Telegram Web Link
#ነቢዩ_አሞጽ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
“አሞጽ” ማለት “ሽክም፣ ጭነት” ማለት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ በዚኽ ስም የሚጠሩ ሦስት ሰዎች ያሉ ሲኾን እነርሱም የነቢዩ ኢሳይያስ አባት /ኢሳ.፩፡፩/፣ የምናሴ ልጅ ንጉሥ አሞጽ /፪ኛ ነገ.፳፩፡፲፰/ እንዲኹም ለዛሬ የምናየውና ከደቂቀ ነቢያት አንዱ የኾነው ነቢዩ አሞጽ ናቸው፡፡

➛የቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት እንደሚያስረዳው የነቢዩ አሞጽ አባት ቴና ሲባል እናቱ ደግሞ ሜስታ ትባላለች፡፡ ነገዱም ከነገደ ስምዖን ወገን ነው፡፡

📌ነቢዩ አሞጽ ከመጠራቱ በፊት የላም ጠባቂና የወርካ ለቃሚ ነበር፡፡ ነቢይ ወይም የነቢይ ልጅም አልነበረም፤ #እግዚአብሔር በጐችን ከመከተል ጠራው እንጂ /አሞ.፯፡፲፬-፲፭/፡፡ ምንም እንኳን ከግብርና የመጣ ቢኾንም ንግግር የማይችል፣ ያልተማረ፣ ድፍረት የሌለው ነቢይ አልነበረም፡፡

➛ነቢዩ አሞጽ ምንም እንኳን ከደቡባዊው መንግሥት ቢኾንም እንዲያስተምር የተላከው ለሰሜናዊው ክፍልም ጭምር ነበር፡፡
በራሱ መጽሐፍ እንደነገረን በዘመኑ የነበረው የይሁዳ ንጉሥ ዖዝያን ሲኾን በእስራኤል የነበረው ንጉሥ ደግሞ ዳግማዊ ኢዮርብዓም ይባላል /አሞ.፩፡፩/፡፡ በነቢይነት ያገለገለውም ከ፯፻፹፯-፯፴፭ ቅ.ል.ክ. ላይ ነው፡፡

📌በነቢዩ አሞጽ ዙርያ የነበረው ነባራዊ ኹኔታ
➛ነቢዩ አሞጽ በሚያገለግልበት ወራት የይሁዳና የእስራኤል ኃጢአት ጣራ የነካበት ጊዜ ነበር፡፡ ከእኛ ዘመን ጋርም በእጅጉ ይመሳሰላል፡፡ አንባቢያን ይኽን ቀጥሎ ከተጠቀሰው ጋር ማነጻጸር ይችላሉ፡፡ ምንም እንኳን በአንጻራዊ መልኩ ነቢዩ አሞጽ በነበረበት ወራት ሰላም የነገሠበት ቢኾንም ሕዝቡ ግን የ #እግዚአብሔር ሕግ ጥሏል፤ ትእዛዙን አይጠብቅም፡፡ ባለጸጐች የሚባሉት በሀብት ላይ ሀብት ጨምረው የሚኖሩ ቢኾኑም ድኾቹ ግን ከዕለት ወደ ዕለት ከድጡ ወደ ማጡ የሚኼዱ ነበሩ፡፡ ጻድቁን ስለ ብር፣ ችግረኛውን ስለ አንድ ጥንድ ጫማ የሸጡበት ጊዜ ነበር፡፡ የድኾችን ራስ በምድር ትቢያ ላይ ይረገጣል፤ የትሑታን መንገድ ይጣመማል፡፡ ቅዱሱን የ #እግዚአብሔር መንገድ ያረክሳሉ፡፡ አባትና ልጅ ለዝሙት ግብር ወደ አንዲት ሴት ይገባሉ፡፡ ጻድቁ በጽድቅ መንገድ ልኺድ ቢል ከእነርሱ ጋር ስላልተስማማ ያስጨንቁታል፡፡ እውነትን የሚናገር ሰው አምርረው ይጸየፉታል፡፡ #እግዚአብሔር  ነቢያቱን እየላከ ሐሳቡና ፈቃዱ ምን እንደኾነ ደጋግሞ ቢነግራቸውም አይመለሱም፡፡ ቅን ነገርን ማድረግ አያውቁም፡፡ ችጋረኛውን ይውጡታል፡፡ የአገሩን ድኻ ያጠፋሉ፡፡ ሚዛኑን አሳንሰው በሐሰት ይሸጣሉ፡፡ ንጹሕ እኽል ሳይኾን ግርዱን ለገበያ ያቀርባሉ፡፡ ድኻውን ይደበድቡታል፤ ይበድሉታል፤ ፍርድ ያጣምሙበታል፤ ያስጨንቁታል፤ ጉቦ ይቀበሉታል፡፡ በዚያም ላይ ቀረጥን ያበዙበታል፡፡ ለራሳቸው ግን ከተጠረበ ድንጋይ ቤቶችን ይሠራሉ፡፡ ያማሩ የወይን ቦታዎችን ይተክላሉ፡፡ ግፍንና ቅሚያን በአዳራሾቻቸው ያከማቻሉ፡፡ ከዝሆን ጥርስ በተሠራ አልጋ ላይ ይተኛሉ፡፡ በምንጣፋቸው ላይ ተደላድለው ይቀመጣሉ፡፡ አምጡ እንብላ እንጠጣ ይላሉ፡፡ ከበጐች መንጋ ጠቦቱን ከጋጥም ውስጥ ጥጃን ይበላሉ፡፡ በመሰንቆ ድምፅ ይንጫጫሉ (ይዘፍናሉ)፡፡ በዚያ ዘመን የነበሩ ካህናትና ነቢያት ለገንዘብ የሚሠሩ ነበሩ፡፡
በቅርብ ጊዜ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው በአኹኑ ሰዓት የዓለማችን ሰማንያ ከመቶ ሃብትና ንብረት በሃያ ፐርሰንት ግለሰቦች ብቻ የተያዘ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ በዓለማችን ፍትሐዊ የኾነ የሃብት ክፍፍል የለም ማለት ነው፡፡ በአገራችን ያለውን ነባራዊ ኹኔታ ስናየውም ቢብስ እንጂ ከዚኹ አይሻልም፡፡ ነቢዩ አሞጽ በሚያገለግልበት ወራት የነበረው ኹናቴ ከአኹኑ ኹኔታ ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል ያልነውም ከዚኽ ተነሥተን ነው፡፡
በሌላ መልኩ በመጽሐፈ ነገሥት ካልዕ ምዕራፍ ፲፬ ከቁጥር ፳፫ እስከ ፍጻሜ ያለውን ኃይለ ቃል ስናነብ ኢዮርብዓም ወደ አምልኮ ጣዖት ማዘንበሉን እናነባለን፡፡
በሕዝቡ ዘንድ የነበረው የእምነትና የጸሎት ኹኔታ በእጅጉ የወደቀ ነበር፡፡ ምንም እንኳን በዓላትን እንዲያከብሩ፣ የተቀደሰ ጉባዔ እንዲያደርጉ፣ የሚቃጠለውን መሥዋዕት እንዲኹም የእኽል የቊርባን እንዲያቀርቡ፣ በመሰንቆ እንዲያመሰገኑ የነገራቸውና ያዘዛቸው #እግዚአብሔር ራሱ ቢኾንም ነቢዩ ሆሴዕ፡- “ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን ከሚቃጠለውም መሥዋዕት ይልቅ #እግዚአብሔርን ማወቅ እወዳለኹ” እንዳለ /ሆሴ.፮፡፮/ ግብራቸው እጅግ የከፋ ስለኾነ ይኽን ቢያቀርቡለትም አልተቀበላቸውም፡፡ “ዓመት በዓላችኹን ጠልቼዋለኹ፤ ተጸይፌውማለኹ፤ የተቀደሰውን ጉባዔአችሁ ደስ አያሰኘኝም፡፡ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችኹ የእኽሉን ቊርባናችሁን ብታቀርቡልኝም እንኳ አልቀበለውም፤ ለምስጋና መሥዋዕት የምታቀርቡልኝን የሰቡትን እንስሶች አልመለከትም፡፡ የዝማሬኽንም ጩኸት ከእኔ ዘንድ አርቅ፤ የመሰንቆኽንም ዜማ አላደምጥም” ያላቸው ስለዚኹ ነው /አሞ.፭፡፳፩-፳፫/፡፡ መፍትሔውም #እግዚአብሔርን መፈለግ ብቻ መኾኑን ተናግሯል /አሞ.፭፡፬-፱/፡፡ በሕይወት ይኖሩ ዘንድ መልካሙን እንዲፈልጉ፣ ይኽን ቢያደርጉም የሠራዊት ጌታ #እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር እንደሚኾን ተናግሯል /አሞ.፭፡፲፬-፲፭/፡፡

                 #ትንቢተ_አሞጽ

ከኋለኛው ዘመን ነቢያት የተናገረውን ትንቢት በመጻፍ የመዠመሪያው ነው፡፡ የአሞጽ ትንቢተ በአብዛኛው በእስራኤልና በአከባቢው ባሉ አገሮች ላይ የሚመጣውን ፍርድ ማስታወቅ ነው፡፡ ፵፩ ጊዜ “ #እግዚአብሔር እንዲኽ ይላል” እያለ መናገሩም ይኽንኑ ያስረዳል፡፡ የሚዠምረውም በአሕዛብ ላይ ማለትም በቂር፣ በኤዶም፣ በደማስቆ፣ በሶርያ፣ በቴማን፣ በጢሮስ፣ በሞዓብ ሊመጣ ያለውን ፍርድ በማስታወቅ ነው /አሞ.፩ ሙሉውን ያንብቡ/፡፡ ቀጥሎም በይሁዳና በእስራኤል ሊመጣ ያለውን ፍርድ ይናገራል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከላይ ለመግለጥ እንደሞከርነው የሕዝቡ በግዴለሽነት መኖር ያመጣው መዘዝ ነው፡፡
ነቢዩ አሞጽ ክብር ይግባውና #ጌታችንና_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በተሰቀለበት ጊዜ ስለሚኾነው ተአምር ናግሯል፡፡ ሕዝብና አሕዛብ በክርስቶስ አንድ እንደሚኾኑ መናገሩም ቅዱሳን ሐዋርያት ጠቅሰዉታል /፱፡፲፩-፲፪፣ ሐዋ.፲፭፡፲፭-፲፰/፡፡

➛በአጠቃላይ መጽሐፉን እንደሚከተለው መክፈል እንችላለን፡-
1, ፍርድ በእስራኤል ጐረቤት አገሮች /፩:፩-፪፡፭/፤
2, ፍርድ በእስራኤልና በይሁዳ ላይ /፪፡፮-፫፡፮/፤
3, ፍርድ በእስራኤል በደል ምክንያት /፫፡፩-፮፡፲፬/፤
4, ፍርድ በአምስት ዓይነት መንገድ /፯፡፩-፱፡፲/፤ በዚኽም መካከል የአሜስያስና የአሞጽ ታሪክ /፯፡፲-፲፯/፤
5, በፍጻሜው ዘመን ስላለው የእስራኤል ተስፋ /፱፡፲፩-ፍጻሜ/፡፡

የነቢዩ አሞጽ የመጨረሻው ዕረፍት
ስለ ነቢዩ አሞጽ የመጨረሻው ዕረፍት መረጃ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ግንቦት ፳፩ ላይ የሚነበበው ስንክሳርም ነቢዩ በዚያ ዕለት እንደሚታሰብ ከመናገር ውጪ ያለው ነገር የለም፡፡

#ወስብሐት_ለእግዚአብሔር!!
💐🌻"በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።🌻💐

           #መስከረም ፩ (1) ቀን።

እንኳን #ለርእሰ_ዐውደ_ዓመት_ለቅዱስ ዮሐንስ፤ #ከዘመነ_ቅዱስ_ዮሐንስ_ወደ_ዘመነ_ቅዱስ_ማቴዎስ አሸጋግሮ #እግዚአብሔር አምላክን በሰላምና በጤና አደረሰን።
                                                              #የተባረከ_የመስከረም_ወር_የግብፅና #የኢትዮጵያ_ዓመታት_ወሮች_ርእስ_ነው። የቀኑ ሰዓትም ከሌሊት ሰዓት የተስተካከለ ዐሥራ ሁለት ነው። ከዚህ በኋላ እያነሰ ይሔዳል። አሁንም በፍጹም ንጽሕና ታላቅ በዓልን አድርገን ልናከብር ይገባናል።

ይህች ዕለት ከሌሎች ዕለታት ተለይታ የተባረከች ናትና ከክፉ ሥራዎችም ሁሉ ተለይተን እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝባቸውን አዳዲስ የሆኑ በጎ ሥራዎችን እንሥራ። ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ "እነሆ የቀደሙት ሥራዎች አልፈው ሁሉ በክርስቶስ ሐዲስ ሆነ" እንዳለ። ይህም ከ #እግዚአብሔር ዘንድ እንዲሁ የጐላ የተረዳ ሆነ እርሱም በ #ክርስቶስ ልጅነትን በመስጠት ይቅርታውንና ቸርነቱን አደለን።

ኢሳይያስም እንዲህ አለ "በኔ ህልውና ያለ ያዋሐደኝ ሕይወቴ #መንፈስ_ቅዱስ ስለርሱ ድኆችን በልብ ያዘኑ ሰዎችን ደስ አሰኛቸው ዘንድ ለተማረኩም ሰዎች ነፃ መውጣትን አስተምራቸው ዘንድ ዕውሮችም ያዩ ዘንድ #እግዚአብሔር የወሰነውን ዘመን የተመረጠ እለው ዘንድ ፍዳ የሚደረግባትንም ቀን ደግ እላት ዘንድ ያዘኑትንም ሰዎች ደስ አሰኛቸው ዘንድ ላከኝ"።

ነቢዩ ዳዊትም ዳግመኛ እንዲህ አለ "የምሕረትህንም ዓመት እህል ትባርካለህ። ምድረ በዳዎችም ከበረከትህ ጠሎችን ይጠግባሉ። ምንጭ፦ የመስከረም 1 ስንክሳር።
#መስከረም_1

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም አንድ በዚህች ቀን የከበረ መልአክ #ቅዱስ_ራጉኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው፣ #ጻድቁ_ኢዮብ በፈሳሽ ውኃ ታጥቦ ከደዌው ሁሉ ተፈወሰ፣ ሐዋርያ #ቅዱስ_በርቶሎሜዎስ ምስክር ሁኖ አረፈ፣ ሊቀ ጳጳሳት #አባ_ሜልዮስ አረፈ፣ የቊልዝም ሰው የሆነ ፍጽም ጸድቃ #አባ_ሚልኪ አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ራጉኤል_መልአክ

መስከረም አንድ በዚህች ቀን ከተስዓቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ የከበረ መልአክ ራጉኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው።

ራጉኤል ማለት የብርሃናት አለቃ ማለት ነው። የብርሃናት አለቃ ሲባል ፀሐይን፣ ጨረቃን እና ከዋክብትን በማመላለስና ለሰው ልጆች፣ ለአዝርዕት፣ ለእንስሳት፣ ለአራዊት ሁሉ ብርሃንን የሚመግብ ነው ማለት ነው። አንድም ራጉኤል ማለት የሚበቀል ማለት ነው። የሚበቀል ነው ማለት በቀል የሚገባው ለጠላት ነው የሰው ልጅ ጠላት ደግሞ ዲያብሎስ ነው፤ ስለሆነም ቅዱስ ራጉኤል #እግዚአብሔርን አምነው ሕገ #እግዚአብሔርን ጠብቀው በፍርሐተ #እግዚአብሔር አምልኮቱን ለሚፈጽሙ ሁሉ ጠላት ዲያብሎስን የሚያርቅላቸው ወደ እነርሱም ፈጥኖ በመድረስ የሚታደጋቸው ነው ማለት ነው። ሔኖክ 6:4፡፡ አንድም ራጉኤል ማለት የኃያላን ኃያል #እግዚአብሔር ማለት ነው። የኃያላን ኃያል ያለው የ #እግዚአብሔርን ኃያልነት ከምድር ፍጥረታት ዘንድ ኃያል ከሚባሉት ሁሉ ሊገለጽ የማይችል ኃያልነቱን ለመግለጽ ኃያልነቱም ከ እስከ የሌለው መሆኑን ለመግለጽ የተቀመጠ ነው። ስለዚህ #እግዚአብሔር ኃያል የኃያላን ኃያል መሆኑን የሚገልጽ ትርጉም አለው።

አንድም ራጉኤል ማለት ጽኑ #እግዚአብሔር ማለት ነው። የ #እግዚአብሔር አምላክን ጽኑነት ለማጉላት ሲል ጽኑ አለው። #እግዚአብሔር የማይወላውል የማይዋዥቅ የማይከዳ ነው ለማለትም ሲል ይህ ስያሜ ተሰጠው። የ #እግዚአብሔርን ጽናት የሚያሳይ ትርጉም ያለው ስያሜ ነው። የሊቀ መላእክት የቅዱስ ራጉኤል አገልግሎት እና ስልጣን፡- እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከዚህ ዓለም በ64 ዓመቷ ካረፈች በኋላ ሥጋዋ ወደ ዕፀ ሕይወት ሲነጠቅ (ሲያርፍ) አብሮ ለሔደው እና ስጋዋን በእጣን ሲያጥን ለነበረው ለፍቁረ እግዚእ ለቅዱስ ዮሐንስ ኅብስትን የመገበ መልአክ ነው።

በብርሃናት ሁሉ ላይ የሰለጠነ መልአክ ነው። ከአዳም ሰባተኛ ትውልድ የሆነ በ #እግዚአብሔር ፊት ግሩም ያማረ ሥራው የሰመረ እስከዛሬ የሞት ወጥመድ ያልያዘው የሞት ጥላ ያላረፈበት ነብዩ ሔኖክ "ከቅዱሳን መላእክት አንዱ የሆነ ጸላዒ ዲያብሎስን የሚበቀለው ራጉኤል በብርሃናት ላይ የሰለጠነ ነው" ሲል ስለ እርሱ ተናግሯል፡፡

#እግዚአብሔር ዓለምን ይቆጣጠር ዘንድ የሾመው ታላቅና ቅዱስ መልአክ ነው። (ድርሳነ ራጉኤል ዘ ጥቅምት ገጽ 23) አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ለመተካት ዓለምን የመለወጥ ሥልጣን የተሰጠው ቅዱስ መልአክ ነው። ከ #እግዚአብሔር የጌትነቱ አዳራሽ ይገባና ይወጣ ዘንድ ስልጣን ያለው ከኪሩቤልና ከሱራፌል ጋር ከፈጣሪ የጌትነት ዙፋን ፊት የሚቆም ነው። ሎጥን ሚስቱንና ልጆቹን ከእሳተ ጎመራ ያዳነ የበለአምን እርግማን ወደ በረከት የለወጠ እርሱ ነው።

በቅዱስ ራጉኤል ስነ ሥዕል ላይ የምናየው ይህ ባለ አራት እራስ ንስር ከአርባእቱ ኪሩቤል አንዱ ገጸ ንስር ነው። የሥላሴን የጌትነት ዙፋን የሚሸከሙ አርባዕቱ እንስሳት ናቸው። የሚሸከሙት ሲባል ጫማ የሰውን ልጅ እንደሚሸከመው እንጂ ችለውትስ አይደለም። እነርሱም የሰው ገጽ፣ የእንስሳ ገጽ፣ የንስር ገጽ እና የአንበሳ ገጽ ያላቸው ናቸው። ይህንንም ነብዩ ሕዝቅኤል "ለእያንዳንዱ እንስሳትም የተለያዩ አራት ገጾች ነበሩት። ይህውም በስተቀኝ በኩል የእንስሳ መልክ፣ በስተ ግራ የላም ገጽ፣ በበስተ ኋላም የንስር ገጽ የሚመስሉ ነበሩ" ብሏል ሕዝ 1፡6-13፡፡ ከዚህ የምንገነዘበው ነገር ቢኖር አራት ገጽ ካላቸው ኪሩቤል መካከል አንዱ ንስር መሆኑን ነው። ቅዱስ ራጉኤል ደግሞ የእነዚህ ኪሩቤል አለቃቸው (የጌትነቱ ዙፋን ጠባቂ) በመሆኑ በዚህ ምክንያት ማለትም እነርሱ ዙፋኑን ተሸካሚ እርሱ ደግሞ አጠገባቸው መቆሙ መንበሩን ጠባቂ በመሆኑ በዚህ አይነት የአገልግሎት ድርሻ አብረው ሊሳሉ ችለዋል። ቅዱስ ያሬድም በድጓው "አርባእቱ እንስሳ አልቄንጥሩ እንደሚባለው ንስር ፊት ለፊት አይታዩም አንዱም በመራቸው ይሔዳሉ እነርሱም እያንዳንዳቸው አራት ገጽ ሲኖራቸው ሳያርፉና ሳይደክሙ የሚያመሰግኑ ናቸው" በማለት ጽፏል። አንድም መላእክት ነገደ ሱራፌል እና ነገደ ኪሩቤል በመባል ይከፈላሉ። በነገደ ሱራፌል እነ ቅዱስ ሚካኤል፣ ቅዱስ ሩፋኤል ወዘተ ሲሆኑ በነገደ ኪሩቤል ደግሞ ቅዱስ ገብርኤል ቅዱስ ራጉኤል ወዘተ ያጠቃልላል። ስለዚህ ቅዱስ ራጉኤል ነገዱ ከነገደ ኪሩቤል ነው በዚህም ላይ የነገደ ኪሩቤል አልቄንጡራ (አራት እራስ ንስር) አለቃቸው ቅዱስ ራጉኤል ነው። በዚህም ምክንያት አብረው ሊሳሉ ችሏል። አንድም መላእክትን ሁሉ እንደ እየስራቸው መለያ ስነ ሥዕላቸውን መሳል ልማድ ነውና። ለምሳሌ ቅዱስ ሚካኤል ከቅድስት አፎምያ ጋር፣ ቅዱስ ገብርኤል ከሠለስቱ ደቂቅ ጋር፣ ቅዱስ ዑራኤል ከእዝራ ሱቱኤል ጋር እንደሚሳሉት ሁሉ ማለት ነው። በዚህም መሰረት ቅዱስ ራጉኤልም ዐቃቤ መንበር ነውና መንበሩን በሚሸከሙት ኪሩቤል ከሚመሰሉት ንስሮች ጋር አብረው ሊሳሉ ችለዋል፡፡

ሊቀ መላእክት ቅዱስ ራጉኤል ከአምላክ የተሰጠው ቃል ኪዳን #እግዚአብሔር አምላክ በስሙ ለታመኑት ቅዱሳን፣ ጻድቃን፣ ሰማእታት፣ ሐዋርያት፣ ዘወትር ያለማቋረጥ ስሙን ለሚጠሩት ቅዱሳን መላእክት ሁሉ ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል። የሰጣቸውም ቃል ኪዳን ዘላለማዊ እና ሊሻር የማይችል ነው። ለመላእክት አለቃ ለቅዱስ ራጉኤልም ይህን ቃል ኪዳን ሰጥቶታል "የራጉኤል አምላክ ይቅር በለኝ በማለት አንዲት ቃልስ እንኳን ቢናገር እንደ ወዳጄ እንደ አብርሃም፣ እንደ ባለሟሌም እንደ ይስሐቅ፣ እንደ አከበርኩትም እንደ ያዕቆብ ክብርን ባለሟልነትን እሰጠዋለሁ በራሱ ላይም አክሊል አቀዳጀዋለሁ እረጅም ዘመናት ሰፊ ወራትም እሰጠዋለሁ" ሲል ቃሉን ሰጥቶታል፡፡ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ራጉኤል መስከረም 1 ቀን ከሊቃነ መላእክት በ4ተኛ ደረጃ የተሾመበት ዕለት ነው። ግንቦት 1 ቀን ለታላቁ አባት ለሄኖክ ምሥጢራትን የገለጸበት በዓሉ ነው፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ራጉኤል አማልጅነት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ጻድቁ_ኢዮብ

በዚችም ዕለት ኢዮብ በፈሳሽ ውኃ ታጥቦ ከደዌው ሁሉ ተፈወሰ። ይህም ለሰዎች ልማዳቸው ሁኖ ዓመቱ ዙሮ ሲመጣ ፈሳሹ ውኃም በመላ ጊዜ በአዲስ ውኃ ይጠመቃሉ በእርሱም ይባረካሉ።

ጻድቁ ኢዮብ በዘመኑ እንደርሱ ያለ ዕውነተኛ ደግ ሰው እንደ ሌለ በቅዱሳት መጻሕፍትም ስለርሱ እንደተነገረ #እግዚአብሔር መሰከረለት።

ሰይጣንም ቀንቶበት በገንዘቡና በልጆቹ ላይ ያሠለጥነው ዘንድ ወደ #እግዚአብሔር ለመነ። የጻድቅ ኢዮብን ትዕግሥት #እግዚአብሔር ስለሚያውቅ አሠለጠነው ለመጪ ትውልድም አርአያና ምሳሌ እንዲሆን ፈቀደለት።

ስለርሱም ሐዋርያ ያዕቆብ በመልእክቱ እነሆ የጻድቅ ኢዮብን ትዕግሥቱን ሰምታችኋል አለ። ከዚህ በኋላም በአንዲት ቀን ገንዘቡ ሁሉ ጠፋ ሥጋውም በደዌ ሥጋ ከራሱ እስከ እግሩ ድረስ ተመታ። በዚህም በአስጨናቂ ደዌ ውስጥ ኖረ #እግዚአብሔርንም አመሰገነው።
አንዲት ቃልን እንኳ በፈጠረው #እግዚአብሔር ላይ አላጉረመረመም ነገር ግን የተወለደባትን ቀን ረገመ። እንስሶቹና ገንዘቡ ሁሉ በጠፋ ጊዜ #እግዚአብሔር ሰጠ #እግዚአብሔርም ነሣ የ #እግዚአብሔርም ስም የተመሰገነ ይሁን አለ።

በዚህ መከራ በነበረበት ዘመናት በተራራ ላይ ተጥሎ ሳለ የወዳጆቹና የሚስቱ ዘለፋ በዝቶበት ነበረ። እርስዋ እንዲህ ብላ መከረችው እስከ መቼ ድረስ በሞኝነት ትኖራለህ እንግዲህስ ስደበውና ሙት ዳግመኛ #እግዚአብሔርን ደጅ እጠናዋለሁ መከራውንም እታገሣለሁ የቀድሞ ኑሮዬን ተስፋ አደርጋለሁ ትላለህን አለችው።

እንዲህስ እንዳትል ከዚህ ዓለም እነሆ ስም አጠራርህ ጠፋ ሴቶች ልጆቼና ወንዶች ልጆቼ ሞቱ እኔም ዘጠኝ ወር ሳረግዝ ሳምጥ ስወልድ ላይረቡኝ ላይጠቅሙኝ በከንቱ ደከምኩ ።

አንተም በመግል ተውጠህ በትል ተከበህ ትኖራለህ ሌሊቱን ሁሉ ስትዛብር ታድራለህ እኔም እየዞርኩ እቀላውጣለሁ ካንዱ አገር ወዳንዱ አገር ካንዱ ቤት ወዳንዱ ቤት እሔዳለሁ ከድካሜ በኔ ላይ ከመጣው ከችግሬም አርፍ ዘንድ ከጧት ጀምሮ ፀሐይ እስቲገባ ድረስ እጠብቃለሁ አሁን ግን #እግዚአብሔርን የማይገባ ቃል ተናግረኸው ሙት አለችው።

ኢዮብም ሚስቱን እየተመለከተ ሰማት። ሥርዓት እንዳልተሠራባቸው ከአሕዛብ ሴቶች እንዳንዲቱ ተናገርሽን ከዚህ ቀድሞ በጎውን ነገር ከ #እግዚአብሔር እጅ ተቀበልን ከዚህ በኋላ መከራውን አንታገሥምን አላት። በዚህ ባገኘው መከራ ሁሉ ኢዮብ ጌታን የበደለው በደል የለም።

ኢዮብም ወርቅ በእሳት እንዲፈተን ፈጽሞ ተፈተነ። #እግዚአብሔርም በደመና ውስጥ ተነጋገረው። ከተናገረውም በኋላ ከደዌው ፈወሰው ጥሪቱን ሁሉ ከቀድሞ እጥፍ አደረገለት ሌሎች ልጆችንም ሴቶችና ወንዶችን ሰጠው።

ኢዮብም ከደዌው ከተፈወሰ በኋላ መቶ ሰባ ዘመን ኖረ የኖረውም ዘመን ሁሉ ሁለት መቶ አርባ ስምንት ዓመት ነው። በበጎ ሽምግልናም #አግዚአብሔርን አገልግሎ በሰላም አረፈ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጻድቁ ኢዮብ ጸሎት ይማረን ለዘለአለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሐዋርያው_ቅዱስ_በርቶሎሜዎስ

ዳግመኛም በዚህች ቀን ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ሐዋርያ በርቶሎሜዎስ ምስክር ሁኖ አረፈ። ለዚህም ሐዋርያ ሒዶ ያስተምር ዘንድ እልዋህ በሚባል አገር ዕጣው ወጣ። እርሱም ከጴጥሮስ ጋር በአንድነት ሔደ የክብር ባለቤት በሆነ በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስም አስተማሩ ልባቸውንም የሚያስደነግጥ ድንቆች ተአምራትን በፊታቸው ከአደረጉ በኋላ #እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ መለሷቸው።

ከዚህም በኋላ ወደ ከተማው ውስጥ ገብቶ ያስተምር ዘንድ ምክንያት አደረገ ቅዱስ ጴጥሮስም እንደ ባሪያ ሸጠው።ባለ ጸጋ ለሆነ መኰንንም በወይን አትክልት ውስጥ የሚያገለግል ሆነ ድንቅ ተአምርን በማድረግ የተቆረጡ የወይን ቅርንጫፎች በሠራተኞች እጅ ላይ ሳሉ አፈሩ። የአገረ ገዥውም ልጅ በሞተ ጊዜ ከሞት አሥነሣው የሀገር ሰዎችም ሁሉ አመኑ #እግዚአብሔርንም ወደ ማወቅ ተመለሱ።

ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ _ክርስቶስ በርበር ወደሚባል አገር ሔዶ ያስተምር ዘንድ ሐዋርያ በርቶሎሜዎስን አዘዘው እንዲረዳውም ሐዋርያ እንድርያስን ከደቀ መዝሙሩ ጋር ላከለት። የዚያች አገር ሰዎች ግን እጅግ የከፉ ስለሆኑ በፊታቸው ድንቆች ተአምራቶችን እያደረጉላቸው ሐዋርያትን አልተቀበሏቸውም ።

#ጌታችንም ሰውን ከሚበሉ አገር አንዱን ገጸ ከልብ ይታዘዝላቸው ዘንድ በሚያዙት ሁሉ ትእዛዛቸውን እንዳይተላለፍ አዘዘው። ሐዋርያትም ወደዚያች አገር ሁለተኛ ይዘውት ገቡ የሀገር ሰዎችም ሐዋርያትን ይበሏቸው ዘንድ ነጣቂዎች የሆኑ አራዊትን አወጡ። ያን ጊዜም ያ ገጸ ከልብ በአራዊቱ ላይ ተነሥቶ እየነጠቀ በላቸው ይህንንም ገጸ ከልብ ከመፍራት የተነሣ ከሰዎች በድንጋጤ የሞቱ ብዙዎች ናቸው።

የሀገር ሰዎች ሁሉም የክብር ባለቤት በሆነ በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አመኑ ከሐዋርያትም እግር በታች ሰገዱ የሚሉአቸውን ሁሉ የሚያደርጉ ታዛዦች ሆኑ። ሐዋርያትም ቤተ ክርስቲያን ሠርተውላቸው ካህናትንም ሹመውላቸው ከእነርሱም ዘንድ ወጥተው #እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ሔዱ።

ሐዋርያ በርቶሎሜዎስም #እግዚአብሔርን የማያውቁ ሰዎች ወደሚኖሩት በባሕር ዳርቻ ወዳሉ አገሮች ሔዶ የክብር ባለቤት በሆነ በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስም ሰበከላቸው በፊታቸውም ተአምራትን አደረገ ሁሉም የ #ጌታችን በሆነች በቀናች ሃይማኖት አመኑ።

ሐዋርያ በርቶሎሜዎስም ከዝሙት ርቀው ንጹሐን እንዲሆኑ ሰዎችን የሚያዝዝ ሆነ። ንጉሥ አግሪጳም ስለርሱ በሰማ ጊዜ በከበረ ሐዋርያ በርቶሎሜዎስ ላይ እጅግ ተቆጣ። በማቅ ከረጢት ውስጥ እንዲአደርጉትና አሸዋ ሞልተው ከባሕር እንዲጥሉት አዘዘ።እንዲሁም ይህን አደረጉበት ምስክርነቱንና ተጋድሎውንም በዚች ዕለት ፈጸመ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባታችን በሐዋርያው በርቶሎሜዎስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ሜልዮስ

በዚህችም ቀን ዳግመኛ የታላቂቱ አገር የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሜልዮስ አረፈ። እርሱም ለአባታችን ሐዋርያና ወንጌላዊ ለሆነ ማርቆስ ሦስተኛ ነው።

ይህም አባት የሮሜ ንጉሥ አስባስያኖስ በነገሠ በዐሥራ አምስት ዓመት ተሾመ ይኸውም የክብር ባለቤት ጌታችን በዐረገ በአርባ ዓመት ነው ክብር ይግባውና የክርስቶስን መንጋዎች በበጎ አጠባበቅ ጠበቃቸው በሹመቱም ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖረ። እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም በፍቅር አንድነት አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ሚልኪ_ቊልዝማዊ

በዚችም ቀን ደግመኛ የቊልዝም ሰው የሆነ ፍጽም ጻድቃ አባ ሚልኪ አረፈ። የዚህም ጻድቅ ወላጆቹ ከቊልዝም አገር ከታላላቆች ወገን ናቸው። እርሷም ከላይኛው ግብጹ አውራጃ ውስጥ ናት እነርሱም በብርና በወርቅ የበለጸጉ ናቸው ለድኖችና ለችግረኞች ምጽዋትን የሚሰጡ #እግዚአብሔርንም እጅግ የሚወዱ ናቸው።

ነገር ግን ልጅ አልነበራቸውም ከዕለታትም በአንዲቱ ከመምህር ዘንድ የሚማሩ ልጆችን አዩ በእጆቻቸውም ሠሌዳዎችን ይዘዋል። በሠሌዳዎቹም ውስጥ እንዲህ የሚል ጽሑፍ አለ እኛ የሕያው #እግዚአብሔር ልጆች እንድንሆን በሕይወታቸው ሳሉ ያስተማሩን አባቶቻችንን አስባቸው አቤቱ ነፍሶቻቸውንም ከተመረጡ ቅዱሳን ጻድቃንና ሰማዕት አሳርፍ።

የአባ ሚልኪ አባትም ከልጆች አንደበት ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ከዚህ ዓለም ከሔድኩ በኋላ ልጅ የሌለኝ እኔን ማን ያስበኛል ወዮልኝ እያለ እጅግ በማዘን ተከዘ።

ከዚህም በኋላ በጾም በጸሎት ምጽዋትንም በመስጠት ከሚስቱ ጋር ምህላ ያዘ። የክብር ባለቤት #እግዚአብሔርም ልመናቸውን ሰምቶ ወንድና ሴት ሁለት ልጆችን በአንዲት ጊዜ ሰጣቸው በእነርሱም ፈጽሞ ደስ አላቸው።

ወደ ክርስትናም በአስገቧቸው ጊዜ ወንዱን ልጅ ሚልኪ አሉት እኀቱን ስፍና አሏት ትርጓሜዋ ርግብ ማለት ነው በመልካም አስተዳደግ አሳደጓቸው።

ለሚልኪ ሰባት ዓመት ሲሆነው አባቱ ወስዶ ለመምህር ሰጠው የብሊያትንና የሐዲሳት መጻሐፍትን ሁሉ ተማረ #መንፈስ_ቅዱስም አደረበት። ከሕፃናቱም ጋር አይጫወትም አይስቅም በቀንም በሌሊትም አዘውትሮ መጸሕፍትን ያነባል እንጂ።

ዕድሜውም ዐሥራ ዘጠኝ ዓመት በሆነው ጊዜ ወላጆቹ ጠርተው ስለ ጋብቻ ሚስት አብግቶ መታሰቢያችው ይሆን ዘንድ ተናገሩት። እርሱም ይህን አልወደደም ነገር ግን በተንኰል እሺ ቃላችሁን ተቀብዬ ያዘዛችሁኝን ሁሉ አደርጋለሁ አላቸው እርሱ ግን ከዓለም ሸሽቶ ያመልጥ ዘንድ ያስባል።
ከዚህም በኋላ አባቱን እንዲህ አለው አባቴ ሆይ ከእኔ ጋራ ለተማሩ ልጆች ለባልንጀሮቼም ምሳ ላደርግላቸው እሻለሁ ምሳንም በባልንጀሮቹ ያዘጋጅላቸው ዘንድ አባቱ አንድ ሺህ የወርቅ ዲናርን ሰጠው። ዳግመኛም ለሚያስፈልገው ሥራ እንዲገለግሉ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮችን አዘዘለት።

ከዚህም በኋላ በፈረስ ተቀምጦ ከአባቱ ፊት ወጣ ሎሌዎቹንም እንዲህ አላቸው መቶ የወርቅ ዲናርን ወስዳችሁ በፍጥነት ምሳ አዘጋጁልን ልጆች ባልንጀሮቼን እኔ ብቻዬን ሒጄ እጠራቸዋለሁ። ዘመዶቹም ሰምተው ተመለሱ እርሱም ብቻውን ሒዶ ያንን ወርቅ ለድኖችና ለምስኪኖች በተነ ፈረሱንም ለአንድ ድኃ ሰጠ በላዩ ካለ ልብስ በቀር ምንም ምን አላስቀረም።

መምጣቱም በዘገየ ጊዜ ፈለጉት ግን አላገኙትም። እያለቀሱም ተመልሰው ለአባቱና ለእናቱ ነገሩአቸው እነርሱም የመረረ ልቅሶን አለቀሱ ከለቅሶ ብዛትም የተነሣ የእናቱ ዐይኖቿ ታወሩ ለሞትም አደረሳት።

ይህ አባ ሚልኪ ግን ጡር ወደምትባል ገዳም ሔደ ይቺም ስሙ አባ አውጊን ለሚባል ለእናቱ ወንድም ገዳሙ ናት።

ይህም አባ አውጊን ብዙ ትሩፋትን የሚሠራ ጻድቅ ሰው ነው በእርሱም ሥር የተመረጡ ሰባ ሁለት መነኰሳት ነዋሪዎች አሉ። አባ ሚልኪም ከእግሩ በታች ሰግዶ አባቴ ሆይ በጥላህ ሥር እንድኖር የምንኲስናንም ልብስ ታለብሰኝ ዘንድ እሻለሁ አለው። አባ አውጊንም ከወዴት አገር ነህ ብሎ ጠየቀው እርሱ አባ ሚልኪም አገሩ ቊልዝም ለአባ አውጊንም የእኀቱ ልጅ መሆኑን ነገረው ሰምቶም ፈጽሞ ደስ አለው።

ሦስት ዓመትም በአመክሮ አቆየው ከዚህም በኋላ የምንኲስናን ልብስ አለበሰው ዜናው በፋርስ አገር ሁሉ እስቲሰማ ትጋትንና ተጋድሎን አበዛ።

#እግዚአብሔርም የመፈወስን ሀብት ሰጥቶት አጋንንትን ከሰዎች ላይ አሰወጥቶ ይሰዳቸዋል።

ከዕለታትም በአንዲቱ ዕለት የዳዊትን መዝሙር እያነበበ ብቻውን ሲጓዝ ታላቅ ጒድጓድ ወዳለበት ደረሰ በአጠገቡም የበለስ ዛፍ አለ ብዙ እረኞችም በዚያ ያለቅሱ ነበር። አባ ሚልኪም ምን ያስለቅሳችኋል አላቸው። እረኞችም እንዲህ ብለው መለሱለት የአገረ ገዢው ልጅ ከእኛ ጋራ ከበለስ ፍሬ ሲበላ ታላቅ ዘንዶ ወጥቶ ልጁን ውጦ ወደ ጒድጓድ ተመለሰ አሉት። እረኞችም እየነገሩት ሳለ የሕፃኑ አባት ልብሱን በመቅደድ ፊቱንም በመጽፋት ከብዙ ሰዎች ጋር መጣ ቅዱስ ሚልኪንም ስለ ልጁ ማለደው። አባ ሚልኪም ልጄ ሆይ በ #እግዚአብሔር ታመን እንጂ አትፍራ የጌትነቱንም ድንቅ ሥራ ታያለህ አለው።

ያን ጊዜም ፈቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ ረጅም ጸሎትን ጸለየ ጸሎቱንም በጨርሰ ጊዜ ዘንዶውን ጠርቶ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስም ሕፃኑን ይተፋው ዘንድ አዘዘው ምንም ሕማም ሳይነካው ጒዳትም ከቶ ሳያገኘው ወዲያውኑ ተፋው በከይሲውም አድሮ ያለ ሰይጣን እንዲህ ብሎ ጮኸ የቊልዝም ሰው ሚልኪ ከአንተ የተነሣ ወዴት ልሒድ ይህንንም ብሎ እንደ ጢስ ተበተነ።

የሕፃኑም አባት ይህን ድንቅ ሥራ ልጁም እንደ ዳነ በአየ ጊዜ እጅግ ደስ አለው። ለቅዱስ አባ ሚልኪም ብዙ ወርቅትና ብር አመጣ አባ ሚልኪም መቀበልን አይሆንም አለ ግን በጽድቅ ሥራ አንድ እንድንሆን ገዳምን ሥራ አለው:: አገር ገዢው የሕፃኑ አባትም ደስ አለው ሦስት መቶ የመነኰሳት ቤቶችን ሠራ ዙሪያውንም በግንብ አጠረ መዝጊያውንም ከብረት ሠራ::

ቤተክርስቲያንንም ሲሠሩ ሦስት መቶ ሰዎች ሊአንቀሳቅሷት የማይችሉ ለማዕዘን የምትሆን ደንጊያን አገኙ በጻድቁ በአባ ሚልኪ ጸሎትም ራስዋ ተነሥታ እንደሚፈልጓት ሁና ተሠራች::

ከዚህም በኋላ በዚያ ገዳም ሦስት መቶ ሰዎች ተሰብስበው የተመረጡ መነኰሳትን ሆኑ:: የቅዱስ አባ ሚልኪም ዜናው በሀገሩ ሁሉ ተሰምቶ በየዓይነቱ ደዌ ያለባቸውን በክፉዎች አጋንንትም የተያዙትን ወደርሱ የሚያመጡአቸው ሆኑ ሁሉም በጸሎቱ ይፈወሱ ነበር::

በዚሁ ጻድቅ ጸሎትና ምልጃ የፋርስና የሮም ሰዎች ተጠብቀው የሚኖሩ ሆኑ::

ከዚህም ብኋላ አባ ሚልኪ ከዋሻ ውስጥ ገብቶ የዋሻውን በር ዘጋ በልቡም እስከ ዕድሜዬ ፍጻሜ ከዚህ ዋሻ አልወጣም ብሎ ቃል ገባ::

የበጎ ሥራ ጠላት ሰይጣንም እንዲህ ብሎ ዛተበት ጠብቀኝ እኔ ከዚህ ከበዓትህ አስወጥቼ የተሳልከውን ቃል አፈርሳለሁ ይህንንም ብሎ ሒዶ በሮም ንጉሥ ልጅ ላይ አድሮ አሳበዳት እርሷም እየጮኸች እንዲህ አለች ከቊልዝማዊው ሚልኪ በቀር የሚያድነኝ የለም::

ንጉሥ አባቷም ሰምቶ ከወታደሮቹ ውስጥ አራት መቶ ሰዎችን ላከ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው በሁሉ ቦታ ተግታችሁ አባ ሚልኪን ፈልጋችሁ ወደ እኔ አምጡት እኔም በጎ የሆነ ዋጋችሁን እከፍላችኋለሁ:: ይህ ካልሆነ ግን ራሶቻችሁን በሰይፍ ልቆርጥ ምያለሁ::

የተላኩ ወታደሮችም ፈልገው በጭንቅ አገኙትና ለብፁዕ አባ ሚልኪ የንጉሡን መልእክት ልጁን ጋኔን እንደአደረባት የምትናገረውንም ነገር ነገሩት። እርሱም እኔ ሽማግሌ ሰው ነኝ ወደ ሮም አገር ለመሔድ አልችልም አላቸው። እነርሱም አባታችን ሆይ አንተ ከእኛ ጋር ካልሔድክ ንጉሥ በሰይፍ ቆርጦ እንደሚገድለን ነግሮናል አሉት።ስምቶም እጅግ አዘነ እንዲህም አላቸው ልጆቼ ሒዱ እኛ እርስ በርሳችን በሮም ከተማ መግቢያ እንገናኛለን።

ቃሉንም ሰምተው ሔዱ በዓመቱም ፍጻሜ ከሮሜ ከተማ መግቢያ መድረሳቸውን በ #መንፈስ_ቅዱስ አውቆ ወደ #እግዚአብሔር ጸለየ ያን ጊዜም ደመና ተሸክማ ከሮሜ ከተማ መግቢያ አደረሰችው። የንጉሥ መልእክተኞችም በአዩት ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው።ለንጉሡም የከበረ አባ ሚልኪ መምጣቱን ነገሩት።

እርሱም ወጥቶ በክብር ተቀብሎ ወደ እልፍኙ አስገባው ስለ ልጁ ስለ ደዌዋ ነገረው ቅዱስ አባ ሚልኪም አምጧት ብሎ አዘዘ። በአመጧትም ጊዜ ጋኔኑ ጥሎ አረፋ አስደፈቃት ሞተች ብለው እስከሚጠራጠሩ። ያን ጊዜም አባ ሚልኪ ተነሥቶ ጸለየ በፊቷ ላይም ውኃን ረጨ ዘይትንም ቀባት ሰይጣንንም ከርሷ ይወጣ ዘንድ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስም አዘዘው። ያን ጊዜም በጥቁር ባርያ አምሳል ከእርሷ ወጣ።

ቅዱስ አባ ሚልኪም ሰይጣንን በሥውር ይዞ በቤት ውስጥ ዘጋበት በዚያም አሠረው። ንጉሡም ይህን ድንቅ ሥራ አይቶ ከእግሩ በታች ሰገደ ለገዳሙ ለሚአስፈልገው ነገር እንዲሆነው ብሎ ብዙ ወርቅና ብርን አመጣለት እርሱም መቀበልን እምቢ አለ።

ንጉሡም አባቴ ሆይ ከዚህ ተቀመጥ እኔም ገዳም እሠራልሃለሁ አለው አባ ሚልኪም ልጆቼን መተው አይሆንልኝም አለው ግን በሽተኞችን እየፈወሰ በሮሜ ከተማ ጥቂት ቀኖች ተቀመጠ።

ወደ አገሩ ይመለስ ዘንድ ተነሥቶ በወጣ ጊዜ ንጉሡም ከመኳንንቱ ጋራ ሊሸኘው ተነሣ። ከንጉሥ ግቢ በስተውጭ የንጉሥ ፈረሶች የሚጠጡበት ታላቅ የደንጊያ ገንዳ የተበሳ ታላቅ የሆነ ደንጊያን አባ ሚልኪ አይቶ ንጉሡን ይህን ገንዳ ይህንንም የተበሳ ታላቅ ደንጊያ ለገዳም አገልግሎት እሻዋለሁና ስጠኝ አለው። ንጉሡም ዐሥራ አራት ሰዎች ከምድር ከፍ ሊአደርጉት የማይቻላቸው ወደ ገዳምህ እንዴት ይደርሳል ተሸክሞ ወደ ፈለግከው ቦታ የሚያደርስ ኃይል ካለህ እኔ ሰጠሁህ አለው።

ያን ጊዜም ቅዱስ አባ ሚልኪ ሰይጣንን ከአሠረበት ቦታ አምጥቶ ያንን የተበሳ ደንጊያ በአንገቱ ውስጥ አንጠለጠለ ገንዳውንም ተሸክሞ በፊት በፊቱ ተገልጦ እንዲጓዝ አዘዘው። ሰይጣንም እነዚያን ገንዳዎች የተበሳውንም ደንጊያ ተሸክሞ በፊት በፊቱ ይጓዝ ጀመረ። ንጉሡና የተሰበሰቡት ሕዝብ አይተው እጅግ አደነቁ ለሚፈሩት ለሚያመልኩት ይህን ያህል ጸጋ የሚሰጥ ምስጉን #እግዚአብሔርንም አመሰገኑት።
የከበረ አባ ሚልኪም እነዚያን ደንጊያዎች ሰይጣንን አሸክሞ ወደ ገዳሙ አደረሰው በገዳሙም ደጃፍ አጠገብ እንዲአስቀምጣቸው አዘዘው እስከዛሬም በዚያ ይኖራሉ። ሰይጣንንም ዳግመኛ ወጥቶ እንዳይፈትነው በዓለት ዋሻ ውስጥ ዘግቶ በ #መስቀል ምልክት ለዘላለሙ አሸገው።

አባ ሚልኪም ከመነኰሰ አርባ አምስት ዓመታት ሲሆነው እንዲህ የሚል ቃል ከሰማይ ወደርሱ መጣ እነሆ የምታርፍበት ቀን ቀርቧል ከሦስት ቀን በቀር አልቀረህም ወደ ዘላለምም ተድላ ደስታ ትሔዳለህ።

ያን ጊዜም ልጆቹን ሁለ ጠርቶ ሰይጣን ከሚያመጣው ስሕተት እንዲርቁና እንዲጠብቁ በፍርሃትም ሁነው #እግዚአብሔርን እንዲአገለግሉ አዘዛቸው። ከሦስት ቀንም በኋላ ቅዱሳን አባቶች መነኰሳት አባ እንጦንስ አባ መቃርስ አባ ሲኖዳ አባ ብሶይ አባ ጳኵሚስ ወደርሱ መጥተው እንዲህ አሉት ወንድማችን ወደእኛ ና ከእኛ ጋርም ፍጹም ተድላ ደስታ ባለበት በ #እግዚአብሔር መንግሥት ደስ ይበልህ ይህንንም ሲሉት ነፍሱ ከሥጋው ወጣች። መላእክትም በዓለም ውስጥ በገድል በትሩፋት የደከመ ለዘላለሙ በሕይወት ይኖራል እያሉ በክብር በምስጋና ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት አወጡት።

ከዚህም በኋላ ጳጳሳት ኤጲስቆጶሳት ሁሉም ካህናት ተሰብስበው ገነዙት በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ ቀበሩት ከመቃብሩም ቍጥር የሌላቸው ታላላቅ የሆኑ ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ።

#እግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ጻድቅ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም_1_ግንቦት እና #ከገድላት_አንደበት)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_1_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ቆሮ 6
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ አብረንም እየሠራን የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ እንዳትቀበሉ ደግሞ እንለምናለን፤
² በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ በመዳንም ቀን ረዳሁህ ይላልና፤ እነሆ፥ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤እነሆ፥ የመዳን ቀን አሁን ነው።
³ አገልግሎታችንም እንዳይነቀፍ በአንዳች ነገር ማሰናከያ ከቶ አንሰጥም።
⁴ ነገር ግን በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን፤
⁵ በብዙ መጽናት፥ በመከራ፥ በችግር፥ በጭንቀት፥ በመገረፍ፥ በወኅኒ፥ በሁከት፥ በድካም፥ እንቅልፍ በማጣት፥
⁶ በመጦም፥ በንጽህና፥ በእውቀት፥ በትዕግሥት፥ በቸርነት፥ በመንፈስ ቅዱስ፥ ግብዝነት በሌለው ፍቅር፥ በእውነት ቃል፥
⁷ በእግዚአብሔር ኃይል፥ ለቀኝና ለግራ በሚሆን በጽድቅ የጦር ዕቃ፥ በክብርና በውርደት፥
⁸ በክፉ ወሬና በመልካም ወሬ ራሳችንን እናማጥናለን፤ አሳቾች ስንባል እውነተኞች ነን፤
⁹ ያልታወቁ ስንባል የታወቅን ነን፤ የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን፤ የተቀጣን ስንሆን አንገደልም፤
¹⁰ ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፤ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፤ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ያዕቆብ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁸ እናንተ ደግሞ ታገሡ፥ ልባችሁንም አጽኑ፤ የጌታ መምጣት ቀርቦአልና።
⁹ ወንድሞች ሆይ፥ እንዳይፈረድባችሁ እርስ በርሳችሁ አታጉረምርሙ፤ እነሆ፥ ፈራጅ በደጅ ፊት ቆሞአል።
¹⁰ ወንድሞች ሆይ፥ የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ የሆኑትን በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያትን ተመልከቱ።
¹¹ እነሆ፥ በትዕግሥት የጸኑትን ብፁዓን እንላቸዋለን፤ ኢዮብ እንደ ታገሠ ሰምታችኋል፥ ጌታም እንደ ፈጸመለት አይታችኋል፤ ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነውና።
¹² ከሁሉም በፊት፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ በሰማይ ቢሆን በምድርም ቢሆን በሌላ መሐላም ቢሆን በምንም አትማሉ፤ ነገር ግን ከፍርድ በታች እንዳትወድቁ ነገራችሁ አዎን ቢሆን አዎን ይሁን፥ አይደለምም ቢሆን አይደለም ይሁን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² በሐዋርያትም እጅ ብዙ ምልክትና ድንቅ በሕዝብ መካከል ይደረግ ነበር፤ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው በሰሎሞን ደጅ መመላለሻ ነበሩ።
¹³ ከሌሎችም አንድ ስንኳ ሊተባበራቸው የሚደፍር አልነበረም፥
¹⁴ ሕዝቡ ግን ያከብሩአቸው ነበር፤ የሚያምኑትም ከፊት ይልቅ ለጌታ ይጨመሩለት ነበር፤ ወንዶችና ሴቶችም ብዙ ነበሩ።
¹⁵ ስለዚህም ጴጥሮስ ሲያልፍ ጥላውም ቢሆን ከእነርሱ አንዱን ይጋርድ ዘንድ ድውያንን ወደ አደባባይ አውጥተው በአልጋና በወሰካ ያኖሩአቸው ነበር።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_1_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"አድኅንኒ እምእለ ሮዱኒ እስመ ይኄይሉኒ። ወአውጽነ እሞሕቅ ለነፍስየ። ከመ እግነይ ለስምከ እግዚኦ"። መዝ 141፥6-7።
"እጅግ ተቸግሬአለሁና ወደ ልመናዬ አድምጥ፤ በርትተውብኛልና ከሚያሳድዱኝ አድነኝ። አቤቱ፥ ስምህን አመሰግን ዘንድ ነፍሴን ከወህኒ አውጣት፤ ዋጋዬን እስክትሰጠኝ ድረስ ጻድቃን እኔን ይጠብቃሉ"።
መዝ 141፥6-7።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_1_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 11
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ኢየሱስም አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ማዘዝ በፈጸመ ጊዜ በከተሞቻቸው ሊያስተምርና ሊሰብክ ከዚያ አለፈ።
² ዮሐንስም በወህኒ ሳለ የክርስቶስን ሥራ ሰምቶ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከና፦
³ የሚመጣው አንተ ነህን? ወይስ ሌላ እንጠብቅ? አለው።
⁴ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ሄዳችሁ ያያችሁትን የሰማችሁትንም ለዮሐንስ አውሩለት፤
⁵ ዕውሮች ያያሉ አንካሶችም ይሄዳሉ፥ ለምጻሞችም ይነጻሉ ደንቆሮችም ይሰማሉ፥ ሙታንም ይነሣሉ
⁶ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤ በእኔም የማይሰናከለው ሁሉ ብፁዕ ነው።
⁷ እነዚያም ሲሄዱ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ሊናገር ጀመረ እንዲህም አለ፦ ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ?
⁸ ነፋስ የሚወዘውዘውን ሸምበቆን? ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ቀጭን ልብስ የለበሰ ሰውን? እነሆ፥ ቀጭን ልብስ የለበሱ በነገሥታት ቤት አሉ።
⁹ ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችኋለሁ፥ ከነቢይም የሚበልጠውን።
¹⁰ እነሆ፥ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ ተብሎ የተጻፈለት ይህ ነውና።
¹¹ እውነት እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ በመንግሥተ ሰማያት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል።
¹² ከመጥምቁም ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፥ ግፈኞችም ይናጠቋታል።
¹³ ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ፤
¹⁴ ልትቀበሉትስ ብትወዱ፥ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ ነው።
¹⁵ የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።
¹⁶ ነገር ግን ይህን ትውልድ በምን እመስለዋለሁ? በገበያ የሚቀመጡትን ልጆች ይመስላሉ፥ እነርሱም ባልንጀሮቻቸውን እየጠሩ።
¹⁷ እንቢልታ ነፋንላችሁ ዘፈንም አልዘፈናችሁም ሙሾ አወጣንላችሁ ዋይ ዋይም አላላችሁም ይሉአቸዋል።
¹⁸ ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ፥ እነርሱም፦ ጋኔን አለበት አሉት።
¹⁹ የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፥ እነርሱም፦ እነሆ፥ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፥ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ ይሉታል። ጥበብም በልጆችዋ ጸደቀች።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱሳን_ሐዋርያት ወይም የ #ቅዱስ_ዮሐንስ_ወልደ ነጎድጓድ ቅዳሴ ነው። መልካም የመልአኩ የቅዱስ ራጉኤል በዓለ ሲመቱ፣ የሐዋርያው የቅዱስ በርተሎሜዎስም የዕረፍት በዓልና የታላቁ አባት የአባ ሚልኪ የዕረፍት በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

🌻አዲሱን ዓመት ንስሐ ገብተን #ቅዱስ_ሥጋውንና #ክቡር_ደሙን የምንቀበልበት ዓመት ያድርግልን🌻
#መስከረም_2

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ሁለት በዚህች ቀን #ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ ሰማዕት ሆነ፣ #ቅዱስ_ዳስያ_ሰማዕት ሰማዕት ሆነ፣
#ቅዱስ_ዲዲሞስና_የቅድስት_መሪና መታሰቢያቸው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ

መስከረም ሁለት በዚህች ቀን የካህኑ የዘካርያስ ልጅ የከበረ አጥማቂው ዮሐንስ ሕግን አፍራሽ በሆነ በንጉሥ ሄሮድስ እጅ ሰማዕት ሆነ።

ይህም እንዲህ ነው በፊልጶስ ሚስት በሄሮድያዳ ምክንያት ነቢዩ ዮሐንስ በገሠጸው ጊዜ ፊልጶስ ወንድሙ ስለሆነ ቅዱስ ዮሐንስም የወንድምህን ሚስት ልታገባ አይገባህም ይለው ነበርና።

ቅዱስ ዮሐንስም ሄሮድስን የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን ስለማግባቱና ሌላም ያደርገው ስለነበረ ክፉ ሥራ ሁሉ ይገሥጸው ነበር። ደግሞም በተግሣጽ ላይ ተግሣጽን ጨመረ። ስለዚህም ዮሐንስን ተቀየመውና በግዞት ቤት አኖረው።

ሄሮድስም ዮሐንስን ይፈራው ነበር ጻድቅ ቅዱስ ሰው እንደሆነ ያውቅ ነበርና ብዙ ይጠባበቀውም ነበር። ሄሮድስ የተወለደባትን ቀን በዓል የሚያከብርባት ዕለት ነበረች መኳንንቱን አለቆቹን መሣፍንቱን ሹሞቹን በገሊላ አገር ያሉትን ታላላቅ ሰዎች ግብር አገባ።

የሄሮድያዳ ልጅም ወደ አዳራሹ ገብታ ዘፈነች ሄሮድስንም ደስ አሰኘችው ከእርሱ ጋር በማዕድ የነበሩትንም ንጉሡም ያቺን ብላቴና የምትሺውን ለምኚኝ እሰጥሻለሁ አላት። እስከ መንግሥቱ እኩሌታ ድረስም ቢሆን የለመነችውን ሊሰጣት ማለላት።

ወጥታም እናቷን ምን ልለምነው አለቻት እናቷም የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ አለቻት። ያን ጊዜም እየሮጠች ወደ ንጉሡ ገብታ የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ በወጭት አሁን እንድትሰጠኝ እሻለሁ ብላ ለመነችው። ንጉሡም ስለ መሐላው አብረውት ስለ ነበሩትም ሰዎች አዘነ እምቢ ሊላት ግን አልወደደም።

ያን ጊዜም ባለወጎችን ላከ በእሥር ቤትም ሳለ የዮሐንስን ራስ ቆረጡ ራሱንም በወጭት አምጥተው ለዚያች ብላቴና ሰጡአት እርሷም ወስዳ ለእናቷ ሰጠች። በዚያችም ቀን የቅዱስ ዮሐንስ ራስ ከሄሮድያዳ ከእጆቿ ላይ ወደ አየር ስለ በረረች ታላቅ ድንጋፄ ሆነ።

ደግሞም ሄሮድስ ሆይ የወንድምህን ሚስት ልታገባ አይገባህም እያለች በመጮኽ ዘልፋዋለችና። ደቀ መዛሙርቱም በሰሙ ጊዜ መጥተው በድኑን ወስደው ቀበሩት።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበረ በአጥማቂው ቅዱስ ዮሐንስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዳስያ_ሰማዕት

በዚችም ቀን በግብጽ ውስጥ ታዕዳ ከሚባል አገር ዳስያ ሰማዕት ሆነ። ይህንንም ቅዱስ የእንዴናው አገረ ገዥ አርያኖስ አሠቃየው ጽኑ ሥቃይንም ከአሠቃየው በኋላ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዲዲሞስና_የቅድስት_መሪና_ሰማዕት

በዚህችም ቀን የሰማዕት ዲዲሞስና የቅድስት መሪና መታሰቢያቸው ነው።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም_3)
2024/09/21 11:37:40
Back to Top
HTML Embed Code: