልሽ እንዲህ ተልፈስፍሰሽስ ከማይ ከነማስጨነቅሽ የድሮዋ ሜላት ትምጣብኝ!!» ሲለኝ እናቴ በተሟጠጠ አቅሟ ልትነሳ ሁላ ቃጣት። «እረፍ ብያለሁ!» ብላ ጮኸች ፣ አጎቴ አፍንጫውን እየነፋ ወጣ!

ማለቂያ የሌለው የጥያቄ ጎርፍ ሳንፎለፉልለት ቆይቼ አጎቴ ከነገረኝ ገጣጥሜ የገባኝ እድገቴ እንዲህ ነው። ከዛን የመዓት ቀን በኋላ እናቴ የሆነችውን ለወንድሟ ነግራው አባቴ እንኳን ሳይቀበር እኛን ትታ ተሰደደች። አጎቴ ልጅም ሚስትም ያልነበረው ላጤ ስለነበር ምድር ዞሮበት እንደነበር ነገረኝ። አባቴንና በዛን ቀን በሞት ያጣናቸውን ወገኖቻችንን ቀብረን መንደሬው ማቁን እንደለበሰ ከረመ። ከዛን ቀን በኋላ ቀሚስ ጠላሁ። ስለብሳቸው ቀሚስ የሚያካክሉትን የአባቴን አላባሾች መልበስ ጀመርኩ። ቁጭ ብዬ የአባቴን ሱሪዎች ለእኔ እንዲሆኑ ቆርጬ እና ሰፍቼ መልበስ ጀመርኩ። አንድ እለት ለበዓል በጌጥ ያሸበረቀ ቀሚስ ገዝቶልኝ መጣ።

«እኔ ይሄን አልለብስም! ሴት መሆን አልፈልግም።» አልኩ። ምናልባት በሴትነት ውስጥ የእናቴን ስቃይ በወንድነት ውስጥ የአባቴን ጀግንነት ነድፌ ይሆናል እናቴን ከመሆን አባቴን ሆኜ ሞትን እንኳን ለመግጠም ራሴን መሞረድ የጀመርኩት። ሴት ሊያደርጉኝ የሚችሉ ድርጊቶችን ማጀትን ጀምሮ ሸሸሁ። አጎቴ ትምህርት ቤት ከኪዳን ጋር ቢልከንም ትምህርቴን አልቀጥልም ብዬ አሻፈረኝ አልኩ። ትኩረቴ ሁሉን ሁሉ ጉልበት እና ጡንቻ ማካበት ላይ አደረግኩ። ውሎዬ ከጎረምሳ ጋር ኳስ መራገጥ ፣ ጅራፍ ማጮህ ፣ እንደእኩዮቼ ወንዶች ጡንቻ መለካካት ፣ ከሰፈሩ ፈልፈላ ጋር ሜዳ ላይ ማን ስንት ፑሽ አፕ ይሰራል አፈሩን ስንልስ መዋል ፣ የሰፈሩን አህያና ውርንጭላ ሁላ መጋለብ ….. ሆነ። ይሄን ሲነግረኝ አጎቴ ፈገግ ብሎ

«በአዛኝቷ! እንደው ሞገደኛ ነበርሽኮ!! ቆሜ ካልሸናሁ ብለሽ ጉድ አፍልተሽ ነበርኮ!» ብሎ ክትክት ብሎ ሳቀ። ቆሞ እንደወንድ የመሽናት ሀሳቡ አብሬው እንድስቅ አደረገኝ።

በየቀኑ የምደባደበው ሰው ፈልጌ ተደባድቤ እገባለሁ። በምለብሰው የአባቴ ልብስ ሲስቁብኝ እጣላለሁ።  ሁሌም አሽተው አሰባብጠው ይለቁኛል በነገታው አሁንም ነገር ፈልጌ እወቀጣለሁ። በተለይ ትልቁ ገበያ ስንሄድ ከጠላቶቻችን ወገን የሆነ ሰው ከገጠመኝ ፍፃሜዬ ደማምቶ መምጣት ቢሆንም ነገር ከመፈለግ አልቦዝንም። በዱላ ብዛት የትኛውም ድብደባ ቅም የማይለኝ ደነዝ ሆንኩ። ቁጥር አልባ ቡጢ እና ሽመል ከፈጀሁ በኋላ አንድ ቀን አሸንፌ መጣሁ። ውጤቱ ማሸነፍ ሆነ እንጂ አፍንጫ እና ጉንጬ እስኪደባለቅ ተወግሬ ነበር።

«በጭራሽ አልገባኝም ነበር። <እንደው ከዚህ ሁሉ ምናለ ድብድቡ ቢቀር? መቼም አንድ ቀን አንዱ አጉል ቡጢ የሰነዘረብሽ እንደው 32 ጥርስሽን በእጅሽ ይዘሻት መምጣትሽ ነው። እንደው ምን ባደርግሽ ይሻለኛል?> ስልሽ <ተደባድቤ ጉልበቴን ካልፈተንኩ እንደምችላቸው በምን አውቃለሁ? ድንገት ብንገጣጠም ሽመል ወይ ኮረት ፍለጋ ልዟዟር ነው?> ብለሽ መለሽልኝ። ለካንስ አጅሪት አባትሽ ከሞተ ቀን ጀምሮ የአባትሽን ገዳዮች እንዴት እንደምትበቀዪ ስታሰዪ ነው ውሎ አዳርሽ።» አለ በሰዓቱ ስላልተረዳኝ እየከፋው።

ወንድ የመሆን ትጋቴን መቼም እንደማላቆም ሲያውቅ ፣ በራሴ ልጅነት ውስጥ መኖሬን አቁሜ በአባት እና በእናቴ በደል ውስጥ እየዋኘሁ እንደሆነ ሲረዳ ለምኜው እንቢ ብሎኝ የነበረውን የሆነ ከከተማ የመጣ ልጅ የእድር ቤቱ አዳርሽ ውስጥ የሚያስተምርበት ካራቴ ቤት በ15 ዓመቴ አስመዘገበኝ። እንደዛ ቀን የተደሰትኩበትን ቀን አይቶ እንደማያውቅ ነገረኝ። ኪዳንን ትምህርት ቤት አድርሼ የምመልሰው እኔ ነበርኩ። በኮባ የተሰራ ጠብመንጃ ትከሻዬ ላይ አንግቼ ፣ እንጨት ፈቅፍቄ የሰራሁትን የእንጨት ሽጉጥ ወገቤ ላይ ሽጬ …….. ከፍተኛ ጥበቃ እያደረግኩለት እንደሆነ አስመስላለሁ። ሰውነቴ እየፈረጠመ …..  ልቤም በማንአለብኝነት እያበጠ ….. <ፀብ ሆይ ወዴት ነህ?> ብዬ እያልኩ ማሸበር ስጀምር ….. የሰፈሩ ሰው ወንድ ልጆቻቸውን እንኳን <እሷ የሴት ተፈጥሮ አልፈጠረባትም። ወንዳወንድ ናት ከእርሷ ጋር እንዳትገጥሙ> እያሉ መከልከል ሲጀምሩ ……. የጠገበ ልቤን የሚወጥር ሙገሳ ጆሮዬ ገባ። ኪዳን ከልጆች ጋር ተጣልቶ ሲያለቅስ የሰፈር ማቴ ለእኔ ሊያሳብቅ ሲሮጥ አንድ አልፎ ሂያጅ
«አሁን አንተ የአባትህ ልጅ ነህ? ያ አባትህ ቢያይህ እንዴት ይክፉው? ወንድ አይደለህ እንዴ ምን ያነፋርቅሃል? ልጅማ ወልዷል የሴት ወንድ፣ የአባቷ ልጅስ እሷ ናት።» ያለውን ኪዳን ሲነግረኝ ጥጋቤ አናቴ ላይ ወጥቶ አጎቴን አሳር አሳየሁት። እየሰነባበተ የሆነ ቀን አንድ የኛ መንደር ልጅ እና የአባቴ ገዳዮች ወገን ልጅ ገበያ መሃል በተነሳ የግል ፀብ ሲያያዙ መሃል ጥልቅ ብዬ  <እጇ ላይ መሞቱ ነው> ብሎ ሰው ጠልቃ እስኪገባ ድረስ በጥላቻዬ ልክ ቀጠቀጥኩት። ከአጎቴ ውጪ ማንም የከፋው አልነበረም። ይባሱኑ መንደርተኛው «ቁርጥ አባቷን፣ የአባቷ ቢጤ አመፀኛ ፣ ይህቺማ የመንደሩ መድሃኒት ናት ፣ ቱ በሉ የአባቷን ደም ትመልሳለች። » እያለ ልክ እንዳደረግኩ ዓይነት በየቡናው እና ጠላ ቤቱ በወሬ ሲቀባበለኝ ባሰብኝ።

«እንደአባቴ ጫካ ካልገባሁ አልሽ!» ብሎ ሳቀ አሁንም ይሄን ሲያስታውስ «አንድ ቀን እርሻ ውዬ ስመለስ አጅሪት ለካ ያንቺ ቢጤ ወጠጤ ጎረምሶች ሰብስበሽ ሄደን ጠላቶቻችንን ካልገጠምን ብለሽ ልባቸውን ዝቅ አድርገሽ ልከሻቸው፣ ይሄ ውሻ ቢያሯሩጠው ሱሪው ላይ የሚንበጫበጭ ማቲ ሁላ <መሸፈቴ ስለሆነ ስንቅ አዘጋጁልኝ> ብሎ እናቱን ሲያውክ የሰፈሩ እናቶች ተሰብስበው ጠበቁኝ። <ይህችን ልጅ አደብ አስይዝልን! የልጆቻችንን ልብ ወደ ጫካ እያሸፈተች ነው።> ቢሉኝ እንደው ሳቄን መቆጣጠር ተሳነኝ ስልሽ! (አሁንም ከት ብሎ እየሳቀ) በሽመል ጦርነት ልትገጥሚ መሆኑ ነውኮ!!» እንባው እስኪወርድ ሳቀ። አጎቴ ሲያወራው ልጅነቴን ከመራራነቱ ይልቅ የተዋዛ ጨፍጋጋ ያደርገዋል። እያንዳንዷን ክስተት በቅደም ተከተል ሳይስት ሲያወራኝ ያኔ ተሰምቶኝ የነረውን ነገር ባላውቅም ዛሬ ላይ ግን ስሰማት ሜላት ምሬት ብቻ አልነበረችም።

17 ዓመት ሲሆነኝ ከአባቴ ሞት በኋላ ረጭ ብሎ የነበረው የሁለቱ ወገኖች ቁርሾ በሽመል የማይመከት የፀብ ጉርምርምታ ሆኖ ተጀመረ። ወጣቶቹ መሳሪያ ያለው በመሳሪያ የሌለው በጦር እና በጎራዴ እንዴት ጠላቶቻቸውን እንደሚመክቱ ሲመካከሩ አንደኛ የነገር ጠንሳሽ ሆኜ ተገኘው። ለካንስ ፀብ ፈጥሬ ቁምነገራቸውን ሳይቋጩ ስለምረብሻቸው ፈርተው ዝም አሉኝ እንጂ ከሴት ጋር በፀብ አውድማ መሰለፍን እንደውርደት ቆጥረውት ኖሮ ለአጎቴ መጥተው ነገሩት። ብመከር ብዘከር የ<አባቴን ገዳዮች፣ የእናቴን ደፋሪዎች የማገኝበት ብቸኛ አጋጣሚዬ ይሄ ነው። ቢከለክሉኝ ራሱ ተደብቄ እከተላቸዋለሁ።> ብዬ ፈረጠምኩ። የዛን ቀን በሩን ቆልፎብኝ የእህል ማዳበሪያ ሊቀበል ደርሶ እስኪመለስ የሳንቃውን በር ገንጥዬ ወንዶቹ የሚመካከሩበት ጫካ ሄጃለሁ። አጎቴ በጥቆማ ከቦታው ሲደርስ ከወንዶቹ መሃል ቆሜ <እኔ ነኝ ያለ ወንድ እጅ በእጅ አንድ ለአንድ ይግጠመኝ። አንዳችሁ ካሸነፋችሁኝ እቀራለሁ። አልበጠብጣችሁም። ሁላችሁንም ካሸነፍኩ ግን አብሬያችሁ እሄዳለሁ።> እያልኩ የሚጣላኝ ስጋብዝ ደረሰ። አጎቴ እንዳለኝ ከሴት ጋር ተደባድበው ቢሸነፉ ቅሌት እንደሆነ ስለገባቸው ሊደባደበኝ የደፈረ የለም። <መቼም አንቺም አንዱን ከጣልሽው በኋላ ወንድ ነኝ ያለ ደፍሮ ለመውደቅ አይመጣም ብለሽ እንጂ ያን ሁሉ ወጠምሻ እንደማትጥዪው ታውቂው ነበር።> አለኝ እንደመኩራት እያደረገው።

ከዛ በኋላ በምንም ሴትነቴ እንደማይመለስ ተስፋ ቆረጠ። እኔ እንዳላገኘው ደብቆ ያስቀመጠውን የአባቴን ሽጉጥ እና ታጣቂዎች በየቤቱ እየፈተሹ ነው ተብሎ ተቆፍሮ የተቀበረ ክላሽንኮቭ ጠመንጃውን አውጥቶ ሰጠኝ። ከመንደር አርቆ ወስዶ ኢላማ ያስለምደኝ ጀመር። አባቴ ከልጅነቴም መሰረታዊ ነገሮችን ከእናቴ ደብቆ ይዞኝ እየሄደ ያሳየኝ ስለነበር ብዙ አላስለፋሁትም። በመጨረሻም የአባቴን ገዳዮች የመጨረስ ሀሳብ ብቻውን ልቤን በሀሴት ሲሞላው ነው ሽማግሌ ልከው ፀቤ ላይ ውሃ የቸለሱበት።

ከእኔ ውጪ የቀረው ወጠምሻ መሳሪያውን ለታጣቂ አስረክቦ ጦርና ጎራዴውን ቀጥቅጦ የሽንኩርት መክተፊያ ቢላ አድርጎ ለሚስት እና ለእናቱ ሰጠ። ምንም እንዳልሆነ ሁሉ ሰላማዊ ህይወት መኖር ጀመረ። ጭራሽ ገበያ መሃል ሲገናኙ ሰላምታ መለዋወጥ ጀመሩ። ሚስቶች በመሃከላቸው ያለ የትዬለሌ ኪሎሜትር ርቀት ሳያግዳቸው ሽሮ መበዳደር ጀመሩ። እንደአጎቴ እምነት ከዚህ በኋላ ሴትነቴን ብቻ ሳይሆን ሰውነቴንም በከፊል ከዳሁ። የበቀል ጥሜን ያብርድልኝ እንጂ በመንገዴ የሚመጣ ማንም ሰው ቢሆን ከማስቀየም ወደኋላ የማልል አውሬ ሆንኩ። ቁጣዬን የምገልፅበት የማውቀው ብቸኛ መንገድ ፀብ ስለነበር <የምትጣዪው ብታጪ ከቆመ ግንድ ተጣልተሽ ትገቢ ነበር። የማደርገው ጭንቅ ጥብብ አለኝ።> ነበር ያለኝ አጎቴ። ሰላሙን የተቀበለ ሁሉ አጎቴንም ጨምሮ ጠላቴ ሆነ። መራር ሆንኩ። የቀን ተቀን የሆነ ቀን እንደምገድላቸው ነበር። አጎቴ በማያውቀው ምክንያት እንደዛ ሰፈርተኛውን እያሳቀቅኩ ግን ቆየሁ። አንድ ቀን ጭንቅህ ይብዛ ሲለው አንድ ወዳጁ ቲቪ ገዝቶ ሊያሳየን ተለማምኖ ይዞኝ እስከሄደ ቀን ድረስ። ቲቪ እንግዳ የሆነበት ብዙ መንደርተኛ ሰብሰብ ብሎ እስክሪኑ ላይ ባፈጠጠበት ያ ሰውዬ …… እናቴ ስትደፈር መጥቶ አይቶ ሱሪውን ሊፈታ ብሎ ሲጠራ የወጣው ሰውዬ አመዳም ካኪውን አውልቆ በውሃ ሰማያዊ ሱፍ ንግግር ያደርጋል። ሰውየው ሚንስትር ሆኖ ተሹሞ ብልግናውን ከአንድ ከተማ ወደ ሀገር አቀፍ የማዛመት እድል ከማግኘቱ በላይ የመንደሬው ማሽቋለጥ አንድዶኝ በጠበጥኩኝ።

«ሙሉሰውን አያችሁት? አሁንማ ጆሮው ቢቆረጥ የማይሰማ ባለስልጣን ሆነ።» እየተባባሉ ከዓመታት በፊት መንደራችንን አጋይቷት ፣ ሬሳ አስታቅፎን እየፎከረ እንደሄደ ረስተውት በኩራት ያወሩለታል። ብቻዬን የተበደልኩ አድርጌ የተሰበሰበውን ሰው ተሳድቤ ወጣሁ። በሚቀጥለው ቀን ኪዳንን አስከትዬ አጎቴ በሌለበት ቀዬውንም ለቅቄ ወጣሁ።

«ከዛስ?» አልኩኝ ተመስጬ ስሰማው ቆይቼ

«ከዛማ በእጄ ያሳደግኩሽ ልጄ ወሬሽን በእሩቅ የምሰማ ባዳዬ ሆንሽ። ብፈልግ ባስፈልግ እንዳትገኚ ስለፈለግሽ አጣሁሽ። አንቺም እንደእናትሽ ላትመለሺ መሄድሽን አምኜ ተስፋ በቆረጥኩ ሰዓት አንድ ቀን መንደርተኛው ጠላ ቤት ውስጥ ጉድ ጉድ እያለ ወሬ ሲፈጭ ደረስኩ። የምሽት የቴሌቭዥን ፕሮግራም ላይ መታየትሽን <ልጅህ ዘንጣለች> ብለው ነገሩኝ። ምን ስታደርግ ታየች ብል <አታውቅም ኖሯል እንዴ የሚንስትሩ የሙሉሰው ሚስትም አይደለች? ከእርሱ ጎን ሆና ነው ባለፊልሙ የቀረፃት> ብለው መርዶዬን እንደምስራች ጋቱኝ።» ሲለኝ ጆሮዬም መሰለኝ።

«ሙሉ ሰው እናቴ……. » መጨረስ አንቆኝ ስንተባተብ

«ልትገያቸው ከመዘገብሻቸው ሰዎች መሃል ዋንኛውን ማግባትሽን ስሰማ የፍቅር እንዳልሆነ ጠርጥሬ ተከፋሁ። እንደባዳ ዜናሽን ከሰውም አይደል የምሰማው ? እንደፈራሁትም <ሚንስትሩ በገዛ ሚስታቸው በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ።> የሚለው ዜና ሀገሪቷን ይንጣት ጀመር።» ብሎ ኩርምት ብሎ ተከዘ።

እቤት ካዝና ውስጥ ያገኘሁት የጋብቻ ሰርተፊኬት ትዝ አለኝ። ሙሉሰው!! ጠላቴን ነው ያገባሁት? ምን ምክንያት ይኖረኝስ ይሆን?


   .......... አልጨረስንም ...........

@wegoch
@wegoch
@paappii
በሳቅ ድክም እያለች ድንግልናዬን የወሰደችበትን ቀን የትላንትና ያህል አስታውሰዋለሁ። ለነገሩ ልርሳውስ ቢሉ እንዴት ተብሎ ይረሳል? እሷን በሴክስ ያሳ'ኩትን ያህል እኮ ማንንም በቀልድ አስቄ አላውቅም።

ስትስቅብኝ ተናድጄ ያለኝን ወንድነት ሁሉ አሟጥጨ ታገልኳት። መፍጨርጨሬን ስታይ እንደምንም ሳቋን ለመቆጣጠር እየሞከረች <<አ...አ...አል...አልገባም'ኮ!>> አለች በተንጋለለችበት እንባዋ ኮለል ብሎ እየወረደ።
የሰማይ አምላክ ምስክሬ ነው ከዛች ቀን ውጭ በኔ ምክኒያት እንባ ወጥቷት አያውቅም። ቆንጆ ክረምት ነው ያሳለፍነው። ለቀጣዩ ክረምት ልንገናኝና የጀመርነውን ፍቅር...ጫፍ ልናደርሰው ቃል ተገባብተን ተለያዬን።
ከዛ ቡኃላ ያዬኋት አንድ ማለዳ ሳታስፈቅደኝ ቤቴ ገብታ ነው። ኢቢኤስ ቲቪ ላይ ፕሮግራም እየመራች ነበር።

እውነት ለመናገር...ፈልጋችሁ ያጣችሁትን ሰው....ችግር ሳይገጥመው...ደስተኛ ሆኖ ስታዩት...የሆነ ግራ የሚያጋባ ነገር አለው። ስትፈልጉት'ኮ <<በጤናው ባገኘሁት!>> እያላችሁ ነው ስትመኙለት የነበረው። የምርም በጤናው መሆኑን ስታውቁ ግን ግራ ያጋባል። ግራ ያጋባል ብቻ ሳይሆን ያሸብራል። ናፍቆታችሁ ወደ ንፁህ ጥላቻ ይቀዬራል። <<ደህና ከሆነ ለምን አልፈለገኝም?>> ትላላችሁ። ያንኑ ሰው በየቀኑ ቲቪ ላይ እያያችሁት እንደመኖር ያለ ደግሞ ለመልመድ የሚከብድ ህመም የለም። ምክኒያቱም ያ ሰው...ያለመፈለጋችሁ ቋሚ ምልክት ነው!

የአቢቲ ትልቁ ችግሯም ይሔ ነው። በተራዬ ልጠፋት እየፈለግኩ ልጠፋት አልችልም። ካለችበት ሁና ያለሁበት ድረስ ትመጣለች። እስመ አልቦ ነገር...ዘይሳኖ ለዚች ቢች!

በአራት አመት የምትበልጠኝ የዩንቨርስቲ ተማሪ ጋር መተኛቴ ተሰምቶኝ የማያውቅ ወንድነት እንዲሰማኝ አድርጎኝ ነበር። ጥንን ብዬ ላዩዋ ላይ ወጣሁ። ሳትኳት። ተንከትክታ ሳቀች። ስትስቅብኝ የደነገጥኩት ድንጋጤ መልሶ ዛጎሌ ውስጥ ከተተኝ። በዛው አልተወችኝም። መልሼ በራስ መተማመኔን እስካገኘው ድረስ ደጋገመችኝ።
አልጋ ላይ ስንወጣ እንደፈለገች አይደለም የምታደርገኝ...እንደፈለገች ነው የምሆንላት።
አንዳንዴ ሳስበው <<የሚያዬኝ የለም...እሱም ልጅ ነው አያውቅብኝም!!>> ብላ ኢሞሽናሊ አቢውዝ ያደረገችኝ ይመስለኛል! (እሷ አስራ ዘጠኝ...እኔ አስራ አምስት ነበርን። የመሆን ዕድል አለው።)
ታዲያ የሆነ ነገሬን ብታዛባው ነው'ጂ ለምንድን ነው ዛሬም ድረስ ሁለት ወልደው የፈቱ ሴቶች ሳይ ራሴን መቆጣጠር እስኪያቅተኝ አምሮት የሚያናውዘኝ? ለምንድን ነው እኩያዎቼ የሚከብዱኝ? ወንድ በሴት አቢውዝ ይሆናል ብሎ የሚያምንም አልነበረም በዛ ጊዜ። <<አቢውዝ ተደርጌያለሁ>> ብትል በተዘዋዋሪ መንገድ እየተጎራህባቸው ነው የሚመስላቸው። (በፖሊስ ነበር'ኮ ላስፈልጋት የሚገባ የነበረው። ይቺ ሬፒስት!! ይቺ ያልተያዘች ወንጀለኛ!! ይቺ...)

ቆም ብዬ የዛሬውን አለባበሷን አስተዋልኩት።

ልዩነታችን እንዳለ ሆኖ የለበሰችው አጭር ቀሚስ "መጥፎ ነው" የሚባል አይደለም። ኧረ እንዲያውም "ደህና" ነው። "ያምራል" ልለውም እችላለሁ።
ንፋስ ሲነፍስ ተሰማኝ።
መስኮቱን ዘጋሁ። ንፋሱ አልቆመም። በሩን ዘጋሁ። ንፋሱ አሁንም አላቆመም። ከበሩ ወደ መስኮቱ ስመላለስ...የተራቆቱ እግሮቿ ከቲቪው እስከ ሳሎኔ ድረስ ዘርግታ አሰናከለችኝ። ተንገዳግጄ ቲቪው ፊትለፊት ካለው ወንበር ላይ ተቀመጥኩ። ለካስ ንፋሱ የተነሳው ከውስጤ ነበር። እግሮቿን ደግሜ እያዬሁ በእግሮቼ መሀል እጄን ላኩት። "ወቀሳ የሚገባኝ ከንቱ ሰው ነኝ!" የሚለው የበውቀቱ ትረካ ጆሮዬ ላይ እያቃጨለብኝ ቀጠልኩት። የስሜት ጫፍ ላይ ደረስኩ። የጀመርኩትን ሳታስጨርሰኝ <<አሁን ደግሞ ወደማስታወቂያ እንለፍ!>> ብላ አቋረጠችኝ። በሷ የጀመርኩትን...በደርባ ሲሚንቶ ጨረስኩት!

እንዲህ ነች አቢቲ። ሁሉንም ነገር ታስጀምርና ልክ ሲለምዷት ጥላ እብስ ትላለች። መጎብኘት እንጂ መለመድ አትወድም። የአማልክቱን እግር አሳይታህ ሰፍ ስትል ለ'ነደርባ ሲሚንቶ አሳልፋ ትሰጥሀለች።

ከተቀመጥኩበት ሳልነሳ...ተመልሳ መጣች። ሀፍረት ተሰማኝ። ሪሞቱን አንስቼ ቲቪውን አጠፋሁት። ቲቪው ውስጥ የሆነ ሰውዬ ሳይ <<የማነው ዥልጥ?>> ልል ብዬ...ካፌ አድርሼ መለስኩት። የጣዲቁ ያለህ!...ቲቪውን መልሼ አበራሁት። እኔ ጠፋሁ። እሷ በራች።

<<...ማስታወቂያው እስኪያልቅ ታግሰው ስለጠበቁን ከልብ እናመሰግናለን! የትም እንዳትሔዱ ብዙ ፕሮግራም ነው ያለን ዛሬ!!>> አለች።
እንጀራ ሁኖባት ነው እንጂ እንደዚህ አይነት አሰልቺ ፕሮግራም የሚያይ አንድም ጤነኛ ሰው እንደማይኖር'ኮ ታውቀዋለች። እኔም "እግር ጥሎኝ" ነው!
<<Blue Fashion የተሰኘው ሳምንታዊ ፕሮግራም አርባ አንደኛ ክፍል ዛሬ ማታ በጊዮን ሆቴል ይካሔዳል። እኛም አንቀርም እርሶም ተጋብዘዋል። እዛው እንገናኝ!>> አለች በቀጣፊ አይኖቿ እየተስለመለመች።
<<ዝምብለሽ ማስታወቂያውን ስሪ...ያንቺ መምጣት አለመምጣት ግድ የሚሰጠው የለም!!>> አልኩ ሳላስበው ቲቪው ላይ እየጮህኩ።
ግን በቃ የሚመክራት ሰው የለም ማለት ነው? ዛሬም ትላንትና ላይ ነው ያለችው? ዛሬም እሷ መሪ ተዋናይ እኛ ደቃቅ ገፀባህሪዎች እንደሆንን ነው የምታምነው? አሁን ዝግጅቱ ላይ የሷ መመምጣትና አለመምጣት ለኛ ምናችን ነው?

አንድ ያለሁት ግድ የሚሰጠኝ ሰው እኔ ነበርኩ። እኔንም እንዳይለመደኝ አድርጋ አስተምራኛለች።

<<አንጣ እጅህን ልምታልህ? ማሪያምን ክረምት ላይ ማለት ነው? እ?...ልክ ትምሕርት እንዳለቀ ወዳንተ ነው እየከነፍኩ የምመጣው! እንገናኛለን!!>> ነበር ያለችኝ የዚያኔ ስንለያይ።

የልጅ ልቤ አመናት። የህይወቴን ረጅሙን በጋ አሳለፍኩ። የናፈቅኩት ክረምት መጣ። ጭል ጭል ሲል የከረመው ወንዝ ሞልቶ መሻገሪያ ጠፋ። ወበቅ በካፊያ...አቧራውም በጭቃ ተተካ። "ከአመት አመት ያድርሰን" እያሉ የሔዱት ልጆች "ሆያሆዬ" እያሉ ተመለሱ። ክረምት አለቀ። ደመራ ተለኮሰ። የመስቀል ወፍ መጣች። እሷ ግን ቀረች። ቀጠሮ በማክበር ወፍ በለጠቻት።
በመሀከላችን የነበረው ነገር ትክክለኛ ግንኙነት መስሎኝ...አቤት ስንት ግጥም ፃፍኩላት?! አቤት ስንት ወግ ወገወግኩላት?! አቤት ስንት ቀን በናፍቆት ተወዘወዝኩላት?! ካደግኩ ቡኃላ ነው ነገሩ የተገለጠልኝ። ለካስ <<እንገናኛለን>> ያለችኝ በስንብት ጊዜ የሚመጡ አላስፈላጊ ስሜቶችን ለመሸሽ ነው። ለካስ በአዋቂዎች አለም <<እንገናኛለን!>>....የ<<ቻው>> ሌላ ስሙ ነው!

አሁን አደግኩ። እፀ-በለሱን በላሁ። አይኖቼ ተገለጡ። ክፉና ደጉን ለዬሁ። በእንዲህ አይነት ዲስኩሮች መሸወድ አቆምኩ። እሷንና መሰሎቿን ተፀይፍኳቸው። ቢቀርቡኝም ላልቀርባቸው ለራሴ ቃል ገባሁ።
እሷ ለኔ አበባ አይደለችም። የአበባ ለምድ የለበሰች መቀስ ነች።

<<ከፕሮግራሙ ጥሩነት አንፃር ካዬነው የትኬቱ ዋጋ በጣም ተመጣጣኝ የሚባል ነው። አምስት መቶ ብር ብቻ ከፍለው ያገኙታል...>> እያለች ትንበለበላለች።
እንደው ለመታዘብ ብዬ የተወሰነ አዬኋት።
<<ብዙ ነው!!>> ብላ ያካበደችላት ፕሮግራም ወዲያውኑ አለቀች።
ለምን እንደሆነ አላውቅም የሷ ፕሮግራም ሲያልቅ ቻናል መቀዬሩ አይመጣልኝም። ቲቪውን አጥፍቼ ልብሴን እያስተካከልኩ ተነሳሁ። ደሞ አምስት መቶ ብር አስገቡታ ያንን ትኬት? አሁንስ ምርር ያለኝ በየሳምንቱ ዋጋ የሚጨምሩት ነገር ነው!!

@wegoch
@wegoch
@paappii

By #Mickel Azmeraw
#የመኖር አካፋይ ፣ የመ ፤ ሞ ፣ ት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል አስራ አራት)
(ሜሪ ፈለቀ)


«ከዛ ሰውዬ ጋር አብሬው ተኛሁ? ምንድነው ያደረግኩት?» መልሱን ማናቸውም እንደማያውቁት እያወቅኩ ደጋግሜ እጠይቃቸዋለሁ። እነርሱም መልሱን ጠብቄ እንዳልጠየቅኳቸው ስለልገባቸው አይመልሱልኝም። ከዚህ ቀዬ ከወጣሁ በኋላ የተፈጠረውን ነገር ካወቀ ሊያውቅ የሚችለው ኪዳን ብቻ ነው።

እናቴን ካገኘሁ በኋላ ያለፈውን ራሴን የመፈለግ ውጥረቴ ትቶኝ ነበር። አጎቴ ታሪኬን ነግሮኝ ሲያበቃ እንደአዲስ ያቅበጠብጠኝ ጀመር። ምንድነው ያደረግኩት? ምን ዓይነት አቅል መሳት ላይ ደርሼ ነው ያን ሰውዬ ያገባሁት?

«እናቴ? ስለኪዳን የነገርኩሽን የምታስታውሺውን ሁሉ እስኪ ንገሪኝ! ከተመታሁኮ ሁለት ወር አለፈ። እንዴት አይፈልገኝም? እንዴት አይደውልልኝም?»

«እኔ እንጃ ልጄ! ብዙውን ያወራሽኝ ስለመውደድሽ ፤ ጎበዝ ተማሪ ሆኖ በማዕረግ ስለመመረቁ ፣ ፈረንጅ ፍቅረኛ እንዳለችው እና ሰርጉ ሀገሩ እንዲሆን ፈልጎ አንቺ እንቢ ማለትሽን …… እንዲህ እንዲህ ያለ ነገር ነው የነገርሽኝ እንጂ የምትገናኙበትን መንገድ አላውቅም ልጄ። ከመሞቴ በፊት ባየው ብዬሽ <በህይወት መኖርሽን አያውቅም። እንዴት እንደምነግረው እንጃ ግን እነግረዋለሁ> አልሽኝ።» እያለችኝ ሌላ የምታስታውሰው ነገር መኖሩን የጭንቅላቷን ጓዳ ትበረብራለች

«ለምን እንቢ አልኩት? ማለቴ ሰርጉን?»

«አንቺን ማጥቃት የፈለገ ሰው ሊያጠቃሽ የሚችልበት ብቸኛ መንገድ እሱ በመሆኑ አንድ ነገር እንደሚያደርጉብሽ ነው የነገርሽኝ። ሁኔታውን ልትነግሪኝ አልወደድሽም እንጂ ከዚህ በፊት በእሱ እንዳገኙሽ ነግረሽኛል።»

ድፍንፍን ያለ ነገር ሆነብኝ። ወደቤቴ መመለስ ፈለግኩ። ፍለጋዬን የት እንደምጀምር ባላውቅም እዛ የሆነ ፍንጭ አላጣም መሰለኝ። ያቺ መልእክት አስቀምጣ የነበረችው እመቤትስ? ያ የደወልንለት ሰውዬ ቃሊቲ እስር ቤት ናት ያላት እመቤት! ማን ያውቃል ለእሷ የሆነ ነገር ነግሬያት ይሆናል። ግን እስር ቤቱጋ ሄጄ በደፈናው እመቤትን ነው የምለው? ምናልባት አንድ ሀገር እመቤት የሚባል ሴት ይኖራል። አላውቅም ብቻ እዚህ ተቀምጬ ሀሳብ ከማመነዥክ መሞከሩ አይከፋም!

ምናልባት ደግሞ ያ ስልባቦት የመሰለ ዳዊት የሚሉት ፍቅረኛዬ! ለእርሱስ ምንም ልነግረው አልችልም ኸረ! ማን ያውቃል ግን? ግን እንዴት ባለ ዘዴ ነው ትውስታዬን ማጣቴን ሳልነግረው ስለኪዳን የሚያውቀው ነገር መኖሩን የማወጣጣው?

እናቴ የቀሯትን ቀናት እዛው መሆን መፈለጓን እኔ እንዳይከፋኝ በማባበል በማስፈቀድ ለዛ ስትጠይቀኝ ግራ ገባኝ። በሽታዋ የማህፀን ካንሰር ነው። ምንም ማድረግ እስከማይችሉበት ሰዓት ድረስ ሀኪሞች ብዙ ትሪትመንት ሞክረውላታል። ያገኘኋት ጊዜ ሀኪም ቤት ካልወሰድኩሽ ብዬ ስነዘንዛት

«ልጄ አንቺው እኮ ነሽ ስታሳክሚኝ የቆየሽው! ከሀገር ውጪ ወጥተሽ ካልታከምሽ ብለሽኝኮ ምንም ፋይዳ እንደሌለው ሀኪሞቹ ነግረውሽ ነው የተውሽው። አምላክ በታምሩ ይሄን ደስታ ቀምሰሽ ሙቺ ሲለኝ እንጂ እንዲህም መች ትቆያለች ተባልኩ?» ብላኝ ነበር። ሀኪሞቹ ከገመቱት ቀን በላይ መቆየቷ ተዓምር እንደሆነ ሁሉ ብትታከም ድጋሚ ተዓምር ሊፈጠር ይችል ይሆናል ብዬ ላሳምናት ብሞክርም <ደከመኝ> አለችኝ። ማረፍ ብቻ ነው የፈለገችው። መሞትን ሳትፈራው ቀርታ ይሁን ወይስ እንዳይታወቅባት ውጣው ለመሞት የተዘጋጀች ነው የምትመስለው። በመጣ ቀን <እንኳን ደህና መጣህ! ስጠብቅህ ነበር> ብላ የምትቀበለው።

«እሺ!» አልኳት እና ወደጎንጥ ዞሬ «አንተ ነገውኑ ባሻህ ሰዓት ተመለስ! እኔ እዚህ ከእናቴ ጋር እሆናለሁ! » አልኩት

«ማይደረገውን!! እኔ እዚህ መሆኔ ካልከበዳችሁ በቀር ወደየትም የመሄድ መሻት የለኝም!!» (አለ ወደአጎቴ እያየ)

«ኸረ ምን ከብደኸኝ? ባደረገውና እዚሁ በባጀህ! እኔማ የሚያነጋግረኝ አገኘሁ!» አለ አጎቴ።

ከመጣን ጀምሮ ጎንጥ ከዚህ በፊት የሚያውቀው ቤት እና ቤተሰብ ውስጥ የተቀላቀለ ነበር የሚመስለው። እጅጌውን ሰብሰብ አድርጎ እንጨት ለመፍለጥ ሰዓታት አልፈጀም። ሊወድቅ ያዘመመውን የከብቶቹን ቤት ያጋደለውን እንጨት እያስተካከለ ሲተክል በእንግድነት ውሎ አላደረም ነበር። ሱሪውን ሰብስቦ እንደቁምጣ አሳጥሮ የአጎቴን የጓሮ ማሳ ሲያርም …… የኖረበት …. የሚያውቀው እንደሆነ ያሳብቅበት ነበር። አጎቴ በእርሱ መገኘት ደስ መሰኘቱን ለማወቅ ብዙ ሂሳብ አያሰራም።

«እኔ እዚህ ምን እሆናለሁ? እዚህ ጠላት የለኝም ሲገባኝ። ዝምብዬ ነው የምፈራው እንጂ ምናልባትም ማንም እያደባብኝ አይደለም። የሚያስፈልግ ነገር ሲኖር ባይሆን ትመጣለህ።» አልኩት እናቴን ላገኛት የሄድኩ ቀን እንደዛ ተንበጭብጬ ምንም ያለመፈጠሩን እያሰብኩ።

«ህም!! ክፋት የከጀለ ልብ አይደለም እዝህች ሲኦል ከመውረድ የሚያግደው የለም!» አባባሉ ስለእርሱ ያለኝን ጥርጣሬ ቀሰቀሰብኝ። የሆነ ያልነገረኝ የሚያውቀው ነገርማ አለ።

«አይሆንም አንቺም እዚህ አትከርሚም!» አለች እናቴ ጠልቃ ገብታ « ….. በአካል ባልዳብሰው እንኳን የኪዳንን ድምፅ ሰምቼ አንዴ አውርቼው ባልፍ …… ይሄ ባይሆን እንኳን ለወንድምሽ ታስፈልጊዋለሽ። አግኝው!» አለችኝ አሁንም በልምምጧ። ልቤ መሃል ላይ ዋለለብኝ። እሺ የት ብዬ ነው የምፈልገው? እሱን ለማግኘት እኔ ስዳክር እናቴ ብታመልጠኝስ? ምን ያህል እንደሆነ የማላውቀውን የቀረንን ቀን ትቻት እንዴት ነው የምሄደው?

«የእኔ አበባ ? አትከፊብኝ! እዚህ አብረሽኝ ብትሆኝም ሞትን አታስመልጪኝም! ለእኔ አምላክ በእድሜዬ ማታ አንቺን መልሶልኝ ሀሴት ሰጥቶኛል። ወንድምሽን ባላገኘው እንኳን ደህና መሆኑን ማወቄ እረፍት ነው!! ስንት ቀኖች እና ስንት ለሊቶች <ልጆቼን ለየትኛው ጅብ ዳርጌያቸው ይሆን? ምን ዓይነት ህይወት እየኖሩ ይሆን? ትቻቸው ባልሄድ የተሻለ ህይወት ይሆንላቸው ነበር?> እያልኩ በፀፀት ነድጃለሁ መሰለሽ? ያንቺ እናት ስለሆንኩ እኔ እድለኛ ነኝ። ብቻ አንድ ነገር ቃል ጊቢልኝ! ያለፍሽውን ብታስታውሺም ባታስታውሺም ወደቀደመው ህይወትሽ ላትመለሺ ቃል ጊቢልኝ!! ልብሽን ያየ አምላክ ሁለተኛ እድል ሰጥቶሻል። ያለፈውን ለመድገም ሌላ አዲስ ህይወት ባላስፈለገሽ ነበር። አዲስ ህይወትን ገንቢ የእኔ አበባ! ……. » የስንብት የሚመስል ብዙ አለችኝ። ያለእርሷ የኖርኩትን ህይወት እንዴት እንደኖርኩት ባላውቅም አሁን ያለእርሱ የምኖራቸውን ቀናት ሳስብ በረደኝ።

ግማሽ ልቤን እናቴጋ ትቼ፤ ፈጣሪ ትንሽ ቀን ቢጨምርላት፣ ኪዳንን ባገኝላት እና ብትሰማው ወይ ብታየው እየለመንኩ በተከፋች ግማሽ ልቤ ከጎንጥ ጋር ወደቤት መንገዱን ተያያዝነው።

«ይገርማል! የዛን ቀን ሞቼ ቢሆን ኖሮምኮ መሞቴን እናቴም አጎቴም አይሰሙም። በዚህ አይነት ኪዳንም አይሰማም ነበር። ሊቀብረኝ ራሱ የሚመጣ ሰው ይኖር ይሆን?» አልኩኝ 

« ህም የሌላውን እንጃ። እኔ የት ሄጄ ነው የማልኖር?»

«ሬሳዬን የሚሸኝ ስለማይኖር ሰብአዊነት ተሰምቶህ እንጂ መቼም <ወየው እትይ!> እያልክ አትቀብረኝም ነበር።» ስለው አይኑን ለአፍታ ከመንገዱ ወደእኔ አዙሮ ፈገግ ብሎ ዝም አለ። በሱው የፈገግታ ለዛ ቀጥዬ  «ሆስፒታል እንኳን መጥተህ እየኝ ብዬ ብልክብህ <የቀጠሩኝ ደጆን እንድጠብቅ ነው > ብለህ አልላክብኝም? ዛሬ ቤቱን ጥለህ ገጠር ለገጠር አብረኸኝ ልትንከራተት?»
«ህም መች ሰው ባሰበበት ይውላል?» አለ ከንፈሩን ብቻ ሸሸት አድርጎ። እኔ አንድ ሀገር አውርቼ ከአምስት ቃል ያልዘለለ ነው የሚመልስልኝ። ያለማቋረጥ መለፍለፌ ለራሴ እንኳን እንግዳ አይነት ስሜት ሰጥቶኛል። መልሼ ይሄንንም ያንንም ሳወራ ራሴን አገኘዋለሁ እንጂ። ምናልባት ከእናቴ ጋር የነበረኝ ጊዜ፣ ወይ ደግሞ ያስታወስኩት የትውስታዬ ሽራፊ፣ ወይም ትውስታዬ የመመለስ ተስፋ እንዳለው ማወቄ፣ አልያም አጎቴ ያወራልኝ የህይወቴ ክፍል …… አላውቅም! አንዳቸው ወይም ሁሉም ተደምረው ግን የሆነ ስሄድ ከነበረው ቅልል ያለ ስሜት ስመለስ እንዲኖረኝ አድርገውኛል።

«ከመመታቴ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ያደረግኩት ምን ይሆን? ለመጨረሻ ያገኘሁት ሰው ማን ይሆን? ያስቀየምኩት ወይስ በጥሩ የሚያስታውሰኝ ሰው ይሆን?» ያልኩት እንዲመልስልኝ አልነበረም።

«የዚያን እለት ከቤት ወጥተሽ ብዙም ሳትቆዪ ነው የሆነው ነገር የሆነው። በመንገድሽ የገጠመሽ ካልነበረ ለመጨረሻ ያወራሽው እኔን ነው የሚሆን!» አለ ስሜቱን ለማንበብ በሚከብድ ፊት። ያልጠበቅኩት መልስ ሆኖ መሰለኝ ተስተካክዬ ተቀመጥኩ።

«ምንድነው ያወራሁህ? መጥፎ ነገር ነው? ጥሩ?»
«ያለፈውን ከኋላችን እንተወው ተባብለንም የለ?» መመለስ የማይፈልገው ነገር ሲሆን የሚያመልጥበት ዘዴው ነው።
«በናትህ? ለምንድነው ግን ያለፈውን ስጠይቅህ የምትሸሸው? ልቤ የሚነግረኝ ከነገርከኝ በላይ ብዙ የምታውቀውን ነገር እንደደበቅከኝ ነው ግን ዝም ብዬ እያመንኩህ ነው።» ….. ብዬ ጥርጣሬዬን ላስከትል ስንደረደር የሚቀጥለውን ለማስቆም በሚመስል

«ፀያፍ ነገር ነው!! እኔ አሁን የማልደግመውን ፀያፍ ነገር ብለሽኝ ነው የወጣሽ! እንደእውነቱስ አፍሽን ከፈትሽ ነው የሚባል።» አለ እንዲመልስልኝ ስላደረግኩት እየተናደደብኝ።

«እሺ በሙሉ ልቤ እንዳምንህ አስረዳኝ! እንደዛ ፀያፍ ነገር የምናገርህ ሴት ሆኜ እቤቴ ምን አቆየህ? ስራዬ ፣ እንጀራዬ ምናምን ብለህ ልትሸነግለኝ አትሞክር! እኔ የምከፍልህን ደመወዝ ብዙ እጥፍ ከፍሎ የሚያሰራህ ሰው አታጣም ባንተ ብዙ ችሎታ! ሲጀመር የአንድ ቤት ዘበኛ፣ መኪና መንዳት የሚችል፣ ሽጉጥ የታጠቀ ፣ ክብር ሀቅ እውነት እሴቶቹ የሆነ ሰው ……  አፏን የምትከፍትበት ሴት ደጅ ምን ያደርጋል?»

«ውል የሌለው አድርገሽ አትቆጣጥሪውማ! ሹፍርና እሰራ እንደነበርኮ አውግቼሽ ነበር። ወታደር ቤት ስለነበርኩ መሳሪያውም አዲሴ አይደለም። ሽጉጡንም ያስታጠቅሽኝ አንቺው ነበርሽ! ይከው ነው!!» አለ

«አሁን ያልከው በሙሉ ለምን እኔጋ እንደቆየህ አያብራራም! እሺ ንገረኝ እስኪ የት ነው የተገናኘነው? ማለቴ ስራውን እንዴት አገኘኸው? ወይም እኔ እንዴት ቀጠርኩህ?»

ለማውራት አፉን ከመክፈቱ በፊት በረጅሙ ተነፈሰ። ግንባሩ ላይ ያሉት መስመሮች ብዛታቸው ጨመረ። ዞር ብሎ ሳያየኝ

«ሰው ነው ያገናኘን! አንቺ ጠባቂ እንደምትፈልጊ እኔ ስራ እንደሚያስፈልገኝ የሚያቅ ሰው!» አለ በድፍኑ። አጀማመሩ እስከነገ የማያልቅ ታሪክ ሊያወራኝ ነበርኮ የሚመስለው።

«በቃ!? ሰው?» ድምፄን ጨመርኩ።
«ቆይ እኔ የምጎዳሽ አለመሆኔን እንድታምኚ ምንድነው ማድረግ ያለብኝ?»
«እያወራን ካለነው ጋር ይሄ የሚያገናኘው ነገር የለም! ትጎዳኛለህ ብዬ ባስብማ አብሬህ አልገኝም!! አንተ መናገር ያልፈለግከው ወይም እየደበቅከኝ ያለ ነገር እንዳለ እየተሰማኝ ግን ምንም ሳትጠይቂ በጭፍኑ እመኚኝ ማለት አይዋጥልኝም።» አልመለሰልኝም። አሁንም በረዥሙ ተንፍሶ ዝም አለ። በዝምታችን ውስጥ ከራሴ ሳወራ ለካንስ ምንም ነገር ለእኔ የማስረዳት ግዴታም የለበትም። <የራስሽ ጉዳይ> ብሎ ጥሎኝ ቢሄድስ መብቱ አይደል? ያኔም ለምን አብሮኝ እንደቆየ አሁን ለምን አብሮኝ እንዳለ ምክንያቱን ማወቅ አልችልም። ስለእርሱ የማወቅ መብት እንዳለኝ እንዲሰማኝ ያደረገኝ ራሱ አይደል ግን?

ሀሳብ ሳዛቁል ስልኬ ጠራ። የማላውቀው ቁጥር ነው። ለምን እንደማደርገው ባላውቅም የማላውቀው ስልክ ሲደወል ጎንጥ አጠገቤ ካለ ድምፁን ስፒከር ላይ አደርገዋለሁ። ምናልባት የመጀመሪያ ቀን ስልኬ ሲከፈት ድንብርብሬ ወጥቶ ስንተባተብ እሱ ስልኩን ተቀብሎኝ ስላወራ እንደልምድ ወስጄው ይሆናል። አነስቼ ሀሎ አልኩ።

«እሺ ሜላት!! ሁልጊዜ ጀግና አይኮንም! አንድ ቀን አገኝሻለሁ ብዬሽ አልነበር?» ወፍራም ድርብ የወንድ ድምፅ ነው።
«ማን ልበል?»
«ማን እንደሆንኩማ አሳምረሽ ታውቂዋለሽ!! ዛሬውኑ እስከማታ ድረስ የምልሽን ታደርጊያለሽ!! ህም እመኚኝ ይሄ እንደሌላ ጊዜው ማስፈራሪያ አይደለም። ምንም አይነት ወጥመድ ከጀርባዬ ሸርባለሁ ብትዪ ወንድምሽን 12 ትንንሽ አድርጌ በየተራ እልክልሻለሁ። ……. » ጎንጥ መኪናዋን ሲጢጥ አድርጎ አቆማት። እየሆነ ያለው ነገር በቅጡ ሳይገባኝ ሰውየው ማውራቱን ቀጠለ « …… ልታናግሪው ከፈለግሽ አጠገቤ ነው። ቪዲዮ ላድርግልሽ ከፈለግሽ?» (እያላገጠብኝ ነው የሚያወራው) ይሄኔ ጎንጥ ከመኪናው ፊትለፊት ያለ ወረቀት አንስቶ ከኪሱ እስኪሪብቶ አውጥቶ የፃፈውን አሳየኝ። <ምንድነው የምትፈልገው? በይው።> ሰውየው ይሄን ሲሰማ እንደመደሰት አደረገው።

« የሰውን ስስ ጎን ማግኘት ደስ ሲል።አየሽ  የምትሳሺለት ነገር ሲያዝብሽ እንዲህ ነው የሚያንገበግበው። ከገባሽ! አንደኛ ወለም ዘለም ሳትዪ የቪዲዮን ያሉሽን ቅጂዎች በሙሉ ካስቀመጥሽበት ሰብስበሽ ነይ የምልሽ ቦታ ይዘሽ ትመጫለሽ። ሁለተኛ አንቺን ማመን ስለማይቻል ማስተማመኛ እንዲሆነኝ እዚህ ከመጣሽ በኋላ በይ የምልሽን እያልሽ እንቀርፅሻለን። ይቅርታ እንግዲህ ባላምንሽ … ያለመታመን ልምድሽ አቻ ባይኖረው ነው።» እኔ እሱ የተናገረው ምኑም አልገባኝ እሱ ይገለፍጣል። ጎንጥ ፅፎ ያሳየኛል።

«እኮ ምንድነው እንድቀርፅልህ የምትፈልገው?»
«ቆቅ አልነበርሽ? ይህቺ ትጠፋሻለች? በማስፈራራት ያለፍሻቸውን እዚህም እዛም የሰራሻቸው ህገወጥ ነገሮች ሲሰበሰቡ እድሜ ልክ ዘብጥያ የምትበሰብሺበት ሆኖ አጊንቼዋለሁ። ብዙም እንዳትቸገሪ መረጃዎቹንም ሰብስቤልሻለሁ። አንቺ የሚጠበቅብሽ የሰራሻቸውን ወንጀሎች በመረጃ አስደግፈሽ አምነሽ ቃል መስጠት ነው። ከምታምኛቸው ውስጥ ፌክ የምስል ቅንብር እና መረጃ ሰርተሽ እኔን በማስፈራራት የግል ጥቅም ለማግኘት ያለመታከት መልፋትሽ ይካተትበታል። ያው እዝህችጋ ምንም ያህል የረቀ ሴራ ብትሰሪ እኔ ወደር የሌለኝ ለሀገሬ ታማኝ አገልጋይ መሆኔን አክለሽ ብትጠቅሽም አይከፋኝም። ሃሃሃሃሃ» እኔ ምኑም እየገባኝ ካለመሆኔ እየተነጋገሩ ያሉት ሰውየውና ጎንጥ ናቸው የሚመስሉት

«ኪዳንን አገናኘኝ? ማስረጃ እፈልጋለሁ።» ብሎ ጎንጥ የፃፈልኝን አነበብኩለት

«ምን ችግር። ቆዪማ ቪዲዮ ላድርገው?» ሲለኝ ጎንጥ ስልኩን ዘጋው እና እኔ ላይ አፈጠጠ።

«ወንድምሽን ስታዪው የተደናገጠ ሰው እንዳትመስዪ ፣ ድሮ የሚያውቋትን ሜላት መሆንሽን አሳምኛቸው። ምንም እንደማያውቅ ሰው አትምሰዪ ….. የማታውቂውን ነገር አትጠይቂ!! ምንም ቢፈጠር እንደማታስታውሺ እንዳትናገሪ ….. የምልሽን ብቻ አድርጊ!!» ብሎ በቁጣ እያስጠነቀቀኝ ስልኬን ተቀብሎኝ የሆነ ነገር እንደሚፈልግ ሰው ጣቱን ካመላለሰ በኋላ ከመጡለት ዝርዝሮች የሆነች ቀይ ምልክት ነገር ተጭኖ እየመለሰልኝ ስልኩ ጠራ። ድንብርብሬ ሲወጣ በሁለቱም እጆቹ ትከሻዬን በሁለቱም በኩል አጥብቆ እየያዘ « ታምኚኛለሽ?» ያለኝ ስለምን እንደሆነ ሳይገባንኝ ጭንቅላቴን ወደ ላይ ወደታች ናጥኩ!! «ተረጋጊና ያልኩሽን አድርጊ!!»
«እኔኮ ኪዳንን እንኳን ላልለየው እችላለሁ?» አልኩ አፌ ውስጥ ምራቄ ደርቆብኝ ትን የሚለኝ እየመሰለኝ። ስልኩ ጠርቶ እንዳይዘጋ እየተቻኮለ ስልክ ያልያዝኩበትን እጄን ቀለብ አድርጎ ጨብጦ ከቅድሙ በተረጋጋ ድምፅ

«ትለይዋለሽ ግድ የለም!» አለኝ። የድምፁ መርገብ ይሁን የያዘኝ እጁ ያረጋጋኝ መርበትበቴን ገትቼ የያዘኝን እጄን አስለቅቄ ስልኩን ካነሳሁ በኋላ እንዲይዘው መልሼ ሰጠሁት።                                                      

........ አልጨረስንም.....

@wegoch
@wegoch
@paappii
« ለቅሶ አለብኝ... ልብስ ምረጥልኝ» ብላ የተከፈተ ቁምሳጥኗ ፊት ለፊት አቆመችኝ። የተጠቀጠቀ የጥቁር ልብስ መአአአአአት።

'ይጥቆር እንጂ ደግሞ ለለቅሶ ልብስ መረጣ የምን ቅብጠት ነው። ' አልኩ በሆዴ ... ታዝቤያት። እጄን በግዴለሽነት ሰድጄ አንዱን ጥቁር ጎተትኩትና ፊቷ ዘረጋሁት። ቀሚስ ነበር።

“ ውይ ... ይሄንን ቀሚስማ ሰዓሊው ወዳጄ ሲሞት ለቅሶ ደርሼበታለሁ ፤ አልለብስም።»

«ለለቅሶ የለበስሽውን ቀሚስ አትደግሚም? »

«ሀዘን ይደገማል? » ጥያቄዬን በጥያቄ። «በል ሌላ ምረጥ!»

ምን አከራከረኝ፤ ያነሳሁትን ወለል ላይ ጥዬ ሌላ ጥቁር መዘዝኩ። ባለአንገት ሹራብ።

«ዘፋኙ ጓደኛዬን ቀብሬበታለሁ እሱን። ቀይር»

ሆሆ... ጥዬ ሌላ መዘዝኩ። ሸሚዝ

« የጋዜጠኛ እህቴን አስከሬን በሱ ነበር የሸኘሁት። »

ጣልኩ። አነሳሁ። አንዱን ቀብራበታለች።
ጣልኩ.. አነሳሁ። ለአንዷ አንብታበታለች።
ወለሉ በጥቁር ልብስ፣ ጆሮዬ በሙታን ፕሮፋይል ተሞላ።

እንደ ድንገት አንዷን ሳብኳት። የምታምር ጥቁር ሱሪ። አማረችኝ።

«አታምርም? »

«በጣም ታምራለች። ለምን ይህቺን አትለብሻትም? »

«ቆጥቤያት ነውኮ። በጣም የምወደው ሰው ሲሞት ነው የምለብሳት። »

«ማን ሲሞት?»

«አንተ ነሃ የኔ ፍቅር!»

« ያድኅነነ ከመዓቱ ይሰውረነ ! ምነው በናትሽ»

«ከልቤ ነውኮ። የዛሬ ወር ሾፒንግ ወጥቼ ተሰቅላ ሳያት ትዝ ያልከኝ አንተ ነህ። እንዴት እንደምወድህም ያወቅኩት ያኔ ነው። »

« እርፍ!»

« እርፍ ስትል ነውኮ እለብሳታለሁ ያልኩህ! በዛ ላይ ሰሞኑን እያሳለህ ነው... »

«ምን በወጣኝ ነው የምትወጂኝ በማርያም? ካልጠፋ ሰው እኔን ለምን ወደድሽኝ በሩፋኤል?! »

« ኧረ አንተ ብቻ አይደለህም ውዴ። ያንተን እንደውም ከገዛሁት ቆየሁ። ቁም ሳጥን ውስጥ አልከተትኳቸውም እንጂ... አባቴ... መምህሬ... ክርስትና እናቴ ፣ የእህቴ ባል ፣ ያ ደሞ አቀናባሪው... በየተራቸው ሲታመሙ ጊዜ... “ድንገት ከሞቱ ብዬ” የምለብሰው ገዝቼ አስቀምጫለሁ። እኛ የኪዳነምሕረቱ ቄስ... እኚያ ሰባኪው አወቅካቸው? የምወዳቸው ? ቄሱ... ? ከሰሞኑ ታመዋል ሲሉ ሰምቻለሁ። ከዛሬው ቀብር መልስ... ለሳቸው ለቅሶ የሚሆን ነገር ታጋዛኛለህ »

አሃ... !
ለካ አልቃሾች አዲስ ጥቁር ሲሸምቱ..፣ አዲስ ድንኳን ሲጎትቱ፣ አዲስ ሙሾ ሲሸመድዱ፣ አዲስ አለቃቀስ ሲለማመዱ... መደንገጥ ነበረብን?

ለካ የሞት መላዕኮቻችንን ከምንጠብቅ ፣ አልቃሾቻችን አዲስ ጥቁር ልብስ እስኪገዙ ብንጠብቅ፣ መች እንደምንሞት ይገለጥልን ኖሯል !?

አሳዘነችኝ።
ቁም ሳጥን ሙሉ ልብስ አገላብጣም፣ ለዛሬው ለቅሶ የምትለብሰው ጥቁር አላገኘችም። በርግጥ... እኔ ጋር ገና ያልለበስኩት ጥቁር ካፖርት አለ። «ልስጥሽ?» አልላት ነገር ፈራኋት።

«ሲያምር! እኔ ስሞት ለብሰኸው ትቀብረኛለህ!»
ብትለኝስ?

@wegoch
@wegoch
@paappii

By Rediet aseffa
#የመኖር አካፋይ ፣ የመ ፤ ሞ ፣ ት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል አስራ አምስት)
(ሜሪ ፈለቀ)

በአትኩሮት ቢያየኝ እኮ በአፌ ልትወጣ የደረሰች ልቤ ስትደልቅ የለበስኩትን ሸሚዝ እያርገበገበችው ነው። በጀርባዬ የሚንቆረቆር ላቤ ለአፍታ ሌሎች ድምፆች ረጭ ቢሉ፤ ከማጅራቴ ወደ መቀመጫዬ ሲወርድ እንደ ዝናብ <ጠብ> ሲል ይሰማ ነበር። ስክሪኑ ላይ ያለውን የራሴን ምስል ሳየው ለመኮሳተር (የማላስታውሳትን የድሮዋን ሜላት ለመምሰል) በታገልኩ ቁጥር የዞረበት ፊት እያሳየሁ እንደሆነ ገባኝ። እጄን የያዘው የጎንጥ እጅ (ገባቶት ነው መሰለኝ) እንደመጭመቅ ሲያደርገኝ ትኩረቴን ከራሴ ፊት ላይ ወደ ኪዳን መለስኩ። መስሎኝ የነበረው ከወንበር ጋር ታስሮ እየተሰቃየ የማየው ወይም ያ ድምፁን የሰማሁት ሰውዬ ግንባሩ ላይ ሽጉጥ ደግኖበት አልያም ፊቱ በድብደባ ብዛት አባብጦ እና በደም ተለውሶ ነገር የማየው ነበር የመሰለኝ። የሆነው ግን ሌላ ነው። ኪዳንና ሰውየው እየተዝናኑ እንጂ አጋች እና ታጋች በማይመስል ሁኔታ አጠገብ ላጠገብ ተቀምጠዋል። ኪዳንን ለመለየት አልተቸገርኩም። የስልኬ ስክሪን ላይ ካለው መልኩ ምንም ለውጥ የለውም። አስቀድሞም በግራ መጋባት የጦዘውን ጭንቅላቴን ልክነት ያጠራጠረኝ የኪዳን መረጋጋት ነው። የሆነ ልክ ሰላም ልንባባል የተደዋወልን አስመስሎ

«ሜልዬ! ደህና ነሽልኝኣ?» አለ። ምንድነው እየሆነ ያለው? ኪዳን አይደለም ይሆን? ሰውየው ቅድም 12 ቦታ ቀነጣጥሼ እልክልሻለሁ ሲለኝ አልሰማም ማለት ነው? አሁንም የጎንጥ እጅ አነቃኝ።

«እኔ ደህና ነኝ! አንተስ?» ይባላል ቆይ? ከአጋቹ ጋር የተቀመጠ ሰው ደህና እንደማይሆን ግልፅ አይደል? እሱ ዝንቡ እንኳን እሽ እንዳልተባለ ሰው ዘና እያለ ታዲያ ምን ልበል? ምናልባት ለእኔ ብሎ ይሆን? እኔን ለማረጋጋት?

«አታስቢ ደህና ነኝ! ከልቤ ደህና ነኝ።» እያለ ምንም ያለመጎዳቱን ሊያሳየኝ ስልኩን እያራቀ ከተቀመጠበት ተነስቶ መላ አካላቱን አሳየኝ። እያባበለኝ ነገር መሰለኝ።

«እንዴት ነው የማላስበው? መዝናኛ ቦታ …… » እኔ ባልገባኝ  ምክንያት  ለእርሱ ግን ልክ በመሰለ እንድናገር አልፈለገም። ወዲያው አቋርጦኝ

«ሜል እንዲሁ ተጨነቂ ስልሽ ነው። እኔኮ ደህና ነኝ አልኩሽ። » ሲለኝ ጎንጥ ምን እንዳናደደው ሳይገባኝ ተበሳጭቶ ጥርሱን ነክሶ እኔን ባልያዘው እጁ አየሩን በቦክስ ጠለዘው። እየሆነ ያለው ነገር አፍና ጭራው የጠፋኝ እኔን ብቻ ነው? እኔ ሳይገባኝ እሱ የገባው አብረን ከሰማነው የደህና ነኝ መልእክት ውጪ ውስጠ ወይራ አለው? « በኋላ እንገናኝ የለ? እስከዛ ደህና ሁኚልኝ! ደግሞ አምላክን በልመና አታድክሚ!!! የምትችውዪውን አድርጊና በተረፈው አመስግኚው። ያመሰገንሽው አምላክ የጎደለውን ይሞላልሻል።» አለኝ ጭራሽ። የድሮዋ ሜላት ፀሎተኛ እንዳልነበረች ጠፍቶት ነው? ይሄንኑ ዓረፍተ ነገር ግን ከዚህ በፊት የሆነ ሰው ብሎት ሰምቻለሁ!! የት ነው የሰማሁት?

እስካሁን ድምፁ ያልተሰማው ሰውዬ ስልኩን ተቀበለውና በአይኑ እንደመጥቀስ አድርጎኝ ዘጋው!!  አፌን እንደከፈትኩ ስልኩ ላይ አፍጥጬ ቀረሁ።

«ይሄ የውሻ ልጅ አውቆታል!» አለ ጎንጥ። መኪና ውስጥ ሆነ እንጂ ሜዳ ላይ ቢሆን <ዘራፍ> የሚል ነው የሚመስለው።
«ምኑን?» አልኩኝ ከድንዛዜዬ ሳልወጣ

«እየቀረፅሽው እንደሆን !» ብሎ ስልኩን እንድሰጠው እጁን ዘረጋልኝ። ስሰጠው ስልኩ ስክሪኑ ቆልፎ ስለነበር እንድከፍትለት መልሶ ሰጠኝ። ያለኝን የምከውነው ምኑም ገብቶኝ አይደለም። ያለውም የገባኝ ነገር የለውም።

«ማን ነበርኩ? ከምን ጋር የተቆላለፈ ህይወት ነው የነበረኝ? የምን ቪዲዮ ነው የምወስድለት? ስልኬ ውስጥ ያለ ነገር ይሆን?»

«ህም! ስልክሽ ውስጥ ልታኖሪው አትችዪም!» ሲለኝ አፌን ከፍቼ ቀረሁ። ስለቪዲዮው ያውቃል!!

«ምን ይመስልሃል ቪዲዮው?»

«እሱን በምን አውቄው! ብቻ ቅሌቱን የተሸከመ ነገር ነው የሚሆን»

ድንዝዝ እንዳልኩ አይኔ ብቻ ሲንቀዋለል ስልኩ ላይ ቅድም የተጫናት ምልክት ስክሪኑን መቅጃ መሆኗን እና ሰውየው እንደመረጃ እንዳንይዝበት ኪዳንን ምንም የተለየ ምልክት እንዳይሰጥ አስጠንቅቆት እንደሆነ እርግጠኛ ሆኖ ከነገረኝ በኋላ እኔን ረስቶ የተቀዳውን ቪዲዮ እየደጋገመ ወደፊት ወደኋላ ቅርብ …. ራቅ እያደረገ ያያል። እኔ ደግሞ ዝም ብዬ እሱን አየዋለሁ።

«በስተመጨረሻ ልመና አታብዥ ያለው ነገር ያላስፈላጊ ቦታ የተዶለ አይመስልሽም? ላንቺ የሚያስታውስሽ ነገር አለ?» አለኝ አሁንም ከስክሪኑ አይኑን ሳይነቅል።

«የሆነ ሰው ሲለው የሰማው ይመስለኛል። አላውቅም!! ራሴም እለው የነበረ ነገር ይመስለኛል። ምንም መጨበጥ አልቻልኩም።» ስለው እንባዬ ዓይኔን ሞልቶታልኮ እሱ ግን አላየኝም። ቪዲዮውን ኪዳን ስለምስጋና ያነሳበት ጋር አቁሞ

«ተመልከች እዚህ!!» ብሎ ሰውየውን ጠቆመኝ « ልክ ኪዳን ሲናገር ፊቱ አንድ አፍታ ይቀየራል። ተመልከች! ያ ማለት ይህ መስመር እንዲናገር ከተፈቀደለት ውጪ ነው ማለት ነው! ሊገልጥልሽ የፈለገው አንድ መልእክት ቢኖረው ነው።»


«ጎንጥ?» አልኩት ፍስስ ባለ ድምፅ

«ወይ!» አለ አይኑን እዛው እንደሰነቀረ

«ማ ነ ህ? » አልኩት እንባዬ አብሮ ከቃላቱ ጋር ዱብ ዱብ እያለ። እዛ ነጥብ ላይ ጎንጥ ዘበኛዬ ብቻ እንዳልሆነ ገብቶኛል። የሚያስለቅሰኝ በትክክል ምን እንደሆነ እንጃ።

«ኸረ በመድሀንያለም?! » አለ ደንግጦ የሚያደርገው ጠፍቶት ። እጄን ሊይዘኝ እጁን ሲሰድ መንጭቄ ቀማሁት

«እንዳትነካኝ! ሁሉንም ነገር ታውቃለህ! ይሄን ሁሉ ጊዜ ስሰቃይ እያወቅክ ምንም እንደማያውቅ አብረህ ስታፋልገኝ ነበር። ሰውየው ያወራው ሁሉ ነገር ገብቶሃል። ንገረኝ አንተም የእነሱ ወገን ነህ? ምን ፈልገህ ነው?» እንባዬ ባይቆምልኝም ሰውነቴ ሲቆጣ ፣ ደሜ ሲሞቅ ይታወቀኛል።

«መድሀንያለም በሚያውቀው እንደሱ አይደለም!! አንች ያሰብሽውና የእኔ ድርጊት ለየቅል ነው!! ሀሳቤ ጠላትነት ከነበር ምን እጠብቅ ነበር? ከጠዋት እስከማታ እጀ ላይ አልነበርሽ?»

«አላውቅም! የሆነ የምትፈልገው ነገር ይኖራላ!!» ተነስቼ ከመኪናው ወረድኩ። ትንፋሽ እስኪያጥረኝ ድረስ ንዴቴ ያጨሰኝ ጀመር። የመኪናውን ጎማ በሃይል መጠለዜን ያወቅኩት የእግሬን አውራ ጣት ሲያመኝ ነው። የሆነ ውስጤ ተኝቶ የነበረ አውሬ የነቃ ይመስል የምቦጫጭቀው ነገር ፣ ቁጣዬን የምወጣበት ነገር ፈለግኩ። እሪሪሪ ብዬ መጮህም ፈለግኩ። የመኪናውን ኮፈን በቡጢ እየነረትኩ ማቆም እፈልጋለሁ ግን እጄን የምሰነዝርበት ቁጥር በጨመረ ልክ ሰውነቴ እየረገበ ፣ ቁጣዬ እየበረደ ስለተሰማኝ አላቆምኩም። ከመኪናው ወርዶ መምጣቱን ያወቅኩት አጠገቤ መጥቶ ሁለቱን እጄን ለቀም አድርጎ ሲያስቆመኝ ነው።

«አትንካኝ አልኩኮ!! » ብዬ ከመጮሄ እኩል በምን ቅፅበት እንደሰነዘርኩት ያልተቆጣጠርኩት ለቡጢ የተጨበጠ እጄ ጉንጩ ላይ አርፏል። ያደረግኩትን ሳውቅ ደንግጬ የመታሁበትን እጄን እንደበዓድ እጅ አየሁት። ከመኪናው ኮፈን ድብደባ ይሆን ከእርሱ ጉንጭ እጄ በልዟል። ወደኋላ ዞሮ አፉ ውስጥ የሞላውን ደም ከተፋ በኋላ ወደ እኔ እየዞረ በሱ ብሶ ይጮህ ጀመር
« ከበረደልሽ ድገሚኝ!! እ? በያ!» እያለ ለፀብ ይጋብዘኛል። ትቼው ወደመኪና ልገባ ስል እየተከተለ ሆነ ብሎ ይገፋፋኛል። «ይህችን ታህል ነው የተናደድሽብኝ? ለዝህችው ነው የጎፈላሽው?» ሲለኝ እንዴት ዥው ብዬ እንደዞርኩ አላውቀውም። እጄን ስሰነዝር በሚያስደነግጥ ፍጥነት በመዳፉ ቀለበው። ያልቆጠርኩትን ያህል ጊዜ ተከላክሎ አንዴ ነው አጓጉል ያገኘሁት። ዋጥ አደረጋት!! ቁጣዬ ረጭ ማለቱን ያወቅኩት ይሄኛው የድሮዋ ሜላት ማንነት መሆኑን መገንዘብ ስጀምር ነው።

«ደግ! አሁን ከሰከንሽ እየተጓዝን ስለኪዳን እናውጋ?» አለኝ የመታሁትን ጉንጭ እያሻሸ ወደመኪናው እየገባ
«ጉንጭህን አገላብጠህ ስለሰጠኸኝ እንዳምንህ ነው የምትጠብቀው?»
«እና ምን ይሁን ነው የምትይ? እዚሁ ቁመን ይምሽ? አንዱን አካሉን እዚሁ እንዲልኩልሽ ነው ያሰብሽ?» እየጮኸብኝኮ ነው። ከቃላት ሁላ በላይ ሆነብኝ እና አፌን ከፍቼ አፍጥጬ አየው ጀመር

«አንተ ግን የምርህን ነው? ካንተም ብሶ …….. » አልጨረስኩትም እየሮጥኩ መኪና ውስጥ ገባሁና ስልኬን አነሳሁ። አጎቴጋ ደወልኩ። ተከትሎኝ ገብቶ የማደርገውን በትኩረት ያያል።

«አጎቴ እናቴን አገናኘኝ እስቲ የሆነ ሳልጠይቃት የረሳሁት ነገር ትዝ አለኝ።» አልኩት

«እናቴ ? በቀደም <አምላክን በልመና አታድክሚ!!! የምትችውዪውን አድርጊና በተረፈው አመስግኚው!! ። ያመሰገንሽው አምላክ የጎደለውን ይሞላልሻል> ብለሽኝ ነበርኣ?»

«አዎ የእኔ አበባ ምነው?»

«አጎቴንም እንደዛው ስትዪው ሰምቻለሁኣ?»

«ሁሌምኮ የምለው ነገርኮ ነው ልጄ?» አለች ግራ እየገባት።

«የተለየ ትርጉም ነገር አለው እንዴ?»
«ኸረ ምንም ቅኔ የለውም ልጄ! ምን ጉድ ነው?»
«እንዲሁ ነው የሆነ ሚስጥር የያዘ አረፍተነገር ይመስል ውስጤ ተመላለሰ። ድንገት ሌላ መልዕክት ካለው ብዬ ነው።»
«በፍፁም! ሁሌም ሰዎች እጅ እግራቸውን አጣጥፈው በቀላሉ መስራት በሚችሉት ነገር ሁሉ ሳይቀር ፈጣሪን በልመና ሲያደክሙ እንደዛ እላለሁ። »

«እሺ በቃ እናቴ» ስልኩን ዘግቼ አስባለሁ። ምንም ሳይለኝ መኪናውን መንዳት ቀጠለ።

«እኔን አይደል የሚፈልጉት? እኔ ሄድላቸዋለሁ! እኔን የሚያደርጉትን ያድርጉና ወንድሜን ይለቁታል።» አልኩኝ ለራሴ ያሰብኩትን ድምፄን አውጥቼ እየተናገርኩት

«ህእ! አንቺን ቢፈልጉ እስከዛሬ ላንቺ የሚሆን አንድ ጥይት ጠፍቷቸው ይመስልሻል? ካንቺ በላይ የያዝሽባቸውን መረጃ ይፈልጉታል።» አለ <ቂል ነሽ እንዴ?> በሚል ለዛ

«ሊገድሉኝ ሞክረው የለ?»
«እኔን ከጠየቅሽኝ በፍፁም እነሱ አይመስሉኝም!!»

«እሺ ያለውን ቪዲዮ የምናገኝበት ፍንጭ ታውቃለህ? መቼም የማታውቀው ነገር የለም!» አልኩት አፍንጫዬን እየነፋሁ።
«አላውቅም!!» አለኝ በመድከም አይነት።

«ስለዚህ እሄዳለሁ። አትከተለኝም። እውነቱን እነግራቸዋለሁ።» አልኩኝ ፍርጥም ብዬ
«የማይደረገውን!!» አለ ኮስተር ብሎ

                            ............ አልጨረስንም ..........

@wegoch
@wegoch
@paappii
#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል አስራ ስድስት )
(ሜሪ ፈለቀ)

«ብዙውን አላውቅም። እየሆነ ስላለው ነገር ምንም እውቀት እንደሌለሽ ያወቁ ሰዓት ግን እንደሚገድሉሽ በአስር ጣቴ ፈርማለሁ።  ስራ አቀለልሽላቸው!! አንቺም ከእነርሱ እኩል የሚፈልጉትን ማስረጃ የት እንዳለ የማታውቂ ፣ ገና እያፈላለግሽ እንደሆነ ልቦናቸው ካወቀ ምን ትሰሪላቸዋለሽ?»

«እኮ ያ ማለት ጠላታቸው አይደለሁም እኔን የሚያሳድዱበት ወንድሜንም የሚያፍኑበት ምክንያት የላቸውም!»

«አንችዬ ጅልም ነሽሳ? ያስታወስሽ ማግስት እንደገና ራስምታታቸው እንደምትሆኚ እያወቁ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልሽ! ብለው እንዲሸኙሽ ነው የምታስቢ?»

«አንተስ የሆነ ቀን ማን እንደሆንክ እንደማስታውስ ግን በሀሳብህ ሽው ብሎ ያውቃል??»

«አይከፋኝም ዓለሜ!! ያኔ ከምታውቂኝ በላይ አሁን ነውስ ምታውቂኝ !!» አለ ዘወር ብሎ አይቶኝ መልሶ «ያለፈውን ብነግርሽ ታምኚኝ ይመስልሻል?»

«ስላልነገርከኝም እያመንኩህ አይደለም። ቢያንስ አውቄው ራሴ ልወስን!! ካልሆነ ግን እንድች ብዬ እግሬን ካንተጋ የትም አላነሳም!»

«አራት አስርት ዓመት እዝህች ምድር ባጀሁኮ!! ምኑን አውግቼሽ ምኑን ትቼው እዘልቀዋለሁ? የትየለሌ ነው!!» አለ በንግግሩ ብዙዙዙ እያስመሰለው።

«እኔ የ40 ዓመት ታሪክህ ምን ያደርግልኛል? እኔ ደጅ ያደረሰህን ታሪክ ነው የምፈልገው። አንድ ዓመት ያከረመህንም!!»  በረዥሙ ተነፈሰ። ሁል ጊዜ እንደሚያደርገው። ሊነግረኝ ነው ብዬ ስጠብቅ አጀማመሩን አርዝሞ የቆመ ጆሮዬን ኩም እንደሚያደርገው

«አንዱ ከሌላው ይተሳሰራል። ሁሉን ካልነገርኩሽ ቁንፅል ነው የሚሆን። እንደው በጥቅሉ ደጅሽ ያመጣኝ እንዳልኩት ሰው ነው። ደጅሽ ያቆየኝ አንድ እለት የዋልሽልኝ ውለታ ነው!» ብሎ የማንነቱን እንቆቅልሽ ሁሉ የፈታልኝ ይመስል ጭጭ አለ። ተናደድኩ።

«ኸረ? ውለታ? እያዋረድኩህ እንኳን ደጄ የነበርከው ለአንድ እለት ውለታ ነው? ትንሽ እንኳን የሚመስል ነገር ብታወራ ምን አለበት? ማስታወስ እንጂ ያቃተኝ ጡጦ የሚጠባ ህፃን እኮ አይደለሁም!!»

«ምንአለበት? የሰው ልጅ ለአንዲት ቀን በደል እድሜውን ሙሉ ቂም ይዞ  ይኖር የለ? ለአንዲት ቀን በደል ለዓመታት በቀል ሲጎነጎን ይከርም የለ? ምናለበት ለአንዲት ቀን ደግነት ብዙ ዓመት ደግ ቢሆን?» ዋናውን ርዕስ እየሸሸ መሆኑ ገብቶኛል። ስልኬ ላይ መልዕክት ገባ።

«ምሽት 2 ሰዓት ላይ ፒክ የሚያደርጉሽ ሰዎች በዚህ አድራሻ ይጠብቁሻል። ሰው አይደለም የሰው ጥላ ቢከተልሽ ያልኩሽን አትርሺ!! የምልክልሽን ስጦታ!!» ይላል። ምን እንደሆነ እንድነግረው ዘወር ብሎ እያየ ይጠብቃል።

«እናቴ ናት!! በአጎቴ ስልክ ደህና መግባታችንን ለማወቅ ነው መልእክት የላከችው።» አልኩት።

ለመጀመሪያ ጊዜ ዋሸሁት! ለመጀመሪያ ጊዜ ደበቅኩት። ግን ልክ ያደረግኩ መሰለኝ አልከፋኝም!! አዲስ አበባ ገብተን ለምናልባቱ የተሻለ ፍንጭ ካገኘን ቃሊቲ እየሄድን ነው። በልቤ ወስኜ ጨርሻለሁ። ከቃሊቲ መልስ ፣ መልስ ባገኝም ባላገኝም ጎንጥን የሆነ ቦታ አመልጠዋለሁ። ለሽንቴ እንኳን ስወርድ ልጠፋበት እንደምችል ጠርጥሮ መሰለኝ በቆቅ አይኖቹ ይከተለኛል። እንዴት እንደማመልጠው አላውቅም። ግን ከእርሱ ጋር የሚቀጥለውን እርምጃ አልራመድም። አሁን ላይ ማንን እና ምን እንደማምን ግራ ገባኝ። ለምኜዋለሁኮ ስላለፈው ህይወቴ የሚያውቀውን እንዲነግረኝ። ምንም እንደማያውቅ ሲነግረኝ አምኜው ምንም ሳልደብቀው በእሱ ላይ ዘጭ ብዬ እምነቴን ስጥልበት ትንሽ እንኳን አይከብደውም? የምሸሸው ምን እንደሆነ እንኳን ሳላውቅ በፍርሃት ነፍሴ ሲርድ እና ስፈራ አላሳዝነውም? እርሱን ከምንም በላይ አምኜኮ ለሳምንታት እጁን ይዤ እንቅልፌን ተኝቻለሁ። ምን ይሆን ያስብ የነበረው? በልቡ <አይ ሞኞ> ብሎኝ ይሆን?

«እመቤት በአንድ ወቅት ከእነርሱ ወገን የነበረች ጋዜጠኛ መሆኗን ሰምቻለሁ። ወዳጃምነታችሁ እምንድረስ እንደነበር የማውቀው ባይኖረኝም ለጊዜው መዘንጋትሽን ግልፅልፅ አድርገሽ ባትነግሪያት እመክርሻለሁ።» አለኝ ልንቃረብ ገደማ። አስቤ የነበረው ሁሉንም ነግሪያት የምታውቀውን መጠየቅ ስለነበር ካልጠየቅኳት የመሄዴ ትርጉም ራሱ ምን እንደሆነ ግራ ገባኝ። ቢሆንም ሄድን!!


በሩ ላይ ስንደርስ የሆነ ልጅ እግር ጠባቂ «ይሄ ባሻሽ ሰዓት እየመጣሽ እገሌን ጥሩልኝ የምትዪበት የጎረቤትሽ ቤት መሰለሽ እንዴ? እስረኛ መጠየቂያ ቀንና ሰዓት አለውኮ!!» ብሎ ፊቱን ወደ ውስጥ መለሰ
«እናውቃለን! እንደው የሞት ሽረት ጉዳይ ገጥሞን ነው! እንደው ለ2 ደቂቃ!» አለ ጎንጥ
«አትሰማኝም እንዴ ሰውየው?  ስራዬን ልስራበት ከዚህ ራቁ!! እንደውም እዚህ አቅራቢያም መቆም አይቻልም ዞር በሉ ብያለሁ።» ብሎ አምባረቀ። ምንም ተስፋ እንደሌለው ሲገባኝ

«እሺ የእስረኛ መጠየቂያ ቀን መቼ ነው?» አልኩ። ይሄኔ ሌላኛው በእድሜ በሰል ያለ ጠባቂ «ምንድነው? » እያለ ብቅ አለ። ልጅ እግሩ ምንም የሚለንን የማንሰማ መሆናችንን እያብራራለት ሰውየው እኔን በትኩረት ካየ በኋላ

«አጅሪት? መቼም ካንቺ ውጪ እዚህ በር ላይ ሁከት የሚፈጥር የለም!! ስትጠፊኮ ሌላ ቦታ ሸቤ ገብታ ነው ወይም ከባርች ጋር ተጣልታ!  ብለን አስይዘን ነበር። ኸረ ለውጥ ቁርጠቴ በቀሚስ?» አለኝ። አወራሩ የእስር ቤት ጠባቂ ሳይሆን የሆነ የወዳጅነት ነው። ልጅ እግሩ ጠባቂ ግራ ገብቶት ያየዋል። « ከባርች ጋር ተጣልታችሁ ነው መምጣት ያቆምሽው??» ካለኝ በኋላ ወደልጅ እግሩ ጠባቂ ዞሮ « …. ቁርጠቴ የሴቶቹ ካቦ ነበረች እዚህ እያለች።» ሲል ልጅ እግሩ የሆነ ነገር እንደማስታወስ ብሎ ከላይ እስከታች ካየኝ በኋላ « ቁርጠቴ ማለት እሷ ናት? የሰማሁትን አትመስልም!» አለ

« ምን እንታዘዝ ታዲያ? መጠየቂያ ቀን አለመሆኑን ታውቂያለሽ መቼም!!» አለ በሰል ያለው ጠባቂ ወደ እኔ እየተጠጋ
«ብያለሁ አልሰማ ብለውኝ ነው። እመቤት የምትባል ነው የሚሉት?» አለ ልጅ እግሩ እኔ ሰውየው የሚጠራቸው ቅፅል ስሞች የማን እንደሆኑ ሳላውቅ ያለቦታው ሰክቼ ስህተት እንዳልሰራ ስደነባበር። ንግግሩ ያለመፍቀድ ዓይነት አይደለም። የመፍቀድም አይነት አይደለም። ግራ የገባ ነገር አለው። ይሄኔ ጎንጥ ጠጋ ብሎ እየጨበጠው

«እግዜር ይስጥልን ጌታዬ!! የሞት ሽረት ጉዳይ ባይሆን ካለቀኑ መጥተን ባላስቸገርን!!» አለው። ሰውየው ሳቅ ብሎ የጨበጠበት እጁን ከልጅ እግሩ ጠባቂ ደበቅ አድርጎ ገለጠው። ገንዘብ ነው ያቀበለው። ገንዘብ መፈለጉ እንዴት ገባው? ቆይ እሱ የማያውቀው ነገር ምንድነው? ሰውየው ዞር ብሎ ለልጅ እግሩ እመቤት ያለችበትን ምድብ ይመስለኛል የሆነ ቁጥር ነግሮት እንዲጠራ አዘዘው። ልጁ እየተነጫነጨ የተባለውን አደረገ። ምን መጠየቅ እንዳለብኝ እና እንደሌለብኝ መወሰን አቃተኝ። እንደማላስታውሳትስ መንገር አለብኝ? እሷስ የእኔ ወዳጅ ናት ወይስ እንደጎንጥ ማንነቷን የደበቀችኝ ሴት? የስራውን ይስጠው እንኳን ጠርጥርትያት ብሎ ሹክ ብሎኝ እንዲሁም ጥላዬን የምጠራጠር ጠርጣራ አድርጎኛል:: ስትደርስ ለቅሶ እና ሳቅ የተደባለቀው ነገር ሆነች። በእኔ ተመሳሳይ እድሜ የምትገኝ ዓይነት ሴት ናት። ጎንጥ ጆሮውን ቢተክል የምናወራውን ሊሰማ በሚችልበት ርቀት ቆሟል።
«በህይወት አለሽ? በህይወት እያለሽ ነው ልታዪኝ ያልፈለግሽው? ምን ሆነሽ እንደሆነ ብቻ ንገሪኝ? ደህና ሆነሽ ነው?» እያለች ማልቀስ ጀመረች። በጥይት መመታቴን ነገርኳት። መርሳቴን ግን ዘለልኩት። ደግሞ ወቀሳዋን ትታ ለእኔ ማዘን ጀመረች። ዞር ብላ ጎንጥን በ<ማንነው ?> አይነት ምልክት ሰጠችኝ። አጠያየቋ እንደምነግራት እርግጠኛ የሆነ ነው። የቀረቤታዋ ልክ ብዙ ነገር የምናወራ ሰዎች እንደነበርን ያስታውቃል።

«ጎንጥ ዘበኛዬ ነበር።» አልኳት። ለምን <ነበር> እንዳልኳት አላውቅም!
«ጎንጥ ጎንጤ? ጎንጤ ጥጋቡ? » ብላ ጮኸች። ስለጎንጥ የምታውቀው ምን እንደሆነ ባላውቅም የግርምት አጯጯኋ ስለዘበኝነቱ ብቻ እንዳልነገርኳት ያስታውቃል። ለአንድ አፍታ ሁሉንም ዝርግፍ አድርጌ ነግሬያት የምታውቀውን ብትነግረኝ ተመኘሁ።

«ኪዳንን ይዘውታል! ቪዲዮዎቹን ካልሰጠኋቸው እንደሚገድሉት ነግረውኛል።» አልኳት የማወራው ነገር አዲሷ እንደማይሆን እርግጠኛ ሆኜ።

«ኪዳን ምን ሊሰራ መጥቶ አገኙት? ሺት!! እርግጠኛ ነሽ? እኚህ አጋሰሶች!! የፈራሽው አልቀረም!! » ብላ በድንጋጤ እና በንዴት መሃል ዝም አለች።
«አዎ በቪዲዮ አይቼዋለሁ። አውርቼዋለሁም። ምን እንደማደርግ ግራ ገባኝ?» አልኳት ሌላ ፍንጭ ከሰጠችኝ ብዬ
«መቼም አትሰጫቸውማ? ሌላ መላ መቼም አይጠፋሽምኣ? »
«በኪዳን ነፍስ ቁማር መጫወትም አልችልም!»
«እየቀለድኩ ነው በይኝ!! ጥይቱ የዋህ አድርጎሻል ልበል? ወይስ ሚሞርሽንም ነው ያጠበልሽ?» ያለችው ለአባባል ነበር እኔ ግን አዎ ብያት ሁሉንም ብትነግረኝ ፈለግኩ። የጎንጥን ማስጠንቀቂያ ችላ ማለትም ከበደኝ። እራሱን ሳላምነው ቃሉን ለምን እንደማምን ምክንያት የለኝም። ግን መጠንቀቅ አይከፋም። እሷ ቀጠል አድርጋ

«ከዚህ በፊት ከእጃቸው ፈልቅቀሽ ወስደሽዋል። አሁንም ተረጋግተሽ አስቢ እና መላ አታጪም!!»
«ተረጋግቼ የማስብበት ጊዜ የለኝም!! የሰጡኝ ሰዓት ሊያልቅ ሶስት ሰዓት ነው የቀረው!» ስላት የሆነ ግራ ያጋባኋት አይነት በጥያቄ አስተዋለችኝ። አለባበሴን ጭምር በዓይኗ ለቀመች እና
«ምንድነው እሱ? ከመቼ ወዲህ ነው እንዲህ መልፈስፈስ ያወቅሽበት? የሆነማ ልክ ያልሆነ ነገር አለ። ደግሞ ልስጣቸውም ብትይ ሴትየዋን በ3 ሰዓታት ውስጥ አጊንተሽ አንደኛውን ኮፒ ልትቀበያት አትችዪም!! ነው ወይስ ኦልረዲ አጊንተሻታል?»

«ሴትየዋን?» ካልኩ በኋላ ሳላስበው « የአቅሜን እሞክራለኋ» አልኳት መልሼ!! መልስ የሰጠችኝ መሰለኝ። ለሰዎቹ የሰጡኝን የጊዜ ገደብ ማራዘሚያ ምክንያት!! የምጠይቃት ብዙ ቢኖርም!! በምን መንገድ እን,ደምጠይቃት ካለማወቄ የእሱን እንቢታ ጥሶ ሌላኛው ጠባቂ እመቤትን እንዲጠራልኝ ያስገደደው ልጅ እግር ጠባቂ ሰዓታችን ማለቁን ከግልምጫ ጋር ይነግረኛል። ለእመቤት መልሼ እንደምመጣ ነግሬያት። ወደከተማ መመለስ ጀመርን።

«ሴትየዋ ያለችሽ ማን ትሆን?» ሲለኝ ያወራነውን ሁሉ እንደለቀመ ገባኝ።
«አላውቅም! መርሳትሽን አትንገሪያት አላልክም? ማናት ብዬ እንዴት መጠየቅ እችላለሁ? ሁሉን ነገር ታውቅ የለ? ይሄ እንዴት አመለጠህ?» ብዬ ጮህኩበት

«ታዲያ ምን የሚያስቆጣ ተናገርሁ? ቃሌን ያለማመንና ሴትዮይቱን ማመንምኮ ያንቺ ድርሻ ነበር።» አለ ተረጋግቶ።

«ለማንኛውም እቤት ንዳኝ!! ተረጋግቼ የማስብበት ሰዓት እፈልጋለሁ።» አልኩኝ። ከዛ ማውራት የእሱ ተራ ዝም ማለት የእኔ ተራ ሆነ።

« አሁን እኔና አንቺ አንባጓሮ የምንፈጥርበት ሰዓት አይደለም! በአንድነት መላ ብንዘይድ አይበጅም? ከሰውየው ጠባቂዎች አንዱ ወዳጄ ነው። ኪዳን ያለበትን አድራሻ ማግኘት ከቻልን መልዕክት አኑሬለታለሁ። እስታሁን የምትመጪበትን አድራሻ አልላኩም? መላክ ነበረባቸው!! ትክክለኛ አድራሻውን እንደማይልኩልሽ ግልጥ ነው። ከሆነ ቦታ ይቀጥሩሽና ነው በራሳቸው መኪና የሚወስዱሽ!! እርግጥ አድራሻውን ከደረስንበት እነርሱ የቀጠሩሽ ቦታ ሲመጡ እኛ ቀድመናቸው ቦታው እንደርስ ነበር ….. » እሱ እቅዱን ከጅምር እስከ ፍፃሜ ሲነግረኝ እኔ ደግሞ የራሴን እቅድ ከጅምር እስከ ፍፃሜ የሌለው አቅዳለሁ። እቤት እንደደረስን እዛ መሳቢያ ውስጥ ያለውን ሽጉጥ እወስዳለሁ። ምን እንደማደርግበት የማውቀው የለኝም። በሆነ መላ ከጎንጥ እሰወራለሁ። የቀጠሩኝ ቦታ ብቻዬን እሄዳለሁ። የሚወስዱኝ ቦታ ስደርስ (ኪዳን ይኖራል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ) ሁሉንም ኮፒ ለማግኘት በቂ ጊዜ ስላልነበረኝ ተጨማሪ አንድ ቀን እንዲሰጡኝ እጠይቃለሁ። የሚፈልጉት ቪዲዮ የዚን ያህል አንገብጋቢ ከሆነ አይገድሉኝም። የጠየቅኩትን ጊዜ ይሰጡኛል። በተቃራኒው ሊሆን እንደሚችል ሳስብ ልቤ ይደልቃል:: ትልቁ ፍላጎቴ ግን ለትንሽ ደቂቃ ከወንድሜ ጋር እንዲተውኝ ማድረግ ነው። ብቸኛ ላምነው የምችለው እና ሊያውቅ የሚችል ሰው እሱ ነው። ይሄ ጎንጥ እንዳለው የጅል እቅድ ሊሆን ይችላል። እጄን አጣጥፌ እየጠረጠርኩት ያለሁትን ጎንጥን ከመከተል ውጪ ሌላ የተሻለ እቅድ ግን የለም። ያን ደግሞ አላደርግም!!

እቤት እንደደረስን ተናኜ የማያቆም ጥያቄ እና ወሬ ታከታትላለች። እንደማልሰማት እንኳን የምታስተውልበት ፋታ አትወስድም። ጎንጥ ከገባ ጀምሮ በሩ ላይ እንደተገተረ ነው። ጮክ ብዬ ጎንጥ እንዲሰማ

« አንድ ላይ የምንበላው እራት አሰናጂ!! ምን እንደሚፈጠር አይታወቅም! እራት አንድ ላይ እንቋደስ!» አልኩኝ ለእሷ ግራ እንደሚያጋባት ሳልረዳ

«ምነው እትይ የት ልትሄጅ ነው?»
«የትም አልሄድ! ያልኩሽን ዝም ብለሽ አድርጊ!» አልኳት። ቅር እያላት ገባች። ለመሄድ የሚያስፈልገኝን ነገር ካሰናዳሁ በኋላ ጥርጣሬውን ለመቀነስ ልብሴን አልቀየርኩትም። እራት ሶስታችንም ቀርበን እየበላን። አስተያየቱ እንዳላመነኝ፣ ነገረ ስራዬ እንዳላማረው ያስታውቃል።

«አድራሻውን ልከውልኛል።» አልኩት
«የት ነውስ?» አለ ቀና ብሎ ስልኬን እንድሰጠው መሰለኝ እጁን እየዘረጋ። ስልኬን የለበስኩት ሹራብ ኪስ ውስጥ የከተትኩት ለራሴ እቅድ እንዲመቸኝ በመሆኑ እጁን ችላ ብዬ

«እንዳልከው ነው። ቀበና የሚባል ሰፈር የሆነ ካፌ ፊትለፊት ነው። ስልኬ መኝታ ቤት ነው አሳይሃለሁ። ከዛ ነው ከእነርሱ ጋር ሊወስዱኝ ያሰቡት! ምንድነው የምናደርገው? ወዳጅህ እስከአሁን አልመለሰልህም?።» አልኩት። ይመነኝ አይመነኝ ባላውቅም በእርሱ እቅድ እየተመራሁ እንደሆነ እንዲመስል ጣርኩ። አስተያየቱ ያመነኝ አይመስልም። ከጎሮሮዬ አልወርድ ያለውን እህል እንደምንም ካጋመስኩ በኋላ

« …… በልተሽ ስትጨርሺ እዚህ ላይ አንድ ስኒ ቡና ብታጠጪኝ ደግሞ?» አልኳት ተናኜን። ልትነሳ ሲዳዳት ተረጋግታ እንድትጨርስ ነግሪያት ወደጓዳ እጄን እንደሚታጠብ ሰው ገባሁ። እጅ መታጠቢያውን ውሃ ክፍት አድርጌ አስቀድሜ ክፍቱን በተውኳቸው በሮች የምፈልገውን ይዤ በጓዳ ወጣሁ። መጣ አልመጣ አድብቼ እየተርበተበትኩ የአጥሩን በር ከፍቼ ስወጣ ከኋላዬ የሚያባርረኝ ያለ ነበር የሚመስለው አሯሯጤ። የቤቴ በር ከአይኔ እስኪሰወር እሮጥኩ። ያገኘሁትን ታክሲ አስቁሜ ወደተላከልኝ አድራሻ እየሄድኩ።

«ማን ስለሆነ ነው ቆይ እንዲህ የምደበቀው? ያውም በገዛ ቤቴ?» እላለሁ በልቤ!!

………. አልጨረስንም……

@wegoch
@wegoch
@paappii
#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል አስራ ሰባት)
(ሜሪ ፈለቀ)

የምጣደፈው ጎንጥን ሽሽት ይሆን ኪዳንጋ ለመድረስ ተቻኩዬ ወይም በሁለቱም ምክንያት የታክሲው ሹፌር ትዕግስቱን እስኪያንጠፈጥፍ ድረስ አቻኩለው ጀመር። <ምን ያህል ቀረን?>  ፤ <ትንሽ ፈጠን ማለት አትችልም?> ፤ < ሌላ ያልተዘጋጋ አማራጭ መንገድ አይኖርም?> ፤ < አሁንም ብዙ ይቀረናል?> አንድ አይነት ጥያቄ በየሁለት ደቂቃው እየደጋገምኩ ፤ ግማሽ ጎኔ ወደፊት ግማሽ ጎኔ ወደኋላ በሆነ አቀማመጥ ፤ በአንድ ዓይኔ ወደኪዳን (ወደፊት) በአንድ ዓይኔ ወደጎንጥ (ወደኋላ) ሳማትር

«ሴትዮ ካልሆነ ውረጂ እና ሌላ ታክሲ ተሳፈሪ! አይታይሽም እንዴ በማይነዳበት እየነዳሁልሽ? ሆ! ዛሬ ምኗን ነው የጣለብኝ ባካችሁ?» አለ ያለመታከት ሲመልስልኝ ቆይቶ ከትዕግስቱ በላይ ስሆንበት

«ይቅርታ በጣም ስለቸኮልኩ ነው። ይቅርታ በቃ እንደሚመችህ አድርገህ ንዳ!!» አልኩኝ። ታክሲው ውስጥ በቦርሳ የያዝኩትን የቱታ ሱሪ ከቀሚሴ ስር ለብሼ ሳበቃ ቀሚሴን አውልቄ ወደቦርሳው ከተትኩ።

እያደረግኩት ያለሁት ድፍረት ይሁን ድድብና መመዘን የምችልበት መረጋጋት ላይ አልነበርኩም። ምናልባት አለማወቅ ደፋር ያደርግ ይሆናል ወይም ደደብ!! ጎንጥ ሰዎቹን ስለሚያውቃቸው ይሆናል የሚጠነቀቀው እና የሚፈራልኝ። የማላውቀውን ሰው ወይም ልገምት የማልችለውን የሚገጥመኝን ነገር በምነኛው መጠን ልፈራ እችላለሁ? እስከገባኝ ድረስ ቢያንስ አለማወቄ ጎንጥን እስከአለመከተል ድረስ ደፋር ወይም አላዋቂ አድርጎኛል።

የተባለው ቦታ ስደርስ ለቀጠሯችን 20 ደቂቃ ይቀረኛል። ከታክሲው ከወረድኩ በኋላ እንደማንኛውም በአካባቢው እንዳለ ተንቀሳቃሽ ግለሰብ የአዘቦት ክንውን እየከወንኩ ለመምሰል ጣርኩ እንጂ እንደሌባ ዓይኖቼም አካሌም እየተቅበጠበጠ ነበር። እስከዚህ ደቂቃ ያልተሰማኝ ፍርሃት አጥንቴ ድረስ ዘልቆ ይገለባበጥ ጀመር። መቆምም መራመድም መቀመጥም ሰው ይቸግረዋል? ወደላይ ትንሽ ራመድ እልና ደግሞ በተቃራኒው አቅጣጫ እመለሳለሁ። በመሃል እንደማቅለሽለሽም ያደርገኝና መሃል የእግረኛ መንገድ ላይ ቁጢጥ እላለሁ። ከመንበጭበጬ ብዛት ሽንቴን እላዬ ላይ የምለቀው መሰለኝ። ሰዓቴን በ60 ሰከንድ ውስጥ 120 ጊዜ አያለሁ። ደቂቃው ሰዓቴ መስራቱን ያቆመ ይመስል ፈቅ አይልም። ለአፍታ የጎንጥ እጅ ናፈቀኝ። ወላ ተከትሎ ደርሶብኝ በሆነና የፈራሁ ሲመስለው ሁሌም እንደሚያደርገው በዛ ሰፊ መዳፉ እጄን አፈፍ አድርጎ እጁ ውስጥ ቢደብቀው። «……. እኔ የት ሄጄ? …… ማን አባቱንስ እና ነው? » ቢለኝ። ሜላት ምንድነው ያደረግሽው?

የምጠብቀው እንዲህ ነበር። የሆነ ቀን እንዳየሁት የሆነ ፊልም። ጥቁር መኪና መጥቶ አጠገቤ ገጭ ብሎ ይቆምና ! በሩ ብርግድግድ ብሎ በተጠና ስልት ሲከፋፈት ፊታቸው የማይታዩ  መሳሪያ የታጠቁ ግባብዳ ሰዎች ከመኪናው ዱብ ዱብ ብለው ያስቀመጡትን የሆነ ሻንጣ ብድግ እንደማድረግ ብድግ አድርገውኝ እየጮህኩ እግሬ አየር ላይ ተንጠልጥሎ ስፈራገጥ ምንም ሳይመስላቸው ወደመኪናው ይወረውሩኝና ልክ እንደቅድሙ በተጠና መንገድ በሩን ድው ድው አድርገው ዘጋግተው ይዘውኝ ይሄዳሉ።

የሆነው እንዲህ ነው። እግሬን ብርክ ይዞት ጉልበቴን ደገፍ ብዬ ባጎነበስኩበት አንዲት ቆንጅዬ ጅንስ ሱሪ በቲሸርት ለብሳ አጭር ጥቁር ጃኬት የደረበች ወጣት ሴት ከጀርባዬ ጠራችኝ። «ሜላት!» ለሰላምታ እጇን ዘረጋችልኝ። እነሱማ ሰላም ሊሉኝ አይችሉም ብዬ እያሰብኩ እጄን ዘረጋሁ!!

«ዝግጁ ነሽ?» ስትለኝ ማሰቢያዬ ተዛባ! ለምኑ ነው የምዘጋጀው? ለመታገት ዝግጅት? <አዎ! እጄን ለካቴና በቅባት አሸት አሸት አድርጌ አዘጋጅቸዋለሁ። ድንገት እጃችሁ ካረፈብኝ ዱላ መቻያ ደንደን እንዲል ቆዳዬን ወጠርጠር አድርጌ አለማምጄላችኋለሁ….. > እንድላት ነው ተዘጋጀሽ የምትለኝ? እሷ ቀጠል አድርጋ ከፊቴ ወደቆመ ዘናጭ ነጭ መኪና እየጠቆመችኝ ፈገግታዋ የሆነ የተንኮል ዓይነት እየሆነ « …. ግርግር አንፈልግም አይደል?» ብላ አጭሩን ጃኬቷን ከፈት አድርጋ ሽጉጧን አሳየችኝ። ለስሙማ እኔምኮ ሽጉጤን ጎኔ ላይ ሽጬዋለሁ። ምን ላደርግበት እንደሆነ ያሰብኩት ባይኖርም ለዝህች በቆንጆ ፊቷ ለሸወደችኝ ልጅ ግን ሽጉጥ ሳይሆን የመዘዝኩት እጄን ነው ለሰላምታ የዘረጋሁት።

ወዳሳየችኝ መኪና ሄድኩ። እያገተችኝ ሳይሆን የሆነ በክብር እንግድነት የተጠራሁበት ቦታ ልታደርሰኝ ነው የሚመስለው። የኋላውን በር ከፍታ ያንን ተንኮለኛ ፈገግታዋን እያሳየችኝ እንድገባ ጋበዘችኝ። በአጠገባችን የሚያልፉ ሰዎችን <ኸረ በትኩረት ለአፍታ እዩኝ እየወሰዱኝ ነው!> ብል ደስ ባለኝ። ማንም ለአፍታ እንኳን ገልመጥ አድርጎ ያየኝ የለም። በየእለት ተእለት ውሏችን ልብ ያላልናቸው ስንቶች ይሆኑ ከአይናችን ስር ብዙ የሆኑት?

መኪና ውስጥ ከኋላ ታግቼ ባይሆን « ምን ሆኖ ነው እንዲህ የቆነጀው?» የምለው የሚመስለኝ ፈርጣማ ወንድ ተቀምጧል። እንደገባሁ ቀለበኝ ማለት ይቀላል። ፓንቴ ስር መግባት እስኪቀረው እንያንቀረቀበ ሲፈትሸኝ ልጅቷ ከፊት ወንበር ሆና ሽጉጧን አስተካክላ ትጠብቀቃለች። የምራቸውን ነው? እዝህች የክብሪት ቀፎ የምታክል መኪናቸው ውስጥ ከነሹፌሩ ለሶስት ከበውኝ ታጠቃናለች ብለው ነው ሽጉጡ?  ሽጉጤን ከፊት ለተቀመጠችው ሴት እንደመወርወር አድርጎ አቀብሏት በምትኩ የሆነ ጨርቅ ስትወረውርለት ነገረ እቅዴ ሁሉ ጎንጥ እንዳለው የጅል መሆኑ ገባኝ። የሰውየው መዋከብ ቶሎ የመጨረስ ውድድር ያለበት ነው የሚመስለው። በጨርቁ ዓይኔን ሲሸፍነው መኪናው መንቀሳቀስ ጀመረ። በዚያው ፍጥነት እጄ ላይ ካቴና አሰረ።

ለምን ያህል ደቂቃ እንደተጓዝን አላውቅም!! ወይ ከላይ ወይ ከታች እንዳያመልጠኝ ከሰውነቴ ጋር ግብ ግብ ላይ ነበርኩ። የእነርሱ ዝምታ ደግሞ ጭራሽ ያለሁት መኪና ውስጥ ሳይሆን ከሞት በኋላ የሰይጣን ፍርድ ዙፋን ስር ቀርቤ አስፈሪ ፍርድ ለምሳሌ እንደ < ለእሷ እሳቱ አስር እጥፍ ይጨመር!! ይሄማ ለሷ ሻወር መውሰጃዋ ነው!! ይንተክተክላት ውሃው እንጂ! > የሚል ፍርድ እየተጠባበቅኩ መሰለኝ። ከመኪናው ወርደን የበረበረኝ ሰውዬ ይመስለኛል ብብቴ ስር ገብቶ ጨምቆ ይዞኝ እየነዳኝ በእግር የሆነ ያህል እንደተጓዝን አይኔን የሸፈነኝ ጨርቅ ሲነሳ የተንጣለለ በውብ እቃዎች የተሞላ ሳሎን ራሴን አገኘሁት። ያሰረልኝ ሰውዬ ከእጄ ላይ ካቴናውን አወለቀው።

እንግድነት የሄድኩ ይመስል እንድቀመጥ ታዘዝኩ። ያ ሰውዬ በቪዲዮ ያወራሁት ሰውዬ እና አንዲት መሬቱን የነካ ጌጠኛ ቀይ ቀሚስ የለበሰች ሴት ተቀምጠዋል። ከእነርሱ በተጨማሪ ይዞኝ የገባው ሰውዬ እና ትንሽ ቁመቱ አጠር ያለ መሳሪያ የታጠቀ ሰውዬ ብቻ ናቸው ክፍሉ ውስጥ ያሉት። ሴትየዋ የጠቆመችኝ ከፊታቸው ያለ ሶፋ ላይ ለመቀመጥ ቂጤን ሳሾል

«ከመጨዋወታችን በፉት እንዳው ለመተማመኑ ….. » ብላ አጠገቤ ደርሳ የለበስኩትን ሹራብ ግልብ ስታደርገው ግራ ገባኝ እና መነጨቅኳት። የቆሙትን ጠባቂዎች (መሰሉኝ) ፊታቸውን እንዲያዞሩ በምልክት ስትሰጣቸው ሶፋው ላይ ያለው ሰውዬ እራቁቴን የማየት መብት እንዳለው ሁሉ ዝም አለችው። ከንግግሯ ምናልባት የምናወራውን የምቀዳበት ነገር ሰውነቴ ላይ ደብቄ እንደሆነ ገባኝ። በፓንት እና በጡት ማስያዣ ስቀር አይኑን ከሰውነቴ ላይ ለመንቀል ምንም ሀሳብ የሌለውን ሰውዬ እያየሁ መዋረድ አንገበገበኝ። ሴትየዋ ጡቴ ስር ገብታ ስታንቀረቅበኝ ጡቶቼን የምትመዝናቸው እንጂ የሆነ መቅጃ ያለችውን ነገር እየፈለገች አይመስልም። ጥርሴን ነክሼ ዋጥኩት። ሆነ ብላ
የምታደርግ ነው የሚመስለው። ጣቷ የእንትኔን ጫፍ እስኪነካው ድረስ እጇን ፓንቴ ውስጥ ስትሰድ እስኪያማት ድረስ የእጇን አልቦ ማሰሪያ ጨመደድኩት።

«ok ok » ብላ እጇን አወጣች። የያዝኳትን ስለቀው ቦታው ደም መስሏል። ፊቷ ላይ ያስታውቃል። ከመፈተሿ በላይ እኔን ማዋረዷ ተመችቷታል። እንድለብሰው ልብሴን ከመሬት አንስታ ወረወረችልኝ። ከሰውየው ጋር ተያይተው ያልገባኝን መልዕክት ተለዋወጡ። ይዤው የነበረውን ቦርሳ አንስታ አመሳቅላ በረበረችው።

«አላመንከኝም እንጄ ነግሬህ ነበር,» አለችው። ሰውየው ባለችው ነገር ሙሉ በሙሉ ያመነ አይመስልም።
«እሺ ሜላት!! የታሉ ቪዲዮዎቼ?» አለ
«ወንድሜን በአይኔ ሳላየው ምንም ነገር አልነግርህም!!» አልኩት ለመኮሳተር እና ያልፈራ ለመምሰል እየሞከርኩ።
«ሜላት ይሄ ኔትፍሊክስ ላይ ተጥደሽ ስታዪ የምትውዪው የሆሊውድ ፊልም አይደለም። አጉል ጀግና ጀግና አትጫወቺ!! የትም አትደርሺም!!» አለ ልጥጥ ብሎ እንደተቀመጠ። አልመለስኩለትም።
«እየሰማሽኝ አይደለም? ዛሬ የምጫወትበትን ጠጠር የምመርጠው እኔ ነኝ። ያልኩሽን ነው የምታደርጊው።» ብሎ አምባረቀ።
«ወንድሜን ካላየሁ ምንም የማደርገው ነገር የለም አልኩ እኮ!!» ብዬ ለመጮህ ሞከርኩ።
ለቆመው አጭሩ ጠባቂ ምልክት ነገር ሰጠው። የታመቀ ትንፋሼን በረዥሙ ለቀቅኩት። ኪዳን ሲገባ ምንም የተጎዳ ነገር ያለው አይመስልም። ሲያየኝ ፊቱ ላይ ከቃላት በላይ የሆነ ስቃይ አየሁበት።
«I am so sorry» አለኝ ገና ስንተያየኝ። አልከለከሉኝም! ሄጄ አቀፍኩት። አጥብቆ አቀፈኝ። «ይቅርታ ሜል!»

«መልሰው!!» ብሎ ጮኸ። አብሬው እንድቆይ ብለምንም ሊሰማኝ እንኳን ግድ አላለውም። ምንድነበር ያሰብኩት? ናፍቆትሽ እስኪወጣልሽ እንጠብቅሻለን ከወንድምሽ ጋር ትንሽ ተወያዩ እንዲሉኝ ነበር? የምርም እንዴት ያለ የቂል እቅድ ነው ያወጣሁት? ኪዳን ተመልሶ ሲሄድ የተሸነፍኩ መስዬ ላለመታየት ሞከርኩ። ሰውየው ወደእኔ አፈጠጠ።
«ሁሉንም ኮፒ እንዳመጣልህ አይደል ፍላጎትህ? በሰጠኸኝ አጭር ጊዜ ላመጣልህ አልችልም!! ተጨማሪ 24 ሰዓት ስጠኝ እና የምትፈልገውን በሙሉ እሰጥሃለሁ።» ስለው ያሳቃቸው ጉዳይ አልገባኝም ሁለቱም ከጣሪያ በላይ ሳቁ።

«ብዬህ ነበርኮ! በል ብሬን ወዲህ በል!» አለችው ሰትየዋ እጇን እየዘረጋች።
«እያወቅሽኝ ካላረጋገጥኩ መች አምናለሁ?» መለሰላት። እየሆነ ያለው ሙሉው ባይገባኝም እያላገጡብኝ እንደሆነ ገብቶኛል። ከኪሱ የሆኑ ብሮች ኖት አውጥቶ አቀበላት።
«ባንቺ ቤት አቃቂለሽኝ ሞተሻል!! ካንቺ ውጪ ማንም መረጃዎችሽን የት እንደምታስቀምጪ እንደማያውቅ ገምቻለሁ። እመቤትን ነበር የጠረጠርኩት እንደገባኝ እሷም የረዳችሽ ነገር የለም። አንቺም የት እንዳስቀመጥሽ እንዳታስታውሺ ትውስታሽ ላይመለስ ከድቶሻል። ንገሪኝ እስኪ ምን ልሁን ብዬ 24 ሰዓት ልጠብቅሽ?» ሲለኝ የበለጠ ጅልነት ተሰማኝ።
ባለፈው ከደበደቡኝ ጎረምሶች የተሻለ እነዚህ ሰዎች መረጃ ከፈለጉ በቀላሉ ማግኘት አይችሉም ብዬ እንዴት አሰብኩ? ምኗ ቂል ነበርኩ? አሁን ይገድሉኛል? እሺ ኪዳንንስ? ምንድነው ያደረግኩት?
በሩ ተከፍቶ የቅድሟ ሴት በሩ ላይ ላለው ጠባቂ የሆነ ነገር አንሾካሽኳ ወጣች። ጠባቂውም የሆነ ነገር ለሰውየው አንሾካሾከ። ሰውየው በጣም የተገረመ መሰለ።
«ያንቺው ጉድ ነው!» አላት ወደሴትየዋ እያየ። ሴትየዋ ግራ የተጋባች መሰለች። በጣም በመገረም ወደበሩ እያየች።
«ምን ልሁን ነው የሚለው አስገቡት እስኪ!»
ዓይኔ የሳተው ነገር ቢኖር ነው። ጆሮዬም እንደዛው? <የሷው ጉድ> ነው ያለው ወይስ <የአንቺው ጉድ> ነው ያለው? የእኔው ጉድ ጎንጥማ የሷው ጉድ ሊሆን አይችልም። ወይም ሌላ ጎንጥ ይሆናል እንጂ የእኔው ጎንጥማ አይሆንም!! በሩን አልፎ ሲገባ ቤቱ ነው የሚመስለው!! ልክ የእናት አባቱ ቤት እራት ሊበላ እንደመጣ ነገር ዘና ብሎ ከሶፋው ተሻግሮ ያለ ወንበር ሳብ አድርጎ ተቀመጠ።

እስከአሁን የነበረው ምኑም ያየኋቸውን ፊልሞች አይመስልም ነበር። ይሄ ግን ፊልም እንጂ እውን አይመስልም።

«ምን ትሰራለህ?» ብላ ሴትየዋ ጮኸች።
«ስራዬን ነዋ!!» አለ እንደማላገጥ ብሎ
ሆድቃዎቼ ቦታ የተቀያየሩ ነገር መሰለኝ። ሆዴ ውስጥ ተለዋወሰብኝ።

       ............... አልጨረስንም ...........

@wegoch
@wegoch
@paappii
" ብቸኝነት እንደዚህ ነው ጓዙን ጠቅልሎ ሲመጣብህ ዘመድ ባዳ አይልም ሁሉም በህብረት ያድሙብሀል
(አንድ አይነት አገፋፍ )"

(ካሊድ አቅሉ)

የሚዋጋ ብርድ መጠቋቆር በጀመረው ሰማይ ላይ ያንዣብባል ። ስር የሚሰድ ለስለስ አርጎ ገብቶ ማይወጣ በሽታ የሚተክል ።

" ስንት ሰዓት ተገተርኩ ? መመለሴ ነው በቃ!! " በንዴት ቤዝ በስልክ ውስጥ ያሰማችው የብሶት ድምፅ ነበር ። 

በለበስኩት ቅንጣቢ ቲሸርት ጨርቄን ማቄን ሳልል ከቤቴ ተስፈንጥሬ ወጣው።ለስለስ እያለ እያሳሳቀ ብርድ ከበበኝ መንገደኛው ሁላ ብርዱን መከላከያ ሹራብና ጃኬት እንዳንዱም ስከርቭ አልቀረውም ከስንት አንዱ ኮፍያ አርግዋል ። እጆቼን አነባብሪ እየተንሰፈሰፍኩ በፈጠነ እርምጃ እጓዛለው።   ባዶነት ጎበኘኝ መንገደኛው ባይኑ እንደዚህ መውጣቴ አጅቦት ባይኑ ገረፍ እያረገኝ ያልፍል ይበልጥ መነጠል ተሰማኝ ይበልጥ ተንሰፈሰፍኩ እንዴት ሰው መነጠልን ተጋሪ አንድ ሰው ያጣል?ብቸኝነት ሲተነተን በአካል ብቻ ሳይሆን በሀሳብም ከሰው መሀል መገለል ነው። ሁሉም ብርዱን ሽሽት ጨርቅ ውስጥ ሲሸሸግ ባዶነት የጎበኘው አይምሮዬን የት ልሸሽገው ?

በመገለል ደዌ እግሬ እርምጃዬን አፍጥኖ ቤዛ ፊት ጉብ አረገኝ ።ያኮረፈ ፊት ተቀበለኝ ከመገለል ወደ መገለል ነፍሴ ተሻገረች . . .  ለምን አረፈድክ ብሎ ፊትን ከማጥፋት እንዴት በዚህ ብርድ እንደዚህ ለብሰህ መጣህ አይቀድምም ?

ብቸኝነት እንደዚህ ነው ጓዙን ጠቅልሎ ሲመጣብህ ዘመድ ባዳ አይልም ። ሁሉም በህብረት ያድሙብሀል ። ( አንድ አይነት አገፋፍ )

@wegoch
@wegoch
@paappii
#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል አስራ ስምንት)
(ሜሪ ፈለቀ)

መቼም ሰው <ልቤ ዝቅ አለብኝ> የሚለው አሁን እኔ እንደሚሰማኝ ልቤ አቃፊዋን ለቃ የወጣች የሚመስል ስሜት ሲሰማ ነው የሚሆነው። የኔዋማ ዝቅ ከማለትዋም እነ ሳንባ ጉበትን <ዞር በሉ በናታችሁ> ብላ ገፋ ገፋ አድርጋ አንጀቴ ላይ ዛል ብላ ጋደም ያለች ይመስለኛል። አጅሬው እኔን ድዳና ሽባ አድርጎ በድንጋጤ አደንዝዞኝ እሱ እቴ በሙሉ አይኑ እንኳን አላየኝምኮ!!

ለመሆኑ ስሙስ የምር ጎንጥ ነው? የሚያወራው የሀገርኛ ለዛውስ ዘበኛ ለመምሰል ያስመሰለው ይሆን? ቅድም እንዴት ነበር ያወራው? ንፋስ ሲሆን ትከሻው ላይ ጣል የሚያደርጋት ፎጣውስ የትወናው አካል ትሆን? ዘበኛም ሆኖ አንዳንዴ ስንወጣ የሚለብሰውን ዓይነት ጅንስ በሸሚዝ ስለለበሰ የአለባበሱን ትወና መለየት ይቸግራል።

«ስራህንማ በአግባቡ ተወጣህ!» አለችው ሴትየዋ። ሙገሳ አይደለም! የሆነ ለበጣ ያለበት ነገር ነው! ቀጥላ የሆነ በእኔ ፊት ወይም በሰውየው ፊት መናገር ያልፈለገችውን ነገር ለብቻቸው እንዲያወሩ መሰለኝ። « ….. እኔ እና አንተ ብዙ የምናወራርደው ነገር አለ።» ብላ እጁን መንጨቅ አድርጋ ይዛው ልትሄድ ስትሞክር ከተቀመጠበት ሳይነሳ እጁን መነጨቃት። አስከትሎ ከእግሯ እስከ አናቷ በግልምጫ ካበጠራት በኋላ ራሱ ከተቀመጠበት ተነስቶ ቀድማው ከሳሎኑ እንድትወጣ ምልክት አሳያት። (እንደለመደው ነዳት ብል ይቀላል) በተጫማችው ሂል ጫማ እንደዝግዛግ ያለ አረማመድ እየረገጠች ሳሎኑን ለቃ ስትወጣ ተከትሏት እየተቆለለ ወጣ!! ከትውውቅ አልፈው መደነቋቋል ላይ የደረሱ ወዳጃማሞች መሆናቸውን ለማወቅ ምንም ሂሳብ አያስፈልግም!!

< ሄሎ!! እዚህ ነኝ! ሜላት! አስታወስከኝ? ከአንድ ቀን በፊት እመኚኝ ብለህ እንደወፍጮ ቤት እህል አየር ላይ ያንቀረቀብከኝ? አልታይህም?> ይላል ውስጤኮ አፌን ቃል ማን ያበድረው? ከሳሎኑ ከወጡ በኋላ የሚያወሩት ባይሰማኝም ጭቅጭቅ ላይ መሆናቸው ከድምፃቸው ያስታውቃል። ጎንጥ እንዲህ ይጮሃል እንዴ ሲያወራ? እኔ ንግግሩን ሳልሰማ ድምፁ እንዲህ ያስደነገጠኝ እሷ እዛች ሚጢጥዬ ፊቷ ላይ ሲጮህባት ወትሮም ያነሰች ፊቷ አለመትነኗ!!

የሁለቱ ሁኔታ ግራ የገባው ከመሰለው ሰውዬ ጋር ተፋጠን ሁለታችንም ከማይሰማው የሁለቱ ጭቅጭቅ ቃላት ለመልቀም ጆሯችንን አሹለን እንቃርማለን!! ፀጥ ያሉ መሰለ ወይም ድምፃቸው ለኛ መሰማቱን አቆመ።

«ለመሆኑ እኔ ማን እንደሆንኩ ታውቂያለሽ?» አለኝ ሰውየው በተፈጠረው ክፍተት። የሆነ ተራ ጥያቄ የጠየቀኝ አስመስዬ አፍንጫዬን ነፍቼ ለማለፍ ሞከርኩ።

«ጊዜ ግን ሲገርም!! በተሰቀለው!! ምንም ምንም አታስታውሺም?» ብሎ ሊገለፍጥ ዳዳው « መቼም ግፍሽ ነው!! በቁጥር እኮ አይደለም አንቺ የህዝብ ግፍ ነው ያለብሽ!! ሃሃሃሃ ሰውኮ የዘራውን ነው የሚያጭደው ሃሃሃ ስንቱን እንዳልከዳሽ የራስሽ ጭንቅላት ይክዳሽ? እረስታለች ሲሉኝ ማመን ያቃተኝ ቀጥ ብለሽ ስትመጪ ነው። ምንም የምታውቂው እና የምታስታውሺው ሳይኖር …… » ብሎ ሲጨርስ

«እኔ እንዳልረሳው አይጠፋህምሳ መቼም!» እያለ ገባ ጎንጥ!! ሴትየዋ ትንሽ ቀይ ፊቷ ሚጥሚጣ የተነፋበት ሰሃን መስሎ ተበሳጭታ ተከትላው ገባች።

«እሷ ትሄዳለች። ወንድምየው እኛጋ ይቆያል።» አለች በኮሳሳ ድምፅ ትዕዛዝም ሀሳብ ማቅረብም በመሰለ አነጋገር - ለሰውየው። ሰውየው ከተቀመጠበት ተነስቶ ሲደነፋ እና ሲጯጯሁ «ኪዳንን ትቼ አልሄድም!» ያልኩትን የሰማኝ የለም!! ጎንጥ አጠገቤ ደርሶ ቁጢጥ እንደማለት አለ እና

«እባክሽ እንዳታስቸግሪኝ (ይሄኛው ልመና ነገር ነበር) የምልሽን አድርጊ! ካለበለዚያ ያንቺንም የእኔንም የኪዳንንም ህይወት ነው እሳት ምትሰጅበት (ትዕዛዝ ነገር ሆነ) ለዛሬ! ለዝህች ደቂቃ ልታምኝኝ ይቻልሻል? (ልምምጥ ነገር ሆነ)» አልመለስኩለትም!! ሰውየውና ሴትየዋ በጥፍራቸው ቆመው ይጨቃጨቃሉ።

«ታምኚኛለሽ?» ሲል ግን በፍጥነት
«አላምንህም!!» አልኩት። ይህችን ለመተንፈስ ሰዓት እየጠበቅሁ ይመስል ተቅለብልቤ

«ሜላት እኔና አንቺ የምንነታረክበት ጊዜ የለንም! ስትፈልጊ አትመኚኝ ያልኩሽን ካልሰማሽ ሙት ነሽ!! (ይሄ ድብን ያለ ቁጣ ነው!!) እኔ እና አንቺ አሁን ወጥተን እንሄዳለን!! አንቺን እንጂ ኪዳንን አይፈልጉትም!! በምትወጅው ኪዳን ይሁንብሽ ለአንዴ እመኝኝማ! (እዚህጋ እኔን ማስረዳት የደከመው መሰለ) ኪዳን ምንም አይሆንም!! (ድምፁን ቀነስ አድርጎ) ኪስሽው ውስጥ አሁን እንዳታስታውቂ ! ኪዳን መልዕክት አኑሮልሻል!! ከዚህ ከወጣን በኋላ ታይዋለሽ!! አሁን እንሂድ? (ይሄ እባክሽ እንቢ እንዳትዪኝ የሚል ማባበል ነው።)።» ምላሴን ምን ያዘብኝ? እሺም እንቢም ማለት ጠፋኝ!! ሰዎቹ ጭቅጭቃቸውን ማቆማቸውን ያወቅኩት

« I knew it!! ወደሃት ነዋ!» ብላ እግሬ ስር ቁጢጥ ያለውን ጎንጥ በትንግርት እያየችው የሆነ ግኝት የተገለጠላት ዓይነት አስመስላ ስትጮህ ነው። ጎንጥ አቀማመጡን ገና አሁን ያስተዋለው ይመስል ተመንጭቆ ተነስቶ ክምር ተራራ አክሎ ተገተረ። ሴትየዋ አላቆመችም። እንደንቀትም፣ እንደ መገረምም ፣ እንደመናደድም …… እንደብዙ ነገር በሆነ ድምፅ እና እይታ « ጎንጥ ለዝህች? (በአይኗ አቅልላ የጤፍ ፍሬ አሳከለችኝ) ማን ያምናል? በምን አገኘችህ በናትህ?»

«አፍሽ ሲያልፍኮ አይታወቅሽም!! እረፊ ብያለሁ!» ብሎ ተቆጣ።

ቆይ እዚህጋ የትኛውን ሀሳብ አስቀድሜ የትኛውን አስከትዬ የቱን ምኑጋ ሰካክቼ ልከኛውን ምስል ላግኝ? ሰው ሀሳብ ይበዛበታል አይሉም በአንዴ ራሱን ጎንጥን የሚያካክል መአት ሀሳብ ወርውረውብኝ እዛ እንደተቀመጥኩ የሚዘነጉት? ኸረ ቆይ ጎንጥ ወዶኝ ነው የሚለውን ላስቀድም? ኸረ አይደለም! <ይህችን?> ብላ ምላሷ ላይ ያሟሸሸችኝ እኔ አስቀያሚ ነኝ እንዴ? አይደለም ኸረ ቆይ ጎንጥ ሴትየዋን ምን ቢላት ነው እኔን ይዞ እንዲሄድ የተስማማች? ኸረ ሌላው ደሞ እሱስ <ወድጃት አይደለም> ከማለት ይልቅ የሚደነፋው ወዶኝ ነበር ማለት ነው? አይ እነዚህ ሁሉ ይቅሩ እንዴት አምኜው ነው ኪዳንን ትቼው የምሄደው? ግን ምርጫስ አለኝ? ኸረ ኪዳን በምን ቅፅበት ነው መልዕክት ያስቀመጠልኝ? ምን ይሆን የሚለውስ? ደሞ ሌላ አለ እንጂ ቆይ ጎንጥ እኔን ቢወደኝ እሷ ምን እንዲህ ይንጣታል?

በአይኑ ከተቀመጥኩበት እንድነሳ ምልክት ሰጠኝ። በአይኑ አስነሳኝ። እጁን ሰጠኝ ወይም እጄን ተቀበለኝ እኔእንጃ ብቻ እጄን ያዘው እና ወደበሩ መራመድ ጀመረ። ጠባቂዎቹ ትዕዛዝ የሚጠብቁ ይመስላል ከበሩ አልተንቀሳቀሱም!! ሰውየው በአገጩ የሆነ ምልክት ሰጣቸው!! ከበሩ ገለል አሉ!! ሴትየዋ መናጥዋ በረታባት!!

«እመነኝ ጎኔ ይህችን አታልፋትም!! አስከፍልሃለሁ!! እመነኝ ትከፍላታለህ!!» አለች እየጮኸች። <ጎኔ> ብላ ነው ያቆላጰሰችው? ዛሬማ የሆነኛው ፊልም ተዋናይት ሆኛለሁ እንጂ እየሆነ ያለው እውን በእኔ ህይወት እየሆነ ያለ አይደለም!! እንዲህ አፍና ጭራው ያልተለየ እውነተኛ ህይወት ሊኖር አይችልም።
በሩን አልፈን እንደወጣን የቅድሟ ሴት ተቀበለችን። ስመጣ ያሰሩልኝን ጨርቅ ይዛ ስትቀርበኝ የያዘኝን እጁን ለቅቄ በጥያቄ አየሁት!! የታከትኩት መሰለ እና በቁጣ ጮኸ « እየገባሽ አይደለም አንቺን መምረጤ? ከዚህ በላይ ምን ባደርግ ነው የምታምኝኝ በይ? ያለፈውን ካላወቅኩ ነው? አንድም ሳይቀር አወጋሻለሁ! እዝህችው ቆመን 19 መቶ ብዬ እንዳወጋሽ አይደለማ ሀሳብሽ?» ቅድም ሴትየዋ ላይ እንደጮኸው ነው የጮኸው!! ጨርቁን እንድትሰጠው ለልጅቷ እጁን ሲዘረጋ ልጅቷ እንደማቅማማት አለች። ጮክ ብሎ ሲያፈጥባት የመወርወር ያህል እጁ ላይ ጣለችው። ከሁኔታዋ ከዚህ በፊት የሚተዋወቁ የምትፈራው ሰው መሆኑ ያስታውቃል። ምናልባት አለቃዋ ነበር? ዛሬማ የሆነ ፊልም ገፀ ባህሪ ሆኛለሁ።

ከሴትየዋ እጅ ተቀብሎ እሱ እያሰረልኝ እንደዛ እንዳልጮኸ ልስልስ ብሎ ነገር «መግቢያ መውጫቸውን እያየሽ እንድትሄጂ በጀ አይሉሽም!! ለዛሬ የምልሽን እሽ በይ በሞቴ?» አለ። ማደንዠዣ እንደወጉት በሽተኛ ፍዝዝ ድንግዝ አልኩ። ጨርቁን ካሰረልኝ በኋላ እጄን አጥብቆ ይዞ መራመድ ጀመረ። የምረግጠው ምን እንደሆነ ሳላውቅ እግሬን እያነሳሁ ተከተልኩት። መኪና ውስጥ ገባን!! ባላይም መኪናው ውስጥ ከእኔና ከእርሱ በተጨማሪ ያቺ እንደጥላ የምታጅበኝ ሴት እና ሹፌር እንዳሉ አውቂያለሁ። እኔእና እሱ መጓዝ ጀምረን የያዘኝ እጁ መያዝ ብቻ ሳይሆን መዳበስ ነገር ያደርገኛል። ልቤ የምን አጃቢ ናት አብራ የምትቀልጠው?  ትንፋሹ እንዳልተረጋጋ ያስታውቅበታል። አካሉም ይቅበጠበጣል። ከእርሱ ሁኔታ በመነሳት አሁንም እርግጠኛ የሆነ ማምለጥ አለማምለጤን ጠረጠርኩ። ቆይ እራሱ የሆነ ቦታ አግቶ ይዞኝ እየሄደ ቢሆንስ? እሱንስ እንዴት አመንኩት?

«ሴትየዋ ማናት? ምንህ ናት?» አልኩት  ከዛ ሁሉ አናቴን ከወጠረው ጥያቄ ይሄን ለምን እንዳስቀደምኩ አላውቅም!! በረዥሙ ተንፍሶ

«የልጄ እናት ናት!! ምሽቴ ነበረች» አላለኝም? ከዚህ በላይ ከእውነታ የራቀ ቀን አለ እሺ?
«እ?» የምትለዋ ፊደል ከየትኛው ቃል አምልጣ በአፌ እንደሾለከች አላውቅም!! ብቻ ለምሳሌ <እንደ> ከሚለው ቃል ቢሆን ተጣልተው የፈረጠጠችው ……  <ን> ን እና <ደ>ን ትርጉም አልባ አድርጋ ጥላቸው ብቻዋን ስትፈረጥጥ …… ተንደርድራ አምልጣ መሆኑ የሚያስታውቀው አፌ ፊደሏን ሊያስወጣ እንደተበረገደ አልተከደነም!!

«ባሏ ነው!!» አለ አክሎ። ሰውየውን መሆኑ ገባኝ ግን ጥንቅላቴ ውስጥ ሀሳቦቹ ተጠላለፉ ነገር። የሰውየው የአሁን ሚስት የጎንጥ የድሮ ሚስት የልጁ እናት! ከዛ ግን ዛሬም ውሉን ያልጨበጥኩትን ስራ (እገታ እና ስለላ ማለት ይቀላል) አብረው የሚሰሩ? ነው ወይስ ያልገባኝ ነገር አለ? ይሄ ቢገባኝም እንኳን በ2 ወር ከአስር ቀኔ እንደምንም ያጠራቀምኩትን አዲስ ትውስታ ሁላ ነው የሚያጠፋብኝ።


  መኪናው ቆመ። ከአይኔ ላይ ጨርቁ ሲነሳ መኪናዋ  የቆመችው ከከተማ የራቀ ጭር ያለ ቦታ መሆኑን አስተዋልኩ። በቅርብ ርቀት የእኔ መኪና ቆማለች። እዚህ ደቂቃ ላይ ማመንም መጠራጠርም አይደለም የተሰማኝ። ምንም ነው!! ጎንጥ ግን የሆነ ነገር እንዳላማረው ያስታውቃል። ዙሪያ ገባውን ከቃኘ በኋላ እስከአሁንም ያልለቀቀውን እጄን አፈፍ አድርጎ ወደመኪናችን እየሄድን።

«ከአይናችን ተሰወሩ ማለት የሉም ማለት አደለም!! አሁን አንቺን ማጥፋት ቀላሉ መፍትሄያቸው ስለሆነ ማስታወስ ችለሽ ከምትፈጃቸው በፊት የአቅማቸውን ይሞክራሉ።» እያለኝ እኔን ባልያዘው እጁ ወገቡ ላይ ያለ ሽጉጡን ጨብጦ ወደኋላ እና ወደጎን እየተገለማመጠ መሬቱን በረጃጅም እርምጃው ይመትረው ጀመር። ያደረሰችን መኪና ከኛ በተቃራኒ አቅጣጫ ሄደች። ከአይናችን ስትሰወር መኪናችንጋ ደርሰናል። ስንቀርብ የመኪናችን ጎማ መተኛቱን አይቶ ጎንጥ ጎማውን በእግሩ ሲነርተው አየሁ።

ከየት መጣ ሳይባል አንድ ፒካፕ መኪና እየበረረ ፒስታውን መንገድ አቧራ እያጨሰ መጣ። እየሆነ ያለው ነገር ከመፈጣጠኑ የተነሳ ውዥብርብር አለብኝ። በቅፅበት የተኩስ ድምፅ ተሰማ!! ማናቸው ቀድመው እንደተኮሱ እንኳን አላውቅም ምክንያቱም ጎንጥም እየተኮሰ ነው። በየትኛው ቅፅበት ሽጉጡን እንዳወጣ እንኳን አላየሁም!! የትኛው ቅፅበት ላይ እጄን እንደለቀቀኝም አላውቅም! ማየት እስኪያቅተን የበዛ አቧራ እያቦነነ እና እየተኮሰ አልፎን የሄደው መኪና በሄደበት ፍጥነት አዙሮ ተመልሶ ወደእኛ ሲመጣ በአንድ እጁ የመኪናውን በር ከፍቶ

«ግቢ!!  ገብተሽ ወደታች ዝቅ በይ!!!! ከወለሉ ተኝ!» ብሎ ጮኸ! ምንድነው እግሬን ከመሬቱ የሰፋው? እኔ የድርጊቱ አካል ያልሆንኩ ይመስል ዓይኔ አንዴ ጎንጥን አንዴ በፍጥነት እየመጣ ያለውን መኪና ያያል። በሩን ከፍቶበት በነበረው እጁ ከጎኑ ወደጀርባው ገፈተረኝ። አፈሰኝ ማለት ይገልፀዋል። እኔንም ራሱን መከላከል የማይችልበት አጣብቂኝ ውስጥ እንደከተትኩት ገብቶኛል ግን በምን በኩል ሰውነቴን ልዘዘው? ዓይኔ ስር ፊልም እየተሰራ ያለ ዓይነት ስሜት ነው ያለው። እኔን ወደጀርባው በደበቀኝ ቅፅበት ለጊዜው ምኑጋ እንደሆነ ያልለየሁት ቦታ እሱ ተመታ። እኔ የተመታሁ ዓይነት መሰለኝ። ጭንቅላቴ ለቅፅበት ያን ቦታ ትቶ ሄደ። ቅፅበት ናት ግን ድንዝዝዝ  ያለ..... ብዥዥኅኅ ያለ ቅፅበት .... ጎንጥ የተመታበትን ቦታ በአንድ እጁ ይዞ

«ወዳጄ ይደርሳል። ከእርሱ ጋር ሂጂ!! እቤት እንዳትሄጅ!! » ይለኛል ጮክ ብሎ!!

«ትቼህማ አልሄድም!!» ዓይኔ ከፒካፑ መኪና ጀርባ እየመጣ ያለ መኪና በአቧራው ውስጥ ቢያይም ጭንቅላቴ ግን እዛው ገትሮኝ ሄዷል። አንድ ጥይት በጎኔ አልፎ መኪናውን ደነቆለው:: ሰውነቴ አይታዘዝም!! ደንዝዟል::

"ዝቅ በይ!" እያለ ይጮሃል ጎንጥ በከፊል ዘወር ሲል ከጎኑ የሚፈስ ደሙን እያየሁ ሀሳቤ ሄደ .... እዛ ቀን ላይ!!

ጥይቱ የተከፈተ የመኪናዬን መስኮት አልፎ ጡቴ ስር ሲመታኝ!! የመጀመሪያውን ህመም በቅጡ አስተናግጄ ሳልጨርስ ሁለተኛው ተመሳሳይ ቦታ ሲያገኘኝ። - የተመታሁ ቀን!! አንድ በአንድ ቁልጭ ብሎ ስዕሉ ጭንቅላቴ ውስጥ መጣ!! የማደርገው እና የማስበው በአንድ እኩል ቅፅበት ነበር። እጄን ማዘዜን አላስታውስም ብቻ ከጎንጥ እጅ ላይ ሽጉጡን እንደቀማው አውቃለሁ። ክፍቱን በተተወው የመኪና በር ግማሽ ሰውነቴን ከልዬ ሳደርገው የኖርኩት ልምዴ መሆኑን እርግጠኛ የሆንኩበትን ድርጊት እከውናለሁ። ከኋላ የመጣው መኪና በእኛና በፒካፑ መሃል ገብቶ ቆመ።

« ሂጅ እኮ አልኩ!!» ብሎ አምባረቀብኝ። በእጁ ጎኑን ደግፎ መሬቱ ላይ ተቀምጦ የመኪናውን ጎማ እንደተደገፈ።

«ደፋር እየሸሸ አይሞትም! እየተዋጋ እንጂ!» ስለው በህመሙ መሃል በስቃይ የታጀበ ፈገግታ አሳየኝ። ትውስታዬ ሳይከዳኝ በፊት አዘውትሬ የምለው አባባል ስለነበር ገባው። ጭንቀቱ የቀለለው መሰለ እና ህመሙን ማድመጥ ጀመረ። ፒካፕዋ መኪና ከአይኔ ራቀች። ወዳጄ ነው ያለው ሰውም ከመኪናው ወርዶ ወደኛ መጣ!! ሁለት ቦታ ነው የተመታው። አንዱ ከትከሻው ዝቅ ብሎ ሌላኛው ጎኑ ላይ የጎድን አጥንቶቹ መሃል ……. የለበስኩትን ሹራብ አውልቄ የሚንዥቀዥቅ ደሙን ለማቆም ከአንዱ ቁስል ወደ አንዱ እላለሁ።

« ሁሉንም?» ይለኛል አይኑን ላለመክደን እየታገለ።
« ምኑን ነው ሁሉንም?»
«ያስታወሽው?»
«መሰለኝ!!» አልኩት። ሁሉንም ላስታውስ የጎደለ ይኑረው በምን አውቃለሁ?

..............   አልጨረስንም!! ...................

@wegoch
@wegoch
@paappii
2024/09/22 06:42:17
Back to Top
HTML Embed Code: