Telegram Web Link
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_2_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ቆሮንቶስ 6
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ከእናንተ አንዱ ከባልንጀራው ጋር ሙግት ቢኖረው በቅዱሳን ፊት በመፋረድ ፋንታ በዓመፀኞች ፊት ሊፋረድ ይደፍራልን?
² ቅዱሳን በዓለም ላይ እንዲፈርዱ አታውቁምን? በዓለምስ ላይ ብትፈርዱ ከሁሉ ይልቅ ትንሽ ስለሚሆን ነገር ልትፈርዱ አትበቁምን?
³ የትዳር ጉዳይ ይቅርና በመላእክት እንኳ እንድንፈርድ አታውቁምን?
⁴ እንግዲህ ስለ ትዳር ጉዳይ የፍርድ ቤት ቢያስፈልጋችሁ በቤተ ክርስቲያን የተናቁትን ሰዎች ፈራጆች አድርጋችሁ ታስቀምጣላችሁን?
⁵ አሳፍራችሁ ዘንድ ይህን እላለሁ። እንደዚህ ነውን? በወንድሞች መካከል ሽማግሌ ሊሆን የሚችል አንድ አስተዋይ ሰው በእናንተ ዘንድ አይገኝምን?
⁶ ነገር ግን ወንድም ወንድሙን ይከሳል፥ ይህም በማያምኑ ፊት ይደረጋልን?
⁷ እንግዲህ ፈጽሞ የእርስ በርስ ሙግት እንዳለባችሁ በእናንተ ጉድለት ነው። ብትበደሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን?
⁸ ነገር ግን እናንተ ትበድላላችሁ ታታልሉማላችሁ፥ ያውም ወንድሞቻችሁን።
⁹ ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ
¹⁰ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ዮሐንስ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁰ የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ የተገለጡ ናቸው፤ ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም።
¹¹ ከመጀመሪያ የሰማችኋት መልእክት፦ እርስ በርሳችን እንዋደድ የምትል ይህች ናትና፤
¹² ከክፉው እንደ ነበረ ወንድሙንም እንደ ገደለ እንደ ቃየል አይደለም፤ ስለ ምንስ ገደለው? የገዛ ሥራው ክፉ፥ የወንድሙም ሥራ ጽድቅ ስለ ነበረ ነው።
¹³ ወንድሞች ሆይ፥ ዓለም ቢጠላችሁ አትደነቁ።
¹⁴ እኛ ወንድሞችን የምንወድ ስለ ሆንን ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ወንድሙን የማይወድ በሞት ይኖራል።
¹⁵ ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 13
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁴ ከመምጣቱ በፊት ዮሐንስ አስቀድሞ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የንስሐን ጥምቀት ሰብኮ ነበር።
²⁵ ዮሐንስም ሩጫውን ሲፈጽም ሳለ፦ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ታስባላችሁ? እኔስ እርሱን አይደለሁም፤ ነገር ግን እነሆ፥ የእግሩን ጫማ እፈታ ዘንድ ከማይገባኝ ከእኔ በኋላ ይመጣል ይል ነበር።
²⁶ እናንተ ወንድሞቻችን፥ የአብርሃም ዘር ልጆች ከእናንተ መካከልም እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሆይ፥ ለእናንተ የዚህ የመዳን ቃል ተላከ።
²⁷ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሰዎችና አለቆቻቸው እርሱንና በየሰንበቱ የሚነበቡትን የነቢያትን ድምፆች ስላላወቁ በፍርዳቸው ፈጽመዋልና፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_2_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ወይርአዩ አሕዛብ በቅድመ አዕይንቲነ። በቀለ ደሞሙ ለአግብርቲከ ዘተክዕወ። ይባዕ ቅድሜከ ገዐሮሙ ለሙቁሓን"። መዝ.78፥10-11።
"አሕዛብ፦ አምላካቸው ወዴት ነው? እንዳይሉ፥ የፈሰሰውን የባሪያዎችህን ደም በቀል በዓይኖቻችን ፊት አሕዛብ ይወቁ።
የእስረኞች ጩኸት ወደ ፊትህ ይግባ፤ እንደ ክንድህም ታላቅነት ሊገደሉ የተፈረደባቸውን አድን"። መዝ.78፥10-11።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_2_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማርቆስ 6
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁴ ስሙም ተገልጦአልና ንጉሡ ሄሮድስ በሰማ ጊዜ፦ መጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ተነሥቶአል ስለዚህም ኃይል በእርሱ ይደረጋል አለ።
¹⁵ ሌሎችም፦ ኤልያስ ነው አሉ፤ ሌሎችም፦ ከነቢያት እንደ አንዱ ነቢይ ነው አሉ።
¹⁶ ሄሮድስ ግን ሰምቶ፦ እኔ ራሱን ያስቈረጥሁት ዮሐንስ ይህ ነው እርሱ ከሙታን ተነሥቶአል አለ።
¹⁷ ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን አግብቶ ነበርና በእርስዋ ምክንያት ራሱ ልኮ ዮሐንስን አስይዞ በወኅኒ አሳስሮት ነበር፤
¹⁸ ዮሐንስ ሄሮድስን፦ የወንድምህ ሚስት ለአንተ ልትሆን አልተፈቀደም ይለው ነበርና።
¹⁹ ሄሮድያዳ ግን ተቃውማው ልትገድለው ትፈልግ ነበር አልቻለችም፤
²⁰ ሄሮድስ ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው እንደ ሆነ አውቆ ይፈራውና ይጠባበቀው ነበር፤ እርሱንም ሰምቶ በብዙ ነገር ያመነታ ነበር፤
²¹ በደስታም ይሰማው ነበር። ሄሮድስም በተወለደበት ቀን ለመኳንንቱና ለሻለቆቹ ለገሊላም ሹማምንት ግብር ባደረገ ጊዜ ምቹ ቀን ሆነላትና
²² የሄሮድያዳ ልጅ ገብታ ስትዘፍን ሄሮድስንና ከእርሱ ጋር የተቀመጡትን ደስ አሰኘቻቸው። ንጉሡም ብላቴናይቱን፦ የምትወጂውን ሁሉ ለምኚኝ እሰጥሽማለሁ አላት፤
²³ የመንግሥቴ እኩሌታ ስንኳ ቢሆን የምትለምኚውን ሁሉ እሰጥሻለሁ ብሎ ማለላት።
²⁴ ወጥታም ለእናትዋ፦ ምን ልለምነው? አለች። እርስዋም፦ የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ አለች።
²⁵ ወዲያውም ፈጥና ወደ ንጉሡ ገብታ፦ የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በወጭት አሁን ልትሰጠኝ እወዳለሁ ብላ ለመነችው።
²⁶ ንጉሡም እጅግ አዝኖ ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ስለ ተቀመጡት ሊነሣት አልወደደም።
²⁷ ወዲያውም ንጉሡ ባለ ወግ ልኮ ራሱን እንዲያመጣ አዘዘው። ሄዶም በወኅኒ ራሱን ቈረጠ፥
²⁸ ራሱንም በወጭት አምጥቶ ለብላቴናይቱ ሰጣት፥ ብላቴናይቱም ለእናትዋ ሰጠች።
²⁹ ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው መጡ በድኑንም ወስደው ቀበሩት።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ዮሐንስ_ወልደ_ነጎድጓድ ቅዳሴ ነው። መልካም የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መጥምቀ _መለኮት_ቅዱስ_ዮሐንስ ታሪክ ምን ያስተምረናል.....

#አስቀድሞ መሐላ መማል ፈጽሞ ተገቢ እንደልሆነ፡- "የሄሮድያዳ ልጅ ንጉሥ ሄሮድስን በዘፈኗ በጣም አድርጋ ስላስደሰተችው
እርሱም በተራው ሊያስደስታት ፈለገ፡፡ ‹እስከ መንግሥቱ እኩሌታ ድረስም ቢሆን
የለመነችውን ይሰጣት ዘንድ በሕዝቦቹና በመኳንንቱ ሁሉ ፊት እንዳይከዳት በፅኑ ቃልኪዳን ማለላት፡፡› እንዲህም እያለ
‹የፈለግሽውን ጠይቂኝ፣ የመንግሥቴንም እኩሌታ ቢሆን እሰጥሻለሁ ምን ላድርግልሽ?›
እያለ በመሐላ ባላት ጊዜ በእናቷ ምክር የዮሐንስን አንገት ቆርጦ ይሰጣት ዘንድ ለመነችው፡፡ ንጉሥ ሄሮድስም ይህን ልመና
ከአፏ በሰማ ጊዜ ‹የፈለግሽውን እሰጥሻለሁ› ብሎ በሕዝቡ ፊት ስለማለ ለሰው ይምሰል አዘነ፣ ተከዘ፡፡ ኃዘኑም ስለ ዮሐንስ መሞት
አይደለም፣ ዮሐንስን ሕዝቡ ይወደው ስለነበር እነርሱን ስለ መፍራቱና መሐላ ምሎ ከዳ
እንዳይባል ነው እንጂ፡፡ ስለ ዮሐንስ አዝኖ ቢሆን ኖሮ ቀድሞውንም በግፍ እንዲታሰር ባላደረገው ነበር፡፡

#ወንድሞቼ እኅቶቼ ሆይ! ከመሐላ የተነሣ መፍራት ይገባችኋል፡፡ ‹የለመንሽውን ሁሉ
እሰጥሻለሁ› ብሎ ስለማለ ሄሮድስ የዮሐንስን አንገት እንድትቆረጥ አደረገ፡፡

📌ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በቅዱስ ወንጌል ‹ፈጽማችሁ አትማሉ› ብሏል፡፡ ከዚህ በኋላ ወታደሮች ሠይፍ ይዘው የዮሐንስን አንገት ይቆርጡ ዘንድ ወደ መኅኒ ቤት ሄዱ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም የሄሮድስ ጭፍሮች ሊገድሉት
እንደመጡ በመንፈስ ቅዱስ ፀጋ ስላወቀ ከጨለማው ቤት ውስጥ አንገቱን በመስኮት አውጥቶ እንደሚመቻቸው አድርጎ ጠበቃቸው፡፡ የሄሮድስን ቃል እንዳያቃልሉ ጭፍሮቹም የ"መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን"
አንገት ስለ መሐላው ቆረጡት፡፡ በመሐላ ምክንያት ባይሆን ኖሮ ሄሮድስ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን ባላስገደለው ነበር፡፡ ስለዚህ
ወንድሞቸ እኅቶች ሆይ! እናንተም ከመሐላ የተነሣ መፍራት ይገባችኋል፣ ፈጽማችሁም መማል የለባችሁም፡፡››

📌ስካርና ዘፈን ከሚገኙበት ቦታ አጋንንትና ኃጢአት ከዚያ አሉ፡-
‹‹ወንድሞችና እኅቶች ሆይ! አለልክ መብላትና መጠጣት ካለበት ቦታ #እግዚአብሔርን መበደል፣ ማስቀየምና ማስቆጣት ይገኝበታል፡፡ ስካር ከሚገኝበት ቦታ አጋንንትና ኃጢአት ከዚያ አሉ፡፡ ስካርና ዘፈን ከሚገኝበት
ቦታ የ #እግዚአብሔር መቅሰፍት የፈጣሪያችን ቁጣና በቀል ይፈጸምበታልና፡፡ እናንተ ሕዝበ ክርስቲያኖች ሆይ! ከስካር፣ ከዘፈንና
ከዝሙት መራቅ ይገባችኋል፡፡

📌መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን ያስገደለው
ዘፈን፣ ስካርና የዜማ ፍቅር መሆኑን ልብ በማለት መገንዘብ አለባችሁ፡፡››
#መስከረም_3

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ሦስት በዚች ቀን #ሊቀ_ጳጳስ_አባ_ዲዮናስዮስ የተሾመበት፣ #አባ_ሙሴ_ዘገዳመ_ሲሐት አረፈ፣ #አባ_አንበስ_ኢትዮጵያዊ ዕረፍታቸው ነው

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሊቀ_ጳጳሳት_አባ_ዲዮናስዮስ

መስከረም ሦስት በዚች ቀን የከበረ አባት ሊቀ ጳጳሳት አባ ዲዮናስዮስ ከተሾመ በሁለተኛው ዓመት በእስክንድርያ ከተማ የኤጲስቆጶሳት የአንድነት ጉባዔ ተደረገ።

ይኸውም አባት የትንሣኤ ሙታንን ድርሳን የደረሰው ነው፡፡ ይህም ጉባዔ የሆነው ነፍስ ከሥጋዋ ጋር ትሞታለች በዕለተ ትንሣኤም ከሥጋዋ ጋር አብራ ትነሣለች ስለሚሉ ክፉዎች በዐረቢያ አገር ስለ ተነሡ ሰዎች ነው። እነርሱም ለከፋችና ብልሹ ለሆነች ሃይማኖታቸው የፈጠራ ድርሰትን ደርሰው በእስክንድርያ ከተማ ወደሚኖሩ ሰዎች ላኩ።

አባታችን ሊቀ ጳጳሳት አባ ዲዮስናስዮስም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ ከዚህ ከክፉ ሥራም እንዲመለሱ አስተማራቸው ገሠጻቸውም እነርሱ ግን አልሰሙትም አልተመለሱም። ስለዚህም በእነርሱ ላይ ይህን ጉባዔ ሰብሰቦ ተከራከራቸው ስሕተታቸውንም ገልጾ አስረዳቸው እነርሱ ግን ሰይጣን አሳውሮአቸዋልና ተጸጽተው አልተመለሱም ይህም ጉባኤ ረግሞ ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ለይቶ አሳደዳቸው። ይህም አባት ዲዮናስዮስ ስለርሳቸው ድርሳናትን ደረሰ በውስጣቸውም እንዲህ የሚል እንጂ በቸርነቱ ስጦታ ውስጥ የ #እግዚአብሔር ፍቅር የጎላ የተረዳ ሆነ ነፍስ ረቂቅ ስለሆነች እንደ መላእክት በሕይወት እንድትኖር እንጂ እንዳትሞት እንዳትጠፋ ማድረጉ ነው።

ከሥጋዋም በምትወጣ ጊዜ ስለ በጎ ሥራዋ እንደሚገባት መጠን ወደ ሕይወት ቦታዋ ይወስዷታል ወይም እንደ ሥራዋ ክፉነት ወደ ሥቃይ ይወስዷታል። በትንሣኤ ቀንም ንቃሕ መዋቲ ተብሎ ዓዋጅ ሲነገር በፈጣሪያቸው ትእዛዝ የሙታን በድኖች ሲነሡ ነፍሳት እንዲህ ይሆናሉ እያንዳንዲቱ ነፍስ ከሥጋዋ ተዋሕዳ አብራ ትነሣለች።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን አባቶቻችን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ሙሴ_ዘገዳመ_ሲሐት

በዚህችም ቀን የገዳመ ሲሐት አባ ሙሴ አረፈ ። ይህም ቅዱስ ከመነኰሰ ጀምሮ ዓለምን ትቶ ከበረሀ ገብቶ በጾም በጸሎት በመጠመድ ተጋደለ ። #እግዚአብሔር ዘይቶንና የተምር አትክልት ያለባትን የአትክልት ቦታ በማየት ልቡን ብሩህ እስከ አደረገለት ድረስ በወሩ መባቻም ከዘንባባ ዕንጨትና ከዘይቶን የወደቀውን ፍሬ ወስዶ ይበላል ።

ምግቡም ታናሽ ወፍ በሚመገበው መጠን ልክ ነው ልብሱም ከዘንባባ ቅጠል የተሠራ ሰሌን ነው ። ስለዚህ ለሚያስጨንቅ ለክረምት ቅዝቃዜና ለበጋ ቃጠሎ የተጋለጠ ከዚህም ጋር በጾምና በጸሎት የተጠመደ ነው ።

ነገር ግን መጻሕፍትን የሚያውቅ አይደለም የዱር አራዊትም በየወገናቸው ወደርሱ ይመጡ ነበር እርሱም ያረጋጋቸዋል። የጸሎት ጊዜም ሲደርስ በእጁ ሲጠቅሳቸው ይሔዳሉ ። ድርቅ የሆነ እንደሆነም ሊያነጋግሩት እንደሚሹ ሁነው መጥተው በፊቱ ይቆማሉ እርሱም የሚሹትን በ #መንፈስ_ቅዱስ አውቆ በጸሎቱ ዝናብን ያወርድላቸዋል ። እንዲሁም እያደረገ ከእርሳቸው ጋር አርባ አምስት ዓመት ኖረ ።

ሰይጣንም ቀናበት ዘመኑ በአለፈና እጅግ በአረጀ ሽማግሌ አምሳል በጥቂት በጥቂት ሲያዘግም ከበዓቱ ውስጥ ሁኖ አየው ለዚህ ቅዱስ አባ ሙሴም ገዳማዊ መናኒ መስሎት ወደርሱ ሒዶ አምጥቶ ወደ በዓቱ አስገባው አራዊት ግን በሽማግሌ የተመሰለውን ሰይጣን በአዩት ጊዜ ከእርሱ ሸሹ።

ከዚህ በኋላ አባ ሙሴን አገሩንና ሃይማኖቱን ጠየቀው እርሱም ሁሉን ነገረው ደግሞ አባ ሙሴ ኑሮው እንዴት እንደሆነ ሽማግሌውን ጠየቀው ። በሽማግሌ የተመለሰ ሰይጣንም እንዲህ ብሎ መለሰለት እኔ በዓለም ኃጢአት በመሥራት ብዙ ዘመናት ኖርኩ አንዲት ሴት ልጅንም ወለድኩ ። ከዚያም የዓለምን ኃላፊነትና ጠፊነት አሰብኩ ከዓለምም ወጥቼ በበረሀ ውስጥ አርባ ዓመት ኖርኩ ።

ልጄን ያገባት እንደሌለ በአሰብኩ ጊዜ በዚህ ነገር ምክንያት ወዳንተ መጣሁ ከአንተ በቀር የሚያገባት የለምና በሞትኩም ጊዜ የምትቀብረኝ አንተ ነህ ብዙ ስፍራዎችና የአታክልት ቦታዎችም ስላሉኝ ሁሉንም እንተ ትወርሳለህ ።

አባ ሙሴም ሰምቶ ደነገጠ እኔ መነኲሴ ስሆን ይህን እንዴት አደርጋለሁ አለ የተመረጡ ጻድቃን ሲሆኑ ሚስቶች የነበሩአቸው አብርሃምን ሙሴን ዳዊትን ከብሉያት መጻሕፍት ምስክር ማስረጃ አድርጎ አመጣለት በዚህም ወደ ተንኰሉ ልቡን አዘነበለው ።

በውስጡ ያጌጠች ሴት ልጅ ያለችበትን የተሸለመ አዳራሽ አሳየውና ከዚያም በኋላ እንደሞተ ሆነ አባ ሙሴም አይቶ በላዩ አለቀሰ ገንዞም ቀበረው ።

ልጅቷ ወዳለችበት ለመግባት በፈለገ ጊዜ ጥቅል ነፋስ ነፍሶ የኋሊት ጣለው ከዚህ በኋላ ልቡ ሲመለስለት አዳራሹንም ልጅቷንም የአትክልት ቦታዎችንም አጣ ፈጽሞ እያደነቀ ወደ ማደሪያው ተመለሰ ከዕንጨቱም ፍሬ ምግቡን ሊመገብ ፈለገ በአፉም ውስጥ መራራ ሆነበት በረኃብም ስለ ተጨነቀ ወደ ዱር ወጥቶ ሔደ ።

ከዚህም በኋላ በአህያው ላይ ተቀምጦ ወደ እስክንድርያ በሚሔድ በሽማግሌ ነጋዴ አምሳል ሰይጣን ተገናኝው መብልና መጠጥም ይዞ ነበር አባ ሙሴንም ከርሱ ጋር ወሰደው ወዳንድ አገርም አድርሶ በዚያ ደሴት ተወው ።

ዳግመኛም በገዳማዊት በመናኒነት በምትኖር አምሳል ሰይጣን ታየው እርሷም ውኃ የምትቀዳ መስላ ነው ሥራውን ጠየቀችው ሰይጣን እንደ ፈተነው ሁሉን ነገራት በልቧም ሳቀችበት ወደ ቤቷም ወስዳው አብልታ አጠጥታ ከዚያ በኋላ የጋብቻን ነገር አሳሰበችው ብዙ ገንዘብም እንዳላት እርሷም የሟች ንጉሥ እንደ ሆነች ነገረችው ።

ልቡም እንደአዘነበለ አይታ እኔ አይሁዳዊት ነኝ እኛም ብዙዎች ነን ሃይማኖቱንም እስከካደ ድረስ በብዙ ተንኰል ተስፍ አስደረገችው ።

ዳግመኛም እንዲህ አለችው ና ወደ በረሀ እንውጣና ያኖርኩትን ገንዘብ እንውሰድ ብላ ውኃ ወደሌለበት በረሀ ወሰደችው ከተራራ በላይም ወጥታ ተለወጠችበት እንዲህም አለችው እኔ ብዙዎችን ያሳትኩ ሰይጣን ዚህ አንተነንም ከገዳምህ አስመጣሁህ ሃይማኖትህንም አስካድኩህ እነሆ በዚህ በረሀም ሙተህ ነፍስህ ወደገሃነም ትወርዳለች ይህንንም ብሎ ሰይጣን ከርሱ ተሠወረ ።

በተመለሰም ጊዜ በቀኝም በግራም መንገድ አጣ የሚጠጣውም ውኃን አላገኘም ምድር ጠበበችው በምድር ላይም ወድቆ በፊቱ ውስጥም አፈርን በተነ ነፍሱም ከሥጋው ለመለየት እስከደረሰች ደረስ ተንከባለለ ጭኸ መሐሪና ይቅር ባይ ሰውን የሚወድ #እግዚአብሔር ራራለት ያጽናናው ዘንድ መልአኩን ላከለት እርሱም ኃጢአትህ ተሠረየልህ እስከ ሰባት ቀንም ታርፍለህ የ #እግዚአብሔር አገልጋይ ሳሙኤልም ይቀብርሃል ብሎ አጽናናው ሰላምታም ሰጥቶት ዐረገ ።

ያን ጊዜም ሳሙኤል መጣ ንጉስ ኢጋቦም በበረሃ ውስጥ ወደአነፃት ቤተ ክርስታያን ወሰደው እርሷም ገዳማውያን የሚሰበሰቡባት ተሰውራ የምትትኖር ናት ወደርሷም በደረሱ ጊዜ ቅዱሳን ተሰብስበው መሥዋዕትን ሲያሳርጉ አገኙና በአንድነት ሥጋውንና ደሙን ተቀበሉ ሰንብትም ከሆን በኋላ ከቅዱሳን መቃብር በረከትን ሊቀበሉ ከአባ ሳሙኤል ጋራ አብረው ሔዱ ዘኪያም ደርሶ አባ ሙሴ ሰገደ ወዲያውም አረፈ አባ ሳሙኤልም ቀበረው ገድሉንም ጻፈ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሁሉም ቅዱሳን በጸሎታቸው ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_አንበስ_ኢትዮዽያዊ
ከቅድስናው የተነሣ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሰው በአንበሳ ላይ ተጭኖ ነው፡፡ ተአምራትን በማድረግና ወንጌልን በማስተማር በጾም ጸሎት አብዝቶ የደከመ ሲሆን ስለ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሌት ተቀን በጸሎት ይተጋ የነበረ ታላቅ አባት ነው፡፡ አቡነ አንበስ ትውልዱ ትግራይ አድዋ በእንጭጮ ወረዳ ነው፡፡ በስሙ ትግራይ አድዋ "እንጭጮ አቡነ አንበስ ገዳም" እና በትግራይ ሽሬ ሁለት ትላልቅ ገዳማት አሉት፡፡ ቅዱስ ያሬድ በድርሰቱ ደጋግሞ የጠቀሳቸው ሲሆን የያሬድንም የድርሰቱን የአቋቋም ሥርዓት ያመጡት አቡነ አንበስ ናቸው፡፡

አቡነ አንበስ በአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እና በአቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ ጊዜ የነበሩ ሲሆን እሳቸውንም አንበሶች ያገለግሏቸው ነበር፡፡ ጻድቁ አቡነ አንበስ ከአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጋር የተገናኘ ትልቅ ታሪክ አላቸው፡፡ የላዕላይ ግብጹ አባ ብንያም፣ በአቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ እና የሐዘሎው አቡነ አንበስ እነዚህ 3ቱ ቅዱሳን ከየአሉበት በአንበሳቸው ተጭነው ዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ዘንድ እንደደረሱ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንበሶች የ3ቱንም ቅዱሳን አንበሶች ዋጡዋቸው፣ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስም በዚህ አዝነው ከበዓታቸው ወጥተው አንበሶቻቸውን ‹ትፉ› ብለው የበሉአቸውን አንበሶቻቸውን አስተፍተዋቸው ለ3ቱም ቅዱሳን የተበሉባቸውን አንበሶቻቸውን መልሰውላቸዋል፡፡ ይኸውም የሆነው እንዲህ ነው፡- አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በዝቋላ 7ቱ ሊቃነ መላእክት እየረዷቸው 70 ሺህ እልፍ አጋንንትን በእሳት ሰይፍ ፈጅተው ካጠፏቸው በኋላ ወደ ምድረ ከብድ ተመለሱ፡፡ ከዚህም በኀላ #መንፈስ_ቅዱስ የጠራቸው ሦስቱ ቅዱሳን አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ አቡነ አንበስ ዘሐዘሎ እና የላዕላይ ግብጹ አቡነ ብንያም በአንበሶቻቸው ሆነው ወደ ጻድቁ አባት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ዘንድ ምድረ ከብድ ገዳም መጡ፡፡

አባታችን ግን ስለተሰወራቸው እስከ 7 ቀን ድረስ በምህላ ሰነበቱ፡፡ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንበሶችም መጥተው የ3ቱን ቅዱሳን አንበሶች በልተውባቸው ተሰወሩ፡፡ 3ቱም ቅዱሳን ፈጽመው ደነገጡ፡፡ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስም የቅዱሳኑን ሀዘንና ድንጋጤ ተመልክተው በታላቅና በሚያስፈራ ግርማ ሆነው ስልሳ ነብሮችንና ስልሳ አንበሶችን አስከትለው ተገለጡላቸው፡፡ ቅዱሳኑም ከአቡነ ገብረ መንፈስቅዱስ ግርማ የተነሣ ስለደነገጡ እንዳይፈሩም አረጋጉአቸው፡፡

ከዚህም በኃላ አባታችን "በምን ምክንያት ወደዚህ ገዳም ወደ እኔ መጣችሁ?" አሏቸው፡፡ ሦስቱ ቅዱሳን እንዲህ አሉ፡- "ጸሎትህ ቅድስት እንደሆነች ባወቅን ጊዜ ወደ አንተ መጣን፤ አንተ በሁሉ ርእሰ ባሕታውያን ነህና የ #እግዚአብሔርን ሥራ ትነግረን ዘንድ መጣን፤ ባላገኘንህም ጊዜ እስከ 7ቀን አለቀስን" አሉት፡፡

ዳግመኛም "አንበሶችህ መጥተው አንበሶቻችንን ደማቸውን ጠጡ ቆዳቸውንም በጥፍራቸው በጣጠሱ" ብለው ነገሯቸው፡፡ አባታችንም ይህንን ሲሰሙ አንበሶቻቸውን "እስከ ዕለቴ ሞቴ ድረስ በእግሬ ከረገጥኩት ትቢያ በቀር ምንም እንዳትበሉ ታዛችሁ የለምን? #እግዚአብሔር ያላዘዛችሁትን ለምን በላችሁ? በሉ አሁንም የበላችሁትን ትፉ" አላቸው፡፡ እነዚያም አንበሶች አፋቸውን ከፍተው አንዳች ሳያስቀሩ አጥንታቸውን ሥጋቸውን በሙሉ ተፉአቸው፡፡ ጻዲቁ አባታችንም ወደ ምሥራቅ ተመልሰው #እግዚአብሔርን ከለመኑ በኃላ በአንበሶቹ ሥጋ ላይ ባረኩና "በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ተነሡ" አሏቸው፡፡ አንበሶቹም እንደ ዐይን ፈጥነው ተነሥተው እንደ ቀድሞው ሆኑ፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ለዘላለሙ ከእኛ ጋር ትኑር አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም_3 እና #ከገድላት_አንደበት)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_3_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ተሰሎንቄ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹³ እናንተ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ መልካም ሥራን ለመሥራት አትታክቱ።
¹⁴ በዚህ መልእክት ለተላከ ቃላችን የማይታዘዝ ማንም ቢኖር፥ ይህን ተመልከቱት፥ ያፍርም ዘንድ ከእርሱ ጋር አትተባበሩ።
¹⁵ ነገር ግን እንደ ወንድም ገሥጹት እንጂ እንደ ጠላት አትቍጠሩት።
¹⁶ የሰላምም ጌታ ራሱ በሁሉ መንገድ ዘወትር ሰላምን ይስጣችሁ። ጌታ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።
¹⁷ በገዛ እጄ የተጻፈ የእኔ የጳውሎስ ሰላምታ ይህ ነው፤ የመልእክቴ ሁሉ ማስረጃ ይህ ነው፤ እንዲህ እጽፋለሁ።
¹⁸ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ዮሐንስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁸ ሙሉ ደመወዝን እንድትቀበሉ እንጂ የሠራችሁትን እንዳታጠፉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።
⁹ ለሚወጣ ሁሉ በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት።
¹⁰ ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት፤
¹¹ ሰላም የሚለው ሰው በክፉ ሥራው ይካፈላልና።
¹² እንድጽፍላችሁ የምፈልገው ብዙ ነገር ሳለኝ በወረቀትና በቀለም ልጽፈው አልወድም፥ ዳሩ ግን ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ወደ እናንተ ልመጣ አፍ ለአፍም ልናገራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 20
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁸ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።
²⁹-³⁰ ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_3_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
  "እስመ አድኀንካ ለነፍስየ እሞት። ወለአዕይንትየኒ እምአንብዕ። ወለእገርየኒ እምዳኅዕ"። መዝ 55፥13
“ነፍሴን ከሞት፥ እግሮቼን ከመውደቅ አድነሃልና፥ በሕያዋን ብርሃን እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው ዘንድ።" መዝ 55፥13
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_3_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 18
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁸ እውነት እላችኋለሁ፥ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል።
¹⁹ ደግሞ እላችኋለሁ፥ ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል።
²⁰ ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።
²¹ በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ወደ እርሱ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ልተውለት? እስከ ሰባት ጊዜን? አለው።
²² ኢየሱስ እንዲህ አለው፦ እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ አልልህም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ 
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ዲዮስቆሮስ ቅዳሴ ነው። መልካም የአባ አንበስ፣ የሊቀ ጳጳስ የአባ ዲዮናስዮስና የአባ ሙሴ ዘሲሐት የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ እና #ነቢዩ_ኤልያስ

ቅዱስ ዮሐንስ በበርካታ መንገዶች ከነቢዩ ኤልያስ ጋር ተያይዟል፡፡ ነቢዩ ሚልክያስ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ መምጣትና መንገድ ጠራጊነት ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር፡፡
«እነሆ ታላቁና የሚያስፈራው የ #እግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ቴስቢያዊውን ኤልያስን እልክላችኋለሁ … እርሱም የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፣ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል፡፡» /ሚል.4÷5-6/
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም የቅዱስ ዮሐንስን መወለድ ለአባቱ ለዘካርያስ በቤተ መቅደስ ሲያበሥረው እንዲህ ብሎ ነበር፡፡
«… እርሱም የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የከሐድያንንም ሐሳብ ወደ ጻድቃን ዕውቀት ይመልስ ዘንድ ሕዝብንም ለ #እግዚአብሔር የተዘጋጀ ያደርግ ዘንድ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል» /ሉቃ.1÷17/

በዚህም ምክንያት ሕዝቡ ከመሲህ መምጣት በፊት የኤልያስን መምጣት ይጠብቁ ነበር፡፡ ለምሳሌ #ጌታችንን ደቀመዛሙርቱ «ጻፎች ኤልያስ አስቀድሞ ይመጣ ዘንድ አለው ለምን ይላሉ?» ብለው ጠይቀውት ነበር፡፡ /ማቴ.17÷10፣ ማር.9÷11/
#ጌታችንም ኤልያስ ይመጣል ተብሎ የተነገረው ስለ መጥምቁ ዮሐንስ መሆኑን እንዳስረዳቸው እነርሱም እንደተረዱ ቅዱስ ማቴዎስ ይነግረናል /ማቴ.17÷11-13/
«ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለችው «አዎን፤ ኤልያስ አስቀድሞ ይመጣል፤ ሁሉንም ያቀናል፡፡ ነገር ግን እላችኋለሁ፡፡ ኤልያስ ፈጽሞ መጥቷል፤ የወደዱትንም አደረጉበት እንጂ አላወቁትም …» ከዚህም በኋላ ደቀመዛሙርቱ ስለ መጥምቁ ዮሐንስ እንደነገራቸው አወቁ፡፡»

ከአንድ ታላቅ እና ታዋቂ ሰው በኋላ የሚነሱ ደጋግ ሰዎችን በእዚያ በታላቁ ሰው ስም መጥራት በትንቢቶች ውስጥ የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ዳዊት እሥራኤላውያን የሚወዱትና ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ንጉሣቸው ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት ካለፈ በኋላ #እግዚአብሔር ደጋግ ነገሥታትን እንደሚያስነሳላቸው ለእሥራኤል ተስፋ ሲሰጥ ዳዊትን አስነሳላችኋለሁ ይላቸው ነበር፡፡
«ባርያዬም ዳዊት በላያቸው ላይ ንጉሥ ይሆናል፤ ለሁሉም አንድ እረኛ ይሆንላቸዋል» /ሕዝ.37÷24/
«ለ #እግዚአብሔርም ለማስነሣላቸው ለንጉሣቸው ለዳዊትም ይገዛሉ» /ኤር.3ዐ ÷9/፡
አሁንም የተደረገው ይኸው ነው፡፡ አይሁድ ኤልያስን በጣም ይወዱትና ያከብሩት ነበር፡፡ አሁንም ድረስ ያሉ አይሁዳውያን የፋሲካን በዓል በሚያከብሩበት ዕለት ለማዕድ ሲቀመጡ «ለኤልያስ» ብለው አንድ ቦታ ይተዋሉ፤ የወይን ጠጅ የተሞላ ብርጭቆም ያስቀምጣሉ፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ መምጣት «ኤልያስ ይመጣል» ተብሎ የተነገረው ለዚህ ነው፡፡ «እንደ ኤልያስ ያለ የኤልያስን ዓይነት ሥራ የሚሠራ ነቢይ ይወጣል» ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ለካህኑ ለዘካርያስ የተናገረው ይህንኑ የሚያመለክት ነው፡፡ «…በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል…»

በእርግጥም ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅን እና ነቢዩ ኤልያስን ብዙ የሚያመሳስሉአቸው ነገሮች አሉ፡፡
#አለባበሳቸው፡- የነቢዩ ኤልያስ አለባበስ በሁለተኛው መጽሐፈ ነገሥት እንዲህ ተብሎ ተገልጿል፡፡ «እነርሱም ሰውየው ጠጉራም ነው፡፡ በወገቡም ጠፍር ታጥቆ ነበር አሉት፡፡ እርሱም ቴስብያዊው ኤልያስ ነው አለ» /2ኛነገ.1÷8/

#ትምህርታቸው፦ የሁለቱም ነቢያት ትምህርት ትኩረት የእስራኤል ሕዝብ ኃጢያታቸውን ትተው ወደ #እግዚአብሔር እንዲመለሱ ማድረግ ሲሆን፤ የሁለቱም ተግሳጽ የተሞላበት ነበር፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ኤልያስ «የ #እግዚአብሔር ከሆናችሁ የ #እግዚአብሔር ብቻ ሁኑ፤ የበአል /የጣኦት/ ከሆናችሁ የበአል /የጣኦት/ ብቻ ሁኑ» እያለ ጠንካራ ንግግሮች ይናገር ነበር፡፡

#ነገሥታትን መገሰጻቸው፡- ነቢዩ ኤልያስ ንጉሡን አክአብንና ንግሥቲቱ ኤልዛቤልን ናቡቴን ርስቱን ቀምተው በግፍ በማስገደላቸው ገስጿቸዋል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህንን አስመልክቶ ባስተማረው ትምህርት «በእርግጥም የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ትህርምት እጅግ የሚያስደንቅ ነበር፤ አይሁድንም በእርሱ ውስጥ ነቢዩ ኤልያሰን እንዲያዩ አድርጓቸዋል» ብሏል፡፡

#ቅዱስ_ዮሐንስ ክብር እና መዓርጋት

ቅዱስ ዮሐንስ ክብሩ በጣም ከፍ ያለ ነው፡፡ የክብሩ ምስክሮችም #ጌታችንና_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ እና መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ናቸው፡፡
#ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ እንዲህ ሲል የመጥምቁን ክብር ተናግሯል፡፡
«ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጥታችኋል? ከነፋስ የተነሣ የሚወዛወዛውን ሸንበቆ ነው? ወይስ ምን ልታዩ መጥታችኋል ቀጭን ልብስ የለበሰ ሰውን ነውን? እነሆ ቀጭን ልብስ የሚለብሱማ በነገሥታት ቤት አሉ? ምን ልታዩ መጥታችኋል ነቢይ ነውን? አዎን እርሱ ከነቢያት እጅግ ይበልጣል፤ እነሆ በፊትህ መንገድህን የሚጠርግ መልእክተኛዬን እልካለሁ ተብሎ ስለ እርሱ የተጻፈለት ይህ ነውና፡፡ እውነት እውነት እላችኋለሁ ሴቶች ከወለዷቸው ወገን ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም» /ማቴ.11÷7-11/
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም እንዲህ ሲል ክብሩን ተናግሮለታል፡- «እርሱ በ #እግዚአብሔር ፊት ታላቅ ይሆናል» /ሉቃ.1÷15/

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ «የቅዱስ ዮሐንስ ክብር እና ከፍ ከፍ ማለት ምንጮች ሁለት ናቸው፡፡» ይላሉ፡፡
1. በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ስለሆነ
ከመጥምቁ ዮሐንስ በፊት የ #እግዚአብሔር መንፈስ ወደ ብዙ ሰዎች መምጣቱ ተጽፏል፡፡ ለምሳሌ ያህልም
➛ሳሙኤል ሳኦልን ቀብቶ ባነገሠው ጊዜ «የ #እግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ ወረደ» ተብሏል /1ኛሳሙ.10÷10/፡፡
➛ሳሙኤል ዳዊትን በንግሥና በቀባው ጊዜ «የ #እግዚአብሔር መንፈስ ከዚያ ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ መጣ» ተብሏል 1ኛ ሳሙ.16÷13፡፡
➛«የ #እግዚአብሔር መንፈስ ከሶምሶን ጋር ይሄድ ነበር» ተብሎም ተጽፏል /መሳ.13÷24/፡፡ ይሁን እንጂ የ #እግዚአብሔር መንፈስ «ሞልቶታል» የተባለ ግን ማንም አልነበረም፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ግን በ #መንፈስ_ቅዱስ የተሞላ ነበር፡፡ የከበረ እና ታላቅ በመሆኑ አንዱ ምክንያት ይህ ነው፡፡
#መንፈስ_ቅዱስ የተሞላው ግን መቼ ነበር? በመንፈስ ቅዱስ የተሞላው ገና በማኅፀን ሳለ እናቱ ኤልሳቤጥ የእመቤታችንን የሰላምታ ድምፅ በሰማችበት ቅፅበት ነው፡፡
«ኤልሳቤጥም የ #ማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ፤ ፅንሱ በማኅፀኗ ዘለለ፤ በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ መላባት» /ሉቃ.1÷14/
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል «ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ ይመላበታል» ብሎ የተናገረው በዚህን ጊዜ ተፈጽሟል፡፡

2. ተጋድሎው
#መንፈስ_ቅዱስ ስጦታ በእኛ ሕይወት ፍሬ ሊያፈራ የሚችለው እኛ በድርጊታችንና በተጋድሎአችን ስንጠብቀው፣ ስንንከባከበውና ስንሠራበት ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ይህንን በሚገባ አድርጓል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ ያደገው በበረሃ ውስጥ፣ በብሕትውና /በብቸኝነት/፣ የግመል ጠጉር እየለበሰ፣ አንበጣ እና የበረሃ ማር ብቻ እየተመገበ ነው፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ እንዲህ ብለዋል «እርሱ በበረሃው ውስጥ ጸሎትና ተመስጦን፣ ድፍረትን እና ፍርሃት አልባነትን፣ ጥንካሬን እና እምነትን ተምሯል፡፡ #እግዚአብሔር #እመቤታችንን አምላክን ፀንሣ ለመውለድ በቤተ መቅደስ እንዳዘጋጃት እርሱን ደግሞ ለመንገድ ጠራጊነት ተልእኮው በበረሃ አዘጋጅቶታል፤ እኛም የእነዚህ ነገሮች ባለቤት ለመሆን የብቸኝነትና የትህርምት ጊዜ የምናሳለፍበት የየራሳችን በረሃ ያስፈልገናል፡፡»

#ቅዱስ_ዮሐንስ መዓርጋት
ቅዱስ ዮሐንስ በርካታ መዓርጋት አሉት፤ የተወሰኑትን ቀጥለን እንመለከታለን፤
#መጥምቅ /መጥምቀ መለኮት/፡- #ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስን በማጥመቁ
#ነቢይ ከእኔ በፊት የነበረውና ከእኔ የሚበልጠው ይመጣል ብሎ ትንቢት በመናገሩ
#ካህን ሕዝቡን በማጥመቁ
#ወንጌላዊ ያስተማረው ትምህርት እንደነቢያቱ ይመጣል ይወለዳል ብቻ ሳይሆን መጥቷል፣ ተወልዷል፣ እነሆ በመካከላችሁ ቆሟል የሚል ለመሆኑ፤ እንደ ነቢያቱ ለቅጣት ምርኮን፣ ለስጦታ /ደስታ/ ምድረ ከነዓንን ሳይሆን ለቅጣት የዘለዓለም ሕይወትን፤ ለስጦታ መንግሥተ ሰማያትንና ገሃነመ እሳትን ማስተማሩ፤ የሥነ ምግባር ትምህርቱም እንደ ወንጌል ትሩፋትን የሚሰብክ በመሆኑ
#ርእሰ_ዓውደ_ዓመት ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ በብሉይ ኪዳን እና በሐዲስ ኪዳን መሸጋገሪያ ላይ የነበረ ነቢይ በመሆኑ የዓመቱ መጀመሪያና የዘመን መለወጫ በዓል በሆነው መስከረም አንድ ቀን የእርሱ መታሰቢያ እንዲደረግበት፣ በዓሉም «ቅዱስ ዮሐንስ» ተብሎ እንዲጠራ አባቶቻችን ወስነዋል፡፡ ቅዱስ ያሬድም በድጓው «ውስተ ርእሰ ዓውደ ዓመት ተጽሕፈ ተዝካርከ፤ ባርከኒ እንሣእ በረከተከ»፤ «መታሰቢያህ በርእሰ ዓውደ ዓመት ተጻፈ፤ በረከትህን አገኝ /እውሰድ/ ዘንድ «ባርከኝ» ብሎ ምሥጋናና ጸሎት ደርሷል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ መልክአ ዮሐንስ ደግሞ «ርእሰ ዓውደ ዓመት ዮሐንስ ወላዴ መጥቅዕ ወአበቅቴ» ይለዋል /ሠላም ለሥዕርተ ርእስከ/፡፡ «የመጥቅዕ እና የአበቅቴ ወላጅ፣ አስገኚ» ማለት ነው፡፡ ይህም ስም የተሰጠው የዓመቱ ክብረ በዓላት የሚውሉባቸው ቀናትና ዕለታትን ለማስላት የሚጠቅሙት መጥቅዕ እና አበቅቴ የሚባሉት ቁጥሮች በዚሁ በመስከረም አንድ ቀን ስለሚወጡ /ስለሚስሉ/ ነው፡፡
#ሰማእት /ምስክር/፡- ስለ #ጌታችን አምላክነትና መድኃኒትነት እንዲሁም ስለ እውነት ስለመሰከረ፤ በመጨረሻም በአላውያን ነገሠታት እጅ ስለ ተገደለ፡፡

ከእነዚህ ሁሉ ስሞች የሚበልጠው ግን መጥምቅ /መጥምቀ መለኮት/ የሚለው ነው፡፡ ምክንያቱም ቅዱስ ዮሐንስ ካደረጋቸውና ከሆናቸው ነገሮች ሁሉ የሚበልጠው #አምላክን ማጥመቁ ነው፡፡ #ጌታችንም ስለ እርሱ ክብር በተነገረ ጊዜ «እውነት እላችኋለሁ፤ ሴቶች ከወለዱአቸው ወገን ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም…» በማለት ይህንን ስያሜ አጽድቆለታል፡፡

#ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ ለእኛ

ቅዱስ ዮሐንስ በዘመኑ የነበሩ ሰዎችን ገሥጾና አስተምሮ ወደ #እግዚአብሔር አቅርቧቸዋል፡፡ እኛስ በዚህ ዘመን ያለን ሰዎች ከእርሱ ምን እንጠቀማለን? ሁለት ነገሮችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
1. ያስተምረናል፡፡
2. ያማልደናል፡፡

1. ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ያስተምረናል
ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ በቃሉ /በስብከቱ/፣ በሕይወቱ እና በአገልግሎቱ ዛሬ ድረስ ያስተምረናል፡፡
#በስብከቱ /በቃሉ/ ያስተምረናል
አንድ ሰው የድኅነትን ጸጋ /ስጦታ/ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለመቀበል ሦስት ነገሮች ያስፈልጉታል፡፡ እነዚህም እምነት፣ ምሥጢራትን መካፈል እና ምግባር ናቸው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በእነዚህ በሦስቱም ዙሪያ ትምህርቶችን ያስተምረናል፡፡

#እምነት፡- ቅዱስ ዮሐንስ «አብ ወልድን ይወዳል፤ ሁሉንም ነገር፤ በእጁ ሰጥቶታል፡፡ በወልድ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ በወልድ የማያምን ግን የ #እግዚአብሔር ቁጣ በእርሱ ላይ ይሆናል እንጂ ሕይወትን አያይም» እያለ ምሥጢረ ሥላሴን ምሥጢረ ሥጋዌን ያስተምረናል፤ ካላመንም የዘለዓለም ሕይወት እንደሌለን ይነግረናል፡፡
ምስጢራትን መካፈል፡- ቅዱስ ዮሐንስ «መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ፡፡»፣ «ከእኔ በኋላ የሚመጣው በመንፈስ ቅዱስ እና በእሳት ያጠምቃችኋል»፣ «የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የ #እግዚአብሔር በግ እነሆ» እያለ ምሥጢራትን /ምስጢረ ጥምቀት፣ ምስጢረ ንስሐን እና ምስጢረ ቁርባንን/ እንድንካፈል ያስተምረናል፡፡

#ምግባር፡- «እናንት የእፉኝት ልጆች ለመሆኑ ከሚመጣው ቁጣ እንድታመልጡ ማን መከራችሁ፤ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አፍሩ፤ … እነሆ ምሳር የዛፎችን ሥር ሊቆርጥ ተዘጋጅቷል፤ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል፡፡» እያለ ምግባር እንድንሠራ ያስተምረናል፤ ያስጠነቅቀናል።

ለ/ በሕይወቱ ያስተምረናል
ከቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ በሕይወቱ #እግዚአብሔርን ያስደሰተ፤ «ከሴቶች ከተወለዱ የሚያህለው የለም» የተባለለት ስለሆነ አርአያ ልናደርገው፤ ለዚህ ክብር ያበቃውን ነገር ልንመረምርና በመንገዱ ልንከተለው ይገባናል፡፡ ከሕይወቱ ብዙ ልንማራቸው የሚገቡ ነገሮች ቢኖሩም ጥቂቶቹን ለጊዜው እንመልከት፡-
#ትሁት ነው፡- ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ #ጌታ «ከሴቶች ከተወለዱት ወገን የሚያህለው የለም» እያለ ቢያመሰግነውም እርሱ ግን ያሉትን መልካምና ታላላቅ ነገሮች በሙሉ ችላ ብሎ «እኔ የጫማውን ማሰሪያ ልፈታ የማይገባኝ ነኝ» ይል ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ቅዱስ ያሬድ «ዘወጠነዝ ትርሢተ ክብር ትሕትና ወፍቅር ትሕትና ወፍቅር ርእዮ እበዩ ለዮሐንስ…» እያለ የቅዱስ ዮሐንስ የክብሩ ጌጥ፣ የታላቅነቱ ምንጭ ትሕትናው እና #እግዚአብሔርን ማክበሩ መሆኑን ይገልጻል፡፡ #እመቤታችን በጸሎቷ «ትሁታንን ግን ከፍ ከፍ አደረጋቸው» /ሉቃ.1÷52/ እንዳለችው እርሱ ትሁት ሲሆን #እግዚአብሔር ከሁሉ በላይ አከበረው፡፡

የቅዱስ ዮሐንስ ትሕትና ግን ምንጩ ምንድን ነው?
ትሕትና ማለት ምንም ነገር የሌለው መሆን ማለት አይደለም፡፡ #እግዚአብሔር በባሕርይው ትሁት ነው፡፡ #ጌታ «ከእኔ ተማሩ፣ እኔ ትሁት ነኝ» ይላል፡፡ የ #እግዚአብሔር ትሕትና ምንጩ ክቡር፣ ባዕለ ጸጋ መሆኑ ነው፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ ትሕትና ምንጭም ይኸው ነው፤ በእምነትና በምግባር ያጌጠ ባለ ብዙ ፍሬ ባለ ጸጋ መሆኑ ማንም ትሕትናን የሚፈልጋት ቢኖርም ማድረግ ያለበት ይህንኑ ነው፤ ባለብዙ ምግባር፤ ባለ ትልቅ እምነት መሆኑ፤ ያን ጊዜ ትሕትናው አብሮ ይመጣል፡፡

➛ሁለተኛው የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ትሕትና ምንጭ የ #እግዚአብሔርን ማንነትና ባሕርይ በሚገባ ማወቁ፤ የራሱን ማንነቱንና አቅሙንም መረዳቱ ነው፡፡ እኛም ትሕትናን ገንዘብ ልናደርግ ብንወድ የ #እግዚአብሔርን ማንነት፣ ባሕርይ፣ እና ክብር የተቻለንን ያህል ለማወቅ መጣር፤ ራሳችንንም ዘወትር መመርመር፣ ድካማችንን መረዳትና ይህንንም ደግመን ደጋግመን ለራሳችን መንገር አለብን፡፡
ጸጋውን ተጠቅሞ ፍሬ አፍርቷል፡ – ቅዱስ ዮሐንስ በእናቱ ማኅፀን ሳለ #መንፈስ_ቅዱስ መልቶበት ነበር፡፡ እርሱም ይህንን ጸጋውን አትርፎበታል፤ሕዝቡም ካህናቱም አመጸኞች በነበሩበት በዚያ አስከፊ ዘመን /ሐዋ.5÷3ዐ-39/ ጻድቅ ሆኖ ተገኝቷል፤ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም በረከት ሆኖ ነበር፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ እንዳሉት ለዚህ የበቃው «የበረሃ እና የተራሮች ልጅ» በመሆኑና በብህትውና /በብቸኝነትና/ እና በትህርምት በመኖሩ ነው፡፡
እያንዳንዳችን ከጥምቀታችን ቀጥሎ በሚፈጸምልን ምሥጢረ ሜሮን አማካኝነት #መንፈስ_ቅዱስ ያድርብናል፡፡ ይህንን ተጠቅመን ሥራ ለመሥራት እኛም እንደ መጥምቁ የራሳችን በረሃ ያስፈልገናል፤ በትህርምትና ራስን በመግዛት መኖር አለብን፡፡
ይህንን ማድረግ የሚገባቸውና የሚችሉት በገዳም ያሉ ሰዎች ብቻ አይደሉም፡፡ በዓለም የምንኖር ሰዎችም ብቻችንን የምንሆንበትና በጸሎት፣ በተመስጦ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ፣ ራሳችንን በመመርመር የምናሳልፈው ጊዜ በመመደብ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በወጣትነት ዘመኑ እንዳደረገው መኖሪያ ቤቶቻችንን ገዳማት ማድረግ እንችላለን፡፡ ሁኔታዎችን እያመቻቸን ወደተለያዩ ገዳማት እየሄድን ጊዜ ማሳለፍም ጠቃሚ ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ምግባችንን፣ መጠጣችንን እና ልብሳችንን በልክ እያደረግን መጥምቁን ባለ ብዙ ፍሬ በሆነበት ጎዳናው ልንከተለው ይገባናል፡፡

በአግልግሎቱ ያስተምረናል፡ -ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ከቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ አገልግሎት ልንማራቸው የሚገቡ በርካታ ቁም ነገሮች አሉ በማለት የሚከተሉትን ይዘረዝራሉ፡፡
ቅድስ ዮሐንስ ያገለገለው ለአጭር /ከስድስት ወራት ብዙ ላልበለጠ/ ጊዜ ብቻ ቢሆንም በርካታ ሥራዎችን ሠርቶ አልፏል፡፡ እኛም አገልግሎታችንን ልንመዝነው የሚገባን በርዝመቱ ሳይሆን በጥልቀቱ፣ በውጤታማነቱ፣ በሚያፈራው ፍሬ እና በሚያመጣው ለውጥ ነው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ሲያገለግል ዓላማው ሰዎችን ከ #እግዚአብሔር ጋር ማገናኘት እንጂ ሰዎችን በእርሱ ዙሪያ መሰብሰብና መክበር አልነበረም፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ እንደሚነግረን «ከኢየሩሳሌም፣ ከመላው ይሁዳ፣ በዮርዳኖስ ዙሪያ ባለው ነገር ሁሉ ሰዎች ወደ እርሱ ይጎርፉ ነበር፡፡» /ማቴ.3÷5-6/ እርሱ ግን «እኔ በውኃ ለንስሐ አጠምቃችኋለሁ፤ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፡፡» እያለ ሰዎቹ እርሱን እንዲከተሉ ሳይሆን የ #ጌታችንን መምጣት ተስፋ እንዲያደርጉ የሚያደርግ ትምህርት ያስተምራቸው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት የቅዱስ ዮሐንስ ደቀመዛሙርት በኋላ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብተዋል፡፡

የመጀመሪያዎቹ #ጌታችንን የተከተሉት ደቀመዛሙርት የዮሐንስ ደቀመዛሙርት ነበሩ፡፡ ስለዚህ በዚህ ዘመን መታጀብ /በሕዝብ መከበብ/ ለሚያስደስተን የ #እግዚአብሔርን ሳይሆን የእኛን ተከታዮች እንደ ፈሪሳውያን ለምንፈልግ አገልጋዮች ትልቅ ተግሳጽ ነው፡፡
«በማግስቱ ዮሐንስ ከሁለቱ ደቀመዛሙርቱ ጋር እንደገና በእዚያው ቦታ / #ጌታችን በተጠመቀበት/ ቦታ ነበር፡፡ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም በዚያ ሲያልፍ አይቶ «እነሆ የ #እግዚአብሔር በግ» አለ ሁለቱ ደቀመዛሙርትም ይህን ሲናገር ሰምተው #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስን ተከተሉት» /ዮሐ.1÷35-37/

የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍም በርካታ የዮሐንስ ደቀመዛሙርት የነበሩና የእርሱን ጥምቀት የተጠመቁ ሰዎች በቀላሉ ወደ ክርስቲያኖች ማኅበር እንደተቀላቀሉ ይነግረናል፡፡ /ሐዋ.18÷24-19፣ 6፣ 13÷24/
ራሱም ይህንን አቋሙን እንዲህ በማለት ልብ በሚነኩ ቃላት እንዳጋለጠው ወንጌላዊው ዮሐንስ በወንጌሉ መዝግቦታል፡፡
ሰዎች ወደ ቅዱስ ዮሐንስ መጥተው «መምህር፣ በዮርዳኖስ ከአንተ ጋር የነበረው፣ ስለ እርሱም የመሰከርክለት … ሰው ሁሉ ወደ እርሱ እየሄዳ ነው» ባሉት ጊዜ እንዲህ ሲል መለሰ «ከላይ ካልተሰጠው በቀር ማንም አንዳች ሊቀበል አይችልም፡፡ «እኔ #ክርስቶስ አይደለሁም፤ ነገር ግን ከእርሱ በፊት ተልኬአለሁ» እንዳልሁ እናንተ ራሳችሁ ትመሰክራላችሁ፡፡ ሙሽራይቱ የሙሽራው ነች፡፡ ድምፁን ለመስማት በአጠገቡ የሚቆመው ሚዜ ግን የሙሽራውን ድምፅ ሲሰማ እጅግ ደስ ይለዋል፤ ያ ደስታ የእኔ ነው፤ እርሱም አሁን ተፈጽሟል፡፡ እርሱ ሊልቅ፤ እኔ ግን ላንስ ይገባል፡፡»
እውነት ነው፡፡ ሙሽራይቱ ቤተ ክርስቲያን የሙሽራው የ #ክርስቶስ ነች፡፡ አገልጋዮች ሚዜ ናቸው፡፡ ሥራቸውም ሙሸራይቱን ወደ ሚዜው ማቅረብ ነው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ሲያገለግል በድፍረት ነው፡፡ እርሱ በነበረበት ወቅት ሔሮድስ አንቲጳስ የወንድሙን ሚስት አግብቶ የሚገሥጸው ጠፍቶ ነበር፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ግን በበረሃው ሳለ ደፋር፣ ለሰው ፊት የማያደላ፣ መሆንን ተምሮ ነበርና ገብቶ ገሠፀው፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ እንዲህ ይላሉ «ከአገልግሎቱ ሊያዘገየው ወይም ሊያስተጓጉለው የሚችል ቢሆንም እንኳን ተገቢውን ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ አላለም፡፡ አስተሳሰቡም እንዲህ ነው « #እግዚአብሔር እንዳገለግል ፈቃድ ከሆነ አገለግላለሁ፤ ካልሆነም የእርሱ ፈቃዱ ይሁን፡፡ ዋናው ነገር እውነትን መመስከር ነው» ቅዱስ ዮሐንስ ስለእውነት ራሱን አሳልፎ ቢሰጥም ከሞተ በኋላም ቢሆን የትምህርቱ ድምፅ ሄሮድስን ሲወቅሰው ኑሯል፡፡»
እውነት ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ከሞተ በኋላም ቢሆን ራሱ አስራ አምስት ዓመት ዙራ አስተምራለች፡፡ ሔሮድስም ከሞት ተነሥቶ የሚመጣ እስኪመስለው ድረስ ይፈራው እንደበር ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ ጽፏል «በዚያን ጊዜ የአራተኛው ክፍል ገዢ የነበረው ሄሮድስ /አንቲጳስ/ ስለ #ኢየሱስ ዝና ሰማ፤ ባለሟሎቹንም እንዲህ ከሆነ መጥምቁ ዮሐንስ ከሞት ተነሥቶ መጥቶአል ማለት ነው፤ ይህ ሁሉ ድንቅ ተዓምራት በእርሱ የሚደረገውም ለዚህ ነው» አላቸው፡፡ /ማቴ.14÷1-2/፡፡

#ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ_ያማልደናል

ቅዱስ ዮሐንስ ዛሬ እኛን #እግዚአብሔር ለወዳጆቹ በሰጠው ቃል ኪዳን መሠረት በጸሎቱ ከ #እግዚአብሔር ያማልደናል፡፡
ቤተ ክርስቲያንም ዘወትር «ሰአል ለነ ዮሐንስ» «ዮሐንስ ሆይ ለምንልን»፤ ትለዋለች፤ «በአንተ ዮሐንስ መጥምቅ መሐረነ» «ስለ ዮሐንስ ስትል ማረን» እያለችም ትጸልያለች፡፡ እኛም ገድሉንና፣ መልኩን በመጸለይ፣ መታሰቢያው በሚደረግበት ጊዜም በስሙ ዝክር በመዘከር፣ ቸርነት በማድረግ በረከትን ለማግኘት ልንተጋ ይገባናል፡፡
«ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ውኃ ብቻ በደቀመዛሙርቶቼ ስም ቢያጠጣ፤ እውነት እላችኋለሁ ዋጋው አይጠፋበትም» /ማቴ.10÷42/
«የቅዱስ ዮሐንስ ጸሎቱና በረከቱ ይደርብን! አማላጅነቱ ይደረግልን»

#ወስብሐት_ለእግዚአብሔር

ምንጭ፡­­ ©ማኅበረ ቅዱሳን
#መስከረም_4

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም አራት በዚህች ቀን #ወንጌላዊው_ቅዱስ_ዮሐንስ ልደቱ ነው፣ የድባው #አቡነ_ሙሴ እረፍታቸው ነው፣ #ነቢዩ_ኢያሱ_ወልደ_ነዌ አረፈ፣ #አባ_መቃርስ_ሊቀ_ዻዻሳት አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዮሐንስ_ወንጌላዊ

መስከረም አራት በዚህች ዕለት ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ከእናቱ ማርያም ባውፍልያ ከአባቱ ዘበዴዎስ የተወለደበት ዕለት እንደሆነ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌልን ለመስበክ ዕጣ የደረሰው እስያ ስለነበር ደቀ መዝሙሩን አብሮኮሮስን አስከትሎ ሄደ፡፡ ይኽችውም ኤፌሶን በጥንቱ በታናሽ እስያ በዛሬው የቱርክ ግዛት ውስጥ ከተማ ናት፡፡ ዛሬ ኢያዞሎክ ተብላ የጥንት ታሪኳ ጠፍቷል፡፡ አስቀድሞ ቅዱስ ጳውሎስ ወንጌልን ሰብኮባታል፡፡ ደቀ መዝሙሩን ቅዱስ ጢሞቴዎስንም በከተማዋ ላይ ኤጲስቆጶስ አድርጎ ሾሞት ነበር፡፡ እርሱም በግፍ እስከተገደለበት ጊዜ ድረስ ቅዱስ ዮሐንስን እየረዳው በከተማዋ ብዙ አገልግሏል፡፡ በኋላ ግን በግፍ ገድለውታል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ወደ ኤፌሶን ለመሄድ በመርከብ ሲሳፈር መርከቡ በማዕበል ተሰበረ፡፡ ደቀ መዝሙሩን አብሮኮሮስን መዕበሉ ወደ አንዲት ደሴት አደረሰው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ግን በመርከቡ ስባሪ ተንጠልጥሎ በባሕሩ ማዕበል መካከል 40 ቀንና 40 ሌሊት ከኖረ በኋላ ማዕበሉ ተፍቶ አብሮኮሮስ ካለበት ደሴት አደረሰውና ተያይዘው ኤፌሶን ከተማ ገቡ፡፡ የከተማይቱም ሰዎች እጅግ ክፉዎች ስለነበሩ መጀመሪያ ላይ ቅዱስ ወንጌልን መስበክ አልቻሉም ነበር፡፡ እነርሱም እጅግ ክፉዎች መሆናቸውን ስላወቀ ቅዱስ ዮሐንስ ገና ዕጣው ሲደርሰው በሀዘን አልቅሶ ነበር፡፡ አሁንም ከተማው በገቡ ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ ምክንያት በመፍጠር ሮምና ለምትባል ሴት የውሽባ ቤቷ እሳት አንዳጅ ሆኖ አብሮኮሮስም ዕቃ አጣቢ ሆነው ተቀጠሩ፡፡ የቀጠረቻቸው ሴትም እጅግ ታሠቃያቸው ጀመር፡፡ ባሮቿ እንደሆኑ ተስማምተው ስለጻፉላት ትደበድባቸውም ነበር፡፡

እነርሱም በታላቅ ጉስቁልና ውስጥ እየኖሩ እያለ በአንዲት ዕለት የአገረ ገዥው ልጅ ለመታጠብ ወደ ውሽባው ቤት ገባ፡፡ በውሽባ ቤቱም የሰይጣን ኃይል ስለነበረበት የመኰንኑን ልጅ አንቆ ገደለው፡፡ የአገሪቱም ሰዎች ሁሉ ለሞተው የመኰንን ልጅ ሊያለቅሱ ሲሰበሰቡ ቅዱስ ዮሐንስም አብሮ ቆሞ ሲመለከት ሮምና መጥታ "በጌታዬ ልጅ ሞት ልትደሰት መጣህን" እያለች ረገመችው፡፡ እርሱም "አይዞሽ አትዘኚ" አላትና ወደ ሞተው ልጅ ቀርቦ በመስቀል ምልክት ካማተበበት በኋላ በፊቱ እፍ አለበት፡፡ የሞተውም ልጅ ድኖ ተነሣ፡፡ የሀገሪቱም ሰዎች እጅግ ደነገጡ፡፡ ሮምናም ደንግጣ " #እግዚአብሔር የሚሉት አምላክ አንተ ነህን" ብላ ጠየቀችው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም "በፍጹም እኔ አምላክ አይደለሁም፣ እኔ የእርሱ አገልጋዩና ሐዋርያው ነኝ እንጂ" አላት፡፡ ሮምናም ስለበደለቻቸው በደል ሁሉ መሪር ዕንባን እያለቀሰች ይቅር እንዲሏት ለመነቻቸው፡፡ እነርሱም አረጋጉዋት፡፡ ከሕዝቡም ውስጥ ብዙዎቹ በ #ጌታችን አመኑ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ሌሎች ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን እያደረገ ወንጌልን እየሰበከ ከጣዖት አገልጋዮች በቀር ሁሉንም አሳምኖ አጠመቃቸው፡፡ አገልጋዮችን ኤጲስቆጶሳትን፣ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ከሾመላቸው በኋላ ወደ ሌሎች አቅራቢያ አገሮች ሄደ፡፡

በመጨረሻም በከሃዲውና በጨካኙ በድምጥያኖስ ዘመን በጣዖት አምላኪዎች ተከሶ ለፍርድ ቀረበ፡፡ በፈላ ውኃ ካሠቃዩት በኋለ በፍጥሞ ደሴት አጋዙት፡፡ በዚያም ሳለ ራእዩን ተመልክቶ ጻፈው፡፡ ድምጥያኖስም ከተገደለ በኋላ ከግዞቱ ተመልሶ ሦስቱን መልእክታቱንና ቅዱስ ወንጌሉን ጽፏል፡፡ #ጌታችንም አስቀድሞ ሞትን እንደማይቀምስ ለዮሐንስ ቃል ገብቶለት ነበርና (ዮሐ 21፡22) ጥር 4 ቀን እንደ ኤልያስና ሄኖክ ሞትን እንዳያይ ወደ ብሔረ ሕያዋን ወስዶታል።

#ጌታችን ለዮሐንስ ያልነገረው እርሱም ያላስተማረው ምሥጢር የለም፡፡ ወንጌሉን መጻፍ ሲጀምር "በመጀመሪያ ቃል ነበረ፣ ቃልም በ #እግዚአብሔር ዘንድ ነበረ…" ብሎ የ #ጌታችን ነገር ተመራምሮ ለመድረስ ሲል በመሀል መልአኩን በዮርዳኖስ ባሕር ላይ ሲሄድ አገኘው፡፡ መልአኩም የዮርዳኖስን ባሕር በእንቁላል ቅርፊት እየጨለፈ ወደ ውጭ ሲያፈስ ተመለከተው፡፡ ዮሐንስም ተገርሞ "ምን ማድረግህ ነው" አለው፡፡ መልአኩም "የዮርዳኖስን ባሕር ቀድቼ እየደፋሁ ልጨርሰው ነው" ሲለው ዮሐንስም መልሶ "ታዲያ በእንቁላል ስባሪ ነውን?" አለው፡፡ መልአኩም "አዎን" አለው፡፡ ዮሐንስም "በከንቱ ደከምክ" አለው፡፡ ይህን ጊዜ መልአኩም መልሶ "አንተስ እንጂ ደግሞ የአምላክን መገኘት፣ አኗኗሩንም ተመራምረህ በጥበብ ለማግኘት ብለህ 'በመጀመሪያ ቃል ነበረ፣ ቃልም በ #እግዚአብሔር ዘንድ ነበረ..' ብለህ ጀምረህ የለምን? አንተ #ጌታን ተመራምረህ ካገኘህና ከደረስክበት እኔም የዮርዳኖስን ወንዝ በዚህ እንቁላል ቅርፊት ቀድቼ እጨርሰዋለሁ" አለው፡፡ ዮሐንስም ይህን ጊዜ ደንግጦ ዝቅ ብሎ "ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ…" ብሎ ሀሳቡን ለወጠና ሌላ ታሪክ ቀጠለ፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ #ጌታችንን እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ በመከተሉ ክርስቲያኖችን ሁሉ ወክሎ #እመቤታችንን በአደራ የተቀበለ እርሱም ለእመቤታችን በአደራ የተሰጠ ሲሆን #እመቤታችንን ከወሰዳት በኋላ ለ16 ዓመት እየተንከባከበ ጠብቋታል፡፡ እናቱም በሕፃንነቱ ስለሞተች #እመቤታችን ናት እየተንከባከበች ያሳደገችው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ በመልኩም ከ #ጌታችን ጋር ይመሳል ነበር፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ሥዕል የመሳል ተሰጥኦም ነበረው፡፡ #ጌታችን በተሰቀለበት ዘመን የነበረው ጢባርዮስ ቄሳር ልጁ በሽተኛ ነበር፡፡ የ #ጌታችንን የማዳን ሥራ እየሰማ እነ ጲላጦስም ስለ #ጌታችን የሚጽፉለትን ይሰማ ስለነበር ልጁን ከ #ጌታችን መቃብር ላይ እንዲያኖሩለት ላከው፡፡ ልጁም ፈጥኖ ተፈወሰለት፡፡ ጢባርዮስ ቄሳርም በልጁ መዳን ምክንያት የ #ጌታችንን ውለታ ማስቀመጥ ፈልጎ የ #ጌታችንን ሥዕሉን የሚሥልለትን ሲያጠያይቅ ዮሐንስን አገናኙት፡፡ ዮሐንስም #ጌታችንን ልክ በዕለተ ዓርብ እንደተሰቀለ አድርጎ በመሣል ለጢባርዮስ ቄሳር ሰጠው፡፡ ሲሥለውም በመጀመሪያ #ጌታችንን ልክ እንደተሰቀለ አድርጎ ራቁቱን ነበር የሳለው፡፡ ዮሐንስ የሳለው የ #ጌታችን ሥዕልም አፍ አውጥቶ "በመጀመሪያ አይሁድ በኢየሩሳሌም ራቁቴን ሰቀሉኝ፣ አሁን ደግሞ አንተ ድጋሚ በሮም ራቁቴን ትሰቅለኝን?" ብሎ ተናገረው፡፡ ዮሐንስም እጅግ ደንግጦ "እንዴት አድርጌ ልሳልህ?" ብሎ የሳለውን ሥዕል ቢጠይቀው ሥዕሉም "ከለሜዳ አልብሰህ ሳለኝ" አለው፡፡ ዮሐንስም እንዳለው ከለሜዳ አልብሶ ከሳለው በኋላ ሥዕሉን ትኩር ብሎ ተመልክቶ ቢስመው ከንፈሩ አንድ ቀን ተኩል ያህል ተጣብቆ ቆይቷል፡፡ ዛሬም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የምትጠቀምባቸውን የ #ጌታችንን ስነ ስቅለት የሚያሳዩ ሥዕሎች መገኛቸው ይህ ወንጌላዊው ዮሐንስ የሳለው ሥዕል ነው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ በተለያዩ ስሞች ይጠራል፦
በሕይወቱና በኑሮው ሁሉ #ጌታችንን ለመምሰል ይጥር ነበርና ጌታችንም እጅግ ይወደው ስለነበር "#ፍቁረ_እግዚእ" ተባለ፣ የታላቁ ያዕቆብ ታናሽ ወንድም ስለሆነና አባቱም ዘብድዮስ ስለሚባል "#ዮሐንስ_ወልደ_ዘብድዮስ" ተባለ፣ ለ #ጌታችን ባለው ቅናትና ከወንድሙ ጋር ሆነው ባሳዩት የኃይል ሥራ እንዲሁም የ #ጌታችንን አምላክነት በመግለጡ "#ወልደ_ነጎድጓድ" ተብሏል፡፡ ነገረ መለኮትን ከሌሎቹ በበለጠ ሁኔታ አስፍቶና አምልቶ በማስተማሩ "#ነባቤ_መነኮት ወይም #ታኦሎጎስ" ተብሏል። ኃላፊውንና መጻዒውን ጊዜ በራእዩ ስለገለጠ "#አቡቀለምሲስ" ተባለ፣ ይህም በግሪክኛ #ባለራእይ ማለት ነው፡፡ የጌታችንን መከራ መስቀሉን እያስታወሰ 70 ዘመን ሙሉ እያለቀሰ ስለኖረና ፊቱም በሀዘን ስለተቋጠረ "#ቁጹረ_ገጽ" ተብሏል፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሐዋርያው በቅዱስ ዮሐንስ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ሙሴ_ዘድባ

በዚህች ቀን የድባው አቡነ ሙሴ እረፍታቸው ነው። የትውልድ አገራቸው እስራኤል ልዩ ቦታው ቃና ዘገሊላ ነው። ጽንሰታቸውን ቅዱስ ሩፋኤል መጋቢት 8 ቀን ሲያበስር ልደታቸውን ደግሞ ቅዱስ ገብርኤል ታኅሣሥ 8 ቀን የመወለዳቸውን ብሥራት ተናግሯል፡፡ ሲወለዱ ሚካኤል ወገብርኤል በሰው አምሳል ተገልጠው "የ #እግዚአብሔር ሰው ሙሴ" ብለው ስም አወጡላቸው፡፡

በተወለዱም በ40ኛ ቀናቸው ከተጠመቁ በኋላ ቅዱስ ሚካኤል አቅፎ ይዟቸው #ጌታችን በቅዱሳን እጆቹ አቁርቧቸዋል፡፡ በእሳቸውም ምክንያት በዚያች ዕለት በቤተ ክርስቲያን የነበሩት ሰዎች ሁሉ ክቡራን በሆኑ በ #ጌታችን እጆች ቆርበዋል፡፡ የአቡነ ሙሴ አባታቸው ዮስጦስ ለሐዋርያው ናትናኤል አጎቱ ነው፡፡ እናታቸው ጵርስቅላ ጌታችን በሠርግ ቤት ተገኝቶ ውኃውን ወደ ወይን የለወጠለት የዶኪማስ ልጅ ናት፡፡

#ጌታችን ወደ ዶኪማስ ቤት ሠርግ ተጠርቶ የሄደው ዶኪማስ ናትናኤልን ‹‹ሠርጌን እንዲባርክልኝ #ጌታ_ኢየሱስን ከእናቱ ጋር ጥራልኝ›› ብሎት ነው፡፡ #ጌታችን በስብከቱ ‹‹ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልሏቸው›› ብሎ ብሎ ካቀፋቸውና
ካስተማረባቸው ሕፃናት አንዱ ይኽ አቡነ ሙሴ ናቸው፡፡ ጻድቁ ዋሻዎችን እየፈለፈሉ የቅዱሳን ሐዋርያትን ዐፅም በክብር ያስቀምጡ ነበር፡፡ የተሠወሩ አብያተ ክርስቲያናትን በማነጽ ወንጌልን በማስተማር ብዙ መከራ የተቀበሉ አባት ናቸው፡፡ በ #እግዚአብሔር ፈቃድ በግብፅ "ንጉሥ አንስጣስዮስ" ተብለው 40 ዓመት በንግሥና እና በድንግልና ኖረዋል፡፡

ከዚህም በኋላ በ #እግዚአብሔር ፈቃድና ትእዛዝ በመልአክም ምክር ዮናኒ የተባለውን ሌላ ሰው አንግሠው ወደ አስቄጥስ ገዳም ገብተው መነኮሱ፡፡ በገዳሙም በታላቅ ተጋድሎ ከኖሩ በኋላ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የእኛ ጳጳስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ሲያርፉ በቅዱስ አትናቴዎስ ተሹመው 2ኛው የኢትዮጵያ ጳጳስ ሆነው ‹‹አቡነ ሰላማ ካልዕ›› ተብለው ተሾመው ወደ አገራችን መጡ፡፡ ከመሾማቸው በፊት አባቶቻችን አቡነ አትናቴዎስን ‹‹ጳጳስ ይላኩልን›› ብለው መልእክት ሲልኩባቸው አቡነ አትናቴዎስም ወደ አስቄጥስ ገዳም በመሄድ #እግዚአብሔርን በጸሎት ቢጠይቁት የታዘዘ መልአክ መጥቶ ‹‹የ #እግዚአብሔር ሰው ሙሴን ላክላቸው›› አላቸው፡፡ መነኮሳቱም ሁሉ እንዲሁ አሉ፡፡ ከዚህም በኋላ ሲሾሙ ሚካኤልና ገብርኤል በወርቅ ወንበር ላይ አስቀምጠዋቸው ‹‹ይገባዋል ይገባዋል›› ብለው ቅብአ ክህነት ቀብተዋቸዋል (ጵጵስና ሾመዋቸዋል፡፡) አቡነ ሙሴም ከተሾሙ በኋላ 14000 መነኮሳትን አስከትለው ወደ ቅድስት አገራችን መጡ፡፡ አቡነ ሙሴ ንግሥናቸውን ትተው ወደ ኢትዮጵያ መተው 16 ፍልፍል ቤተመቅደሶችን የሠሩ ሲሆን 8ቱ የተሰወሩ ናቸው፡፡

በገዳማቸው በቅድስቱ ውስጥ ጥልቀቱ የማይታወቅ እጅግ ጥልቅ የሆነ ጉድጓድ አለ፡፡ በውስጡም ስውራኑ አብያተ ክርስቲያናት ይገኙበታል፡፡ ከአንድ ወጥ ድንጋይ የተቀረጸውና ፍልፍል የሆነው የገዳማቸው የቤተልሔሙ ስፋት ሜትር ከሃያ ሲሆን ጣራው እንደ አቡነ አሮን ክፍት ሆኖ ሳለ ዝናብ ግን አይገባበትም፡፡ ዝናብ የማያስገባው የቀዳዳው ስፋት አንድ ሜትር በአንድ ሜትር ነው፡፡ ጻድቁ በሀገራችንም ዕፁብ ድንቅ የሆኑ ብዙ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናትን በማነጽና ወንጌልን በማስተማር ብዙ ደክመዋል፡፡ በተለይም በዋናነት የሚታወቁት በሰሜን ወሎ አውራጃ ወልድያ ወረዳ መቄት ልዩ ቦታው ገረገራ የሚገኘው ‹‹አዲስ አንባ ዋሻ መድኃኔዓለም›› እና መጀመሪያ እንደመጡ ያረፉባት ‹‹ድባ ማርያም›› ይጠቀሳሉ፡፡

ይህችውም ድባ ማርያም ገዳም ታላቁ አባት አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ የመነኮሱባት ናት፡፡ ጻድቁ አቡነ ሙሴ መስከረም 4 ቀን ጌታችን ቃልኪዳን ሲገባላቸው እነዚህን ሁለት ገዳማቸውን ‹‹እንደ አስቄጥስ ገዳም እንደ አቡነ እንጦንስ ማኅበር ይሁኑልህ›› ብሏቸዋል፡፡ በገዳማቸው ከሚኖሩት ቅዱሳን ውስጥ 400 ወንዶች መነኮሳትና 200 ሴቶች መነኮሳያት እንደተሰወሩ መጽሐፈ ገድላቸው ይናገራል፡፡

ጻድቁ ሌላው ለየት የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር ገና በእናቷ ማኅፀን ሳትፀነስ የቅድስት አርሴማን ጽላት ያሠሩላት መሆናቸው ነው፡፡ ቁመቱ 2 ሜትር ከ70 የሆነ ግሩም ቤተ መቅደስም ፈልፍለው አንጸውላታል፡፡ #ጌታችንም የሰማዕቷን ጽናትና ረድኤት ከቦታው እንደማይለይባቸው ቃል ገብቶላቸዋል፡፡ በቃል ኪዳናቸው የታመኑትን ልጆቻቸውን መተትና መርዝ አይጎዳቸውም፡፡ ይህም #ጌታችን የሰጣቸው ልዩ ቃልኪዳናቸው ነው፡፡ ጻድቁ እንደ አቡነ ዘርዐ ቡሩክ 12 ክንፍ የተሰጣቸው ታላቅ የምሕረት አባት ናቸው፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጻድቁ አቡነ ሙሴ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ነቢይ_ኢያሱ_ወልደ_ነዌ

ኢያሱ ማለት የቃሉ ትርጉም መድኃኒት ማለት ነው፡፡ ኢያሱ መባሉ ስለሁለት ነገር ነው አሜሊቃዊያን ድል አድርጎ እስራኤልን ምድረ ርስት እንዲወርሱ አድርጎልና ሁለተኛው ኢያሱ ለ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ምሳሌ እንዲሆን አስቀድሞ #ጌታ ያውቃልና ይህም ኢያሱ አሕዛብን ድል አድርጎ ምድረ ርስት እንዳስገባቸው የሁላችን #ጌታ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ዲያቢሎስን ድል አድርጎ መንግስቱን አውርሶናልና ኢያሱ በ #ጌታችን ይመሰላል፡፡

ኢያሱ ነቢይ የተወለደው በምድረ ግብጽ በባርነት ከነበሩ እሥራኤላውያን ሲሆን የቀደመ ስሙ አውሴ ይባላል:: ዘመኑ #‎እግዚአብሔር ሕዝቡን ከ215 ዓመታት ባርነት ሊያወጣ የተቃረበበት ነውና ሙሴ ነቢይ ከምድያም ሲመለስ ከመረጣቸው ተከታዮቹ ዋነኛው ኢያሱ ነበር:: እሥራኤል ከባርነት ሲወጡ ሙሴ 80 ዓመቱ ኢያሱ ደግሞ 40 ዓመቱ ነበር። ሕዝቡ ልበ ደንዳና አልታዘዝ ባይ ነበርና ለአርባ ቀናት ብቻ የታሠበላቸውን መንገድ አርባ ዓመታት እንዲሆን አደረጉት:: በዚህ ጊዜ ኢያሱ ከመምህሩ ከሙሴና ከሕዝቡ አልተለየም::

ሊቀ ነቢያት ሙሴ ‎ደብረ ናባው ላይ ባረፈ ጊዜ ሕዝቡን ካህናቱንና ታቦተ ጽዮንን ተረከበ:: በዚህ ወቅትም እድሜው ሠማንያ ዓመት ነበር፡፡ #እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ሾመው፡፡ ሕዝቡንም በትጋት ያገለግል ነበር፡፡ በድንቅ ተዓምራት ዮርዳኖስን ከፍሎ አሻገረ የኢያሪኮን ቅጥር አፈረሰ ጠላቶቹን ድል ነስቶ ምድረ ርስት ከነአንን በ #እግዚአብሔር በኢያሱ መሪነት እንድወርሱ አድርጎል፡፡

ታላቁ ነቢይ ኢያሱ ግን በተወለደ በ120 ዓመቱ መስከረም 3 ቀን በእዚች ዕለት በወገኖቹ መካከል ዐርፎ በያዕቆብ መቃብር ተቀበረ:: እሥራኤልም ለሠላሳ ቀናት አለቀሱለት::
#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በረከቱ ይደርብን እኛንም በቅዱሱ ምልጃ ይማረን ለዘላለሙ አሜን፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_መቃርስ_ሊቀ_ዻዻሳት

ዳግመኛም በዚህች ቀን ቅዱስ አባት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ መቃርስ አረፈ። እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ከቍጥራቸው ውስጥ ነው።

ይህም አባት ከታናሽነቱ ጀምሮ በገድል የተጠመደ ሆነ የምንኲስናንም ልብስ ሊለብስ ወዶ ወደ አስቄጥስ ገዳም ወጣ። በዚያም በመጀመሪያው አባት በአባ መቃርስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መነኰሰ በምንኲስና ያለውንም ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ።

እርሱም ሁልጊዜ መጻሕፍትን የሚያነብና ትርጓሜያቸውንም የሚያስረዳ ሁኗልና በትሩፋት ስራ ከፍ ከፍ ባለ ጊዜ ቅስና ተሾመ። ከእርሱ በፊት የነበረ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤልም በአረፈ ጊዜ ኤጲስቆጶሳቱ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔዱ።

ከእርሳቸውም ጋር ሃይማኖታቸው የቀና ብዙዎች አዋቂዎች ካህናት ነበሩ በአስቄጥስ ገዳም ከሚኖሩ ከታላላቅ መነኰሳትም ጋራ ስብሰባ አድርገው ለዚች ለከበረች ሹመት ስለሚገባው ሰው እየመረመሩ ብዙ ቀኖች ተቀመጡ።

ከዚህም በኋላ የተሻለና ለዚች ለከበረች ሹመት የሚገባ ይህን አባ መቃርስን አግኝተው ሊቀ ጵጵስና ሊሾሙት ሁሉም በአንድ ምክር ተስማው። ስለ ትሩፋቱና ስለ ተጋድሎው በአስቄጥስ ገዳም የሚኖሩ ብዙ መነኰሳት ምስክሮች ሁነዋልና ይዘውትም ሊሔዱ ያለ ፍቃዱ ይዘው አሰሩት እርሱ ግን እንዲህ እያለ ይጮህ ነበር።

እኔ ለዚች ለከበረች ሹመት የማልገባ ነኝ እናቴ ሁለት ባሎችን አግብታ ስለነበር ይህንንም ያለው እንዲተዉት እንጂ እናቱ ግን በአንድ ባል ብቻ የኖረች ሌላ የማታውቅ ንጽሕት እንደሆነች ስለርሷ ብዙዎች ምስክሮች ሁነዋልና። ስለዚህ እሊቀ የተናገረውን ምክንያት አልተቀበሉትም።

ከዚህም በኋላ ወደ እስክንድርያ ወስደው ሊቀ ጵጵስና ሾሙት ከዚያም ወደ ምስር አውጥተው በመዓልቃ በሚገኘው አምላክን በወለደች በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሹመቱ ደብዳቤ በዮናኒ በቅብጥ በአረብ ቋንቋ ተነበበች።

ከዚህም በኋላ በሹመቱ ወራት በጎ ስራ ትሩፋትን ተጋድሎውን አብዝቶ የሚሰራ ሆነ ። ሁል ጊዜም ለህዝቡ #እግዚአብሔርን እንዲፈሩ ያስተምራቸዋል ስለ ነፍሳቸውም ድኀነት ይገሥጻቸው ነበር።

በሹመቱ ወራትም ከራሱ ከሚገባው ከግብሩ ለቤተ ክርስቲያን ይሰጣል ለድኆችና ለችግረኞችም ይመጸውታል እንጂ ከቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ምንም ምን አልወሰደም። በሹመቱም ሃያ ሰባት ዓመት ኖረ #እግዚአብሔርንም አገልግሎ ደስ አሰኝቶ በሰላም በፍቅር ሳለ አረፈ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ለዘላለሙ ከእኛ ጋር ትኑር አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኅ_መስከረም_4#ከገድላት_አንደበት)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_4_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጢሞቴዎስ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን ቢፈልግ መልካምን ሥራ ይመኛል የሚለው ቃል የታመነ ነው።
² እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤ የማይነቀፍ፥ የአንዲት ሚስት ባል፥ ልከኛ፥ ራሱን የሚገዛ፥ እንደሚገባው የሚሰራ፥ እንግዳ ተቀባይ፥ ለማስተማር የሚበቃ፥
³ የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ ነገር ግን ገር የሆነ፥ የማይከራከር፥ ገንዘብን የማይወድ፥
⁴ ልጆቹን በጭምትነት ሁሉ እየገዛ የራሱን ቤት በመልካም የሚያስተዳድር፤
⁵ ሰው ግን የራሱን ቤት እንዲያስተዳድር ባያውቅ፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ይጠብቃታል?
⁶ በትዕቢት ተነፍቶ በዲያብሎስ ፍርድ እንዳይወድቅ፥ አዲስ ክርስቲያን አይሁን።
⁷ በዲያብሎስ ነቀፋና ወጥመድም እንዳይወድቅ፥ በውጭ ካሉት ሰዎች ደግሞ መልካም ምስክር ሊኖረው ይገባዋል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁹ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት።
¹⁰ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል ያጸናችሁማል ያበረታችሁማል።
¹¹ ለእርሱ ክብርና ኃይል እስከዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን።
¹² እየመከርኋችሁና የምትቆሙባት ጸጋ እውነትኛ የእግዚአብሔር ጸጋ እንድትሆን እየመሰከርሁላችሁ፥ የታመነ ወንድም እንደ ሆነ በቈጠርሁት በስልዋኖስ እጅ በአጭሩ ጽፌላችኋለሁ።
¹³ ከእናንተ ጋር ተመርጣ በባቢሎን ያለች ቤተ ክርስቲያን ልጄም ማርቆስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።
¹⁴ በፍቅር አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። በክርስቶስ ላላችሁ ለሁላችሁ ሰላም ይሁን። አሜን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 7
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁴⁴ እንዳየው ምስል አድርጎ ይሠራት ዘንድ ሙሴን ተናግሮ እንዳዘዘው፥ የምስክር ድንኳን ከአባቶቻችን ዘንድ በምድረ በዳ ነበረች፤
⁴⁵ አባቶቻችንም ደግሞ በተራ ተቀብለው እግዚአብሔር በፊታቸው ያወጣቸውን የአሕዛብን አገር በያዙት ጊዜ ከኢያሱ ጋር አገቡአት፥ እስከ ዳዊት ዘመንም ድረስ ኖረች።
⁴⁶ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝቶ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያን ያገኝ ዘንድ ለመነ።
⁴⁷ ነገር ግን ሰሎሞን ቤት ሠራለት።
⁴⁸-⁵⁰ ነገር ግን ነቢዩ፦ ሰማይ ዙፋኔ ነው ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ ለእኔ ምን ዓይነት ቤት ትሠራላችሁ? ይላል ጌታ፥ ወይስ የማርፍበት ስፍራ ምንድር ነው? ይህንስ ሁሉ እጄ የሠራችው አይደለምን? እንዳለ፥ ልዑል የሰው እጅ በሠራችው አይኖርም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_4_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ወወሀብኮሙ ትእምርተ ለእለ ይፈርሁከ። ከመ ያምሥጡ እምገጸ ቅስት። ወይድኀኑ ፍቁራኒከ"። መዝ 59፥4-5።
"ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ፥ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው። ወዳጆችህ እንዲድኑ በቀኝህ አድን፥ አድምጠኝም"።መዝ 59፥4-5።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_4_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዮሐንስ 10
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ወደ በጎች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚወጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነው፤
² በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው።
³ ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰሙታል፥ የራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል።
⁴ የራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል፥ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፤
⁵ ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፥ የሌሎችን ድምፅ አያውቁምና።
⁶ ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን የነገራቸው ምን እንደ ሆነ አላስተዋሉም።
⁷ ኢየሱስም ደግሞ አላቸው፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እኔ የበጎች በር ነኝ።
⁸ ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ ዳሩ ግን በጎቹ አልሰሙአቸውም።
⁹ በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፥ ይገባልም ይወጣልም መሰማርያም ያገኛል።
¹⁰ ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ።
¹¹ መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል።
¹² እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም ይበትናቸዋል።
¹³ ሞያተኛ ስለ ሆነ ለበጎቹም ስለማይገደው ሞያተኛው ይሸሻል።
¹⁴-¹⁵ መልካም እረኛ እኔ ነኝ፥ አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ።
¹⁶ ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምፄንም ይሰማሉ፥ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ።
¹⁷ ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል።
¹⁸ እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም። ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ።
¹⁹ እንግዲህ ከዚህ ቃል የተነሣ በአይሁድ መካከል እንደ ገና መለያየት ሆነ።
²⁰ ከእነርሱም ብዙዎች፦ ጋኔን አለበት አብዶአልም፤ ስለ ምንስ ትሰሙታላችሁ? አሉ።
²¹ ሌሎችም፦ ይህ ጋኔን ያለበት ሰው ቃል አይደለም፤ ጋኔን የዕውሮችን ዓይኖች ሊከፍት ይችላልን? አሉ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ሠለስቱ_ምዕት ቅዳሴ ነው። መልካም የሐዋርያው የቅዱስ ዮሐንስ የልደት በዓል እና የብፁዕ አባ ሙሴ ዕረፍት፣ የቅዱስ ኢያሱ ወልደ ነዌ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_5

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም አምስት በዚች ቀን #ቅድስት_ሶፊያ_ሰማዕት ከሁለት ልጆቿ ጋር በሰማዕትነት አረፈች፣ #አቡነ_አሮን_መንክራዊ እረፍት ነው፣ #ቅዱስ_ማማስ_ሰማዕት በሰማዕትነት አረፈ፣ ኢትዮጵያዊው ጻድቅ #አፄ_ልብነ_ድንግል እረፍቱ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ሶፊያ_ሰማዕት

መስከረም አምስት በዚች ቀን የከበረች ሶፊያ ከሁለት ልጆቿ አክሶስናና በርናባ ከሚባሉት ጋር በሰማዕትነት ሞተች ።

ዘመነ ሰማዕታት በሚል በሚታወቀው 3ኛው መቶ ክ/ዘመን ብዙ ቅዱሳት እናቶቻችን ስለ ፍቅረ ክርስቶስ አንገታቸውን ሰጥተዋል:: አንዳንዶቹ ደግሞ ሕይወታቸው እጅግ የሚያምር ነበር:: ከእነዚህ ቅዱሳት እናቶቻችን አንዷ ዛሬ የምናከብራት ሐጊያ ሶፊያ ናት::

በዚህ ስም ከሚጠሩት አንዷ ስትሆን በቀደመ ሕይወቷ #ክርስቶስን አታውቅም ነበር:: ጣዖትን የሚያመልኩ ወላጆቿ አሳድገው አጋቧት:: ከትዳሯም 2 ቡሩካት ሴቶች ልጆች ወልዳለች:: ስማቸውም አክሶስናና በርናባ ይባላል:: ልጆቿ ልብ እያገኙ በሔዱ ጊዜ ቅድስት ሶፍያ ስለ እውነተኛው አምላክ ትመራመር ገባች::

በወቅቱ የነበሩ ብዙ ሃይማኖቶችን መዘነች:: ከክርስትና በቀር ግን ሌሎቹ ሚዛን እንደማይመቱም አስተዋለች:: "እውነተኛው አምላክ ሆይ! ምራኝ እርዳኝም" ስትል ጸለየች:: #መድኃኔዓለም ለጠሩት አያሳፍርምና ፈጥኖ በጐውን ጐዳና አሳያት።

ድኅነት ለልጆቿም ይሆን ዘንድ ሁለቱንም ጠርታ ስለ ክርስትና አማከረቻቸው:: ደስ ብሏቸው ተቀበሏት:: እርሷም ጊዜ ሳታጠፋ ወደ ዻዻስ ሒዳ ማሕተመ ክርስትና: ሃብተ ውልድናን ትቀበል ዘንድ ከልጆቿ ጋር ተጠመቀች:: በቅድስናና ደስ በሚያሰኝ አኗኗርም እስከ መከራ ቀን ቆየች::

የመከራ ጊዜ ሲደርስም ልጆቿን ጠርታ "ስለ ክርስቶስ ፍቅር እንሙት" አለቻቸው:: ቡሩካቱ አክሶስናና በርናባም ደስ እያላቸው "እሺ" አሏት:: ወዲያውም በመኮንኑ ፊት ቀርበው ክርስቶስን ከመካድና ከስቃይ ሞት የትኛውን እንደሚመርጡ ቢጠየቁ እነርሱ መሞትን መረጡ:: ወደ እሥር ቤትም ከተቷቸው::

ቅድስት ሶፍያ 2 ልጆቿ ይጸኑላት ዘንድ አዘውትራ ገድለ ሰማዕታትን እና ክብራቸውን ትተርክላቸው ነበር:: በተለይ የታላቁዋን አንጌቤናይት (እመቤት) ሶፍያንና የ3 ልጆቿን (ዺስጢስ: አላዺስና አጋዺስ) ተጋድሎ እየነገረች ታጸናቸው ነበር።

ከእሥር በኋላ ግርፋት ታዞባቸው እናት ራቁቷን ስትገረፍ መልአክ ወርዶ ሲጋርዳት ልጆች በማየታቸው ደስ አላቸው:: ቅድስት ሐጊያ ሶፍያና 2 ልጆቿ እጅግ የበዛ ስቃይን ስለ ቀናች እምነት ተቀበሉ:: ምላስ እስከ መቆረጥም ደረሱ:: በመጨረሻ ግን በዚህች ቀን ተገድለው አክሊለ ሰማዕታትን ገንዘብ አደረጉ

የመከራ ዘመን ካለፈ በኋላ ታላቁ ንጉሥ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ የሁሉን ቅዱሳን ቤት ሠርቶ የእርሷን በመዘንጋቱ ለራሱ ባሰራው ቤተ መንግስት ላይ ተአምር ታይቷል። ለ3 ያህል ጊዜ ስሙን ሲያስቀርጽ መልአክ እየወረደ ይፍቀው የሶፍያንም ስም ይጽፈው ነበር።

በመጨረሻም ንጉሡ ልጁን እስከ መገበር ደርሶ ቤተ መንግስቱ የቅድስት ሶፍያና የ2 ልጆቿ ቤተ ክርስቲያን ለመሆን በቅቷል:: ምንም ለ3 ጊዜያት ያህል ሙሉ እድሳት ቢደረግለትም ዛሬ አሕዛብ የያዙትን ይህንን ቅርስ ንጉሡ የሠራው ከ1700 ዓመታት በፊት ነው።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_አሮን_መንክራዊ

በዚህች ቀን አቡነ አሮን መንክራዊ ዕረፍታቸው ነው፡፡ አቡነ አሮን ወላጅ አባታቸው የላስታው ጻድቁ ንጉሥ ዐፄ ገብረ መስቀል ናቸው፡፡ እናታቸው አመተ ማርያም ይባላሉ፡፡ የላስታ ነገሥታት የዘር ሐረጋቸው ከንጉሥ ሰሎሞን ዘር ሲያያዝ የመጣ ነው፡፡

ከ10ኛው እስከ 13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን (920-1253 ዓ.ም ገደማ) በላስታ ቡግና ምድር የነገሡ የላስታ ቡግና ተወላጅ የሆኑ የኢትዮጵያ ቅዱሳን ነገሥታት የንግሥናቸው መጠሪያ ‹‹የዛጉዌ ሥርወ መንግሥት›› ወይም ‹‹የላስታ መንግሥት›› በመባል ይታወቃል፡፡ የንጉሥ ሰሎሞን ዘር የሆነው መራ ክርስቶስ 3 ልጆችን ወለደ፡፡ እነርሱም ጠንጠውድም፣ ግርማ ስዩምና ዣን ስዩም ናቸው፡፡ ጠንጠውድም ገብረ መስቀልን ወለደ፣ ገብረ መስቀልም አቡነ አሮንን ወለደ፣ ግርማ ስዩም ይምርሐነ ክርስቶስን ወለደ፣ ዣን ስዩም ደግሞ ገብረ ማርያምንና ላሊበላን ወለደ፡፡ ገብረ ማርያምም ነዓኲቶ ለአብን ወለደ፡፡ እነዚህ ቅዱሳን ነገሥታት እንደ መልከጼዴቅ (ዘፍ14፡18) ክህነትን ከንግሥና፣ ቅድስናን ከንጽሕና ጋር አንድ አድርገው በመያዝ #እግዚአብሔርንም ሕዝብንም በቅድስናና በንጽሕና አገልግለው አልፈዋል፡፡

አቡነ አሮን ግን ገና በ7 ዓመታቸው ነው ዓለምን ፍጹም ንቀው በአቡነ በጸሎተ ሚካኤል እጅ የመነኮሱት፡፡ በ16 ዓመታቸውም ዋልድባ ገዳም ገብተዋል፡፡ ነሐሴ 5 ቀን ገና ሲወለዱ ሙት አስነሥተዋል፡፡ በሀገራችን እየተዘዋወሩ ወንጌልን ሲሰብኩ የሸዋው ንጉሥ አንኮበር ድረስ ጠርቷቸው ሲሔዱ አዋሽ ወንዝ ሞልቶባቸው አገኙት፡፡ ሲሻገሩም ዳዊታቸውን ወስደባቸው፡፡ ‹‹ልጆቼን አመነኮስክብኝ›› በሚል ሰበብ ንጉሡ 7 ዓመት በግዞት አስሮ አስቀመጣቸው፡፡ ነገር ግን ከ7 ዓመት በኋላ አቡነ አሮን ተመልሰው በአዋሽ ወንዝ ሲመጡ መልአክ መጣና ‹‹መቋሚያህን ወደ ወንዙ ላክ›› አላቸው፡፡ መቋሚያቸውንም ቢልኩ ከ7 ዓመት በፊት ወደ ወንዙ ገብቶባቸው የነበረውን ዳዊታቸውን ይዘው አወጡ፡፡ ዳዊቱም በውኃው አልራሰም ነበር፣ ይልቁንም አቧራውን አራግፈው ፈጣሪያቸውን አመስግነው ዳዊታቸውን ይዘው ሄደዋል፡፡ ያ ዳዊታቸው ዛሬም ድረስ በጋይንት አበርጉት ቅዱስ ሚካኤል ይገኛል፡፡

ሰሜን ወሎ መቄት ወረዳ ውስጥ የሚገኘው እጅግ አስደናቂ ገዳማቸው ፍልፍል ዋሻ ሲሆን ጣራው ክፍት ነው፣ ክፍት በሆነው ጣራ በኩል ፀሐይ ሲገባ ስለሚያቃጥል ጥላ ይይዛሉ ነገር ግን የጻድቁ ግዝት ስላለበት ዝናብ ወደ መቅደሱ ፈጽሞ አይገባም፡፡ እጅግ አስደናቂ ነው፡፡ አቡነ አሮን በዋድላ ሜዳ አልፈው ሲሄዱ አንችም ሜዳ ላይ እንደ ኢያሱ ፀሐይን በቃላቸው ገዝተው አቁመዋታል፡፡

ከታች ጋይንት ተነሥተው መንገድ ሲሄዱ በሰንበት ቀን በሬ ጠምዶ ሲያርስ የነበረን ገበሬ ‹‹ለምን በሰንበት ታርሳለህ?›› ቢሉት ‹‹ምቀኛ መነኩሴ›› ብሎ በጅራፉ ቢገርፋቸው በሬዎቹ ግን ፈጽሞ አልንቀሳቀስ ብለው ቆመዋል፡፡ በዚህ የተናደደው ገበሬም አቡነ አሮንን መሬት ላይ ጥሎ ገረፋቸው፡፡ እሳቸውም ተነሥተው ሲሄዱ ዛፎች ተነቅለው እየተከተሏቸው፣ ቃልም አውጥተው በሰው አንደበት አመስግነዋቸዋል።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጻድቁ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ማማስ_በሰማዕት

በዚህችም ቀን ቅዱስ ማማስ በሰማዕትነት ሞተ የአባቱ ስም ቴዎዶስዮስ የእናቱም ያኖች ናቸው። በንጉሥ ዑልያኖስ ዘመንም ስለ ሃይማኖታቸው ይዘው አሠሩአቸው በእሥር ቤትም ሳሉ አረፉ።

አንዲት ክርስቲያናዊት ሴት መጥታ ይህን ሕፃን ወስዳ እንደ ልጅዋ አድርጋ አሳደገችው። ስሙንም ማማስ ብላ ሰየመችው ትርጓሜውም። የሙት ልጅ ማለት ነው አባትና እናት የለውምና።
ዐሥራ ስምንት ዓመትም በሆነው ጊዜ ወደ ከሀዲው ገዢ ሒደው ክርስቲያን ነው ብለው ወነጀሉት ይዘውም በበትሮች ደበደቡት በአንገቱም የሚከብድ ሸክም ታላቅ የዓረር ደንጊያ አንጠልጥለው ከባሕር ውስጥ ጣሉት። ክብር ይግባውና በ #እግዚአብሔር ኃይል ከባሕር ስጥመት ዳነ ወጥቶም በዋሻ ውስጥ ተሠውሮ ከጎሽ ወተትን እየተመገበ ተቀመጠ።

ከዚህም በኃላ ሁለተኛ ያዙት ወስደውም ከሚነድ እሳት ውስጥ ጨመሩት ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም አዳነው። ዳግመኛም ተነጣጥቀው እንዲበሉት አንበሶችን በላዩ ሰደዱ በ #እግዚአብሔርም ኃይል በአንበሳ ላይ ተቀመጠ።

ከዚህም በኃላ ብዙ አሠቃዩት ሕዋሳቶቹ እስቲለያዩና የሆድ ዕቃው እስቲፈስ ጎተቱት ተጋድሎውንና ምስክርነቱን በዚህ ፈጽሞ የሰማዕትነት አክሊልን በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም እኛንም በቅዱስ ማማስ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አፄ_ልብነ_ድንግል

በዚህችም ቀን #እግዚአብሔርን የሚወድ ሃይማኖቱ የቀና ደግ ጻድቅ የኢትዮጵያ ንጉሥ ልብነ ድንግል አረፈ።

እኒህ ንጉሥ ኢትዮዽያን ለዓመታት (ከ1500 እስከ 1532 ዓ.ም) ቢያስተዳድሩም 15ቱ ዓመት ያለቀው በስደት ነው። ከደጋጉ አፄ ናዖድና ንግሥት ወለተ ማርያም ተወልደው በሥርዓቱ አድገው ቢነግሡም በክፉ መካሪዎች ጠንቅዋይ ወደ ቤታቸው ገብቶ ሃገሪቱን ለመከራ ዳርጓታል።

ዛሬም ድረስ ጠባሳው ያለቀቀው የግራኝ ወረራ ለ15 ዓመታት ሃገሪቱን ያለ ካህንና ቤተ ክርስቲያን አስቀርቷት ነበር። ብዙ ክርስቲያኖችም ሰልመው ቀርተዋል። አፄ ልብነ ድንግል ግን ደብረ ዳሞ ገዳም ውስጥ ገብተው ንስሃ ጀመሩ አለቀሱ ተማለሉ።

እመቤታችን ተገልጣም "ይቅርታን በነፍስህ እንጂ በሥጋህ አታገኝም" አለቻቸው። እርሳቸውም ሱባኤውን ቀጥለው ስብሐተ ፍቁርን፣ መልክአ ኤዶምን የመሰሉ መጻሕፍትን ደርሰው በዚህች ቀን ዐርፈዋል። እኛ ክርስቲያኖችም እናከብራቸዋለን።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም_5#ከገድላት_አንደበት እና #ዝክረ_ቅዱሳን)
2024/09/21 09:54:32
Back to Top
HTML Embed Code: