Telegram Web Link
#ጳጒሜን_3

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጳጒሜን ሦስት በዚህች ዕለት የሰዎች ሁሉ ጸሎት የሚያርግባት #ርኅወተ_ሰማይ ትባላለች፣
የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ #ቅዱስ_ሩፋኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው፣ ለእግዚአብሔር ልጅ ምሳሌው የሆነ #የካህኑ_መልከጼዴቅ መታሰቢያው ነው፣ የኢትዮጵያ ንጉሥ መልካም ስም አጠራር ያለው #ቅዱስ_ዘርዐ_ያዕቆብ አረፈ፣ ሰንዱን ከሚባል አገር #ቅዱስ_ሰራጵዮን አረፈ፣ አቡነ ቀጸላ ጊዮርጊስ ዕረፍታቸው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ርኅወተ_ሰማይ

ጳጒሜን ሦስት በዚህች ዕለት የሰዎች ሁሉ ጸሎት የሚያርግባት፣ አራተኛው መጋቢ ኮከብ የሚያልፍባት፣ ለሰው ልጆች ከፈጣሪያቸው ጸጋ በረከት የሚሰጥባት ዕለት ስለሆነች ርኅወተ ሰማይ (ሰማይ የሚከፈትባት) ቀን ትባላለች።

አሁን በሰማይ መዘጋት መከፈት ኑሮበት አይደለም። የሰው ልጆችን ልመና ቅዱሳን መላእክት ያለ ከልካይ የሚያሳርጉበት አንድም ቅዱስ ሩፋኤል የዓመቱን የጸሎት መዝገብ የሚከፍትበት ቀን ስለሆነ እንዲህ ተባለ እንጂ።

እመቤታችን #ድንግል_ማርያም ለአጼ ናዖድ እንደ ነገረቻቸው በዚህች ዕለት ሁሉም ቅዱሳን ስለሚታሰቡ፣ የ #እግዚአብሔር የምሕረት መዝገቡ ስለሚከፈት፣ ዕለቷን ክብርት ያሰኛታል። በቅዱስ ሩፋኤል አበጋዝነት (መሪነት) በዚህች ዕለት ለዓመት የሚበቃ ምሕረት ይገኛል።

ስለዚህም አባቶቻችን በዚህች ሌሊት ሦስት መቶ ስልሳ አምስት አቡነ ዘበሰማያትን ሲጸልዩ ያድራሉ። በሌላ ወገን ደግሞ የጌታ ዳግም ምጽዓቱ መታሰቢያ እንደ መሆኗ ትልቅ ትኩረትም ይሰጣታል። ቸሩ #ጌታችን ከተከፈተች ገነት ከተነጠፈች ዕረፍት ሁላችንንም ያድርሰን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሩፋኤል_ሊቀ_መላእክት

በዚህች ቀን የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ የሩፋኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው። እርሱም ከመላእክት አለቆች ሦስተኛ የሆነ ነው። ደግሞም ከእስክንድርያ ውጭ በደሴት የታነፀች ቤተ ክርስቲያኑ በከበረ ሊቀ ጳጳሳት ቴዎፍሎስ ዘመን በውስጧ ተአምር የተገለጸባት የከበረችበት ነው።

ይህም እንዲህ ነው ሀብታም ሴት ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ መጥታ ሳለ ከእርሷ ጋርም ብዙ ሰው ነበረ። ከባሏም የወረሰችው ብዙ ገንዘብ አላት በሊቀ ጳጳሳቱ ቤት አንጻር ያለውን ኮረብታ አስቆፈረችው በጥቅምት ወር ዐሥራ ስምንት ቀን እንደጻፍን የወርቅ መዝገብ ተገለጠ።

በዚያም ወርቅ ብዙዎች አብያተ ክርስቲያናትን አነፀ ከእርሳቸውም አንዲቱ የመላእክት አለቃ በሆነ በከበረ መልአክ ሩፋኤል በስሙ የታነፀች ይህች ናት። ሥራዋንም በፈጸመ ጊዜ እንደዛሬው በዚች ቀን አከበራት።

ብዙ ምእመናንም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ ፈጽማ ተናወጸች ያቺ ደሴት በታላቅ አንበሪ ጀርባ ላይ የቆመች ናትና። የሰዎች ብዛትም በከበደው ጊዜ ቤተ ክርስቲያኒቱን ያፈርሳት ዘንድ ሰይጣን አነሣሣው። ወደ ክብር ባለቤት #እግዚአብሔርም በከበረ መልአክ ሩፋኤል ስም ጮኹ ያን ጊዜ ይህ የከበረ ሩፋኤል ያንን አንበሪ በጦሩ ወግቶ እንዲህ አለው እግዚአብሔር አዞሃልና ከቦታህ ሳትናወጽ ጸጥ ብለህ ቁም። አንበሪውም ጸጥ ብሎ ቆመ አልታወከም በውስጧም ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ ለሕሙማንም ፈውስ ሆነ።

ይቺም ቤተ ክርስቲያን እስላሞች እስከተነሡበት ዘመን ኖረች ከዚህም በኋላ ሁለተኛ ያ አንበሪ ተናወጸ ደሴቲቱም በላይዋ ከሚኖሩ ብዙ ሕዝብ ጋራ ሠጠመች።

#ዳግመኛም የቊስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሐንስ ጻድቅ ለሆነ ንጉሥ አኖሬዎስ ተናገረ። እንዲህም አለው ንጉሥ ሆይ እኛ ወዳንተ ልንመጣ በመርከብ እንደተሳፈርን ዕወቅ በጒዞ ላይ ሳለንም በቀዳሚት ሰንበት ቀን በደሴት ውስጥ ታናሽ ቤተ ክርስቲያን አየን ወደ ወደቡም ደርሰን በዕለተ እሑድ ሥጋውን ደሙን እንቀበል ዘንድ ወደርሷ ሔድን።

ለዚያች ቤተ ክርስቲያንም በጐኗ ታናሽ ገዳም አገኘን በውስጧም ወንድሞች መነኰሳት አሉ በክብር ባለቤት ጌታችንም ፈቃድ ወደ ርሳቸው ደረስን ። መነኰሳቱንም በቀደሙ አባቶች ዘመን የተጻፈ አሮጌ መጽሐፍ በእናንተ ዘንድ እንዳለ እጽናናበት ዘንድ እርሱን ሰጡኝ አልኳቸው። እንዲህም ብለው መለሱልኝ እኛ ትርጓሜያቸውን የማናውቀው መጻሕፍቶች በዕቃ ቤት አሉ። እኔም አያቸው ዘንድ ወደዚህ አምጡልኝ አልኳቸው። በአመጡአቸውም ጊዜ መረመርኳቸው #ጌታችንም በደቀ መዛሙርቱ ፊት ያደረጋቸውን ኃይሎችና ድንቆች ተአምራቶችን ስለ ሰማይና ምድርም ጥንተ ተፈጥሮ አገኘሁ።

ሁለተኛም ስመረምር ስለ ሰባቱ ሊቃነ መላእክት ሹመትና መዐርግ አባቶቻችን ንጹሐን ሐዋርያት የጻፉትን አገኘሁ ይኸውም #ጌታችን በደብረ ዘይት ከእሳቸው ጋራ እያለ የመለኮቱን ምሥጢር በገለጠላቸው ጊዜ። ሐዋርያትም እንዲህ ብለው እንደለመኑት #ጌታችንና ፈጣሪያችን ሆይ የከበረ የሩፋኤልን ክብሩን ታስረዳን ዘንድ እንለምንሃለን በየትኛው ዕለት በየትኛው ወር ሾምከው።

ከባልንጀሮቹ የመላእክት አለቆችም ትክክል ነውን የበዓሉን መታሰቢያ ያደርጉ ዘንድ በዓለም ውስጥ ስለርሱ እንድናስተምር እርሱም በመከራቸው ጊዜ ይረዳቸው ዘንድ በአማላጅነቱም በአንተ ዘንድ ይቅርታን ያገኙ ዘንድ።

ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አዘዘና ከሦስተኛው ሰማይ ሦስቱ የመላእክት አለቆች ሚካኤል፣ ገብርኤልና ሩፋኤል መጡ በታላቅ ደስታም ለክብር ባለቤት ለ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሰገዱ። #ጌታችንም ሩፋኤልን እንዲህ አለው የክብርህን ገናናነት የባልንጀሮችህንም ልዕልናቸውን እንዲያውቁ ለሐዋርያት ንገራቸው።

ያን ጊዜም ለ #ጌታችን ሰገደ ይነግራቸውም ዘንድ ጀመረ እንዲህም አላቸው ደገኛው የመላእክት አለቃ ሚካኤል ለሁሉም መላእክት አለቃቸው ነው ስሙም ይቅር ባይ ይባላል።

ሁለተኛም የመላእክት አለቃ ገብርኤል የስሙ ትርጓሜ አገልጋይም ጌታም የሆነ የዓለሙ ሁሉ እመቤት የሆነች አምላክን የወለደች ቅድስት #ድንግል_ማርያምን ያበሠራት ነው። የእኔም ስሜ ሩፋኤል ነው ይህም ደስ የሚያሰኝ ቸር መሐሪ ቅን የዋህ ማለት ነው እኔም ኃጢአተኞችን በ #እግዚአብሔር ዘንድ አልከሳቸውም ከኃጢአታቸው በንስሓ እስኪመለሱ ስለ ቅንነቴ በእነርሱ ላይ እታገሣለሁ እንጂ።

በሃያ ሦስቱ የመላእክት ነገድ ሠራዊት ላይ #እግዚአብሔር የሾመኝ እኔ ሩፋኤል ነኝ #እግዚአብሔር አብን ይቅር ባይ ልጁን አጽናኝና አዳኝ የሆነ #መንፈስ_ቅዱስን እናመሰግነው ዘንድ።

በደብረ ጽዮን በሚደረገው የሺህ ዓመት ተድላ ደስታ የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ የክብር ጽዋን በሚሰጣቸው ጊዜ ለቅዱሳኖቹ በጎ ነገርን እንድሰጣቸው #እግዚአብሔር ያዘዘኝ ሩፋኤል እኔ ነኝ። ደግሞም በዚች ቀን ከዕፀ ሕይወት ዐጽቅ ወስጄ ለተመረጡ ክርስቲያኖች በእጄ እንድሰጣቸው #እግዚአብሔር ያዘዘኝ ሩፋኤል እኔ ነኝ።

የሰማያት መዛግብትም ከእጄ በታች ተጠብቀው የሚኖሩ እኔ ሩፋኤል ነኝ። እኔም #እግዚአብሔር እንዳዘዘኝ እከፍታቸዋለሁ እዘጋቸዋለሁም።

በምድር ሰው ለባልንጀራው ስለ ስሜ በጎ ነገር ቢያደርግ እኔ በመከራው በችግሩ ረዳዋለሁ ወይም የሹመቴን ነገር የሚጽፍ ወይም ከቅዱሳን ጋራ ስሜን የሚያስብ ወይም በስሜ ለቊርባን የሚሆነውን የሚሰጥ ወይም በበዓሌ ቀን ምጽዋትን የሚሰጥ ይኸውም #እግዚአብሔር በሊቃነ መላእክት ክብር የሾመኝና ያከበረኝ ጳጕሚን ሦስት ቀን ነው። ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት እስከማስገባው በብርሃን ሠረገላ እኔ እሸከመዋለሁ በምድር ላይ ከቶ እንደርሱ ያለ የማይገኝ መዐዛው እጅግ ጣፋጭ በሆነ ሽቱ ነፍሶቻቸው እርሱን በማሽተት ደስ እንዲላቸው አደርጋለሁ።
ሐዋርያት ሆይ በ #እግዚአብሔር ፊት እስከምትቆሙ እጠብቃችሁ ዘንድ ከእኔ ርዳታን ሹ። የዚህ የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ ሩፋኤል ተአምራቶቹ ብዙ ናቸው ስለእኛ ይማልድ ዘንድ የበዓሉን መታሰቢያ ልናደርግ ይገባናል።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_መልከጼዴቅ

በዚህችም ቀን ለ #እግዚአብሔር ልጅ ምሳሌው የሆነ የመልከጼዴቅ መታሰቢያው ነው። መልከጼዴቅም ዐሥራ አምስት ዓመት በሆነው ጊዜ ከአዳም ሥጋ ጋር እንዲልከውና በምድር መካከል እንዲያኖረው #እግዚአብሔር ኖኅን አዘዘው እርሷም ቀራንዮ ናት። የዓለም #መድኃኒት_ክርስቶስም መጥቶ በዚያ እንደሚሠዋ አዳምንም ከልጆቹ ሁሉ ጋር እንደሚያድነው አመለከተው።

ከዚህም በኋላ በአባቱ በኖኅ ትእዛዝ ሤም መልከጼዴቅን በሥውር ወሰደው የ #እግዚብሔርም መልአክ እየመራቸው ሔደው ወደ ቀራንዮ ተራራም አደረሳቸው መልከጼዴቅም ክህነትን ተሾመ። ዐሥራ ሁለት ደንጊያዎችንም ወስዶ መሠዊያ ሠራ ከሰማይ የወረደለትንም ኅብስትና ወይን መሠዊያ በሠራቸው ደንጊያዎች ላይ መሥዋዕትን አሳረገ።

ምግቡንም መላእክት ያመጡለታል ልብሱም ዳባ ነው በአባታችን አዳም ሥጋ ዘንድ ሲያገለግል ኖረ። አብርሃምም ከጦርነት ነገሥታትን ድል አድርጎ በተመለሰ ጊዜ ኅብስትንና ወይንን አቀረበለት አብርሃምም ከገንዘቡ ሁሉ ከዐሥር አንድ ሰጠው እርሱ ካህንም ንጉሥም ሁኖ ተሹሟልና።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አፄ_ዘርዓ_ያዕቆብ_ጻድቁ

በዚህችም ቀን የኢትዮጵያ ንጉሥ መልካም ስም አጠራር ያለው ዘርዐ ያዕቆብ አረፈ። ዘርዐ ያዕቆብ ብሎ ስሙን መልአክ ነው ያወጣለት፡፡ ሲወለድም ብርሃን ቤቱን ሞለቶት ታይቷል፡፡ ግማደ መስቀሉን ከአባቱ ከዐፄ ዳዊት ተረክቦ በማስመጣት በግሸን አስቀምጦታል፡፡ ንግሥቲቱ የዐፄ ዳዊት ሚስት የጻድቁን የደብረ ቢዘኑን የአቡነ ፊሊጶስን እግራቸውን አጥባቸው ስትጨርስ የእግራቸውን እጣቢ ከጠጣችው በኃላ የእምነቷን ጽናትና ጥልቀት አይተው ጻድቁ ባደረባቸው መንፈስ ቅዱስ ትንቢትን በመናገር "ከማኅፀንሽ ፍሬ ታላቅ ጻድቅ ልጅ ይወጣል" ብለው ትንቢት ነገሯት፡፡ በትንቢታቸውም መሠረት ታላቁ ጻድቅ ንጉሥ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ተወልዱ፡፡

ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ለሀገራችንም ሆነ ለቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ ውለታ ውለዋል፡፡ ጣዖት አምልኮን ከሃገራችን ለማጥፋት ብዙ ሺህ ካህናትን አሰልጥነው በመላ አገራችን አሰማርተዋል፡፡ የኑፋቄ ችግሮችን ለመቅረፍ ጉባኤያትን አዘጋጅተዋል፡፡ ተአምረ ማርያምን ጨምሮ ከ11 ያላነሱ መጻሕፍትን በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ደርሰው ለአገልግሎት አብቅተዋል፡፡ ብዙ መጻሕፍትን ከውጪ አስመጥተው አስተርጉመዋል፡፡ ሰው ሁሉ ለእመ ብርሃንና ለቅዱስ መስቀሉ ፍቅር እንዲገዛ ጥረት አድርገዋል፡፡ እመቤታችንን በፍጹም ልባቸው ከመውደዳቸው የተነሳ ዛሬም ድረስ በሃገራችን #ድንግል_ማርያም "የዘርዓ ያዕቆብ እመቤት" እየተባለች ትጠራለች፡፡ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን አንጸው ብዙ ሥርዓቶችም በሊቃውንት እንዲሠሩ አድርገው ሌሎች ብዙ በጐ ተግባራትንም ፈጽሞ በዚህች ዕለት በሰላም ዐርፈዋል፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሰራጵዮን_ዘሰንዱን

በዚህችም ቀን ሰንዱን ከሚባል አገር ቅዱስ ሰራጵዮን አረፈ። ይህም ቅዱስ ከታናሽነቱ ጀምሮ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትን ትርጓሜያቸውንም ተማረ የዚህንም ዓለም ገንዘብ ሁሉ ትቶ ወደ አረሚ አገር ሔደ ራሱንም በሃያ ብር ሸጦ ማገልገል ጀመረ የሽያጩንም ዋጋ ጠበቀው። እንጀራ ሳይበላ ውኃ ሳይጠጣ ከስሕተታቸው ይመልሳቸው ዘንድ ሁል ጊዜ ወደ #እግዚአብሔር ይጸልይ ነበር።

ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት በሆነ በ #ክርስቶስ አሳመናቸው ሕግንና ሥርዓትንም ሁሉ አስተማራቸው ከዚህም በኋላ ስለርሳቸው ራሱን ባሪያ አድርጎ እንደሸጠ እንጂ እርሱ ባሪያ እንዳልሆነ ነገራቸው ሽያጩንም ለድኆች እንዲሰጡት ሰጣቸው።

ከዚህም በኋላ መንካያውያን ወደሚባሉ ሕዝቦች ሒዶ ለነርሱም ራሱን ሸጠ የክብር ባለቤት ወደሆነ #ክርስቶስ እምነት እስከመለሳቸው ድረስ ተገዛላቸው። ከዚህም በኋላ ደግሞ ወደ ሮሜ አገር ሒዶ በሰላም እስከ አረፈ ድረስ በጾምና በጸሎት እየተጋደለ ኖረ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ቀፀላ_ጊዮርጊስ

ትውልዳቸው አገው ሲሆን ከብዙ ጽኑ ተጋድሎአቸው በኋላ እንደ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ስድስት ክንፍ የተሰጣቸው ታላቅ አባት ናቸው። አቡነ ቀፀላ ጊዮርጊስ በ16ኛው መ/ክ/ዘ የነበሩ ሲሆን ታላቁን ቀብጽያ አንድነት ገዳምን የመሠረቱት ናቸው። ጻድቁ በመጀመሪያ የአባ አሞኒን ገዳም ለመገደም ወደ ትግራይ ቀብጽያ ሲሄዱ በእግዚአብሔር ታዘው የአቡነ አሞፅን ገዳም በሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስም መሠረቱ። ገዳሙም "ቀብጽያ አሞፅ ወቀፀላ ጊዮርጊስ አንድነት ገዳም" ተባለ።

አቡነ ቀፀላ ጊዮርጊስ 200 ተከታይ መነኰሳትን አስከትለው ሌሎች 6 አስደናቂ ገዳማትን ገድመዋል። ገዳማቱም ማይወኒ ቅዱስ ሚካኤል፣ ውጅግ ቅዱስ መርቆሬዎስ፣ ጅል ውኃ ቅዱስ ማርቆስ፣ ዶቅላኮ አርባእቱ እንስሳ፣ አንጓ ቅድስት ማርያም እና ድቁል ማርያም ይባላሉ።

ጻድቁ ስድስት ክንፍ እስኪሰጣቸው ድረስ ብዙ ተጋድሎ ያደረጉት በቀብጽያ ገዳም ነው። ዕረፍታቸውም ጳጒሜን 3 ቀን ነው። በዘንዶዎች የሚጠበቀው ይህ አስደናቂ ገዳም በብዙ መልኩ ከሌሎች ገዳማት የተለየ ነው። የገዳሙን አፈር ቅዱሳን መላእክት ናቸው ከገነት ያመጡት። ጌታችን 12 እልፍ መላእክቱን ልኮ ከገነት አፈር አምጥተው በዝናብ አምሳል በቀብጽያ ገዳም ላይ እንዲነሰንሱት አዟቸዋል።

ገዳሙን የተሳለመ ሰው ኢየሩሳሌም በጎልጎታን እንደተሳለመ የሚቆጠርለት ሲሆን በገዳሙ ውስጥ የተቀበረ ሰው ወቀሳ የለበትም። ከአካሉም ላይ ፀጉሩን ወይም ጥፍሩን ቆርጦ በገዳሙ ክልል ውስጥ የቀበረ ሰው ቢኖር መልአከ ሞትን ፈጽሞ እንደማያይና ገዳሙ የሚገኝበት አካባቢ በእግር ለመጓዝ አስቸጋሪ ቢሆንም ቦታውን የረገጠ እስከ 15 ትውልድ ምሕረትን እንደሚያገኝ ጌታችን በቃል ኪዳን አጽንቶታል።

ቀብጽያ ገዳምን ለየት የሚያደርገው ነገር ቢኖር ፈዋሹ ጠበል ከጻድቁ አቡነ አሞፅ መቃነ መቃብር ሥር የሚፈልቅ መሆኑ ነው፡፡ ከዋሻው ሥር የተንጠባጠበው ጠበል ወደ ጠንካራ ዐለትነት የሚቀየር ሲሆን እርሱን ለእምነት የተጠቀሙበት ሰዎች ከተለያዩ በሽታዎች ተፈውሰዋል፡፡ በቅርቡም ከ6 ዓመት በፊት በዚህ እምነት የተሻሸች አንዲት ሴት ከዘመኑና መድኃኒት ካልተገኘለት ከHIV በሽታና ከመካንነቷ ተፈውሳ ልጅ ወልዳለች፡፡ ይህ አስደናቂ ቀብጽያ ገዳም ፍልፍል ዋሻ ቤተ መቅደስ ቢሆንም ከጊዜና ብዛት ጉዳት ስለደረሰበትና የሚያድሰው አካል ስላላገኘ በአሁኑ ወቅት ሌላ አዲስ ቤተ መቅደስ እየታነጸ ይገኛል፡፡

በቀብጽያ ገዳም ውስጥ 336 ዓመት የሆነው የወይራ ዛፍ የሚገኝ ሲሆን በቅርቡ ስውራን የሆኑ ቅዱሳን ሦስት ጊዜ ደወል ሲደውሉበት ተሰምቷል፡፡ ገዳሙን አቡነ ቀፀላ ጊዮርጊስ ይገድሙት እንጂ በቦታው ላይ አቡነ አሞፅ አስቀድመው መቶ ዓመት በታላቅ ተጋድሎ ኖረውበታል። አቡነ አሞፅ ትውልዳቸው ሸዋ ሲሆን የመነኰሱት ደብረ ሊባኖስ በአቡነ ዮሐንስ ከማ እጅ ነው፡፡ አቡነ ዮሐንስ ከማ በመልአክ ታዘው 10 መነኰሳት 500 ሕዝብ ተከትሏቸው ወደ ትግራይ ሲሄዱ ሳምረ ወረዳ ላይ ሲደርሱ ሕዝቡ ቢራብ ዋርካ ዕለቱን አብቅለው ባርከው መግበውታል፣ ውኃም አፍልቀው አጠጥተውታል፡፡ ከዚኽም በኋላ የበቁትንና ቅዱሳን የሆኑትን ዓሥሩን መነኰሳት ገዳም እንዲገድሙ ወደተለያዩ ቦታዎች ላኳቸው፡፡ ከእነዚኽም ዓሥር ቅዱሳን መነኰሳት መካከል አቡነ አሞፅ አንዱ ናቸው፡፡ እርሳቸውም
ጽላተ ማርያምን ይዘው በቅዱሳን መላእክት ታጥራ ወደምትገኘው ምድረ ቀብጽያ መጥተው መቶ ዓመት በታላቅ ተጋድሎ ኖሩ።

አቡነ አሞፅ ሰቆቃወ ድንግል የሚባለውን የእመቤታችን መከራ የሚተርከውን ድንቅ ድርሰት ሙሉውን ክፍል በብራና ላይ በሥዕል ገልጸው በክብር አስቀምጠውታል፡፡ ከሰማይ የወረደላቸው የወርቅ መስቀላቸውም በገዳሙ ይገኛል፡፡

አቡነ አሞፅ በ1592 ግንቦት 26 አርብ ቀን ሲያርፉ ጌታችን ከድንግል እናቱ ጋር ተገልጾላቸው ከላይ ያየናቸውን አስደናቂ ቃልኪዳኖች ከሰጣቸው በኋላ ነፍሳቸውን እመቤታችን አቅፋ አሳረገቻቸው፡፡ ዐፅማቸው ያረፈበትን መካነ መቃብር ታላላቅ ዘንዶዎች ይጠብቁታል፡፡ ጠበላቸውም የፈለቀው ከመቃብራቸው ሥር ነው፡፡ ቦታው በስውራን ስለሚገለገል የከበሮ ድምፅ የሚሰማ ሲሆን የእጣንም ሽታ ይሸታል፡፡ ከአባታች ከአቡነ ቀፀላ ጊዮርጊስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎታቸውም ይማረን!።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በመልአኩና በቅዱሳኑ አማላጅነት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጳጉሜን_3#ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ እና #ከገድላት_አንደበት)
"በስመ #አብ_ወወልደ_ወመንፈስ_ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

እንኳን #የጌታችን_የአምላካች_የመድኃኒት #የኢየሱስ_ክርስቶስ_ዳግም_ምጽአት_ስለ_ዓለም_መጨረሻ#ስለ_ምሥጢረ_ትንሣኤ ለሚነገርበት ለዓመቱ የመጨረሻ #ዕለተ_ሰንበት (እሑድ) እግዚአብሔር አምላክ በሰላም በጤና አደረሰን።

#በዚህ_ሳምንት_መዝሙር፦ ሃሌ ሉያ በ፪ "ከመ እንተ መብረቅ ዘይወጽእ እምጽባሕ ወያስተርኢ እስከ ዓረብ ከማሁ #ምጽአቱ_ለወልደ_እግዚአብሔር ምስለ ኃይል ሰማያት በንጥረ መባርቅት (ከማሁ) ምስለ አዕላፍ መላእክት ወኵሎሙ ሊቃነ መላክት (ከማሁ) አክሊለ አክሊላት ዲበ ርእሶሙ ለካህናት። ትርጉም፦ መብረቅ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ እንዲታይ ከመላእክት አለቆች ሁሉ ጋር ከሰማያት ኃይል ጋር በመብረቆች ብልጭታ በካህናት ራስ ላይ አክሊልን የሚቀዳጅ #የወልደ_እጓለ_እመሕያው_የክርስቶስ ምጽአት እንዚሁ ነው። #ሊቁ_ቅዱስ_ያሬድ_በድጓው_ላይ

#የኢትዮጵያ_ኦርቶዶክስ_ተዋሕዶ_ቤተ_ክርስቲያን #ስለ_ዳግም_ ምጽአትና_ስለ_ዓለም_መጨረሻ፣ ስለ ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንም ሁልጊዜ የምታስተምር ቢሆንም በተለይ በዐቢይ ጾም ውስጥ "ደብረ ዘይት" በሚለው ዕለት ሰንበትና በዓመቱ መጨረሻም በወርኃ ጳጒሜን ስለ ዳግም ምጽአትና ስለ ዓለም ፍጻሜ ከቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ነገረ ምጽአቱንና ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን የሚመለከቱ ጥቅሶችን እያነበበችና ምዕመናንን እያስጠነቀቀች በየጊዜም ትኵረት ሰጥታ ታስተምራለች። በእነዚህ ወቅቶች በቤተ ክርስቲያን የሚዘመረው መዝሙር፣ ቅዳሴና ትምህርቱም ሁሉ ይህንኑ የተመለከተ ነው።
#ጳጒሜን_4

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጳጒሜን አራት በዚህች ቀን #የአባ_ባሞይን (#አባ_ጴሜን)ና #የ6ቱ_ወንድሞቹ እንዲሁም #የሮሜ_ሊቀ_ጳጳሳት_አባ_ሊባርዮስ የእረፍታቸው መታሰቢያ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ባይሞን (#አባ_ጴሜን)

ጳጒሜን አራት በዚህች ቀን ተጋዳይ አባ ባይሞን አረፈ። ይህም ቅዱስ ከምስር ሀገር ነው ስማቸው ዮሐንስ፣ ኢዮብ፣ ዮሴፍ፣ ላስልዮስ፣ ያዕቆብ፣ አብርሃም የሚባል ስድስት ወንድሞች አሉት ሁሉም መነኰሳት ሁነዋል። ከእሳቸውም ዮሐንስ ይልቃል ነገር ግን በእውቀትና በጥበብ ባይሞን ይበልጣል።

ሁሉም ተስማምተው ከዓለም ወጡ ከሰውም ሩቅ በሆነ ቦታ የሚኖሩ ሆኑ የክብር ባለቤት የሆነ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም ቀንበር ተሸክመው ከዘመድም ተለይተው በጠባብ መንገድ ተጓዙ።

እናታቸውም ልታያቸው ወዳ ወደ በዓታቸውም ደርሳ በውጭ ቆመች ወደርሷም መጥተው እንድታያቸው ላከችባቸው እነርሱም ወደርሷ እንዲህ ሲሉ ላኩ በዚህ በኃላፊው ዓለም ልታይን ከወደድሽ በወዲያኛው ልታይን አትችይም እርሷም አስተዋለች አልመለሰችላቸውም መንገዷን ተጓዘች።

ይህም አባት ባይሞን በአስቄጥስ ገዳም ለሽማግሌዎችም ለጐልማሶችም አረጋጊ ወደብ ሆነ። ከጠላት ሰይጣን ፈተና የሃይማኖት ጥርጥር ወይም ደዌ ያገኘው ሁሉ ወደርሱ ይመጣል ወዲያውኑ ያረጋጋዋል ከደዌውም ይፈውሰዋል። ይህም አባት በምንኲስና ሕግ ስለ መጋደል ስለ አምልኮም ብዙ ድርሳናትንና ተግሣጻትን ደረሰ።

በትምህርቱም እንዲህ አለ የተሰነካከለ ወንድምን ብታይ ስለርሱ ተስፋ አትቁረጥ ልቡን አንቃለት እንጂ ከወደቀበትም እንዲነሣ አጽናንተህ ሸክሙን አቃልለት። አፍህ የተናገረውን ይሠራ ዘንድ ልብህን አስተምረው አለ።

አንድ ወንድም እንዲህ አለው ሥራው መልካም የሆነ ወንድም ያየሁ እንደሆነ ደስ ይለኛል ወደቤቴም አስገብቼ ባለኝ ነገር ደስ አሰኘዋለሁ። ግን ሥራው ብልሹ የሆነ ወንድም ያየሁ እንደሆነ አልፈቅደውም ወደ ቤቴም አላስገባውም። አባ ባይሞንም እንዲህ ብሎ መለሰለት ሥራው በጎ ለሆነው እንዳረግኸው ለዚህም ሥራው ብልሹ ለሆነው ዕጥፍ አድርገህ በመሥራት ደስ አሰኘው ለታመመ መድኃኒት ያደርጉለት ዘንድ ይገባልና።

ከዚህም በኋላ ለዚያ ከርሱ ጋር ለሚነጋገር ወንድም እንዲህ ብሎ ነገረው በመነኰሳት ገዳም ስሙ ጢሞቴዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ በኃጢአትም ወድቆ አቤቱ ይቅር በለኝ እያለ የሚጮህና የሚያለቅስ ሆነ። ከሰማይም እንዲህ የሚል ቃል መጣ አንተ ወንድምህን በመከራው ጊዜ ቸለል ያልከው ባትሆን እኔ ባልጣልኩህም ነበር።

ይህ አባት ደግሞ እንዲህ አለ እኛ የወንድማችን በደል ብንሰውር እግዚአብሔርም በደላችንን ይሠውርልናል። ይህም አባት ዕድሜውን በተጋድሎና በትሩፋት ሥራ ከፈጸመ በኋላ ወደ መልካም ዕርግና ደርሶ እግዚአብሔርን አገልግሎ በሰላም አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሊቀ_ጳጳሳት_አባ_ሊባርዮስ_አረፈ

ዳግመኛም በዚችም ቀን የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሊባርዮስ አረፈ። ይህም አባት አርዮሳዊ በሆነ በሁለተኛው ቈስጠንጢኖስ ዘመን ተሾመ። የቈስጠንጢኖስም ወንድሙ ቊንስጣ በሮሜ ነግሦ ነበር።

ሐዋርያዊ አትናቴዎስንና ጳውሎስን ከመንበረ ሢመታቸው በአሳደዳቸው ጊዜ እነርሱም ወደዚህ አባት ሊባርዮስ መጡ። ይረዳቸውም ዘንድ ለመኑት እርሱም ተቀበላቸው ከደብዳቤ ጋርም ወደ ንጉሥ ቊንስጣ ላካቸው ንጉሡም ደብዳቤያቸውን ተቀብሎ በጎ ነገር እንዲያደርግላቸው ወደ መንበረ ሢመታቸውም እንዲመልሳቸው ወደ ወንድሙ ቈስጠንጢኖስ ደብዳቤ ጻፈላቸው።

እርሱም የወንድሙን ደብዳቤ በአነበበ ጊዜ አትናቴዎስን ወደ መንበረ ሢመቱ እስክንድርያ፣ ጳውሎስንም ወደ መንበረ ሢመቱ ቊስጥንጥንያ መለሳቸው።

ከዚህም በኋላ ቊንስጣ ንጉሥ በዓመፀኞች በተገደለ ጊዜ ቈስጠንጢኖስ ወደዚህ አባት ሊባርዮስ መልእክት ላከ ሐዋርያዊ አትናቴዎስን ያሳድደው ዘንድ የአርዮስንም ወገን እንዲቀበላቸው ብዙ ቃል ኪዳናትንም ገባለት እርሱ ግን አልተቀበለውም በምክሩም ከእርሱ አልተስማማም።

ስለዚህም ይህን አባት ሊባርዮስን ሩቅ አገር አጋዘው። ከዚህም በኋላ ወንዱሙ ቈንስጣን የገደለውን ጭፍራ ልኮ ገደለው። ከዚህም በኋላ ቈስጠንጢኖስ ወደ ሮሜ ከተማ ሔደ ስለዚህ አባት ሊባርዮስም የገዳማትና የአድባራት ሊቃውንት ካህናቱም ሁሉ ወደ መንበረ ሢመቱ ይመልሰው ዘንድ ንጉሡን ለመኑት እርሱም ምልጃቸውን ተቀብሎ ወደ መንበረ ሢመቱ መለሰው።

ይህ አባት ወደ መንበሩ በተመለሰ ጊዜ በቀናች ሃይማኖት ይጸኑ ዘንድ ሁልጊዜ መንጋዎቹን ማስተማር ጀመረ ብዙ ድርሳናትንና ተግሣጻትንም ደረሰ የአርዮስ ወገኖችንም እየተቃረናቸው ኖረ ያወግዛቸውና ያሳድዳቸውም ነበር። ከስደት ከተመለሰ በኋላ በሰባት ዓመት በሰላም አረፈ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጳጉሜን_4)
Forwarded from Eyuel
ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ምን ላይ የተሾመ መላእክ ነው?
Anonymous Quiz
23%
የሀይላት አለቀ
20%
የሥልጣናት አለቃ
40%
የመናብርት አለቃ
18%
የአርባብ አለቃ
Forwarded from Eyuel
እግዚአብሔር አምላክ ቅዱስ ሩፋኤልን በስንት የመላእክት ነገድ ሠራዊት ላይ ሾመው?
Anonymous Quiz
29%
በ23 ነገድ ላይ
0%
በ25 ነገድ ላይ
15%
በ13 ነገድ ላይ
56%
በ3 ነገድ ላይ
Forwarded from Eyuel
ተዓምረ ማርያምን የተረጎመና ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልዩ ፍቅር የነበረው አጼ ዘርዓ ያዕቆብ አባቱ ማን ይባላል?
Anonymous Quiz
6%
አጼ ዮሐንስ
47%
አጼ ገብረ መስቀል
13%
አጼ ናኦድ
34%
አጼ ዳዊት
Forwarded from Eyuel
አብርሃምም ከጦርነት ነገሥታትን ድል አድርጎ በተመለሰ ጊዜ ኅብስትንና ወይንን አቀረበለት አብርሃምም ከገንዘቡ ሁሉ ከዐሥር አንድ ሰጠው እርሱ ካህንም ንጉሥም ሁኖ ተሹሟልና ይህ ቅዱስ ማን ይባላል?
Anonymous Quiz
0%
ቅዱስ አዳም አባታችን
4%
ቅዱስ ኖኅ
93%
ቅዱስ መልከጼዴቅ
4%
ቅዱስ ይስሐቅ
2024/09/21 23:04:16
Back to Top
HTML Embed Code: