Telegram Web Link
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ሐምሌ_22_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ቆሮ 12
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ትምክህት የሚያስፈልግ ነው፤ አይጠቅምም ነገር ግን ከጌታ ወዳለው ራእይና መገለጥ እመጣለሁ።
² ሰውን በክርስቶስ አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም ወይም ከሥጋ ውጭ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ እንዲህ ያለው ሰው ከአሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ።
³ እንዲህ ያለውንም ሰው አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ ወይም ያለ ሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤
⁴ ወደ ገነት ተነጠቀ፥ ሰውም ሊናገር የማይገባውን የማይነገረውን ቃል ሰማ።
⁵ እንደዚህ ስላለው እመካለሁ፥ ስለ ራሴ ግን ከድካሜ በቀር አልመካም።
⁶ ልመካ ብወድስ ሞኝ አልሆንም፥ እውነትን እላለሁና፤ ነገር ግን ማንም ከሚያይ ከእኔም ከሚሰማ የምበልጥ አድርጎ እንዳይቆጥረኝ ትቼአለሁ።
⁷ ስለዚህም በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ፥ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ፤ ይኸውም እንዳልታበይ ነው።
⁸ ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ።
⁹ እርሱም፦ ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ።
¹⁰ ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁶-⁷ በዚህም እጅግ ደስ ይላችኋል፥ ነገር ግን በእሳት ምንም ቢፈተን ከሚጠፋው ወርቅ ይልቅ አብልጦ የሚከብር የተፈተነ እምነታችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ፥ ለምስጋናና ለክብር ለውዳሴም ይገኝ ዘንድ አሁን ለጥቂት ጊዜ ቢያስፈልግ በልዩ ልዩ ፈተና አዝናችኋል።
⁸-⁹ እርሱንም ሳታዩት ትወዱታላችሁ፤ አሁንም ምንም ባታዩት በእርሱ አምናችሁ፥ የእምነታችሁን ፍፃሜ እርሱም የነፍሳችሁን መዳን እየተቀበላችሁ፥ በማይነገርና ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ይላችኋል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁶ በዚያን ጊዜ አዛዡ ከሎሌዎች ጋር ሄዶ አመጣቸው፥ በኃይል ግን አይደለም፤ ሕዝቡ እንዳይወግሩአቸው ይፈሩ ነበርና።
²⁷ አምጥተውም በሸንጎ አቆሙአቸው።
²⁸ ሊቀ ካህናቱም፦ በዚህ ስም እንዳታስተምሩ አጥብቀን አላዘዝናችሁምን? እነሆም፥ ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞልታችኋል፤ የዚያንም ሰው ደም በእኛ ታመጡብን ዘንድ ታስባላችሁ ብሎ ጠየቃቸው።
²⁹ ጴጥሮስና ሐዋርያትም መልሰው አሉ፦ ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል።
³⁰ እናንተ በእንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን የአባቶቻችን አምላክ አስነሣው፤
³¹ ይህን እግዚአብሔር፥ ለእስራኤል ንስሐን የኃጢአትንም ስርየት ይሰጥ ዘንድ፥ ራስም መድኃኒትም አድርጎ በቀኙ ከፍ ከፍ አደረገው።
³² እኛም ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን፥ ደግሞም እግዚአብሔር ለሚታዘዙት የሰጠው መንፈስ ቅዱስ ምስክር ነው።
³³ እነርሱም ሲሰሙ በጣም ተቈጡ ሊገድሉአቸውም አሰቡ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሐምሌ_22_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
   "ወኢይትኀበር ውስተ ማኅበሮሙ ዘደም። ወኢይዜከር አስማቲሆሙ በአፉየ። እግዚአብሔር መክፈልተ ርስትየ ወጽዋዕየ"። መዝ 15፥4-5።
"ወደ ሌላ ለሚፋጠኑት መከራቸው ይበዛል፤ የቍርባናቸውን ደም እኔ አላፈስሰውም፥ ስማቸውንም በከንፈሬ አልጠራም።
እግዚአብሔር የርስቴ እድል ፈንታና ጽዋዬ ነው፥ ዕጣዬንም የምታጠና አንተ ነህ"። መዝ 15፥4-5።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሐምሌ_22_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማርቆስ 13
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁴ ነገር ግን በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኵሰት በማይገባው ስፍራ ቆሞ ብታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፥ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፥
¹⁵ በሰገነትም ያለ ወደ ቤት አይውረድ ከቤቱም አንዳች ይወስድ ዘንድ አይግባ፥
¹⁶ በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ።
¹⁷ በዚያን ወራትም ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው።
¹⁸ ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤
¹⁹ በዚያን ወራት እግዚአብሔር ከፈጠረው ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያልሆነ ደግሞም የማይሆን የመከራ ዓይነት ይሆናልና።
²⁰ ጌታስ ወራቶቹን ባያሳጥር፥ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም፤ ነገር ግን ስለ መረጣቸው ምርጦች ወራቶቹን አሳጠረ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ 
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ባስልዮስ ወይም የ #ቅዱስ_ያዕቆብ_ዘሥሩግ ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ዑራኤል በዓል፣ የአቡነ ጴጥሮስ የዕረፍት በዓል፣ የሰማዕት ቅዱስ መቃርስ ዕረፍት በዓል፣ የሰማዕት ቅዱስ ለውንትዮስ ዕረፍት በዓልና አበ መነኮሳት የአባ እንጦንስ በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ሐምሌ_23

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሐምሌ ሃያ ሦስት በዚች ቀን #ቅድስት_መሪና ሰማዕት ሆነች፣ #ቅዱስ_ለንጊኖስ ሰማዕት ሆነ፣ የመናገሻ ገነተ ጽጌ #ቅዱስ_ጊዮርጊስ_ቤተ_ክርስቲያን (አራዳ ጊዮርጊስ) #ቅዳሴ_ቤቱ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_መሪና

ሐምሌ ሃያ ሦስት በዚች ቀን ቅድስት መሪና ሰማዕት ሆነች። የዚችም ቅድስት የአባቷ ስም ዳኬዎስ ነበር እርሱም በአንጾኪያ ሀገር ለጣዖታት ካህናት አለቃ ነበር ያን ጊዜ ንጉሡም ከሀዲው ዳኬዎስ ነበር።

አምስት ዓመትም በሆናት ጊዜ እናቷ ሞተች አባቷም ከከተማ ውጭ ለምትኖር ሞግዚት ሰጣት እርሷም ክርስቲያናዊት ነበረች የ #ክርስቶስ የሆነ የሃይማኖት ትምህርትን ሁሉ አስተማረቻት። ዐሥራ አምስት ዓመትም በሆናት ጊዜ አባቷ ሞተ።

ከዚህም በኋላ ሰዎች የሰማዕታትን ተጋድሏቸውንና መከራቸውን ሲናገሩ ሰምታ የ #ጌታ_ክርስቶስ ፍቅር በልቧ አደረ በሰማዕትነት መሞትንም ፈልጋ ሔደች።

በዚያን ጊዜም ከሀዲ መኰንን ወደዚያች አገር ደረሰ እርሷንም አይቶ ወደርሱ አስመጣትና ከወዴት ነሽ አላት #ክብር_ይግባውና_ከጌታ_ኢየሱስ ሰዎች ወገን ነኝ ስሜም መሪና ነው አለችው። ደም ግባቷንና ላሕይዋንም አይቶ መታገሥ ተሳነው እሺ ትለው ዘንድ በብዙ ነገር አባበላት። እርሷ ግን ረገመችው የረከሱ አማልክቶቹንም ረገመች።

ያን ጊዜም በብረት ዘንጎች ይደበድቧት ዘንድ ደሟ እንደ ውኃ እስኪፈስ ሕዋሳቷን ይቆራርጡ ዘንድ አዘዘ። ያን ጊዜም ወደ ጌታ #እግዚአብሔር ጸለየች የመላእክት አለቃ #ቅዱስ_ሚካኤልም መጥቶ አዳናት። ሁለተኛም ወደ ወህኒ ቤት ያስገቧት ዘንድ አዘዘ #ጌታችንም ወደ ሰማይ አውጥቶ የቅዱሳን ሰማዕታትንና የጻድቃንን ማደሪያዎች አሳይቶ ወደ ቦታዋ መለሳት። በማግሥቱም ሥጋዋን በመጋዝ እንዲሠነጥቁ ጐኖቿንም እንዲሰነጣጥቁና በእሥር ቤት እንዲጥሏት አዘዘ ያን ጊዜም የመላእክት አለቃ #ቅዱስ_ሚካኤል መጥቶ አዳናት።

በወህኒ ቤቱ ውስጥም ቁማ ስትጸልይ እጅግ የሚያስፈራ ታላቅ ዘንዶ ወደ ርሷ መጣ በአየችውም ጊዜ ደነገጠች ሰውነቷ ሁሉ ተንቀጠቀጠ መናገርም ተሳናት። ያን ጊዜም እጆቿ በ #መስቀል ምልክት አምሳል እንደተዘረጉ በልቧም ስትጸልይ ወደርሷ ቀርቦ ዋጣት። ያን ጊዜም ሆዱ ተሠንጥቆ ያለ ጉዳት ወጣች #እግዚአብሔርንም አመሰገነችው።

ሁለተኛም በጥቁር ሰው አምሳል ሰይጣንን አየችው እጆቹም በጉልበቶቹ ላይ ተጨብጠው ነበር። ፊቷንም በ #መስቀል ምልክት አማትባ በራሱ ጠጉር ይዛ ደበደበችው። በእግሮቿም ረገጠችው ያን ጊዜም #ክብር_ይግባውና_የጌታ_ክርስቶስ #ዕፀ_መስቀል ተገለጠላት በላዩም ነጭ ርግብ ተቀምጣ እንዲህ ብላ አነጋገረቻት መሪና ሆይ የ #መንፈስ_ቅዱስን የጸጋ አረቦን ተቀብለሻልና ደስ ይበልሽ።

በማግሥቱም መኰንኑ ልብሷን አራቁተው ዘቅዝቀው ሰቅለው እንዲአቃጥሏት ደግሞም ውኃ ከአፈሉበት ጋን ውስጥ እንዲጨምሩዋት አዘዘ። በውስጡም ሁና ስትጸልይ ከሰማይ ርግብ መጣ በአፉም ውስጥ የወርቅ አክሊል ነበር ማሠሪያዋንም ፈትቶ በ #አብ#ወልድ#መንፈስ_ቅዱስ ስም ሦስት ጊዜ አጠመቃት #እግዚአብሔርንም እያመሰገነች ከውኃው ውስጥ ወጣች።

መኰንኑም እንደ ዳነች በአየ ጊዜ ራሷን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ። ወደ ሰማዕትነቱ ቦታም በደረሰች ጊዜ ነፍሷን በፍቅር ይቀበል ዘንድ ወደ #ጌታችን ጸለየች። #ክብር_ይግባውና_ጌታችንም ተገለጠላት ስሟን ለሚጠራ መታሰቢያዋንም ለሚያደርግ ገድሏንም ለሚጽፍ ወይም ለሚያነበውና ለሚሰማው ኃጢአቱን እንዲአስተሠርይለት ለርሷም ርሱን እንዲሰጣት ቃል ኪዳን ሰጣት።

ከዚህም በኋላ ራሷን በሰይፍ ቆረጡ ከእርሷም ብዙ ተአምር ተገለጠ ዕውራን አይተዋልና፣ ሐንካሶች በትክክል ሔደዋልና፣ ደንቆሮዎችም ሰምተዋልና፣ ዲዳዎችም ተናግረዋልና ቁጥር የሌላቸው ብዙ ሰዎችም #ክብር_ይግባውና_በጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አመኑ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት መሪና ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ለንጊኖስ_ሰማዕት

በዚችም ቀን ከቀጰዶቅያ አገር ለንጊኖስ ሰማዕት ሆነ። ይህም ቅዱስ ከጲላጦስ ጭፍሮች ውስጥ ነበር #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስለ ዓለም ደኅንነት መከራ እንዲቀበል የፈቀደበት ሰዓት በደረሰ ጊዜ በእርሱ ላይ የፈለጉትን ያደርጉ ዘንድ ለዐመፀኞች ፈቅዶላቸው ነበር። ይህም ለንጊኖስ #ጌታን ይሰቅሉት ዘንድ ጲላጦስ ከአዘዛቸው ወታደሮች ውስጥ ነበር።

በመስቀል ላይ ከሞተ በኋላ #ጌታችንን የቀኝ ጐኑን ወጋው ከጐኑም ደምና ውኃ ፈሰሰ። ይህንንም አይቶ እጅግ አደነቀ ከዚህም በፊት ፀሐይ እንደጨለመ፣ ጨረቃ ደም እንደሆነ፣ ዐለቱም እንደተሠነጠቀ፣ ሙታንም እንደተነሡ አይቶ ነበር።

#ጌታችንም በተነሣ ጊዜ ስለ ትንሣኤው የሆነውን ሰምቶ ይህን ምሥጢር ይገልጽለት ዘንድ ወደ #እግዚአብሔር ጸለየ። ሐዋርያው ጴጥሮስንም ላከለት እርሱም ነቢያት ስለ #ጌታችን፣ ስለ መከራው፣ ስለ መሰቀሉ፣ ስለ መሞቱ፣ ስለ መነሣቱ፣ ስለ ዕርገቱም ትንቢት እንደተናገሩ ነገረው። እርሱም ከቅድስት #ድንግል በሥጋ ተወልዶ ዓለምን ለማዳን የመጣ የሕያው #እግዚአብሔር ልጅ #ክርስቶስ እንደሆነ አስረዳው።

ያን ጊዜም በቅዱስ ጴጥሮስ ቃል አመነ የምድራዊ ንጉሥ አገልግሎትንም ትቶ ወደ ቀጰዶቅያ ሔደ በውስጧም ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_በኢየሱስ_ክርስቶስ ስም እንደ ሐዋርያት ሰበከ።

አይሁድም በጠላትነት ተነሡበት በመሳፍንትም ዘንድ ከሰሱት በላዩም የሐሰት ምስክር አስነሡበት ስለዚህም ራሱን በሰይፍ አስቆረጡት የሰማዕትነትንም አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት አፄ ምኒልክ በአደዋ ጦርነት ጊዜ ለረዳቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ከድሉ ከተመለሱ በኋላ በአዲስ አበባ መሐል ከተማ ላይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ቤተክርስቲያን አሠሩ ስሟንም ገነተ ጽጌ ብለው ሰየሟት የባረኳትም ሊቀ ጳጳሱ ግብፃዊው አቡነ ማቴዎስ ናቸው፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት የቅዱስ ጊዮርጊስ ልመናው አማላጅነቱ ከእኛ ጋር ይሁን አሜን!!! ተአምረ ጊዮርጊስ ተአምር 17 ላይ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ሐምሌ_23)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ሐምሌ_23_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ቆሮ 9
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁵ እንግዲህ እንደ በረከት ሆኖ ከስስት የማይሆን ይህ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ አስቀድመው ወደ እናንተ መጥተው፥ አስቀድማችሁ ተስፋ የሰጣችሁትን በረከት አስቀድመው እንዲፈጽሙ ወንድሞችን እለምን ዘንድ እንዲያስፈልገኝ አሰብሁ።
⁶ ይህንም እላለሁ፦ በጥቂት የሚዘራ በጥቂት ደግሞ ያጭዳል፥ በበረከትም የሚዘራ በበረከት ደግሞ ያጭዳል።
⁷ እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፥ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም።
⁸-⁹ በተነ፥ ለምስኪኖች ሰጠ፥ ጽድቁ ለዘላለም ይኖራል ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ እግዚአብሔር፥ ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ፥ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል።
¹⁰ ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል ያበረክትላችሁማል፥ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል፤
¹¹ በእኛ በኩል ለእግዚአብሔር የምስጋና ምክንያት የሚሆነውን ልግስና ሁሉ እንድታሳዩ በሁሉ ነገር ባለ ጠጎች ትሆናላችሁ።
¹² የዚህ ረድኤት አገልግሎት ለቅዱሳን የሚጎድላቸውን በሙሉ የሚሰጥ ብቻ አይደለምና፥ ነገር ግን ደግሞ በብዙ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይበዛል፤
¹³ በዚህ አገልግሎት ስለ ተፈተናችሁ፥ በክርስቶስ ወንጌል በማመናችሁ ስለሚሆን መታዘዝ እነርሱንና ሁሉንም ስለምትረዱበት ልግስና እግዚአብሔርን ያከብራሉ፥
¹⁴ ራሳቸውም ስለ እናንተ ሲያማልዱ፥ በእናንተ ላይ ከሚሆነው ከሚበልጠው ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሣ ይናፍቁአችኋል።
¹⁵ ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ያዕቆብ 2
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁴ ወንድሞቼ ሆይ፥ እምነት አለኝ የሚል፥ ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል? እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን?
¹⁵ ወንድም ወይም እኅት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብንም ቢያጡ፥
¹⁶ ከእናንተ አንዱም፦ በደኅና ሂዱ፥ እሳት ሙቁ፥ ጥገቡም ቢላቸው ለሰውነት ግን የሚያስፈልጉትን ባትሰጡአቸው ምን ይጠቅማቸዋል?
¹⁷ እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው።
¹⁸ ነገር ግን አንድ ሰው፦ አንተ እምነት አለህ እኔም ሥራ አለኝ፤ እምነትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፥ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ ይላል።
¹⁹ እግዚአብሔር አንድ እንደ ሆነ አንተ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ፤ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል።
²⁰ አንተ ከንቱ ሰው፥ እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን?
²¹ አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን?
²² እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደ ነበረ፥ በሥራም እምነት እንደ ተፈጸመ ትመለከታለህን?
²³ መጽሐፍም፦ አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት ያለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ።
²⁴ ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ።
²⁵ እንደዚሁም ጋለሞታይቱ ረዓብ ደግሞ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን?
²⁶ ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 16
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹³ በሰንበት ቀንም ከከተማው በር ውጭ የጸሎት ስፍራ በዚያ መሆኑን ስላሰብን ወደ ወንዝ አጠገብ ወጣን፤ ተቀምጠንም ለተሰበሰቡት ሴቶች ተናገርን።
¹⁴ ከትያጥሮን ከተማም የመጣች ቀይ ሐር ሻጭ እግዚአብሔርን የምታመልክ ልድያ የሚሉአት አንዲት ሴት ትሰማ ነበረች፤ ጳውሎስም የሚናገረውን ታዳምጥ ዘንድ ጌታ ልብዋን ከፈተላት።
¹⁵ እርስዋም ከቤተ ሰዎችዋ ጋር ከተጠመቀች በኋላ፦ በጌታ የማምን እንድሆን ከፈረዳችሁልኝ፥ ወደ ቤቴ ገብታችሁ ኑሩ ብላ ለመነችን፤ በግድም አለችን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሐምሌ_23_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ኢይቀሥፍ ወትረ ወኢይትመዓዕ ዘልፈ። አኮ በከመ ኃጢአትነ ዘገብረ ለነ። ወኢፈደየነ በከመ አበሳነ"። መዝ 102፥9-10 ።
"ሁልጊዜም አይቀሥፍም፥ ለዘላለምም አይቈጣም። እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፥ እንደ በደላችንም አልከፈለንም"። መዝ 102፥9-10 ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሐምሌ_23_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዮሐንስ 19
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³¹ አይሁድም የማዘጋጀት ቀን ስለ ሆነ ያ ሰንበት ትልቅ ነበረና ሥጋቸው በሰንበት በመስቀል ላይ እንዳይኖር፥ ጭናቸውን ሰብረው እንዲያወርዱአቸው ጲላጦስን ለመኑት።
³² ጭፍሮችም መጥተው የፊተኛውን ጭን ከእርሱም ጋር የተሰቀለውን የሌላውን ጭን ሰበሩ፤
³³ ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ግን እርሱ ፈጽሞ እንደ ሞተ አይተው ጭኑን አልሰበሩም፤
³⁴ ነገር ግን ከጭፍሮች አንዱ ጎኑን በጦር ወጋው፤ ወዲያውም ደምና ውኃ ወጣ።
³⁵ ያየውም መስክሮአል፤ ምስክሩም እውነት ነው፤ እናንተም ደግሞ ታምኑ ዘንድ እርሱ እውነት እንዲናገር ያውቃል።
³⁶ ይህ የሆነ፦ ከእርሱ አጥንት አይሰበርም የሚል የመጽሐፉ ቃል እንዲፈጸም ነው።
³⁷ ደግሞም ሌላው መጽሐፍ፦ የወጉትን ያዩታል ይላል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ ወይም #እግዚእነ ቅዳሴ ነው። መልካም በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ሐምሌ_24

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሐምሌ ሃያ አራት በዚች ቀን ከንሒሳ ከተማ #ቅዱስ_አባ_ኖብ ሰማዕት ሆኖ ሞተ፣ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_አባ_ስምዖን አረፈ፣ ኢትዮጵያዊው ጻድቅ ጣና ክብራን ገብርኤል ገዳምን የመሠረቱት #አቡነ_ዘዮሐንስ_ጻድቅ ዕረፍታቸው ነው፣ #አቡነ_ተወልደ_መድኅን_ ዕረፍታቸው ነው፣ #ባሕታዊ_አባ_ሄላ_ድንግል_ የበዐላቸው መታሰቢያ ነው፣ #አቡነ_ጊዮርጊስ_ዘመንበረ ኢትዮጵያ የበዐላቸው መታሰቢያ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ኖብ

ሐምሌ ሃያ አራት በዚች ቀን ከደቡባዊ ግብጽ ከታችኛው ምድር አውራጃ ከንሒሳ ከተማ ቅዱስ አባ ኖብ ሰማዕት ሆኖ ሞተ።

የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ ቅዱሳን ንጹሐንና የሚራሩ ነበሩ። ይህንንም ቅዱስ ኖብን በወለዱት ጊዜ ዐሥራ ሁለት ዓመት እስኪሆነው ፈሪሀ #እግዚአብሔርን እያስተማሩ አሳደጉት። ቤተ ክርስቲያንን የመጻሕፍትን ቃል መስማትንና መማርን የሚወድ ሆነ።

ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_በኢየሱስ_ክርስቶስ ስም የክርስቲያን ወገኖችን ዲዮቅልጥያኖስ በአሠቃያቸው ጊዜ ይህ ቅዱስ ደሙን ስለ #ጌታችን ሊአፈስ አሰበ ያን ጊዜም ወደ ቤተ ክርስቲያን ገባ ቄሱንም ምእመናንን እንዲህ እያለ ሲያስተምራቸውና ሲያበረታቸው ‘’ጣዖታትን ከምታመልኩ ክብር ይግባውና ስለ መድኃኒታችን ስለ ክርስቶስ ነፍሳችሁን ለሞት አሳልፋችሁ ብትሰጡ ለእናንተ መልካም ነው’’ ሲላቸው ሰማው።

ይህም ቅዱስ እያዘነና እየተከዘ ወደ ቤቱ ተመለሰ አባቱም የተወለትን ወርቁንና ብሩን ልብሶችን ሁሉ ተመልክቶ እንዲህ አለ ሁሉ ነገር የዚህ ዓለም ፍላጎቱም ሁሉ እንደ ሚያልፍ እነሆ ተጽፏል። ከዚህም በኋላ ገንዘቡን ሁሉ ወስዶ ለድኆችና ለችግረኞች ሰጠ።

ከዚህም በኋላ ወደ ሀገረ ገምኑዲ ሔደ በእግሩም ሲጓዝ በባሕሩ ዳርቻ ሉስዮስ የሚባለውን መኰንን አገኘው በፊቱም ቁሞ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስም ታመነ። መኰንኑም ታላቅ ሥቃይን አሠቃየው። ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለት በእርሱ ላይም የሚደርሰውን ሁሉ ነግሮት አጽናናው።

ከዚህም በኋላ መኰንኑ ወደ ሰሜን አገር ሲጓዝ የከበረ ኖብን ከእርሱ ጋራ በመርከብ ወሰደው በመርከቡም ምሰሶ ላይ ዘቅዝቆ ሰቀለው መኰንኑም ሊበላና ሊጠጣ ተቀመጠ በመኰንኑም እጅ የነበረው ጽዋ ወዲያውኑ እንደ ደንጊያ ሆነ የወታደሮቹም ዐይኖቻቸው ታወሩ የእግዚአብሔር መልአክም ከሰማይ ወርዶ አባ ኖብን ፈትቶ ከተሰቀለበት አወረደው በአፍንጫውና በአፉ የወረደውንም ደሙን አሻሸለት።

ከዚህ በኋላም መልካም ነፋስ ነፍሶ መርከቢቱ ተጓዘች። ወደ አትሪብ ከተማም ደረሱ ወታደሮችም ይህን ድንቅ ተአምር አይተው ትጥቃቸውን ፈተው በመኰንኑ ፊት ጣሉ። ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስም ታመኑ ሰማዕታትም ሆነው ራሳቸውን ቆረጡአቸው የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበሉ።

መኰንኑም በአትሪብ ከተማ ቅዱስ አባ ኖብን ታላቅ ሥቃይን አሠቃየው በብረት ዐልጋ ላይም አስተኝተው ከበታቹ እሳትን አነደዱ በጸለየ ጊዜም እግዚአብሔር ከእሳት አዳነው። ከዚህም በኋላ በመጋዝ መገዙት ሕዋሳቱንም ቆራረጡ የእግዚአብሔር መልአክም ወርዶ አዳነው ያለ ጉዳትም በጤና አስነሣው።

ከዚህም በኋላ ወደ እስክንድርያ ከተማ ወሰዱት በዚያም ብዙ አሠቃዩት በላዩም እባቦችን ሰደዱ ግን አልቀረቡትም ከእባቦችም አንዱ ሒዶ በመኰንኑ አንገት ተጠመጠመ ያስጥሉትም ዘንድ ሟርተኞቹን አዘዛቸው ግን አልተቻላቸውም ከዚህም በኋላ ያድነው ዘንድ ቅዱስ አባ ኖብን ለመነው ቅዱሱም ከይሲውን ትቶት ከአንገቱ እንዲወርድ አዘዘው።

መኰንኑም ሁለተኛ በእሳት እንዲአቃጥሉት ሟርተኞችንና ሥራየኞችን አዘዛቸው እሳቱም ምንም አልነካውም። አቅፋሐስ ከሚባል አገርም ዮልዮስ መጣ ከእርሱም እንደ ተረዳ ገድሉን ጻፈ። መኰንኑም ማሠቃየቱን በሰለቸ ጊዜ አንገቱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ።

ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም ተገልጾለት አጽናናው እንዲህ ብሎም ቃል ኪዳን ሰጠው ሥጋህ በሚኖርበት ቦታ ከእርሱ ታላቅ ፈውስ ይሆናል እንዲሁም በመከራው ጊዜ ስምህን በመጥራት ከእግዚአብሔር ርዳታ ለሚሻ ሁሉ ድኅነት ይደረግለታል። መታሰቢያህንም ለሚያደርግ ሁሉ የተራበ ለሚያጠግብ፣ የተጠማም ለሚያጠጣ፣ ለቤተ ክርስቲያንም በስምህ መባ ለሚሰጠው፣ የገድልህንም መጽሐፍ ለሚጽፍ ኃጢአቱን ይቅር እለዋለሁ መንግሥተ ሰማያትንም አወርሰዋለሁ።

ከዚህም በኋላ ራሱን በሰይፍ ቆረጡ ተጋድሎውንም ፈጸመ ሥጋውንም ቅዱስ ዮልዮሰ አንሥቶ ከሁለት አገልጋዮቹ ጋራ ንሒሳ ወደ ሚባል አገሩ ላከው። የመከራውም ወራት በተፈጸመ ጊዜ አብያተ ክርስቲያናትን ሠሩለት በውስጣቸውም ብዙዎች ድንቆችና ተአምራቶች ተገለጡ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ኖብ ጸሎት ይማረን በረከቱም በእኛ ላይ ይደር ለዘለዓለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ስምዖን

በዚህችም ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት አርባ ሁለተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባ ስምዖን አረፈ። ይህም ቅዱስ ከምሥራቅ አገር ሰዎች ወገን ነው። ወላጆቹም ከእስክንድርያ በስተምዕራብ ወዳለች በውስጧም የቅዱስ ሳዊሮስ ሥጋ ወደ አለባት ገዳም አመጠትና በዚያ መንኵሶ ጽሕፈትን ተማረ የቤተ ክርስቲያንንም መጻሕፍት ሁሉ አጠና ቅስናም ተሾመ።

ከዚህም በኋላ ሊቀ ጳጳሳት ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር መረጠው። በተሾመ ጊዜም መንፈሳዊ መምህሩ የሊቀ ጵጵስናውን ሥራ አስተማረው በጾምና በጸሎት እየተጋደለ ኖረ። እንጀራና ጨውም አይበላም ነበር ነገር ግን በእሳት ያላበሰሉትን ጎመን ከተልባ ጋራ ይበላ ነበር። እንዲህም አድርጎ ደማዊት ነፍሱን ለነባቢት ነፍሱ አስገዛ።

እግዚአብሔርም ታላላቅ የሆኑ ብዙዎች ድንቆችንና ተአምራትን በእጆቹ ላይ አደረገ ከእነዚህም ከእስክንድርያ ካህናት ክፉዎች ሰዎች ቀኑበት ወደመተተኞችም ሒደው ብዙ ገንዘብ ሰጧቸው የሚገድል መርዝንም አዘጋጁለት እሊህ ክፉዎችም ያን መርዝ ወስደው ከሚጠጣው መጠጥ ጋራ በብርሌው ውስጥ ደባለቁት ጠጥቶም ይባርካቸው ዘንድ እንዲጠጣ እየለመኑት ለሊቀ ጳጳሳቱ ሰጡት እርሱም ቅዱስ ቍርባንን ከተቀበለ በኋላ ያንን መርዝ ጠጣው ከክፉም ነገር ምንም ምን አልደረሰበትም ሁለተኛም ሦስተኛም ሰጥተውት ምንም ምን አልጎዳውም ከመዳኑም የተነሣ አደነቁ።

ከዚህም በኋላ ወደ ገበያ ሒደው ሁለት አዳዲስ በለስን ገዙ በውስጡም የሚገድል መርዝን አደረጉ ቅዱስ ቍርባንን ከመቀበሉ በፊት በጾም ሳለ ይሰጡት ዘንድ ተስማሙ መሠርያኖች ይህን በለስ ከቍርባን በፊት ቢበላ ሆዱ ይሠነጠቃል ብለዋቸው ነበርና።

ያን ጊዜም ወደርሱ በተንኮል ሒደው ከዚያ በለስ ይበላ ዘንድ ሊቀ ጳጳሳቱን ለመኑት አብዝተውም አስገደዱት ከቅዱስ ቍርባን በፊት ሳይፈቅድ በእጁ ውስጥ አደረጉለትና በላ ነገር ግን መሠርያኖች እንዳሉአቸው አልሆነም ሆዱም አልተሠነጠቀም ነገር ግን አርባ ቀን ታመመ።

ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጸለትና የደዌውን ምክንያት አስረዳው ያንን መርዝ ያደረጉበትንም ስማቸውን ገለጠለት።
በዚያ ወራትም የግብጽ ንጉሥ አብዶ አልዓዚዝ ወደ እስክንድርያ ከተማ መጣ ይህ አባት ሊቀ ጳጳሳት ስምዖንም ሊቀበለው ወጣ ንጉሡም በሊቀ ጳጳሳቱ ፊት ላይ የደዌ ምልክት አይቶ መሳፍንቶቹን መልኩ እንዲህ እስኪለወጥ ድረስ ሊቀ ጳጳሳቱ ምን ደረሰበት ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም ክፉዎች ካህናት በእርሱ ላይ እንዳደረጉበት መርዝንም እንዳበሉት ነገሩት ንጉሡም ተቆጣ ካህናቱንና መሠርያኑንም በእሳት እንዲአቃጥሏቸው አዘዘ ያን ጊዜም ይህ አባት ከንጉሡ እግር በታች ወድቆ ይምራቸው ዘንድ እያለቀሰ ለመነው ንጉሡም አይደለም እንደሚገባቸው ያቃጥሏቸው እንጂ አለው። ይህም አባት ስለእኔ አንተ ከአቃጠልካቸው ለእኔ ክህነትና ሊቀ ጵጵስና አይገባኝም አለው። ንጉሡም ሰምቶ ከየዋህነቱና ከርኅራኄው የተነሣ አደነቀ እነዚያን ካህናትና መሠርዮች ከእስክንድርያ እንዲያሳድዷቸው አዘዘ።

ንጉሡም ይህን አባት እጅግ ወደደው አከበረውም እንደወደደም አብያተ ክርስቲያናትን ገዳማትን ይሠራ ዘንድ ፈቀደለት። እርሱም በምስር ሰሜን አልዋህ በሚባል አገር አብያተ ክርስቲያን ሠራ በሹመቱም ዘመን ሌሎች ብዙዎችን ሠራ።

ካደረጋቸው ተአምራቶቹ ሌላው ይህ ነው ሚናስ የሚባል አንድ ቄስ ነበረ ሙቶ ከተገነዘ በኋላ በዚህ አባት ጸሎት ተነሣ። የመነሣቱ ምክንያትም እንዲህ ነበር ይህ አባት ስምዖን በመላው አብያተ ክርስቲያናት ንብረት ንዋየ ቅድሳትና አልባሳት ላይ መጋቢ አድርጎ ይጠብቅ ዘንድ ቄሱን ሾመው። ሁልጊዜም የቤተ ክርስቲያንን ገንዘብ በቤትህ ውስጥ አታኑር እያለ ያዝዘው ነበር።

ከዚህም በኋላ ድንገተኛ ደዌ አገኘውና አንደበቱና ጒረሮው ተጣጋ። ሊቀ ጳጳሳቱም ሰምቶ እጅግ አዘነ ስለ አቢያተ ክርስቲያናትም ንብረት ያንን ቄስ ከሞት ያድነው ዘንድ በዚያች ሌሊት እግዚአብሔርን እየለመነ መላዋን ሌሊት ለጸሎት ተጋ።

መንፈቀ ሌሊትም በሆነ ጊዜ ያ ቄስ ለመሞት እንደተቃረበ ይህ አባት ሰምዖን ሰማ ስለ አቢያተ ክርስቲያናት ነብረት ይጠይቃት ዘንድ አዝዞ ወደ ቄሱ ሚስት ረዳቱን ላከ።

ወደ ቄሱ ቤትም በቀረበ ጊዜ ሰዎች እያለቀሱለት ጩኸታቸውን ሰማ በገባ ጊዜም ሙቶ ልብሰ ተክህኖ መጐናጸፊያ ሲያለብሱት በዐልጋ ላይም ሲያስተኙት ብዙዎችም በዙሪያው ሲያለቅሱ አገኛቸው ያም ረዳቱ የቄሱን በድን ሊሳለም ዘንበል አለ። ያን ጊዜም ያ የሞተው ቄስ ተነሥቶ አቀፈውና የክቡር አባ ስምዖን ፈጣሪ እግዚአብሔር ሕያው ነው አለው። ረዳቱም በርታ አትፍራ አለው። ቄሱም በጌታው በአባ ስምዖን ጸሎት አዎ በእውነት ጸናሁ እግዚአብሔር ሕይወትን ሰጥቶ ከሞት አስነሥቶኛልና አለ።

ያን ጊዜም ያ ረዳት ስለ መሞቱ ደንግጠው የነበሩትን ካህናት እነሆ ቄሱ ከሞት ተነሥቷል ብሎ ጠራቸው። ካህናቱና ሕዝቡም ወደርሱ በቀረቡ ጊዜ ቄሱ እንዲህ አላቸው እኔ ሙቼ እንደነበረ ዕወቁ ክብር ይግባውና በክርስቶስ ዙፋን ፊት አቆሙኝ ከአባት ሐዋርያ ማርቆስ እስከ አባ ይስሐቅ ያሉትን ሁሉንም የጳጳሳት አለቆች ክብር ይግባውና በክርስቶስ ዙፋን ፊት ቁመው አየኋቸው እኔንም ከወንድማችን ከሊቀ ጳጳሳት ስምዖን የአብያተ ክርስቲያናትን ንብረት ለምን ሸሸግህ ብለው ገሠጹኝ። ያን ጊዜም ጌታ ክርስቶስ ይቺን ነፍስ በውጭ ወዳለ ጨለማ ውሰዱአት ብሎ አዘዘ።

ሊወስዱኝም በጐተቱኝ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ዙፋን ፊት የጳጳሳት አለቆች ሰገዱ እንዲህ እያሉም ማለዱ ይህን ሰው አንድ ጊዜ ማረው ንብረታቸውን ስለሚጠብቅላቸው አብያተ ክርስቲያናት ብሎ ወንድማችን ስምዖን ስለ እርሱ እነሆ ቁሞ ይጸልያልና። ጌታችንም ልመናቸውን ተቀብሎ ነፍሴን ወደ ሥጋዬ መለሰ እንዲህም አለኝ እነሆ ስለ ምርጦቼና ስለ ወንድማቸው ስለ ሊቀ ጳጳሳት ስምዖን ማርኩህ አንተም የአብያተ ክርስቲያናትንም ንብረት ግለጥለት። አለዚያ ግን ወደዚህ እመልስሃለሁ የእነዚህንም ልመናቸውን ስለአንተ ሁለተኛ አልቀበልም።

በዚያ የነበሩም ሰዎች ይህን በሰሙ ጊዜ እጅግ አደነቁ ምስጉን እግዚአብሔርንም አመሰገኑት ኀዘናቸውም ወደ ደስታ ተለወጠ ይህም ቄስ ይህን ተአምር ለሁሉ እየተናገረ ብዙ ዘመናት ኖረ።

ይህም አባት ስምዖን በበዐቱ ውስጥ በገድል የተጸመደ ሁኖ ኖረ መንጋዎቹንም ያስተምራቸው፣ ይገሥጻቸውና በቀናች ሃይማኖትም ያጸናቸው ነበር። ከዚህም በኋላ በሰላም አረፈ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎታቸው ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ዘዮሐንስ_ጻድቅ_ዘክብራን_ገብርኤል (ኢትዮዽያዊ)

ዳግመኛም በዚህች ቀን ጣና ክብራን ገብርኤል ገዳምን የመሠረቱት አቡነ ዘዮሐንስ ዕረፍታቸው ነው፡፡ ይኸውም አባቱ ዘካርያስና እናቱ ሶፍያ #እግዚአብሔርን በማመን የተመሰገኑ ምግባር ሃይማኖታቸው የቀና ደጋግ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ የሀገር ሰዎችም መክረው ዘካርያስን በእነርሱ ላይ ጌታና ገዥ አደረጉት፡፡ እርሱም በጥሩ አገዛዝ በፍቅር ገዛቸው፡፡ እነርሱም እንደ አሽከሮች ሆኑት፣ እርሱም እስከ አማራ ጠረፍ ድረስ ለሸዋ ሰዎች እንደ ቸር እረኛ ሆናቸው፡፡ ዘካርያስና ሚስቱ ሶፍያም በጎ ሥራን ሁሉ አላቋጡም፡፡ ምጽዋትን መስጠትን፣ ከገንዘባቸውም ከፍለው ለ #እግዚአብሔር አሥራት መስጠትን አላቋረጡም፡፡ የተቸገሩትን፣ የተራቡትንና የተጠሙትን ሁሉ ያበላሉ፣ ያጠጣሉ፡፡ ይህንንም ሲሄዱም ሲመለሱም ሁልጊዜ ያደርጋሉ፡፡

#ጌታችንን_የኢየሱስ_ክርስቶስንና የቅድስት #ድንግል_ማርያምን፣ የ #ጻድቃንና#ሰማዕታን መታሰቢያም ያድርጋሉ፡፡ ልጅም አልነበራቸውምና ሁልጊዜ እግዚአብሔርን ይማፀኑ ነበር፡፡ ሶፍያም ጠዋት ማታ እንዲህ እያለች ትጸልይ ነበር፡- ‹መካን ለነበረች ለሐና ልጅ እንደሰጠኻት፣ ለአብርሃም ሚስት ለሣራም፣ ለጸጋ ዘአብ ሚስት እግዚእ ኀረያም እንደሰጠኻቸው አቤቱ እንደ እነርሱ አንተን ደስ የሚያሰኝህን ልጅ ስጠኝ› እያለች #እመቤታችንንም እየተማፀነች ታለቅስ ነበር፡፡ #እግዚአብሔርም መጥምቁ ዮሐንስን የመሰለ ልጅ ‹አባ ዘዮሐንስ› የተባለ ቅዱስ ልጅ ሰጣቸው፡፡ እሱም በሸዋ፣ በመራቤቴ እስከ አማራ ጠረፍ ድረስ የሚያበራ መብራት ሆነ፡፡››

በኋላም በጣና ሐይቅ ላይ የሚገኘውን ‹‹ክብራን ቅዱስ ገብርኤል ገዳምን›› የመሠረቱት እኚህ አባ ዘዮሐንስ የተባሉ ጻዲቅ ናቸው፡፡

ለአባ ዘዮሐንስ በጌታ ዘንድ ታዘው ነቢዩ ኤልያስና ዮሐንስ በእኩለ ሌሊት ተገልጠውላቸው አስኬማና ቆብ ሰጥተዋቸዋል፡፡ #እመቤታችንም ተገልጣላቸው ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄደው እንዲመነኩሱ ነግራቸው ኤልያስና ዮሐንስ እየመሩ ከቦታው አድርሰዋቸዋል፡፡ ሰባት ዓመትም በዚያ ሲያገለግሉ ኖሩ፡፡ ስግደታቸውም ሁልጊዜ ስምንት ሺህ ነበር፡፡ ጌታም በደብሊባኖስ ሲያጥኑ ተገልጦላቸው ስምህ ‹‹ዘዮሐንስ ይሁን›› ብሎ ትልቅ ቃልኪዳን ሰጥቷቸዋል፡፡ ደመናም ተሸክማ ወስዳ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም አድርሳቸው በዚያም ከቆዩ በኋላ ደመናዋ መልሳ ወደ ሸዋ አምጥታቸዋለች፡፡ በትግራይ ለራሳቸው መጠለያ ሲሠሩ የ #ጌታ ፈቃድ አልነበረምና ከባድ የሆድ ሕመም መጣባቸው፡፡ ደመናዋም ደራ ሮቢት አደረሰቻቸው፡፡ በዚያም እንደደረሱ ገብርኤልና መስቀል ክብራ በሚባሉ #እግዚአብሔርን በሚወዱ ደጋግ ባለትዳሮች ቤት ዕረፍት አደረጉ፤ ለሰባት ቀናትም በዚያ ቆዩ፡፡ ከዚያም መልአኩ ተገልጦ ወደ ደሴቷ እንዲሄዱና እርሷም ዕጣ ክፍላቸው እንደሆነች ነገራቸው፡፡
አባ ዘዮሐንስም በደሴቷ ላይ በጾም በጸሎት ጸንተው ተቀመጡ፣ ትሎችም ሰውነታቸውን እንዲመገቡ ያድርጉ ነበር፡፡ ገብርኤልና መስቀል ክብራ የተባሉትም ደጋግ ባለትዳሮች የሚያስፈልጋቸውን ይወሰዱላቸው ነበርና ባገኙዋቸው ጊዜ ትሎቹን ከሰውነታቸው ላይ ሲያራግፉላቸው ‹‹ተዋቸው እኔን ሊመገቡ ተፈቅዶላቸዋል›› አሏቸው፡፡ አባታችን አንድ ቀን የሰው ድምፅ ሰምተው ወደ ውጭ ወጥተው ሲመለከቱ የአካባቢው ሰዎች አንድ ማድጋ ወተት፣ አንድ በግና አንድ ከብት ለዘንዶ ሲገብሩ አይተው ያንን ዘንዶ በ #ሥላሴ ስም በመስቀል ምልክት አማትበው ከሰዎቹ ፊት ገደሉት፡፡ ይህን የሰማውና ሰዎቹን እንዲገብሩ የላካቸው ጃን ቹሐይ የተባለው ጣኦት አምላኪ የአገሩ ሹም ‹‹የማመልከውን ዘንዶ እንዴት ትገድላለህ?›› በማለት እንዲታሰሩ አደረጋቸው፡፡ ንጉሥ ዐምደ ፅዮንም ይህን ሲሰማ ሠራዊቱን ልኮ ያንን ጣኦት አምላኪ የአገሩን ሹም ገድለው አባ ዘዮሐንስ እንዲፈቷቸው አደረገ፡፡

አባ ዘዮሐንስም ወንጌልን እያስተማሩ፣ ሙትን እያስነሱና ታላላቅ ተአምራትን እያደረጉ በደሴቷ ላይ ተወስነው ተቀመጡ፡፡ በደመናም ተጭነው ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው ታቦተ ቅዱስ ገብርኤልን አምጥተው በደሴቷ ላይ ክብራን ገብርኤል ገዳምን መሠረቱ፡፡ ደመናም ደሴቷ ላይ ስታደርሳቸው ኤልያስና ዮሐንስ በቀኝ በግራው እየተራዱአቸው እርሳቸው ሠራዒ ቄስ ሆነው ቀደሱ፡፡ ደሴቷንም መጀመሪያ እንደመጡ ባሳረፈቻቸው ገደኛ ሴት ስም ሰየሟት፡፡ ለሴቶች መነኮሳት ከዚያው አጠገብ የሚገኘውን እንጦንስ ገዳምን አድርገው ክብራን ገብርኤልን ለወንዶች ብቻ አደረጓት፡፡

አንድ ቀን አባ ዘዮሐንስ በደብረ ሊባኖስ መሥዋዕት ለማቅረብ እያጠነ ሳለ ለስም አጠራሩ ክብርና ምስጋና ይግባውና #ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ከሌላ ሀገር የመጣ እንግዳ ሰው መስሎ ታየውና ‹ሰላም ለአንተ ይሁን› አለው፡፡ አባታችን ዘዮሐንስም ‹ወንድሜ ሆይ! የ #እግዚአብሔር ፍቅር አንድነት ከአንተ ጋር ይሁን› አለው፡፡ ‹አንተ እንግዳ ሰው ከየት ሀገር የመጣህ ነህ? ከዚህ በፊት አላውቅህም› አለው፡፡ #ጌታችንም ከልቡናው ፍግግ አለና ‹ከእናትህ ማኅፀን ሳትወጣ እኔ አውቅሃለሁ› አለው፡፡ ይህንንም ብሎ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ድረስ ያደረገለትን ከመወለዱም አስቀድሞ የሆነውን ሁሉ፣ ከተወለደም በኋላ እስከዚያ ቀን ድረስ ያደረገለትን፣ አባቱንም በአመፀኛው በጎዶልያ እጅ ከመሞት እንዳዳነው፣ እናቱንም ዕቁባቱ ሊያደርጋት እንደነበረ ምሥጢሩንም ሁሉ ነገረው፡፡ ይህንንም ብሎ ዳግመኛ ተነጋገረው፡- ‹ከዛሬ ጀምሮ ስምህ ዘዮሐንስ ይሁን፣ አንተ የዓለሙ ሁሉ ደስታ ነህና የሚያለቅሱም በአንተ ደስ ይላቸዋል› አለው፡፡›› ‹‹በደመናም ተጭነው ኢየሩሳሌም ደርሰው ታቦተ ቅዱስ ገብርኤልን አምጥተው ክብራን ገብርኤል አስገብተው በዚያም ሲኖሩ በጣም አርጅተው ነበርና ራሳቸውን ወደ ምድር አጎንብሰው ይሄዱ ነበር፡፡

ከዚህም በኋላ ሐምሌ 10 ቀን ለዓርብ አጥቢያ ሲጸልዩና በግንባራቸው ወደ ምድር ሲሰግዱ ለስም አጠራሩ ስግደት የሚገባው #ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክረስቶስ ሚካኤልንና ገብርኤልን አስከትሎ መጥቶ ‹ወዳጄ አባ ዘዮሐንስ ሆይ! ከድካም ወደ ዕረፍት፣ ከበሽታ ወደ ሕይወት፣ ከዚህ ዓለም ዐይን ወዳላየውና ጆሮ ወዳልሰማው ተድላ ደስታ ወዳለበት ገነት አሳርፍህ ዘንድ ወደ አንተ መጣሁ› አለው፡፡ ይህንንም ብሎ ስሙን ለሚጠራና መታሰቢያውን ለሚያደርግ ከእርሱ በረከት እንደማይጠፋ ቃልኪዳን ሰጠው፡፡ ‹ገድልህን የሚጽፍ ወይም የሚያነብ እኔን እንደመሰለ እንደ መልከጼዴቅ ካህን በእኔ ዘንድ የተመረጠና የተወደደ ይሆናል፣ በበዓልህ ማኅሌት የቆመ የመላእክት ባልንጀራ ይሆናል፣ እነዚህን ልጆችህንም የመላእክት አምሳያ አደርጋቸዋለሁ› አለው፡፡ ‹ይህችን ደሴት እንደ ኢየሩሳሌም ሀገሬ፣ እንደ ደብረ ዘይትና ለባሪያዬ ለሙሴ ሕግን እንደ ሰጠሁባት እንደ ደብረ ሲና አድርጌያታለሁ፣ በረከቴም ከእርሷ አይታጣም፣ እኔም ከእርሷ አልለይም ይልቁንም በተጠመቅሁባት ቀን ከዚህች ገዳምህ አልለይም፣ የዚህች ደሴትና የሀገሬ የኢየሩሳሌም መክፈቻ በአንድ ላይ አንድ ይሁን› አለው፡፡ ‹ከዚህች ሀገርም ያለንስሓ የሕፃናትና የጎልማሶች ሞት አይሁን፣ እስከ ዘለዓለምም ድረስ ጸሎት ከእርሷ አይቋረጥ› አለው፡፡

ጌታችንም ለአባ ዘዮሐንስ ይህን ከተናገረው በኋላ ቡራኬ ሰጥቶት ከቅዱሳን መላእክት ጋር ወደቀደመ ቦታው በክብር ዐረገ፡፡›› ጻድቁ በ105 ዓመታቸው ሐምሌ 24 ቀን በክብር አርፈዋል፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጻድቁ በአባ ዘዮሐንስ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘለዓለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ሄላ_ድንግል

ባሕታዊ አቡነ ሄላ ድንግል የትውልድ ሀገራቸው ባሕርዳር ነው። በብሕትውናቸው እጅግ የታወቁ ወንጌልን ዞረው ሲያስተምሩ ሕይወታቸው ያለፈ ታላቅ አባት ናቸው። እጅግ ድንቅ ድንቅ የሆኑ ተአምራትንም በማድረግ ይታወቃሉ። ዓባይ በክረምት ሞልቶ ለመሻገር አስቸጋሪ ሆኖ ቢያገኙት በቅዱስ መስቀላቸው ባርከው ለሁለት ከፍለውት ተሻግረዋል። ወንዙ ሳይቀር ቆሞ ያሳለፋቸው ባሕታዊው አቡነ ሄላ ድንግል ወንጌልን ሲሰብኩ፣ ሕሙማንን ሲፈውሱ ኖረው በመጨረሻ ከዚህ ዓለም ድካም ሐምሌ 24 ቀን ዐርፈው ጎጃም ደብረ ጽላሎ ተቀብረዋል።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎታቸው ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ጊዮርጊስ_ዘመንበረ_ኢትዮጵያ

እኚህ ጻድቅ ሀገራቸው ጎጃም ሲሆን የአባታቸውና የእናታቸው ሀገር ግን ሰሜን ጎንደር ናቸው። ሲወለዱ መልአክ መጥቶ ወስዶ 24ቱ ካህናተ ሰማይን አሳይቶ ቅዱስ ያሬድም ሲዘምር ጥዑም ዜማውን አሰምቷቸውል። የቅዱስ ያሬድም ፍቅር በዚያው ልባቸው ተቀርጾ ቀረ።

ጻድቁ ዋሸራ ገዳም ሁሉንም ተምረው ጨርሰው በ25 ዓመታቸው ከመነኰሱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በቅዱስ ያሬድ ስም ቤተ ክርስቲያን አሠርተዋል። ታቦቱንም አስገብተው በዚያው እያገለገሉ ሲኖሩ "እንደ ኤልያስና እንደ አንተ ሞትን እንዳላይ ለምንልኝ..." እያሉ ቅዱስ ያሬድን ዘወትር ሲማፀኑት ቅዱስ ያሬድም አንድ ቀን ከእነ አቡነ አረጋዊ፣ ተክለ ሃይማኖት፣ ዘርዐ ቡሩክ ዘግሽ ጋር በመሆን ተገልጦላቸው "አይዞህ ፈጣሪዬ ያልከውን ያደርግልሃል" ብሏቸዋል።

አስደናቂውን ባለ ሦስት ዓምድ የሆነውን የቅዱስ ያሬድንም ገድል የጻፋት እሳቸው ነበሩ ነገር ግን ቅዱስ ገድሉን ደርቡሾች ከወሰዱት በኋላ የት እንደደረሰ አይታወቅም። ቅዱስ ገድሉም 382 ገጽ ያሉት ሲሆን 69 አስደናቂ ሥዕላት ነበሩት፣ በ132 ሐረጎችም ያሸበረቀ ነበር። ጻድቁ ቅዱስ ያሬድን "እንደ አንተ እንዳልሞት ጸልይልኝ" ብለው በለመኑት መሠረት ራሱ ቅዱስ ያሬድ በተሰወረበት ቦታ በሰሜን ተራራ ምድረ ጸለምት ተሰውረዋል። በስማቸው የተሠራው ቤተ ክርስቲያን ጎንደር ይገኛል።

#ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በርከታቸውም ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን።

#ሐምሌ_24 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ ዘክብራን (ኢትዮጵያዊ)
2.ቅዱስ አባ ኖብ ሰማዕት
3.መቶ ዘጠና ሺህ ሰማዕታት (የአባ ኖብ ማኅበር)
4.አባ ተክለ አዶናይ ዘደብረ ሊባኖስ
5.አቡነ ተወልደ መድኅን (ኢትዮጵያዊ)
6.አባ ስምዖን ጻድቅ ሊቀ ጳጳሳት
7.ቅድስት ክብራ (መስቀል ክብራ) ዘእንጦንስ ኢየሱስ
#ወርኀዊ_በዓላት
1.ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
2.ቅዱስ አጋቢጦስ (ጻድቅ ኤጲስቆጶስ)
3.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
4.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
5.ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
6.ሃያ አራቱ ካኅናተ ሰማይ (ሱራፌል)
7.ቅዱስ አባ ሙሴ ጸሊም (ኢትዮጵያዊ)

††† "ስለዚህ እኔ ደግሞ በእናንተ ዘንድ ስለሚሆን በጌታ በኢየሱስ ስለማመንና ለቅዱሳን ሁሉ ስለሚሆን መውደድ ሰምቼ ስለ እናንተ እያመሰገንሁ ስጸልይ ስለ እናንተ ማሳሰብን አልተውም::" †††
(ኤፌ. ፩፥፲፭)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ሐምሌ_24 እና #ከገድላት_አንደበት)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ሐምሌ_24_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ቆሮ 7
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁸ በመልእክቴ ያሳዘንኋችሁ ብሆን እንኳ አልጸጸትም፤ የተጸጸትሁ ብሆን እንኳ፥ ያ መልእክት ጥቂት ጊዜ ብቻ እንዳሳዘናችሁ አያለሁና አሁን ለንስሐ ስላዘናችሁ ደስ ብሎኛል እንጂ ስላዘናችሁ አይደለም፤
⁹ በምንም ከእኛ የተነሣ እንዳትጎዱ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ አዝናችኋልና።
¹⁰ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ጸጸት የሌለበትን፥ ወደ መዳንም የሚያደርሰውን ንስሐ ያደርጋልና፤ የዓለም ኀዘን ግን ሞትን ያመጣል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ እንግዲህ እኔ፥ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ የክርስቶስም መከራ ምስክር ደግሞም ሊገለጥ ካለው ክብር ተካፋይ የሆንሁ፥ በመካከላቸው ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ፤
² በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤
³ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ፤
⁴ የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ።
⁵ እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 16
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³⁵ በነጋም ጊዜ ገዢዎቹ፦ እነዚያን ሰዎች ፍታቸው ብለው ሎሌዎቻቸውን ላኩ።
³⁶ የወኅኒውም ጠባቂ፦ ትፈቱ ዘንድ ገዢዎቹ ልከዋል፤ እንግዲህ አሁን ወጥታችሁ በሰላም ሂዱ ብሎ ይህን ቃል ለጳውሎስ ነገረው።
³⁷ ጳውሎስ ግን፦ እኛ የሮሜ ሰዎች ስንሆን ያለ ፍርድ በሕዝብ ፊት ደብድበው በወኅኒ ጣሉን፤ አሁንም በስውር ይጥሉናልን? አይሆንም ራሳቸው ግን መጥተው ያውጡን አላቸው።
³⁸ ሎሌዎቹም ይህን ነገር ለገዢዎች ነገሩ። የሮሜ ሰዎችም እንደ ሆኑ በሰሙ ጊዜ ፈሩ፤
³⁹ መጥተውም ማለዱአቸው፥ አውጥተውም ከከተማ ይወጡ ዘንድ ለመኑአቸው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሐምሌ_24_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ማእምርየ ወዐውቅየ። ዘኅቡረ አስተጠዓምከ ሊተ መባልዕተ። ወነሐውር ቤተ እግዚአብሔር በአሐዱ ልብ"። መዝ 54፥13-14።
"አንተ ግን፥ እኩያዬ ሰው፥ ባልንጀራዬና የልቤ ወዳጅ፤ መብልን ከእኔ ጋር በአንድነት ያጣፈጥህ፤ በአንድ ልብ በእግዚአብሔር ቤት ተራመድን"። መዝ 54፥13-14።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሐምሌ_24_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 19
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁶ እነሆም፥ አንድ ሰው ቀርቦ፦ መምህር ሆይ፥ የዘላለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ላድርግ? አለው።
¹⁷ እርሱም፦ ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም የሆነ አንድ ነው፤ ወደ ሕይወት መግባት ብትወድ ግን ትእዛዛትን ጠብቅ አለው።
¹⁸ እርሱም፦ የትኞችን? አለው። ኢየሱስም፦ አትግደል፥ አታመንዝር፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥
¹⁹ አባትህንና እናትህን አክብር፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ አለው።
²⁰ ጐበዙም፦ ይህንማ ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ፥ ደግሞስ የሚጐድለኝ ምንድር ነው? አለው።
²¹ ኢየሱስም፦ ፍጹም ልትሆን ብትወድ፥ ሂድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ፥ መዝገብም በሰማያት ታገኛለህ፥ መጥተህም ተከተለኝ አለው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ሠለስቱ_ምዕት_ቅዳሴ ነው። መልካም የአባ ኖብ የዕረፍት በዓል፣ የሊቀ ጳጳስ ስምዖን የዕረፍት በዓልና የአቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ ዘክብራን የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2024/09/23 17:25:30
Back to Top
HTML Embed Code: