Telegram Web Link
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ሐምሌ_21_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ቲቶ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹-² ለገዦችና ለባለ ሥልጣኖች የሚገዙና የሚታዘዙ፥ ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ፥ ማንንም የማይሰድቡ፥ የማይከራከሩ፥ ገሮች፥ ለሰው ሁሉ የዋህነትን ሁሉ የሚያሳዩ እንዲሆኑ ኣሳስባቸው።
³ እኛ ደግሞ አስቀድመን የማናስተውል ነበርንና፤ የማንታዘዝ፥ የምንስት፥ ለምኞትና ለልዩ ልዩ ተድላ እንደ ባሪያዎች የምንገዛ፥ በክፋትና በምቀኝነት የምንኖር፥ የምንጣላ፥ እርስ በርሳችን የምንጠላላ ነበርን።
⁴ ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ፥
⁵ እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፤
⁶-⁷ ያን መንፈስም፥ በጸጋው ጸድቀን በዘላለም ሕይወት ተስፋ ወራሾች እንድንሆን፥ በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ አትርፎ አፈሰሰው።
⁸ ቃሉ የታመነ ነው። እግዚአብሔርንም የሚያምኑት በመልካም ሥራ በጥንቃቄ እንዲጸኑ፥ እነዚህን አስረግጠህ እንድትናገር እፈቅዳለሁ። ይህ መልካምና ለሰዎች የሚጠቅም ነው፤
⁹ ነገር ግን ሞኝነት ካለው ምርመራና ከትውልዶች ታሪክ ከክርክርም ስለ ሕግም ከሚሆን ጠብ ራቅ፤ የማይጠቅሙና ከንቱዎች ናቸውና፤
¹⁰-¹¹ መለያየትን የሚያነሣ ሰው ጠማማ እንዲሆን በራሱም ላይ ፈርዶ ኃጢአትን እንዲያደርግ አውቀህ፥ አንድ ጊዜ ሁለት ጊዜም ከገሠጽኸው በኋላ እንዲህ ከሚመስል ሰው ራቅ።
¹² አርጢሞንን ወይም ቲኪቆስን ወደ አንተ ስልክ፥ ወደ ኒቆጵልዮን ወደ እኔ እንድትመጣ ትጋ፤ በዚያ ልከርም ቈርጬአለሁና።
¹³ ሕግ አዋቂውን ዜማስንና አጵሎስን ምንም እንዳይጎድልባቸው በጉዞአቸው ተግተህ እርዳ።
¹⁴ ከወገናችንም ያሉት ደግሞ ፍሬ ቢሶች ሆነው እንዳይቀሩ፥ የግድ ስለሚያስፈልገው ነገር በመልካም ሥራ እንዲጸኑ ይማሩ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁶ እንደ ሰዎች በሥጋ እንዲፈረድባቸው በመንፈስ ግን እንደ እግዚአብሔር እንዲኖሩ ስለዚህ ምክንያት ወንጌል ለሙታን ደግሞ ተሰብኮላቸው ነበርና።
⁷ ዳሩ ግን የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቦአል። እንግዲህ እንደ ባለ አእምሮ አስቡ፥
⁸ ትጸልዩም ዘንድ በመጠን ኑሩ፤ ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ።
⁹ ያለ ማንጐራጐር እርስ በርሳችሁ እንግድነትን ተቀባበሉ፤
¹⁰ ልዩ ልዩን የእግዚአብሔርን ጸጋ ደጋግ መጋቢዎች እንደ መሆናችሁ፥ እያንዳንዳችሁ የጸጋን ስጦታ እንደ ተቀበላችሁ መጠን በዚያው ጸጋ እርስ በርሳችሁ አገልግሉ፤
¹¹ ማንም ሰው የሚናገር ቢሆን፥ እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢሆን፥ እግዚአብሔር በሚሰጠኝ ኃይል ነው ብሎ ያገልግል፤ ክብርና ሥልጣን እስከ ዘላለም ድረስ ለእርሱ በሚሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 28
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ በደኅና ከደረስን በኋላ በዚያን ጊዜ ደሴቲቱ መላጥያ እንድትባል አወቅን።
² አረማውያንም የሚያስገርም ቸርነት አደረጉልን፤ ዝናብ ስለ ሆነም ስለ ብርዱም እሳት አንድደው ሁላችንን ተቀበሉን።
³ ጳውሎስ ግን ብዙ ጭራሮ አከማችቶ ወደ እሳት ሲጨምር እፉኝት ከሙቀት የተነሣ ወጥታ እጁን ነደፈችው።
⁴ አረማውያንም እባብ በእጁ ተንጠልጥላ ባዩ ጊዜ፥ እርስ በርሳቸው፦ ይህ ሰው በእርግጥ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ከባሕርም ስንኳ በደኅና ቢወጣ የእግዚአብሔር ፍርድ በሕይወት ይኖር ዘንድ አልተወውም አሉ።
⁵ እርሱ ግን እባቢቱን ወደ እሳት አራገፋት አንዳችም አልጐዳችውም፤
⁶ እነርሱም፦ ሊያብጥ ወይም ወዲያው ሞቶ ሊወድቅ ነው ብለው ይጠባበቁት ነበር ብዙ ጊዜ ግን ሲጠባበቁ በእርሱ ላይ የሚያስገርም ነገር ምንም ባላዩ ጊዜ፦ ይህስ አምላክ ነው ብለው አሳባቸውን ለወጡ።
⁷ በዚያም ስፍራ አጠገብ ፑፕልዮስ የሚሉት የደሴት አለቃ መሬት ነበረ፥ እርሱም እንግድነት ተቀብሎን ሦስት ቀን በፍቅር አሳደረን።
⁸ የፑፕልዮስም አባት በንዳድና በተቅማጥ ታሞ ተኝቶ ነበር፤ ጳውሎስም ወደ እርሱ ገብቶ ጸለየለት እጁንም በላዩ ጭኖ ፈወሰው።
⁹ ይህም በሆነ ጊዜ የቀሩት ደግሞ በደሴቲቱ ደዌ የነበረባቸው እየመጡ ተፈወሱ፤
¹⁰ በብዙ ክብርም ደግሞ አከበሩን፥ በተነሣንም ጊዜ በመርከብ ላይ የሚያስፈልገንን ነገር አኖሩልን።
¹¹ ከሦስት ወርም በኋላ በደሴቲቱ ከርሞ በነበረው በእስክንድርያው መርከብ ተነሣን፥ በእርሱም የዲዮስቆሮስ አላማ ነበረበት።
¹² ወደ ሰራኩስም በገባን ጊዜ ሦስት ቀን ተቀመጥን፤
¹³ ከዚያም እየተዛወርን ወደ ሬጊዩም ደረስን። ከአንድ ቀን በኋላም የደቡብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜ በሁለተኛው ቀን ወደ ፑቲዮሉስ መጣን።
¹⁴ በዚያም ወንድሞችን አግኝተን በእነርሱ ዘንድ ሰባት ቀን እንድንቀመጥ ለመኑን፤ እንዲሁም ወደ ሮሜ መጣን።
¹⁵ ከዚያም ወንድሞች ስለ እኛ ሰምተው እስከ አፍዩስ ፋሩስና ሦስት ማደሪያ እስከሚባለው ሊቀበሉን ወጡ፥ ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነ ልቡም ተጽናና።
¹⁶ ወደ ሮሜም በገባን ጊዜ ጳውሎስ ከሚጠብቀው ወታደር ጋር ለብቻው ይቀመጥ ዘንድ ተፈቀደለት።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሐምሌ_21_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ያዐርግ ደመናተ እምአጽናፈ ምድር። ወገብረ መብረቀ ለጊዜ ዝናም። ዘያወጽኦሙ ለነፍሳት እመዛግብቲሆሙ"። መዝ 134፥7።
“ከምድር ዳር ደመናትን ያወጣል፤ በዝናብ ጊዜ መብረቅን አደረገ፤ ነፋሳትንም ከመዛግብቱ ያወጣል።” መዝ 134፥7።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሐምሌ_21_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማርቆስ 6
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁴⁷ በመሸም ጊዜ ታንኳይቱ በባሕር መካከል ሳለች እርሱ ብቻውን በምድር ላይ ነበረ።
⁴⁸ ነፋስ ወደ ፊታቸው ነበረና እየቀዘፉ ሲጨነቁ አይቶ፥ ከሌሊቱ በአራተኛው ክፍል በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ፤ ሊያልፋቸውም ይወድ ነበር።
⁴⁹ እነርሱ ግን በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ ምትሀት መሰላቸውና ጮኹ፥
⁵⁰ ሁሉ አይተውታልና፥ ታወኩም። ወዲያውም ተናገራቸውና፦ አይዞአችሁ፤ እኔ ነኝ፥ አትፍሩ አላቸው።
⁵¹ ወደ እነርሱም ወደ ታንኳይቱ ገባ፥ ነፋሱም ተወ፤ በራሳቸውም ያለ መጠን እጅግ ተገረሙ፤
⁵² ስለ እንጀራው አላስተዋሉምና፤ ነገር ግን ልባቸው ደንዝዞ ነበር።
⁵³ ተሻግረውም ወደ ምድር ወደ ጌንሴሬጥ ደረሱ ታንኳይቱንም አስጠጉ።
⁵⁴ ከታንኳይቱም ሲወጡ ወዲያው አውቀውት
⁵⁵ በዚያች አገር ሁሉ ዙሪያ ሮጡና እርሱ እንዳለ ወደ ሰሙበት ስፍራ ሕመምተኞችን በአልጋ ላይ ያመጡ ጀመር።
⁵⁶ በገባበትም ስፍራ ሁሉ፥ መንደርም ከተማም ገጠርም ቢሆን፥ በገበያ ድውዮችን ያኖሩ ነበር፤ የልብሱንም ጫፍ እንኳ ሊዳስሱ ይለምኑት ነበር የዳሰሱትም ሁሉ ዳኑ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የ ሚቀደሰው ቅዳሴ የ #እመቤታችን_ማርያም ወይም የ #ቅዱስ_ኤጲፋንዮስ ቅዳሴ ነው። መልካም ዕለተ ሰንበት ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
††† እንኳን ለሰማዕታት አበው አቡነ ጴጥሮስ ኢትዮጵያዊ : ቅዱስ መቃርስ እና ቅዱስ ለውንትዮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ታላቁ ኢትዮጵያዊ ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስ †††

††† ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ምንም እንኳ ለሃገራቸውና ሃይማኖታቸው ያን ያህል ዋጋ ቢከፍሉም ትውልዱም : መንግስቱም : ራሷ ቤተ ክርስቲያናችንም ተገቢውን ክብር ሰጥተው እያሰቧቸው አይደለም:: እስኪ እንዲያው ቢያንስ እንደ ክርስቲያን : አንድም እንደ ኢትዮጵያዊ እነዚህ ነገሮቻቸውን እናስብ::

ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ከልጅነታቸው ጀምረው ትምሕርት : ትሕርምትና ደግነት ወዳጅ እንደ ነበሩ ይነገራል:: ወቅቱ ኢትዮጵያ የራሷን ጳጳሳት የምትሻበት ጊዜ ነበርና በፈቃደ እግዚአብሔር ለመጀመሪያ ጊዜ የሃገራችን አራት አባቶች ጵጵስናን ተሾሙ::

እነርሱም ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ እና አበው አባ ሚካኤል: አባ አብርሃም እና አባ ይስሐቅ ናቸው:: የተሾሙትም ግንቦት 18 ቀን 1921 ዓ/ም ነው:: አቡነ ጴጥሮስ ከተሾሙ በኋላ በሐዋርያዊ አገልግሎትና በጸሎት ተግተው ኑረዋል::

በ1928 ዓ/ም ፋሺስት ጣልያን ሃገራችንን በወረረች ጊዜ ቆራጡ ጳጳስ በዱር በገደል ለመሔድ ተነሱ:: በየበርሃው እየሔዱ አርበኞችን ሲያጽናኑ : ሲናዝዙ : ሲባርኩም ቆይተዋል:: ለሃገራቸውና ለሃይማኖታቸው ረሃብ : ጥም : እንግልትን ታግሰዋል::

በተያዙባት በዚያች ሌሊትም በጣልያኖች ለሮም እምነትና ለአገዛዙ እንዲያጐበድዱ ተጠየቁ:: ቆራጡ ሰው ግን እንቢ ቢሉ የሚደርስባቸውን እያወቁ "አይደረግም" አሉ:: በማግስቱ በአደባባይ መትረየስ ተደግኖባቸው አሁንም ጥያቄ ቀረበላቸው::

አቡነ ጴጥሮስ አፋቸውን ከፍተው ሊናገሩ ጀመሩ:- "የሃገሬ ሕዝብ ሆይ! ለሃገርህ : ለሃይማኖትህ ባትጋደል ትውልድ ይፋረድህ:: ለጣልያን ግን እንኳን ሰው ዛፍ ቅጠሉ መሬቱ እንዳይገዛለት አውግዣለሁ" አሉ:: በደቂቃዎች ልዩነት በግራዚያኒ ትዕዛዝ የመትረየስ ጥይት ዘነበባቸው::

አካላቸው ተበሳስቶ በሰንሰለት እንደ ታሠሩ መሬት ላይ ወደቁ:: አንዱ ወታደር ቀርቦ ቢመለከት ትንሽ ትንፋሽ ነበረቻቸው:: "ይሔ ቄስ አልሞተም" ብሎ ጭንቅላታቸው ላይ ተኮሰባቸው::

አቡነ ጴጥሮስ ለሃገራቸውና ሃይማኖታቸው ተሠው:: ነገሩ በአርበኞች ዘንድ ሲሰማ ትግሉ ተቀጣጠለ:: ይሄ የተደረገው ሐምሌ 22 ቀን በ1928 ዓ/ም ነው:: አቡነ ጴጥሮስም በተ/መ/ድ (UN) የሺህ ዓመቱ ምርጥ ሰማዕት (MARTYR OF THE MILLENIUM) በመባል ይታወቃሉ::

††† ቅዱስ መቃርስ ሰማዕት †††

††† ሰማዕቱ ተወልዶ ያደገው በአንጾኪያ (ሶርያ) በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ሲሆን የታላቁ ቅዱስ ፋሲለደስ እና የቅድስት ሶፍያ ልጅ ነው:: ምንም በቤተ መንግስት ውስጥ ቢያድግም ከወላጆቹ ፍቅረ ክርስቶስን : ንጽሕናንና ደግነትን ወርሷል::

በተለይ ነዳያንን ሰብስቦ ዕለት ዕለት ያበላ ነበር:: (መቃርስ ማለት በልሳነ ዮናኒ ብጹዕ : ንዑድ : ክቡር ማለት ነው::) ቅዱሱ ያ የመከራ ዘመን ሲመጣ ሁሉም ቤተሰብ ስለ ክርስቶስ መሞትን በመምረጡ እርሱም ደስ እያለው የመከራው ተካፋይ ሆኗል::

ያን የመሰለ የቤተ መንግስት ክብር ስለ ክርስትና ናቀው:: ተገረፈ:: ተሰቃየ:: በእሳትም ተቃጠለ:: አንድ ጊዜም በአደባባይ የሞተ ሰው በጸሎቱ አስነስቶ "መስክር" አለው:: ከሞት የተነሳውም የክርስቶስን አምላክነት በመመስከሩ በአደባባይ የነበሩ ብዙ አሕዛብ በክርስትና አምነው ተሰይፈዋል::

ቅዱስ መቃርስን ግን ብዙ አሰቃይተው በዚህች ቀን አንገቱን ቆርጠውታል:: ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ አጽሙን አፍልሶ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን በስሙ ቤተ ክርስቲያን አንጾለታል::

††† ቅዱስ ለውንትዮስ ሰማዕት †††

††† ቅዱሱ የተወለደው በተመሳሳይ ዘመን (በቅዱስ መቃርስ) ሲሆን ሃገሩ ጠራብሎስ ትባላለች:: በወቅቱ በወታደርነት ነገሥታቱን ያገለግል ነበር:: ድንግል : ደም ግባት የሞላለት ወጣት ስለ ነበር በሰዎች ፊት ሞገስ ነበረው::

እርሱ ግን ምንም ወታደር ቢሆን ጾምና ጸሎትን ያዘወትር ነበር:: በተለይ ደግሞ የዳዊትን መዝሙር እየመላለሰ ይጸልየው : ይወደው ነበር:: ንግግሩ ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ጨውነት የታሸ ነውና ብዙ ጓደኞቹን ከክህደት ወደ ሃይማኖት : ከክፋት ወደ ደግነት መልሷል::

የመከራ ዘመን በደረሰ ጊዜም በገሃድ ስመ ክርስቶስን ይሰብክ ነበር:: ክፉ ሰዎች ከሰውት በመኮንኑ ፊት በቀረበ ጊዜም አልፈራም:: ወታደሮቹ መሬት ላይ ጥለው እየደበደቡት : ደሙ እንደ ጐርፍ እየተቀዳ እርሱ ግን ይዘምር ነበር::

በመጨረሻም ስለ ክርስቶስ ፍቅር በዚህች ቀን አንገቱን ተሰይፏል:: ቅዱስ ለውንትዮስ እጅግ ተአምረኛ ሰማዕት ነውና በእምነት እንጥራው::

††† እግዚአብሔር ዐጽመ ሰማዕታትን ይጠብቅልን:: ከሰማዕታቱ ጽናትን : ጸጋ በረከትን ይክፈለን::

††† ሐምሌ 22 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕት (ኢትዮጵያዊ)
2.ቅዱስ መቃርስ ሰማዕት (የፋሲለደስ ልጅ)
3.ቅዱስ ለውንትዮስ (ክቡር ሰማዕት)
4.አባ እንጦንስ አበ መነኮሳት (ቅዳሴ ቤታቸው)
5.ቅዱስ መርካሎስ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ
3.ቅዱስ ደቅስዮስ (የእመቤታችን ወዳጅ)
4.አባ ጳውሊ የዋህ

††† "እንግዲህ አትፍሯቸው:: የማይገለጥ የተከደነ: የማይታወቅም የተሠወረ ምንም የለምና:: በጨለማ የምነግራችሁን በብርሃን ተናገሩ:: በጆሮም የምትሰሙትን በሰገነት ላይ ስበኩ:: ሥጋንም የሚገድሉትን: ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ:: ይልቅስ ነፍስንም: ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ::" †††
(ማቴ. ፲፥፳፮)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ሐምሌ_22_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ቆሮ 12
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ትምክህት የሚያስፈልግ ነው፤ አይጠቅምም ነገር ግን ከጌታ ወዳለው ራእይና መገለጥ እመጣለሁ።
² ሰውን በክርስቶስ አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም ወይም ከሥጋ ውጭ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ እንዲህ ያለው ሰው ከአሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ።
³ እንዲህ ያለውንም ሰው አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ ወይም ያለ ሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤
⁴ ወደ ገነት ተነጠቀ፥ ሰውም ሊናገር የማይገባውን የማይነገረውን ቃል ሰማ።
⁵ እንደዚህ ስላለው እመካለሁ፥ ስለ ራሴ ግን ከድካሜ በቀር አልመካም።
⁶ ልመካ ብወድስ ሞኝ አልሆንም፥ እውነትን እላለሁና፤ ነገር ግን ማንም ከሚያይ ከእኔም ከሚሰማ የምበልጥ አድርጎ እንዳይቆጥረኝ ትቼአለሁ።
⁷ ስለዚህም በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ፥ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ፤ ይኸውም እንዳልታበይ ነው።
⁸ ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ።
⁹ እርሱም፦ ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ።
¹⁰ ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁶-⁷ በዚህም እጅግ ደስ ይላችኋል፥ ነገር ግን በእሳት ምንም ቢፈተን ከሚጠፋው ወርቅ ይልቅ አብልጦ የሚከብር የተፈተነ እምነታችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ፥ ለምስጋናና ለክብር ለውዳሴም ይገኝ ዘንድ አሁን ለጥቂት ጊዜ ቢያስፈልግ በልዩ ልዩ ፈተና አዝናችኋል።
⁸-⁹ እርሱንም ሳታዩት ትወዱታላችሁ፤ አሁንም ምንም ባታዩት በእርሱ አምናችሁ፥ የእምነታችሁን ፍፃሜ እርሱም የነፍሳችሁን መዳን እየተቀበላችሁ፥ በማይነገርና ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ይላችኋል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁶ በዚያን ጊዜ አዛዡ ከሎሌዎች ጋር ሄዶ አመጣቸው፥ በኃይል ግን አይደለም፤ ሕዝቡ እንዳይወግሩአቸው ይፈሩ ነበርና።
²⁷ አምጥተውም በሸንጎ አቆሙአቸው።
²⁸ ሊቀ ካህናቱም፦ በዚህ ስም እንዳታስተምሩ አጥብቀን አላዘዝናችሁምን? እነሆም፥ ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞልታችኋል፤ የዚያንም ሰው ደም በእኛ ታመጡብን ዘንድ ታስባላችሁ ብሎ ጠየቃቸው።
²⁹ ጴጥሮስና ሐዋርያትም መልሰው አሉ፦ ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል።
³⁰ እናንተ በእንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን የአባቶቻችን አምላክ አስነሣው፤
³¹ ይህን እግዚአብሔር፥ ለእስራኤል ንስሐን የኃጢአትንም ስርየት ይሰጥ ዘንድ፥ ራስም መድኃኒትም አድርጎ በቀኙ ከፍ ከፍ አደረገው።
³² እኛም ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን፥ ደግሞም እግዚአብሔር ለሚታዘዙት የሰጠው መንፈስ ቅዱስ ምስክር ነው።
³³ እነርሱም ሲሰሙ በጣም ተቈጡ ሊገድሉአቸውም አሰቡ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሐምሌ_22_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
   "ወኢይትኀበር ውስተ ማኅበሮሙ ዘደም። ወኢይዜከር አስማቲሆሙ በአፉየ። እግዚአብሔር መክፈልተ ርስትየ ወጽዋዕየ"። መዝ 15፥4-5።
"ወደ ሌላ ለሚፋጠኑት መከራቸው ይበዛል፤ የቍርባናቸውን ደም እኔ አላፈስሰውም፥ ስማቸውንም በከንፈሬ አልጠራም።
እግዚአብሔር የርስቴ እድል ፈንታና ጽዋዬ ነው፥ ዕጣዬንም የምታጠና አንተ ነህ"። መዝ 15፥4-5።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሐምሌ_22_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማርቆስ 13
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁴ ነገር ግን በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኵሰት በማይገባው ስፍራ ቆሞ ብታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፥ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፥
¹⁵ በሰገነትም ያለ ወደ ቤት አይውረድ ከቤቱም አንዳች ይወስድ ዘንድ አይግባ፥
¹⁶ በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ።
¹⁷ በዚያን ወራትም ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው።
¹⁸ ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤
¹⁹ በዚያን ወራት እግዚአብሔር ከፈጠረው ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያልሆነ ደግሞም የማይሆን የመከራ ዓይነት ይሆናልና።
²⁰ ጌታስ ወራቶቹን ባያሳጥር፥ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም፤ ነገር ግን ስለ መረጣቸው ምርጦች ወራቶቹን አሳጠረ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ 
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ባስልዮስ ወይም የ #ቅዱስ_ያዕቆብ_ዘሥሩግ ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ዑራኤል በዓል፣ የአቡነ ጴጥሮስ የዕረፍት በዓል፣ የሰማዕት ቅዱስ መቃርስ ዕረፍት በዓል፣ የሰማዕት ቅዱስ ለውንትዮስ ዕረፍት በዓልና አበ መነኮሳት የአባ እንጦንስ በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ሐምሌ_23

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሐምሌ ሃያ ሦስት በዚች ቀን #ቅድስት_መሪና ሰማዕት ሆነች፣ #ቅዱስ_ለንጊኖስ ሰማዕት ሆነ፣ የመናገሻ ገነተ ጽጌ #ቅዱስ_ጊዮርጊስ_ቤተ_ክርስቲያን (አራዳ ጊዮርጊስ) #ቅዳሴ_ቤቱ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_መሪና

ሐምሌ ሃያ ሦስት በዚች ቀን ቅድስት መሪና ሰማዕት ሆነች። የዚችም ቅድስት የአባቷ ስም ዳኬዎስ ነበር እርሱም በአንጾኪያ ሀገር ለጣዖታት ካህናት አለቃ ነበር ያን ጊዜ ንጉሡም ከሀዲው ዳኬዎስ ነበር።

አምስት ዓመትም በሆናት ጊዜ እናቷ ሞተች አባቷም ከከተማ ውጭ ለምትኖር ሞግዚት ሰጣት እርሷም ክርስቲያናዊት ነበረች የ #ክርስቶስ የሆነ የሃይማኖት ትምህርትን ሁሉ አስተማረቻት። ዐሥራ አምስት ዓመትም በሆናት ጊዜ አባቷ ሞተ።

ከዚህም በኋላ ሰዎች የሰማዕታትን ተጋድሏቸውንና መከራቸውን ሲናገሩ ሰምታ የ #ጌታ_ክርስቶስ ፍቅር በልቧ አደረ በሰማዕትነት መሞትንም ፈልጋ ሔደች።

በዚያን ጊዜም ከሀዲ መኰንን ወደዚያች አገር ደረሰ እርሷንም አይቶ ወደርሱ አስመጣትና ከወዴት ነሽ አላት #ክብር_ይግባውና_ከጌታ_ኢየሱስ ሰዎች ወገን ነኝ ስሜም መሪና ነው አለችው። ደም ግባቷንና ላሕይዋንም አይቶ መታገሥ ተሳነው እሺ ትለው ዘንድ በብዙ ነገር አባበላት። እርሷ ግን ረገመችው የረከሱ አማልክቶቹንም ረገመች።

ያን ጊዜም በብረት ዘንጎች ይደበድቧት ዘንድ ደሟ እንደ ውኃ እስኪፈስ ሕዋሳቷን ይቆራርጡ ዘንድ አዘዘ። ያን ጊዜም ወደ ጌታ #እግዚአብሔር ጸለየች የመላእክት አለቃ #ቅዱስ_ሚካኤልም መጥቶ አዳናት። ሁለተኛም ወደ ወህኒ ቤት ያስገቧት ዘንድ አዘዘ #ጌታችንም ወደ ሰማይ አውጥቶ የቅዱሳን ሰማዕታትንና የጻድቃንን ማደሪያዎች አሳይቶ ወደ ቦታዋ መለሳት። በማግሥቱም ሥጋዋን በመጋዝ እንዲሠነጥቁ ጐኖቿንም እንዲሰነጣጥቁና በእሥር ቤት እንዲጥሏት አዘዘ ያን ጊዜም የመላእክት አለቃ #ቅዱስ_ሚካኤል መጥቶ አዳናት።

በወህኒ ቤቱ ውስጥም ቁማ ስትጸልይ እጅግ የሚያስፈራ ታላቅ ዘንዶ ወደ ርሷ መጣ በአየችውም ጊዜ ደነገጠች ሰውነቷ ሁሉ ተንቀጠቀጠ መናገርም ተሳናት። ያን ጊዜም እጆቿ በ #መስቀል ምልክት አምሳል እንደተዘረጉ በልቧም ስትጸልይ ወደርሷ ቀርቦ ዋጣት። ያን ጊዜም ሆዱ ተሠንጥቆ ያለ ጉዳት ወጣች #እግዚአብሔርንም አመሰገነችው።

ሁለተኛም በጥቁር ሰው አምሳል ሰይጣንን አየችው እጆቹም በጉልበቶቹ ላይ ተጨብጠው ነበር። ፊቷንም በ #መስቀል ምልክት አማትባ በራሱ ጠጉር ይዛ ደበደበችው። በእግሮቿም ረገጠችው ያን ጊዜም #ክብር_ይግባውና_የጌታ_ክርስቶስ #ዕፀ_መስቀል ተገለጠላት በላዩም ነጭ ርግብ ተቀምጣ እንዲህ ብላ አነጋገረቻት መሪና ሆይ የ #መንፈስ_ቅዱስን የጸጋ አረቦን ተቀብለሻልና ደስ ይበልሽ።

በማግሥቱም መኰንኑ ልብሷን አራቁተው ዘቅዝቀው ሰቅለው እንዲአቃጥሏት ደግሞም ውኃ ከአፈሉበት ጋን ውስጥ እንዲጨምሩዋት አዘዘ። በውስጡም ሁና ስትጸልይ ከሰማይ ርግብ መጣ በአፉም ውስጥ የወርቅ አክሊል ነበር ማሠሪያዋንም ፈትቶ በ #አብ#ወልድ#መንፈስ_ቅዱስ ስም ሦስት ጊዜ አጠመቃት #እግዚአብሔርንም እያመሰገነች ከውኃው ውስጥ ወጣች።

መኰንኑም እንደ ዳነች በአየ ጊዜ ራሷን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ። ወደ ሰማዕትነቱ ቦታም በደረሰች ጊዜ ነፍሷን በፍቅር ይቀበል ዘንድ ወደ #ጌታችን ጸለየች። #ክብር_ይግባውና_ጌታችንም ተገለጠላት ስሟን ለሚጠራ መታሰቢያዋንም ለሚያደርግ ገድሏንም ለሚጽፍ ወይም ለሚያነበውና ለሚሰማው ኃጢአቱን እንዲአስተሠርይለት ለርሷም ርሱን እንዲሰጣት ቃል ኪዳን ሰጣት።

ከዚህም በኋላ ራሷን በሰይፍ ቆረጡ ከእርሷም ብዙ ተአምር ተገለጠ ዕውራን አይተዋልና፣ ሐንካሶች በትክክል ሔደዋልና፣ ደንቆሮዎችም ሰምተዋልና፣ ዲዳዎችም ተናግረዋልና ቁጥር የሌላቸው ብዙ ሰዎችም #ክብር_ይግባውና_በጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አመኑ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት መሪና ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ለንጊኖስ_ሰማዕት

በዚችም ቀን ከቀጰዶቅያ አገር ለንጊኖስ ሰማዕት ሆነ። ይህም ቅዱስ ከጲላጦስ ጭፍሮች ውስጥ ነበር #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስለ ዓለም ደኅንነት መከራ እንዲቀበል የፈቀደበት ሰዓት በደረሰ ጊዜ በእርሱ ላይ የፈለጉትን ያደርጉ ዘንድ ለዐመፀኞች ፈቅዶላቸው ነበር። ይህም ለንጊኖስ #ጌታን ይሰቅሉት ዘንድ ጲላጦስ ከአዘዛቸው ወታደሮች ውስጥ ነበር።

በመስቀል ላይ ከሞተ በኋላ #ጌታችንን የቀኝ ጐኑን ወጋው ከጐኑም ደምና ውኃ ፈሰሰ። ይህንንም አይቶ እጅግ አደነቀ ከዚህም በፊት ፀሐይ እንደጨለመ፣ ጨረቃ ደም እንደሆነ፣ ዐለቱም እንደተሠነጠቀ፣ ሙታንም እንደተነሡ አይቶ ነበር።

#ጌታችንም በተነሣ ጊዜ ስለ ትንሣኤው የሆነውን ሰምቶ ይህን ምሥጢር ይገልጽለት ዘንድ ወደ #እግዚአብሔር ጸለየ። ሐዋርያው ጴጥሮስንም ላከለት እርሱም ነቢያት ስለ #ጌታችን፣ ስለ መከራው፣ ስለ መሰቀሉ፣ ስለ መሞቱ፣ ስለ መነሣቱ፣ ስለ ዕርገቱም ትንቢት እንደተናገሩ ነገረው። እርሱም ከቅድስት #ድንግል በሥጋ ተወልዶ ዓለምን ለማዳን የመጣ የሕያው #እግዚአብሔር ልጅ #ክርስቶስ እንደሆነ አስረዳው።

ያን ጊዜም በቅዱስ ጴጥሮስ ቃል አመነ የምድራዊ ንጉሥ አገልግሎትንም ትቶ ወደ ቀጰዶቅያ ሔደ በውስጧም ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_በኢየሱስ_ክርስቶስ ስም እንደ ሐዋርያት ሰበከ።

አይሁድም በጠላትነት ተነሡበት በመሳፍንትም ዘንድ ከሰሱት በላዩም የሐሰት ምስክር አስነሡበት ስለዚህም ራሱን በሰይፍ አስቆረጡት የሰማዕትነትንም አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት አፄ ምኒልክ በአደዋ ጦርነት ጊዜ ለረዳቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ከድሉ ከተመለሱ በኋላ በአዲስ አበባ መሐል ከተማ ላይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ቤተክርስቲያን አሠሩ ስሟንም ገነተ ጽጌ ብለው ሰየሟት የባረኳትም ሊቀ ጳጳሱ ግብፃዊው አቡነ ማቴዎስ ናቸው፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት የቅዱስ ጊዮርጊስ ልመናው አማላጅነቱ ከእኛ ጋር ይሁን አሜን!!! ተአምረ ጊዮርጊስ ተአምር 17 ላይ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ሐምሌ_23)
2024/10/02 00:24:53
Back to Top
HTML Embed Code: