Telegram Web Link
#ባለ ማዕተቦችን ወደዚህ
   ግሩፕ ይጋብዙ

ለመቀላቀል 👉 
@ortodoxtewahedo
🕊

✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞

[  "እንኩዋን ለታላቁ "ጻድቅና ሰማዕት አቡነ አቢብ": "አባ ዕብሎይ" እና "ቅዱስ ዮልዮስ ሰማዕት" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ"  ]


†  🕊  አቡነ አቢብ [ አባ ቡላ ]  🕊  †

ይህን ታላቅ ቅዱስ በምን እንመስለዋለን!

- እኛ ኃጥአን ጣዕመ ዜናውን: ነገረ ሕይወቱን ሰምተን ደስ ተሰኝተናል !

- ቅዱሱ አባታችን :- "ቡላ - የእግዚአብሔር አገልጋይ" ብለን እንጠራሃለን::

- ዳግመኛም "አቢብ - የብዙኃን አባት" ብለን እንጠራሃለን::

- እርሱ ቅሉ አባትነትህ አንተን ለመሰሉ ቅዱሳን ቢሆንም እኛን ኃጥአንን ቸል እንደማትለንም እናውቃለን::

- አባ! ማነው እንዳንተ የክርስቶስን ሕማማት የተሳተፈ!

- ማን ነው እንዳንተ በፈጣሪው ፍቅር ብዙ መከራዎችን የተቀበለ!

- ማንስ ነው እንዳንተ በአንዲት ጉርሻ አማልዶ ርስትን የሚያወርስ!

- የፍጡራንን እንተወውና በፈጣሪ አንደበት ተመስግነሃልና ቅዱሱ አባታችን ላንተ ክብር: ምስጋናና ስግደት በጸጋ ይገባሃል እንላለን::

†    ልደት    †

አባታችን አቡነ አቢብ የተወለደው በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ሲሆን ሃገረ ሙላዱ ሮሜ ናት:: ወላጆቹ ቅዱስ አብርሃምና ቅድስት ሐሪክ እጅግ ጽኑ ክርስቲያኖች ነበሩ:: ልጅ ግን አልነበራቸውም:: ዘመነ ሰማዕታት ደርሶ ስደት በሆነ ጊዜ እነርሱም በርሃ ገቡ::

በዚያም ሳሉ በቅዱስ መልአክ ብሥራት ሐሪክ ጸንሳ ብሩሕ የሆነ ልጅ ወለደች:: ቅዱሱ ሕጻን ሲጸነስ ማንም ሳይተክለው የበቀለው ዛፍ ላይ መልአኩ እንዲህ የሚል የብርሃን ጽሑፍ ጽፎበት ወላጆቹ ዐይተዋል::
"ቡላ ገብሩ ለእግዚአብሔር: ወቅዱሱ ለአምላከ ያዕቆብ: ዘየኀድር ውስተ ጽዮን"

†     ጥምቀት     †

ቅዱሱ ሕጻን ከተወለደ በሁዋላ ሳይጠመቅ ለ ፩ ዓመት ቆየ::
ምክንያቱም ዘመኑ የጭንቅ ነውና ካህናትን እንኩዋን በዱር በከተማም ማግኘት አይቻልም ነበር:: እመቤታችን ግን ወደ ሮሙ ሊቀ ዻዻሳት አባ ሰለባስትርዮስ ሒዳ "አጥምቀው" አለችው::

ወደ በርሐ ወርዶ ሊያጠምቀው ሲል ሕጻኑ ተነስቶ: እጆቹንም ዘርግቶ:- "አሐዱ አብ ቅዱስ: አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውዕቱ መንፈስ ቅዱስ" ብሎ አመስግኖ ተጠመቀ:: ከሰማይም ሕብስትና ጽዋዕ ወርዶላቸው ሊቀ ዻዻሳቱ ቀድሶ ሁሉንም አቆረባቸው:: የሕጻኑ ወላጆች "ለልጃችን ስም አውጣልን" ቢሉት "ቡላ" ብሎ ሰየመው:: እነርሱም ምሥጢሩን ያውቁ ነበርና አደነቁ::

†   ሰማዕትነት   †

የቅዱሱ ቡላ ወላጆች ለ፲ ዓመታት አሳድገውት ድንገት ሕዳር ፯ ቀን ተከታትለው ዐረፉ:: ሕጻኑን የማሳደግ ኃላፊነትን የአካባቢው ሰዎች ሆነ:: ሕጻኑ ቡላ ምንም የ፲ ዓመት ሕጻን ቢሆንም ያለ ማቁዋረጥ ሲጾም: ሲጸልይ ክፉ መኮንን "ለጣዖት ስገዱ" እያለ መጣ::

በዚህ ጊዜ በሕጻን አንደበቱ አምልኮተ ክርስቶስን ሰበከ:: በዚህ የተበሳጨ መኮንኑ ስቃያትን አዘዘበት:: በጅራፍ ገረፉት: በዘንግ ደበደቡት: ቆዳውን ገፈፉት: በመጋዝ ቆራርጠውም ጣሉት:: ነገር ግን ኃይለ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበርና 2 ጊዜ ከሞት ተነሳ:: በመጨረሻ ግን ሚያዝያ ፲፰ ቀን ተከልሎ ሰማዕት ሆኗል::

†   ገዳማዊ ሕይወት     †

ቅዱስ ቡላ ሰማዕትነቱን ከፈጸመ በሁዋላ ቅዱስ ሚካኤል በአክሊላት አክብሮ ወስዶ በገነት አኖረው:: ከሰማዕታትም ጋር ደመረው:: በዚያም ቡላ ቅዱስ ጊዮርጊስን ተመልክቶ ተደነቀ:: መንፈሳዊ ቅንዐትን ቀንቷልና "እባክህን ወደ ዓለም መልሰኝና ስለ ፍቅርህ እንደ ገና ልጋደል" ሲል ጌታን ለመነ::

ጌታችን ግን "ወዳጄ ቡላ! እንግዲህስ ሰማዕትነቱ ይበቃሃል::
ሱታፌ ጻድቃንን ታገኝ ዘንድ ግን ፈቃዴ ነውና ሒድ" አለው:: ቅዱስ ሚካኤልም የቅዱስ ቡላን ነፍስ ከሥጋው ጋር አዋሕዶ: ልብሰ መነኮሳትንም አልብሶ ግብጽ በርሃ ውስጥ አኖረው::

†    ተጋድሎ    †

አባ ቡላ ወደ በርሃ ከገባ ጀምሮ ዐርብ ዐርብ የጌታን ሕማማት እያሰበ ራሱን ያሰቃይ ገባ:: ራሱን ይገርፋል: ፊቱን በጥፊ ይመታል: ሥጋውን እየቆረጠ ለአራዊት ይሰጣል: ከትልቅ ዛፍ ላይ ተሰቅሎ ወደ ታች ይወረወራል::

በጭንቅላቱ ተተክሎ ለብዙ ጊዜ ጸልዮ ጭንቅላቱ ይፈሳል:: ሌላም ብዙ መከራዎችን የጌታን ሕማማት እያሰበ ይቀበላል:: ስለ ጌታ ፍቅርም ምንም ነገር ሳይቀምስ ለ፵፪ ዓመታት ጹሟል:: ጌታችንም ስለ ክብሩ ዘወትር ይገለጥለት ነበር::

የሚታየውም እንደ ተወለደ: እንደ ተጠመቀ: እንደ ተሰቀለ: እንደ ተነሳ: እንዳረገ እየሆነ ነበር:: አንድ ቀንም ጌታችን መጥቶ "ወዳጄ ቡላ! እንዳንተ ስለ እኔ ስም መከራ የተቀበለ ሰው የለም:: አንተም የብዙዎች አባት ነሕና ስምህ አቢብ [ሃቢብ] ይሁን" አለው::

"እስከ ይቤሎ አምላክ ቃለ አኮቴት ማሕዘኔ:
ረሰይከኑ ለባሕቲትከ ኩነኔ:
ዘመጠነዝ ታጻሙ ነፍስከ በቅኔ" እንዲል::

†     ዕረፍት     †

አቡነ አቢብ ታላቁ ዕብሎን ጨምሮ በርካታ ደቀ መዛሙርትን አፈራ:: ከእመቤታችን ጋርም ዕለት ዕለት እየተጨዋወተ ዘለቀ:: በተጋድሎ ሕይወቱም ከ፲ ጊዜ በላይ ሙቶ ተነስቷል:: በዚህች ቀን ሲያርፍ ገዳሙ በመላእክት ተሞላ::

ጌታም ከድንግል እናቱ ጋር መጥቶ "ወዳጄ ቡላ! ስምህን የጠራውን: መታሰቢያህን ያደረገውን እምርልሃለሁ:: አቅም ቢያጣ "አምላከ አቢብ ማረኝ" ብሎ ፫ ጊዜ በዕለተ ዕረፍትህ የሚለምነኝን: በስምሕ እንኩዋ ቁራሽ የሚበላውን ሁሉ እምርልሃለሁ" ብሎት ነፍሱን በክብር አሳረገ: በሰማይም ዕልልታ ተደረገ::


†  🕊  ታላቁ አባ ዕብሎይ 🕊  † 

ይህ ቅዱስ የአቡነ አቢብ ደቀ መዝሙር ሲሆን በዚህ ስም ከሚጠሩ ቅዱሳንም ቀዳሚው ነው:: ብዙ መጻሕፍት "ርዕሰ ገዳማውያን" ይሉታል:: የቅዱሱ ተጋድሎ እጅግ ሰፊ በመሆኑ በዕለተ ዕረፍቱ [የካቲት ፫ ቀን] እንመለከተዋለንና የዚያ ሰው ይበለን::


†   🕊 ቅዱስ ዮልዮስ ሰማዕት 🕊  †

ከሁሉ አስቀደሞ ስለ ሰማዕታት ዜና ሲሰማ ለዚህ ቅዱስ አንክሮ [አድናቆት]: ክብርና የጸጋ ውዳሴ ይገባዋል:: ምክንያቱም ገድለ ሰማዕታትን የጻፈልን እርሱ ነውና:: ነገር ግን መጻፍ ሲባል: ነገሮች እንዲህ እንደ እኛው ዘመን ቀላል እንዳይመስሏችሁ:: ቅዱሱ ዜና ሰማዕታትን ለማዘጋጀት ሃብቱን: ንብረቱን: ቤተሰቦቹንና ሕይወቱንም ሰውቷል::

ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ :-

በመጨረሻው ዘመነ ሰማዕታት [በ፫ኛው መቶ ክ/ዘ] ዓለም በደመ ሰማዕታት ስትሞላ እንኩዋን የሰማዕታቱን ዜና የሚጽፍ: ሥጋቸውን እንኩዋ የሚቀብር አልተገኘም:: "ወኃጥኡ ዘይቀብሮሙ - የሚቀብራቸውም አጡ" እንዳለ ቅዱስ ዳዊት:: [መዝ.፸፰፥፫]

እግዚአብሔር ግን ስለ ወዳጆቹ ሰማዕታት ይህንን ቅዱስ አስነሳ:: ቅዱስ ዮልዮስ በዘመኑ ደግ ክርስቲያን: ትዳርና ልጆች ያሉት: እጅግ ባለ ጸጋና ፫ መቶ አገልጋዮች ያሉት: ምጽዋትንም የሚወድ ሰው ነበር::

በወቅቱ የክርስቲያኖች በየመንገዱ ወድቀው መታየታቸው ዕረፍት ቢነሳው ከቤተሰቦቹ ጋር መክሮ መልካም ግን ደግሞ ከባድ ውሳኔን አስተላለፈ:: ውሳኔውንም ታጥቆ ይተገብረው ጀመር::
በእውነት ድንቅ ሰው ነው:: በምን እንመስለዋለን! እርሱን የፈጠረውን ጌታ "ዕጹብ ዕጹብ" ብለን ከማድነቅ በቀር::

#ባለ ማዕተቦችን ወደዚህ
   ግሩፕ ይጋብዙ

ለመቀላቀል 👉 
@ortodoxtewahedo
የቀጠለ 👇

ሰማዕታቱም ስለ ደግነቱ የሚመልሱለት ቢያጡ ዝም ብለው ይመርቁት ነበር::+እንዲህ: እንዲህ እያለ ዘመነ ሰማዕታት ሊፈጸም ወራት ቀሩት:: በዚህ ጊዜ ለሰማዕትነት ከመነሳሳቱ የተነሳ ጌታችንን ተማጸነ:: ጌታችንም ተገልጾለት "ሒድና ሰማዕት ሁን: ፈቅጄልሃለሁ" አለው:: እርሱም ደስ እያለው ዜና ሰማዕታቱን ለሁነኛ ሰው ሰጥቶ: ሃብት ንብረቱን ለነዳያን አካፈለ::

ቀጥሎም ቤተሰቦቹንና አገልጋዮቹን ጨምሮ ወደ ሃገረ ገምኑዲ ሔደ:: በመኮንኑ ፊት የክርስቶስን አምላክነት ቢመሰክር ፈጽመው አሰቃዩት:: በማግስቱም ወታደሮቹ ለጣዖት ካልሰገድክ ሲሉት "ቆዩማ ላሳያችሁ" ብሎ በጸሎቱ ጣዖታትን ከነ ካህናቶቻቸው ምድር ተከፍታ እንድትውጣቸው አደረገ:: በተአምሩም መኮንኑና ሠራዊቱ አምነው ተከተሉት::

በፍጻሜውም በሌላ ሃገር መኮንኑ ቅዱስ ዮልዮስን ከቤተሰቡና ከ፩ ሺህ ፭ መቶ ያህል ተከታዮቹ ጋር: ፪ቱን የሃገረ ገዥዎች ጨምሮ አንገታቸውን አሰይፏቸዋል::

አምላከ ጻድቃን ወሰማዕት በቃል ኪዳናቸው እንዲምረን ቸርነቱ ይርዳን:: በረከታቸውንም አትርፎ ይስጠን::

🕊

[  †  ጥቅምት ፳፭ [ 25 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. አቡነ አቢብ [አባ ቡላ]
፪. አባ ዕብሎይ ገዳማዊ
፫. ቅዱስ ዮልዮስ ሰማዕት
፬. ቅዱሳን አብርሃምና ሐሪክ
፭. ቅዱሳን አሞኒና ሙስያ [የታላቁ ዕብሎ ወላጆች]

[    † ወርሐዊ በዓላት   ]

፩. ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
፪. ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
፫. ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
፬. ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
፭. ቅዱስ አቡፋና ጻድቅ
፮. ታላቁ አባ ቢጻርዮን

" እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ:: መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ:: ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል:: ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል:: " [ማቴ.፲፮፥፳፬]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

      

  #ባለ ማዕተቦችን ወደዚህ
   ግሩፕ ይጋብዙ

ለመቀላቀል 👉 
@ortodoxtewahedo
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞ ጥቅምት ፳፯ (27) ✞

✞✞✞ እንኩዋን ለፈጣሪያችን "መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ" እና ለቅዱሳኑ "አባ መቃርስ": "አቡነ መብዓ ጽዮን" "ወአባ ጽጌ ድንግል" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+*" መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ "*+

=>ጌታችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ለእኛ ሲል በፈጸመው
የማዳን ሥራ ክፉዎች አይሁድ ከምሽቱ 3:00 ጌቴሴማኒ
ውስጥ ያዙት::
¤ሙሉውን ሌሊት ከቀያፋ ወደ ሐና: ከሐና ወደ ቀያፋ
ሲያመላልሱት: አስረው ሲደበድቡት አድረዋል::

+ዝም ቢላቸው ዓይኑን ሸፍነው በጥፊ መቱት::
¤ምራቃቸውን ተፉበት:: ዘበቱበት::
¤ራሱንም በዘንግ መቱት::
¤እርሱ ግን ሁሉን ታገሰ::
¤በጧት ከገዢው ዘንድ ሞት እንዲፈረድበት አቀረቡት::

+በሠለስት (3:00 ላይ) አካሉ እስኪያልቅ እየተዘባበቱ
6,666 ገረፉት::

¤ሊቶስጥሮስ አደባባይ ላይ እርጥብ መስቀል አሸክመው
ወደ ቀራንዮ ወሰዱት::
¤6:00 ላይ በረዣዥም ብረቶች 5 ቦታ ላይ ቸንክረው
ሰቀሉት::

+7 ታላላቅ ተአምራት በምድርና በሰማይ ታዩ::
¤ዓለም በጨለማ ሳለች ጌታ በመስቀል ላይ 7 ቃላትን
ተናገረ::
¤ከቀኑ 9:00 አካባቢ በባሕርይ ስልጣኑ ቅድስት ነፍሱን
ከቅዱስ ሥጋው ለየ::

+በዚያች ሰዓትም ወደ ሲዖል ወርዶ የታሠሩትን ሁሉ
ፈታ::

¤11:00 ላይ ደጋጉ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከታላቅ ክብርና
ሐዘን ጋር በአዲስ መቃብር ቀበሩት::
በዚአች ቀን ድንግል ማርያም ልቧ በሐዘን ተቃጠለ::
ወዳጁ ቅዱስ ዮሐንስም ፍፁም ለቅሶን አለቀሰ:: ቅዱሳት
አንስት በዋይታ ዋሉ::

+ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለው መጋቢት 27
ቀን ቢሆንም በዓሉ ወደ ጥቅምት እንዲመጣ ያደረጉት
አበው ሊቃውንት ናቸው:: ምክንያቱም ብዙ ጊዜ መጋቢት
27 የሚውለው ዓቢይ ጾም ውስጥ በመሆኑና የንግሥ
በዓላት በዓቢይ ጾም ስለማይፈቀዱ ነው::

+ምንም እንኩዋ በቅርብ ጊዜ በዓቢይ ጾም የሚያነግሡ
አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ቢኖሩም አባቶቻችን ግን
እንዲህ ያለውን ሥርዓት አላቆዩልንም:: ከበሮና የቸብቸቦ
ዝማሬም በወቅቱ የተፈቀደ አይደለም::

+በዚህም ምክንያት የበዓለ ስቅለት ንግሡ ወደ ጥቅምት
27 ሲመጣ: የመጋቢት 5 ገብረ መንፈስ ቅዱስ ንግሥ
ወደ ጥቅምት 5: የመጋቢት 10 መስቀል ወደ መስከረም
17 መጥቶ እንዲከበር ሆኗል::

+"+ ቅዱስ መቃርስ ብጹዓዊ +"+

=>በዚህ ስም የሚጠሩ ቅዱሳን ብዙ ናቸው:: "ታላቁ
መቃርዮስ": "መቃርስ እስክንድርያዊ": "መቃርስ
ባሕታዊ"ን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል:: ይህኛው
ቅዱስ ደግሞ "መቃርስ ኤዺስ ቆዾስ: መቃርስ ብጹዓዊ:
መቃርስ ዘሃገረ ቃው" ይባላል:: ሁሉም መጠሪያዎቹ
ናቸው::

+ቅዱሱ የ5ኛው መቶ ክ/ዘመን ሰው ሲሆን የቅዱስ
ቄርሎስና የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ተከታይ ነው:: ከሕይወቱ
ማማርና ከቅድስናው መሥመር የተነሳ አበው
አመስግነውት አይይጠግቡም:: ልበ አምላክ ቅዱስ
ዳዊት "ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል" እንዳለው:: (መዝ. 91)

+ዳግመኛ "ወይከውን ከመ ዕጽ እንተ ትክልት ኀበ
ሙሐዘ ማይ" (መዝ. 1:3) እንዳለው ቅዱስ መቃርስ
እጅግ ብዙ ትሩፋቶችን አፍርቷል:: ከሁሉ አስቀድሞ
በበርሃ ኗሪ ከሆነበት ቀን ጀምሮ ስለ ጌታ ፍቅር እንባው
እንደ ዥረት እየፈሰሰ:: ራሱን በብረት ዘንግ ይመታ ነበር::

+"ቃው" በምትባል ሃገር ዻዻስ ሆኖ በተሾመ ጊዜም
ተጋድሎውን አልቀነሰም:: ዻዻስ ቢሆንም የሚለብሰው
የበርሃዋን ደበሎ ነው:: ከብቅዓቱ የተነሳ የሕዝቡ
ኃጢአት በግንባራቸው ላይ ተጽፎ እየታየው ስለ ወገኖቹ
ያለቅስ ነበረ:: በቤተ መቅደስ ውስጥ ቆሞ አንጀቱ ቅጥል
እስኪል ድረስም ያለቅስ ነበር::

+ሁልጊዜ ሲቀድስ ጌታችንን ከመላእክቱ ጋር ያየው
ነበር:: አንድ ቀንም ጌታ ቅዱስ መቃርስን "ዻዻሱ ሆይ
ሕዝቡን ገስጻቸው:: ብትገስጻቸውና ባይሰሙህ እዳው
በእነርሱ ላይ ነው" አለው:: ቅዱስ መቃርስም ሕዝቡ
ከኃጢአታቸው ይመለሱ ዘንድ ይመክራቸው:
ይለምንላቸውም ነበር::

+ከዚህ ሁሉ በሁዋላ በጉባኤ ኬልቄዶን (ጉባኤ አብዳን)
636 ዻዻሳት ንጉሡን ፈርተው ሃይማኖታቸውን ሲክዱ
ቅዱሳኑ ዲዮስቆሮስና መቃርስ "ተዋሐዶን አንክድም"
በማለታቸው ዘበቱባቸው:: ብዙ አሰቃይተውም ወደ ጋግራ
ደሴት አሳደዷቸው::

+ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ጋግራ ውስጥ ሲሞት ቅዱስ
መቃርስ ወደ እስክንድርያ ተመልሶ ሕዝቡን ሲመክር
ያዙት:: ከመሬት ላይ ጥለውም እየደጋገሙ ኩላሊቱን
ረገጡት:: ከመከራው ብዛትም በዚህች ቀን ነፍሱን
አሳልፎ ሰጠ:: ቅዱሱ ሙታንን ማስነሳትን ጨምሮ ብዙ
ተአምራትን ሠርቷል::

+አበውም ስለ ቅዱስ መቃርስ ብሎ ጌታ እንዲምራቸው
እንዲህ ይጸልዩ ነበር:-
"ሰላም ሰላም ለፈያታዊ ዘቀደሶ::
ሃገረ ጽጌ የአኀዝ ምስለ ጻድቃን በተዋርሶ::
ተዘከረኒ ክርስቶስ አመ ትመጽእ ለተዋቅሶ::
በእንተ መቃርስ ጻድቅ እንተ መጠወ ነፍሶ::
ወበበትረ መስቀል ዘይዘብጥ ርዕሶ::" (አርኬ ዘጥቅምት 27)

+*" አቡነ መብዓ ጽዮን "*+

=>ሃገራችን ኢትዮዽያ እጅግ በርካታ ቅዱሳንን ስታፈራ
አንዳንዶቹ ደግሞ የተለዩ ናቸው:: ጻድቁ አባ መባዓ ጽዮን
በ15ኛው መቶ ክ/ዘመን በሽዋ (ሻሞ) አካባቢ የተነሱ
ጻድቅ ናቸው:: ገና ከልጅነታቸው የእመቤታችንና የጌታችን
ፍቅር የሞላባቸው ነበሩ::

+በ3 ዓመታቸው ከእንግዳ የወሰዷት ስዕለ አድኅኖ
ተለይታቸው አታውቅም ነበር:: በወጣትነታቸው ጊዜም
ብሉያት ሐዲሳትን: ቅኔንም ጨምሮ ተምረው:
ከቤተሰባቸው አስፈቅደው በምናኔ ገዳም ገቡ::

ከዚያ በሁዋላ ያለውን ገድላቸውን ማን ችሎ
ይዘረዝረዋል!

+በተለይ ዐርብ ዐርብ የጌታን 13 ሕማማት ለማዘከር
ሲቀበሉት የኖሩት መከራ እጅግ ብዙ ነው:: ድንጋይ
ተሸክመው እንባና ላበታቸው እየተንጠፈጠፈ ይሰግዳሉ::
በድንጋይ ደረትና ጀርባቸውን ይደቃሉ:: ራሳቸውን
ይገርፋሉ:: በዋንጫ ሐሞት (ኮሶ) ሞልተው ይጠጣሉ::

+ከዚህ ሁሉ በሁዋላ ወር በገባ በ27 ስለ መድኃኔ
ዓለም ጠላ ጠምቀው: ንፍሮ ነክረው ወደ ገበያ ይወጡና
ይዘክሩ ነበር:: ከዝክሩ የነካ ሁሉ ይፈወስ ነበር:: ከእንባ
ብዛት ዓይናቸው ቢጠፋ ድንግል ማርያም መጥታ
ብርሃናዊ ዓይንን ሰጠቻቸው:: ስለዚህም "ተክለ ማርያም
(በትረ ማርያም)" ይባላሉ::

+ጌታችንም ስለ ፍቅራቸው በአምሳለ ሕጻን
ይገለጽላቸው: እርሳቸውም አቅፈው ይስሙት ነበር::
ጻድቁ ተናግረን የማንጨርሰውን ተጋድሎ ተጋድለው ጌታ
በዚህ ቀን ነፍሳትን ከሲዖል እንዲያወጡበት ስልጣንን
ሰጣቸው:: አባታችን ቅዱሱና ጻድቁ መብዓ ጽዮን ከብዙ
ትሩፋት በሁዋላ ዐርፈዋል::

+"+ አባ ጽጌ ድንግል ዘወለቃ +"+

=>ጻድቁ አቡነ ጽጌ ድንግል በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን
የነበሩ ሊቅና ገዳማዊ ናቸው:: የዘር ሐረጋቸው ምንም
ከቤተ እሥራኤል እንደሚመዘዝ ቢታወቅም ኢትዮዽያዊ
ናቸው:: አስቀድመው አይሁዳዊ በመሆናቸው ኢየሱስ
ክርስቶስንና ድንግል እናቱን አያምኑም ነበር::

+የተማሩትም ብሉይ ኪዳንን ብቻ ነበር:: በጊዜውም
"ክርስቶስ አልተወለደም:: ትክክለኛው እምነት ይሁዲ
ነው::" እያሉ ከክርስቲያኖች ጋር ይከራከሩ ነበሩ:: አንድ
ቀን ግን ከታላቁ ሊቅና ገዳማዊ አቡነ ዜና ማርቆስ ጋር
ተገናኙ::

+ጻድቁን ስላልቻሏቸው ተሸንፈው በክርስቶስ አመኑ::
አቡነ ዜና ማርቆስም አስተምረው ክርስትና ሲያነሷቸው
(ሲያጠምቁዋቸው) "ጽጌ ድንግል" አሏቸው::

ሲመነኩሱም "ጽጌ ብርሃን" ተብለዋል:: ቀጥለውም
በጾምና በጸሎት ሲጋደሉ: እመቤታችንንም ሲለምኑ
ምሥጢር ተገለጠላቸው::
+የእመ ብርሃንን ስዕለ አድኅኖ በአበባ ተከባ: በብርሃንም
ተውጣ ተመለከቱ:: በዚህ ምክንያትም ዛሬ በጣፋጭነቱ
የሚታወቀውን ማኅሌተ ጽጌን 150 ዓርኬ አድርገው
ደረሱ:: እስከ ዕለተ ዕረፍታቸውም እመቤታችንና ልጇን
በገዳማቸው (ወለቃ አካባቢ የሚገኝ) ሲያመሰግኑ
ኑረዋል:: በዚህች ቀንም ዐርፈዋል::

=>አምላከ ቅዱሳን በአማኑኤል ስሙ: በማርያም እሙ:
በፈሰሰ ደሙ: በተወጋ ጐኑ: በንጹሐን ቅዱሳኑ ይማረን::
ከመስቀሉና ከቅዱሳኑ በረከትም አይለየን::

=>ጥቅምት 27 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን
በዓላት=
1.ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
2.ቅዱስ መቃርስ ብጹዓዊ
3.አቡነ መብዓ ጽዮን ጻድቅ
4.አባ ጽጌ ድንግል ዘወለቃ

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ)
2.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
3.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
4.ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት
5.ማር ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት

=>+"+ በእውነት ደዌአችንን ተቀበለ:: ሕማማችንንም
ተሸክሟል:: እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ
ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቆጠርነው:: እርሱ ግን ስለ
መተላለፋችን ቈሰለ:: ስለ በደላችንም ደቀቀ::
የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ:: በእርሱም
ቁስል እኛ ተፈወስን:: +"+ (ኢሳ. 53:4)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

#ባለ ማዕተቦችን ወደዚህ
   ግሩፕ ይጋብዙ

ለመቀላቀል 👉 
@ortodoxtewahedo
#በዓለ መዳኀኔአለም ጥቅምት 27

+"+ በእውነት ደዌአችንን ተቀበለ:: ሕማማችንንም
ተሸክሟል:: እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቆጠርነው:: እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ:: ስለ በደላችንም ደቀቀ::
የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ:: በእርሱም
ቁስል እኛ ተፈወስን:: +"

+ (ኢሳ. 53:4)
"ወዳጄ ሆይ ሮማውያን ወታደሮች ጎንጉነው በጌታችን እራስ ላይ እሾህ እዳቀዳጁት ባሰብህ ጊዜ እጅግ ማዘንህ አይቀርም ። ሆኖም አንተም እሾህ የተባለውን አንድ ኃጢአት በሰራህ ቁጥር በጌታችን ላይ የተደፉትን እሾኾች ቁጥር እንደጨመርህ አስብ ።በፈጣሪ የማያምኑት ሮማውያን ወታደሮች ከጎነጎኑት እሾኽ በላይ የጌታችንን እራስ የበለጠ ዘልቆ የሚወጋው ደሙን አፍስሶ ያዳነን እኛ ክርስቲያኖች በኃጢአታችን የምንጎነጉነው የእሾኽ አክሊል ነው ።{ስለመተላለፋችን የቆሰለው አምላክ በመተላለፋችንም ይቆስላል ።!}

{በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን ከሚለው ርዕስ የተወሰደ )

[ ሕማማት]
{በዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ}

መድኃኔዓለም ሆይ አባት ሆይ ይቅር በላቸው በማለት በታላቅ ቃል በመስቀል ላይ ፥ ለተናገረ ቃልህ ሰላም እላለሁ በመስቀል ላይም በሰቀሉህ ጊዜና ጎንህን በጦር በወጉ ጊዜ አንዳችም የተቃውሞ ትንፋሽ ላልተነፈሰ እስትንፋስህም ሰላም እላለሁ ።
መድኃኔዓለም ሆይ ጻድቃንን ያይደለ ኃጥአንን ለማዳን በራሱ ደም ራሱ ለተጥለቀለቀ ስነ መልክህ ሰላም እላለሁ !

( መልክአ - መድኃኔአለም )27

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

#ባለ ማዕተቦችን ወደዚህ
   ግሩፕ ይጋብዙ

ለመቀላቀል 👉 
@ortodoxtewahedo
#ባለ ማዕተቦችን ወደዚህ
   ግሩፕ ይጋብዙ

ለመቀላቀል 👉 
@ortodoxtewahedo
በኮሪደሪ ልማቱ

1- ምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን
2- መንበረ ፓትርያርክ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን
3- ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን
4- እንጦጦ ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን
5- እንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን
6- ደብረ ኤልያስ እና ራጉኤል ቤተክርስቲያን

ከለገሃር እስከ እንጦጦ አዲሱ መናፈሻ ድረስ ለሚሰራውና የኮሪደርልማት በሚባለው ፕሮጀክት የአብያተ ክርስቲያናት ግቢ ከግማሽ በላይ እንደሚፈርስ ነው የተነገረው።

በተለይም ምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለምና ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያኖች ካላቸው ጠበባ ቦታ ላይ ተቀንሶና ግቢያቸው ፈርሶ ነው ለአበባ መትከያና ለሳይክል መንጃ ይደረጋል የተባለው። ምስካየ ኅዙናን በመጀመርያም ጊቢው ጠባብ በመሆኑ ከዚሁ ላይ ደግሞ ፈርሶ እንዲቀነስ ተወሰዱ ኖበታል።

የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስት ማርያም ግቢ አጥሩ ብቻ ሳይሆን ቤተልሄሙና የአስተዳደር ቢሮዎችም ሊነሱ እንደሚችሉ ነው የተነገረው። አብያተክርስቲያናት አባቶቻችን አክብረውና አስከብረው ያቆዩትን ይዞታ በማን አለብኝነት ሲነጠቅ ዝም ብለው የሚያዩ የቤተክርስቲያኒቱ ሰዎች ወደ ፊት ተወቃሽ ናቸው።

በርካታ ምዕመናን ከአካባቢያቸው ተነስተው አብያተክርስቲያናቱ ብቻቸውን እየቀሩ መሆኑም በግልፅ አየታየ ያለ ችግር ቢሆንም የቤተክርስቲያኒቱ ሰዎች በሙስና ተጨማልቀው እርስ በርሳቸው ውዝግብ ላይ በመሆናቸው የምዕመናን መፍለስና የቤተክርስቲያን ይዞታ መዘረፍ አያሳስባቸውም።

ከመተግበሩ በፊት የቤተክርስትያንን ይዞታ ማስከበር ይታሰብበት ። ሸሮሜዳ አከባቢ ያለን ምዕመናን የሽሮሜዳ ቅድስት ሥላሴ አጥሩ ትይዩ የተሰሩ ሱቆች ፈርሰዋል የኢንባሲዎች አጥር እየተከበሪ በዚ ደረጃ ቤተ ክርስትያንን ስትነካ ያማል የሚመለከታቹ በቅዱስ ሲኖዶስ በኩል መልዕክቱ ይድረስ።
ጥቅምት ፳፯ ዝክረ ጥንተ ስቅለቱን ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ የፈጸመልንን የማዳን ሥራ በመዘከር ታከብረዋለች።

#ባለ ማዕተቦችን ወደዚህ
   ግሩፕ ይጋብዙ

ለመቀላቀል 👉 
@ortodoxtewahedo
መድኃኔዓለም (በዓለ ስቅለት) ጥቅምት ፳፯
ለመድኃኔ ዓለም ዓመታዊ ክብረ በዓል እንኳን አደረሰን፤ አደረሳችሁ!!!
በመ/ር ጌታቸው በቀለ ጥቅምት ፳፯ ቀን የጌታችን አምላካችን የመድኃኔዓለም የስቅለቱ መታሰቢያ በዓል ነው፡፡ ይህች ቀን ጻድቁ አባ መብዓ ጽዮን ቃል ኪዳን ቀን የተቀበሉበት፣ የማሕሌተ ጽጌ ደራሲው አባ ጽጌ ድንግል ዘወለቃ እና ቅዱስ አባት የሀገረ ቃው ኤጲስ ቆጶስ አባ መቃርስ የዕረፍታቸው መታሰቢያ ዕለት ነው፡፡
የጌታችን መድኃኒታችን ኢሱስ ክርስቶስ ጥንተ ስቅለቱ መጋቢት ፳፯ ቀን ሲሆን፤ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በዲሜጥሮስ ቀመር መሠረት አጽዋማትን በሠሩበት ወቅት መጋቢት ፳፯ ቀን በዐቢይ ጾም ስለሚውል፤ በዐቢይ ጾም ሐዘን እንጂ ደስታ ስለሌለ፤ በዓል ማክበርም ስለማይፈቀድ፤ ወደ ጥቅምት ፳፯ ተዛውሮ ደስ ብሎን እንድናከብረው ቤተክርስቲያን ሥርዐት ሠርታለች፡፡ ስለዚህ ጥቅምት ፳፯ ቤተክርስቲያናችን ጌታችን በመስቀሉ ስለፈጸመልን የማዳን ሥራ ታስተምራለች፡፡
በዓለ ስቅለት
ጥቅምት ፳፯ ቀን የአምላካችን የመድኃኔዓለም የስቅለቱ መታሰቢያ ነው። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች ድኅነት ሲል ራሱን ወድዶ ፈቅዶ ለሞት አሳልፎ በመስጠት ፍጹም ፍቅሩን አሳይቶናል። በቅዱስ ወንጌልም እርሱም መድኃኒታችን "ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር የለም" ብሎ ነግሮናል። እውነት ነው፣ ራስን አሳልፎ ከመስጠት በላይ ምን ምን ድንቅ ፍቅር አለ?

የአስቆሮቱ ይሁዳ ሊያስይዘው የሊቃነ ካህናቱን አገልጋዮች እየመራ አመጣቸው። እነርሱንም “ማንን ትፈልጋላችሁ” ሲላቸው “የናዝሬቱ ኢየሱስን” አሉት፣ “እኔ ነኝ” ቢላቸው ወደ ኋላቸው ተስፈንጥረው ወደቁ። በኋላ በፈቃዱ ከያዙት በኋላ እያዳፉና እየጎተቱ በሰንሰለት አስረው ወደ ቀያፋና ሐና ግቢ ወሰዱት፣ እስከ ሦስት ሰዓትም አላሳረፉትም ሲያሰቃዩት አድረዋል፣ በራሱም ላይ የእሾህ አክሊል አደረጉበት፡፡ እያፌዙ ምራቃቸውን ይተፉበትና በዘንግም ደጋግመው ይመቱት ነበር። እየተፈራረቁ ያለ ምንም ርኅራኄ ስድስት ሺህ ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ጽኑዕ ግርፋትን ገርፈውታል። በሊቶስጥራ አደባባይ ያንን ዕርጥብ መስቀል አሸክመው ወደ ቀራንዮ ወሰዱት። እርሱ ግን ይህን ኹሉ ግፍ ሲያደርሱበት አንድም አልተናገረም ነበር። በቀራንዮም በአምስት ጽኑዕ ቅንዋት (ሳዶር፣ አላዶር፣ ዳናት፣ አዴራ እና ሮዳስ) ቸንክረው ሰቀሉት።

በዚህች ቀን ድንግል ማርያም ልቧ በሐዘን ተሰበረ፤ ወዳጁ ቅዱስ ዮሐንስም ፍጹም ለቅሶን አለቀሰ እናቱንም እናት ትሆነው ዘንድ በእግረ መስቀሉ አደራን ተቀበለ። ኢየሱስ ክርስቶስ በሥልጣኑ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው ለየ። ሰባት ድንቅ የኾኑ ተአምራትንም አድርጎ አምላክ መኾኑን ገለጠ። ይህም ጽኑዕ የኾነ ለሰማይ ለምድር የከበደ ነገር ሲከሰት ፀሐይ አምላኬን ዕርቃኑ እንዴት አያለሁ ብላ ጨለመች። ጨረቃ ደም ኾነች፣ ከዋክብቱም ረገፉ፣ ንዑዳን ክቡራን ንጹሐን መላእክትም ትዕግሥቱን እያደነቁ በጽኑዕ ሐዘንና መደነቅ ከቅዱስ ዕፀ መስቀሉ ፊት እንደሻሽ ተነጠፉ። ዐሥራ አንድ ሰዓት በሆነም ጊዜ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከታላቅ ክብርና ሐዘን ጋር ቅድስት ሥጋውን ከመስቀሉ አውርደው በክብር ገንዘው በአዲስ መቃብር ቀበሩት። በሦስተኛውም ቀን እንደተናገረ ተነሣ።

በዛሬዋ ቀን ቤተ ክርስቲያን የመድኃኔለምን የስቅለት በዓል በደማቁ ታከብራለች፤ ይህም የለውጥ በዓል ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰው ሥጋውን የቆረሰው መጋቢት ፳፯ ቀን ነው፤ ይህ በዓል ግን በዐቢይ ጾም ስለሚውል በዐቢይ ጾም ሐዘን እንጂ ደስታ ስለሌለና በዓል ማክበር ስለማይፈቀድ፤ ወደ ጥቅምት ፳፯ ተዛውሮ እንዲከበር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሠርታልናለች፡፡
መጋቢት ፳፯ ቀን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል በተሰቀለ ጊዜ፤ የተሰቀለው የክብር ባለቤት ሰማይን የፈጠረ ነውና ፀሐይ ጨልማለች፣ ጨረቃ ደም ሆኗል፣ ከዋክብት ረግፈዋል። የተሰቀለው የክብር ባለቤት ምድርንም የፈጠረ ነውና በምድር የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለኹለት ተቀዷል፤ ምድር ተናውጣ ዐለቶች ተሠንጥቀዋል፤ መቃብራት ተከፍተዋል፤ ከ፭፻ በላይ ሙታን ተነሥተዋል (ማቴ ፳፯ )፡፡ “አዳምን የፈጠሩ እጆች በመስቀል ቀኖት ተቸነከሩ ወዮ፤ በገነት የተመላለሱ እግሮች በመስቀል ቀኖት ተቸነከሩ ወዮ፡፡” እንዲል ቅዳሴ ዮሐንስ አፈወርቅ በዝክረ ጥንተ ስቅለቱ በጥቅምት ፳፯ በመስቀል የተደረገልንን አስበን እናመሰግነዋለን፡፡ በዚሁ ቀን ዛሬዋ ቀን ቤተ ክርስቲያን የመድኃኔለምን የስቅለት በዓል በደማቁ ታከብራለች፡፡
አቡነ መብዓ ጽዮን

በዚህች ቀን ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ መብአ ጽዮን የእረፍት ቀናቸው ነው፤ ትውልዳቸው ሸዋ ትጉለት ውስጥ ነው እኚህ ጻድቅ በጣም የሚታወቁበት ተጋድሎ አላቸው፤ ይህም ዓርብ ዓርብ ቀን የጌታችንን ሞቱን ለማሰብ ትልቅ ድንጋይ በጀርባቸው አዝለው እልፍ እልፍ እየሰገዱ ማታ ላይ ኮሶ ይጠጡ ነበር፤ ሐሞት መጠጣቱን ለማሰብ፤ ከጽድቃቸው ብዛት የተነሣ መቋሚያቸውን ቢተክሉት ሎሚና ትርንጎ አፈርቷል፡፡
አባ መብዓ ጽዮን በ፲፭ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ልጅ በማጣታቸው በጾምና በጸሎት ፈጣሪያቸውን ከሚለምኑ ባልና ሚስት ተወለዱ። የንቡረ እድ ሳሙኤል ረባን የሆነው መብዓ ጽዮን አባቱ እስከ ዳዊት ያለውን ትምህርት አስተማረውና ዲቁናን ተቀበለ። ልጁ የትምህርት ዝንባሌ እንዳለው አባቱ ተረድቶ ቤተ ማርያም ከሚባለው ደብር ወስዶ ተክለ አማኅጸኖ ከሚባል የቅኔ መምህር ዘንድ አስገባው። በዚያም ቅኔና እና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ዕውቀቶችን ገበየ።

አባ መብዓ ጽዮን አባ ገብረክርስቶስ ጋር በመቀመጥ ሥርዓተ ምንኩስናን ካጠኑ በኋላ ከአባ ገብርኤል ዘንድ ሄደው የቅስናን ማእረግ ተቀበሉ። ከዚያም በኋላ በአበው ሕግ በምንኩስና ተወስነው፤ በበአታቸው ሆነው ‹‹ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የዕለተ ዓርቡን መከራህን አሳየኝ፤ ስለራሴ ፈጽሞ አለቅስ ዘንድ›› ብለው በጸልዩ ጊዜ “መከራ መስቀሉን ለማየት ትፈቅዳለህን?›› ብሎ ጠየቃቸው። ጻድቁ አባ መብዓ ጽዮንም ‹‹አዎ አይ ዘንድ እወዳለሁ” ሲሉ ለጌታቸው መለሱለት። ያን ጊዜም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዕፀ መስቀል ተተከለ። በመስቀሉ ላይም እጆቹና እግሮቹ ተቸንክረውና ተዘርግተው ታዩ ፤በራሱ ላይም የእሾህ አክሊል ደፍቶ ነበር። ጌታችን ለአባ መብዓ ጽዮንም ታያቸው። ከዚህም በኋላ አባ መብዓ ጽዮን የጌታችን የመድኃኔዓለምን ሕማሙን፣ መከራውን፣ ግርፋቱን፣ እስራቱን በጠቅላላ ፲፫ቱን ሕማማተ መስቀል በማሰብ ጀርባቸውን በአለንጋ ይገርፉ፤ ራሳቸውንም በዘንግ ይመቱ ነበር። የጌታን መከራ መስቀል እያሰቡ ዐይኖቻቸው አስከሚጠፉ ድረስ ያለቅሱ ነበር። ጌታችን ግንደ መስቀሉን (የመስቀሉን ግንድ) አንደተሸከመ በማሰብ ትልቅ ድንግያ ተሸክመው ይሰግዱ ነበር።

መራራ ሐሞት መጠጣቱን በማሰብ ዓርብ ዓርብ ኮሶ ይጠጡ ነበር። ጻድቁ አባ መብዓ ጽዮንም እንደ ዮሐንስ ወንጌላዊ የጌታችንን መከራ መስቀል እያሰቡ ከዓለም ተድላና ደስታ ተለይተው በትምህርት፣ በትሩፋት ፣ በገድል ጸንተው ኖረዋል። የጻድቁ መታሰቢያ በዓል በየዓመቱ ጥቅምት ፳፯ ቀን ከመድኃኔዓለም የስቅለት በዓል ጋር ይከበራል።

አባ ጽጌ ድንግል

በ፲፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ ሊቅ ሲኾን፤ አባ ጽጌ ድንግል (ጽጌ ብርሃን) ሀገሩ ይፋት ሃይማኖቱ ኦሪት ነበረ፡፡ በንጉሥ ሰሎሞን ፈቃድና በካህኑ አዛርያስ መሪነት ታቦተ ጽዮንን ከኢየሩሳሌም ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ከመጡትና የብሉያት መጻሕፍት ሊቃውንት ከነበሩት ከ318 ሌዋውያን (ከቤተ እስራኤላውያን) ነገድ ነው፡፡ የተወለደውም በሰሜን ሸዋ በይፋት አውራጃ ውስጥ ነው፡፡

አቡነ ዜና ማርቆስም ጽጌ ብርሃንን ለመዓርገ ምንኵስና አበቃው፤ የአባ ጽጌ ብርሃንም ጽጌ ድንግል የሚል ቅጽል ስም አለው፣ አባ ጽጌ ብርሃንም በወሎ ክፍለ ሀገር በወራይሉ አውራጃ፣ ልዩ ስሙ ደብረ ሐንታ ለሚባለው ገዳም ከጓደኛው ከአባ ገብረ ማርያም ጋር እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ እንደ አንድ ልብ መካሪ በመሆን፣ እመቤታችንንና ፈጣሪ ልጇን በጎ በጎ መዓዛ ባላቸው አበባዎችና ፍሬዎች እየመሰለ የሚያመሰግነውን ማኅሌተ ጽጌ የተባለውን ድርሰት፣ በአባቷ በዳዊት መዝሙር መጠን 150 አድርጎ ደረሰ፡፡ ፍሬ ከአበባ አበባም ከፍሬ እንደሚገኝ ኹሉ በማኅሌተ ጽጌ እመቤታችንን በአበባ፥ ጌታችን በፍሬ፤ ወይም እመቤታችንን በፍሬ፥ ጌታችን በአበባ እየተመሰሉ የሚመሰገኑበት ምስጋና ነው።

አባ ጽጌ ብርሃንና አባ ገብረ ማርያምም የዘመነ ጽጌ የማኅሌት አገልግሎትን ሳይለያዩ በሰላምና በፍቅር (በአንድነት) አገልግለዋል፣ ማለትም አንድ ዓመት አባ ገብረ ማርያም የክረምት መውጫና የዘመነ ጽጌ ዋዜማ በሆነው መስከረም ፳፭፣ ቀን ከደብረ ሐንታ መጥቶ ገዳመ ጽጌ (ደብረ ብሥራት) ገብቶ ከመስከረም ፳፮ ቀን እስከ ኅዳር ፭ ቀን ያለውን የዘመነ ጽጌ የ፵ ቀን አገልግሎትን ከአባ ጽጌ ብርሃን ጋር ፈጽሞ ኅዳር ፰ ቀን ወደ ደብረ ሐንታ ይመለሳል፤ በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ አባ ጽጌ ብርሃን ከገዳመ ጽጌ (ከደብረ ብሥራት) ወደ ደብረ ሐንታ ሄዶ እንደዚሁ እንደ አባ ገብረ ማርያም 40ውን ቀን አገልግሎ ይመለሳል፡፡


የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፤
የአቡነ መብዓ ጽዮን፣ የአባ ጽጌ ድንግል ጸሎት፣
ረድኤት በረከታቸው አይለየን፡፡ አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ዋቤ መጻሕፍት
✍️ ድርሳነ ማኅየዊ
✍️ ስንክሳር ዘወርኀ ጥቅምት
✍️ የማኅሌተ ጽጌ ትርጉምና ማብራሪያው
✍️ ገድለ አቡነ መብዓ ጽዮን

ምንጭ፡ EOTC TV

#ባለ ማዕተቦችን ወደዚህ
   ግሩፕ ይጋብዙ

ለመቀላቀል 👉 
@ortodoxtewahedo
#ባለ ማዕተቦችን ወደዚህ
   ግሩፕ ይጋብዙ

ለመቀላቀል 👉 
@ortodoxtewahedo
2024/11/06 01:27:08
Back to Top
HTML Embed Code: