Telegram Web Link
† እንኳን ለአባታችን ቅዱስ ድሜጥሮስ ዓመታዊ የተአምር በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

† ቅዱስ ድሜጥሮስ ድንግል †

††† ቅዱስ ድሜጥሮስ በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን የተወለደ: በመንፈሳዊ ለዛ ከአጐቱ ደማስቆስ ጋር ያደገ የዘመኑ ደግ ሰው ነበር:: በዘመኑ ክርስቲያኖች በሰማዕትነት ያለቁበት በመሆኑ ቤተሰቦቹ የአጎቱን ልጅ ልዕልተ ወይንን እንዲያገባ ግድ አሉት::

ቅዱስ ድሜጥሮስ የነርሱን ፈቃድ ለመፈፀም ጋብቻውን በተክሊል ፈፀመ:: የፈጣሪውን ፈቃድ ለመፈፀም ደግሞ ከቅድስት እናታችን ልዕልተ ወይን ጋር ተስማምተው ለ48 ዓመታት በአንድ አልጋ ላይ እየተኙ: አንድ ምንጣፍና ልብስ እየተጋሩ በድንግልና ኑረዋል::

ቅዱስ ሚካኤልም ስለ ክብራቸው ከመካከላቸው ሆኖ ቀኝ ክንፉን ለርሱ : ግራ ክንፉን ለርሱዋ ያለብሳቸው ነበር:: ከ48 ዓመታት በሁዋላ ቅዱስ ድሜጥሮስ የግብፅ 12ኛ ሊቀ ዻዻስ ሆኖ ተሹሞ: ምስጢር በዝቶለት ባሕረ-ሐሳብን ጽፎ ሠርቷል::

ሰይጣን በሰዎች አድሮ ቅዱሱን ሚስት አለው በሚል ቤተ ክርስቲያን ላይ ሁከት በመፈጠሩ ቅዱስ ድሜጥሮስ በመልዐኩ ትእዛዝ ሕዝቡን ሰብስቦ: እሳት አስነድዶ: ከቅድስት ልዕልተ ወይን ጋር እሳቱ ውስጥ ገብተው ለረዥም ሰዓት ጸልየዋል::

ሕዝቡም ይሕን ተአምር አይተው: የቅዱሳኑን ንጽሕና ተረድተው: "ማረን" ብለው በፍቅር የተለያዩት በዚሕ ዕለት ነው::

ቅዱስ ድሜጥሮስና እናታችን ልዕልተ ወይን ተረፈ ዘመናቸውን በቅድስና አሳልፈዋል:: በተለይ ሊቀ ዻዻሳቱ ድሜጥሮስ ብዙ ድርሳናትን ደርሷል:: እነ አርጌንስ (Origen) ና ቀሌምንጦስ ዘእስክንድርያ (Clement of Alexandria) የመሰሉ መናፍቃንንም አውግዟል::

ከጣዕመ ስብከቱም የተነሳ አርጅቶ እንኩዋ ምዕመናን እየተሰበሰቡ ይማሩ ነበር:: በአልጋ ተሸክመውም ይባርካቸው ነበር:: ቅዱሱ በ107 ዓመቱ ያረፈው በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን አጋማሽ አካባቢ ነው::

††† አምላከ ድሜጥሮስ ንጽሕናውን ያሳድርብን:: ጸጋ በረከቱን ደግሞ ያትረፍርፍልን::

††† መጋቢት 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ድሜጥሮስ ሊቀ ዻዻሳት (ደንግልናው የተገለጠበት)
2.ቅድስት ልዕልተ ወይን
3.ቅዱስ መላዚ ሰማዕት

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላዕክት (ጠንቁዋዩን በለዓምን የገሰጸበትና አህያዋን እንድትናገር ያደረገበት)
2.ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
3.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
4.ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ (ሰማዕት)
5.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
6.አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ

††† "ሥጋዊ ፈቃዳቸውን የሚሠሩ ሁሉ እነርሱ በላይኛው ዓለም የሞቱ ናቸው:: ግን በመንፈሳዊ ሥራ የሥጋችሁን ፈቃድ ድል ከነሳችሁት ለዘለዓለም በሕይወት ትኖራላችሁ:: የእግዚአብሔር መንፈስ የሚወደውን ሥራ የሚሠሩ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው::" †††
(ሮሜ. 8:13)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ለ40 ቅዱሳን እና ለታላቁ ቅዱስ መቃርስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ታላቁ ቅዱስ መቃርስ †††

††† ታላቁ ቅዱስ መቃርስ (ቅዱስ መቃሬ) "ጽድቅ እንደ መቃርስ" የተባለለት: የመነኮሳት ሁሉ አለቃ: ከ80 ዓመታት በላይ በበርሃ የኖረ: በግብፅ ትልቁን ገዳም (አስቄጥስን) የመሠረተ: ከ50,000 በላይ መነኮሳትን ይመራና ይመግብ የነበረ ፍፁም ጻድቅ ነው::

በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን በዚሕች ዕለት አርዮሳውያን ደጉን ታላቅ አባት በሰንሰለት አስረው ከግብፅ ወደ እስያ በርሃ ከጉዋደኛው ቅዱስ መቃርዮስ እስክንድርያዊ ጋር አሰድደውታል:: በዚያ ለ2 ዓመታት ስቃይን ከተቀበሉ በሁዋላ በአረማውያን ፊት ድንቅ ተአምር አድርገው አረማውያንን ከነ ንጉሳቸው አጥምቀዋል::

በተሰደዱባት ሃገርም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ (ስም አጠራሩ ይክበርና) እመቤታችንን: ቅዱሳን ሐዋርያትን: አዕላፍ መላእክትን: በተለይ ደግሞ ቅዱሳኑን ዳዊትን: ዮሐንስ መጥምቁንና ወንጌላዊውን: ማርቆስን: ዼጥሮስን: ዻውሎስን አስከትሎ ወርዶ ተገልጦላቸዋል::

በቅዱስ አንደበቱም የምሕረት ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል:: ታላቁ ቅዱስ መቃርስና ባልንጀራው መቃርዮስ ከ2 ዓመታት ስደትና መከራ በሁዋላ ስደት በወጡባት በዚችው ዕለት መልዐኩ ኪሩብ በክንፉ ተሽክሞ ወደ ግብፅ መልሷቸዋል:: በወቅቱም ጻድቁን ለመቀበል ከ50,000 በላይ የሚሆኑ ልጆቻቸው መነኮሳት በዝማሬ ወጥተዋል::

††† ከቅዱሳን አባቶቻችን የስደት በረከት ፈጣሪ አይለየን::

††† አርባ ሐራ ሰማይ †††

††† አርብዐ ሐራ ሰማይ ማለት በዘመነ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ሰማዕትነትን የተቀበሉ 40 ጭፍሮች ናቸው:: "ሐራ ሰማይ" የተባሉት በምድር ሲሠሩት የቆዩትን የውትድርና ሥራ ትተው የክርስቶስ (የሰማያዊው ንጉሥ) ጭፍራ ለመሆን በመብቃቸው ነው::

አርባው ባልንጀሮች ወጣትና ጐበዝ ክርስቲያኖች ነበሩ:: በእርግጥ እነርሱ ሰማዕትነት የተቀበሉበት ጊዜ ዘመነ ሰማዕታት አልነበረም:: ነገር ግን ሰማዕትነት የጊዜ : የቦታ : የሁኔታ : የእድሜ : የጾታ : የዘር . . . ልዩነት አያግደውምና እነዚህ ወጣቶች ለዚህ ክብር በቅተዋል::

ነገሩ እንደዚህ ነው:-
በ330ዎቹ አካባቢ የዓለም ንጉሥ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ አንዱን መኮንኑን ወደ ቂሣርያ አካባቢ ይልከዋል:: የተላከው አካባቢውን ለማስተዳደር ሲሆን ቦታው ስብስጥያ (ሴባስቲ) ይሰኛል::

መኮንኑ ክርስቲያኖችን እንዲንከባከብ ጥብቅ ትዕዛዝ ከንጉሡ ቢሰጠውም ፍቅረ ጣዖት በልቡ የነበረበት ሰው ነውና ክርስቲያኖችን ይጨቁን : ያሰቃይ : ይገድል : አብያተ ክርስቲያናትን ያፈርስ ገባ::

በጊዜው ይህንን የተመለከቱት 40ው ጭፍሮች በአንድነት መክረው መኮንኑን ገሠጹት:: ስመ ክርስቶስንም ሰበኩለት:: እርሱም በፈንታው 40ውን አስሮ ብዙ አሰቃያቸው::

በመጨረሻ ግን 40ውንም የበረዶ ግግር አስቆፍሮ: ከነ ሕይወታቸው እስከ አንገታቸው ቀብሮ : ለ39 ቀናት ያለ ምግብ በጽኑ ስቃይ አቆያቸው:: በ40ኛው ቀን ግን ከ40ው አንዱ "ይህን ሁሉ መከራ የምቀበል ለምኔ ነው?" ብሎ "አውጡኝ!" እያለ ጮኸ::

ክርስቶስን አስክደው ወደ ውሽባ ቤት (ሻወር ቤት) ሲያስገቡት ፈጥኖ ሞተ:: በነፍስም በሥጋም ተጐዳ:: ነገር ግን ከአረማውያን ወታደሮች አንዱ "እኔን አስገቡኝ" ስላለ እንደገና 40 ሆኑ::

በዚህች ዕለትም 40ውን ጭን ጭናቸውን በመጅ እየሰበሩ ሲገድሏቸው ቅዱሳን መላእክት በአክሊል ከልለው : በዝማሬ አጅበው ወደ ገነት ወስደዋቸዋል:: ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስም በጊዜው ነበርና ገድላቸውን ጽፎ ውዳሴ ደርሶላቸዋል:: ቤተ ክርስቲያናቸውንም አንጾ የካቲት 16 ቀን እንዲቀደስ አድርጉዋል::

ብጹዕ አባታችን አባ ሕርያቆስም በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ ላይ በቅዱሳኑ ላይ የሆነውን ነገርና ሥልጣነ እግዚአብሔርን እያደነቀ እንዲህ ሲል ተናግሯል::

"ኦ አውጻኢሁ ለዘእንተ ውስጥ:: (በውስጥ ያለውን የምታስወጣ)"
"ወአባኢሁ ለዘእንተ አፍአ:: (በውጪ ያለውንም የምታስገባ)"
"ወይእዜኒ ስማዕ አውያቶሙ ለሕዝብከ እለ ይጼውዑከ በጽድቅ:: (እንግዲህ በእውነት የሚጠሩህን የወገኖችህን ጩኸት /ልመና/ ስማ)" ((ቅዳሴ ማርያም ቁ.146))

ስለዚህ በውስጥ ያለን አንታበይ:: ያለንበት የእኛ አይደለምና:: እንዳንወድቅም እንጠንቀቅ:: ብዙዎቹ የቆሙ ሲመስላቸው ወድቀዋልና:: ያሉ ሲመስላቸውም ወጥተዋልና::

በውጪ ያለንም ተስፋ አንቁረጥ:: ወደ ሁዋላም አንበል:: ወደ ቤቱ ሊመልሰን : በክብሩ ማደሪያ ሊያኖረን የታመነ አምላክ አለንና::

††† ቸሩ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ገብቶ ከመውጣት : አግኝቶ ከማጣት ይሠውረን:: ከሰማዕታቱ በረከትም አይለየን::

††† መጋቢት 13 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ታላቁ ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ-ስደቱ)
2.ቅዱስ መቃርዮስ እስክንድርያዊ
3.40 ቅዱሳን ሰማዕታት (ከሃገረ ስብስጥያ)
4.ቅዱስ ዲዮናስዮስ (ጻድቅ ሊቀ ዻዻሳት)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.እግዚአብሔር አብ
2.ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላዕክት
3."99ኙ" ነገደ መላዕክት
4.ቅዱስ አስከናፍር
5."13ቱ" ግኁሳን አባቶች
6.ቅዱስ አርሳንዮስ ጠቢብ ገዳማዊ
7.አቡነ ዘርዐ ቡሩክ

††† "ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብጹዓን ናቸው:: መንግስተ ሰማያት የእነርሱ ናትና:: ሲነቅፏችሁና ሲያሳድዷችሁ: በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብጹዓን ናችሁ:: ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ:: ሐሴትንም አድርጉ:: ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳደዋቸዋልና::" †††
(ማቴ. 5:10)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
#ከቅዱስ_ዲሜጥሮስ_ሊቅ ጋር በአንድ መኝታ ሆነው #በንጽሕና እና #በድንግልና የኖረች #ቅድስት ማን ናት?
Anonymous Quiz
42%
#ልዕልት_ወይን
30%
#ፍቅርተ_ማርያም
14%
#ማርያም_ሞገሳ
15%
#ሐረግ_ወይን
የበለዓም _____________አወራች #መልአኩን ስታይ
Anonymous Quiz
85%
አህያ
4%
በግ
3%
ፍየል
8%
እህት
"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

      #መጋቢት ፲፬ (14) ቀን።

እንኳን #ለሐዋያው_ለቅዱስ_ቶማስ ሰባት ዓመት ያህል የጋኔን ግንኑኙነት በአስቸገራት በአንዲት ሴት ላይ ተአምራትን ላደረገበት በዓል፣ ለአረጋውያን ፍጹማን መነኰስ አመንዝራ ሴቶች ብር እየሰጠ በጥበብ ለትዳርና ምንኵስና ላበቃ #ለአባ_ባጥል ለዕረፍት በዓል፣ ለቅዱስ አባት #ለአባ_ሲኖዳ ሰማዕትነት ለተቀበሉበት ለዕረፍት በዓል፣ ለእስክድርያ ሰባ አምስተኛ ሊቀ ጳጳሳት #አባ_ቆርሎስ ለዕረፍት በዓል፣ ለከበሩ #ቅዱሳን_አጋንዮስ_ለአውንድርያኖስና_ለብንድዮስ ሰማዕትነት ለተቀበሉበት ለዕረፍታቸው በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።

                            
#ሐዋርያው_ቅዱስ_ቶማስ ሰባት ዓመት ያህል የጋኔን ግንኑኙነት በአስቸገራት በአንዲት ሴት ላይ ያደረው ተአምራትን ይህ ነው፦ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስንም በአየችው ጊዜ "የክርስቶስ ሐዋርያው ሆይ እጅግ ከሚያሠቃየኝ ጠላት አድነኝ" ብላ ወደርሱ ጮኸች። እርሱም "በምን ምክንያት አገኘሽ" አላት። እርሷም "ከመታጠቢያ ከውሽባ ቤት ስወጣ እንደ ሰው ድው ድው እያደረገ በመታወክ መጣ ድምጡም ሰላላና ቀጭን ነው በሴትና በወንድ ሥራ ሁሉ ነይ እርስበርሳችን አንድ እንሁን አለኝ በተኛሁም ጊዜ በሌሊት መጥቶ ከእኔ ጋር አንድ ሆነ ብሸሽም አይተወኝም መጥቶ ያሠቃየኛል እንጂ እኔም ከጸሎትህ የተነሣ አጋንንት እንደሚንቀጠቀጡ አውቃለሁና ጸልይልኝ አድነኝም" አለችው።

ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስም ሰምቶ ጸለየ ጋኔኑንም ከእርሷ እንዲወጣ አዘዘው ያንጊዜም በእሳትና በጢስ አምሳል ከሴቲቱ ላይ ወጥቶ ተበተነ ከዚህ በኋላ በክርስቶስ መስቀል በላይዋ አማተበ ሥጋውንና ደሙንም አቀበላት ወደ ዘመዶቿም አሰናበታት። የሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ልዩ የሆነች በረከቱም በሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ላይ ትደር ለዘላለሙ አሜን።

                            
#አባ_ባጥል፦ ይህም ቅዱስ ሰው ከአባ ዮሐኒ የተባለ አበ ምኔት በመነኰሳት ላይ ነገረ ሠሪን እንደሚቀበል በሰማ ጊዜ በዓቱን ትቶ ወደ እስክንድርያ መጥቶ የሴት አዳሪዎችንና የአመንዝራዎችን ሁሉ ስማቸውን ጻፈ። ከኪራይ ሠራተኞችም ጋራ ሲሠራ ይውላል። ደመወዙን በተቀበለ ጊዜ የሽንብራ ቂጣ ገዝቶ ይበላል የቀረውንም ገንዘብ ይዞ ወደ አንዲቱ ሒዶ ይሰጣታል "በዚች ቀን ከአንቺ ጋራ አድራለሁና ራስሽን ለእኔ አዘጋጂ" ይላታል። ከኀጢአትም ሊጠብቃት ከእርስዋ ዘንድ ያድራል ሌሊቱን ሁሉ ተነሥቶ ሲጸልይና ሲሰግድ እግዚአብሔር ሲለምን ያድራል ሲነጋም ሥራውን ለማንም እንዳትገልጥ አምሏት ወደ ተግባሩ ይሔዳል።

በየዕለቱም ወደ የአመንዝራዎቹ እየሔደ እንዲህ ያደርግ ነበር አንዲቱም ሴት ምሥጢሩን ገለጠች ጋኔንም ይዞ አሳበዳት። ሰዎችም ስለዚህ ክፉ ሽማግሌ ክፉ ሥራ የለበትም ብላ ወሽታለችና እግዚአብሔር መልካም አደረገባት ተባባሉ። እርሷም "እንዳናመነዝር ገንዘብ በመስጠት ከኃጢአት ይጠብቀናል እንጂማ ነውር የለበትም" ብላ ነበርና። የቀሩት አመንዝራዎች በእርሷ ላይ የሆነውን በአዩ ጊዜ ደነገጡ እንደርሷም እንዳያብዱ እውነቷን ነው ማለትን ፈሩ። እርሱም "ይችስ በእገሌ ዕለት ትጠብቀኛለች" ይል ጀመረ ሰዎችም ሁሉ ያሙት ጀመር እርሱም "እንደ ሰው ሁሉ ሥጋ የለኝምን ወይስ እግዚአብሔር መነኰሳትን ተቆጥቶ በፍትወት ተቃጥለው እንዲሞቱ ትቷቸዋልን" አላቸው። እነርሱም "ልብስህን ለውጠህ ሚስት አግባ ይህ ይሻልሃልና" አሉት። እርሱም "አዎን ብወድ በሚስቴ እጠነቀቃለሁ በዚህም በክፉ አኗኗር እኖራለሁ እናንተ ግን ከእኔ ዘንድ ሒዱ ምን ትሻላችሁ በእኔ ላይ እግዚአብሔር ፈራጆች አድርጓችኋልን ይልቁንስ እናንተ እንዳይፈረድባችሁ ለራሳችሁ አስቡ ፈራጅ አንድ ነውና ዕለቲቱም አንዲት ናትና" አላቸው።

ይህም ቅዱስ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት አገኘ በሰው ዘንድ ግን የተናቀ ሁኖ ኖረ። ከእርሱ ጥቅም የአገኙ አመንዝራዎችም ዝሙታቸውን ተዉ። ከእርሳቸውም ሕጋዊ ጋብቻ ተጋብቶ የኖረ አሉ ወደ ገዳምም ገብቶ መንኵሶ በጾም በጸሎት ተወስኖ የኖሩ አሉ።

በአንዲት ዕለትም ከአንዲት አመንዝራ ቤት ሲወጣ ያቺን ሴት አስቀድሞ የለመዳት አንድ ሰው አገኘውና "ይህ ሽማግሌ እስከ መቼ ድረስ በዚህ በክፉ ሥራ ይኖራል" ብሎ ፊቱን በጥፊ መታው።

ከዚህም በኋላ በአንዲት ቀን በበዓቱ ውስጥ ሰግዶ ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ሰጥቶ በቤቱም መድረክ "የዚች አገር ሰዎች ጊዜው ሳይደርስ በማንም ላይ አትፍረዱ እንዳይፈረድባችሁ" የሚልም ጽሑፍ ተጽፎ ተገኘ። ከአባ ባጥል በጸሎቱ የሚገኝ በረከቱ ከእኛ ጋራ ለዘላለሙ ይኑር አሜን።

                             
#አባ_ሲኖዳ፦ እርሱም በግብጽ አገር ከብሕንሳ ነው። ወደ መክስምያኖስም ክርስቲያናዊ ሲኖዳ "አማልክትን የሚያመልክ ነው" ብለው ነገር ሠሩበት። እርሱም አስቀርቦ ስለ ሃይማኖቱ ጠየቀው በንጉሡም ፊት በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ እርሱም ዕውነተኛ አምላክ እንደ ሆነም መሰከረ።

መክስምያኖስም ይህን የከበረ አባ ሲኖዳን በምድር ላይ ዘርግተው በበትሮች እንዲደበድብት አዘዘ። ዐጥንቶቹ እስቲሠነጠቁ ደሙም በምድር ላይ እንደ ውኃ እስቲፈስ እንዲሁ አደረጉበት። ከዚህም በኋላ እግሩን ይዘው ጐትተው ወስደው ሽታው በሚከረፋ በጨለማ ወህኒ ቤት ጣሉት የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ተገለጠለት። ቊስሎቹንም አድኖ ጤነኛ አደረገው አበረታውም "በርታ አትፍራ ስለ መከራህም የክብር አክሊል ተዘጋጅቶልሃልና ደግሞም በጽኑዕ ሥቃይ ትሠቃይ ዘንድ አለህ እግዚአብሔር እንዳዘዘኝ እኔም ከአንተ ጋራ እኖራለሁ" አለው። ከዚያም ከእርሱ ተሠወረ።

በነጋ ጊዜም "የነገሥታትን ትዕዛዝ የሚተላለፍ ያንን ዓመፀኛ ሒዳችሁ እዩት ሙቶም ከሆነ ለውሾች ጣሉት" ብሎ መክስምያኖስ ወታደሮቹን አዘዘ። ወደርሱም በደረሱ ጊዜ ቁሞ ሲጸልይ አግኝተውት "ያለምንም ጥፋት ጤነኛ እንደሆነና በሥጋውም ውስጥ የሕማም ምልክት እንደሌለ እርሱም ከቶ ምንም ሥቃይ እንዳላገኘው ጤነኛና ደስ እንዳለው ሰው ተግቶ እንደሚጸልይ" ስለርሱ ለንጉሡ ነገሩት። ንጉሡም ወደርሱ አስመጣው ከሕይወቱም የተነሣ አደነቀ ልብሶቹንም አስወልቆ ያለጉዳት ጤነኛ እንደሆነ ሥጋውን አየ ደግጦም "ይህ ያየሁት ሥራይ ታላቅ ነው" አለ። ከዚያም ዘቅዝቀው ሰቅለው ከታቹ እሳትን እንዲያነዱ አዘዘ። ይህንንም አደረጉበት ደግሞ በመንኰራኵር አሠቃዩት በአለንጋዎችም አብዝተው ገረፉት ደበደቡትም።

ማሠቃየቱንም በሰለቸ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ቆርጠው ለውሾች እንዲጥሉት አዘዘ ውሾች ግን ፈጽሞ አልቀረቡትም ሌሊትም ሲሆን ምዕመናን መጥተው ሥጋውን ወሰዱ በአዳዲሶች ልብሶችና በጣፋጭ ሽቶዎች ገነዙት በሣጥንም አድርገው ቀበሩት። ከሥጋው ብዙዎች አስደናቂዎች ተአምራቶች ተደረጉ። የአባ ሲኖዳ በረከቱ ከእኛ ጋራ ለዘላለም ትኑር አሜን።
                             
#አባ_ቄርሎስ፦ ይህም አባት የእስክንድርያ ሰባ አምስተኛ ሊቀ ጳጳሳት ነው። እርሱም በምግባሩ ፍጹም ዐዋቂ ሆነ በአገሩ ፍዩም ይባላል በእርሷም ቅስና ተሹሞባት ነበር። ከዚያም ለቆ ወደ አባ ፊቅጦር ገዳም ደረሰ እርሱም ከምስር ከተማ ውጭ የኢትዮጵያውያን ዐዘቅት የዐባይ ግድብ በአለበት ነው። በዚም ታላቅ ገድልን እየተጋደለ ብዙ ዘመናትን ኖረ። ብዙ መጻሕፍትንም ተምሮ ትርጓሜያቸውንና ምሥጢራቸውን ጠንቅቆ ዐወቀ። አሸናፊ ወደሚባለውም ንጉሥ አደባባይ ቀርቦ የእስላሞች ታላላቅ ሊቃውንቶቻቸውና ከምሁራኖቻቸው ውስጥ መምህሮታቸውን ተከራከሩት። ጠቃሚ የሆነ ዕውቀት የተመላበትን መልስ አገኙ የሚጠይቁትንም ሁሉ በመልካም አመላለስ ነገራቸው ከዚህ በኋላ የዕውቀቱና የቅድስናው ዜና በተሰማ ጊዜ ያለ ፈቃዱ ይዘው በእስክንድርያ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት መንጋውንም ጠበቀ በጸሎትና በቅዳሴ ያገለግሉ ዘንድ ለካህናት ሥርዓትንና መመሪያን ሠራ።

ይህም አባት በሊቀ ጵጵስናው ሰባት ዓመታት ከዘጠኝ ወር ከዐሥር ቀኖች ኖረ። ከቀኑም በሦስት ሰዓት መጋቢት14 ቀን ዐረፈ። በምስክርነት አደባባይም ተቀበረ። ከአባ ቄርሎስ በጸሎቱ የምትገኝ በረከቱም ከእኛ ጋራ ለዘላለሙ ትኑር አሜን።

                             
የከበሩ #ቅዱሳን_አጋንዮስ_አውንድርያኖስና_ብንድዮስ፦ እሊህም ቅዱሳን ከአባቶቻቸው ጀምሮ ክርስቲያኖች ናቸው። አምላካዊ ትምህርትንም ሁሉ የተማሩ ናቸው።

በእግዚአብሔርም ሕግ ጸንተው ሲኖሩ የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አርሞስ መርጦ ኤጲስቆጶሳት አድርጎ ሾማቸው ግን በታወቁ ቦታዎች ላይ አይደለም በብዙዎች አገሮች ውስጥ እንዲሰብኩ ላካቸው እንጂ። በአገሮችም ያሉ ከሀድያን ያዟቸው ያለርህራሄም አብዝተው ገረፏቸው በደንጊያም ወገራቸው መጋቢት 14 ቀን ነፍሳቸውንም በጌታች እጅ ሰጡ። የከበሩ ቅዱሳን አጋንዮስ፣ አውንድርያኖስና ብንድዮስ በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ለዘላለም ትኑር አሜን። ምንጭ፦ የመጋቢት14 ስንክሳር።

                             
"#ሰላም_ለቶማስ_እንዘ_ይገብር_መድምመ። እምነ ብእሲት አግኂሦ ትድምርተ ጋኔን ኅሡመ። መንጽሔ ኃጢአት መጠዋ ሥጋ ወደመ። በጊዜ ትቤሎ ሀበኒ ማሕተመ። ከመ ላዕሌየ ኢይግባእ ዳግመ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የመጋቢ_14

                            
#የዕለቱ_ምስባክ፦ "እስመ መምህረ ሕግ ይሁብ በረከተ። ወየሐውር እምኃይል ውስተ ኃይል። ወያስተርኢ አምላከ አማልክት በጽዮን"። መዝ 83፥6-7። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ቆሮ 7፥9-ፍ.ም፣ ያዕ 4፥6-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 6፥1-8። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 7፥1-15። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ባስልዮስ ቅዳሴ ነው። መልካም የጾም ጊዜና በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።

https://www.tg-me.com/joinchat-AAAAAFGQ22bI0Ij80hYpFA

https://www.facebook.com/profile.php?id=100063896616886

https://www.facebook.com/profile.php?id=61552828743736&mibextid=ZbWKw
††† እንኳን ለሰማዕቱ ቅዱስ ሰለፍኮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ሰማዕቱ ሰለፍኮስ †††

††† ቅዱስ ሰለፍኮስ በዘመነ ሰማዕታት የነበረ ክርስቲያን ወጣት ነው:: በወቅቱ ያ የጭንቅና የመከራ ዘመን ከመምጣቱ በፊት በተቀደሰ ጋብቻ ለመኖር አስጠራጦኒቃ የምትባል ደግ የሆነች ክርስቲያናዊት ወጣት አጭቶ ነበር::

በዕጮኝነት ዘመናቸው ጾምን: ጸሎትንና ንጽሕናን በመምረጣቸው ያየ ሁሉ ያደንቃቸው ነበር::
ታዲያ የሠርጋቸው ቀን እየቀረበ ሲመጣ ያ የመከራ ዘመን (ዘመነ ሰማዕታት) ጀመረ::

ሁለቱ ንጹሐን ወጣት ክርስቲያኖች ተመካከሩና ወሰኑ:: በምክራቸውም መሠረት ሁለቱም ከነ ድንግልናቸው ሰማዕትነትን ለመቀበል ተዘጋጁ:: በዚች ዕለትም ስለ ቀናች ሃይማኖትና ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ከብዙ ስቃይ በሁዋላ በከሃዲው ንጉሥ ትዕዛዝ ቅዱስ ሰለፍኮስ በሰማዕትነት አልፏል::

††† ከቅዱሱ ሰማዕት በረከት አምላከ ቅዱሳን ያድለን::

††† መጋቢት 15 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ሰለፍኮስ ሰማዕት
2.እናታችን ቅድስት ሣራ ጻድቅት (ግብፃዊት)
3.አባ ሕልያስ ሰማዕት
4.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሐዲስ

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ
2.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ አፈ በረከት
3.ቅዱስ ሚናስ ግብፃዊ
4.ቅድስት እንባ መሪና
5.ቅድስት ክርስጢና

††† "ሰው ሁሉ እንደ እኔ ሊሆን እወዳለሁና:: ነገር ግን እያንዳንዱ ከእግዚአብሔር ለራሱ የጸጋ ስጦታ አለው:: አንዱ እንደዚህ ሁለተኛውም እንደዚያ:: ላላገቡና ለመበለቶች ግን እላለሁ:: እንደ እኔ ቢኖሩ ለእነርሱ መልካም ነው:: ነገር ግን በምኞት ከመቃጠል መጋባት ይሻላልና ራሳቸውን መግዛት ባይችሉ ያግቡ::" †††
(1ቆሮ. 7:7)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
2024/09/24 17:20:44
Back to Top
HTML Embed Code: