Telegram Web Link
የ፵፪ ኛው አጠቃላይ ዓለም አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የአኅጉረ ስብከቶች ሪፖርት ተጠናቀቀ

ከጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ ያለው የአጠቃላይ ዓለም አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የአኅጉረ ስብከቶችን የ2015 ዓ.ም የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ሲያዳምጥ ቆይቷል።

በዛሬው ዕለትም ቀሪ የውጭ አገራት አኅጉረ ስብከቶችን ሪፖርት አዳምጦ የሪፖርት መርሐ ግብሩን አጠናቋል።

የሪፖርት ማቅረብ መርሐ ግብሩ መጠናቀቅን ተከትሎ የሰ/ት/ቤት ማደራጃ መምሪያ ከሰ/ት/ቤት አንድነት ጋር በጋራ በመሆን ለሰ/ት/ቤቶች መማሪያ በተዘጋጀው ሥርዓተ ትምህርት ዙሪያ መወያየት ጀምሯል።
👍4
ለሰ/ት/ቤቶች መማሪያነት የተዘጋጀውን ሥርዓተ ትምህርት ተግባራዊ ለማድረግ የሁሉም ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ በኩል ተዘጋጅቶ ወደ እንቅሰቃሴ እየገባ በሚገኘው የሰ/ት/ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት ዙሪያ ለ አጠቃላይ ዓለም አቀፍ  ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች ማብራሪያ ቀርቧል።

ማብራሪያውን የሰጡት የአገር አቀፍ ሰ/ት/ቤት አንድነት ም/ሰብሳቢ ዲ/ን ስንታየሁ ምስጋናው እንደተናገሩት የሰ/ት/ቤች ሥርዓተ ትምህርትን ለመቅረጽ እጅግ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል።

አሁን ተቀርጾ ወደ ተግባር እንዲገባ የሚጠበቀው ሥርዓተ ትምህርት 6 ዋና ርእሶች እና አንድ ደጋፊ ርእስ ያለው ሲሆን ለዘንድሮው ዓመት ትግበራ እንዲሆን 42 መጽሐፍት ታትመው እና በሊቃውንት ጉባኤ ተገምግሞ ዝግጁ ሆኗል።

አቅራቢው በተጨማሪ እንደገለጹት ሥርዓተ ትምህርቱ አሁን ያለው ትውልድ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ተረድቶ መንፈሳዊ ወጣት እንዲሆን የሚያስችል ዕውቀትን የያዘ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለተግባራዊነቱ እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል።

ብፁዕ አቡነ አብርሃም የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቃ ጳጳስ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዳሉት አሁን ያለውን ትውልድ ለማዳን ሰ/ት/ቤትን ማጠናከር የግድ ይለናል ብለዋል።

በተጨማሪም ሁሉም አኅጉረ ስብከቶች ሥርዓተ ትምህርቱ ተግባራዊ እንዲሆን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ መልእክት አስተላልፈዋል።
👍43👎2
፵፪ ኛው ዓለምአቀፍ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ
****

ለ፵
፪ ኛ ጊዜ የሚካሔደው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዓለም አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የተዋጣለት፣የተሳካና ውጤታማ በሆነ መልኩ መከናወን ይችል ዘንድ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎቹ በሚገባ ታቅደው፣ ለእያንዳንዱ ተግባር አስፈጻሚና ፈጻሚ አካል ተቀምጦለት የተከወነ ከመሆኑም በላይ የእያንዳንዱ ኮሚቴ የሥራ አፈጻጸምና አጠቃላይ የቅድመ ዝግጅት ሥራው አፈጻጸም በብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሚመሩት አስተዳደር ጉባኤ ተገምግሞ  ማስተካከያ  የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ከተስተካከሉና ከታረሙ በኋላ ወደ ተግባር እንዲለወጡ ተደርጓል፤ ይህም በመደረጉ እያንዳንዱ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ያማረና የተዋበ እንዲሆን ማድረግከመቻሉም በላይ በአፈጻጸም ደረጃም ውጤት የተመዘገበበት መሆን ችሏል።

ጉባኤው ውጤታማ ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር እንዲረዳን በየዕለቱ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት  ጸሎትና ቡራኬ ተከፍቶ በቅዱስነታቸው ሊቀ መንበርነትና መመሪያ መሠረት እየተካሄድ ይገኛል ፡፡

በተለይም ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ጉባኤውን ፍትሐዊ በሆነ መልኩ በመምራታቸው የሰዓት መዛነፍና የተንዛዛ ሪፖርት እንዳይቀርብ ማድረግ ያስቻለ ሲሆን ከመርሐ ግብር ውጪ የሆኑና  መስመራቸውን የሳቱ እንዲሁም ከእውነተኝነት የራቁ   ሪፖርቶችን በማረቅ ሐቁ በግልጽ እንዲቀመጥ ያደረጉበት ጥረትም የብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁን የጉባኤ አመራር ጥበብና ብቃት ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ተግባር ሆኖ ተመዝግበዋል። ጉባኤውም በተደጋጋሚ ጊዜ ይህን ሐቅ በጭብጨባ ሲገልጽ ተስተውሏል።
👍20
ሌላውና በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ዘመነ ሢመት ሥር ነቀል ማስተካከያ የተደረገበት ከዚህ በፊት ተጀምሮ መቀጠል የተሳነው ብዙዎች በየዓመቱ በሚካሔደው ጉባኤ ሲተቹት የሚሰማው ውይይት ለምን አይደረግም? የገንዘብ ሪፖርት ብቻ ነው የሚሰማው፣ ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎችን የመለሰና በቡድን የተደረገ ውይይትን በጋራ ማብራሪያ የሚሰጥበት አሠራር ተጠናክሮ እንደገና የተጀመረው በብፁዕ አቡነ አብርሃም  የአመራር ዘመን እንደሆነ እርግጥ ነው።

በዘንድሮ  ዓለም አቀፍ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይም  ልዩ ልዩ ወቅታዊ ጥያቄዎችን በማንሣት ውይይት ቢቀር ጥሩ ነው የሚል ዐሳብ ያነሡ የነበሩ ብዙዎች ቢሆኑም ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ግን ውይይት ሊፈራ አይገባውም። መለመድ አለበት። ችግሮች መፍትሔ የሚያገኙት በውይይት ነው።ስለዚህ ውይይት መካሔድ አለበት የሚል ጽኑዕ አቋም  በማራመዳቸው የጋራም የቡድንም  ውይይት በ፵፪ ኛው ዓለም አቀፍ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ  ጉባኤ እንዲካሔድ  በአስተዳደር ጉባኤ ተወስኖ  በመርሐ ግብሩ ተካቶ እነሆ ተፈጻሚ የሚሆንበት ጊዜ ሰሌዳ ላይ ደርሰናል።

በሚደረገው የቡድንም ሆነ የጋራ ውይይት ችግሮቻችንን የምንመለከትበት፣ለችግሮቻችን መፍትሔ የምንሰጥበት ሁኔታ እንደሚፈጠርም በዛሬው  ዕለት በተጀመረው የውይይት መርሐ ግብር ላይ የተነሡት ዐሳቦችና ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የተሰጡት ማብራሪያዎች በቂ ማሳያዎች ናቸው። በቀሪው ጊዜም ይህን መሰል  ገንቢና አስተማሪ ዐሳቦችን በሚገባ በማንሸራሸር በተቋም ደረጃ መፍትሔ የሚፈለግበትን መንገድ በመጠቆም በጉባኤው ላይ የተነሡ ዐሳቦችን መሠረት በማድረግ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ የሚያርፍበትን ሁኔ ታ በማመቻቸት ቢያንስ  በዚህ ዓመት ችግሮቻችንን  በውል  ተገንዝበን ከችግሮችን መውጣት በመጀመር ቅድስት ቤተክርስቲያናችንን መታደግ እንድንጀምራለን የሚል ተስፋ አለን።

በአጠቃላይ  በዘንድሮ  ጉባኤያችን ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ጉባኤው መገባደጃ ቀን ድረስ የተመዘገቡ ውጤታማ ተግባራትን እውቅና መስጠት ተገቢ ስለሆነ ጉባኤው ያማረና የተሳካ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት ያደረጉት ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ዶ/ር የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒውዮርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ፣በልዩ ልዩ ኮሚቴዎች በመታቀፍ ውጤታማ ሥራ ላከናወናችሁ የኮሚቴ አባላት፣ለጉባኤው ሞገስ በመሆን ለሰነበታችሁ ለመላው ጉባኤ አባለት ምስጋና ሊቸራችሁ ይገባል።

ከሁሉ በላይ  ዘመኑን የሚመጥን አባታዊ  መልዕክት በማስተላለፍ፣  በጸሎት በመክፈትና በመዝጋት ፣አባታዊ  ምክርና ትምህርት በመስጠት በትዕግሥት ጉባኤውን ሲመሩ የሰነበቱት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ቅድስት ጸሎትዎና ቡራኬዎ ለጉባኤያችን ሞገስ ሆኖታልና ዘወትር ቡራኬዎ እንዳይለየን እንጸልያለን።

"ልዑል እግዚአብሔር ጉባኤያችንን  በሰላም ያስጨርሰን! "

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
         ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
      ጥቅምት ፱ ቀን ፳፻ ፲ወ ፮ዓ.ም
           አዲስ አበባ -ኢትዮጵያ
👍31👎3
የ፵፪ ኛው አጠቃላይ ዓለም አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አምስተኛ  ቀን ውለ ተጀምራል። በዛው ዕለት በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የቡድን ውይይት የሚካሄድ ይሆናል።

ብፁዕ አቡነ አብርሃም የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጰጳስ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እንደገለጹት የዛሬው የቡድን ውይይት በተመረጡ ርእሶች ላይ የሚያተኩር ሲሆን የሚነሱ የመፍትሔ ሐሳቦችም መሬት ላይ የሚወርዱ እና ለውጥ የሚያመጡ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በዛሬው ውይይት ላይ መነሻ ተደርገው የተቀመጡት ርእሰ ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው

1. የቤተ ክርስቲያን የፈተና እና ምክንያቶች
2. ለቤተ ክርስቲያናችን ተግዳሮት የሆኑ ውስጣዊ ችግሮቻችን እና መፍትሔዎቻቸው
3. ውጫዊ ችግሮቻችን እና መፍትሔዎቻቸው
4. የአብያተ ክርስቲያናት ስደት፣ መከራ እና የንብረት ውድመት በተመለከተና መፍትሔዎቻቸው
5. የቤተ ክርስቲያን አንድነት እንዴት ይቀጠል
6. የሀገራዊ ምክክር ላይ የቤተ ክርስቲያን ድርሻ ምን መሆን አለበት
7. በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚነሱ የሐሰት ትርክቶችን በተመለከተ ቤተ ክርስቲያን ምን ታድርግ
8. ሙስናን ስለመከላከል
9. የሀገራዊ ሰላምን በተመለከተ የቤተ ክርስቲያን ድርሻ ምን ይሁን
10. ክብረ ክህነትን ለማስጠበቅ ከእያንዳንዳችን ምን ይጠበቃል

የሚሉ ሲሆኑ ተወያዮች በቡድን በመከፋፈል በርእሰ ጉዳዮቹ ላይ መወያየት ጀምረዋል።
👍6
ማኅበረ ቅዱሳን በድርቅ ለተጎዱ በደቡብ ኦሞ ዞን ቡራና ቦላ ቀበሌዎች ለሚገኙ ወገኖቻችን ድጋፍ ተደረገ።
+++

በዚህ ወቅት በመላ ሀገራችን እያጋጠሙ ባሉት ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ብዙ ወገኖቻችን ለከፋ ማኅበራዊ ቀውሶች ተጋልጠዋል። ከእነዚህ ውስጥ በጠረፋማና ገጠራማ አካባቢዎች ያጋጠመው ድርቅ ተጠቃሽ ነው።

በተለይ ደግሞ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት ከተገቢው የማኅበራዊ አገልግሎት ጋር በበቂ ሁኔታ ካለመቀናጀቱ የተነሣ መሰል ቀውሶች ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈሉ እንደሚገኝ የታወቀ ነው።

ማኅበረ ቅዱሳንም የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አገልግሎት  በሚጠቅበት ደረጃ እንዲነቃቃና ተገቢውን ሚና መወጣት እንዲቻል ሰፊ ሥልታዊ ተግባራትን ቀርጾ እየሰራ ይገኛል። ከእነዚህ ውስጥም አስቸኳይ ማኅበራዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ወገኖች ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግ መረጃን መሠረት ያደረጉ ፕሮጀክቶችን እየቀረጸ ገቢ በማሰባሰብ ተግባራዊ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
👍14
ስለሆነም ማኅበሩ በደቡብ ኦሞ ዞን በስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር ተደራሽነት በትኩረት ለሚሠራባቸው የበናፀማይ ወረዳ ቡራ እና ቦላ ቀበሌዎች ለሚገኙ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ጥቅምት 4 ቀን 2016 ዓ.ም  በቦታው በመገኘት 150 ኩንታል አስቸኳይ የምግብ ግብዓቶች ድጋፍ አድርጓል። ለዚህ ድጋፍም 722,000 (ሰባት መቶ ሃያ ሁለት ሺህ) ብር ወጭ ተደርጓል። ድጋፉ በአሜሪካን ቨርጂንያ ከተማ ከሚገኙ የሰማእቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጽዋ ማኅበር በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የተከናወነ ነው።
በድጋፉም ርክክብ ወቅትም የማኅበረ ቅዱሳን ጅንካ ማእከል ልዑካን ፣ የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ተወካይ ቀሲስ ፍሬ ሃይማኖት በቀለ፣ የወረዳው የመንግስት ተወካዮችና ቁጥራቸው ከ600 በላይ የሆኑ የቡራ እና ቦላ ቀበሌ ነዋሪዎች በተገኙበት የድጋፍ ሥርጭት ተደርጓል። በዕለቱም የወረዳ አስተዳዳሪ ተወካዩን ጨምሮ የሀገር ሽማግሌዎች አባቶች እና እናቶች ከማኅበሩ በተደረገላቸው ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።

ማኅበረ ቅዱሳን በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ለሚፈጠሩ ማኅበራዊ ቀውስና ሃይማኖት ተኮር ጥቃትን በስፋት በማጥናት ላለፉት 4 ዓመታት በአርሲ፣ በሐረር ፣ በባሌ፣ በወሊሶ፣ በሻሸመኔ፣ በመተከል፣ በቤንሻጉል ጉምዝ ፣በቦረና፣ በትግራይ እና በአማራ ክልል እንዲሁም በሌሎች የሀገራችን ክፍል ያጋጠሙ ማኅበራዊ ቀውስና ሃይማኖታዊ ጥቃቶችን መረጃ በማደራጀት ፕሮጀክቶችን በመንደፍ ድጋፍ አድራጊ ምእመናንና በጎ አድራጊ ተቋማትን እያስተባበረ የአልባሳት፣ የምግብ እና መሠል አስቸኳይ ድጋፎችን በስፋት ሲያደርግ ቆይቷል። አሁንም አጠናክሮ ቀጥሏል።

ማኅበሩ በቅርብ ጊዜያት ብቻ በሻሸመኔና በወለቴ ጉዳት ለደረሰባቸው የሰማዕታት ቤተሰቦች፣ በትግራይ ክልል ለሚገኙ 10 ገዳማትና አገልጋዮች፣ በቦረና ያቤሎ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች፣ በጦርነቱ ተፈናቅለው በጎንደር አዘዞ ለሚገኙ ተፈናቃዮችና በዋግኸምራ ለሚገኙ፣ ከስልጤ ተፈናቅለው ቡታጅራ ለሚገኙ ተጎጅዎች ተመሳሳይ ድጋፎች አድርጓል።

ማኅበረ ቅዱሳን በቀጣይ ጊዜም በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በማኅበራዊ ቀውስ ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች ተጨማሪ ድጋፎችን ለማደረስ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን መሰል የነፍስ አድን የአስቸኳይ ድጋፍና መልሶ ማቋቋም ሥራዎችን አጠናክሮ ለመቀጠል በሚደረገው የሰብአዊ ድጋፍ ሥራ ምእመናን፣ ማኅበራት፣ ልዩ ልዩ ተቋማትና በጎ አድራጊ ድርጅቶች የተለመደ ትብብራችሁን አድርጉልኝ ሲል ጥሪውን ያቀርባል።

ለዚህ የማኅበራዊ ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግም፡- በማኅበረ ቅዱሳን የማኅበራዊ ድጋፍና መልሶ ማቋቋም ሒሳብ ቁጥሮች፡-

1.  በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ - 1000309803648
2.  በአሐዱ ባንክ - 0025393810901
3.  በወጋገን ባንክ - 0837331610101
4.  በአቢሲንያ ባንክ - 37235458
5.  በአዋሽ ባንክ - 01329817420400 መጠቀም የምትሉ መሆኑን እንገልጻለን።
ለበለጠ መረጃ
•  09 84 18 15 44
•  09 43 00 04 03
•  ማኅበረ ቅዱሳን ሕንጻ 1ኛ ወለል
የማኅበረ ቅዱሳን ሙያና ማኅበራዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ
👍11
2025/07/12 22:16:18
Back to Top
HTML Embed Code: