Telegram Web Link
በተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ለነበሩ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች የሽኝት መርሐ ግብር ተከናወነ።
 
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደረጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን  አቡዳቢ ልዩ ግንኙነት ጣቢያ ከሊባኖስ፣የተባበሩት ዐረብ ኢምሬትስ እና የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገረ ስብከት ጋር በመተባበር ለትምህርት ወደ ተባበሩት ዐረብ ኤሜሬትስ በመሄድ ሲማሩ ለቆዩ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች የሽኝት መርሐ ግብር አከናወነ።

የመጀመሪያ ዓመት ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ አገር ቤት ለሚመለሱ ተማሪዎች ግንቦት 4 ቀን 2016 ዓ.ም በተከናወነው የሽኝት መርሐ ግብር ላይ ብፁዕ አቡነ ዲሜጥሮስ በሊባኖስና የተባበሩት አረብ ኢምሬትና የመካከለኛው ምስራቅ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ ፤ የሀገረ ስብከቱ ስራ አስኪያጅ ቀሲስ ደረጀ ጂማ፣ መላከ ሰላም መምህር ለይኩን ብርሃኑ፣ መምህር ኪሩቤል ይገዙ፣ ሊቃውንተ ቤተክርቲያናት እንዲሁም የልዩ ግንኙነት ጣቢያው አባላትና ተባባሪ አካላት ተገኝተዋል።

ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎችን ከመቀበል ጀምሮ፣ በግቢ ቆይታቸው መንፈሳዊ ሕይወታቸውንም አጠንክረው እንዲወጡ የተለያዩ ትምህርቶችን በመስጠት እና እንዲያገለግሉ በማድረግ ከፍተኛ ሥራ እየሠራ የሚገኘው ማኅበረ ቅዱሳን በኢማራት ዩኒቨርስቲ ግቢ ጉባኤ ሲያስተምራቸው የነበሩት እነዚህ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችም በመርሐ ግብሩ ላይ ወረብ እና መዝሙር፤  በኢማራት ላይ የአንድ አመት ቆይታቸውን በተመለከተ ውይይት ፤ እንዲሁም የአብነት ትምህርት ሁለንተናዊ ሕይወትንም የሚያስገነዝብ ትእይንትም አቅርበዋል።
የራስ አልኬማ ደብረ ይድራስ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን መምህር የሆኑት መጋቤ ምሥጢር ቀሲስ ናሁ ሠናይ “ ከእኔ ተማሩ” በሚል ርዕስ በመርሐ ግብሩ ላይ  ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ድሜጥሮስ የሊባኖስ፣የተባበሩት ዐረብ ኢምሬትስ እና የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ቃለ በረከት እና ቃለ ምዕዳን ሲሰጡ ባስተላለፉት መልእክት የእኛ አገልግሎት ሰዎች ሁሉ ቤተክርስቲያንን እንዲያውቁ እና በቤተክርስቲያን ምሥጢራት ውስጥ አልፈው ለጽድቅ እንዲዘጋጁ ማድረግ ነው ብለዋል። ለዚህ መከሩ ብዙ ለሆነ የእግዚአብሔር አገልግሎት ኦርቶዶክሳዊ የሆንን በሙሉ በተሰጠን ጸጋ እና በተቀበልነው ኃላፊነት ማገልገል ይገባል ብለዋል። ነገ የቤተሰብ፣የቤተክርስቲያን እና የሀገር መሪ የሚሆኑ የከፍተኛ ተቋም ተማሪዎችን ማስተማር እና አብሮአቸው መቆም ለምናገለግለው ጽድቅ፣ ለሚገለገሉት መለኮታዊ ምሪት፣ ለቤተሰብ፣ለቤተክርስቲያን እና ለሀገር ደግሞ ኅያው ሥራ ነው ካሉ በኋላ  መልካም ትውልድ የመቅረጽ ኦርቶዶክሳዊ ድርሻችንን በመወጣት ሰዎችን ወደ ቤተክርስቲያን እያቀረብን  ከሁሉ በላይ  የሆነችውን ቤተክርስቲያን ሁለተናዊ አገልግሎት እናስፋፋ ብለዋል።
የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ያዘጋጀው የግእዝ እና የአማርኛ የሐዲስ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስ የድምጽ ቅጂ ተመረቀ።

የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር በመተባበር ለዓይነ ስውራን፣ መጻፍ እና ማንበብ ለማይችሉ ምእመናን እንዲሁም ለአብነት ተማሪዎች የሚያገለግል የአማርኛ እና የግእዝ የሐዲስ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናዊ መሣሪያ በድምጽ ቅጂ ተዘጋጅቶ በዛሬው ዕለት በቦሌ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ካቴድራል ተመርቋል።

በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ብፁእ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የባሕር ዳር እና ሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁእ አቡነ ማርቆስ የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ አገልግሎት መምሪያ የበላይ ኃላፊ ፣ ብፁእ አቡነ ቀሌምንጦስ የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ  የበላይ ኃላፊ እንዲሁም የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ሊቀ ኅሩያን ይልማ ጌታሁን በመርሐ ግብሩ ላይ እንደገለጹት የመጽሐፍ ቅዱስ የድምጽ ቅጂ መሣሪያው አገልግሎት ላይ እንዲውል ከ11 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ሲሆን ከ26 በላይ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት እና ባለሙያዎች በሥራው ላይ ተሳትፈዋል ብለዋል።

ዋና ጸሐፊው ጨምረው እንደገለጹት የድምጽ መሣሪያውን አዘጋጅቶ ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመታትን የወሰደ ሲሆን አጠቃላይ ወጪው "Faith comes by hearing" በተሰኘ ዓለም አቀፍ ተቋም እንደተሸፈነ ተናግረዋል።
ብፁእ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የባሕርዳር እና ሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመርሐ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ዛሬ የተመረቀው የድምጽ መሣሪያ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጸው በሥራው ላይ ተሳታፊ ለነበሩት አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ብፁእነታቸው ጨምረው እንደተናገሩት የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ቤተክርስቲያን በቅርበት እየተከታተለች እንደምትደግፍ ገልጸው በተለይ ማኅበሩ  የጀመረውን መጽሐፍ ቅዱስን በኦሮምኛ ቋንቋ የመተርጎም ሂደት በባለቤትነት እንደምትከታተለው ገልጸዋል።

በመጨረሻም በድምጽ ቅጂ ሥራው ላይ ለተሳተፉ አካላት የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።
2024/09/28 02:18:38
Back to Top
HTML Embed Code: