Telegram Web Link
#ጌታዬ_ኢየሱስ_ሆይ ከሁሉ ይልቅ በሦስትነትህ መታመን ይበልጣል። አንተ በወለደችህ በ #ማርያም መማጸን መልካም ዕድል። #ፈጣሪዬ_ክርስቶስ_ሆይ ከቤተ መንግሥትና ከቤተ ክህነት ወገን የአንተን ሰው መሆን የሚጠራጠር ወይም አምላክ ሰው፤ ሰው አምላክ መሆኑን የሚክድ ቢኖር ዕመቀ እመቃት መንጸፈ ደይን ወርዶ ይንኮታኮት።

#መልክአ_ኢየሱስ
#ነሐሴ_30

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሠላሳ በዚች ቀን ከዐሥራ ስድስቱ ነቢያት አንዱ #ታላቅ_ነቢይ_ሚልክያስ ያረፈበት እና ጌታ ባሕር ውስጥ #ለሐዋርያ_እንድርያስ በሊቀ ሐመር አምሳል ተገልጦ ድንቅ ተአምር ያደረገለት ቀን ነው፣ የእናታችን #ቅድስት_ዜና_ማርያም የእረፍቷ መታሰቢያ ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ነቢዩ_ሚልክያስ

ነሐሴ ሠላሳ በዚች ቀን ከዐሥራ ስድስቱ ነቢያት አንዱ ታላቅ ነቢይ ሚልክያስ አረፈ። ይህም ነቢይ የእስራኤል ልጆች ከተሰደዱበት ከባቢሎን ሀገር በተመለሱ ጊዜ የ #እግዚአብሔርን ትእዛዝ በመተላለፋቸው ገሥጿቸዋል።

ሁለተኛም ነቋር ስለሆነ መሥዋዕት ስለ አሥራትና በኵራት ገሥጿቸዋል። በዚህ ነቢይ አንደበት #እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናግሯልና ርኅራኄ አድርጋችሁ ምጽዋትን መጽውቱ፣ ዐሥራቴንና በኵራቴንም አስገቡና እስቲ ፈትኑኝ እኔ ከሰማይ ዝናሙን ባላወርድላችሁ በረከትንም አስቲበቃችሁ ባልጨምርላችሁ የምድራችሁንም ፍሬ ነቀዝና መሰክ እንዳይበሉት እከለክላለሁ።

ዳግመኛም ከክብር ባለቤት #መድኃኒታችን_ክርስቶስ አስቀድሞ መጥምቁ ዮሐንስ ስለ መምጣቱ ስለ ነቢዩ ኤልያስም ተናገረ። ደግሞ ስለ አይሁድ የሥርዓተ ክህነት ፍጻሜ ተናገረ በአሕዛብም አገር ውስጥ ለ #እግዚአብሔር የሚቀበላቸውን መሥዋዕት የሚያሳርጉ ዕውነተኞች ንጹሐን ካህናት እንዳሉ ገለጠላቸው።

በበጎ ተጋድሎውም #እግዚአብሔርን ከአገለገለ በኋላ ከዚህ ዓለም በመፍለስ በሰላም አረፈ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ነብይ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።


✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሐዋርያው_ቅዱስ_እንድርያስ

በዚችም ቀን #ጌታችን በባሕር ውስጥ ለሐዋርያ እንድርያስ በሊቀ ሐመር አምሳል ተገልጦ ድንቅ ተአምር አደረገለት።

እንድርያስም #ጌታችንን በመርከብህ አሳፍረን ነገር ግን የምንከፍልህ የመርከብ ዋጋ የለንም አለው። በሊቀ ሐመር የተመሰለ #ጌታችንም ስለምን የላችሁም አለው እንድርያስም በከረጢታችን ወርቅን፣ ብርን እንዳንይዝ ስለአዘዘን ነው አለው። #ጌታችንም እንዲህ ከሆነ ወደ መርከቤ ወጥታችሁ ተሳፈሩ አላቸው ያንጊዜም ወደ መርከብ ወጥተው ተሳፈሩ።

ከዚህም በኋላ #ጌታችን እንድርያስንና ደቀ መዛሙርቱን ከባሕሩ ማዕበል የተነሣ መታገሥ እንድትችሉ ተነሥታችሁ እንጀራ ብሉ አለ። እንድርያስም አድንቆ እንዲህ አለው በመንግሥተ ሰማያት የሕይወት እንጀራ #እግዚአብሔር ይስጥህ። ደቀ መዛሙርቱ ግን በባሕር ላይ ጉዞ ስለአልለመዱ ከባሕሩ ማዕበል ፍርሀት የተነሣ መብላት መነጋገርም ተሳናቸው ።

#ጌታችንም እንድርያስን ደቀ መዛሙርትህን ወደ ምድር እንዲወርዱ እዘዛቸው ሲፈሩ አያቸዋለሁና ይህ ካልሆነ እንዳይፈሩ አንተ የ #ኢየሱስ ደቀ መዝሙሩ ከሆንክ ጣዕም ባለው ቃል አስተምራቸው እነሆ ከየብስ ርቀናልና አለው። #ጌታችንም መርከቡን መቅዘፍ ጀመረ እንድርያስም ማስተማርና ማጽናናት ያዘ በልቡም ጸለየ ያን ጊዜም ከባድ እንቅልፍን አንቀላፉ ስለተኙለትም እንድርያስ ደስ አለው።

እንድርያስም ወደ #ጌታችን ተመልሶ እንዲህ አለው ዐሥራ አራት ጊዜ በባሕር ላይ ጒዞ አድርጌአለሁ እንዳንተ የሚቀዝፍ አላገኘሁም። #ጌታም መልሶ እንዲህ አለው እኛስ በባሕር ላይ ስንጓዝ ሁል ጊዜ እንቸገራለን። ነገር ግን አንተ የክብር ባለቤት የ #ኢየሱስ_ክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንደሆንክ ባሕር ስለአወቀችህ ማዕበሏን በአንተ ላይ አላነሣችም እንድርያስም በታላቅ ቃል እንዲህ ብሎ ጮኸ። የክብር ባለቤት #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ አመሰግንሃለሁ ከሚያከብርህ ሰው ጋር ተገናኝቼ ተነጋግሬአለሁና።

ከዚህም በኋላ #ጌታችን እንድርያስን እንዲህ አለው አንተ የ #ክርስቶስ ደቀ መዝሙሩ ነህና ንገረኝ። አይሁድ የ #እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ስለምን አላመኑም የሠራውን ብዙ ድንቅ ተአምርን ሰምተናልና አለው። እንድርያስም እንዲህ አለው አዎን ወንድሜ እርሱ የ #እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ገልጦልናል አንካሶችንም በትክክል እንዲሔዱ አድርጓልና፣ ደንቆሮዎችንም አሰምቷልና፣ ዲዳዎችንም አናግሮአልና፣ ለምጻሞችንም አንጽቷልና፣ ውኃውንም ወይን አድርጓልና፣ አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣን አንሥቶ ያዘ ሕዝቡንም በመስክ ሣር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ ሣሩም እንጀራ እስቲለብስ ድረስ በልተው ጠገቡ የተረፈውንም በብዙ ቅርጫቶች አነሣን ይህም ሁሉ ሲሆን አላመኑም።

#ጌታ_ኢየሱስም እንዲህ አለው ይህን ያደረገ በግልጥ ነው ወይስ በሥውር። እንድርያስም እንዲህ አለው ይህንስ በግልጥ ነው ያደረገ በሥውር ያደረገውም አለ ግን የምትፈትነኝ መሰለኝ #ጌታችንም እንዲህ አለው ወንድሜ ሆይ ልቤን ደስ ስለሚላት ነውና ንገረኝ።

እንድርያስም እንዲህ አለው ልጄ ሆይ በጎ ሥራህን ሀሉ #እግዚአብሔር ይፈጽምልህ አሁንም ስማ #ጌታችን ያደረገውን ተአምር እኛ ዐሥራ ሁለታችን ሐዋርያቶቹ ከእርሱ ጋራ ስንጓዝ ከሊቃነ ካህናትና ከሕዝቡ ብዙዎች አሉ። ወደ ምኵራብም ደረስን #ጌታችንም እንዲህ አለ በሰማይ ባሉ በኪሩቤልና በሱራፌል አምሳል በምድር ላይ ሰው የሠራትን ይቺን የተቀረጸች ሥዕል ታያላችሁን።

ከዚህም በኋላ ወደሥዕሊቱ ተመልሶ ብልህ ሰው የተጠበበብሽ የሰማያውያን መልክን ያደረግሽ አንቺን እላለሁ ከቦታሽ ተነቅለሽ ውረጂ የካህናት አለቆችንም ወቀሻቸው እኔም ዕሩቅ ብእሲ ወይም #እግዚአብሔር እንደሆንኩ መስክሪ አላት። ወዲያውኑ ከቦታዋ ተነቅላ ወረደች እንደሰውም በመናገር እንዲህ አለች እናንተ የደነቆራችሁ አይሁድ የራሳችሁ መደንቆር ያልበቃችሁ ሌሎችንም ለማደንቆር የምትሹ ለድኅነታችሁ ሰው የሆነ #እግዚአብሔርን እንዴት ዕሩቅ ብእሲ ትሉታላችሁ አስቀድሞ ሰውን የፈጠረው በንፍሐት ልጅነትንም የሰጠው ይህ ነው።

አብርሃምን የተናገረው፣ ይስሐቅንም ከመታረድ ያዳነው፣ ያዕቆብንም ወደ አገሩ ያስገባው ይህ ነው ለሚፈሩት በረከትን የሚሰጥ ለማይታዘዙለት ቅጣትን የሚያዘጋጅ ይህ ነው ።

እውነት እነግራችኋላሁ እናንተ ስለምትክዱት ሕጉንና ሥርዓቱንም ትለውጣላችሁና ስለዚህ እነሆ መስዋዕታችሁ ይሻራል ምኵራቦቻችሁም በዋሕድ ወልደ #እግዚአብሔር ስም አብያተ ክርስቲያናት ይሆናሉ። ይህንንና የሚመስለውን ተናግራ ዝም አለች።

እኛም የካህናት አለቆችን መልሰን እንዲህ አልናቸው እነሆ ቅርጺቱ ሥዕል ተናግራ ወቀሰቻችሁ ታምኑ ዘንድ ይገባችኋል። የካህናት አለቆችና አይሁድም እንዲህ አሉን ይህ የሚያናግረው በሥራይ ነው አብርሃምን በወዴት አገኘው ከሞተ ዘመኑ ብዙ ነውና።

#ጌታ_ኢየሱስም ወደ ቅርጺቱ መለስ ብሎ እንዲህ አላት አብርሃምን እንዳነጋገርኩት አላመኑምና ሔደሽ እንዲህ በይው። አስቀድሞ አዳምን የፈጠረው፣ አንተንም ወዳጁ ያደረገህ፣ አንተ ልጆችህ ይስሐቅና ያዕቆብን ይዘህ ተነሥ ከመቃብርም ወጥተህ ወደዚህ ኑ የካህናት አለቆችን ትወቅሱአቸው ዘንድ እኔ የማውቃችሁና የተነጋገርኳችሁ መሆኔን አስረዷቸው። ቅርጺቱም ሥዕል ይህን ሰምታ እያየናት ሔደች ወደ አብርሃምም መቃብር ደርሳ በውጭ ቁማ ጠራቻቸው። ወዲያውኑ ከሦስቱ አርእስተ አበው ጋር ዐሥራ ሁለቱ ወጡ ከእኛ ውስጥ ወደ ማን ነው የተላክሽ አሏት። ቅርጺቱም እንዲህ ብላ መለሰች ወደ ሦስቱ የአባቶች አለቆች ነው እናንተ ግን እስከ ትንሣኤ ሙታን ድረስ ተኙ ያን ጊዜም ወደ መቃብራቸው ተመለሱ።
እሊህ ሦስቱ አባቶችም የካህናት አለቆችና እኛ ወደ አለንበት ከቅርጺቱ ሥዕል ጋር መጥተው ወቀሷቸው የ #እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነም ነገሩአቸው።

ከዚህም በኋላ #ጌታችን አባቶችን ወደቦታችሁ ሒዱ አላቸው ወዲያው ተመለሱ ቅርጺቱንም ወደቦታሽ ተመለሽ አላት እርሷም ወደ ቀደመው አኗኗርዋ ተመለሰች ይህንንም አይተው የካህናት አለቆች አላመኑም ሌላም ብዙ አለ ብነግርህ መወሰን አትችልም ነገር ግን ለብልህ ጥቂት ቃል ትበቃዋለች ለሰነፍ ግን ቢነግሩት በቁም ነገር ላይ አይታመንም።

ከዚህም በኋላ #ጌታችን ማነጋገሩን ገታ ራሱንም እንደሚያንቀላፋ አደረገ እንድርያስም አንቀላፋ እንድርያስንና ደቀ መዛሙርቱን እንዲሸከሙአቸውና ሊገቡበት ወደሚሹት አገር በውጭ እንዲአኖሩዋቸው መላእክትን አዘዛቸው።

ከዚህም በኋላ እንድርያስ በነቃ ጊዜ ዐይኖቹን ገለጠ የከተማውንም በር ተመለከተ በየብስም ላይ እንዳለ አውቆ ደነገጠ አደነቀም። ደቀ መዛሙርቱንም አነቃቸውና እንዲህ አላቸው #ጌታችንን በባሕር ላይ ሳለን ያላወቅነው ምን አደረገብን ሲፈትነን መልኩን ለውጦ እንደ ሰው ሁኖ ታይቶናልና።

ደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አሉት እኛም በጌትነቱ ዙፋን ላይ ሁኖ የመላእክት ሠራዊት ሁሉ በዙሪያው ሁነው #ጌታችንን አየነው አብርሃምን፣ ይስሐቅን፣ ያዕቆብንም ቅዱሳንን ሁሉ አየናቸው ንጉሥ ዳዊትም በመሰንቆ ይዘምር ነበር። እናንተንም ዐሥራ ሁለት ሐዋርያት በፊቱ ቁማችሁ ዐሥራ ሁለቱንም የመላእክት አለቆች በፊታችሁ ሌሎች መላእክት በኋላችሁ ሁነው አየናችሁ። #እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስንም መላእክትን እንዲህ ብሎ ሲያዛቸው ሰማነው የሚሉአችሁን ሁሉ ሐዋርያትን ስሟቸው።

እንድርያስም በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ አለው ይህን ድንቅ ምሥጢር ያዩ ዘንድ ደቀ መዛሙርቱ የሚገባቸው ሆነዋልና። ከዚህም በኋላ እንድርያስ ዐይኖቹን ወደ ሰማይ አቅንቶ እንዲህ ብሎ በታላቅ ድምጽ ጮኸ #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሆይ ከእኛ ከባሮችህ ሩቅ እንዳልሆንክ አወቅሁ። ነገር ግን በመርከብ ላይ እኔ እንደማስተምረው ሰው መስለኸኝ በድፍረት ተናግሬሃለሁና #ጌታዬ ይቅር በለኝ ።

በዚያንም ጊዜ የክብር ባለቤት #መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ለእንድርያስ ዳግመኛ ተገለጠለት እንዲህም አለው። አዎን እኔ ነኝ በሊቀ ሐመር አምሳል በባሕር ውስጥ የተገለጥኩልህና መርከቡን የቀዘፍኩልህ። አትፍራ አትደንግጥ እኔ ከአንተ ጋራ እኖራለሁ ይህንንም ብሎ ወደ ሰማያት በክብር ዐረገ እንድርያስም መንገዱን ሄደ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጌቶቻችን ሐዋርያት በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ጻድቋ_ቅድስት_ዜና_ማርያም

በዚህች ዕለት የእናታችን ቅድስት ዜና ማርያም የእረፍቷ መታሰቢያ ነው፡፡ ከአባቷ ከገብረ ክርስቶስ ከእናቷ አመተ ማርያም በ11መቶ ክፍለ ዘመን በቅዱስ ላሊበላ ዘመነ መንግሥት በምድ ነጋሲ በጎጃም ምድር ግንቦት 30 ቀን የተወለደች ሲሆን ለአቅመ ሔዋን በደረሰች ጊዜ በንፅህ ድንግልና በምድረ ሂንፍራንስ ጣራ ገዳም አካባቢ በሚገኘው በአቡነ እንድርያስ ዋሻ ለ25ዓመት በጾም በፀሎት ምንም አይነት የላመ የጣፈጠ እህል ሳትቀምስ በቅል ውስጥ የሚገኘውን መራራ ፍሬ ከኮሶ ጋር በአንድነት ደርጣ (አዋህዳ) በመዘፍዘፍ ከ3 ቀን በኃላ በመመገብ እስከ ሕይወቷ ፍጻሜ ድረስ #ጌታችን_አምላካችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በቀራንዮ አደባባይ ላይ የቀመሰውን መራራ ሐሞትን በማሰብ ሙሉ ሕይወቶን እየተመገበች ታላቅ ተጋድሎዋን ፈፅማለች፡፡ ከዚህ የተነሳ ሸክላ ማርያም ተብላ ትጠራ የነበረችው ቦታ ስያሜ ተቀይሮ ደሪጣ ዜና ማርያም ዋሻ ተብሎ እስከ አሁን ድረስ በስሞ እየተጠራ ይገኛል፡፡

ከአቡነ እድርያስ ዋሻ በመቀጠል ከአዲስ አበባ ተነስተን ስንጓዝ አዲስ ዘመን ከተማ በስተቀኝ በኩል ተገንጥለን 15ኪሜ ያክል የጥርጊያ መንገድ እንደተጓዝን በስሞ የተሰየመውን ደሪጣ ጻድቋ ቅድስት ዜና ማርያም ገዳም ላይ ቀሪ ሕይወቷን ምንም አይነት ዋሻ ባልነበረበት በከፍተኛ ተራራ ላይ እጅግ አስቸጋሪ ቀዝቃዛ አየር ባለበት ብርዱን፣ ፀሐዩን፣ ቁሩን፣ ረኃቡንና ጥሙን በመቋቋም ራቁቶን በመሆን መራራ ምግቦችን አዋህዳ በመመገብ በጾም በፀሎት በመትጋት አስቸጋሪ የሆነውን ተጋድሎዋን በመፈፀም በዚሁ በተቀደሰ ስፍራ በዚህች ቀን በታላቅ ክብር አርፋለች፡፡

በዚህም ወቅት #ጌታችን_አምላካችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ከእናቱ ከቅድስት #ድንግል_ማርያምና ከእልፍ አላፋት ቅዱሳ መላዕክት ጋር እንዲሁም ከሐዋርያት ፣ ከሰማዕታት ፣ ከጻድቃን ፣ ከደናግል ጋር በመሆን ከሰማይ በመውረድ በታላቅ ክብር ዕረፍቷን አክብሮላታል ታላቅ ኪዳንም ገብቶላታል፡፡

በዚሁ በተቀደሰ ስፍራ ላይ ወይንም በአሁኑ ሰዓት መቃብሯ በሚገኝበት ዋሻ ቤተመቅደስ አካባቢ በተጋድሎዋ ጊዜ ራቁቷን በሆነች ሰዓት መላ ገላዋን የሸፈነላት ፀጉር በእየ ዛፎቹ ላይ እስከ አሁን ድረስ አለ ፡፡ ይህም የጸጉር አምሳያ ከገዳሙ በመውሰድ ብዙ ሰዎች በቤታቸው በመታጠን ከአስም እንዲሁም ከተለያዩ በሽታዎች እየተፈወሱና እየዳኑ ሲሆን ታላላቅ ታምራትን እያደረገ ይገኛል፡፡

በዚህ ገዳም ከሌሎች ገዳማት ለየት የሚያደርገው ታሪክ #ጌታችን_አምላካችን_መድኃኒታችንን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ከሰማይ በመውረድ ራሱ የባረከው ልዩ ታሪክ ያለው ጠበል የሚገኝ ሲሆን ይህም ጠበል በቦታው ላይ ሆኖ የተጠመቀ ፣ የጠጣ ፣ አልያም በአለበት ቦታ ሆኖ የተጠቀመ እስከ አሁን ድረስ መካን የሆኑ ሰዎች በፍጥነት ልጅ የሚያገኙ ከመሆናቸው ባሻገር ከማንኛውም ከተለያዩ በሽታዎች በመፈወስ ታላላቅ ታምራትን እየሰራ ይገኛል፡፡

በ11ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቅዱስ ላሊበላ በ #ጌታችን_በአምላካችን_በመድኃኒታችን_በኢየሱስ_ክርስቶስ ትዕዛዝ መሰረት ወደዚሁ ታላቅ ስፍራ በመምጣት የጻድቋ ማረፈያ/መታሰቢያ ዋሻ ቤተ መቅደስ በመፈልፈል የሰራላት ሲሆን በመቀጠል አፄ ይስሐቅ በ14ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ይህን ገዳም በስሟ በመገደም በዚሁ ዋሻ ውስጥም የጻድቋ የቅድስት ዜና ማርያም መቃብሯ እንዲሁም የመታሰቢያዋ ፅላት የሚገኝ ከመሆኑ አንጻር በአካባቢው ያሉት ሕዝበ ክርስትያን ከካህናት ጋር በመሆን ሥርዓተ አምልኮ በመፈፀም እየተገለገሉበት ይገኛሉ፡፡

ይህ ዋሻም አስቀድሞ ሦስቱ ቅዱሳን ማለትም አቡነ እንድርያስ ዘጣራ ገዳም ፣አቡነ ተክለኃይማኖት ዘደብረ ሊባኖስ፣ ጻድቋ ቅድስት ዜናማርያም ዘደሪጣ ውስጥ ለውስጥ በ #መንፈስ_ቅዱስ ገላጭነት በፀጋ #እግዚአብሔር ይገናኙበት የነበረ ሲሆን በአሁን ሰዓትም #እግዚአብሔር የመረጣቸው ቅዱሳን ይመላለሱበታል፡፡

ለጻድቋ ቅድስት ዜና ማርያም የተሰጠ ቃል ኪዳን #እግዚአብሔር አምላክ መርጦና ፈቅዶ በጻድቋ አማላጅነት ካለበት ስፍራ ተነስቶ የጻድቋ ደጃን የረገጠ ለ3 ግመል ጭነት ጤፍ ወይም የሦስት አህያ ጤፍ ያህል ነፍሳትን እምርልሻለሁ፤ ከሲዖልም እሳት ነፍሳትን አወጣልሻለሁ የሚል ቃል ኪዳን ለጻድቋ ቅድስት ዜና ማርያም ተሰቶታል።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጌቶቻችን ሐዋርያት በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_30#ከገድላት_አንደበት_ግንቦት_30)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_30_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዕብራውያን 11
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³² እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ ስለ ሶምሶንም ስለ ዮፍታሔም ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና።
³³ እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፥ ጽድቅን አደረጉ፥ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፥
³⁴ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን ኃይል አጠፉ፥ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፥ ከድካማቸው በረቱ፥ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፥ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ።
³⁵ ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤
³⁶ ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤
³⁷ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤
³⁸ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ።
³⁹-⁴⁰ እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው ሳሉ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አላገኙም፥ ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ እግዚአብሔር ስለ እኛ አንዳች የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ አይቶ ነበርና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ይሁዳ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁷ እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ቀድሞ የተነገረውን ቃል አስቡ፤
¹⁸ እነርሱ፦ በመጨረሻው ዘመን በኃጢአተኝነት እንደ ገዛ ምኞታቸው እየሄዱ ዘባቾች ይሆናሉ ብለዋችኋልና።
¹⁹ እነዚህ የሚያለያዩ ሥጋውያንም የሆኑ መንፈስም የሌላቸው ሰዎች ናቸው።
²⁰ እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፥
²¹ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ።
²² አንዳንዶች ተከራካሪዎችንም ውቀሱ፥ አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ፥
²³ አንዳንዶችንም በሥጋ የረከሰውን ልብስ እንኳ እየጠላችሁ በፍርሃት ማሩ።
²⁴ ሳትሰናከሉም እንዲጠብቃችሁ፥ በክብሩም ፊት በደስታ ነውር የሌላችሁ አድርጎ እንዲያቆማችሁ ለሚችለው
²⁵ ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ይሁን፤ አሜን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² በዚያን ጊዜ ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ እርሱም ከኢየሩሳሌም የሰንበት መንገድ ያህል የራቀ ነው።
¹³ በገቡም ጊዜ ወደሚኖሩበት ሰገነት ወጡ፥ ጴጥሮስና ዮሐንስም፥ ያዕቆብም፥ እንድርያስም፥ ፊልጶስም፥ ቶማስም፥ በርተሎሜዎስም፥ ማቴዎስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም፥ ቀናተኛ የሚባለው ስምዖንም፥ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳም።
¹⁴ እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_30_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"መንክር ተላህያ ለባሕር። መንክርሰ እግዚአብሔር በአርያሙ። ስምዐ ዚአከ እሙን፡ፈድፋደ"። መዝ 92፥4-5 ወይም መዝ 100፥6-7።
"ከብዙ ውኆች ድምፅ ከባሕርም ታላቅ ሞገድ ይልቅ እግዚአብሔር በከፍታው ድንቅ ነው። ምስክርህ እጅግ የታመነ ነው፤ አቤቱ፥ እስከ ረጅም ዘመን ድረስ ለቤትህ ቅድስና ይገባል"። መዝ 92፥4-5
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_30_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 24
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹³ እነሆም፥ ከእነርሱ ሁለቱ በዚያ ቀን ከኢየሩሳሌም ስድሳ ምዕራፍ ያህል ወደሚርቅ ኤማሁስ ወደሚባል መንደር ይሄዱ ነበር፤
¹⁴ ስለዚህም ስለ ሆነው ነገር ሁሉ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር።
¹⁵ ሲነጋገሩና ሲመራመሩም፥ ኢየሱስ ራሱ ቀርቦ ከእነርሱ ጋር ይሄድ ነበር፤
¹⁶ ነገር ግን እንዳያውቁት ዓይናቸው ተይዞ ነበር።
¹⁷ እርሱም፦ እየጠወለጋችሁ ስትሄዱ፥ እርስ በርሳችሁ የምትነጋገሩአቸው እነዚህ ነገሮች ምንድር ናቸው? አላቸው።
¹⁸ ቀለዮጳ የሚባልም አንዱ መልሶ፦ አንተ በኢየሩሳሌም እንግዳ ሆነህ ለብቻህ ትኖራለህን? በእነዚህ ቀኖች በዚያ የሆነውን ነገር አታውቅምን? አለው።
¹⁹ እርሱም፦ ይህ ምንድር ነው? አላቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት፦ በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በሥራና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ስለ ኢየሱስ፤
²⁰ እርሱንም የካህናት አለቆችና መኳንንቶቻችን ለሞት ፍርድ እንዴት አሳልፈው እንደ ሰጡትና እንደ ሰቀሉት ነው።
²¹ እኛ ግን እስራኤልን እንዲቤዥ ያለው እርሱ እንደ ሆነ ተስፋ አድርገን ነበር፤ ደግሞም ከዚህ ሁሉ ጋር ይህ ከሆነ ዛሬ ሦስተኛው ቀን ነው።
²² ደግሞም ከእኛ ውስጥ ማልደው ከመቃብሩ ዘንድ የነበሩት አንዳንድ ሴቶች አስገረሙን፤
²³ ሥጋውንም ባጡ ጊዜ፦ ሕያው ነው የሚሉ የመላእክትን ራእይ ደግሞ አየን ሲሉ መጥተው ነበር።
²⁴ ከእኛም ጋር ከነበሩት ወደ መቃብር ሄደው ሴቶች እንደ ተናገሩት ሆኖ አገኙት፥ እርሱን ግን አላዩትም።
²⁵ እርሱም፦ እናንተ የማታስተውሉ፥ ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ፤
²⁶ ክርስቶስ ይህን መከራ ይቀበል ዘንድና ወደ ክብሩ ይገባ ዘንድ ይገባው የለምን? አላቸው።
²⁷ ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን ተረጐመላቸው።
²⁸ ወደሚሄዱበትም መንደር ቀረቡ፥ እርሱም ሩቅ የሚሄድ መሰላቸው።
²⁹ እነርሱ፦ ከእኛ ጋር እደር፥ ማታ ቀርቦአልና ቀኑም ሊመሽ ጀምሮአል ብለው ግድ አሉት፤ ከእነርሱም ጋር ሊያድር ገባ።
³⁰ ከእነርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጦ ሳለ እንጀራውን አንሥቶ ባረከው፥ ቈርሶም ሰጣቸው፤
³¹ ዓይናቸውም ተከፈተ፥ አወቁትም፤ እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ።
³² እርስ በርሳቸውም፦ በመንገድ ሲናገረን መጻሕፍትንም ሲከፍትልን ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን? ተባባሉ።

ወይም

ማርቆስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ።
²-³ እነሆ፥ መንገድህን የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ተብሎ በነቢዩ በኢሳይያስ እንደ ተጻፈ፥
⁴ ዮሐንስ በምድረ በዳ እያጠመቀ የንስሐንም ጥምቀት ለኃጢአት ስርየት እየሰበከ መጣ።
⁵ የይሁዳም አገር ሁሉ የኢየሩሳሌምም ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ ይወጡ ነበር፥ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር።
⁶ ዮሐንስም የግመል ጠጉር ለብሶ በወገቡ ጠፍር ይታጠቅ አንበጣና የበረሀ ማርም ይበላ ነበር።
⁷ ተጎንብሼ የጫማውን ጠፍር መፍታት የማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ በኋላዬ ይመጣል።
⁸ እኔ በውኃ አጠመቅኋችሁ እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል እያለ ይሰብክ ነበር።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱሳን_ሐዋርያት_ቅዳሴ ነው። መልካም የነቢዩ ቅዱስ ሚልክያስ የዕረፍት በዓልና የሐዋርያው ቅዱስ እንድርያስ የመታሰቢያ ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነቢዩ_ሚልክያስ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

“ሚልክያስ” ማለት “መልአክ፣ ሐዋርያ፣ መልእክተኛ” ማለት ነው፡፡ ጥር ፰ ቀን የሚነበበው ስንክሳር እንደሚያስረዳው ነቢዩ ሚልክያስ የተወለደው ሕዝቡ ከፄዋዌ (ከምርኮ) ከተመለሱ በኋላ ነው፡፡ ከሕፃንነቱ አንሥቶም የ #እግዚአብሔርን መንገድ የሚወድ ነበር፡፡ ሕዝቡም ይኽን አካኼዱን አይተው እጅግ ያከብሩት ነበር፡፡ ይኽን መልካምነቱንም አይተው “ከ #እግዚአብሔር የተላከ ነው” ሲሉ ስሙን ሚልክያስ ብለው ጠሩት፡፡

ነቢዩ ሚልክያስ ከጸሐፍት ነቢያት የመጨረሻው ነቢይ ነው፡፡ ከሐጌና ከዘካርያስ በኋላም በነቢይነት አገልግሏል፡፡ ከ፬፻፶-፬፻ ቅ.ል.ክ. ላይ እንደነበረም ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ዕዝራና ነህሚያ ቤተ አይሁድን በሚስተካክሉበት ጊዜ ሚልክያስም ተባባሪያቸው ነበር፡፡

➛በነቢዩ ዙረያ የነበረው ነባራዊ ኹኔታ

➛በምርኮ የነበሩት አይሁድ በ፭፻፴፰ ቅ.ል.ክ. ላይ ከምርኮ ወደ አገራቸው መመለስ እንደሚችሉ ሲነገራቸው ከኹለት ቡድን ተከፍለዋል፡፡ አንደኛውና የሚበዛው ቡድን ወደ ተስፋይቱ ምድር መመለስን ያልወደደና በባቢሎን አገር በሀብትና ንብረት የተደራጀ ነው፡፡ ይኼ ቡድን ምንም እንኳን በባዕድ አገር የሚኖር ቢኾንም ባርነቱ የተመቸው ይኽንንም ዓለም የወደደ ነው፡፡ ይኼ ቡድን #እግዚአብሔር ለአባቶቹ የገባውን ቃል ኪዳን ለመካፈል ያልፈለገ ቡድን ነው፡፡ በሕገ ኦሪቱ መሠረት #እግዚአብሔርን እያመለከ ለመኖር ያልፈቀደ ቡድን ነው፡፡

➛ኹለተኛውና የሚያንሰው ቡድን ደግሞ ወደ ተስፋይቱ ምድር የተመለሰው ነው፡፡ ይኼ ቡድን ከምርኮ ሲመጣ የኢሩሳሌምን አጥር፣ ቤተ መቅደሱን ለመሥራት፤ እንዲኹም የቀድሞውን አምልኮተ #እግዚአብሔር ለመመለስ ነበር፡፡ ነገር ግን ከእነዚኽም መካከል ቤታቸውን ለመሸላለም “የ #እግዚአብሔር ቤት የሚሠራበት ዘመን ገና ነው” የሚሉ ነበሩ፡፡ አኹንም ከእነዚኽ ከተመለሱት ቅሪቶች መካከል ምንም እንኳን ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ቢያከናውኑም አካኼዳቸው ግን ከልብ አልነበረም፡፡ መሥዋዕታቸው የቃየን መሥዋዕት ነበር፡፡ ሲዠምር “የ #እግዚአብሔር ማዕድ አስናዋሪ ነው” ይላሉ፡፡ በፊቱ የተዘጋጀ እኽሉም “አባር የመታው እንክርዳድ ነው” ይላሉ፡፡ እነርሱም ለመሥዋዕት ዕውሩን አንካሳውን እንስሳ ያመጣሉ /፩፡፰/፡፡

#ነቢዩ_ሚልክያስ የተላከበት ምክንያትም ይኽን አካኼዳቸውን እንዲያስተካክሉ ለማሳሰብ ነበር፡፡
#ነቢዩ_ሚልክያስ በነገሥታቱ ዘመን እንደነበረው ዓይነት ስብከት አልሰበከም፤ የባዕድ አምለኮ ዐፀዶችን እንዲያፈርሱም አልተናገረም፡፡ ልክ እንደ ዕዝራ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አላሳሰባቸውም፤ ልክ እንደ ነህምያም የኢየሩሳሌምን አጥር ቅጥር እንዲሠሩ አላሳሰባቸውም፡፡ ወደ ውሳጣዊ ሕይወታቸው ዘልቆ በቅድስና ከ #እግዚአብሔር ጋር ኅብረት እንዲኖራቸው አሳሰባቸው እንጂ፡፡ #እግዚአብሔር በእውነትና በመንፈስ የሚያመልኩት አምላክ ነውና ከምንም በፊት ውሳጣዊ ማንነታቸውን ወደ አገራቸው ወደ ሰማይ እንዲመልሱ፣ የነፍሳቸው የኢየሩሳሌምን አጥር ቅጥር እንዲሠሩ ነበር ያሳሰባቸው፡፡

#ትንቢተ_ሚልክያስ

ትንቢተ ሚልክያስ እጅግ መሳጭና የ #እግዚአብሔር ፍቅር እንደምን ጥልቅ እንደኾነ የምናነብበት መጽሐፍ ነው፡፡ #እግዚአብሔር የሰው ልጆችን በሙሉ ያለማዳለት ይወዳል፡፡ #እግዚአብሔር ሲወድ አንዱን በመጥላት ሌላውንም በመውደድ አይደለም፡፡ ያለ ማዳላት ኹላችንም ይወደናል እንጂ፡፡ ሰዎች በ #እግዚአብሔር ዘንድ የተጠሉ የሚኾኑት ከራሳቸው ክፋት የተነሣ ነው፡፡ ሕጉንና ትእዛዙን ሳያከብሩ ሲቀሩ #እግዚአብሔር አይቀበላቸውም፡፡ አፍአዊ በኾነ አምልኮ #እግዚአብሔርን መቅረብ ወደ ሕይወትም መጋበዝ አይቻልምና እነዚኽ ሰዎች በ #እግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነት የሌላቸው ይኾናሉ፡፡ በትንቢተ ሚልክያስ የምናገኘው አንዱ አንኳር ነጥብ ይኸው ነው /፩፡፪-፭/፡፡

ነቢዩ ሚልክያስም ለዚኹ ኹሉ ችግር መፍትሔው አንድና አንድ ብቻ እንደኾነ ይሰብካል፤ ይኽ ከ #እግዚአብሔር የተቀበለውንም መልእክት ለሕዝቡ ያስተላልፋል፡፡ “ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለኹ ይላል የሠራዊት #ጌታ_እግዚአብሔር” በማለት /፫፡፯/፡፡ ይኽ ለሰው ኹሉ የተከፈተ በር ነው፡፡ የእኛ ደንዳናነት ካልኾነ በስተቀር ይኽን የድኅነት በር መዝጋት የሚችል አካል የለም፡፡ እንኳንስ ፍጡር ይቅርና #እግዚአብሔርም ቢኾን ስለማይችል ሳይኾን ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ ይኽን በር በማንም ሰው ፊት አይዘጋውም፡፡ #እግዚአብሔርስ እርሱ እንዳይገባ የዘጋንበትን በር እንድንከፍትለት ያንኳኳል እንጂ አይዘጋውም፡፡ “ወድጃችኋለኹ ይላል የሠራዊት ጌታ #እግዚአብሔር” /፩፡፪/፡፡

ትንቢተ ሚልክያስን ገና ማንበብ ስንዠምር ከምርኮ የተመለሰው ሕዝብ አንድን ነገር ጠብቆ እንደመጣ እንገነዘባለን፡፡ ሕዝቡ አፍአዊ የኾነ በረከትን ሽቶ እንደ ነበር እንረዳለን፡፡ ከዚኽ በፊት ነቢያቱ ስለ መሲሑ የተናገሩት ኹሉ በጊዜአቸው የሚፈጸም መስሎአቸው እንደ ነበር እናስተውላለን፡፡ የዳዊት ድንኳን እንደገና በዘመናቸው እንደምትሠራ፥ ፈርሶና ተዳክሞ የነበረው መንግሥታቸውም እንደገና አንሰራርቶ በዓለም ላይ ገናና መንግሥት እንደሚኾን ገምተው እንደ ነበር እንረዳለን፡፡ እነርሱ እንዳሰቡት አፍአዊ የኾነ ነገር ሳይፈጸም ሲቀር ግን ግርምት ይዞአቸው #እግዚአብሔርን፡- “በምን ወደድኸን?” እንዳሉት እናነባለን /፩፡፪/፡፡ እንዲኽ ዓይነት የግርምትና የመደነቅ ንግግርም በብዙ ቦታ ላይ ሲናገሩት እናገኛቸዋለን፡፡ “ስምኽን ያቃለልነው በምንድነው?” /፩፡፮/፤ “ያረከስንኽ በምንድነው?” /፩፡፯/፤ “ያታከትነው በምንድነው?” /፪፡፲፯/፤ “የምንመለሰው በምንድነው?” /፫፡፯/፤ “የሰረቅንኽ በምንድነው?” /፫፡፰/፤ “በአንተ ላይ ድፍረት የተናገርነው በምንድነው?” /፫፡፲፫/፤ “ትእዛዙንስ በመጠበቅ በሠራዊት #ጌታ#እግዚአብሔር ፊት ኀዘንተኞች ኾነን በመኼድ ምን ይረባናል?” /፫፡፲፬/ እንዲል፡፡ #እግዚአብሔር ግን እነዚኽ ሰዎች ምድራዊውን ሳይኾን ሰማያዊውን፣ ጊዜአዊውን ሳይኾን ዘለዓለማዊውን፣ አፍአዊውን ሳይኾን ውሳጣዊውን፣ ብልና ዝገት የሚያገኘውን ሳይኾን በሰማያዊው መዝገብ የተቀመጠውን እንዲሹ ይጠራቸዋል፡፡ ነውረኛ መሥዋዕትን እያቀረቡ #እግዚአብሔርን ከመሸንገል ተመልሰው /፩፡፲፬/፣ የግፍ ሥራቸውን በልብስ መክደንን ትተው /፪፡፲፮/፣ “ክፉን የሚያደርግ ኹሉ በ #እግዚአብሔር ዘንድ መልካም ነው” ፥ እንዲኹም “የፍርድ አምላክ ወዴት አለ?” /፪፡፲፯/፣ “የሚታበዩትን ሰዎች ብፁዐን እንላቸዋለን” እያሉ /፫፡፲፭/ እግዚአብሔርን ከመፈታተን ተመልሰው ስሙን እንዲፈሩና የክፋት በረዶአቸው በጽድቅ ፀሐዩ እንዲቀልጥላቸው፥ በሕይወትም እንዲኖሩ ይጠራቸዋል /፬/።

በአጠቃላይ መጽሐፉ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “በመንፈሱ በውስጥ ሰውነታችሁ በኃይል እንድትጠነክሩ፥ ክርስቶስም በልባችሁ በእምነት እንዲኖር፥ … የእናንተ ሥርና መሠረት በፍቅር ይጸና ዘንድ፥ ከቅዱሳን ኹሉ ጋር ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቀቱም ምን ያኽል መኾኑን ለማስተዋል፥ ከመታወቅም የሚያልፈውን የ #ክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ …” እንዳለው /ኤፌ.፫፡፲፮-፲፱/ #እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር እንደምን ጥልቅ እንደኾነ፣ የመንግሥተ ሰማያትን ደጅ የሚከፍት የተትረፈረፈው የ #እግዚአብሔር ጸጋ ለሰው ልጆች እንደምን ብዙ እንደኾነ፣ ከአፍአ ሳይኾን ከልቡ የተመለሰ ሰው ምን እንደሚያገኝ የሚያስረዳ ድንቅ መጽሐፍ ነው፡፡ ድኅነትን
የምትሻ ነፍስ መልስ የምታገኝበት ግሩም መጽሐፍ ነው፡፡ በውስጡም በዘመነ ሐዲስ ስለሚቀርበው ቊርባን /፩/፣ ስለ ጋብቻ ምንነት /፪/፣ እንዲኹም ስለ አስራት አሰጣጥ /፫/ በጥልቀት ያስተምራል፡፡

መጽሐፉን እንደሚከተለው መክፈል እንችላለን፡-
1. ምዕራፍ አንድን ስናነብ፥ ምንም እንኳን #እግዚአብሔር አባታቸው መኾኑን ቢያውቁም፣ ምንም እንኳን #እግዚአብሔር #ጌታ እንደኾነ ቢረዱም በገቢር ግን የአባትነትም ኾነ እንደ ጌትነቱ የመፈራት ክብርን አለመስጠታቸው ይገልጣል፡፡ ነውረኛ የኾነ መሥዋዕትን በማቅረባቸው የ #እግዚአብሔርን ስም እንዴት እንደናቁት ያሳያል፡፡ በሌላ አገላለጽ የእምነትና የምግባር አንድነትን የሚያስረዳ እውነተኛና ተቀባይነት ያለው አምልኮ ምን እንደሚመስል የሚያረዳ ነው፡፡
2. ምዕራፍ ኹለትን ስንመለከት ደግሞ የካህናቱን ኢሞራላዊነት ይናገራል፡፡ በዚኽ ድርጊታቸውም የ (እግዚአብሔርን ኪዳን እንዴት እንዳፈረሱት ለበረከት የኾነውም እንደምን ለመርገም እንዳደረጉት ያስረዳል፡፡

3. ምዕራፍ ሦስትና አራት ላይ #እግዚአብሔር እንደሚመጣና ሕዝቡንም ኾነ ቤተ መቅደሱን እንደሚቀድስ ይናገራል፡፡ ምዕራፍ ሦስት ላይ በመዠመሪያ ምጽአቱ ላይ ክብር ይግባውና #ጌታችንና_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሕዝቡን (ቤተ መቅደሱን) በገዛ ደሙ ለመዋጀት እንደሚመጣና ሕዝቡም እርሱን ለመቀበል በገቢር እንዲመለሱ ሲጠይቅ በምዕራፍ አራት ላይ ደግሞ የጽድቅ ፀሐይ የተባለው #ጌታችንና_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ጨለማ የተባለውን ክፋት ከሰው ልጆች ለማራቅ እንደሚመጣ ይናገራል፡፡ በዚያ አንጻርም በሕያዋንና በሙታን ላይ ዳግም ለመፍረድ እንደሚመጣ ይገልጣል፡፡

እኛስ ከዚኽ ምን እንማራለን?
© #እግዚአብሔርን በከንፈራችን ሳይኾን በገቢር እንደምንወደው መግለጥ እንዳለብን፤ ንጹሕ መሥዋዕትም ይኸው እንደኾነ /፩/፤
© እንዲኽ ካልኾነ ግን ብንጦምም፣ ብንጽልይም፣ ብንመጸውትም፣ ቤተ ክርስቲያን ብንመላለስም፣ መባ ብናቀርብም መሥዋዕታችን ኹሉ ፋንድያ እንደኾነ /፪፡፫/፤
© ምንም ያኽል ኃጢአተኞች ብንኾንም ልንመለስ እንደሚገባን /፫፡፯/፤ እርሱም ከየትኛውም ዓይነት ኃጢአታችን እንደሚያነጻን፤ የእርሱ ገንዘብ እንደምንኾንና አንድ ሰው የሚያገለግለው ልጁን እንደሚምረው የሠራዊት #ጌታ_እግዚአብሔርም እንደሚምረን /፫፡፲፯/፤
© እንዲኽ ከተመለስን በኋላ የጽድቅ ፀሐይ #ክርስቶስ ላይጠልቅ በሕይወታችን ላይ አብርቶ እንደሚኖር እንማራለን፡፡

…ተመስጦ…
ቸርና ቅዱስ #እግዚአብሔር ሆይ! በሕይወታችን እጅግ ጐስቋሎች ኾነን ስምኽን ብናቃልለውም ደካሞች ነንና በከንፈራችን ብቻ ሳይኾን በገቢርም እንድናውቅኽ እንድናመልክኽም እርዳን፡፡ ሊቀ ካህናችን #ኢየሱስ_ክርስቶስ ሆይ! እውነተኛ ካህናት እንድንኾን እርዳን፡፡ አባቶቻችን ካህናት ቅዱስ ሥጋኽና ክቡር ደምኽን ለምእመናን ለኹላችንም ሲያቀብሉ እኛም በክህነታችን ቁራሽ ዳቦና ኩባያ ውኃ ለድኾች መስጠት እንድንለማመድ እርዳን፡፡ የጽድቅ ፀሐይ #ኢየሱስ_ክርስቶስ ሆይ! ቅድስናኽ እኛን ቢቀድሰን እንጂ ኃጢታችን አንተን አያረክስኽምና በእኛ ዘንድ እደር፡፡ በኹለንተናችን ላይም አብራ፡፡ ጨለማን ከእኛ ዘንድ አስወግድልን፡፡ ለዘለዓለሙ አሜን!!!
#ጳጒሜን_1

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የተባረከ የጳጒሜን ወር ባተ። በዚህች ቀን ጳጒሜን አንድ #ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ የታሰረበት፣ የወንጌላዊ የቅዱስ #ዮሐንስ ረድእ #የዑቲኮስ_ሐዋርያና #ቀሲስ_አባ_ብሶይ የእረፍታቸው መታሰቢያ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ

ጳጒሜን አንድ ቀን በዚህች ዕለት ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ወደ እሥር ቤት ገብቷል። ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦ ንጉሡ ሔሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሔሮድያዳን በማግባቱና በመሰል ክፋቶቹ ቅዱስ ዮሐንስ ይገስጸው ነበር። ቅዱስ ዮሐንስ "መምሕር ወመገስጽ ዘኢያደሉ ለገጽ" "ፊት አይቶ የማያዳላ" ነውና ገሰጸው።

ሔሮድስ ቅዱሱን ይፈራው ያከብረውም ነበር። በኋላ ግን ፈቃደ ሥጋው ስላየለበት በተለይ ደግሞ ከሰባት ቀናት በኋላ ልደቱን ሲያከብር እንዳይረብሸው በመስጋት በዚህች ቀን በወታደሮቹ አስይዞ እሥር ቤት ውስጥ
ጥሎታል። ለሰባት ቀናት በጨለማ ውስጥ አሥሮ መስከረም 2 ቀን አስቆርጦታል።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዑቲኮስ_ሐዋርያ

በዚህች ቀን የወንጌላዊ ዮሐንስ ረድእ ሐዋርያና ሰማዕት የከበረ ዑቲኮስ አረፈ ።

ይህም ቅዱስ ወንጌላዊ ዮሐንስን ሲያገለግለውና ሲታዘዘው ኖረ። ከዚያም ከሐዋርያ ጳውሎስ ጋራ ሔደ እርሱም የክብር ባለቤት በሆነ በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስም እንዲሰብክ አዘዘው በአረማውያንና በዮናናውያንም መካከል ሰበከ። የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስንም ወደማወቅ ብዙዎችን መለሳቸው የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው።

የጣዖታት ቤቶችን አፍርሶ አብያተ ክርስቲያናትን ሠራ። ከከሀድያንም ብዙ መከራ ደረሰበት መታሠርና ብዙ ቀኖች ግርፋቶችን በመቀበል፤ የ #እግዚአብሔርም መልአክ ወደ እሥር ቤት ከምግብ ጋር መጥቶ ይመግበዋል።

ከዚህም በኋላ ከእሳት ውስጥ ጣሉት እሳቱም ከቶ አልነካውም ሁለተኛም ለአንበሶች ጣሉት እነርሱም እንደ በጎች ሆኑለት። ከዚህም በኋላ ወደቍስጥንጥንያ ሀገር ሔደ። ሲሔድም የ #እግዚአብሔር መልአክ ይመራውና ያጸናናው ነበር ተጋድሎውንም ፈጽሞ በበጎ ሽምግልና ወደ እግዚአብሔር ሔደ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሐዋርያው ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቀሲስ_ብሶይ_ሰማዕት

በዚችም ቀን የአባ ሖር ወንድም ቀሲስ ብሶይ በሰማዕትነት ሞተ። ይህም ቅዱስ ከአንፆኪያ አገር ክብር ካላቸው ወገኖች ውስጥ ነው ስለ ዕውቀቱና ስለ ሃይማኖቱ ጽናት ቅስና ተሾመ።

ወንድሙ አባ ሖርና እናቱ ወደ ግብጽ አገር ሔደው በሰማዕትነት ከሞቱ በኋላ እርሱም ተነሥቶ ወደ እስክንድርያ ሥጋቸውን ያይ ዘንድ ሔደ። ገንዘቡን ሁሉ ለድኆች ሰጠ ከሦስት እንጀራና ከሚመረጐዛት ከአንዲት የሰኔል በትር በቀር ምንም አልያዘም ነበር።

ወደ እስክንድርያ አገርም በደረሰ ጊዜ የዘመዶቹ በድን ወዳለበት ሰዎች መርተው አደረሱት የእናቱንና የወንድሙንም ሥጋ በአየ ጊዜ ከእርሳቸው ስለ መለየቱ መሪር ልቅሶን አለቀሰ። ከዚህም በኋላ ወደ መኰንኑ ሒዶ በፊቱ ቁሞ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ።

ለመኰንኑም የአባ ሖር ወንድም እንደሆነ ነገሩት መኰንኑም ታላቅ የደንጊያ ምሰሶ በሆዱ ላይ እንዲአቆሙበት አዘዘ ይህንንም በአደረጉበት ጊዜ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ሰጠ።

ከዚህም በኋላ ደግሞ ሥጋውን ከወንድሙና ከእናቱ ሥጋ ደግሞ ቍጥራቸው ሰማንያ ስምንት ከሆነ ከሌሎች ሰማዕታት ሥጋ ጋር በአንድነት ያቃጥሉ ዘንድ መኰንኑ አዘዘ ወደ እሳት በጨመሩአቸውም ጊዜ ከቶ እሳቱ አልነካቸውም።

ምዕመናን ሰዎችም መጥተው የከበሩ የአባ ሖርንና የወንድሙ የአባ ብሶይን የእናታቸውንም ሥጋ ወሰዱ። ሀገሯ ዲብቅያ የሚባል የቅድስት ዳሞንንም ሥጋ፣ ሀገሩ በረሞን የሚባል የቅዱስ ቢማኮስንም ሥጋ፣ ጡልያ ከሚባል አገር የመጣ የውርሱኑፋን ሥጋም፣ አብስላሲ ወደሚባል አገር እስከሚያደርሷቸው በመርከብ ጫኗቸው። የስደቱ ወራት እስከሚፈጸም አክብረው ወስደው በመልካም ቦታ አኖሩዋቸው።

ከዚህም በኋላ አብያተ ክርስቲያን ተሠርቶላቸው ሥጋቸውን በውስጣቸው አኖሩ ከእርሳቸውም ተአምራት ተገለጡ ለሕሙማንም ፈውስ ሆኑ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእኒህ ቅዱሳን ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጳጉሜን_1#ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጳጒሜ_1_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ፊልጵስዩስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህ የደረሰብኝ በእውነት ወንጌልን ለማስፋት እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ።
¹³ ስለዚህም እስራቴ ስለ ክርስቶስ እንዲሆን በንጉሥ ዘበኞች ሁሉና በሌሎች ሁሉ ዘንድ ተገልጦአል፥
¹⁴ በጌታም ካሉት ወንድሞች የሚበዙት ስለ እስራቴ ታምነው የእግዚአብሔርን ቃል እንዲነግሩ ያለ ፍርሃት ከፊት ይልቅ ይደፍራሉ።
¹⁵ አንዳንዶች ከቅንአትና ከክርክር እንኳ ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብኩታል፤
¹⁶ እነዚህ ወንጌልን መመከቻ ለማድረግ እንደ ተሾምሁ አውቀው በፍቅር ይሰብካሉ፥
¹⁷ እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ መከራን ሊያመጡብኝ መስሎአቸው፥ ለወገናቸው የሚጠቅም ፈልገው በቅን አሳብ ሳይሆኑ ስለ ክርስቶስ ያወራሉ።
¹⁸ ምን አለ? ቢሆንም በሁሉ ጎዳና፥ በማመካኘት ቢሆን ወይም በቅንነት ቢሆን፥ ክርስቶስ ይሰበካል ስለዚህም ደስ ብሎኛል።
¹⁹ ወደ ፊትም ደግሞ ደስ ይለኛል፤ ይህ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ መሰጠት ለመዳኔ እንዲሆንልኝ አውቃለሁና፥
²⁰ ይህ ናፍቆቴ ተስፋዬም ነውና፤ በአንድ ነገር እንኳ አላፍርም ነገር ግን በሕይወት ብኖር ወይም ብሞት፥ ክርስቶስ በግልጥነት ሁሉ እንደ ወትሮው አሁን ደግሞ በስጋዬ ይከብራል።
²¹ ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና።
²² ነገር ግን በስጋ መኖር ለእኔ የሥራ ፍሬ ቢሆን፥ ምን እንድመርጥ ኣላስታውቅም።
²³ በእነዚህም በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤
²⁴ ነገር ግን በሥጋ መኖሬ ስለ እናንተ እጅግ የሚያስፈልግ ነው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ዮሐንስ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ክርስቶስ ነው ብሎ በኢየሱስ የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዶአል፥ ወላጁንም የሚወድ ሁሉ ከእርሱ የተወለደውን ደግሞ ይወዳል።
² እግዚአብሔርን ስንወድ ትእዛዛቱንም ስናደርግ የእግዚአብሔርን ልጆች እንድንወድ በዚህ እናውቃለን።
³ ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም።
⁴ ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው።
⁵ ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው?
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 18
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²¹ ነገር ግን ሲሰናበታቸው፦ የሚመጣውን በዓል በኢየሩሳሌም አደርግ ዘንድ ይገባኛል እግዚአብሔር ቢፈቅድ ግን ወደ እናንተ ደግሞ እመለሳለሁ አላቸው። ከኤፌሶንም በመርከብ ተነሣ።
²² ወደ ቂሣርያም በደረሰ ጊዜ ወጥቶ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምታ ከሰጠ በኋላ ወደ አንጾኪያ ወረደ።
²³ ጥቂት ቀንም ቆይቶ ወጣ፥ ደቀ መዛሙርትንም ሁሉ እያጸና በገላትያ አገርና በፍርግያ በተራ አለፈ።
²⁴ በወገኑም የእስክንድርያ ሰው የሆነ ነገር አዋቂ የነበረ አጵሎስ የሚሉት አንድ አይሁዳዊ ሰው ወደ ኤፌሶን ወረደ፤ እርሱም በመጻሕፍት እውቀት የበረታ ነበረ።
²⁵ እርሱ የጌታን መንገድ የተማረ ነበረ፥ የዮሐንስንም ጥምቀት ብቻ አውቆ በመንፈስ ሲቃጠል ስለ ኢየሱስ ይናገርና በትክክል ያስተምር ነበር።
²⁶ እርሱም በምኵራብ ገልጦ ይናገር ጀመር። ጵርስቅላና አቂላም በሰሙት ጊዜ፥ ወስደው የእግዚአብሔርን መንገድ ከፊት ይልቅ በትክክል ገለጡለት።
²⁷ እርሱም ወደ አካይያ ማለፍ በፈቀደ ጊዜ፥ ወንድሞቹ አጸናኑት፥ ይቀበሉትም ዘንድ ወደ ደቀ መዛሙርት ጻፉለት፤ በደረሰም ጊዜ አምነው የነበሩትን በጸጋ እጅግ ይጠቅማቸው ነበር፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጳጒሜ_1_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"እስመ ጽድቀ ወምጽዋተ ያበድር እግዚአብሔር። እግዚአብሔር ይሁብ ክብረ ወሞገሰ። እግዚአብሔር ኢያስተፄንሶሙ እምበረከቱ ለእለ የሐውሩ በየዋሃት"። መዝ 83፥11።
“እግዚአብሔር አምላክ ምሕረትንና እውነትን ስለ ወደደ፥ ሞገስንና ክብርን ይሰጣል፤ እግዚአብሔር በቅንነት የሚሄዱትን ከመልካም ነገር አያሳጣቸውም።” መዝ 83፥11።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጳጒሜ_1_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 14
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ በዚያ ዘመን የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስ የኢየሱስን ዝና ሰማ፥
² ለሎሌዎቹም፦ ይህ መጥምቁ ዮሐንስ ነው፤ እርሱ ከሙታን ተነሥቶአል፥ ስለዚህም ኃይል በእርሱ ይደረጋል አለ።
³ ሄሮድስ በወንድሙ በፊልጶስ ሚስት በሄሮድያዳ ምክንያት ዮሐንስን አስይዞ አሳስሮት በወህኒ አኑሮት ነበርና፤
⁴ ዮሐንስ፦ እርስዋ ለአንተ ትሆን ዘንድ አልተፈቀደም ይለው ነበርና።
⁵ ሊገድለውም ወዶ ሳለ፥ ሕዝቡ እንደ ነቢይ ስለ አዩት ፈራቸው።
⁶ ነገር ግን ሄሮድስ የተወለደበት ቀን በሆነ ጊዜ፥ የሄሮድያዳ ልጅ በመካከላቸው ዘፈነች ሄሮድስንም ደስ አሰኘችው፤
⁷ ስለዚህም የምትለምነውን ሁሉ እንዲሰጣት በመሐላ ተስፋ አደረገላት።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ዮሐንስ_ወልደ_ነጎድጓድ ቅዳሴ ነው። መልካም የጾም ጊዜና በዓል ለሁላችን ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጾመ_ዮዲት

ዮዲት በናቡከደነጾር ዘመነ መንግሥት ትኖር የነበረች ባሏ የሞተባትና በንጽሕና ተጠብቃ፣ በጸሎትና በሕገ እግዚአብሔር የምትኖር ሴት ነበረች፡፡ በዚያን ጊዜ ንጉሡ ሥልጣኑን መከታ በማድረግ የእግዚአብሔርን ሕዝብ በግድ እያስገደደ እጅ መንሻ ይቀበል ነበር፡፡ የመንግሥቱን ትእዛዝ ያልተቀበለውንም እየገደለ፣ ጭፍሮቹ ኃያልነቱንና ገናናነቱን በዓዋጅ በጦር አዛዦች ጭምር እያሳወጀ፣ በርካታ የጦር ሠራዊቶችን አሰልፎ ከአይሁድ ከተማ ገባ፡፡ በዚያም ነዋሪዎችን በማስፈራራት የመንግሥቱን ትእዛዝ ያልተቀበሉትን ሁሉ እያሳደደ ስላስጨነቃቸው ማቅ ለብሰው፣ አመድ ነስንሰውና ድንጋይ ተንተርሰው ወደ ፈጣሪያቸው በመጮህ መለመን ጀመሩ። በጭካኔ የተሞላው የጦር አበጋዙ ሆሎፎርኒስም ይበልጥ እጅግ እንዲሰቃዩ ውኃ የሚቀዱበትን ስፍራ ተቆጣጠረው፤ በግዴታ ማርኮም እጅ እንዲሰጡ እንዳደረጋቸው በመጽሐፈ ዮዲት ላይ ተጽፏል፡፡ በአካባቢው ይኖር የነበረ ዖዝያን የተባለ አንድ ሰው የአባቶቻቸው አምላክ ጸሎታቸውን እንዲሰማቸው ለአምስት ቀናት በትዕግሥት ይጾሙና ይጸልዩ ዘንድ ሕዝቡን መከራቸው፤ እነርሱም በትዕግሥት ሊጠብቁ ተስማሙ፡፡ (ዮዲ. ፪፥፪)

የእስራኤል ልጆች የናቡከደነጾርን ጦር ብንችል ተዋግተን እንረታለን፤ ካልሆነም እጅ እንሰጣለን በማለት ይመካከሩ ጀመር። ሆኖም ዮዲት #እግዚአብሔርን የምትፈራ ብቸኛዋ ሴት እርሷ ነበረችና ምክክራቸውን ስትሰማ ለምን «እግዚአብሔር ያድነናል አትሉም» ብላ ገሠጸቻቸው፡፡ ማቅ በመልበስ፣ አመድ በመነስነስና ድንጋይ በመንተራስም ሱባኤ ገባች። በሦስተኛው ቀንም #እግዚአብሔር አምላክ ሕዝቧን የምታድንበትን ጥበብ ገለጸላት፤ ዮዲትም #እግዚአብሔር የሰጣትን ውበት ተጠቅማ ሕዝቧን ከጥፋት የምትታደግበትን ጥበብ ተረዳች። (ዮዲት ፯፥፲)

የክት ልብሷን ለብሳ፣ ሽቱ ተቀብታና ተውባ የጠላት ሠራዊት ወዳሉበት የጦር ሰፈር በድፍረት አመራች፡፡ ሠራዊቱም ውበቷን አይተው እጅግ በመደነቅ «ይህችስ ለአለቃችን ትገባለች» ተባብለው ከጦር መሪያቸው ዘንድ ወሰዷት። እርሷም ቀድማ ማምለጫ መንገድ አዘጋጅታ ነበርና ወደ አዛዡ ከገባች በኋላ «ክቡር ጌታዬ ሆይ ርስት ተወስዶብኛል፤ እንድትመልስልኝ አስቀድሜ ደጅ ልጠና መጥቻለውና ርዳኝ፤ ትብብርህ አይለየኝ» አለችው፡፡ በስሜት ፈረስ ታውሮ የነበረው የሠራዊቶቹ አዛዥም የጠየቀችውን እንደሚፈጽምላት ቃል ገባላት። ባማረ ድንኳን እንዲያስቀምጧት ሎሌዎቹን አዘዘ። ዮዲትም የተሰጣትን ጥበብ ተጠቅማ፣ መውጣት ስትፈልግ የምትወጣበትን እና የምትገባበትን ዕድል በ

#እግዚአብሔር አጋዥነት ዐወቀች፡፡ ከቀናት በኃላ የጦር አበጋዙ ለሠራዊቱ የምሳ ግብዣ አዘጋጅቶ ዮዲትን ከጎኑ አስቀመጣት፤ ከበሉና ከጠጡ በኋላም ሁሉን ሰው አስወጣ፤ እልፍኙን በመዝጋት ከእርሷ ጋር ብቻውን ሆነ፤ ነገር ግን እንቅልፍ ጣለው፡፡ እርሷም ወደ አምላኳ ጸለየች፤ ፈጣሪዋ እንዲረዳትም አጥብቃ ለመነች። በኋላም ከራስጌው ሰይፍ አንስታ አንገቱን ቀላችው፤ በድኑንም ከመሬት ጣለችው። የሆሎፎርኒስን ሞት ሠራዊቱ ሲሰሙ አውራ እንደሌለው ንብ ተበተኑ፤ ከፊሎቹ ሞቱ። እስራኤላውያንም ከሞት ተርፈው በ #እግዚአብሔር ኃይል ድል አደረጉ፤ በደስታም ፈጣሪያቸውን አመሰገኑ። (ዮዲት ፰፥፪)

ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ የሚያስረዳን ዮዲት ጠላቶቿን ድል ያደረገችው በጾምና በጸሎት እንደሆነ ነው፡፡ ለእኛም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ምንም እንኳ ወርኃ ጳጉሜን የፈቃድ ጾም ቢሆንም በሀገራችን የተጋረጠውን ችግር እናልፍ ዘንድ በፈቃደኝነት እንጾማለን። #እግዚአብሔር አምላካችን ለሁላችንም ጥበብ ሰጥቶናል። ይህም ችግሮችን ሁሉ የምንፈታበት መንገድ ነው። በዚህም የዓመተ መሸጋገሪያና የክረምቱ ወር ማብቂያ በመሆኑ ዕለተ ምጽአት ስለሚታሰብበት በየዓመቱ በጳጉሜ ወር ከሌሊት ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን ተገኝተን ጠበል በመጠመቅ፣ በማስቀደስና በመጸለይ እንዲሁም ሥጋ ወደሙን በመቀበል ልናሳልፍ ይገባል። ዕለተ ምጽአትም ከዚህ ዓለም ወደ ወዲያኛው ዓለም መሸጋገሪያችን ነውና በቀኙ እንቆም ዘንድ እንጾማለን፡፡ የሚመጣውን አዲስ ዘመንም በንጽሕና ለመቀበል ስላለፈው ዓመት ኃጢአታችን ንስሓ የምንገባበት ጾምም ነው።

ከተጋረጠብን ችግር « #እግዚአብሔር ያድነናል» በማለት ልክ እንደ ዮዲት ሱባኤ ገብተን፣ ማቅ ለብሰን፣ አመድ ነስንሰንና ድንጋይ ተንተርሰን አብዝተን ልንጾምና ልንጸልይ ይገባል፡፡ ሊለያየን፣ ሊነጣጥለን፣ ሊበታትነን እና ሊገድለን ካሰበው እንዲሁም ፍቅርን፣ መተሳሰብንና አንድነትን ሊነፍገን ከቃጣው ጠላትና ሃይማኖታችንን ሊያስተወን ከሚመጣ ፀረ ሃይማኖት እንድናለን። ስለዚህ ከፊታችን ያለችውን አምስቱን የጳጉሜን ቀን በፍቅር፣ በአንድነትና በሃይማኖት ጸንተን፣ ጾመን፣ ጸልየን ለዘመነ ማቴዎስ እንድንደርስ #እግዚአብሔር አምላካችን ይርዳን፤ አሜን።

#ወስብሐት_ለእግዚአብሔር
+++ #ልብስህን_ማን_ወሰደው? +++

በአንድ ወቅት "አባ ሰራብዮን" ወደ እስክንድርያ በሄደ ጊዜ፣ በገበያም ስፍራ አንድ ከልብስ የተራቆተ ነዳይ አገኘ፡፡ ለራሱም ‹ይህ ደሃ ሰው ታርዞ መነኩሴ የተባልኩ እኔ እንዴት ለብሼ እታያለሁ? በእውነት ይህ ‹ታርዤ አልብሳችሁኛልና› ብሎ የተናገረው ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ አይደለምን? በዚህ ብርድ እየተሰቃየ ነው እኮ!› ብሎ ፈጥኖ የገዛ ልብሱን ከራሱ በማውለቅ ይለብስ ዘንድ ለዚያ ደሃ ሰጠው፡፡ ከዚያም በእጁ ያለውን መጽሐፍ ቅዱስ እንደያዘ እርቃኑን በጎዳናው ዳር ተቀመጠ፡፡ እርሱን የሚያውቀው አንድ የከተማው ባለጠጋ ሰው አባ ሰራብዮን ባለበት ሥፍራ ሲያልፍ ተመልክቶት ወደ እርሱ ቀረበና ‹አባ ሰራብዮን ሆይ ልብስህን ማን ወሰደው?› ሲል ጠየቀው፡፡ ቅዱሱም በእጁ ወደ ያዘው መጽሐፍ ቅዱስ እየጠቆመ ‹ልብሴን የወሰደው ይህ ነው!› አለው፡፡ ያም ባለጠጋ አዲስ ልብስ ገዝቶ አለበሰው። ከዚህም በኋላ አባ ሰራብዮን ከእርሱ እንደ ተለየ በመንገድ ሲሄድ ዕዳውን መክፈል ባለመቻሉ እያንገላቱ ወደ ወኅኒ ቤት የሚወስዱትን አንድ ሰው ተመለከተ፡፡ እርሱም የያዘውን መጽሐፍ ቅዱስ ፈጥኖ በመሸጥ የዚያን ሰው ዕዳ ከፍሎ ነጻ አደረገው፡፡ ይህንንም አድርጎ ጉዞውን ሲጀምር እንደ ገና ሌላ የታረዘ ነዳይ ሲለምን ተመለከተ። አባ ሰራብዮንም እንደ ቀድሞው የለበሰውን ልብስ አውልቆ ለነዳዩ በመስጠት እርሱ እርቃኑን ወደ በአቱ ተመለሰ፡፡ ደቀ መዛሙርቱም መምህራቸውን እርቃኑን ባዩት ጊዜ ደንግጠው ‹መምህር! ልብስህ ወዴት አለ?› ብለው ጠየቁት፡፡ እርሱም ‹መጸወትኩት› አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም መልሰው ‹እኛን የምታጽናናበት መጽሐፍ ቅዱስህስ አባታችን?› ሲሉ ደግመው ጠየቁት፡፡ አባ ሰራብዮንም ‹በእጄ የነበረው መጽሐፍ ቅዱስ ሁል ጊዜ ‹ሂድ ያለህን ሽጠህ ለድሆች ስጥ› ይለኛል፤ ስለዚህ ያለኝ እርሱ ነበር እርሱንም ሸጥኩት› አላቸው፡፡

ምንጭ :–Paradise of the monks, P 89

ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እንደሚናገረው ምጽዋት የፊት መብራት ናት፡፡ አንድ ሰው በጨለማ ሲጓዝ ከኋላው መብራት ቢያበሩለትም እንኳ ከፊቱ የሚቀድመው የገዛ የአካሉ ጥላ እንቅፋት እየሆነበት ይጥለዋል፡፡ ወደ ፊት ያለውን መንገድ አጥርቶ እያየ ያለ ስጋት ለመሄድ እንዲችል የግድ የፊት መብራት ያስፈልገዋል፡፡ ጾም ፣ጸሎት እና ሌሎች መንፈሳዊ ትሩፋት እንደ ኋላ መብራት ናቸው፡፡ የፊት መብራት የተሰኘች ምጽዋት ካልታከለችባቸው እነዚህ ብቻቸውን ዋጋን አያሰጡንም፡፡ ከምጽዋት በላይ ታላቅ ነገር እንደሌለ ልንረዳ ይገባል፡፡ ዓለም ሁሉ ከነበረበት የበደል ዕዳ የዳነው ቸር እረኛ በሆነው በመድኃኔ ዓለም በአካሉ ምጽዋትነት (በሥጋው በደሙ መሰጠት) ነውና!!!
#ጳጒሜን_2

#ቅዱስ_ቲቶ_ሐዋርያ

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጳጒሜን ሁለት በዚህች ቀን ሐዋርያ ጳውሎስ መልእክት የጻፈለት የከበረ ሐዋርያ ቲቶ አረፈ። የዚህም ቅዱስ ትውልዱ ቀርጤስ ከሚባል አገር ነው። እርሱም ለዮናናውያን ወገን ለሆነ ለአገረ ገዥው እኅት ልጅዋ ነው።

ከታናሽነቱም የዮናናውያንን ትምህርትና ፍልስፍና ተምሮ እጅግ አዋቂ ሆነ በጠባዩም ቅን ሥራው ያማረ ለድኆችና ለችግረኞች መራራት የሚወድ ነው። ከሌሊቶችም በአንዲቱ ቲቶ ሆይ ስለ ነፍስህ ድህነት ተጋደል ይህ ዓለም አይጠቅምህምና የሚለውን በሕልሙ አየ። ከእንቅልፉም በነቃ ጊዜ ደነገጠ ምን እንደሚሠራም አላወቀም።

ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት የ #መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ትምህርት በተሰማ ጊዜ ብዙዎች ሰዎችም ተአምራቱን እርስበርሳቸው ተነጋገሩ የአክራጥስ መኰንንም ሰምቶ አደነቀ ዕውነት እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ወይም የሥራይ እንደሆነ ሊያውቅ ሽቶ የሚልከው ብልህ ሰው ፈለገ የእኅቱንም ልጅ ቲቶንን መረጠው ከእርሱ የሚሻል የለምና። ሲልከውም ታላቅና ጥልቅ የሆነ ምርመራ እንዲመረምር አዘዘው።

ቲቶም ከይሁዳ ምድር በደረሰ ጊዜ የ #መድኃኒታችንን ድንቆች የሆኑ ተአምራቶቹን አየ ሕይወትነት ያላቸው ትምህርቶቹንም ሰማ። ከዮናናውያንም በትምህርታቸውና በሥራቸው መካከል ታላቅ የሆነ መራራቅን አግኝቶ የዮናናውያን ሃይማኖታቸው የቀናች እንዳልሆነች ለይቶ ዐወቀ።

ከዚህም በኋላ በክብር ባለቤት በ #ጌታችን_ኢየሱስ አመነ፤ ደቀ መዝሙሩም ሁኖ ተከተለው። ወደ እናቱ ወንድም ወደ አገረ ገዥውም መልእክትን ላከ የክብር ባለቤት #ጌታ_ኢየሱስ_ክርስቶስ የሚያስተምረውና የሚሠራው ዕውነት እንደሆነ ነገረው።

#ጌታችንም ከሰባ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ውስጥ የተቆጠረ አደረገው ከዕርገቱም በኋላ ከሐዋርያት ጋር የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ተቀብሎ ከእሳቸው ጋር በሀገሮች ሁሉ ዙሮ አስተማረ። #ጌታችንም ጳውሎስን ጠርቶ ሐዋርያው በአደረገው ጊዜ ያን ጊዜ ሐዋርያ ጳውሎስን ተከተለው በብዙ አገሮችም ወንጌልን ሰበከ።

የከበረ ጳውሎስም በሮሜ ከተማ ምስክር ሆኖ ከሞተ በኋላ ቅዱስ ቲቶ ወደ ሀገረ አክራጥስ ተመለሰ ቤተ ክርስቲያንም ሠርቶ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾመላቸው በዙሪያቸው ላሉ አገሮችም እንዲሁ አደረገ።

ከዚህም በኋላ ሐዋርያዊ አገልግሎቱን ፈጽሞ ወደ ወደደው #እግዚአብሔር ሔደ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ቲቶ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጳጒሜን_2)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጳጒሜ_2_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ቲቶ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹-² የእግዚአብሔር ባሪያና የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ በእግዚአብሔር ለተመረጡት እምነት እንዲሆንላቸው በዘላለምም ሕይወት ተስፋ እንደ አምልኮት ያለውን እውነት እንዲያውቁ የተላከ፤ ስለዚህም ሕይወት የማይዋሽ እግዚአብሔር ከዘላለም ዘመናት በፊት ተስፋ ሰጠ፥
³ በዘመኑም ጊዜ፥ መድኃኒታችን እግዚአብሔር እንዳዘዘ፥ ለእኔ አደራ በተሰጠኝ ስብከት ቃሉን ገለጠ፤
⁴ በሃይማኖት ኅብረት እውነተኛ ልጄ ለሚሆን ለቲቶ፤ ከእግዚአብሔር አብ ከመድኃኒታችንም ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን።
⁵ ስለዚህ ምክንያት የቀረውን እንድታደራጅ በየከተማውም፥ እኔ አንተን እንዳዘዝሁ፥ ሽማግሌዎችን እንድትሾም በቀርጤስ ተውሁህ፤
⁶ የማይነቀፍና የአንዲት ሚስት ባል የሚሆን፥ የሚያምኑም ልጆች ያሉት፥ ስለ መዳራትም ወይም ስለ አለመታዘዝ የማይከሰስ ማንም ቢኖር፥ ሹመው።
⁷ ኤጲስ ቆጶስ፥ እንደ እግዚአብሔር መጋቢ፥ የማይነቀፍ ሊሆን ይገባዋልና፤ የማይኮራ፥ የማይቆጣ፥ የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ፥ ነውረኛ ረብ የማይወድ፥
⁸ ነገር ግን እንግዳ ተቀባይ፥ በጎ የሆነውን ነገር የሚወድ፥ ጠንቃቃ፥ ጻድቅ፥ ቅዱስ፥ ራሱን የሚገዛ ይሁን፤
⁹ ሕይወት በሚገኝበት ትምህርት ደግሞ ሊመክር ተቃዋሚዎቹንም ሊወቅስ ይችል ዘንድ፥ እንደተማረው በታመነ ቃል ይጽና።
¹⁰ የማይታዘዙና ከንቱ የሚናገሩ የሚያታልሉ ይልቁንም ከተገረዙት ወገን የሚሆኑ ብዙ ናቸውና፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ጴጥሮስ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁷ አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሳት ቀርተዋል።
⁸ እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ፥ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፥ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን እንደ ሆነ ይህን አንድ ነገር አትርሱ።
⁹ ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።
¹⁰ የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፥ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፥ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል።
¹¹-¹² ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፥ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፥ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል? ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይፈታል፤
¹³ ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³¹ ከጸለዩም በኋላ ተሰብስበው የነበሩበት ስፍራ ተናወጠ፥ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ የእግዚአብሔርንም ቃል በግልጥ ተናገሩ።
³² ያመኑትም ሕዝብ አንድ ልብ አንዲትም ነፍስ ነበሩአቸው፥ ገንዘባቸውም ሁሉ በአንድነት ነበረ እንጂ ካለው አንድ ነገር ስንኳ የራሱ እንደ ሆነ ማንም አልተናገረም።
³³ ሐዋርያትም የጌታን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ በታላቅ ኃይል ይመሰክሩ ነበር፤ በሁሉም ላይ ታላቅ ጸጋ ነበረባቸው።
³⁴ በመካከላቸው አንድ ስንኳ ችግረኛ አልነበረምና፤ መሬት ወይም ቤት ያላቸው ሁሉ እየሸጡ የተሸጠውን ዋጋ ያመጡ ነበርና፥
³⁵ በሐዋርያትም እግር አጠገብ ያኖሩ ነበር፤ ማናቸውም እንደሚፈልግ መጠን ለእያንዳንዱ ያካፍሉት ነበር።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጳጒሜ_2_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ቀዳሚሃ ለጥበብ ፈሪሃ እግዚአብሔር። ምክር ሠናይት ለኵሉ ዘይገብራ። ወስብሐቲሁኒ ይነብር ለዓለም"። መዝ 110፥10።
“የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፥ ለሚያደርጓትም ሁሉ ደኅና ማስተዋል አላቸው፤ ምስጋናውም ለዘላለም ይኖራል።” መዝ 110፥10።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጳጒሜ_2_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 10
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ከዚህም በኋላ ጌታ ሌሎቹን ሰብዓ ሾመ፥ ሁለት ሁለትም አድርጎ እርሱ ሊሄድበት ወዳለው ከተማና ስፍራ ሁሉ በፊቱ ላካቸው።
² አላቸውም፦ መከሩስ ብዙ ነው፥ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ለመከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት።
³ ሂዱ፤ እነሆ፥ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ።
⁴ ኮረጆም ከረጢትም ጫማም አትያዙ፤ በመንገድም ለማንም እጅ አትንሡ።
⁵ ወደምትገቡበት ቤት ሁሉ አስቀድማችሁ፦ ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን በሉ።
⁶ በዚያም የሰላም ልጅ ቢኖር፥ ሰላማችሁ ያድርበታል፤ አለዚያም ይመለስላችኋል።
⁷ በዚያም ቤት ከእነርሱ ዘንድ ካለው እየበላችሁና እየጠጣችሁ ተቀመጡ፤ ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋልና። ከቤት ወደ ቤት አትተላለፉ።
⁸ ወደምትገቡባትም ከተማ ሁሉ ቢቀበሉአችሁ፥ ያቀረቡላችሁን ብሉ፤
⁹ በእርስዋም ያሉትን ድውዮችን ፈውሱና፦ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀረበች በሉአቸው።
¹⁰ ነገር ግን ወደምትገቡባት ከተማ ሁሉ ባይቀበሉአችሁ፥ ወደ አደባባይዋ ወጥታችሁ፦
¹¹ ከከተማችሁ የተጣበቀብንን ትቢያ እንኳን እናራግፍላችኋለን፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ግን ወደ እናንተ እንደ ቀረበች ይህን እወቁ በሉ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱሳን_ሐዋርያት_ቅዳሴ ነው። መልካም የሐዋርያው የቅዱስ ቲቶ የዕረፍት በዓልና የጾም፣ የጸሎትና የምሕላ ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2024/09/21 20:26:47
Back to Top
HTML Embed Code: