‘’ኑ የእግዚአብሔርን ቤት በጋራ እንሥራ’’ በሚል መሪ ቃል ሥልጠናና ውይይት መካሄዱን በማኅበረ ቅዱሳን የደ/ታቦር ማእከል ገለጸ፡፡

መጋቢት ፫/፳፻፲፯ ዓ.ም

በማኅበረ ቅዱሳን የደ/ታቦር ማእከል በደ/ታቦር ከተማ ከሚገኙ የሰንበት ት/ቤት ሥራ አስፈጻሚዎች ጋር ‘’ኑ የእግዚአብሔርን ቤት በጋራ እንሥራ’’ በሚል መሪ ቃል ሥልጠናና የጋራ ውይይት አካሄዷል፡፡

መርሐ ግብሩ በደ/ታቦር ከተማ ከሚገኙ 50 የሰንበት ት/ቤት ሥራ አስፈጻሚዎች ጋር የሥልጠና፣ ተሞክሮ እና ውይይትያደረገ ሲሆን የሰ/ት/ቤቶች ምስረታ፣ ተግዳሮቶች፣ የአኃት አቢያተ ክርስቲያናት ተሞክሮ እና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች የሚሉ ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ያተኮረ ሥልጠና  በማኅበረ ቅዱሳን የደ/ታቦር ማእከል ሰብሳቢ በዲ/ን ዶ/ር ለማ ጉልላት ተሰጥቷል፡፡

አሠልጣኙ ሰ/ት/ቤቶቻችን መሰረታዊ ዕውቀትን ማስገንብ፣ ነገረ ድኅነትን መሠረት ያደረገ  አገልግሎት፣ መጭውን ዘመን መቅደም፣ ትውልዱን በሁለም መንገድ መጠበቅ፣ በሁሉም ነገር አዎንታዊ ተጽእኖ መፍጠር፣ አቅዶ መሥራትና በጋራ መልማት ላይ ሊያተኩሩ ይገባል ሲሉ ማጠቃለያ ሰጥተዋል፡፡

ከሥልጠናው በኋላም እንደ ደ/ታቦር ከተማ ሰ/ትቤቶቻችን ያሉበት ሁኔታ፣ ተሞክሮዎች እና ወደ ፊት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች በሚሉ ነጥቦች ላይ ያወያዩትና ማጠቃለያ የሰጡት በደ/ጎንደር ሀ/ስብከት የሰ/ት/ቤቶች አንድነት ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ተስፋገኝ ጎበዜ ናችው፡፡
ኦርቶዶክሳዊ ቤተሰብንና ማኅበረሰብን ለመፍጠርና  ሥልጠና ለመሥጠት ከሚሴ ማእከል ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት አደረገ።

መጋቢት ፫/፳፻፲፯ ዓ.ም

የማኅበረ ቅዱሳን ሙያ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ሥልታዊ ትኩረት አድርጎ ከሚሠራቸው አገልግሎቶች አንዱ በሁለንተናዊ የምክክር አገልግሎት የሚሰማሩ ካህናትና ባለሙያዎችን በማሠልጠንና በማሰማራት ኦርቶዶክሳዊ ቤተሰብንና ማኅበረሰብን የሚያጠናክሩ አካላትን ማፍራት አንዱ ነው።

በዚሁ መሠረት ከመጋቢት 20 እስከ 21/2017 ዓ.ም  በከሚሴ ሀገረ ስብከትና ማኅበረ ቅዱሳን  በከሚሴ ማእከል አስተባባሪነት ለምእመን እና ካህናት አባቶች ሥልጠናውን ለመስጠት ከሰ/ት ት/ቤት፤ ከተስፋ ነደያን በጎ አድራጎት እና ከተለያዩ ጽዋ ማኅበራት  ስራ አስፈፃሚዎች ጋር ውይይት ተደርጓል።

በውይይቱ ክብረ ክህነትና አበ ነፍስ፣ መንፈሳዊ የምክክር አገልግሎት አሰጣጥና የምክክር መስጫ ስለመፍጠር፣ ኦርቶዶክሳዊ ጋብቻና የልጆች አስተዳደግ፣ የሱስ ችግሮችን ለማቃለል የአመካካሪዎች ሚና እንዲሁም ምጣኔ ሐብታዊና ማኅበራዊ እድገትን በተመለከተ የተዘጋጁ ይዘቶች ተዳሰው እንደሚሠጡ ገለፃ ተደርጓል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ለዝግጅቱ መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ለሚተባበሩት የከሚሴ ሀገረ ስብከትና በገንዘብና ቁሳቁስ ጭምር ድጋፍ ለሚያደርጉ የቤተ ክርስቲያን አካላት በቅንጅት አብረው እንደሚሠሩ በሰፊው ውይይት ተደርጓል፡፡
ሥልጠናው በሁለት ወረዳ ማእከላት ሲሰጥ የቆየ መሆኑን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የስብከተ ወንጌል ተደራሽነትን በሀገሪቱ ከፍሎች ለማስፋፋት ሥራዎች እየተሠሩ  አንደሚገኙ በማኅበረ ቅዱሳን የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ አስታወቀ


መጋቢት ፬/፳፻፲፯ ዓ.ም


በማኅበረ ቅዱሳን የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ የስብከተ ወንጌል ተደራሽነትን በሀገሪቱ ክፍሎች ለማስፋፋት ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡

የማስተባበሪያው ዳይሬክተር ዲያቆን ሙሉጌታ ነጋ እንደገለጹት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል ለሰው ልጆች እንዲዳረስና የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ እንዲሳካ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት የርቀት ትምህርት የመስጠት፣በድምፅ ወምስል የቤተ ክርስቲያን ትምህርቶችን በልዩ ቋንቋዎች የማሰራጨት፣ሰባክያነ ወንጌል መምህራንን የማሠልጠንና በቴክኖሎጂ የሀሎ መምህር አገልግሎት የመስጠት ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

እየተከናወነ በሚገኘው የወንጌል አገልግሎት አዳዲስ አማንያን አምነው ተጠምቀው የሥላሴ ልጅነት ማግኘታቸው፣ ቤተ ክርስቲያን በሌለባቸው አካባቢዎች እየታነጹ መሆናቸው እንዲሁም ከተጠመቁት ውስጥ ተምረው ሰባክያነ ወንጌል፣ካህናት፣ዲያቆናትና የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት መገኘታቸው በመሠረታዊ አዲስ ለውጥ እንደሚጠቀሱ ዳይሬክተሩ አንሥተዋል፡፡

ዲያቆን ሙሉጌታ አክለውም የጸጥታ ችግሮች፣ የአጽራረ ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች መብዛት፣የበጀት እጥረቶች፣ የቤተ ርስቲያን አገልግሎት ከማኅበራዊ፣ከኢኮኖሚያዊና ከልማታዊ ሥራዎች ጋር አለመቀናጀት ስብከተ ወንጌልን ለማዳረስ ተግዳሮቶች ቢሆኑም በተቻለ አቅም የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ውጤታማ እንዲሆን እየተሠራ  ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በቀጣይነትም የወንጌል አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ ሥራዎች በትኩረት እየተሠሩ በመሆናቸው ምእመናንና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ መልእታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በዚህ ዓመት 20 ሺህ 57 አዳዲስ አማንያን ተጠምቀው ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተቀላቀሉ ሲሆን 1ሺህ 19 ተማሪዎች በአማርኛና በኦሮምኛ ቋንቋዎች የርቀት ትምህርት እየተማሩ ይገኛሉ፡፡

በተጨማሪም በ0111 55 32 32 32 ወደ ሀሎ መምህር በመደወል ከሰኞ እስከ ዐርብ ባሉት ቀናት ሃይማኖታዊ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ምላሽ ማግኘት እንደሚቻል ተገልጿል፡፡
2025/03/14 08:26:11
Back to Top
HTML Embed Code: