Telegram Web Link
††† እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ማትያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ሐዋርያው ቅዱስ ማትያስ †††

††† በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ ከእመቤታችን በቀር ከቅዱሳን ሐዋርያት የሚበልጥ አልተነሳም:: "ሐዋርያ" ማለት "ፍንው: ልዑክ: የተላከ: የጽድቅ መንገደኛ" እንደ ማለት ነው:: በምሥጢሩ ግን "ባለሟል" ብለው ሊቃውንቱ ተርጉመውታል::
ይህስ እንደምን ነው ቢሉ:-
¤የፍጥረታት ሁሉ ጌታ: የክብር ባለቤት መድኃኔ ዓለም ከድንግል ማርያም ተወልዶ: አድጐ: ተጠምቆ: ጾሞ: ከገዳመ ቆረንቶስ ሲመለስ ቀዳሚ ሥራው ያደረገው ደቀ መዛሙርቱን መጥራት ነበር::

ከተከተሉት የ5 ገበያ ሕዝብ መካከል "ወሐረየ እምሰብአ ዚአሁ አሠርተ ወክልኤተ ሐዋርያተ" እንዲል በመጀመሪያ 12ቱን ሐዋርያት መረጠ::

††† እሊህም:-
1.ዼጥሮስ የተባለ ስምኦን
2.እንድርያስ (ወንድሙ)
3.ያዕቆብ ወልደ ዘብዴዎስ
4.ዮሐንስ (ወንድሙ)
5.ፊልዾስ
6.በርተሎሜዎስ
7.ቶማስ
8.ማቴዎስ
9.ያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ
10.ታዴዎስ (ልብድዮስ)
11.ናትናኤል (ቀናተኛው ስምዖን) እና
12.ማትያስ (በይሁዳ የተተካ) ናቸው:: (ማቴ. 10:1)

††† እነዚህን 12 አርድእቱን ከጠራ በሁዋላ ለ3 ዓመታት ከ3 ወራት ከዋለበት ሲማሩ ይውሉ ነበር:: ሌሊት ደግሞ ምሥጢር ሲያስተረጉሙ ያድሩ ነበር::

ጌታ እንደሚገባ ካስተማራቸው በሁዋላ ከፍ ያለ ኃላፊነትን ሾማቸው:: ለዓለም እረኞች: የእርሱም ባለሟሎች ሆኑ:: እጅግ ብዙ መከራ እንደሚገጥማቸው ነገራቸው:: (ማቴ. 10:16, ዮሐ. 16:33) በዚያው ልክ ክብራቸውንም አከለላቸው:: (ማቴ. 19:28)

ሥልጣናቸው ደግሞ እስከዚህ ድረስ ሆነ:: "በምድር ያሠራችሁት በሰማይ የታሰረ ይሆናል: በምድር የፈታችሁት በሰማይ የተፈታ ይሆናል::" (ማቴ. 18:18) "ይቅር ያላችሁዋቸው ኃጢአታቸው ይቀርላቸዋል: ያላላቹሃቸው ግን አይቀርላቸውም::" (ዮሐ. 20:23)

የመንግስተ ሰማያትን መክፈቻ (ማቴ. 16:19): እረኝነትን (ዮሐ. 21:15) ተቀበሉ:: ጌታ በንጹሕ አንደበቱ ሐዋርያቱን እጅግ ሲያከብራቸው "ጨው: የዓለም ብርሃናት" (ማቴ. 5:13) አላቸው:: ወንድሞቹም ተባሉ:: (ዮሐ. 7:5) ከዚህም በሚበልጥ በሌላ ክብር አከበራቸው::

ከዚህ ሁሉ ነገር በሁዋላ በጌታ ሕማማት ጊዜ ገና ነበሩና አንዳንዶቹ ፈርተው ተበተኑ:: ተመልሰው ግን በጽርሐ ጽዮን ሲጸልዩ ሰንብተው የጌታን ትንሳኤ ተመለከቱ:: እጆቹን: እግሮቹንም ዳስሰው ሐሴትን አደረጉ::

ለ40 ቀናት መጽሐፈ ኪዳንን: ትምሕርተ ኅቡዓት: ሌላም በፍጡር አንደበት የማይነገር ብዙ ምሥጢራትን ተምረው: ጌታ ሊቀ ዽዽስናን ሹሟቸው ዐረገ::

ለ10 ቀናት በእመ ብርሃን ሥር ተጠልለው ሲጸልዩና በአንድ ልብ ሲተጉ ሰንብተው መንፈስ ቅዱስ ወረደላቸው:: በአንዴም ከፍርሃት ወደ ድፍረት ተመልሰው ፍጹማን: ብርሃናውያን ሆኑ:: 71 ልሳናትን ነስተው በአንዲት ስብከት ብቻ 3ሺ ነፍሳትን ማረኩ:: (ሐዋ. 2:41)

ቅዱሳን ሐዋርያት በኅብረት ለአንድ ዓመት ያህል በኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ እየተመላለሱ አስተምረው ብዙ እሥራኤላውያንን ወደ ክርስትና ማርከዋል:: ከዚህ በሁዋላ ግን እንደ ትውፊቱ ዓለምን በእጣ ለ12 ተካፈሏት::

ይህ ሲሆን መንፈስ ቅዱስ አብሯቸው ነበርና ለእያንዳንዳቸው እንደሚገባቸው አሕጉረ ስብከቶች ደረሷቸው:: እነርሱም ደቀ መዛሙርቶቻቸውን አስከትለው ለታላቁ መንፈሳዊ ዘመቻ ወረዱ::

በሔዱበት ቦታም ከተኩላ: ከአንበሳና ከነምር ጋር ታገሉ:: በጸጋቸውም አራዊትን (ክፉ ሰዎችን) ወደ በግነት መልሰው ለክርስቶስ አስረከቡ:: በየሃገሩ እየሰበኩ ድውያንን ፈወሱ:: ለምጻሞችን አነጹ:: እውራንን አበሩ:: አንካሶችን አረቱ:: ጐባጦችን አቀኑ:: ሙታንንም አስነሱ:: እልፍ አእላፍ አሕዛብንም ወደ መንጋው ቀላቀሉ::

ስለዚህ ፈንታም ብዙዎቹ በእሳት ተቃጠሉ:: ቆዳቸው ተገፈፈ:: በምጣድ ተጠበሱ:: ደማቸው በምድር ላይ ፈሰሰ:: ከአንድ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በቀር ሁሉም ይህችን ዓለም በሰማዕትነት ተሰናበቱ:: ጨው ሆነው አጣፍጠዋልና: ብርሃንም ሆነው አብርተዋልና እናከብራቸዋለን:: "አባቶቻችን: መምሕሮቻችን: ጌቶቻችንና ሊቆቻችን" እንላቸዋለን::

ቅዱስ ማትያስ ስም አጠራሩ ይክበርና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተሰቦቼ ብሎ ከመረጣቸው 120 ቅዱሳን አንዱ: 3 ዓመት ከ3 ወር ከጌታችን እግር ቁጭ ብሎ የተማረ: በይሁዳ ፈንታ ከ12ቱ ሐዋርያት ይቆጠር ዘንድ መንፈስ ቅዱስ የመረጠው ሐዋርያ ነው::

ቅዱሱ ሐዋርያ በዕጣ በደረሰው ሃገረ ስብከቱና በሌሎቹም ዓለማት ለወንጌል አገልግሎት ብዙ ደክሙዋል:: በተለይ የሰውን ሥጋ ወደሚበሉ ሰዎች ሃገር ገብቶ ወንጌልን ቢሰብክላቸው ዓይኖቹን አውጥተው ከብዙ ስቃይ ጋር ለ30 ቀናት ሣር አብልተውታል::

እሱ ግን በትእግስትና በፈጣሪው ኃይል ድንቅ ተአምር አድርጐ አሳምኖ አጥምቋቸዋል:: ከብዙ ተጋድሎና ቅድስና በሁዋላም በዚሕች ቀን በመልካም ሽምግልና አርፏል::

††† አምላከ ቅዱሳን ሐዋርያት ቸርነቱን ያብዛልን:: በምልጃቸው ከክፉ ጠብቆ ከበረከታቸው ይክፈለን::

††† መጋቢት 8 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)
2.ቅዱስ አርያኖስ ሰማዕት (በዘመነ ሰማዕታት ብዙ ክርስቲያኖችን ያሳድድ የነበረና ጌታ በንስሃ የጠራው)
3.ቅዱስ ዮልዮስ ሊቀ ዻዻሳት

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
2.ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳ)
3.አባ ብሶይ (ቢሾይ)
4.አቡነ ኪሮስ
5.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን

††† ". . . እንዲህም ብለው ጸለዩ:: 'አቤቱ ልብን ሁሉ የምታውቅ አንተ ከእነዚህ ከሁለቱ የመረጥከውን አንዱን ግለጥ?' . . . ዕጣ አጣጣሉአቸው ዕጣውም በማትያስ ላይ ወጣ:: ከዐሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋርም ተቆጠረ::" †††
(ሐዋ. 1:24-26)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ኩትን ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ሐዋርያው ቅዱስ ኩትን †††

††† ቅዱስ ኩትን በዘመነ ሐዋርያት የነበረ: ከአሕዛብ ወደ ክርስትና በቅዱስ ዻውሎስ አማካኝነት የተመለሰ: ከቅዱሳን ሐዋርያት እግር ሥር ቁጭ ብሎ ይማር ዘንድ የታደለ: በፍፁም ድንግልናው የተመሰገነ ሐዋርያዊ አባት ነው::

ይህ ቅዱስ ሚስት ነበረችው:: ግን በትዳር ውስጥ ሆኖ ድንግልናን መጠበቅ እንደሚቻል ያሳየ የሐዲስ ኪዳን ሰው ነው:: ቅዱስ ኩትን በንጽሕናው: በአገልግሎቱና በጣዕመ ስብከቱ በሐዋርያትና ምዕመናንም ተወዳጅ ነበር:: ለብዙ ዘመናት በወንጌል አገልግሎት ኑሮ በዚሕች ቀን በመልካም ሽምግልና አርፏል::

††† ፈጣሪ ከበረከቱ ያድለን::

††† መጋቢት 9 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ኩትን ሐዋርያ
2.ቅዱስ እንድርያኖስ ሰማዕት
3.ቅዱስ አውሳብዮስ ሰማዕት
4."2,000" ሰማዕታት (የአባ ኖብ ማሕበር)

††† ወርሐዊ በዓላት
1.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ኁሉ አባት)
2.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ (ኢትዮዽያዊ)
3."318ቱ" ቅዱሳን ሊቃውንት (ርቱዐነ ሃይማኖት ዘኒቅያ)
4.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
5.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ (ኢትዮዽያዊ)
6.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ (ዓለመ ብፁዐንን ያየ አባት)

††† ". . . ስለ ድንግልናው ያፈረ ሰው ቢኖር የወደደውን ያድርግ:: ቢያገባም ኃጢአት የለበትም:: ሳይናወጥ በልቡ የጸና ግን ግድ የለበትም:: የወደደውን እንዲያደርግ ተፈቅዶለታል:: ድንግልናውንም በልቡ ይጠብቅ ዘንድ ቢጸና መልካም አደረገ:: እንዲሁም ድንግልን ያገባ መልካም አደረገ:: ያላገባም የተሻለ አደረገ::" †††
(1ቆሮ. 7:36-38)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
እንኩዋን ለዲማው ኮከብ "አቡነ ተከሥተ ብርሃን" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

+*" አቡነ ተከሥተ ብርሃን ዘድማኅ "*+

=>ደብረ ድማኅ (የአሁኑ ዲማ ጊዮርጊስ) እጅግ የበረከት ቦታ ነው:: ከጻድቃን እነ አቡነ ተክለ አልፋን : ከሊቃውንት የኔታ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬን የመሰሉ አበው ፍሬ አፍርተውበታል:: ጻድቁ ተከሥተ ብርሃንም ተጋድሏቸውን የፈጸሙት በዚሁ ቦታ ነው::

+ደብሩ (ዲማ ጊዮርጊስ) ያሳተመው መጽሔት እንደሚለው የጻድቁ ስማቸው አባ በኪሞስ ነው:: "ተከሥተ ብርሃን" የተባሉት በቅድስናቸውና ብርሃን ይወርድላቸው ስለነበር ነው::

+የተወለዱት በምድረ ሽዋ በ13ኛው መቶ ክ/ዘመን ሲሆን የታላቁ ኮከብ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ደቀ መዝሙር ሆነው በደብረ ሊባኖስ አገልግለዋል:: ያመነኮሷቸውም ራሳቸው ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ናቸው::

+ቅዱስ ተክለ ሥላሴ በ1296 ዓ/ም ሲያርፉ እርሳቸውን ቀብረው በዓመቱ (ማለትም በ1297 ዓ/ም) በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ወደ ዲማ በርሃ መጥተዋል:: በዲማ (ጐጃም)ም ተጋድሏቸውን ከማስፋታቸው ባለፈ በስብከተ ወንጌል ተግተዋል::

+ጸበል አፍልቀውም ብዙ ድውያንን ፈውሰዋል:: በተለይ ደግሞ በቦታው እናቶችን ታስቸግር የነበረችውን ቡላድን (ዛር ናት) ከአካባቢው አሰድደዋታል:: ዛሬም ድረስ የጻድቁ ጸበል ለእናቶቻችን (ለሁሉም ሰው) ትልቅ ፈውስ እየሰጠ መሆኑን እንሰማለን::

+ጻድቁ አቡነ ተከሥተ ብርሃን ግን ተጋድሏቸውን ፈጽመው በዚያው በዲማ : መጋቢት 10 ቀን ዐርፈዋል:: ዛሬም በዲማ ጊዮርጊስ በዓላቸው ይከበራል::

=>የጻድቁን ክብርና በረከት አይለይብን:: በጸሎታቸው እኛንም : ቤተ ክርስቲያናችንንም ከክፉ ጠላት ይጠብቅልን::

=>+"+ እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና::
ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና::
ለዘለዓለምም ይጠብቃቸዋል. . .
ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ::
በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ::
የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል::
አንደበቱም ፍርድን ይናገራል::
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው::
በእርምጃውም አይሰናከልም:: +"+ (መዝ. 36:28-31)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
††† እንኳን ለጻድቁ አቡነ አሌፍ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† አባ አሌፍ †††

††† ጻድቁ ገድላቸውን የፈጸሙት በኢትዮዽያ ቢሆንም ሃገረ ሙላዳቸው የጥንቱ የሮም ግዛት የሆነችው ታናሽ እስያ ናት:: አባ አሌፍ ከዘጠኙ (ተስዓቱ) ቅዱሳን አንዱ ናቸው:: ዘጠኙ ቅዱሳን ተወልደው ያደጉት ምንም በአንድ የሮም ግዛት ሥር ቢሆንም መነሻ ቦታቸው ግን የተለያየ ነው::

ሁሉንም አንድ ያደረጋቸው መንፈስ ቅዱስ በኪነ ጥበቡ ነው:: በምክንያት ደረጃ እንግለጸው ከተባለ ደግሞ የአንድነታቸው ምሥጢር:-
1.የቀናች ሃይማኖታቸው ተዋሕዶ::
2.ዓላማ (የእግዚአብሔር መንግስት) እና
3.ገዳማዊ ሕይወት ነው::

አባ አሌፍን ጨምሮ ሁሉም ቅዱሳን ዘራቸው ከቤተ መንግስት ነው:: እነርሱ ግን ምድራዊውን ክብር ንቀው ሰማያዊውን ክብር ገንዘብ ማድረግን መርጠዋል:: አስቀድመው ቅዱሳት መጻሕፍትን ያጠኑት አበው በተለያየ ጊዜ እየመነኑ ከሮም ግዛት ወደ ግብጽ በርሃዎች ወርደዋል::

በምናኔ ቅድሚያውን አባ ዸንጠሌዎንና አቡነ አረጋዊ ይይዛሉ:: ዘመኑ የተዋሕዶ አማኞች የሚሰደዱበት 5ኛው መቶ ክ/ዘመን ነበርና እምነትን ላለመለወጥ ዘጠኙ ቅዱሳን ስደትን መረጡ::

በወቅቱ ደግሞ ለስደት መጠለያ የምትሆንና ከኢትዮዽያ የተሻለች ሃገር አልነበረችም:: ስለዚህም በ470ዎቹ ዓ/ም አልዓሜዳ በኢትዮዽያ ነግሦ ሳለ ቅዱሳኑ በአረጋዊ መሪነት መጡ::

ንጉሡም ሲጀመር የእግዚአብሔር እንግዳ ስለሆኑ: ሲቀጥል ደግሞ ቅድስናቸውን ተመልክቶ መልካም አቀባበልን አደረገላቸው:: ማረፊያ ትሆናቸውም ዘንድ አክሱም ውስጥ አንዲት ቦታን ወስኖ ሰጣቸው:: ይህች ቦታ ቤተ ቀጢን ትባላለች::
አባ አሌፍና 8ቱ ቅዱሳን ወደ ሃገራችን እንደ ገቡ የመጀመሪያ ሥራቸው ቋንቋን መማር ነበር::

ልሳነ ግዕዝን በወጉ ተምረው እዛው አክሱም አካባቢ ሥራቸውን አንድ አሉ:: በወቅቱ በአቡነ ሰላማ: በአብርሃ ወአጽብሐና በአቡነ ሙሴ ቀዳማዊ የተቀጣጠለው ክርስትና በተወሰነ መንገድ ተቀዛቅዞ ነበርና እነ አባ አሌፍ እንደ ገና አቀጣጠሉት::

ሕዝቡን በራሱ ልሳን ለክርስትና ይነቃቃ ዘንድ ሰበኩት:: የካደውን እየመለሱ: የቀዘቀዘውን እያሟሟቁ ለዓመታት ወንጌልን ሰበኩ:: ቀጣዩ ሥራቸው ደግሞ መጻሕፍትን መተርጐም ሆነ::

ከሃገራቸው ያመጧቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት ተከፋፍለው ወደ ግዕዝ ልሳን ተረጐሟቸው:: በዚህም ለሃገራችን ትልቁን ውለታ ዋሉ:: ይህ ሁሉ ሲሆን እነ አባ አሌፍ የሚመገቡትም ሆነ የሚጸልዩት በማሕበር ነበር:: በመካከላቸውም ፍጹም ፍቅር ነበር:: ጸጋ እግዚአብሔር አልተለያቸውም::

††† የነ አባ አሌፍ ቀጣዩ ተግባራቸው ደግሞ ገዳማዊ ሕይወትን ማስፋፋት ሆነ:: ይህንን ለማድረግ ግን የግድ መለያየት አስፈለጋቸው:: እያንዳንዱም መንፈስ ቅዱስ ወደ መራው ቦታ ሔደ::
*ዸንጠሌዎን በጾማዕት::
*ገሪማ በመደራ::
*ሊቃኖስ በቆናጽል::
*አረጋዊ በዳሞ::
*ጽሕማ በጸድያ::
*ሌሎችም በሌላ ቦታ ገዳማትን መሠረቱ::
*አባ ይምዓታ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ምርጫቸው ገርዓልታ (እዛው ትግራይ) ሆነ::

አባ አሌፍ የተወለዱት አውሎግሶንና አትናስያ ከተባሉ ደጋግ ወላጆች ቂሳርያ ውስጥ በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ጻድቁ በሕጻንነታቸው ወደ አባ እንጦንስ ገዳም ገብተው ከዓመታት ተጋድሎ በሁዋላ ከ8ቱ ጉዋደኞቻቸው ጋር ወደ ኢትዮዽያ የመጡ ሲሆን ከተስዓቱ /9ኙ/ ቅዱሳን አንዱ ናቸው::

በዐፄ አልዓሜዳ ዘመን አክሱም አካባቢ (ቤተ ቀጢን) የሃገራችንን ቋንቋ አጥንተው ቅዱሳት መጻሕፍትን ተርጉመዋል:: ለሕዝቡም የወንጌልን የምሥራች ሠብከዋል::

ከዚያም ገዳም መሥርተው: 500 መነካሳትን ሰብስበው ለ70 ዓመታት በቅድስና ኑረዋል:: ለዘጠኙ ቅዱሳን ሁሉ ስም ያወጡት የዘመኑ ሰዎች ቀድመው ወደ አክሱም ስለ ገቡ ጻድቁን "አሌፍ" ብለዋቸዋል:: በዕብራይስጥኛ "አንደኛ" ማለት ነው:: ጻድቁ ከፈጣሪያቸው የምሕረት ቃል ኪዳን ተቀብለው በዚሕች ቀን አርፈዋል::

††† አምላከ አበው ቅዱሳን በምልጃቸው ይማረን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::

††† መጋቢት 11 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አባ አሌፍ ጻድቅ (ከተስዓቱ ቅዱሳን)
2.ቅዱስ ቴዎቄጤኖስ ሰማዕት
3.ቅዱስ ባስሊዖስ (ዻዻስና ሰማዕት)
4.አባ ኤፍሬም ሰማዕት
5.አባ ኤልያስ ሰማዕት

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ያሬድ ካህን
2.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት
3.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
4.ብፁዐን ኢያቄም እና ሐና
5.አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ

††† "ከእናንተ አንዱ ከባልንጀራው ጋር ሙግት ቢኖረው በቅዱሳን ፊት በመፋረድ ፋንታ በዓመፀኞች ፊት ሊፋረድ ይደፍራልን? ቅዱሳን በዓለም ላይ እንዲፈርዱ አታውቁምን? . . . የትዳር ጉዳይ ይቅርና በመላእክት እንኩዋ እንድንፈርድ አታውቁምን?" †††
(1ቆሮ. 6:1-3)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

          #መጋቢት ፲፪ (12 ) ቀን።

እንኳን #ለኢትዮጵያዊው_ጻድቅ "በዓለም ነግሦ መኖር አልፈልግም" ብለው ለመነኑ፤ #ለንጉሡ_ዐፄ_ዳዊት_ልጅና_ለዐፄ_ዘርዓያዕቆብ_ወንድሜ_ለሆኑት፤ በመስቀላቸው በመባረክ በሐምሌ ወር የዠማን ወንዝ አቁመው ለተሻገሩ ለታላቅ አባት #አቡነ_ተስፋ_ጽዮን_ዘሸዋ ለዕረፍቸው በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።

                             
#አቡነ_ተስፋ_ጽዮን፦ የተባሉት ጻድቅ አገራቸው ሸዋ ሲሆን የንጉሡ የዐፄ ዳዊት ልጅና የዐፄ ዘርያቆብ ወንድሜ ናቸው። ስንክሳሩ መናኔ መንግሥት ወብእስት በማለት ይጠራቸዋል። "በዓለም ነግሦ መኖር አልፈልግም" በማለት የዓለምን ጣዕም ንቀው በመተው ገዳም ገብተዋል። በታላቅ ተጋድሎ እየኖሩ አጠቃላይ የመርሐ ቤቴ ገዳማትን ሲመሩና ሲያስተዳድሩ ነበር።

ጻድቁ በመስቀላቸው በመባረክ በሐምሌ ወር የዠማን ወንዝ አቁመው የተሻገሩ ታላቅ አባት ናቸው። ብዙ ሙታንን በማስነሣትና ታላላቅ ተአምራትን በማድረግ ነው ወንጌልን ሲሰብኩ የነበረው። በተለያየ አገር የሚኖሩ ቢሆኑም ከወለቃው አቡነ ዘአማሩኤል ጋር በመንፈስ ቅዱስ መሪነት እየተገናኙ ስለ ገዳማት ይወያዩ ነበር። ጻድቁ በትግራይ ትልቅ ገዳም ያላቸው ሲሆን በደብረ በግዕና በዜና ማርቆስ ገዳም ደግሞ ቅዱስ ገድላቸው ይገኛል። ጻድቁ ከብዙ ተጋድሎ በኋላ ጌታችን ተገልጦላቸው ታላቅ ቃልኪዳን ከሰጣቸው በኋላ መጋቢት12 ቀን በታላቅ ክብር ዐርፈዋል። ከአባታች አቡነ ተስፋ ጽዮን ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። በጸሎታቸው ይማረን!። ምንጭ፦መዝገበ ቅዱሳን።

በየቀኑ ይህን ቴሌግራም ላይ ማግት ከፈለጉ ከታች ያለውን ሊንክ ተጭነው ይቀላቀሉ።

@sigewe

https://www.tg-me.com/joinchat-AAAAAFGQ22bI0Ij80hYpFA

https://www.facebook.com/profile.php?id=100063896616886

https://www.facebook.com/profile.php?id=61552828743736&mibextid=ZbWKw
2024/09/24 19:26:01
Back to Top
HTML Embed Code: