Telegram Web Link
የጤና ባለሙያ ነኝ!
ብዙ ራዕይ አለኝ!!
ትውልድ ላይ አሻራ ማሳረፍ ፈልጋለሁ።
ለሀገሬ በሙያዬ ማበርከት የምፈልጋቸው ብዙ ሀሳቦች አሉኝ። እጅግ የምወዳትና ተስፋዋ እኔ ላይ ያለ እናት አለችኝ በብዙ መዋደድና ደስታ አብሬ ማሳለፍ የምፈልጋቸው ፤ ስኬታቸውን ማየት የሚያጓጓኝ እህትና ወንድም አሉኝ። ወልደን ከብደን ቀሪ እድሜአችንን በመተጋገዝ እንድንኖር ቃል የሰጠሁት ባል አለኝ፤ ይሄ ሁሉ የሚሳካው ግን ስኖር ነው። ያንተ ትንሽ የጎደለች ጥንቃቄ እኔን ህይወት ልታስከፍለኝ ትችላለች። አንተ ብትታመም አንተን ለመርዳት እምቢ እንደማልልህ አንተም ቀድመህ ለመጠንቀቅ እምቢ አትበለኝ።
በአንተ ጥንቃቄ ጉድለት ወረርሽኙ ቢስፋፋ ከምወዳቸውና ከሚወዱኝ ተለይቼ ፤ እራሴን አደጋ ላይ ጥዬ አንተን ለመርዳት ግዳጅ የምወጣበት ቀን ሳይመጣ እኔም አንተም እንጠንቀቅ።
#ህልም አለኝ! #በመጠንቀቅ እርዳኝ!
#HealthProfessionalsChallenge !

@wegoch
@wegoch
#hiwi_ye_enatua_lih
#ኑርልኝ_የኔ_ኮሮና
#ለፈገግታ

ሰሞኑን ኑሮ በጣም ተስማምቶኛል። ባንድ ሳምንት ብቻ ሳልወፍር አልቀረሁም። አኗኗሬ ተቀይሯል። ሆቴል ስሄድ እንደ ድሮው በኪሴ ብር አልይዝም። ሶፍት ነው የምይዘው ከዚያም የፈለኩትን ምግብ አዛለሁ። ስለ ዋጋው አልጨነቅም። ምግቤን አጣጥሜ ከበላሁ በኋላ ሶፍቴን አውጥቼ እንዳላበው ሰው ግንባሬን እጠርጋለሁ። በተለይ ቢሉ ሲመጣ ዝም ብሎ አስነጥስ አስነጥስ ይለኛል ሁኔታዬ ያጠራጠራት አስተናጋጅ መጥታ
«ጌታዬ ምግቡ አልተስማማዎትም እንዴ? ችግር አለ ?» ትለኛለች «ኸረ የለም። ግን ከባድ ትኩሳትና ሳል ይዞኛል» ብየ ኡሁ ኡሁ ማለት እጀምራለሁ። አስተናጋጇ …በድንጋጤ ሁለት ሜትር ለመራቅ ትሞክራለች። 8335 ስትደውል እንደተለመደው መስመር ተይዟል ይላታል። «እሙ ሶፍት የለም? ሶፍቴን ጨርሼ ላበቴን በብር እየጠረኩ ነው ለማንኛውም ግን ሂሳብ » ብዬ ገንዘብ እንዳለው ሰው ከኪሴ ስገባ «በፈጠረህ ተወው ! ሂሳብ በቤቱ ነው» እባላለሁ። ደሞ እኔ ያጨማለኩትን ገንዘብ ማን ይነካል ? ኮራ ጀነን እያልኩ ወደ ቀጣዩ ሆቴል

( አቢ ጌቱ )

@wegoch
@wegoch
"በአንድ ዲንጋይ ሁለት ወፍ "

ቅድም ጠዋት ቤተክርስቲያን ስሜ እየመጣው መንገድ ላይ ሁለት
ትንንሽ ልጆች እድሜያቸው ከ 8-10 ውስጥ ያሉ ናቸው እየተሰዳደቡ ነበር የደረስኩባቸው አንደኛው አጭር ከሲታ ነው አንደኛው ነቃ ያለ መካከለኛ ሰውነት አለው መካከለኛው ልጅ እያከረረ ሊመታው ሲጠጋ ከሲታው እኮ ነው

"ስማ እርቀትህን ጠብቅ ! ስትጠጋኝ አታፍርም ኧረ
በድብድብ ሰበብ ፍጥረህ አጅሬ ኮሮናን ልታስተላልፍ እ ከተማ ለከተማ አትዙር ሲባል እየተንቀጀቀጅክ ያመጣኸውን ልትሰጠኝ 😂 ብሎ ፍራቻ ከኮሮና ስጋት ጋር ቀላቅሎ ተናገረው አንድም ይመታኛል ብሎ በኮሮና አሳቦ መሸሹ ነው ሌላም ሰሞኑን እየሰማ ያለው ነገር ጥሩ አይደለም እና ከኮሮና እራሱን መጠበቁ ነው ያኛው ተናዶ
ሊመታው ሲጠጋ ፖሊስ አጠገባቸው ቁሞ ይህን ትዕይንት ይከታተል
ነበር እና አንተ ብሎ ሲጮኽበት ሁለቱም በተለያየ አቅጣጫ ተፍተለኩ
እኔ እና ፖሊሱ እርቀታችንን ጠብቀን አሽካካን አይገልፀውም ፍሪውን
ልጅ ግን አድንቄዋለሁ በአንድ ዲንጋይ ሁለት ወፍ ነው ^ ጣ ^ ያደረገው ስለተመቸኝ እናንተም ዘና እንድትሉ ብዬ
አጋራዋቹ ።
ሸጋ ድምቅምቅ ያለች ቅዳሜ ተመኘውላችሁ !!
በቃለአብ

@wegoch
@wegoch
አንጋፋው ደራሲና የሐሳብ ሰው ስብሐት ገብረእግዛብሔር ለሰላምታ አምስት ጣቱን ዘርግቶ አይጨብጥም ነበር :: ከዚያ ይልቅ አምስቱንም ጣቶቹን የራሱ እጅ መዳፉ ላይ ጨብጦ ( እጅን ለቦክስ እንደማዘጋጀት ) እድርጎ ነበር እጁን ለሰላምታ የሚዘረጋው ::

እናም ይህ ልማዱን ያስተዋለው ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ እንዲህ ብሎ ጠየቀው

" ስብሐት ለምድንነው ለሰላምታ ግዜ በእጅህ ሰው የማትጨብጠው !? "

የስብሐት መልስ አጭርና ቅኔን ያዘለ ነበር ...


" ሰው እኮ የሚሄደው በእግሩ ሳይሆን በእጁ ነው "


( በስብሐት ገለጻ ' መሄድ ' ማለት ' መሞት ' ማለት ይሆን !? )

////

( ውድ ወገኖቼ እጃችሁን ጠብቁ :: ከልክሉም !! )
@wegoch
@wegoch
@wegoch
የታጋቹ ማስታወሻ
( በእውቀቱ ስዩም)

ዛሬ በጠዋት ተነሳሁ፤ አጠር ያለ ስፖርት ሰራሁ፤ ሳሎኔን አስር ጊዜ ዞርኩት፤ ከዚያ ሳሎኑ በተራው ዞረብኝ፤ ብዙ አልቆየሁም፤ በቁሜ ወደቅሁ፤ ከመድርደርያ ላይ እንደወደቀ የመርቲ ጣሳ እየተንከባለልሁ አራት ደረጃ ወደ ታች ! እምገርም ነው! እስከዛሬ አይቸው የማላውቀው ቤዝመንት አገኘሁ! ቤቱ ባለ ቤዝመንት እንደሆነ አከራዩ ለምን አልነገሩኝም? ተመስጌን ነው! የወደቅሁት ከቤቴ ውጭ ቢሆን ኖሮ አልቆልኝ ነበር፤ ይሄማ አናቱ ላይ ፊጥ ብሎበታል ይሉና በአንቡላንስ አፋፍሰው ይወስዱኝ ነበር! ከዚያ መርምረው ሲያጡብኝ “ ለዛሬ ኔጌቲቭ ነህ ! ይሁን እንጂ ቅድም አቅፎ የጫነህ የአምቡላንሱ ሾፌር ፖዘቲቭ መሆኑን አሁን ስለደረስንበት ከሳምንት በሁዋላ ተመልስህ ና” ሊሉኝ ይችላሉ ፡፡ በማስቀጠል፤ መስኮቴ ላይ ሆኘ ፤በጦር ሜዳ መነፅር አካባቢውን ቃኘሁት ፤ ፖሊስ የለም! ምፅ! ፖሊስ ራሱ ከቤት መስራት ጀመረ ማለት ነው! ያማሪካ ፖሊስ ከቤት ሲሰራ አስቡት!
ዜጋ- “ሄሎ ኦፊሰር ?
ፖሊስ- አቤት”
ዜጋ - ሌባ የቤቴን ሰብሮ ገብቱዋል
ፖሊስ - you kidding me?” እየቀለድህ መሆን አለበት
ዜጋ- ከምሬ ነው
ፖሊስ “- እስቲ አገናኘኝ
ከቤቴ ወጣሁ እና ፓርኩ ላይ በሚገኘው አግዳሚ ወንበር ቁጭ አልኩ! የተራቡ ርግቦች እግሬ ስር ተሰበሰቡ! ትናንት ከቁርስ እስከ እራት ድረስ ቅርፁን እየቀያየርሁ የበላሁትን በሶ በተነንኩላቸው፤ በሶው ኤክስፓየርዴቱ እንዳለፈ ያወቅሁት ሁለቱ ወፎች እዛው አረፋ ደፍቀው ሲሞቱ ሳይ ነው! ወገን! እና ጊዜው ያለፈበት በሶ በልቼ ያልሞትኩት ሰውየ የተበየደ ፍሬሽ ጉንፋን ይገለኛል ተብሎ ይታሰባል? እሱስ ድብን አድርጎ ሊገለኝ ይችላል! ብቻ የምችለውን ያክል ተጠንቅቄና አስጠንቅቄ ከሞትኩም አይደብረኝም! በሳልና በሳቅ መሀል ለመሞት ዝግጁ ነኝ፤ ድንገት በየነ ናፈቀኝ! ልደውልለት ስልኬን ካነሳሁ በሁዋላ መልሼ ተውኩት ፤ በዩማ (በየነ ሲቆላመጥ ነው) ከሶስት ቀን በፊት ስልኩ ከእጁ አምልጦ ተፈጥፍጦበታል ፤ በዚህ ዘመን ስልክህ ከወደቀ እጢህ ወደቀ ማለት ነው፤ አንደ ወትሮው ፤ ሞባይል ቤት ሄደህ ማሳከም አትችልም፤ በዚህ ብቸኝነት ላይ ስልክ ጎድሎበት አስበው! አስቢው! ስልኩ እንዴት እንደ ተፈጠፈጠበት በሚቀጥለው ክፍል እፅፋለሁ በዚህ ሳቢያ የበየነ አመል ከፋ !
ባለፈው በሜሴንጀር ደወልኩለት
“ ምን ፈለግህ? “ ብሎ አንባረቀብኝ!
“ ትርፍ ማስክ ካለህ እንድትልክልኝ ፈልጌ ነበር” አልኩት፤
“ ያንተን ፊት ማስክ አይመክተውም! መለስተኛ ድንኩዋን ሰፍተህ ጣል ብታረግበት ይሻልሃል”
በጣም ነቀልኩ! ለእልኩ ብየ፤ ከንፁህ አንሶላና ከሽራ ጫማ ማሰርያ የተደቀለ ቆንጆ ማስክ ሰርቼ ለብሼ ሰልፊ ተነስቼ ላክሁለት፤ ፎቶየን አይቶት ሲያበቃ እንዲህ እሚል ምላሹን ሰደደልኝ፤
“ በስመአብ! አላሙዲ አጥሮ የዘነጋውን መሬት መስለሀል ! ደሞ ያምርብሃል! ወረርሽኙ ከተወገደ በሁዋላ እንኩዋ እንዳታወልቀው ፓርኩ ውስጥ ያለው አየር በጣም ንፁህ ነው! የመኪና ፈስ የኢንዱስትሪ ግሳት አልበከለውም! ይሄ ንፁህ አየር ተመልሼ ላላገኘው እችላለሁ ! ለምንም ለምንም ብየ አንድ ጀሪካን ቀድቼ ወደ ቤቴ ገባሁ!

@wegoch
@wegoch
@wegoch
የታጋቹ ማስታወሻ(2)
ካለፈው የቀጠለ
(በእውቀቱ ስዩም)
“hi ”
የሚል መልክት ስልኩ ውስጥ ገባ! ገረመው! ካራት ወር በፊት ለላከላት ሰላምታ ዛሬ ምላሽ መስጠቱዋ ነው ፤ መልስ ትሰጠኛለች ብሎ ጠብቆ አያውቅም ፤ ዝነኛ ተዋናይት እና በተምሳሌትነት የታወቀች ሴት ናት ፤ እንደሱ ላለ ሰው ጊዜ አልነበራትም ! ዛሬ ግን ምላሽ ሲያገኝ ገረመው! ግን ብዙ ሊገርመው አይገባም! ቀሳ ወጥታለች! ውሎዋ ከስልኩዋ ጋር ነው! ለከረሙ መልክቶች ሁሉ በፅሞና ምላሽ የምትሰጥበት ጊዜ አላት: :
“ እንዴት እንደምወድሽኮ” የሚል ምላሽ ሰደደላት!
“ አመሰግናለሁ”
“ የህይወት ዘመን ፎንቃየ ነሽ ብልሽ አታምኚኝም”
“ አይ እንግዲህ ! ”
“ የሚገርምሽ ከመደወልሽ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ፤ ፕሮፋይ ላይ ያለውን ፎቶሽን እያየሁ ስመታ ነበር፤”
“ ምንድነው እምትመታው?
“ ከበሮ!”
“ ተው ባክህ!”
“ ቁመናየን ይንሳኝ”
ትንሽ ሲያወጉ ከቁዩ በሁዋላ ፤
“ ያው እንደምታቂው ሞት ከቦናል ! እኔ ከፋም ለማም አብይም እስካሁን ኖርያለሁ ! ከዚህ በሁዋላ በህይወቴ የምጠይቀው አንድ ነገር ነው ! ጡትሽን! ጡትሽን ፎቶ አንስተሽ ላኪልኝ! “
የላከውን አይታ ከድፍረት ቆጥራ asshole (ብሽቅ!) ብላ ብሎክ ታረገኛለች ብሎ ጠብቆ ነበር፤
“ ምን ይጠቅምካል ?” የሚል መልስ ላከችለት!
“ ለመጨረሻ ጊዜ ደስ ብሎኝ ልሙት ! ከተረፍኩ ደግሞ ባንች ሰበብ እንደተረፍኩ እቆጥረዋለሁ”
“አልገባኝም”
“ እውነቱን ንገረኝ ካልሽኝ በጣም ደብሮኛል! መሞት ፈርቼ እንዳይመስልሽ! ህይወቴንና ዶላሬን ለሀገሬ ስቆጥብ የኖርኩ ሰው ነኝ! አገሬ ገብቼ፤ ህዳሴው ግድብን ከግብፅ ወረራ እየተከላከልኩ ከመሰዋት ያለፈ አላማ ኖሮኝ አያውቅም! በቻይና ቫይረስ ተነድፌ ፤ ባሜሪካ ሆስፒታል ውስጥ መሞቴን ግን ልቀበለው እማልችለው አሰቃቂ ቅዤት ነው ! ደሞኮ እንዳገራችን ወግ በፍትሃት በፀሎትና በሙሾ መሸኘት በስንት ጣሙ ! ከሞትኩ፤ ብድግ አድርገው የቄራ ፍሪጅ የተገጠመለት ሲኖትራክ ውስጥ ይወረውሩኛል !
“ ያ እንዳይሆን በተቻለኝ መጠን አጥብቄ እጠነቀቃለሁ! ቤት ውስጥ ሳይቀር ማስክ አደርጋለሁ፤ ፈረንጅ ስለማላምን ራሴ የሰራሁት ማስክ ነው ነው እማደርግ ! ማስኬ ባለሶስት ገበር ነው! የፊትና የሁዋላ ኪስ ሳይቀር አለው፤ በርግጥ፤ ወፍራምና ክብ ፊቴ ለማስክ አልተፈጠረም! ቅድም በመስታውት ራሴን ስመለከት አዘንሁ! … ዳንቴል የለበሰ ግማሽ ድፎ መስያለሁ ፤ ደሞ ስተኛ ራሱ አላወልቀውም! ታፍኜ እንዳልሞት ፀልይልኝ”
“ የኔ ጡት መላክ ከዚህ ሁሉ ጋር ያለው ግኑኝነት አልገባኝም” አለቺው፤
“ ጡትሽን ብትኪልኝ በድብርትና በትካዜ ሳቢያ ስራ ያቆሙት ህዋሳቴ ይነቃቃሉ፤ ተነቃቅተው የተፈጥሮ ሞርታርና ባዙቃ ያመርታሉ፤ ኮሮናን ለወሬ ነጋሪ ሳያስቀር ይደመስሱታል፤ በመጣበት እግሩ ይመልሱታል”
ፀጥ ብላ ቆየች፤
ከዚያ
…typing typing
ዝም!
ከዚያ
...uploading picture
ትንፋሹን ዋጥ አድርጎ ጠበቀ!
ወድያው የስልኩ ስክሪን ወገግ አለ!
ጡት!
ማተብ የሚያነጥር ጡት!
እንኩዋን በዳበሳ፤ በመብረቅ የማያቀል-ጡት
ጡት!
ስልኩ ከጣቶቹ ላይ አመለጠ! ከደረጃው እየነጠረ ወርዶ ከታች ባለው የድንጊያ ንጣፍ ላይ ተኛ ! ከጥቂት ሰከንዶች በፊት ስልክ የነበረው አሁን ዝሆን የረገጠው የሰርዲን ጣሳ መስሎ ተጋደመ ! በየነ በድንጋጤ ውሃ ሆኖ፤ የስልኩን ስክሪን ገልብጦ ተመለከተው ! እውር ሸረሪት ያደራው ድር መስሎ ነበር!

@wegoch
@wegoch
ጓደኛዬ ነው

እጮኛ አለችው የምትወደው አንድ ቀን ቤተሰቦቿ ጋር እራት ልትጋብዘው ቀጠረችው፣ ሰው ለ እራት ግብዣ ወደ ግሮሰሪ ሄዶ ውስኪ ወይ ወይን ይገዛል እሱ ግን የሄደው ወደ ፋርማሲ ነው።
ለፋርማሲስቱ ሰውዬ ምን ይለዋል የውልህ እጮኛዬ ዛሬ እራት ጋብዛኛለች ከእራት በኋላ መኝታ ቤቷን ላስጎብኝህ ማለቷ ስለማይቀር አጋጣሚውን ለመጠቀም ኮንደም መያዝ አለብኝ አንድ ኮንዶም ስጠኝ አለና ገዝቶ ሊወጣ በሩ ጋር ከደረሰ በኋላ ተመልሶ... በነገራችን ላይ ሌላ አንድ ብትጨምርልኝ ደስ ይለኛል እጮኛዬ በጣም ቆንጆ እህት አለቻት እና ሁሌ አይኗ እኔ ላይ ነው ስለዚህ የሷንም ክፍል የምጎበኝበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል። አሁንም ሊወጣ በሩ ጋር ከደረሰ በኋላ ጌታዬ መቼም አትታዘበኝ የእጮኛዬ እናት እንዴት ያለች ቆንጆና አማላይ መሰለችህ በዛ ላይ ብዙ ጊዜ አስተያየቷ ሌላ ፍላጎት እኔ ላይ እንዳላት የሚናገር ነው የሷንም መኝታ ቤት ልጎበኝ የምችልበት አጋጣሚ ስለሚኖር አንድ ኮንደም ጨምርልኝ። አለና በተቀጠረበት ሰአት የእራት ግብዣው ላይ ተገኘ ሁሉም ቤተሰቦች ለእራት ተቀምጠው ደረሰ በጠረጴዛው ላይም እጮኛው በቀኝ በኩል የእጮኛው እህት በግራ በኩል የእጮኛው እናት ከእህትየው ጎን እና አባትየው ፊት ለፊት ተቀምጠዋል። ድንገት ጀለሴ እኔ ጸሎት ጸልያለሁ ከምግቡ በፊት ብሎ አቀርቅሮ ጸሎት ጀመረ
ሲጸልይ
ሲጸልይ
30 ደቂቃ አለፈው ሁሉም ግራ ተጋቡ ጸሎቱ ረዘመባቸው እጮኛው ወደ ጆሮው ጠጋ ብላ የኔ ውድ ይህን ያህል ጸሎተኛ መሆንህን አላውቅም ነበር እኮ ስትለው አንገቱን ቀና ሳያረግ የኔ ውድ እኔም እኮ አባትሽ ፋርማሲስት መሆኑን አላውቅም ነበር። 😊

@wegoch
@wegoch
@paappii

#biniyam behaylu
★★ሞቴን ቀማኝ…… ክፍል 1

"እግዜር የሰውን ልጅ የፈጠረው እንዲያመሰግነው ነው።" ይለኝ ነበር አባቴ … …

እንዳመሰግነው አንድስ እንኳን ሽራፊ ምክኒያት ያልተወልኝ ፈጣሪ የምስጋና ነዶ በምን ሂሳብ ከኔ ይጠብቃል?

የምኖርበት አንዳችም ምክኒያት የለኝም። …… አንዳችም የመኖር እንጥፍጣፊ ፍላጎትም የለኝም። …… ራሴን ላጠፋ ነው። ቢሆንም ከመሞቴ በፊት ወደ ደጁ እየሄድኩ ነው…… ነፍሴን እንዲምራት ልማፀነው አይደለም…… በፍፁም……… ቢሻው አይማራት። ……

ለብዙ ዓመታት ሀዘኔ ሲበረታ እንዳደረግኩት "በእሳት ውስጥ አንተ መንገድ አለህ፣ በውሃም፣ በወጀብም መሃል…… መውጫዬን አበጅልኝ……" ምናምን እያልኩ የማይሰማ ፀሎት ላደርስም አይደለም ደጁ የምገሰግሰው። …… ዛሬ ደጁን ለመጨረሻ ጊዜ የምጎበኘው ለምስጋናም፣ ለወቀሳም፣ ለልመናም…… ከእግዜሩ ጋር በተያያዘ አይደለም። …… ለፅድቁም ይሁን ለኩነኔው ልሄድለት አይደል?…… እዛው ለማገኘው ለደቂቃዎች ልዩነት እሱን ፍለጋ አልመጣም። ……………

የምሰናበተው ዘመድ አዝማድ የለኝም። ብሞት የምጎዳው አንድም ወገን የለም። ……… ግን የምሰናበተው ትዝታ አለኝ። የልጅነት ፣ የወጣትነት፣ የፍቅር… …… ትዝታ!!!

እናም ደጁ ተሰየምኩ። የእግሩን ኮቴ እንደሚቆጥር ሰው እግሮቼን እየጎተትኩ ደብሯን ዞርኳት። …… አንዱን ዛፍ ተጠግቼ ሳሩ ላይ ተቀመጥኩኝ። ………

"ኪዳነምህረት ምን በደልኩሽ ግን?" አልኳት… …… ድሮ ህፃን እያለሁ እንደማስበው ኪዳነምህረት በሴትነቷ ካዘነችልኝ ብዬ ነው መሰለኝ። ……

ደብሩ ከፈጣሪ ጋር መገናኛዬ ብቻ አልነበረም። ያለፈው ዝፍዝፍ 23 አመታት ህይወቴ ገፆች ነው። …… አባቴ እዚሁ ቄስ ነበር። ……… ሰባኪ ብቻ አይደለም። …… ቅንነት ያልተለየው የሰበከውን ሊኖር የሚታገል የዋህም ነበር። …… ሽንብራ ቆርጥሞ የጮማ የሚያመሰግን፣ ውሃውን ጨልጦ የወይን የሚያወድስ…… ልግስና ከእጁ፤ ፈዋሽ ፈገግታ ከፊቱ የማይለየው ቸር ሰው።

… የደብሩ ሳሮች ላይ የልጅነቴ ዳናዎች አሉ። ……… በአባዬ ትከሻ ላይ እንኮኮ ተቀምጬ እየተንጠራራሁ የዳበስኳቸው ዛፎች ላይ አሻራዎቼ አሉ።

…… እማዬ ልታቆርበኝ መስቀልኛ ባሰረችልኝ ነጠላዬ ውስጥ የእንጀራ ድርቆሽ ደብቄ ስኮረሽም አጠገባችን የቆሙት ሽማግሌ
"ይህችን ልጅ አታቁርቧት እህል ብጤ እያላመጠች ነው።" ሲሏት ሰምቼ የተፋሁት የላመ ድርቆሽ ሳሩ ላይ ትዝታው አለ።

ብዙም ሳይርቅ ከደብሩ ጀርባ የኔታ ሀ ሁ ሂ… …… ሲያስቆጥሩኝ

"በይ ይህቺን በያት" ሲሉኝ

"የኔታ ሽንቴ መጣ" ስመልስ

"በይ ሰበብ አትወሽክቺ በያት" ሲሉኝ

"ቀ " ስለመልስ

"በይ አሁን ዝለቂና ሸንተሽ ነይ" ሲሉኝ

"አይ…… የኔታ አሁንማ ይተውት ቀሚሴ ላይ አመለጠኝ" መልሼላቸው የፊደል ቤቱ ማቲ ሁላ በሳቅ ያውካካብኝ… ……
የኔታ ባለቀ ጥርሳቸው እየሳቁ ለአባዬ የነገሩብኝ።……… የልጅነት ትዝታዬ…
ሳቃቸው ጆሮዬ ላይ አለ።

ፍቅረኛዬ የአብስራም እዚሁ ደብር የአባቶች እግር ስር ሲማር ፣ አባቴጋ አሹቅ ላደርስ ስመጣ ነው የማውቀው… … ሁለታችንም ቤተሰቦቻችንም ሆነ እኛ ከደብሩ ውጪ ህይወት የሌለን ነበርና መገናኛችን እዚሁ ነበር። ደጁ ተሰይመን ፍቅራችንን እንዲያበዛልን ስንቴ ለምነነዋል? ……… "ኪዳነምህረትዬ ቶሎ እንዲያገባኝ አድርጊው" ብዬ የአብዬ ሳይሰማ የለመንኳትስ እዚሁ አይደል? ……

በዚያ አዝግም የህይወት ጎዳናዬ የማውቃቸው፣ የምኖርላቸው፣ የሚኖሩልኝ… … ሶስት ሰወች ከዚህ ደብር ጋር የተዛመዱ ናቸው። ……… ከመሞቴ ደቂቃዎች በፊት ልሰናበት የመጣሁት የነሱን ትዝታ ነው። እነሱን ነው። ………

አባዬን በሞት ሳጣው ፈጣሪን አላማረርኩም። ……

ለቤተሰቦቼ ተስለው በስተርጅና የወለዱኝ ብቸኛ ልጃቸው ነኝ። …… ከአድባር አድባር እየዞሩ ተስለው ፍሬያቸውን ለማየት ሳይታደሉ አመታት ተቆጠሩ። በስተመጨረሻ አባዬ ኪዳነምህረት መጥቶ ተሳለ… …… ልጅ ከሰጠችው እስከእለተ ሞቱ በደብሯ ሊያገለግል…… ሰማችው…… ዘመድ አዝማዴን ሳይል በወጣትነቱ ወደተወው ድቁንና ተመልሶ ሲማር ኖረ…… ሲያስተምር አረጀ። …… ሞተ።…… የሱን ሞት ተከትላ እማዬ ታመመች። ………

በአመት ልዩነት እናቴን ሲደግማትም… … "ምናለ እኔንም ብትወስደኝ?" ብዬ መመረሬን ደጁ ተነጥፌ ማረኝ ብዬዋለሁ። ………

ብቸኝነቴን በፍቅር የሞላው የአብዬ እንዳመሰግነው ብዙ ምክንያቴ ነበር። …… በየእለቱ ተመስገንን አላጎደልኩም። …… አሁን ግን የምስጋና ቋቴ ደረቀ። ……… የአብስራ ከአለምና ከኔ ፍቅር የፈጣሪው ፍቅር አየለበት። ……… "እኔ ሚስት አላገባም። የመድሀኒያለም ባሪያ ሆኜ መኖርን መርጫለሁ።" ብሎኝ ከአለም ጋር ክዶኝ ሄደ።

ለምን ባለፀጋ አልሆንኩም? ለምንስ ከፊደል ቆጠራ የዘለለ አዋቂ አልሆንኩም? ብዬ ጠይቄ አላውቅም። ………"……… ካንተ ምንም አልፈልግም በምድርም ያለ ሀብት፣ በተራሮች ያሉ ከብቶች፣ በሰማይም ያለ ሁሉ የኔ ነው" ያለ ባለፀጋ ፈጣሪ መበልፀግን እንደማይፀየፍ ባውቅም……… አሹቅ እየቃሙ ማመስገንን ተምሬያለሁና ከእለት እንጀራዬ ያለፈ ልመና የለኝም።

"ጤና ስላደረገሽ አመስግኚው" ይለኝ ነበር አባዬ

ጤንነት ምንድነው? ብቸኝነት ከካንሰር የበለጠ እንደሚያቆስል አያውቅማ!!
ፍቅርን ማጣት ከደም ብዛት በላይ ነፍስን ከስጋ እንደሚነጥል አያውቅማ!!!

ለምን ልኑር? ለማን ልኑር? …… ኖሬ የምሞላው የትኛውን ሽንቁር ብዬ? ኖሬ የምፈታው የትኛውን ቋጠሮ ብዬ? ……… ……
…………
…………
የስንብት ቃል የለኝም እና እንባዬ ብቻ ይፈሳል። ሳግ የሰማሁ መስሎኝ ዞርኩ። …… …… አልተሳሳትኩም። አምስት ክንድ በሚያህል ርቀት አየሁት። …… በጉልበቶቹ መሬቱ ላይ ተንበርክኮ አይኖቹን ወደሰማይ ሰቅሎ እጆቹን ደረቱ ላይ ወደ ትከሻው መስቀለኛ አጣምሮ በአራት መንገድ የሚፈሰውን እንባውን ሳይ የሰማሁት ሲታገል ያመለጠውን ሳግ እንደሆነ ገባኝ። የእኔንም እንባ እንዲያነባልኝ የሰጠሁት ይመስል …… እንባዬ ደርቆ አየው ጀመር። ……
ከሚፈሰው እንባው ጋር የምስጋና ናዳውን ያዥጎደጉደው ጀመር። ……… እንባው ከሃዘንም ጥልቅ መሆኑ ያስታውቃል። ግራ ገባኝ። …… እያመሰገኑ ለቅሶ
……… ተጠግቼ ብጠይቀው በወደድኩ። …… ፈራሁት። "ማነሽ? ወደየት ታውቂኛለሽ? ምንስ አገባሽ?" ያለኝ እንደሆነስ? ብዬ ፈራሁ። እውነትስ ምን አገባኝ? የኔን ሀዘን ማን ይዘንልኝ ብዬ ነው በሞቴ ጫፍ ላይ የማላውቀው ሰው እንባ የሚገደኝ? ፊቴን መለስኩኝ። ………… ሀሳቤን መመለስ ግን አልቻልኩም። ……

………
………
……
አልጨረስንም……


@wegoch
@wegoch
@paappii

#meri_feleke
© ዳንኤል ክብረት
አንዳንድ ሰው አለ ከጣና 'ሚሰፋ
ካባይ የሚጋፋ
ከዋርካ 'ሚፋፋ።
አንዳንድ ሰው አለ ሁሉ የሚሰጠው
ሁሉ 'ሚጨብጠው
ሁሉ 'ሚያዳምጠው።
አንዳንድ ሰው አለ
አንድ ቦታ በቅሎ ለሁሉ 'ሚበቃ
ሁሉን የሚያነቃ
ሁሉን የሚያበቃ።
አንዳንድ ሰው አለ የሁሉ ማረፊያ
ሁሉን መደገፊያ
ሁሉን መታቀፊያ።
በዘመናት መሐል ድንገት ተከሥቶ
ለሰው ሁሉ ታይቶ
ያንን ዘመን ዋጅቶ
ፈጣሪ መኖሩን ለሰው አመልክቶ
ወደላይ የሚሄድ ከወደ ላይ መጥቶ።
አንዳንድ ሰው አለ.....
.................................................................
"አላህ በከንፈር የሚሸነገል ሞኝ አይደለም! አላህ
የሚፈልገው ልብን ነው።"
(*ተቀዳሚ ሙፍቲህ፥ ዑመር ኢድሪስ)
===============
ክቡር ተቀዳሚ ሙፍቲህ የጸሎት መርኀ ግብር ላይ እንዲህ አሉ፡-
"ዱአ አድርግ ስትሉኝ 'አይኾንም' ያልዃችሁ
ወንድሞቻችን የኦርቶዶክስ አባቶች ሲጸልዩ
ኹላችንም ቁመን 'አሚን!' ብለናል። ያ ጸሎት በቂ
ነው ብዬ እንጂ ለሌላ አይደለም፤" አሉ ።
እኒህ ታላቅ አባት ንግግራቸውን ቀጠሉና፣ እንዲህ አሉ፥
"ከተመለስን ከልባችን እንመለስ! አላህ በምላስ
የሚሸኝ ጌታ አይደለም፤ አላህ በከንፈር የሚሸነገል
ሞኝ አይደለም።
አላህ የሚፈልገው ልብን ነው፤ አላህን
ምን እንዳስቀየምነው ታውቁታላችኹና
አልነግራችሁም።
አላህ የምንሠራውን ያውቃል!
ዛሬ ወንዱም ሴቱም ተጨመላልቋል፤ ወንዱ - 'ሴት
ካልሆንኹ' አለ፤ ሴቱም- 'ወንድ ካልሆንኹ' አለ፤
በቤተ ክርስቲያንም በመስጂድም ፈጣሪን በደልነው፤
በዘር ተከፋፍለን አስቀየምነው፤ በዚህም ምክንያት
'እናንተ አገልጋዮቼ አይደላችሁም ጠላቶቼ ናችሁ' ብሎ
ከቤተ ክርስቲያንም ከመስጂድም አስወጣን።
አላህ ቸር ነው!
በአንዴ ማጥፋት ይችል ነበር። ነገር ግን
አላደረገውም። በነፋስ አስፈራራን፤ በጎርፍ አስፈራራን፤
እኛ ግን አልተመለስንም።
አኹን ደግሞ መድኃኒት የሌለው በሽታ አመጣብን፤
አኹንም ከዚህ የባሰ መከራ እንዳይመጣብን
ከልባችን ኾነን ወደ አላህ እንመለስ!
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ፣ ኹሉም ፖለቲከኛ ከልብ
ኾኖ ሕዝብ ይስማ! የሃይማኖት አባቶችም ከልብ
አላህን እናገልግለው!
ሕዝብም የአባቶችን ምክር ይስማ! እርስ በርሳችንም
እንተዛዘን እንተሳሰብ! እንደዚህ የኾነ እንደኾነ አላህ
ይቅር ይለናል። መከራውንም ይመልስልናል።
ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሰደብበት፤ የሃይማኖት
አባቶች የሚሰደቡበት ወቅት ላይ ነው ያለነው። እኛ
ብንሞኛኝ አላህ አይሞኝም፤ ስለዚህ ከታች ጀምሮ ሥነ
ሥርዓት ይያዝ!
ወላጆች ልጆቻቸውን ሥነ ሥርዓት ያስይዙ!
መምህራንም ተማሪዎችን ሥነ ሥርዓት ያስይዙ!
መሪዎቻችንም ሕዝብ የሚላችሁን ስሙ!
እኛም እርስ በርሳችን እንተዛዘን!
የዚህ ወረርሽ መድኃኒቱ ይገኛል፤ ኢንሻ አላህ!!
ትንሹም ትልቁም 'ከእኔ በላይ የለም' የሚለው ኹሉ
ተንቀጥቅጧል። አላህ ከልባችን የምንመለስ
ያድርገን!" አሉ።
ለእኚህ ትልቅ ሰው አምላክ ረጅም ዕድሜ ከጤና ጋር ይስጥልን።
@wegoch
@wegoch
@wegoch
★★★ ሞቴን ቀማኝ ★★★
(ክፍል ሁለት)

አጠገቡ ተጠግቼ ተቀመጥኩ። …… አቅፌ ባባብለው በወደድኩ…… ስርቅታው እንዳይሰማ ሲያፍነው የፊቱ ገፅታ ልብን የሚሰብር ማሳዘን አለው፣ የአንጀቱ መንሰፍሰፍ ሆድ ያላውሳል…… የኔ መጠጋት ከለቅሶውም ከምስጋናውም አላናጠበውም። …… የጎረቤት ጨቅላ በአደራ እንደምትጠብቅ ባልቴት… የማደርገው ጠፍቶኝ… ዶፍ ለቅሶውን እስኪያባራ ፈዝዤ እጠብቀው ጀመር…… እንባዬ ደርቋል። ለመሞት ማቀዴ በጭላንጭል ትዝ ይለኛል……

ፊቱን በእጆቹ ደባብሶ ከተንበረከከበት ተነሳ…… እንዳልተንሰቀሰቀ…… እንዳልተከፋ… … ምንም እንዳልሆነ ሁሉ ሄደ…… ፈዝዤ ለቅሶውን እንደቅዳሴ እንዳልሰማሁት ከአይኔ ርቆ ሄደ… … ለምንድነበር የጠበቅኩት? …… ለምን እንደጠበቅኩት፣ ምን እንደምለው… ሳይገባኝ ተከተልኩት…… ማን ብዬ እንደምጠራው ስላልገባኝ በሩጫ ደረስኩበት። እጁን ስይዘው ከእንቅልፉ እንደባነነ ሰው ደነገጠ።……

የሞት ጫፍ ላይ የነበረ የህይወት ጎዳናዬን ችላ ብዬ ለምን በሰው ጎዳና እንደምቧችር አላወቅኩትም። ራሴን በማላውቀው ሰው ጎዳና ላይ ዶልኩት። …… ከብዙ ውትወታ በኋላ ውሃ ቅመስ ብዬ ከደብሩ ብዙ በማይርቅ ከደሳሳ መጠለያዬ ደጅ ሳሩ ላይ አሳረፍኩት። …… ውሃ አልሰጠሁትም። …… አይን አይኑን እያየሁ የሚያወራውን እሰማዋለሁ…… ከአፉ የሚወጡት ፊደላት ሳይሆኑ እንቁዎች መሰሉኝ። አፍሼ ብንቆጠቆጥባቸው ተመኘሁ።……

"ህይወት ሁሌም ስለሰዎች አይደለችም። …… ስለራስሽም ናት። ሁሌ ደግሞ ስለራስሽ አይደለችም ስለሌሎችም ናት" ያለኝ ከሀሁ ቆጠራ ላላለፈ የእውቀቴ ጥግ ከበደብኝ……

ከሶስት ሳምንት በፊት:— እንደምትሰበር ጌጥ የሚሳሳላት ሚስቱን ከወንድሙ ጋር ስትባልግ እንደያዛት ነገረኝ። …… በበነጋው ሁለት ልጆቻቸውን ይዛ ከወንድሙ ጋር ከቤት ከመውጣቷ በመኪና አደጋ ሁሉም ህይወታቸው ማለፉን ተረዳ። …… በአንድ ቀን ሁለት ልጆቹን፣ ብቸኛ ወንድሙን እና ሚስቱን የቀበረ እለት ራሱን ስቶ ሀኪም ቤት ገባ…… በህይወት ለመኖር የቀሩት ቀናት ብቻ መሆናቸው እንደተነገረው እያወራኝ በብዙ ሀዘን የታጀለ ፀዳል ፈገግታ ብልጭ አደረገልኝ። ……

"ጌታን የምታመሰግነው ምንም ስላሳጣህ ነው?" አልኩት ሰቆቃው ከሰቆቃዬ ሲነፃፀር ገለባ እየሆነብኝ

"በህይወት ብኖር በቁም ከመሞት የዘለለ እጣ ፈንታ አይኖረኝም ነበር። ሚስቴና ልጆቼን አጥቼ መኖር እንደሚከብደኝ የሚያውቅ አምላክ ሲጠራኝ ከማመስገን ውጪ ምን ይወጣኛል? ለንሰሃ ጊዜ ለሰጠኝ ፈጣሪ ከምስጋና ውጪ ምን ኩነኔ ከአፌ ይወጣል?" አለኝ አቀርቅሮ ለስላሳ እጆቹን እየፈተለ…… የምጠይቀውን አላውቀውም… … ቢመልስልኝ ግን ደስ ይለኛል። …… ምን እንደምመልስለት እንጃ… … ቢጠይቀኝ ግን ደስ ይለኛል።

"ራሴን ላጠፋ ነበር።" አልኩት። ባልገባኝ ምክንያት ስሜቴ ሁሉ የሚገባው ፍፁም መሰለኝ። …… አልደነገጠም። አይኖቹን አጥብቦ ሲያየኝ ሁሉንም ነገርኩት።

"ማንም ሰው ወደአንቺ ህይወት ጎዳና ሲቀላቀል ወይም አንቺ በሌሎች የመኖር ጎዳና ስትቀላቀዪ አንዲት ነገር ይቀበልሻል ወይ ይሰጥሻል። …… በመኖር ዘመንሽ ሁሉ አብሮሽ የሚኖር አንቺ ብቻ ነሽ። አየሽ ህይወት ስለሌሎች የሚሆነው ባጣሻቸው ሰወች መኖርሽ ሲመሰቃቀል ነው። ስለራስሽ የሚሆነው አሁንም ህይወትሽን የሚቀላቀሉ ሌሎች ኮከቦች እንዳሉ ስታውቂና መኖር ስትቀጥዪ ነው። ባለቀ ዘመኔ አንቺ እንደመጣሽው……" ሊለኝ የፈለገው በትክክል እኔ እንደገባኝ መሆኑን እንጃ… … የተናገራቸው ቃላት እውቀትን ይሁን መንፈስን የሰጡኝ እንጃ… … ከተራራ አናት ላይ ብቅ እንዳለች የጠዋት ፀሃይ የሩቅ ተስፋ ስሜት ሰጠኝ። ……

"ስንት ዓመት ይሆንሻል?" አለኝ

"ያለፈው ህዳር ሚካኤል 23 ዓመቴ"

"ካንቺ በሁለት ዓመት የሚበልጥ በልጅነቴ የወለድኩት ልጅ አለኝ። ምን እንደሚመስል አላውቅም። አይቼው አላውቅም። …… " የዳመነ አይኑን ለማስታገስ ዝም አለ።

በልጅነቱ እቤታቸው ከምትሰራ ሰራተኛ መውለዱን እና ቤተሰቦቹ ስላባረሯት ወደ ገጠር መምጣቷን ነገረኝ። …… በሞቱ አፋፍ ላይ አጠያይቆ ከኛ ደብር በእግር የ8 ሰዓት መንገድ ርቀት ላይ ያለ ገጠራማ ቦታ ከእናቱጋ መኖሩን ስለሰማ ሊያየው መምጣቱን ነገረኝ።

"ይቅርታ እንዲያደርግልኝ አልጠብቅም። …… አይኑን ብቻ አይቼው መሄድ ነው የምፈልገው።" አለኝ ፀፀቱ አይኖቹ ውስጥ እየጮኸ… …

ሲሄድ እያየሁት ልቡ ብቻ ሳይሆን እግሩም የተሰበረ፣ ከትከሻው የጎበጠ መሰለኝ። …… ብቻዬን ቀረሁ። …… ወደቅድሙ ብቸኝነቴ ግን መመለስ አልቻልኩም…… ላለቅስ ብፈልግ እንባ ራቀኝ፣ መከፋት ብፈልግም ልቤ በማያውቀው ተስፋ ይፈነጥዛል…… ምን አገኘሁ? ኸረ ምንስ ቢለኝ ነው? ለዚያውም ካለኝ ከግማሽ በላዩ ነው ያልገባኝ…… ከየት የመጣ ተስፋ ውስጤ ፈነጠቀ? …… የተናገረኝ ቃላት ህይወት ነበረው። ዓረፍተ ነገሩ ግልፅ ባይልልኝም…… ነፍስ እፍ ሲልበት ለነፍሴ መነቃቃት ሰጥቷታል። ……

በማላውቀው የደስታና የተስፋ ውሽንፍር እየተላጋሁ በሶስተኛው ቀን አመሻሽ ላይ የቆርቆሮ በሬ ተንኳኳች። …… ያ እየሞተ ለኔ መኖር የሆነኝ ሰው ነበር። …… አብሮት ያለው ወጣት ልጁ መሆኑን መናገር አይጠበቅበትም። …… የጠፋ ወዳጁን እንዳገኘ ሰው ተጠምጥሜ አቀፍኳቸው። …… የተሰማኝ እንደዛ ነው……የቅርብ ሰወች……

"እሰይ! እንኳን ኪዳነምህረት ተለመነችህ! …… " አልኩት ገብተው ከመደቡ እንዳረፉ
ከደቂቃዎች በኋላ መለወጡ ታየኝ

"ምነው? አመመህ እንዴ?" አልኩት

"ትንሽ አወን!"

አባዬ እያለ እንግዳ እቤታችን ሲያርፍ እንደሚደረገው ለእግራቸው የወዘፍኩትን ውሃ አቅርቤ ከብዙ እንቢታቸው በኋላ እግራቸውን ተራ በተራ አጠብኳቸው። ……

እኔና አባቱ ስንጫወት ምንም ቃል ሳይተነፍስ የቆየው ያሬድ
"ለምን ጠዋት አብረሽን አዲሳባ አትሄጂም?" አለኝ

"እውይ…… ምን አደርግ ብዬ?" መለስኩለት

"እኔ ከብቶቹን ጥዬ ብዙ መሰንበት ስለማልችል ታስታምሚዋለሽ።" አለ

አባቱ ላይ ያለውን ቅሬታ እንዳላነሳ ገባኝ። ከሁለት ሳምንት ያልበለጠ ጊዜ ለሚቆይ አባቱ ከብቶቹን ማስቀደሙ ቅያሜውን ማሳያ መሰለኝ።

"ትንሽ ራስሽን የምትደግፊበት ነገር ላደርግልሽ አስቢያለሁ።" አለኝ አባቱ… … ያሬድ ደስ አላለውም። የተከፋ ፊት አሳየ…… ……
……
……
አልጨረስንም……
………

@wegoch
@wegoch
@paappii

#meri_feleke
Forwarded from Mykey (Mikiyas Liyew Mykey)
''ጥንቃቄ ይጠብቅሃል  ÷
ማስተዋልም ይጋርድሃል''
ምሳሌ 2÷11

@Mykeyonthestreet
ተቃራኒ ለሚወዱ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን መውጣት ያለበት ዐዋጅ።
#daniel_kibret

ስማ ስማ፣ ያልሰማህ ተሰማማ። ከዛሬ ጀምሮ ማንም ቤቱ እንዳይቀመጥ። የቻለ ከከተማ ውጭ፣ ያልቻለ ከተማ ውስጥ፣ ያልቻለም ሠፈር ውስጥ ያውደልድል። ቤቱ የተገኘ የ3 ወር ደመወዙን ይቀጣል። መብራትና ውኃም ይቋረጥበታል። እጅ መታጠብ ለአንድ ዓመት ተከልክሏል። እጁን ሲታጠብ፣ ሲፈትግ የተገኘ የታጠበበትን ውኃ እንዲጠጣው ይደረጋል። በሳሙና ከታጠበ ደግሞ ዐረፋ የሞላ በርሜል ውስጥ ውሎ ያድራል። ሰው ሁሉ ከቻለ ተዛዝሎ፣ ካልቻለ አንዱ ሌላውን አንጠልጥሎ፣ ያም ካልሆነ ተቃቅፎ ፣ ከባሰም ተደጋግፎ እንዲሄድ። ሲራራቅ የተገኘ ከፍ ብሎ አንገቱን ዝቅ ብሎ ባቱን ይቆረጣል። ይህ ዐዋጅ ቢወጣ፣ ሕዝቡ በተቃራኒው ስለሚሠራ የተፈለገው ለውጥ ይመጣ ነበር።

@wegoch
@wegoch
ቁጥርና ቅዳሜ
(ልዑል ሀይሌ)

20 ሰው ጭኖ ሲሄድ የነበረ ታክሲ እሷ ከታክሲው ስትወርድ እንዴት በቅፅበት ባዶ ሆነብኝ?... እንዴት አንድ ሴት በአንዴ 20 ሰው ልትሆንብኝ ቻለች? ...ተመለሺ ልላት ስልኳ ሊሆን የሚችል ቁጥር ለመገመት በማሰላሰል ላይ ሳለሁ "ሂሳብ!" ሲለኝ "ስንት ነው?" ስለው "4 ከ 50" ሲለኝ ስልኳ 45 ቤት ሊሆን እንደሚችል ጠረጠርኩ "መልስ ስጠኝ!" አልኩት ረዳቱን "ምን አስሬ ትጨቀጭቀኛለህ?" ሲለኝ 0945 ቀጣዩ ቁጥሯ 10 ሊሆን እንደሚችል ለመጠርጠር አፍታም አልፈጀብኝ 094510...ቀጣዮቹን የልጅቷ ቁጥር ለመገመት የሆነ አንዳች ጭቅጭቅ መፍጠር ስለነበረብኝ "ምንድነው ታክሲው መስኮት የለውም? ታግተን ነው? ወይስ ተሳፍረን?" ስል የሌሎቹም ተሳፋሪዎች ድጋፍ ተሰጠኝ..."አዎ ይከፈት!..ታፍነን እንሙት እንዴ?.." እኔ ይህን የጭቅጭቅ ርዕስ ያመጣሁት ቁጥር ቢጠሩና የልጅቷን ስልክ ለመገመት ቢረዳኝ ብዬ እንጂ ውጪ የሚጥለውን በረዶ የቀላቀለ ዝናብ እያየሁ...እንኳን መስኮቱ ይከፈት ልል ይቅርና ታክሲው ለያንዳንዱ ተሳፋሪ ብርድ ልብስ ቢኖረው
የመጀመሪያው ለባሽ እኔ እሆን ነበር የምሆነው... በመሃል አጠገቤ ያለው ተሳፋሪ ወደኔ ዞር ብሎ "ይገርምሃል ይሄ መንገድ ከተሰራ 15 ቀን አይሞላውም ግን ጎርፉ እንዴት እንዳጥለቀለቀው ተመልከት" ሲለኝ "ጥሩ ነዋ!" ብዬው የልጅቷን ቁጥር ግምቴን ገፋሁበት ……15 ቀን ካልሞላው 14 መሆን አለበት 09451014... ይሄን ቁጥር ፅፌ ካጠገቤ ያወራኝን ተሳፋሪ ተመልሼ ሳየው "ያመዋል እንዴ?!" በሚመስል የግርምት እይታ ሲያየኝ አስተዋልኩ...እኔም ምላሼን 'ጠረባ' በሚባል ክፉ እይታ አንስቼ አፈረጥኩት... ቀጣዩን የቁጥር ግምት የማገኝበትን ሰበብ እየፈለግኩኝ ባለበት ሰዓት ከኋላ ወንበር የነበረችው ተሳፋሪ "ወራጅ አለ!..አንዴ አሳልፈኝ" ስትል ጆሮዬ ውስጥ ጥልቅ አለ። እኔም የተሰጠቺኝን ቁጥር የስልኬ 'በተን' (ቁጥር መምቻ) ላይ ፅፌ ሰፊውን ህዝብ
ለማሳተፍ በሚል በግድ ባስከፈትኩት መስኮት ጆሮዬን አስግጌ ማዳመጥ በጀመርኩበት ቅፅበት አንድ ኬት እንደመጣ ያላወቅኩት አንድ ንፋስ የሆነ ቀማኛ ስልኬን ከነግምቴ እና ከገመትኳቸው ቁጥሮች ጋር ይዞት ሲጠፋ። ከገባሁበት የሐሳብ ባህር ወጥቼ ታክሲውን ባንድ እግሩ ባቆመውም የሄደው ላይመለስ በወጣበት ቀረ መውረጃችንም ሲደርስ ስወርድ ሌላኛው ረዳት እኛ ወደነበርንበት
ታክሲ መጥቶ ሹፌሩን "አንተ ቆይ በምን ፍጥነት ነው በዚህ ሰዓት ሁለት ቢያጆ ደርሰህ የመጣኸው?.." ሲለው 4 የልጅቷ ቀሪው ቁጥር 4 ሊሆን እንደሚችል ጠረጠርኩ ግን ደሞ ዜሮም ሊሆን እንደሚችል እየጠረጠርኩ በ 0 እና በ 4
መካከል እንደሆንኩ ወደቤቴ ተራመድኩ። ሁለቱንም ስልኮች የመሞከር ዕድሉ ቢኖረኝም ስልኬ በሌላ ሰው እጅ ትገኛለች። ስልክ ሲይዙ ቁጥሩ እየጠፋ ቁጥሩን አገኘሁ ሲሉ ስልኩ እየጠፋ ራስ ላይ ያለው ነገር እየተቀያየረ ቁጭት እየፈጠረ ህይወትን ያስቀጠላል። ...ግን ያቺ ልጅ እንዴት 20 ሰው ልትሆንብኝ ቻለች?...እስቲ በቀጣዩ ቅዳሜ ልፈልጋት ...ምርጡን ቅዳሜ
ተመኘሁላችሁ!!..

@wegoch
@wegoch
@wegoch
በታገተው ፓስታና ማኮሮኒ ዙሪያ የተሰጡ አስተያየቶች፡-

👉 በዕውቀቱ ሥዩም፡- ‹‹ጅብ›› የሚለው ሥም የመጣው ከጅቡቲ ነው ብዬ ስናገር ያመነኝ አልነበረም፡፡

👉 አቶ ንጉሱ፡- በዛሬው እለት ጅቡቲ ሁለት መርከብ ፓስታና መኮሮኒ የማገት
አዝማሚያ አሳይታ የነበረ ቢሆንም፣ መንግሥታችን ባደረገው ድርድር ከፓስታና መኮሮኒው በተጨማሪ አንድ መርከብ ሩዝ ማስመለስ ተችሏል፡፡ የቀረውን የማስመለስ ሒደቱም ተጠናክሮ የቀጠለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡

👉 ታምራት ነገራ፡- የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊቱን ልኮ ከፓስታና መኮረኒውን በተጨማሪ ጅቡቲን ማስመለስ አለበት፡፡

👉 ዶክተርዬ፡- ዛሬ ከወንድሜ እስማኤል ኦመር ገሌ ጋር በስልክ ተደዋውለን ሁለቱ አገራት ፓስታና መኮሮኒውን በጋራ መቀቀል እንደሚኖርባቸው ተነጋግረናል፡፡ ብሎም ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ፓስታውን ለመብላት በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ጅቡቲ የሹካ ድጋፍ ታደርጋለች›› በማለት ፕሬዝዳንቱ ቃል ገብተውልኛል፡፡

👉 ሥዩም ተሾመ፡- ጅቡቲ ላይ ለተራገፈው ፓስታና መኮሮኒ ከእስራኤል
ያገኘውን ዶላር ሰጥቶ የማራገፊያ ወጪውን የሸፈነው አብን ግማሹን ሊካፈል የተወሰኑ አመራሮቹን ወደ ጅቡቲ መላኩን የሚገልጽ አፈትላኪ መረጃ ደርሶኛል፡፡

👉 ከንቲባችን፡- ፕሬዝዳንት ኦመር ገሌ ጆንያ ተሸክመው የተነሱትን ፎቶ ሶሻል
ሚዲያ ላይ ባለጠፉበት ሁኔታ የእኛ ፓስታና ማኮሮኒ ጅቡቲ ላይ ተራግፏል
ለማለት እቸገራለሁ፡፡

👉 አንዱዓለም ቡኬቶ፡- ‹‹መለስ ዜናዊ አሰብን አሳልፎ ባይሰጥ ኖሮ ፓስታውም
ባልተራገፈ፣ እሱም በሰላም ባረፈ ነበር››
ሳባዊ ደሳለኝ፡- ወያነን እኮ አለማድነቅ አይቻልም! ይሄን የጅቡቲን ባሕርይ
ስለምታውቅ ነበር ከፕላስቲክ የተሰራ ሩዝ ስታስገባ የነበረው!

👉 ቬሮኒካ መላኩ፡- ‹‹የሚቀቅለውን የተነጠቀ ሕዝብ ቀቃዩን ይበላል›› በማለት ማካቬሌ እንደተናገረው… የኢትዮጵያ ሕዝብ ፓስታና መኮሮኒው ከመቁላላቱ በፊት ያለ ምንም ጦር መሣሪያ በሹካ ብቻ ጅቡቲን ቀቅሎ የተወሰደበትን ማስመለሱ አይቀርም፡፡

👉 ጌታቸው ረዳ፡- ሼፍ መሆን ሲገባቸው የአገር መሪ መሆን የቻሉ ወፈፌዎች ፓስታና መኮሮኒ ባስወሰዱ ቁጥር ሥራችንን ትተን ስለ እንዲህ አይነት ትርኪ ምርኪ የምናወራበት ጊዜ የለንም፡፡ እኛ ዘንድ ሹካ የማኮሮኒ መብሊያ ሳይሆን መቆፈሪያ ሆኖ ሸሚዛችንን ሰቅስቀን የአርሶ አደራችንን ማሳ እያለማንበት ነው፡፡ 😂

@wegoch
@wegoch
@paappii
ባህላዊ
(በእውቀቱ ስዩም)
ወይዘሮ አልጣሽ ስመጥር የባህል ህክምና አዋቂ ናቸው ፤ አምስት መቶ በላይ ብራናዎችን መርምረዋል:: ከምስጢራዊ ጠቢባን ተምረዋል- ይባላል፤ የሆነ ጊዜ ላይ ወደ ቤታቸው ሄድኩ፤ ለካርድ አምስት መቶ ብር አስቀድሜ ከፈልኩ፤ካርዱ ራሱ ባህላዊ እንዲሆን ታስቦ ከሰኔል የተሰራ ነው፤ ወይዘሮ አልጣሽ ደርበብ ያሉ ውብ ሴትዮ ናቸው፤ አፈወርቅ ተክሌ ስእል ውስጥ ከሚታዩት እናቶች አንዲቱን ይመስላሉ::
“ምንህን ነው የሚያምህ?” ሲሉ ጠየቁኝ::
“ ራሴን! ራሴን በጣም ያመኛል”
“ ህምም …መች መች ነው እሚነሳብህ?”
“ማለዳ ከንቅልፌ ስነሳ"
ወይዘሮ አልጣሽ በዙፋን ቅርፅ በተሰራው ሶፋቸው መከዳ ላይ ተለጥጠው ተመቻቹና እንዲህ አሉ፤
“ በሰው ልጆች ታሪክ የመጀመራው ራስ ምታት ታማሚ ናምሩድ ነው፤ ናምሩድ የተወለደው ባቢሎን ውስጥ ነው ይላሉ ፤ ስተት ነው ፤ትውልዱ ፊንቃዊ ለመሆኑ ጥርጥር የለኝም!! እስከ ሰላሳ ዘመኑ ድረስ ኢትዮጵያ መጥቶ ተቀምጦ ነበር:: ባመመው ቁጥር በራሱ ዙርያ እሚጠመጥማት ነጭ ሻሽ ለብዙ ዘመን ባክሱም ኖራለች:: ልኡል ራስ መንገሻ ዮሀንስ ጠምጥመዋት ፎቶ ተነስተዋል፤ በነገርህ ላይ የልኡሉ ማእረግ ንጉስ ነው! ራስ መንገሻ ይባሉ የነበሩት ጥኑ ራስ ምታት ስለነበረባቸው ነው:: አጤ ምኒልክ ራስ መገሻን ድል ካደረጉ በ ሗላ ሻሺቱን ራሳቸው ይጠመጥሟት ጀመር! "
እምለው ቸግሮኝ ዝም አልኩ::
“ አባትህ ራስ ምታት አለባቸው”?
“ የለበትም ” ብየ መለስኩ::
አልጣሽ ቀጠሉ:-
“ ህምም! ንጉስ ናምሩድ ሁለት ልጆች ነበሩት፤ አንደኛው ዱርየ ሲሆን ፤ ሌላኛው ጭምት ነበር ዱርየው ልጅ አባቱ ለዘመቻ በወጣ ቁጥር የቤቱን እቃ ጆሮውን እያለ ፈጀው ፤ ጭምቱ ልጅ ግን ዱርየው የሸጠውን እቃ እንደገና በውድ ዋጋ ገዝቶ ወደ ቤቱ ይመልሳል፤ ናምሩድ ሊሞት ሲል ለጨዋ ልጁ ዘውዱን ከራሱ አውልቆ ሲሰጠው ለዱርየ ልጁን ደግሞ ራስ ምታቱን አወረሰው ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መንግስትም ራስ ምታትም በዘር እሚተላለፉ ሆነዋል! ይህንን ነገር መፅሀፈ ኩፋሌ አምልቶ አስፍቶ ፅፎታል፤ ለመሆኑ ራስህን ሲያምህ ምን ታደርጋለህ?”
“ ቡና ጠጣለሁ”
“ ቡና ይቅርብህ! “ አሉ ወይዘሮ አልጣሽ “ በነገራችን ላይ በሰው ልጆች ታሪክ የመጀመርያው የቡና ሱሰኛ አፄ ሱስ-ንዮስ ነበር፤ ኢሉምናምንቴዎች ፖርቱጋሎች የቡናን አመል ከታች ማዶ አምጥተው አለመዱት! ሱስ-ንዮስ አገራችንን ለፖርቱጋሎች ትቶ : ቡናውን አስፈልቶ ፤ ፈንድሻውን አስቆልቶ፤ አጫጭሶ ከልጁ ጋር አብሮ ፏ-ሲል ይውል ነበር፤ፏ-ሲል የሚለው አነጋገር በጊዜ ብዛት " ፋሲል "ሆኗል“ ራስ ምታቴ እየጨመረ ሲመጣ ይሰማኝ ጀመር! በመጨረሻ በጉጉት ስጠብቀው የነበረውን መዳኒት የሚያዙልኝ ጊዜ ደረሰ ፤ የሆነ የሰለሞን እፅ ይሰጡኛል ብየ ጠብቄ ነበር፤ ፓራሲታሞል እንዳዘዙልኝ ስመለከት ግን ውሃ ሆኘ ቀረሁ::
" ምነው?" አሉኝ መደናገጤን አጢነው፤
“ ባህላዊ መድሃኒት ነበር ከርስዎ የጠበኩት”
“ ጃኖ ወይም በርኖስ ለብሰህ ከዋጥከው ባህላዊ መሆኑ መች ይቀራል?”

@wegoch
@wegoch
#ቢዋሹ ቢዋሹ ከፈጣሪ አይሸሹ!!

አንድ ሃብታም የማይመስል ሃብታም ሰው ነበር ኑሮው ሁሉ ከድሃ ያንሳል የአካባቢው ነዋሪ ሁሉ የሆነ የሃብቱ ብዛትና አኗኗሩ ሰማይና ምድር የሆነ ችጋራም ሃብታም ይለዋል… ከቤተሰቡ ጀምሮ ለማንም ለምንም ነገር ቢጠይቅ ምንም ነገር አይደማውም የለኝም ቸግሮኛል ብሎ ማማረር ብቻ ነው የሚያውቀው።

ታዲያ ይህ ሰው አንድ ቀን ቁጭ ብሎ እንዲህ ብሎ ፀሎት ያደርጋል … “ጌታዬ እንደምታየኝ ቡቱቶ ቆሻሻ ለባሽ ደሃ ባርያህ ነኝ ሰዎች እንደሚሉት ሃብታም አይደለሁም ከማንም የማልሻል ደሃ ፉጡርህ ነኝ ሰዎች የሚሉትን አትስማቸው እኔ ምንም የሌለኝ ደሃ ነኝ እርዳኝ"


ሲል ጎረቤቱ የሆኑቱ ሰሙትና ከተለመደባቸው በላይ ጮክ ብለው እየሰቁበት… “ስማ አንተ ሰው አትሳሳት ያለህን የለኝም ማለት የሰጠሀን አልሰጠሀኝም እንደማለት ይቆጠራል ጌታህ የሰጠህን ያለህን አንተ ከምታውቀው ከሚገባህ ባላይ ያውቀዋል

ሁሉም ሰው ጌታውን ስለሚለምን ሁሉም ፀሎት አድራጊ ችግረኛ ስለሆነ አለም የችግር ውጥንቅጥ ውስጥ ስለተዘፈቀች አምላክ ችግረኛን ብቻ ነው የሚያውቀው ብለህ ችግርህን ብቻ አትንገረው ችግርህንም

ድሎትህንም ደስታህንም ሁሉንም ነገርህን ያውቃል ቢሆንም ቢሆንም ንገረው የሚያውቀውን ንገረው ከሁሉ በላይ ባለህ ነገር አመስግነው ለሰጠሀኝ ነገር ተመስገንልኝ በለው እያለህ እየሰጠህ የለኝም ስትል አልሰጠሀኝም እንደማለት ነው እሱ ደሞ ክፋት ነው

ያለህን እንዳይነጥቅህ ተጠንቀቅ… እኛ ሰዎች ሲሰጥህ አላየንም ምን እንዳለህም አናውቅም ስትቸገርም ችግርህን አናየውም ልንረዳህም አንችልም አንተም ልትረዳንም አትችለም የሰጠህን ያለህን የሚሰጥህን

የሚወስድብህ ጌታህ ነው ለሱ እንኳን ታመንና ለምነው እራሱ የሰጠህን ከራሱ ትደብቃለህ ተው እንጂ" ብለውት ሰውየው ሄደ።

ነጋዴው ሲሸጥ ገዢን ሲያጭበረብር ገዢው ስላላውቀ ጌታህም ማጭበርበርህን አያውቀምን? ውይስ ገዢው እኮ አላውቀም ብለን ፈጣሪንም አላወቀም ልንል ነው?

እንሰርቃለን፣ እናጭበረብራለን፣ እንዋሻለን እኛ ይሄን ስናደርግ የተደረገበት ሰው ላያውቅ ይችላል የሁለታችንን ልብ የሚያውቀው ፈጣሪስ አያውቅም?

እሱን አንፈራም?
ከሰዉ ተደብቀን ልናልፍ እንችላለን ሁሉንም ከሚያየው ፈጣሪ በምን እናልፈዋለን ማጭበርበር ማወናበድ ፋሽን ከሆነብን በጣም ቆየ ከላጭበረበርክ ካልሰረክ አያልፍልህም ብሎ ሰባኪ… አልሰረኩም

አልጨበረበርኩም ሰዎቹን አትመናቸው ብሎ የሚፀልይ ከበዛ ነገን መፍራት አለብን በአፋችን በስራችን ከገባንበት በላይ አዘቅት እንዳንገባ መፍራት አለብን… ለሁሉም ከጠፋነው ያለማነውን ይይልን (ካለ ማለት ነው)።
@wegoch
@wegoch
@wegoch
Audio
#የአንድ_እብድ_ትንቢት
( ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት )
@wegoch
@wegoch
@wegoch
★★★ ሞቴን ቀማኝ………#3★★★
(ሜሪ ፈለቀ)

በህይወቴ የሚመጡ ሰወች ሁሉ ኮከቦች ሊሆኑ አይችሉም። ወይ የማያደምቁ ወይ የማይሞቁ ሰወች በምን ስሌት ኮከቦቼ ይሆናሉ? ብዬ ማሰብ ጀመርኩ።

ያሬድ እንደዚያ አይነት ሰው ነው። ምን ያህል እንደሆነ የማላውቀውን የአባቱን ንብረት ስለተካፈልኩት እምብርቴ ላይ ቆሟል። …… አየኸኝን ላስታምመው የተስማማሁት ንብረቱን ከልጁ ጋር እኩል እንደሚያካፍለኝ ከማወቄ እጅግ አስቀድሞ ነው። …… ቀድሞ ነገር ንብረት ይኑረው አይኑረውም አላውቅም። …… ለጥቆ ነገር ከንብረቱ በላይ የመኖር ተስፋዬን ያለመለመ ሰው ነው። …… ሰልሶ ነገር ንብረት ምኔም ያልሆነ ሴት ነኝ። ……

አየኸኝ አዲሳባ መጥቶ ብዙም ሳይቆይ ሆስቲታል ገባ…… የከተማው ድንግርግር፣ ለማየው ነገር ሁሉ እንግዳ መሆኔ…… ሳይለቀኝ የህይወቴ ፈርጥ ኮከብ የህይወት ክሩ ጫፍ ላይ መሆኑን አወቅኩ። …… ህይወት ተለዋጭ ብትሆን የምለውጠው ሁሉ ይመስለኛል። …… አዲስአበባ እንደደረስን ያለውን ንብረት በሙሉ ከልጁ ጋር እንዳካፈለን ነገረን። …… ከዚያች ዓረፍተ ነገር በኋላ ያሬድ ቃል አልተነፈሰም። …… ሆስፒታል በቀን አንዴ ብቅ እያለ አባቱን ያየዋል። …… አያናግረውም። ……

"ከአባቴጋ ያላችሁ ግንኙነት ምንድነው?" አለኝ የሆነ ቀን

"ልጄ ሲለኝ አልሰማህም? ልጁ ነኛ!" መለስኩለት

"እንቦቃቅላ ጨቅላ አደረግሽኝ እንዴ አንቺው? ተሱ እንዳልተወለድሽ አውቃለሁ! ምን ሲሆን አየሽው በይ? እንደየት እንደየት ብለሽ አጠመድሽው? ንብረቱን ብለሽ እንጂ መቼም……" ……  የገጠር አነጋገር ለዛው ያዝ እያደረገው ……  አልጨረሰውም

"በናትህ ተወኝ! ከፈለግክ ሁሉንም ንብረት ውሰደው!! አንተ አባትህ ሞት አፋፍ ላይ ሆኖ የሚያስጨንቅህ ንብረት ነው?" አልኩት አልመለሰልኝም።

"እንኳን እኛ የወረስነው የለፋበትም አልኖረበት!" ቀጠልኩ

"ምንድነው የምዘላብጂው?" ብሎ ትቶኝ ሄደ።

አየኸኝ አፉ ሲያዝ ብዙም አልቆየም። ሀኪሞቹ ሆስፒታል መቆየቱ ምንም ጥቅም ስለሌለው ወደ ቤት እንዲሄድ ነገሩት። …… ቁጭ ብሎ ሞትን መጠበቅ እንዴት ያማል? ለኔ ስቃይ ሆነብኝ። አየኸኝ ግን በስቃይ ውስጥ ሆኖ እንኳን ፈገግታው አልከሰመም።……

"ካልተሻለው ለምን ወደ ቤት አመጣሽው?" አለኝ ያሬድ በሆነው ቀን

"የሚሰጡት ህክምና ስለሌለ እዛ መተኛቱ ምንም ጥቅም የለውም።" መለስኩት

"ታዲያ የተሻለ ሀኪም ቤት ይሂዳ?"

"ቀልድ ነው የያዝከው? ምን ያለኸው ክፉ ነህ? ሲሆን ባለቀች እድሜው በፍቅር ልትሸኘው ሲገባህ……" ብዬ መጨረስ አቃተኝ። ከእንባዬ ግብ ግብ መግጠም አልፈለግኩም። ተሸነፍኩ። አነባሁ።

"ይታከም ማለት ክፋት ነው?" አለ ለዘብ ብሎ

ይሄኔ ግራ ተጋባሁ። አንድ ያልገባኝ ነገር መኖሩ ተገለጠልኝ። ……

"ለመሆኑ በሽታው ምን እንደሆነ ታውቃለህ?" አልኩት። በጭንቅላቱ ውዝወዛ አለማወቁን ነገረኝ። ይሄኔ ሁሉም ግልፅ አለልኝ። አባቱ እንደሚሞት አያውቅም።

"አባትህ ሀብቱን የተናዘዘው ለምን መሰለህ ታዲያ?" አልኩት

"ሲሻለው ገዳም እንደሚገባ ነው የነገረኝ።"
ግራ ተጋባሁ። ለምን ደበቀው? አየኸኝ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ያሬድ ማወቅ እንዳለበት አሰብኩ። …… ከአባቱጋ እንዴት እንደተዋወቅን ስነግረው… …

"አንድ ቀን ካያት ሴት እኩል ንብረቱን ያካፍለኛል?" ሲል ውስጤ ሲረግብ ተሰምቶኛል።

"በማየት ከሆነ እኮ እንደውም ካንተ ቀድሞ ነው ያየኝ። እውቂያችን ብዙም አይራራቅም።" አልኩት ብስጭት ብዬ

"ልጁ ነኝ‘ኮ" አለኝ ጥርሱን ነክሶ……

"አባትህ ከሳምንት ያለፈ እድሜ የለውም። ይሞታል። …… የጭንቅላት እጢ ነው ያሉት በሽታውን……" ስላበሳጨኝ ሌላ ቦታ እያየሁ ነው ያወራሁት። እስከምን እንደሰማኝም አላውቅም። ከአጠገቤ ተነስቶ ወደአባቱ ክፍል ሮጠ። …… ተከተልኩት። ……

"ለምንድን ያልነገርከኝ?" እያለ በሩን በርግዶ ገባ። አየኸኝ እስከዛሬ ያላየሁት መመሳቀል ፊቱ ላይ ታየኝ። …… አፍን ሊከፍት ታገለ…  ቃላቶቹ እዛው ከንፈሩ ላይ ድምፅ ሳይሆኑ ይዋጣሉ። እጁን ሊያነሳ ሞከረ…… ጣቱን ከማንቀጥቀጥ ያለፈ ማድረግ አልቻለም። ……

"25 ዓመት እስኪሆነኝ ሳትፈልገኝ… … ልትሞት ስትል ለምን ፈለግከኝ? ሀዘን ልታሸክመኝ? ለምንስ እውነቱን አልነገርከኝም? በፀፀት ልትፈጀኝ?"

እውነቱን ለማውራት አነጋገሩ ያሳዝናል። ደረቱን እየደቃ ጮክ ብሎ ነው የሚያወራው። …… እየሰማሁት እያለቀስኩ መሆኔ የገባኝ እንባዬ የአገጬ ደርዝጋ ሲደርስ ነው።

"ለምን አገኘኸኝ? አባት እንደሌለኝ አምኜ እየኖርኩ ነበር። ለምን መጣህብኝ? ለምን እንደተውከኝ አልቀረህም? ለምን አገኘኸኝ?" እያለቀሰ መሆኑን ሳይ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግራ ተጋባሁ። የአየኸኝ ስቃይ አሰቃየኝ። እንባዬን ጠርጌ ያሬድ አጠገብ ደረስኩ። እጁን ያዝኩት። መነጨቀኝ። አጥብቄ ድጋሚ ያዝኩት።

"ምን?" አለኝ እያፈጠጠ

"ያሬድ መናገር አይችልም እኮ እያስጨነቅከው ነው።" አልኩት… … አልሰማኝም መንጭቆኝ ሄዶ አባቱ አልጋ አጠገብ በጉልበቱ ተነጠፈ።

"ታውቃለህ? ትልቅ እስክሆን የሆነ ቀን አባቴ ሊፈልገኝ ይመጣ ይሆናል ብዬ እጠብቅህ እንደነበር? አታውቅም! ታውቃለህ እናቴ ብዙ ሆና እንዳሳደገችኝ? አታውቅም! ታውቃለህ አባቴን ብዬ ባስጨነቅኳት ቁጥር እንደምትንሰቀሰቅ? አታውቅም!! ምንም አታውቅም!! በዛ ሁሉ የናፍቆት ጥበቃዬ ዝር አላልክም። ልትሞት ስትል ግን አገኘኸኝ። ለምን? ምን አደረግኩህ? ለምን ሌላ ናፍቆት ትደርብብኛለህ? ምናለ ክፋትህን እንዳመንኩ ብኖር?" …… ስርቅታው አላናግር አለው። ……

"ወየው…… ወየው…… ወየው ፈጣሪዬ ምን በደልኩህ?" ብሎ ሲጮህ እሪ ብዬ አብሬው መጮህ አምሮኝ ነበር። …… ጭንቅላቱን ይዞ እሪታውን አስነካው። አየኸኝ የአንድ አይኑ እንባው ወደጆሮው ሲሄድ አየሁት። …… ያደረግኩትን ያወቅኩት ካደረግኩት በኋላ ነው። …… እሱ እንዳደረገው መሬቱ ላይ በጉልበቴ ተንበረከኩ። …… አጥብቄ አቀፍኩት። …… አልታገለኝም። ድምፁን አውጥቶ ተንሰቀሰቀ። ……
……
………
አሁንም አልጨረስንም……

@wegoch
@Wegoch
@paappii

#meri_feleke
2024/09/25 18:11:52
Back to Top
HTML Embed Code: