Telegram Web Link
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_15_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ቆሮንቶስ 12
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁸ አሁን ግን እግዚአብሔር እንደ ወደደ ብልቶችን እያንዳንዳቸው በአካል አድርጎአል።
¹⁹ ሁሉም አንድ ብልት ቢሆንስ አካል ወዴት በሆነ?
²⁰ ዳሩ ግን አሁን ብልቶች ብዙዎች ናቸው አካል ግን አንድ ነው።
²¹ ዓይን እጅን፦ አታስፈልገኝም ልትለው አትችልም፥ ወይም ራስ ደግሞ እግሮችን፦ አታስፈልጉኝም ሊላቸው አይችልም።
²² ነገር ግን ደካሞች የሚመስሉ የአካል ብልቶች ይልቁን የሚያስፈልጉ ናቸው፤
²³ ከአካልም ብልቶች ያልከበሩ ሆነው የሚመስሉን በሚበዛ ክብር እናለብሳቸዋለን፥ በምናፍርባቸውም ብልቶቻችን ክብር ይጨመርላቸዋል፤
²⁴-²⁵ ክብር ያላቸው ብልቶቻችን ግን ይህ አያስፈልጋቸውም። ነገር ግን ብልቶች እርስ በርሳቸው በትክክል ይተሳሰቡ ዘንድ እንጂ በአካል መለያየት እንዳይሆን፥ ለጎደለው ብልት የሚበልጥ ክብር እየሰጠ እግዚአብሔር አካልን አገጣጠመው።
²⁶ አንድም ብልት ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ አንድ ብልትም ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል።
²⁷ እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ።
²⁸ እግዚአብሔርም በቤተ ክርስቲያን አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን፥ ሁለተኛም ነቢያትን፥ ሦስተኛም አስተማሪዎችን፥ ቀጥሎም ተአምራት ማድረግን፥ ቀጥሎም የመፈወስን ስጦታ፥ እርዳታንም፥ አገዛዝንም፥ የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችንም አድርጎአል።
²⁹ ሁሉ ሐዋርያት ናቸውን? ሁሉስ ነቢያት ናቸውን? ሁሉስ አስተማሪዎች ናቸውን? ሁሉስ ተአምራትን ይሠራሉን?
³⁰ ሁሉስ የመፈወስ ስጦታ አላቸውን? ሁሉስ በልሳኖች ይናገራሉን? ሁሉስ ይተረጉማሉን?
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ይሁዳ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁷ እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ቀድሞ የተነገረውን ቃል አስቡ፤
¹⁸ እነርሱ፦ በመጨረሻው ዘመን በኃጢአተኝነት እንደ ገዛ ምኞታቸው እየሄዱ ዘባቾች ይሆናሉ ብለዋችኋልና።
¹⁹ እነዚህ የሚያለያዩ ሥጋውያንም የሆኑ መንፈስም የሌላቸው ሰዎች ናቸው።
²⁰ እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፥
²¹ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ።
²² አንዳንዶች ተከራካሪዎችንም ውቀሱ፥ አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ፥
²³ አንዳንዶችንም በሥጋ የረከሰውን ልብስ እንኳ እየጠላችሁ በፍርሃት ማሩ።
²⁴ ሳትሰናከሉም እንዲጠብቃችሁ፥ በክብሩም ፊት በደስታ ነውር የሌላችሁ አድርጎ እንዲያቆማችሁ ለሚችለው
²⁵ ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ይሁን፤ አሜን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² በዚያን ጊዜ ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ እርሱም ከኢየሩሳሌም የሰንበት መንገድ ያህል የራቀ ነው።
¹³ በገቡም ጊዜ ወደሚኖሩበት ሰገነት ወጡ፥ ጴጥሮስና ዮሐንስም፥ ያዕቆብም፥ እንድርያስም፥ ፊልጶስም፥ ቶማስም፥ በርተሎሜዎስም፥ ማቴዎስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም፥ ቀናተኛ የሚባለው ስምዖንም፥ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳም።
¹⁴ እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_15_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ውስተ ኵሉ ምድር ወፅአ ነገሮሙ። ወእስከ አፅናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ። ወውስተ ፀሓይ ሤመ ጽላሎቶ"። መዝ 18፥4-5።
"ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ፥ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ። በእነርሱም ውስጥ የፀሐይን ድንኳን አደረገ፥ እርሱም እንደ ሙሽራ ከእልፍኙ ይወጣል፤ እንደ አርበኛ በመንገዱ ለመሮጥ ደስ ይለዋል"። መዝ 18፥4-5።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_15_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 10
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ፥ እንዲያወጡአቸው በርኩሳን መናፍስት ላይ ደዌንና ሕማምንም ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣን ሰጣቸው።
² የአሥራ ሁለቱም ሐዋርያት ስም ይህ ነው፤ መጀመሪያው ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን ወንድሙ እንድርያስም፥ የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብም ወንድሙ ዮሐንስም፥
³ ፊልጶስም በርተሎሜዎስም፥ ቶማስም ቀራጩ ማቴዎስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም ታዴዎስም የተባለው ልብድዮስ፥
⁴ ቀነናዊውም ስምዖን ደግሞም አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ።
⁵ እነዚህን አሥራ ሁለቱን ኢየሱስ ላካቸው፥ አዘዛቸውም፥ እንዲህም አለ፦ በአሕዛብ መንገድ አትሂዱ፥ ወደ ሳምራውያንም ከተማ አትግቡ፤
⁶ ይልቅስ የእስራኤል ቤት ወደሚሆኑ ወደ ጠፉት በጎች ሂዱ እንጂ።
⁷ ሄዳችሁም፦ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች ብላችሁ ስበኩ።
⁸ ድውዮችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አውጡ፤ በከንቱ ተቀበላችሁ፥ በከንቱ ስጡ።
⁹ ወርቅ ወይም ብር ወይም ናስ በመቀነታችሁ፥
¹⁰ ወይም ለመንገድ ከረጢት ወይም ሁለት እጀ ጠባብ ወይም ጫማ ወይም በትር አታግኙ፤ ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋልና።
¹¹ በምትገቡባትም በማናቸይቱም ከተማ ወይም መንደር፥ በዚያ የሚገባው ማን እንደ ሆነ በጥንቃቄ መርምሩ፤ እስክትወጡም ድረስ በዚያ ተቀመጡ።
¹² ወደ ቤትም ስትገቡ ሰላምታ ስጡ፤
¹³ ቤቱም የሚገባው ቢሆን ሰላማችሁ ይድረስለት፤ ባይገባው ግን ሰላማችሁ ይመለስላችሁ።
¹⁴ ከማይቀበላችሁም ቃላችሁንም ከማይሰሙ ሁሉ፥ ከዚያ ቤት ወይም ከዚያች ከተማ ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፉ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ሚቀደሰው_ቅዳሴ የቅዱሳን የ #ሐዋርያት_ቅዳሴ ነው። መልካም የጾም ጊዜና በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_16

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ዐሥራ ስድስት በዚህች ቀን አምላክን የወለደች #የእመቤታችን_ድንግል_ማርያም ሥጋዋ ወደ ሰማይ ያረገበት መታሰቢያዋ ሆነ፣ የሰማዕታት አለቃ #የቅዱስ_ጊዮርጊስ ሥጋው የፈለሰበት ነው፣ #ቅዱስ_ጊጋር በሰማዕትነት ሞተ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ዕርገተ_ማርያም

ነሐሴ ዐሥራ ስድስት በዚህች ቀን አምላክን የወለደች የእመቤታችን #ድንግል_ማርያም ሥጋዋ ወደ ሰማይ ያረገበት መታሰቢያዋ ሆነ ። ከዕረፍቷም በኋላ ከእርሳቸው ስለመለየቷ ሐዋርያት ፈጽሞ እያዘኑ ነበር ።

ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ ተገለጠላቸው እርሷን በሥጋ ያዩ ዘንድ እንዳላቸውም ተስፋ ሰጣቸው ። ወንጌላዊ ዮሐንስም እስያ በሚባል አገር እያስተማረ ሳለ በነሐሴ ወር ዐሥራ ስድስተኛ ቀን ተድላ ደስታ ወደአለባት ገነት በ መንፈስ_ቅዱስ ተነጠቀ ።

የክብር ባለቤት #ጌታ_ኢየሱስ_ክርስቶስን የእመቤታችን #ማርያም ሥጋዋ ካለበት ከዕፀ ሕይወት ሥር ተቀምጦ አየው። የንጽሕት እናቱንም ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሩዋት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው ። እነርሱም የንጽሕት እናቱን ሥጋ ታወጪ ዘንድ #እግዚአብሔር አዞሻል አሏት ። ያን ጊዜም ከዕፀ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን #ማርያም ሥጋዋ ወጣ ።

የክብር ባለቤት #ጌታችንም እንዲህ እያለ አረጋጋት የተወደድሽ የወለድሽኝ እናቴ ሆይ ዘላለማዊ ወደ ሆነ መንግሥተ ሰማያት አሳርግሽ ዘንድ ነዪ ። ያን ጊዜም በገነት ያሉ ዕፀዋት ሁሉም አዘነበሉ መላእክት የመላእክት አለቆች ጻድቃን ሰማዕታትም እየሰገዱላትና ፈጽሞ እያመሰገኗት አሳረጓት ።

አባቷ ዳዊትም ንግሥት እመቤታችን ወርቀ ዘቦ ለብሳ ደርባ ደራርባ በቀኝህ ትቀመጣለች እያለ በበገና አመሰገናት ። በኪሩቤል ሠረገላ ተቀምጣ ከዐረገች በኋላ በልጁዋና በፈጣሪዋ ቀኝ በታላቅ ክብር ተቀመጠች ።

ወንጌላዊ ዮሐንስም ከእርሷ በረከትን ተቀብሎ ሰግዶላት ተመልሶ ከሰማይ ወረደ ሐዋርያትን ተሰብስበው ስለ እመቤታችን ቅድስት #ድንግል_ማርያም ሥጋ ፈጽሞ ሲያዝኑና ሲተክዙ አገኛቸው ። እርሱም እንደ አየ እንደ ሰማ ሥጋዋንም በታላቅ ክብር በምስጋና እንደ አሳረጓት ነገራቸው ።

ሐዋርያትም በሰሙ ጊዜ ዮሐንስ እንዳየና እንደሰማ ባለማየታቸውና ባለመስማታቸው እጅግ አዘኑ ። ከዚህም በኋላ እያዘኑ ሳሉ እነሆ የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ተገለጠላቸውና የፍቅር አንድነት ልጆች ሰላም ይሁንላችሁ ስለ እናቴ #ማርያም ሥጋ ለምን ታዝናላችሁ ። እነሆ እኔ እርሷን በሥጋ ላሳያችሁ ልባችሁም ደስ ሊለው ይገባዋል አላቸው ይህንንም ብሎ ከእርሳቸው ዘንድ ወደ ሰማያት ዐረገ ።

ሐዋርያትም ዓመት ሙሉ ቆዩ የነሐሴም ወር በባተ ቀን ለሐዋርያት ዮሐንስ እንዲህ አላቸው አምላክን የወለደች የእመቤታችንን ሥጋዋን ለማየት የተዘጋጀን አድርጎ ያሰየን ዘንድ ኑ ይህን ሁለት ሱባዔ በመጾም የክብር ባለቤት #ጌታችንን_ኢየሱስ_ክርስቶስን እንለምነው በልጅዋ በወዳጅዋ ቀኝ ተቀምጣ አይተን በእርሷ ደስ እንዲለን ።

በዚያን ጊዜም ዮሐንስ እንዳላቸው በጾም በጸሎት ሱባዔ ያዙ የነሐሴ ወር እንደ ዛሬ ዐሥራ ስድስተኛ ቀን በሆነ ጊዜ የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሁሉንም ሐዋርያት ወደ ሰማይ አወጣቸው ። በታላቅ ክብር በተወደደ ልጅዋ ቀኝ ተቀምጣ ከሥጋዋ ተዋሕዳ ተነሥታ እመቤታችን #ማርያምን አዩዋት። እጆቿንም ዘርግታ የከበሩ ሐዋርያትን እያንዳንዳቸውን ባረከቻቸው በልባቸውም እጅግ ደስ አላቸው።

የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም በከበረ ሥጋውና ደሙ ላይ ሠራዒ ካህን ሆነ ። እስጢፋኖስም አዘጋጀ ዮሐንስም በመፍራት ቁሙ አለ ። ሁሉም ሐዋርያት በመሠዊያው ዙሪያ ቆሙ በዚያን ጊዜ ከቶ እንደርሱ ሆኖ የማያውቅ ታላቅ ደስታ ሆነ።

#ጌታችንም የቅዳሴውን ሥርዓት በፈጸመ ጊዜ ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸው ። ከዚያም በኪሩቤልና በሱራፌል ሠረገላ ተቀምጣ በምታርግ ጊዜ የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ እናቱ እመቤታችን #ማርያምን እንዲህ ብሎ ተናገራት።

በዚች ቀን የሆነ የዕርገትሽን መታሰቢያ በዓለም ውስጥ እንዲሰብኩ ልጆችሽ ሐዋርያትን እዘዣቸው ። መታሰቢያሽን የሚያደርገውን ሁሉ ተጠብቆም በዚች ቀን ቅዱስ ቁርባንን የሚቀበለውን ኃጢአቱን እደመስስለታለሁ ። የእሳትን ሥቃይ ከቶ አያያትም መታሰቢያሽን ለሚያደርግ ሁሉ በዚች ቀን ለድኆች በስምሽ ለሚመጸውት ቸርነቴ ትገናኘዋለች ይህም ሥጋሽ ወደ ሰማይ ያረገበት ነው።

እመቤታችን ቅድስት #ድንግል_ማርያምም ክብር ይግባውና #ጌታችንን እንዲህ አለችው ልጄ ሆይ እነሆ በዐይኖቻቸው አዩ በጆሮቻቸውም ሰሙ በእጆቻቸውም ያዙ ሌሎችም ታላላቅ ደንቆች ሥራዎችን አዩ ። እመቤታችንም ይህን ስትናገር #ጌታችን ሰላምታ ሰጥቷቸው በታላቅ ደስታ ወደ ደብረ ዘይት ተመለሱ ።

የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ በፍጹም ደስታ መታሰቢያዋን እናደርግ ዘንድ ይገባናል እርሷ ስለእኛ ወደ ተወደደ ልጅዋ ሁልጊዜ ትማልዳለችና ።

#ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በእመቤታችን በቅድስት #ድንግል_ማርያም አማላጅነት ይማረን ። በረከቷም ከርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከአባ ማትያስ ከሁሉም ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስቆጶሳት ጋራ ሐዋርያት ከሰበሰቧት ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ከሁላችን ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#የቅዱስ_ጊዮርጊስ_ፍልሰተ_አጽሙ

በዚህችም ዕለት የሰማዕታት አለቃ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሥጋው ከፋርስ አገር ወደ አገሩ ልዳ በክብር የፈለሰበት ነው። የሥጋውም ፍልሰት ከእመቤታችን #ድንግል_ማርያም የሥጋ ፍልሰት ጋር አንድ ሆኗል ስለዚህም እርሷን መውደዱን የሚያወቁ ሥዕሉን ከሥዕሏ አጠገብ ይሥላሉ በስሙ ለሚማፀኑ የድኅነት ወደብ ይሆን ዘንድ።

#ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በኃያሉ ተጋዳይ በቅዱስ ጊዮርጊስም ጸሎት በእኛ ላይ ምህረት ይቅርታ ቸርነት ይሁን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ጊጋር_ሰማዕት

በዚህችም ቀን የሶሪያ መስፍን ጊጋር በሰማዕትነት ሞተ። ሰማዕት የሆነበትም ምክንያት #ጌታችን ከእመቤታችን ከእናቱ ከ #ድንግል_ማርያም ጋራ በተሰደደ ጊዜ በሊባኖስ ተራራ ሳለ ኄሮድስ ሰምቶ ከበው ይዘው ይገድሏቸው ዘንድ ጭፍሮቹን ላከ ጊጋርም ጭፍሮች እንዳገኟቸው አሸሻቸው።

ስለዚህም ኄሮድስ ተቆጣ ጊጋርንም ይዞ ጽኑ ሥቃይን አሠቃየው ሕዋሳቱንም ሁሉ ቆራረጠ። ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ተገልጦለት ስሙን ለሚጠራ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ገድሉንም ለሚጽፍ ቃል ኪዳን ሰጠው ከዚህም በኋላ ራሱን በሰይፍ ቆረጡት በሦስት አክሊሎችም ተጋረደ ሦስት አክሊላትን ተቀዳጀ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአማላጅነቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_16)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_16_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሮሜ 8
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³¹ እንግዲህ ስለዚህ ነገር ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል?
³² ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው ያው ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም?
³³ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፥ የሚኰንንስ ማን ነው?
³⁴ የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው።
³⁵ ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን?
³⁶ ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው።
³⁷ በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።
³⁸ ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥
³⁹ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ዮሐንስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹-² በእኛ ስለሚኖርና ከእኛ ጋር ለዘላለም ስለሚሆን እውነት፥ እኔ ሽማግሌው በእውነት ለምወዳቸውና እኔ ብቻ ሳልሆን እውነትን የሚያውቁ ሁሉ ደግሞ ለሚወዱአቸው ለተመረጠች እመቤትና ለልጆችዋ፤
³ ከእግዚአብሔር አብና ከአብ ልጅ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም በእውነትና በፍቅር ከእኛ ጋር ይሆናሉ።
⁴ ትእዛዝን ከአብ እንደ ተቀበልን ከልጆችሽ በእውነት የሚሄዱ አንዳንዶችን ስለ አገኘኋቸው እጅግ ደስ ብሎኛል።
⁵ አሁንም፥ እመቤት ሆይ፥ እርስ በርሳችን እንድንዋደድ እለምንሻለሁ፤ ይህች ከመጀመሪያ በእኛ ዘንድ የነበረች ትእዛዝ ናት እንጂ አዲስ ትእዛዝን እንደምጽፍልሽ አይደለም።
⁶ እንደ ትእዛዛቱም እንሄድ ዘንድ ይህ ፍቅር ነው፤ ከመጀመሪያ እንደ ሰማችሁ፥ በእርስዋ ትሄዱ ዘንድ ትእዛዙ ይህች ናት።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² በዚያን ጊዜ ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ እርሱም ከኢየሩሳሌም የሰንበት መንገድ ያህል የራቀ ነው።
¹³ በገቡም ጊዜ ወደሚኖሩበት ሰገነት ወጡ፥ ጴጥሮስና ዮሐንስም፥ ያዕቆብም፥ እንድርያስም፥ ፊልጶስም፥ ቶማስም፥ በርተሎሜዎስም፥ ማቴዎስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም፥ ቀናተኛ የሚባለው ስምዖንም፥ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳም።
¹⁴ እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_16_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ቀደሰ ማኅደሮ ልዑል። እግዚአብሔር ውስተ ማዕከላ ኢትትሀወክ ወይረድአ እግዚአብሔር ፍጽመ"። መዝ.45÷4-5
"የወንዝ ፈሳሾች የእግዚአብሔርን ከተማ ደስ ያሰኛሉ፤ ልዑል ማደሪያውን ቀደሰ።
እግዚአብሔር በመካከልዋ ነው አትናወጥም፥ እግዚአብሔርም ፈጥኖ ይረዳታል"። መዝ.45÷4-5
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_16_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 26
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁶ ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና፦ እንካችሁ፥ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ።
²⁷ ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ፦ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤
²⁸ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።
²⁹ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር ከዚህ ከወይን ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ከዛሬ ጀምሬ አልጠጣውም።
³⁰ መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ሚቀደሰው_ቅዳሴ ቅዳሴ #እግዚእነ ነው። መልካም የእመቤታችን ቅድስት #ድንግል_ማርያም የትንሣኤና የዕርገት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_17

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ዐሥራ ሰባት በዚች ቀን አሞራዊ #ቅዱስ_እንጣዎስ በሰማዕትነት ሞተ፣ ከደቡብ ግብጽ አቡስ ከሚባል አውራጃ መኑፍ ከሚባል ታናሽ መንደር #ቅዱስ_ያዕቆብ በሰማዕትነት ሞተ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_እንጣዎስ_አሞራዊ

ነሐሴ ዐሥራ ሰባት በዚች ቀን አሞራዊ ቅዱስ እንጣዎስ በሰማዕትነት ሞተ። ይህም ቅዱስ አስቀድሞ #ክርስቶስን የካደ ነበር ገንዘብ ለማከማቸትም የሚተጋ ነበር።

በአንዲትም ዕለት ወደ ደማስቆ ከተማ ሔደ የበዓላቸው ቀን ነበርና ሕዝቡ ተሰብስበው ሳሉ ወደ ምሥራቃዊው ቅዱስ ቴዎድሮስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገባ ገብቶም ዕቃዎችን ማቃጠል ጀመረ #መስቀልንም ሰበረ።

ከዚህም በኋላ በሰማይ ውስጥ የእሳት ፍላፃዎችን ይዘው ከሀዲዎችን ሲነድፏቸው አየ እርሱንም የቀኝ ጐኑን አንዲት ፍላፃ ነደፈችው። ያን ጊዜም ተጨንቆ ላቡ ተንጠፈጠፈ ከጥልቅ ልቡም እንዲህ ብሎ ጮኸ የቅዱስ ቴዎድሮስ አምላክ የሕያው #እግዚአብሔር ልጅ #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ አመንኩብህ ከእንግዲህ ዳግመኛ ሌላ አምላክ እንዳያመልክ በልቡናው ቃል ገባ።

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖችም በእርሱ ላይ የሆነውን አላወቁም ነገር ግን ጩኸቱንና የሚናገረውን ሰምተው አደነቁ እምነታቸውም ጠነከረ እጅግም ጸና። እንጣዎስም #ኤልያስ ወደ ሚባል ጳጳስ ሒዶ በርሱ ላይ የሆነውን ሁሉ ነገረው የክርስትና ጥምቀትንም ያጠምቀው ዘንድ ለመነው።

ጳጳሱም በውኃው ላይ በጸለየ ጊዜ የብርሃን ምሰሶ እንደ ቀስተ ደመና ሁኖ ሕዝቡ ሁሉ እያዩት ወረደ ቅዱስ እንጣዎስም ተጠመቀ። ከእርሱም ጋራ ከአይሁድና ከአረሚ ዐሥር ሽህ ሰባት መቶ ዘጠና ስምንት ያህል ሰዎች ተጠመቁ። ክብር ይግባውና የ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስን ሥጋውንና ደሙን ተቀበሉ።

ቅዱስ እንጣዎስም እንዲህ አለ እነሆ ይህን እያደነቅሁ ሳለ በእንቅልፌ ሕልምን አየሁ። ብርሃንን የለበሰች ሴት እጄን ያዘችኝ ወስዳም ወደ ኢየሩሳሌም አደረሰችኝ ወደ መሠዊያውም አቀረበችኝ እኔም ቅዱስ ቊርባንን ለመቀበል ተዘጋጀሁ በመሠዊያውም ውስጥ ነጭ በግን አየሁ ካህኑም በዕርፈ #መስቀል በሠዋው ጊዜ ደሙ ጽዋው ውስጥ ተጨመረ ከእርሱም የ #ክርስቶስን ሥጋና ደም በተቀበልሁ ጊዜ ሥጋው ንጹሕ ኅብስት ደሙም ጥሩ ወይን ሆነ።

ከዚህም በኋላ በደማስቆ ጐዳና ሲጓዝ አስቀድሞ የሚያውቁት ያዙት ወደ ንጉሡም ወሰዱት ንጉሡም #ክርስቶስን በማመን እንደጸና አይቶ ጥርሶቹ እስቲበተኑ አፉን በበሎታ እንዲመቱት አዘዘ አፉም ደምን ተመላ። ከዚህም በኋላ እህል ውኃን ሳይሰጡ በተበሳ ግንድ ውስጥ ሰባት ቀን ያህል አሠሩት ከዚያም አውጥተው ዲን፣ ሙጫ፣ ዝፍት ከስብ ጋራ ባፈሉበት እሳት ውስጥ ጨመሩት ከእርሱም የመልካም መዓዛ ሽታ ወጣ።

ወታደሮችም ከእሳት ውስጥ ቁሞ ሲጸልይ አገኙት። እሳቱም አልነካውም ወደ ንጉሥም ወሰዱት ንጉሡም የሥራይን ኃይል መቼ ተማርክ አለው ቅዱስ እንጣዎስም ንጉሡን እንዲህ አለው ሥራይንስ አላውቅም ነገር ግን ክብር ይግባውና በ #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ኃይል አሳፍርሃለሁ።

ንጉሡም ቁጣን ተመልቶ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ። ከዚህም በኋላ ቅዱስ እንጣዎስ ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ ቆመ እጆቹንም ዘርግቶ ነፍሱን ወደ #እግዚአብሔር አማፀነ ሲጸልይም ወደርሱ እንዲህ የሚል ቃል መጣ ከእስጢፋኖስና ከጊዮርጊስ ጋራ ታርፍ ዘንድ አገልጋዬ በሰላም ና። ጸሎቱንም በፈጸመ ጊዜ ራሱን ቆረጡት ምስክርነቱንም ፈጸመ ከሥጋውም ቁጥር የሌላቸው ድንቆችና ተአምራት ተገለጡ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ሰማዕት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ያዕቆብ_ግብጻዊ

በዚህችም ቀን ከደቡብ ግብጽ አቡስ ከሚባል አውራጃ መኑፍ ከሚባል ታናሽ መንደር ቅዱስ ያዕቆብ በሰማዕትነት ሞተ። የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ #እግዚአብሔርን የሚፈሩ ክርስቲያኖች ነበሩ ከእርሱ መወለድም በፊት ሦስት ሴቶች ልጆችን ወልደው ነበር።

ጥቂትም በአደጉ ጊዜ እንዲያስተምሩአቸውና በፈሪሀ #እግዚአብሔር እንዲአሳድጓቸው በገዳም ለሚኖሩ ደናግል ሰጧቸው። የብሉይና የሐዲስ መጻሕፍትንም ተማሩ። ወላጆቻቸውም ሊወስዷቸው በወደዱ ጊዜ እነርሱ ከደናግል ገዳም መውጣትን አልወደዱም። ነገር ግን ለ #ድንግል_ማርያምና ለልጅዋ ለ #ክርስቶስ ሙሽሮች ይሆኑ ዘንድ መረጡ ወላጆቻቸውም ከእርሳቸው በመለየታቸው አዘኑ።

መሐሪ ይቅር ባይ #እግዚአብሔርም በዚህ ቅዱስ ያዕቆብ መወለድ አጽናናቸው። ሰባት ዓመትም በሆነው ጊዜ አባቱ ዐውሎ ወደ ሚባል አገር ጥበብን ይማር ዘንድ ላከው ትምህርትንም ተምሮ በትምህርት ሁሉ ፍጹም ሆነ።

አባቱም ለገንዘቡና ለጥሪቱ ለእንስሶቹም ሁሉ ተቈጣጣሪ አደረገው በዚያም አንድ በሥውር ብዙ ትሩፋትን የሚሠራ የበጎች ጠባቂ ነበረ በክረምትም በበጋም ብዙ ጊዜ ወደ ውኃ ጒድጓድ እየወረደ መላዋን ሌሊት ሲጸልይ ያድር ነበር።

ቅዱስ ያዕቆብም ሽማግሌው የበግ ጠባቂ በሚያደርገው አምሳል እያደረገ በዚህ ሥራ ብዙ ዘመን ኖረ። ከዚህም በኋላ ሰይጣን በክርስቲያን ወገኖች ላይ መከራን አስነሣ ብዙዎች ክርስቲያኖችም በሰማዕትነት ሞቱ።

በዚያንም ጊዜ ቅዱስ ያዕቆብ በሰማዕትነት ይሞት ዘንድ ከዚያ ሽማግሌ ጋራ ተስማማ ቅዱስ ያዕቆብም ከሽማግሌው ጋራ ሒዶ ይመለስ ዘንድ አባቱን ፈቃድ ጠየቀ እርሱም ሒድ አለው።

በሔዱም ጊዜ በላይኛው ግብጽ የንጉሥ ልጅ ቅዱስ ዮስጦስን መኰንኑ ሲአሠቃየው አገኙት ሽማግሌውም ልጄ ሆይ ይህ የንጉሥ ልጅ መንግሥቱን ትቶ እውነተኛውን ንጉሥ #ክርስቶስን እንደ ተከተለ ከሚስቱና ከልጆቹም እንደተለየ ተመልከት። እኛ ድኆች ስንሆን ለምን ችላ እንላለን ልጄ ሆይ እንግዲህ ተጽናና ከወላጆችህም በመለየትህ አትዘን አለው።

ከዚህም በኋላ ወደ መኰንኑ ቀርበው ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ታመኑ የረከሱ አማልክቶቹንም ረገሙ ያን ጊዜም መኰንኑ አስቀድሞ ሽማግሌውን ይዞ ጽኑ ሥቃይን አሠቃየው ራሱንም በሰይፍ ፈጥኖ አስቆረጠው ምስክርነቱንም ፈጸመ።

ቅዱስ ያዕቆብን ግን ታላቅ ሥቃይን አሠቃየው ከገመድ በተሠራ ጅራፍ ገረፈው ድንጋይም በእሳት አግለው በሆዱ ላይ አኖሩ። ዐይኖቹንም አቅንቶ ክብር ይግባውና ወደ #ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ጸለየ #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሆይ ከዚህ መከራ ርዳኝ አጽናኝም ያን ጊዜም ያለ ምንም ጉዳት አስነሣው።

ከዚህም በኋላ በማቅ ውስጥ አስጠቅልሎ በባሕር ውስጥ አስጣለው የ #እግዚአብሔርም መልአክ አውጥቶ ያለ ጉዳት በመኰንኑ ፊት አቆመው። መኰንኑንም አሳፈረው የረከሱ አማልክቶቹንም ረገመ።

ከዚህም በኋላ ፈርማ ወደሚባል አገር ላከው በዚያም የፈርማ መኰንን ጽኑ ሥቃይን አሠቃየው ምላሱን ቆረጠው፣ ዐይኖቹንና ቅንድቦቹንም አወጣ፣ በመንኰራኩርም ውሰጥ አኬዱት፣ በመጋዝም መገዙት፣ ሕዋሳቱ ሁሉም ተሠነጣጠቁ። ደሙም እንደ ውኃ ፈሰሰ የእግዚአብሔር መልአክ ሱርያል ወርዶ ቊስሎቹን አዳነለት።

መኰንኑም ከማሠቃየቱ የተነሣ በሠለቸ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡት ዘንድ አዘዘና ቆረጡት የሰማዕትነትንም አክሊል ተቀበለ። ከገምኑዲ ሀገር የሆኑ አብርሃምና ዮሐንስም ከእርሱ ጋራ ሰማዕታት ሆነው ሞቱ።

#ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሰማዕታት ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_17+)
2024/09/22 01:59:07
Back to Top
HTML Embed Code: