Telegram Web Link
#ሐምሌ_29

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ሐምሌ ሃያ ዘጠኝ በዚች ቀን ክብር ይግባውና የ #መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ የልደቱ መታሰቢያ ነው። ለርሱ ክብር ምስጋና ይሁን በእኛ ላይም ይቅርታው ምህረቱ ይደረግልን ለዘላለሙ አሜን። #አቡነ_ዮሐንስ_ዘጠገሮ ዕረፍታቸው ነው፣ #የቅዱስ_ሐዋርያ_ታዴዎስ የሥጋው ፍልሰት ሆነ፣ #ቅዱስ_ወርስኖፋ በሰማዕትነት አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#እጨጌ_አባ_ዮሐንስ_ዘጠገሮ (ዘጐንድ)

ሐምሌ ሃያ ዘጠኝ በዚች ቀን አቡነ ዮሐንስ ዘጠገሮ ዕረፍታቸው ነው፡፡ ጻድቁ አባታችን የተወለዱት በኢየሩሳሌም አውራጃ ልዩ ስሙ ሳሬራ በሚባል ቦታ ነው፡፡ የካቲት 28 ቀን ተፀንሰው ህዳር 29 ተወለዱ፡፡ አባታቸው ድላሶር እናታቸው እምነ ጽዮን ይባላሉ፡፡ ሲወለዱ በወላጆቻቸው ቤት ውስጥ ብርሃን ወርዷል፡፡ ወላጆቻቸውም እግዚአብሔርን የሚፈሩ ደጋግ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ አባታችን ገና በተወለዱ በ5 ዓመታቸው ወላጆቻቸው ወደ እግዚአብሔር ቤት ይዘዋቸው የእመቤታችንን ሥዕል ተመልክተው በደስታ ተመልተው ሳቁ፡፡ አምላክን የወለደች የብርሃን እናቱ እመቤታችንም ከምሥሉ ወጥታ ‹‹በምን አውቀኸኝ ነው?›› ብላ አቅፋ ሳመችውና ‹‹ከእንግዲ ወዲህ የልጄ አገልጋይ ትሆናለህ ኑሮህም እንደ መላእክት ይሆናል በአንተ ምክንያት ብዙ ሰዎች ይድናሉ በምድር ላይም 500 ትኖራለህ…›› ብላ ባርካው ተሰወረች፡፡

ከዚያችም ቀን ጀምሮ አባ ዩሐንስ ለክርስቶስ ተላልፎ ተሰጠ፡፡ 50 ዓመትም በበረሃ ሲጋደል ኖሮ ከ50 ዓመት በኃላ በደመና ተጭኖ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል መሪነት ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ መጡ፡፡ ጻድቁ አባታችን በአቡነ ተክለሃይማኖት ዘመን መጨረሻ የመጡ ሲሆን ምንኩስና ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ተቀብለው በዚያው በድብረ ሊባኖስ ገዳም ለ50 ዓመት በጾምና በጸሎት በተጋድሎ ኖዋል፡፡ ከዚኽም በኋላ አባ ዩሐንስ ወደ ተዘጋቸላቸው ምድር በቅዱስ ገብርኤል አሳሳቢነት ወደ ጠገሮ መጡ፡፡ ይኽም ጠገሮ ያለው ገዳማቸው በሰሜን ሸዋ በመንዝና ይፋት ክልል መዘዞ በሚባል ቦታ ሲደርሱ በእግር አንድ ሰዓት ከተጓዙ በኃላ ይገኛል፡፡

ሕዝቡ በተለምዶ እጨ ዮሐንስ እያለ ይጠራቸዋል እንጂ ስማቸው እጨጌ ዮሐንስ ነው፡፡ አቡነ እጨጌ ዮሐንስ መስቀል ከሰማይ የወረደላቸው ታላቅ አባት ናቸው፡፡ መስቀሉም ሁልጊዜ ተአምር ይሠራል፡፡ በልደታቸው ቀን ኅዳር 29 ቀን መስቀሉ ከመቅደሱ ወጥቶ በካህናቱ ታጅቦ ወደ ጸበሉ ሲወርድ ከየት እንደመጣ ሳይታሰብ ደመና መጥቶ ከመስቀሉ ላይ ብቻ እረቦና እንደ ጃንጥላ ተዘርግቶ አብሮ ወደ ጸበሉ ይወርዳል፡፡ እዛው ቆይቶ መስቀሉ ሲመለስም አብሮ አጅቦ ይመለስና መስቀሉ ቤተ መቅደስ ውስጥ ሲገባ ደመናው ወዴት እንደተበተነ ሳይታወቅ ይጠፋል፡፡ ይህ በዘመናችንም ጭምር እየታየ ያለ ታላቅ ተአምር ነው፡፡

አባታችን በታላቀ ተጋድሎ ሣሉ ሰይጣን የሀገሩን ሰዎች በጠላትነት እንዲነሡባቸው አደረገ፡፡ ሰዎቹም አባታችንን እንዴት እንደሚያጠፏቸው ይማከሩ ጀመር፡፡ ሊገድሏቸው ፈልገው ቅድስናቸው በሁሉ ዘንድ የታወቀ ነውና ፈሩ፡፡ ከዚኽም በኋላ ‹‹ለምን ከመንደራችን ከወንድ ያረገዘች ሴት ፈልገን እሳቸው አስረገዟት ብለን በሐሰት እንከሳቸው?›› ብለው ተማከሩ፡፡ ብዙ ወርቅና ብርም ለአንዲት ሴት ሰጥተው በሐሰት ከእርሱ አርግዣለሁ ብላ እንድትመሰክር አደረጓት፡፡ አባታችንም በሕዝብ ፊት በሐሰት ተከሰሱ፡፡ ጻድቁም ‹‹አንቺ ሴት ከእኔ ነው ያረገሽው?›› አሏት እርሷም ‹‹አዎ ከአንተ ነው ልትክድ ነው እንዴ?›› አለቻቸው፡፡ አባታችንም በዚህ አዝነው ‹‹በአንቺና በእኔ መካከል እግዚአብሔር ይፍረድ›› ሲሉ ያች ሴት ወዲያው ለሁለት ተሰንጥቃ ሞተች፡፡ የአገሩ ሰዎችም እጅግ ፈሩ፡፡ አባታችንም ምድሪቱን እረገሟት፡፡ ‹‹የተዘራው ዘር አይብቀልብሽ፣ የተተከለው አይፅደቅ፣ ብርድና ውርጭ ይፈራረቅብሽ›› ብለው እረግመዋት በደመና ተጭነው ወደ ሰሜን ጎንደር እስቴ ጉንደ ተክለተሃማኖት ሔዱ፡፡

አቡነ ዩሐንስ በመላው ኢትዮጵያ ወንጌልን እየተዘዋወሩ ያስተማሩ ሲሆን ከቅድስናቸው የተነሣ በፀሐይ ላይ 50 ዓመት፣ በጨረቃ ላይ 50 ዓመት፣ በደመና ላይ 50 እንዲሁም ዓለምን በክንፋቸው በመዞር በደመና ላይ 50 የኖሩ ከሰው ተወልደው ከመላእክት የተደመሩ ታላቅ ጻድቅ ናቸው፡፡ በይፋት ጠግሮ በዓለወልድ፣ በአፋር አዘሎ፣ በመንዝ ፍርኩታ ኪዳነምሕረት፣ በደብረ ሊባኖስ፣ በጎንድ ተክለ ሃይማኖት በሌሎችም ቦታዎች በመዘዋወር በታላቅ ተጋድሎ ኖረዋል፡፡ አባታችን ከሰማይ መስቀል የወረደላቸው ሲሆን ዛሬም በገዳማቸው የሔደ ሰው በወረደው በእጃቸው መስቀል እየተዳበሰ ቆመው በጸለዩበት ባሕር በጠበላቸው ይጠመቃል፡፡ በተጨማሪም ይይዙት በነበረውም መቋሚያቸው በመዳበር በረከትን ማግኘት ይቻላል፡፡ ቆመው ከጸለዩበት ባሕር ውስጥ ደረቅ አሸዋ ይወጣል፡፡ አባ ዩሐንስ 500 ዓመት ከኖሩ በኃላ እረፍተ ዘመናቸው ሲደርስ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ከ15 ነቢያት፣ ከ12 ሐዋሪያት፣ ሄሮድስ ያስፈጃቸው ከመቶ አርባ አራት ሺ ሕፃናት፣ ከአብርሃም ከይስሐቅ፣ ከዕቆብ ጋር ሁሉንም ነገደ መላእክትን፣ ጻድቃን ሰማዕታትን ሁሉ አስከትሎ መጥቶ ታላቅ ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡ ‹‹ስምህን የጠራ ገዳምህን የረገጠ፣ መባ የሰጠ፣ ቤተ ክርስትያንህን የሠራ ያሠራ የረዳ፣ ገድልህን የሰማ ያሰማ ያስተረጎመ፣ መታሰቢያን ያደረገ እስከ 10 ትውልድ እምርልሀለው፤ ንስሀ ሳይገባ አይሞትም፣ ልጅ መውለድ ባይችል እኔ ልጅ እሰጠዋለሁ፤ ገድልህን በቤትህ ያስቀመጠ እርኩስ መንፈስ፣ ክፉ አጋንንት ቸነፈር ወባ መልአከ ጽልመት አይነካውም፡፡ በገዳምህ መነኩሴ ቢቀበር በሰማይ ክንፍ አበቅልለታለሁ፤ አይሁድም አረማዊም ያላመነ ያልተጠመቀ በገዳምህ መጥቶ ቢያርፍ ይቅር እልልሃለሁ፣ እንደ መቃብሬ ጉልጎታ እንደተቀበረ አድርጌ እቆጥርልሃለሁ…›› የሚል ቃል ኪዳን ከሰጣቸው በኃላ ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡

ቅዱስ አባታችንም በ500 ዓመታቸው ሐምሌ 29 ቀን ዐርፈው በጎንድ ተክለ ሃይማኖት ተቀብረዋል፡፡ በሰሜን ጎንደር የሚገኘውን ይህንን ገዳም ጻድቁ ራሳቸው ናቸው የመሠረቱት፡፡ ነገር ግን የገዳሙን ስያሜ በአባታቸው በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ስም አድርገውታል፡፡ አቡነ ዮሐንስ ካረፉ በኋላ በእርግማናቸው መሠረት በመንዝና በይፋት ብርዱ ድርቁ ስለበዛባቸው አንድ ብቁ ባሕታዊ ከበዓታቸው ወጥተው ‹‹በሐሜታችሁ ምክንያት እጨ ዮሐንስ ስለረገማችሁ ነው የእርሱን ዐፅም ካላመጣችሁ ብርዱ ውርጩ ድርቁም አይጠፋላችሁም›› አሏቸው፡፡ ሕዝቡም አባታችን በጉንድ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከተቀበሩ ከ134 ዓመት በኃላ በቅዱሳን እየተመሩ ሄደው በሌሊት ግማሽ ዐፅማቸውን አምጥተው በሀገራቸው አምጥተው ስላስቀመጡ ብርዱና ውርጩ በመንዝ እየቀነሰላቸው መጥቷል፡፡ ዛሬም በሀገሩ ብርዱና ውርጭ ሲበዛ የጻድቁን ታቦት ሲያወጡ ውርጩ ይጠፋል፡፡ ጠገሮ በሚባለው ገዳማቸው ውስጥ የሚገኘው ጠበላቸው እጅግ አስደናቂ ነው፡፡ ግማሽ ዐፅማቸውን ከጉንደ ተክለሃይማኖት አምጥተው አርባ ሐራ መዳኒዓለም አጠገብ በላይ በፍሩክታ ኪዳነምሕረት መጋቢት 18 ፍልሰተ ዐፅማቸው ተከናወነ፡፡ ምድሪቷም ተባረከች፣ የዘሩትንም አበቀለች፣ ውርጩም ብርዱም ቀነሰ፣ ዝናብ አልዘንብ ሲል ወይም ሰብል የሚጨርስ አንበጣ ሲመጣ ታቦታቸው ወጥቶ ምህላ ይያዛል-ወድያውም መቅሰፍት ይርቃል፣ ዝናብም ይዘንባል፡፡ ጻድቁ ደመናን፣ ጨረቃንና ፀሐይን በእጃቸው እየያዙ ይጸልዩ ነበር፡፡ በጠገሮ፣ በአዘሎ፣ በፍርኩታና በሌሎቹም ታላላቅ ቦታቦዎች ላይ
በእያንዳንዱ ገዳም ሃምሳ ሃምሳ ዓመት በጸሎት ኖረው በአጠቃላይ በ500 ዓመታቸው ነው ያረፉት፡፡ ዐፅማቸው መንዝ ከአርባ ሐራ መድኃኔዓለም አጠገብ ፍርኩታ ኪዳነ ምሕረት ገዳም ውስጥ ይገኛል፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ታዴዎስ_ሐዋርያ (ፍልሠቱ)

በዚህችም ቀን ከሶሪያ አገር ወደ ቁስጥንጥንያ ከተማ የቅዱስ ሐዋርያ ታዴዎስ የሥጋው ፍልሰት ሆነ። ይህም የሆነ ክርስቶስን የሚወድ ጻድቅ ቁስጠንጢኖስ በነገሠ ጊዜ ነበር። በሱ ትእዛዝም የቅዱስ ሐዋርያ ታዴዎስን ሥጋ አፈለሱ ያማረች ቤተ ክርስቲያን ሠርተው ሥጋውን በውስጧ አኖሩ።

በዚችም ቀን አከበሩዋት ከእርሱም ብዙ የሆኑ ድንቆችና ተአምራቶች ተገለጡ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዋርስኖፋ_ሰማዕት

በዚህችም ቀን ቅዱስ ወርስኖፋ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ቅድስ አዋቂ ሃይማኖቱ የቀና የዋህና በገድል የተጠመደ ሰው ነበረ። ኤጲስቆጶስነት ሊሾሙት በፈለጉት ጊዜ ከእርሳቸው ሸሸ ወደ አንዲት አገርም ደርሶ እግዚአብሔርን በሚወዱ ሁለት መነኰሳት ዘንድ አደረ።

በዚያቺም ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለት ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዲ ታመን የሰማዕትነትንም አክሊል እንዲቀበል አዘዘው። በነቃም ጊዜ ለእኒህ ለሁለቱ ወንድሞች ያየውን ነገራቸው። እነርሱም ከእርሱ ጋር በሰማዕትነት ይሞቱ ዘንድ ተስማሙ። ከዚህም በኃላ መኰንኑ ወደ አለበት ሔዱ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ ታላቅ ሥቃይንም አሠቃያቸው ከዚያም ሰንዑር ወደሚባል አገር እስከሚሔድ ድረስ በወህኒ ቤት ጨመራቸው።

የሚሔድበትም ሰዓት በደረሰ ጊዜ ከእርሱ ጋራ ወሰዳቸው በዚያም ታላቅ ሥቃይን አሠቃያቸው በሚያሠቃያቸውም ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ያጸናቸውና ቁስላቸውን ይፈውስ ነበር።

ከዚህም በኃላ ፃ ወደሚባል አገር ወሰዳቸው። በዚያም ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃያቸው ብዙዎች አማንያንንም ሰብስቦ ስለ አምልኮ ጣዖት የሚያዝዝ የከሃዲውን ንጉሥ ደብዳቤ አነበበላቸው። ይህም ቅዱስ ወርስኖፋ ተነሥቶ ያቺን ደብዳቤ ከአንባቢው እጅ ነጥቆ ቀደዳት መኰንኑም አይቶ እጅግ ተቆጣ እሳትንም እንዲያነዱና ቅዱስ ወርስኖፋን በውስጡ እንዲያነዱና ቅዱስ ወርስኖፋን በውስጡ እንዲጨምሩት አዘዘ። ሰማዕትነቱንና ተጋድሎውን በእሳቱ እቶን ውስጥ ፈጸመ።

እነዚህንም ሁለት ወንድሞች ራሶቻቸውን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዝዞ ቆረጧቸው የሰማዕትነትንም አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ሐምሌ_29 እና #ከገድላት_አንደበት)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ሐምሌ_29_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ገላትያ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁵ ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ሰው ልማድ እላለሁ። የሰው ስንኳ ቢሆን እርግጠኛውን ኪዳን ማንም አይንቅም ወይም አይጨምርበትም።
¹⁶ ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ። ስለ ብዙዎች እንደሚነገር፦ ለዘሮቹም አይልም፤ ስለ አንድ እንደሚነገር ግን፦ ለዘርህም ይላል፥ እርሱም ክርስቶስ።
¹⁷ ይህንም እላለሁ፤ ከአራት መቶ ሠላሳ ዓመት በኋላ የተሰጠው ሕግ አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተረጋገጠውን ኪዳን የተስፋውን ቃል እስኪሽር ድረስ አያፈርስም።
¹⁸ ርስቱ በሕግ ቢሆንስ እንግዲያስ በተስፋ ቃል አይሆንም፤ በተስፋ ቃል ግን እግዚአብሔር ለአብርሃም ሰጥቶአል።
¹⁹ እንግዲህ ሕግ ምንድር ነው? ተስፋው የተሰጠው ዘር እስኪመጣ ድረስ በመካከለኛ እጅ በመላእክት በኩል ስለ ሕግ መተላለፍ ተጨመረ።
²⁰ መካከለኛውም ለአንድ ብቻ አይደለም እግዚአብሔር ግን አንድ ነው።
²¹ እንግዲህ ሕግ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል የሚቃወም ነውን? አይደለም። ሕያው ሊያደርግ የሚቻለው ሕግ ተሰጥቶ ቢሆንስ በእውነት ጽድቅ ከሕግ በሆነ ነበር፤
²² ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ከማመን የሆነው የተስፋ ቃል ለሚያምኑ ይሰጥ ዘንድ መጽሐፍ ከኃጢአት በታች ሁሉን ዘግቶታል።
²³ እምነትም ሳይመጣ ሊገለጥ ላለው እምነት ተዘግተን ከሕግ በታች እንጠበቅ ነበር።
²⁴ እንደዚህ በእምነት እንጸድቅ ዘንድ ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚያመጣ ሞግዚታችን ሆኖአል፤
²⁵ እምነት ግን መጥቶአልና ከእንግዲህ ወዲህ ከሞግዚት በታች አይደለንም።
²⁶ በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤
²⁷ ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና።
²⁸ አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ዮሐንስ 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁹ በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፥ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና።
¹⁰ ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም።
¹¹ ወዳጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል።
¹² እግዚአብሔርን ማንም ከቶ አላየውም፤ እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ሆኖአል።
¹³ ከመንፈሱ ስለ ሰጠን፥ በእርሱ እንድንኖር እርሱም በእኛ እንዲኖር በዚህ እናውቃለን።
¹⁴ እኛም አይተናል አባትም ልጁን የዓለም መድኃኒት ሊሆን እንደ ላከው እንመሰክራለን።
¹⁵ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በሚታመን ሁሉ እግዚአብሔር በእርሱ ይኖራል እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል።
¹⁶ እኛም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነንማል። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፥ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል።
¹⁷ በፍርድ ቀን ድፍረት ይሆንልን ዘንድ ፍቅር በዚህ ከእኛ ጋር ተፈጽሞአል፤ እርሱ እንዳለ እኛ ደግሞ እንዲሁ በዚህ ዓለም ነንና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 9
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁰ ወዲያውም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በምኵራቦቹ ሰበከ።
²¹ የሰሙትም ሁሉ ተገረሙና፦ ይህ በኢየሩሳሌም ይህን ስም የሚጠሩትን ያጠፋ አይደለምን? ስለዚህስ ታስረው ወደ ካህናት አለቆች ይወስዳቸው ዘንድ ወደዚህ አልመጣምን? አሉ።
²² ሳውል ግን እየበረታ ሄደ፥ በደማስቆም ለተቀመጡት አይሁድ ይህ ክርስቶስ እንደ ሆነ አስረድቶ መልስ ያሳጣቸው ነበር።
²³ ብዙ ቀንም ሲሞላ አይሁድ ሊገድሉት ተማከሩ፤
²⁴ ሳውል ግን አሳባቸውን አወቀ። ይገድሉትም ዘንድ በሌሊትና በቀን የከተማይቱን በር ሁሉ ይጠብቁ ነበር፤
²⁵ ደቀ መዛሙርት ግን በሌሊት ወስደው በቅጥር ላይ አሳልፈው በቅርጫት አወረዱት።
²⁶ ሳውልም ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከደቀ መዛሙርት ጋር ይተባበር ዘንድ ሞከረ፤ ሁሉም ደቀ መዝሙር እንደ ሆነ ስላላመኑ ፈሩት።
²⁷ በርናባስ ግን ወስዶ ወደ ሐዋርያት አገባውና ጌታን በመንገድ እንዴት እንዳየውና እንደ ተናገረው በደማስቆም በኢየሱስ ስም ደፍሮ እንዴት እንደ ነገረ ተረከላቸው።
²⁸ በጌታም በኢየሱስ ስም ደፍሮ እየተናገረ በኢየሩሳሌም ሲወጣና ሲገባ ከእነርሱ ጋር ነበረ፤
²⁹ ከግሪክ አገርም መጥተው ከነበሩት አይሁድ ጋር ይነጋገርና ይከራከር ነበር፤ እነርሱ ግን ሊገድሉት ፈለጉ።
³⁰ ወንድሞችም ይህን ባወቁ ጊዜ ወደ ቂሣርያ ወሰዱት ወደ ጠርሴስም ሰደዱት።
³¹ በይሁዳም ሁሉና በገሊላ በሰማርያም የነበሩት አብያተ ክርስቲያናት በሰላም ኖሩ ታነጹም፤ በእግዚአብሔርም ፍርሃትና በመንፈስ ቅዱስ መጽናናት እየሄዱ ይበዙ ነበር።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሐምሌ_29_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ወእምኵሉ ያድኅኖሙ እግዚአብሔር። እግዚአብሔር የዐቅዐብ ኵሎ አዕፅምቲሆሙ። ወኢይትቀጠቀጥ አሐዱ እምውስቴቶሙ"። መዝ 33፥19-20።
"የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው፥ እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል።
እግዚአብሔር አጥንቶቻቸውን ሁሉ ይጠብቃል፥ ከእነርሱም አንድ አይሰበርም"።
መዝ 33፥19-20።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሐምሌ_29_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 12
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ በዚያን ጊዜ የሕዝብ አእላፍ እርስ በርሳቸው እስኪረጋገጡ ድረስ ተሰብስበው ሳሉ፥ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ይል ጀመር፦ አስቀድማችሁ ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠበቁ፥ እርሱም ግብዝነት ነው።
² ነገር ግን የማይገለጥ የተከደነ፥ የማይታወቅም የተሰወረ ምንም የለም።
³ ስለዚህ በጨለማ የምትናገሩት ሁሉ በብርሃን ይሰማል፥ በእልፍኝም ውስጥ በጆሮ የምትናገሩት በሰገነት ላይ ይሰበካል።
⁴ ለእናንተም ለወዳጆቼ እላችኋለሁ፥ ሥጋን የሚገድሉትን በኋላም አንድ ስንኳ የሚበልጥ ሊያደርጉ የማይችሉትን አትፍሩ።
⁵ እኔ ግን የምትፈሩትን አሳያችኋለሁ፤ ከገደለ በኋላ ወደ ገሃነም ለመጣል ሥልጣን ያለውን ፍሩ። አዎን እላችኋለሁ፥ እርሱን ፍሩ።
⁶ አምስት ድንቢጦች በአሥር ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ስንኳ በእግዚአብሔር ፊት አትረሳም።
⁷ ነገር ግን የእናንተ የራሳችሁ ጠጕር ሁሉ እንኳ የተቈጠረ ነው፤ እንግዲያስ አትፍሩ ከብዙ ድንቢጦች ትበልጣላችሁ።
⁸ እላችሁማለሁ፥ በሰው ፊት የሚመሰክርልኝ ሁሉ፥ የሰው ልጅ ደግሞ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይመሰክርለታል፤
⁹ በሰውም ፊት የሚክደኝ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይካዳል።
¹⁰ በሰው ልጅም ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ መንፈስ ቅዱስን የሚሰድብ ግን አይሰረይለትም።
¹¹ ወደ ምኵራቦችና ወደ መኳንንቶችም ወደ ገዢዎችም ሲጐትቱአችሁ፥ እንዴት ወይም ምን እንድትመልሱ ወይም እንድትናገሩ አትጨነቁ፤
¹² መንፈስ ቅዱስ በዚያች ሰዓት ልትናገሩ የሚገባችሁን ያስተምራችኋልና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ዲዮስቆሮስ ቅዳሴ ነው። መልካም በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ከሃዲው መኮንን ለአማንያን አምልኮ ጣዖት የሚያዝዝ የከሃዲውን ንጉሥ ደብዳቤ ባነበበላቸው ጊዜ ያቺን ደብዳቤ ከመኮንኑ እጅ ነጥቆ የቀደዳትና በእቶ እሳት ውስጥ ተጥሎ ሰማዕትነትን የተቀበለው ቅዱስ ማን ይባላል?
Anonymous Quiz
13%
ቅዱስ ብንያሚን
31%
ቅዱስ ዮስጦስ
31%
ቅዱስ ዋርስኖፋ
25%
ቅዱስ ታዴዎስ
ጻድቁ አባታችን አቡነ እጨጌ ዮሐንስ የተወለዱት መቼ ነው?
Anonymous Quiz
38%
ታኅሳስ 29
18%
ጥር 29
26%
ህዳር 29
18%
የካቲት 29
ከአምላካችን ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ከ9ኙ ዐበይት በአላት መካከል ያልሆነው የቱ ነው?
Anonymous Quiz
0%
በዓለ ልደቱ
28%
በዓለ ብሥራቱ(ፅንሰቱ)
9%
በዓለ ሆሳዕና
63%
ቃና ዘገሊላ
ጻድቁ አባታችን አቡነ እጨጌ ዮሐንስ የተወለዱት በኢየሩሳሌም አውራጃ ልዩ ስሙ ምን በሚባል ቦታ ነው የተወለዱት?
Anonymous Quiz
49%
ጠገሮ በሚባል ቦታ
22%
ሳሬራ በሚባል ቦታ
12%
ብሕንሳ በሚባል ቦታ
17%
ምስር በሚባል ቦታ
ጻድቁ አቡነ እጨጌ ዮሐንስ ዘጠገሮ ወደ ሃገራችን ኢትዮጵያ ከ50 በኃላ ከመጡ በኃላ በማን እጅ ምንኩስናን ተቀበሉ?
Anonymous Quiz
26%
በአቡነ ዜና ማርቆስ
10%
በአቡነ ሳሙኤል
57%
በአቡነ ተክለ ሐይማኖት
7%
በአቡነ መድኃኒነ እግዚእ
ጻድቁ አቡነ እጨጌ ዮሐንስን ይራዳቸው የነበረው መልአክ ማን ነው?
Anonymous Quiz
33%
ቅዱስ ሩፋኤል
21%
ቅዱስ ገብርኤል
21%
ቅዱስ ሚካኤል
24%
ቅዱስ ሱርያል
የጻድቁ አባታችን አቡነ እጨጌ ዮሐንስ ከጉንደ ተክለሃይማኖት ወደ አርባ ሐራ መዳኒዓለም አጠገብ በላይ ፍሩክታ ኪዳነምሕረት ፍልሰተ አጽማቸው የተከናወነው መቼ ነው?
Anonymous Quiz
20%
መጋቢት 20
23%
የካቲት 18
30%
መጋቢት 18
28%
ሚያዝያ 28
#ሐምሌ_30

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ሐምሌ ሠላሳ በዚች ቀን ቅዱሳን የገሊላ ሰዎች #ቅዱሳን_መርቆሬዎስና_ኤፍሬም በሰማዕትነት አረፈ፣ ክብርንና ብልጽግናን ንቆ የተወ #ቅዱስ_ጳውሎስ_መናኒ አረፈ፣ #ቅዱስ_ሐዋርያ እንድርያስ ተአምራትን አደረገ፣ የንጉሥ ናዖድ ሚስት #ንግሥት_ማርያም_ክብራ አረፈች።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_መርቆሬዎስና_ኤፍሬም (ሰማዕታት)

ሐምሌ ሠላሳ በዚች ቀን ቅዱሳን የገሊላ ሰዎች መርቆሬዎስና ኤፍሬም በሰማዕትነት አረፈ። እሊህም ከአክሚም ከተማ የመጡ የሚዋደዱ በ #መንፈስ_ቅዱስ ወንድማሞች በሥጋም ዘመዳሞች ነበሩ መንፈሳዊ ስምምነትንም ተስማምተው በላይኛው ግብጽ ካሉ ገዳማት በአንዱ ገዳም መነኰሱ በጾም በጸሎትና በስግደት እየተጋደሉ በገዳሙ ውስጥ ሃያ ዓመት ያህል ኖሩ።

ከዚህም በኃላ ጠላት ሰይጣን በአብያተ ክርስቲያናት ላይ ከአርዮሳውያን ችግርን በአመጣ ጊዜ አርዮሳውያኑ በአርዮሳዊ ንጉሥ ትእዛዝ መሥዋዕትን ሊሠው ወደ ኦርቶዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገቡ ቀንተው ወደ ቤተ ክርስቲያን ገቡና አርዮሳውያን ያኖሩትን መሥዋዕት በተኑት።

እንዲህም አሏቸው በ #ሥሉስ_ቅዱስ ስም ያልተጠመቀ መሥዋዕትን ያሳርግ ዘንድ አይገባውም። ያን ጊዜም አርዮሳውያን ይዘው ደበደቧቸው ታላቅ ግርፋትንም ገረፏቸው ዐጥንቶቻቸውም እስኪሰበሩ ድረስ በምድር ላይ ጥለው ረገጧቸው ነፍሶቻቸውንም በ #እግዚአብሔር እጅ ውስጥ ሰጡ የሰማዕትነትንም አክሊል ተቀበሉ ምእመናንም መጥተው ሥጋቸውን ወሰዱ በአማሩ ልብሶችም ገንዘው በመልካም ቦታ አኖርዋቸው ከእነሱም ለበሽተኞች ታላቅ ፈውስ ሆነ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእኒህ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዻውሎስ_መናኒ

በዚህችም ቀን ክብርንና ብልጽግናን ንቆ የተወ ጳውሎስ አረፈ። ይህም ቅዱስ ባለጸጋ ነበር። ደግ የሆነች ሚስትና የተባረኩ ልጆችም ነበሩት። መነኮስ ሊሆን ወደደ ሚስቱንና ልጆቹንም ጠርቶ እነሆ ክብር ይግባውና ስለ #ክርስቶስ ፍቅር እሸጣችሁ ዘንድ ወደድኩ አላቸው እነርሱም አሳዳሪያቸን ነህና የወደድከውን አድርግ አሉት።

ከዚህም በኋላ ገንዘቡን ሁሉ ወስዶ ለድኆችና ለችግረኞች በተነ ሚስቱንም ወደ ደናግል ገዳም ወሰዳት እመምኔቷንም ጠራትና እንዲህ አላት ለገዳምሽ አገልጋይ ትሆን ዘንድ ሚስቴን ልሸጥልሽ እወዳለሁ እርሷም እሺ አለችው የመሸጫዋንም ደብዳቤ ጻፈ የሺያጭዋን ዋጋ ተቀብሎ ለድኆች ሰጠ ልጆቹንም ወደ አበ ምኔቱ ወስዶ እንደ እናታቸው ሸጣቸው ለአበ ምኔቱም አሳልፎ ሰጣቸው።

ከዚህም በኃላ ወደ ሌላ ቦታ ሔደ ራሱንም ለገዳሙ አለቃ ሸጠ አለቃውንም ወደ ቤተ ክርስቲያን ብቻዬን ልገባ እሻለሁ አለው በገባም ጊዜ በሩን በላዩ ዘጋ። እጆቹንም ዘርግቶ ቆመ በታላቅ ድምፅም እንዲህ ብሎ ጮኸ አቤቱ በፍጹም ልቡናዬ ወዳንተ እንደ መጣሁ አንተ ታውቃለህ።

ወደርሱም እንዲህ የሚል ቃል መጣ ሀሳብህን ሁሉ አውቅሁ በፍጹም ልቤም ተቀበልኩህ። ከዚህም በኃላ መነኮስ አስጨናቂ የሆኑ የገዳሙን ሥራዎች ሁሉ እንደ ባሪያ እየሠራ ኖረ ራሱንም ከሁሉ እጅግ አዋረደ ነገር ግን ስለ መዋረዱ እግዚአብሔር ከፍ ከፍ አደረገው። ከእርሱም ብዙዎች ድንቆችና ተአምራቶች ተገለጡ ከዚህም በኃላ በሰላም አረፈ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን ለዘላለሙ አሜን

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_እንድርያስ_ሐዋርያ

በዚችም ቀን ቅዱስ ሐዋርያ እንድርያስ ተአምራትን አደረገ። እንድርያስ በጽርዕ አገር እያለ #ክብር_ይግባውና_ጌታችን_ኢየሱስ ተገልጦ እንዲህ አለው ማትያስን ከእሥር ቤት ታወጣው ዘንድ ሰውን ወደሚበሉ ሰዎች አገር ሒድ የዚያች አገር ሰዎች ከሦስት ቀን በኃላ ሊበሉት ያወጡታልና ።

እንድርያስም ጌታችንን እንዲህ አለው የቀረው ሦስት ቀን ከሆነ እንዴት እደርሳለሁ ነገር ግን ፈጥኖ የሚያወጣውን ከመላእክት አንድ ላክ እንጂ።

#ጌታችንም ለእንድርያስ እንዲህ ብሎ መለሰለት ስማ ሀገሪቱን ወደዚህ ነዪ ከልዃት በውስጧ ከሚኖሩ ሁሉ ጋር ትመጣለች አንተና ደቀ መዘሙሮችህ ግን ጠዋት በሆነ ጊዜ ተነሥታችሁ ወደ ባሕር ሒዱ የተዘጋጀ መርከብንም ታገኛላችሁ እርሱም ያደርስሃል ይህንንም ብሎ ከእርሱ ዘንድ በክብር ዐረገ። በነጋ ጊዜም እንድርያስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ተነሥቶ ወደ ወደብ ደረሰ ጥሩ መርከብንም አየ #ጌታችንንም በሊቀ ሐመር አምሳል አየው #ጌታችን እንደሆነ አላወቀም ሊቀ ሐመር ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን አለው #ጌታም#እግዚእብሔር ሰላም ይደርብህ አለው እንደርያስም ደግሞ በዚህ መርከብ ወዴት ትሔዳለህ አለው ሰውን ወደ ሚበሉ ሰዎች አገር እሔዳለሁ አለው እንድርያስም ሊቀ ሐመሩን ወንድሜ ሆይ ከአንተ ጋር ትጭነኝ ዘንድ እለምንሃለሁ አለው ሊቀ ሐመሩም እሺ ብሎ ወደ መርከቡ አወጣቸው። በባሕሩ ላይም ሲጓዙ #ጌታችን እንድርያስን እንዲህ ብሎ ጠየቀው #ጌታህ ምን ኃይል አደረገ እንድርያስም #ጌታችን ከአደረጋቸው ተአምራቶች ሊነግረው ጀመረ #ጌታችን እንደሆነ አላወቀም ነበርና።

ከዚህም በኋላ ሊቀ ሐመሩ እነደሚአንቀላፋ ሰው ሆነ ያንጊዜም እንድርያስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ተኛ በዚያን ጊዜም #ጌታችን እንድርያስንና ሁለቱን አርድእቱን ይሸክሙአቸው ዘንድ መላእክትን አዘዛቸውና ወስደው በባሕሩ ዳርቻ አኖሩዋቸው። እንድርያስም ከእነቅልፍ በነቃ ጊዜ መረከብን አላገኘም እጅግም አደገቀ ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አላቸው ልጆቼ ሆይ በመርከብ ውስጥ ከ #ጌታችን ጋር ነበርን ግን አላወቅንም።

ከዚህም በኋላ እንድርያስ ተነስቶ ጸለየ ክብር ይግባውና #ጌታችንም በመልካም ጎልማሳ አምሳል ተገለጸለት እንዲህም አለው ወዳጄ እንድርያስ አትፍራ እኔ ይህን አድርጌአለሁና አንተ በሦስት ቀን አልደርስም ብለህ ነበር ስለዚህ በፍጥረት ሁሉ ላይ ኃይል እንዳለኝ የሚሳነኝም እንደሌለ ታውቅ ዘንድ እንግድህም ወደ ከተማው ገብተህ ማትያስን ከእሥር ቤት አውጣው ከእርሱ ጋር ያሉትንም ሁሉ።

ከዚህም በኋላ እንድርያስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተነሥቶ ወደ ከተማ ገባ ማትያስ ወዳለበትም እስር ቤት ሔደ። በደረሰም ግዜ የወህኒ ቤቱ ደጀ ራስዋ ተከፈተች በገባ ጊዜም ማትያስን ተቀምጦ ሲዘምር አገኘው እርስ በርሳቸውም ሰላምታ ተሳጣጡ እንድርያስም ማትያስን ከሁለት ቀን ቡኋላ አውጥተው እንደ እንስሳ አርደው ይበሉኛል አልክ አንተ በ #ጌታችን ዘንድ ያየናትን ያቺን ምሥጥር ረሰሃትን በምንናገረት ጊዜ ሰማይና ምድርን ይናወጣሉ አለው። ማትያስም ወንድሜ ሆይ እንሆ ይህን አወቅሁ ነገር ግን በዚች ከተማ ውስጥ ሥራዬን እንድፈጽም የ #ጌታችን ፍቃድ እንደ ሆነ እኔ እናገራሎህ እርሱ ራሱ እንሆ እኔ እንደ በጎች በተኲላዎች መካከል እልካችኋለሁ ብሏልና ወደ ዝህም እሥር ቤት በጨመሩኝ ጊዜ ክብር ይግባውና #ጌታችንን ጠራሁት እርሱም ሃያ ሰባት ቀን ሲፈጸም ወንድምህ እንድርያስን ወዳንተ እልከዋሎህ እርሱም ከእሥር ቤት ያወጣሃል ከአንተ ጋራ ያሉትን ሁሉ ያወጣችዋል ብሎ ገለጠልኝ እንሆም ደርሰሃል የምትሠራውን አስተውል አለው።

እንድርያስም ወደ እስረኞች በተመለከተ ጊዜ እንደ እንስሳ ሥር ሲበሉ አይቶ አዘነ አለቀሰም ሰይጣንንም ከሠራዊቱ ጋር አሥረው ከዝህ በኃላ አንድርያስና ማትያስ ተነሥተው ወደ #እግዚአብሔር ማለዱ እጆቻቸውንም በእሥረኞች ሁሉ ላይ ጫኑ አእምሮአቸውም ተመለሰ ከከተማው ውጭ ወጥተው በዝያ በአንድነት እንድቀመጡ አዘዙአቸው።
እኒያ ሐዋርያትም የሚሆነውን ያዩ ዘንድ ወጥተው በሀገሩ ጎዳና ዳር ተቀመጡ የከተማው ሰዎችም እነደ ልማዳቸው የሚበሉትን ከእሥረኞች ውስጥ ሊአመጡ መጡ የእሥር ቤቱን ደጅ ክፍት ሆኖ አገኙ እሥረኞችም አልነበሩም ደነግጠውም በእኛ የደረሰብን ምንድነው ወዮልን አሉ ያን ጊዜም ሰይጣን በሰው መስሎ ሐዋርያት ይህን እንዳደረጉ ነገራቸው የአሉበትንም አመለከታቸው የከተማው ሰዎችም በመቀዳደም ሮጡ እንድርያስንና ማትያስንም ይዘው በከተማው ጥጋጥግ አስጎተቱአቸው በሌሊትም በእሥር ቤት ያሳድሩአቸው ነበር ሦስት ቀናትም እንዲህ አደረጉባቸው ደማቸውም እንደ ውኃ ፈሰሰ።

ከዚህም በሗላ ሰለ ከተማዋ ሰዎች ድኀነት ወደ #እግዚአብሔር ጸለዪ ጸሎታቸውንም በፈጸሙ ጊዜ በላዩ ምስል ወደአለበት የዕብነ በረድ ምሶሶ ቀርበው በመስቀል ምልክት አመተቡት እንዲህም አሉት አንተ ምሶሶ ፍራ ከበታችህም እንደ ጥፋት ውኃ ያለ ብዙ ውኃን በዚች ከተማ ላይና በውስጧ የሚኖሩ ሁሉ ላይ አውጣ ያን ጊዜም ከምሶሶው ሥር ብዙ ውኃ መነጨ የከተማው ሰዎችንም ያሠጥማቸው ዘንድ ገነፈለ ሰዎችም ከከተማው ወጥተው ሊሸሹ ወድደው ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ያዙ ውኃውም በዝቶ ከበባቸው ማምለጥም አልቻላቸውም ውኃውም እስከ እስከ አንገታቸው ደረሰ ያን ጊዜም አለቀሱ እንዲህም አሉ ወዮልን ይህ ሁሉ በእኛ ላይ የመጣው በእነዚህ በተመረጡ ሰዎች በ #እግዚአብሔር አገልጋዮች ምክንያት ነው እኛም በአምላካቸው እናምናለን። እንድርያስም የዕብነ በረደ ምሰሶ እንግዲህስ በቃህ እነሆ የጥፋት ጊዜ አለፈ ያን ጊዜም ውኃው ተገታ ውኃውም እንደተገታ የከተማው ሰው አይተው ወደ ሐዋርያት ሔዱ ስለዚያች ከተማ ሰዎች ድኅነትም ቁመው እጆቻቸውን ዘርግተው ወደ #እግዚአብሔር ሲጸልዩ አገኙአቸው ሐዋርያትን ይቅር በሉን ብለው ለመኑአቸው። ሐዋርያትም በሕያው #እግዚአብሔር እመኑ እንጂ አትፍሩ አሏቸው ሐዋርያትም ሁለተኛ ጸለዩ በውኃ ስጥመት የሞቱትንም ሙታን አስነሡአቸው በዚያም ውኃ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቋቸው። ሥጋውንና ደሙንም አቀበሏቸው ቤተ ክርስቲያንንም ሠሩላቸው። ሕግንና ሥርዓትንም ሁሉ አስተምረው በቀናች ሃይማኖት አጸኑአቸው እንዲህም አሏቸው ያዘዝናችሁን ጠብቁ ከእናንተ በኃላ ለሚነሡ ልጆቻችሁም አስተምሯቸው።

ከዚህም በኃላ የአራዊትን ጠባይ ከእነርሱ ያርቅ ዘንድ #እግዚአብሔርን ለመኑት ክብር ይግባውና #ጌታችንም ይህን የአራዊት ጠባይ አራቀላቸው። ሰዎች የሚመገቡትንም የሚመገቡ የዋሆች ሆኑ። አባቶቻችን ሐዋርያትም ብዙ ተአምራትን አደረጉ በሽተኞችን ሁሉ ፈወሱ ከዚህም በኃላ እንድርያስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ወደ ግሪክ አገር ተመለሰ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባቶቻችን ሐዋርያት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ማቲያስ ከሀሉም ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት ከክርስቲያን ወገኖችም ሁሉም ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#እናታችን_ማርያም_ክብራ

በዚህችም ቀን የንጉሥ ናዖድ ሚስት ንግሥት ማርያም ክብራ አረፈች። እርሷም መንፈሳዊ የሆነ በጎ ተግባርን ሁሉ የጠበቀች ትሩፋትንና መጋደልንም በጾምና በጸሎት የፈጸመች ነበረች በደብረ ሊባኖስም ተቀበረች።

በተጨማሪም በዚችም ቀን የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት የአባ ጢሞቴዎስ የሥጋው ፍልሰት ከምስር በአስቄስጥ ወደ አለ ወደ አባ መቃርስ ገዳም ሆነ። በረከታቸው ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

ዳግመኛ በዚህች ቀን የእስራልዩ ቤተ ክርስቲያን የከበረችበት ነው ይኸውም ሱርያል መልአክ ነው። አማላጅነቱና ረድኤቱ ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

#እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባቶቻችን ነቢያትና ሐዋርያት በጻድቃንና በሰማዕታት በደናግልና በመነኮሳት በቅዱሳን መላእክትም በተመረጡ ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስቆጶሳት በቀሳውስትና በዲያቆናት ሃይማኖታቸው በቀና በአእሩግና ሕፃናት በእነዚህ ሁሉ ጸሎት ይማረን።

አምላክን የወለደች የእመቤታችን የቅድስት #ድንግል_ማርያም በረከቷ በርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ማቲያስ በሁሉም ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስቆጶሳት እንዲሁም በሁላችን በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ላይ ይደር ለዘላለሙ አሜን።

በሐምሌ ወር የሚነበብ ንባብ ደረሰ ተፈጸመ። ለ #እግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ሐምሌ_30)
2024/09/23 19:27:17
Back to Top
HTML Embed Code: