Telegram Web Link
ቃለመጠይቁ___

ጥያቄ: ሀገሪቷ ዳግም ኢጣሊያንን ያሸነፈችው መቼ ነው?

መልስ: ትግሉ ለአምስት አመታት እየተደረገ ቢቆይም በ1933 ዓ.ም. በድል ተደምድሟል።

ጥያቄ: በእዚህ ጦርነት ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ ሰዎችን ስም ዝርዝር ጥቀስ?

መልስ: በሂደቱ ውስጥ በርካታ ሰዎች አስተዋጽኦ አድርገዋል። ስም መዘርዘር ከጀመርኩ አንዱን አንግሶ ሌላውን አንኳስሶ ይሆንብኛል።

ጥያቄ: ሙስና የሀገሪቱ ዋነኛ ጠላት ነው ብለህ ታስባለህ?

መልስ: ይሄንን ጉዳይ እያጣራ ያለ መንግስት ያቋቋመው ኮሚቴ አለ። ኮሚቴው የሚያወጣውን ሪፖርት ካየሁ በኋላ መልስ ልሰጥበት እችላለሁ።

ቃለመጠይቅ አድራጊዎቹ የሥራ አመልካቹ በሰጠው መልስ እጅግ በመርካትና በመደነቅ ውጤቱን ደጅ ሆኖ እንዲጠባበቅ እንዲሁም ለሌሎቹ የሥራ አመልካቾች ጥያቄዎቹን እንዳይነግራቸው አስጠንቅቀው አሰናበቱት።

••••

ወጣቱ የሥራ ተወዳዳሪ ከክፍሉ እንደወጣ ከእርሱ ቀጥሎ የሚገባው አመልካች ምን ምን ጥያቄ እንዳቀረቡለት እንዲነግረው ይነዘንዘው ጀመር። ወጣቱም "ለቃለመጠይቅ አድራጊዎቹ ጥያቄውን ለሌላ አመልካች እንደማልናገር ቃል ገብቻለሁ።'" ሲል ይመልሳል።

ሌላኛው ተወዳዳሪ ጥቂት አሰብ ካደረገ በኋላ "እሺ መልሶቹን ነገረኝ?!" ብሎ ይጠይቀዋል።

ወጣቱም ቃለመጠይቅ አቅራቢዎች "ጥያቄዎቹን ለማንም እንዳትናገር!" ብቻ ብለው እንዳስጠነቀቁት በማስታወስ "መልሶቹን አትንገር አላሉኝም!" ብሎ ለእራሱ ካወራ በኋላ የመለሳቸውን ሶስት መልሶች ለሌላኛው አመልካች ይነግረዋል። የተነገረውም አመልካች መልሶቹን በልቦናው መዘገበ።

•••

ከጥቂት ደቂቃ በኋላ ሁለተኛው አመልካች ለቃለመጠይቁ ወደ ውስጥ ተጠርቶ ገባ።

ጥያቄ: መቼ ነው የተወለድከው?

መልስ: ትግሉ ለአምስት አመታት እየተደረገ ቢቆይም በ1933 ዓ.ም. በድል ተጠናቅቋል።

ቃለመጠይቅ አድራጊዎች በመልሱ እንደተደናገሩ ወደ ሁለተኛው ጥያቄ ይሄዳሉ...

ጥያቄ: የአባትህ ስም ማን ይባላል?

ሙልስ: በሂደቱ ውስጥ በርካታ ሰዎች አስተዋጽኦ አድርገዋል። ስም መዘርዘር ከጀመርኩ አንዱን አንግሶ ሌላውን አንኳስሶ ይሆንብኛል።

ቃለመጠይቅ አድራጊዎቹ ግራ ተጋብተው..

"ያምሀል እንዴ ሰውዬ?!"

"ይሄንን ጉዳይ እያጣራ ያለ መንግስት ያቋቋመው ኮሚቴ አለ። ኮሚቴው የሚያወጣውን ሪፖርት ካየሁ በኋላ መልስ ልሰጥበት እችላለሁ!"
••••

ምንጭ: ድረገጽ


@wegoch
@wegoch
@paappii
ይሉኝታ(ክፍል 1)


  እግዜሩ ያለ የሌለ አቅሙን ሙጥጥ አድርጎ የሰራውን ይሉኝታ ሁሉ የሆነ ጊዜ ላይ መሸከም ከብዶት ሳለ ወደ ቀራንዮ ጫፍ መስቀሉን ሲጎትት ቀረብ ብሎ እንዳገዘው ምስኪን እኔም ጠጋ ብዬ"አባት ሆይ! ይህን ሁሉ ይሉኝታ ብቻህን?ባይሆን ትንሽ ላግዝህ !"ብዬ ያንን ለምድር ለሰማይ የከበደ ይሉኝታ ተቀበልኩት።እሱም በይሉኝታ መቅረቤን አይቶ "ላለው ይጨመርለታል"በሚለው መርህ በእገዛ ሰበብ የተቀበልኩትን ይሉኝታ መልሶ ሳይወስድልኝ ቀረ።እነሆ እኔም ከዛ ወዲህ ትልቅ ትንሹ  ሲያሻው እንደ ስጋጃ እየረገጠ፣ሲፈልግ እንደማስቲካ እያላመጠ፣ባስ ካለም እንደ እንቧይ እያፈረጠ በይሉኝታዬ እኔው ላይ ዳንኪራውን ይመታል።

  "ልጅ ደስታ!እስቲ ና ወዲህ" ይሉኛል እማ አልጣሽ ከመንገዱ ጫፍ ወገባቸውን ይዘው ይቆሙና።

  እማ አልጣሽን ሳያቸው አስማተኛ አሮጊት ይመስሉኛል።በፈገግታቸው ተሸፍኖ ያለውን ከባድ ቁጣ ከእግዚአብሔር በላይ ሳልፈራው አልቀርም።እንደው አንዲት ነገር አዝዘውኝ እምቢ ብላቸው  ፈገግ ያለ ገፃቸውን በቅፅበት ክስክስ ያደርጉና በቅርባቸው ያለ ጭራሮ ቢጤ አንስተው ድግምት ነገር እያነበነቡ መሬቱን ጫር ጫር ቢያደርጉት ሽንቴን ልሸና ምናምኔን አውጥቼ ባንከፈረርኩበት እንደ እንጨት አድርቀው የሚያስቀሩኝ ይመስለኛል።ወይ ስፈራቸው!🙆

  "አቤት እማ አልጣሽ" እላለሁ አጠገባቸው ስደርስ።

"ደስታየነህ...እንደው መቸም አንዴ ሲፈጥርህ የአሮጅትና የሽማግሌ መጫወቻ ሁን ብሎሀል...አንተም ጣድቅ ነህ መቸም አልታዘዝም አትልም...እንደው እሱ መድሀኔዓለም ምቀኛህን ውጋት ይዘዝበት!"

"አሜን እማማ"

"እንደው ያችን እላይ መንደር ያለችዋን አትጠገብን አወቅሀትም አይደል?"

"እትየ አትጠገብ የጋሽ ባህሩን ባለቤት አይደል?"

"እ...የባህሩ ምሽት!ሰልስትና እለታ ቸግሮኝ 50 ሳህኔ ማሽላ ተበድሬአት ነበር...አሁን የሻለቃ(ሻለቃ ማለት በደርግ ጊዜ በውትድርና ያገለግል የነበረ ባለቤታቸው ነው።)  ጡረታ ሲመጣ ሸምቸ መግባቴ ነው...ንስማ አድርሰህላት ና ጀታየነህ እመርቅሀለሁ"አሉኝ እግራቸው ስር በማዳበሪያ ታስሮ ወደተቀመጠው እህል እያዩ።የእትዬ አትጠገብን ቤት ርቀት ሳስብ ማዳበሪያው ገና ሳልሸከመው ደከመኝ።በመንገዴ የማገኛት ክፉ አቀበት ከጦሳ ተራራ ገዝፋ ብትታየኝም 'እምቢ' ግን አልልም።ይሉኝታዬን ለማን ሸጬው?

  እንደፈረደብኝ ያንን በግምት 65 ኪሎ የሚሆን ማዳበሪያ ተሸከምኩትና መንገዴን ጀመርኩ።እትየ አልጣሽ ከሁዋላዬ ሲመርቁኝ አልፎ አልፎም በሞኝነቴ ሙድ ቢጤ ሲይዙብኝ ይሰማኛል።

"ተባረክ ደስታየነህ ብሩክ ሁን!አሁን የማን ልጅ እሽ ብሎ ይታዘዛል በዚህ ዘመን?እድሜ ይስጥህ!ወገብህን ተውልቃት፣እጅህን ተቁርጥማት ይሰውርህ!"ይሉና ደሞ ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው

"አይይይ እንደው መድሃኔዓለም!እንደው እንዲህ ማንም የሚጭነው አህያ ሆኖ ይቅር!ኧረ አህያስ ሲበዛባት ትለግማለች..." ሲሉ ከነሸክሜ ዞር ስል እንደገና ድምፃቸውን ሞቅ ያደርጉና

"እንጀራ ይውጣልህ ደስታየነህ!ምቀኛህን እግሩን ያልምሸው የኔ ዓለም!ውለህ ግባልኝ ክፉ አይንካህ!" ይሉኛል።

ይቀጥላል

ማዕዶት ያየህ

17/07/2015 ዓ.ም.

@wegoch
@wegoch
@paappii
ይሉኝታ(ክፍል 2)

  ያገኘኝ ሁሉ ሲልከኝና ሲያዘኝ ውዬ የዛለ ሰውነቴን እየጎተትኩ ቤቴ እገባለሁ።እናቴ የቡና እቃዎቿን እያቀራረበች በመሀል ቀና እያለች ስታስተውለኝ ትቆይና

"አዋጥተው እንደገዙት መጋዣ ሲጭኑህ ይውላሉ አይደል?እንደው እምቢ አልፈጠረብህም አቡሽ?እምቢ አትልም?"

"ይረግሙኛል ብዬ ነውኮ"

"ኤዲያ!የረገሙህስ እንደው?አንድ ሳህን  ጤፍ ይገዙልህ መሰለህ?አዬ አለመታደል!እንዲህ እብን ሆነህ ትቀር?አድገሀልኮ ደስታ!18 ሞላህኮ!ልጅ አትባል ከንግዲህ"
ስትለኝ በመሀል አንድ ድምፅ አቋረጣት

"እንዴት ውላችሁዋል እናንተ?"እያሉ ወደውስጥ ዘለቁ እትየ አትጠገብ።እኚህን ሴትዮ ሳያቸው ያጥወለውለኛል።በነገር ሰው ሲወጉ ወደርም የላቸው።በቀደም ከመሸ ተልኬ ስወጣ ከማህሌት(የሰፈሬ ልጅ) ጋር ሱቅ ተገናኘንና የሆነ ያልሆነውን እያወራን ስንራመድ እትየ አትጠገብ በዛ ረጅም ቁመታቸው ሀውልት መስለው ከፊትለፊታችን ተገነጨሩ።ማህሌት ትከሻ ላይ ጣል ያረኩትን እጄን በፍጥነት አውርጄ ሰላምታ አቀረብኩላቸው።በውሉ ያልተሰማኝን ነገር አልጎምጉመው ሄዱ።በነጋታው ቤታችን መጡና

"እንዴት ውላችሁዋል ቤቶች?"አሉ በጎንዮሽ እያገረመረሙኝ።ወዲያው ወደኔ ዘወር አሉና

"ደስታ...ምነዋ ዛሬስ የጋሽ አለሙ ልጅ የት ሄዳ ነዋ?"አሉኝ።በአስማት እንዳደረቁኝ ሁላ ቀጥ ብዬ ቀረሁ።አባቴ

"ኧ?ደሞ የጋሽ አለሙ ልጅ እዚህ ምን ታረጋለች ?" ጥያቄአዊ አስተያየቱን እያነጣጠረብኝ።

"አብረው አያጠኑም እንዴት?ትናንት እዚህ አምሽታ ስትወጣ ያየሁዋት መስሎኝ"ብለው እርርርፍ!ምን ያልተመኘሁላቸው እርግማን አለ?ሙሴ በበትሩ ለድድ ሩብ ጉዳይ የሆነ ጥርሳቸውን ቢያረግፈው ደስታዬ! ኢያሱ ያቆማት ፀሀይ እንትናቸውን ለምች ትስጠው!ሌላ ክፉ አልመኝም!

"ኧረ ማታኮ ሱቅ ተገናኝተን እየሸኘሁዋት ነው ያዩን እዚህ አላመሸችም"አልኩኝ እየተርበተበትኩ።

እናቴ 'ለዚህም ደርሰሀላ?!'አይነት አስተያየት አየችኝ።እየተጎተቱ መጥተው የነገር መርዛቸውን አርከፍክፈውት ሄዱ።ከዛ ወዲህ ቤታችን ሲመጡ በጤና አይመስለኝም።እስኪወጡ ሱባኤ እይዛለሁ።ዛሬ ደግሞ ምን ሊሉኝ ነው እያልኩ ስብሰለሰል

"ደስታየ...ነገ ትምህርት አለህ?"አሉኝ።

ይቀጥላል

ማዕዶት ያየህ(ዘማርቆስ)
(gize_yayeh)

@wegoch
@wegoch
@paappii
ጠላ እየጠጣን ከጓደኞቼ ጋ ተሰባስበን እየቀደድን ሳለ ፦

ምድር ላይ የትኛውን ገጠመኝህን በይበልጥ ትወዳዋለህ የሚል ቀደዳ ጀመርን

ፍሬንድ ቀጠለ

"አንድ እለት እሁድ ጠዋት እናቴ ቡና እየጠጣች ፣ እየመከረችኝ ፣ እየመረቀችኝ ፣ እየሰደበችኝ ሳለ

በጣምምም ደስስ የሚልሽ ምን ብታገኝ ነው  አልኳት  አጠያየቄ ድንገት ነበር

ላሊበላ ፣  አክሱም ጽዮን ፣ ውቅሮ ማርያም ካዲ ብሄድ ደስ ይለኛል አለቺኝ

ፊቷ ላይ ያለው ምኞት የደስታ ዳር ይመስል ነበር።  ። በነጋታው ስጣደፍ ሄጄ ቢሮ አንድ መቶ ሺ ብር  ተበደርኩ ፍቃድ ወሰድኩ

ሎተሪ ደረሰኝ ብያት  ላሊበላ ፣  አክሱም ጽዮን ፣ ውቅሮ ማርያም ካዲ ወሰድኳት   ደስስ አላት ፀለየች  ፣ ለነዲያን መፀወተች ፣ እጄን ይዛ መረቀቺኝ ። 

ከዛ ከተመለስን በኋላ ሶስት ወርም አልቆየች ትንሽ አሞት ሞተችብኝ። ሳለቅስ ፣ ሳዝን ያፅናናኝ እና ያበረታኝ ህልሟን ማሳከቴ ነበር

ቀጠለ ሌላ ፍሬንድ ፦

"አንድ ቀን ክላስ ቀጥቼ ዩኒፎርሜን እንደለበስኩ  ጠላ ቤት ደቅ ብዬ አባቴ ከጓደኞቹ ጋር  ከች አለ ሳየው ስካሬ ጠፋ ።

ልጄ ነው ብሎ ለፍሬንዶቹ  አስዋወቀኝ ። ሃይለኛ ስለነበር እዛው ካልገደልኩ ይላል ብዬ ነበር። ምንም አላለኝም ። እንደውም የጠጣሁበትን ከነ ፍሬንዶቼ ከፈለልኝ ። ቀድሜው ወጣሁ ፦

አላመንኩትም የሚገድለኝን አገዳደል እያሰብኩ  ስፈራ ስቸር እቤት አምሽቼ ገባሁ ። እሱ ምንም አላለኝም ።

በሳምንቱ "ጋሻው ዛሬ ትምህርት የለህም አይደል "

"አዎ"
"በቃ ዛሬ አብረን እንዋል አለኝ" እሺ ብዬው የሚሰራበት
አብረን ሄድን

ውሎውን አዋለኝ ። የሆነ ህንፃ ይጠብቃል ፣ ህንፃው ጋ የሚቆም መኪና ይጠብቃል ፣ መኪና ያጥባል ።

የጠበቀበትን እና ያጠበበትን  ብር እንዲሰጡት ደጅ ይጠናል ፤ ትንሹም ትልቁም ይጠራዋል ፣ ያዙታል ያን ቀን አባቴ በጣም አሳዘነኝ

ከፊቱ ገሸሽ ብዬ አለቀስኩ

እንዴት እንደሚያሳድገኝ ያኔ ነው የገባኝ ። ምን እያለ እንደመከረኝ ፣ በእኔ ጉዳይ ለምን እንደሚናደድ ገባኝ

የዛ ቀን ህይወቴ ተቀየረ ።

ሌላ ፍሬንድ ቀጠለ ፦

"አንድ ቀን  እቃ ጠፍቶኝ ቤታችንን ሳምሰው
የታናሽ እህቴ ዲያሪ አገኘሁት በማላውቀው ምክንያት የማስሰውን ነገር ትቼ ደቅ ብዬ ማንበብ ስጀምር ።

ጥጋቤ ፣ ድፍረቴ እልሄ ተነፈሰ ። የግሩፕ ጠብ አጓጉል ውሎዬ ጣጣ  ለመጀመሪያ ጊዜ ገባኝ። ለመጀመሪያ ጊዜ መፍራት ጀመርኩ ፤ ለቤተሰባችን ምን ያህል እንደማስፈልግ ማስታወሻዋ ነገረኝ" 

ለካ አንዳንድ ቀን ብቻውን ዘመን  ያህላል !!

   by Adhanom Mitiku

@wegoch
@wegoch
@paappii
ወግ ብቻ pinned «ጠላ እየጠጣን ከጓደኞቼ ጋ ተሰባስበን እየቀደድን ሳለ ፦ ምድር ላይ የትኛውን ገጠመኝህን በይበልጥ ትወዳዋለህ የሚል ቀደዳ ጀመርን ፍሬንድ ቀጠለ "አንድ እለት እሁድ ጠዋት እናቴ ቡና እየጠጣች ፣ እየመከረችኝ ፣ እየመረቀችኝ ፣ እየሰደበችኝ ሳለ በጣምምም ደስስ የሚልሽ ምን ብታገኝ ነው  አልኳት  አጠያየቄ ድንገት ነበር ላሊበላ ፣  አክሱም ጽዮን ፣ ውቅሮ ማርያም ካዲ ብሄድ ደስ ይለኛል አለቺኝ…»
የምወድደው አለቃዬን ዛሬ አገኘሁት፣ ከዓመታት በኋላ። ያለፈውን ጊዜ አንስተን እንደ አዲስ ተሳሳቅን። በተለይ የሚከተለውን ገጠመኜን።
*
ባንክ ተቀጥሬ አመት ያህል እንደሆነኝ አንድ እሁድ እለት ከጓደኞቼ ጋር ኳስ ለማየት ከቤት ወጣን። ይሁንና ኳስ እያየን ድራፍት እየጠጣን የነበርን ጎረምሶች ባላሰብነው ሁኔታ በከተማው የሚገኙ አንድ ባለሀብት ባስወረዱልን ውስኪ እስከ እኩለ ሌሊት ስንራጭ አመሸን።

ጠዋት ላይ አንድ ጓደኞዬ ቤት ስነቃ ፣ እራሴን መሸከም አቅቶኛል። ቤቱ በመጠጥ ሽታ ተሞልቷል። በእርግጠኝነት በእዚህ መልኩ ሥራ መሄድ እንደማልችል ስለገባኝ ወደ አለቃዬ ስልክ ደውዬ...

"ዘመድ ስለሞተ ለመቅበር ወደ ገጠር እየሄድኩ ስለሆነ ፍቃድ ፈልጌ ነበር..." ስል ፈቃድ ጠየቅኩ።

ተፈቀደልኝ።

መሀል ላይ ሌላ መስሪያ ቤት የሚሰራ ጓደኛዬም ከእንቅልፉ ነቅቶ ወደ ቢሮው ደውሎ ለቅሶ ገጥሞኛል በማለት ሥራ ካስፈቀደ በኋላ የእኔን ጠየቀኝ።

"እንዲህ ሀንጎቨር ሳይለቅቀኝ ሥራ ገብቼማ የመጠጥ ሽታ ስጋብዛቸው አልውልም። እኔም አለቃዬ ጋ ደውዬ ዘመድ ሞቶብኛል ብዬ ዋሸሁ። ጌታ ይቅር ይበለኝ!" አልኩት።

"እኔማ አሁን ላይ ዘመዶቼን በሙሉ ጨርሼ በጎረቤት ሞት ምናምን ማስፈቀድ ጀምሬአለሁ" አለኝ። ተሳሳቅን።

ይሁንና እየተሳሳቅን ሰዐት ለማየት ስልኬን ሳነሳ ሳላውቅ ነክቼው ኖሮ አለቃዬ ጋ ደውሎ እየቆጠረ አገኘሁት። በእርግጠኝነት ንግግራችንን ሰምቷል። ቆሌዬ ተገፈፈ፣ መሬት ተከፍታ እንድትውጠኝ ተመኘሁ። ነግቶ አለቃዬን እንዴት ፊቱን እንደማየው ሲጨንቀኝ ዋለ፣ ማታም በሐሳብ ስገላበጥ፣ እንቅልፍ ባይኔ ሳይዞር ነጋ።

በማግስቱ ጭንቀት እየተጫጫነኝ፣ ልቤ እየደለቀ፣ አንገቴን ደፍቼ ወደ ምሰራበት ባንክ ሄድኩ። አለቃዬ እንደወትሮው በጠዋት ቢሮ ገብቷል። በጭንቀት እንደተዋጥኩ ፊቴን ከስክሼ ይቅርታ ለመጠይቅ ወደ እርሱ ሄድኩ።

ልክ እንዳየኝ ፊቱ ከንዴት ይልቅ በፈገግታ እንደተሞላ "ቀብር ደረስክ?!" ሲል ጠየቀኝ። ዝም አልኩ። ከፊቴ ላይ መሳቀቄን አንብቦ ነው መሰለ የእኔን ምላሽ ሳይጠብቅ...

"አይዞህ! አትጨነቅ። እኔም የሆነ ጊዜ ላይ እንዳንተው ጎረምሳ ነበርኩ። እረዳለሁ። ሌላ ጊዜ እንዳትዋሸኝ። አሁን ወደ ሥራህ ሂድ" አለኝ።
***

@wegoch
@wegoch
@paappii
በዚህ ዘመን ሰው ሆድ እንዲብሰው እንደማድረግ ቀላል ነገር የለም ። ሰዉ እንዳለ ስስ ሆኗል ። ቀኑ እንዲጨረብ ትንሽ ምክንያት ይበቃዋል ።

አጠገብህ ያለውን ስራ ፈት በብሄርህ ምክንያት ነው ስራ ያላገኘኸው ብትለው ሲብሰከሰክ ይውላል ።

አንዱ ጓደኛህ ሲደውልልህ "እየነዳሁ ነው መልሼ እደውልልሃለሁ" ብትለው ቀኑን ሙሉ ይቆዝማል ።

የሆነችን ልጅ "በጣም ወፍረሻል" ብትላት ለጊዜው የሆነ የሆነ ነገር ትልህና መስታወት ፊት ቆማ ትብሰለሰላች ። 

እስኪ አንዱ ሲስቅ ጠብቀህ  "ሳይኖርህ አትሳቅ" በለው ፤ ወዲያው ይከስማል።

እፊቱ እንግሊዘኛ ስታወራ የሚከፋው ሰውም አለ።

አፍቅሮ የተጎዳ ሰው "እህህህ" እንዲል የፌስቡክ ጨለምተኞች ከblack and white ፎቶ ጋር የሚለጥፉት አጭር ጽሑፍ ይበቃዋል ።

ናፋቂውን ምንም አትበለው ፤ ገና ደመና ሲያይ ውስጡ ይረበሻል ።

ለማልቀስ "ፍቅርሽ ነው የጎዳኝ" የሚል ዘፈን ብቻ የሚበቃው አለ ።

ደህና ነሽ ? ስትላት እንባዋ ግጥም የሚል አለች ።

ህልምህ ምን ነበር ? ብለህ ብትጠይቀው የማይከፋው አለ ? ።

ፀሐይ ሲመታው ብቻ ኑሮ የሚመረው አለ ።

ሰዉ እንደ ድሮው ረጅም የታክሲ ሰልፍ የመጠበቅ አቅም የለውም ። መኪና የለኝም ወይም የራይድ የለኝም ብሎ ያዝናል ።

እና ይሄ በሆዱ እንባ ያጠራቀመ ህዝብን ማስለቀስ ምን ሞያ ይጠይቃል ?

ከባዱ ነገር ተስፋ መስጠት ነው ። ተስፋ  ስጠው ስልህ ምክረው ማለቴ አይደለም ። ከምር ተስፋ ስጠው ። አስቀው ። አለሁ በለው ። ራሱን እንዲችል አድርገው ። ባዶ ሆዱን አትሰክሰው ። አብልተህም አትሰክሰው ። ዕድል ስጠው ። እመነው ። እቀፋት ። ተቃቀፉ ። ምናምን...

Via: Hab HD

@getem
@getem
@getem
ውርስ!
•••
ቅርንጫፌ ውስጥ ካሉ ቆጣቢ ደንበኞች መካከል ትልቅ ተቀማጭ ገንዘብ ያለው ደንበኛ ነው። በየጊዜው የሚያስቀምጠው ገንዘብ ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አይቼ አላውቅም። ታታሪ ሰራተኛ፣ ባተሌ እንደሆነ ገንዘብ ሊያስገባ ለብሶት የሚመጣው የቆሸሸ የሥራ ቱታ ምስክር ነው። አንድ ትልቅ ጋራዥ እንዳለው አጫውቶኛል።
ለተወሰኑ ወራት ዐይቼው ስለማላውቅ አሳስቦኝ ስልኩ ላይ በተደጋጋሚ ስደውል ስልኩ አይሰራም።
                             *
አንድ ቀን ጠዋት አዳፋ፣ ለሐዘን ቀለም የተነከረ ነጠላ የለበሱ፣  እጅግ የተጎሳቆሉ እናትና ፊቷ በማድያት የጠቆረ ሴት ከእኔ ቀድመው ቢሮ ጠበቁኝ።
ወንበሬ ላይ ተደላድዬ እንደተቀመጥሁ የፍርድ ቤት የውርስ ውሳኔ እንዲሁም ከባንኩ ዋናው መሥሪያ ቤት የህግ መምሪያ የተሰጠ አስተያየትና የባንክ ደብተር አቀበሉኝ። የባንክ ደብተሩን ስገልጸው ከታታሪው ደንበኛዬ ፎቶ ጋር ተፋጠጥኩ።
"ምን ሆኖ ነው?!"
"ሥራ ቦታ አደጋ ደርሶበት አረፈ ልጄ!" አሉኝ - አሮጊቷ።
የሰማሁትን ለማመን አልቻልኩም። እጅግ ደነገጥሁ። የፍርድ ቤት ውሳኔውን አነበብኩት የውርስ ውሳኔው በቅርንጫፋችን ያለው ገንዘብ ለእናቱና ለእህቱ እንዲካፈል የሚያዝዝ ነው። እንዲህ የተጎሳቆሉት ሴት በእርግጥም የእዚያ የባተሌ፣ የእዚያ በየሳምንቱ በብዙ ሺህ ብሮች ሂሳቡ ላይ የሚያስገባ፣ የእዚያ ሚሊዮን ብሮች ሒሳቡ ላይ ያጠራቀመው ደንበኛዬ እናት መሆናቸው እጅግ ገረመኝ።
"እግዚአብሔር ያጽናዎ እናቴ! ነፍስ ይማር! እጅግ የማከብረው ደንበኛዬ ነበር። እጅግ ታታሪ ሰው ነበር። ስልኩ ላይ ደጋግሜ ስደውል የማይነሳው ለካ ለእዛ ነበር ለካ?! ወይኔ ወንድሜ!" አልኋቸው።
"ይኸው እንዲህ ጥሎ ለሚሞተው ገንዘብ 'ሥራ፣ ሥራ!' ሲል የት ወደቅሽ ሳይለኝ፣ ታምሜ ሳይጠይቀኝ፣ ቁራሽ ተቸግሬ ሳይረዳኝ፣ እህቱን ሳይረዳ፣ የዘመድ ለቅሶ በልቶ፣ ከዘመድ ተቆራርጦ ማንም ሳያስበው በድንገት ሞተ። ሲሞት ተደወለለኝ፣ መጥቼ ቀበርኩት። የማህጸን ማሟሻዬ፣ የበኩሬ ነበር፣ ሙት አይወቀስም ይሉኛል፣ እኔ ግን ስወቅሰው እኖራለሁ።" አሉኝ በእንባ ብዛት የሞጨሞጨ አይናቸውን በአዳፋ ነጠላቸው ጫፍ እየጠረጉ።
"አይዞዎት እናቴ! በርታ ይበሉ! እርሱስ ቢሆን ይሄ ይመጣል ብሎ አለች አሰበ?! ያው ህይወት ሩጫ ናት፣ ምናልባት አልሞላ ብሎት..."
አላስጨረሱኝም።
"እድሜዬ ካለቀ፣ መቃብሬ ከተማሰ ብር አውርሶኝ፣ የልጅነት ፍቅሩን ነፍጎኝ፣ መኖሬን እንድጠላ አድርጎኝ ሞተ። በህይወት መኖሩ ብቻ መጽናዬ ነበር። ልጄ እናት አለችህ?!"
"አዎን እማ!"
"ዛሬን ጠይቃት፣ 'እንዴት አደርሽ' በላት። ሞት መምጫው ስለማይታወቅ ለነገ ምንም አታሳድር ልጄ። ልጄ ሲለፋበት የኖረውን፣ እኔን ያስተወውን ብሩን ወረስኩ፣ ፍቅሩን ግን ሳያወርሰኝ ሞተ። እኔ እንደምወድደው አውቃለሁ እርሱም ያውቃል፣ ወጣትነቴን ሰውቼ ያለአባት አሳድጌዋለሁ። እንደሚወድደኝ ሳያሳየኝ፣ እንደሚወድደኝ ሳላውቅ ሞተ" አሉኝ።
                               ****
የውርስ ገንዘቡን አካፍያቸው እንደጨረስኩ ከጓደኞቼ ጋር ዱባይ ሄጄ ልዝናና ከቆጠብኩት ብር ወደ ላይ ግማሹን አውጥቼ ለእናቴ ከላኩላት በኋላ ስልክ ደውዬ "እማ በዓል አብሬሽ ነው የማከብረው፣ ለበዓል ጨምርልኝ ያልሽኝን ብርም አስገብቼልሻለሁ፣ አወድሻለሁ እማ!" አልኳት።
ባልተለመደ ባህሪዬ የተገረመችው እናቴ "ምን ነው ጥልዬ በቀን መጠጣት ጀመርክ እንዴ?!" ስትል ጠየቀችኝ።
እንደምወዳት የምነግራት ሞቅ ሲለኝ ብቻ ስለነበረ አልተቀየምኳትም።
                           •••••
ሐሳብ ወለድ ታሪክ!

@wegoch
@wegoch
@paappii

By Tilahun Girma Ang
አባቴ እናዝናለን ፡ ካሁን በኋላ በምድር ላይ የሚቆዩት ግፋ ቢል ለስድስት ወራት ያህል ነው ።
........

እኚህ በምስሉ ላይ የሚታዩት አባት  Stamatis Moraitis የሚባሉ በወጣትነት ዘመናቸው ሀገራቸው ግሪክን በወታደርነት ያገለገሉ ሰው ናቸው ።
እና በአንድ ወቅት ልጆቻቸውን እና የልጅ ልጆቻቸውን ለመጎብኘት በሄዱበት አሜሪካ ትንሽ ህመም ይሰማቸውና ወደ ሆስፒታል ይሄዳሉ ።
ሀኪሙ  ግሪካዊውን ሰው በተለያየ አይነት የህክምና ዘዴ ከመረመረ በኋላ ፡ ሰውየው በማይድን የሳንባ ካንሰር እንደተያዙና ፡ ካሁን በኋላ በህይወት የሚቆዩት ለስድስት ወራት እንደሆነ ነገራቸው ።  የዶክተሩን  የምርመራ ውጤት ካዩ በኋላም ዘጠኝ አባላት ያሉት የዶክተሮች ቡድን ፡ ስለውጤቱ ትክክለኛነት ፈረሙበት ።

ይህን የሰሙት ሚስተር Stamatis አዘኑ ፡ ወደልጆቻቸው ቤት ከተመለሱ በኋላም መርዶውን ነግረዋቸው ተያይዘው ተላቀሱ ።
እንግዲህማ ወደ ሀገሬ ግሪክ ልሂድ ፡ ሞቴ እዛ ይሁን ቀብሬም  አባት አያቶቼ ባረፉበት ቦታ ይፈፀማል በማለት ፡ ከጥቂት ቀናት ቆይታ በኋላ ወደ ሀገራቸው ግሪክ ተመለሱ ።

Stamatis Moraitis ወደ ግሪክ ከተመለሱ በኋላ ምንም እንኳን ከስድስት ወራት በኋላ እንደሚሞቱ ፡ በአስር ሀኪሞች የተፈረመ ፡ ወረቀት ቢይዙም ፡ ለወትሮ ከሚሰሩት ስራ አልታቀቡም ።
በህይወታቸው ውስጥ የተከሰተ ምንም አይነት ለውጥ እንደሌለ ቆጥረው ፡ እንደድሮው አትክልቶቻቸውን ይንከባከባሉ ፡ ወራት ለቀረው እድሜ ፡ ለመድረስ አመታትን የሚፈልጉ ፍራፍሬዎች ይተክላሉ ፡

እንዲህ እንዲህ እያሉ ፡ ሳይታወቅ ያቺ የቀጠሮ ወር ደረሰችና ፡ ለመሞት ቀናትን  መቁጠር ጀመሩ ። ግን  ምንም የለም ። ሰውነታቸው ደክሞ ከዛሬ ነገ ድንገት እወድቅ ይሆን እያሉ በስጋት በመጠባበቅም  ፡ ስድስት ወሩን አለፉት ።
ሰባተኛ ወር ገባ ። ምንም የለም ።
አመት አለፈ ። ሰውየው ጭራሽ ንቁና ብርቱ መሆን ጀመሩ ። ሁለት ሶስት አመት አለፈ ። እንዲህ እንዲህ እያለ ፡ አስር አመት ሆናቸው እንደውም  ፡ በፊት አልፎ አልፎ ይሰማቸው የነበረው የህመም ስሜት ራሱ ጠፋ ።

እናም በአስረኛ አመታቸው ፡ ልጆቻቸውና ፡ የልጅ ልጆቻቸው ወደ ሚኖሩበት አሜሪካ ሄደው ሊያዩዋቸው ፈለጉና ወደዛ ተጓዙ ።
ካሁን አሁን መርዶ እንሰማ ይሆን ብለው ለአመታት የጠበቁት ዘመዶቻቸው ጋር በአካል ተገናኙ ።
...........
ከቀናት ቆይታ በኋላ ፡ ከዛሬ አስር አመትበፊት ፡ ለመሞት ስድስት ወራት ብቻ እንደሚቀራቸው የነገሯቸው ዶክተሮች ያሉበት ሆስፒታል ሄደው ሰላም ሊሏቸው በዛውም አስሩም ዶክተሮች የፈረሙበትን ወረቀት ለዶክተሮቹ  ሊያሳዩዋቸው ያዙና ወደ ሆስፒታሉ ሄዱ ።
ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታ ፡ አንድም ዶክተር ማግኘት አልቻሉም ። ሁሉም ሀኪሞች በተለያየ ጊዜ በህመም አልፈዋል ።
......
ግሪካዊው Stamatis Moraitis ከአስር አመታት በፊት ይህን ምርመራ ሲያደርጉ የስልሳ አመት አዛውንት ነበሩ ። እና ይሞታሉ ከተባሉ በኋላ ለሌላ ለ42 አመታት በህይወት ኖረው ፡ በ102 አመታቸው ከጥቂት አመታት በፊት አልፈዋል ።
.............
ጥያቄው  አስር ዶክተር ፈረመ ?  ሳይሆን ፡  ከላይ ተፈርሟል ወይ ነው  ።

@wegoch
@wegoch
@wegoch

By wasihun
ለመሆኑ ለትዳር እንዴት ተመራረጣችሁ? ሲባሉ

“ያው አስተሳሰቡ
ህልሙ
እውኑ
ምናምን የሌለ ተመቸኝ።" ብለው ያዝጉሃል።

ይቺ መልስ ግን deep inside የምርጫ ቅስቀሳ እንደሆነች ሁላችንም እናውቃታለን።

እርግጠኛ አደለሁም
ብቻ 2009 ላይ ይመስለኛል
አዲስ አበባ ውስጥ ለፍርድ ቤት ከቀረቡ ክሶች መካከል ከ57 በመቶ በላይ የሚሆኑት የፍቺ መሆናቸውን አስታውሳለሁ። ጊዜው ስለረዘመ ቁጥሩ ላይ ስህተት ልፈጥር እችላለሁ

አንዳንዴ የተጋነነ impression ይዞ ወደ ትዳር መግባት የማታ የማታ የሚያመጣው መዘዝ ይህ ነው አይባልም።

በቀደም አንድ ጓደኛየን ልጠይቀው ቤቱ ሄጄ ነበር።
ሚስቱ አንድ የሚንቦራች ልጅ እየጠበቀች የቤተሰብ ጨዋታን ስታይ ደረስኩ።

ባልሽ የለም እንዴ?

ፊቷን ሀዘን እየመተረው ፈልፈላውን እያሳየችኝ
"እሱ 'ኮ ነው።”

ምን ተፈጥሮ ነው?

“በቃ ነጋ ስጭኝ ነው!
ጠባ ስጭኝ ነው!
ምግብ ላቀርብ ጎንበስ ካልኩ ዘሎ ጉብ ነው!
ተው ብለው አልሰማኝ አለ።
አሁን እንደምታየው ነው እየመነመነ እየመነመነ እየመነመነ ሄዶ የትልቁ ልጃችንን እኩያ መስሎ አረፈው። እስኪ አንተ ፍረደኝ አሁን ይሄ ባል ነው መጥገር?"

አናደደኝ
ገላመጥኩት
እዛው ሚስቱ ክንድ ላይ ሽጉጥ እንዳለ
"ካቹፓራ ሳያት አያስችለኝም” አለኝ

በሌላ ቀን ደግሞ
ሚስቱ ደጅ ላይ ኩርሲ ላይ ተቀምጣ አንድ አራስ ራቁቱን ጭኗ ላይ አስተኝታ ሰውነቱን በቅባት እያሸች ፀሀይ ታሞቀዋለች።

ባልሽስ?

እንባዋ ዠደደደደ እያለ ጭኗ ላይ የተኛውን አራስ ቂጡን ቸብ ቸብ አደረገችው

ባሏ ነበር
አደነጋገጤ

ባል ቀና ብሎ የእንጀራ እናቱን እየጠባ
ምን አለኝ?

“ጉጉጋጋ”

እንባየ ደርሶ ግጥም አለ🥴

@wegoch
@wegoch
@paappii

By Tamiru temesgen
ከሚያነበው መጽሐፍ ገጽ ውስጥ የሰርግ ወሬ ሲነፍስበት ላፍታ ንባቡን ገታ አድርጎ፤ ሶፋ ላይ ተደላድላ ስልክ ላይ ያፈጠጠችውን ልጁን አያት። የእድሜዋ መናር አሳሰበው። ደግሶ ድሮ የመመረቅ እና የመጎረር፣ የመደነቅ ስሜት በአምሮት ናጠው።

"ለምን ነው ፍቅረኛ ይዘሽ ወደ ትዳር ጎዳና ማትራመጂው? እስከመቼ እንዲሁ በዋል ፈሰስ ትባክኛለሽ?" አላት።

ዐይኗን ከስልኳ ሳትነቅል "መች አለና" የሚል መልስ አሽቀነጠረች።

"ምኑ?"

"ፍቅርም፣ ሁነኛ ፍቅረኛም"

መልሷ ከነከነው። ህልምን ፈርቶ እንዴት ከመተኛት ያፈገፍጋል ሰው? "ፍቅር ላንቺ ምንድን ነው?"

"ክርስቶስ"

መልሷ ግማሽ ልቡን ሀሴት አጠጣው፤ ግን ድፍን መልስ አይወድም። "አብራሪው!"

"በቃ ለሚወዱት ሰው እስከሞት ድረስ ታምኖ መጓዝ፤ ያውም ያለማፈግፈግ፣ አሁን ያለው ወንዱም ሴቱም ታምኖ ሚሄደው ተቃቅፎ የልቡን እስኪያደርስ፤ ስጋውን እስኪያስደስት፣ ኪሱን እስክታልብ ነው። ስሜት እና ብልጠት እንጂ ፍቅር የለም አባ" ምርር አለች።

"ምን ያህል የፍቅር ሰው ነኝ ትያለሽ? ፍቅርንስ በገለጽሽው መንገድ ለመኖር ምን ያህል ዝግጁ ነሽ?"

ጨነቃት!
መልስ ከውስጧ ተሰለበ።
ዝም አለች!
ዝምታዋን ታክካ ራሷን መመርመር ያዘች።

#ኤልዳን
by @eldan29

@wegoch
@wegoch
@paappii
ድቅድቁ መሀል ያሉ ፋኖሶች
(ካሊድ አቅሉ)

የቦሌ መድሃኒያለም ቤተክርስትያንን አጥር ይዤ ቁልቁል አዘግማለው ፀሀይዋ እየሸሸች ለምሽት ምድርን ልታስረክብ ሽር ጉድ እያለች ነው ። የቤተክርስትያኑ አስተምሮት ለመስማት በጉዞዬ መሀል ጆሮዬን ለባለ ግርማ ሙገስ ድምፅ ባለቤት አባት ሰጠው " እውነተኛ  ደግ ጎተራው ሞላ አልሞላ እንብላ ብሎ ለምስኪን የቤቱን በር በሰፊው ሚከፍት ነው ። በሩን ዘግቶ አቅሉን እስኪስት ከተመገበ ብሃላ የከመረው መብል አላልቅ ሲለው ካደረማ ይበላሻል ለምስኪን እንስጠው ያሉት ደግ ነን ለማለት ሲዳዳቸው ይታያል ፤ ሞኞች ምስኪኑማ ተርቦ በራቹ ላይ እያለ ከርችማቹ መለሳቹት እኮ ያለ ሰዓቱ የመጣ ፈውስ ይባስ ቁስሉን ያመረቅዘዋል ። በጥሙ ሰዓት ያልደረሰ ውሃ ህይወቱ ካጣ ብሃላ እንደ ወንዝ ብታዘንቡለት አስክሬኑን ከማጠብያነት ውጪ ምን መላ ፈይዶ ? ስትሰጡ ኪሳቹ እስኪሞላ አትጠብቁ 'የመቅዶንያ ሰዎች ካላቸው ጥልቅ ድህነት ላይ ይሰጣሉ ' ይልም የለ ቃሉ"


ከመቅደሱ  ስለ ደግነት ሚማርክ ትምህርት ሲሻገር የኔዋ ደግ ባለቤቴ ፌቴ ላይ ድቅን አለችብኝ ሁሉን ነገርዋን ተቆጣጠረች ድግነትዋን ግን እንዴት ፋታ ትስጠው እጅዋ እና ልብዋ በምንም ቢከረቸሙ ከመከፈት አይታቀቡም ልግስና የመኖርዋ ዋስትና ነው ካልሰጠች የመኖርዋ ትርጉም ይጠፋታል ። አስተነፋፈስዋ ሚስተካከለው በቻለችው አቅም ክንድዋን ስትዘረጋ ነው ውይ ታድላ የነደደው ማፍቀሬ ላይ ቤንዝል አርከፈከፈችበት ቸርነትዋ አንገበገበኝ ከሷ ሌላ ማሰብ ተሳነኝ ። አንዳንድ ሰው አለ ደግሞ ክፉ ሰው እራሱ ደግ ሚለው ፍጥረተ አለሙን ሚያነቃቃ በመራር ከማጣፈጥ አልፎ ድባቡን በሙላ ሚቀይር አፍንጫችንን ይዘን በምንሄድበት መንገድ "ውይ ደስ የሚል ሽታ " ብለን የጠላነውን መንገድ በፍቅር ደጋግመን እንድንመላለስ ሚያረጉን እህቶች, አባቶች , እናት ,አክስት , ጓደኛ ጎረቤት ወዘተ . . . . .  አሉ አበቃልን ብለን የቁም ሞት ሊወርሰን ሲሰናዳ ከመንጋጋው ሚያድኑን . . . ህይወትን በእንባ ብቻ እንዳንከትባት የሳቅን ዙፋን ይዘው ከተፍ ሚሉልን ጭንቅን መውጫ መሰላሎች ድቅድቁ መሃል ያሉ ፋኖሶች  . . . . ።

~    ~    ~   ~   ~

@wegoch
@wegoch
@wegoch
ሥዕል ለማሳል በ+251984740577
ወይም @gebriel_19 ላይ  ፎቶ  በመላክ በ ተመጣጣኝ ዋጋ  ማዘዝ ይችላሉ!


@seiloch
@seiloch
ዝንቁል
።።።።።።

ከአያቴ ስድቦች ሁሉ ግንባሬ ላይ የተለጠፈ እስኪመስለኝ ሳስበው የሚያሳፍረኝ ስድብ ነው...ዝንቁል!ከሆነ ጊዜ በሁዋላ ከስድብነት ወደ ቅፅል ስምነት ተቀየረና ሳልወድ "አቤት" የምልበት መጠሪያዬ ሆኖ አረፈው።

"ዝንቁል ነይ አያ ከባዱ መጧል ሰላም በይው"ትለኛለች የምወደው አጎቴ ሲመጣ።
"ምነው እማ ስንቄ ካልጠፋ ስም?"ይላል አጎቴ እየሳቀ።ሰው ስሜን ሰምቶ ሲስቅ ለጉድ ነው 'ምሸማቀቀው!አንገቴን ወደ መሬት ትክል!በተለይ አጎቴ ከሳቀ!
"ምን ላርጋት እህ ብልጠት ያልሰራባትን!ነክሮ የተዋትን ከባድሰው!እንደው ፍርጃ ነውኮ እናንተየ!ሰው እንዴት በአስራ አምስት አመቱ እሳትና ውሀ አይለይም?ወይ አንች የአብማይቱ አታሳይኝ የለሽ!"ትላለች ሞኝነቴን ስታጎላ።በእርግጥ ሱቅ ስላክ ባለሱቆቹ ይከስራሉ ብዬ ስለማስብ መልስ አልቀበልም ብዬ አልቅሼ አውቃለሁ...አልክድም አምና አያቴ ለእንግዳ ሰርታ ያስቀመጠችውን ድንች ወጥ አሙቂ ያለችኝ ጊዜ እንዲጣፍጥላትና እንድትመሰገን ብዬ ብርጭቆ ሙሉ ስኳር ጨምሬበታለሁ።

"የሆነስ እንደሆን ስሙ ተዋህዷት አለቅጥ ቂል ያረጋታል እንጂ ምን ይበጃታል እማ ስንቄ?"ይሄኔ የእማ ስንቄ ቀይ መብራት ይበራል።ርዕስ ታስቀይራለች።በስሜ አልያም በጅልነቴ ዙሪያ ምክር ወይ አስተያየት ቢጤ ሊሰጧት ከቃጡ መስሚያዋ ጥጥ ነው።

"አንተ ከባዱ...እንደው ያች በቅሎህ ተሻላት አደራህ?"ትላለች የዝንቁልነቴን መዝገብ ትከድንና።እሷ ለመጣ ለሄደው የሞኝነቴን ነገር ተናግራ አልታክታት ቢልም እኔ ግን መስማቱ መረረኝና አንድ ቀን እንዲህ አልኳት።

"እማ ስንቄ"

"ኧ!ስንቋ አለቀኮ ብያለሁ እችን የቋቁቻም ዘር!እሰሰይ!የቆሎ ጓደኛዋ መሰልኳት?"

"ሁለተኛ ዝንቁል እንዳትይኝ!እናቴ ያወጣችልኝ ወርቅ የሆነ ስም አለኝ!ማንጠግቦሽ በይኝ"

"የጠገበ አህያ ይውጣብሽና ያላልኩሽ እንደሁ ትመችኝ?" አኩርፌ ወደውስጥ ስገባ የጎረቤታችንን የእማ ዝማምን ድምፅ ሰማሁ።ዘውትር  እየተጨናበሱ የሚመጡት እሳት ሊጭሩ ነው...የምጭርላቸው እኔ ብሆንም ...የአያቴ ጥሪ ተከተለ

"ዝንቁል ነይ ለዝማም እሳት ጫሪላት"

ማዕዶት ያየህ(ዘማርቆስ)
(
@gize_yayeh)

08/09/2015 ዓ.ም.


@wegoch
@wegoch
@paappii
አክስቴን እንዴት ፖለቲከኛ እንዳደረጉብኝ
።።።።።፡።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።

ጊቢያችን በሰጠን የ9ቀን  እረፍት ምን እንደምሰራበት ሳቅድ 5ኛው ቀን ላይ ደረስኩ...ያለ ቁምነገር!ወይ አላነበብኩ...ወይ ወግ ቢጤ አልሞነጨርኩ...ወይ ስካርፌን ጠምጥሜና ፀጉሬን አጎፍሬ የተነሳሁትን የአብዮተኛ ገጣሚት ፎቶ ፌስቡኬ ላይ አልለጠፍኩ...ብቻ የሆነ ቀን አክስቴ ዓይኔ ላይ ውል ስትልብኝ ተነሳሁና ቤቷ ሄድኩ።

"ቅንጭር ከየት ተገኘሽ?" አለችኝ።ከሲታነቴን ስታጋንን ነው "ቅንጭር"የምትለኝ።

"እታባ ደግሞ!እይ እስቲ እንዴት እንደወፈርኩ...ባህርዳርኮ ተመችቶኛል" ሰው ከሲታነቴን ሲነግረኝ ደሜ ነው ሚፈላው።

"አየሁት እቴ!ጣውላ ቂጥ!ምንሽ ነው የወፈረው?ያው የተላገ ጣውላ እንደመሰልሽ ነው!እንደው በምስክር ሞት ምናል ደህና ደህና ነገር ብትበይ?"

"ማነው ደግሞ ምስክር?"

"ምስክር ነዋ!"

"እኮ አላወቅሁትም"

"አይ እንግዲህ!አላወቅሁትም አይባልም አላወቅነውም ነው 'ሚባለው" ብላኝ እርፍ።ከመቀመጤ ሪሞቷን ቀሰረችና የጦፈ የፓለቲካ ክርክር ያለበትን ጣቢያ መርጣ ተደላድላ መከታተል ጀመረች።

"እታባ ኧረ ቀይሪው በማርያም!"

"ዝም በይ!ጁንታ!ምን ታውቂያለሽ ስለሀገር?ዝፈኝ አይበሉሽ እንጂ!"

"መቼስ ከሞት ዜና ዘፈን ይሻላል"

"እዬዬም ሲደላ ነው ቅንጭር!አታድርቂኝ !እዚሁ ደፍቼሽ መቃብርሽ ላይ ችግኝ እንዳልተክል!"

(ምንድነው ያስነኩብኝ ይችን ሴትዮ?ጊቢ ልሄድ ስል ልትቆርብ እያኮበኮበች አልነበር?ማነው የፖለቲካ ጋኔል ያስመታብኝ? 🤔🤔)

"እታባ ቆረብሽ አይደል?"

"ሲኖዶሱን ከፍለውት በየት በኩል?"( 🙄🙄 ምንም ብጠይቅ መልሷ ውስጥ ፖለቲካ አለ)
ወዲያው  4ዓመት የሞላው የልጅ ልጇ(የአክስቴ ልጅ) ወዲህ ወዲያ እያለ ሲጫወት ድመታቸው ላይ ቆመባትና አስጮሀት ።አክስቴ ብስጭት ብላ አምባረቀችበት

"የ20ሚሊየኑ  ባስ እላይህ ላይ ይውጣ!አፍርጠህ ትገድላት?" ለደቂቃዎች ክርክሩን ስትከታተል ቆየችና

"ቅንጭር...ጥሩ ቀን መጣሽ...ያች እምትወጃት አለችልሽ ሂጅ አቅርቢና ብይ"አለችኝ።መኮረኒ በአትክልቴን እየበላሁ ቤቱ ግድግዳ ላይ የተለጠፉትን አዳዲስ ምስሎች መታዘብ ጀመርኩ።ከፊት ለፊት ያለው ግድግዳ ላይ የዘመነ ካሴን ምስል ከነ ንግግሩ የያዘ መጠነኛ ባነር ተሰቅሏል።ከዓመት በፊት እዚሁ ግድግዳ ላይ የመድሃኔዓለም ስዕለ-አድህኖ ተሰቅሎ እንደነበር ትዝ አለኝና ደነገጥኩ።የቀኝ ግድግዳው ላይ የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ምስል ተሰቅሏል።ከምስሉ በታች ያለውን ፅሁፍ ሳነብ ነው አክስቴ እንደለየላት የገባኝ።

"ባሏን ብታይ ውሽማዋን ጠላች ሆኖብኝ ነው ስትሞት ስለት ማስገባቴ!እሱ ቸሩ መድሃኔዓለም ነፍስህን በገነት ያኑራት!
                                     ያንተው ወይንሸት "


ወደሌላኛው ግድግዳ ስዞር አንድ ሱፍ ያጠለቀ ሰው  "ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን" ከሚለው ንግግሩ ጋር ተዘቅዝቆ ተሰቅሏል።

"እታባ ይሄን ሁሉ አንቺ ነሽ የለጠፍሽው?"

"ኋላስ ማን ሊለጥፈው ኖሯል!ግድግዳ ኬኛ!"

"በይ ደህና እደሪ ልሂድ"

"ልሂድ አይባልም ...እንሂድ ነው ሚባለው ቅንጭር"

(🙄🙄🙄🙄🙄🙄🙄🙄)

ማዕዶት ያየህ(ዘማርቆስ)
(@gize_yayeh)

10/09/2015 ዓ.ም.

@wegoch
@wegoch
@wegoch
ማንም በኬኔዲ እንዳይመጣብኝ!
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።

   ኬኔዲ መንገሻን እንዴት እንደምወደውና ስስ ጎኔ መሆኑን ያወቁ አጠገቤ ሙዚቃውን ይከፍታሉ ።ተለክፌበት ነው መሰለኝ ድምፁን ከሰማሁ ጠላቴ ቤትም ሳልገባ አልቀርም።ለምን ቤተመንግስት አይሆንም?

  እና ኬኔዲን በተመለከተ የዛሬ ሁለት አመት ገደማ ያጋጠመኝ ትዝ አለኝ።ከቤታችን ጀርባ አንድ ፅድት ያለ ጊቢ ለብቻው ተከራይቶ የሚኖር የቅቤ ነጋዴ ነበር።ስሙን ቄስ ይጥራውና ቅዱስ ነበር ስሙ።

  ዘውትር ወደትምህርት ቤት ስሄድ ቪትዙን በአጠገቤ እያራመደ(ቪትዝ የያዘ ሰው እግረኛ ነው ሚመስለኝ😂 ተርቱብኝ ከፈለጋችሁ)

"ሄይ ቆንጆ" ይለኛል የሚያኝከውን ማስቲካ እስከ ሮቡዕ ገበያ እያስጮኸ።

"እንዴት አደርክ ቅዱስ?"

"አለሁልሽ...'ወደክላስ' ነሻ?ልሸኝሻ!"

"ውይ በጣም አመሰግናለሁ...ጓደኛዬ እየጠበቀችኝ ነው።"

"ታዲያ ምን ችግር አለው?ልሸኛችሁአ...ደውይላት" እንደማይተወኝ ሳውቅ ለጓደኛዬ ደወልኩ።ከቤት ትምህርት ቤት ያለው መንገድ በህይወቴ እንደዚያ ቀን ረዝሞቦኝ የሚያውቅም አይመስለኝም።ንግግሩ...ቀልዱ...ሳቁ...ወላ አተነፋፈሱ ይኮሰኩሳል።የሆነ parasite አንጀቴ ውስጥ የሚላወስ እስኪመስለኝ ነው ያቅለሸለሸኝ።

"ይገርማችሁዋል በጣም ሰቃይ ተማሪ ነበርኩ።ግን ከልጅነቴ ጀምሮ እኛ ኢትዮጵያውያን ቅቤ ላይ ያለን inspiration እንዳስደነቀኝ ነው።ቅቤ መነገድ አብሮኝ ያደገ ህልሜ ነበር..."አላለም?ቅርድድ!ማትሪክን 1.2 አምጥቶ ከትምህርት ጋር መቆራረጡን ያልሰማን መስሎት!

"By the way Gize...you is very talented...why not singing to me?"ሲል ትምህርት ቤታችን በር ላይ መድረሱን አላስተዋለም ነበር።RIP English!

  ከቀናት በሁዋላ  እንዲሁ ወደትምህርት ቤቴ ሳዘግም ከአጠገቤ ሲደርስ ቪትዙን አቁሞ

  "ሃይ ጊዜ"አለኝ።
ፀጉሩን እንደ ኬኔዲ መንገሻ ተቆርጧል።የሱን የሚመስል ሸሚዝ...ሱሪ...ጫማ...ከመኪናዋ ሙዚቃ ማጫወቻ የኬኔዲ ሙዚቃ ይንቆረቆራል።

  "ተው አአትከልክሏት
   ታንኳኳው በሬን
   ገብቷት ከመጣች
    ወዳ መውደዴን
    .........................
   እንደ ዱር ዝንጀሮ
    ጫካ እንደለመደ
   ቤት መግባት ይጠላል
    እሷን የወደደ..."

ቪትዙ ማርቼዲስ ሆና ታየችኝ ብላችሁስ?ከምኔው መኪና ውስጥ እንደገባሁና ክፍል ገብቼ እንደተቀመጥኩ አላውቅም።ብቻ የኒውተንን ህጎች እየተማርኩ ጭንቅላቴ ላይ የሚያቃጭል ዜማ ነበር።

"...ትዝብት ነው እቴ ትዝብት ነው
    ትዝብት ነው እቴ ትዝብት ነው
    ወዳጅ ከዞረ ፊቱ
     ከጨከነ አንጀቱ...."

በኬኔዲ አትምጡብኝ!

ማዕዶት ያየህ (ዘማርቆስ)
(
@gize_yayeh)
14/09/2015 ዓ.ም.


@wegoch
@wegoch
@paappii
ከተበሉስ አይቀር በጎጃም ቡዳ!
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።

   ጎጃሜ ነኝ።ያውም ማርቆሴ!የበላይ ዛር የሚያክለፈልፈኝ!እናላችሁ አምና እናት ከተማ ማርቆስን ለቅቄ ለአስኳላ ወደባህር   አዝግሜ ኖሮ ጠሀዩ ልብ ልቤን ሲጠብሰኝ ጊዜ በሳምንቴ ተመልሼ ወደማርቆስ!

  "ኧግ 'የኢንበርስቲ' ተማሪ!ይኸ ነው እንግዲህ ?በሳምንት ምላሽ ሆነ?"ኮብራ ምላሷ ጎረቤታችን ስንቴ ናት የምትለክፈኝ።

"የረሳሁዋቸው እቃዎች ስላሉ ትምህርት ሳይጀመር ልውሰዳቸው ብዬ ነው።''
  ''ነው?እምምምምም" ከንፈሯን አጣማ ትታኝ ሄደች።ከስንቴ ጋር ስሆን የETV ዜና ሳይቀር ይናፍቀኛል።የመሰለ ገ/ሕይወት ለንቦጭ ሁላ ውል ይልብኛል።ከያዘች አትፈታማ!ጥቃቅን ማብራሪያን ፍለጋ ልብህን እንደ ሎሊ ፖፕ ትጠባዋለች ነው 'ምልህ!!

አሁን በቀደም ዕለት ሱሪ ለብሼ የማላውቀው እኔ ቬል ሱሪዬን ወትፌ ስመናቀር አገኘችኝና

"ኧሯ!ሚጡ...ሱሪ ሲያምርብሽ አንቺ!"

"አመሰግናለሁ ...ያው የጊቢ ተማሪ እንምሰል ብለን ነው!"

"ኧራ!ልበሽ ኧረ!ለማናባቱ ብለሽ ደሞ!ይወጭቀው!ስንት ገዝተሽው ነው?"አለችኝ ሱሪዬን ቀለሙ እስኪለቅ እያየች።

"ቀላል ነው...950 "

"ዘጠኝ ከአምሳይ?ሸጋ ነው አንች!ተየት ነው የገዛሽው?ተአዲሱ ገበያ ነው?"

"አዎ ከዛው ነው"

"አምሮብሻል ነጋ ይሙት!ተንግዲህ ቀሚስ እንዳትለብሽ እንዲያውም...እና..."አቋረጥኳት

"በይ እሺ ሰላም ዋይ ስንቴ ጓደኞቼ እየጠበቁኝ ነው""ብያት ሄድኩ።'እህ ብዬ ከሰማሁዋት የገዛሁበትን ቀንና ሰዓት...ያጋዛኝን ሰው...የሸጠልኝን ሰው ...የልብሱን ብራንድ...መጠየቋ አይቀርም።ደሞ 'አምሮብሻል' ይባልልኛል!(😒😒ሰፈር ውስጥ "እናንተ!ያች የወለላ ልጅ ተበላሽታ አይል!ያችን የዶሮ ኩላሊት እምታክል ቂጧን በሱሪ ወትፋ ስትሞላፈጥ አይቻት..."እንደምትል መች ጠፍቶኝ?ዶሮ ኩላሊት ባይኖራት ራሱ የኔን ቅጥነት ለማጉላት ሲሆን እነስንቴ ቤት አላት)

የረሳሁዋቸውን እቃዎች ሸክፌ ወደ ባህርዳር ከተመለስኩ በሁዋላ ከዶርም ጓደኞቼ ጋር ብዙ ጊዜ እሰጥ አገባ ውስጥ የሚከተን ነገር ነበር።"ጎጃሜ ቡዳ ነው " የሚሏት ነገር!

"ጎጃሜ ቡዳ ነው
ብለሽ ያወራሽው
ሰው ሰውን ሲበላ
የታባሽ አየሽው?"  ከአፌ የማይጠፋ ግጥም ሆነ። በጨዋታችን መሀል አቦሰም ጥለን ዕድሉ የኔ ከሆነ "ድሮስ ጎጃሜ!"ይላሉ አፋቸውን ሸርመም አድርገው።ነገሮች በአንድም በሌላም መንገድ የዕድል ገፃቸው ወደኔ ከዞረ "ጎጃሜ አይደለች?"የሚሉት ጥቂት አይደሉም።አንዱማ እንዲያውም የሆነ ቀን  'ላማክርሽ እፈልጋለሁ'ብሎ በቁምነገር ቀጠረኝና ተገናኘን።

"እየውልሽ ጊዜ...እእ...እንትን ነው"
"ምን?"
"የሆነች ልጅ ወድጄ..."
"ኧረ?ማናት?"
"አታውቂአትም"
"እና አናግረሀታል?"
"ለሱ ነውኮ የፈለኩሽ"
"እንዳናግርልህ?"
"ኧረ በንግግር የሚገባት አይደለችም ልጅቱ"
"እና ምን ላርግልህ?"
"ያ...ው...ጎጃሜ አይደለሽ?እናንተኮ እዚህ ነገር ላይ አትታሙም...መ...ስተፋቅር እንድትሰሪልኝ ወይ እንድታሰሪልኝ ነበር" ብሎኝ እርርርርርፍ!
     ከዚህም ከዚያም የጎጄን ቡዳነት ሲደጋግሙብኝ መገንፈሉን እየተውኩ እኔው ራሴ በራሴ መቀለድ ጀመርኩ።

"ጎጃሜ ቡዳ ነው
  ብለሽ ያወራሽው
  ሰውን ሰው ሲበላው
  የታባሽ አየሽው ?"

እል የነበርኩት ልጅ

"ቡዳ ነው ይሉታል
  ጎጃምን በሙሉ
መች ጣዕሙ ሊታወቅ
ሰው ይዘው ካልበሉ"  ማለት ጀመርኩ።በሊታን መምረጥ ቢቻል ከተበሉስ አይቀር በጎጃም ቡዳ!ፍቅር ነዋ ምትለፈልፈው!!

  ማዕዶት ያየህ(ዘማርቆስ)
(
@gize_yayeh)

15/09/2015 ዓ.ም.


@wegoch
@wegoch
@paappii
...
ዝም ያለ መልክ ረጋ ያለ ሰውነት ያስደነግጣል?
ለምን እንደምደነግጥ እኮ ነው ያልገባኝ።
ልክ ሳየው ልቤ ምቱን ያፈጥነዋል፤ እጆቼ መንቀጥቀጥ ፊቴ መቅላት ይጀምራል። አይኖቼን ምን ለይ እንደማሳርፍ እንዴት ማውራት እንዳለብኝ ግራ እጋባለው። መንገድ ለይ ከሆንኩ ደግሞ ልክ ገና ከቤት እንደወጣ ሰው እግሬ ይማታብኛል፤ አየር ለይ የምረግጥ ይመስል እወላከፋለው። ስለ ራሴ የነበረኝ መረዳት ሚዛኑን ይስትና ፊቴ ለይ ያለች ትንሽዬ ነጥብ ትታየው ይሆን ብዬ ስጨነቅ ራሴን አገኘዋለው።

አይንን ያዝ በሚያደርግ መልኩ አይደለም አይኖቼን አስሮ ያቆያቸው፤ አንደበተ-ርትዑነቱም አይደለም ሲያወራ በሰማሁት የሚያሰኘኝ፤ በሩቅ በሚታየው ሞገሱም አይደለም ልቤን ሲያርደው የሚውለው።

እዩኝ በሚሉ መልኮች መሀል ነው የሱን ዝም ያለ ውበት ያየሁት፤ ከብዙ ተናጋሪዎች መሀል ገኖ ነው የሱ አድማጭነት እልፍ የሚያስወራኝ እልፍ የሚያፅፈኝ። ስክነት ያለው ህይወቱ ነው በሺህ ችኩል በሺህ ጥድፊያ መሀል ሁሉን አደብዝዞ እሱን ብቻ የሚያስመለክተኝ። የእውነቱን ኑሮ ነው ኑረቱን እንድወድለት ያስገደደኝ።

ያወራኝ እለት ቃላት ብቻ አልነበረም ከአንደበቱ የሰማሁት፤ ዝም ቢል እንኳን ብዙ መናገር የሚችል ገፅ ተችሮታል። እሱ ሲያወራ ስረታ እሱ ሲናገር ስርድ ይታወቀኛል። መቼ አምኜ መቼ እንደተቀበልኩት መቼስ ልቤን አሳልፌ እንደሰጠው እንጃ። ግን ከነበርኩበት ሁካታና ጥድፊያ አውጥቶ ሲያሰክነኝ ይሰማኛል። ዘመንን ማዘዝ ይችል ይመስል እሱ ጋር ስሆን የረሳሁት ሰላም የረሳሁት ፀጥታ በእርጋታ ከሚፈስ ጊዜ ጋር ዙሪያዬን ይከበኛል። ሰው ለመማረክ አለኝ የሚለውን የማንነት መልክ ይዞ ከውድድር አይሰለፍም ይልቁንስ ባለበት ይቆያል እንጂ። ከራሱ ጋር፤ የታይታ ካልሆነው ገዢ ስብዕናው ጋር።
እናም ሚዛን ልኬቱን ማጣት ይጀምራል። ከተናገሩት ሁሉ ይልቅ እሱ ይደመጣል፤ ከታዩት ሁሉ ይልቅ አይን ለማረፊያው እሱን ይናፍቃል፤ ከተገዳደሩት ሁሉ ይልቅ እሱ ሳይታገል ይጥላል። በቀደዱለት አይፈስም ነገር ግን በዙሪያው ያለውን ሁሉ ይዞ ወደ እራሱ መንገድ መሻገር ይቻለዋል።

"ይሄ ሰው ማንነው?" ያሰኘኛል፤ ማንነው? የጊዜው ኑረት እንዲህ የሚገላበጥለት። ማንስ ነው? ብቻውን ኑሮ በብዙ ሚረታው። እንዴት ሆኖለት ነው ሲያደምጥ መሰማት ሲመለከት ማውራት ለሱ የተቻለው። እንዴት ብረዳው እንዴት ቢገባኝ ነው ሚዛኔን በእሱ ተክቼ ሰው የማገዝፈው ከልኬት ማወረደው። ምኔን ቢያገኘው ምኔን ቢነካው ነው ዛሬ ገና መኖር የጀመርኩ ይመስል እጆቹ ካልያዙኝ የምንገዳገደው።

በዚህ ልክ የራስ ሰው በዚህ ልክ አዋቂ በዚህ ልክ አስተዋይ... ይሄ ሰው ማነው?

@wegoch
@wegoch
@paappii

By mahi
#ለወንዶች_ብቻ

ይኸውልህ።

ዋቴ ብልጽግና በሳይንስ ሳይሆን በጥንቁልናና በትንቢት የሚያስተዳድራት አገር በአምስት አመት ውስጥ 1.5 ትሪልዮን ዶላር የጦርነት ኪሳራ አምጥታ፣ አሁን አለም ላይ የሌለ 107% Hyperinflation ውስጥ ገብታ ሕዝቦቿን በኑሮ ውድነት እየለበለበች፣ በ15 ቢልዮን ዶላር ቅንጡ ቤተ መንግስት ትሰራለች። ላቲንም በለው ኤዥያ፣ አፍሪቃም ጭምር - Developing Countries የተሰኙ አዳጊ አገራት ውስጥ ቅንጡ ቤተ መንግስት አይሰራም፤ ድሃ ናቸዋ!

ስማ ስማ።

በቀጣይ ሁለት አመታት ኑሮ ከዚህ በላይ ይወደዳል። Anarchy ይሰፍናል። ደሞዝህ ከወር እስከ ወር ስለማያደርስህ ከሚስትህ ጋራ ትጣላለህ፣ ትዳርህ ይበጠበጣል። ''አላቅልሽም አብቃቂ'' እያልክ በየቀኑ ልትጨቃጨቅ ነው። እሷም ''ብሩን ጠጣህበት፣ ተዝናናህበት'' ብላ ልትበጠብጥህ ነው።

መፍትሄውን እንካ።

1 - ቆጥብ፣ ወጪህን በ60% ቀንስ። ስለ Minimalism አንብብ። ከካናዳዊው የF.I.R.E አቀንቃኝ Mr Money Mustache፣ ስለ ችጋራም አኗኗር እና ስለ Early Retirement የጻፋቸውን ከጉግል አጥና።

-

2 - ዝም ብለህ ውለታ አትዋል። ቢሮክራሲ አትቀንስ፣ መረጃ በነፃ አታቀብል። ኮሚሽን ጠይቅ። ደልል። አስከፍል። ክፈሉ ለማለት አትፈር። ሰው ሁሉ አስከፍሎ ነው ቀላልና ከባድ ጉዳይ የሚያሳልጠው።

-

3 - ስረቅ። አጭበርብር። ጉቦ ተቀበል። የእጅ ውረዱ ማለትን ተለማመድ። ስራ ላይ በኔትዎርክ ተደራጅተህ ስረቅ። (አትመፃደቅ - የብልጽግና መንግስት የሱን ብሔር ሰዎች ሰብስቦ ዝረፉ ብሎ ሲያሰማራ አንተ ጨዋ ጨዋ ከሰራህ ተግጠህ ታልቃታለህ)

-

4 - ውጪ አገር ወንድም፣ እህት፣ ጓደኛ ካለህ - ''ገንዘብ ካልላክልኝ ሁለተኛ እንዳትደውል'' በለው። ዳያስፖራ ጨለል ነው፣ ቀውሶች ናቸው። ብቸኝነት ሲያገረጣቸው በየሳምንቱ ይደውሉልህ እና ስለ ኑሮ ውድነት ጠይቀውህ ራሳቸውን ያጽናናሉ። አስር ብር ግን አይፈለጡም።

''ስንቴ ልንገርህ፣ ደህና ገንዘብ፣ ወይንም ወሳኝ እቃ ካልላክልኝ ሁለተኛ አትደውል፣ ቢዚ ነኝ'' ብለህ ጆሮው ላይ ዝጋበት።

-

5 - ቅጥረኛ አትሁን። ደሞዝተኛ አትሁን። በጠዋት ወጥቶ የታክሲ ወረፋ ተሰልፎ፣ ሙሉ ቀን ሰርቶ፣ የአለቃን Expectations አሟልቶ፣ በወር መጨረሻ የተመታ ደሞዝ መቀበል #ያደነዝዛል#ዶማ ያደርጋል። . . .ስራ ለቅቄስ? አትበለኝ። እሱማ ለራሴ ሰዎች የተያዘ ሚስጥር ነው፤ አልነግርህም።

-

ብቻ ይሄንን ጥሬ ሐቅ ልብ በል - በእነዚህ ሰዎች የስልጣን ዘመን እዚህ አገር ላይ ጠንክሮ መስራት #ያደኸያል

-

አትፍዘዝ፣
ታመጣለህ መዘዝ!

@wegoch
@wegoch
@paappii

By Eyob mihretab
iPhone ባይኖርህ iPhone ያለው ጓደኛ ይኑርህ
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።

  "መልክ ይስጠኝ እንጂ ሙያ ከጎረቤት እማራለሁ" ትላለች እናቴ።

"Snapchat ይኑር እንጂ ሙያ ከጎረቤት እማራለሁ" ዘመን ላይ ሳንደርስ በፊት።ዕድሜ ለካሜራ ጥራትና ለSnapchat እኔና መሰል መልከጥፉአውያን መልክን ትተን ስለሙያ መጨነቅ ከጀመርን ቆየን!በቀደም አንዷ የሰፈሬ ልጅ ቴሌግራሟ ላይ የለጠፈችውን ፎቶዋን አይቼ ጉድ ብዬ አልበቃኝ አለ!ሳውቃትኮ ትል ያላመጠው ቲማቲም ነው ምትመስለው!እንዲያውም የአፍንጫዋን ትልቅነት በተመለከተ እናቷ ወ/ሮ አበሩ ሲቀልዱባት

  "ዝንጀር እስቲ ወጡን አሽትችና ጨውን ንገሪኝ" ይሏታል።ሰፈር ውስጥ ሁሉም "ዝንጀር" ነው የሚላት...ዕውነተኛ ስሟ "ጤና"እስኪረሳ ድረስ!ታዲያ ዝንጀር ዩኒቨርስቲ ስትገባ አጎቷ ከካናዳ IPhone ላከላት።በሄደች በሳምንቷ "ለእታባ አሳይልኝ"ብላ ጊቢ የተነሳቻቸውን ፎቶዎቿን በቴሌግራም ላከችልኝ።

  ወ/ሮ አበሩ ስልኬን እያገላበጡ ፎቶውን አዩትና

  "ሚጡ...የዝንጀርን ፎቶ አምጭው እንጅ"
  "ይኸው ዝንጀር ናትኮ"
   "ክይ!ቅማላም!...መሀይም ነኝ እንጅ መቀለጃ ነኝ?"
   "ኧረ ማርያምን አበርዬ!ይኸ ባለፈው የገዙላት ቲሸርት አይደል እንዴ?"
   "የት ገብቶ ነው ያ ለምቦጭ?ያ ሁላ ቡግር ምን ዋጠው?"
   "አገሩ ተመችቷት ይሆናላ"
   "በሳምንት?እኔ መልኳ መለስ ቢል ብየ በየሳምንቱ የቅቤ ስቀፈቅፍ ኖሬ እዛ ኸዳ በሳምንት ይኸን ያህል ወዝ?ይች በልቶ ካጅ!""

ዝንጀር ለእረፍት ስትመጣ በስልኳ የተወሰኑ ፎቶዎች አስቀረሁና ፌስቡኬ ላይ ለጠፍኩ።ከዚህ ቀደም ለፎቶዎቼ የተሰጡኝን አስተያየቶች መለስ ብዬ ቃኘሁ።

  ጥሎብኝ አንድ መፅሀፍ ባነበብኩ ቁጥር ከመፅሃፉ ጋር ፎቶ ተነስቶ የመለጠፍ ልምድ አለኝ።''የኢትዮጵያ ታሪክ ከኖኅ እስከ ኢህአዴግ"ከሚለው መፅሐፍ ጋር ፀጉሬን አጎፍሬ ለተነሳሁት ፎቶ አንዱ ተንከሲስ እንዲህ የሚል አስተያየት አስቀምጦልኛል።

  "የ77ቱ ድርቅ መልክ ቢኖረው አንቺን ይመስላል።ዘቅዝቄ እንደ መጥረጊያ ብጠቀምሽ ጉራንጉሩ ሁላ አይቀርሽም ስታፀጅው።"

ዝቅ ብሎ ደግሞ ሌላኛው

   "አንቀፅ 39 ፊት!ፊትሽ የመገንጠል ስሜቴን ቀሰቀሰው!ከኢትዮጵያ ውጣ ውጣ የሚለኝ መጣ!" ብሎኛል።ወረድ ስል ደግሞ

  "ፀሀዩ ከሮ ጥላ ተወዶ ፊት!ፊትሽ ህልም ይመስላል...አይቼው ልጮህም አማረኝ ልሮጥም አማረኝ ግን አልቻልኩም...ፍቺና ወይ አስፈቺና ገላግይን አቦ!" ሌላው ደግሞ

"ይኸን ግንባር ይዘሽ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብትሄጂ የራስሽ ክልል ይኖርሽ ነበር!"

  ከኔ ፎቶ በላይ 'ኮመንቶቹ' ናቸው ላይክ ያገኙት።በዝንጀር iPhone ታሪክ ሳይቀየር በፊት...ከአሁኖቹ "ኮመንቶች" በጥቂቱ

   "ፍንጭትሽ ደስ ስትል...ካንቺ ፍንጭት ከኔ ዲምፕል 'ሼር' አርገን ለምን አንዲት ቆንጅዬ ልጅ አንወልድም?"

  "ዓይኖችሽ  አንድነት ፓርክን ያክላሉ።ፍቀጂልኝና ሰልፊ ልነሳባቸው"
   
  

ወይ iPhone ወይ iPhone ያለው ጓደኛ ይኑርህ!

ማዕዶት ያየህ(ዘማርቆስ)
(
@gize_yayeh)

15/09/2015 ዓ.ም.


@wegoch
@wegoch
@paappii
2024/11/19 22:54:06
Back to Top
HTML Embed Code: