Telegram Web Link
ታኅሣሥ 9

እንኩዋን ለጻድቅና ሰማዕት "ቅዱስ በአሚን" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

+*" ቅዱስ አባ በአሚን "*+

=>የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የተጻፈው በብራናና በብዕር አይደለም:: ይልቁኑ:-
¤እንደ ቀለም የሰማዕታት ደማቸው::
¤እንደ ብዕር አጥንታቸው::
¤እንደ ብራና ቆዳቸው ሆኖ ተጽፏል እንጂ:: ሰማዕታት ለሃይማኖታቸው የከፈሉት ዋጋ እጅግ ታላቅ ነው::

+ስለዚህም "ተጋዳዮች : የሚያበሩ ኮከቦች : የቤተ ክርስቲያን ሻማዎች" ተብለዋል:: እነሱ እየቀለጡ አብርተዋልና::

+ሰማዕትነት በብሉይ ኪዳን የጀመረና እስከ ዳግም ምጽዐተ ክርስቶስም የሚቀጥል ቢሆንም "ዘመነ ሰማዕታት" የሚባለው ከ150 እስከ 312 ዓ/ም ድረስ ያለው ዘመን ነው::

+በተለይ ግን ከ270ዎቹ እስከ 312 ዓ/ም ድረስ ያሉ ዓመታት እጅግ የከፉ ነበሩና የክርስቲያኖች ደም በምድር ላይ ፈሷል:: የሰማዕታት ምሥጢራቸው ቃለ ወንጌል: የጌታ ስብከትና ሕይወት እንጂ ሌላ አይደለም:: (ማቴ. 10:16, ማር. 13:9, ሉቃ. 12:4, ዮሐ. 16:1, ሮሜ. 8:35, ራዕይ. 2:9)

+የቅዱሳን ሰማዕታት መነሻቸው ቅዱስ እስጢፋኖስ ሲሆን ፍጻሜአቸው ደግሞ ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ዻዻሳት ነው::

=>ከዓበይት ሰማዕታትም አንዱ ቅዱስ በአሚን ነው:: በቤተ ክርስቲያን "ሰማዕት ዘእንበለ ደም (ሰይፍ)" የሚባሉ ቅዱሳን አሉ:: ሰማዕት ዘእንበለ ደም ማለት "እንደ ሰማዕታት መከራውን ሁሉ ተቀብለው ሳይሰየፉ (ሳይገደሉ) የመከራውን ዘመን ያለፉ" ናቸው::

+ለምሳሌ ከሠለስቱ ምዕት (ከ318ቱ ሊቃውንት) አብዛኞቹ እንደዚህ ባለ ሕይወት ያለፉ ናቸው:: ቅዱስ በአሚንም እንዲሁ ዓይነት ዜና ሕይወት ያለው አባት ነው::

¤ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

+ቅዱስ በአሚን ተወልዶ ያደገው በደቡብ ግብጽ በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ቅዱሱ ከልጅነቱ ክርስትናን የተማረ ነበርና ሰው ሁሉ የሚወደው ታማኝ ሰው ሆነ:: ምንም ሃብታም ሰው ባይሆንም ተቀጥሮ ሠርቶ በሚያገኛት ገቢው መልካምን ይሠራ ነበር::

+በዘመኑም ከቅንነቱ የተነሳ "መታመንስ እንደ በአሚን" ይባል ነበር:: ቅንነቱን የወደዱ ሁሉ ይሹት ነበር:: በከተማው ውስጥ እጅግ ብዙ ሃብት የነበራቸው ባል እና ሚስትም ወደ ቤታቸው ወስደው መጋቢ (ተቆጣጣሪ) አደረጉት::

+ጠባዩን ከተረዱ በሁዋላ ግን ሙሉ ሃብት ንብረታቸውን በእጁ አስረክበውት ያስተዳድርላቸው ነበር:: ሲወጡና ሲገቡም እያዩት ደስ ይሰኙበት ነበር:: እርሱ ግን ልቡ በክርስቶስ ፍቅር የተመሰጠ ነበርና ለዚህ ዓለም ጉዋዝ ትኩረትን አይሰጥም ነበር:: ይጾም ይጸልይ ነበር እንጂ::

+አንድ ቀን ግን የቤቱ ባለቤቶች (ባልና ሚስት) ሲመጡ ቤታቸው እንደሚገባ ተደራጅቶ: ቁልፉ ተቀምጦ አገኙት:: ወዳጃቸው በአሚን ግን የለም:: ደንግጠው ቢያፈላልጉት ሊያገኙት አልቻሉም:: በመጨረሻ ግን መንኖ ገዳም መግባቱን ሰምተው ፈጽመው አዘኑ::

+ከእርሱ መለየትን አይፈልጉም ነበርና:: አልቅሰው ወደ ቤታቸው ሊመለሱ ሲሉ ሚስት "አይሆንም! ሔደን እናምጣው" ስላለች ወደ መነነበት ገዳም ሔደው: እያለቀሱ ይመለስላቸው ዘንድ ለመኑት::

+እርሱ ግን "ለሰማያዊ ሠርግ ታጭቻለሁና ከእንግዲህ የክርስቶስ ነኝ" አላቸው:: እንዳልተሳካላቸው ሲያውቁ ፈጽመው እያዘኑ ወደ ቤታቸው ተመለሱ:: ቅዱስ በአሚን ግን ገዳማዊ ሕይወትን በተጋድሎ ጀመረ::

+ይጾማል: ይጸልያል: ይሰግዳል: ይታዘዛል:: በዚህ መንገድ ሥርዓተ ገዳምን በበርሃ ሆኖ ሲፈጽም በዓለም እነ ዲዮቅልጢያኖስ ክርስቲያኖችን ይገድሉ ነበር::

ዜና ሰማዕታትም ቀስ እያለ ቅዱሱ ወዳለበት ገዳም ደረሰ::

+ነገሩን ሲሰማ ደስ አለው:: እርሱ ስለ ክርስቶስ ሲሉ ደምን ማፍሰስና መከራን መቀበል ከሁሉም ነገር የተሻለ እንደ ሆነ ያውቅ ነበርና:: ቀጥሎም ወደ ከተማ ሒዶ ደሙን ለማፍሰስ በቁርጥ ወስኖ ዘለቀ::

+በዚያም የንጉሥ ወታደሮች አግኝተውት ለጣዖት ይሰዋ ዘንድ ታዘዘ:: ቅዱስ በአሚን ግን "መስዋዕት የሚገባው ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ: ለባሕርይ አባቱ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ነው:: ለፍጡር አልሰዋም" ሲል መለሰላቸው:: በዚህም ምክንያት ወታደሮች እየተፈራረቁ ደበደቡት::

+ደሙንም አፈሰሱት:: ምንም እንዳልተለወጠ ሲያውቁ ወደ እስር ቤት ጨመሩት:: ከዚያም በቀን በቀን እያወጡ ይደበድቡት: በእሳት ያቃጥሉት: በተለያዩ ማሰቃያዎች በመከራ ያውሉት ነበር:: እርሱ ግን ክርስቶስን ከመቀደስ በቀር አንዳች አይመልስላቸውም ነበር::

+በብዙ አሰቃይተው እንቢ ቢላቸው ወስደው በጨለማ ቤት ዘጉበት:: በዚያም ጥለውት ዓመታት አለፉ:: ሁሉንም በጊዜው የሚሠራ ጌታ ግን እነዚያን የመከራ ዘመናት አሳልፎ ዲዮቅልጢያኖስና መክስምያኖስን አጠፋቸው::

+በፈንታቸውም መፍቀሬ ክርስቶሳውያን ቅዱስ ቆስጠንጢኖስን አነገሠ:: አብያተ ክርስቲያናት ታነጸ:: ስለ ክርስቶስ የታሠሩ ሁሉ ነጻ ወጡ:: በዚህ ጊዜ ምዕመናን መጥተው ቅዱስ በአሚንን ከወደቀበት አነሱት::

+በወቅቱም ንጉሡ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ "አጽመ ሰማዕታትን ሰብስቡ: በመከራው አልፈው በእድሜ ካሉትም መካከል መምጣት የሚችሉትን አምጡልኝ" ብሏልና ቅዱስ በአሚንን የመሰሉ 72 ክቡራን ተገኙ:: ከእነርሱም መካከል ታላቁ አባ ኖብና አባ ዘካርያስ ይገኙበታል::

+እነዚህ አበው ቅዱሱን ንጉሥ ባርከውት ሲመለሱ ቅዱስ በአሚን ወደ እስሙናይን ተጉዞ በበዓቱ ተቀመጠ:: በዚያም ደቀ መዛሙርት በዝተውለት እንደ ገና ገዳማዊ ሕይወቱን ቀጠለ:: በበዚያም ሳለ ብዙ ተአምራትን ሠራ::

+ድውያንን ፈወሰ:: መናፍቃንንም በጸሎቱ ከአካባቢው አራቀ:: አንድ ቀንም የሮም ንጉሠ ነገሥት ሚስት ወደ እርሱ ዘንድ መምጣቷን ሰማ:: ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ገብተው "አባ! ንግሥቲቱ ትፈልግሃለች" አሉት::

+እርሱ ግን "እኔ ከምድራዊ ንግሥት ዘንድ ምን አለኝ! አልወጣም" አላቸው:: ደቀ መዛሙርቱ ግን መልሰው "አባ! እዘንላት: በመከራ ውስጥ ናት" ሲሉት "እሺ" ብሎ ወጣ::

+ንግሥቲቱ ምንም ብዙ ሠራዊት ብታስከትል አንጀቷ ታጥፎ ተጐንብሳ ነበር የምትሔደው:: እርሱም በጀሮዋ ጠጋ ብሎ የሕመሟን ምሥጢር ሲነግራት ተገርማ እግሩ ሥር ወድቃ ተማጸነችው:: ነገሩ እንዲህ ነው:-

+ከ15 ዓመታት በፊት አንድ የተባረከ ዲያቆን በቤተ መንግስቷ አካባቢ ይኖር ነበር:: እርሱም (ዮሐንስ ይባላል) የዮሐንስን ራዕይ ቁሞ ዘወትር ያነብላታል:: በዚህ የቀኑ የንጉሡ ባለሟሎች በሃሰት "ሚስትህን ዲያቆኑ እያማገጠ ነው" ሲሉ ለንጉሡ ነገሩት::

+ንጉሡም ነገሩ እውነት ስለ መሰለው ወታደሮቹን ዮሐንስን ከነ ሕይወቱ ባሕር እንዲያሰጥሙት አዘዘ:: ይሕንን የሰማችው ንግስት ለቀናት ስታለቅስ አንጀቷ በመቃጠሉ ታመመች:: እየቆየም ሆዷ ታጠፈ:: ለ15 ዓመትም የሚያድናት አጥታ ተንከራተተች::

+በሁዋላ ግን ሰዎች ስለ ቅዱስ በአሚን ቅድስና ሲናገሩ ሰምታ መጣች:: ለዛ ነው ቅዱስ በአሚን ምሥጢሯን ሹክ ያላት:: ቀጥሎም 2 በጐ ነገርን ፈጸላት:: መጀመሪያ ጸሎት አድርጐ ሆዷን ቢዳስሳት በቅጽበት ድና ቀና አለች::

+2ኛው ግን "ያ የምትወጂው የተባረከ ዲያቆን ዮሐንስ አልሞተም:: መላዕእክት ከባሕር አውጥተው እገሌ በሚባል ደሴት አኑረውታል" አላት::
እርሷም ተመልሳ በደስታ ለባሏ ነገረችው::
+ንጉሡም ተጸጽቶ ዮሐንስን ካለበት አስመጣው:: አበውም የሮሜ ሊቀ ዻዻሳት አድርገውት ብዙ መጻሕፍትን ተርጉሟል:: ቅዱስ በአሚን ግን በቅድስና ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፎ በዝማሬ ተቀብሯል::=>አምላከ ቅዱስ በአሚን በጸሎቱ ይማረን:: ከትእግስቱ ይክፈለን:: ከበረከቱም ያሳትፈን::

=>ታሕሳስ 9 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አባ በአሚን (ጻድቅና ሰማዕት)
2.ቅድስት አርምያ
3.ቅዱስ ዘካርያስ

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱሳን 318ቱ ሊቃውንት
2.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ኁሉ አባት)
3.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ
4.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
5.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ
6.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ

=>+"+ አባቶች ሆይ! ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃቹሃልና እጽፍላቹሃለሁ:: ጐበዞች ሆይ! ክፉውን አሸንፋቹሃልና እጽፍላቹሃለሁ:: ልጆች ሆይ! አብን አውቃቹሃልና እጽፍላቹሃለሁ:: አባቶች ሆይ! ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃቹሃልና እጽፍላቹሃለሁ:: ጐበዞች ሆይ! ብርቱ ስለ ሆናችሁ: የእግዚአብሔርም ቃል በእናንተ ስለሚኖር: ክፉውንም ስላሸነፋችሁ እጽፍላቹሃለሁ:: +"+ (1ዮሐ. 2:13)

   <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
" ታኅሣሥ 10 "

<<< እንኩዋን ለቅዱሳን ሊቃውንት "አባ ኒቆላዎስ" : "አባ ሳዊሮስ" እና "ቅድስት ሱርስት" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ >>>

+*" ቅዱስ ኒቆላዎስ ሊቅ "*+

=>ቅዱስ ኒቆላዎስ:-
*ሃይማኖቱ የቀና::
*ምግባሩ የጸና ሊቅ::
*ብዙ መከራን የተቀበለ ሰማዕት::
*ብዙዎችን ያሳመነ ሐዋርያ::
*በበርሐ ለዘመናት የተጋደለ ጻድቅ::
*በዽዽስና ያገለገለ እረኛ እና:
*ከ318ቱ ሊቃውንት አንዱ ነው::

+የተወለደው በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ሲሆን ሃገሩ ሜራ ትባላለች:: ይህች ሃገር ዛሬ የት እንዳለች ማወቅ ባንችልም ታሪክ ግን የቀድሞዋ ሮም ግዛት እንደ ነበረች ይነግረናል:: የቅዱስ ኒቆላዎስ ወላጆች የዘመኑ ጥሩ ክርስቲያኖች ነበሩ::

+በሕጉ: በሥርዓቱ: በሥጋ ወደሙና በምጽዋት ቢኖሩም ልጅ አልነበራቸውም:: እግዚአብሔርን ሲለምኑ የጉብዝናቸው ዘመን አልፎ አረጁ:: ልጅ መጠየቁንም ተውት:: ልክ እነሱ መጠየቁን ሲያቆሙ ግን እግዚአብሔር ይሕንን ቅዱስ ፍሬ በዮና ማሕጸን ላይ ፈጠረ::

+እነርሱም ተገርመው ፈጣሪን እያመሰገኑ ተወለደ:: እንደ ተወለደ ግን ዓይናቸው ድንቅ ነገርን ተመለከቱ:: አትበው ሊያነሱት ሲጐነበሱ በራሱ ጊዜ ብደግ ብሎ ፈጣሪውን ሲያመሰግን ሰሙት::

+ለ2 ሰዓት ያሕልም ምንነቱን ያላወቁትን ጸሎት ሲያደርስ ቆየ:: መቼም የዕለት ሕጻን ይሕንን ማድረጉ እጅግ ድንቅ ነው:: ከዚህ በሁዋላም የሕጻኑ ቅዱስ ኒቆላዎስ አስገራሚ ነገሮቹ ቀጠሉ::

+ለምሳሌ:- በአጽዋማት: በረቡዕና በዓርብ ዕለታት 9 ሰዓት ካልሆነ የእናቱን ጡት አይጠባም:: ሁሌም ደግሞ የፈለገውን ያህል ቢፈስ የእናቱን የግራ ጡት አይጠባም ነበር:: ሁሌም የሚጠባው በስተቀኝ ያለውን ጡቷን ብቻ ነበር እንጂ::

+እንዲህ እንዲህ እያለ ቅዱስ ኒቆላዎስ አደገ:: እርሱ ወጣት በሆነ ጊዜ አረጋውያን ወላጆቹ ብዙ ሃብት: 400 የወርቅ ዲናርና የመሳሰለውን ትተውለት ዐረፉ:: እርሱ ግን ሁሉንም ትቶት በ16 ዓመቱ በርሃ ገባ::

+በዚያ ሲጾም: ሲጸልይ: ሲሰግድ ያዩ አበው ሁሉ ይገረሙ ነበር:: ሲሠራም: ሲታዘዝም: ሲሰግድም እንደ መንኮራኩር ፈጣን ነበርና:: በሕጻን ገላው ይሕንን ማድረጉ በእርግጥ ይደነቃል:: የቀናውን የሃይማኖት ትምሕርትንም ቶሎ በማጠናቀቁ ገና በ19 ዓመቱ ቀሲስ አድርገው ሾሙት::

+ቅስናን ከተሾመ በሁዋላ ተጋድሎውንም: አገልግሎቱንም አስፋፋ:: ካለበት ገዳም እየተነሳ ብዙ አካባቢዎችን በስብከት ያደርስ ነበር:: በወንጌል አገልግሎቱ ጊዜም ብዙ ተአምራትን ሲሠራ በተለይ በአንድ ቀን የአንድን አካባቢ ሕዝብ ጥቂት ሕብስትን እንደ ፈጣሪው አበርክቶ አብልቷል::

+የተረፈውም ብዙ መሶብ ተነስቷል:: (ዮሐ. 6:5) ጌታችን "በእኔ የሚያምን እኔ የምሠራውን እርሱ ደግሞ ይሠራል" ብሏልና:: (ዮሐ. 14:12) በተረፈም ፈዋሴ ዱያን: መንስኤ ሙታን ሆኖ ዘመናትን አሳልፏል::

+አንድ ቀን ግን በበአቱ እያለ የአንድ ሰውና የ4 ሴት ልጆቹ ነፍስ ሊጠፋ መሆኑ ይታወቀዋል:: ይሔውም በአቅራቢያው ባለ ከተማ የሚኖር አንድ ባለ ጠጋ ሃብቱ አልቆበት ተቸግሯልና ሰይጣን ክፉን እንዲሠራ ሹክ አለው:: ሰውየውም ለ4 ሴት ልጆቹ 4 ቤት አሰናድቶ በዝሙት ሊሸጣቸው ተዘጋጀ::

+ይሕንን በጸጋ ያወቀው ቅዱስ ኒቆላዎስ "ከመገስጽ መርዳት ይቀድማል" ብሎ: ማንም ሳያየው ወላጆቹ ከተውለት 400 የወርቅ ዲናር 100ውን ከፍሎ በሌሊት ከሰውየው በር ላይ ጥሎለት ተሰወረ:: ሰውየውም ተገርሞ የኃጢአት ሃሳቡን ተወ::

+ያ ሥራ ፈት ሰው ግን እንደ ገና ገንዘቡን በልቶ ተመሳሳይ ድርጊት ሊፈጽም ማሰቡን ቅዱሱ አወቀ:: አሁንም ተደብቆ 100 የወርቅ ዲናር ጣለለት:: ይህ ነገር 3ኛና 4ኛም ተደገመ:: በ4ኛው ግን ሰውየው ወደ ልቡናው ተመልሶ ይሕንን ያሕል ቸርነት የሚያደርግለትን ሰው ተደብቆ አየው::

+ሩጦም ሒዶ ከቅዱስ ኒቆላዎስ እግር ላይ ወደቀ:: "አባቴ! ነፍሴን ከእሳት አወጣሃት" አለው:: ቅዱሱም መልሶ መክሮ: ምሥጢሩን ግን ለማንም እንዳይናገር አሳስቦት ተመለሰ:: ያ ሰው ከዚያ በሁዋላ በጐ ክርስቲያን መሆን ችሏል::

+ለቅዱስ ኒቆላዎስ ግን አንድ ቀን ጌታችን: እመቤታችን: ቅዱስ መልአክ መጥተው ስጦታን አበረከቱለት:: መልአኩ ዙፋን: እመ ብርሃን የክብር ልብስን ሲሰጡት ጌታ ደግሞ ወንጌሉን ሰጠው::

+ወዲያውም አበው ካለበት በርሃ መጥተው የሜራ ዻዻስ እንዲሆን ሾሙት:: የተሾመበት ጊዜ ዘመነ ሰማዕታት ነበርና የሜራን ሕዝብ አጽንቶ ለሰማዕትነት በማብቃት ትልቁ ሃላፊነትም ተወጥቷል::

+ነገር ግን ዜና ሕይወቱ በነገሥታቱ ዘንድ ሲሰማ ለፍርድ አቀረቡት:: ስለ ክርስቶስ ሰብከሃል በሚል ስቃይና ሞት ተፈረደበት:: ወደ አውደ ስምዕ (የሰማዕታት አደባባይ) ወስደው ገረፉት: በእሳት አቃጠሉት: ደሙንም አፈሰሱት::

+ነገር ግን እግዚአብሔር ለሌላ ሙያ ይፈልገዋልና አልሞተም:: እነርሱ ግን በጭካኔ ለዘመናት አሰቃዩት:: በመጨረሻም እስር ቤት ውስጥ ጣሉት:: እርሱ በእስር ቤት ሳለም ዘመነ ሰማዕታት ተፈጸመ:: ቆስጠንጢኖስ ነገሠ::

+በዚህ ጊዜም ምዕመናን ቅዱስ አባታቸውን ከእስር ፈትተው በመንበሩ ላይ አኖሩት:: ለ13 ዓመታት ሕዝቡን ሲመራ ቆይቶ አርዮስ በካደ ጊዜ ወደ ኒቅያ አመራ:: በዚያም ለቅዱሳን ሊቃውንት 318ኛ ሆኖ ተቆጠረ:: በጉባኤው ፊትም ተአምራትን አሳየ::

+በኒቅያ ከባልንጀሮቹ ጋር አርዮስን አውግዞ: ሥርዓትን ሠርቶ: መጻሕፍትን ጽፎም ወደ ሃገሩ ተመልሷል:: በመንበሩ ላይ 40 ዓመታት ሲሞሉትም ዐርፎ በዚህች ቀን ተቀብሯል::
<<ኒቆላዎስ ማለት "መዋኤ ሕዝብ - ሕዝብን የሚያሸንፍ" ማለት ነው>>

+"+ ቅድስት ሱርስት +"+

=>ይህቺ ቅድስት እናት በዘመነ ጻድቃን ከተነሱ ስመ ጥር እናቶች አንዷ ናት:: ገና ከልጅነቷ በቤተ መንግስት ውስጥ ብታድግም ከመልካም እናቷ መልካምነትን ወርሳለች:: እጅግ በተቀማጠለ ኑሮ ውስጥ ሆና ሕይወቷን ክርስቶስን አልዘነጋችውም::

+ደም ግባቷ እጅግ የተወደደ ነበርና ገና በ12 ዓመቷ ለነገሥታቱ ልጆች ሚስት ትሆን ዘንድ ታጨች:: መቼም ሃብትን: ክብርን እንኩዋን እንዲህ በለጋ እድሜ አርጅተንም ቢሆን መናቁ አይሳካም::

+ቅድስት ሱርስት ግን አንድ ቅን ሃሳብ መጣላት:: ወደ አባቷ ዘንድ ሔዳም "ወደ አድባራት ሔጄ ከሠርጌ በፊት እንድሳለም ፍቀድልኝ" ስትል ጠየቀችው:: እርሱ ግን "ከሠርግሽ በሁዋላ ይደርሳል" ቢላት "በድንግልናየ ሳለሁ መቃብርህን እስማለሁ ብዬኮ ለፈጣሪየ ተስያለሁ" አለችው::

+አባቷም ከ300 ዲናር ወርቅና ከብዙ ሠራዊት ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ላካት:: ቅድስቷ ሕጻንም በዚያ የጌታን መቃብር ተሳልማ ወታደሮችን ጠፋቻቸው:: ከዚያ በሁዋላ የት እንደ ደረሰች ያወቀ የለም:: ሱርስት ግን ከኢየሩሳሌም ግብጽ ወርዳ ወርቁ ገዳም እንዲታነጽበት አደረገች::

+እርሷ ግን መንኩሳ ወደ በርሃው ገባች:: በዚያም 27 ዓመት ሙሉ ማንንም ሳታይ: በጭንቅ: በመከራ: በአርምሞ ተጋደለች:: አንድ ቀን ግን ባሕታውያንን የሚመግብ ሲላስ የሚሉት ካህን አግኝቶ ዜናዋን ከነገረችው በሁዋላ ሰግዳ ዐርፋለች:: በ39 ዓመቷም በዚህች ቀን ቀብሯታል::
+*" ታላቁ ቅዱስ ሳዊሮስ "*+
=>ቅዱስ ሳዊሮስ በ6ኛው መቶ ክ/ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በሶርያ አንጾኪያ የተነሳ አባት ነው:: ወቅቱ መለካውያን (2 ባሕርይ ባዮች) የሰለጠኑበት እንደ መሆኑ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን ያነሱበትና የሚሰደዱበት ጊዜ ነበር:: በዚህ ጊዜ ነበር ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ሳዊሮስ በሥላሴ ፈቃድ ለቤተ ክርስቲያን የተነሳው:: ሊቃውንት አንበሳ ሲሉ ይጠሩታል::

+ቅዱሱ ለተዋሕዶ ብዙ ሆኖላታል:: የመናፍቃን ጸር በመሆኑ ብዙ ድርሰቶችን ደርሷል:: ንጉሡን ዮስጢያኖስን (Justinian) ሳይቀር በይፋ ይገስጸው ነበርና ንጉሡ ሊገድለው ቆረጠ::

+ሃይማኖቷ የቀና ንግሥቲቱ ታኦድራ ግን ይህንን ስትሰማ በሌሊት ወደ ሊቁ ሒዳ "እባክህን ሽሽ" አለችው:: እርሱ ግን "ሞት ለእኔ ክብር ነውና አልሔድም" ሲል መለሰላት:: አባቶችን ሰብስባ "ስለ ቤተ ክርስቲያን ስትል" ብለው ለምነው ወደ ግብጽ ሸኙት::

+እርሱ እየሔደ ገዳዮቹ ያሳድዱት ገቡ:: መንገድ ላይ ቢደርሱበትም ተሰወረባቸው:: ለብዙ ቀናትም አብሯቸው ተጉዋዘ:: እነርሱ ተስፋ ቆርጠው ሲመለሱ እርሱ ግን ምድረ ግብጽ ደረሰ::

+በምድረ ግብጽም የዽዽስና ልብሱን ትቶ የመነኮሳትን አሮጌ ልብስ ለብሶ ሕዝቡንና መነኮሳቱን አስተማረ: አጸና:: በየቦታውም ብዙ ተአምራትን ሠራ::

+አባቶች መነኮሳትም ማንነቱን ባወቁ ጊዜ ሰገዱለት:: ዶርታኦስ (ዱራታኦስ) በሚባል አንድ ደግ ሰው ቤትም በ6ኛው መቶ ክ/ዘ አጋማሽ አካባቢ የካቲት 14 ቀን ዐርፏል:: ዛሬ የታላቁ ሊቅ በዓለ ፍልሠቱ ነው::

=>አምላከ ቅዱሳን ይርዳን: ይቅርም ይበለን:: ከበረከታቸውም ያሳትፈን::

=>ታሕሳስ 10 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ኒቆላዎስ ሊቅ
2.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
3.ቅድስት ሱርስት ገዳማዊት
4.ቅዱስ ጥዋሽ ሕጽው
5.ቅዱሳን ተላስስና አልዓዛር

  ወርኀዊ  የቅዱሳን  በዓላት
1.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ
2.አቡነ መልክዐ ክርስቶስ
3.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ እልፍዮስ)
4.ቅድስት ዕሌኒ ንግስት
5.ቅዱስ ዕፀ መስቀል
6.ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር
<<< ታሕሳስ 15 >>>

=>+"+ እንኩዋን ለአበው ቅዱሳን "ጐርጐርዮስ ዘአርማንያ" እና "አቡነ ኤዎስጣቴዎስ" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+

+*" ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘአርማንያ "*+

=>ይህ ቅዱስ አባት ከሰማዕታት: ከጻድቃን: ከሊቃውንትና ከዻዻሳት ዝርዝር ውስጥ ይገኛል:: በቤተ ክርስቲያንም ዓበይት ከሚባሉ አበው አንዱ ነው:: ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሮማዊ ሲሆን ከክርስቲያን ወላጆቹ የተወለደው በዘመነ ሰማዕታት (በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን) ነው::

+አበው በትውፊት እንደ ነገሩን ከሆነ ቅዱሱ የታላቁዋ ሰማዕት ቅድስት አርሴማ ትልቅ ወንድም ነው:: በዜና ሰማዕታት ተጽፎ እንደሚገኘው በዚያ የመከራ ዘመን ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሦስት ኃላፊነቶች ነበሩበት:-

1.ቅድስት አርሴማን ጨምሮ ደናግሉን ማጽናት:
2.ትምሕርተ ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ ማጥናት:
3.የሚመጣውን መከራ ለመቀበል ራሱን ማዘጋጀት::

+ቅዱሱ 3ቱንም ኃላፊነቶች በሚገባ በመወጣቱ ከራሱ አልፎ ለሌሎቹ አርአያ መሆን ቻለ:: ያቺን ንጽሕት አርበኛ ቅድስት አርሴማንም አጽንቶ የደናግሉ መሪ አደረጋት:: መከራው በጣም ገፍቶ እስከ መጣበት ጊዜ ድረስ በአንድ የደናግል ገዳም ውስጥ ሆነው ይጸልዩ: ይጾሙ: ገዳማዊ ሥራንም ይሠሩ ነበር::

+ለዚህም ነው ቅድስት አርሴማና ቅዱስ ጐርጐርዮስ ጻድቃን የምንላቸው:: በሁዋላ ግን ማሕደረ ሰይጣን ዲዮቅልጢያኖስ በመልኩዋ ተማርኮ ቅድስት አርሴማን ካላገባሁ በማለቱ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ድንግሏን አርሴማን ጨምሮ ክርስቲያኖችን ይዞ ወደ አርማንያ ተሰደደ::

+በአርማንያም በአንድ ገዳም ውስጥ ተደብቀው በጾምና በጸሎት ለጥቂት ጊዜ ቆዩ: ነገር ግን ረሃብ ፈጃቸው:: የሚላስ የሚቀመስ ነገር በአካባቢው ባለ መኖሩ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ወደ ከተማ ለመውጣት ተገደደ::

+በዚያም በድርጣድስ ቤተ መንግስት ውስጥ ባርነት ተቀጠረ:: በሚያገኛት ገንዘብም ወገኖቹን ይረዳ ነበር:: መከራው ግን አለቀቃቸውም:: ርጉም ዲዮቅልጢያኖስ ቅዱሳኑ ወደ አርማንያ መሔዳቸውን ስለ ሰማ ይዞ እንዲልክለት ድርጣድስን ላከው::

+ድርጣድስ ግን ቅድስት አርሴማን ባያት ጊዜ ከውበቷ የተነሳ መታገስ ባለመቻሉ "ካላገባሁሽ" አላት:: ድንግሊቱ ግን "እኔ የክርስቶስ ሙሽራ ነኝ: አይሆንም" አለችው:: ሊያስፈራራት ሞከረ:: ዐይኗ እያየ ደናግሉን ጨፈጨፋቸው::

+አልሳካልህ ቢለው በአደባባይ በግድ ሊያገባት ቢሞክር እጁን ጠምዝዛ በሰው ሁሉ ፊት መሬት ላይ ጣለችው:: እጅግ ስላፈረ አስገረፋት: አሰቃያት: ዐይኗንም አወጣ:: በመጨረሻም አንገቷን አስቆርጦ ከሰማዕታቱ ጋር ተራራ ላይ ጣላት::

+ወዲያው ደግሞ የቅዱስ ጐርጐርዮስ ማንነቱ በመታወቁ ይዘው አካሉ እስኪያልቅ ገረፉት:: በእሳትም አቃጠሉት:: በብዙ ስቃይም አሰቃዩት::

+በመጨረሻ ግን ከነ ሕይወቱ እንዲቀበር ተወሰነበት:: ወደ መጸዳጃ ቤት ወስደውም ከነ ሕይወቱ ቀበሩት:: ነገር ግን የእግዚአብሔር መልአክ ወርዶ መተንፈሻ ቀዳዳን ሠራለት:: አንዲት ሽማግሌ ክርስቲያንም በዚያች ቀዳዳ ቂጣ እየጣለችለት ለ15 ዓመታት ተቀብሮ ኖረ::

+አካሉና አፈሩ ተጣበቀ:: እርሱ ግን ፈጣሪውን እያመሰገነ ቆየ:: ከነገር ሁሉ በሁዋላ ድርጣድስና ባለሟሎቹ ለአደን በሔዱበት ርኩስ መንፈስ ወደ አውሬነት (እሪያነት) ቀየራቸው::

+የንጉሡ እንስሳ (አውሬ) መሆን በአርማንያ ታላቅ ድንጋጤን ፈጠረ:: የንጉሡ እህት ስታለቅስ በራዕይ "ለእመ ኢያዕረግምዎ ለጐርጐርዮስ አልብክሙ ድኂን-ጐርጐርዮስን ከተቀበረበት ካላወጣችሁት አትድኑም" አላቸው:: ወዲያውም በዚያች ሽማግሌ መሪነት ቆፍረው አወጡት::

+አካሉንም እግዚአብሔር መለሰለት:: ቅዱሱ እንደ ወጣ ዕረፍትን አልፈለገም:: ለ15 ዓመታት ቀባሪ አጥቶ የተበተነውን የቅድስት አርሴማንና የሰማዕታቱን አጽም ሰብስቦ በክብር አኖረው:: ድርጣድስና ባለሟሎቹንም ወደ በርሃ ሒዶ ፈወሳቸው::

+ወደ ሰውነትም መልሶ መላ አርማንያን ወደ ክርስትና መለሰ:: የንጉሡን እግር ግን የአውሬ አድርጐት ቀርቷል:: በመጨረሻም ቅዱስ ጐርጐርዮስ የአርማንያ ሊቀ ዻዻሳት ሆኖ ተሹሞ ብዙ መጻሕፍትን ደረሰ:: ከ318ቱ ሊቃውንትም አንዱ ሆኖ ተቆጠረ:: ዛሬ ታሕሳስ 15 ቀን ዕረፍቱ ነው::

+*" አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ረባን "*+

=>ሐዋርያዊው ጻድቅ ኢትዮዽያዊ (ኤርትራዊ) ሲሆኑ በዓለም ደረጃ የሚታወቅ አገልግሎት ያላቸው አባት ናቸው:: በመካከለኛው ዘመን የኢትዮዽያ ታሪክ የኤወስጣቴዎስንና የተክለ ሃይማኖትን ያህል ስሙ የጐላ ጻድቅ አይገኝም::

+ጻድቁ በ1265 ዓ/ም አካባቢ እንደ ተወለዱ ሲታመን ወላጆቻቸው ክርስቶስ ሞዐና ስነ ሕይወት ይባላሉ:: የጻድቁ የመጀመሪያ ስም "ማዕቀበ እግዚእ" (ለጌታ የተጠበቀ) ነው:: ኤዎስጣቴዎስ የተባሉ በሁዋላ ነው::

+ገና ከልጅነታቸው መንፈሰ እግዚአብሔር አድሮባቸዋልና ለዚህ ዓለም ግድ አልነበራቸውም:: ከመምሕር ዘንድ ገብተው: ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምረው: ዲቁናን ተቀብለው ያገለግሉ ገቡ:: በዲቁና አገልግሎታቸው ስሉጥ (ፈጣን) በመሆናቸውም የዘመኑ አበው "ዳግማዊ እስጢፋኖስ" እያሉ ይጠሯቸው ነበር::

+ከዚያ በወጣትነት እድሜአቸው ምናኔን መርጠው: ጾምና ጸሎትን ከስግደት ጋር አዘወተሩ:: እንዲህ ባለ ሕይወት ሳሉ አንድ ቀን ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ዘንድ መጣ::

+በዘባነ ኪሩብ: በግርማው ቢያዩት ደነገጡ:: ጌታ ግን "ወዳጄ ኤዎስጣቴዎስ! ገና ከእናትህ ማሕጸን መርጬሃለሁ:: ከኢትዮዽያ እስከ አርማንያም ሐዋርያ ትሆን ዘንድ ሹሜሃለሁ:: "ዘኪያከ ሰምዐ: ኪያየ ሰምዐ . . . አንተን የሰማ እኔን ሰማ:: አንተን እንቢ ያለ እኔን እንቢ አለ::" ብሏቸው: ባርኩዋቸው ዐረገ::

+ጻድቁ ፈጣሪያቸውን ስለ ስጦታው እያመሰገኑ ቅስናን ተቀብለው ስብከትን ጀመሩ:: ስም አጠራራቸውም ፈጥኖ በሃገሪቱ ተሰማ:: በየቦታው እየዞሩ ያላመነውን አሳምነው እያጠመቁ: ያመነውን በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እያጸኑ: ሕይወተ ገዳምን እያስፋፉ ኖሩ::

+አሁን ኤርትራ ውስጥ የሚገኘውንና እርሳቸው የመሠረቱትን ገዳም ጨምሮ ለገዳማዊ ሕይወት መስፋፋት አስተዋጽኦ አድርገዋል:: በገዳማቸውም አባ አብሳዲን ጨምሮ በርካታ አርድእትን አስተምረዋል: አፍርተዋል::

+አቡነ ኤዎስጣቴዎስ በተለይ የሚታወቁት ቀዳሚት ሰንበት እንዳትናቅ (እንድትከበር) ባደረጉት ጥረት ነው:: ደግሞም ተሳክቶላቸዋል:: ቅርብ ጊዜ ከምናየው የድፍረት ሥራ በቀር በሃገራችን 2ቱም ሰንበቶች ክቡር ናቸው::

+አቡነ ኤዎስጣቴዎስ 2 ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም በእግራቸው ተጉዘዋል:: መሔዳቸው ግን ለመሳለም ብቻ አይደለም:: ይልቁኑ የወንጌል ዘርን እየዘሩ: ፍሬውንም እየለቀሙ እንጂ:: እርሳቸው መቼም ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ቸል አይሉምና::

+በመጨረሻ ሕይወታቸውም በገዳማቸው ላይ ደቀ መዝሙራቸውን አባ አብሳዲን ሹመው ለአዲስ ጉዞ ተነሱ:: እኩሎች ልጆቻቸውን በገዳማቸው ትተው እኩሎችን አስከትለው ጉዞ ወደ አርማንያ ተደረገ::

+በመንገድም ወደ ባሕረ ኢያሪኮ ሲደርሱ የሚሻገሩበት መርከብ አጡ:: ድንቅ አባት ናቸውና በእምነት አጽፋቸውን (ኩታቸውን) አውልቀው ባሕሩ ላይ ጣሉት:: በላዩ ላይም በትእምርተ መስቀል አማትበው ተቀመጡበት::

+ደቀ መዛሙርቶቻቸውም ባሕሩ ላይ በተነጠፈው ኩታ ላይ ከበው ተቀመጡ:: ከሰማይም ጌታችን ወርዶ በመካከላቸው ቆመ:: ሚካኤል በቀኝ ገብርኤልም በግራ ቆሙ:: ጻድቁ ደግሞ ልጆቻቸውን ያስተምሯቸው: ይተረጉሙላቸው ገቡ::
+በመካከል ግን አንዱ (የማነ ብርሃን ይሉታል በቅኔ ቤት) በመጠራጠሩ እርሱ የተቀመጠባት ብቻ ተቀዳ ሰጠመ:: በሁዋላ ግን ጻድቁ ተመልሰው አውጥተው: ከሞት አስነስተውታል:: በዚህም ምክንያት 'ዘአደወ ባሕረ-ማዕበልን የተሻገረ' ይባላሉ::

+አቡነ ኤዎስጣቴዎስ በአርማንያ ለዘመናት ሰብከው: ሕይወተ ገዳምን አስፋፍተው: ብዙ ተአምራትን ሠርተው: በተወለዱ በ80 ዓመታቸው: በ1345 ዓ/ም ዐርፈዋል:: በብዙ ዝማሬ በመቅደሰ መርምሕናም ተቀብረዋል:: በኢትዮዽያ: ኤርትራ: ግብጽና አርማንያ ይከብራሉ:: ዛሬ ጻድቁ ማዕበሉን የተሻገሩበት መታሰቢያ ቀን ነው::

=>አምላከ ቅዱሳን ስለ አባቶቻችን ሲል በምሕረቱ ይጐብኘን:: ከበረከታቸውም ያሳትፈን::

=>ታሕሳስ 15 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሊቅ (ዘአርማንያ)
2.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ረባን
3.ቅዱስ ሉቃስ ዘዓምድ
4.አባ ይምላህ

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)
2.ቅድስት እንባ መሪና
3.ቅድስት ክርስጢና
4.ቅዱስ ሚናስ ሰማዕት
5.ቅዱስ ቂርቆስ ሰማዕት
4.ብጽዕት ኢየሉጣ ሰማዕት

=>+"+ ጻድቃን ጮሁ:: እግዚአብሔርም ሰማቸው::
ከመከራቸውም ሁሉ አዳናቸው::
እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው::
መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል::
የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው::
እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል::
እግዚአብሔር አጥንቶቻቸውን ሁሉ ይጠብቃል:: +"+ (መዝ. 33:17)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
እንኩዋን ለኃያል "መሥፍነ እሥራኤል ቅዱስ ጌዴዎን" እና "ማርያም እህተ ሙሴ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

+*" ኃያል ጌዴዎን "*+

=>እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን: 22ቱን ሥነ ፍጥረትን ፈጥሮ አዳምን ገዢ አደረገው:: አክሎም በነፍስ ሕያው አድርጐ: በመንፈስ ቅዱስ አክብሮ: ነቢይና ካህን አድርጐ: ካንዲት ዕፀ በለስ በቀር በፍጥረት ሁሉ ላይ አሰለጠነው::

+አባታችን አዳም ግን ስሕተት አግኝቶት ከገነት ወጣ:: መከራና ፍዳም አገኘው:: በሁዋላም ለ100 ዓመት አልቅሶ ንስሃ ገባ:: ጌታም ንስሃውን ተቀብሎ "ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ" የሚል ተስፋ ድህነትን ሰጠው::

+ስለዚህም ምክንያት ለ5,500 ዓመታት ትንቢት ሲነገር: ሱባኤ ወደ ታች ሲቆጠር: ምሳሌም ሲመሰል ኖረ:: ከደግ ፍጥረት አዳም እስከ ኖኅ ድረስ: የሴት ልጆች እግዚአብሔርን በንጽሕና ሁነው በደብር ቅዱስ አመለኩ::

+ትንሽ ቆይተው ግን ስለተቀላቀሉ ከቃየን ልጆች ጋር በማየ ድምሳሴ ጠፉ:: በጻድቅ ሰው ኖኅ የተጀመረው ትውልድም እግዚአብሔርን ለመዘንጋት ጊዜ አልፈጀበትም:: ነገር ግን ከሴም ዘር ቅንና ጻድቅ ሰው አብርሃም ተገኘ::

+ከእርሱም ይስሐቅ: ከዚያም ያዕቆብ (ደጋጉ) ተገኙ:: ያዕቆብም "እሥራኤል" ተብሎ: በልጆቹ "ሕዝበ እግዚአብሔር" የተባለ ነገድ ተመሠረተ:: በተስፋይቱ ምድር በከነዓን እንዳይኖሩም ረሃብ ምድረ ግብጽ አወረዳቸው::

+በዚያም ለ215 ዓመታት በጭንቅ የባርነትን ሕይወትን አሳለፉ:: እግዚአብሔርም ስለ ወዳጁ አብርሃም ሲል እሥራኤልን አሰባቸው:: የዋሕና ጻድቅ ሰው ሙሴን አስነስቶ እሥራኤልን ከግብጽ ባርነት አዳናቸው::

+ይኸውም በጸናች እጅ: በበረታችም ክንድ: በ9 መቅሰፍት: በ10ኛ ሞተ በኩር: በ11ኛ ስጥመት ግብጻውያንን አጥፍቶ ነው:: በየመንገዱም ጠላቶቻቸውን እየተበቀለላቸው ነው:: ከዚህ ዘመን ጀምሮም እሥራኤል በመሳፍንትና በካህናት የሚተዳደሩ ሆኑ::

+አስቀድሞ ሙሴ በምስፍና: አሮን በክህነት መሯቸው:: ቀጥሎም በቅዱስ ሙሴ ኢያሱ: በአሮን አልዓዛር ተተኩ:: እንዲህ እንዲህ እያለም ከኃያል ሰው ጌዴዎን ደረሱ:: ይኸውም ከዓለም ፍጥረት 4,151 ዓመታት በሁዋላ መሆኑ ነው::

+በጊዜው እሥራኤል ጣዖትን እያመለኩ እግዚአብሕርን ስላሳዘኑት ለጠላቶቻቸው አሳልፎ ይሰጣቸው ነበር:: የአካባቢው መንግስታት እነ አሞን: አማሌቅ: ኢሎፍሊ ስንኩዋ ያኔ ዛሬም ቢሆን እንደምትመለከቱት ዶሮና ጥሬ ናቸው::

+ከክርስቶስ ልደት 1,349 ዓመታት በፊትም በእሥራኤል ላይ ምድያማውያን (ይህቺ ሃገር የኢትዮዽያ ግዛት ነበረች ይባላል) በጠላትነት ተነስተውባቸው ተጨነቁ::

+አምላካችን እግዚአብሔርም ሊያድናቸው ወዶ መልአኩን ወደ ጌዴዎን ላከው:: ቅዱስ መልአክም ወደ እርሱ ቀርቦ "ኃያል የእግአብሔር ሰው" ሲል ጠራው:: ጌዴዎን ግን "ባሮች ስንሆን ምን ኃይል አለን!" ሲል መለሰለት::

+መልአኩም "እግዚአብሔር ካንተ ጋር ነውና ሒድ! እሥራኤልን ከምድያም እጅ አድናቸው" አለው:: ጌዴዎን ምልልሱን ቀጠለ:: "እግዚአብሔር ከእኔ ጋር መሆኑን በምን አውቃለሁ?" ሲል ጠየቀው::

+ጌዴዎን ይህንን ያለው ፈጣሪውን ተጠራጥሮት አይደለም:: ይልቁኑ ጥበበ እግዚአብሔር ይገለጥ ዘንድና በሁዋለኛው ዘመን የሚፈጸመውን ምሥጢረ ሥጋዌ ሊያስረዳ እንጂ::

+መልአኩም መስፍኑ የሰዋውን መስዋዕት አሳረገለት:: ቀጥሎም ጌዴዎን "ጸምር (ብዝት ጨርቅ) ልዘርጋ:: ጠል (ዝናብ) በጸምሩ ላይ ይውረድ:: ዳር ዳሩ ግን ይቡስ (ደረቅ) ይሁን" አለ:: በጠዋትም እንዳለው ሆኖ አገኘው::

+በጸምሩ ላይ የወረደውን ጠል ጨምቆ በመንቀል ሞልቶ ቢጠጣው ሰማያዊ ኃይል ወረደለት:: ጥያቄውን አሁንም ቀጠለ:: "ጌታ ሆይ! እንደ ገናም ነገሩ ይቀየርልኝ:: ጠል በጸምሩ ላይ አይውረድ:: ዳር ዳሩ ግን ይውረድበት" አለ::

+እንዳለውም ሆነ:: ይህ ሁሉ ምሳሌ ነው:: ለጊዜው ጸምር የእሥራኤል: ጠል የረድኤት: ምድር የአህዛብ ምሳሌ ነው:: ጠል በጸምር እንጂ በምድር ላይ እንዳልወረደ ረድኤተ እግዚአብሔር ለእሥራኤል እንጂ ለአሕዛብ ያለ መደረጉ ምሳሌ ነው::

+አንድም ምሳሌውን ይለውጧል:: ጠል የሚለውን ብቻ እንቀይረውና ጠል የመቅሰፍት ምሳሌ: በ2ኛው ጠል በምድር ላይ እንጂ በጸምር ላይ እንዳልወረደ: መቅሰፍቱም እሥራኤልን ትቶ በአሕዛብ ላይ ወርዷልና:: ( ይህ ጊዜአዊ ምሥጢሩ ነው:: )

+አማናዊ ምሥጢሩ ግን ወደ ሐዲስ ኪዳን ያመጣናል:: ጸምር የእመቤታችን: ጠል የጌታ ምሳሌ:: ጠል በጸምር እንጂ በምድር ላይ አለመውረዱ ጌታ ከድንግል ማርያም ብቻ መወለዱን ያሳያል::

+በ2ኛው ምሳሌ ደግሞ ጠል የፍዳ: የመርገም ምሳሌ ይሆናል:: ጠል በምድር ላይ እንጂ በጸምር ላይ አለመውረዱ ድንግል ማርያም ፍዳ መርገም የሌለባት ንጽሕት መሆኗን ያሳያል::

+ይህ ሁሉ የተደረገለት ጌዴዎንም በወገኖቹ መካከል አዋጅ አስነግሮ 32ሺ ሠራዊትን ሰበሰበ:: ግን እግዚአብሔር የእሥራኤላውያንን ክፋት (ማለትም በራሳችን ኃይል አሸነፍን) እንደሚሉ ያውቃልና "የፈራ ይመለስ በል" አለው::

+22ሺ ሠራዊት ፈርቶ ተመለሰ:: ምክንያቱም የምድያም ሠራዊት ከ100ሺ በላይ ነበርና:: አሁንም "10ሺው ብዙ ነው:: ወደ ወንዝ አውርደህ ለያቸው" አለው:: ጌዴዎንም ወደ ወንዝ አውርዶ "ውሃ ጠጡ" አላቸው::

+ከ10ሺው 300ው በእጃቸው እየጠለፉ ሲጠጡ 9,700 ያህል ሰራዊት ግን ተጐንብሰው በአፋቸው ጠጡ:: በዚህም "ሌሎቹን (የተጐነበሱትን) አስመልሰህ በ300ው ተዋጋ" ተባለ::

+እርሱም 300ውን ተከታዮቹን ይዞ: መለከትና መብራት በሸክላ ይዞ በምድያም ሠራዊት አካባቢ አደረ:: በዚያች ሌሊትም ጌዴዎንና ሠራዊቱ በምድያም መካከል ገብተው እንስራቸውን ሰበሩ::

+መለከቱንም ነፉ:: እንደ አንበሳም "ኃይል ዘእግዚአብሔር: ኩዊናት ዘጌዴዎን - ኃይልን ከእግዚአብሔር: ጦርን ከጌዴዎን" እያሉ ገጠሙ::

+በድንጋጤ የተመቱት ምድያማውያንም እርስ በርሳቸው ተዋግተው በአንድ ሌሊት ብቻ 102,000 ሠራዊት አለቀባቸው:: ቀሪዎቹም ወገኖቻቸው አፈሩ:: እሥራኤል ግን በፈጣሪያቸው ኃይል ተፈሩ:: ጌዴዎንም ለ40 ዓመታት እሥራኤልን አስተዳድሮ በዚህች ቀን ዐርፏል:: (መሣ. 6:1---8:35)

+"+ ማርያም እህተ ሙሴ +"+

=>ይህች እናት የሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴና የሊቀ ካህናቱ ቅዱስ አሮን ትልቅ እህት ስትሆን ወላጆቿ እንበረምና ዮካብድ ይባላሉ:: እሥራኤል ከግብጽ ባርነት እንዲወጡ የእርሷን ያህል አስተዋጽኦ ያደረገች ሴት የለችም::

+ከመነሻውም ቅዱስ ሙሴን የጠበቀች: በሕግ በሥርዓት እንዲያድግ ከእናቱ ጋር ያገናኘች: ወገኖቿ ከግብጽ ሲወጡም ሴቶችን የመራች እናት ናት:: ወንድሞቿን ሙሴንና አሮንንም ታገለገላቸው ነበር:: በተለይ እግዚአብሔር ባሕረ ኤርትራን የብስ ሲያደርጋት ከበሮን አንስታ "ንሴብሖ ለእግዚአብሔር" ብላ ፈጣሪዋን አመስግናለች:: (ዘጸ. 15:20)

+አንድ ጊዜም "ኢትዮዽያዊቷን ሲፓራን ለምን አገባህ" በሚል ስለ ተናገረችው እግዚአብሔር ተቆጥቶ በለምጽ መቷታል:: (ዘኁ. 12:1) ቆይቶም በቅዱሱ ምልጃ ምሯታል:: ማርያም በመንገድ ሳሉ: ወደ ርስት ሳይደርሱ ዐርፋ ተቀብራለች:: (ዘኁ. 20:1)

=>አምላከ ኃያላን መንፈሳዊ ኃይልን ልኮ ጠላትን ያድክምልን:: ከወዳጆቹ በረከትም ይክፈለን::

=>ታሕሳስ 16 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ጌዴዎን ኃያል
2.ማርያም እህተ ሙሴ
=>ወርኀዊ በዓላት
1.ኪዳነ ምሕረት (የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም)
2.ቅድስት ኤልሳቤጥ (የመጥምቁ ዮሐንስ እናት)
3.ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮዽያ
4.ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ
5.ቅዱስ አኖሬዎስ ጻድቅ
6.አባ ዳንኤል ገዳማዊ
7.አባ አቡናፍር ገዳማዊ

=>+"+ እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ: ስለ ሶምሶንም: ስለ ዮፍታሔም: ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም: ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና:: እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ:: ጽድቅንም አደረጉ . . . +"+ (ዕብ. 11:32)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
2024/10/01 15:29:29
Back to Top
HTML Embed Code: