Telegram Web Link
ጻድቁ የጌታችን መከራ በማሰብ ከተወለዱ ጀምሮ ተላጭተውት የማያውቁትን ፀጉራቸውን ከትልቅ ዛፍ ላይ እያሠሩ ይጸልዩ ነበር፡፡ እንዲሁ አድርገው ዛፍ ላይ ራሳቸውን ሰቅለው 40 ቀንና 40 ሌሊት ሲጸልዩ በመጨረሻ የታሠሩበት ፀጉራቸው ተነቅሎ ከመሬት ላይ የወደቁት አባት ማን ይባላሉ?
Anonymous Quiz
18%
አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ
32%
አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ
36%
አቡነ ሳሙኤል ዘቆይጻ
14%
አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ሃሌሉያ
አቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ለሃገራችን ኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሊቀ ጳጳስ ተደርገው የተሾሙበት ቀን መቼ ነው?
Anonymous Quiz
35%
መጋቢት 18
31%
መስከረም 18
23%
ጥቅምት 18
12%
ታኅሳስ 18
አቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ለሃገራችን ኢትዮጵያ ጳጳስ አድርገው ሹመው የላኩልን የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ማን ይባላሉ?
Anonymous Quiz
9%
ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ቴዎፍሎስ
17%
ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ቄርሎስ
57%
ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ አትናቴዎስ
17%
ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ እለእስክንድሮስ
በቁስጥንጥንያ የተሰበሰቡ የመቶ ሃምሳ ቅዱሳን ኤጲስቆጶሳት ሊቀ ጉባኤ ሆኖ መቅዶንዮስንና ሰባልዮስን አቡሊናርዮስንም የተከራከራቸው ቅዱስ አባት ማን ይባላል?
Anonymous Quiz
9%
የሮም ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ጢሞቴዎስ
45%
የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ጢሞቴዎስ
32%
ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ እለእስክንድሮስ
14%
ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ቴዎፍሎስ
አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ ያረፈው ክብር ይግባውና ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋዊ(ሥጋን ከለበሰ)____ዓመት በኃላ ነው።
Anonymous Quiz
19%
ከ10 ዓመት
22%
ከ15 ዓመት
26%
ከ16 ዓመት
33%
ከ25 ዓመት
#ሐምሌ_27

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሐምሌ ሃያ ሰባት በዚህች ቀን ኢትዮጵያዊቷ #ቅድስት_መስቀል ክብራ ዕረፍቷ ነው፣

#ቅድስት_መስቀል_ክብራ

በዚህችም ቀን ኢትዮጵያዊቷ ቅድስት መስቀል ክብራ ዕረፍቷ ነው፡፡ ይኽችም ቅድስት የቅዱስ ላሊበላ ባለቤት ስትሆን የትውልድ ሀገሯ ወሎ ላስታ ቡግና ነው፡፡ የታላቁ ጻድቅ ንጉሥ የቅዱስ ላሊበላ ሚስት ናት፡፡ ከእርሱም ደገኛውን ይትባረክን ወልዳለች፡፡ ቅዱስ ላሊበላን እና ቅድስት መስቀል ክብራን ሁለቱ እንዲጋቡ ያዘዛቸው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ቅዱስ ላሊበላን ወደ ሰማይ ነጥቆ ወስዶ የሚያንጻቸውውን የሕንጻ ዲዛኖችና ሌሎችንም ብዙ ምሥጢራትን ካሳየውና ወደ ምድር ከመለሰው በኃላ ድጋሚ ተገልጦለት "እንዳንተ የተመረጠች ናት እንደ ልብህም ትሆናለች፣ ሥራዋም ከሥራህ አያንስም እርሷ የተመረጠች የእግዚአብሔር አገልጋይ ናትና" በማለት መልአኩ የቅድስት መስቀል ክብራን ንጽሕናና ቅድስና መስክሮላታል፡፡

ቅዱስ ላሊበላ 11 እጅግ አስደናቂ የሆኑ ፍልፍል ቤተ መቅደሶቹን ከመላእክት ጋር ሲያንጽ ብታየው ልቧ በመንፈሳዊ ተመስጦ ተመልቶ እርሷም እግዚአብሔር ፈቅዶላት አስደናቂውን የአባ ሊባኖስን ቤተመቅደስ ራሷ እንዳነጸችው መጽሐፈ ገድሏና ገድለ ቅዱስ ላሊበላ ያስረዳል፡፡

ቅድስት መስቀል ክብራን ወደ ትግራይ እየመራ የወሰዳት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ እርሷን በትግራይ ቅዱስ ሚካኤል እንዲጠብቃት ከተዋት በኃላ ቅዱስ ላሊበላን ደግሞ ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ መንግሥተ ሰማያት አውጥቶታል፡፡

ቅድስት መስቀል ክብራም በትግራይ ሆና መልአኩ እየጠበቃት ከሰው ተለይታ በታላቅ ተጋድሎ ኖረች፡፡ በቀን እልፍ እልፍ እየሰገደች በታላቅ ተጋድሎ ስትኖር ጌታችን ተገልጦ ክብሯ ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት ጋር እኩል መሆኑን ነግሯታል፡፡

ይኽችም ቅድስት ብዙ ሐዋርያዊ አገልግሎት ፈጽማለች፡፡ ለምሳሌ በመስቀል ጦርነት ጊዜ እስላሞች ከባሕር ማዶ እየፈለሱ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በፍቅር እየተቀበለችና እያስተናገደች ሃይማኖትንና ሕገ እግዚአብሔርን እያስተማረች ወደ ክርስትና እንደገቡና እንዱጠመቁ አድርጋለች፡፡

ቅድስት መስቀል ክብራም በትግራይ ክልል ሽሬ አውራጃ መደባይ ታብር በተባለው ቦታ ላይ በስማ የተሰራ ትልቅ ገዳም አላት። እጅግ ውብ በሆኑ ሰንሰላታማ ትላላልቅ ድንጋዮች መካከል የሚገኝ አስደናቂና ጥንታዊ ገዳም ነው። ገዳሙ ከሽሬ ከተማ በእግር የ 7 ሰዓት መንገድ ያስኬዳል።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት መስቀል ክብራ ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#ሐምሌ_27

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሐምሌ ሃያ ሰባት በዚህች ቀን #ቅዱስ_አሞን በሰማዕትነት ዐረፈ፣ የአዳም ልጅ #ቅዱስ_ሴት ዕረፍቱ ነው፣ #የወንጌላዊው_ቅዱስ_ዮሐንስ በእስክንድርያ #ቤተ_ክርስቲያኑ_የከበረችበት_ነው፣ በተጨማሪ በዚች ቀን ከሰማዕቱ #ቅዱስ_አሞን ጋር ሰማትነት የተቀበለች የድንግል #ቅድስት_ትዮጲላ መታሰቢያዋ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሰማዕቱ_ቅዱስ_አሞን

ሐምሌ ሃያ ሰባት በዚህች ቀን ቅዱስ አሞን በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡ ይኸውም ቅዱስ ተርኑጥ ከሚባል አገር የተገኘ ሰማዕት ነው፡፡ ወደ ላይኛው ግብጽ በሄደ ጊዜ የእንዴናው ገዥ ሰማዕታትን ይዞ በጽኑ ሲያሠቃያቸው ተመለከተ፡፡ እርሱም በመኮንኑ ፊት ቀርቦ የጌታችንን አምላክነት መሰከረ፡፡ መኮንኑም ይዞ ታላቅ ሥቃይን አሠቃየው፡፡ ሥጋውን ሁሉ ሰነጣጥቆ ከጣለው በኋላ ዳግመኛ በትላልቅ ችንካሮች ቸነከረው፡፡ ነገር ግን ጌታችን አጽናንቶ ከቁስሉ ፈውሶ ጤነኛ አደርጎ አስነሣው፡፡

መኮንኑም ማሠቃየት በሰለቸው ጊዜ ቅዱስ አሞንን ወደ እስክንድርያ ከተማ ላከው፡፡ በዚያም ሳለ ጌታችን ተገለጠለትና ስሙን ለሚጠራና ገድሉን ለሚጽፍ በሕይወት መጽሐፍ እንደሚጽፍ ቃልከዳን ከገባለት በኋላ ሰማዕትነቱን በድል እንዲፈጽም ነገረው፡፡

ወዲያውም ይዘው ጽኑ በሆኑ ልዩ ልዩ ሥቃዮች አሠቃዩት፡፡ ጌታችንም ከመከራው እያዳነው ልዩ ልዩ ተአምራትን ስላደረገለት ይህንን ያዩ ብዙዎች ‹‹በቅዱስ አሞን አምላክ አምነናል›› እያሉ በመመስከር ሰማዕትነትን ተቀበሉ፡፡ እነርሱም ውስጥ ቲዮጲላ የምትባል ድንግል ነበረች፡፡ እርሷም ወደ መኮንኑ ዘንድ በመሄድ በጌታችን ታመነች፡፡ መኮንኑም እቶን እሳት ውስጥ ከተታት ነገር ግን እሳቱ አላቃጠላትም፡፡ በመጨረሻም ራሷን በሰይፍ ቆረጡትና የሰማዕትነት አክሊልን ተቀዳጀች፡፡

ከዚህም በኋላ አባለ ዘሩንና አካሉን ሁሉ በሰይፍ እየቆረጡ ቅዱስ አሞንን እጅግ ካሠቃዩት በኋላ አንገቱን በሰይፍ ቆረጡትና የሰማዕትነቱ ፍጻሜ ሆነ፡፡ በመንግሥተ ሰማያትም የክብር አክሊልን ተቀዳጀ፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሴት_ነቢይ

ዳግመኛም በዚህች ቀን የአዳም ልጅ ሴት ዕረፍቱ ነው፡፡ እርሱም ሁለት መቶ አምስት ዓመት ኖረ፡፡ ሔኖስንም ወለደው፡፡ ሔኖስንም ከወለደ በኋላ ሰባት መቶ ሰባት ዓመት ኖረ፡፡ ወንዶችንና ሴቶች ልጆችንም ወለደ፡፡ መላ ዕድሜውም ዘጠኝ መቶ ዐሥራ ሁለት በሆነ ጊዜ በሰላም ዐረፈ፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ሐምሌ_27 እና #ከገድላት_አንደበት)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ሐምሌ_27_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዕብራውያን 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁷ እርሱም በስጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፥ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት፤
⁸ ምንም ልጅ ቢሆን፥ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤
⁹-¹⁰ ከተፈጸመም በኋላ በእግዚአብሔር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ስለ ተጠራ፥ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው።
¹¹ ስለ እርሱም የምንናገረው ብዙ ነገር አለን፥ ጆሮቻችሁም ስለ ፈዘዙ በቃል ልንተረጕመው ጭንቅ ነው።
¹² ከጊዜው የተነሳ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነትን ትምህርት እንዲያስተምራችሁ እንደ ገና ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም።
¹³ ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅምና፤
¹⁴ ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በስራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ዮሐንስ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁷ ዓመፃ ሁሉ ኃጢአት ነው፥ ሞትም የማይገባው ኃጢአት አለ።
¹⁸ ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን እንዳያደርግ፥ ነገር ግን ከእግዚአብሔር የተወለደው ራሱን እንዲጠብቅ ክፉውም እንዳይነካው እናውቃለን።
¹⁹ ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን።
²⁰ የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ መጣ፥ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፥ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁰ እናንተ በሰቀላችሁት እግዚአብሔርም ከሙታን ባስነሣው በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይህ ደኅና ሆኖ በፊታችሁ እንደ ቆመ፥ ለእናንተ ለሁላችሁ ለእስራኤልም ሕዝብ ሁሉ የታወቀ ይሁን።
¹¹ እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት፥ የማዕዘን ራስ የሆነው ይህ ድንጋይ ነው።
¹² መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።
¹³ ጴጥሮስና ዮሐንስም በግልጥ እንደ ተናገሩ ባዩ ጊዜ፥ መጽሐፍን የማያውቁና ያልተማሩ ሰዎች እንደ ሆኑ አስተውለው አደነቁ፥ ከኢየሱስም ጋር እንደ ነበሩ አወቁአቸው፤
¹⁴ የተፈወሰውንም ሰው ከእነርሱ ጋር ቆሞ ሲያዩ የሚመልሱትን አጡ።
¹⁵ ከሸንጎም ወደ ውጭ ይወጡ ዘንድ አዝዘው፦ በእነዚህ ሰዎች ምን እንሥራ?
¹⁶ የታወቀ ምልክት በእነርሱ እጅ እንደ ተደረገ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሁሉ ተገልጦአልና፥ እንሸሽገው ዘንድ አንችልም፤
¹⁷ ነገር ግን በሕዝቡ ዘንድ አብዝቶ እንዳይስፋፋ፥ ከእንግዲህ ወዲህ ለማንም ሰው በዚህ ስም እንዳይናገሩ እየዛትን እንዘዛቸው ብለው እርስ በርሳቸው ተማከሩ።
¹⁸ ጠርተውም በኢየሱስ ስም ፈጽመው እንዳይናገሩና እንዳያስተምሩ አዘዙአቸው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሐምሌ_27_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ወቅዱሰ እስራኤል ንጉሥነ። ውእቱ አሚረ ተናገርኮሙ በራእይ ለደቂቅከ። ወትቤ እሬሲ ረድኤተ በላዕለ ኃይል"። መዝ 88፥18-19።
"ረድኤታችን ከእግዚአብሔር ከንጉሣችንም ከእስራኤል ቅዱስ ነውና። በዚያ ጊዜ ለልጆችህ በራእይ ተናገርህ እንዲህም አልህ፦ ረድኤቴን በኃይል ላይ አኖርሁ፤ ከሕዝቤ የተመረጠውን ከፍ ከፍ አደረግሁ"። መዝ 88፥18-19።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሐምሌ_27_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዮሐንስ 10
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³⁰ እኔና አብ አንድ ነን።
³¹ አይሁድ ሊወግሩት ደግመው ድንጋይ አነሡ።
³² ኢየሱስ፦ ከአባቴ ብዙ መልካም ሥራ አሳየኋችሁ፤ ከእነርሱ ስለ ማናቸው ሥራ ትወግሩኛላችሁ? ብሎ መለሰላቸው።
³³ አይሁድም፦ ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፤ ስለ ስድብ፤ አንተም ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለ ማድረግህ ነው እንጂ ብለው መለሱለት።
³⁴ ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ እኔ፦ አማልክት ናችሁ አልሁ ተብሎ በሕጋችሁ የተጻፈ አይደለምን?
³⁵ መጽሐፉ ሊሻር አይቻልምና እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው፥
³⁶ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ እናንተ አብ የቀደሰውን ወደ ዓለምም የላከውን፦ ትሳደባለህ ትሉታላችሁን?
³⁷ እኔ የአባቴን ሥራ ባላደርግ አትመኑኝ፤
³⁸ ባደርገው ግን፥ እኔን ስንኳ ባታምኑ አብ በእኔ እንደ ሆነ እኔም በአብ እንደ ሆንሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ሥራውን እመኑ።
³⁹ እንግዲህ ደግመው ሊይዙት ፈለጉ፤ ከእጃቸውም ወጣ።
⁴⁰ ዮሐንስም በመጀመሪያ ያጠምቅበት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ እንደ ገና ሄደ በዚያም ኖረ።
⁴¹ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው፦ ዮሐንስ አንድ ምልክት ስንኳ አላደረገም፥ ነገር ግን ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ነበረ አሉ።
⁴² በዚያም ብዙዎች በእርሱ አመኑ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈ_ወርቅ ቅዳሴ ነው። መልካም የአምላካችን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለቱ መታሰቢያ በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምነን በዕለተ ቀዳሚት የሚነበብ የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዜናውን እንናገር እነሆ #የመድኃኔአለም ትእምርተ #መስቀሉ #የእግዚአብሔር ምሳሌው። ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ ከ #እግዚአብሔር ጋር ያለ ትእምርተ መስቀል የከበረ ነው።

#የእግዚአብሔር ምሳሌው የሆነ ትእምርተ #መስቀል ከሁሉ አስቀድሞ ተፈጠረ። በእሱ አምሳል አዳምን ፈጠረው። ለመላእክት የ #መስቀል ምልክት አክሊል አላቸው። እንደ መብረቅ ያለ ዘውድም አላቸው። የ #መስቀል አምሳል በትርም አላቸው። ፊታቸውን በ #መስቀል ምልክት ይሸፍናሉ። የ #መስቀል ማዕዘኑ አራት እንደሆነ የመንበሩም ጎኖቹ አራት ናቸው።

ይህ #መስቀል የሄኖስ የሽቱ እንጨት ነው። የአብርሃም የወይራ እንጨቱ የይስሐቅ የነጭ ሐረጉ የያዕቆብ የዕጣኑ እንጨት ነው።

ይህ #መስቀል የሙሴ የሃይማኖት በትሩ ነው። ይህ #መስቀል ክንድን በኤፍሬምና በምናሴ ራስ ላይ በማስተላለፍ የጥላ ምልክት ነው።

ይህ #መስቀል የኤርሚያስ የሎሚ በትሩ ነው። የኢሳይያስ የስሙ መታሰቢያ ነው። ይህ #መስቀል ሰለሞን ያለ የእንኮይ እንጨት ነው። ከእንኮይ አነሳሁህ በዚያም የወለደችህ እናትህ ታመመች ብላ ይህች ሙሽራ ስለሙሽራዋ ብዙ ተናግራለችና።

ስለ #መስቀሉም ከጥላው በታች መቀመጥን ወደድሁ አለች ስለ ሥጋውም ፍሬው ለጉሮሮዬ ጣፋጭ ነው። ስለ ጎኑ ውሃም ወዳጅ ለኔ እንደተቋጠረ ከርቤ ነው አለች። ስለ #መስቀሉም በሱ ሰላም አገኛለሁና አለች ቤተ ክርስቲያንም ሙሽራዋ #መድኃኔአለምን እንዲሁ ትለዋለች።

ያዕቆብ የሴፍን አሕዛብን የሚወጋቸው የላም ቀንድ ነውን የላም ጥጃ ነው ብሎ በባረከው ጊዜ ሙሴ የተናገረው ትንቢት ምንድነው።

ላሚቱ በችግራችን ጊዜ የምታድነን #እመቤታች_መድኃኒታችን_ድንግል_ማርያም ናት። ጥጃውም በድንግልና ከሷ የተወለደ ይህ #መድኃኒታችን ነው። የቀንዱም ትርጓሜ ይህ #መስቀሉ ነው።

ሁለት ቀንዶችም የ #መስቀሉ ግንዶች ናቸው። የናዝሬቱ #ኢየሱስ የተሸከመውና የቀራንዮ ስምዖን የተሸከመው አንዱ ወደላይ የቆመው አንዱ የተጋደመው የ #መስቀል ግንድ ነው።

ነጭ በግ በነጭ ሐረግ ተይዞ ከሰማይ እንደወረደ እነሆ የሚያስደነግጥ የላም ጥጃ #መድኃኒታችን ነው።

እንደዚሁ ሀሉ #ክርስቶስ_መስቀሉን ተሸክሞ ሔደ ይህ #መስቀል ለቅዱሳን በመንገድ የተተወ የ #መድኃኒታችን ፍለጋው ነው። መንገድም ማለት #ቅዱስ_ወንጌል ነው።

ይህ #መስቀል አጋንንትን የሚያሳድዳቸው ሰይጣናትን የሚበትናቸው ነው። ኦሪት አንዱ ሺውን ትውልድ ያሸንፋቸዋል። ሁለቱ እልፉን ያሳድዷቸዋል እንዳለች። አንዱ ማለት ይህ #መስቀል ነው። ሁለቱም የ #መድኃኒታችን ቅድስ ሥጋው ክቡር ደሙ ነው።

ይህ #መስቀል የባሕር ፀጥታው የመርከቦችም ወደብ ነው። ይህ የቀራንዮ #መስቀል የቁርባን ኅብስት ያፈራው ነው። ይህ #መስቀል የጎኑ ውሃ ያጠጣው የጎኑ ደመም ያረካው ነው።

ይህ #መስቀል መጠጊያችን ኃይላችን የድኅነታችን ምልክት የነጻነታችን ምስክር ነው።

ይህ #መስቀል እንደ #እግዚአብሔር የከበረ እንደ ድንግል #ማርያምም ከፍ ያለ ነው። ሦስትነታቸው ትክክል የሚሆን እንደ #አብ እንደ #ወልድ እንደ #መንፈስ_ቅዱስም ፈጽሞ የማይለይ ነው። እንደዚሁም #መድኃኒታችን ከእናቱና ከ #መስቀል ጋር ሦስትነታቸው ትክክል ነው።

እንዲህ እናምናለን እናመልካለንም እንዲህ እንናገራለን እናመሰግናለንም። እንዲህ የሚያምን ይድናል እንዲህ የማያምን ይደየናል። የመብዓ ጽዮን ጸሎቱ የ #መድኃኔአለም ይቅርታውና ቸርነቱ ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን።

#ድርሳነ_መድኃኔአለም_ዘቀዳሚት_ሰንበት
#ሐምሌ_28

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሐምሌ ሃያ ስምንት በዚህች ቀን የደብረ ሊባኖሱ #አቡነ_ፊሊጶስ ዕረፍታቸው ነው፣ ክርስቶስን የሚወዱ #የቅዱስ_እንድራኒቆስና የሚስቱ #የቅድስት_አትናስያ መታሰቢያቸው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ፊልዾስ_ጻድቅ (ዘደብረ ሊባኖስ)

ሐምሌ ሃያ ስምንት በዚህች ቀን የደብረ ሊባኖሱ አቡነ ፊሊጶስ ዕረፍታቸው ነው፡፡ የደብረ ሊባኖሱ አቡነ ፊሊጶስ፡- በተወለዱ በ15 ዓመታቸው በምናኔ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገቡ፡፡ ከብዙ ጊዜ አገልግሎትም በኋላ በአቡነ ተክለሃይማኖት እጅ መንኩሰው ከእርሳቸውም ዕረፍት በኋላ ሦስተኛ አበምኔት ሆነው አገልግለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ከተወለዱት የመጀመሪያ ፓትርያርክ ሆነዋል፡፡

‹‹ክቡር አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት ከዚህ ዓለም ተለይቶ የሚሄድበት ጊዜ ሲደርስ ‹ከአንተ በኋላ አንተን ተክቶ በዙፋንህ የሚቀመጥ ማነው?› አሉት፡፡ እርሱም ‹ብዙ ዘመን አይኖርም እንጂ ኤልሳዕ በእኔ ተተክቶ ይቀመጥ› አለ፡፡ ስለ ፊሊጶስ ግን አላነሳም፣ ኤልሳዕ ካረፈ በኋላ በእርሱ ተተክቶ አባት ይሆን ዘንድ #ጌታችን የተሸለመ ፊሊጶስን እንደመረጠው ስም አጠራሩ ለልጅ ልጅ ዘመን እንደሚጸና ያውቅ ነበርና ስለዚህ ‹አልሳዕ በእኔ ተተክቶ አባት ይሁናችሁ› አለ፡፡ ክቡር አባታችንም በታላቅ ክብር ዐረፈ፡፡

አንድ ቀን አንድ ዲያቆን ዐረፈና ሬሳውን ገንዘው አጠቡት፣ ይቀብሩትም ዘንድ አስክሬኑን ይዘው ሲሄዱ በአልጋ ላይ ሳለ አስክሬኑ ተንቀሳቀሰ፡፡ የተሸከሙትም ደንግጠው መሬት ላይ አስቀመጡትና ከመግነዙ ፈቱት፡፡ እርሱም ተነሥቶ ሦስት ጊዜ ተነፈሰ፡፡ ወንድሞችም ‹ምን እያልክ ነው?፣ ወዴትስ ነበርክ?› አሉት፡፡ ያ የከበረና የተመረጠ ዲያቆንም ‹ክቡር አባታችን ተክለሃይማኖት ‹ኤልሳዕ ወደኔ ይምጣ፣ ፊሊጶስ ስለ እኔ ተሹሞ በወንበሬ ይቀመጥ እርሱ ለብዙዎች አሕዛብ አባት ይሆናልና የ #ክርስቶስንም መንጋ በጽድቅና በቅን ይጠብቃል› ብሎኛል› ብሎ ይህን ተናግሮ ተመልሶ ዐረፈ፡፡ ወንድሞችም ኤልሳዕ እንደልማዱ ጎኑን ሳያሳርፍ በወንበር ላይ እንደተደገፈ በሞት ማረፉን አላወቁም ነበር፡፡››

አቡነ ፊሊጶስ በ #እግዚአብሔር ተመርጠው የመንፈስ ቅዱስም ማደሪያ ሆነዋልና ገና በሕፃንነታቸው በተወለዱባት ሰላሌ ክፍለ ሀገር ዝማ በምትባል ልዩ ቦታ ውስጥ ሰይጣን በጠንቋይ ላይ አድሮ በነደደ በእሳት ውስጥ በመግባትና የተለያዩ ተአምራትን በማድረግ በአካባቢው ራሱን ያስመልክ የነበረን ሰይጣን በእሳት ውስጥ እንዳለ በስመ #ሥላሴ አማትበውበት አመድ አድርገውታል፡፡ በዚህ በአቡነ ፊሊጶስ ድንቅ ተአምር የጠንቋዩ ቤተሰቦችና የአካባቢው ሰዎችም አምነው ሊጠመቁ ችለዋል፡፡ ይህንንም ያደረገው ገና ሕፃን ሳለ ነው፡፡ መልአከ #እግዚአብሔር ተገልጦለት የትውልድ መንደሩን ትቶ ወደ ግራርያ ሀገር ደብረ አስቦ ሄዶ ቅዱስ ተክለሃይማኖትን እንዲያገኝ በነገረው መሠረት አንድ ቀን ያህል ተጉዞ ተክለሃይማኖትን አገኛቸውና ባርከውት ከመነኮሳት ጋር እንዲያርፍ አደረጉት፡፡ ሦስት ዓመት እነርሱን በመልካም ሥራ ፍጹም ሆኖ ሲያገለግላቸው ከቆየ በኋላ ‹‹ሁሉም በአንድነት አሁን ልብሰ ምንኩስና ይገባዋል›› አሉ፡፡ ቅዱስ አባታችን ተክለሃይማኖትም የምንኩስናን ሥራ የሚያሠራ ቅድስናን ሰጠው፡፡ በሌላም ጊዜ ቅስናን ይቀበል ዘንድ ወደ ጳጳሱ ዘንድ ላኩት፡፡

አቡነ ፊሊጶስ በንጉሥ አምደ ፅዮን ዘመነ መንግሥት ሥጋቸው አልቆ አጥንታቸው እስኪቀር ድረስ ሲገረፉ ደማቸው እሳት ሆኖ ገራፊዎቻቸውን ያሳደደ ቅዱስና ጻዲቅ አባት ናቸው፡፡ ንጉሥ አምደ ጽዮን በክፉ ጠንቋዮች ምክር ተታሎ ‹‹ያልወለደችህን የአባትህን ሚስት ብታገባ መንግሥትህ ትፀናለች›› ብለው ክፉ ምክርን መክረውት የእንጀራ እናቱን አገባትና ንግሥት አደረጋት፡፡ አቡነ ፊሊጶስም ይህን ሲሰሙ ነቢዩ ኤልያስ ንጉሡ አክአብንና አልዛቤልን በድፍረት እንደገሠጻቸው እርሳቸውም በቀጥታ ሄደው ንጉሡን ዘልፈው ገሠጹት፡፡ ወደ ንጉሡም ከመሄዳቸውም በፊት በዚህ ምክንያት ሰማዕት እንደሚሆኑ አውቀውት ነበርና ልጆቻቸውን ተሰናብተውና የሚተካቸውን ሰው ነግረዋቸው ነው የሄዱት፡፡ ንጉሡ አምደ ጽዮንም አጥንታቸው እስኪቀር ድረስ አስገረፋቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቶቻቸውም መሬት ላይ እየተቆረሰ የወደቀውን ሥጋቸውን እያነሱ ለበረከት ወሰዱት፡፡ ደማቸውም እንደ እሳት ሆኖ ገራፊዎቻቸውን ያቃጥላቸው ነበር፡፡ 300 አንስራ ውኃ አምጥተው ከደሙ በወጣው እሳት ላይ ቢያፈሱትም የውኃው ብዛት እሳቱን ማጥፋት አልቻለም፡፡ ንጉሡም በፍርሃት ከዙፋኑ ላይ ወርዶ ሸሸ፡፡

የንጉሡ ጭፍሮች ግን በጋለ ማረሻ ጀርባና ግንባራቸውን ደረታቸውንም ተኮሷቸው፡፡ ኃፍረታቸውንም እንዳይሸፍኑ እጆቻቸውን ወደ ኋላ አስረው ራቁታቸውንም በከተማው ሁሉ ሲያዞሯቸው ዋሉ፡፡ ማታም ንጉሡ ‹ታስረው ለኖሩ ኃይለኛ ውሾች ስጡት› ብሎ በማዘዝ ውሾቹ እንዲቦጫጭቋቸው ቢያደርጉም ውሾቹ ግን ከእግራቸው ስር ሰግደዋል፣ እርሳቸውም በእግራቸው ባረኳቸው፡፡ አማካሪዎቹም ንጉሡን ‹‹ከዚህ መነኩሴ ጋር ምን አጨቃጨቀህ በግዞት አርቀህ ስደደው ብለው›› ብለው መክረውት ‹‹እስከ ቆርቆራ አገር አውጥታችሁ ወደ ትግሬ አገር ውሰዱት›› ብሎ አዘዘ፡፡ እርሳቸውም ንጉሡን ከ3 ዓመት በኋላ ትሞታለህ ብለው ትንቢት ነገረውት በወታደሮች ተወሰዱ፡፡

በግርፋት ብዛት የተቆረሰ ሥጋቸው ድውያንን ይፈውስ ነበር፡፡ ደማቸውም አስረው የሚወስዷቸውን የአንዱን ወታደር አንድ ስውር ዐይኑን ፈወሰለትና ወታደሮቹም አምነው ከእርሳቸው ጋር በዚያው ተሰደው መከራን ተቀብለዋል፡፡ እሳቸው በትግራይ ታላላቅ ተአምራትን እያደረጉ ሲያስተምሩ በትንቢታቸው መሠረትም ንጉሡ ከሦስት ዓመት በኋላ ሞተና ልጁ ነገሠ፡፡ ልጁም አባታችንን ከስደት መለሳቸውና ከተክለሃይማኖት መቃብር ደብረ አስቦ ገቡ፡፡ የነገሠውንም ልጅ አንድ ክፉ ሰው ‹‹ከአንድ በላይ ማግባት ትችላለህ፣ በገና ወቅትም ረቡዕና አርብን መጾም ተገቢ አይደለም›› ብሎ ስለመከረው ጳጳሱን ወደ ሀገራቸው ግብፅ እንዲሰደዱ ሲያደርግ አቡነ ፊሊጶስን ደግሞ ‹‹ረቡዕና አርብን በጠዋት ካልቀደስክ›› ብሎ ወደ ደራ ተሰደው እንዲሄዱ አደረገ፡፡

አባታችን በአጠቃላይ አምስት ጊዜ ተሰደው በትግራይ፣ በደራ፣ በዝዋይ ባሕረ ደሴት፣ በዳሞት ገማስቄ እና በወለቃ በስደት ቆይተዋል፡፡ ጳጳሱን አባ ሰላማን በአቃሊት ቅበረኝ ብለዋቸው በቃሬዛ አድርጎ ከጌርጌሳ ወደ አቃሊት ወሰዷቸው፤ እዚያም ሐምሌ 28 ቀን በሰላም ዐረፉ፡፡ አጽማቸውም ከተቀበረ ከ140 ዓመት በኋላ በመጋቢት 23 ቀን ወደ ደብረ ሊባኖስ በክብር መጥቶ ዐርፏል፡፡ #ጌታችን_አምላካችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም ሰባት አክሊላት አቀዳጅቷቸዋል፡፡

ስለ አሁኑ ዘመን የአቡነ ፊሊጶስ ትንቢት!፡- በወቅቱ የነበሩት ጳጳስ አባ ያዕቆብ በብዙ ልመናና ምክር አቡነ ፊሊጶስን ጳጳሱ ራሱ የሚለብሰውን የክብር ልብስ አልብሶ በሸዋ አገር ላይ ኤጲስ ቆጶስነት ሾመው፡፡ ከተሾሙም በኋላ አቡነ ፊሊጶስን ‹ሌሎችን ሹምልን› የሚሉ በርካቶች ሲያስቸግሯቸው እሳቸው የሰጡት ምላሽ ‹‹በሥልጣን ፍለጋ ምክንያት ይህችን የትርህምትና የፅሙናን ቦታ (ደብረ ሊባኖስን) የጨዋታ የተድላ ቦታ እናደርጋታለን›› በማለት በወቅቱ ማንንም አልሾምም ብለው ነበር፡፡ አያይዘውም በዚሁ በሹመት ሽኩቻ ምክንያት ወደፊት የሚፈጠረውን ነገር በመንፈስ ቅዱስ መነፅርነት አይተውት የሚከተለውን ትንቢት ተናግረዋል፡- ‹‹እውነት እላችኋለሁ በመጨረሻው ዘመን ደጋጎች ሰዎችን ክፉዎችና ተሳዳቢዎች የሚያደርጉ፣ ሐሰተኞችና ዋዛ
ፈዛዛ የሚወዱትን ደጋጎች የሚያደርጉ ሰዎች ይመጣሉ፡፡

በመጨረሻው ዘመን ኃጥአን በጻድቃን ይመሰላሉ፣ ጻድቃንን ኃጢአተኞች ያደርጓቸዋል፡፡ በዚያን ዘመን እውነተኛዎቹ መምህራን አይሾሙም፣ ኃጢአተኞች መማለጃ ሰጥተው ወሬ እያቀበሉ ይሾማሉ፣ እንደ እባብ ክፉ ነገርን ለማድረግ ፍላፃቸውን ያሾሉ ደጋግ ሰዎችን በነገር ያጠፏቸው ዘንድ በእውነት ንጹሕ የሆኑትን ሰዎች አመፅን በተመላ አንደበታቸው ሹመትን ከመውደድ የተነሣ በቅናት ያጠፏቸዋል፡፡ በዚያን ዘመን መጻሕፍትን የሚያውቁ አይሾሙም፣ ነገርን የሚያመላልሱና የአገሮችን ቋንቋ የሚያውቁ ከመኳንንትና ከነገሥታት ዘንድ ሔደው ነገርን የሚሠሩ ሰውን የሚያጣሉ በአመፅ ሹመትን የሚያገኙ ብቻቸውን ይሾማሉ እንጂ ደጋጎች አይሾሙም፡፡ በሚመረጡበትም ጊዜ ከአባታቸው ከሰይጣን ጋር ሆነው ‹እገሌ መጻሕፍትን ያውቃል፣ የአገሮችን ቋንቋ የሚያውቅ ይሾም› ይላሉ፡፡ ያንጊዜም አመፅ ይበዛል፣ ፍቅርም ትጎድላለች፡፡ ከእኔ በኋላ የሚሆነውን እነሆ ነገርኳችሁ ይህንንም አውቃችሁ በልቡናችሁ ያዙ፡፡››
#ጌታችን ለአቡነ ፊሊጶስ የገባላቸው ልዩ ቃልኪዳን፡- ‹‹ገድልህንና ስለ እኔ የታገስካቸውን መከራዎችህን የጻፈውን ከሁላቸው ከቅዱሳንና ከሰማዕታት ጋር በሰማያዊት ኢየሩሳሌም በወርቀ ቀለም ለዘለዓለሙ ስሙን እጽፍልሃለሁ፡፡ ሥጋህ ከተቀበረበት ቦታ ይቅርታዬንና ቸርነቴን አደርጋለሁ፡፡ መቃብርህ የበረከት ቦታ ትሆናለች፡፡››

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_ጻድቃን_እንድራኒቆስና_አትናስያ

በዚህች ቀን# ክርስቶስን የሚወዱ የእንድራኒቆስና የሚስቱ የአትናስያ መታሰቢያቸው ነው። እነርሱም ከአንጾኪያ ከተማ ነበሩ። በወርቅና በብርም የከበሩ ባለጸጎች ነበሩ ከገንዘባቸውም ለድኆችና ለችግረኞች ይሰጡ ነበር።

ከዚህም በኃላ አንድ ወንድ ልጅና አንዲት ሴት ልጅን ወለዱ ወንዱን ዮሐንስ ሴቲቱንም ማርያም ብለው ሰየሟቸው ልጆችም አደጉ እንዲራኒቅስና ሚስቱም እንግዳ በመቀበል ለድኆችና ለምስኪኖች በመመጽወት በጎ ሥራን አበዙ እነርሱም መገናኘትን ትተው ሰውነታቸውን በንጽሕና ጠበቁ።

ልጆቻቸውም ዐሥራ ሁለት ዓመት በሆናቸው ጊዜ የሆድ ዝማ በሽታ ታመው በአንዲት ቀንም ሞቱ እንዲራኒቆስም አይቶ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_በኢየሱስ_ክርስቶስ ሥዕል ፊት ራሱን ጥሎ እንዲህ ብሎ አለቀሰ ከእናቴ ማሕፀን ራቁቴን ወጣሁ ወደ #እግዚአብሔርም ራቁቴን እሔዳለሁ እርሱም ሰጠ እርሱም ወሰደ የ #እግዚአብሔር የጌትነቱ ስም የተባረከ ይሁን ለዘላለሙ አሜን።

እናታቸውም ለሞት እስከምትደርስ እጅግ አዘነች ልጆቿ ወደ ተቀበሩበት ወደ ዐፀደ ቤተ ክርስቲያን ሔደች ከኀዘንዋም ብዛት የተነሳ አንቀላፋች በእንቅልፏም ውስጥ በልጆችሽ ሞተ አታልቅሺ እነርሱ ግን በሰማያት ደስ እያላቸው ናቸው እያለ በመነኰስ አምሳል ሲነግራት አየች። ይህንንም ሰምታ ሒዳ ለባሏ ነገረችው።

ከዚህም በኃላ ይህን ዓለም ይተዉ ዘንድ ተስማሙ ገንዘባቸውንም ሁሉ ምንም ሳያስቀሩ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ሰጡ በሌሊትም ወጥተው ወደ እስክንድርያ ከተማ ደረሱ ሚስቱንም በዚያ ትቶ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ በአባ ዳንኤል ዘንድ መነኰሰ። ከዚያም ተመልሶ ሚስቱ አትናስያን ወደ ሴቶች ደናግል ገዳም ወሰዳት በዚያም ተዋት።

ከዐሥራ ሁለት ዓመትም በኃላ እንድራኒቆስ ከቅዱሳት መካናት ይባረክ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሔድ አባ ዳንኤልን ለመነው ፈቀደለትም በ #መድኃኒታችንም ቸርነት ሚስቱ አትናስያ በወንድ አምሳል በጉዞ ላይ ተገናኘችው ሚስቱ እንደሆነችም አለወቀም እርሷ ግን አወቀችው ነገር ግን ሚስቱ እንደሆነች አልገለጠችለትም።

ወደ ቅዱሳት መካናትም በደረሱ ጊዜ ሥራቸውን ፈጽመው ወደ አባ ዳንኤል በአንድነት ተመለሱ። አባ ዳንኤልም ሚስቱ እንደሆነች በ #መንፈስ_ቅዱስ አውቆ እንድራኒቆስን ባልንጀራ ካደረግኸው ከዚህ መነኰስ ጋራ በአንድ ቦታ ኑሩ እርሱ ቅዱስ ነውና አለው። ዐሥራ ሁለት ዓመትም በአንድነት ኖሩ ማንም የአወቀ አልነበረም።

አባ ዳንኤልም ይጎበኛቸውና ስለ ነፍሳቸው ጥቅም ያስተምራቸው ነበር። ከዚህም በኃላ አትናስያ በታመመች ጊዜ ለእንድራኒቆስ አባታችንን አባ ዳንኤልን ጥራልኝ አለችው ሒዶም ለአባ ዳንኤል እንዲህ ብሎ ነገረው ባልንጀራዬ ታሞ ለመሞት ተቃርቧልና ትጎበኘው ዘንድ ና። በደረሰም ጊዜ በታላቅ ሕመም ላይ አገኛት እርሷም ታቆርበኝ ዘንድ እሻለሁ አለችው ያን ጊዜም ተፋጠነና ሥጋውንና ደሙን አቀበላት ከዚህም በኃላ አረፈች በሚገንዟትም ጊዜ ሴት እንደሆነች አገኙ ዳግመኛም ታሪኳንና ለባሏ ያወራቻቸውን ምልክቶች አገኙ።

እንድራኒቆስም በአነበበ ጊዜ እርሷ ሚስቱ እንደሆነች አወቀ ደንግጦም ልቡ ተሠወረ ፊቱንም እየጻፈ ጮኸ ያለቅስ ጀመረ።ከጥቂት ቀን በኃላም ታመመ አረጋውያንም መጥተው በረከቱን ተቀበሉ ሥጋውንና ደሙንም ተቀበሉ በሰላም አረፈ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ሐምሌ_28 እና #ከገድላት_አንደበት)
2024/09/23 17:23:33
Back to Top
HTML Embed Code: