Telegram Web Link
    የዐቢይ ጾም አራተኛ ሳምንት    

መ ጻ ጉ ዕ   

አራተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹መጻጒዕ› ይባላል፡፡

ስያሜው በዮሐንስ ወንጌል ፭፥፩ ላይ ከሚገኘው ኃይለ ቃል የተወሰደ ነው፡፡ በዚህ የወንጌል ክፍል ጌታችን በቤተ ሳይዳ ሕሙማንን እንደ ፈወሰ ተነግሮአል፡፡ ብዙ ሕሙማን ፈውስ ሽተው አንዲት የመጠመቂያ ሥፍራን ከበው ይኖሩ ነበር፡፡ በዚያች ሥፍራ ቀድሞ የወረደ እና የተጠመቀ አንድ በሽተኛ ብቻ ይፈወስ ነበር፡፡

ጌታችን በዚህ ሥፍራ ተገኝቶ በሽተኞችን ጐብኝቷል፡፡ በዚያም ልዩ ልዩ ደዌ ያለባቸው አምስት ዓይነት ሕሙማን እንደ ነበሩ ተገልጧል ፤ እነዚህም ፦ ሰውነታቸው የደረቀ ፣ የሰለለና ያበጠ ፤ እንደዚሁም ዕውራን እና ሐንካሳን ነበሩ፡፡ ከዚህ አምስት የተለያየ ዓይነት በሽታ ከተያዙ ሰዎች መካከል ደዌው የጸናበት ፣ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት በደዌ ዳኛ ፣ ባልጋ ቍራኛ ተይዞ የኖረው ፤ ከደዌው ጽናት የተነሣ ‹መጻጒዕ› ተብሎ የተጠራው በሽተኛ አንዱ ነበር፡፡

መጻጒዕ ስም አይደለም፡፡ ደዌ የጸናበት በሽተኛ ሕመምተኛ ማለት ነው እንጂ፡፡ ሰውየው ከበሽታው ጽናት የተነሣ ስሙ ጠፍቶ በበሽታው ሲጠራ የነበረ ነው፡፡ አምላካችን ይህን ሰው "አልጋህን ተሸክመህ ሒድ" ብሎ ሠላሳ ስምንት ዘመን የተኛበትን አልጋ ተሸክሞ ወደ ቤቱ እንዲገባ ማድረጉ የሚነገርበት ወቅት በመኾኑ ሳምንቱ ‹መጻጒዕ› ተብሎ በተፈወሰው በሽተኛ ስም ተሰይሟል፡፡ [ሙሉ ታሪኩን በዮሐንስ ወንጌል ፭፥፩-፲፯ ይመልከቱ]፡፡

ዛሬም ቢኾን በሰዎች ላይ ልዩ ልዩ ደዌያት አሉ ፤ የሥጋውን ደዌ ሐኪሞች ያውቁታል፡፡ ከዚህ የከፉ የነፍስ ደዌያት እጅግ ብዙዎች ናቸው፡፡ በኃጢአት ብዛት ልባቸው የደረቀና ያበጠ ፤ ሰውነታቸው የሰለለ ፤ ዓይነ ሕሊናቸው የታወረ ፤ እግረ ልቡናቸው የተሰበረ ብዙዎች ሕሙማን አሁንም አሉ፡፡ ፈውስን ይሻሉ ፤ ድኅነትን ይፈልጋሉ፡፡ እንደ መጻጕዕ ቦታቸውን ሳይለቁ እግዚአብሔርን በተስፋ ቢጠብቁት አንድ ቀን ይፈወሳሉ፡፡

[ በመምህር ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ ]

@ortodoxtewahedo
“ችግሮች ቢኖሩም ራሳቸውን ለቤተ ክርስቲያን አሳልፈው የሚሰጡ ልጀች እንዳሉ አይተናል፤ ቤተ ክርስቲያን መሻገሯ አይቀርም”

ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የባሕር ዳርና ሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

+++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++

የማኅበረ ቅዱሳን የ2016 ዓ.ም የሥራ አመራር ጠቅላላ ጉባኤ በመጨረሻ ቀን ውሎው ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የባሕር ዳርና ሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተገኝተው ነበር።

የማኅበሩ ሰብሳቢ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም ለብፁዕነታቸው ገለጻ ያደረጉ ሲሆን በዚህ የሥራ አመራር ጉባኤ በሀገር ውስጥ ካሉን 55 ማእከላት ውስጥ ጦርነት ውስጥ ካሉ አካባቢዎች ሳይቀር ከ48 ማእከላት ሰብሳቢዎች እና ተወካዮች እንዲሁም ከውጭ 9 ማእከላት ተሳትፈዋል ብለዋል።

ሰብሳቢው አክለውም ጉባኤው በሁለት ቀን ውሎው የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አሁናዊ ችግሮችና መፍትሔዎች እንዲሁም የማኅበረ ቅዳሳን የአገልግሎት ድርሻ ላይ መወያየታቸውን አስታውቀዋል።

“ጽና፤ እጅግም በርታ” በሚል ኃይለ ቃል ቃለ ምእዳን የሰጡት
ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የባሕር ዳርና ሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

“የኛ የሆነውን አሳልፎ ላለመስጠትና በክብር የተቀበልነውን በክብር ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ጥንካሬ ያስፈልጋል፤ እናንተም ጽናት ባይኖራችሁ በዚህ ሁሉ መከራ መሀል አትገኙም።ችግሮች ቢኖሩም ራሳቸውን ለቤተ ክርስቲያን አሳልፈው የሚሰጡ ልጀች እንዳሉ አይተናል” ብለዋል።

ትውልዱ ጽናት ያለው የሚመስል ነገር ግን በጉዞ መሐል የሚንቀጠቀጥ የሚንገዳገድ ትውልድ መሆን የለበትም ሲሉም አብራርተዋል ።

“ከምእመን እስከአባቶች ከበረታን ቤተ ክርስቲያን ከእነሙሉ ክብሯ ትተላለፋለች፤ መሻገሯም አይቀርም” ያሉት ብፁዕ አቡነ አብርሃም “ ሌላ ጉልበት የለንም ጉልበታችንም ጽናታችንም እግዚአብሔር ነው፤ አቅጣጫ የሚሰጠንም ቃሉ ነው፤ እግዚአብሔር ሁሉን እንደሚያስተካክል እናምናለን የእኛ ድርሻ ግን እንወጣ ” ብለዋል።

ብፁዕነታቸው ማኅበሩ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጋር የበለጠ በመናበብና ግብዓት በመስጠት በፍቃደ እግዚአብሔርና በጥበብ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እናሻገር ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።

በመጨረሻም ከውጭ ሀገራት የተሳተፉ አባላትን መነሻ በማድረግም “ጽኑ፤ በምትሠሩት መንፈሳዊ አገልግሎትም ቤተ ክርስቲያንን ድምጽ ስለሆናችሁ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ስም አመሰግናለሁ” ብለዋል።

@ortodoxtewahedo
Audio
የጌታ ጅራፍ
                         
Size 31.4MB
Length 1:30:08

  በርዕሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን ግርማ

@ortodoxtewahedo
24 አቡነ ተክለሃይማኖት !!

" አቡነ ተክለ ሃይማኖት ተክለ ሃይማኖት ማለት የሃይማኖት ተክል፣ ተክለ አብ ተክለ ወልድ ተክለ መንፈስ ቅዱስ ማለት ነው ፡፡"

ተክል› ማለት ፍሬያማ ዕንጨት፣ ዛፍ፣ ቅመም፣ ቅጠላ ቅጠል፣ የሚበላ፣ የሚሸተት፣ ገነታዊ ዕፅ፣ እንዲሁም ሕግ፤ ስርዓት ማለት ነው ( ማቴ.፲፭፥፲፫ ) ፡፡ ‹ሃይማኖት› ማለት ደግሞ በሀልዎተ እግዚአብሔር፣ እግዚአብሔር የሁሉ አስገኚ መሆኑን፣ በስላሴ አንድነትና ሶስትነት፣ በቅዱሳን ተራዳኢነት ማመን አምኖም መመስከር ማለት ሲሆን ‹ተክለ ሃይማኖት› የሚለው ሐረግም የሃይማኖት ተክል፣ ይኸውም የጽድቅ ፍሬን ያፈራ፣ ከኃጢአት ሐሩር ማምለጫ ዛፍ፣ ምእመናንን በቃለ ወንጌል ያጣፈጠ ቅመም፣ መዓዛ ሕይወቱ የሚማርክ፣ ቢመገቡት ረኃበ ነፍስን የሚያስወግድ ቅጠል፣ የጻድቃን መጠለያ ዕፅ የሚል ትርጉም አለው ፡፡
‹‹ተክለ ሃይማኖት ማለት የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ተክል ማለት ነው›› ሲል የጻድቁን ስም ይተረጉመዋል ፡፡

ጻድቁ አባታችን ሕይወታቸዉን ሙሉ ለእግዚአብሔር በመስጠት፣ እንደ በሬ ተጠምደው፣ እንደ ገበሬ ታጥቀው፣ ይህንን ዓለም ንቀው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው በብሕትውና በመኖራቸው፤ እርሳቸው በአሚነ ስላሴ ጸንተው ሌሎችንም እንዲጸኑና እንዲያምኑ በማድረጋቸው፤ እንደዚሁም እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ በመስበክ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድውያነ ስጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የፈወሱ ሰባኬ ወንጌል በመሆናቸው ‹‹ተክለ ሃይማኖት›› ተብለው ይጠራሉ ፡፡

ፃድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሀይማኖት ምልጃ በረከታቸው አይለየን ለሀገራችን ሰላምን ለህዝባችን ፍቅር አንድነትን ያምጡልን አሜን !!

@ortodoxtewahedo
#ለሞተው ወንድማችን በጋሻው እናልቅስለት

#ከኦርቶዶክሳዊ የቀና እምነቱ ወርዶ ተሐድሶ ሆነ፣
#ከተሐድሶነቱ ወርዶ የቄሳር ወታደር ሆነ፣
#ከቄሳር ወታደርነቱ ወርዶ ጴንጤ ሆነ፣
#ከጴንጤነቱ ወርዶ የቃል እምነት አስተማሪ ሆነ፣
#ከቃል_እምነት አስተማሪነቱ ወርዶ የብልጽግና ወንጌል ሰባኪ ሆነ፣
#ከብልጽግና ወንጌል ሰባኪነቱ ወርዶ የጆቫዊትነስ ሰባኪ ሆነ፣
#ወርዶ_ወርዶ የቀረው መስለምና ‘ፔገን’ መሆን ነው።

#ምስኪኑ የጴንጤ እምነት ተከታይም ለኦርቶዶክስ ባለው ጥላቻ ብቻ ዶግማ ምን እንደሆነ ስለማያውቅ ኦርቶዶክስን የተቃወመውን ሁሉ እየተከተለ አሜ.......ን እያለ ማጨብጨብ ነው።

#ስለዚህ ለሞተው ወንድማችን በጋሻው እናልቅስለት!

✍🏾ቀሲስ ዲበኩሉ በላይ

@ortodoxtewahedo
“የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።”

— ኤፌሶን 6፥17

@ortodoxtewahedo
‹‹ጌታዬ ሆይ! በሰው ፊት ክብሬን አትግለጥብኝ››

አቡነ ሀብተ ማርያም የዘውትር ጠባቂያቸው ቅዱስ ሚካኤል ካዘዛቸው በቀር ምንም አይሠሩም ነበር፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትንም ባነበቡ ጊዜ ኃይለ ቃሉን እየተረጎመ ምሥጢራትን ይነግራቸዋል፤ የተሰወረውንም ይገልጥላቸዋል፡፡ ከእንስሳት ጩኸት ጀምሮ ከዱር አራዊት ድምፅና እስከ አእዋፍ ቋንቋ ያለውን ያስረዳቸው ነበር፡፡

ይኸውም ቅዱስ መልአክ አንድ ቀን አቡነ ሀብተ ማርያምን ወደ ቤተ ክርስቲያን አስገብቷቸው ሥጋ ወደሙን ለመቀበል ተዘጋጅተው ሳለ ወንጌል የሚነበብበት ሰዓት ሲደርስ ያልተማረ ቄስ የክርስቶስ ጌትነቱን የምትናገር ወንጌልን ሲያነብ ‹‹ወዮሴፍ ብእሲሃ ለማርያም ጻድቅ ውእቱ›› የሚል ከቄሱ አፍ ይህን ንባብ አባታችን ሲሰሙ እጅግ ደንግጠው ወንጌል ወደሚነበብበት ስፍራ ሄደው የሚያነበውን ቄስ ገሠጹት፡፡ ‹‹ወዮሴፍሰ ፈሃሪሃ ለማርያም ጻድቅ ውእቱ በል እንጂ ብእሲሃ አትበል›› ብለው መከሩት፡፡ ቄሱም አቡነ ሀብተ ማርያም እንዳዘዙት ከስህተቱ ወደ ቀና ንባቡ ተመለሰ፡፡ ይህን ጊዜ ጌታችን ለአባታችን ድጋሚ ተገልጦላቸው ‹‹ሀብተ ማርያም ሆይ ይህን ትምህርትህን ወድጄ አመሰገንኩህ፣ የእናቴን የድንግል ማርያምን የድንግልናዋን ንጽሕና ስለ አከበርክ እኔም በመንግስተ ሰማያት ፈጽሜ አከብርሃለሁ›› አላቸው፡፡ ዳግመኛም ጌታችን ‹‹አሁንም ዮሴፍ ብእሲሃ ለማርያም የሚሉትን ሁሉ ለያቸው እንጂ አትተዋቸው፤ እንዲህ የሚል ጽሑፍም ብታገኝ እንዳይኖር እርሱን ፍቀህ ፈሃሪሃ ለማርያም የሚለውን ጻፍ›› ብሎ አባታችንን ካዘዛቸው በኋላ ሰላምታ ሰጥቷቸው ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡

አባታችንም በዚህ ጊዜ ፊታቸው ላይ ብርሃን ስለተሳለባቸውና እንደ ፀሐይ ስላበራ ሰዎችም አይተው ባደነቁ ጊዜ ወደ በዓታቸው ገቡና ጌታችንን ‹‹አቤቱ ጌታዬ ሆይ በሰው ፊት ክብሬን አትግለጥብኝ ሰውርልኝ፣ በቸርነትህም አድነኝ›› ብለው ጸለዩ፡፡እንዲህም ብለው በጸለዩ ጊዜ ፊታቸው መልኩ ተለውጦ እንደ ቀድሞው ሆነ፡፡

የአቡነ ሀብተ ማርያም የከበረች በረከታቸው ትደርብን!

@ortodoxtewahedo
† እንኳን ለጻድቁ አባታችን አቡነ ሀብተ ማርያም በዓል በሰላም በጤና አደረሰን †

† ሰላም ለአራኅከ ነሣኤ ኅለት ዘአሚን::
ዘይትባሕዩ ቦቱ አባግዒከ ዝርዋን::
ሀብተ ማርያም መርስ ሀብተ ማርያም ዛኅን::
ይሱቀኒ እምትንታኔ ጸሎትከ በትረ ሐፂን::
ለቁረተ ነፍስየ ካዕበ ቃልከ ክዳን::

† በአለም የተበተኑ በጏች የተባሉ ልጆችህ የሚጠበቅበት የእምነት ዘንግን ለጨበጠ መሐል እጅህ ሰላምታ ይገባል::
ጻድቁ አባቴ ሀብተማርያም ሆይ የዚች አለም ጸጥታዋና ሰላሟ አንተ ነህ እኮ እኔን ለመውደቅ የተፍገመገምኩትን እንደብረት ዘንግ የሆነ ጸሎትህ ከወደቅኩበት መሬት ያንሳኝ ይደግፈኝ ሁለተኛም የጏሰቆለች ነፍሴን ቃልኪዳንህ አይለያት::

📖 መልክአ አቡነ ሀብተ ማርያም

@ortodoxtewahedo
† እግዚአብሔር የቅዱሳንን ነፍስ ይጠብቃል ከሃጢአት እጅም ያድናቸዋል::†
📖 መዝ.96፡10

እንኳን ለታላቁ ጸድቅ ለጻድቁ አባታችን አቡነ ሀብተ ማርያም በዓል በሰላም በጤና አደረሰን አደረሳችሁ::

ጻድቁ አቡነ ሀብተማርያም በፈሪሃ እግዚአብሔር በትምህርት አደገ፡፡ ከዕለታት በአንድ ቀን ካህናቱ በቤተክርስቲያን ምህላ ሲያደርሱ "እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ" እያሉ ሲፀልዩ ሰምቶ በልቡናው ይህች ፀሎት በጣም ጥሩና መልካም ፀሎት ናት አለ በዚህ ፀሎት ከዓለም አሳችነት ከገሃነም እሳት እንድንባት ዘንድ አውቃለሁ የንስሐ መንገድ ናት ብሎ ተናገረ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ አባታችን አቡነ ሀብተማርያም በዚህች ፀሎት ተጠምዶ በጾምና በፀሎት በስደት የሚኖር ሆነ::

(ገድለ አቡነ ሀብተ ማርያም)

@ortodoxtewahedo
2024/09/28 17:22:45
Back to Top
HTML Embed Code: