Telegram Web Link
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ሐምሌ_30_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ቆሮንቶስ 2
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ እኔም፥ ወንድሞች ሆይ፥ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ በቃልና በጥበብ ብልጫ ለእግዚአብሔር ምስክርነቴን ለእናንተ እየነገርሁ አልመጣሁም።
² በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበርና።
³ እኔም በድካምና በፍርሃት በብዙ መንቀጥቀጥም በእናንተ ዘንድ ነበርሁ፤
⁴-⁵ እምነታችሁም በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን፥ ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበረ እንጂ፥ በሚያባብል በጥበብ ቃል አልነበረም።
⁶ በበሰሉት መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፥ ነገር ግን የዚችን ዓለም ጥበብ አይደለም የሚሻሩትንም የዚችን ዓለም ገዦች ጥበብ አይደለም፤
⁷ ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን፥ ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን።
⁸ ከዚችም ዓለም ገዦች አንዱ እንኳ ይህን ጥበብ አላወቀም፤ አውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ጴጥሮስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ምንም ብታውቁ በእናንተም ዘንድ ባለ እውነት ምንም ብትጸኑ፥ ስለ እነዚህ ዘወትር እንዳሳስባችሁ ቸል አልልም።
¹³ ሁልጊዜም በዚህ ማደሪያ ሳለሁ በማሳሰቤ ላነቃችሁ የሚገባኝ ይመስለኛል።
¹⁴ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳመለከተኝ ከዚህ ማደሪያዬ መለየቴ ፈጥኖ እንዲሆን አውቃለሁና።
¹⁵ ከመውጣቴም በኋላ እነዚህን ነገሮች እንድታስቡ በየጊዜው ትችሉ ዘንድ እተጋለሁ።
¹⁶ የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችሁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ጴጥሮስና ዮሐንስም በጸሎት ጊዜ በዘጠኝ ሰዓት ወደ መቅደስ ይወጡ ነበር።
² ወደ መቅደስም ከሚገቡት ምጽዋት ይለምን ዘንድ፥ ሰዎች ተሸክመው መልካም በሚሉአት በመቅደስ ደጅ በየቀኑ ያስቀምጡት የነበሩ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ አንካሳ የሆነ አንድ ሰው ነበረ።
³ እርሱም ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ መቅደስ ሊገቡ እንዳላቸው ባየ ጊዜ፥ ምጽዋትን ለመናቸው።
⁴ ጴጥሮስም ከዮሐንስ ጋር ትኵር ብሎ ወደ እርሱ ተመልክቶ፦ ወደ እኛ ተመልከት አለው።
⁵ እርሱም አንድ ነገር ከእነርሱ እንዲቀበል ሲጠብቅ ወደ እነርሱ ተመለከተ።
⁶ ጴጥሮስ ግን፦ ብርና ወርቅ የለኝም፤ ይህን ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ አለው።
⁷ በቀኝ እጁም ይዞ አስነሣው፤ በዚያን ጊዜም እግሩና ቍርጭምጭምቱ ጸና፥
⁸ ወደ ላይ ዘሎም ቆመ፥ ይመላለስም ጀመር፤ እየተመላለሰም እየዘለለም እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ከእነርሱ ጋር ወደ መቅደስ ገባ።
⁹ ሕዝቡም ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ሲመላለስ አዩት፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሐምሌ_30_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"እምውኂዝ እምሰጠት ነፍስነ። እምሰጠት ነፍስነ እማየ ሀከክ። ይትባረክ እግዚአብሔር አምላክነ ዘኢያግብአነ ውስተ መሥገርተ ማዕገቶሙ"። መዝ 123፥4-5።
"በዚያን ጊዜ ውኃ ባሰጠመን ነበር፥ በነፍሳችንም ላይ ፈሳሽ ባለፈ ነበር፤ በዚያን ጊዜ የጐርፍ ውኃ በነፍሳችን ላይ ባለፈ ነበር።
መዝ 123፥4-5።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሐምሌ_30_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማርቆስ 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³⁵ በዚያም ቀን በመሸ ጊዜ፦ ወደ ማዶ እንሻገር አላቸው።
³⁶ ሕዝቡንም ትተው በታንኳ እንዲያው ወሰዱት፥ ሌሎች ታንኳዎችም ከእርሱ ጋር ነበሩ።
³⁷ ብርቱ ዐውሎ ነፋስም ተነሣና ውኃ በታንኳይቱ እስኪሞላ ድረስ ማዕበሉ በታንኳይቱ ይገባ ነበር።
³⁸ እርሱም በስተኋላዋ ትራስ ተንተርሶ ተኝቶ ነበር፤ አንቅተውም፦ መምህር ሆይ፥ ስንጠፋ አይገድህምን? አሉት።
³⁹ ነቅቶም ነፋሱን ገሠጸው ባሕሩንም፦ ዝም በል፥ ፀጥ በል አለው። ነፋሱም ተወ ታላቅ ፀጥታም ሆነ።
⁴⁰ እንዲህ የምትፈሩ ስለ ምን ነው? እንዴትስ እምነት የላችሁም? አላቸው።
⁴¹ እጅግም ፈሩና፦ እንግዲህ ነፋስም ባሕርም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው? ተባባሉ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ የቅዱሳን #ሐዋርያት_ቅዳሴ ነው። መልካም በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
መንፈሳዊ የሆነ በጎ ተግባርን ሁሉ የጠበቀች ትሩፋትንና መጋደልንም በጾምና በጸሎት የፈጸመች አርፋ በደብረ ሊባኖስም የተቀበረችው የንጉሥ አጼ ናኦድ ሚስት ማን ትባላለች?
Anonymous Quiz
27%
ቅድስት መስቀለ ክብራ
16%
ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
13%
ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ
44%
ቅድስት ማርያም ክብራ
ለሐዋርያው እንድርያስ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦ____ ከእሥር ቤት ታወጣው ዘንድ ሰውን ወደሚበሉ ሰዎች አገር ሒድ የዚያች አገር ሰዎች ከሦስት ቀን በኃላ ሊበሉት ያወጡታልና ብሎ የነገረው ስለ ማን ነው?
Anonymous Quiz
22%
ስለ ሐዋርያው በርተለሜዎስ
49%
ስለ ሐዋርያው ማትያስ
11%
ስለ ሐዋርያው ዮሐንስ
18%
ስለ ሐዋርያው ታዴዎስ
ክብርንና ብልጽግናን ንቆ የተወ ራሱንና ሁሉንም ቤተሰቡ ስለ ጽድቅ የሸጠ የሽያጩንም ዋጋ ለነዳያንና ለተቸገሩት የሰጠው ቅዱስ ማን ይባላል?
Anonymous Quiz
43%
ቅዱስ መርቆሬዎስ
23%
ቅዱስ ጳውሎስ
15%
ቅዱስ ኤፍሬም
19%
ቅዱስ ጢሞቴዎስ
በሌላ ስሙ "እሥራልዩ"("የእሥራኤል ረዳት") እየተባለ የሚጠራው ሊቀ መላእክ ማን ነው?
Anonymous Quiz
18%
ቅዱስ ሱርያል
6%
ቅዱስ ገብርኤል
73%
ቅዱስ ሚካኤል
3%
ቅዱስ ሰዳካኤል
ሊቀ መላእክ ቅዱስ ሱርያል የማን አለቃ(መሪ) ነው?
Anonymous Quiz
25%
የሀይላት
31%
የአርባብ
24%
የሥልጣናት
20%
የሊቃናት
#ነሐሴ_1

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የተባረከው #የነሐሴ_ወር_የቀኑ_ሰዓት_ዐሥራ_ሦስት ነው ከዚህም በኋላ ይጎድላል።
ነሐሴ አንድ በዚህች ቀን አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም እናቷ #የቅድስት_ሐና መታሰቢያዋ ነው፣ የዮስጦስ ልጅ #ቅዱስ_አቦሊ በሰማዕትነት አረፈ፣ የከበሩ ሰዎች #ቅዱሳን_የዮሴፍና_የኒቆዲሞስ መታሰቢያቸው ነው፣ በተጨማሪም በዚህች ቀን የፋኑኤል ልጅ የነብይት #ሐና፣ የንግሥት ሶፍያ ልጆች የቅዱሳት ደናግል መታሰቢያቸው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ሐና (የእመ ብርሃን እናት)

ነሐሴ አንድ በዚህች ቀን አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም እናቷ የሐና መታሰቢያዋ ነው። ይህችም ቅድስት ከኢየሩሳሌም አገር ከሌዊ ነገድ ከካህኑ አሮን ትውልድ የሌዊ የሜልኪ ልጅ ለሆነ ለማጣት (ጣ ጠብቆ ይነበብ) ልጁ ናት። ለማጣትም ሦስት ሴቶች ልጆች አሉት የታላቂቱም ስሟ ማርያም ናት ሁለተኛዋም ስሟ ሶፍያ ሦስተኛዪቱም ስሟ ሐና ናት ታላቂቱ ማርያምም ለባል ተድራ አዋላጅ የሆነች ሰሎሜን ወለደቻት እርሷም #መድኃኒታችንን ከወለደችበት ጊዜ ጀምሮ በስደቷም ወራት ከአረጋዊ ዮሴፍ ጋር እመቤታችንን #ድንግል_ማርያምን ያገለገለቻት ናት።

ሶፍያም ለባል ተድራ ለመጥመቁ ዮሐንስ እናቱ የሆነች ቅድስት ኤልሳቤጥን ወለደቻት። ይችንም ቅድስት ሐናን ከይሁዳ ነገድ ለሆነ ጻድቅ ስሙ ኢያቄም ለሚባል አጋቧት። (ሰሎሜና ኤልሳቤጥ ለቅድስት ሐና የእኅትማማች ልጆች ናቸው።)

ቅድስት ሐና ኢያቄምን አግብታ ስትኖር የቴክታና እና የጴጥሪቃ ምክነት በዘር ወርዶ መክና በመኖሯ የዐይኗ ማረፊያ የልቧ ተስፋ የሚሆን ልጅ እንዲስጣት ፈጣሪዋን ስትማጸን ኖራለች።

የነገሩትን የማይረሳ የለመኑትን የማይነሳ አምላክ ልመናዋን ሰምቶ ሐምሌ ፴ ራእይ አየች። ራእዩንም ከባሏ ከኢያቄም ጋር ተወያየተው ምንጣፍ ለይተው ሱባኤ ገቡ።

ከአንድ ሱባኤ በኋላ ነሐሴ ፯ ቀን #ጌታ ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ እንደሚወልዱ አበሠራቸው። ከዚያም እመቤታችን ጸንሳ ልዩ ልዩ ተአምራትን አድርጋለች። ሳምናስን ከሞት አስነስታለች። በርሴባን ዐይኗን አብርታለች። ከዚያም በአይሁድ ተንኮልና አሳዳጅነት ወደ ሊባኖስ ተራራ ተሰዳ #ድንግል_ማርያምን ወልዳለች። በመውለዷም ሕዳሴ አካል አግኝታ ከኖረች በኋላ ዐርፋለች።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሐናና ኢያቄም ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ይደርብን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አቦሊ

በዚህችም ቀን የዮስጦስ ልጅ ቅዱስ አቦሊ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ቅዱስ አቦሊ ከመንግሥት ልጆች ውስጥ ነበር ዐላውያንን ወግቶ በተመለሰ ጊዜ ዲዮቅልጥያኖስን ክብር ይግባውና #ክርስቶስን ክዶ አገኘው።

ያም አቦሊና አባቱ ዮስጦስ ሌሎችም የመንግሥት ልጆች ሁሉ ከሀዲ ዲዮቅልጥያኖስን ሊያጠፉትና መንግሥትን ከእርሱ ሊወስዱ ችሎታ ሲኖራቸው የማታልፍ ሰማያዊት መንግሥትን አሰቡ።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ አቦሊ ወደ ንጉሡ ቀርቦ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ታመነ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስም አብዝቶ አባበለው። እንዲሁም አባቱ ዮስጦስንና የከበረች እናቱ ታውክልያን አባበላቸው እነርሱ ግን አልሰሙትም ልባቸው በ #መድኅን_ክርስቶስ ፍቅር ተነድፏልና። ንጉሡም እነርሱን በዚያ ማሠቃየትን ፈራ ስለዚህም ከመልእክት ደብዳቤ ጋር ወደግብጽ ስሙ ኄርሜኔዎስ ወደሚባል የእስክንድርያ ገዥ ላካቸው በመልእክቱም እንዲህ አለው ዮስጦስና ሚስቱ ታውክልያ ልጃቸው አቦሊም ወደአንተ በሚደርሱ ጊዜ አባብላቸው አለዚያም እየአንዳንዳቸውን ለያያቸው።

በዚያችም ሌሊት ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ለዮስጦስና ለሚስቱ ታውክልያ ለልጃቸው አቦሊም ተገልጦላቸው አጽናናቸው ከእነርሱም የሚሆነውን ነገራቸው የጸና ቃል ኪዳንም ሰጣቸው።

ወደ መኰንኑ ኄርሜኔዎስም በደረሱ ጊዜ ስለእነርሱ እጅግ አደነቀ እነርሱ መንግሥታቸውን ትተዋልና ክፋ ነገርንም ሊናገራቸው አልደፈረም ከምክራቸው ይመለሱ ዘንድ በለሰለሰ ቃል ሸነገላቸው እንጂ ነገር ግን አልሰሙትም።

ከዚህም በኋላ በእነርሱ ላይ ተቆጥቶ ለእየብቻቸው ለያያቸው ቅዱስ ዮስጦስን ወደ እንዴናው ከተማ ሚስቱን ታውክሊያን ፃ ወደ ሚባል አገር ልጃቸው አቦሊንም ብስጣ ወደ ሚባል አገር ሰደዳቸው ለእያንዳንዳቸውም የሚአገለግላቸው አንዳንድ አገልጋይ ሰጣቸው። ቅዱስ አቦሊም ወደ ሀገር ብስጣ በደረሰ ጊዜ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በመኰንኑ ፊት ታመነ። መኰንኑም ጽኑ ሥቃይን በእሳት ቃጠሎና በመንኰራኵር አሰቃየው ሕዋሳቱንም ቆራርጦ ለአንበሶች ጣለው ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም ከሥቃዩ ሁሉ አድኖ ያለ ጉዳት በጤና አነሣው።

ብዙዎች ሰዎችም ስቃዩንና ዳግመኛ መዳኑን በአዩ ጊዜ እጅግ አደነቁ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_በአምላካችን_በመድኃኒታችን_በኢየሱስ_ክርስቶስም አምነው ሰማዕታት ሆኑ።

መኰንኑ ግን እጅግ ተቆጥቶ የቅዱስ አቦሊን ቆዳውን እንዲገፍፉትና ጨውና መጻጻን በማቅ አምጥጠው ቍስሉን እንዲያሹ አዘዘ ይህንንም ሁሉ አደረጉበት።

ከዚህም በኋላ ቆዳውን አሸክመው በከተማ ውስጥ ሁሉ አዞሩት ወደ #ጌታችንም እንዲህ ብሎ ጸለየ የሕያው #እግዚአብሔር_ልጅ_ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሆይ ርዳኝ ከዚህ ሥቃይም አድነኝ። ያን ጊዜም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ወደርሱ መጣ ሁለመናውንም ዳስሶ አዳነው።

መኰንኑም በእርሱ ላይ የሚያደርገውን እስኪያስብ ከእሥር ቤት እንዲጨምሩት አዘዘ። ቅዱስ አቦሊም ቁሞ ጸለየ ያን ጊዜም ክብር ይግባውና #ጌታችን ተገለጠለትና የመረጥኩህ አቦሊ ሰላም ለአንተ ይሁን እኔም ከአንተ ጋር እኖራለሁ አለው #ጌታችንንም በአየው ጊዜ እጅግ ደስ አለው ክብር ይግባውና ለ #ጌታችንም ሰገደለት።

ስሙ አብስኪሮን የሚባል አንድ ባለ ጸጋ ነበር የቤቱንም ግድግዳ አፍርሰው አዲስ ይሠሩለት ዘንድ ሠራተኞችን አመጣ ሥራቸውንም እስኪጨርሱ ከዚያ ይቆሙ ዘንድ ሁለቱን ልጆቹን አዘዛቸው።

ከግርግዳውም ላይ በወጡ ጊዜ ግርግዳው ተደርምሶ ዐሥራ ስድስት ሰዎችና ሁለቱ ልጆቹ ሞቱ። ባለጸጋውም የሆነውን በአየ ጊዜ ልብሱን ቀደደ ጩኾም አለቀሰ ወደ ቅዱስ አቦሊም ሒዶ ከእግሩ በታች ሰገደለት እንዲህም አለው ራራልኝ ሁለቱ ልጆቼ ሙተዋልና ከእነርሱም ጋራ ዐሥራ ስድስት ሰዎች ሞቱ። ከሞትም ብታሥነሣቸው እኔ በአምላክህ አምናለሁ።

ያን ጊዜም ቅዱስ አቦሊ ተነሣ እንዲህ ብሎ ጸለየ ስለ ቅዱስ ስምህ መከራን እቀበል ዘንድ የመረጥከኝ #ጌታዬ_አምላኬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሆይ በእኒህ በሞቱ ሰዎች ላይ ኃይልህን ግለጥ። እኒህ ሰዎች ሁሉ እንዲአምኑ ያለ አንተም ሌላ አምላክ እንደሌለ ያውቁ ዘንድ ከሞት አንሣቸው። ላንተም ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።

ከዚህም በኋላ የተገፈፈ ቆዳውን ወስዶ በሞቱት ሰዎች ላይም ዘረጋውና በሕያው እግዚአብሔር ልጅ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከሞት ተነሡ አለ። ወዲያውም ሁሉም ድነው ተነሡ በዚያ ያሉ ሕዝብም ይህን ድንቅ ሥራ በአዩ ጊዜ የክርስቲያን አምላክ የቅዱስ አቦሊም አምላክ #ኢየሱስ_ክርስቶስ አንድ ነው እኛም እናምንበታለን ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለምና እያሉ ጮኹ።

ባለ ጸጋው አብስኪሮንም መጥቶ ለቅዱስ አቦሊ እንዲህ እያለ ሰገደ #ኢየሱስ_ክርስቶስ ክብር ይግባውና እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ዛሬ አወቅሁ እኔም አምንበታለሁ። ከቤተሰቦቹም ሁሉ ጋር አመኑ መኰንኑም አፈረ።
ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ለቅዱስ አቦሊ ተገለጠለት እንዲህም ብሎ ቃል ኪዳን ሰጠው። በመከራ ውስጥ ያለ ሰው በስምህ ርዳታ ቢለምን እኔ እሰማዋለሁ ልመናውን ፍላጎቱንም እፈጽምለታለሁ። በስምህ ቤተ ክርስቲያን ለሠራም እኔ በሰማያት ብርሃናዊ ማደሪያ ቤት እሠራለታለሁ የገድልህን መጽሐፍ የሚጽፈውን ወይም የሚያነበውን ወይም የሚሰማውን እኔ በኪሩቤል ክንፎች ላይ ስሙን እጽፉለሁ በአብርሃም በይስሐቅና በያዕቆብ እቅፍም አሳርፈዋለሁ ተድላ ደስታ ካለባት ከገነት ፍሬዎችም እመግበዋለሁ።

ብዙ ኃጢአትን ሠርቶ የበደለውንም በስምህ ወደኔ እየለመነ ንስሐ ቢገባ በደሉን ሁሉ ይቅር እለዋለሁ። ከጻድቃንም ጋርም እቈጥረዋለሁ ሰላሜም ካንተ ጋራ ይሁን ይህንንም ብሎ በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ።

መኰንኑም ከማሠቃየቱ የተነሣ በደከመ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡት ዘንድ አዘዘ የከበረች ራሱን ቆረጡት የሕይወት አክሊልንም ተቀበለ። ሥጋውም ከምስር ከተማ ውጭ ሕንቅ በሚባል ገዳም ይኖራል ከእርሱም ብዙዎች ድንቆችና ተአምራት ተገለጡ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ መስተጋድል ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አበው_ሐዋርያት_ዮሴፍና_ኒቆዲሞስ

በዚህችም ቀን ለአምላካዊት ምሥጢር አገልጋዮች ሊሆኑ የተገባቸው የከበሩ ሰዎች የዮሴፍና የኒቆዲሞስ መታሰቢያቸውን እናደርግ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አባቶች አዘዙ።

በፈቃዱ መከራ ተቀብሎ ስለ ደኅንነታችን በሞተ ጊዜ የደኅንነታችንንም ምሥጢር በፈጸመ ጊዜ የሕያው #እግዚአብሔርን ልጅ የ #መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስን ሥጋ እነርሱ ከ #መስቀል ላይ አውርደዋልና። የአይሁድም መገርመም ከጲላጦስ ዘንድ የ #መድኃኒታችንን ሥጋ እስከ ለመኑ ድረስ አላስፈራቸውም።

ጲላጦስም በፈቀደላቸው ጊዜ የእጆቹንና የእግሮቹን ችንካሮች ነቅለው ከ #መስቀል አውርደው በትክሻቸው ተሸከሙት ሲገንዙትም እንዲህ የሚል ቃል ከበድኑ ሰሙ። #ቅዱስ_እግዚአብሔር #ቅዱስ_ኃያል #ቅዱስ_ሕያው_የማይሞት#ቅድስት_ድንግል_ማርያም የተወለደ አቤቱ ይቅር በለን።

#ቅዱስ_እግዚአብሔር #ቅዱስ_ኃያል #ቅዱስ_ሕያው_የማይሞት በዮርዳኖስ የተጠመቀ በእንጨት #መስቀልም የተሰቀለ አቤቱ ይቅር በለን። #ቅዱስ_እግዚአብሔር #ቅዱስ_ኃያል #ቅዱስ_ሕያው_የማይሞት በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ የተነሣ በክብር ወደ ሰማያት ያረገ በአባቱም ቀኝ የተቀመጠ ዳግመኛም በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ የሚመጣ አቤቱ ይቅር በለን።

#አብ ምስጋና ይገባል ለ #ወልድ ምስጋና ይገባል ለ #መንፈስ_ቅዱስ ምስጋና ይገባል ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን አሜን ይሁን ይሁን። ልዩ ሦስት ሕያው #እግዚአብሔር ይቅር በለን።

ይህንንም በሰሙ ጊዜ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሃይማኖታቸው ጸናች። ዮሴፍም በፍታ ኒቆዲሞስም ሽቶዎችን አምጥተው #ጌታችንን ገነዙት በአዲስ መቃብር ውስጥም ቀበሩት።

ይህ ዮሴፍም ለሰማዕታት መጀመሪያ ለእስጢፋኖስ ዘመድ ለሆነው ለቀለዮጳ ወንድሙ ለኒቆዲሞስ ዘመዱ ነው ኒቆዲሞስም የአይሁድ አለቃ ፈሪሳዊ ነበር እርሱም ወደ #ጌታ_ኢየሱስ አስቀድሞ በሌሊት የሔደና ከ #እግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣ ያመነ ነበር። #ጌታችንም ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው ወደ #እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንደማይችል የነገረው ነው።

ይህ ኒቆዲሞስም የ #ጌታችንን ቃል በሚአቃልሉ ጊዜ አይሁድን ይገሥጻቸው ነበር። ከተነሣ በኋላም በኢማሁስ መንገድ ሲሔድ #ጌታችን_ኢየሱስ የተገናኛቸው እሊህ ኒቆዲሞስና ቀለዮጳ ናቸው። እነርሱም ሳያውቁት በእርሱ ላይ የሆነውን ሁሉ ነገሩት። እርሱም ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤው ነቢያት ትንቢት እንደ ተናገሩ አስተማራቸው።

ከዘህም በኋላ እርሱ መሆኑን ባወቁት ጊዜ ተሠወራቸው እነርሱም ተመልሰው ለደቀ መዛሙርቱ ነገሩ። ክብር ይግባውና የ #ጌታችንን ሥጋ ስለ ቀበረ ሊገድሉት ፈልገው አይሁድ ዮሴፍን በወህኒ ቤት አሠሩት። የወህኒ ቤቱም በር በሊቃነ ካህናቱና በጲላጦስ ማኅተም ተቆልፎ ሳለ #ጌታችን በኪሩቤል ሠረገላ ተቀምጦ ዮሴፍ ወደ አለበት ገባ ከእርሱ ጋርም እልፍ አእላፋት መላእክት ነበሩ። ሱራፌልም በዙሪያው ቁመው በፊቱ ያጥናሉ በቀኝ በኩል ተሰቅሎ የነበረ ወንበዴውም ብሩህ ልብስ ለብሶ በቀኝ ቁሞአል ባለሟልነትን በልዑል ፊት አግኝቶአልና ስለ ኃጢአተኞች ይማልድ ነበር።

የወህኒ ቤት ጠባቂዎችም በአዩ ጊዜ ደነገጡ ፈርተውም መንቀጥቀጥ ያዛቸው #ጌታችንም ዮሴፍን ጠርቶ እንዲህ አለው ከአይሁድ ግርማ የተነሣ አትፍራ ከማሠሪያህ ልፈታሕ እኔ መጣሁ አንተ መከራዬን የተሳተፍከኝ የናዝሬቱ #ኢየሱስ እኔ ነኝ እኔ #ጌታህና የዓለሙ ሁሉ #ጌታ እንደሆንሁ ፈጽመህ ታውቅ ዘንድ የተቸነከሩ እጆቼንና እግሮቼን የተወጋ ጐኔንም እይ።

ከዚያም ዮሴፍን ነጥቆ ወደ አገሩ አርማትያስ ወሰደው። የወህኒ ቤቱ ጠባቂዎችም ሔደው #ጌታችን ያደረገውን ሁሉ ዮሴፍንም ይዞ ከእርሱ ጋር እንደወሰደው ለካህናት አለቆች ነገሩ። የካህናት አለቆችም በሔዱ ጊዜ የወህኒ ቤቱ በር ተቆልፎ አገኙ እሽጉም አልተለወጠም ነበር። እሊህ ቅዱሳንም ከሐዋርያት ጋር ወንጌልን እየሰበኩ ኖሩ ብዙ መከራም አገኛቸው። ከዚህም በኋላ በሰላም አረፉ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ሐና_ነቢዪት

በዚህም ዕለት ከአሴር ወገን የሆነች የፋኑኤል ልጅ ነቢዪት ሐና አረፈች፡፡ የእርሷም ዘመኗ አልፎ ነበር በድንግልና ከኖረች በኋላ ከባሏ ጋር ሰባት ዓመት ኖረች። ሰማንያ አራት ዓመት ፈት ሁና ኖረች በጾምና በጸሎትም እያገለገለች ቀንም ሌትም ከምኲራብ አትወጣም ነበር።

ጌታችን ኢየሱስን ከተወለደ በኋላ በአርባ ቀን ወደ ቤተ መቅደስ በአስገቡት ጊዜ በዚያን ሰዓት ተነሥታ አመነች እግዚአብሔርንም አመሰገነችው። የኢየሩሳሌምን ድኅነት ተስፋ ለሚያደርጉ ሁሉ ስለርሱ ነገረች። ከዚህም በኋላ በሰላም አረፈች።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_1)
ጾመ ፍልሰታ/ጾመ ማርያም/ 
  
   🌺ፍልሰታ ማለት ፈለሰ፤ ተሰደደ፤ ተጓዘ፤ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሄደ ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ቃል ሲሆን ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ «ፈለሰት ማርያም እምዘይበሊ ኀበኢይበሊ፤ ድንግል ማርያም ከሚያልፈው ዓለም ወደማያልፈው ዓለም፣ ከምድር ሕይወት ወደ ሰማያዊ ሕይወት፣ ተሻገረች» በማለት ፍልሰታ የሚለውን ቃል ትርጓሜ አመሥጥሮ ገልጾታል፡፡

  🌺ጾመ ፍልሰታ ከእመቤታችን ድንግል ማርያም የዕረፍት ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እመቤታችን በዚህ ዓለም ፷፬ ዓመታትን በሕይወተ ሥጋ ከቆየች በኋላ ጌታችን የእናቱን ተድላ ነፍሷን እንጂ ተድላ ሥጋዋን አይወድምና ጥር ፳፩ ቀን ፵፱ ዓመተ ምሕርት አረፈች፡፡ ዕረፍቷም እንደሌላው ሰው በሕማምና በድካም አይደለም፡፡ በገነት ዕፀዋት መዓዛ ተመስጣ ቅድስት ነፍሷ ከሥጋዋ ተለይታለች፡፡

  🌺ታሪኩ በነገረ ማርያም እንደተጻፈው ሐዋርያት እመቤታችንን በአጎበር አድርገው አክብረው ወደጌቴሴማኒ መካነ መቃብር ይዘዋት ሲሄዱ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉም ነበርና ቀድሞ ልጇን ተነሣ ዐረገ እያሉ ሲያውኩ ኖረዋል፤  እርሷን ደግሞ ተነሣች ዐረገች እያሉ ሊያውኩን ነውና «ኑ የማርያምን ሥጋ በእሳት እናቃጥለው» ብለው በምቀኝነት ተነሱ፡፡ ከመካከላቸው አንድ ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ ከሐዋርያት እጅ ለመንጠቅ ዘሎ ሄዶ የአልጋውን ሸንኮር ሲይዝ የታዘዘ መልአክ በረቂቅ ሰይፉ እጆቹን ቆረጠው፡፡ እጆቹም በአልጋው ሸንኮር ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ፡፡ የምሕረት እናት የሆነችው ድንግል ማርያም ቅዱስ ጴጥሮስ ጸልዮ እጆቹን እንዲመልስለት ነግራው እንደነበረ አድርጎለታል፡፡

  🌺የእመቤታችን ሥጋዋን መላእክት ከዮሐንስ ወንጌላዊ ጋር በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር ወስደው አስቀምጠውታል፡፡ ሥጋዋ ያለበትን ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ አይቶ እነርሱ ባለማየታቸው እመቤታችን ባረፈች በ፮ኛው ወር ከነሐሴ ፩ ቀን እስከ ፲፬ ቀን ድረስ ከጾሙ በኋላ በ፲፬ኛው ቀን ሥጋዋን እንደገና ከጌታ ተቀብለው በጌቴሴማኒ ባለው መቃብር ቀብረውታል፡፡

  🌺ከዚህ በኋላ እንደ ልጇ በ፫ኛው ቀን ተነሥታ መላእክት እየዘመሩላት ወደሰማያት ስታርግ፤ ሐዋርያው ቶማስ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለሰ ዕርገቷን በማየቱ መላእክት «እመቤትህ እርሷ ናት፤ስገድላት» አሉት፤ እርሱም «ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ ይላል፤ከደመናው ሊወድቅ ወደደ» ምክንያቱም ቀድሞ የልጇን ትንሣኤ፤ ዛሬ ደግሞ የእርሷን ትንሣኤ ለማየት ብሎ ነው፡፡ እመቤታችንም «ትንሣኤየን ያየህ አንተ ነህ ሌሎቹ አላዩም» ብላ ሐዋርያት ገንዘው የቀበሩበትን የሐር ግምጃ ሰጥታ አጽናንታ ሰደደችው፡፡

  🌺ቅዱስ ቶማስ ኢየሩሳሌም ሲደርስ የእመቤታችን ነገር እንዴት ሆነ ብሎ ጠየቃቸው፤እነርሱም አግኝተው እንደቀበሯት ነገሩት፤ እርሱም ያየውን ምሥጢር በልቡ ይዞ «ሞት በጥር፤ በነሐሴ መቃብር፤ ለሰሚውም አያምር፤ይህ እንዴት ይሆናል?»፤ ቢላቸው ቅዱስ ጴጥሮስ «ድሮም አንተ ተጠራጣሪ ነህ፤ማን ያርዳ የቀበረ፤ ማን ይናገር የነበረ እንዲሉ፤ ገንዘን የቀበረን እኛ እያለን እንዴት ትጠራጠራለህ» ብለው ወደ መቃብሯ ሄደው መቃብሯን ቢከፍቱት ባዶ ሆኖ አገኙት፡፡ በዚህ ተደናግጠው ተያዩ፤ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ቶማስ «አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችን ተነሣች፤ዐረገች፤ ይኸው ምልክቱ» ብሎ ገንዘው የቀበሩበትን ሰበን አሳያቸው፤ እነርሱም አምነው ሰበኗን ለበረከት ተካፈሉት፡፡

  🌺በዓመቱ ነሐሴ ፩ ቀን ሐዋርያት በመንፈሰዊ ቅናት ተነሳስተው «ቶማስ ትንሣኤዋን አይቶ እኛ ሳናይ እንዴት ይቀርብናል» በማለት ነሐሴ ፩ ቀን ሱባኤ ጀምረው በ፲፮ኛው ቀን የሐዋርያትን ሱባኤ ተቀብሎ እመቤታችንን መንበር ጴጥሮስን ተራዳኢ፣ ካህን እስጢፋኖስን ሠራዔ ዲያቆን አድርጉ ቀድሶ አቁርቧቸዋል፡፡ ከዚያ ጊዜ በኋላም ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፭ ቀን  ጾመ ፍልሰታ ተብሎ ሁሉም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ይጾመዋል፡፡

💛የጾሙ እና የትንሣኤዋ በረከት ተካፋይ ያድረገን፤ አሜን💛
#ነሐሴ_2


አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሁለት በዚች ቀን መኑፍ ከሚባል አገር #ቅድስት_አትናስያ አረፈች፣ ከነገሥታት ወገን የሆነች #ቅድስት_ኢዮጰራቅስያ አረፈች፣ በተጨማሪ በዚች ቀን #ዲያቆናዊት_ኢዮኤልያና ዕረፍት፣ #ሰማዕቱ_ደሚናና ሰማዕታት የሆኑ ወንድሞቹ መታሰቢያቸው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_አትናስያ_ቡርክት

ነሐሴ ሁለት በዚች ቀን መኑፍ ከሚባል አገር ቅድስት አትናስያ አረፈች።

የዚችም ቅድስት ወላጆቿ ባለጸጎች ነበሩ እነርሱም በሞቱ ጊዜ ቤቷን ለእንግዳ ማደሪያ ታደርግ ዘንድ በጎ ኃሳብ አሰበች ወደርሷም የሚመጡትን እንግዶች ሁሉ ትቀበላቸው ነበር። በገዳም ለሚኖሩ መነኰሳትም የሚያስፈልጓቸውን ትሰጣቸው ነበር ስለ በጎ ሥራዋም ይወዷት ነበር።

ከዚህም በኋላ ግብራቸው የከፋ ክፉዎች ሰዎች ወደርሷ ተሰብስበው ኃሳቧን ወደ ኃጢአት ሥራ መለሱትና ኃጢአትን አብዝታ ትሠራ ጀመር። በአስቄጥስ ገዳም በሚኖሩ አረጋውያን ቅዱሳን ዘንድም ወሬዋ ተሰማ ስለእርሷም እጅግ አዘኑ አባ ዮሐንስ ሐጺርንም ጠርተው ስለርሷ የሆነውን ነገሩት አስቀድማም ከእነርሱ ጋራ በጎ ስለ ሠራች ወደ እርስዋ ይሔድ ዘንድ ነፍስዋንም ለማዳን ይወድ ዘንድ ለመኑት።

እርሱም ትእዛዛቸውን ተቀበለ በጸሎታቸውም እንዲረዱት ለመናቸው ያን ጊዜም አባ ዮሐንስ ሐጺር ተነሥቶ ሔደ አትናስያ ወዳለችበት ቦታ ደረሰ ለበረኛዋም ለእመቤትሽ ስለእኔ ንገሪ አላት። በነገረቻትም ጊዜ ለረከሰ ሥራ እንደሚፈልጓት ሰዎች ሁሉ የመጣ መሰላትና አጊጣ በዐልጋዋ ላይ ሁና ጠራችው። ወደርሷም ገባ እርሱም እንዲህ እያለ ይዘምር ነበር በሞት ጥላ ውስጥ ብሔድም እንኳ ክፉን አልፈራውም አንተ ከእኔ ጋራ ነህና።

ከእርሷ ጋራም አስቀመጠችው ያን ጊዜም ራሱን ዘንበል አድርጎ አለቀሰ ለምን ታለቅሳለህ አለችው እርሱም ሰይጣናትን በላይሽ ሲጫወቱ አየኋቸው ክብር ይግባውና #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስን ለምን አሳዘንሺው የቀድሞ በጎ ሥራሽን ትተሽ ወደ ጥፋት ሥራ ተመልሰሻልና አላት።

ቃሉንም ሰምታ ደነገጠችና ተንቀጠቀጠች ምን ይሻለኛል አለችው ንስሐ ግቢ አላት እርሷም #እግዚአብሔር ይቀበለኛልን አለችው እርሱም አዎን አላት እርሷም ወደምትሔድበት ከአንተ ጋራ ውሰደኝ አለችው እርሱም ነዪ ተከተይኝ አላት።

ያን ጊዜም ፈጥና ተነሥታ በኋላው ተከተለችው ከገንዘቧም ምንም ምን አልያዘችም። በመሸም ጊዜ ለማደር ወደ ጫካ ውስጥ ገቡ በዚያም ለእርስዋ ቦታ አዘጋጅቶ እስኪነጋ በዚህ አረፍ ብለሽ ተኚ እኔም ወደዚያ እሆናለሁ አላት። ይህንንም ብሎ ከእርሷ ጥቂት ተገልሎ እየጸለየ ብቻውን ተቀመጠ።

በሌሊቱ እኩሌታም ሊጸልይ ተነሣ ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ የብርሃን ምሰሶ አየ የ #እግዚአብሔርም መላእክት የከበረች ነፍስን ተሸክመው ሲወጡ አይቶ አደነቀ። በነጋም ጊዜ ወደ ርሷ ሔደ ሙታም አገኛት እጅግም አዘነ ስለ ርሷም ያስረዳው ዘንድ እየሰገደ ወደ #እግዚአብሔር ለመነ።

ወደርሱም እንዲህ የሚል ቃል መጣ ከቤቷ በወጣች ጊዜ #እግዚአብሔር ንስሓዋን ተቀብሎ ኃጢአትሽ ተሠረየልሽ ብሎአታል። ከዚህም በኋላ ሒዶ ለአረጋውያን የሆነውን ሁሉ ነገራቸው እነርሱም እርሱ እንዳያት ማየታቸውን ነገሩት የኃጢአተኛን ወደ ንስሐ መመለሱን እንጂ ሞቱን የማይሻ #እግዚአብሔርን አመሰገኑት።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቷ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ኢዮዸራቅስያ_ድንግል

በዚህችም ቀን ከነገሥታት ወገን የሆነች ቅድስት ኢዮጰራቅስያ አረፈች። የእርስዋም የአባቷ ስም ኢጣጎኖስ ነው የንጉሥም አማካሪ ነበር የእናቷም ስም ኢዮጰራቅስያ ነው እነርሱም ደጎች ነበሩ ጾምና ጸሎትንም ወደ #እግዚአብሔር የሚያቀርቡ ነበሩ። ይችንም ቅድስት በወለዷት ጊዜ በእናቷ ስም ኢዮጰራቅስያ ብለዉ ጠሩዋት።

ከጥቂት ጊዜ በኋላም አባቷ አረፈ ዕድሜዋም ስድስት ዓመት በሆነ ጊዜ እናቷ ወደ ደናግል ገዳም ከእርሷ ጋር ወሰደቻት ይህችም ቅድስት ደናግሉ ሲያገለግሉ አይታ ስለ ምን እንዲህ ደክማችሁ ትሠራላችሁ አለቻቸው እነርሱም ክብር ይግባውና ስለ #ክርስቶስ ነው ብለው መለሱላት ወደ ዲያቆናዊትም ሒዳ ያመነኲሷት ዘንድ ለመነች እነርሱም ለእናቷ ነገሩዋት እናቷም ለዲያቆናዊተዋ ሰጠቻት በደናግሉም ሁሉ ዘንድ አደራ ሰጠቻት ከጥቂትም ቀኖች በኋላ እናቷ አረፈችና ቀበሩዋት።

ከዚህም በኋላ ቅድስት ኢዮጰራቅስያ የምንኲስና ልብስን ለበሰች በጾም በጸሎትና በሰጊድ ተጋድሎ ጀመረች በየሰባት ቀንም ትጾም ነበር ሰይጠንም በእርሷ ላይ ቀንቶ ሊፈትናት ጀመረ ወደ ውኃ ውስጥ እርስዋን የሚጥልበት ጊዜ ነበር እንጨትም ስትፈልጥ በምሳር የሚአቊስልበት ጊዜ ነበር። የፈላ ውኃም በላይዋ የሚያፈሰበት ጊዜ ነበር ነገር ግን ምንም ምን የጐዳት የለም።

ለደነግሎችም ስታገለግል ብዙ ዘመናት ኖረች ምንም አትታክትም ነበር በምድርም ላይ አትተኛም መላዋን ሌሊት ቁማ በጸሎት ታድር ነበር እንጂ ከገድሏ ጽናትም የተነሣ ደናግሉ እስከሚያደንቁ ድረስ አርባ ቀን ቁማ ትፈጽም ነበር።

ከዚህም በኋላ #ጌታችን በሽተኞችን በማዳን አጋንንትን በማስወጣት የዕውሮችን ዐይን በመግለጥ የአንካሶችንም እግር በማስተካከል ድንቆችንና ተአምራቶችን በእጆቿ ገለጠ።

ዲያቆናዊት ኢዮኤልያም ለኢዮጰራቅስያ መጸሐፍትንና የምንኵስናንም ሥርዓት አስተማረቻት በሥራም ሁሉ ትሳተፋት ነበር እጅግም ይፋቀሩ ነበር እርሷም ሰማያዊ ሙሽራ ወደአለበት የመንግሥት አዳራሽ የማያልቅ ተድላ ደስታም ወደአለበት ኢዮጵራቅስያን ሲያወጧት ራእይን አየች።

በነቃችም ጊዜ ለደናግል ነገረቻቸው ወደርሷ ሲሔዱም በትኩሳት በሽታ ታማ አገኟት ስለእነርሱም እንድትጸልይ ለመኑዋት እርሷም ደግሞ በጸሎታቸው እንዲአስቧት ለመነቻቸው ያን ጊዜም ጸሎት አድርጋ መረቀቻቸውና በሰላም አረፈች በእናቷም መቃብር ውስጥ ቀበሩዋት።

ወዳጅዋ ኢዮኤልያም ወደ መቃብርዋ ሒዳ ጸለየችና በሦስተኛው ቀን አረፈች ከእርሷም ጋር ተቀበረች።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_2)
2024/09/23 21:27:26
Back to Top
HTML Embed Code: