Telegram Web Link
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ሐምሌ_19_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የተነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዕብራውያን 11
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³³ እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፥ ጽድቅን አደረጉ፥ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፥
³⁴ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን ኃይል አጠፉ፥ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፥ ከድካማቸው በረቱ፥ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፥ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ።
³⁵ ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤
³⁶ ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤
³⁷ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤
³⁸ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ።
³⁹-⁴⁰ እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው ሳሉ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አላገኙም፥ ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ እግዚአብሔር ስለ እኛ አንዳች የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ አይቶ ነበርና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² ወዳጆች ሆይ፥ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ ድንቅ ነገር እንደ መጣባችሁ አትደነቁ፤
¹³ ነገር ግን ክብሩ ሲገለጥ ደግሞ ሐሤት እያደረጋችሁ ደስ እንዲላችሁ፥ በክርስቶስ መከራ በምትካፈሉበት ልክ ደስ ይበላችሁ።
¹⁴ ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ።
¹⁵ ከእናንተ ማንም ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ክፉ አድራጊ እንደሚሆን ወይም በሌሎች ጒዳይ እንደሚገባ ሆኖ መከራን አይቀበል፤
¹⁶ ክርስቲያን እንደሚሆን ግን መከራን ቢቀበል ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር።
¹⁷ ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት ተነሥቶ የሚጀመርበት ጊዜ ደርሶአልና፤ አስቀድሞም በእኛ የሚጀመር ከሆነ ለእግዚአብሔር ወንጌል የማይታዘዙ መጨረሻቸው ምን ይሆን?
¹⁸ ጻድቅም በጭንቅ የሚድን ከሆነ ዓመፀኛውና ኃጢአተኛው ወዴት ይታይ ዘንድ አለው?
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 23
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁰ ብዙ ጥልም በሆነ ጊዜ የሻለቃው ጳውሎስን እንዳይገነጣጥሉት ፈርቶ ጭፍሮቹ ወርደው ከመካከላቸው እንዲነጥቁት ወደ ሰፈሩም እንዲያገቡት አዘዘ።
¹¹ በሁለተኛውም ሌሊት ጌታ በአጠገቡ ቆሞ፦ ጳውሎስ ሆይ፥ በኢየሩሳሌም ስለ እኔ እንደ መሰከርህ እንዲሁ በሮሜም ትመሰክርልኝ ዘንድ ይገባሃልና አይዞህ አለው።
¹² በጠባም ጊዜ አይሁድ ጳውሎስን እስኪገድሉት ድረስ እንዳይበሉና እንዳይጠጡ በመሐላ ተስማሙ።
¹³ ይህንም ሴራ ያደረጉት ሰዎች ከአርባ ይበዙ ነበር፤
¹⁴ እነርሱም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ሽማግሌዎቹ መጥተው፦ ጳውሎስን እስክንገድል ድረስ ምንም እንዳንቀምስ ተረጋግመን ተማምለናል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሐምሌ_19_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የተነበበው_የተዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
   "ይትኀፈሩ ኵሎሙ እለ ይሰግዱ ለግልፎ። ወእለ ይትሜክሑ በአማልክቲሆሙ። ወይሰግዱ ሎቱ ኵሎሙ መላእክቲሁ"። መዝ 96፥7።
“ለተቀረጸ ምስል የሚሰግዱ ሁሉ፥ በጣዖቶቻቸውም የሚመኩ ይፈሩ፤ መላእክቱ ሁሉ፥ ስገዱለት።” መዝ 96፥7።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሐምሌ_19_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 11
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁵ በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አለ፦ አባት ሆይ፥ የሰማይና የምድር ጌታ፥ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤
²⁶ አዎን፥ አባት ሆይ፥ ፈቃድህ በፊትህ እንዲህ ሆኖአልና።
²⁷ ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፥ ከወልድም በቀር ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም።
²⁸ እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ።
²⁹ ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤
³⁰ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ 
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ያዕቆብ ዘሥሩግ ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ገብርኤል፣ የቅዱሳን ሰማዕታት ቅዱስ ቂርቆስና ቅድስት ኢየሉጣ የሰማዕት የቅዱስ በጥላን ዓመታዊ በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ሐምሌ_20

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሐምሌ ሃያ በዚህች ቀን #እመቤታችን_ድንግል_ማርያም ከተወለደች በኋላ በሰማንያ ቀን ከርግብ ገላግልቶች ጋራ ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበት ነው፣ ታላቅና ክቡር የሆነው የሠራዊት አለቃ #ቅዱስ_ቴዎድሮስ በሰማዕትነት ሞተ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#በዓታ_ለእግዝእትነ_ማርያም

ሐምሌ ሃያ በዚህች ቀን እመቤታችን #ድንግል_ማርያም ከተወለደች በኋላ በሰማንያ ቀን ከርግብ ገላግልቶች ጋራ ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበት ነው፣

ለስም አጠራሯ ክብር ይሁንና እመ ብርሃን #ድንግል_ማርያም በዚህች ቀን ወደ ቤተ መቅደስ ገብታለች:: በዓሉ ከሰላሳ ሦስቱ የእመቤታችን በዓላት እንደ አንዱ አይቆጠርም:: ምክንያቱም ቅዱሳን ሊቃውንት በዓታ ከበዓታ ጋር ይስማማል ብለው የታኅሣሥ ሦስትን በዓል ከሰላሳ ሦስቱ ደምረውታል::

#እመቤታችን ወደ ቤተ መቅደስ የገባችው ሁለት ጊዜ ሲሆን:-

1.ዛሬ የምናከብረውና በተወለደች በሰማንያ ቀኗ የገባችበት ነው:: (ከግንቦት 1 ጀምረን እናስላው 80 ቀን ይመጣል::)

ኦሪት እንዳዘዘው ቅዱሳን ኢያቄምና ሐና ንጽሕት ሕፃን #ድንግል_ማርያምን ታቅፈው የርግብ ልጆች (ግልገሎች) ዋኖስም ይዘው ወደ ቤተ መቅደስ ሒደዋል::

ካህናቱ ዘካርያስና ስምዖን ወጥተው በደስታ ተቀብለዋቸዋል:: እመቤታችን ለወላጆቿ ማኅጸን የከፈተች በኩር ናትና በእግዚአብሔር ፊት አቅርበዋታል::

2.ከሦስት ዓመታት በኋላ እንደ ስዕለታቸው ወደ ቤተ መቅደስ ወስደው #ለእግዚአብሔር ሰጥተዋት ተመልሰዋል::

#እግዚአብሔር ዛሬ ያልቃል ነገ ይደቃል የማይባለውን የድንግል እናቱን ፍቅር አብዝቶ ያድለን:: በረከቷም በእኛ ላይ ጸንቶ ይኑር::

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ቴዎድሮስ

ዳግመኛም በዚህች ቀን ታላቅና ክቡር የሆነው የሠራዊት አለቃ ቅዱስ ቴዎድሮስ በሰማዕትነት ሞተ። የዚህ ቅዱስ አባት ስሙ ዮሐንስ ይባል ነበር። እርሱም ከላይኛው ግብጽ ሰጥብ ከምትባል መንደር ነበር። ወደ አንጾኪያ ከተማም ከሠራዊቱ ጋራ ወሰዱትና በዚያ ኖረ ከዚያች ከተማ መኳንንቶችም ያንዱን ልጅ አገባ እርሷም ጣዖትን ታመልክ ነበር። ባሏ ዮሐንስ የሚያመልከውን ግን አታውቅም ነበር።

ከዚህም በኋላ ይህን ቅዱስ ቴዎድሮስን በወለዱት ጊዜ እናቱ ወደ ጣዖቷ አቅርባ አምልኮትዋን ልታስተምረው ፈለገች አባቱ ግን አስተወው ስለዚህም ተቆጥታ ባሏ ዮሐንስን አባረረችው ሕፃኑ ቴዎድሮስም በእናቱ ዘንድ ቀረ።

አባቱ ዮሐንስም ልጁ ቴዎድሮስን ወደ እውነተኛ መንገድ ይመራው ዘንድ ወደ #እግዚአብሔር ይጸልይና ይማልድ ነበር። ሕፃኑ ቴዎድሮስም በአደገ ጊዜ ጥበብን ተማረ ጌታችንም ልቡን ብሩህ አደረገለት ስሙ አውላኪስ ወደሚባል ኤጲስቆጶስም ሒዶ የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቀ። እናቱም ታላቅ ኅዘንን አዘነች።

ከዚህም በኋላ ስለ አባቱ በሕይወት እንዳለ ወይም እንደሌለ ጠየቀ ከአገልጋዮቹም አንዱ የአባቱን ሥራ በሥውር ነገረው። ቅዱስ ቴዎድሮስም ጐለመሰ እጅግም ብርቱ ሆነ ንጉሡም የሠራዊት አለቃ አድርጎ ሾመው።

የፋርስ ሰዎችንም ሊወጋቸው በወጣ ጊዜ ይህ ቅዱስ ቴዎድሮስ በረታ የፋርስ ንጉሥንም ልጅ ይዞ ማረከው ከእርሱም ጋር ምሥራቃዊው ቴዎድሮስ ነበር የፋርስንም ሠራዊት አሳደዱአቸው።

ከጥቂት ወራቶች በኋላም የፋርስና የበርበር ስዎች በሮማውያን ላይ ተነሡ። ብዙ ከተሞችንም አጠፉ ዲዮቅልጥያኖስም በሰማ ጊዜ እጅግ ፈራ ቴዎድሮስንም ጠርቶ ምን እናድርግ ሠራዊትህን ሁሉ የጦር መሣሪያህንም ሁሉ ይዘህ ወደ ሰልፍ ውጣ አለው።

ቅዱስ ቴዎድሮስም እንዲህ ብሎ መለሰለት አንተ የጦር መሣሪያህን ወስደህ ለአሽከሮችህ ስጣቸው እኔ ክብር ይግባውና በፈጣሪዬ #ኢየሱስ_ክርስቶስ ርዳታ እተማመናለሁና የጦር መሣሪያ አልሻም እኔም ብቻዬን ወደ ጦርነቱ እሔዳለሁ ከወታደሮችም አንድ እንኳ ከእኔ ጋራ አልወስድም። በእጄ ውስጥ ያለ ይህ ጦር የተቀመጥኩበትም ፈረስ ይበቃኛል ከእኔ ጋራ የሚወጣ ፈጣሪዬ እርሱ ይረዳኛልና። ንጉሡም እነሆ ጠላቶቻችን ወደእኛ ቀርበዋልና የወደድከውን አድርግ አለው።

በማግሥቱም ቅዱስ ቴዎድሮስ ወደ ሰልፍ ወጣ ንጉሡም የበርበርን ሰዎች ትወጋቸው ዘንድ ምን ኃይል አለህ እነርሱ ብዙ ወገኖች ናቸውና አለው። ቅዱሱም ለንጉሡ እንዲህ ብሎ መለሰለት አንተ ከሠራዊትህ ጋራ በዚህ ቁም እኔም ወደ እነርሱ ብቻዬን እሔዳለሁ በነርሱም ላይ የሚደርሰውን ታያለህ። እኔ በ #እግዚአብሔር ኃይል እንደማጠፋቸው አውቃለሁና። ከእነርሱም አንዱ እንኳ ወደቤቱ አይመለስም። ንጉሡም አደነቀ ከእርሱ ጋር ያሉትም አደነቁ።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ቴዎድሮስ ወደ ጦርነቱ ብቻውን ሔደ ንጉሡንም ከእርሱ ሩቅ በሆነ ቦታ ተወው። ወደ በርበር ሰዎችም ደርሶ ትዋጋላችሁን ወይስ በሰላም ወደ አገራችሁ ትመለሳላችሁ አላቸው። እነርሱም ከአንተ በቀር ለሰልፍ የመጣ አናይምና ከማን ጋር እንዋጋለን አሉት እርሱም ማንም ከእኔ ጋር እንዲመጣ አልሻም። እኔ ብቻዬን በ #ፈጣሪዬ ኃይል አጠፋችኋለሁ አላቸው።

ምናልባት ውሻ ልታባርር መጥተህ ይሆናል ከፈቀድህ ግን ወደ አንተ ይመጣ ዘንድ ከእኛ ውስጥ አንዱን ምረጥና ሁለታችሁ ተጋጠሙ አሉት።

ያን ጊዜ ቅዱስ ቴዎድሮስ ከፈረሱ ላይ ወረደና ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ እንዲህ እያለ ጸለየ ጣዖታትን እስከ አጠፋቸውና የባቢሎንን ከተማ ዘንዶ እስከ ገደለው ድረስ ነቢዩ ዳንኤልን ያጸናኸው ጌታዬ አምላኬ ሆይ እንዲሁም ዛሬ ከእኔ ጋራ ሁን በረድኤትህም አጽናኝ #አብ_ወልድ_መንፈስ_ቅዱስ ሆይ ምስጋና ይገባሀል ለዘላለሙ አሜን።

ጸሎቱንም በፈጸመ ጊዜ ጦሩን አንሥቶ በላዩ በመስቀል ምልክት አማተበ በፈረሱ ላይም ተቀምጦ በበርበር ሰዎች ላይ እንዲህ እያለ ጮኸ እንዋጋ ዘንድ ወደኔ ኑ ክብር ይግባውና ለ #እግዚአብሔር_ኢየሱስ_ክርስቶስ እኔ ባሪያው ነኝ እንዲህም እያለ በመካከላቸው ገብቶ የበርበርን ሰዎች አጠፋቸው ከእነርሱም ፈረሰኛንም ሆነ እግረኛን ምንም አላስቀረም የመኳንንቶቻቸውንም ቸብቸቦ ቆርጦ ወደ ንጉሡ አቀረበ። ንጉሡም ተቀበለው ሠራዊቱም ሁሉ ሰገዱለት። የአንጾኪያም ከተማ ሰዎች ሁሉም ወጥተው የበርበርን አገር ማረኩ።

አውኪስጦስ በሚባል አገርም ሰዎች የሚያመልኩት ታላቅ ዘንዶ ነበረ ይበላቸውም ዘንድ በየዕለቱ ሁለት ሁለት ሰዎችን ይሰጡት ነበር ሁለት ልጆችም ያሏት አንዲት ክርስቲያናዊት መበለት ነበረች። እንዲበላቸውም ልጆችዋን ወሰደው ለዘንዶው አቀረቧቸው።

በዚያን ጊዜም ቅዱስ ቴዎድሮስ ወደዚያ አገር ደረሰ ያች መበለትም በፊቱ ቆመች ልጆቿን ወስደው እንዲበላቸው ለዘንዶው እንዳቀረቧቸው በእርሷ ላይ የሆነውን ሁሉ አልቅሳ ነገረችው።

ክርስቲያን እንደሆነችም ባወቀ ጊዜ በልቡ ይችን ሴት በድለዋታል #እግዚአብሔርም ይበቀልላታል አለ። ወዲያውኑም ከፈረሱ ወረደና ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ ጸለየ። ከዚህም በኋላ ወደ ዘንዶው ቀረበ የከተማው ሰዎችም ሁሉ ወደርሱ ይመለከቱ ነበር። በጦሩም ወግቶ ያንን ዘንዶ ገደለው። ርዝመቱም ሃያ አራት ክንድ ሆነ የመበለቷንም ልጆች አዳናቸው።

ከዚህም በኋላ አባቱን ይፈልገው ዘንድ ወደ ላይኛው ግብጽ ሔደ አባቱንም አገኘው አባቱም ልጁ እንደሆነ በምልክቶቹ አወቀው ቅዱሱም አባቱ እስከ አረፈ ድረስ በዚያ ኖረ።

ከዚህም በኋላ ወደ አንጾኪያ ከተማ ተመለሰ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስንም ክብር ይግባውና #ክርስቶስን እንደካደና ጣዖትን እንደአመለከ ክርስቲያኖችንም ሲአሠቃያቸው አገኘው።
ከዚህም አስቀድሞ የከተማው ሰዎች የሚያመልኩትን ዘንዶ እርሱ እንደ ገደለው የአውኪስጦስ አገር ሰዎች ወደ ንጉሥ ከሰውት ነበርና ስለዚህ ንጉሥ ልኮ አስቀረበው።

ቅዱስ ቴዎድሮስም ወደ ንጉሡ በቀረበ ጊዜ ንጉሡን እንዲህ ብሎ ዘለፈው አንተ የክፉ ሥራ ሁሉ መገኛ የሆንክ ሰማይንና ምድርን የፈጠረ የክብር ባለቤትን ትተህ የረከሱ ጣዖታትን ያመለክ የኃጢአት ልጅ ሆይ ወዮልህ #እግዚአብሔርም ፈጥኖ መንግሥትህን ያጠፋታል።

በዚያን ጊዜም ንጉሡ ተቆጥቶ ከመሬት ላይ ጥለው ይገርፉት ዘንድ ወታደሮችን አዘዛቸው። ይህንንም አደረጉበት ደሙም እንደ ውኃ ፈሰሰ። እጆቹንና እግሮቹንም ከግንድ ጋር ቸነከሩት።

በሥቃይም ውስጥ ሳለ ከ #እግዚአብሔር የታዘዘ የመላእክት አለቃ #ቅዱስ_ሚካኤል ወደርሱ ወረደ እንዲህም አለው ጽና እነሆ የገድልህ ፍጻሜ ቀርቦአል ሥጋህ በውስጡ በሚኖርበትም ቦታ ድንቆችና ተአምራቶች ይገለጣሉ እነሆ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ቃል ኪዳን ሰጠህ መታሰቢያህን ለሚያደርግ ሁሉ፣ ወይም በስምህ የተራበ ለሚያጠግብ፣ የተጠማውን ለሚያጠጣ፣ ወይም ለቤተክርስቲያንህ መባን መጻሕፍትንም ለሚሰጥ እኔ ኃጢአቱን ሁሉ እደመስስለታለሁ። ገድልህንም የሚጽፈውን፣ ወይም የሚያነበውን፣ የሚሰማውን፣ ወይም የሚገዛውን እኔ ስሙን በሕይወት መጽሐፍ እጽፋለሁ።

ከዚህም በኋላ ብዙዎች ከንጉሥ ሠራዊትና ከሕዝቡ ተሰብስበው በንጉሡ ላይ እንዲህ ብለው ጮኹበት አንተ ከሀዲ #እግዚአብሔር ያጥፋህ ከጠላቶቻችን ያዳነንን ኃያልና ጽኑዕ የሆነውን የከበረ ቴዎድሮስን ታሠቃየዋለህና ይህንንም ብለው በክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ታመኑ ያን ጊዜም ንጉሥ ተቆጥቶ ሁሉንም አስገደላቸው ሰማዕትም ሆኑ የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበሉ።

ከዚህም በኋላ ንጉሡ አዘዘ የብረት ዐልጋም አምጥተው ቅዱሱን በላዩ አስተኙት ከበታቹም እሳትን አነደዱ ቅዱስ ቴዎድሮስም እንዲህ ብሎ ጸለየ አቤቱ ፈጣሪዬ ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት ምድጃ እንደ አዳንካቸው አድነኝ። ወዲያውኑም ያ እሳት ጠፋ እንደ ንጋት ጊዜ ቊርም ሆነ።

ከሰማይም እንዲህ የሚል ቃል መጣ ክብር ይግባውና ከ #ጌታ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ኃይል የተሰጠህ ሆይ ጽና በርታ ያን ጊዜም ቅዱሱ ተነሥቶ በንጉሡ ፊት ቆመ እንዲህም አለው ክብር ይግባውና #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ አድኖኛልና አንተ ከሀዲ እፈር አለው። የንጉሡም የጭፍራ አለቃ ይህን በአየ ጊዜ ክቡር ቴዎድሮስ ከሚያመልከው ክብር ይግባውና ከ #ጌ_ ከኢየሱስ_ክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለም ብሎ ጮኸ ርሱንም ራሱን አስቆረጠውና በሰማዕትነት ሞተ።

ቅዱስ ቴዎድሮስንም ብዙ ከአሠቃየውና ማሠቃየቱ ከሰለቸው በኋላ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ ሥጋውንም እንዲአቃጥሉ አዘዘ። በ #ጌታችንም ፈቃድ ከእናቱ ደጅ ወስደው እራሱን ቆረጡ ከእርሱም ደም፣ ወተትም ፈሰሰ ታላቅ እሳትም አንድደው ሥጋውን በውስጡ ጨመሩ እሳቱም ከቶ አልነካውም። እናቱም ለወታደሮች ብዙ ወርቅ ሰጥታ ሥጋውን ወሰደች በአማሩ ልብሶችም ገነዘችው እስከ መከራው ፍጻሜም በቤቷ ውስጥ አኖረችው።

ከዚያ በኋላም አብያተ ክርስቲያናት ተሠሩለት ስብጥ በሚባል በአባቱ አገርም በተሠራች ገዳም ሥጋውን አኖሩ ከሥጋውም ድንቆችና ተአምራቶች ተደረጉ ታላቅ ፈውስም ሆነ።

#ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ሐምሌ_20 እና #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ሐምሌ_20_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ቆሮ 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁷ ነገር ግን የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን፤
⁸ በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤
⁹ እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤
¹⁰ የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን።
¹¹ የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሚሞት ሥጋችን ይገለጥ ዘንድ እኛ ሕያዋን የሆንን ከኢየሱስ የተነሣ ዘወትር ለሞት አልፈን እንሰጣለንና።
¹² ስለዚህ ሞቱ በእኛ ሕይወቱም በእናንተ ይሠራል።
¹³ ነገር ግን፦ አመንሁ ስለዚህም ተናገርሁ ተብሎ እንደ ተጻፈ ያው አንዱ የእምነት መንፈስ ስላለን፥ እኛ ደግሞ እናምናለን ስለዚህም እንናገራለን፤
¹⁴ ጌታን ኢየሱስን ያስነሣው እኛን ደግሞ ከኢየሱስ ጋር እንዲያስነሣን ከእናንተም ጋር እንዲያቀርበን እናውቃለንና።
¹⁵ በብዙዎች በኩል የተትረፈረፈው ጸጋ ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋናን ያበዛ ዘንድ፥ ሁሉ ስለ እናንተ ነውና።
¹⁶ ስለዚህም አንታክትም፥ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል።
¹⁷-¹⁸ የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² ወዳጆች ሆይ፥ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ ድንቅ ነገር እንደ መጣባችሁ አትደነቁ፤
¹³ ነገር ግን ክብሩ ሲገለጥ ደግሞ ሐሤት እያደረጋችሁ ደስ እንዲላችሁ፥ በክርስቶስ መከራ በምትካፈሉበት ልክ ደስ ይበላችሁ።
¹⁴ ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ።
¹⁵ ከእናንተ ማንም ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ክፉ አድራጊ እንደሚሆን ወይም በሌሎች ጒዳይ እንደሚገባ ሆኖ መከራን አይቀበል፤
¹⁶ ክርስቲያን እንደሚሆን ግን መከራን ቢቀበል ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር።
¹⁷ ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት ተነሥቶ የሚጀመርበት ጊዜ ደርሶአልና፤ አስቀድሞም በእኛ የሚጀመር ከሆነ ለእግዚአብሔር ወንጌል የማይታዘዙ መጨረሻቸው ምን ይሆን?
¹⁸ ጻድቅም በጭንቅ የሚድን ከሆነ ዓመፀኛውና ኃጢአተኛው ወዴት ይታይ ዘንድ አለው?
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 24
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁷ ከብዙ ዓመትም በኋላ ለሕዝቤ ምጽዋትና መሥዋዕት አደርግ ዘንድ መጣሁ፤
¹⁸ ይህንም ሳደርግ ሳለሁ ሕዝብ ሳይሰበሰብ ሁከትም ሳይሆን በመቅደስ ስነጻ አገኙኝ።
¹⁹ ነገር ግን በእኔ ላይ ነገር ያላቸው እንደ ሆነ፥ በፊትህ መጥተው ይከሱኝ ዘንድ የሚገባቸው ከእስያ የመጡ አንዳንድ አይሁድ አሉ።
²⁰-²¹ ወይም በመካከላቸው ቆሜ፦ ዛሬ ስለ ሙታን መነሣት በፊታችሁ በእኔ ይፈርዱብኛል ብዬ ከጮኽሁት ከዚህ ከአንድ ነገር በቀር፥ በሸንጎ ፊት ቆሜ ሳለሁ በእኔ አንድ ዓመፃ ያገኙ እንደ ሆን እነዚህ ራሳቸው ይናገሩ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሐምሌ_20_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ሕገ ለእግዚአብሔር ንጹሕ ወይመይጣ ለነፍስ። ስምዑ ለእግዚአብሔር እሙን ወያጠብብ ሕፃናተ። ኵነኔሁ ለእግዚአብሔር ርቱዕ ወያስተፌሥሕ ልበ"። መዝ 18፥7-8።
"የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው፤ ነፍስን ይመልሳል፤ የእግዚአብሔር ምስክር የታመነ ነው፤ ሕፃናትን ጠቢባን ያደርጋል።
የእግዚአብሔር ሥርዓት ቅን ነው፥ ልብንም ደስ ያሰኛል፤ የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው፥ ዓይንንም ያበራል"። መዝ 18፥7-8።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሐምሌ_20_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዮሐንስ 6
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³⁵ ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም።
³⁶ ነገር ግን አይታችሁኝ እንዳላመናችሁ አልኋችሁ።
³⁷ አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፥ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም፤
³⁸ ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና።
³⁹ ከሰጠኝም ሁሉ አንድን ስንኳ እንዳላጠፋ በመጨረሻው ቀን እንዳስነሣው እንጂ የላከኝ የአብ ፈቃድ ይህ ነው።
⁴⁰ ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።
⁴¹ እንግዲህ አይሁድ፦ ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ ስላለ ስለ እርሱ አንጐራጐሩና፦
⁴² አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? እንግዲህ፦ ከሰማይ ወርጃለሁ እንዴት ይላል? አሉ።
⁴³ ኢየሱስ መለሰ አላቸውም፦ እርስ በርሳችሁ አታንጐራጕሩ።
⁴⁴ የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።
⁴⁵ ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ ተብሎ በነቢያት ተጽፎአል፤ እንግዲህ ከአብ የሰማ የተማረም ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል።
⁴⁶ አብን ያየ ማንም የለም፤ ከእግዚአብሔር ከሆነ በቀር፥ እርሱ አብን አይቶአል።
⁴⁷ እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ የ #እመቤታች_ማርያም ቅዳሴ ነው። መልካም በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
††† እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና ለታላቁ ሰማዕት ማር ቴዎድሮስ ሊቀ ሠራዊት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም †††

††† ለስም አጠራሯ ክብር ይሁንና እመ ብርሃን ድንግል ማርያም በዚህች ቀን ወደ ቤተ መቅደስ ገብታለች:: በዓሉ ከሰላሳ ሦስቱ የእመቤታችን በዓላት እንደ አንዱ አይቆጠርም:: ምክንያቱም ቅዱሳን ሊቃውንት በዓታ ከበዓታ ጋር ይስማማል ብለው የታኅሣሥ ሦስትን በዓል ከሰላሳ ሦስቱ ደምረውታል::

እመቤታችን ወደ ቤተ መቅደስ የገባችው ሁለት ጊዜ ሲሆን:-
1.ዛሬ የምናከብረውና በተወለደች በሰማንያ ቀኗ የገባችበት ነው:: (ከግንቦት 1 ጀምረን እናስላው: 80 ቀን ይመጣል::)
ኦሪት እንዳዘዘው ቅዱሳን ኢያቄምና ሐና ንጽሕት ሕፃን ድንግል ማርያምን ታቅፈው: የርግብ ልጆች (ግልገሎች): ዋኖስም ይዘው ወደ ቤተ መቅደስ ሒደዋል::
ካህናቱ ዘካርያስና ስምዖን ወጥተው በደስታ ተቀብለዋቸዋል:: እመቤታችን ለወላጆቿ ማኅጸን የከፈተች በኩር ናትና በእግዚአብሔር ፊት አቅርበዋታል::

2.ከሦስት ዓመታት በኋላ እንደ ስዕለታቸው ወደ ቤተ መቅደስ ወስደው ለእግዚአብሔር ሰጥተዋት ተመልሰዋል::

እግዚአብሔር ዛሬ ያልቃል: ነገ ይደቃል የማይባለውን የድንግል እናቱን ፍቅር አብዝቶ ያድለን:: በረከቷም በእኛ ላይ ጸንቶ ይኑር::

††† ቅዱስ ቴዎድሮስ ሰማዕት †††

††† በቤተ ክርስቲያን የሰማዕታት አለቅነት ከተሰጣቸው ሰማዕታት አንዱ የሆነው ማር ቴዎድሮስ የተወለደው በምድረ አንጾኪያ (ሶርያ) በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: አባቱ ዮሐንስ በትውልድ ግብጻዊ የሆነ ክርስቲያን ነው:: እናቱ ግን አስቸጋሪና ጣዖት አምላኪ ሶርያዊት ነበረች::

ባልና ሚስት አብረው ሲኖሩ ሚስት ባሏ ክርስቲያን መሆኑን አታውቅም ነበር:: ቴዎድሮስ (የእግዚአብሔር ስጦታ ማለት ነው) በተወለደ ጊዜ ግን ጠብ ተነሳ:: እሱ ክርስትና ለማስነሳት: ሚስት ደግሞ ወደ ጣዖት ቤት ለመውሰድ ተጋጩ:: ሚስት ወገኖቿ ባለስልጣኖች ናቸውና ልጁን ቀምታ ባሏን ዮሐንስን ወደ ግብጽ አሳደደችው::

ዮሐንስ በስደት ባለበት ሃገር ስለ ልጁ ፈጽሞ ይጸልይ: ያለቅስም ገባ:: እግዚአብሔር ደግሞ ልመናውን ሰማ:: ማር ቴዎድሮስ ወጣት በሆነ ጊዜ ማንም ሳይጠራው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሔዶ ተማረ: ተጠመቀ:: ዕለት ዕለትም ጾምና ጸሎትን ከምጽዋት ጋር ያበዛ: ድንግልናውን ለመጠበቅ ይተጋ ነበር::

በዛው ልክ ደግሞ ገና በሃያ ዓመቱ በጉልበቱ ኃያል: በውበቱም ደመ ግቡ: በጠባዩም ገራገር ነበርና ተወዳጅ ነበር:: ነገሥታቱም የአንጾኪያ የጦር ሠራዊት አለቃ አድርገው ሾሙት:: እነሆ እስከ ዛሬ "የሠራዊት አለቃ" ተብሎ ይጠራል::

ማር ቴዎድሮስ በተሳተፈባቸው ጦርነቶች ሁሉ ተሸንፎ አያውቅም:: ይልቁኑ የነገሥታቱን (የጠላት) ልጆች በመማረክ ነው የሚታወቀው:: እንዲያውም አንድ ጊዜ ከአሕዛብ ጋር በተደረገ ጦርነት ብቻውን አሸንፏቸዋል::

የፋርስ ሰዎች ሊዋጉ ሲመጡ መልአክ ከሰማይ ወርዶ ሰይፍ ሰጠው:: ፋርሶችን "በከንቱ ከምትጠፉ ወደ ሃገራችሁ ተመለሱ" አላቸው:: እነርሱ ግን ተሳለቁበት:: ከፈረሱ ወርዶ ወደ ምስራቅ ዙሮ ጸልዮ በመስቀል አማተበ:: በመካከላቸው ገብቶም በመልአኩ ሰይፍ ለወሬ ነጋሪ ሳያስቀር አጠፋቸው::

አንድ ቀን ወደ አንድ ከተማ ቢገባ ዘንዶ ሲመለክ አገኘ:: ይባስ ብሎ የአንዲት ክርስቲያን ልጆችን ለመስዋዕትነት ሲያቀርቧቸው ተመለከተ:: በስመ ሥላሴ አማትቦ: በፈረሱ ላይም ተቀምጦ ዘንዶውን በጦር ገደለው:: የዘንዶውም ርዝመት ሃያ አራት ክንድ ነበር::

ከነገር ሁሉ በኋላ ቅዱስ ቴዎድሮስ ስለ አባቱ ወሬ ሰምቶ: ካለበት ሥፍራ አፈላልጎ አግኝቶ ደስ አሰኘው:: እስኪያርፍ አብሮት ቆይቶ: ቀብሮት ወደ አንጾኪያ ሲመለስ ግን የሚያሳዝን ነገር ጠበቀው::
ክርስቶስ ተክዶ:
ጣዖት ቁሞ:
አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለው:
የክርስቲያኖች ደም ፈሶ:
ከተማዋ በግፍ ተሞልታ ተመለከተ:: እርሱም በዚያች ሰዓት መወሰን ነበረበትና አደረገው:: የሁሉ ሠራዊት አለቃ ቢሆንም የክብር ልብሱን አውልቆ: ባጭር ታጥቆ በንጉሡ ዲዮቅልጢያኖስ ፊት ቆመ::

††† ማር ቴዎድሮስ በአደባባይ እንዲህ ተናገረ:- "አንሰ አመልኮ ለክርስቶስ ንጉሠ ስብሐት በኩሉ ልብየ: ወእሠውዕ ሎቱ - እኔስ የክብር ባለቤት ክርስቶስን በፍጹም ልቤ አመልከዋለሁ: ለእርሱም ብቻ እሠዋለሁ::" ንጉሡ በቁጣ መሬት ላይ ጥለው እንዲደበድቡት አዘዘ:: ወታደሮቹ ደሙ እስኪንጠፈጠፍ ገረፉት::

በብዙ መክፈልተ ኩነኔ አሰቃይተው በእሳት አቃጠሉት:: እርሱ ግን በጸሎቱ እሳቱን ውኃ አደረገው:: ወታደሮቹ እርሱን በብዙ አሰቃዩ:: እርሱ ግን በእግዚአብሔር ኃይል ጸና: ታገሠ::

በመጨረሻም ጌታችን በግርማ ወርዶ "ወዳጄ ቴዎድሮስ ስምህን የጠራ: መታሠቢያህን ያደረገ: ገድልህን (ዜናህን) የጻፈ: ያጻፈ: ያነበበ: ገዝቶ በቤቱ ውስጥ ያኖረውን ሁሉ እምርልሃለሁ" አለው::

በስሙም ረድኤት እንደሚደረግ ነግሮት ዐረገ:: ወታደሮቹም በዚህ ቀን አንገቱን ሰይፈው የክብር አክሊልን ተቀብሏል:: እጅግ ብዙ ሺህ ሰዎችም አብረውት ተሰይፈዋል::

††† ቸሩ ፈጣሪ ከሰማዕቱ በረከት ይክፈለን::

††† ሐምሌ 20 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም (በሰማንያ ዕለት)
2.ቅዱስ ወክቡር ማር ቴዎድሮስ ሰማዕት (የሠራዊት አለቃ)
3.ቅዱስ ጢሞቴዎስ ዘእስክንድርያ
4.አራት መቶ አራት ሰማዕታት (የቅዱስ ቂርቆስ ማኅበር)
5.ቅድስት አውስያ (የማር ቴዎድሮስ እናት - በልጇ ምክንያት ያመነች እናት ናት)

††† ወርኀዊ በዓላት
1..ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር
2.ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ
3.ቅዱስ አፄ ካሌብ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
4.አባ አሞንዮስ ዘሃገረ ቶና
5.ቅድስት ሳድዥ የዋሒት

††† "እግዚአብሔር ለኛ የሰማዕትነትን ሥራ ይሰጠን ዘንድ ቅዱሳን ስለሚሆኑ ሰማዕታት እንማልዳለን::" †††
(ሥርዓተ ቅዳሴ ቁ. ፸፫)

††† "በጐንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው? ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብጹዓን ናችሁ:: ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ:: አትናወጡም:: ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስን በልባችሁ ቀድሱት:: በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ:: ነገር ግን በየውሃነትና በፍርሃት ይሁን::" †††
(፩ጴጥ. ፫፥፲፫-፲፮)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም : ቅዱስ ዑራኤል እና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ድንግል እመቤታችን እና ቅዱስ ዑራኤል †††

††† በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት በዚህች ቀን ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ የሆነው ቅዱስ ዑራኤል:-
1.ድንግል ማርያም በአካለ ሥጋ እያለች ወደ ሰማይ አሳርጓታል:: በሠረገላ ብርሃን ጭኖ: በክንፎቹም ተሸክሞ: አስቀድሞ ገነትን ቀጥሎም ሲዖልን አስጐብኝቷታል:: በዚህም ምክንያት እመ ብርሃን ስለ ኃጥአን የምታለቅስ: የምትለምንና የምትማልድ ሆናለች:: ለምናም አልቀረች የምሕረት ቃል ኪዳን ተቀብላለች::

2.ቅዱሱ መልአክ እመ ብርሃንን በስደቷ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መርቶ አምጥቷታል:: በክንፉ ተሸክሞ: በአራቱም አቅጣጫ አዙሮ አሳይቶ አሥራት እንድትቀበል አድርጓል::

3.ጌታችን በተሰቀለ ጊዜ ደሙን በጽዋዕ አድርጐ በኢትዮጵያ ወንዞች ላይ አፍስሷል::

4.ለብዙ ቅዱሳን (አባ ጊዮርጊስን ጨምሮ) ጽዋዐ ልቡናን አጠጥቷል::

††† አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ኢትዮጵያዊ †††

††† ወላጆቻቸው ማርቆስ እና እግዚእ ክብራ ይባላሉ:: ተአምራትን ገና ከእናታቸው ማኅጸን ጀምሮ ይሠሩ የነበሩት ጻድቁ በልጅነታቸው መጻሕፍትን ተምረው መንነዋል:: በስብከተ ወንጌልም ትግራይና አካባቢውን አድርሰዋል:: በነዚህም ጊዜያት ብዙ አርድእትን አፍርተዋል::

በጋስጫ ገዳም መስርተው የወንድና የሴት ብለውም ለይተዋል:: ሲጸልዩም ሆነ ሲያስተምሩ ተደሞ ይመጣባቸው የነበረ ሲሆን አንድ ቀን እባቡን ዓሣ አድርገው ደቀ መዛሙርትን አስደንቀዋል::

ከጾም: ከጸሎትና ከስግደት ባሻገር ከወቅቱ ንጉሥ ዓምደ ጽዮን መከራ በመቀበላቸው እንደ ሰማዕትም ይቆጠራሉ:: ከብዙ የገድል ዓመታት በኋላም በ1330 ዓ/ም በዚህች ቀን ትግራይ ውስጥ ዐርፈዋል:: በቆይታ ግን ወደ ጋስጫ ዐጽማቸው ፈልሷል::

††† ቅዱስ ላዕከ ማርያም ኢትዮጵያዊ †††

††† ቅዱሱ የአፄ ናዖድ የልጅ ልጅ : የቅድስት ሮማነ ወርቅ ልጅ : የልብነ ድንግል የእህት ልጅና የገላውዴዎስ አጐት ነው:: በግራኝ አህመድ ዘመን ተማርኮ ወደ የመን : ከዛም ቱርክ ተወስዷል::

ሃይማኖቴን አልክድም ስላለ ብዙ አሰቃይተው : አባለ ዘሩን ቆርጠው ጃንደረባ አደረጉት:: በድንቅ ተአምር ግን ወደ ሃገሩ ተመለሰ:: እስከ ዕለተ ሞቱም ነዳያንን ሲያበላ ኑሮ ዛሬ ዐርፏል::

††† ቅዱስ ሱስንዮስ †††

በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረ የኤፌሶን ሰው ሲሆን ጃንደረባም ነበር:: በ431 ዓ/ም ሁለት መቶውን የጉባዔ ኤፌሶን ሊቃውንት አገልግሎ በዛው ዓመት አርፏል:: ቅዱስ ቄርሎስ ገንዞ ቀብሮታል::

††† ብጹዕ አወ ክርስቶስ †††

ከተባረከች ሚስቱ ጋር በአንድ ቤት ውስጥ : ግን ደግሞ በድንግልና ኑረዋል:: ቀን ቀን እንግዳ ሲቀበሉ: ነዳያንን ሲያበሉ ውለው ሌሊት ሲገሰግዱና ሲጸልዩ ያድሩ ነበር:: ጌታችን ከሰማይ መስክሮላቸው ዛሬ ዐርፈዋል::

††† ቅዱስ ዮራኖስ †††

በሉቃስ ወንጌል ላይ (ሉቃ. 23:47) የምናገኘው የመቶ አለቃው ሲሆን በጌታችን ትንሣኤ ቀን የጠፋች ዓይኑ በርታለት በክርስቶስ አምኖ ለሰማዕትነት በቅቷል::

††† ከእመቤታችን ድንግል ማርያም ጣዕሟን ፍቅሯን : ከቅዱሳኑ ሁሉ ጸጋ በረከትን እግዚአብሔር ያድለን::

††† ሐምሌ 21 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅድስት ድንግል እግዝእትነ ማርያም ወላዲተ አምላክ
2.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
3.አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ጻድቅ (ኢትዮጵያዊ)
4.ቅዱስ ላዕከ ማርያም ሔር (ኢትዮጵያዊ)
5.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ (ኢትዮጵያዊ) ልደታቸው
6.ብጹዕ አወ ክርስቶስና ሚስቱ (ጻድቃን)
7.ቅዱስ ሱስንዮስ ጻድቅ
8.ቅዱስ ዮራኖስ መኮንን (የመቶ አለቃው)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.አበው ጎርጎርዮሳት
2.አቡነ ምዕመነ ድንግል
3.አቡነ አምደ ሥላሴ
4.አባ አሮን ሶርያዊ
5.አባ መርትያኖስ ጻድቅ

††† "እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ: ስለ ሶምሶንም: ስለ ዮፍታሔም: ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም: ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና:: እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ:: ጽድቅንም አደረጉ:: . . ." †††
(ዕብ. ፲፩፥፴፪)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
2024/10/02 02:45:05
Back to Top
HTML Embed Code: