Telegram Web Link
ጌታችንም ጊዜው ሲደርስ ከሐዋርያት ጋር በአንድነት መጣ፤ ስምዖንም ከቤቱ ወጥቶ ሮጦ ከጌታ እግር ሥር ሰገደ፤ ወደ ቤቱም ከሐዋርያት ጋር አስገባቸው፡፡ ይሁዳ ግን ይህን ሰዓት አልነበረም፤ ውጪ ከሻጭና ለዋጭ ጋር ገንዘብ ሲደራደር ነበር፤ ስምዖንም ለሚስቱ አክሮሲና ጌታና ሐዋርያት የሚገቡበት በእግራቸው የሚረግጡት ምንጣፍ እንድታነጥፍ አዘዛት፡፡ አክሮሲና ግን የጌታን መልክ አታውቀውም ነበር፤ ያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ጸሎት ሲጸልዩ አይታ ‹‹ከእናንተ ውስጥ መምህሩ ማነው›› አለቻቸው፤እነርሱም ዝም አሉ፤ መልከ መልካም ወደ ሆነውና የጌታ ወዳጅ ወደሆነው ዮሐንስ ተመልክታ እርሱ ይሆን አለች፤ ጴጥሮስ ግን ቀበል አድርጎ ‹‹ጌታ ኢየሱስ ከውስጠኛው ክፍል ቆሞ ይጸልያል፤ ጌታ እርሱ ነው›› አላት፡፡ እርሷም ገብታ ሰገደችለት፤ ይሁዳም በመጨረሻ ሳጥን ተሸክሞ መጣ፤ ጠባቂውንም እኔ የጌታ ደቀ መዝሙር ነኝ አለው፡፡ በር ጠባቂውም እለእስክንድሮስም የተነጠፈውን እስካጥፍ ጠብቅ ብሎ ዘለፈው፤ ልብሱንም አንስቶ አስገባው፤ /ግብረ ሕማማት ፭፻፹፫-፫፻፹፭/፡፡

በአንደኛው ሰዓት ሌሊት (ሐሙስ ለአርብ ምሽት)፤

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ልብሱን አኖረ፤ማበሻ ጨርቅም አንስቶ ወገቡን ታጠቀ፤ ይህችውም ሥራ የምታሠራና የምታስጌጥ ናት፤ ለዛሬው የመነኮሳት መታጠቂያ አብነት ናት፡፡ ለምሳሌ፡- ኢዮአብ ወደ ሰልፍ ሲገባ እየለበሳት ይገባ እንደነበረችው ያለ ዓይነት ነው፤ ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጥብ ዘንድ በጴጥሮስ ጀመረ፤ ጴጥሮስ ግን እኔ ባንተ ልታጠብ አይገባኝም አለ፤ ጌታችንም መልሶ ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፤ እኔ እግርህን ካላጠብኩህ ከእኔ ጋር ዕድል ፈንታ የለህም›› (ዮሐ.፲፫፥፰)፡፡ ሌሎቹንም ሐዋርያት አጠባቸው፤ አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳንም እግሩን አጠበው፡፡ ጌታ አሳልፎ እንደሚሰጠው ሳያውቅ ቀርቶ አልነበረም፤ ፍቅርን ሲያስተምረውና ለንስሐ ጊዜ ሲሰጠው ነው እንጂ፤ እኛንም ለሚወደን ብቻ ሳይሆን ለሚጠላን እንኳን በጎ ማድረግ እንደሚገባ ሲያስተምረን ነው፡፡

ጌታችን ጾመና ጹሙ አለን፤ተጠመቀና ተጠመቁ አለን፤ ጸለየና ጸልዩ፤ ሰገደናም ስገዱ አለን፤ የሐዋርያትንም እግር አጥቦ እናንተም እንዲህ አድርጉ ብሎ መምህረ ትሕትናነቱን ገለጠልን፡፡ ዛሬም ከፓትርያርኩ ጀምሮ ሊቃነ ጳጳሳት፤ካህናት በየመአርጋቸው የምእመናኑን እግር በማጠብ የጌታን የትሕትና ሥራ ያስቡታል፡፡

ለሐዋርያት ትሕትናን ሲያስተምራቸው ጌታችን እግራቸውን እንደ አጠባቸው ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡ ከዚያም ዝ ውእቱ ሥጋየ ዝ ውእቱ ደምየ ብሎ ሥጋውንና ደሙን ሰጣቸው፤ ዛሬም የልጅነት ጥምቀት የሚቀበሉ ምእመናን በዚያኑ ዕለት ከክርስትና ቤት ወደ ቤተ መቅደስ ሔደው የጌታን ክቡር ሥጋና ደም ይቀበላሉ፤ መሠረቱም ጌታችን ለሐዋርያት ያደረገውን ተመርኩዞ ነው፡፡ ከፍ ከፍ ሊል የሚወድ ራሱን ዝቅ ያድርግ ብሎም አስተምሯቸዋል፤ አባ ጊዮርጊስ በመጽሐፈ ምሥጢር ጌታ ለጴጥሮስ ‹‹እኔ እግርህን ካላጠብኩህ ከእኔ ጋር ዕድል ፈንታ የለህም›› ያለውን ሲተረጉሙ ‹‹እኔ በአገልጋይ አምሳል እግርህ ካላጠብኩህ አንተም ከበታችህ ላሉት ራስህን ዝቅ ለማድረግ አትችልም፤ ራስህን ዝቅ ዝቅ ካላደረግህ አለቃ ልትሆን አትችልም›› ለማለት ነው ብለው ተርጉመውታል፡፡ ጌታችን ደግሞ አምላክ ፈጣሪ መምህር ሳለ ዝቅ ብሎ እንዳጠባቸው እነርሱም ክህነታቸውንና መምህርነታቸውን በትሕትና እንዲጀምሩ ሲያስተምራቸው ነው፡፡

በሁለተኛው ሰዓተ ሌሊት ምሽት፤

ጌታችን ሕብስቱን ባርኮ ለዐሥራ ሦስት ፈትቶ ሰጣቸው፤ ዐሥራ ሦስተኛውን እርሱ የሚቀበለው ነውና ነገር ግን የሚረባውና የሚጠቅመው አይደለም፤ ‹‹ዝ ውእቱ ሥጋየ ዝ ውእቱ ደምየ›› ብሎ ሕብስቱን ባርኮ ‹‹ይህ ሥጋዬ ነው እንካችሁ ብሉ ›› ወይኑንም ባርኮ ‹‹ይህ ደሜ ነው እንካችሁ ጠጡ›› ብሎ ሰጣቸው፡፡አስራ ሦስት አድርጎ መፈተቱ ሐዋርያትን እንዳይገርማቸው (እንዳያስፈራቸው) ነው፤ እራሱም ጥዒሞ አጥዐሞሙ/ቀምሶ አቀመሳቸው/ እንዲል አብነት ለመሆን፤ አንድም ነገ በመልዕተ መስቀል አስራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል እቀበላለሁ ሲል ነው፤ ጌታ ይህን ባያደርግ ኖሮ ዛሬ ካህኑ የጌታን ሥጋና ደም ሳይቀበል አቀብሎ ብቻ በሄደ ነበርና ለእነርሱ ለማስተማር ነው፡፡

ማዕዱንም እየበሉ ጌታችንም ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ! ከእናንተ መካከል አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል›› አላቸው፤ (ዮሐ.፲፫፥፳፩)፡፡ ሐዋርያት ሁሉ ደነገጡ! እርስ በርሳቸው ተያዩ፤‹‹እኔ እሆን? እኔ እሆን?›› ተባባሉ፤ ጴጥሮስም ዮሐንስን ጠጋ ብሎ ‹‹ማነው አሳልፎ የሚሰጠህ ብለህ ጌታን ጠይቀው›› አለው፤ወንጌላዊው ዮሐንስም ጌታን ጠጋ ብሎ ጠየቀው ጌታችንም ‹‹ከእኔ ጋር እጁን ከወጪቱ የሚያገባ እርሱ አሳልፎ ይሰጠኛል›› አለ፤ (ማቴ.፳፮፥፳፫/ሉቃ.፳፪፥፳፩)፡፡ ሐዋርያትም ‹‹ሁላችን ከወጪቱ የምንጠቅስ አይደለምን?›› ሲሉ ጌታችን ‹‹እኔ ከወጡ አጥቅሼ የምሰጠው ነው›› አላቸው፤ ያንጊዜ አጥቅሶ ለአስቆሮቱ ይሁዳ ሰጠው፤ ስለዚህ ወንጌላውያኑ ይህን ታሪክ ይዘው አንድ ሳለ በተለያየ አገላለጥ ገለጡልን፡፡

ይሁዳም እንደቸኮለ ሰው ይቅበዘበዝ ነበር፤እርሱም ጌታን እንዴት አሳልፎ እንደሚሰጠው በልቡ እያሰበ ነበር፡፡ ጌታም ወደ ይሁዳ ጠጋ ብሎ ‹‹ወዳጄ ይሁዳ ሆይ! ልትሠራው የምትሻው ሥራ ካለ ሒድ›› አለው፤ (ዮሐ.፲፫፥፳፯)፤ ይሁዳም ፈጥኖ ወጥቶ ወደ አይሁዳውያን ጌታን አሳልፎ ሊሰጥ ዋጋ ሊነጋገር ሔደ፡፡

ከሦስተኛው ሰዓተ ሌሊት እስከ አምስተኛይቱ ሰዓተ ሌሊት ድረስ

ለደቀ መዛሙርቱ ሲመክራቸው የመንፈስ ቅዱስንም መምጣት አብዝቶ ሲነግራቸው፤ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ አቀና፤ እርሱ ከአባቱ ጋር አንድ እንደሆነም ነገራቸው፤ ለብቻው ፈቀቅ ብሎ ወዙ እንደ ደም እስኪፈስ እየሰገደ ጸለየ፤ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመለሰ፤ ተኝተው አገኛቸው፤ ቀሰቀሳቸው፤ ጴጥሮስንም አንድ ሰዓት ያህል እንኳን ከእኔ ጋር መትጋት አቃታችሁን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ አለው! (ሉቃ.፳፪፥፲፬-፵፮)፡፡

የጌታችን በአይሁድ መያዝ (ስድስተኛው ሰዓተ ሌሊት)

ጌታችንም ከአብ ጋር ስላለው አንድነትና ክብር ለሐዋርያት ካስተማራቸው በኋላ ‹‹ኢየሱስም ይህን ተናግሮ አትክልት ወደ አለበት ስፍራ ወደ ቄድሮስ ወንዝ ማዶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወጣ፤ በዚያም ገባ›› (ዮሐ.፲፰፥፩)፡፡ወንዙን ተሻግሮ ያለውን ዛፍ አልፎ ወዳለው ዱር ገባ፡፡ ይሁዳም ይህችን ስፍራ ቀድሞ ጌታ ይመጣባት ስለነበር ያውቃት ነበርና ጭፍሮችንና የካህናት አለቆችን ፈሪሳውያን ሌሎች ፋና ጋሻ ጦርም የያዙትን አስከትሎ መጣ፡፡ ጌታችንም ‹‹ተነሡ እንሂድ! እነሆ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቧል›› አላቸው ወደ እነርሱ መጥቶ ቀረበ፤ ይሁዳም ወደርሱ ቀርቦ፤ ‹‹መምህር ሆይ ቸር ውለሃል፤ ሰላም ላንተ ይሁን›› ብሎ ሳመው፤ ይህ መሳም ለአይሁድ ጥቆማ ወይም ምልክት ነበር፡፡ ምክንያቱም የጌታ መልክና የወንጌላዊው የዮሐንስ መልክ ይመሳሰልባቸው ነበርና ሲለይላቸው ነው፤ ጌታችንም ‹‹በስኢምኑ ታገብኦ ለወልደ ዕጓለ እመሕያው፤ የሰውን ልጅ በመሳም አሳልፈህ ትሰጠዋለህን?›› አለው (ሉቃ.፳፪፥፵፰)፡፡
ይሁዳም ከጭፍሮቹ ጋር መጣ፤ ጌታ ኢየሱስንም ከበውት ወደ ሽማግሌዎችና የካህናት አለቃ ቀያፋ ወዳለበት ወሰዱት፤ ጴጥሮስ ግን ከሩቅ ሆኖ ይከተለው ነበር፤ የነገሩንም ፍጻሜ ያይ ዘንድ ከአንደኛው ቅጥር ግቢ ገብቶ ተቀመጠ፡፡ አይሁድም በክርስቶስ ላይ ሁለት የሐሰት ምስክሮችን አመጡ ‹‹ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ በሦስተኛው ቀን እሰራዋለሁ›› ብሏል ብለው ከሰሱት፤ ሊቀ ካህናቱም ተነስቶ ‹‹እንዲህ ሲያጣሉህ አትሰማምን›› አለው፡፡ ጌታችን ግን ምንም አልመለሰለትም፤ሊቀ ካህናቱም ‹‹ክርስቶስ ተብሎ የተነገረልህ የእግዚብሔር ልጅ አንተ እንደሆንክ ንገረኝ›› አለው፡፡ ጌታችንም ‹‹አንተ አልክ›› አለው፤ ያን ጌዜ ሊቀ ካህናቱ ተናዶ ልብሱን ቀደደው፤ራሱንም በብረት ዘንግ መቱት፤ የስቃዩ ጅማሬ ይህን ጊዜ ነበር፡፡
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደረጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም እና የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ መምህር ዋሲሁን በላይ ዛሬ ሚያዚያ 24/2016 ዓ.ም ከመኖሪያ ቤታቸው በጸጥታ አካላት መወሰዳቸው ታውቋል።

የሁለቱ አገልጋዮች መኖሪያ ቤት መፈተሹም ተገልጿል።

በአሁኑ ሰዓት ሜክሲኮ ፌዴራል ፓሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ የሚገኙ ሲሆን የተያዙበት ምክንያት አልታወቀም።

ዝርዝር እንደደረሰን እናቀርባለን።
ዓርብ ስቅለት (የድኅነት ቀን)

እንኳን አደረሰን!

ዓርብ ስቅለት የዕዳ ደብዳቤያችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለመጨረሻ ጊዜ የተደመሰሰበት፤ ከአጋንንት አገዛዝ ነጻ የወጣንበት ዕለት ስለኾነ ‹የድኅነት ቀን› ይባላል፡፡ ጌታችን ከተያዘባት ሰዓት አንሥቶ አይሁድ ከቀያፋ ወደ ሐና፣ ከሐና ወደ ቀያፋ ሲያመላልሱት አደሩ፡፡ ሲነጋ ከቀያፋ ወደ ጲላጦስ አደባባይ አስረው ወሰዱት (ማቴ. ፳፯፥፩-፶፯)፡፡ አይሁድ ይህን አጥፍቶአል የሚሉት ነጥብ ሳይኖራቸው ነውና ጌታችንን ለፍርድ ያቀረቡት ጲላጦሰ እነርሱ ወደ ተሰባሰቡበት ቦታ ወጥቶ ‹‹ይህን ሰው ወደ እኔ ያመጣችሁበት በደል ምንድን ነው?›› ሲል በጠየቃቸው ጊዜ በቂ ምላሽ አላቀረቡም፡፡

‹‹ክፉ የሠራ ባይኾንስ ወደ አንተ ባላመጣነውም ነበር›› በሚል የሸፍጥ ቃል ሲያጕረመርሙ ጲላጦስ መልሶ ‹‹እኔ ምንም ጥፋት አላገኘሁበትም፤ እናንተወስዳችሁ እንደ ሕጋችሁ ፍረዱበት፤›› አላቸው፡፡ አይሁድም ኦሪት ‹‹ኢትቅትል ብእሴ ጻድቀ ወኀጥአ ኢታኅዩ፤ ጻድቅን ሰው አትግደል፤ ኀጥኡንም ከፍርድአታድን፤›› ትላለችና ‹‹እኛስ ማንንም ልንገድል አልተፈቀደልንም፤›› ብለዋል (ዮሐ. ፲፰፥፳፰-፴፩)፡፡ ይኸውም መንፈስ ቅዱስ ‹‹በሕጋችን ጻድቀ ባሕርይክርስቶስን መግደል አይገባንም ሙሉ በሙሉ ጥፋተኞች ነን፤›› ሲያሰኛቸው ነው፡፡ በኋላም እርሱ ሞቶ ዓለም ይድን ዘንድ ወደ ምድር መጥቷልና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ጥፋቱ ሞት ተፈረደበት፡፡ ስለዚህም ገርፈው ሰቀሉት፡፡

ጌታችን ሲሰቅልም የሚከተሉት ሰባት ተአምራት ተፈጽመዋል፤

፩. ፀሐይ ጨለመ፤

፪. ጨረቃ ደም ኾነ፤

፫. ከዋክብት ረገፉ፤

፬. የቤተ መቅደስ መጋረጃ ተቀደደ፤

፭. አለቶች ተፈረካከሱ፤

፮. መቃብራት ተከፈቱ፤
፯. ሙታን ተነሡ (ማቴ. ፳፯፥፶፩-፶፬)፡፡

ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ የሚከተሉትን ሰባት ዐበይት ቃላት አሰምቶ ተናግሯል፤

፩. ‹‹ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ (አምላኪየ አምላኪየ ለምን ተውኸኝ?)››፤

፪. ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ››፤

፫. ‹‹አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁትምና ይቅር በላቸው››፤

፬. እመቤታችንን ‹‹ሴትዮ ሆይ፣ እነሆ ልጅሽ››፤ ደቀ መዝሙሩንም ‹‹እናትህ እነኋት›› በማለት የቃል ኪዳን እናትነትና ልጅነት ማከናወኑ፤

፭. ‹‹አባት ሆይ በአንተ እጅ ነፍሴን አደራ እሰጣለሁ››

፮. ‹‹ተጠማሁ››፤

፯. ‹‹ዅሉ ተፈጸመ›› (ማቴ. ፳፯፥፵፭-፵፮፤ ሉቃ. ፳፫፥፵፫-፵፮፤ ዮሐ. ፲፱፥፲-፴)፡፡

ከስድስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ጨለማ ኾኖ ከቈየ በኋላ ከዘጠኝ እስከ ማታ እንደ ተለመደው ብርሃን ኾኖአል፡፡ ‹‹ወፍና ሠርክ ይበርህ ብርሃነ ፀሐይ›› እንዲል (ዘካ. ፲፬፥፯)፡፡ በዚህ ዕለት ሰባት መስተፃርራን (ጠበኞች) ታረቁ፤ ተስማሙ፡፡ እነዚህም፡- ሰውና እግዚአብሔር፣ ሰውና መላእክት፣ ሕዝብና አሕዛብ፣ ነፍስና ሥጋ ናቸው (ኤፌ. ፪፥፲፤ ቈላ. ፩፥፳)፡፡ ጌታችን ጠዋት በሦስት ሰዓት ተገረፈ፤ በስድስት ሰዓት ተሰቀለ (ማቴ. ፳፯፥፩-፴፯፤ ሉቃ. ፳፫፥፩-፵፬፤ ዮሐ. ፲፱፥፩)፡፡

በዘጠኝ ሰዓት ጌታችን በውኃው ተጠምቀን፣ ደሙን ተቀብለን የእግዚአብሔር ልጆች እንኾን ዘንድ ከቀኝ ጎድኑ ጥሩ ውኃ፣ ትኩስ ደም አፈሰሰልን (ዮሐ. ፲፱፥፴፬)፡፡ በዐሥራ አንድ ሰዓት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከመስቀል አውርደው ሽቶ እየረበረቡ በድርብ በፍታ ገንዘው ቀበሩት (ሉቃ. ፳፫፥፶-፶፬፤ ዮሐ. ፲፱፥፴፰-፵፪)፡፡ ቅድስት ነፍሱ ወደ ሲኦል ወርዳ ነፍሳትን ነጻ አወጣች (፩ኛ ጴጥ. ፫፥፲፱)፡፡ በዚህ ጊዜ በርሃነ መለኮቱ በሲኦል ተገለጠ፡፡ ስለዚህም ‹‹ንሴብሖ ለእግዚአብሔር›› እየተባለ ይዘመራል፡፡ ከሆሣዕና አንሥቶ ተከልክሎ የነበረው ኑዛዜ ይናዘዛል፤ ጸሎተ ፍትሐት ይደረጋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም እና የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ መ/ር ዋሲሁን በላይ በትናንትናው ዕለት ሚያዚያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም በመንግሥት የጸጥታ አካላት ከመኖሪያ ቤታቸው ተወስደው ሜክሲኮ በሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ እንደሚገኙ አሳውቀን ነበር።


በዛሬው ዕለት ሚያዚያ 25 ቀን 2016 ዓ.ም ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን እየገለጽን፣ በሂደቱ ጉዳዩን በመረዳት አፋጣኝ ምላሽ የሰጡንን የመንግሥት የጸጥታ አካላት እናመሰግናለን።

በተጨማሪም በትዕግሥት ስትከታተሉና በጸሎት ስታስቡ ለነበራችሁ አባቶች፣ ምእመናን እና የማኅበረ ቅዱሳን አባላት እያመሰገንን፣ በዓሉ የሰላምና የበረከት እንዲሆንላችሁ እንመኛለን።

ማኅበረ ቅዱሳን!
እንኳን አደረሰን!

“በእምነት ትንሣኤ፣ በአምልኮተ እግዚአብሔር ትንሣኤ፣ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ትንሣኤ፣ በፍቅር ትንሣኤ፣ በሰላም ትንሣኤ፣ በይቅርታ ትንሣኤ፣ በመከባበር ትንሣኤ፣ በአንድነት ትንሣኤ፣ በመተሳሰብ ትንሣኤ ወዘተ በመሳሰሉ ሃይማኖታዊና ግብረ ገባዊነት ጸንተን መኖር ከቻልን የፊተኛው ትንሣኤ ማለት እሱ ነው፡፡ “ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

#ቃለ_በረከት_ዘብፁዕ_ወቅዱስ_አቡነ_ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘዕሥራ ምእት ዐሠርቱ ወስድስቱ ዓመተ ምሕረት፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤

የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ሁሉ፡-
የትንሣኤ ሙታን በኲር በመሆን ቀድሞ የተነሣው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ ስድስት ዓመተ ምሕረት በዓለ ትንሣኤ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!
“ወይእዜኒ ክርስቶስ ቀደመ ተንሥኦ እምኲሎሙ ሰብእ ሙታን@ አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት ሁሉ በኲር ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል” (1 ቆሮ 05.!)
በዛሬው ዕለት በከፍተኛ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት የሚከበረው የጌታችን ትንሣኤ ለሰው ልጅ ያለው መንፈሳዊ ትርጉም እጅግ የላቀ ነው፤ እግዚአብሔር ፍጥረታትን በሙሉ በተለይም የሰው ልጅን ሲፈጥር በፍጹም ፍቅር ነው፡፡
ለዚህም የሰው በአርአያ እግዚአብሔር መፈጠር በቂ ማስረጃ ነው፤ ሰው በበደሉ ምክንያት ለሞት ቢዳረግም የእግዚአብሔር ፍጹም ፍቅር ጨርሶ አልተለየውም፤ እግዚአብሔር አንድ ቀን ሞትን ከሰው ጫንቃ አሽቀንጥሮ እንደሚጥል በየጊዜው ይገልጽ ነበረ፤ ያም በራሱ ልዩ ጥበብ እንደሚከናወን አረጋግጦ ለሰው ልጅ ተስፋውን አሳውቆ ነበር፤ ያም ልዩ ጥበብ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
የእግዚአብሔር ዕውቀትና ጥበብ ድንበር የለውምና ከፍጥረተ ዓለም በፊት ሳይቀር የሰው ድኅነት በኢየሱስ ክርስቶስ ደም እንደሚፈጸም በእግዚአብሔር ዘንድ የተቈረጠ ነገር ነበረ፤ ጊዜው ሲደርስም በህላዌና በክዋኔ ከእርሱ ጋር አንድ የሆነ እግዚአብሐር ወልድ የሰውን ሰውነት ተዋሕዶ ሰውን የማዳን ስራውን አንድ ብሎ ጀመረ፡፡
ሰዎች በኃጢአትና በዲያብሎስ በደዌና በሞት ላይ ሥልጣን ያለው አዳኝ እሱ እንደሆነ ያውቁ ዘንድ የማዳን ስራውን በመዋዕለ ሥጋዌው በስፋት አከናወነ፡፡
ልዩ ልዩ ደዌና በሽታ የሚያሠቃያቸውን ፈወሰ፤ ኃጢአተኞችን በይቅርታ ተቀበለ፤ ኃጢአታቸውንም ደመሰሰ፤ አጋንንትንም በትእዛዝ አስወጣ፤ ወደ ጥልቁም አሰመጣቸው፤ ዲያብሎስንም ድል ነሥቶ አባረረ፤ ሙታንንም አነሣ፤ በባሕር ላይ በእግሩ ተራመደ፤ ነፋሳትን ገሠጸ፤ በአምስት እንጀራ ከአምስት ሺሕ ሕዝብ በላይ መገበ፤ ውሀውንም ወደ ጠጅ ለወጠ፡፡
ሰውን ሁሉ በፍቅርና በይቅርታ ይቀበልና ያገለግል ነበር እንጂ በአንዱ ስንኳ የመጨከንና የማግለል መንፈስ አላሳየም፤ ይህ ሁሉ ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፍቅር ማሳያ ነበረ፡፡
በፍጥረት ሁሉ ላይ መለኮታዊ ሥልጣን እንዳለውም ማረጋገጫ ነበረ፤ መልእክቱም ዓለም መዳኛዋና አዳኝዋ እሱ መሆኑን አውቃ በአእምሮ እንድትከተለውና የድኅነቱ ተቋዳሽ እንድትሆን ማስቻል ነው፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!

በእግዚአብሔር አሠራር ኃጢአት ያለ ቤዛነት አይሰረይም፤ በመሆኑም ሰው በእግዚአብሔር ፊት ፍጹም ኃጢአተኛ ሆኖ ስለተገኘ ቤዛ ሆኖ የሚያድነው ያስፈልገው ነበር፤ ቤዛ መሆን የሚችለው አካል ደግሞ ራሱ ፍጹም ንጹህ መሆን ነበረበት፡፡

ከዚህም አንጻር በእግዚአብሔር ፊት ለሱ የሚመጥን ንጹህ ኣካል ከፍጡራን ወገን አልተገኘምና እሱ ራሱ ሰው ሆኖ የሰው ቤዛ ለመሆን በሥጋ ተገለጠ፤ በዚህም መሠረት የሰው ቤዛ ሆኖ በመስቀል ላይ በመሰቀል ንጹህ ደሙን አፈሰሰ፤ በዚህ ደም ምክንያት የሰው ኃጢአት በሥርየት ተዘጋ፤ ለዚህም ነው ቅዱስ መጽሐፍ “ያለ ደም ሥርየት ወይም ይቅርታ የለም” ብሎ የሚነግረን፡፡
ከዚህ ደም መፍሰስ በኋላ ወደ ሲኦል ወርዶ በዚያ የነበሩ የኃጢአት ግዞተኞችን በሙሉ ፈትቶ ወደ ቀደመ ስፍራቸው ወደ ገነት መለሰ፤ ከስቅለተ ክርስቶስ ጀምሮ እስከ መጨረሻ ያለው የሰው ኃጢአት በሙሉ በክርስቶስ ደም ይደመሰሳል፡፡

ሆኖም ይህ ሥርየት የሚገኘው በእምነት መሆኑን ቅዱስ መጽሐፍ አበክሮ ይነግረናል፣ በክርስቶስ አምኖ በደሙ የነጻ ሁሉ ክርስቶስ በተነሣው ዓይነት ትንሣኤ ይነሣል፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
የጌታችንን ትንሣኤ ስናከብር የኛንም ትንሣኤ በማሰብ ሊሆን ይገባል፤ ትልቁ ነገርም የኛን ትንሣኤ ማሰቡ ላይ ነው፤ ምክንያቱም የክርስቶስ ትንሣኤ ለኛ ተብሎ የተደረገ በመሆኑ ነው፡፡

የሱ ትንሣኤ ለኛ ትንሣኤ በኲር ነው፤ ማሳያና ማረጋገጫም ነው፤ እግዚአብሔር በየዕለቱ የሚፈልገው የኛን ትንሣኤ ማየት ነው፤ የኛ ትንሣኤ በአንድ ቀን በቅፅበት የሚሆን አይደለም፤ ትንሣኤያችን አምነን ስንጠመቅ ተጀምሮ ከመቃብር ስንነሣ የሚጠናቀቅ ነው፡፡
እግዚአብሔር ዛሬም እያንዳንዱ ሰው በትንሣኤ ሕይወት እንዲመላለስ ይጠራል፤ ምክንያቱም የኋለኛው ትንሣኤ የሚገኘው በፊተኛው ትንሣኤ እንደሆነ እግዚአብሔር በመጽሓፉ ነግሮናልና ነው፤ በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕ ነው፤ በሱ ላይ ሞት ሥልጣን የለውምና ነው፤ ለሰው ልጆች ተጠብቆልን ያለው ተስፋ ይህ ነው፡፡

ተስፋውን እውን ማድረግ የሚቻለውም በኛ ሃይማኖታዊና ተግባራዊ ተሳትፎ እንደዚሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ ደም ነው፤ የነገውን ትንሣኤ ተሳታፊ ለመሆን ዛሬ መነሣት ግድ ይላል፤ ይህም የሚቻል እንጂ የማይቻል አይደለም፡፡

በእምነት ትንሣኤ፣ በአምልኮተ እግዚአብሔር ትንሣኤ፣ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ትንሣኤ፣ በፍቅር ትንሣኤ፣ በሰላም ትንሣኤ፣ በይቅርታ ትንሣኤ፣ በመከባበር ትንሣኤ፣ በአንድነት ትንሣኤ፣ በመተሳሰብ ትንሣኤ ወዘተ በመሳሰሉ ሃይማኖታዊና ግብረ ገባዊነት ጸንተን መኖር ከቻልን የፊተኛው ትንሣኤ ማለት እሱ ነው፡፡ ዛሬ እግዚአብሔር እያንዳንዳችን ይህንን ትንሣኤ እውን አድርገን ስንኖርና ስንመላለስ ማየት ይፈልጋል፡፡
በአንጻሩም ክሕደትን፣ ከሕገ ተፈጥሮ ያፈነገጠ ጸያፍ ተግባርን፣ ጥላቻን፣ ጦርነትን፣ መለያየትን፣ ራስን ብቻ መውደድን፣ መጨካከንን፣ ግብረ ኃጢአትን፣ ፈሪሐ እግዚአብሔር ገንዘብ አለማድረግን፣ ፈጣሪን አለማመንን የተጸየፈ ምእመንን ማየት ይፈልጋል፡፡
ምክንያቱም ሁሉም ኃጣውእ አፅራረ ትንሣኤ ናቸውና ነው፤ ኃጣውእ በምድርም በሰማይም የሰው ጠላቶች ናቸው፤ በምድር ለሥጋዊና መንፈሳዊ በሽታ ይዳርጉናል፡፡

በተለይም በእግዚአብሔር ፊት እጅግ አስጸያፊ የሆነው የነውረ ኃጢአት ርኲሰትና በጋብቻ ያልታሰረ ሩካቤ ሥጋ ትውልድን እንደ ቅጠል እያረገፈው እንደሆነ፣ ምንም ዓይነት ፈውስ ላልተገኘለት የኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ ዋነኛ መተላፊያም ይህ ነውረ ኃጢአት እንደሆነ ተደጋግሞ ተነግሮአል፡፡
ይሁንና አሁንም ጥንቃቄ በጎደለው ድርጊት ስሕተቱ በመቀጠሉ በጦርነት ከሚያልቀው ሕዝብ ባልተናነሰ በዚህ ገዳይ በሽታ ብዙ ወገን እያለቀ ነውና እባካችሁ ሕዝበ እግዚአብሔር አንድ ለአንድ በመተሣሰርና በተቀደሰ የጋብቻ ሕይወት በመወሰን ትንሣኤያችንን እናብስር፡፡

በመጨረሻም
በዓለ ትንሣኤ የእግዚብሔር ፍቅር መገለጫና የተስፋችን ማሳያ መሆኑን በመገንዘብ ለእግዚአብሔር ክብርና ለሰው ልጆች ደኅንነት በአንድነት በመቆም ለተራቡት፣ ለተጠሙት፣ ለታረዙት፣ ለታመሙትና ለታሰሩትም ሁሉ ካለን ከፍለን በመስጠት ከኛ ጋራ በመንፈስና በሞራል በዓለ ትንሣኤውን እንዲያሳልፉ እናደርግ ዘንድ መንፈሳዊ ጥሪያችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን።
በድጋሚ በዓሉን የሰላም የዕርቅ የይቅርታ የትንሣኤ ኅሊና ወልቡና ያድርግልን፤
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
አሜን።

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ሚያዝያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም
አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
2024/09/28 12:14:07
Back to Top
HTML Embed Code: