Telegram Web Link
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
❀እንኳን አደረሳችሁ!

#ማርያም እግዝእት (ጼዴንያ)
#መስቀል ዕጸ ሕይወት
#ማክዳ ንግሥት
#ሐና ዕብራዊት
#ዮዲት ቅድስት
#አትናስያ ቡርክት
#መጥሮንያ ሰማዕት
#ማርታ ብጽዕት
#ኢያቄም ወላዴ በረከት
#ግርማሥሉስ ገባሬ መንክራት
#መስከረም_11

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ዐሥራ አንድ በዚህች ቀን #ቅዱስ_ፋሲለደስ በሰማዕትነት አረፈ፣ #ቅዱስ_ቆርኔሌወስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፣ #ቅድስት_ታዖድራ አረፈች፣ #ቅድስት_በነፍዝዝ የስሟ ትርጓሜ ጣፋጭ የሆነ በሰማዕትነት አረፈች፣ #ሦስቱ_ቅዱሳን_ገበሬዎች (#ሱርስ#አጤኬዎስ#መስተሐድራ) በሰማዕትነት አረፉ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ፋሲለደስ_ሰማዕት

መስከረም ዐሥራ አንድ በዚህች ቀን ለአንጾኪያ ነገሥታት አባታቸውና መካሪያቸው የሆነ ቅዱስ ፋሲለደስ በሰማዕትነት አረፈ።

እርሱም ለሮም ንጉሥ የሠራዊት አለቃ ነው መንግሥቱም ሁለመናዋ በእርሱ ምክር የጸናች ናት። ብዙዎችም ወንዶችና ሴቶች የቤት ውልዶች አገልጋዮች አሉት።

ዝምድናውም እንዲህ ነው ስሙ ኑማርያኖስ የተባለ የሮም ንጉሥ ለቴዎድሮስ በናድሌዎስ እናቱ የሆነች የቅዱስ ፋሲለደስን እኅት አግብቶ ዮስጦስን፣ ገላውዴዎስን፣ አባዲርን ወለደችለት እሊህም ለቅዱስ ፋሲለደስ የእኅቱ ልጆች ናቸው። የቅዱስ ፋሲለደስም ሚስት ለቅዱስ ፊቅጦር እናት እኅት ናት ከእርሷም ስማቸው አውሳብዮስና መቃርስ የተባሉ ሁለት ልጆችን ወለደ።

በዚያም ወራት የቊዝና የፋርስ ሰዎች የሮምን ሰዎች ሊወጓቸው በላያቸው ተነሡ ያን ጊዜ የንጉሥ ልጅ ዮስጦስን የፋሲለደስ ልጅ አውሳብዮስን ከጦር ሠራዊቶቻቸው ጋር ለውጊያ ላኳቸው።

ንጉሡ ኑማርዮስም ሌሎች ጠላቶች በተነሡበት በኩል ለጦርነት ሒዶ በውጊያው ውስጥ ሞተ የሮም መንግሥትም የሚጠብቃትና የሚመራት የሌላት ሆነች።

እንዲህም ሆነ በዚያ ወራት ስለ ጦርነት ለመደራጀት የሮም ሰዎች ከሀገሩ ሁሉ አርበኞች የሆኑ ሰዎችን ሰበሰቡ ከውስጣቸውም ከላይኛው ግብጽ ስሙ አግሪጳዳ የሚባል የፍየሎች እረኛ የሆነ አንድ ሰው አለ። እርሱንም መኳንንቱ ወስደው በመንግሥት ፈረሶች ላይ ባልደራስ አድርገው ሾሙት እርሱም በጠባዩና በሥራው ሁሉ ኃይለኛና ብርቱ ነበር።

ከንጉሥ ኑማርያኖስ ሴቶች ልጆች አንዲቱ ወደርሱ በመስኮት ተመለከተች ወደደችውም መልምላም ወስዳ አገባችው ስሙንም ዲዮቅልጥያኖስ ብላ ሰይማ አነገሠችው። ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ሰማይና ምድርን የፈጠረ #እግዚአብሔርን ትቶ ጣዖታትን አመለከ ቅዱስ ፋሲለደስም ሰምቶ እጅግ አዘነ የመንግሥትንም አገልግሎት ተወ።

ከዚህም በኋላ የንጉሥ ኑማርያኖስ ልጅ ዮስጦስና የፋሲለደስ ልጅ አውሳብዮስ ጠላቶቻቸውን ድል አድርገው የጠላቶቻቸውንም አገሮች አጥፍተው ደስ ብሏቸው ተመለሱ። ነገር ግን የነገሠው ዲዮቅልጥያኖስ የክብር ባለቤት #ክርስቶስን ክዶ አምልኮ ጣዖትን አቁሞ አገኙት እጅግም አዘኑ ተቆጥተውም ተነሡ ሰይፎቻቸውን መዝዘው ዲዮቅልጥያኖስን ገድለው የንጉሥ ኑማርያኖስን ልጅ ዮስጦስን ሊያነግሡ ወደዱ ፋሲለደስም ከዚህ ሥራ ከለከላቸው።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ፋሲለደስ ዘመዶቹን፣ ሠራዊቱን፣ አገልጋዮቹንም ሁሉ ሰበሰባቸውና በክብር ባለቤት በክርስቶስ ስም ደሙን ሊያፈስ እንደፈለገ አስረዳቸው ሁሉም እንዲህ ብለው መለሱለት አንተ በምትሞትበት ሞት እኛ ከአንተ ጋር እንሞታለን በዚህም ምክር በአንድነት ተሰማሙ።

ከዚህም በኋላ በንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ፊት ቁመው ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ታመኑ ከእርሳቸውም ግርማ የተነሣ ታላቅ ፍርሃትን ፈራ እነርሱ የመንግሥት ልጆች ናቸውና።

የቅዱስ ፊቅጦር አባት ኀርማኖስም ወደ ግብጽ አገር ይልካቸው ዘንድ በዚያም እንዲያሠቃዩዋቸው መከረው ሁሉንም እየአንዳንዳቸውን ለብቻቸው አድርጎ ላካቸው አባዲርንና እኀቱ ኢራኒን ወደ አንዲት አገር፣ አውሳብዮስንና ወንድሙ መቃርስን ወደሌላ ቦታ፣ ገላውዴዎስንም እንዲሁ አደረጉ። በናድሌዎስ ቴዎድሮስም እሼ በሚባል ዕንጨት ላይ በመቶ ሃምሳ ሦስት ችንካር ተቸንክሮ ገድሉን ፈጸመ።

ቅዱስ ፋሲለደስን ግን አምስት ከተማዎች ወዳሉበት ወደ አፍሪካ ምድር ወደ መኰንኑ ወደ መጽሩስ ላከው መጽሩስም በአየው ጊዜ መንግሥቱን ክብሩን ስለ ተወ እጅግ አደነቀ።

ክብር ይግባውና #ጌታችን_ክርስቶስም መልአኩን ልኮ በመንፈስ ወደ ሰማይ አውጥቶ በብርሃን ያጌጠ መንፈሳዊ ማደሪያን አሳየው ነፍሱም እጅግ ደስ አላት ከዚህም በኋላ ወደነበረበት መለሰው። ባሮቹን ግን ነፃ ያወጣቸው አሉ የቀሩትም ከእርሱ ጋር የሰማዕትነት አክሊልን የተቀበሉ ሰባት ሺህ ሠላሳ ሦስት የሚሆኑ አሉ።

ቅዱስ ፋሲለደስንም ታላቅ ስቃይን አሰቃዩት በመንኰራኲርና በተሣሉ የብረት ዘንጎች ሥጋውን ሰነጣጥቀውት ሞተ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም ያለ ጥፋት ከሞት አድኖ አስነሣው አሕዛብም ሁሉ ይህን ድንቅ ተአምር በአዩ ጊዜ አደነቁ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም አመኑ መኰንኑንም ረገሙት ጣዖቶቹንም ሰደቡ በእነርሱ ላይም ተቆጥቶ ራሶቻቸውን በሰይፍ ይቆርጧቸው ዘንድ ወታደሮቹን አዘዘ የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበሉ ቊጥራቸውም ዐሥራ አራት ሺህ ሰባት መቶ ወንዶች ሠላሳ ሰባት ሴቶች ናቸው።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ፋሲለደስን ሥጋው ሁሉ ቀልጦ እንደ ውኃ እስከሚሆን በብረት ምጣድ ውስጥ አበሰሉት መኰንኑም በተራራ ላይ ጥልቅ ጒድጓድ ቆፍረው በዚያ እንዲቀብሩት አዘዘ እንዲሁም አደረጉ። ያን ጊዜም ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ቅዱስ ፋሲለደስን ከሞት ደግሞ አስነሣው ወደ መኰንኑም መጥቶ እንዲህ ብሎ ጮኸ መኰንን መጽሩስ ሆይ እፈር ከሀዲ ንጉሥህም የረከሱ ጣዖቶችህም ይፈሩ እነሆ ክብር ይግባውና #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ያለ ጉዳት ከሞት ጤነኛ አድርጎ አስነሥቶኛልና።

ሕዝቡም ይህን ተአምር በአዩ ጊዜ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አምነው በሰማዕትነት ሞቱ ቁጥራቸውም ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ሆነ።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ፋሲለደስን በውስጧ መጋዝ ካላት መንኰራኲር ላይ አውጥቶ ታላቅ ሥቃይን አሠቃየው ዳግመኛም በብረት ዐልጋ ላይ በሆዱ አስተኝተው ከበታቹ እሳትን አነደዱ ያን ጊዜም ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ተገለጠለት ከዚያ ስቃይም ውስጥ አንስቶ ያለ ጉዳት ጤነኛ አደረገው እንዲህም ብሎ ቃል ኪዳን ሰጠው ፋሲለደስ ሆይ ዕውቅ መታሰቢያህን ለሚያደርግ ሁሉ ወይም ለድኆች በስምህ ምጽዋትን ለሚሰጥ ወይም ለተራቈተ ልብስን ወይም በመታሰቢያህ ቀን ለቤተ ክርስቲያን መባ ለሚሰጥ በብዙም ቢሆን በጥቂት መታሰቢያህን ለሚያደርጉ ሁሉ እኔ በደላቸውን ሁሉ እተውላቸዋለሁ መኖሪያቸውንም በመንግሥተ ሰማያት ከአንተ ጋራ አደርጋለሁ።

ጌታችንም ይህን ካለው በኋላ በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ ቅዱስ ፋሲለደስም በፍጹም ደስታ ደስ ተሰኘ።

ከዚህም በኋላ መጽሩስ መኰንን ከአማካሪዎቹ ጋር ተማከረ እንዲህም አላቸው ስሙ ፋሲለደስ ስለሚባል ስለዚህ ሰው ምን ላድርግ እርሱን ያላሠቃየሁበት የሥቃይ መሣሪያ ምንም የቀረ የለም ከሐሳቡም አልተመለሰም እነርሱም እንዲህ ብለው መከሩት ራሱን በሰይፍ ቆርጠህ ከእርሱ ተገላገል እነሆ የዚች አገር ሰዎች በእርሱ ምክንያት አልቀዋልና።

በዚያንም ጊዜ የቅዱስ ፋሲለደስን ራስ በሰይፍ እንዲቆርጡ መኰንኑ አዘዘና ቆረጡት የድል አክሊልን ተቀበለ ንቆ ሰለ ተዋት ምድራዊት መንግሥት ፈንታም ሰማያዊት መንግሥት አገኘ። ከሥጋውም ድንቆች የሆኑ ታላላቅ ተአምራት ተገለጡ ከእርሱም ጋር ሰማዕት ሁነው የሞቱ ሁሉም ቊጥራቸው ሃያ ሦስት ሺህ ሰባት መቶ ዘጠና ሦስት ሆነ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ፋሲለደስና በሰማዕታት ሁሉ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#ቅዱስ_ቆርኔሌዎስ_ሐዋርያዊ

በዚህችም ቀን የጭፍራ አለቃ የሆነ ትሩፋቱና ገድሉም ያማረ ጻድቅ ሰው ቆርኔሌዎስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው እርሱም በቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያት ዘመን #እግዚብሔርን ያገለገለ ነው።

#እግዚአብሔር መልአክም ተገልጦለት ሐዋርያ ጴጥሮስን ይጠሩት ዘንድ ሰዎችን እንዲልክ ጴጥሮስም ወደርሱ እንዲመጣ ሊሠራው የሚገባውን ከእርሱ ከጴጥሮስ እንዲሰማ አዘዘው።

ጴጥሮስም ወደርሱ በደረሰ ጊዜ የ #እግዚአብሔርን ቃል አስተማረው ለርሱና ከእርሱ ጋር ላሉት ሁሉ ከሁሉ ቤተሰቡ ጋር አምኖ ተጠመቀ። ከዚህ በኋላ ጴጥሮስ ለእስክንድርያ አገር ቅስና ሾመው ወደርሷ በደረሰ ጊዜ የጣዖታትን አምልኮ ተመልታ አገኛትና አስተማራቸው ብዙዎችንም ወደቀናች ሃይማኖት መልሶ አጠመቃቸው መኰንኑ ድሜጥሮስም አምኖ ከወገኖቹ ጋር በእርሱ እጅ ተጠመቀ።

የኑሮውን ዘመንና ሐዋርያዊ ተጋድሎውን አድርሶ በሰላም አረፈ እርሱም ከአሕዛብ አስቀድሞ ያመነ የመጀመሪያ አማኒ ነው።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሱ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ታዖድራ

በዚህችም ቀን ከእስክንድርያ አገር በንጉሥ ዘይኑን ዘመን ቅድስት ታዖድራ አረፈች።

ይችንም ቅድስት ሌላ ሰው አስገድዶ ከባሏ ወስዶ ከባሏ ጋር ያላትን አንድነት አበላሸ ያን ጊዜም ታላቅ ኀዘን በማዘን ተጸጸተች መሪር ልቅሶንም አለቀሰች የወንዶችንም ልብስ ለብሳ ወንድ መሰላ ከእስክንድርያ በሥውር ወጣች ስሟንም ቴዎድሮስ ብላ ሰየመችና ወደ ወንዶች ገዳም ገባች የምንኲስና ልብስንና የመላእክትን አስኬማ ለበሰች።

የሚያዩዋት ሁሉ እርሷ እንደ ጃንደረባ የሆነች ወንድ ትመስላቸው ነበር እርሷ ግን በረኃብ፣ በጽምዕ ሌሊት በመትጋት ቀን በመቆም ጸንታ በመጋደል ላይ ታገሠች እንዲህም በመጋደል ተጠምዳ ብዙ ዘመን ኖረች።

በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ አንድ ሰው ከአንዲት ብላቴና ጋር አመነዘረ እርሷም ፀንሳ ወንድ ልጅን ወለደች ወላጆቿም ድንግልናሽን ያጠፋው ማነው ብለው ጠየቋት እርሷም በገዳም ውስጥ የሚኖር አባ ቴዎድሮስ እርሱ ደፍሮኝ ከእርሱ ፀነስኩ ብላ በዚች ቅድስት ታኦድራ ላይ በሐሰት ተናገረች።

ወላጆቿም በሰሙ ጊዜ እጅግ አዘኑ ሕፃኑንም ወደዚያ ገዳም አበ ምኔት ወሰዱት እንዲህም አሉት ይህ ሕፃን የልጅህ የመነኵሴው የቴዎድሮስ ልጅ ነው ። ያን ጊዜም አበ ምኔቱ ይቺን ቅድስት ታኦድራን ጠራትና እንዲህ አላት ይህን ክፉ ሥራ ለምን ሠራህ በመነኰሳቱም ሁሉ ላይ ኀፍረትንና ጒስቁልናን አመጣህ እርሷ ሴት መሆኗን አላወቀምና እርሷም አባቴ ሆይ በድያለሁና ይቅር በለኝ አለችው።

አበ ምኔቱም ተቆጥቶ ከገዳሙ አስወጥቶ አባረራት በበረሀ ውስጥ ሰባት ዓመት ኖረች ያም ሕፃን ከእርሷ ጋር ሁኖ ከሰይጣናት በሚመጡባት በብዙ መከራዎች ብዙ መከራዎች ላይ ታገሠች ብዙ ሥቃያትንም ፈጽሞ አሠቃዩዋት።

ከዚህም በኋላ ዳግመኛ ተቀብለው ወደ ገዳም አስገቡአት ጥቂት ቀንም ኖረች መልካም ተጋድሎዋንም ፈጽማ በሰላም አረፈች ነፍሷንም በ #እግዚአብሔር እጅ ሰጥታ የዘላለም ሕይወትን አገኘች።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቷ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_በነፍዝዝ_ሰማዕት

በዚህች ቀን የስሟ ትርጓሜ ጣፋጭ የሆነ የከበረች በነፍዝዝ በሰማዕትነት አረፈች። ይቺም ቅድስት በእድሜዋ ፈጽማ የሸመገለች ነበረች በፋርስ ንጉሥ በሳቦር ዘመንም መከራ ተቀበለች ከዘጠኝ መቶ ክርስቲያን ጋር ማርከው ወስደው አሠሩዋት የሠራዊቱም አለቃ ታላቅ ሥቃይን አሠቃይቶ ከዚያ በኋላ ራሷን በሰይፍ ቆረጠ።

ራሷንም ከአስቆረጣት በኋላ ከአንገቷ የፈሰሰው ደም እስከ ራቀ ድረስ ወደ ላይ ወጣ ከዚያ የተቀመጡ ጠላቶችም ኃይላቸው ደከመ። የፀሐይ ብርሃንም ጨለመ በዚያም ቦታ ደግሞ ጣፋጭ የሆነ መዐዛ ተመላ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቷ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሦስቱ_ቅዱሳን_ገበሬዎች
(ሱርስ፣ አጤኬዎስ፣ መስተሐድራ)

በዚህችም ቀን ስማቸው ሱርስ፣ አጤኬዎስ፣ መስተሐድራ የሚባል ሦስት ገበሬዎች የእስና አገር ሰዎች በሰማዕትነት አረፉ ። አርያኖስም ከሀገሪቱ በስተደቡብ ምንም ሳያስቀር ወታደሮቹ እስከ ደከሙ ድረስ ሰይፋቸውንም ወደ አፎቱ መልሰው ነበር የአገር ሰዎችን ጨርሶ ገድሎ ሲመለስ እሊህ ሦስቱ ገበሬዎች ከዱር ሲመለሱ በከተማ መካከል በተገናኙት ጊዜ እኛ ክርስቲያኖች ነን ብለው በግልጥ ጮኹ አርያኖስም ሰምቶ ወታደሮቹን እሊህን ገበሬዎች ትገድሏቸው ዘንድ ይገባል አላቸው።

ወታደሮቹም እኛ ደክመናል ሰይፎቻችንንም ወደ አፎታቸው አስገብተናል አሉት እሊህ ቅዱሳንም ሰምተው እነሆ መቆፈሪያዎች ከእኛ ጋራ አሉ በእነርሱ ግደሉን አሉ ከዚያም አንገታቸውን በደንጊያ ላይ አድርገውላቸው ቆረጡአቸው።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ሁሉ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም_11)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_11_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዕብራውያን 12
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹-² እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።
³ በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ።
⁴ ከኃጢአት ጋር እየተጋደላችሁ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም፤
⁵-⁶ እንደ ልጆችም ከእናንተ ጋር፦ ልጄ ሆይ፥ የጌታን ቅጣት አታቅልል፥ በሚገሥጽህም ጊዜ አትድከም፤ ጌታ የሚወደውን ይቀጣዋልና፥ የሚቀበለውንም ልጅ ሁሉ ይገርፈዋል ብሎ የሚነጋገረውን ምክር ረስታችኋል።
⁷ ለመቀጣት ታገሡ፤ እግዚአብሔር እንደ ልጆች ያደርግላችኋልና፤ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው?
⁸ ነገር ግን ሁሉ የቅጣት ተካፋይ ሆኖአልና ያለ ቅጣት ብትኖሩ ዲቃላዎች እንጂ ልጆች አይደላችሁም።
⁹ ከዚህም በላይ የቀጡን የሥጋችን አባቶች ነበሩን እናፍራቸውም ነበር፤ እንዴትስ ይልቅ ለመናፍስት አባት አብልጠን ልንገዛና በሕይወት ልንኖር በተገባን?
¹⁰ እነርሱ መልካም ሆኖ እንደ ታያቸው ለጥቂት ቀን ይቀጡን ነበርና፥ እርሱ ግን ከቅድስናው እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል።
¹¹ ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፥ ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ያዕቆብ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ወንድሞቼ ሆይ፥ ከእናንተ ብዙዎቹ አስተማሪዎች አይሁኑ፥ የባሰውን ፍርድ እንድንቀበል ታውቃላችሁና።
² ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለንና፤ በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር እርሱ ሥጋውን ሁሉ ደግሞ ሊገታ የሚችል ፍጹም ሰው ነው።
³ እነሆ፥ ፈረሶች ይታዘዙልን ዘንድ ልጓም በአፋቸው ውስጥ እናገባለን፥ ሥጋቸውንም ሁሉ እንመራለን።
⁴ እነሆ፥ መርከቦች ደግሞ ይህን ያህል ታላቅ ቢሆኑ በዐውሎ ነፋስም ቢነዱ፥ የመሪ ፈቃድ ወደሚወደው ስፍራ እጅግ ታናሽ በሆነ መቅዘፊያ ይመራሉ።
⁵ እንዲሁም አንደበት ደግሞ ትንሽ ብልት ሆኖ በታላላቅ ነገር ይመካል። እነሆ፥ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል።
⁶ አንደበትም እሳት ነው። አንደበት በብልቶቻችን መካከል ዓመፀኛ ዓለም ሆኖአል፤ ሥጋን ሁሉ ያሳድፋልና፥ የፍጥረትንም ሩጫ ያቃጥላል፥ በገሃነምም ይቃጠላል።
⁷ የአራዊትና የወፎች የተንቀሳቃሾችና በባሕር ያለ የፍጥረት ወገን ሁሉ በሰው ይገራል፥ ደግሞ ተገርቶአል፤
⁸ ነገር ግን አንደበትን ሊገራ ማንም ሰው አይችልም፤ የሚገድል መርዝ የሞላበት ወላዋይ ክፋት ነው።
⁹ በእርሱ ጌታንና አብን እንባርካለን፤ በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን፤
¹⁰ ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ። ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህ እንዲህ ሊሆን አይገባም።
¹¹ ምንጭስ ከአንድ አፍ የሚጣፍጥንና የሚመርን ውኃ ያመነጫልን?
¹² ወንድሞቼ ሆይ፥ በለስ ወይራን ወይስ ወይን በለስን ልታፈራ ትችላለችን? ከጨው ውኃም ጣፋጭ ውኃ አይወጣም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 10
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ በቂሣርያም ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራ የመቶ አለቃ የሆነ ቆርኔሌዎስ የሚሉት አንድ ሰው ነበረ።
² እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ለሕዝብም እጅግ ምጽዋት የሚያደርግ ወደ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ የሚጸልይ ነበረ።
³ ከቀኑም ዘጠኝ ሰዓት ያህል፦ ቆርኔሌዎስ ሆይ የሚለው የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ሲገባ በራእይ በግልጥ አየው።
⁴ እርሱም ትኵር ብሎ ሲመለከተው ደንግጦ፦ ጌታ ሆይ፥ ምንድር ነው? አለ። መልአኩም አለው፦ ጸሎትህና ምጽዋትህ በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያ እንዲሆን አረገ።
⁵ አሁንም ወደ ኢዮጴ ሰዎችን ልከህ ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን አስመጣ።
⁶ እርሱ ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ዘንድ እንግድነት ተቀምጦአል፤ ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል።
⁷ የተናገረውም መልአክ በሄደ ጊዜ፥ ከሎሌዎቹ ሁለቱን፥ ከማይለዩትም ጭፍሮቹ እግዚአብሔርን የሚያመልክ አንዱን ወታደር ጠርቶ፥
⁸ ነገሩን ሁሉ ተረከላቸው ወደ ኢዮጴም ላካቸው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_11_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ወይርአዩ አሕዛብ በቅድመ አዕይንቲነ። በቀለ ደሞሙ፡ለአግብርቲከ፡ዘተክዕወ። ይባዕ ቅድሜከ ገዐሮሙ ለሙቁሓን"። መዝ 78፥10-11።
"አሕዛብ፦ አምላካቸው ወዴት ነው? እንዳይሉ፥ የፈሰሰውን የባሪያዎችህን ደም በቀል በዓይኖቻችን ፊት አሕዛብ ይወቁ።
የእስረኞች ጩኸት ወደ ፊትህ ይግባ፤ እንደ ክንድህም ታላቅነት ሊገደሉ የተፈረደባቸውን አድን"። መዝ 78፥10-11።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_11_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 21
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² ከዚህም ሁሉ በፊት እጃቸውን በላያችሁ ይጭናሉ ያሳድዱአችሁማል፤ ስለ ስሜም ወደ ምኵራብና ወደ ወኅኒ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ ወደ ነገሥታትና ወደ ገዥዎችም ይወስዱአችኋል፤
¹³ ይህም ለምስክርነት ይሆንላችኋል።
¹⁴ ስለዚህ እንዴት እንድትመልሱ አስቀድማችሁ እንዳታስቡ በልባችሁ አኑሩት፤
¹⁵ ወደረኞቻችሁ ሁሉ ሊቃወሙና ሊከራከሩ የማይችሉትን አፍና ጥበብ እሰጣችኋለሁና።
¹⁶ ወላጆችም ስንኳ ወንድሞችም ዘመዶችም ወዳጆችም አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ ከእናንተም አንዳንዱን ይገድላሉ፤
¹⁷ በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።
¹⁸ ከራሳችሁም አንዲት ጠጉር ስንኳ አትጠፋም፤
¹⁹ በመታገሣችሁም ነፍሳችሁን ታገኛላችሁ።
²⁰ ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ባስልዮስ_ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ፋሲለደስ የዕረፍት በዓል፣ የቅድስት ታዖድራ፣ የቅዱስ ቀርኔሌዎስ፣ የቅድስት በነፍዘዝ ሰማዕትና የቅዱሳን ሱርስ፣ አጤኬዎስ፣ መስተሐድራ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_12

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ዐሥራ ሁለት መላእክት አለቃ #የቅዱስ_ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው፣ #ጉባኤ_ኤፌሶን የቅዱሳን የሁለት መቶ ኤጲስቆጶሳት ስብሰባ ሆነ

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሚካኤል_ሊቀ_መላእክት

መስከረም ዐሥራ ሁለት በዚች ቀን የመላእክት አለቃ የቅዱስ ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው።

በዚችም ቀን ክብር ይግባውና #እግዚአብሔር ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢይ ኢሳይያስ ላከው ይቅርም ብሎት ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሕዝቅያስ ሒዶ #እግዚአብሔር ይቅር እንዳለውና ከደዌው እንዳዳነው በዕድሜውም ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እንደ ጨመረለት ይነግረው ዘንድ አዘዘው። ንጉሱም ሚስት አግብቶ ምናሴን እስከወለደው ድረስ እንዲሁ ሆነ።

ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ለንጉሥ ሕዝቅያስ ያደረገለት ተአምር፡-

ከጻድቁ ንጉሥ ከቅዱስ ዳዊት በኋላ በእስራኤል እንደ ሕዝቅያስ ያለ ሌላ ጻድቅ ንጉሥ አልተነሣም፡፡ ከሕዝቅያስ በኋላ የተነሡት ሁሉም ጣዖትን አምልከዋል፣ ለጣዖታቱም የሚሆን መሠዊያ ሠርተዋል፡፡ ንጉሡ ሕዝቅያስ በነገሠ ጊዜ ግን ጣዖታትን ሰባብሯቸዋል፣ የእስራኤል ልጆች ያመልኩት የነበረውን የነሐስ እባብ ቆራርጦታል፡፡ #እግዚአብሔርንም በማመኑ መንግሥቱ እጅግ ሰምሮለታል፡፡ #እግዚአብሔርም ያሳጣው በጎ ነገርም የለም፡፡

ሕዝቅያስ በነገሠ በ14ኛው ዘመን የፋርሱ ነጉሥ ሰናክሬም መጥቶ ኢየሩሳሌምን ከበባት፡፡ ይህም ሰናክሬም በወቅቱ እንደ እርሱ ያለ ኃይለኛ የለም ነበርና ሁሉም የምድር ነገሥታት ይፈሩትና ይገዙለት ነበር፡፡ ሕዝቅያስም ከሰናክሬም ግርማና የጦሩ ብዛት የተነሣ ፈርቶ ኢየሩሳሌምን እንዳያጠፋት ብዙ ወርቅና ብር እጅ መንሻ ቢልክለትም ሰናክሬም ግን እጅ መንሻውን አልቀበልም ብሎ ኢየሩሳሌምን ያጠፋ ዘንድ ተነሣ፡፡ ለሕዝቅያስም ‹‹አምላካችሁ #እግዚአብሔር ከእኔ እጅ ሊያደናችሁ ከቶ አይችልም›› የሚል የስድብን ቃል ላከለት፡፡

ሁለተኛም በልዑል #እግዚአብሔር ላይ የስድብን ቃል ጽፎ ደብዳቤ ላከለት፡፡ ሕዝቅያስም ይህን ሲሰማ ወደ #እግዚአብሔር ቤት ገብቶ አለቀሰ፡፡ ልብሱንም ቀዶ ማቅ በመልበስ የሰናክሬምን ድፍረትና በኢየሩሳሌምና በሕዝቧ ላይ ሊያደርስ ያሰበውንም ጥፋት ወደ #እግዚአብሔር አሳሰበ፡፡ ቀጥሎም ሕዝቅያስ ሰናክሬም የተናገረውን ይነግሩት ዘንድ ስለ ሕዝቡም እንዲጸልይ ለነቢዩ ኢሳይያስ መልእክት ላከበት፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስም ወደ #እግዚአብሔር አመለከተ፡፡

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ሚካኤል ስለ ንጉሡ ለነቢዩ መልእክትን አመጣለት፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስም የመጣለትን መልስ እንዲህ ብሎ ለሕዝቅያስ ላከለት፡- ‹‹ልብህን አጽና፣ አትፍራ፡፡ በዓለሙ ሁሉ እንደ እርሱ ያለ ያልተሰማ ዕፁብ ድንቅ የሆነ ሥራ በሰናክሬም ላይ #እግዚአብሔር ይሠራል›› አለው፡፡ ከዚህም በኋላ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ከ #እግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ መጥቶ 185,000 (መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ) የፋርስ ሠራዊቶችን በአንድ ሌሊት ገደላቸው፡፡ 2ኛ ነገ 17፣19፡፡ የለኪሶ ሰዎችም ሲነጋ በተነሡ ጊዜ ምድሪቱን በእሬሳ ተሞልታ ስላገኟት በድንጋጤና በፍርሃት ከንጉሣ ጋር ሸሽተው ነነዌ አገር ገቡ፡፡

ንጉሡ ሰናክሬምም ወደ አምላኩ ወደ ጣዖቱ ቤት ገብቶ ሲጸልይ የገዛ ልጆቹ በሰይፍ መትተው ገደሉትና ወደ አራራት ኩበለሉ፡፡2ኛ ነገ ምዕራፍ 19፡፡ ንጉሥ ሕዝቅያስም ከሰናክሬም እጅ ያዳነውን #እግዚአብሔርን አመሰገነ፡፡

ከዚህም በኋላ ሕዝቅያስ ታሞ ለሞት በደረሰ ጊዜ ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ እርሱ መጥቶ ‹‹ #እግዚአብሔር ‹ትሞታለህ እንጂ አትድንም› ብሎሃል›› አለው፡፡ ነገር ግን ሕዝቅያስ አሁንም ልብሱንም ቀዶ ማቅ በመልበስ ጸሎቱን ወደ #እግዚአብሔር አቀረበ፡፡ በዚህ ጊዜ ነው ቅዱስ ሚካኤል #እግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ መጥቶ ነቢዩ ኢሳይያስን ወደ ንጉሡ ሕዝቅያስ ሄዶ በዕድሜው ላይ 15 ዓመት እንደተጨመረለት እንዲነግረው ያዘዘው፡፡

መልአኩ እንዳዘዘው ነቢዩ ኢሳይያስ ንጉሥ ሕዝቅያስን " #እግዚአብሔር የአባትህ የዳዊት አምላክ ጸሎትህን ሰማሁ፣ ዕንባህንም አየሁ፣ እነሆ እኔ አድንሃለሁ፡፡ በዘመኖችህም 15 ዓመት ጨምሬልሃለሁ፡፡ ከፋርስ ንጉሥ እጅም አድንሃለሁ፡፡ ይህችን አገር ስለ እኔና ስለ ባለሟሌ ዳዊት አጽንቼ እጠብቃታለሁ›› ብሎሃል ብሎ የተላከውን ነገረው፡፡ ከዚህም በኃላ ንጉሥ ሕዝቅያስ የ #እግዚአብሔር ኃይል ስላደረበት የምድር ነገሥታት ሁሉ ፈርተውት እየተገዙለት እጅ መንሻን ያገቡለት ጀመር፡፡ ንጉሡም ዕድሜው ከተጨመረለት በኃላ ሚስት አግብቶ ምናሴን እስኪወልድ ድረስ ቆየ፡፡ በመንበረ መንግሥቱም 29 ዓመት ነግሦ ከኖረ በኋላ #እግዚአብሔርን አገልግሎ በሰላም ዐረፈ፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ጉባኤ_ኤፌሶን

በዚችም ቀን ደግሞ በኤፌሶን ከተማ የቅዱሳን የሁለት መቶ ኤጲስቆጶሳት ስብሰባ ሆነ ይህም ለታላላቆች ጉባኤያት ሦስተኛ ነው።

ስብሰባቸውም የተደረገው የታላቁ ቴዎዶስዮስ ልጅ አርቃድዮስ የወለደው ታናሹ ቴዎዶስዮስ በነገሠ በሃያ ዓመት ነው። የስብሰባቸውም ምክንያት የቊስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት በሆነ በንስጥሮስ ነው። እርሱ ስቶ እንዲህ ብሏልና እመቤታችን #ድንግል_ማርያም አምላክን በሥጋ አልወለደችውም እርሷ ዕሩቅ ሰውን ወልዳ ከዚህ በኋላ በውስጡ የ #እግዚአብሔር ልጅ አደረበት ከሥጋ ጋር በመዋሐድ አንድ አልሆነም በፈቃድ አደረበት እንጂ። ስለዚህም ክርስቶስ ሁለት ጠባይ ሁለት ባህርይ አሉት የተረገመ የከ*ሐዲ ንስጥሮስ የከፋች ሃይማኖቱ ይቺ ናት።

ስለ እርሱም የተሰበሰቡ እሊህ አባቶች ከእርሱ ጋር ተከራከሩ ከቅድስት #ድንግል_ማርያም የተወለደው አምላክ እንደሆነ ቅዱስ ገብርኤል መልአክ በአበሠራት ጊዜ ከተናገረው ቃል ምስክር አመጡ። እንዲህ የሚል #እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው ከአንቺ የሚወለደውም ጽኑዕ ከሀሊ ነው የልዑል #እግዚአብሔር ልጅም ይባላል ።

ዳግመኛም እነሆ #ድንግል በድንግልና ፀንሳ ወንድ ልጅን ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች ብሎ በትንቢቱ ከተናገረው ከኢሳይያስ ቃል ሁለተኛም ከእሴይ ዘር ይተካል ከእርሱም ለአሕዛብ ተስፋቸው ይሆናል።

ዳግመኛም የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ቄርሎስ ገሠጸው መከረው ስለዚህም እንዲህ ሲል አስረዳው ክብር ይግባውና የ #ክርስቶስ የመለኮቱና የትስብእቱ ባሕርያት በመዋሐድ አንድ ከሆኑ በኋላ አይለያዩም አንድ ባሕርይ በመሆን ጸንተው ይኖራሉ እንዲህም አምነን ሰው የሆነ #እግዚአብሔር ቃል አንዲት ባሕርይ ነው እንላለን።

ከ*ሀዲ ንስጥሮስ ግን ከክፉ ሐሳቡ አልተመለሰም ከሹመቱም ሽረው እንደሚአሳድዱትም ነገሩት። እርሱ ግን የጉባኤውን አንድነት አልሰማም ስለዚህም ከሹመቱ ሽረው ረግ*መው ከቤተ ክርስቲያን ለይተው አሳደ*ዱት ወደ ላይኛውም ግብጽ ሒዶ በዚያ ምላሱ ተጎልጒሎ እንደ ውሻ እያለከለከ በክፉ አሟሟት ሞተ።

እሊህም ሁለት መቶ ኤጲስቆጶሳት አባቶች ሃይማኖትን አጸኑዋት በዚህም ጉባኤ ውስጥ እንዲህ ብለው ጻፉ እመቤታችን ቅድስት #ድንግል_ማርያም ከእርሷ ሰው የሆነውን የ #እግዚአብሔርን አካላዊ ቃል በሥጋ ወለደችው።

ከዚህም በኋላ ሥርዓትን ሠርተው ሕግንም አርቅቀው በእጆቻቸው ጽፈው ለምእመናን ሰጡ። እኛም የሕይወትንና የድኅነትን መንገድ ይመራን ዘንድ #እግዚአብሔርን እንለምነው። ለእርሱም ክብር ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።
በተጨማሪ በዚች ሰማዕት #ቅዱስ_አፍላሆስ መታሰቢያውና የሥጋው ፍልሰት ነው። የእስክድርያ አገር የሆኑ ባልንጀሮቹ ሰማዕታትም መታሰቢያቸው ነው። #የሰማዕታት_ቅዱሳን_ሉዩራስና_ባሌኒኮስ#ቅዱስ_ኢያቄምና_ቅድስት_ሐናም መታሰቢያቸው ነው።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን አማላጅነት ይማረን ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም_12 እና #ከገድላት_አንደበት)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_12_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ቆሮ 9
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ለቅዱሳን ስለሚሆነው አገልግሎት ልጽፍላችሁ አያስፈልግምና፤
² በጎ ፈቃዳችሁን አውቄአለሁና፤ ስለዚህም፦ አካይያ ከአምና ጀምሮ ተዘጋጅቶአል ብዬ ለመቄዶንያ ሰዎች በእናንተ እመካለሁ፥ ቅንዓታችሁም የሚበዙቱን አነሣሥቶአል።
³ ነገር ግን ለእነርሱ እንዳልሁ፥ የተዘጋጃችሁ ትሆኑ ዘንድ በዚህም ነገር ስለ እናንተ ያለው ትምክህታችን ከንቱ እንዳይሆን ወንድሞችን እልካለሁ፤
⁴ ምናልባት የመቄዶንያ ሰዎች ከእኔ ጋር ቢመጡ፥ ያልተዘጋጃችሁም ሆናችሁ ቢያገኙአችሁ፥ እናንተ እንድታፍሩ አላልንም እኛ ግን በዚህ እምነታችን እንድናፍር አይሁን።
⁵ እንግዲህ እንደ በረከት ሆኖ ከስስት የማይሆን ይህ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ አስቀድመው ወደ እናንተ መጥተው፥ አስቀድማችሁ ተስፋ የሰጣችሁትን በረከት አስቀድመው እንዲፈጽሙ ወንድሞችን እለምን ዘንድ እንዲያስፈልገኝ አሰብሁ።
⁶ ይህንም እላለሁ፦ በጥቂት የሚዘራ በጥቂት ደግሞ ያጭዳል፥ በበረከትም የሚዘራ በበረከት ደግሞ ያጭዳል።
⁷ እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፥ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም።
⁸-⁹ በተነ፥ ለምስኪኖች ሰጠ፥ ጽድቁ ለዘላለም ይኖራል ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ እግዚአብሔር፥ ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ፥ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል።
¹⁰ ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል ያበረክትላችሁማል፥ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል፤
¹¹ በእኛ በኩል ለእግዚአብሔር የምስጋና ምክንያት የሚሆነውን ልግስና ሁሉ እንድታሳዩ በሁሉ ነገር ባለ ጠጎች ትሆናላችሁ።
¹² የዚህ ረድኤት አገልግሎት ለቅዱሳን የሚጎድላቸውን በሙሉ የሚሰጥ ብቻ አይደለምና፥ ነገር ግን ደግሞ በብዙ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይበዛል፤
¹³ በዚህ አገልግሎት ስለ ተፈተናችሁ፥ በክርስቶስ ወንጌል በማመናችሁ ስለሚሆን መታዘዝ እነርሱንና ሁሉንም ስለምትረዱበት ልግስና እግዚአብሔርን ያከብራሉ፥
¹⁴ ራሳቸውም ስለ እናንተ ሲያማልዱ፥ በእናንተ ላይ ከሚሆነው ከሚበልጠው ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሣ ይናፍቁአችኋል።
¹⁵ ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ያዕቆብ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ አሁንም እናንተ ባለ ጠጎች፥ ስለሚደርስባችሁ ጭንቅ ዋይ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ።
² ሀብታችሁ ተበላሽቶአል፥ ልብሳችሁም በብል ተበልቶአል።
³ ወርቃችሁም ብራችሁም ዝጎአል፥ ዝገቱም ምስክር ይሆንባችኋል ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላል። ለኋለኛው ቀን መዝገብን አከማችታችኋል።
⁴ እነሆ፥ እርሻችሁን ያጨዱት የሠራተኞች ደመወዝ በእናንተ ተቀምቶ ይጮኻል፥ የአጫጆችም ድምፅ ወደ ጌታ ፀባዖት ጆሮ ገብቶአል።
⁵ በምድር ላይ ተቀማጥላችኋል በሴሰኝነትም ኖራችኋል፤ ለእርድ ቀን እንደሚያወፍር ልባችሁን አወፍራችኋል።
⁶ ጻድቁን ኰንናችሁታል ገድላችሁትማል፤ እናንተን አይቃወምም።
⁷ እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሡ። እነሆ፥ ገበሬው የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እስኪቀበል ድረስ እርሱን እየታገሠ የከበረውን የመሬት ፍሬ ይጠብቃል።
⁸ እናንተ ደግሞ ታገሡ፥ ልባችሁንም አጽኑ፤ የጌታ መምጣት ቀርቦአልና።
⁹ ወንድሞች ሆይ፥ እንዳይፈረድባችሁ እርስ በርሳችሁ አታጉረምርሙ፤ እነሆ፥ ፈራጅ በደጅ ፊት ቆሞአል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 19
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²¹ ይህም በተፈጸመ ጊዜ ጳውሎስ፦ ወደዚያ ደርሼ ሮሜን ደግሞ አይ ዘንድ ይገባኛል ብሎ በመቄዶንያና በአካይያ አልፎ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ በመንፈስ አሰበ።
²² ከሚያገለግሉትም ሁለቱን ጢሞቴዎስንና ኤርስጦንን ወደ መቄዶንያ ልኮ ራሱ በእስያ ጥቂት ቀን ቆየ።
²³ በዚያም ጊዜ ስለዚህ መንገድ ብዙ ሁከት ሆነ።
²⁴ ብር ሠሪ የሆነ ድሜጥሮስ የሚሉት አንድ ሰው የአርጤምስን ቤተ መቅደስ ምስሎች በብር እየሠራ ለአንጥረኞች እጅግ ትርፍ ያገኝ ነበርና፤
²⁵ እነዚህንም ይህንም የሚመስለውን ሥራ የሠሩትን ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፦ ሰዎች ሆይ፥ ትርፋችን በዚህ ሥራ እንደ ሆነ ታውቃላችሁ።
²⁶ ይህም ጳውሎስ፦ በእጅ የተሠሩቱ አማልክት አይደሉም ብሎ፥ በኤፌሶን ብቻ ሳይሆን ከጥቂት ክፍል በቀር በእስያ ሁሉ ብዙ ሕዝብን እንደ አስረዳና እንደ አሳተ አይታችኋል ሰምታችሁማል።
²⁷ ሥራችንም እንዲናቅ ብቻ አይደለም፥ እስያ ሁሉ ዓለሙም የሚያመልካት የታላቂቱ አምላክ የአርጤምስ መቅደስ ምናምን ሆኖ እንዲቆጠር እንጂ፥ ታላቅነትዋም ደግሞ እንዳይሻር ያስፈራል።
²⁸ ይህንም በሰሙ ጊዜ ቍጣ ሞላባቸው፦ የኤፌሶን አርጤምስ ታላቅ ናት እያሉም ጮኹ።
²⁹ ከተማውም በሙሉው ተደባለቀ፥ የመቄዶንያም ሰዎች የጳውሎስን ጓደኞች ጋይዮስንና አርስጥሮኮስን ከእነርሱ ጋር ነጥቀው በአንድ ልብ ሆነው ወደ ጨዋታ ስፍራ ሮጡ።
³⁰ ጳውሎስም ወደ ሕዝቡ ይገባ ዘንድ በፈቀደ ጊዜ ደቀ መዛሙርት ከለከሉት።
³¹ ከእስያም አለቆች ወዳጆቹ የሆኑት አንዳንዶች ደግሞ ወደ እርሱ ልከው ወደ ጨዋታ ስፍራ ራሱን እንዳይሰጥ ለመኑት።
³² ወዲያና ወዲህም እያሉ ይጮኹ ነበር፤ በጉባኤው ድብልቅልቅ ሆኖ የሚበልጡት ስንኳ ስለ ምን እንደተሰበሰቡ አላወቁም ነበርና።
³³ አይሁድም ሲያቀርቡት፥ እስክንድሮስን ከሕዝቡ መካከል ወደ ፊት ገፉት፤ እስክንድሮስም በእጁ ጠቅሶ በሕዝብ ፊት እንዲምዋገትላቸው ወደደ።
³⁴ አይሁዳዊ ግን እንደ ሆነ ባወቁ ጊዜ፥ ሁሉ በአንድ ድምፅ፦ የኤፌሶን አርጤምስ ታላቅ ናት እያሉ ሁለት ሰዓት ያህል ጮኹ።
³⁵ የከተማይቱም ጸሐፊ ሕዝቡን ጸጥ አሰኝቶ እንዲህ አለ፦ የኤፌሶን ሰዎች ሆይ፥ የኤፌሶን ከተማ ለታላቂቱ አርጤምስ ከሰማይም ለወረደው ጣዖትዋ የመቅደስ ጠባቂ መሆንዋን የማያውቅ ሰው ማን ነው?
³⁶ ይህንም የሚክደው ከሌለ፥ ጸጥ እንድትሉና አንዳች በችኮላ እንዳታደርጉ ይገባል።
³⁷ የመቅደስን ዕቃ ያልሰረቁ አምላካችንንም ያልሰደቡ እነዚህን ሰዎች አምጥታችኋቸዋልና።
³⁸ ድሜጥሮስና ከእርሱ ጋር ያሉት አንጥረኞች ግን በሰው ላይ ነገር እንዳላቸው፥ የመጋቢያ ቀንና አገረ ገዢዎች አሉ፤ እርስ በርሳቸው ይምዋገቱ።
³⁹ ስለ ሌላ ነገር እንደ ሆነ ግን አንዳች ብትፈልጉ፥ በተደነገገው ጉባኤ ይፈታል።
⁴⁰ ዛሬ ስለ ተደረገው፦ ሁከት ነው ሲሉ እንዳይከሱን ያስፈራልና፤ ስለዚህም ስብሰባ ምላሽ መስጠት አንችልም፥ ምክንያት የለምና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_12_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ምድርኒ ትሁብ ፍሬሃ። ወይባርከነ እግዚአብሔር አምላክነ ወይባርከነ እግዚአብሔር"። መዝ.66÷6-7
"ምድር ፍሬዋን ሰጠች፤ እግዚአብሔር አምላካችንም ይባርከናል። እግዚአብሔር ይባርከናል፥ የምድርም ዳርቻ ሁሉ ይፈሩታል"።
መዝ.66÷6-7
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_12_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማርቆስ 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁴ አላቸውም፦ ምን እንድትሰሙ ተጠበቁ። በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል ለእናንተም ይጨመርላችኋል።
²⁵ ላለው ይሰጠዋልና፤ ከሌለውም ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።
²⁶ እርሱም አለ፦ በምድር ዘርን እንደሚዘራ ሰው የእግዚአብሔር መንግሥት እንደዚህ ናት ሌሊትና ቀን ይተኛልም ይነሣልም፥
²⁷ እርሱም እንዴት እንደሚሆን ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል ያድግማል።
²⁸ ምድሪቱም አውቃ በመጀመሪያ ቡቃያ ኋላም ዛላ ኋላም በዛላው ፍጹም ሰብል ታፈራለች።
²⁹ ፍሬ ግን ሲበስል መከር ደርሶአልና ወዲያው ማጭድ ይልካል።
³⁰ እርሱም አለ፦ የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን እናስመስላታለን? ወይስ በምን ምሳሌ እንመስላታለን?
³¹ እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት ናት፥ እርስዋም በምድር በተዘራች ጊዜ በምድር ካለ ዘር ሁሉ ታንሳለች፤ በተዘራችም ጊዜ ትወጣለች ከአትክልትም ሁሉ የምትበልጥ ትሆናለች፥
³² የሰማይ ወፎችም በጥላዋ ሊሰፍሩ እስኪችሉ ታላላቅ ቅርንጫፎች ታደርጋለች።
³³ መስማትም በሚችሉበት መጠን እነዚህን በሚመስል በብዙ ምሳሌ ቃሉን ይነግራቸው ነበር፤ ያለ ምሳሌ ግን አልነገራቸውም፥
³⁴ ለብቻቸውም ሲሆኑ ነገሩን ሁሉ ለገዛ ደቀ መዛሙርቱ ይፈታላቸው ነበር።
³⁵ በዚያም ቀን በመሸ ጊዜ፦ ወደ ማዶ እንሻገር አላቸው።
³⁶ ሕዝቡንም ትተው በታንኳ እንዲያው ወሰዱት፥ ሌሎች ታንኳዎችም ከእርሱ ጋር ነበሩ።
³⁷ ብርቱ ዐውሎ ነፋስም ተነሣና ውኃ በታንኳይቱ እስኪሞላ ድረስ ማዕበሉ በታንኳይቱ ይገባ ነበር።
³⁸ እርሱም በስተኋላዋ ትራስ ተንተርሶ ተኝቶ ነበር፤ አንቅተውም፦ መምህር ሆይ፥ ስንጠፋ አይገድህምን? አሉት።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ዮሐንስ_ወልደ_ነጎድጓድ ወይም የ #ቅዱስ_ያዕቆብ_ዘሥሩግ ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ሚካኤል ወራዊ በዓልና የኤፌሶን ጉባኤ የተሰበሰቡ የ200 ኤጲስቆጶሳት በዓልና ዕለተ ሰንበት ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_13

#ቅዱስ_ባስልዮስ_ዘቂሣርያ

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ዐሥራ ሦስት በዚህች ቀን ታላቅና ቅዱስ የሆነ የቂሣርያ ሊቀ ጳጳሳት ባስልዮስ ላደረገው ተአምር መታሰቢያ ሆነ።

ይህም እንዲህ ነው አንድ ጐልማሳ አገልጋይ የጌታውን ልጅ ስለወደዳት ልቡ እርሷን ወዶ እንደ እሳት እስከ ነደደ ድረስ እርሷንም ከመውደዱ ብዛት የተነሣ ወደ አንድ ከሀዲ ሥራየኛ ሔደ። ሥራየኛውም የክህደት ደብዳቤ ጽፎ ሰጠው። ወደ አረሚ መቃብርም ሒዶ በመንፈቀ ሌሊት ደብዳቤዋን ይዞ ወደላይ እጁን አንሥቶ በዚያ እንዲቆም አዘዘው።

ይህም አገልጋይ ይህን ነገር ተቀብሎ ያ መሠርይ እንዳዘዘው አደረገ። በዚያንም ጊዜ ከሰይጣናት አንዱ መጥቶ ወደ አለቃቸው ወስዶ አደረሰው ያቺንም የክህደት ደብዳቤ ከእጁ ወሰደ። እንዲህም ብሎ ጠየቀው "ንጉሥህ #ክርስቶስን ትክደ*ዋለህን? ፈቃድህን ከፈጸምኩልህ በኋላ ወደ እርሱ አትመለስምን?" ይህም ጐስቋላ ባሪያ "አዎን ጌታዬ ያዘዝከኝን ሁሉ አደርጋለሁ" አለው። መስሐቲ ዲያብሎስም ይህን ልታደርግ በእጅህ ደብዳቤ ጻፍልኝ አለው። እርሱም በከበረ ደሙ የዋጀውን የክብር ባለቤት #ክርስቶስን ክዶ በደብዳቤ ውስጥ የክህደቱን ቃል ጻፈለት።

በዚያንም ጊዜ ሰይጣን በጌታው ልጅ ልብ ውስጥ የፍትወት እሳትን አነደደ ይህንንም ባሪያ እጅግ ወደደችው ከእርሱም መታገሥ አልተቻላትም። ወደ አባቷ በመጮህ በግልጥ ከዕገሌ ባሪያህ ጋር ካላጋባኸኝ አለዚያ ራሴን እገድላለሁ ትለዋለች እንጂ መታገሥ አልተቻላትም። አባትና እናቷም ፈጽሞ አዘኑ በምንም በምን ሊያስታግሥዋት አልቻሉም። የዚያም አገልጋይ ፍቅሩ በየዕለቱ በልቧ ይጨመር ነበር እንጂ። ስለዚህም ራሷን እንዳትገድል አባቷ ፈራ ለዚያ ባሪያ ሰጠው። እርሱም የጌታውን ልጅ ተቀብሎ ወደቤቱ አስገባት። ከርሷ ጋር ያለውን ፍላጎቱንም ፈጸመ። ከእርሱም ጋር ረጅም ጊዜ ከኖረች በኋላ አባትና እናቷም ይቅር ብሎ ኀዘናቸውን ከላያቸው ያርቅላቸው ዘንድ ወደ #እግዚአብሔር ኀዘንንና ልቅሶን አብዝተው ነበር።

ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ጩኸታቸውን ሰማ ልመናቸውንም ተቀብሎ ይህ የወደደችው አገልጋይ ጐልማሳ ክርስቲያን እንዳልሆነ አስገነዘባት ከእርሷ ጋር በነበረበት በዚህ በረጅም ዘመን አንዲት ቀን እንኳ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሔድ ሥጋውንና ደሙንም ሲቀበል ወይም አዳኝ በሆነ በ #መስቀል ምልክት ራሱን ሲአማትብ እርሷ አላየችውም።

ስለእምነቱም ጠየቀችው ግን አልገለጠላትም እርሷም እንዲህ አለችው "አንተ ክርስቲያን ከሆንክ ና በአንድነት ወደ ቤተ ክርስቲያን እንሒድና በፊቴ ቅዱስ ቊርባንን ተቀበል።" እንዲህም በአስገደደችው ጊዜ ስለርሷ ያደረገውን ሁሉ ወደ ሥራየኛ እንደሔደም በሰይጣንም አምኖ እምነቱንም በክርታስ ጽፎ ያንን ክርታስ ለሰይጣን እንደ ሰጠው ነገራት።

ይህንንም ነገር ከእርሱ በሰማች ጊዜ ደነገጠች መሪር ልቅሶንም አለቀሰች ራሷንም በማወዛወዝ እጅግ ተጸጽታ አዘነች። ያን ጊዜም ፈጥና ተነሣች የቤተ ክርስቲያን ምሰሶ ወደሆነው ወደ ሀገርዋ ሊቀ ጳጳሳት ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ሔደች ከእግሩ በታችም ወድቃ ሰገደችለት በላይዋ የደረሰውን ሁሉ አስረዳችው ለሰው ልጆች ጠላት ከሆነ ከሠይጣን እጅ ፈጽሞ ያድናት ዘንድ ብዙ በማልቀስ ለመነችው።

ቅዱስ ባስልዮስም ባሏ የሆነውን ባርያ ወደርሱ ልኮ አስመጣውና ጠየቀው እርሱም የሠራውን ሁሉ አስረዳው ቅዱስ ባስልዮስም "ተመልሰህ ክርስቲያን ልትሆን ከሰይጣንም እጅ ልትድን ትወዳለህን?" አለው ያም ባርያ "ጌታዬ ይሆንልኛልን?" አለ ይህ ቅዱስ አባትም የፈጣሪህን ስም እየጠራህ ልብህን አጽና አለው።

ከዚህም በኋላ ከእርሱ ዘንድ በአንድ ቦታ ዘጋበት በ #መስቀል ምልከትም አማተበበት እንዲጸልይም አዘዘው ራሱ ቅዱስ ባስልዮስም ስለርሱ ጸለየ። ከሦስት ቀኖች በኋላም ጎበኘው እንዲህም አለው በእሊህ በሦስት ቀኖች የደረሰብህ ምንድን ነው እርሱም በላዩ በመጮህ ሠይጣናት ሲያስፈራሩት ያንንም ደብዳቤ ሲአሳዩትና በእርሱ ላይ ሲቆጡ በመከራ ውስጥ እንደኖረ ነገረው ቅዱስ ባስልዮስም ከእሳቸው ቁጣ የተነሣ አትፍራ እግዚአብሔር ይረዳሃልና አጽንቶም ይጠብቅሃል አለው።

ከዚህም በኋላ ጥቂት እንጀራና ውኃ ሰጥቶ ወደ ቦታው መለሰው ቅዱስ ባስልዮስም ስለዚያ አገልጋይ ሒዶ ይጸልይ ጀመረ። ዳግመኛም ከሦስት ቀኖች በኋላ ጐበኘውና በእርሱ ላይ ምን እንደ ደረሰበት ጠየቀው ያ አገልጋይም ጩኸታቸውን እሰማለሁ ግን አላያቸውም ብሎ መለሰለት። እንጀራና ውኃም ሰጠውና መከረው ወደ ቦታውም መለሰውና ስለርሱ ሊጸልይ ቅዱስ ባስልዮስ ሔደ። እስከ አርባ ቀኖች ፍጻሜ ድረስ እንዲህ አደረገ። በአርባውም ቀን ፍጻሜ ከእርሱ ስለ ሆነው ጠየቀው ያ አገልጋይም እንዲህ አለው ቅዱስ አባቴ ሆይ ስለ እኔ ሰይጣንን ስትጣላውና ድል አድርገህ ጥለህ ስትረግጠው በዛሬዋ ሌሊት አየሁ አለው።

ቅዱስ ባስልዮስም ይህን ነገር ከእርሱ በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ አለው የገዳማቱን መነኰሳትና ካህናቱንም ጠርቶ ስለዚያ ሰው ያቺን ሌሊት መላዋን እንዲጸልዩባት አዘዛቸ። በነጋ ጊዜም ያንን አገልጋይ ወደ ቤተክርስቲያን እንዲአመጡት የዚያችንም አገር ሕዝብ ሁሉንም ሰብስቦ እጆቻቸውን ወደ ሰማይ አንሥተው አቤቱ #ክርስቶስ ማረን ይቅር በለን እያሉ ወደ #እግዚአብሔር ፈጽሞ እንዲማልዱ አዘዛቸው እንዳዘዛቸውም አደረጉ።

እንዲህም እያሉ ሲማልዱ ያ ሰው ጽፎ ለሰይጣን የሰጠው የክህደት ደብዳቤ ከሰይጣን እጅ በሕዝቡ ሁሉ ፊት ወደቀ ሁሉም ደስ ብሏቸው ምስጉን #እግዚአብሔርን አመሰገኑት የከበረ አባት ባስልዮስም ባረካቸው ሥጋውንና ደሙንም አቀብሎ ወደ ቤቶቻቸው በሰላም በፍቅር አሰናበታቸው ። እነርሱም ስለ ኃጢአታቸው ስርየትና ስለ ድኅነታቸው ፈጽሞ ደስ እያላቸው #እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ይህንን ቅዱስ አባት ባስልዮስን እያከበሩ ወደ ቤታቸው ገቡ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ አባት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_13_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ቆሮንቶስ 7
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² ሌሎችንም እኔ እላለሁ፥ ጌታም አይደለም፤ ከወንድሞች ወገን ያላመነች ሚስት ያለችው ቢኖር እርስዋም ከእርሱ ጋር ልትቀመጥ ብትስማማ፥ አይተዋት፤
¹³ ያላመነ ባል ያላት ሚስትም ብትኖር ይህ ከእርስዋ ጋር ሊቀመጥ ቢስማማ፥ አትተወው።
¹⁴ ያላመነ ባል በሚስቱ ተቀድሶአልና፥ ያላመነችም ሚስት በባልዋ ተቀድሳለች፤ አለዚያ ልጆቻችሁ ርኵሳን ናቸው፤ አሁን ግን የተቀደሱ ናቸው።
¹⁵ የማያምን ግን ቢለይ ይለይ፤ ወንድም ቢሆን ወይም እኅት እንዲህ በሚመስል ነገር አይገዙም፤ እግዚአብሔር ግን በሰላም ጠርቶናል።
¹⁶ አንቺ ሴት፥ ባልሽን ታድኚ እንደ ሆንሽ ምን ታውቂአለሽ? ወይስ አንተ ሰው፥ ሚስትህን ታድን እንደ ሆንህ ምን ታውቃለህ?
¹⁷ ብቻ ለእያንዳንዱ እግዚአብሔር እንደ ከፈለለት እያንዳንዱም እግዚአብሔር እንደ ጠራው እንዲሁ ይመላለስ። እንዲሁም በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እደነግጋለሁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ያዕቆብ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁴ ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽምግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት።
¹⁵ የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም ያስነሣዋል፤ ኃጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል።
¹⁶ እርስ በርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ። ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 19
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁷ ይህም በኤፌሶን በሚኖሩት ሁሉ በአይሁድና በግሪክ ሰዎች ዘንድ የታወቀ ሆነ፥ በሁላቸውም ላይ ፍርሃት ወደቀባቸው፥ የጌታም የኢየሱስ ስም ተከበረ፤
¹⁸ አምነውም ከነበሩት እጅግ ሰዎች ያደረጉትን እየተናዘዙና እየተናገሩ ይመጡ ነበር።
¹⁹ ከአስማተኞችም ብዙዎቹ መጽሐፋቸውን ሰብስበው በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉት፤ ዋጋውም ቢታሰብ አምሳ ሺህ ብር ሆኖ ተገኘ።
²⁰ እንዲህም የጌታ ቃል በኃይል ያድግና ያሸንፍ ነበር።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_13_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ብፁዓን እለ ተኀድገሎሙ ኃጢአቶሙ። ወእለ ኢሐሰበ ሎሙ ኵሎ ጌጋዮሙ። ብፁዕ ብእሲ ዘኢኈለቈ ሎቱ እግዚአብሔር ኃጢአቶ"። መዝ 31፥1-2።
"መተላለፉ የቀረችለት ኃጢአቱም የተከደነችለት ምስጉን ነው። እግዚአብሔር በደልን የማይቈጥርበት በመንፈሱም ሽንገላ የሌለበት ሰው ምስጉን ነው"። መዝ 31፥1-2።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_13_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
  ሉቃስ 11
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁵ እንዲህም አላቸው፦ ከእናንተ ማናቸውም ወዳጅ ያለው፥ በእኩል ሌሊትስ ወደ እርሱ ሄዶ፦ ወዳጄ ሆይ፥ ሦስት እንጀራ አበድረኝ፥
⁶ አንድ ወዳጄ ከመንገድ ወደ እኔ መጥቶ የማቀርብለት የለኝምና ይላልን?
⁷ ያም ከውስጥ መልሶ፦ አታድክመኝ፤ አሁን ደጁ ተቈልፎአል ልጆቼም ከእኔ ጋር በአልጋ ላይ አሉ፤ ተነሥቼ ልሰጥህ አልችልም ይላልን?
⁸ እላችኋለሁ፥ ወዳጅ ስለ ሆነ ተነሥቶ ባይሰጠው እንኳ፥ ስለ ንዝነዛው ተነስቶ የሚፈልገውን ሁሉ ይሰጠዋል።
⁹ እኔም እላችኋለሁ፦ ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል።
¹⁰ የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልግም ያገኛል፥ መዝጊያውንም ለሚያንኳኳው ይከፈትለታል።
¹¹ አባት ከሆናችሁ ከእናንተ ከማንኛችሁም ልጁ እንጀራ ቢለምነው፥ እርሱም ድንጋይ ይሰጠዋልን? ዓሣ ደግሞ ቢለምነው በዓሣ ፋንታ እባብ ይሰጠዋልን?
¹² ወይስ እንቍላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን?
¹³ እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ፥ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው?
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ 
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ባስልዮስ ቅዳሴ ነው። መልካም በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2024/09/22 23:17:59
Back to Top
HTML Embed Code: