Telegram Web Link
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_13_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዕብራውያን 11
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²³ ሙሴ ከተወለደ በኋላ ወላጆቹ ያማረ ሕፃን መሆኑን አይተው በእምነት ሦስት ወር ሸሸጉት የንጉሥንም አዋጅ አልፈሩም።
²⁴ ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ፤
²⁵-²⁶ ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንዲሆን አስቦአልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኵር ብሎ ተመልክቶአልና።
²⁷ የንጉሡን ቍጣ ሳይፈራ የግብፅን አገር የተወ በእምነት ነበር፤ የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና።
²⁸ አጥፊው የበኵሮችን ልጆች እንዳይነካ ፋሲካንና ደምን መርጨትን በእምነት አደረገ።
²⁹ በደረቅ ምድር እንደሚያልፉ በኤርትራ ባሕር በእምነት ተሻገሩ፥ የግብፅ ሰዎች ግን ሲሞክሩ ተዋጡ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ጴጥሮስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁵ ከመውጣቴም በኋላ እነዚህን ነገሮች እንድታስቡ በየጊዜው ትችሉ ዘንድ እተጋለሁ።
¹⁶ የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችሁ።
¹⁷ ከገናናው ክብር፦ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሎአልና፤
¹⁸ እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን።
¹⁹ ከእርሱም ይልቅ እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን፤ ምድርም እስኪጠባ ድረስ የንጋትም ኮከብ በልባችሁ እስኪወጣ ድረስ፥ ሰው በጨለማ ስፍራ የሚበራን መብራት እንደሚጠነቀቅ ይህን ቃል እየጠነቀቃችሁ መልካም ታደርጋላችሁ።
²⁰ ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤
²¹ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 7
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁴⁴ እንዳየው ምስል አድርጎ ይሠራት ዘንድ ሙሴን ተናግሮ እንዳዘዘው፥ የምስክር ድንኳን ከአባቶቻችን ዘንድ በምድረ በዳ ነበረች፤
⁴⁵ አባቶቻችንም ደግሞ በተራ ተቀብለው እግዚአብሔር በፊታቸው ያወጣቸውን የአሕዛብን አገር በያዙት ጊዜ ከኢያሱ ጋር አገቡአት፥ እስከ ዳዊት ዘመንም ድረስ ኖረች።
⁴⁶ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝቶ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያን ያገኝ ዘንድ ለመነ።
⁴⁷ ነገር ግን ሰሎሞን ቤት ሠራለት።
⁴⁸-⁵⁰ ነገር ግን ነቢዩ፦ ሰማይ ዙፋኔ ነው ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ ለእኔ ምን ዓይነት ቤት ትሠራላችሁ? ይላል ጌታ፥ ወይስ የማርፍበት ስፍራ ምንድር ነው? ይህንስ ሁሉ እጄ የሠራችው አይደለምን? እንዳለ፥ ልዑል የሰው እጅ በሠራችው አይኖርም።
⁵¹ እናንተ አንገተ ደንዳኖች ልባችሁና ጆሮአችሁም ያልተገረዘ፥ እናንተ ሁልጊዜ መንፈስ ቅዱስን ትቃወማላችሁ፤ አባቶቻችሁ እንደ ተቃወሙት እናንተ ደግሞ።
⁵²-⁵³ ከነቢያትስ አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን ነው? የጻድቁንም መምጣት አስቀድሞ የተናገሩትን ገደሉአቸው፤ በመላእክት ሥርዓት ሕግን ተቀብላችሁ ያልጠበቃችሁት እናንተም አሁን እርሱን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት ገደላችሁትም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_13_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚአከ ይትፌሥሑ። ወይሴብሑ ለስምከ። መዝራዕትከ ምስለ ኃይል"። መዝ 88፥12-13።
"ሰሜንና ደቡብን አንተ ፈጠርህ፤ ታቦርና አርሞንዔም በስምህ ደስ ይላቸዋል።
ክንድህ ከኃይልህ ጋር ነው፤ እጅህ በረታች ቀኝህም ከፍ ከፍ አለች"። መዝ 88፥12-13።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_13_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 9
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁸ ከዚህም ቃል በኋላ ስምንት ቀን ያህል ቈይቶ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ያዕቆብንም ይዞ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ።
²⁹ ሲጸልይም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም ተብለጭልጮ ነጭ ሆነ።
³⁰ እነሆም፥ ሁለት ሰዎች እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤
³¹ በክብርም ታይተው በኢየሩሳሌም ሊፈጽም ስላለው ስለ መውጣቱ ይናገሩ ነበር።
³² ነገር ግን ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንቅልፍ ከበደባቸው፤ ነቅተው ግን ክብሩንና ከእርሱ ጋር ቆመው የነበሩትን ሁለት ሰዎች አዩ።
³³ ከእርሱም ሲለዩ ጴጥሮስ ኢየሱስን፦ አቤቱ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ አለው፤ የሚለውንም አያውቅም ነበር።
³⁴ ይህንም ሲናገር ደመና መጣና ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም ሲገቡ ሳሉ ፈሩ።
³⁵ ከደመናውም፦ የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።
³⁶ ድምፁም ከመጣ በኋላ ኢየሱስ ብቻውን ሆኖ ተገኘ። እነርሱም ዝም አሉ ካዩትም ነገር በዚያ ወራት ምንም ለማንም አላወሩም።
³⁷ በነገውም ከተራራ ሲወርዱ ብዙ ሕዝብ ተገናኙት።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #እመቤታችን_የማርያም ወይም የ #ቅዱስ_ዲዮስቆሮስ ነው። መልካም የ #ደብረ_ታቦር (ቡሄ) በዓልና የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_14

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ዐሥራ አራት በዚህች ቀን የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በእስክንድርያ ሀገር ድንቅ ተአምርን አደረገ፣ #የአባ_ስምዖንና የወዳጁ #የአባ_የዮሐንስ የዕረፍታቸው መታሰቢያ ሆነ፣ #ቅዱስ_ባስሊቆስ በሰማዕትነት ሞተ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_መስቀለ_ክርስቶስ

ነሐሴ ዐሥራ አራት በዚህች ቀን የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በእስክንድርያ ሀገር ድንቅ ተአምርን አደረገ። ስለርሱም ከአይሁድ ብዙዎች አምነው በእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት በአባ ቴዎፍሎስ እጅ ተጠመቁ እርሱም ለቅዱስ ቄርሎስ የእናቱ ወንድም ነው። ይህም እንዲህ ነው በእስክንድርያ አገር ስሙ ፈለስኪኖስ የሚባል አይሁዳዊ ባለጸጋ ሰው ይኖር ነበር እርሱም እንደ አባቶቹ የኦሪትን ሕግ የሚጠብቅና #እግዚአብሔርን የሚፈራ ነው።

ዳግመኛም ሙያተኛዎች ሁለት ድኃዎች ክርስቲያኖች አሉ በአንደኛውም ላይ ሰይጣን የስድብ መንፈስ አሳድሮበት ጓደኛውን ወንድሜ ሆይ #ክርስቶስን ለምን እናመልከዋለን እኛ ዶኆች ነን ይህ #ክርስቶስን የማያመልክ አይሁዳዊ ፈለስኪኖስ ግን እጅግ ባለጸጋ ነው አለው።

ጓደኛውም እንዲህ ብሎ መለሰለት ዕወቅ አስተውል የዚህ ዓለም ገንዘብ ከ #እግዚአብሔር የሆነ አይደለም ምንም አይጠቅምም ጥቅም ቢኖረው ጣዖትን ለሚያመልኩ ለአመንዝራዎች ለነፍሰ ገዳዮች ለዐመፀኞች ሁሉ ባልሰጣቸውም ነበር።

አስተውል የከበሩ ነቢያት ድኆች ችግረኞችም እንደነበሩ ሐዋርያትም እንደርሳቸው ችግረኞች እንደነበሩ። #ጌታችንም ድኆችን ወንድሞቼ ይላቸው እንደነበረ። ሰይጣን ግን የጓደኛውን ምክር እንዲቀበል ምንም ምን አልተወውም ሃይማኖቱን ምንም ምን አልተወውም ሃይማኖቱን ለውጦ ነፍሱን እስከማጥፋት ድረስ አነሣሣው ቀሰቀሰው እንጂ።

ከዚህም በኋላ ወደ ፈለስኪኖስ ሒዶ በአንተ ዘንድ እንዳገለግል ተቀበለኝ አለው። ፈለስኪኖስም እንዲህ ብሎ መለሰለት በሃይማኖቴ የማታምን አንተ ልታገለግለኝ አይገባም ከቤተ ሰቦቼም ጋራ የማትተባበር ልቀበልህ አይገባኝም። ሁለተኛም ይህ ጐስቋላ ወዳንተ ተቀበለኝ እኔም ወደ ሃይማኖትህ እገባለሁ ያዘዝከኝንም ሁሉ አደርጋለሁ አለው።

አይሁዳዊው ባለጸጋም ከመምህሬ ጋር እስከምማከር ጥቂት ታገሠኝ ብሎ ከዚያም ወደ መምህሩ ሒዶ ድኃው ክርስቲያናዊ ያለውን ሁሉ ነገረው መምህሩም #ክርስቶስን የሚክድ ከሆነ ግረዘውና ተቀበለው አለው።

አይሁዳዊውም ተመልሶ መምህሩ የነገረውን ለዚያ ድኃ ነገረው ያም ምስኪን የምታዙኝን ሁሉ አደርጋለሁ አለ። ከዚህም በኋላ ወደ ምኵራባቸው ወሰደው የምኵራቡም አለቃ በሕዝቡ ሁሉ ፊት እንዲህ ብሎ ጠየቀው። ንጉሥህ #ክርስቶስን ክደህ አይሁዳዊ ትሆናለህን እርሱም አዎን እክደዋለሁ አለ።

የምኵራቡም አለቃ #መስቀል ሠርተው በላዩ የ #ክርስቶስን ሥዕል እንዲአደርጉ መጻጻንም የተመላች ሰፍነግ በዘንግ ላይ አሥረው ከጦር ጋራ እንዲሰጡት አዘዘ ከዚያም ከተሰቀለው ላይ ምራቅህን ትፋ መጻጻውንም አቅርብለት #ክርስቶስ ሆይ ወጋሁህ እያልህ ውጋው አሉት።

ሁሉንም እንዳዘዙት አድርጎ በወጋው ጊዜ ብዙ ውኃና ደም ፈሰሰ ለረጂም ጊዜም በምድር እየፈሰሰ ነበር በዚያን ጊዜም ያ ከሀዲ ደርቆ እንደ ደንጊያ ሆነ። በአይሁድ ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሀት ወደቀባቸው በእውነት የአብርሃም ፈጣሪ ስለእኛ ተሰቅሏል እኛም ዓለምን ለማዳን የመጣ የሕያው #እግዚአብሔር ልጅ እርሱ እንደሆነ አመንበት እያሉ ጮኹ።

ከዚህም በኋላ አለቃቸው ከዚያ ደም ወስዶ የአንድ ዕውር ዐይኖችን አስነካው ወዲያውኑ አየ ሁሉም አመኑ ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ ሒደው የሆነውን ሁሉ ነገሩት። ሊቀ ጳጳሳቱም ከካህናቱ ሁሉ ጋራ ተነሣ አባ ቄርሎስ ከእርሱ ጋራ አለ። ወደ አይሁድ ምኵራብም ሒዶ ውኃና ደም ከእርሱ ሲፈስ #መስቀሉን አገኘው ከዚያም ደም ወስዶ በግንባሩ ላይ ቀብቶ በረከትን ተቀበለ ሕዝቡንም ሁሉ ግንባራቸውን በመቀባት ባረካቸው።

ያንንም #መስቀል አክብረው ተሸክመው እያመሰገኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን ወስደው ያኖሩት ዘንድ አዘዘ። ደም የፈሰሰበትንም ምድር አፈሩን አስጠርጎ ለበረከትና ለበሽተኞች ፈውስ ሊሆን በሸክላ ዕቃ ውስጥ አኖረው።

ከዚህም በኋላ ፈለስኪኖስ ከቤተ ሰቦቹ ሁሉ ጋራ ሊቀጳጳሳት ቴዎፍሎስን ተከተለው ከአይሁድም ብዙዎቹ የቀደሙ አባቶቻቸው በሰቀሉት የክብር ባለቤት በሆነ በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አመኑ የክርስትና ጥምቀትንም በ #አብ#ወልድ#መንፈስ_ቅዱስ ስም አጥምቋቸው ከእርሱ ጋራ አንድ አደረጋቸው ሥጋውንና ደሙንም አቀበላቸው። ከዚህም በኋላ ለዘላለሙ ክብር ምስጉን የሆነ #እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ወደየቤታቸው ገቡ። እኛንም ሁላችን የክርስቲያን ወገኖችን በ #መስቀሉ ኃይል ያድነን አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_አባ_ስምዖንና_አባ_ዮሐንስ

ዳግመኛም በዚህች ቀን የአባ ስምዖንና የወዳጁ የዮሐንስ የዕረፍታቸው መታሰቢያ ሆነ። እሊህ ቅዱሳንም በአማኒው ዮስጦንስ ዘመን መንግሥት የነበሩ ናቸው እሊህም ወንድሞች የከበሩ ክርስቲያን ናቸው።

ከዚህ በኋላ ለከበረ #መስቀል በዓል ቅዱሳት መካናትን ሊሳለሙ ወደ ኢየሩሳሌም ሔዱ ሥራቸውንም አከናውነው ወደ አገራቸው ሲመለሱ በፈረሶቻቸው ተቀምጠው ወደ ኢያሪኮ ቀረቡ።

ዮሐንስም በዮርዳኖስ በረሀ ያለውን የመነኰሳቱን ገዳም አይቶ ወንድሙ ስምዖንን ወንድሜ ሆይ በእሊህ ገዳማት እኮ የ #እግዚአብሔር መላእክት ይኖራሉ አለው ዮሐንስም ከእርሳቸው ጋራ ከሆን አወን ልናያቸው እንችላለን አለው።

ከዚያም ከፈረሶቻቸውን ወርደው ለሰዎቻቸው ሰጥተው እስከምናገኛችሁ በየጥቂቱ ተጓዙ ብለው እንደሚጸዳዱ መስለው ወደ ዱር ገቡ።

የዮርዳኖስንም ጐዳና ተጒዘው ከሰዎቻቸው በራቁ ጊዜ እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ ጸሎት እናድርግ ከእኛም አንዳንችን ወደ መነኰሳቱ ገዳም በምታደርስ ጐዳና ቁመን ዕጣ እንጣጣል #እግዚአብሔር ከፈቀደ ዕጣችን ወደ ወጣበት እንሔዳለን።

ከዚህም በኋላ ስምዖን በዮርዳኖስ ጐዳና ቆመ ዮሐንስም ወደ ሀገራቸው በሚወስድ ጐዳና ላይ ቆመ ዕጣውንም በአወጡበት ጊዜ ዮርዳኖስ ጐዳና ላይ ወጣ እጅግም ደስ አላቸውና ስለ ደስታቸው ብዛት እርስ በእርሳቸው ተያይዘው ተሳሳሙ።

አንዱም አንዱ ወደኋላ እንዳይመለስ ስለጓደኛው ይጠራጠርና ይፈራ ነበር አንዱም ሁለተኛውን ይመክረውና ለበጎ ሥራ ያተጋው ነበር።

ዮሐንስ ስለ ስምዖን ይፈራ ነበር ስለ ወለላጆቹ ፍቅር አንዳይመለስ ስምዖንም ስለ ዮሐንስ ይፈራ ነበር እርሱ በዚያ ወራት መልከ መልካም የሆነች ሚስት አግብቶ ነበርና።

ከዚህም በኋላ ወደ #እግዚአብሔር ጸለዩ እንዲህም አሉ በውስጧ እንመነኵስ ዘንድ ለኛ የተመረጠች ገዳም ደጃፍዋ ክፍት ሆኖ ብናገኝ ምለክት ይሆናል።

የገዳሙም አለቃ ኒቆን የሚሉት በተሩፋት ፍጹም የሆነ ድንቆች ተአምራትን የሚያደርግ ሀብተ ትንቢት የተሰጠጠው ሲሆን በዚያች ሌሊት በጎቼ ይገቡ ዘንድ የገዳሙን በር ክፈተት የሚለውን ራእይ አየ።

ወደርሱም በደረሱ ጊዜ የ #ክርስቶስ በጎች ሆይ መምጣታችሁ መልካም ነው አላቸውና ከ #እግዚአብሔር ዘንድ እንደ ተላኩ ሰዎች አድርጎ ተቀበላቸው።

ከዚህም በኋላ አበ ምኔቱን የምንኵስናን ልብስ ያለብሳቸው ዘንድ ለመኑት እነርሱ በቆቡ ላይ የብርሃን አክሊል አድርጎ መላእክትም ከበውት አንዱን መነኰስ አይተዋልና ስለዚህም ፈጥነው ይመነኵሱ ዘንድ ተጉ።
ከዚያም በማግስቱ አበ ምኔቱ የምንኲስናን ልብስ አለበሳቸው በቀን እንደሚተያዩ በሌሊትም እርስበርሳቸው የሚተያዩ እስቲሆኑ በፊታቸው ላይ የመንፈስ ቅዱስ ብርሃን በራ ሁለተኛም በዚህ መነኵስ ላይ እንደሰዩ በራሶቻቸው ላይ የብርሃን አክሊል አዩ።

ከዚህም በኋላ ከመነኰሳቱ መካከል ተለይተው ወደ በረሀ ይገቡ ዘንድ ኀሳብ መጣባቸው። በዚያችም ሌሊት ብርሃንን የለበሰ ሰው ለአበ ምኔቱ ተገልጾ የ #ክርስቶስ በጎች እንዲወጡ የገዳሙን በር ክፈት አለው በነቃም ጊዜ ወደ በሩ ሒዶ ተከፍቶ አግኝቶት እያዘነና እየተከዘ ሳለ ሊወጡ ፈለገው እሊህ ቅዱሳን መጡ በፊታቸውም በትረ መንግስትን አየ።

በአያቸውም ጊዜ ደስ ብሎት ተገናኛቸው እነርሱም በልባቸው ያሰቡትን ነግረውት እንዲጸልይላቸው ለመኑት ለረጅም ጊዜም አለቀሰ ከዚህም በኋላ ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ በቀኙና በግራው አቆማቸው እጆቹንም ወደ ሰማይ ዘርግቶ ጸሎት አድርጎ ከክፉ ነገር ሁሉ ይጠብቃቸው ዘንድ ወደ #እግዚአብሔር አደራ አስጠበቃቸው። ከዚያም በፍቅር አሰናበታቸው።

ከዚህም በኋላ አርጋኖን ወደ ምባል ወንዝ ሔዱ በዚያም አንድ ገዳማዊ በዚያን ወራት ያረፈ በውስጡ የኖረበትን በዓት አገኙ በውስጡም ያ ሽማግሌ ገዳማዊ ሲመገበው የነበረ ለምግባቸው የሚያስፈልጋቸውን የእህል ፍሬዎችን አገኙ ምግባቸውን በአዘጋጀላቸው በ #እግዚአብሔርም እጅግ ደስ አላቸው።

በድንግያ ውርወራ ርቀት መጠን አንዱ ከሁለተኛው የተራራቁ ሁነው ሰፊ በሆነ ተጋድሎ ቡዙ ዘመናት ኖሩ። ሰይጣንም ቡዙ ጊዜ ይፈታተናቸው ነበር ግን አባታቸው ቅዱስ ኒቅዮስ በራእይ ወደ እሳቸው መጥቶ ስለ እነርሱ ይጸልያል ተኝተውም ሳሉ የዳዊትን መዝሙር ያስተምራችዋል በነቁም ጊዜ ያስተማራቸውን ሁሉ በትክክል ያነቡታል እጅግም ደስ ይላቸዋል።

አምላካዊ ራእይም ተሰጣቸው ተአምራትንም ያደርጋሉ በዚያችም በረሀ የክብር ባለቤት በሆነ በ #ክርስቶስ ኃይል ሰይጣንን ድል እስከ አደረጉት ድረስ የቀኑን ሐሩር የሌሊቱን ቊር ታግሠው ሃያ ዘጠኝ ዓመት ነሩ።

ከዚህም በኋላ ስምዖን ወንድሙ ዮሐንስ እንዲህ አለው በዚህ በረሀ በመኖራችን ምን እንጠቃማለን ና ወደ አለም ወጥተን ሌሎችን እንጥቀማቸው እናድናቸውም ዮሐንስም መልሶ እንዲህ አለው ወንድሜ ሆይ ይህ ኀሳብ ከሰይጣን ቅናት የተነሣ ይመስለኛል።

ስምዖን እንዲህ አለው ከሰይጣን አይደለም በዓለም ላይ እንድዘበትበት #እግዚአብሔር አዞኛልና ነገር ግን ና እንጸልይ ያን ጊዜም በአንድነት ጸለዩ ልብሳቸውንም እስከ አራሱት ድረስ እርስበርሳቸው ተቃቅፈው አለቀሱ። ከዚህም በኋላ ስምዖን እስከሚሞትባት ቀን ሥራውን ይሠውርለት ዘንድ ወደ #እግዚአብሔር እየጸለየ ጎዳናውን ተጓዘ።

ወደ ዓለምም ገብቶ ራሱን እንደ እብድ አደረገ እብዶችንም የፈወሰበት ጊዜ አለ እሳትን በእጁ የሚጨብጥበትም ጊዜ አለ። ከዚህም በኋላ ከከተማው በር የሞተ ውሻ አግኝቶ በመታጠቂያውም አሥሮ እየጐተተ እንደሚጫወት ሆነ ሰዎች እስከሚሰድቡትና እስከሚጸፉት ድረስ።

በአንዲት ቀን እሑድ ከቅዳሴ በፊት የኮክ ፍሬ ይዞ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገባ መቅረዞችንም ሰበረ። ሴቶችንም መትቶ ከእርሳቸው ጋራ እንደሚተኛ ጐተታቸው ባሎቻቸውም ደበደቡት።

ዕረፍቱም ሲቀርብ የ #እግዚአብሔር መልአክ የእርሱንም የወንድሙ የዮሐንስንም የዕረፍታቸውን ጊዜ ነገረው ወደ ወይን ሐረግ ሥር ገብቶ ከወንድሙ ዮሐንስ ጋራ ነፍሱን በ #እግዚአብሔር እጅ ሰጠ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎታቸው ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ባስሊቆስ

በዚህችም ቀን ቅዱስ ባስሊቆስ በሰማዕትነት ሞተ። በእሥር ቤትም እርሱ ሳለ የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ተገልጦለት እንዲህ አለው የምስክርነትህ ፍጻሜ ደርሷልና ሒደህ ዘመዶችህን ተሰናበታቸው።

ከዚህም በኋላ ወታደሮችን ከእርሱ ጋራ ወደ ቤቱ ይሔዱ ዘንድ ለመናቸው ሒደውም ወደ ቤቱ ገቡ እናቱንና ዘመዶቹንም ተሰናበታቸው። በማግሥቱም የከበረ ባስሊቆስን ወደ ፍርድ ሸንጎ አቀረቡትና በሁለት ምሰሶዎች መካከልም አሥረው ሲደበድቡት ዋሉ በእግሮቹም ችንካሮችን አደረጉበት ደሙም በምድር ላይ ፈሰሰ ያየው ሁሉ አለቀሰለት።

ከዚህም በኋላ ከደረቀ ዕንጨት ላይ አሠሩት ዕንጨቱም በቀለና ቅርንጫፍና ቅጠሎችን አወጣ። ሰዎችም የልብሱን ጫፍ ለመንካት የሚጋፉ ሆኑ በበሽተኞችና በዚህ ዕንጨት ላይ ያደረገውን ተአምር አይተዋልና።

ከዚህም በኋላ ዋርሲኖስ ወደሚባል አገር በመርከብ ወሰዱት ወታደሮችም እንዳትሞት እህልን ብላ አሉት እርሱም እኔ ከሰማያዊ መብል የጠገብኩ ነኝ ምድራዊ መብልን አልመርጥም አላቸው።

ወደ መኰንኑም በአቀረቡት ጊዜ ለአማልክት መሥዋዕትን አቅርብ አለው የከበረ በባስሊቆስም እኔ አንድ ለሆነ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የምስጋና መሥዋዕትን አቀርባለሁ አለው።

ሁለተኛም ወደ ጣዖታቱ ቤት እንዲአስገቡት አዘዘ እርሱም ቁሞ ወደ #እግዚአብሔር ጸለየ ያን ጊዜ እሳት ወርዶ ጣዖታቱን አቃጠላቸው መኰንኑም ፈርቶ ሸሽቶ ወደውጭ ወጣ። ቁጣንም ተመልቶ ይገድሉት ዘንድ ያ መኰንን አዘዘ ከዚህም በኋላ ቅዱስ ባስሊቆስ ወደ #እግዚአብሔር ጸለየ መከራውን ይሳተፍ ዘንድ ስለ አደለውም አመሰገነው።

ከዚህም በኋላ ራሱን በሰይፍ ቆረጡት ብዙዎችም መላእክት ነፍሱን ሲያሳርጓት አዩዋት #ጌታችን_ኢየሱስም ወዳጄ ባስሊቆስ ወደ እኔ ና እኔ የምዋሽ አይደለሁም ተስፋ ያስደረግሁህን እፈጽምልሃለሁ ብሎ ጠራው። እንዲህም ተጋድሎውን ፈጸመ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_14)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_14_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ቆሮንቶስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁰ ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ።
¹¹ ወንድሞቼ ሆይ፥ በመካከላችሁ ክርክር እንዳለ ስለ እናንተ የቀሎዔ ቤተ ሰዎች አስታውቀውኛልና።
¹² ይህንም እላለሁ፦ እያንዳንዳችሁ፦ እኔ የጳውሎስ ነኝ፥ እኔስ የአጵሎስ ነኝ፥ እኔ ግን የኬፋ ነኝ፥ እኔስ የክርስቶስ ነኝ ትላላችሁ።
¹³ ክርስቶስ ተከፍሎአልን? ጳውሎስስ ስለ እናንተ ተሰቀለን? ወይስ በጳውሎስ ስም ተጠመቃችሁን?
¹⁴-¹⁵ በስሜ እንደ ተጠመቃችሁ ማንም እንዳይል ከቀርስጶስና ከጋይዮስ በቀር ከእናንተ አንድን እንኳ ስላላጠመቅሁ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ።
¹⁶ የእስጢፋኖስንም ቤተ ሰዎች ደግሞ አጥምቄአለሁ፤ ጨምሬ ሌላ አጥምቄ እንደ ሆነ አላውቅም።
¹⁷ ለማጥመቅ ክርስቶስ አልላከኝምና፥ ወንጌልን ልሰብክ እንጂ፤ የክርስቶስ መስቀል ከንቱ እንዳይሆን በቃል ጥበብ አይደለም።
¹⁸ የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና።
¹⁹ የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ ተብሎ ተጽፎአልና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ያዕቆብ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና።
¹³ ማንም ሲፈተን፦ በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም።
¹⁴ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል።
¹⁵ ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች።
¹⁶ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ አትሳቱ።
¹⁷ በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፥ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ።
¹⁸ ለፍጥረቱ የበኵራት ዓይነት እንድንሆን በእውነት ቃል አስቦ ወለደን።
¹⁹ ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቍጣም የዘገየ ይሁን፤
²⁰ የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና።
²¹ ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ።
²² ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 10
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³⁰ ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው፦ በዚች ሰዓት የዛሬ አራት ቀን የዘጠኝ ሰዓት ጸሎት በቤቴ እጸልይ ነበር፤ እነሆም፥ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሰ ሰው በፊቴ ቆመና፦
³¹ ቆርኔሌዎስ ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸሎትህ ተሰማ ምጽዋትህም ታሰበ።
³² እንግዲህ ወደ ኢዮጴ ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስጠራ፤ እርሱ በቍርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በባሕር አጠገብ እንግድነት ተቀምጦአል አለኝ።
³³ ስለዚህ ያን ጊዜ ወደ አንተ ላክሁ፥ አንተም በመምጣትህ መልካም አድርገሃል። እንግዲህ አንተ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዝኸውን ሁሉ እንድንሰማ እኛ ሁላችን አሁን በእግዚአብሔር ፊት በዚህ አለን።
³⁴-³⁵ ጴጥሮስም አፉን ከፍቶ እንዲህ አለ፦ እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ በእውነት አስተዋልሁ።
³⁶ የሁሉ ጌታ በሚሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እየሰበከ ይህን ቃል ወደ እስራኤል ልጆች ላከ።
³⁷ ዮሐንስ ከሰበከው ጥምቀት በኋላ ከገሊላ ጀምሮ በይሁዳ ሁሉ የሆነውን ነገር እናንተ ታውቃላችሁ።
³⁸ እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ቀባው፥ እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና፤
³⁹ እኛም በአይሁድ አገርና በኢየሩሳሌም ባደረገው ነገር ሁሉ ምስክሮች ነን፤ እርሱንም በእንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት።
⁴⁰ እርሱን እግዚአብሔር በሦስተኛው ቀን አስነሣው ይገለጥም ዘንድ ሰጠው፤
⁴¹ ይኸውም ለሕዝብ ሁሉ አይደለም ነገር ግን በእግዚአብሔር አስቀድሞ የተመረጡ ምስክሮች ለሆንን ለእኛ ነው እንጂ፤ ከሙታንም ከተነሣ በኋላ ከእርሱ ጋር የበላን የጠጣንም እኛ ነን።
⁴² ለሕዝብም እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ በእግዚአብሔር የተወሰነ እርሱ እንደ ሆነ እንመሰክር ዘንድ አዘዘን።
⁴³ በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአቱን ስርየት እንዲቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_14_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ዘአዘዝከ መድኃኒቶ ለያዕቆብ። ብከ ንወግዖሙ ለኵሎሙ ፀርነ። ወበስምከ ናኀሥሮሙ ለዕለ ቆሙ ላዕሌነ"። መዝ 43፥4-5።
"አምላኬና ንጉሤ አንተ ነህ፤ ለያዕቆብ መድኃኒትንህ እዘዝ። በአንተ ጠላቶቻችንን እንወጋቸዋለን፥ በስምህም በላያችን የቆሙትን እናዋርዳቸዋለን"። መዝ 43፥4-5።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_14_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 17
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁴ ወደ ሕዝቡም ሲደርሱ አንድ ሰው ወደ እርሱ ቀረበና ተንበርክኮ፦ ጌታ ሆይ፥ ልጄን ማርልኝ፥ በጨረቃ እየተነሣበት ክፉኛ ይሣቀያልና፤
¹⁵ ብዙ ጊዜ በእሳት ብዙ ጊዜም በውኃ ይወድቃልና።
¹⁶ ወደ ደቀ መዛሙርትህም አመጣሁት ሊፈውሱትም አቃታቸው አለው።
¹⁷ ኢየሱስም መልሶ፦ የማታምን ጠማማ ትውልድ ሆይ፥ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ወደዚህ ወደ እኔ አምጡት አለ።
¹⁸ ኢየሱስም ገሠጸው ጋኔኑም ከእርሱ ወጣ፥ ብላቴናውም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ተፈወሰ።
¹⁹ ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን ወደ ኢየሱስ ቀረቡና፦ እኛ ልናወጣው ያልቻልን ስለ ምን ነው? አሉት።
²⁰ ኢየሱስም፦ ስለ እምነታችሁ ማነስ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ተራራ፦ ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም።
²¹ ይህ ዓይነት ግን ከጸሎትና ከጦም በቀር አይወጣም አላቸው።
²² በገሊላም ሲመላለሱ ኢየሱስ፦ የሰው ልጅ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጥ ዘንድ አለው፥ ይገድሉትማል፥
²³ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል አላቸው። እጅግም አዘኑ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #እመቤታች_የማርያም_ቅዳሴ ወይም የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቅዳሴ ነው። መልካም የጾም ጊዜና በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

           #ነሐሴ ፲፬ (14) ቀን።

እንኳን ልክ #እንደ_እመቤታች ገና #በእናታቸው_ማኅጸን_ሳሉም_ድዉይ_ይፈውሱ ለነበሩት፣ እንደ ዘጠኙ ቅዱሳን ከሮም ወደ አገራችን ኢትዮጵያዊ በመምጣት ኤርትራ አገር የሚገኘውን ታላቁ ገዳም #ሙራደ_ቃል_ደብረ_ኮል ለመሠረቱት ለታላቁ ጻድቅ #አቡነ_ቡሩክ_አምላክ_ለዕረፍታቸው በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።

#አቡነ_ቡሩከ_አምላክ፦ ከሴም ወገን ሲሆኑ የትውልድ ሀገራቸው ሮም ነው። አባታቸው ቴዎቅሪጦስ እናታቸው ሚሊዳማ የሚባሉ ከነገሥታት ወገን ሲሆኑ ኹለቱም እንደ አብርሃምና ሣራ በቃል ኪዳን የጸኑ ነበሩ። እነርሱም ብዙ ሀብትና ንብረት ቢኖራቸውም ልጅ ስለሌላቸው ሁልጊዜ እያዘኑ ወደ እግዚአብሔር ይጸልዩ ይለምኑ ነበር። ልዑል እግዚአብሔርም ጸሎታቸውን ሰምቶ ቅዱስ ሚካኤልን ወደ ሚሊዳማ በመላክ እንዲያበሥራት አዘዘው። ሚሊዳማ ዕድሜዋ እንደ ሣራ ገፍቶ ስለነበር ብሥራቱን ስትሰማ መልአኩን "…በዚኽ ዕድሜዬ እንዴት ይሆንልኛል?" አለችው። ቅዱስ ሚካኤልም "ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም" አላት፤ እርሷም እመቤታችንን አብነት አድርጋ "…እሺ እንደ ፍቃዱ ይሁንልኝ" አለች።

አባታችን አቡነ ቡሩክም በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም በዕለተ ጽንሰቷ ነሐሴ 7 ቀን ተፀንሰው በዕለተ ልደቷም ግንቦት 1 ቀን 1290 ዓ.ም ተወለዱ። ጻድቁ ገና በእናታቸው ማሕፀን ሳሉም ድዉይ እንደፈወሱ በገድላቸው ላይ ተጽፏል። ከእናቷ ማሕፀን ጀምሯ የታመመች አንዲት ሴት ነበረች። አቡነ ቡሩከ አምላክ በእናታቸው ማሕፀን ሳሉ የሮሙ ንጉሥ አባታቸውና ንግሥቲቱ እናታቸው ግብዣ አድርገው ሳለ ከተወለደች ጀምሮ እስከ ሠላሳ አምስት ዓመቷ ድዉይ የነበረችው ያቺ የታመመች ሴት ወደ ግብዣው መጥታ ሳለ የአቡነ ቡሩከ አምላክ እናት የሚሊዳማ ጥላዋ ቢያርፍባት ከነበረባት ሕመም ፈጥና ዳነች።

አምላክን የወለደች ቅድስት ድንግል ማርያም በእናቷ በቅድስት ሐና ማሕፀን ሳለች ብዙ ሕሙማንን እንደፈወሰች ኹሉ አቡነ ቡሩከ አምላክም እንዲሁ በእናታቸው ማሕፀን ሳሉ ድዉይ ፈወሱ። ሴቲቱም ፈጽማ ድና እግዚአብሔርን እያመሰገነች በእግሮቿ ቀጥ ብላ ቆማ ወደ ሀገሯ ሔደች። ባልም አግብታ ልጆችን የወለደች ሲሆን ልጆቿ በኋላ የአቡነ ቡሩከ አምላክ ተከታዮችና አገልጋዮች ሆነዋል። አቡነ ቡሩከ አምላክ ገና በተወለዱ በ5ኛ ቀናቸው "አንድ አምላክ ለሚሆን ለአብ ምስጋና ለወልድ ምስጋና ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን" ብለው ፈጣሪያቸውን አመስግነዋል። ዳግመኛም "ለድንግል ማርያም ምስጋና፤ ለኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ምስጋና ይሁን" እያሉ ከእናታቸው ማሕፀን ጀምሮ የጠበቃቸውን አምላካቸውን አመሰገኑ። በ40ኛ ቀናቸውም ሥርዓተ ጥምቀት ሲፈጸምላቸው እስከመጨረሻ ድረስ "…አሜን ይሁን" እያሉ ይቀበሉ ነበር። ስመ ጥምቀታቸውም ዓምደ ሚካኤል ይባላል። ከጥምቀታቸውም በኋላ ዘወትር ረቡዕና ዐርብ የእናታቸውን ጡት አይጠቡም ነበር፣ ሁልጊዜም የእግዚአብሔርን ምስጋና ከአፋቸው አይለይም ነበር። ሦስት ዓመት ሲሆናቸው የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እንዲማሩ ወላጆቻቸው ለመምህር ቢሰጧቸውም እርሳቸው ግን እግዚአብሔር የመጻሕፍትን ምሥጢር ስለገለጠላቸው ቅዱሳን መጻሕፍትን በፍጥነት አጥንተው ዐወቁ።

አባታችን ከልጅነታቸው ጀምረው ምግባቸውንና ልብሳቸውን ለነዳያን ይመጸውቱ ነበር፤ እርሳቸው ግን ከመምህራቸው ሳይለዩ በጾም በጸሎት ተግተው ይኖሩ ነበር። ከዚኽም በኋላ ዕድሜያቸው እንደደረሰ ወላጆቻቸው ሚስት እንዲያገቡ ወሰኑላቸው ነገር ግን አባታችን ከዚኽ ሀሳብ ይድኑ ዘንድ በጸሎት እንዲያግዟቸው ለመምህራቸው በመንገር እርሳቸውም በጸሎት ተግተው እየጸለዩ ሳለ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ መጥቶ ከዚያ ሀገር ተነሥተው ወደ ምድረ አግዓዚ እነ አቡነ አብሳዲና እነ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ዘንድ እንዲሔዱ ነገራቸው። በዚያም የብዙዎች አባት እንደሚሆኑና በእርሳቸው አማካኝነት ብዙዎች እንደሚድኑ ነገራቸው። አቡነ ቡሩክም ማንም ሳያያቸው በመንፈቀ ሌሊት ተነሥተው በመልአኩ መሪነት ቀድሞ ወደነገራቸው ቦታ ወደ ደብረ ማርያም መጡ።

አቡነ ቡሩከ አምላክን እግዚአብሔር እንደነ ነቢዩ ኤርምያስ ገና በእናታቸው ማሕፀን ሳሉ ስለመረጣቸው በ7 ዓመታቸው ዲቁና ከተቀበሉ ከ5 ዓመት በኋላ መመንኰስ እንደሚፈልጉ ለአቡነ ኤዎስጣቴዎስ ነገሯቸው። አቡነ ኤዎስጣቴዎስም "ቅዱስ ሚካኤል እንዳዘዘህ ምንኵስና የምሰጥህ እኔ አይደለሁም፣ ወደ ልጄ አብሳዲ ሒድ" ብለዋቸው ወደ ዓረዛ ቆላ ሰራየ ሔዱ። በዚያም በ12 ዓመታቸው በአቡነ አብሳዲ እጅ መነኰሱ፤ ስማቸውንም ብሩከ አምላክ አሏቸው። አቡነ ቡሩከ አምላክ ከመነኰሱ በኋላ የክብር ባለቤታችን ጌታችን "እኔን ሊያገለግለኝ የሚወድድ ሰው ቢኖር ነፍሱን ይጥላት፣ ጨክኖ የሞቱን መስቀል ተሸክሞ ይከተለኝ፣ ነፍሱን ሊያድናት የሚወድድ ሁሉ ይጣላት፤ ነፍሱን ስለ እኔ ብሎ የጣላት ያገኛታል"፤ ዳግመኛም "ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጠፋ ምን ይጠቅመዋል? ለነፍሱ ቤዛስ ምን ይሰጣል?" በማለት የተናገረውን አስበው የምኵስናን ሥራ ይሠሩ ዘንድ ገባ የተባለ እሾህ አምጥተው ወንድማቸውን "እኔ መንኵሴ ልባል የማይገባኝ ኃጢአተኛ ነኝና የኃጢአት ማስተሠረያ ይሆነኝ ዘንድ በዚኽ ግረፈኝ" አሉት። በእሾሁም በተገረፉ ጊዜ ደማቸው እንደ ውኃ ፈሰሰ።

አቡነ ቡሩከ አምላክ የተገረፈባት ሀገር እስከዛሬ ድረስ ዓዲ-ጋርፋ እየተባለች ትጠራለች። ትርጕሙም የመገረፍ ሀገር ማለት ነው። ምልክቷም ብዙ መነኰሳይያት ይኖሩባታል። ይኽም ገባ በሚባል እሾህ የተገረፈባት ማለት ነው። በሌላም ጊዜ ቆዳው እስኪሰነጣጠቅና ቊስል እስኪሆን ድረስ በሸንበቆ የሚገረፍበት ጊዜ ነበረ፣ ከዚኽም በተጨማሪ መላ አካሉ ቈስሎ ሳለ በላዩ ላይ ግርፋቶችን ይጨምርበታል። በዚኽ ዓለም በመስቀል ላይ እንደተሰቀለ በብረት ችንካሮች እጆቹንና እግሮቹን እንደተቸነከረ የጌታችንን ሕማማቱን እያሰበ ሥጋውን አያሳርፋትም ነበረ። ከታናሽነቱ ጀምሮ የንጉሥ ልጅ ሲሆን ምድራዊ መንግሥትን ትቶ እግዚአብሔርን አገለገለ። ጌታችን በወንጌሉ "ማንም ቢሆን ስለ ስሜ ብሎ ርስትንና ልጆችን፣ ወንድሞችንና እኅቶችን፣ እናትንና አባትን ያልተወ መንግሥተ ሰማያትን ሊወርስ አይችልም" ብሎ የተናገረውን አስቦ ከታናሽነቱ ጀምሮ ጌታውን አገለገለ።

ከዕለታትም በአንዲቱ እህልና ውኃ ወደማይገኝበት ምድረ በዳ ሔደ። ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ሥጋውን በረኃብና በውኃ ጥም ቀጣ፤ ከሰንበቶች በስተቀር ምንም አልቀመሰም። እንደ መላእክት ንጹሕ፣ ለጸሎት ትጉ፣ እውነተኛ መነኵሴ፣ ችግርን ወዳጅ፣ መንግሥትን መናኝና መስቀል ተሸካሚ የሆነ አቡነ ቡሩከ አምላክ ከዚኽ ዓለም አንዳች ነገርን የራሱ አላደረግም።

ጻድቁ የዲቁናና የቅስና ማዕረግ የተቀበሉት ወደ ሸዋ ምድር በመምጣት ነው፤ በዘመኑም የነበረው የኢትዮጵያ ንጉሥ ዐፄ ዳዊት ነበረ። አቡነ ቡሩከ አምላክ በመንፈቀ ሌሊት ቆሞ እየጸለየ ሳለ እግዚአብሔር በሦስትነቱ ተገልጦለት "የኤፍራጥስና የጤግሮስ፣ የኤፌሶንና የግዮን አምሳል ደጋግ መነኰሳት የሚኖሩባት፣ ከጎንህ ውኃ የሚፈስባት የምትኖርባትና በሞት ዐርፈህ የምትቀበርባት ቦታ ደብረ ኮል ናት፣ አጋንንት ከእርሷ ይርቃሉ፤ በእርሷ ዘንድ በጸሎት ውኃዋ ሕሙማን ይፈወሳሉ፣ መላእክትም በውስጧ ይወርዳሉ ይወጣሉ፣ ገዳምህ ደብረ ኮል እንደ
ተወለድኩባት እንደ ቤተልሔም፣ እንደ ተሰቀልኩባት ቀራንዮ የከበረች ትሆናለች…" በማለት ጌታችን ስለ ገዳሙ ደብረ ኮል ነገረው።

አቡነ ቡሩከ አምላክ የአቡነ አብሳዲ ልጅ ሆነው በደብረ ማርያም ገዳም በታላቅ ተጋድሎ ኖረው በኋላም ለዘለዓለም ማረፊያቸው ወደሆነችው ወደ መራጉዝ መጥተው ገዳማቸውን ደብረ ኮልን መሠረቱ። የአቡነ ቡሩከ አምላክ ትውልዱ ከያፌት ወገን ነው፤ ሀገሩ ከዘጠኙ ቅዱሳን ሀገር ከሮም ነው፤ ጥንተ ሙላዱም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ከሚከተሉ ከሮም ነገሥታት ወገን ነው፤ አባቱም የሮም ንጉሥ ነበረ፤ ዘውድ ደፍቶ ሃይማኖታቸው በቀና ሰዎች ላይ ነግሦ ነበረ። ተላላኪው አባ ጌርሎስም ያዘዘውን ኹሉ ይላላከው ነበረ። አቡነ ቡሩከ አምላክንም የቀናች ቅድስት ሥላሴን ማመንን በምትናገር በቀናች የተዋሕዶ ሃይማኖት ያጠመቀው አባ ጌርሎስ ነበረ። አቡነ አብሳዲ ጾሙንና ጸሎቱን፣ ትሕትናውን፣ መላላኩንና ክህነቱን ተመልክቶ "እንግዲህስ አዳምን ለማዳን ሰው የሆነ የጌታህን የኢየሱስ ክርስቶስን ትዕዛዝና የእኔን ትዕዛዝ ፈጽመሃል" አለው። ዳግመኛም "በቅድስት ሥላሴ ስም በመንፈስ ቅዱስና በወንጌል ትምህርት ከአንተ የሚወለዱ ብዙ ሕፃናት እንዲሁም ብዙዎች በምንኵስና ቀንበር ከአንተ ይወለዳሉ። ስብከትህና ወንጌል ማስተማርህ በዓለሙ ሁሉ ይሰማል። የመንፈስ ልጅህ የልጅ ልጅህ ለዘላለም ይኖራል። ትንቢታቸውና ትምህርታቸው እስከ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ድረስ አይጠፋም፤ እነርሱም እንዲሁ አይጠፉም። እኔ የአምላኬን ፈቃድ ፈጽሜአለሁና ዛሬም የእኔ ፈቃድ አይደለም፤ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው እንጂ። አንተም የፈጣሪህን ትእዛዝ ፈጽም። ይህ ነገር ከእኔ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ነውና ስለተናገረኝ እንዲህ እልሃለሁ"። አቡነ ቡሩከ አምላክም ራሱን ዝቅ አድርጎና ከእግሩ በታች ሰግዶ "እሺ በጄ" አለው። አቡነ አብሳዲም ከእንባ ጋር ከምድር አንሥቶ ሳመው፤ "እግዚአብሔር ወደፈቀደልህ ሂድ፤ እኔን ያሳየኝ እሸኝህ ዘንድ ነው" አለው። አቡነ አብሳዲ ይኽንም ያየው በደብረ ማርያም አበ ምኔት ሆኖ ሳለ ነበረ።

በንጉሥ ዐምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ከኢትዮጵያ ተነሥቶ ወደ አርማንያ ሔደ። ዕዝራ ቅድስት ሀገርን በምታለቅስ ሴት አምሳል እንዳያት አባ ኤዎስጣቴዎስ በአርማንያ ሆኖ ሲጸልይ ሳለ አቡነ ቡሩከ አምላክ በኢትዮጵያ ሆኖ በጸሎት ሲተጋ ሲሰግድና የብርሃን ምሰሶ ከሚጸልይበት በኣት ተተክሎ ያይ ነበረ። እግሩ ከረገጠበት ቦታም ኤፍራጥስና ጤግሮስ ኤፌሶንና ግዮን ይመላለሱ ነበሩ። አቡነ ኤዎስጣቴዎስም ይኽን ባየ ጊዜ "ወንጌል የሚያንሰው ይበልጠዋል እንዳለ ይኽም ሕፃን እንደ መልከ ጼዴቅ ክህነትና እንደ አቤል መሥዋዕት ከእኔ ይበልጣል" አለ።

ከዚኽም በኋላ ጻድቁ ወግረ ስኂን ተብሎ ከሚጠራው ከደብረ ማርያም በወረደ ጊዜ የዱር አራዊት ሁሉ ተቀበሉት። እነርሱም አንበሶችና ነብሮች፣ ዝሆኖችና ቀይ ቀበሮዎች፣ ሽኮኮዎች፣ አሳማዎች፣ አውራሪስ፣ ጦጦዎችና ዝንጀሮዎች ናቸው። ኹሉም በስምምነት "አባ ክቡር ሆይ! የት ትሔዳለህ?" እያሉ ሰገዱለት። እግዚአብሔር የአቡነ ቡሩከ አምላክን ሥራ ይገልጥ ዘንድ የሰውን ቋንቋ ገልጦላቸዋልና። አባታችን ወደ ደብረ ኮል ከገቡ በኋላ እያስተማሩ ያመነኰሷቸው መነኰሳት ቊጥራቸው እጅግ ብዙ ሆነ። አባታቸው አቡነ አብሳዲም ጌታችን በቃሉ አዝዟቸው በደመና ተጭነው መጥተው ጎብኝተዋቸው ሹመትንም ሰጥተዋቸዋል። አባታችን ቡሩከ አምላክ ያመነኰሷቸውን ቊጥራቸው መቶ የሚሆኑ ሴቶች መነኮሳይያትን በአንድ ጸንተው እንዲኖሩ ካስተማሯቸው በኋላ ታላቋንና መጻሕፍትን የምታውቀውን ጸበለ ማርያም እመ ምኔት አድርው ሾሙላቸው።

ጻድቁ ሃይማኖቱ በቀና በኢትዮጵያው ንጉሥ በዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ኹለት ሕንጻ አብያተ ክርስቲያናትን አምላክን በወለደች በክብርት እመቤታችን ስም ጋርፋ በምትባል ሀገር እንዲሁም በመላእክት አለቃ በቅዱስ ሚካኤል ስም ቤተ ክርስቲያን አነጹ፤ ነገር ግን የቅዱስ ሚካኤልን ሕንጻ ቤተ መቅደስ ኹለተኛው ሄሮድስ የተባለ ግራኝ አህመድ አቃጠላት። የእመቤታችን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ግን ተሰወረችው። አባታችን ገዳማትን መጎብኘት በፈለገ ጊዜ ደመና ጠርቶ በደመና ተጭኖ ይሔድ ነበረ። ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደተወለደባት ወደ ቤተልሔም ይሔድ ነበረ፤ መጋቢት ሃያ ሰባት ቀንም ጌታ ወደ ተሰቀለበትና ወደ ተቀበረበት ወደ ጎልጎታ፤ ወደ እናቱ መቃብር ወደ ጌቴሴማኒ እንዲሁም ጌታችን ከእናቱ ጋር ወደ አደረባት ወደ ደብረ ቊስቋም በደመና ተጭኖ ይሔድ ነበረ። ይኽንንም ሲያደርግ ከፈጣሪው በቀር ሰው አያውቅበትም ነበረ። ለመነኰሳትም ቤቱ ውስጥ ጸሎት የሚያደርግ ይመስላቸው ነበረ። ከትሕትናውም የተነሣ በቤተ ክርስቲያን በአገልግሎት ጊዜ "መጻሕፍትን አንብብ" በሚሉት ጊዜ "አላነብም አትሮንስ አቀርባለሁ፣ ጥላና መጽሐፍን እይዛለሁ እንጂ" ይላቸው ነበረ። "ዋና ሠራኢ ካህን ሆነህ ቀድስ" በሚሉት ጊዜ "አልችልም" ይል ነበረ። አንድ ቀን ሠራዒ ሆኖ የሚቀድስ ሰው ጠፋ። እነርሱም "እባክህ ዛሬ በሠራዒ ቀድስ" አሉት፤ እርሱም "እሺ በጄ" ብሎ በቀደሰ ጊዜ ከመሬት በአንድ ክንድ ከፍ አለ። ቊጥር የሌላቸው መላእክትም መቅደሷን ከበቧት። "አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ" ባለ ጊዜ እና "ሀበነ ንኅበር" ባለ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በነጭ ርግብ አምሳል በአቡነ ቡሩከ አምላክ ላይ ረበበ። ቀሳውስቱም ይኽንን ተመልተው ገረማቸው፤ "በእውነት ይኽ መነኵሴ ከእኛ ይበልጣል" አሉ። እንዲሁም የካቲት ዐሥራ ስድስት ቀን አባታችን ሠራዒ ሆኖ በቅዳሴ ማርያም ላይ "አንቲ ውእቱ ተስፋሁ ለአዳም" ባለ ጊዜ አምላክን የወለደች ክብርት እመቤታችን ወረደች። እንዲሁ ግንቦት አንድ ቀን "ኦ ማርያም በእንተ ዝ ነዐብየኪ ወናፈቅረኪ" ባለ ጊዜ ቃል በቃል አነጋገረችው፤ "ወዳጄና የልጄ ወዳጅ ቡሩከ አምላክ ሆይ! የአዳምና የሔዋን ብቻ አለኝታ አይደለሁም፣ ለእናትህና ለአባትህ በልጄ ዘንድ አለኝታቸው እኔ ነኝ፤ አንተንም ያገኙህ በእኔ በኩል ነው" አለችው። ዳግመኛም "በጸጋ በጸጋ ሰጠሁህ፤ በሚያምረው ዜማህ ተደስቻለሁና። መኖሪያህንም ከሶርያው ኤፍሬምና ከብህንሳው ከአባ ሕርያቆስ ጋር አደርጋለሁ። አስቀድሜ ከአንተ አልተለየሁም፣ ከእንግዲህም ወዲያ ከአንተ አልለይም" አለችው። እመቤታችን ይኽን ብላ በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገች።

አቡነ ቡሩከ አምላክ በዚህ ገዳም በብሕትውና ተጋድሎ ለ63 ዓመታት ኖረዋል። ጻድቁ በገዳመ ደብረ ኮል ያደረጓቸው ታላላቅ ተኣምራት ተቆጥረው የሚያልቁ አይደሉም። እግዚአብሔር በሰጣቸው ጸጋ እንደ ሙሴ ከዐለት ላይ ያፈለቁት ጠበል ብዙ በደዌ የተያያዙ ምእመናንን እየፈወሰ ይገኛል። ለአቡነ ቡሩከ አምላክ አባታቸው አቡነ አብሳዲ የሰጧቸው ኹለት መቆሚያዎች ነበሯቸው። አንደኛዋ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚደገፉባት ስትሆን ሁለተኛዋ ደግሞ ለአገልግሎት በየቦታው ሲዘዋወሩ ሕሙማንን የሚፈውሱባት ናት።
ከዕለታት በአንደኛው ቀን ወደ ሀገረ እምብርት (ዓዲ ሕምብርቲ) ሔደው ሕዝቡን ወንጌል አስተምረው ጨርሰው ሊሔዱ ሲሉ መቋሚያቸው ያስተምሩበት በነበረው ቦታ ላይ በተኣምር ተተክላ ሥር ሰዳ ተገኘች፤ እርሳቸውም ሊያንቀሳቅሷት ስላልቻሉ ተጨንቀው "አቤቱ ጌታ ሆይ! ምንድነው ያጠፋሁት?" ብለው እግዚአብሔርን በጸሎት ሲጠይቁት የታዘዘ መልአክ መጥቶ "…መቋሚያህ ለሀገሪቱ በረከት ትሆን ዘንድ ከዚሁ ትቀመጥ" አላቸው። መቋሚያዋም ለምልማ ቅጠል አውጥታ ትልቅ ዛፍ ሁና ከሥሯ ጠበል ፈልቆ ጠበሉ
እስከአሁን ሕሙማንን እየፈወሰ ይገኛል።

የክብር ባለቤት ለአቡነ ቡሩከ አምላክ የገባላቸው ቃልኪዳን፡- "በእጅህ የባረክኸው በእግርህም የረገጥከው ዓለም ከመፈጠሩ በፊት በመንፈስ ለአንተና ለልጆችህ ያዘጋጀሁት ይሁንህ" አለው። ዳግመኛም "በገዳምህ ለሚያገለግለውና መታሰቢያህን ለሚያደርገው እምርልሃለሁ ብየ ቃል እንደገባሁልህ በራሴ ማልሁልህ፤ ለባሪያዬ ለኖኅ፣ ለወዳጄ አብርሃም፣ ለታማኜም ለዳዊት ቃል ኪዳን የገባሁ እኔ ነኝ፤ እኔ ሲኦልን በዕለተ ዓርብ እንደበዘበዝኳት ለአንተም የእሳት ፈረስ ሰጠሁህ፤ አንተም ዳግመኛ ሲኦልን ትበዘብዛታለህ፤ መባርቅታና ነጎድጓድ ይከተሉሃል፤ መላእክትም በየወገናቸው ይሸኙሃል፤ ስለገባሁልህ ቃል ኪዳን ሲኦልን ለመማረክ ከአንተ ጋር አንድ ይሆናሉ፤ በሞት ከማረፍህ በፊት በሕይወት ሳለህ ሲኦልን ትበረብራት ዘንድ ፈቀድሁልህ፤ አንተ ከሲኦል የምታወጣቸው ነፍሳት በቊጥራቸው ከሰማይ ከዋክብትና ከምድር አሸዋ ይበዛሉ፤ እንደ ጻድቃንና እንደ ሰማዕት እንደ ሐዋርያትና እንደ ነቢያት ይኽን ሁሉ ፈጸምህ፤ ዳዊት "የድካምህን ዋጋ ተመገብ" እንዳለ። ይኽን ሁሉ የኦሪትና የነቢያትን የወንጌልንና የሐዋርያትን ሥራ የብሉይንና የሐዲስ ትእዛዛትን ፈጸምህ። እኔ የአምስት ገበያ የሚያህሉ ሰዎችን እንዳስተማርኩ አንተም እንዲሁ ስላስተማርህ ቃል ኪዳኔን ሰጠሁህ፤ ዐራቱ ወንዞች ገነትን እንደሚያጠጧት በአራቱ የምድር ማዕዘኖች ወንጌልን አስተማርህ፤ ያልተጠመቁትን ይድኑ ዘንድ ያጠመቅህ፤ ያላመኑትንም ያሳመንህ አንተ ቡሩከ አምላክ ነህ፤ የተጣሉትንም አስታረቅህ፤ በጾምና በጸሎትም አስደሰትከኝ፤ የሰማዕታቱን የጊዮርጊስን የፋሲለደስንና የገላውዴዎስን ተጋድሎ ትፈጽም ዘንድ ገድል ተዘጋጅቶልሃል፤ አንገትህ በሰይፍ ይቆረጣል፤ ጎንህም በጦር ይወጋል"።

አባታችን የሀገረ ገዥ ልጅ ሆነው ሳለ እርሳቸው ግን ለሰማያዊ ንግሥና ራሳቸውን አጭተው ገና በሕፃንነት ዕድሜያቸው ወደ ሀገራችን በመምጣት በብዙ ተጋድሎ ቢኖሩም በዐፄ ዳዊት ዘመን የነበሩ ክፉዎች ወደ አቡነ ቡሩክ ገዳም ወደ ደብረ ኮል መጥተው ስለሃይማኖታቸው ጽናት በሰማዕትነት ገድለዋቸዋል። አቡነ ቡሩከ አምላክም ይህ እንደሚሆን አስቀድመው በራእይ ታይቷቸው ነበርና ገዳዮቻቸውን ተዘጋጅተው ይጠብቋቸው ነበር። የሰማዕትነት አክሊል እየታያቸው ከእርሳቸው ጋር የነበሩ መነኰሳትም "እኔ ነኝ የምቀድመው፣ እኔ ነኝ መጀመሪያ የምሞተው…" ብለው እየተሽቀዳደሙ ነሐሴ 14 ቀን በሰማዕትነት ዐረፉ።

አባታችን በሰማዕትነት የሚያርፉበትን ዕለት አስቀድመው በመንፈስ ቅዱስ ያውቁት ስለነበር ለተከታዮቻቸው እንዲህ አሏቸው፡- "ከእንግዲህስ ከዚኽ ዓለም የምለይበት ኹለት ሳምንት ብቻ ቀረኝ። ከእናንተ መካከልም በሱባዔው ፍጻሜ ነሐሴ ዐሥራ ዐራት ቀን ሕይወቴን አታዩም፤ ሞቴን ግን ታያላችሁ። ያልኳችሁንም በልባችሁ አኑሩት። ከእንግዲህ ከእናንተ ጋር አልኖርም። በእግዚአብሔር ፊት በደና እንገናኝ"። ይኽን ካላቸው በኋላ ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ጸሎቱ ሥፍራ ሔደ። አቡነ ቡሩከ አምላክ ሲጸልይ በነበረበት ቦታ ጌታችን መጥቶ "ወዳጄ! የሰማዕትነትህ ቀን ደረሰ" አለው። በዚያች ዕለትም እግዚአብሔርን የማይፈራው አንድ ሽፍታ መጥቶ ቀኝ ጎኑን በጦር ወጋው፤ የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበለ። አቡነ ቡሩከ አምላክን ገዳዮቹ ጐናቸውን ከወጓቸው ቦታ ላይ ንጹሕ ጠበል ፈልቆ አሁንም ድረስ በርካታ ሕሙማንን እየፈወሰ ድንቅ ድንቅ ተኣምራት እያደረገ ይገኛል። መጠኑም በክረምት አይጨምርም በበጋም አይቀንስም፤ ይኽም እስከ ምጽአተ ክርስቶስ ድረስ እንዲሁ እንደሚቆይ ገድላቸው ይናገራል።

ጻድቁ በሕይወት ሣሉ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነጭ ፈረስ ሰጥቷቸው ስለነበር በሰማዕትነት ከማረፋቸውም በፊት "ስምህን የጠራ፣ ዝክርህን የዘከረ፣ ገድልህ የጻፈና ያጻፈ፣ በስምህ ለተራበ ያበላ፣ ለተጠማ ያጠጣ፣ ለታረዘ ያለበሰ፣ ለገዳምህ ምብዓ ዕጣን ሻማ ስንዴ ወይን የሚሰጥ፣ ቤተ ክርስቲያንህን በትጋት የሚያገለግል፣ የሚሳለም፣ በጠበልህ በእምነት የሚታጠብ፣ በሰጠሁህ በዚህ ነጭ ፈረስ በእሳት መካከል እኔ አሻግረዋለሁ" የሚል ድንቅ የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል። አባታችን አዳም "አዳም ሆይ! መሬት ነበርክና ወደ መሬት ትመለሳለህ" እንደተባለ አቡነ ቡሩከ አምላክም 63 ዓመት በገዳማቸው በደብረ ኮል፣ 62 ዓመት በደብረ ማርያምና አስቀድመው በቤተሰባቸው ዘንድ በጠቅላላ በ125 ዓመታቸው ነሐሴ 14 ቀን 1415 ዓ.ም በክፉዎች ሰዎች እጅ በሰማዕትነት ዐርፈው ከዚህች መከራና ኃጢአት ከበዛባት ዓለም ወደማታልፈው መንግሥተ ሰማያት ተሸጋገሩ።
በተቀበሩበት ቦታ በስማቸው ቤተ ክርስቲያን የታነጸ ሲሆን ከመቃብራቸው ውስጥም ፈዋሽ ጠበል ፈልቆ ብዙ ተኣምራት እያደረገ ይገኛል። ሕሙማንም ከጥንት ጀምሮ እስከአሁን ድረስ ከተለያዩ ዓለማት እየመጡ የጻድቁን መካነ መቃብር ተሳልመው ጠበሉን ጠጥተው እየተፈወሱ ይሔዳሉ።

የአቡነ ቡሩከ አምላክ ገዳም ከአስመራ በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ 73 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን ከመንደፈራ ወደ እምኒ ሓይሊ-ዓዲ ሓውያ በሚባል ቦታ ልዩ ስሙ መራጉዝ በሚባል ቦታ ይገኛል። ገዳሙ "ሙራደ ቃል ደብረ ኮል አቡነ ቡሩከ አምላክ ገዳም" ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በዱር የተሸፈነ በተፈጥሮአዊ አቀማመጡ አስደናቂ ነው። በእግር አንድ ሰዓት ተኩል የሚፈጅ የእግር መንገድ አለው። ገዳሙን የመሠረቱት አቡነ ቡሩከ አምላክ ሲሆኑ እርሳቸውም ከታላቁ ጻድቅ ከአቡነ አብሳዲ ዘደብረ ማርያም ተምረው በዚያም ሲያገለግሉ ከኖሩ በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደ መራጉዝ ሔደው ገዳማቸውን ገድመዋል። ገዳሙ ብዙ ድንቅ ድንቅ ተኣምራት የሚደረጉበት፣ በርካታ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትንና መምህራንን ያፈራ፣ የበቁ ባሕታውያንም መናኸሪያ ነበር። ከአቡነ ቡሩከ አምላክ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን  በጸሎታቸው ይማረን!። ምንጭ፦ በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን በገብረ ሥላሴ የተዘጋጀ መጽሐፍ ገጽ 125_134።
#ነሐሴ_15

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ዐሥራ አምስት በዚህች ቀን አምላክን ስለወለደች #እመቤታችን_ድንግል_ማርያም ሥጋዋን ስለመገነዝ የሐዋርያት ስብሰባ ሆነ፣ #ቅድስት_እንባ_መሪና አረፈች፣ #ቅድስት_ክርስጢና በሰማዕትነት ሞተች፣ #ቅዱስ_ለውረንዮስ በሰማዕትነት አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_እንባ_መሪና_ገዳማዊት

በዚህች ቀን የአንድ ክርስቲያናዊ ባለጸጋ ሰው ልጅ ቅድስት እንባመሪና አረፈች። የዚችም ቅድስት የእናቷ ስም ማርያም ይባላል ሕፃንም ሁና ሳለች እናቷ ሞተች አባቷም አድጋ አካለ መጠን እስከምታደርስ መልካም ትምህርትን እያስተማረ አሳደጋት።

አባቷም እሷን አጋብቶ እርሱ ወደ አንድ ገዳም ሒዶ ይመነኲስ ዘንድ ወደደ። እርሷም አባቷን ያንተን ነፍስ አድነህ የኔን ነፍስ ታጠፋለህን አለችው። እርሱም ስለ አንቺ እንዴት አደርጋለሁ ከገዳም ውስጥ ሴትን አይቀበሉምና አላት እርሷም እንዲህ አለችው አባቴ ሆይ የሴቶችን ልብስ ከላዬ አስወግደህ የወንዶችን ልብስ አልብሰኝና ከአንተ ጋራ ውሰደኝ።

የልቧንም ጽናት አይቶ የወንድ ልብስ አልብሶ ከእርሱ ጋር ወሰዳት የቀድሞ ስሟ መሪና ነበር እርሱ ግን ስሟን ለውጦ እንባመሪና ብሎ ጠራት ገንዘቡንም ሁሉ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች በተነ ልጁንም በወንድ ስም እየጠራ ከእርሱ ጋራ ወስዳት ወደ አንድ የመነኰሳት ገዳምም ደርሰው በዚያ እየተጋደሉ ኖሩ።

ከዚህም በኋላ አባቷ ታመመ ለሞትም በቀረበ ጊዜ አበ ምኔቱን ጠርቶ እርሷን ልጁን አደራ ሰጠው ስለ ገዳም አገልግሎት ከገዳም እንዳትወጣ ከዚያም በኋላ አረፈና ቀበሩት።

የከበረች እንባመሪናም ከአባቷ ተለይታ ብቻዋን ቀረች በጾም በጸሎት በስግደት ከቀድሞዋ ዕጥፍ አድርጋ ተጋድሎ ጀመረች።

ከዚህም በኋላ የገዳሙ መነኰሳት ይህ ወጣት መነኰስ ከእኛ ጋራ ለገዳሙ አገልግሎት ለምን አይወጣም ብለው ተቃወሟት እንዲህም አበምኔቱን በአሰጨነቁት ጊዜ ከእርሳቸው ጋራ ሰደዳት።

ለመነኰሳቱ ቀለብ የሚሆነውን የገዳሙን እህል የሚሰበስብ አንድ ሰው አለ መነኰሳቱም በሚወጡ ጊዜ ከእርሱ ዘንድ አድረው እህላቸውን ይጭናሉ የእንግዳ መቀበያ ቤትም አለው በዚያ ያድራሉ።

በዚያችም ዕለት ከጐረቤቱ አንድ ጐልማሳ ሰው መጥቶ በዚህ ሰው ቤት አድሮ የልጁን ድንግልና አጠፋ ። እንድህም አላት አባትሽ ማን ደፈረሽ ብሎ የጠየቀሽ እንደሆነ አባ እንባመሪና የሚሉት ወጣት መነኰሴ ደፈረኝ በይው።

በፀነሰችም ጊዜ አባቷ አወቀ ማነው የደፈረሽ ብሎ ጠየቃት እርሷም እንዲህ ብላ መለሰችለት አባ እንባመሪና የሚሉት ወጣት መነኵሴ ደፈረኝ።

ያን ጊዜም ተነሥቶ ወደዚያ ገዳም ሒዶ መነኰሳቱን ይረግማቸው ጀመረ። አበምኔቱም ሰምቶ ወጣና መነኰሳቱን ለምን ትረግማቸዋለህ #እግዚአብሔርን አትፈራውምን አለው እርሱም በልጁ ላይ የሆነውን ነገረው አንዲህም አለው አባ እንባመሪና የሚሉት ወጣት መነኰሴ የልጄን ድንግልና ስለደፈረ ነው አለው።

አበ ምኔቱም በሰማ ጊዜ እውነት መሰለውና እጅግ አዘነ ሰውየውንም እንዲህ ብሎ ለመነው በአንድ ሰው በደል ንጹሐን የሆኑ መነኰሳትን በሕዝባውያን ፊት አታዋርዳቸው ይህንንም ነገር ሠውር።

ከዚህም በኋላ ቅድስት እንባመሪናን ጠርቶ ይገሥጻትና ይረግማት ጀመረ እርሷም ስለምን እንደሚረግማት አላወቀችም ነበር በአወቀችም ጊዜ ከእግሩ በታች ወደቃ እኔ ወጣት ነኝና በደሌን ይቅር በለኝ ብላ ለመነችው እርሱም አጅግ ተቆጥቶ ከገዳሙ አባረራት እርሷም ከገዳም ውጭ ሁና እየተጋደለች ኖረች።

ያቺም ልጅ በወለደች ጊዜ የልጅቷ አባት ሕፃኑን አምጥቶ ለቅድስት እንባመሪና ሰጣት እርሷም #እግዚአብሔርን እያመሰገነች ተቀበለችው በላሞችና በበጎች ጠባቂዎች ዘንድ ለሕፃኑ ወተትን እየለመነች መዞርን ጀመረች እንደዚህም አድርጋ ሕፃኑን አሳደገችው።

ከሦስት ዓመትም በኋላ መነኰሳቱ ተሰብስበው አባ ምኔቱን ለመኑት አባ እንባመሪናን ይቅርታ አድርጎለት ወደ ገዳሙ ይመልሰው ዘንድ እርሱም ልመናቸውን ተቀብሎ ከመነኰሳቱ ጋራ ቀላቀላት ይኸውም ከባድ ቀኖና ከሰጣት በኋላ ነው።

ከዚህም በኋላ ጭንቅ የሆኑ ሥራዎችን ትሠራ ጀመረች የመነኰሳቱንም ቤቶች ጠርጋ ተሸክማ ወስዳ ከገዳሙ ውጭ ትጥለዋለች ውኃንም ቀድታ ታጠጣቸዋለች ምግባቸውንም ታዘጋጃለች። ያም ሕፃን አደገ የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርት ተምሮ መነኰሰ።

አርባ ዓመትም ሲፈጸም ሦስት ቀኖች ያህል ታማ በሰላም አረፈች ደወልንም ደውለው መነኰሳቱ ሁሉ ተሰበሰቡ ሊገንዙም ገብተው ልብሶቿን በገለጡ ጊዜ እርሷ ሴት እንደ ሆነች አግኝተዋት ደነገጡ መሪር እንባንም አለቀሱ አበ ምኔቱም በመጣም ጊዜ ያለ በደሏ ከባድ ንስሐ ቀኖና ስለ ሰጣትና በእርሷ ላይ ስለ አደረገው ተግሣጽ መሪር ዕንባን አለቀሰ።

ከዚህም በኋላ መልእክተኞችን ልኮ የዚያችን የሐሰተኛ ልጅ አባቷን አስመጥቶ እንባመሪና ሴት እንደሆነች ነገረው ።

ከዚህም በኋላ በድኗን ተሸክመው ይቅር ይበለን የሚል ቃል ከበድኗ እስከ ሰሙ ድረስ አቤቱ #ክርስቶስ ማረን እያሉ ጸለዩ ከዚያም በኋላ በዝማሬና በማኅሌት ከብዙ ልቅሶ ጋር ገነዟት ከሥጋዋም ተባርከው ቀበሩዋት።

እነሆ #እግዚአብሔር ክፉ ሰይጣንን አዝዞት ያቺን ሐሰተኛ ሴት ልጅና ድንግልናዋን የደፈረውን ጉልማሳ ያዛቸው እያጓተተም አሠቃይቶ ይቀጣቸው ጀመረ ወደ ቅድስት እንባመሪና መቃብር ሔደው ኃጢአታቸውን በሕዝቡ ሁሉ ፊት እስከሚአምኑ እጅግ አሠቃያቸው ። ከመቃብርዋም ቁጥር የሌላቸው ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት እንባመሪና ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ክርስጢና

በዚህች ቀን የመኰንን ርባኖስ ልጅ ቅድስት ክርስጢና በሰማዕትነት ሞተች። አባቷ ጣዖታትን የሚያመልክ ነው። እርሷም አባቷ እንደ አስተማራት ታጥናቸው ነበር።

በአንዲት ዕለትም አስባ ተመራመረች በልቧም #እግዚአብሔርን መፍራት አደረባት ተነሥታም ፊቷን ወደ ምሥራቅ መልሳ ቆመች የምትጓዝበትንም የሕይወት መንገድ ይመራት ዘንድ ጸለየች #መንፈስ_ቅዱስም አንድነቱንና ሦስትነቱን ገለጠላት።

አባቷም በመጣ ጊዜ ልጄ እንዴት አለሽ አላት በክብር ባለቤት በ #ክርስቶስ ሕይወት አለሁ አለችው። አባቷም ሰምቶ ደነገጠ ልብሽን ምን ለወጠው አላት እርሷም ከሰማይ አምላክ ተማረኩ አለችው። ከዚህም በኋላ አባቷ እያዘነ ሔደ።

እርሷም ተነሥታ ወደ #እዚአብሔር ጸለየች ያን ጊዜ የ #እግዚአብሔር መልአክ መጥቶ እንዲህ አላት በርቺ ከሦስት መኳንንት ትሠቃዪ ዘንድ አለሽ አዳኝ በሆነ በ #ጌታችን_ክርስቶስ #መስቀልም አተማት ሰማያዊ ኅብስትንም ሰጣት።

ከዚህም በኋላ ተነሥታ ጣዖታቱ ወደ አሉበት ቤት ገብታ ቀጠቀጠቻቸው። አባቷም አይቶ እጅግ ተቆጣ ልጁንም ይገርፏት ዘንድ አዘዘ ከሥጋዋም ስለ ደም ፈንታ ማር ወጣ። ሁለተኛም በብረት ዐልጋ ላይ አስተኝተው ከበታችዋ እሳትን እንዲያነዱ አዘዘ እርሷን የነካት የለም ግን ከአረማውያን ብዙዎችን አቃጠለ።

ዳግመኛም በታንኳ አድርገው ወደ ባሕር ይጥሏት ዘንድ አዘዘ በጸለየችንም ጊዜ የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ከመላእክት ጋራ መጥቶ ራሱ አጠመቃት ሚካኤልም በእሳት ጉጠት የክብር ባለቤት የሆነ የ #ክርስቶስን ሥጋና ደም አቀበላት ከጣዖታት እድፍም አነጻት በዚያችም ሌሊት አባቷ ርባኖስ ሞተ ። ስሙ ድዮስ የሚባል ሌላ መኰንን መጣ ቅድስት ክርስጢናን አምጥተው ራቁቷን ሰቅለው ከበታችዋ እሳትን እንዲያነዱ አዘዘ ። ሴቶችም ራቁትነቷን አይተው መኰንኑን ረገሙት እነርሱም በሰይፍ
አስቆረጣቸው እርሷን ግን ምንም ምን አልነካትም ሕዝቡም ይህን ተአምር አይተው የክብር ባለቤት በሆነ በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሠላሳ ሺህ ዐሥራ ሁለት ሰዎች አምነው በሰማዐትነት ሞቱ ከሀዲው መኰንን ድዮስም በድንገት ሞተ።

ሦስተኛም መኰንን መጣ የከበረች ክርስጢናንም ይዞ ለአማልክት ትሠዋ ዘንድ አባበለት እርሷም እንዲህ አለችው። አንተና አማልክቶችህ ለዘላለም ወደ ማይጠፋ የገሀነም እሳት ትወርዳላችሁ። እጅግም ተቆጥቶ ወደ እሳት ማንደጃ ውስጥ እንዲጨምርዋት አዘዘ ምንም የነካት የለም።

ዳግመኛም ለአራዊት ይጥሏት ዘንድ አዘዘ እነርሱም የእግርዋን ትቢያ ላሱ እባቦችንም የሚያጠምደውን ነከሱትና ወዲያውኑ ሞተ።

ሁለተኛም ምላሷንና ጡቶቿን ቆረጡ የምላሷንም ቁራጭ አንሥታ ከመኰንኑ ዐይኖች ላይ ጣለችውና ዐይኖቹን አሳወረችው ። ቁጣውንም ተመልቶ ለእባቦች እንዲጥሏት አዘዘ አንዲቷም እባብ ልቧን ነደፈቻት አንዲቱ ደግሞ ጐኗን እንዲህም የምስክርነቷን ተጋድሎ ፈጸመች ነፍሷንም አሳልፋ የድል አክሊልን ተቀዳጀች ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስቷ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ለውረንዮስ_ሰማዕት

በዚህችም ዕለት በንጉሥ ዳስዮስ ቄሣር ዘመን ቅዱስ ለውረንዮስ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ቅዱስ በሃይማኖት የጸና ነው የክብር ባለቤት ስለ ሆነ ስለ #ክርስቶስ ሃይማኖት ሊቀ ዲቁና ተሹሞ የሊቀ ጵጵስናውን ገንዘብ ይጠብቅ ነበር።

ንጉሥ ስለርሱ ሰምቶ አምጥተው ከወህኒ ቤት እንዲአስገቡት አዘዘ በአስገቡትም ጊዜ በዚያ ዕውር ሰውን አገኘና አይኖችህ ይገለጡ ዘንድ በሕያው #እግዚአብሔር ልጅ አምነህ በስሙ ትጠመቃለህን አለው ዕውሩም አዎን ጌታዬ አለ።

ያን ጊዜም በውኃው ላይ ጸልዮ በ #አብ#ወልድ#መንፈስ_ቅዱስ ስም አጠመቀው ያን ጊዜም አይኖቹ ተገለጠ። እንዲህም ብሎ ጮኸ በአገልጋዩ ለውረንዮስ ጸሎት ዐይኖቼን የገለጠ የክብር ባለቤት #ጌታ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ይክበር ይመስገን ብሎ ጮኸ። ይህንንም ድንቅ አይተው ብዙዎች አመኑ።

ንጉሡም በሰማ ጊዜ የከበረ ለውረንዮስን ወደርሱ ያቀርቡት ዘንድ አዘዘ በአቀረቡትም ጊዜ ለአማልክት እንዲሰዋ አግባባው እምቢ ባለውም ጊዜ ጥርሶቹን በደንጊያ ሰበሩ ልብሶቹንም ገፈው በብረት ዐልጋ ላይ አስተኝተው ሥጋው እስከሚቀልጥ ከበታቹ እሳትን አነደዱ።

እርሱም ነፍሱን እስከአሳለፈ ድረስ ወደ ፈጣሪው ይጸልይ ነበር። መላእክትም ሃሌ ሉያ እያሉ ተቀብለው ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት አስገቡት።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_15)
2024/09/22 04:56:21
Back to Top
HTML Embed Code: